You are on page 1of 26

ለ አእምሮ – መጽሔት – አዲሱ የሰኔ 2005 / June 2013 ዕትም

Posted on June 13, 2013

የሰኔ 2005 / June 2013 እትም…ቅጽ 1 ፣ቁጥር 3

ለ አእምሮ – መጽሔት ፤ የሰኔ 2005 / June 2013 እትም…ቅጽ 1 ፣ቁጥር 3 / (እዚህ ይጫኑ!)

~1~

„ሳይደግስ አይጣላም“
Posted on June 12, 2013

„ሳይደግስ አይጣላም“
„ሳይደግስ አይጣላም“ ይላል አንድ በብዙ የሕይወት ተመክሮ ላይ የተመሰረተው የአገራችን አባባል።
ይህ የአባቶች አነጋገር፣ ማመን ለማይፈልግ አንድ ሰው፣ ቢያንስ የቅንጣት ያህል፣ ትንሽ ዕውነት
እንዳለው በዚህ ጽሑፋችን ለማስታወስ እንፈልጋለን።።
…የዋልድባ ገዳም መደፈር፣ …የሞስሊሞቹ የነጻነት ጥያቄ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት በሞት
መለየት፣ ….የግንቦት 25ቱ የሕዝብ ሰልፍ፣ አሁን ደግሞ የአባይ ውዝግብ፣ ….እነዚህ ሁሉን
በአንዴ እና በተከታታይ፣ በአጭር ጊዜያት ውስጥ እናያለን ብሎ የገመተ፣ ሰው የለም።
በሌላ በኩል ፣ ከእንግዲህ ምን ይመጣል ብሎ ከመገመት ሌላ፣ በእርግጠኛነት፣ ይህ ይሆናል ያ
ይደርሳል ብሎ ከአሁኑ ለመናገር አይቻልም። ይህን ለማለት፣ ከእሩቁም ለማየት፣ ነቢይ ወይም
ጠንቋይ መሆንን ይጠይቃል።
እኛ በአለን „ዕውቀት“ሁለቱንም፣ ክፍሎች አንወክላቸውም። ግን፣ በአሁኑ ሰዓት አንድ ማለት
የምንችለው ነገር ቢኖር፣ አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት፣ አንድ ቡድን፣…. በእኛና በአገራችን
በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ የሚወስንበት ጊዜ፣ በትክክል ደፍረን ለመናገር፣ ቀስ እያለ፣ ዘንድሮ በዚህ
አመት እያከተመ የመጣ ይመስላል። ነጮቹ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር፣ „ ዘ ቢግኒንግ ኦፍ ዘ ኢንድ ኦፍ
ዛት ኤራ….“/The beginning of the end of that era…./ ይሉታል።
አሁንም ስለ ነጻነት፣ አሁንም ስለ የሕዝብ ጥያቄ ፣ አሁንም ስለ ፖለቲካ፣ እንደገና አሁንም እኛን
የሚያለያየን ሳይሆን እንድ የሚያደርግን ነገር ምንድነው በሚለው ጥያቄ ዙሪያ፣ ይህን ጽሑፍ፣
ለአእምሮን አዘጋጅትን እንድትመለከቱት፣ አቅርበንላችኋል።
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
ይልማ ኃይለ ሚካኤል

~2~

ለ አእምሮ – መጽሔት – የሰኔ 2005 / June 2013 ዕትም/ ቅጽ 1 ፣ቁጥር 3
Posted on June 12, 2013

አዳዳስ ጽሁፎችና ሰነዶችለ አእምሮ – መጽሔት – አዲሱ የሰኔ 2005 / June 2013 ዕትም
የምን ነጻነት? ለምን፣ ለማን ወይስ… ?
“ሊበርቲ”/Liberty…ዲሞክራሲ
ፖለቲካ ምንድነው? (ክፍል ሁለት)
ጊዜው ደረሰ …
ከኪነ፥ጥበብ ዓለም
OPEN LETTER: SMNE calls on Prime Minister Hailemariam
Desalegn
ግንቦት 25

~3~

የምን ነጻነት? ለምን፣ ለማን ወይስ… ?
Posted on June 12, 2013

ርዕሰ እንቀጽ
የምን ነጻነት? ለምን፣ ለማን ወይስ… ?

/1*

ሁሉም ይናገር! የመናገር መብት ለሁሉም…
„ዝምታው ምንድነው? የፈለክኸውን የልብህን ተናገር እንጂ…“ ይላል አንደኛው ጥሪ። “…እባክህን
እየደጋገምክ የልብህን ጻፍ እንጂ ወዳጄ…ፈረሃቻው ለምንድነው!“ ይላል ሌላው። „…ኑ እኔ ጋ
ተሰብሰቡ! በሩም አዳራሹም ለእናንተ ለልጆቼ ክፍት ነው።“ ይላል ሦስተኛው። „…የልብህን ትርታ
ተከትለህ፣ ሰምተህ ወይ ተቃወም! ወይም ደግሞ ደግፈን እንጂ“ ብሎ ይጣራል አራተኛው።
እንደዚህ ዓይነቱን ጥሪ ሕገ-መንግሥቱን መሰረት አደርገው በሕዝቡ መካከል እዚህ የሚያናፍሱት፣
ተቃዋሚ ፖቲከኞች ሳይሆኑ (ቢያደርጉ የሚከለክላቸው የለም) የጀርመን የግል የቴሌፎን ኩባኒያ
ድርጅቶች፣ የፖስፓና እዚህ ባዶ እየሆነ የመጣው የጀርመን ቤተክርስቲያን ቄሶች ናቸው።
ማስታወቂያውም „ ነጻነትን“ ፈልጎ አግኝቶአል።
አንድ የሰውነት ማጠናከሪያ የጅምናስቲክ ማሰልጠኛ ሰቱዲዮማ „…አትፍራ ቆርጠህ ተነስተህ ፣
ሐሳብህን፣ ፍላጎትህን ዛሬውኑ በሥራ ተርጉመው!… ጎበዝ አይደለህም እንዴ!…“ የሚለውን
የለውጥ ጥሪ ፣ ከተማው ውስጥ በያለበት ለጥፎ፣ ወኔ ለመቀስቅስ ሙከራ –የተከተለው ሰው
ምንያህል እንደሆነ ባይታወቅም– አድርጎአል።
አንዲት ልጅማ „ አሥራ ስምንተኛውን የልደት በዓሌን ብቻዬን ማክበር ስለማልፈልግ፣…አንተም፣
አንቺም፣ እሱም እሱዋም….ሁላችሁም ተጋብዛችሁዋል፣ ኑ! ብሉልኝ ጠጡልኝ…“ ብላ ትዊተሩዋን
ልካ ወደ አምስት ሺህ ሰዎች ተጠራርተው መጥተው የመንደሩን ሰዎች፣… ፖሊሶቹንም ግራ
አጋብተው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተጠይቀዋል። እንግዲህ ሐሳብን መግለጽ ወንጀል አይደለም።
„ሳላንዛዛው” ሐሳቤን ዛሬ በአንድ ግንዛቤ ሸብ ላድርገው።

~4~

ብዙ መንገዶችን በታሪካችን ፣ ሌሎቹ ሲወድቁና ሲነሱ፣ እኛ ኢትዮጵያኖች፣ ብቻችንን ተጉዘናል።
አንድ ትልቅ ቁም ነገር ላይ ግን ሳንደርስ የጀመርነውን መልካም መንገድ እራሳችን ባልሆነ ትምህርትና
ፍልስፍና ሳናውቅበት ቀጭተነው፣ ይኸው ዛሬ ተበታትነን፣ የአውሬ፣… የተኩላ፣… የጅቦች ራት
ለመሆን በጨለማ ዓለም ውስጥ ፣ መውጫና መግብያው በማይታወቀው ጫካ ውስጥ፣ ሁላችንም
ወድቀን ፣ ተዘርተን፣ እንገኛለን።
ለአገራችን ነጻነት፣…. የባዕድ ሰው ጥገኛ አሽከር፣ ….ባርነትን፣ጨርሶ የማንወድ ኢትዮጵያኖች፣ አገር
አቋርጠው ሊይዙን የመጡትን ጠላቶች ሁሉ የፈለገውን ያህል መስዋዕትንተ ከፍለን ፣ የአገራችንን ፣
የባነዲራችንን ነጻነት ጠብቀን እስከ ዛሬ ድረስ (ይህ የእኛ ሳይሆን የአባቶቻችን ሥራ ነው )
ቆይተናል።
ግን የዚያኑ ያህል ፣ እኛ የዛሬው ትውልድ (አባቶቻችንን ብቻ መክሰስ እንወዳለን፣ እንጂ ) ከጨለማ
ወደ ብርሃን፣ „ከባርነት“ ወደ ሙሉ ነጻነት፣ ሰበአዊ ክብሩና መብቱ የማንም ሰው፣ ትልቅ ይሁን
ትንሽ፣ በማንም ( ኮሚኒስት ይሁን ነጻ- አውጪ፣ ሽፍታ ይሁን፣ ተገንጣይ፣ ዲሞክራት ይሁን
ሶሻሊስት፣ ወታደር ይሁን፣…ቄስ ወይም ኢማም….) እንዳይረገጥ፣ እንዳይደፈር፣ የፈለግነውን ፣
ማድረግና መተው፣….መጻፍና መናገር፣ መመራመርና መጠየቅ…መተቸትና መቃወም ፣ በሕግ
ለተረጋገጠብት የፓርላማ ሥርዓት፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ፣ ብድግ ብለን ተነስተን አለመታገላችን፣
የሚያሳዝን ስለሆነ መጠቀስ ያለበት ፣ይቅርታ አድርጉልኝ ፣ጉዳይ ነው። ይህም ስለሆነ፣ ይህቺን ነገር
አነሳለሁ።
የእያነዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሙሉ ነጻነት ጉዳይ፣ ደግሞ፣ በቀጠሮ ገና ሃምሳና መቶ አመት
የሚሰጠው፣ የአራዳ ልጆች ጨዋታ አይደለም። ይህ መብት፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው።
ከፍጡሮች ሁሉ ፣ ከእንስሶችና ከአራዊቶች ሁሉ፣ ለእኛ በአምሳሉ የሰጠን መብት፣ በምላሳችንን
እነድንናገርበት፣ በአእምሮአችን እንድናስብበት፣ በእጃችንን እንድንጽፍበት ነው።…. መናገር መጻፍ፣
ማመዛዘን፣ ክፉን ደጉን ለይቶ፣ መመልከት፣ ዱሮም የነበረ፣ አሁንም ያለ መብት ነው።“
አሁን እንግዲህ ጊዜው፣ ይህን ሐቅ በእርግጥም የምናይበት ጊዜ፣ የደረሰ ይመስላል። እዚያ ላይ
የሚደረሰው ግን በአሁኑ ሰዓት ፣ በዚህ በያዝነው በ21ኛው ክፍለ-ዘመን አንዱ „ሰለመገነጠል“
ሲያወራ፤ ሌላው „ለኢትዮጵያ አንድነት“ ሲጮህ አይደለም።
ወይም አንዱ ሥልጣን ላይ የወጣው ኢህአዴግ፣ ስለ „አምባገነን ሥርዓት“ መኖርና መጠናከር
በኢትዮጵያ ሲከራከር፣ ሌላው „ለዲሞክራቲክ መብቶች መከበር“ ሲታገሉም ብቻ አይደለም።
ሁለቱ እላይ የተጠቀሱት ኢትዮጵያን ለማተረማመስ በአገሪቱ ላይ የተወረወሩት ፍልስፍናዎች፣ ማለት
„የመገንጠልና የአምባገነን ሥርዓት አስተሳሰብ“ ይኸው እንደምናየው ሌሎቹ አገሮችና መንግሥታት
፣ ከሁዋላችን ተነስተው እኛን በሥልጣኔ እርምጃቸው፣ ወደ ኋላ ጥለውን እንዲሄዱ አድርገዋል።
በአለፉት አርባና ሃምሳ አመታት በእነዚህ „ትምህርቶች ተሳክረን“ ምንስ ያመጣነው አዲስ ነገር አለ?
ብለን እራሳችንን እንጠይቅ።… ምንስ ለአገሪቱና ለሕዝቡ የሚጠቅም አዲስ ነገር ፈጠርን? በዓይን
የሚታይ አዲስ ዕውቀትና ጥበብ፣ ልዩ የሆነ ፣ የዓለም ሕዝብ ከእኛ ሊማር የሚችል ነገር ለዓለም
ሥልጣኔ፣ ለመሆኑ በአለፉት አመታት አበረከትን ወይ?… አቀረብን እንዴ? ….እስቲ ምን?
ዞር ብለን ከተመለከትን ትርፉ፣….ሞት፣…ስደት፣ ለቅሶ፣…እሥራትና ግርፋት፣ በሽታና ረሃብ፣
ሁዋላ ቀርነትና ድንቁርና እና ጦርነትን ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ ዱሮ ማንም ያልደፈረውን
መሬታችንን በኢንቨስትሜንት ስም ፣ ቤልጅግና ማዮርካን የሚያካክሉ አገሮች፣ ለሃምሳ፣ ስድሳና
ዘጠና አመታት ለባዕድ መንግሥታትና ቱጃሮች፣ በሊዝ ስም „ ይሸጣሉ“። ነገ ከሃምሳ አመት በሁዋላ
ምን እንደሚመጣ እናውቃለን?
ጓዙን ፣…ኮተቱን፣ ቅራቅንቦውን፣ ዘመዱንና ጠባቂ ወታደሩን ከባህር ማዶ አምጥቶ፣ ከፍዬበታለሁ
ብሎ ቢሰፍርበት ማን ያግደዋል? ደግሞም ይህን ማድረግ ይችላል። ከታሪክ እንደምናውቀው ቀላል
ነው።

