You are on page 1of 16

ታህሣሥ ፳፯ ቀን ፪ ሺህ ፪ ዓ.


ከእውነቱ ተከስተ

ዓይን ያወጣ ቅጥፈት

ለውሸት ለቅጥፈትና ለስድብ የተዘጋጀ ኣፍ ኣንዴ ዲያብሎስ የተጠና ወተው ስለሆነ መርዙን
ከመርጨት እንደማያቋርጥ የታወቀ ነው፡፡
ሆኖም እንዲህ ዐይነቱ ለዘመናት የተጠናወተ ኣጋንንት እየተዛመደ በጀመራቸው ላይ እንዳይጸና
ለማስወገድ እንዲቻል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ የተናገረው ቃል ተፈጻሚነት ኣስፈላጊ ይሆናል፡፡
እጠቅሰዋለሁ፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ምዕ, ፲ ፯ ቁ. ፲ ፬ እስከ ፳፩ ያለው እንዲህ ይላል፥ “ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ ኣንድ
ሰው ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀረበና ተንበርክኮ ጌታ ሆይ ልጄን ማርልኝ በጨረቃ እየተነሳበት ክፉኛ ያሰቃየዋል
ብዙ ጊዜበእሳት ብዙ ጊዜም በወሃ ይወድቃልና ወደ ደቀመዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም
አቃታቸው አለው፥ ኢየሱስም መልሶ የማታምን ጠማማ ትው ልድ ሆይ እስከ መቼ ከናንተ ጋር እኖራለሁ
እስከ መቼስ እታገሳችኋለሁ ወደዚህ ወደእኔ አምጡት አለ፥ ኢየሱስም ገሰጸው ጋኔኑም ከርሱ ወጣ
ብላቴናውም ከዚያች ሰአት ጀምሮ ተፈወሰ፡፡ ከዚህ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና
እኛ ልናወጣው ያልቻልን ለምንድነው? አሉት፡፡ ኢየሱስም ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፥ እውነት እላችኋለሁ
የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያክል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል
የሚሳናችሁም ነገር የለም ይህ ዓይነቱ ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው፡፡ ተራራ የተባለው
ዲያብሎስ ሲሆን አብሮ አደግ ሆኖ የተጠናወተ ዲያብሎስ በጾም በጸሎት ካልሆነ በቀር አይወጣም በማለት
በምሳሌ አስተምሯቸዋል፡፡
ሐሰት ቅጥፈትና ውሸት መከፋፈልንም የሚፈጥረው ዲያቢሎስ የተጠናወተው ሰው ወደ ቅድስቲቱ
አገራችን ሔዶ ቅዱሳን አባቶች ጸልየው ካላጠመቁት በስተቀር ሊለየው ስለማይችል እና ወደ እርስዎም
የሚገባ ስለሚመስል ሐሰትና ስድቡን እያስተማረ የእውነትን መንገድ እንዲስቱ እንዳያደርግዎ ዲያብሎስ
ያስጫረውን ወረቀት መልስ ነው ብለው ማቅረብዎ በጉዳዩ ላይ በነበረው ሕዝብ ምን ያህል ትዝብት
እንደሚያሰጥብዎ መገመት አያዳግትም፡፡

በደብዳቤዎ መግቢያ ላይ ‘’ባልኖሩበት ባላዩትና ባልሰሙት የነበሩና የተገኙ ኣስመስሎ መጻፍ


እግዚአብሔር አምላክ ከመላእክትና ከፍጡራን ሁሉ አብልጦና አፍቅሮ በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው አእምሮ
እንደሌለው እውነቱንና ሐሰቱን መለየት እንደማይችል አድርጎ በመቁጠር ሰውን ለማታለልና ለማሳሳት
መሞከር ለዲያቢሎስ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም ‘’ ብለው የርስዎንና የቄስዎን የሚነገርባችሁን ታሪክ
ሳያውቁት አጋልጠዋል፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱሱ ለዚህ ማስረጃ የሆነውን ምሳሌ ምዕራፍ ፮ ቁጥር ፲ ፮ እስከ ፳ ያለውን አንብበውት
ያውቃሉን? እንዲረዱት እጠቅስልዎታለሁ፡፡ “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው ሰባትንም
ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፡፡ ይልና ትእቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኝ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስ እጅ፥ ክፉ
ሀሳብን የምታበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች
መካከል ጸብን የሚዘራ፥” ይላል፡፡ ስድስቱም እግዚአብሔር የሚጠላቸው ዲያብሎሳዊ አፈጻጸሞች ሲሆኑ
ሰባተኛውን ግን የእግዚአብሔር ነፍስ አጥብቃ የምትጸየፈው በሰዎችና በወንድማማች መካከል ጸብን የሚዘራ
በመሆኑ ይህን ሁሉ በየሔዱበት አገር በመፈጸም የታወቁት ቄስዎ ሲሆኑ አሁንም እርስዎ ተባባሪ ሊሆኑ
ስድብን እየተማሩ በመለማመድ ላይ በመሆንዎ እያዘንኩብዎ አንድ ለቄስዎ የተነገረ ቃል አሰማዎታለሁ፡፡
ሴንትሉስ ከሚባለው ከተማ አንድ ዘመድ ስላለኝ እዚህ ከመምጣቴ በፊት ስልክ ደውዬለት
ከሰላምታ በኋላ ስለ ቤተክርስቲያን ስንወያይ “እባክሕን እኛ እዚህ አሁን ሰላም አግኝተናል ተከፋፍለን
የነበርነው አንድነት ፈጥረናል፡፡ እኛን ከፋፍሎን የነበረው ቄስ አስተርአየ የተባለው ወደካንሳስ ሄዷል እዚህ
ያለው ምእመን “ካንሳስን ኮሶ ታያት ሴንትሉስን ኮሶ አሻራት” እያለ ደስታውን እየገለጸ ነው ብሎ የነገረኝ
እዚህ ስመጣ አየሁት ኣስታወስኩት በጣም ይገርማል!
ጸሐፊ ተብየው አቶ ይበቃል ባልነበርክበት ላሉት የብዕር ሰው ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባዎት
በተከታታይ መልሴ አሳውቆታለሁ፡፡
ጉዳዩን ሳጠና የመድኃኔዓለም ምእመናን በየጊዜው አስነዋሪ ድርጊትና ዲያብሎሳዊ አሠራር
የሚፈጽመው ማን እንደሆነ ተረድቶት በየስብሰባው እያአወገዛችሁ አላዋቂ አድርጋችሁ በማታለል
ከመሰልዎችዎ ጋር በሃሰት የታጀለና አንድ ዐይነት የተስፋ ቃል የምትጠባበቁ ሆናችሁ ስለታያችሁት
ዲያብሎስ መጀመሪያ ሲወድቅ መሰሎቹን ይዞ እንደወደቀው ዐይነት ቆጥሯችሁ ከቄሳችሁ ጋር እንደ ጉልቻ
ጎልቷችሁ የሄደ ለመሆኑ ብቻችሁን መቅረታችሁ እውነተኛው ምስክር ሆኗል እንጂ ሰውን ለማታለልና
ለማሳሳት ሞክረዋል ላሉት የለመዱት ጥቅምና የተስፋ ቃል የሚቀርቦት እርሶ እንጂ የኔ ብዕር ሃሰተኛን
ከምታጋልጥ በስተቀር ህዝቡን የማታልልበትና የማገኘው ጥቅም ያለመኖሩ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
እውነተኛይቱ ብዕሬ የምታተኩረው በእውናተኛው ጉዳይ ላይ እንጂ እንደርሶና እንደ ቄስዎ ላሉት
ተሳዳቢዎች ቦታም አትሰጣቸውም፡፡

ቄስዎን ሲያሞካሹ “በተለያዩ አበይት ጉዳዮች ሲጽፉ መቆየታቸውን” ጠቅሰዋል ለመጫርማ ዶሮም
በአቅሟ ትጭራለች፥ ቄስ እንደምናውቀው የጌታን ቅዱስ ቃል በህዝቡ አእምሮ ማንቆርቆር እንጂ የሰውን
መብትና ህልውና የሚገፍና የሚያጎድፍ ስድብና ዘለፋ እንዲሁም መከፋፈል የተጎናጸፈ የሃሰት ጽሁፍ መጻፍ
አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ዲያብሎሳዊ አሰራር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ብፁዕ “አቡነ ማትያስ ቄስ አስተርአየን ስለማገዳቸው” ለጠቀሱት ቀደም ሲል በጻፍኩት አብራርቼ


የገለጽኩት ስለሆነ አሁን መድገሙ የአንባቢን የስራ ጊዜ ማባከን በመሆኑ November 20, 2009
የጻፍኩትን “ጥቅሙ ምን ይሆን?” የሚለውን መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡

ቀጥለውም “ብፁዕ አባታችን አቡነ ይስሐቅ የቄስ አስተርአየ ትምህርትና እምነት ትክክለኛ ነው
ብለው ህዝቡ ከቄስ አስተርአየ ጋር በሰላም እንዲቀጥል አዘው ሄደዋል” ላሉት ቅጥፈት፡ እግዚአብሔር
በመንግሥቱ ያስባቸውና አባታችን በሞት ከኛ ቢለዩም የሚቀርበውን የሐሰት ጽሁፍ ቃል የሚያየው አምላክ
ከኛ ጋር ስላለ አይፈርድብንም ተብሎ በድፍረት ለማሳሳት መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡
አባታችን አቡነ ይስሀቅ የአቡነ ማትያስን እግድና ግዝት መሻር እንደማይችሉ ለማንም ስውር
አይደለም እንዳጣራሁት በወቅቱ እሳቸውም ለሊቃውንት ጉባኤ አቅርቤ የመጨረሻውን መፍትሄ
እስክልክላችሁ ተጠባበቁ ከማለታቸው በስተቀር በካህናቱም ስብሰባ ያልተገኙና የቄሱን እግድ
ያለማንሳታቸው እንዲሁም ዲሲ በተሰበሰበው የካህናት ጉባዔ መታየቱ እውነተኛ ምስክር ነው፥ እርስዎም
ገልጸዉታል፡፡” የካህናቱም ጉባኤ እግዱን አንስቻለሁ አላለም መብቱም አይፈቅድለትም፡፡

