You are on page 1of 7

የብፁዕ አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የሕይወት ታሪክ

የብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ
ሲኖዶስ አባል አጭር የሕይወት ታሪክ፣

ብፁዕነታቸው ባላቸው ሰፊ ዕውቀትና የሥራ ልምድ ባሳለፉት ረጅም ዘመን የሠሩአቸው


ሥራዎች እጅግ በርካታ በመሆናቸው አጠቃላይ የሕይወት ታሪካቸውና የሥራ ፍሬአቸው፣
ወደፊት በመጽሔት በስፋት የሚገለጽ ቢሆንም ለዛሬው አጠር ባለ መልኩ በሚከተለው
ሁኔታ እናቀርባለን፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ፣

ከአባታቸው ከመምህር መንግሥቱ ረዳ፣

ከእናታቸው ከእመይት እጥሪቱ ብሩ፣

በቀደሞው አጠራሩ ጎጃም ክፍለ ሀገረ በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በቡሬ ሽኩዳድ ወረዳ
በምዕራፈ ቅዱሳን ሱቪ አቡነ ገበረ መንፈስ ቅዱስ በ1911 ዓ.ም ተወለዱ፡፡

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ፀንገፋ ማርያም ከነበሩት ከመሪጌታ ሞገስ ካሣ ከመልክአ


ፊደል እስከ ጸዋትዎ ዜማ ተምረው ከቀዳማዊው ብፁዕ አቡነ አብርሃም መዓረገ ዲቁና
ተቀብለዋል፡፡

ከዚያም ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ ወደ ቅኔ ጉባኤ ትምህርት ቤት በመሄድ፣

ሀ. መንግሥቶ ኪዳነ ምሕረት ከነበሩት ከመምህር ያሬድ ተክለማርያም፣

ለ. ብቸና ደብረ ብርሃን ከየኔታ ውብሸት፣

ሐ. ታዕካ ነገሥት በዓታ ከመጋቤ ብሉይ ጌራ ወርቅ ጥበቡ፣ ቅኔ እስከ አገባቡ

ተምረው ተመርቀዋል፡፡

1
ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ፣

እንደገና ወደ ዜማ ትምህርት ቤት ተመልሰው ከመጀመሪያ መምህራቸው ከመሪጌታ ሞገስ


ካሣ፣ ግምጃ ቤት ማርያም ከነበሩት ከመሪጌታ አዕምሮ የዜማ ትምህርት በሚገባ
ተምረዋል፡፡

እንዲሁም አቋቋም ትምህርት ቤት በመሄድ፣

 ግምጃ ቤት ማርያም ከመሪጌታ ዋካ፣


 ጐንደር ከመሪጌታ ሥርጋዌ፣
 አደባባይ ኢየሱስ ከነበሩት ከታዋቂው ሊቅ ከአለቃ የማነ ብርናን የአቋቋም
ትምህርታቸውን ተምረውና አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡

ትምህርት በቃኝ የማይሉት ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ፣ ወደ መጽሐፍ የጉባ›?


ትምህርት ቤት በመሄድ፣

 ጐንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ከነበሩት ከታዋቂው ሊቅ ከአለቃ አየለ


ዓለሙ፣
 አዲስ አበባ ታዕካ ነገሥት በዓታ ከብሉይ ተክሌ የመጻሕፍተ ብሉያት ትርጉሜ፣
 ጐንደር ግምጀ ቤት ማርያም ከመምህር ክፍሉ የሐዲሳትን ትርጓሜና ፍትሃ
ነገሥት፣
 ጐንደር ኀመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረትና ዐቢየ እግዚእ መጽሐፈ ሊቃውንትና መጽሐፈ
መነኮሳት ተምረዋል፡፡

የብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ ገዳማዊ ሕይወትና የማስተማር ሥራ፣

በዓለም ኑሮን ከመመሥረት ይልቅ ገዳማዊ ሕይወትን የመረጡት ብፁዕ አባታችን አቡነ
በርናባስ በ1974 ዓ.ም በደሴተ ጣና ከሚገኘው ዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ የአንድነት ገዳም
በመግባት በጾምና በጸሎት ተጠምደው፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን ለአራት ዓመታት
አስተምረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ብፁዕ አባታችን ባላቸው መንፈሳዊ ሕይወትና የትምህርት ችሎታ


በ1951 ዓ.ም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ እንደራሴና፣ የሐረርጌ ሀገረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ

2
በመሄድ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የክብር ቦታ ተሰጥቷቸው ለአንድ
ዓመት ቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምረዋል፡፡

ከዚያም በ1952 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድ ወደ ሐረርጌ ሀገረ
ስብከት በመላክ ላዕከ አርድዕትና በሐረር የራስ መኮንን መታሰቢያ መንፈሳዊ ትምህርት
ቤት የግብረ ገብ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ፣

ከዳግማዊ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተለያዩ ጌዜያት፣

ሀ. መዓረገ ምንኩስና፣

ለ. መዓረገ ቅስናና ቁምስና ተቀብለዋል፡፡

ከዚያም ብፁዕነታቸው በ1953 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፓትርያርክ ርዕሰ
ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሐረር ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም አስተዳዳሪ ሆነው በመሾም
ለ17 ዓመታት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው በማስጠበቅ በርካታ ሥራዎችን
ሠርተዋል፡፡

ለደብሩም ካበረከቱአቸው የሥራ ውጤቶች መካከል፣

 15 ክፍሎች ያለው ቤት፣


 የስብከተ ወንጌልና የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ፣
 የእንግዳ መቀበያና የንዋየ ቅድሳት ማስቀመጫ ፎቅ ቤት አሰርተዋል፡፡
 ለሕዝበ ክርስቲያኑ የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት የሚሰጥ የድምፅ ማጉያ ገዝተው
አበርክተዋል፡፡

ይህን ሥራ ሲሠሩም ማኅበረ ካህናቱን በማስተባበር ምዕመናኑን በመምከር በመካከላቸው


ሰላምና ፍቅር ሰፍኖ እንዲኖር ከፍተኛ አባታዊ ሥራ ሰርተዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ ያከናወኑአቸውን በርካታ ሥራዎች ከግምት ውስጥ


በማስገባትና የበለጠ ይሠራሉ ብሎ በማሰብ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በ1970 ዓ.ም ብፁዕነታቸውን ሀገር አቀፍ ወደ

3
ሆነው ቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በአስተዳዳሪነት እንዲሠሩ
መድበዋቸዋል፡፡

በዚህ ታላቅ ገዳምም ብፁዕነታቸው ለአራት ዓመታት የሠሩ ሲሆን ከአከናወኑአቸው


ሥራዎች መካከል፣

 ጥንታውያን ቅርሶችና ንዋየ ቅድሳት የሚቀመጡባቸው ዘመናውያን ባለ መስታወት


የቁም ሳጥኖችን፣
 በርካታ ምዕመናንን እያስተናገደ ያለ የጸበል ማጥመቂያ አዳራሽ እና ዘመናዊ
ቤተልሄም፣
 ወደ ደወል ቤት የሚያወጣ ከሕንፃው ጋር የተያያዘ የብረት መሰላል፣
 ከቁልቢ ከተማ ወደ ገዳሙ ማዞሪያ ላይ የስዕለት መቀበያ ሕንፃ ቤት አሰርተዋል፡፡
 በታዋቂ ሠዓሊ የገዳሙን ቤተ ክርስቲያን በጥሩ ሁኔታ ማሳል እንደ ምሳሌ
የሚጠቀሱ ዓበይት ሥራዎች ናቸው፡፡

በዚህ ሥራ ላይ እንዳሉ በአላቸው የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ ችሎታ ተመርጠው