~5~

አሰብ የተያዘችው፣ በሁዋላም ይህች የኢትዮጵያ አካል „ኤርትራ“ ሚባለውን አዲስ ስም ይዛ
ጣሊያኖች እጅ የገባችው፣ ጅቡቲ…. ኬንያና ኮንጎ፣ ደቡብ አፍሪካና ሮዴይዢያ፣ ጋናና ናይጄሪያ፣
…ሱማሊያ፣ ታንዛኒያ….የትም ቦታ ወረድ ብላችሁ፣ ተዘዋዉራችሁ ተመልከቱ፣ እነዚህ ሁሉ አገሮች
በአውሮፓ ተይዘው በሁዋላ ባሪያና የቅኝ ግዛት የሆኑት፣ በቀላል ዘዴ ነው።
በመጀመሪያ አንድ ሰው መጥቶ ባንዲራውን ይሰቅላል። በሁዋላ ጓደኛው መጥቶ ድንኳኑን ይተክላል።
ከዚያስ? ወታደር መጥቶ ይሰፍርበታል። አሰብ ጥሩ ምሳሌ ናት። የሆነውም ልክ እነደዚሁ ነው።
እንደምናውቀው በዘርና በጎሣ አውሮፓውያኖቹ፣ አፍሪካን ከፋፍለው፣ ጠበንጃና ጦር አቅርበው፣
እርስ በራስ፣ አዋግተውና አፋጅተው፣ በሁዋላ አስታራቂ ሁነው አካባቢውን፣ ድፍን አፍሪካን
መቆጣጠር ችለዋል። ተቆጣጥረዋል። ሰውንም ቀስ ብለው ባሪያ አድርገው ሸጠዋል።… ተግባባን?
እሩቅ አይደለም ፣ በቅርቡ የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሚስተር ሔንሪ ኪስንገር
እንደጻፉት፣….አንዴ ኒክሰንና ማኦ ሴቱንግ „የሰበአዊ መብትን፣ መከበር ጉዳይ አንስተው ሁለቱ
መሪዎች ይከራከራሉ።… ኒክሰን፣ በትክክል፣ አንድ የቻይና ተወላጅ አገሩን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ
መሥራት፣ መጎብኘት አይችልም።…ይህ አሰራራችሁ መቀየር አለበት፣… የሰው ልጅ አገሩንም ለቆ
በነጻ መንቀሳቀስ አለበት፣ ይህ መብቱ እኮ….ነው፣ ሲሉ ማኦ ሴቱንግ ጨዋታውን አቋርጠው“
ኪስንገር ታሪኩን እንደ ተረኩልን “….ለመሆኑ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት… በአሁኑ ሰዓት ስንት ሰው?
…ስንት የቻይና ተወላጅ ፣ አሜሪካን መሬት ላይ ተቀብሎ እነሱን ለማስተናገድ ተዘጋጅቶአል?
….ስንት ሰው አዘጋጅቼ ልላክሎት፣ …20 ሚሊዮን ቻይናዊ ፣ 50 ወይስ 70 ፣ ወይስ… 90
ሚሊዮን ? እርሶ ነገ ኒዎርክ ላይ ፣ እነዚህን ሁሉ ሰዎች በትልቅ ክብር ሊቀበሉ ይችላሉ?…“ ብለው፣
„ታላቁ ሊቀመንበር“ ማኦ፣ ኪስንገር፣ አስደነገጡን ይላሉ።
ሕንድና ቻይና ፣ ነገ በቀላሉ …ወደ ኢትዮጵያና ወደ አፍሪካ ፣ መቶና ሁለት መቶ፣ ሦስትና አራት
ሚሊዮን ሰው ብድግ አድረገው፣ አንጠልጥለው መላክ ይችላሉ። ለእነሱ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ
አገሮች፣ ሁለት መቶ ሚሊዮን ቻይናዊ አገሩን ለቆ ቢሄድ ደስታውንም አይችሉም። ባጀቱም ለዚህ
ተመድቦአል። ይህ፣ በሌለ ነገር „…አማራው ወረረን“ ስለዚህ „ የመገንጠል መብት- ነጻነት“ በሚሉ
ሰዎች ዘንድ፣ ከግምት ውስጥ ለመሆኑ ገብቶ፣ በደንብ ታስቦበታል? እንግሊዝ ዓለምን ያኔ የያዘቺው
በዚሁ መንገድ ነበር።
ዞረን ዞረን እኛ ኢትዮጵያኖች ዛሬ “ ማሰብና፣… የማሰብ ነጻነት“ያስፈልጋል የሚል ደረጃ ላይ
ደረሰናል። ግን ለመሆኑ ….ነጻነት፣ ….ሊበርቲ፣… ሰበአዊ መብቶች፣ የሚባሉ ነገሮች፣
….ምንድንናቸው? ምንድነው? ያስፈልጉናል እንዴ አሁን? „ለጥቁር ሕዝብ ለአፍሪካ፣ ለደሃዋ
ለኢትዮጵያ ደግሞ፣ ሊበርቲ ምን ያደርግላታል?“ „ዲሞክራሲ እኮ የሠለጠኑ ሕዝቦች የነጮች
ጨዋታ ነው።“ ይህን የሚሉ አሉ።
„…አንድ ሰው ፣ አንድ ቡድን ያንን አካባቢ ጸጥ ለጥ አድርጎ፣ (አንድ ድርጅት) በጠበንጃ ያን ሕዝብ
ለ20፣ለ30፣..40 አመትና አመታት በተከታታይ ቢገዛቸው፣ ምን ይሆናሉ“? „እንደ ቻይና፣ እንደ
ሰሜን ኮሪያ አንድ ቀን ለኢትዮጵያም ዕድገት ያመጣላቸዋል።“
„ንጉሱም ይህን ያህል አመት ገዝተዋል። …ለምን „ትግሬዎቹ“ ገዙ ብለን አሁን እንቃወማለን“?
…ይህማ ምቀኝነት ነው!.. ለሌቹም ተራው ያልደረሳቸው፣ ኦሮሞዎቹ፣ ጉራጌዎቹ፣ ሱማሌዎቹም፣…
እነሱም ተራውን ጠብቀው ሥልጣኑን ተቀብለው 20፣30…40 አመት፣ ያቺን አገር መግዛት
አለባቸው።“ የሚሉ ቅዠቶችን ከብዙ አቅጣጫና አካባቢዎች እንሰማለን። ግሩም አስተሳሰብ ነው።
ግን ማን ነው በኢትዮጵያ ሕዝብና በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ መወሰን የሚችለው? ሕዝባዊ ወያኔ?
ወይስ ኢህአዴግ? ጥቂት የፖሊት ቢሮ አባሎች? „ነጻ-አውጪ“ ነን ባዮች? እዚያና እዚህ ብቅ ያሉ
ድርጅቶች? የአውሮፓ ማህበር? የእንግለዚና የአሜሪካ መንግሥታት? ቻይና እና ሕንድ? ወይስ
የኢትዮጵያ ሕዝብ? ሕዝቡስ እንዴት ድምጹን ያሰማ?

~6~

ለመሆኑ „ነጻነት“ ምንድነው? ….የእኔ ነጻነት፣ የአንተ፣ የእሱዋ፣ የእሱ? የጎረቤት ነጻነትና ነጻነታችን
ምን ያህል ነው?
ማነው ዛሬ መናገር የተፈቀደለት? ማነው የተከለከለው? ከልካዩስ ማነው? መከልከሉንስ ለእሱና
ለእሱዋ ማን ፈቀደላቸው?
እንደ ጠበልና እንደ መስቀል በዚህች ዓለም ላይ የሚገኙ አምባገነኖች የሚፈሩት አንድ ነገር ቢኖር፣
ሌላ ነገር ሳይሆን ( ጦርነትማ እንጀራቸው ነው! ጦር አይፈሩም!) ያቺን ፣ … የሕዝብን ነጻ -ንግግር
፣ ነጻ – ሐሳብን፣ ነጻ- ውይይትንን፣…. ነጻ-ጽሑፍንና፣… የሚጠይቅ፣ የሚጠራጠር፤…የሚተች
ነጻ- አእምሮን ፣ (… ዕውነት፣ ዕውነት ፣ እላችሁዋለሁ) ፣ እሱዋን ብቻ ነው። ሥልጣኔ
የተመሰረተው ደግሞ በዓለም ላይ በነጻ-አስተሳሰብ፣ በነጻ- ምርምር፣ በነጻ- ትምህርትና….በነጻነት፣
… በአርነት፣ (በሌላ ቋንቋ) በሊበርቲ፣ አለጥርጥር፣ በትክክል ለመናገር ፣ በአእምሮ ነጻነት ላይ ነው።
Posted in ለ አእምሮ አዲስ እትም, ማህበራዊና ፖለቲካ /Social & political, ርዕስ አነቀጽ / Editorial | Leave a reply Edit
***

“ሊበርቲ”/Liberty…ዲሞክራሲ
Posted on June 12, 2013

ሊበርቲ፣…ዲሞክራሲ
„የሰው ልጆች ነጻ ናቸው። ግን እጅና እግራቸው በብዙ ሰንሰለት ተተብትቦ ታስሮአል።“ ጃን ጃክ ሩሶ
„ነጻነት ማንም የማይቀማኝ፣የማይሸጥ የማይለወጥ፣ የግል ሐብቴ ነው።“ ማርቲን ሐይድገር

ስዕል፥ ፔሪክለስ ለአቴን ዲሞክራሲ ሲታገሉ ለወደቁ ወታደሮች መታሰቢያ ንግግር ሲያደርግ /wikipedia
በምን ተዓምር ነው አምባገነኖች በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ በአራቱም ማዕዘን በአንዴ እንደ አሸን የፈሉት?
ማነው እነሱን የላከብን?… ለቅጣት፣… የእግዚአብሔር ቁጣ ነው ? ወይስ የሰይጣን ሥራ? ወይስ ሟርተኞች
ተደብቀው የተበተቡልን መኣት?…አምባገነኖች ከየት መጡ? እነሱስ እነማን ናቸው?
አምባገነኖች ብቅ ለማለት፣ ለመሰፋፋት፣ ሥር ሰደው እግራቸውን በአካባቢው ለመትከል፣ ሜዳውም አየሩም
አፈሩም ወሃውም፣…የሚያመች መሆን አለበት። አለበለዚያ ጠውልገው ደርቀው እዚያው ክችች ብለው ንፋስ
ይዞአቸው እንደመጣው ሁሉ ነፋሱ እነሱን እያዋከበ ይዞአቸው ይሄዳል።