ታዲያ እሳቸው እግዱን ካነሱላቸው የካህናቱ ስብስብ ጉባኤ ለምን አስፈለገ? ጉዳዩ ይህን ይመስል
እንደነበረ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ብዕሬ እውነቱን ተከታትላ ፈልፍላ እውጥታ ከምታጋልጥ በስተቀር
ሕዝብ እውቆት ያላመነበትን እትከትብም፡፡

እንዲያውም ቄሱ ከታገዱ በኋላ ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን ሲሔዱ ሕዝቡ እንደ ውሻ ውጣ! ይህ ቄስ


ኣይደለም በማለት እስወጥቶ እንዳባረራቸውና ከተማውን ለቀው ሴንትሉስ ወደ ቤታቸው እንደሔዱ ድብቅ
አይደለም እርስዎም በጽሁፍዎ ከቤታቸው ጠርተን አመጣናቸው ብለው ጠቅሰውታል፡፡

በጽሁፍዎ ላይ “ሁለቱ አባቶች የሰጡት መፍትሔ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ አልቻለም” ላሉት አባታችን አቡነ
ይስሐቅ እግዱን እንደሻሩ ለማስመሰል የወሸከቱትን ይህ አባባልዎ የሚያጋልጥዎ ሲሆን አባታችን አቡነ
ማትያስ ግን ቄሱን አግደው ገለልተኛ ባያደርጔቸው ኖሮ በቄሱ ላይ ከፍተኝ የሕይወት ጉዳት ይደርስባቸው
እንደነበር በጊዜው ከነበሩት ወዳጆቻቸው ተወስቷል፡፡

“የቄስ አስተርአየ ትምሕርትና እምነት የግላቸው ሳይሆን የእኛና የአባታችን እምነት ነው የምንለው
ወገኖች አብረን ተለይተን ወጣን”ለተባለው እንዳጠናሁት ፈጣሪውን የካደው ዲያብሎስም ደጋፊ አላጣም፥
ቄስ አስተርአየ የሄዱት ወደቤታቸው ሴንትሉስ ለመሆኑ ከላይ የተገለጸ ሲሆን የተቀሩት ደጋፊዎች ናቸው
ያሉዋቸው ወደየበአታቸው ከተበታተኑ በኋላ አርስዎ የሙጥኝ ብለው አሰባስበዋቸው መድኃኔዓለም
የሚባለውን ቤተክርስቲያን ቄሱ በሌሉበት መመስረታችሁ ጥርጥር የለውም፡፡ በጊዜው ከኪዳነምሕረት ቤተ
ክርስቲያን የወጣውም ምዕመን እንደእርሳቸው ማርያም ኃጢአተኛ ነች በማለት ሳይሆን በመሰረቷት ኪዳነ
ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስነዋሪ ነገር እንዳይፈጸም ለማረጋጋት ለመሆኑ በየጊዜው በመድኃኔ ዓለም
ቤተክርስቲያን በሚደረገው ስብሰባ እመቤታቺንን ሁለተኛ አታንሱ ኃጢአት የለባትም እያሉ ቄሱን
ያወግዙዋቸው እንደነበር በስፍራው የነበሩት አረጋግጠዋል፡፡

ለመሆኑ በማቴዎስ ወን. ምዕ. ፪ ቁ ፲ ፫ እስከ ፲ ፭ ባለው እንደተጠቀሰው ኄሮድስ ልጇን ኢየሱስን
ሊገድልባት በግብፅ በረሃ የተንከራተተችው አንሷት አሁን ቄስ ተብዬውና እናንተ መሰሎቻቸው ኃጢአት
አለባት ካልተባለ አንተውም እያላችሁ የምትጭሩትና ስሟን የምታብጠለጥሉት ለምንድነው? አሁንም
ጥቅሙ ምን ይሆን? ሄሮድስ ሲያሳድዳት በትል ተበልቶ እንደሞተ እናንተም አሁን ኃጢያት አለባት ብላችሁ
የምታሳድዷትን ምን ዐይነት ትል ይበላችሁ ይሆን? እባካችሁን ንሰሐ ግቡ፡፡
ጸሐፊ ተብየው ተጭሮ በተሰጠዎት ጽሁፍ ላይ “አብረን ከሕዝቡ ጋር ለፍተን ደክመን ያቋቋምናትን
ደብረ ብርሃን ኪዳነ ምሕረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እጃችንን አራግፈን በመልቀቅ ተለየን”
ያሉት ምንም እንኳን በአሜሪካ ቤተ ክርስቲያን ማቋቋም እንደ እናንተ ያለው የቢዝነስ ሥራ የሚያደርገው
ቢሆንም ቅሉ ውዲቷ ተዋሕዶ እምነታችን እንዳስተማረችን ማንኛውም ሰው ለቤተ ክርስቲያን ከጉልበቱ
እስከ ቁሳቁስና ገንዘብ የሚለግሰው በፈቃደኛነት እንጂ ተገዶ ባለመሆኑ የተቋቋመችው የኪደነ ምህረት ቤተ
ክርስቲያን ትርፍ ተገኝቶባት የሚከፋፈሏት የቢዝነስ ሥራ ባለመሆኗ የኔ ንብረት ነው ብለው መጠየቅ
አይቻልም፡፡ ከእውነተኛ ምንጭ እንደተጣራው በዚህች ቤተ ክርስቲያን እርስዎ ቄስዎና ግብረአበርዎችዎ
አስተዳዳሪዎችና አዛዦች በነበራችሁበት ጊዜ ለቤተክርስቲያኗ ከየግለሰቡና ከየድርጅቱ በእርዳታነት ይሰበሰቡ
የነበሩትን ኮምፒውተሮች ማሺኖችና ሌሎችንም እየሰበሰባችሁ በቤተ ክርስቲያኗ የንብረት ገቢ መዝገብ
ሳይመዘገብ የት እንደደረሰ ያልታወቀ መሆኑንና ስውር ጥቅም መፈጸሙ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡አሁንም
ከስልጣን አልወርድም ካለው ግብረአበርዎ ጭምር ሩጫውና ጉጉት ያለዎት ለዚህ ይመስላል በማለት
ምስጢር አዋቂው ክፍል እያጋለጠ ነውና በቤተ ክርስቲያን ተሳቦ ቢዝነስ ኣይካሔድም ቤተክርስቲያኗም
የሕዝብ ንብረት ስለሆነች የልባችሁን አድርጋችሁ እጃችንን አራግፈን ወጣን ማለት ማደናገሪያ ነው፡፡ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌሉ “ቤቴ የጸሎት ቤት እንጂ የመሸጫና የመለወጫ ቤት አይደለም ብሏልና
መጋለጥ አይቀርም፡፡
አብረን ወጥተን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አቋቋምን ብለው የጠቀሷቸውም አባላት ቄሱ
በትምህርት አሳበው በቤተክርስቲያኑ አውደ ምሕረት የሚያቀርቡት ስድብና አሽሙር እንዲሁም አሉባልታ
ብሎም ከአስነዋሪ አፈጻጸም እንዲገቱ በስብሰባ አውግዘው ሰሚ በማጣታቸው አስነዋሪ ነገር ማየትና መስማት
ሰልችቷቸው ዓይናችሁ ለአፈር ብለው የተቀደሰና ሥጋና ነፍስን የሚያለመልም እንደ ማር የሚጥም ትምህርት
ወደሚሰጥበት ስድብና ሐሜት ወደማይሰማበት ወደቀድሞው ቤተ ክርስቲያናቸው ወደ ኪዳነ ምሕረት
በመሔድ በሰላም ፈጣሪአቸውን እንደሚያመሰግኑ ከግለሰቦቹ ጠይቄ ያጣራሁና በስፍራውም ተገኝቼ
የተመለከትኩ በመሆኑ እርስዎ ግን የበሬ እንትን ይወድቅልኛል ብላ ከሥር ሥሩ እንደምትሮጠዋ ጭሪ ወፍ
የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን የግልዎ በማድረግ ቢዝነስ ለማካሄድ ከመቋመጥ ይልቅ እንደ ወንድሞችዎ
እየተገኙ የሚጥመውን የእግዚአብሔር ቃል ቢያዳምጡ በመንፈሳዊ ሕይወት ይታደሳሉ በማለት ወንድማዊ
ምክሬን እለግስዎታለሁ፡፡

በጽሁፍዎ “ከየአቅጣጫው የሚሰነዘርብንን ፍላጻ በመቋቋም” የሚል ጠቅሰዋል፥ ፍላፃው


የተሰነዘረባችሁ እኮ ከእውነትና ከመንፈሳዊው ሥራ ስለራቃችሁ ነው፡፡ እንደተረዳሁት እመቤታችን
ኃጢአተኛ ነች እያላችሁ በምታቀርቡትና በሌሎችም አስነዋሪ ድርጊቶች ምክንያት የመድኃኔ ዓለም ቤተ
ክርስቲያን አባላት በየጊዜው ቢያወግዟችሁም እስከ አሁን የሚሰነዘርባችሁ ፍላፃ ለጊዜው አልወጋችሁምና
የመድኃኔ ዓለም ፍላፃ እስኪወጋችሁ ቀናችሁን የምትጠብቁ ትመስላላችሁ፡፡

በጣም የሚገርም ነገር ቢኖር በአንድ በኩል “ጥያቄአችን ጆሮ ዳባ ልበስ ተባለ” እያላችሁ በአሁኑ
ጽሁፍዎ ደግሞ “ስልክ በመደወል የሲኖዶስ አባላትንና የሊቃውንት ጉባኤ አባላትን ለጠየቅነው ጥያቄ ቀሲስ
ወደ አገር ቤት መጥቶ ጉዳዩን ያቅርብ” የሚል መልስ ሰጥተውናል” ብለዋል፡፡
ከነዚህ ሊቃውንት የተሰጠው መልስ ለእናንተ ለሐሰተኞቹ ያልተዋጠላችሁ ሆኖ እንጂ በሕጉ
መሰረት ትክክለኛ መልስ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ እንዴት ቢባል በእናንተ አመለካከት ትክክልም ሆነ
አልሆነ በሕጉ መሰረት ግን ሥልጣኑ የታገደባቸው ቄስ አንድ ቦታ ተቀምጠው ወረቀት እየጫሩ ዘራፍ!
ተደፈርኩ! ከማለት ይልቅ እንደታዘዘው ቀርበው የደረሰባቸውን በደል በቃል ጭምር በማስረዳት ለሲኖዶሱ
ጉባኤ አመልክተው ያገዷቸውም ጳጳስ በአንፃር ቀርበው እውነተኛው ተረጋግጦ ጳጳሱ ተሳስተው እንደሆን
እግዳቸውን እዚያው እንዲያነሱ ተደርጎ የቄሱ ሐቀኛነት ሲረጋገጥላቸው ለሕዝቡ ማገልገል ይችላሉ እንጂ
የሐሰት ጽሁፍ በመርጨት ማወናበዳቸውና የሊቃውንት ጉባኤውንና የቅዱስ ሲኖዶሱን እንዲሁም የጳጳሱን
ስም የሚያጠፉት እንዳጠናሁት አንዴ በታክሲ ሾፌርነት ካልተመቸም ሊቃውንትና ካሕናት በሌሉበት
በየቤተክርስቲያኑ በመዞር በስውር ስሜታቸውን ለማርካት የብቸኝነትን ኑሮ ልምድ አድርገውት ያለእኔ ሊቅ
የለም በማለት በሳምንት አንድ ቀን ቀደስኩ ብለው ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ ዶላር በላይ በማግኘት ደሆቹን
ቤተ ክርስቲያኖች ማራቆት ይቀርብኛል ብለው ነውና በሁሉም አሁን ገና ተጋለጣችሁ፡፡