በመንበረ ፓትርያርክ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ሆነው ለአንድ ዓመት አገልግለዋል፡፡
ከዚያም በ1976 ዓ.ም የመንበረ መንግሥት ግቢ ቅዱስ ገብርአል ገዳምን እንዲያስተዳድሩ
ተመድበው ለሰባት ዓመትት ገዳሙን አስትዳድረዋል፡፡

ለዚህ ታላቅ ገዳምም፣

ሀ. ለገዳሙ አገልግሎት የሚሰጥ ሰፊ ቦታ በማስከለል፣

ለ. ለንዋየ ቅድሳት መሸጫ ሕንፃ ቤት በማሠራት፣

ሐ. ከአንድ ሽህ በላይ ምዕመናንን እያስተናገደ ያለ አዳራሽና ስድስት ሕፃናትን

በአንድ ጊዜ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የሚያሰጥ የክርስትና ማጥመቂያ

ቤት፣

መ. አጠቃላይ የገዳሙን ንብረትና ንዋየ ቅድሳት ሊይዝ የሚችል ታላቅና ሰፊ

መጋዘን አሰርተዋል፣

4
ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ የብሉያትና የሐዲሳት የቅኔና የዜማ እንዲሁም የአቋቋም
ምሁር ከመሆናቸው በላይ በረጅም ጊዜ የሥራ ልምዳቸውና ቅድስና በተመላው መንፈሳዊ
ሕይወታቸው ከታላላቅ አባቶች መካከል በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው ጥቅምት 18 ቀን
1983 ዓ.ም በወቅቱ በነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ
ጳጳሳት ጵጵስና ተቀብለዋል፡፡

በዚህ ደረጃም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ሆነው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን
ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ያለፍርድ የሰው ሕይወትን ይቀጥፍ የነበረው የደርግ መንግሥት


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክትስቲያን ፓትርያርክ የነበሩትን ሰማዕተ ኢትዮጵያ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ያለምንም ጥፋት በእስር ቤት አስፎ ሲያንገላታቸው
ቆይቶ በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል የቀብራቸውንም አድራሻ በማጥፋት መላ ሕዝበ
ክርስቲያኑንና የኢትዮጵያን ሕብረተሰብ ሲያነጋግርና ሲያሳስብ ቆይቶ በኢህአዴግ ዘመነ
መንግሥት መልካም ፈቃድና በቅዱስ ሲኖዶስ አሳሳቢነት በብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ
የኮሚቴ ሊቀ መንበርነትና ግምባር ቀደም የጉዳዩ አንቀሳቃሽነት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ
ቴዎፍሎስን ዓፅም ከ13 ዓመት በኋላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተረክባ ዓፅማቸው
በጸሎተ ፍትሃትና በክብር በመካነ ሕያዋን ጐፋ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በክብር
አርፏል፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ ባላቸው ታላቅ መንፈሳዊ አቋምና የሥራ ወዳድነት
ራሳቸውን ችለው የአንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ቢመደቡ የበለጠ ውጤታማ
እንደሚሆኑ ታምኖበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጰጳሳት
ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አበያተ
ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የዓለም ኃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት
አርቆ አሳቢነትና አስትዋይነት የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ
ተመድበዋል፡፡ በመቀጠልም በቀድሞ አጠራሩ ጐጃም ተብሎ ይጠራ የነበረውን በሙሉ
በሊቀ ጳጳስነት ሲመሩ ቆይተው በ1986 ዓ.ም የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሆነው ተመድበዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ በርናባስ በዚህ ሀገረ ስብከት ተመድበው ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ እጅግ
በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡

5
አንዳንዶችን ለመጥቀስ ያህል ለረጅም ዘመናት ጠፍተው የቆዩትን ገዳማት መልሶ
በማቋቋም ለምሳሌ፣

 በጢስ ዓባይ አካባቢ የሚገኘውን ማይ ሀፁራ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምን በግላቸው
አሰርተዋል፤
 በጣና ሐይቅ መካከል በሚገኘው ደሴት፥ እንጦንስ ኢየሱስ የሴቶች አንድነት
ገዳምን እንደገና መልሶ በመመሥረት፥ በአሁኑ ሰዓት የመናንያን መነኮሳይያት
የአንድነት ገዳም ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
 እንዲሁም በቡሬ ወረዳ የምዕራፈ ቅዱሳን ሱቪ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ደብር
ጠቅላላ ወጭውን ሸፍነው በዘመናዊ ፕላን አሰርተዋል፡፡
 ከዚያም በተጨማሪ በባሕር ዳር ከተማ የፈለገ ግዮን አቡነ ተክለ ሃይማኖት
አንድነት ገዳምና በባሕር ዳር ማረሚያ ቤት ግቢ ለታሪሚው መንፈሳዊ አገልግሎት
በመስጠት ላይ ያለውን የእመቤታችን ብዙኃን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አመራር
በመስጠትና የቅርብ ክትትል በማድረግ አሳንጸዋል፡፡እነዚህን በምሳሌነት ጠቀስን
እንጂ ከ80 በላይ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን አሰርተዋል /አሳንጸዋል/፡፡
 ትምህርት ቤትንም አስምልክቶ ብፁዕነታቸው ባላቸው መንፈሳዊ አባትነት ታዳጊ
ሕፃናት የሀገሪቸውን ባሕል፥ የቤተ ክርስቲያናቸውን ትውፊት ከዘመኑ ትምህርት
ጋር አጣምረው እንዲማሩና ከወላጆቻቸው ጀምረው ለወገኖቻቸውና ለሀገራቸው ለነገ
ታማኝ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ በባሕር ዳር ከተማ በቀበሌ 16 ቤዛ ብዙኃን አፀደ
ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲከፈት አድርገው በአሁኑ ወቅት
በርካታ ታዳጊ ሕፃናት መንፈሳዊና ሥጋዊ ትምህርቱን አጣምረው በመማር ላይ
ይገኛሉ፡፡

ለዚህም ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ከከተማ አገልግሎት ከ2000 ካሬ ሜትር በላይ ተጨማሪ


ቦታ አስፈቅደዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርናባስ በዚህ ትምህርት ቤት ላይ የነበራቸው ራዕይ በሂደት 2ኛ ደረጃና


ከዚያም በላይ እስከ ኮሌጅ ደረጃ ለማሳደግ ነበር፡፡

ለመግቢያ ያሕል ከዚህ በላይ ያሉት ተጠቀሱ እንጂ ብፁዕነታቸው ወደዚህ ሀገረ ስብከት
ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ያሰሯቸው አብያተ ክርስቲያናትና
ያከናወኑአቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

6
በተጨማሪም በቡሬ የደብረ ፀሐይ አግኒ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር መንበር በብር 18.000.00
/አስራ ስምንት ሽህ ብር/ በራሳቸው ወጭ አሠርተው ወደ ቦታው በመላክ በመጠባበቅ ላይ
እንዳሉ ለርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ ህመም
እንደተሰማቸው ተናግረው የነበረ ሲሆን ወደ ሃገረ ስብከታቸው መቀመጫ በመመለስ ያለ
ጻዕረ ሞት በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ግንቦት 20 ለ21 ከምሽቱ በ3፡00 ሰዓት በመንበረ
ጵጵስናቸው ይህን ዓለም በሞት ተሰናብተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው የቅዱስ ሲኖዶስን ስብሰባ ከፈጸሙ በኋላ ጊዜ እረፍታቸው በ21


የእመቤታችን ዕለት መሆኑን አስቀድመው ገዳማዊ ሕይወት ላላቸው አንድ ታላቅ ገዳማዊ
ባሕታዊ ተናግረው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር። መዝ 115፥6