~7~

ሰሜን አሜሪካ ለአንድ አምባገነን መነሳት አመቺ ቦታ አይደለም። አውሮፓም እንደዚሁ።
ላቲን አሜሪካ በተቃራኒ ተደጋግሞ እንደታየው አመቺ መንደር ነው። ግነ እነሱ ከዚያ ከደቡብ አሜሪካ ብቅ
እንዳሉ ወዲያው ተባረው ሄደዋል። ከምሥራቅ አውሮፓም ተነቅለዋል። አረብ አገሮች፣ ለቀሩትና ለተረፉት
ማስጠንቀቂያ ትሰጥቶአቸዋል።አፍሪካስ?
ከደቡብ አፍሪካ፣ ከጋና እና ከናይጄሪያ፣ ከጎረቤት አገር ከኬንያ ጭምር፣ ሁለተኛ እዚህ እንዳትደርሱ ተብለው፣
በጅራፍ፣ በምርጫ ቅጣት ተባረዋል።
A
አምባገነኖች እና የአምባገነን ትምህርት፣ በአጭሩ የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግርኤርትራንም ያጠቃልላል- የእኛ ብቻ „ልዩ በሽታ“ አይደለም።
እርግጥ የኢትዮጵያ ምድር ከሌሎቹ እብዛኛዎቹ ቦታዎችና አካባቢዎች ለአምባገነን አስተሳሰብ መስፋፋት ያመቸ
ሥፍራ ነው። ግን ከሩሲያና ከጀርመን፣ ከጣሊያንና ከእስፔን፣ ከቻይና፣ ወይም ከቬትናምና ከኪዩባ
….አይለይም።
ግን ለምንድነው? በሕንድ የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ እዚያ ያልነገሰው?…እሩቅ ምሥራቅ፣ ጃፓንንስ እንዴት
ናት? …..ኮሪያስ?… የትኛው ኮሪያ?
አንዱ የኢትዮጵያ መንግሥት „የኮራበት“፣ አንደኛው መንግሥት ደግሞ ማንም ሳይመርጠው ፣ ማንም
ሳይጠይቀው„ዝቅ ብሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ይቅርታ“ የጠየቀበት፣ የአገራችን ዘማች ሠራዊት ደማቸውን
ያፈሰሱበት የኮርያ ግማሽ-ደሴት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያኖች “….አምባገነን ከየት ይመጣል?… አምባገነንስ
ምንድነው? …አምባገነን ለዕድገት ያመቻል? ወይስ ያደናቅፋል?.. አምባገነን እሥር ቤት ነው? ወይስ
አይደለም? „ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥሩ የትምህርት ቦታ ይመስለናል።
ጀርመንም፣ ዋና ከተማዋ በርሊንም ስለ አምባገነን ሥርዓቶች፣ ስለ ኮሙኒዝምና ስለ ፋሺዝም፣ ስለ
ቶታሊቴሪያን አስተሳሰብና ሥርዓት፣ ጥናት ለመውሰድ ፈቃደኛ ለሆነ ሰው፣ ከኮሪያ ቀጥሎ ግሩም ሜዳ ነው።
ኮሪያ እንደምናየው፣ ተቃዋሚ፣ ጠያቂና ተቺ በሌለበት አገር፣ አንድ ቡድን ከመሬት ተነስቶ ሥልጣን ላይ ጉብ
ብሎ፣ እንደ የዘውድ አገዛዝ፣… ሥልጣኑንና ወንበሩን፣ አባት ለልጁ፣ እሱ ደግሞ ሲደክም ለበኩር ልጁ፣ ያኛው
ደግሞ ለልጅ ልጁ፣ አገሩንም ሐብቱንም፣ በአለሙሉ ሥልጣኑንም እንደሚያስተላልፍ ለማየትና ለመገንዘብ
አመች ሥፍራ ነው። በአዋጅ፣ አልፈው ተርፈው ሰውን በትዕዛዝ የሚያስለቅሱም ናቸው።
„ንጉሡ ሊቀመንበር“ በሰሜን ኮሪያ ያደረጉትን፣ ጄኔራሎቹንንና የጦር መኮንኖቹን፣ ካድሬዎቹንና የፖሊት ቢሮ
አባሎቹን ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ምንም እነሱን የሚያግዳቸው፣ ነገር የለም። እንግዲህ እዚያ የምናየው
ነገር ሌላም ቦታ ተቆጣጣሪ አካልና ክፍል ከሌለ፣ የማይደገምበት ምንም ምክንያት የለም።
B
በሌላ በኩል፣ ደቡብ ኮሪያና ምዕራብ ጀርመን፣ ሌሎቹ „ወንድሞቻቸው“ በቴክኒክ ዕድገት ወደሁዋላ ሲቀሩ
በምን ታአምር ይኸው እንደምናየው፣ እነሱ አምልጠው ለሄዱ ቻሉ? የሚለውን የብዙዎቻችንን ጥያቄም እነዚህ
ሁለት አገሮችን ማየት ለሚፈልግ ሰው ደህና መልስ ይሰጡናል።
በአጭሩ አንደኛው ወገን የስታሊን እና የሌኒንን፣ የማርክስና የኤንግልስን ፣ የኪሚ እና የሆኔከርን „ዕብድ“
የሚያክሉ ፎቶግራፎች በየአጋጣሚው አደባባይ ላይ፣ አንድም ጥያቄ ሳያነሱ እየተሸከሙ „ሲንቀዋለሉ“፣ ነጻነት
ያለበት የምዕራብ ጀርመን ና የደቡብ ኮሪያ ሰዎች፣ እየተመራመሩ፣ እየጠየቁ፣ እየተቹ፣ ጎበዙን የአዋቂዎቹን
ፓረቲ እየመሩጡ እዚህ፣ ዛሬ የምናየው የቴክኒክ ደረጃ ላይ እነሱ ሊደርሱ ችለዋል።
„ደቡብ ኮሪያ ያደገችው በአምባገነኖቹ ወታደር፣ በጄነራሎቹ ክንድና አገዛዝ ነው፣ ስለዚህ በኢትዮጵያም፣
በኤርትራም እንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት፣ እግሩን ተክሎ ቢቆይ መልካም ነው። ይህ ሥርዓት እንዳይነካም
መታገል ተገቢ ነው „ የሚሉ ብልጣብልጦች ድምጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአንዳንድ አካባቢ ተሰምቶአል። ይህ
ግን የመጨረሻው መንፈራገጫ ምልክት እንጂ ከጀርባው ምንም አሳማኝ ነገር እንደሌለውም የሚታወቅ ነው።

~8~

„የዓለም ዕድገት፣ የታሪክ ጉዞ፣ …ከዝቅተኛው፣ ከጋሪዮሽ ሕብረተሰብ ተነስቶ፣ በፊውዳል አድርጎ፣
ካፒታሊዝምን ይዞ ወይም ይህን ሥርዓት ዘሎ፣ ወደሶሻሊዝም ዘልቆ የማይቀረውን የኮሚኒስት ሕብረተሰብ፣
ወደፊት ይመሰርታል፣ አሰከዚያ ጊዜ ድረስን ጭቆናውንም፣ የአምባገነኑን ዱላ እንደምንም ብለህ ተቀበል ፣
ቻለው፣ አንተ ባትደርስበት ልጆችህ፣ እነሱም ካአልሆነላቸው፣ የልጅ ልጆችህ፣ የሁዋላ ሁዋላ ከጣፋጩዋ
የምድር ላይ ገነት፣ እሱዋ ከምትሰጠው መልካሙዋ ፍሬ፣ እነሱ ቁጭ ብለው ይለቅማሉ፣…እሰከዚያ ጊዜ ድረስ፣
ግን ዝም ብለህ ተገዛ!“ የሚለው የአፍዝ አደንግዝ ቅስቀሳ፣ የሰው ልጆችን ሙሉ ነጻነት፣ የሰበአዊ መብቶችን
መከበር ጉዳይ፣ ብዙዎቹ፣ ዞር ብለው እንዳይመለከቱት፣ መለስ ብለውም እንደይጠይቁና እንዳያስቡበትም፣
እነሱን አድርጎአቸዋል።
„አደሃሪ ቡርጃ፣… ሁዋላ ቀር፣ አቆርቋዠ፣ …ፊውዳል፣…ሰው በላ….“ በሚባሉ ቅጽሎችም ሌላውን ዝም
አሰኝተው፣ አምባገነኖቹ እግራቸውን፣ ቤተ-ምንግሥቱ ውስጥ ዘርግተው፣ በሕዝቡ ላይ እንዲቀልዱም እነሱን
በዓለም ዙሪያ ረድቶአቸዋል። ወደ „አልጋና ዘውድ“ ውርስ የሰሜን ኮሪያ ኮሚኒስቶችም የሄዱበት ምክንያትም
(ሌላ ነገር ሳይሆን) ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
የምዕራቡ ፖለቲከኛ እንደገና ለመመረጥ ተቀናቃኙ አርፎ ስለማይተኛለት፣ ከብዙ ነገሮች ተቆጥቦ (አሉ
ከእነሱም ውስጥ የበግ ደበሎ የለበሱ ተኩላዎች፣ ግን በፕሬሱ ይጋለጣሉ) ለአገሪቱ ችግር መፍትሔ ይፈልጋል፣
ዕውቀቱን ያሻሽላል፣ ከሕዝቡ ጋር ይውላል፣ ችግራቸውንም ያዳምጣል…። የግዛት ዘመኑም እድሜ ልኩን
ሳይሆን ገደብ እንዳለውም ያውቃል። …በሕግ ፊትም ከማንም እኩል እንደሆን እሱም ሕዝቡም፣ ስለሚያውቁ
እንደ ላይኞቹ ቀብጦ እድሜ ልኬን ልግዛችሁ ብሎ አፉንም አያበላሽም።
C
አሁን ብዙውን ሰውና አብዛኛውን ሕዝብና መንግሥታት እየሳበና እየማረከ የመጣው የዓለም አቀፉ የሳበአዊ
መብቶች መከበርና መጠበቅ፣… የዲሞክራቲክ ሥርዓትና የሕግ በላይንት፣…ነጻ-ጋዜጣና ነጻ-የሸንጎ ምርጫ፣
አስተሳሰብ…ከየት መጣ?
እንዲያው ሳይታሰብ ከሰማይ ላይ ዱብ ያለ ነገር አይደለም። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች በተለይ በፋሺሺቶቹ፣
በሒትለርና በሞሶሊኒ በሁለቱ አምባገነኖች በተጫረው ጦርነቶች በእነሱም ሳቢያ ከመጣው ፍጅት የተገኘ
ተመክሮ ነው።
ይህ የብዙ ሚሊዮንን ሰው ሕይወት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያና በሌሎች
አካባቢዎች ይዞ የሄደው ጦርነት፣ እንደገናም በዚህቺ ዓለም ላይ ተመልሶ እንዳይመጣና እንዳይነሳም፣ ለማገድ
ነው።
ይህ አንደኛው ማብራሪያ ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ የላብ-አደሩ ወይም የወዝ-አደሩ አምባገነን ሥርዓት
እተስፋፋ መምጣቱ ነው።
ለዚህ ነው በ1948 ዓ.ም ኢትዮጵያ እራሱዋ በቦታው ተገኝታ በፈረመቺው የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች
መግለጫ ላይ የሚቀጥለው አረፈተ ነገርም እንዲሰፍር የተደረገው። በመግቢያው ላይ አዋጁ “…. ሰበአዊ
መብቶችን ችላ ማለትና መናቅ የሰውን ልጅ ሒሊናን የአስጨነቁ አረመኔያዊ ተግባሮችን አሰከትለዋል…“
ይላል።
ይህም የአረመኔዎች ሥራ በቆዳ ቀለምና በዘር ጥላቻ ላይ ተመስርቶ፣ እነደምናውቀው አይሁዶችን በአውሮፓ፣
ጥቁሮችን በኢትዮጵያ፣ ቻይናንና ኮሪያኖችን በእሲያ በመርዝ ጢስና በጋዝ፣ በቦንብና በእሳት፣ እነዲፈጁ
አድርጎአል።
በሃይማኖት ጥላቻም ላይ ተመስርቶ ሰዎች ለፈለጉት አምላካቸው እንዳይጸለዩ፣ የጸሎት ቤታቸውም እንዲፈርስ
እና እንዲቃጠልም ተደርጎአል።
ይኸው መግለጫ፣ ቀጠል አድርጎ እዚሁ መግብያው ላይ „….ዋነኛው የሰው ልጆች ሁሉ ጉጉት፣ የንግግርና
የእምነት ነጻነት የሚጎናጸፉበት ፣ ከፍርሃትና ከችግር ነጻ የሚወጡበት ዓለም እንዲመጣ ነው“ ብሎ ይህ አዋጅ
ተውጆአል፣ ይለናል።