አባቶቻቺን “እቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮህም” ይላሉ፥ ምናልባት ወደ አገር ቤት


ሄደው ለማመልከት የፈሩት ኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ የፈጸሙት የታወቀ ወንጄል ቢኖርባቸው እንጂ ብዙ
ዘመናት ተለይተውት የቆዩትን አገራቸውን ለመጎብኘት እንኳ ባልፈሩም ነበር፡፡አሁንም ሲኖዶሱንና
የሊቃውንት ጉባኤውን ከመኮነን ብሎም ሕዝቡን ከማወናበድ ሄደው ማመልከት ወይም አፋቸውን መዝጋት
ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡
ስለሌላው አጻጻፍዎ በመጀመሪያው ጽሁፌ ጥርት ባለ ሁኔታ አብራርቼ ጠቅሼዋለሁና መድገም
አያሻም፡፡

“ኤፌሶን ምዕ. ፩ ቁ ፪ በመጥቀስ ቅዱስ ጳውሎስ ነውር የሌለን ሲል የአዳም የውርስ ኃጢአት
ያላገኛቸው ነበሩ ማለት ያመጣል”ብለዋል ታዲያ እኔ በጽሁፌ ቅዱሱ ኤልያስና ሄኖክ በመጽሐፍ ቅዱሱ
ያለመሞታቸው ተጠቅሷል ታዲያ የአዳም ውርስ ኃጢአት አልደረሰባቸውም ማለት ነውን? ብዬ ላቀረብኩት
ጥያቄ “ውሸታም ኖት” ከማለት እውነቱንና የአባ መቃርዮስን መልስ ለምን አልጠቀሱልኝም? ይኸውሎ
ውሸታምስ ጸሀፊዎና እርሶ እንጂ የእኔ ብእር አይደለችም፡፡

እራስዎን የሚያሞካሹበት መንገድ ሲያጡ እርሶንና ቄስዎን ከፍ ለማድረግ ፈልገው “ለኢትዮጵያ


ኦርቶዶክስ እምነት ስንል ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጠን በኦርቶዶክሳዊው እምነታችን ጸንተን የቆየነውን” ካሉ
በኋላ “ክህነታቸውን ለመሥዋዕትነት ዳርገው የአባቶቻቸውን አደራ የጠበቁትን ቄስ አስተርአየ ጽጌን እንደ
ጲላጦስ አሳልፈው መስጠታቸውን ማወቅ አያዳግትም” በማለት በተጫረሎ ጽሁፍ ላይ ተመጻድቀዋል፡፡
ለምን ሄደው አመልክተው አላስወሰኑም? ምስጢር ስለሆነ በርሶ በኩል መልስ የለውም፡፡

ኧረ! ለመሆኑ ውዲቷ ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ሊቃውንት አባቶች ወንድሞች የት ሄደው ነው?
እንደእርሶና እንደጀሌዎችዎ ያላችሁት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሃዶ ትምህርት የግእዝ ፊደላትንና
ቁጥሮችን ማንበብና መለየት እንኳን የሚሳናችሁ እራሳችሁን አክብዳችሁ መመጻደቃችሁ? ቄሳችንስ
የምትሏቸው በስፍራው ተገኝቼ እንዳየኋቸው ሰሞነኛ ቄስ የሚያሳምረውን ቅዳሴ መቀደስና በቃላቸው ኪዳን
መድገም የሚሳናቸው አይደሉምን? በጌታ በየሱስ ምሳሌ እንደ ጲላጦስ አድራጎት አሳልፈው የሚሰጡ
ናቸውን? የችሎታቸውን ማነስ በተመለከተ ወደፊት ብእሬ በምትከትበው አበጥራ ታሪካቸውን ጭምር
ለህዝብ ጆሮ ለማብቃት ትገደዳለች፡፡ ያለበለዚያ ግን በስማቸውም ሆነ በጀሌዎቻቸው ስም እየጻፉ እንዲወጣ
ከሚያደርጉት ዉሸቶች ይቆጠቡ እላለሁ፡፡
ቀደም ሲል በጻፍኩት ላይ በዝርዝር የገለጽኩትን አሁን እንደ አዲስ አስመስለው ለኢትዮጵያ ቅዱስ
ሲኖዶስ ተልኳል ያሉአቸው ጥርቅም ወረቀቶች ከአዋልድ መጻሕፍት ሃይማኖተ አበውን፥ የቅዱስ ያረድን
ድርሰት፥ በግብጹ ጳትርያርክ የተጻፈ መጽሐፍ፥ የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡ ታዲያ እኔ የጠቀስኳቸውን
የቅዱሳን አባቶች መጻሕፍት ለምን አንቀበልም ተብለው ተነቀፉ? አዋልድ መጻሕፍቱ እናንተ በማስረጃነት
ስታቀርቡአቸው ተቀባይነት ይኖራቸዋል ተቃዋሚዎቻችሁ ሲያቀርቡአቸው ተቀባይነት ያጣሉ ማለት ነውን?
በጣም ያሳዝናል፡፡ ቁልጭ አድርጌ ያቀረብኩትን ለመሸሽ የባጥ የቆጡን እየቀበጣጠሩ መላው ሲጠፋብዎ በገዛ
እጆ ወጥመድ ውስጥ እየገቡ ነው ዳርዳሩን አይሽሎክሎኩ አንደኛውን ቄሳችንም ሆኑ እኛ ራሳችንን የቻልን
አንድ ሲኖዶስ መስርተን የምንገለገል ጀብደኞች ነን ቢሉ ይሻልዎታል፡፡ መጀመሪያ ማንነታችሁ መቼ ታወቀ?
የት ናችሁ? እነማን ናችሁ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርባችኋል፡፡

ለዚህ መልስ ላለመስጠት ሊቃውንቱንና ቅዱስ ሲኖዶሱን እየኮነናችሁ “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ
ጅግራ ነች ይሏታል” እንደሚባለው አሳፋሪ የሆነውን ጥገኝነት ለመፈጸም ለግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን
አቤቱታ እንዳቀረባችሁ ሳታፍሩ ትዘላብዳላችሁ፡፡

ዝንጀሮ “የመቀመጫዬ ይቅደም”እንዳለችው በቅድሚያ በየትኛው ሲኖዶስ ስር እንደሆናችሁ


አሳውቁ፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል ቄሳችሁ በሊቃውንቱ መሐል ከገቡ በሊቃውንት መመዘኛ መመዘናቸው
አይቀርምና ባለአዋቂነታቸው ሲጋለጡ እንደልማዳቸው እኔ እናንተ እያላችሁ መናገር አልችልም በማለት
ከመዋረድና ከማፈር በዚሁ ሁኔታ ምስጢራቸውን የማያውቅባቸውን እንደ እርስዎ ያሉትን ተስፈኛ
እያሰባሰቡ ዘራፍ! በማለት ጥገኝነት ፈልጎ ማወናበድ አለባቸው ማለት ነው፡፡

ለመሆኑ ሊቁ መሪጌታ ገብረሥላሴ ̎ኅዳር ፮ ቀን ፪ ሺህ ፪ ዓ.ም የጻፉትን አንብባችሁታልን?


እባካችሁን አንብቡት ጥሩ ትምሕርትና እውቀት ታገኙበታላችሁ፡፡

በጽሁፍዎ ላይ “በቅዱስ ፓትርያሬክ አቡነ ጳውልስና በቅዱስ ፓትርያሬክ ፓፕ ሸኑዳ ፫ኛ የጥንት


የነበረው የሃይማኖት አንድነትን የሚያረጋግጥ ባለ ፲ ፭ ነጥብ ስምምነት በድጋሚ እንዲጸና ተቋርጦ የነበረው
ግንኙነት እንዲቀጥል መደረጉን በመግለጽ ወደ እነሱ አመለከትን”ብለዋል፡፡
ለመሆኑ ስምምነቱ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ
ሳያውቀው በተራና በሲኖዶሱ ባልታቀፈ ጀብደኛ ቄስ የሚስተዳደር ቤተ ክርስቲያን በጻፉላት ብቻ ጣልቃ
ገብታ የማየትና ውሳኔ የመስጠት መብት በስምምነቱ ፊርማ ተረጋግጦ ተሰጥቷታልን? ደግሞስ ከአራቱ
አብያተ ክርስቲያናት ውጭ ለብቻዋ ዳኝነት ማየት ትችላለችን? ይህ ፍጹም ሊሆን አይችልምና የባጥ የቆጡን
ቀባጥረው ለማምታታትና ጥያቄዬን ባለመመለስ የሕዝቡን ልቦና ለመስለብ መሞከር ከባድ ስህተት ነውና
እንዲሕ ዓይነቱን ማምታታት ሕዝቡ ሳይደርስበት አይቀርምና እንዳይዋረዱ፡፡
መግለጫዎችዎንና የተቀረጸውን ቪዲዮ በኢንተርኔት ማውጣታችሁን ገልጸው ይህ ሁሉ ማስረጃ
በማለት አክብደው አቅርበውታል ሲታይ ከእውነት የራቀ እንጂ ምንም የቀረበ አስተማማኝ ማስረጃ
አልታየም፡፡ በቪዲዮ ተቀርጾ ቀርቧል ላሉት ፈጣሪአቺን ክብር ምስጋና ይግባውና በሰዎች ላይ ጥበብን ሞልቶ
በቴክኖሎጂ እየተፈላሰፉ የቀረጹትን እንደሚያመቻቸው በመለዋወጥ የማይፈልጉትን አጥፍተው
የሚፈልጉትን ጨምረው ለማቅረብ ስለሚችሉና ንግግሩም እንደገና ተስተካክል ስለሚቀረጽ እንደአባባልዎ
በቪዲዮ የተቀረጹ ፊልሞች ሁሉ እውነተኛ ድርጊቶች ናቸው ያቀረብነውን እመኑት ማለትዎ የደካማና
ያለአዋቂ አስተሳሰብ ስለሆነ ተመልካች ሁሉ ጥንቃቄ ይወስዳል፡፡