~9~

„…ሰዎች በክፉ አገዛዝና በጭቆና ተማረው ያላቸው የመጨረሻ ምርጫም አመጽ ለማካሄድ እንዳይገደዱም፣
(እነዚህን) የሰበአዊ መብቶችን በሕግ እንዲከበሩ ማድረጉ አሰፈላጊ…ነው“ ብሎ የ1948 ዓ.ም መግለጫ፣
መንግሥታትን ሁሉ እንዲያስቡበት ይመክራል።
እንግዲህ ወረድ ብሎም ይህ ኢትዮጵያ ወዳ የተቀበለቺው፣ የዓለም አቀፉ የሰበአዊ መብቶች አዋጅ፣
የእያንዳንዱን ሰው፣ ትልቅም ይሁን ትንሽ ፣ ሐብታም ይሁን ደሃ፣ በአለሥልጣንም ይሁን ዝቅተኛ ተራ ሰው፣
“…. ሙሉ ነጻነቱን“ በዝርዝር እንደዚህ አድረጎ አንቀጽ፣ በአንቀጽ፣ ከፋፍሎ አሰቀምጦልናል።
እያንዳንዱ ሰው — አንቀጽ ሦስት ላይ እንደሰፈረው — ነጻ ሰው ነው ይላል። አንቀጽ አራት–አዋጁ ላይ
እንደሚነበበው– ባርንትን ይከለክላል። አንቀጽ አምስት ፣ ማንንም ሰው ማሰቃየት ወይም በጭካኔ ና ኢሰበአዊ
በሆነ መንገድ ማጉላላት ወይም ማዋረድ ወይም መቅጣት አይቻልም፣ ይላል። ዘጠኝ ላይ፣ ማንም ሰው
በዘፈቃድ በሆነ መንገድ ሊያዝ፣ ሊታሰር ወይም ሊጋዝ አይችልም፣ የሚለውን አረፍተ ነገር መግለጫው አንስቶ
ይህን ወንጄል፣ ያግዳል። ይከለክላል።
አንቀጽ አሥራ አንድ፣ ትላንት የተጻፈ፣ ከጊዜው የኢትዮጵያኖች ጥያቄም ጋር አብሮም የሚሄድ ይመስላል፣
…ማንም ሰው በተከሰሰበት ወንጀል በሕጋዊ መንገድ፣ እራሱን የመከላከል መብቱ ተጠብቆለት፣ በሕጋዊና
ግልጽ በሆነ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ እነደ ጥፋተኛ አይቆጠርም ይላል።
አንቀጽ 15 ስለ የዜግንት መብት ያነሳል። እዚሁ ላይ ማንም ሰው በዘፍቃድ ንብረቱን በማንም አይነጠቅም
ይላል። አንቀጽ 18 እና 19፣ 20 እና 21 ደግሞ ፣ ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የሚይጠይቀውን
በቅርቡም አዲስ አበባ ላይ ሠልፍ የወጡት ሰዎች ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ …ስለ የሓሳብና የሒሊና
ነጻነት፣… ስለ እምነትና የሃይማኖት ነጻነት፣… ስለ መናገርና ስለ መጻፍ፣ …አስተሳሰብንም ስለ ማስራጨት
ነጻነት፣… ስለ መሰብሰብና መደራጀት ስለ መምረጥና መመረጥ ነጻነት፣ ከጊዜው ጋር ይህ አዋጅ መቼም ሳያረጅ
አብሮ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲሰጥ፣ እንዲታወቅ፣ እንዲከበርም ይጠይቃል።
አንቀጽ 23 ስለ ሥራ መብትና ስለ… ከሥራ አጥነት የመዳን መብት፣ ያነሳል ። 25 ደግሞ፣ ማንም ሰው ምግቡን
፣ ልብሱን፣ ቤቱን የሕክምና አገልግሎቱና …ጡረታውን ከመንግሥት የማግኘት መብት እንዳለው ያስታውሳል።
አንቀጽ 27 የአእምሮ ሥራ በሕብረተሰቡ ውስጥ ከፈተኛ ቦታ እንዳለው ያነሳል።
በዚህም መንፈስ መግለጫው፣ በቁጥር አንድ፣ በመጀመሪያው አንቀጹ ላይ፣ ግሩምና ድንቅ የሆነ ቃል አናቱ ላይ
አስፍሮ፣ የሚከተለውን ያስነብበናል።።
„…የሰው ልጆች ሁሉ“ ይላል መግለጫው „…በነጻነታቸው፣ በክብራቸውና በመብቶቻቸው አንዱ ከአንዱ
ሳይበልጥ፣ እኩል ሁነው የተፈጠሩ ናቸው። በማሰብና በሒሊና ችሎታም (ከሌሎች ፍጡሮች ሁሉ እነሱ) ስለ
ታደሉ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ ይገባል።“ ይለናል። ከዚያም በአንዳዶቹ ዘንድ አሁን
የሚፈራውን የሃማኖት „ግጭትም“፣ እንዳይነሳ መግለጫው፣ ከግምቱ ውስጥ አስገብቶ „ ሰዎች ሁሉ..እርስ
በርሳቸው በወንድማማችነት መንፈስ ሊተያዩ፣“ እላይ እንደሰፈርው „ ይገባል“ ብሎም ስለአንድነት ያነሳል።
D
እንግዲህ ይህን መግለጫ መሰረት አድርገው የምሥራቅ አውሮፓ ሕዝቦች ሳይታሰብ ብድግ ብለው የአንድ
ፓርቲ ኮምኒስት አምባገነን ሥርዓቶችን፣ ገርስሰው፣ ጥለው፣ ነጻ-የዲሞክራቲክ ሕብረተሰብ እነሱ ዛሬ
መሥርተዋል።
ወደ 1820 አካባቢ እየተስፋፋ የመጣው የዲሞክራቲክ ሥርዓትና የኑሮ ዘይቤ፣ ቀስ እያለ መቶ አመት
በማይሞላ አጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰላሳ በሚደርሱ አገርና መንግሥታት ውስጥ ተስፋፍቶ ሌሎቹን ሕዝቦች፣
ይህ ሥርዓት፣ ይማርካል።
ግን ደግሞ ሞሶሊን በጣሊያን፣ ፍራንኮ በስፔን፣ ሌንንእና ስታሊን በሩሲያ፣ ሒትለር በጀርመን ፣ ማኦ ደግሞ
በቻይና… ተነስተው፣ ነጻና በዲሞክራቲክ ሥርዓት የሚተዳደሩ አገሮች ቁጥር ወደ ታች ዝቅ ብሎ፣ በአንዴ
አሥራ ሁለት ይገባል።

~ 10 ~

እንደገናም ይህ ቁጥር ከፍ ይላል። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በሁዋላ በተፈጠረው አዲስ ሁኔታም በፓርላማ
ሥርዓት የሚያምኑና የሰበአዊ መብቶችን የሚያከብሩ መንግሥታት ቁጥር በ1960 ዓ.ም አካባቢ (እ.አ.አ.) ከፍ
ብሎ ሠላሣ ስድስት ይደርሳል።
ቀስ በቀስ በሦስተኛው ዙር ላይ የበርሊን ግንብ ፈርሶ ብዙ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ከትከሻቸው ላይ
አምባገነኖቹን ተራ በተራ አራግፈው፣ በዚህ በያዘነው 21ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራቲክ ሥርዓትን „የተቀበሉ“
አገሮች ቁጥር፣ እንደ ሩሲያ ያሉትን አካቶ፣ (ወደ ሁዋላ ላይ በዝርዝር እንሄድበታለን) በጠቅላላው አንድ መቶ
ሃያ ይሆናል።
„ዲሞክራሲ“ የሚለው ቃልና ሥርዓት፣ ከየት እንደመጣ ፣ አዋቂዎች ቢከራከሩም፣ ለእኛ የአገራችንን ስምና
የእኛን የኢትዮጵያኖችን መልካምና ጥሩ፣ ሸጋ፣… ማንም በዚያን ዘመን ላልደረሰበት ሥነ-ምግባራችንን፣
ከዚያም አልፎ እኛ ኢትዮጵያኖች ማን እንደሆን? ተዘዋውሮ ፣ አይቶ፣ ሰምቶም ለዓለም ጽፎ ለአስተዋወቀው፣
ለታሪኩ ጸሐፊ ለሔሮዶቱስ (484-425 B.C.) እንግዳ ለአልሆነው ሰው፣ ይህ ቃል „ዲሞክራሲና የዲሞክራሲ
ሥርዓት“ ክላይስቴነስ የተባሉ ነገዶች፣ በአቴን ይህን የአኗኗር ዘይቤና ሥርዓት እንደአስተዋወቁ፣ እሱ
ሔሮዶቱስ በመጽሐፉ ላይ ዘግቦአል።
በጥንታዊ ዘመን ከ508 እስከ 322 ድረስ ከክርስቶስ ልደት በፊት አብቦና ደርቶ ይህ ሥርዓት ብዙ
ጭንቅላቶችን አፍርቶ ዓለምን እንደቀየረ ዛሬ መጽሐፍ ላይ እናነባለን።
ስለ ግሪኮች ጥበብ፣ ስለ ክርስቶስ ትምህርት፣ ስለ ሮማውያን ሕጎች፣ ስለ 18ተኛውና 19ነኛው ዘመን ፍልስፍና፣
ስለ ሰላምና ብርሃን ስለ ኢላይትመንት፣ ከመሸጋገራችን በፊት፣ በ1215 በእንግሊዝ አገር ስለ ታወጀው ማግና
ካርታና ኮንስትትውሽናል ሞናሪኪም፣ አንድ ቀን እናነሳለን።
ከዚያ በፊት፣ ሔርደቱስ ስለ ኢትዮጵያ (ይህ ለወጣቱ ትውልድ ነው) በመጽሐፉ ላይ ያሰፈረውን ጠቅሰን „ ስለ
ሊበርቲ“ የሚያትተውን ጽሑፍ፣ እዚህ ላይ እናሳድራለን።
„…በስተደቡብ ምዕራብ በኩል በጣም ራቅ ብሎ የሚገኝ፣ ሰዎች የሚኖሩበት አገር ኢትዮጵያ ነው። በዙህም
አገር ውስጥ በጣም ትላልቅ የሆኑ ዝሆኖች አሉበት። ዞጲና ሁሉም ዓይነት ዛፎች በያለበት በቅለው ይገኛሉ።
ሰዎቹም ከዓለም ሕዝብ ሁሉ ቁመታቸው የረዘመ ውበታቸው የበለጠና ዕድሜአቸውም ረጅም ነው።…“ ብሎ
ሔሮዶቱስ ስለ እኛ ማንነት የዛሬ ሁለት ሺህ አራት መቶ አመት ጽፎአል።

~ 11 ~

ፖለቲካ ምንድነው? (ክፍል ሁለት)
Posted on June 12, 2013

ክፍል ሁለት
ፖለቲካ ምንድነው?

/1*

ፖለቲካ ምንድነው?…ለምንድነው የፖለቲካ ሰዎች ሥልጣን ላይ አንዴ ከወጡ በገዛ ፈቃዳቸው
የማይለቁት?….ሥልጣን ምንድነው?

በሙያ ከሆነ እንደ ገበሬ አዋቂ ሰው የለም። ዘንድሮ ምን መዝራት እንዳለበት ያውቃል።መሬቱ ምን
እነደሚሰጠው በደንብ ያውቃል። እሩቅ ሳንሄድ የጉዋሮው አትክልቱ፣ ጥሩ ሥዕል ስለእሱ ይሰጠናል።
…. ከተሳሳተ፣ …ዞሮበት የተሳሳተ ውሳኔ ላይ ደርሶ ያልሆነ ነገር፣ይህ ሰው ከሰራ፣… እሱና ሚስቱ፣
ልጆቹና ዘመዶቹ ፣ ከብቱና ቤቱ የሚጠብቀው ውሻው ጭምር፣ ከድቶት፣ሁሉም እንደሚበተኑበት፣
እነደሚሞቱበት በደንብ ያውቃል።
ከገባበት ችግር እንደምንም ቢያመልጥም፣በጎረቤቶቹ ዘንድ መሳቂያ መሳለቂያ ፣ ለዘመናት
እንደሚሆነም፣ ይህ ወጣት ገበሬም ፣ በደንብ ያውቃል። ስለዚህ ነው ፣ስንት ኃላፊነት ስለአለበት፣
የአባቱም የአያቱም ምክርና ተመክሮም ከልጅነቱ ጀምሮ፣ እሱን ስለገነባው፣ የት ቦታ፣… በምን
ወራት፣ ምን ዓይነት አዝመራ፣ ዘንድሮ እንደሚዘራ፣ እሱ ተጠንቅቆ እጁን ይዘረጋል። አለበለዚያ ጉድ
ይፈላል።
አንድ ፖለቲከኛ ግን –ያውም የእኛ አገር ፖለቲከኛ- ከገበሬው ጋር ሲተያይና ሲነጻጸር ፍጹም ሌላ
ነው። ረጋ ብሎ አያስብም። ቀዥቀዥ ያደርገዋል። ቀዥቃዣም ነው። ወፈፍ ያደርገዋል። ሳያመዛዝን
ትክክለኛ ነው ብሎ የጨበጠውን በየአለበት ይዘራዋል። ያ ነገርም አንድ ቀን እራሱን ጭምር ያዋክባል
ወይ ብሎም አይጠይቅም። ደግሞ ሲያዋክበው አይደነግጥም። ግን ያዋክበዋል። አርፎ
ስለማይቀመጥም ብድግ ብሎ ያልሆነ ነገር ከመሬት ተነስቶ፣… አፈሩ ይቀበለዋል ፣… አገሩ
ያዳምጠዋል …አየሩ ይስማማዋል ወይ ብሎ …ሳይጠይቅ ና ሳይጨነቅ፣ በሁሉም አቅጣጫ
ያገኘውን ዘር ከንፋሱ ጋር አብሮ እንደገና ይዘራዋል።
በተለይ „ የጥላቻ ዘሩን በጭፍን ዓይኑ“ ይኸው „ቀዥቃዣ፣ የሆነ ፖለቲከኛ“ በአራቱም ማዕዘን
ይለቀዋል። በመጨረሻም እሱንም ሌላውንም ይህ ሥራው ዓይኑን ስለሚያሳውር ገደል ይዞት
ይገባል። በመጀመሪያ አጃቢዎቹና ደጋፊዎቹ ይሸሹታል። በሁዋላ ጓደኞቹ። በመጨረሻ እሱ ብቻውን