“እውነቱ ተከስተ በሚል የፈጠራ ስም ባላዩትና ባልተገኙበት ጉባኤ እንደነበሩ በማስመሰል ሕዝቡን
ለማሳሳት የሞከሩት ሙከራ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው”፡፡ በማለት በድጋሚ የገለጹት ለእርስዎ ውድ አባትዎ
“ይበቃል፡፡ በቃኝ፥፥ በቅቶኛል፤” ብለው በስያሜ እንዳወጡልዎት የእኔም ስም አባቴ እውነቱ ብለው
የሰየሙልኝ እውነተኛ ትክክለኛ ማለት ሲሆን ከላይ እንደገለጽኩልዎ ከፊደላቱ ጋር ስለማትተዋወቁ የአባቴን
ስም ግዕዙንና ሳድሱን ፊደል ለመለየት ባለመቻልዎ እውነቱ “ተከሰተ”ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህች “ስ” ሳድስ
ትባላለችና ይወቋት”ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንዳሉት አባቶቻችን በጽሁፍ ሰውን ለመስደብ
ከመሮጥ ፊደላትን ይማሩ እውነቱ ተከስተ ማለት ለምን እንዳሳዘነዎት አልገባኝም ለእኔም አባቴ እንደ እርስዎ
በስያሜ ያወጡልኝ ስለሆነ አላዋቂነትዎን በይፋ የገለጹት አሳዛኝና አሳፋሪ እርስዎ እንጂ ብእሬ እይደለችም፡፡
ይመስለኛል የብእር ስም ማለት ምን እንደሆነ ስለማይገባዎት በመሆኑ ጠይቀው ይረዱ፡፡፥ በወቅቱ ፍየል
እንዳየ ነብር ሆነው ልቦናዎ ተሰርቆ የጳጳሱ ዘለፋና ስድብ አስደስቶዎት ይቋምጡ ስለነበር አልታየሆትም፡፡
ዋናው ቁምነገር በቦታው ተገኝተው ያዳምጡ የነበሩ እውነተኛ ሰዎች ስለነበሩና አዛውንቱም አባት
በቂ ማስረጃ ስለሚሆኑ ለማስተባበል ሲሞክሩ ከባድ ትዝብት ላይ ወድቀዋል፡፡

“ነገረ ሃይማኖቱን ከአስተዳደር ጋር ቀላቅሎ ማያያዝ ስህተት ነው” ላሉት በእኔ ጽሁፍ ላይ የነገረ
ሃይማኖት እንጂ የአስተዳደር ነገር አልተነሳም አባባልዎ ትክክል አይደለም፡፡ ለዚህም ወሳኙ የሲኖዶሱ ጉባኤ
በመሆኑ ነው፡፡

“ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስር ያልሆነችውን ቤተ


ክርስቲያን መጥተው የወሰኑትን ውሳኔ እርስዎ አፅድቀው ሲቀበሉ ቅዱስ ሲኖዶሱ መልስ ያልሰጠው ደብረ
̎ሣህል መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ስላልሆነች መልስ ሰጭ
ለማግኘት ያዳግታል ማለትዎ አላዋቂና ግብዝ ያሰኝዎታል” ላሉት በበቂ ማስረጃ እንዳጣራሁት በጊዜው
ጭቅጭቁ የተከሰተው በቄስ አስተርአየና በዲያቆን ሳሙኤል እንዲህም በመዘምራንና በምእመናን መካከል
ስለነበር በሁለት ወገን ለተከፈለው ሕዝብ በቄሱና በምእመናኑ መካከል የነበረውን ጭቅጭቅ በአጭር
ለማስወገድ ሁለት ጳጳሳት በምርጫ እንዲመጡና እንዲገላግሉ በስምምነት ተጠይቀው ቄሱም
ተስማምተውበት የመጡ እንጂ ያለ ቄሱ ስምምነት አባታችን አቡነ ማትያስ ያልመጡ ከመሆኑም በላይ
በወቅቱ የነበረው የኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ስለነበር ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ሳይመቻቸው ሲቀሩ
ብፁዕ አቡነ ማትያስ መጥተው ጭቅጭቁን ለማብረድ በጥያቄ ሲሞክሩ ቄሱ ባለ መታገሳቸው በግዴለሽነት
ማርያም ̎ኃጢአት አለባት ብለው በማስተማር የጸቡ መነሻ የሆኑትን ቄስ አስተርአየን አግደው የተነሳውን ፀብ
አብርደው ሰላም አስፍነው ሔደዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማትያስም ሆኑ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ በተሰጣቸው ሥልጣን መሰረት የየራሳቸውን
ጊዜያዊ ውሳኔ ሰጡ እንጂ ሲኖዶሱ ሊያየው የሚገባውን ዳኝነት አላዩም፡፡ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት ቄሱ
ይምጡልኝ ብለው ተስማምተው የመጡት ጳጳስ ለመጡበት ጉዳይ የሰጡትን ከሲኖዶሱ ጉባዔ ጋር አገናኝቶ
ሁለት ቤተ ክርስቲያን እንደነበረ አድርጎ ማቅረብና ማምታታት በጣም አሳፋሪ አቀራረብ ነው፡፡ጳጳሱ
ሐዋርያዊ ሥራ ለመስራትና ቄሱ በሕዝቡ መካከል የፈጠሩትን ብጥብጥ አስወግዶ ሰላም ለማስፈንና
ለማስማማት ተለምነው የመጡ ናቸው እንጂ ሲኖዶሱ አውቆት ልኳቸው የመጡ አይደሉም፡፡ ባይላኩም
ይህን ለመፈጸም የተሰጣቸው ሥልጣን ያስገድዳቸዋል ከመጡም በኋላ በቄሱ ማንአለብኝነት ምክንያት
የተረበሸው ሕዝብ እንዲረጋጋ ትክክለኛውን ውሳኔ ሰጥተው ሕዝቡ ሰላም እንዲያገኝ አደረጉ እንጂ የፈጸሙት
ስሕተት አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ የኔ አቀራረብ ከርስዎ ጭፍን አስተሳሰብ ጋር አይጣጣምም እንደለመዱት
ሕዝቡን ለመበጥበጥ የተዘጋጁትን ስህተተኛ ቄስዎን እንደልማድዎ ደካማ ጎናቸውን ለመጠገን ታጥቀው
የተነሱ ከመሆኑ በስተቀር ከእኔ አባባል ጋር ፈጽሞ አይዛመድም፡፡

ቄሳችን ታገዱ በሚለው ላይ “አንድ ጳጳስ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጉዳዩን በቤተክርስቲያኗ ሊቃውንቶች
አስመርምሮ” ላሉት በጊዜው ከፍተኛ ብጥብጥ እንዲነሳ አድርገው ሕዝቡን ያበጣበጡትን ቄስ ሕዝቡ
እያወገዛቸው ዱላ ቀረሽ ጸብ ሲነሳ ጳጳሱ እያዩ ትተው መሔድና በሊቃውንት እስኪጣራ አቆይቶ በየቀጠሮ
እንዲጓተት አድርገው ሕዝቡን ማደባደብ ነበረባቸው ማለትዎ ስለሆነ ታዘብኩዎት፥ ጳጳሱ በወቅቱ የሰጡት
ውሳኔ ትክክለኛ መፍትሔ በመሆኑ ሕዝቡን ከድብድብ እድነውታልና የሚመሰገኑ እንጂ በእንደእርስዎ ባለው
አንደበት የሚወቀሱ አይደሉም፡፡ በዚሕም ጽሁፍዎ ላይ “መመሪያ ነው የምቀበለው ብሎ ለሚያግድ ጳጳስ
አይደለም” በማለት ቄስዎ የጳጳሱን እግድ መሻራቸውን ያረጋገጡበት አላዋቂነትዎን የሚያስረዳ ሲሆን ጳጳሱ
መመሪያውን ተከትለው ያገዷቸው መሆኑ ባይገባዎት ነው፡እንጂ ቄሱን ያገዳቸው የጳጳሱ ሐዋርያዊው
ሥልጣናቸው ስለሆነ ቄሱ የሻሩትም ሆነ ያቃለሉት የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነት በመሆኑ በከባድ ሁኔታ
ከመጠየቅ የማያድናቸው መሆኑን በድጋሚ እየገለጽኩልዎ ይህ መመሪያ ስለሆነ ሕዝብን የሚበጠብጥ
ጀብደኛ ቄስ ከጳጳስ የሚሰጠው መመሪያ ይህ መሆኑን ጳጳሱ ባለመሰወር ገልጸውላቸዋል፡፡

ሌላው ጥቅስዎ ደግሞ “ለኛ ችግር የፈጠረብን ብፁዕ አቡነ ማትያስ የሮማ ካቶሊክ እምነት የሆነውን
አጽድቀው በመሔዳቸው እንጂ” ይልና “በማሕበረ ካህናቱ ታይቶና ተረጋግጦ በአባታችን በብፁዕ አቡነ
ይስሐቅ ጸድቆ የተመሰከረለት” ከሚል በስተቀር እግዱ የተነሳበትን የሚገልጽ ማስረጃ አልጠቀሱም፥
አላቀረቡምም፡፡ የጠቀሷቸውም የማሕበረ ካህናት ስብስብ የብፁዕ አቡነ ማትያስን እግድ የመሻር ሥልጣን
እንደሌላቸው የታወቀ ነው፡፡ እኔም በጽሁፌ ገልጬዋለሁ፡፡ አቡነ ይስሐቅም እግዱን አንስቼልሀለሁ
አገልግል አላሉም፥ ማለትም አይችሉም፡፡ ለማምታታት የቀረበች ጠቀሳ ነችና ሌላውን ቢያታልሉ ይሻላል፥
አቡነ ማትያስም የሮማን ካቶሊክ እምነት አጽድቄአለሁ አላሉም፡፡ ያልተባለ ሐሰት መቀላመድ አታስተምሩ፡፡

ለመሆኑ ጸሐፊ ተብዬው አያፍሩም? “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ከዚህ ጋር ምን ግንኙነት
አለውና ነው “ከዛሬ ፲ ፪ ዓመት በፊት በዘመነ አቡነ ተክለሃይማኖት ጊዜ ተወግዘዋል”በሚል ያቀረቡት
ከቄስዎ የተማሩት የሐሰት አሉባልታ ቄስዎን ካገዷቸው በኋላ የተጠነሰሰች የቄስ አስተርአየ የቅጥፈት ወሬ
እንጂ ማንም እውነት ነው ብሎ የሚቀበለው የለም፡፡ ምን ይሁን ለማለት ነው እዚህ ላይ የጠቀሳችሁት? ስም
አጥፊነታችሁ ተገለጠባችሁ ከባድ ውርደት ነው፡፡ ቄስ እየተባሉ የመልካም ሰዎች ስም የሚጠፋው በዚህ
መልኩ ነው፡፡ ያሳዝናል ከባድ ጥንቃቄ መውሰድ ያሻል ገደል ማሚቶ ይሏል ይሄ ነው፡፡ ይህ ለእርስዎ ከባድ
ውርደት ነው ስለምን ቢባል እርስዎ በዚያን ጊዜ የት ነበሩ? በጉባኤው ተገኝተው ዓይተዋልን? የቤተክህነት
ሹም ወይም የሲኖዶሱ አባል አልነበሩም እንዲህ እያደረጋችሁ ነው የሰውን ስም የምታጠፉት ያላወቃችሁ
እንደ ትልቅ ሰው ቆጥሮ ቄሳችሁ ከሚያቀርቡላችሁ ተቀብላችሁ እንደ ገደል ማሚቶ የምታስተጋቡትን
የሚመለከት ሁሉ አይናችሁ ላፈር ሳይላችሁ አይቀርም እኔም ወደፊት በዝርዝር በማቀርበው ጽሁፌ
በማጋለጥ ዳሰሳ እዳስሳችኋለሁ፡፡

እንደው የአዋቂነትና የበላይነት ሥልጣን ያምራችኋል ይመስለኛል “ቄስ አስተርአየን ከቤታቸው


አስመጥተን እንዲያገለግሉ ያደረግን እኛ ነን” ላሉት አላዋቂነትዎን ራስዎ እየገለጹት ነው፡ በሌላ መልኩ
ደግሞ የቄሳችን ሥልጣን ተወግዞ ተያዘ ይላሉ፥ የጉዳዩ መሠረት ጠፋብዎት መሰለኝ ጮቤ የሚረግጡበት
ቦታ አልታይ ብልዎት ይዘባርቃሉ፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሐዋርያዊው ጳጳስ በግዝት ያሠሩትን (ያገዱትን) እግድ እናንተ ሽራችሁ
እንዲያገለግሉ ለማድረግ እነማናችሁ? የትኛው ሲኖዶስ ነው የፈቀደላችሁ? ቄስ አስተርአየ በግላቸው
ያቋቋሙላችሁ ሲኖዶስ ነውን? ያስቃልም ያስገርማልም፥ ይኸውልዎ ብእሬ ያቀረበቺው ውሸት ነው ሲሉ
ባቀረቧቸው ጽሁፎችዎ በብዛት እየተጋለጡ መጡ፡፡
ታዲያ እንደ አባባልዎ ማንም እግዱን ሳያነሳላቸው እናንተ የጠራችኋቸውን ምክንያት አድርገው ነዋ
የጳጳሱን ግዝት የሻሩት? ይህን አድራጎታችሁን ሕዝቡ አውቆት በጳጳሱ የታገዱትን ቄስ ሥልጣናቸውን
ለቀናልና ያገልግሉ ብሎ የወሰነበት አለን? ወይስ እርስዎ ብቻ እንደ ብዙ ሰው ተቆጥረው ለምነው
አምጥተዋቸው እግዱን ሽረውላቸው ነው? ቢሖንም ቄሱ አዋቂ ቢሆኑ በሕዝቡ ጥሪ የጳጳሱን እግድ ማፍረስ
ከባድ ወንጀል መሆኑን ማወቅ ነበረባቸው ግን በቋፍ ስለነበሩ ምክንያት አግኝተው ግዝቱን ሻሩት በጣም
አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡
ሆኖም ሁኔታው በትክክል ሲታይ የማያዋጣ ምክንያት ስለሆነ ለቄስ አስተርአየ እግዱን አቡነ ማትያስ
ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ እስካላነሱላቸው ድረስ ከቄስነታቸው ተወግደዋል፥ በቅስና ሥራም ማገልገል
አይችሉም፥ ምዕመናኑም ቢሆኑ የጳጳስ ግዝት በሻሩ ቄስ መገልገል አይችሉም፡፡ ይህን ደግማችሁ ደጋግማችሁ
እወቁት፡፡

ቀጥለውም እግዱ መከበር እንዳለበት ሲገልጹ “አዎን እንዳሉትም የቤተክርስቲያን ሕግና ሥርአት
መከበር አለበት”ካሉ በኋላ አልሸሹም ዞር ነውና “ነገረ ሃይማኖቱን ጠብቀን ቄስ አስተርአየን በመከተል ሕጉን
አክብረናል” ብለዋል፡፡ ይህን ተመልካች ይፍረደኝ ሕጉን አክብረናል የተባለው የተግባር ሳይሆን ሕዝቡን
አላዋቂ ለማድረግ የታቀደ የውሸት አክብሮት ነው፥ ስለምን ቢባል ቄሱ ከታገዱ ጊዜ ጀምሮ ከማገልገል
ያለማቋረጣቸው ከጸሐፊ ተብዬው ጽሁፍ ቄሱን ከቤታቸው ጠርተው አምጥተው እንዲያገለግሉ
ማድረጋቸው ተረጋግጧል፡፡ ሕዝቡም ያውቀዋል ቄሱም አልካዱም፡፡
የነገረ መለኮቱ ጉዳይ በሲኖዶሱ ጉባዔ የሚታይ እስከ ሆነ ድረስ ቄስ አስተርአየ ተገኝተው ውሳኔ
እስኪሰጠው የጳጳሱን እግድ (ግዝት) ሻሩ ይላልን? አይልም፡፡ አንደኛውን ሕጉን ሳይሆን ቄስ አስተርአየን
ከሕጉ በላይ አድርጎ በመደገፍ የጳጳሱን የሐዋርያት ሥልጣነ ክህነት ግዝት ተባብረን ሻርነው አይሉም? ምኑን
ሕጉን ጠበቃችሁት? ቄሱም ሆኑ እናንተ ተባባሪዎቻቸው ሕገወጥ ናችሁ ማለት ነው፡፡ የአፈጻጸሙ ምስጢር
ሌላ ነው በትብብር የሚገኘው ጥቅም ሊያመልጣችሁ ሆነና ጥቅማችሁን አስቀደማችሁ አያሳዝንም?
ጸሐፊ ተብዬው የሚሉት ሲጠፋብዎ “ሁለት ሲኖዶስ አለ ብለው እማይወጡት ስህተት ውስጥ
ወደቁ” ብለው የቄስዎን አነጋገር ደንቅረዋል፥ መርምሬ በትክክል እንደደረስኩበት የኢትዮጵያውና
የአሜሪካው ሲኖዶስ እያሉ ለሕዝብ ሲያስረዱና ሲቀላምዱ የነበሩት የእርስዎ ቄስ አይደሉምን? ሕዝቡ የት
ያውቀዋል? ሁለቱንስ የሚኮንኑ እሳቸው አይደሉምን? ዳሩ በማንአለብኝነት ሁለቱንም ከሚጠሉ በስተቀር
እውነት ከአፋቸው ወጥቶ አመስግነዋቸው እንደማያውቁ ግልጽ ነው፡፡
በመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ በተደረገበት እለት ወደ አንደኛው ሲኖዶስ ሆነን አባት
(ጳጳስ) ይኑረን በማለት ህዝቡ ሲጠይቅ እርስዎስ ሆኑ ቄስዎ በጉዳዩ ተወያይታችሁበት ወደ አንደኛው
ለመሆን የሚያጠኑ ሦስት ሰዎች ይመረጣሉ ተብሎ በስምምነት በኮሚቴው ቀጠሮ ሲያዝ ነበራችሁ ለምን
ሁለት ሲኖዶስ የለም አትሉም ነበር? ተዋረዳችሁ ሁለት ሲኖዶስ መኖሩን አምናችሁ መወያየታችሁን
ዘነጋችሁት? ወይስ እንደ ልማዳችሁ ካዳችሁት? “ተሸፋፍነው ቢተኙ ገልጦ የሚወጋ አምላክ አለ” ይባላልና
ቅጥፈታችሁን ያየው አምላክ ይፈርድባችኋል፥ በስብሰባውም የነበረው ሕዝብ ይታዘባችኋል፡፡ ስለዚህ
የማይወጡት ውሸት ላይ የወደቁት እርስዎ እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡

“ስላልነበሩበት ስብሰባ እንደነበሩ አስመስለው የጻፉት የፈጠራ ትረካዎ” ላሉት ከላይ መልስ
የሰጠሁበት ቢሆንም ቅሉ አልገባዎትምና እንደእርስዎ መልስ አላሳጣዎትም ብዕሬ አይደክማትምና
ትከትበዋለች፡፡ ባይገርምዎት እንጂ የብዕር ሰው መርምሮና አጣርቶ እውነቱን ለሕዝብ ጆሮ የሚያደርስ
ከመሆኑ በስተቀር እዚህ ነኝ ያለሁት ብሎ እንደእርሶ ላለ በሐሰት ለደነዘዘ ራሱን አይገልጽም ውዳሴ ከንቱንም
አይሻም ሐሰት ከትቦ አቅርቦ እንደሆነ በቦታው የነበሩት ለእንደርስዎ ላለው ደጋፊ ያልሆኑት ሐቀኛ ሰዎች
ፈራጅ ይሆኑብኛልና ውሸት ይዤ አልቀርብም በማለት ባስረዳዎትም አይገባዎትም ስለዚህ እንደ እርስዎ
ለመደጋገም አስገደደኝ፡፡
ለመሆኑ እርስዎ ሕሊናዎ በጳጳሱ በአቡነ መቃርዮስ ዘለፋና ስድብ በደስታ ተውጦ መቼ ዞረው ሰውን
አዩና ነው ቪዲዮ ተቀርጿል ያሉት? ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ጥበብን በሰዎች አሳድሮ የቀረጹትን
እንደፍላጎታቸው ለዋውጦ ማቅረብ ስለሚቻል የውሸት ቪዲዮዎን በኢንተርኔት ከማውጣት እቤትዎ
ከግርግዳዎ ሰቅለው እንደሚወዱት ፎቶግራፍዎ ቢመለከቱት ይሻልዎታል እላለሁ፡፡ እውነቱ ተከስተ
የሚባለውን ሰው ለማወቅ ከፈለጉ እኔ ምሳሌ ጠቅሼ ያስረዳሆት አይገባዎትምና በቄስዎ ያስተርጉሙ ስሙ
ሲጠቀስ እንደርስዎ ያለውና አጃቢዎችዎ እንዲሁም ጽሁፉን የሚጭሩልዎት ቄስዎ መላቅጡ ይጠፋባቸዋል
ስለምን ቢሉ እውነትን አበጥሮ የሚያወጣና ለሕዝብ ጆሮ አቅርቦ የሚያጋልጥ ብዕር ስላለው ነው፡፡