~ 12 ~

ይቀራል።ያኔ ደግሞ ጊዜውም፣ ሰዓቱም፣ ትውልዱም ተቀይሮ አውላላ ሜዳ ላይ „ ቅራኔው አንድ ቀን
ከሮ ወደኔ ይመጣሉ ብሎ „ እራሱን ያታልላል።
ግን ስለ የትኛው የፖለቲካ ሰው ነው፣ አሁን የምናወራው?
ስለ „የመሸታ ቤቱ ፖለቲከኛ?“ ….ስለቀማኛው የጫካ ሽፍታ?..በአውሮፓና በአሜሪካ፣…በእሲያና
በላቲን አገር ስለተነሱት የደፈጣና የከተማ ሽብር ፈጣሪዎች? ስለኮሚኒስቶቹ? ወይስ ስለ
አናርኪስቶቹ? ስለ ሶሻል ዲሞክራቶቹ፣ ወይስ ስለ ሊበራሎቹ?
ወይስ ስለ ትግሬ?… ስለ ኦሮሞ?…አማራ፣ ስለ ኤርትራ ፣ ኦጋዴን…አፋርና …ስለ ….ነጻአውጪዎቹ ፖለቲከኛ?… ለመሆኑ ስለማንኛው ፖለቲከኛ ክፍል ነው የምናወራው?

የተለያዩ ድርጅቶች ታሪክ ውስጥ ገብተን ፣ ልዩነቶቻቸውን አንድ በአንድ ዘርዝረን፣ ከመዳረቃችን
በፊት፣ እንዳው፣ በቀላሉ ለመግባባት አንድ ነገር እናንሳና እሱን እንመልከት። እሱም ገበሬው
የሚዘራውን ያውቃል፣ በተቃራኒው ቀዥቃዣው ፖለቲከኛው ግን የጥላቻ ዘሩን በሁሉም አቅጣጫ
ከንፋሱ ጋር አብሮ ይዘራል ብለናል።
ግልጽ እንዲሆንልን በኢትዮጵያ ላይ ከአንዴም ሁለቴ የወረደውን ትራጀዲ፣ያ! ትምህርት ሰጪ፣ ጥሩ
ምሳሌ ስለሆነም እሱን እንመርምር ።
እህአዴግና ሻቢያን፣ እነሱን እናስቀድማቸው። ኦነግን አሁን ለጊዜ እንተወው። መኢሶንና አህአፓን
ደርግንም ልንወስድ እነችላለን። ግን እላይ በተጠቀሱት በሁለቱ ላይ እንቆይ። እነሱ ናቸው አሸናፊ
ሁነው የወጡት።
ወጣ ወረደ ሁሉም በቂ ትምህርት ይሰጣሉ።
ብቻ! ይህኛው፣ እነሱ ለዘመናት ያራመዱት ፖለቲካ „ፖለቲካ „ ከአልነው፣ „…ስለ ስታሊን
የመገንጠል ፖለቲካ“ ስለሆነ ፣ ደህና ትምህርት፣ ለሁላችንም ይሰጠናል። ….ሻቢያ በሚከተለው
ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ከአልተገነጠልኩ ይላል። አለ። ለብዙ አመትም „ታገለ“። ሕዝባዊ ወያኔ
ተገንጠሉ ብሎ ደብዳቤ ለተባበሩት መንገሥታት ድርጅት፣በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ወደ ኒዎርክ ጻፈ።
እነሱም፣እያወቁ ተቀበሉት። እንደ ልጆች ጨዋታ፣ ሁለቱን አካባቢ፣ሁለቱም፣ ድርጅቶች፣
እነደተመኙት ተከፋፍለው ይዘው „ተገነጣጠሉ“። ድግስ ተደገሰ፣ ተጨፈረ…ተበላ፣ ተጠጣ።
እስከዚህ ድረስ ፣እንግዲህ ምንም „ችግር“ በዚያ አካባቢ አልታየም። ግን ከዚህ በሁዋላ ትንሽ ቆይቶ
የሆነው ነገር፣ ደጋፊዎቹም ተቃዋሚዎቹም፣ ሌሎቹም ይደርስብናል ብለው ያልገመቱት ጉዳይ ሆነ።
በባድሜ ድንበር፣ በናፍቃ ብር፣… በቡና እና በቅቤ ንግድ፣በእንጨት፣ በጤፍና በስንዴ …ሁለቱ
ድርጅቶች ሲጣሉ( ምንም የሚያጣላቸው ምንም ምክንያት የላቸውም፣ ባድሜም ኤርትራም
የኢትዮጵያም የአፍሪካም ግዛት ነው) የአዲስ አበባው ገዢ በያለበት ተሰማርተው ትዳር መስርተው ፣
ተቀላቅለውና ተጋብተው ለብዙ መቶ አመታት የሚኖሩትን በሺህና በመቶሺህ የሚቆጠሩ
„ኤርትራውያኖች“„ ለቃቅሞና ስብስቦ ወደ ኤርትራ ሲልካቸው፣ የአሥመረው ገዢ በተራው
ተመሳሳይ እርምጃ፣ቀደም ሲል እነደ ጀመረው ቀጥሎበት፣ እሱም በተራው ትግሬዎችንም ጭምር
ለቃቅሞ ከኤርትራ አባረረ።
የደቡቡ ሕዝቡም „እኛ ትግሬና ኤርትራ መለየት ስለማንችል እናንተው ለዩአቸው ብሎም …“ የገዛ
ጎረቤቱን ወደ አዲስ አበባ ላከ። ነገሩ በጊዜው ሰውን ሁሉ፣ ይህ የሚያሳዝን ሥራ፣ „አስቆአል“ ።
ሌላው የኢትዮጵያ ጠላት „ ሰዎቹ አብደው ይኸው ተበታተኑ“ ብሎ ደስ ብሎታል። ይህ አሁን
የጤነኛ „ፖለቲከኛ ሥራ ነው?“

~ 13 ~


ማክስ ቬበር ( ለዚህ ነው ይህን ሁሉ ታሪክ መልሼ ያነሳሁት) ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ለሚፈልጉ
የዩኒቨርሲት ተማሪዎች ያኔ በአደረገው ንግግሩ፣ ሦስት ነገሮችን ሁልጊዜ ሳይረሱ እንዲመለከቱት፣
እንዲያገናዝቡት፣ እነሱን አደራ ብሎ ለቆአቸዋል። ይህን አደራ „ከእንግዲህ ከኢትዮጵያ እንገንጠል፣
ከአልተገነጠልን፣ ሞተን እንገኛለን“ የሚሉት ኃይሎች ይህን ነገር -ለዚህ ነው የማነሳው- ዞር ብለው
ማየት አለባቸው። በተለይ ስንቱ „ኦሮሞ“ ስንቱ „ኦጋዴን“ ስንቱ „ትግሬ“… ከሌላው ዜጋው ጋር
እንደተጋባ አለማየቱ፣ የላይኛውን ዓይነት ስህተት እንደገና መድገም ይሆናል። … እሱስ ነገ ምን
ይሆናል?… የት ይደርሳል? ስንት ትዳርስ፣ ስንት ቤተሰብስ፣ ይበተናል?… ይፈርሳል። ይህን የማያይ
ፖለቲከኛ፣ ጤነኛ ሳይሆን፣ „ቀዠቃዣ ዕብድ“ ነው።
„ፖለቲካ እንደ ሙያ“ በሚለው ንግግሩ ላይ ቬበር እንዳስቀመጠውና ፣ እሱ እንደጻፈው አንደኛ፣
ዝም ብሎ አንድን ነገር ሳያመዛዝኑ ይዞና ጨብጦ „ከመጋለብ“፣ አንደኛ:- አንድ ፖለቲከኛ „ሚዛናዊ
የሆነ ፍርድን መውሰድ ይገባዋል ይለናል“። ምንድነው ሚዛናዊ ፍርድ?
ሁለተኛው፣ „ፖለቲካ „ በሙሉ ልብና በቀና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ (እሱ ፓሺን በእንግሊዘኛ
ይለዋል) አካሄዱ መመስረት አለበት ብሎ ያስተምራል።
በመጨረሻ ደግሞ ሦስተኛው፣ ለሰሩት ሥራ ሁሉ በሕዝብ ፊትም ሆነ በታሪክ ወይም በፈጣሪም
ዘንድ ኃላፊነቱን ተቀብሎ መቆም፣ እንዳለም መረሳት የለበትም፣ ይላል። ይህም ማለት ልጆችም፣
ዘመዶችም፣ አባቶታቸው፣ ወንድሞቻቸው በሰሩት ሥራ ወደፊት ማፈር የለባቸውም ማለት ነው ።
ከዚያ እንግዲህ ምሁሩ በቀጥታ ወደ ኤቲክና ወደ ሞራል፣ ወደ መልካም ሥነ ምግባርም በሰው ልጆች
መካካል ወደ ማስተማር ይሸጋገራል።
ግን አዚህ ላይ የገዛ የአገሩን ልጅ…“ በለው፣ እረገጠው፣ ደምስሰው፣ እናሸንፋልን፣ እናቸንፋልን፣
አብዮቱ እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ፣… ከርሰ-መቃብራቸው ላይ እንቆማለን….“ እያለ እዚህ
ለደረሰው ትውልድ ፣ ስለ ኤቲክ እና ስለሞራል፣ ስለ መልካም አስዳደርና ስለ የአገር ፍቅር… አሁን
ብናወራለት ከንቱ መሆኑን እናውቃለን።
በሁዋላ ላይ ተመልሶ ለመምጣት ለጊዜው ይህን ጉዳይ አሁን እንዝለለውና ወደ ማክስ ቬበር
ጥያቄዎች፣ እነዚህም የእኛም ጥያቄዎች ስለሆኑ ፣ ወደ እነርሱ አሁን ጎራ እንላለን።
ለምንድነው ሰው ሁሉ በአገራችን ፣ ከአልጠፋ ነገር ፖለቲከኛ የሆነው? „… ሰው ሁሉ፣ ማለት
ባንችልም „አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቢያንስ አንድ ደርጅት ውስጥ የገባው?…ወይም ደግሞ አብዛኛው
ከቢጤዎቹ ጋር ሁኖ የራሱን ድርጅት መሥርቶ ሰውን ሁሉ በሆነውና ባልሆነው „ትምህርቱ፣
በሚከተለው አላማው የሚያዋክበው“?
ለምንድነው በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሰረቱት አብዛኛዎቹ ድርጅቶች „በብሔር – ብሔረሰብ ፣ በጎሳና
በዘር ላይ ብቻ ተምርኩዘው፣ የተመሰረቱት“? ለምንድነው ሌላው ዓለም በዘር ላይ ሳይሆን
„በፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ“ ፓሪቲውን አቋቁሞ ለሽንጎ ምርጫ በሰላም ሕዝብ እንዲመርጠው፣
ብቅ ብሎ የሚወዳደረው?