ወገን በጣም አያሳዝንም? “እስከ አለፈው ፶ ዓመት ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ
ክርስቲያን በግብፅ ኦርቶዶክስ መንበረ ፓትርያሬክ ስር ነበረች” ብለው ዝቅ በማድረግ ጥገኛ አስመስለው
ማቃለልዎ ለማንም ኢትዮጵያዊ ሳያሳዝነው የሚቀር አይደለም፡፡
እውነቱ ግን እርስዎ እደወሸከቱት በዝቅተኛነት ደረጃ ሳይሆን ቅዱስ ማርቆስ በግብጽ በነበረ ጊዜ
በኢትዮጵያ ተጽእኖ አድርገውባት ራሷን ችላ ጳጳስ መሾም አይፈቀድላትም በማለት ተከልክላ ወርቋን
ያለውዴታዋ እያስረከበች ከእስክንድርያ ጳጳስ ታስመጣ ነበር እንጂ በጊዜው በክርስትና ሃይማኖትና
በሊቃውንት ከግብጽ አንሳ ያለመሆኑን በግልጽ መረዳት የሚቻለው በመጽሐፍ ቅዱሱ እንደ ተጠቀሰው
በመዝሙር ፷፯ ቁ ፴፩ ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ታምን በነበረበት ጊዜ ግብፅ በልዩ ልዩ የፈርኦን ጣኦታት
እንደምታመልክ ቅዱስ መጽሐፉ ያስረዳል እግዚአብሔርም እሥራኤላዉያንን እናንተ ለኔ እንደ ኢትዮጵያ
ልጆች አይደላችሁምን? ያላቸው በእግዚአብሔር ማመናቸውን ያረጋግጣል እንጂ የግብጽ የበታች ጥገኛ
አልነበረችም አይደለችምም፡፡ትንቢተ አሞፅ ምዕ.፱.ቁ ፯ ይመልከቱ በተጽእኖ ጳጳስ እንዳትሾም የተደረገው
ተሸፍኖ ለጥቅም ሲባል ያለፈው ፶ ዓመት ድረስ ለግብፅ ጥገኛ ሆና እንደ ኖረችና የበታች እንደ ሆነች አድርጎ
ጽፎ ማቅረብ ከቄስዎም ሆነ ከርስዎ የሚጠበቅ አይደለም አሁንም ቢሆን የግብጽ ሕይወት በአባይ ወሀ
አማካይነት በምታገኘው አፈር ለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነውና ጥቅማችሁን ስትፈልጉ ጥንተ መሠረቷ
በእግዚአብሔር እምነት የሆነውን ውዲቷን ኢትዮጵያን ዝቅ አድርጋችሁ አታቅርቧት መድኃኔ ዓለም
ይፈርድባች̎ኋል ታሪክም ይወቅሳችኋል፡፡

“አቡነ መቃርዮስ ያሉት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ነው እንጂ አባ ሕርያቆስን አላሉም”በማለት


ለማስተባበል መሞከርዎ በጣም አሳዛኝ ነው እባክዎን ጆሮና ልቦና ያለውን ሕዝብ አያወናብዱት በጊዜው
ጳጳሱ ጠቅሰው የተናገሩት አባ ሕርያቆስን እንጂ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሚል አልተናገሩም የጊዮርጊስንም
ስም ፈጽሞ አልጠሩም እርስዎም አያውቁትም ያስተካከሉላቸው ጸሐፊዎ ናቸው ከላይ እንደገለጽኩት
በቪዲዮውም ታስተካክሉላቸውአላችሁ፥ የሆነው ሆኖ እነኚህን ቅዱሳን በመናቅ “አንድ ሰው ተናገረ ተብሎ
የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይለወጥም ነው ያሉት”ብለው ቢያስተባብሉላችውም በመዝሙር ፴ ቁ ፲ ፰ ላይ
“በድፍረትና በትእቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ ስለሚል መድኃኔ
ዓለም ዋጋችሁን የሚስጥበት ጊዜ የራቀ አይሆንም፥ ከቅዱሳን እውቀት የእኛ ይበልጣል የምትሉ ከሆነ
የሚያወዳድራችሁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አትዘንጉ፡፡
ታዲያ አቡነ መቃርዮስ አዋልድ መጻሕፍትን አንቀበልም ካሉና ችሎታ ካላቸው በመጽሐፍ ቅዱሱ
እመቤታችን ማርያም ከዬት እንደመጣች ስለማይገልጽ ከሰማይ ወረደች ሰው አይደለችም ብንል ከነገረ
መለኮቱ ጋር አይጋጭምን? በማለት በአለፈው ጽሁፌም በጥያቄ መልክ አቅርቤዋለሁ ጳጳሱም ሆኑ እናንተ
ለምን አስተማማኝ መልስ ሳትሰጡበት “ዉሾን ያነሳ ውሻ ነው” ብላችሁ ደፈናችሁት? ይህ ከባድ ቁምነገር
ለምን መልስ እንዳላገኘ አንባቢ ይፍረደኝ ለእናንተ ቅጥፈት ይህ ብቻ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
ጸሐፊ ተብዬው አቶ ይበቃል በቦታው ስላልነበሩ ነው ብለው ለደጋገሙት ጽሁፍ ከላይ በቂ የሆነ
መልስ በተደጋጋሚ ሰጥቼበታለሁና ካልገባዎት አርፈው ይቀመጡ እንጂ እንደውዳሴ ማርያም መደጋገም
አያስፈልግም፡፡

“ጳጳሱ ደጋግመው መልስ ሰጥተዋል” ላሉት የውሸት ማስረጃ አድርገው የጠቀሱት የቪዲዮ ጉዳይ
በቂ መልስ የሰጠሁዎት ስለሆነ እንደእርስዎ በቲርኪሚርኪ ሐተታ የአንባብያንን ጊዜ አላበላሽም፡፡

“እኒህ ከላይ አዛውንት ብለው የጠቀሷቸው አባት ለጠየቋቸው ጥያቄዎች ጳጳሱ ተገቢ መልስ
ሰጥተዋቸዋል” ያሉት ከላይ የመለስኩት ቢሆንም በመልስ ጽሑፌ እንደጠቀስኩት ጳጳሱ የተሳደቡትን
ስድብና ዘለፋ እንዲሁም የማቴዎስ ወንጌል ጠቅሰው በአሽሙር የተሳደቡት የእርስዎ የደካማው ሕሊና እንደ
ተቀደሰ ቃልና መልስ አጠንጥኖ እንደቴፕ ቀርጾት ስለነበር ከእርስዎ አንደበት እውነት ቃል ይወጣል ብዬ
አልጠበቅሁም፡፡ የጳጳሱን አነጋገር የሰማው እውነተኛው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ግን ከፍተኛ ትዝብት
እንደወሰደባችሁ አልተረዳችሁም፡፡ ሆኖስ ከቄስዎና ከርስዎ እውነተኛ ቃል ይወጣል ብሎ የሚጠብቅ ያለ
ይመስልዎታልን? አዝናለሁ በደንብ የከለሱትና በቪዲዮ ያቀነባበሩት ይመስለኛል እየደጋገሙ ስለ ቪዲዮ
ያነሳሉ፥ የሐሰት ቪዲዮ ለመሆኑ በዚህ ይረጋገጣል፡፡ዳሩ ምን ያደርጋል አገሩ አሜሪካ ነው ከስምንት ዓመት
ዕድሜ የማይበልጡ ልጆች ካሜራ ተገዝቶላቸው አሳምረው ይቀርጻሉ ታዲያ እናንተስ ከነሱ በምን
ትሻላላችሁ? አባቶቻቺን “ለበሬ ፈስ አፍንጫ አይያዝለትም” ይላሉ፡፡

ቀጥለውም “ጥያቄ ላቀረቡት አንድ አባት እንደተበደሉና እንደ ተነቀፉ አድርገው አቅርበዋል”
ላሉት”በጫማ የሚሔድ በእግሩ የሚሔደውን ጓደኛውን ጉዳት አያውቅለትም” ይባላል፥ ዘለፋውና ስድቡ
የጎዳቸው ተቃዋሚአችሁን አባት ስለ ሆነና እርስዎን ስለአስደሰተዎት ጉዳታቸውን አላወቁላቸውም
“የምናከብራቸው አባታችን ናቸው” ሲሉ የማታለያ ቃል ጽፈዋል የማያውቅባችሁን አታሉ እናንተን
የሚቃወሙ ጥያቄ ሲያቀርቡ መዘለፍ አለባቸው ማለትዎ ነውን?ይገርማል፥ በጣም ጥሩ “እስከ አሁን አብረን
የምናመልክ ነን” ከማለትዎ በስተቀር እኒሕ አባት እንደ ቄስዎና እንደ እርስዎ ማርያም ̎ኃጢአት አለባት
አላሉም እናንተንም ከሚያወግዙት አንዱ ለመሆናቸው መካድ የማይችሉት ሐቅ ነው፡፡
አቶ ይበቃል ፈጣሪውን በቅን ልቦና የሚያመሰግነውን ሕዝብ ግራ ልታጋቡ ታጥቃችሁ ተነስታችኋል
በአንድ በኩል ቅዳሴ ማርያሟን ጠቅሳችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ወጣ ትላላችሁ በአንድ በኩል በመጽሐፍ ቅዱሱ
የሌሉትን አዋልድ መጻሕፍት ተቀባይነት የላቸውም ትላላችሁ የምትጨብጡት መላቅጡ ነው የጠፋባችሁ፡፡
ያለፉት ቅዱሳን አባቶች ከመጽሐፍ ቅዱሱ ቃል ሳይወጡ የጻፉትን የእግዚአብሔር ምስጋና ቃል እየነቀፋችሁ
የእነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን የብፁዕ አቡነ ጳውልስንና የሌሎችንም አቅርባችኋል
የምትጨብጡትን አጥታችኋል ማለት ነው እግዚአብሔር ይማራችሁ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጥገኛ ልትሆን አትችልም
ተብሎ ለተጠየቀው እርስዎ ሲመልሱ “ከዛሬ ፶ ዓመት ወዲህ እራስዋን ችላለች” ላሉት ያልተጠየቁት አስነዋሪ
ጽሁፍ ስለ አገርና ስለ ሃይማኖት ደንታ የሌላቸው ቄስዎ የፈለሰፉልዎት እንጂ እርስዎ የአካሔዳቸው ምስጢር
ሳይገባዎ መናጆ በመሆን ይጓዛሉ፡፡ ይህን በተመለከተ አብራርቼ መልስ ሰጥቼበታለሁና አንባብያን ወደኋላ
መለስ ብለው ይመልከቱት፡፡