ሥልጣንና ኃይልን፣ ( ስለ ፖለቲካ ነው የምናወራው)… መንግሥትንና አስተዳደርን፣ የፖለቲካ
ድርጅትንና ተከታይ አባሎችን፣ የበላይ አለቃና የበታች ታዛዠን፣ ሕግና ሥርዓትን፣ ገዢው መደብና
ተገዢውን ሕዝብ፤ የተለያዩ ተቋሞችንንና የሥልጣን አከፋፈልንና አወራረድ ፣ በዚያች አገር፣
የፖሊስና የጦር ሠራዊትን፣..የባለሥልጣኖች በሥልጣን መባለግና፣ አንድን ሕዝብ አንድ ቡድን
በጠበንጃ የቁም ምርኮኛ አድርጎ ፣ እንደ የግል ቤቱ መዝረፍ….ወዘተ፣ ወዘተ… እነዚህን ሁሉ ቀስ
በቀስ ወደ ግራና ወደ ቀኝ እየመተርን፣ ማክስ ቬበርን መሰረት አድርገን፣ እንመለከታቸዋለን።

~ 14 ~

እዚሁ ውስጥ …የነጻ- ምርጫና የነጻ -ጋዜጣ ሚናንም እንመለከታልን ። በሕብረተሰቡ ውስጥ፣ የነጻፍርድቤትና የተለያዩ የሙያ ድርጅቶች ቦታንም እንመረምራለን። የተለያዩ ሃይማኖት አባቶችና፣
የአገር ሸማግሌዎችም ሚናም እንዴት ነው ብለን እንጠይቃለን። …ጸሐፊና ደራሲዎችን ፣ የኪነትና
የጥበብ ሰዎችን የእነሱንም ሚና ወደፊት እናነሳለን።
„ፖለቲካ እንደ ሙያ… አገዛዝና …አስተዳደር „ በሚለው ጽሑፉ ቬበር እላይ የተነሱትን ነጥቦች
በሥነስርዓቱ ለመረዳትና ለመመለስ፣ ሦስት ቁም ነገር ያላቸው ጥያቄዎችን አንስቶአል። እነሱም:ሀ) እንድ የገዢ መደብ አገሪቱን ለማስተዳደርና ሕዝቡን ለመግዛት፣ በእጁ ላይ የሚገኙት፣ እሱ
የጨበጠው የማስተዳደሪያ መሣሪያዎቹ ምንድናቸው? ብሎ ይጠይቃል።
ለ) ተገዢዎቹን ወይም ሕዝቡን ፣የገዢዎቹን ትዕዛዝና ደንብ እሽ ጌታዬ ብሎ ተቀብሎ ለመገዛት
የሚገፋፋው ነገር ምንድነው? ይላል።
ሐ) በየጊዜው ብቅ ብለው የሚፈነዱትን ችግሮች፣ ለመፍታትና ለመቆጣጠር፣ መልክም ለማስያዝ ፣
መንግሥት ምን ዓይነት ተቋሞችን መሥርቶ ነው፣ ሕዝቡን የሚያስተዳድረው? የሚለውንም
ጥያቄውንም አብሮ ይሰነዝራል።
ይህን የእሱን ጥያቄ ተራ በተራ -ከብዙ በጥቂቱም ያለፈው ጊዜ መልሰናል። ወደፊትም በበቂም ጊዜ
ወስደን እንመልሳለን። ግን ደግሞ እሱ ከቁም ነገር ሳይቆጥራቸው ጥሎአቸው ያለፈውን ሁለት
ጥያቄዎች አብረን ማንሳት ኢዚህ ላይ እንፈልጋለን።

እነሱም:ሀ) አርፎ እንደሌሎቹ ተቀምጦ መኖር ሲቻል ፣ ገዢዉን ቡድን ፣ ወይም አንድ ሰው፣ ያንን አገርና
ያንን ሕዝብ ለመግዛት ፣ለመምራት የሚገፋፉት፣ የገፋፉት ነገሮች ምንድናቸው? መግዛት አለብህ
ብሎ ያንን ሰው „የሚያሳብደው ነገር“ ለመሆኑ ምንድነው?
ለ) ተገዢው ሕዝብስ ደግሞ መአቱ ሲበዛበት፣ በደሉ ሲጠነክርበት፣ አይ አሁንስ አበዛችሁት ፣
በቃችሁ ብሎ፣እነሱን የሚገስጽበት መድረክ፣ አቤት የሚልበት ሜዳ፣ ከዚያም አልፎ ወይዱ ከዚህ
ብሎ የሚያምጽበት „መሣሪያ“ – ጠበንጃ ሳይሆን – ብልሃትና ዘዴ በእጁ ላይ፣ ለመሆኑ ያ! ሕዝብ
አለው ወይ?
እንግዲህ እነዚህ፣ ሁለቱ ተጨማሪ ጥያቄዎች ፣ በቀጥታ ዞረው ዞረው የሚወስዱን ሔልሙት ሼልስኪ
የሚባለው የጀርመኑ ጸሐፊ እንደአለው ፣ ወደ አስተዳደር ውሰጥ ተሣትፎ ወይም ወደ ተቃውሞ
ትግል፣ ወይም ደግሞ ወደ አብዮታዊ ለወጥ ወደ አመጽ፣ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በቀጥታ
ይወስዱናል።
ከሁሉም ለአንዱ ጥያቄ ብቻ — እሱ ነው እኛን፣ እስከ አሁን ድረስ ተብትቦ የያዘን– መልስ
ለመስጠት ሙከራ እናድርጋለን።
ለምንድነው „እኔ ብቻዬን“ አገሪቱንም፣ ሕዝቡንም እስከ ዕድሜ ልክ ድረስ ከአልገዛሁ ብሎ
የፖለቲከውን መደብ ሁሉ፣ በጅምላ በአገሪቱ ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሳበደው፣ያሳበዳቸው ነገር?…
ይህ በሽታ ነው ወይስ ጤነኛ አመለካከት?
ይህ ፣ዕውነቱን ለመናገር፣ የኢትዮጵያኖች ብቻ በሽታ አይደለም። የሁሉም ፖለቲከኛ በሽታ ነው።
ታዲያ ለምንድነው ሌሎቹ በሰላማዊ ትግል በፓርላማ ምርጫ፣ በጊዜ ገደብ ተገደው መድረኩ ላይ
ለመውጣት የቻሉት? ለምንድነው እነሱ „የጨዋታውን ሕግ የሚያከብሩት? ለምንድነው የእኛዎቹ

~ 15 ~

አንዴ እንደምንም ብለው ያውም አወናብደው ሥልጣኑን ከነከሱ፣ አንለቅም ብለው መከራቸውን
የሚያዩት? ….እኛንም የሚያሳዩት?
(ካንትና ፣ሖብስ፣ ጆን ሎክና ቦዲን፣…ሌሎቹም…በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በበቂ ጽፈዋል።)

የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው፣ ሙሉ ነጻነትን ይፈልጋሉ። እንዲያውም ይህን ነጻነቱን ያገኘ ወይም
ያወጀ ሰው– ይህ በጣም የሚገርም ነው– የእራሱን ነጻነት እጁ ከአስገባ በሁዋላ „የፈለኩትን ነገር
ለማድረግ አሁን ሙሉ ነጻነትአለኝ ብሎ“ የሌላውን ነጻነት ወደ መግፈፍ ይሸጋገራል። በጉልበትም
ተጋፍቶ የሌላውን መብት ይነጥቃል። እንግዲህ ኢማኑኤል ካንት ይህን አይቶ፣ „መልካም
አመለካከት“ በሚለው የፖለቲካ ፍልስፍናው „ ከፍርደ ገምድሎችንና ከአረመኔዎች መንጋጋና መድፍ
ለመትረፍ“ የሕግ በላይነት፣ በአንድ ሕብረተስብ ውስጥ ያስፈልጋል ብሎ፣ ይህን ዕውቀቱን
ለተማሪዎቹ እሱ በተራው አሰተምሮአል። እሱ ብቻ አይደለም።
በተለይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሥነ- ጽሑፍ፣ በድርሰትና በቲያትር ዓለም ፣ብዙ ነገሮችን መለስ
ብለን ከተመለከትን እዚያ ውስጥ በርካታ ትምህርቶችን እናገኛለን። ሁሉም ሰው ፣ እኔም ፣ እራሴም
ብሆን „ቁጥጥር ከአልተደረገብኝ፣ የሚቆጣጠር ኃይል በአጠገቤ ከሌለ“፣ ነገ ብድግ ብዬ ባንኩንም
ባልዘርፍ አዝበታለሁ፣ የፈለኩትን እሾማለሁ እሽራለሁ፣ ዙፋኑም ላይ እድሜ ልኬን ብቀመጥበት ደስ
ይለኛል። ከዚያም አልፎ ሚስቴም ልጆቼም፣ ዘመዶቼም፣ ጓደኞቼም እንደኔው ቢደሰቱ፣ በአገሪቱ ላይ
ቢጨፍሩ ደስ ይለኛል። ይህ እነዳይሆን ካንት ከሁሉም በላይ የሆነ ሕግ ያስፈልጋል ይላል። እሱ ብቻ
አይደለም። ሌሎች ነገሮችም ለአንድ ሕብረተሰብ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችም አሉ።
ብቻ! ለጊዜው መንግሥት ፣… መንግሥት ነው ብለን የምንቀበለው፣ አንድ መንግሥት ቢያንስ
ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ሟሙዋላት አለበት። ለዚህ ነው ሕዝብ ፊት ቀርበው ሥልጣኑን ፖለቲከኞች
ሲቀበሉ በመሓላ ቃላቸው፣ „በአገሬና በሕዝቤ ላይ የሚመጣውን አደጋ…“ ለመከላከል፣ ቃል ኪዳን
እገባለሁ“ ብለው የሚምሉት። ቃሉን ባያሟላስ? ይጠየቅበታል።
አንደኛው ፣ የመንግሥት አላማ፣ ወደ ፖለቲካ ፍልስፍና እንመለስ:- ለአገሪቱና ለሕዝቡ ፣ ትርምስን
አጥፍቶ፣ በደልን አስወግዶ፣ በሥልጣን መባለግን ተቆጣጥሮ፣ ቀማኛን እና አረመኔ ሰውን
ከመካከላቸው፣ከሕብረተሰቡ አርቆ ፣ ሰላምን ፣ በአንድ አገር ውስጥ መምጣት ነው። ይህም ማለት፣
የማንም ሰው ቤት አይዘረፍም። ይህ ማለት የድሆች ቤት በአናታቸው ላይ አይፈርስም።… ስልክ
አይጠለፍም። ሰው አለምክንያት ተይዞ አይታሰርም።
ሁለተኛው ፣ የመንግሥት አላማና ሥራ:– ረሃብን አጥፍቶ፣ በሽታን አስወገዶ፣ የሥራ ዕድል ለሁሉም
ዜጋ ከፍቶ፤ የማህራዊ ኑሮ ሁኔታን አሻሽሎ፣ ደካማውን ረድቶ፣ ሀብታሙን አበረታቶ፣ ዕወቀትና
ጥበብን አስፋፍቶ፣ ለአገሪቱ ብልጽግና እን ዕድገትን ማምጣት ነው። እንግዲህ ይህ የአንድ መንግሥት
ሁለተኛው ሥራ ነው።
ሥስተኛው የመንግሥት ሥራ ፣ በህ- መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን ፣በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር
ላይ አገሪቱ (ኢትዮጵያ ) ፈርማ የተቀበለችውን የሰበአዊና የዲሞክራሲያው ፣ የዜጎችን መብቶችን
በሙሉ አንዱም ሳይጣል ሁሉንም፣ ነጻነቱን ማክበር፣ ማስከበር፣ የመንገሥት ዋና ሥራ ነው።
ይህንንም በሥራ ለማገድ የሚምክሩትን ኃይሎች ሁሉ፣ ሕጉን ስሚጻረሩና ስለሚያደናቅፉ፣
የሌላውንም መብት ሰለሚገፉ፣ መንግሥት ይህን የመቆጣጠር፣ ግዴታም አለበት።
በአጭሩ „የመንግሥት ተግባር፣ የመንግሥት ግዳጅ እና ዋና አላማውም ይህ ነው።“
ይህም መሆን አለበት። ከሌለስ?