በጣም ያሳዝናል ይህ ሁሉ እሩጫና ለግብፅ ቤተ ክርስቲያን አቤቱታ ማቅረብ “ሊበሏት ያሰቡዋትን


አሞራ ዥግራ ነች ይሏታል” ይባልየለ የባጥ የቆጡን ወሽክቶ እንደልብ ዘራፍ ለማለትና የራስን የተለየ?
ሲኖዶስ መስርቶ ለመጨፈርና ያሰቡትን ለመፈጸም እናት እገርን ያህል ጸጋ የግብፅ ጥገኛ ነበረች ብሎ
ለማዋረድ መነሳት አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡

በመልስ አሰጣጥዎ ላይ “መንፈሳዊውን የሃይማኖት ነገር በዓለማዊ የአሠራር ዘይቤ ለመቃኘት


ሞክረዋል” ላሉት እርስዎ ይህን ለማለት የበቁት በመንፈሳዊና በአስተዳደር ሥራ ገብተው ያገለገሉበት ጊዜ
አለን? የለም አስመስለው ቄስዎ የጻፉልዎትን ለማምታታት አቀረቡት እንጂ ከሁለቱም አይተዋወቁም
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ለመጀመሪያ ጊዜ በካንሳስ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በማያውቁት
የቤተ ክርስቲያን የኮሚቴ መሪ ሆኑ እንጂ የአስተዳደር መሪነትና የውሳኔ አሰጣጥ እውቀት ስለሌለዎ ለቄስዎ
ብቻ አፈ ቀላጤ በመሆን ሕዝቡን ለማደባደብ አድርሰውት እንደነበረ የታወቀ ሲሆን የሲኖዶሱ ጉባዔ አንድ
ሰው ከክህነቱ ተወግዞ የታገደ ከሆነ እግዱ አስተዳደራዊን አፈጻጸሙ ሃይማኖትን የሚመለከት የተጣመረ
ጉዳይ በመሆኑ ጉባኤው በአንዱ ሥልጣን ብቻ የተወሰነ አይደለም ስለማያውቁት ሳይገባዎት በጭፍን
እንደሚያውቁ ሆነው በመዘላበድዎ አልፈርድብዎትም ያዝ እንደተባለ ውሻ ተገፋፍተው መሆኑን ሁሉም
አውቆብዎታል፡፡

በመሰረቱ “አንድም ሆነ ሁለት ሆናችሁ በተገኛችሁበት እገኛለሁ” ያለውን የጠቀሱት በመንፈሳዊ


ሕይወት ለመልካም ሥራ ተገኝተው ለሚለምኑት ቅን ልቦና ላላቸው የተነገረ እንጂ እንደ እርስዎና እንደ
ቄስዎ እንዲሁም እንደ መሰልዎችዎ ለጥቅም ለሚሮጥና እኵይ ተግባር ለተጠናወተው አይደለም፡፡
የኔ አባባል የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እራሷን የቻለች ስትሆን የኢትዮጵያም ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእኩልነት ደረጃና ሥልጣን እራሷን የቻለች ናት፥ አቡነ ማትያስ ያገዱትን የካህናቱ
ጉባኤ መሻር እንደማይችል ሁሉ የግብፅ ቤተክርስቲያን በተናጠል ከአራቱ እህት አብያተ ክርስቲያናት ተለይታ
በግሏ ጣልቃ በመግባት የማየት ሥልጣንና መብት የላትም ነው፡፡

ከዚሁ አያይዘው “የበፊተኞቹ ቅዱሳን አባቶች በሕይወት የሉም የአሁኖቹ በሕይወትና በአካል አሉ”
ሲሉ የቀድሞ ቅዱሳን አባቶች ሞተዋልና አባባላቸው ተቀባይነት የለውም አሁን ያለነው በሕይወት ስላለን የኛ
ነው ተደማጭነት ያለው ማለትዎ ነውን? “ጥንቸል በሬን አክላላሁ ብላ ተሰንጥቃ ሞተች ይባላል” በዚህ
ኃጢአት በሰለጠነበት ዓለም ለጥቅም የሚሮጡት እርስዎንም ጭምር ከቅዱሳን አባቶች ያወዳደራችሁ
ማንነው? መስመርዎን ስተው ስለገቡ የሰው መሳለቂያ ሆኑ፡፡

ቀጥለውም “ማንም ጣልቃ ያለመግባቱን” ጠቅሰዋል ታዲያ ምንድነው የሚያነታርከን? እባክዎን


መሠረተ ጉዳዩ ሲጠፋብዎ አያምታቱ የአምስቱ አብያተ ክርስቲያናት መብትና ሥልጣን በጋራ በተሰበሰቡበት
ዓይተው የሚወስኑት እንጂ በተናጠል ጣልቃ መግባት መብታቸው ስላይደለ ከባድ ስህተት ተፈጽሟል ነው
የተባለው እንጂ ሃይማኖት የግል ነው የሚል አልተጻፈም “ቅዝምዝም ወደዚህ ጥንቸል ወደዚያ”
እንደተባለው አያድርጉት በጣም ይገርማል “ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” እንደሚባለው ሆነ፥ ለመሆኑ
በኢትዮጵያ ኦርቶዳክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያደጉት እያሉ እርስዎ ማን ሆነው ነው? በጣም የሚገርመው
ሌላ ሰው የጫረልዎትን አሜን ብለው ተቀብለው እንደ ትክክለኛ አድርገው ማስተላለፍዎ ደካማነትዎንና
አላዋቂነትዎን ይገልጻል፡፡ እባክዎን እኔንና አንባቢውን ሕዝብ አይደለም የሚያሞኙት “ላላወቀብሽ ታጠኝ”
እንደሚባለው ለማያውቅብዎ ያታሉ ቤተክርስቲያኗንም እድል አጋጥሞዎት ነው እዚህ አገር መጥተው ምን
እንደምትመስል ያዩዋት፡፡
የሆነው ሆኖ ቅዳሴ ማርያሟ ብቻ ሳትሆን ቅዱሳን አባቶች የጻፉት ሁሉ ለቅድስና ጠቃሚ ለመሆኑ
በ፪ኛ ጢሞቴዎስ ምዕ. ፫ ቁ ፲ ፮ እና ፲ ፯ ላይ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን
ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም
ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” ይላል፡ እርስዎ ቅዳሴ ማርያሟን ከመጽሐፍ ቅዱሱ ያልወጣ መሆኑን እንደ
ጠቀሱት ሁሉ ቅዱሳንም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት እንደ ሃይማኖተ አበውና የጸሎት መጻሕፍት
የመሳሰሉት አይገባዎትም እንጂ ቢያውቋቸው ኖሮ ጥቅሱ እንዳለው ልቦናን የሚያነጻና ወደ ጽድቅ የሚመራ
ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሆኑን ተረድተው ሰው የጻፈልዎትን ብቻ አንጠልጥለው ዘራፍ ባላሉም
ነበር፡፡

የሚሉት ቢጠፋብዎ “እመቤታቺን ከጥንተ አብሶ የነፃችበትን ትክክለኛ ዕድሜ አልጠቀሱም” ላሉት
ለእኔ ይህን ያህል ቅድስና ሰጥተው ትክክለኛ ዕድሜዋን ግለጽ ማለትዎ አላዋቂነትዎ ቢደንቀኝም አባባልዎን
አልዘከርብዎትም ስለምን ቢሉ ከላይ እንደጠቀስኩት ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ጋር ስለማይተዋወቁ
ነው፥ ጥያቄዎን በትክክል የሚመልሱት መጽሐፍ ቅዱሱ ሳይሆን የጠሏቸው አዋልድ መጻሕፍት ስለሆኑና
መጻሕፍቱንም ከአዲሱ ጳጳስዎ ጋር ውድቅ ስላደረጓቸው እንጂ አስተርጉመው በተረዱት ነበር፡፡
ፍሬ ጉዳዩ መዘላበድዎ ሳይሆን እመቤታችንን እግዚአብሔር ሲያነጻት አማካሪ የለውም ያለእሱም
አዋቂ የለም በዚህ መሰረት ከህፃንነቷ ጀምሮ ኃጢአት የለባትም አንጽቶ ቀድሶ ፈጥሯታል ነው የምንለው፥
እርስዎ ገብርኤል ሲያበስራት ነው በማለት በዚህ ኃጢአት በበዛበት ዓለም የተፈጠሩት ሰዎች የጻፉትን
በማመን የቅዱሳን አባቶችን በመንቀፍ በማያውቁት ገብተው ከማተራመስ ትክክለኛ ከኣዳም ጥንተ አብሶ
ቅዱስ ገብርኤል ሲያበስራት ነፃች የሚል ከመጽሐፍ ቅዱሱም ሆነ ከአዋልድ መጻሕፍት ለምን አላመጡም?
ከነ ማስረጃው ጠቅሰው ቁጥሩን ቢገልጹልኝ ደስታውን አልችለውም ነበር ያለበለዚያ እባክዎን አይዘላብዱ
እግዚአብሔር እንዳማከረው መስለው ሰውን አያወናብዱ አፍዎን ቢዘጉ ይሻላል ኃጢአተኛ ነች አይበሉ
ይፈረድቦታል፡፡

ቀጥለውም “በጥቅሉ እርስዎ እንዳሉት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም በሚል ማለፍ የለብንም
ይህንንም ማለት ደግሞ ሁሉንም ነገር መረዳት ወይንም ማወቅ ይቻላል ማለቴ አይደለም ለምሳሌ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ አባት ከመቤታችን ከድንግል ማርያም ተወለደ ይህንን እርስዎ እንዳሉት ለእግዚአብሔር
የሚሳነው ነገር የለምና ብል በፍጹም እምነት ከመቀበል ሌላ ተመራምሮ መጻሕፍትን አገላብጦ ይህን
ምሥጢር የሚደርስበት ማንም የለም” ላሉት ይህንንማ በመጽሐፍ ቅዱሱ እመቤታችን ድንግል ማርያም
ለመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? ስትለው የሚጸነሰው ከመንፈስ ቅሩስ ነው
እሱም ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል በማለት በሉቃስ ወንጌል ምዕ.፩ ፴፩ እስከ ፴፭ በማቴዎስ ወንጌል
ምዕ. ፩ ቁ ፳፪ የተጠቀሱትና ሌሎችም ስለ ኢየሱስ የሚያረጋግጡ አስተማማኝ ማስረጃዎች ሞልተዋል
በእመቤታችን ድንግል ማርያም ተላለፈ ካሉት የውርስ ሃጢያት መኖር አለመኖር ጋራ ይለያያል ነብዩ
ኢሳያስም ቀደም ሲል በምእራፍ ፯ ቁጥር ፲ ፬ ትንቢቱ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም
አማኑኤል ትለዋለች በማለት የተነበየ ሲሆን እርስዎ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ባለመተዋወቅዎ እንጂ ስለ ክርስቶስ
በመጽሐፍ ቅዱሱ የተነገረው ምንም አጠራጣሪ ነገር የለውም፡፡
የእመቤታችን ማርያም ግን መልአኩ ገብርኤል ንጽሕናዋንና ቅድስናዋን ገልጾ ከማክበሩ በስተቀር
በዚህ ጊዜ ከአዳም ጥንተ አብሶ ነጻች (አነጻት) የሚል ከመጽሐፍ ቅዱሱ አልተጻፈም ይህን የሚያውቀው
ማደሪያው አድርጎ የመረጣት እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ማደሪያው
የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከሕፃንነትዋ ጀምሮ ከአዳም ኃጢአት ውርስ (ጥንተ አብሶ) ማንጻት
የሚሳነው ነገር የለም ቢባል እግዚአብሔር ይህን ማድረግ አይችልም እኛ ነን የምናውቀው ብሎ ሰውን
መዝለፍና መሳደብ ይገባልን? እውነት ርቃችኋለችና ምን ይደረጋል፥አቤት ጉድ ነው ለምን “ጥንቸል ወደዚህ
ቅዝምዝም ወደዚያ”እንደሚባለው ያደርጉታል? በእኔ ጽሁፍ በ፰ኛው ቁጥር ላይ የተጠቀሰው እኮ ስለ
አዋልድ መጻህፍትና ድንግል ትጸንሳለች የሰው ዘር አይደለችም የሚል ሳይሆን የኔ ጥያቄ እመቤታችን
ማርያም ከየት መጣች? የማን ልጅ ነች? ከመጽሐፍ ቅዱሱ ይህን የሚገልጽ የለም አዋልድ መጻሕፍቱ
ካልታመኑ ማስረጃው ከምን ተገኘ? የሚል ሲሆን እርስዎ ስለ ድንግል ጽንስ መጽነስ ቁጥር እየጠቀሱ
ያወናብዳሉ መልሱ ከጠፋብዎ ስህተትዎን ያርሙ እንጂ ያልሆነ ነገር ደንቅረው ስለ ብሥራቱና ስለ መጽነሷ
የሚያወሳ ቁጥር አይደርድሩ ይህን ማንም ያውቀዋል ለማምታታት ከመሞከር በቤተ ክርስቲያኗ
አልተማሩባትም አላደጉባትም በጥቅም የተሳሰሩትን ቄስዎን ለመርዳት ስለሆነ አደብ ይስጥዎት እላለሁ፡፡

ስለ ኤልያስና ሄኖክ ሞት የጠቀሳችሁትን ራዕየ ዮሐንስ ምዕ. ፲ ፩ ቁ ፩ እስከ ፰ ስመለከተው


አባቶቻቺን ይህን ብለው ያስተምራሉ ከሚል ወሬ በስተቀር የእነሱን መሞትና ለጠየቅሁት ጥያቄ ግልጽ የሆነ
ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ቁጥር ጠቅሰው አላቀረቡም፥ ቄስዎ ሲሉ ሰምተዋል መሰለኝ አባቶቻቺን ይህን
ብለው ያስተምራሉ በማለት ለማያውቅዎት መመጻደቅዎን ይተውት፥ ለመሆኑ ከየትኛው ገዳም አባት ነው
የተማሩት? ይልቅስ የተጻፈልዎትን ዝም ብለው ያቅርቡ በመጽሐፍ ቅዱሱ ያለው የጠቀሱት ቁጥር
የኤልያስንና የሄኖክን ሞት አይገልጽም ስማቸውንም አይጠራም የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. ፲ ፯ ቁ ፩ እስከ ፫
ያለው ደግሞ ሙሴንና ኤልያስን ከሚጠቅስ በተቀር ኤልያስና ሄኖክ ሞቱ አይልም፥ በአንድ በኩል እንደ
ጳጳስዎ በአዋልድ መጻሕፍት የተጻፈውን ይነቅፋሉ በሌላ መለኩ ደግሞ ሲያ”ምታቱ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ውጭ
የሆነ ቃል ያነበንባሉ አይገርምም? እባክዎን መጀመሪያ ከጸሐፊዎ ተማክራችሁ “ከመጠምጠም መማር
ይቅደም” እንዳሉት አባቶቻቺን ተምረውና አጣርተው ቢያቀርቡ ይሻላል እንጂ አንባቢውን ሕዝብ
በዝባዝንኬ ጽሁፍ ለማሰልቸት አይሞክሩ የርስዎን ሐተታ የሚያነብበት ጊዜ የለውም፥ ሥራውን ይሥራበት
የኔንም ብዕር ሥራ አያስፈቷት፡፡

በማጠቃለያዎ ላይ “በነገረ ሃይማኖቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን ከቅድስት እናት ቤተ


ክርስቲያናችን ጥላና ጥበቃ ስር ወጥታ በገለልተኛነት ብትገኝም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ችግሩ በቅርብ
ተፈትቶ ለማየት ተስፋና ምኞታችን ነው፥ አባታችንም ቄስ አስተርአየ ጽጌ ኦርቶዶክስነታቸውን
አስመስክረዋል፡፡” ላሉት ቀድሞውንስ ቢሆን በቄሳችሁ ጀብደኝነት ቤተ ክርስቲያናችሁ መቼ በእናት ቤተ
ክርስቲያኗ ሥር ሆነችናነው ከናት ቤተክርስቲያኗ ተለይታ ያሉት ማንን ለማታለል ነው? መርምሬ
እንደደረስኩበት የነገረ መለኮት ጉዳይ ሳይነሳም ቢሆን በየሄዱበት ቦታ የቤተክርስቲያንን ምእመናን ይከፋፍሉ
የነበሩት ቄሳችሁ አይደሉምን? እዚህ ከተማስ ከመጡ ወዲህ አብረዋችሁ አልነበራችሁምን? በቄሳችሁ
አማካይነት በሲኖዶስ ሥር አንሆንም እኛ ጀብደኞች ነን ብላችሁ የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ከሲኖዶሱና
ከአባት ጳጳስ ለይታችኋት ሲቸግራችሁ ብቻ አቡነ ይስሐቅን ትጠሩ እንደነበራችሁ እንዴት ረሱት? የቅርብ
ጊዜ ትዝታ ስለሆነ የሚረሳ አይደለም፥ በቅርቡም በቤተ ክርስቲያናችሁ የነበረው ጭቅጭቅ መከፋፈልን
ያጸናው ይኸው ስለነበር አሁን አይመጻደቁ፡፡
በአጠቃላይ ቄሳችሁ ቄስ አስተርአየ ጽጌ በየቦታው እየተዘዋወሩ ባገለገሉባቸው ቤተክርስቲያናት ሁሉ
ራሳቸውን በራሳቸው ሊቅ እያደረጉ እኔ ያልኩትን አሜን ብላችሁ ካልተቀበላችሁ በማለት ከእውንት
የራቀውን አባባላቸውን ያልተቀበሉትን የቤተ ክርስቲያን አባላትና ምዕመናን እንዲሁም መዘምራንና በዚያ
ቤተ ክርስቲያን ተገልጋይ የሆነውን ሁሉ እየከፋፈሉና እያጋጩ ብሎም ካቶሊክ ሆነዋል በማለት እየወሸከቱ
በምቀኝነት ተነሳስተው ለማስጠላት የሚፈጽሙት በጣም አሳዛኝና አስነዋሪ ድርጊት አሁን እያደር ሁሉም
ሰው ስላወቀባቸው እውነት አስመስለው ከሚረጩት ዲያብሎሳዊ መልእክት እንዲገቱ ብትመክሯቸው
መልካም ነው እላለሁ፡፡

የሕዝቡን አመለካከት ለመለወጥና ብሎም ለመበከል ስትሉ “የካቶሊክ እምንት” “ነገረ መለኮት”
እያላችሁ የእውነተኛውን ኦርቶዶክስ አማኝ ሕሊና አትመርዙ፡፡ ነገረ መለኮቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን
ኃጢአተኛ ነች አላለም እናንተ እንዲሁ ሰው አይደለችም ብላችሁ ነገረ መለኮቱን ለማፋለስ ከተነሳችሁ የግል
እምነታችሁ ነው፡፡ እኛ እመቤታችን ሰው ነች ኃጢአት የሚባል ነገር የለባትም ነው የምንለው እባካችሁን
ሄሮድስ ከነ ልጇ ለመግደል እንዳሳደዳት ሁለተኛው ሄሮድስ አትሁኑባት፡፡

እግዚአብሔር አሳዳጆቿን ይገስጽላት፥


ሁላችንንም በበረከት እጁ ባርኮ ይጠብቀን፡፡
አሜን