~ 16 ~


በዚህ አቀራረብ ምንድነው እኛን፣ ኢትዮጵያኖችን አንድ የሚያደርገን ነገር? የሚለውን ጥያቄ ፣ ከብዙ
በጥቂቱ፣ ከተከታተላችሁን በዚህ የመለስን ይመስለኛል።
እዚያው በእዚያው መንግስት እነዚህን እላይ የተጠቀሱትን ሦስት ነገሮች ከአላሟላ ደግሞ ምን
ማድረግ ይገባል ? የሚለውን፣ የአብዛኛውን ኢትዮጵያኖች ጥያቄ፣ ነገሩ የእኛ ብቻ አይደለም፣ የዓለም
ሕዝቦች ጥያቄ ነው፣ ወደ መመለሱ፣ ቀስ ብለን አሁን እንሸጋገር።
እንደምናውቀውና እንደተማርነው፣ የኢትዮጵያም ሕገ-መንግሥት ላይ እንዳነበብነው፣ አዚያ ላይ ስለ
ነጻ -ፍርድ ቤትና ስለነጻ-ዳኛ ያወራል። ስለ ነጻ-ጋዜጣና፣ ስለ ነጻ-ማህበር ምሥረታ ያነሳል። ስለ ነጻምርጫና ስለ ነጻ -ድርጅቶች ምሥረታና ውድድር ያብራራል። ግን ይህ ሁሉ ወረቀት ላይ ሰፍሮ
በሥራ ከአልተተሮጎመ፣ ሥልጣን ላይ የወጣውን ሰው፣ ወይም በድን ፣ ሥልጣን ከሕዝብ የሚወጣ
ስለሆነ ፣ ይህን ዓይነቱን አሰራር የማይቀበል ድረጅት ወይም ግለሰብ፣ ዓለም አቀፉ የተባበሩት
መንግሥታት ድርጅት፣ የሰው ልጆች መብት አዋጅ፣ እንደሚለውና እንደሚፈቅደው፣ እነዚህ ሰዎች፣
አገሪቱንና ሕዝቡን ሳያጠፉ፣ እነሱ በሰላማዊ መንገድ ተወገደው፣ በሌላ አምባገነን ባልሆኑ ነገር ግን ፣
በምርጫ ሥነ ስርዓት ላይ በሚያምኑ ዲሞክራቶች መተካት አለባቸው ይላል።
የፖለቲካ ትግል እና የፖለቲካ አላማና ግቡም በመጨረሻው፣ ፈላስፋዋ ሐና አረንድት ካንትና ቬበርን
ተከትላ እንደምትለው፣ የነጻነትን አየር፣… ሊበርቲን፣ ወይም አርነትን፣ ይህን ጥሩ አየር፣ መተንፈስ
ብቻ ነው፣ ትለናለች።
ግን ደግሞ ይህን የነጻነትን ጥሩ አየር፣ ሊበርቲን…. እናመጣላችሁዋለን ብለው ሥልጣኑ ላይ ጉብ
ብለው፣ ከእንግዲህ „ አፍንጫችሁን ላሱ ያሉ ኃይሎች“ ቁጥር በዓለም ላይ ጥቂት አይደሉም። ለዚህ
ሁሉ መድኀኒቱ፣ ሰይጣን ጠበልና መስቀል እንደሚፈራው ሁሉ፣ እንደገና ለነጻ ምርጫ እና ለነጻፕሬስ፣ ለነጻ- ሕብረተሰብ፣ ለሕግ በላይነት እንደገና፣ ያው ለሰባዊ መብቶች መከበር፣… ለነጻነት
ተነስቶ መታገል፣ የሰው ልጆች የማይቀርላቸው፣ „እዳ“ ነው። አንድን ሕዝብ ከገባበት መከራ
የሚያወጣው፣ ደግሞ እራሱ ነው።
ፖለቲካ ማለት ነጻነት ነው።
ከሣቴ ብርሃን

~ 17 ~

ጊዜው ደረሰ …
Posted on June 12, 2013

ጊዜው ደረሰ

በእነዚህ በሁለት ፣ ነገር ግን አንድ ትርጉም በአላቸው የሕዝብ ጩኸት የተጀመረው የ21ኛው ክፍለ
ዘመን የኢትዮጲያ አብዮት፣ ተጠንቅቆ ለመናገር፤ አዲስ አበባ ላይ ሰሞኑን የታየው የሕዝብ
እንቅስቃሴ፣ የመጨረሻው አለጥርጥር ግልጽና የማያሻማ ነው።

„አላህ ይክበር“ ይላሉ ዘንድሮ የተነሱት የኢትዮጵያ ሞስሊሞች። „እግዚአብሔር ትልቅ ነው „ ይላሉ
ሰሞኑን ከእነሱ ጋር ተደባለቀው አደባባይ የወጡ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች። ሁለቱም ከአይሁድ
ሃይማኖት ጋር አንድ ላይ ሁነው ሦስቱም የፈጣሪችንን „ትልቅነት“ ገና ዱሮ ከጥንት ዘመን ጀምሮ
ይቀበላሉ።
በኢራን በዚህ „አላህ ይክበር“ ጥሪ የተጀመረው አብዮት፣ የነአያቶላን ሆሜኒንና የነአያቶላን
ታባታቢን ሥርዓት የሁዋላ ሁዋላ አምጥቶ፣ ፋርስን እጅና እግሩዋን ተብትቦ፣ እስከ አሁን ድረስ
አንለቅም ፣ አለቅም፣ ብሎ ይዞአታል። በግብጽ ሙባራክን በጋራ ሁሉም ጥለው የእስላም
ወንድማማቾች በምርጫ አሸንፈው፣ ሥልጣኑን ካይሮ ላይ ይዘዋል።
ኢትዮጵያስ?
ኢትዮጵያችን ግን ሌላ ናት።
አትስጉ። አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ የወጡት ሁሉም ናቸው።

መቼ እንደሚያቆም አይታወቅም እንጂ፣ ተርከፍክፎ ልብስን የሚያበሰብሰው፣ አለጃንጥላ ቢጓዙ
ደግሞ ራስንም የሚያረጥበው ዝናብ ሳይሆን ፣ቆሻሻውን ሁሉ ጠራርጎ ከተማይቱን የሚያጸዳው ፣
በነጎድጓድ የታጀበው ዶፍ ዝናብ በኢትዮጵያ ላይ ሊወርድ ፣ አሁን ያንጃበበ ይመስላል።
„እርግጥ የአንድ ቀን ሰልፍ፣ በከተማይቱ በአዲስ አበባ ላይ የታየው ተቃውሞ፣ በምንም ዓይነት
የሰሜን አፍሪካውን ዓይነት የጸደይ አበባ አብዮት በኢትዮጵያ ላይ፣ ብቻውን አያመጣም።
ሊያመጣም አይችልም።“ ይለኛል፣ አንደኛው የቀኝ አንጎሌ።

~ 18 ~

„ለምን አይሆንም? ይሆናል እንጂ!“ይለኛል አንደኛው ልቤ– እኔኑ እዚያው ሲፈታተነኝ።
„እራሳቸው አዘጋጆቹ ፣ ሳይቸግራቸው በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ መልስ ይስጠን፣… ከአልተሰጠን…
በማለታቸው ነው“ ይለኛል የግራው አንጎሌ።
„…እንግዲህ ይህንን ረጋ ብለን እንመልከተው ይለኛል።“ ወዳጄ ልቤም ፣ ከሒሊናዬ ጋር አንድ ላይ
ሁኖ።
„….ሁለችንንም ተራ በተራ ነገሮችን አንስተን እናገላብጣቸው… „ ይላል፣ ረጋ ያለው አእምሮዬ።

የሕዝብ ቁጣ (ይህ ሁል ጊዜ ተደጋግሞ አይታይም) መውጫ ቀዳዳ ሳይታወቅ፣ ሳይታሰብ አንዴ
ከአገኘ በቀላሉ የሚስፋፋ እንደ „የተስቦ በሽታ“ ነው።… እንደ ጉንፋንም፣ያደርገውና ሁሉንም
ይይዛል። እነደ ኩፍኝም ይቃጠዋል ። እንደ ወረርሽኝም በሽታም ብጅ ብሎበት፣ አላፊ
አግዳሚውንም ይለክፋል።
እንደ ነብርማ፣ ከተነሳበት ይቆጣና ይሞነጫጭራል። እነደ ግሥላም ያደርገዋል። እንደ ፈንጣጣም፣
ተቆጥቶ ጠባሳውን ጥሎም ይሄዳል። እንደ አንበሳ ደግሞ አንዴ፣ የሕዝብ ተቃውሞ ከአገሳ፣ምንም
መመለሻ የለውም።
በንኪክትና በንፋስም፣… በስልክም፣… በሹክሹክታም በአንዴ ወሬው፣ ተነስቶ አገሩን ሁሉ
አዳርሶአል። እንግዲህ መጨረሻውን በቅርቡ ያሳየን ይሆናል።
ይህ እንግዲህ ታምቆ ቆይቶ እንደገና የፈነዳው የሕዝብ ቁጣ እንደ ጅረት ተያይዞ ጠንክሮ ቸርችል
ጎዳና ላይ ብቅ ያለው፣ እሁድ ጥዋት ሰልፉን ያዩትን ሰዎች ጠይቀን እንዳዳመጥናቸው ከሆነ ፣
ተንጠባጥቦ፣… እየፈራና እየቻረ፣ እየዳበሰና እየተጠነቀቀ– እነሱ እነዳሉት– ብቅ ብሎአል።
በረንዳ ላይ ቆመው፣በአንዳንድ ቦታ ፍቶግራፎች ላይ እንዳየነው፣ በዓይናቸው ሰልፉን ያጀቡ ሰዎች፣
ጥቂት አልነበሩም። ቡና ቤት በራፍ ላይ ሰብሰብ ብለውም አይተው፣ ከዚያም ወጥተው፣ ተቀላቅለው
ሰልፉን ያዳመቁም፣ትንሽ አልነበሩም።
ኮፊያቸውን የደፉ መስሊሞች ነበሩ። መስቀልና ክራቸውን ያሰሩ ክርስቲያኖችም አብረው ወጥተዋል።
…ተስፋ ያጡ ወጣት ተማሪዎች፣… ሥራ ፈላጊ ኮረዳዎች፣ እንጨት ፈላጭ፣ እቃ ተሸካሚ
ኩሊዎች፣ …ጫማ ጠራጊ ሊስትሮዎች፣ ደላላና ታክሲ ነጂዎች፣ መስራት ያልቻለው ነጋዴ፣
እንዳትሰራ የተከለከለችው እንጀራ ጋጋሪ…
ጠላ ሻጩዋ፣…ሻይና ቡና አፍልቶ በመሸጡና በመሸጡዋ ከአቅም በላይ ግብር የተቆለለባት ቸርቻሪ፣
በአናቱዋ ላይ፣ ከልጆቹዋ ጋር የምትኖርበት ደሳሳ ጎጆዋ የፈረሰባት፣ ደካማ እናት….የከተማው
ለማኝ፣ ጠበቃው፣ ደላላው፣ ጡረታ የሌለው ወታደር፣ የቀድሞ የመንግሥት ሠራተኛ፣….ሁሉም
„በቃን“ የሚለውን ድምጻቸውን ለማሰማት፣ ደፍረው፣ ተያይዘው አብረው ወጥተዋል።

ሰሌዳቸውን እዚህ ሆነን እንዳነበብነው ወጣቶች „… የሥራ ዕድል ይሰጠን ይላሉ“
ምዕመናን „በሃይማኖታችን ውስጥ መንግሥት ጣልቃ አይግባ „ ብለው ይጣራሉ።
„በሥልጣን አትባልጉ..“ ሠልፈኞች ይላሉ።
ሰለ ኑሮ ውድነት አንስተዋል። ስለ ደመውዝ ጭማሪ….

~ 19 ~

የፖለቲካ እሥረኞች፣ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በጥቅሉ:ሕገ – መንግሥቱ ላይ የሰፈሩት፣ አንቀጾች፣“…የመናገር፣የመቃወም፣ የመጻፍ፣ የመተቸት፣
የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶችና ነጻነቶች፣… ይከበሩ፤ ይጠበቁ…“ ይላሉ።
እንግዲህ ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ አብዛኞቹ የሦስት ወር ጊዜ ጥበቃ፣ መልስ ለማግኘት
የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። አንዳዶቹ ደግሞ ፣ በእርግጥም ከሥስት ወር በላይ የሚጠይቁ
እንዲያውም መልስ ለማግኘት ከዚያም በላይ አልፈው የሚሄዱ ናቸው።
አብዛኛዎቹ በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ጥያቄዎች በመሆናቸው፣ ይህ ሕገ-መንግሥት
ደግሞ ተነድፎ ከተሰጠን ቢያንስ ከሃያ አመት በላይ በመሆኑ (ፍላጎት ከአለ) በሃያ አራት ሰዓት ጊዜ
ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ላይ እንዲውል ማዘዝ ብቻ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
የጋዜጣውን ዓለም፣ የፕሬስ ነጻነትን ጥያቄ እንውሰድ። በአቶ አማረ የሚመረው „ሪፖርተር“ ጋዜጣ
በየጊዜው እየታተመ ሲወጣ „ችግር“ በአገሪቱ ላይ እንዳላመጣው ሁሉ፣ ሌሎቹም፣ ተመሳሳይ ዕድል
፣ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው፣እነሱም ማግኘት፣እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። መብታቸውን መንግሥት
መጠበቅ ፣ ማክበር ከፈለገ ደግሞ የተዘጉትን ጋዜጣዎችና የታሰሩትን ጋዜጠኞችን ፈቶ ሥራቸውን
እንዲሰሩ በቀላሉ ማድረግ ይችላል። ለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሦስት ወር ጊዜ ጥናት
አያስፈልጋቸውም።
የራዲዮውን ዓለም እንመልከት። ሸገር ራዲዮ፣… ፋና ራዲዮ፣…የኢትዮጵያ ራዲዮ…እነዚህ ሁሉ
ተከፍተው ይሰራሉ። የቴሌቪዠን ጣቢያም አቶ አማረ፣በየጊዜው ከሚልኩት ማስታወቂያ
እንደምናየው፣ እሳቸው ለመክፈትም አስበዋል። ለሌሎቹም ይህን ሕገ-መንግሥቱ ላይ የሰፈራው
መብት ለእነሱም እንዲሰጣቸው፣ እንዲከበርላቸው ይፈልጋሉ።
ይህ በሁለት ቀን የሚያልቅ መልስ አግኝቶ ማለቅ የሚችል ጥያቄ ነው።
የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታት፣…. በሙስና የተበከሉትን ፍርድ ቤት ማቅረብ፣….አለአግባብ
ቤታቸው በአናታቸው ላይ የሚፈርስባቸውን እርምጃ ማገድ፣….እነዚህ ሁሉ ለጠቅላይ ሚስትሩ ሃያ
አራት ሰዓት የማይፈጁ ትዕዛዞች ናቸው።
በአንድ ስልክ ደወል የሚያልቁም ችግሮች ናቸው። ታዲያ እውነቱን ለመናገር ይህን ለመልስ
ለመንግሥት ሦስት ወር የሚፈጅ፣ የሚያስጠብቅ ነው?
አይመስለንም።
እርግጥ አለአግባብ የኢትዮጵያን መሬት „በወለድ አግድ“ የያዙ መንግሥታትና የግል ኩባኒያዎች
ከያዙት መሬት ላይ ተነስተው ለመሄድ የሦሰት ወር ጊዜ ምናልባት ሊፈጅባቸው ይችላል። ወይም
ከሕዝቡ ጥያቄ አንዱን ብቻ ለመጥቀስ፣ መንግሥት ሆነ የግል ድርጅቶች ፋብሪካ አቋቁመው „ለሥራ
ፈላጊው ክፍል የሥራ ዕድል ለመክፈት…“ የሦሰት ወር ጊዜ አይበቃቸውም።
እንግዲህ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ፍላጎት ከአለው፣ ጥያቄአቸውንም
ለማዳመጥ ጆሮ አለኝ ከአለ፣ነገውኑ የክብ ጠረጴዛ ስብሰባ ጠርቶ፣ ሁሉንም ክፍል ሊያነጋገር
ይችላል። አለበለዚያ– ብዙዎቹ እንደሚሉት– ምርጫው እንደገና አደባባይ ወጥቶ የሚሰማ ከተገኘ
አቤት ማለት ነው። መውጣት!

ኢትዮጵያ ግን (የብዙውን ሰው ፍርሃቻ ለመመለስ) ይህቺ አገር እንደ ኢራን አትሆንም። የግብጽም
ዓይነት ዕድል አያጋጥማትም። እንደ ሱማሌም፣ ነገ ይህች አገር አትበታተንም።

~ 20 ~

አያድርስ ነው እንጂ እኛ መቼም የፈረደብን እና ያልታደልን ፍጡሮች በመሆናችን በገዛ እጃችን
ሁሉንም አይነት ሥርዓት፣ ሳንፈልግ፣ ሳንመርጥም፣ ድምጻችንንም ሳንሰጥበት፣ በግድ ሁሉንም ዓይነት
ሥርዓት ቀምሰናል።
…የኮሚኒስቱን የደርግን አስራ ሰባት አመት፣ጥሩ አድርገን፣ እንደ ሌሎቹ ጠጥተናል።፣ …ፈላጭ
ቆራጩን የግራኝ መሃመድን የሻሪያውን ሥርዓት ለአመታት ሁሉም ቦታ ባይሆን፣ አባቶቻችን ፣
በኢትዮጵያ ደማቸው እየፈሰሰ ፣ እነሱ ተግተውታል።
ለአለፉት 23 አመታት ደግሞ ….በዘርና በጎሣ ፖለቲካ የተለወሰውን የኢህአዴግንና የሻቢያን
አምባገነን ሥርዓት ቀምሰናል። ይኸው ፣ ይክበር ይመስገን ፣ ይህ የአምባገነኖች ሥርዓት ሁላችንንም፣
… አጨብጫቢውን ጭምር፣ አሁን አንገሽግሾታል።
…የዮዲት ጉዲት፣የጥፋት ዘመን ለማንም አይረሳም። የንጉሣዊ አገዛዝን፣…የመሣፍንቱን፣ የጦርነት
ዘመን …የሽፍታውን፣…የወታደሩን፣….የካድሬውን፣….እረ ምኑቅጡ! ሁሉም በአናታችን ላይ
ጨፍረዋል።
እንግዲህ አሁን ደግሞ ይክበር ይመስገን ወሳኝ ጊዜ ውስጥ፣ ድምጻችንን ነገ የምናሰማበት
የምንሰጥበት፣ 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ገብተናል።
ለመሆኑ ምን ይመጣ ይሆን?

ተላላው ተማሪ„…ጊዜው ደረሰ የነጻነቴ ፋና …“ እያለ ያኔ አደባባይ ሲወጣ ከፊቱ ምን ዓይነት
„አጋንንት/ አጋንንቶች“ ቆመው እንደሚጠብቁት፣ ያኔ አልጠየቀም፣ ያኔ ተነስቶ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ
አልተመራመረም፣ ያኔ መጥፎ ቀን ይመጣል ብሎም፣ ያ ትውልድ አልገመተም ነበር።
ይህን በአለማድረጉም ፣ትንሽ ቆይቶ ይህ ትውልድ ያጨደው፣ በደጃፉም ላይ የከመረው ያ እንደ ወሃ
የጠማውን የተመኘውን „ነጻነትንና ነጻ-ሕብረተሰብን“ ሳይሆን ….ቀለሃ ጥይትን፣… ሞትን፣ ስደትና
እሥራትን፣ በአጭሩ አምባገነንነትን ነበር።
ዘንድሮስ፣ ወይስ በቅርቡ ምን ይመጣ ይሆን? እንደሚፈራውና እንደሚባለው „የሻሪያ ሥርዓት“
ተመልሶ ይመጣል?
ወይም „የተበታተነች ኢትዮጲያ ከፊታችን አለች?“… ወይስ „አንዱ የጠገበ አምባገነን“ ሥልጣኑን
ቀምቶ እንደገና ሃያ አመት ወደፊት ይገዛን ይሆን?
አይመስለንም።
ታዲያ ምን ዓይነት ሥርዓት ይመጣ ይሆናል?
ሁሉም አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ፣ በነጻነት መብቱን አስከብሮ የሚኖርባት፣ የዲሞክራቲክ የፓርላማ
ሥርዓት፣ አለጥርጥር፣ በቅርቡ በአገራችን ይመሰረታል።
አራዳ ፖለቲከኞች ግን በእንደዚህ ዓይነቱ አነጋገር ከአንዴም ሁለቴ አታለውን ሥልጣኑን ይዘው ፣
አንለቅም ብለው መከራችንን አሳይተውናል። ግን አሁን ጊዜው፣ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን
ለአምባገነኖች ያከተመ ይመስላል።
ስለ ነጻ ሰውና ፣ ስለነጻ ዜጋ፣ ስለ ነጻነትና ስለ ሊበረቲ ፣ይህ በሰው ልጆች ዘንድ ስለ አለው ከፍተኛ
ቦታ፣ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን በሚቀጥለው ቅጻችን እንመላለስበት ይሆናል።
ቁም ነገሩ የፈለጉትን ቀለም ይያዙ፣ አምባገነኖችን ከኢትዮጵያ ማባረሩ ላይ ነው። ሕገ-መንግሥቱ
ደግሞ ሰላማዊ የተቃውሞ ትግልን ይፈቅዳል።

~ 21 ~

ከኪነ፥ጥበብ ዓለም
Posted on June 11, 2013

ማይስትሮ ግርማ ይፍራሸዋ
ከኪነ፥ጥበብ ዓለም፤ ማይስትሮ ግርማን፣ በዶክተር አሸናፊ ከበደ ፈለግ ሲጓዝ፣ እስቲ እንተዋወቀው!
ንውዩን ፍለጋ ብቻ፣ የቆየውን እንደማይሆን እናድሳለን፣ በማለት፣ ያልበቁ ባለ ሙያዎች፣ ጆሮአችንን
እንደሚያደክሙት ሳይሆን፣ እንደ መንፈስ መነቃነቅ በሚቃጣቸው ጣቶቹ፣ ፒያኒስት ግርማ
ከሙዚቃችን ውበት ጋር ያገናኝናል። ውበት ይጋብዘናል !
ዩትዩብ ውስጥ በድረ ገጽ ላወጡልን ባለጉዳዮች ምስጋን እያቀረብን፣ እነሆ ለእናንተም ይሁን፥

http://www.youtube.com/watch?feature=player_em
bedded&v=SlclKj71EsA
http://www.youtube.com/watch?feature=player_embedded&v=O
4JzIpTpRv0

OPEN LETTER: SMNE calls on Prime Minister Hailemariam Desalegn
Posted on June 5, 2013

SMNE Calls on Prime Minister Hailemariam Desalegn

To Lead Ethiopia towards Change by Answering the Demands of the
People

SMNE OpenLetter To Prime Minister Hailemariam

~ 22 ~

ግንቦት 25
Posted on June 5, 2013

ግንቦት 25 / 2005/
የ ኢትዮጵያ 21ኛው ክፍለ፥ዘመን
የተጀመረበት ቀን ሊሆን ይችላል!
ትግሉ እንዲቀጥል፣
አንዳንድ ቁም ነገሮች…

__________________________________
I/ አንደኛ
- በተለይም የግብጽ ወጣቶች በምን ዘይቤና ብልሃት ወደ ህዝቡ ልቦናና መንፈስ ወስጥ ሰርጾ
በመግባት፣ በሰላማዊ አመጽ፣ በአልገዛም ባይነት፣ ያን እስተአፍጢሙ ድረስ የታጠቀን
የሙባረክ መንግሥትን እንዴት እንዳምበረከኩ፤
- መንግሥት በሰላማዊ ታጋይነታቸው ብቻ ፈርቶዋቸው (መንግሥት የታጠቀ ቡድን አይፈራም!)
በእስር ላይ የሚያማቅቃቸው፣ የመብት ተሟጋች ወገኖቻችንን በሙሉ፣ መንፈሳቸውን ያጠናክርልን
እያልን፣
እኛም ከዳር እስከ ዳር ዘርና ሃይማኖት ሳይለየን፣
አዎ በ መሪው፥ቃል፣ በ “አንለያይም ! አንለያይም !„ መሠረት፣
ግንቦት 25 / 2005/ ን
የ ኢትዮጵያ 21ኛው ክፍለ፥ዘመን የተጀመረበት ቀን አድርገን፣ ትግሉን ለመቀጠል፣

~ 23 ~

ያን የውድ ሃገራችንን ምድር በሰላማዊ ትግል እንዴት እኛም ልናንቀጠቅጠው
እንደምንችል የሚጠቁሙ፣ በተለይ በአፍላው የግብጽ ወጣቶች ትግል ጊዜ፣
ከግብጽ ሰላማዊ አመጽ፣ ለሃገራችን ተጨባጭ እውነታ፣ ምን ምን ለመማር እንደምንችል፣
አንዳንድ ማስታወሻዎች አሉኝ፥— ተመልከቱት፥
Short Lessons …. From NEW EGYPT –
HOW They Did It!
________________________________
II/ ሁለተኛ
የ ኢትዮጵያ 21ኛው ክፍለ፥ዘመን
የወጣቱ ነው፤ ስለሆነም የኢትየጵያ ወጣት ሚናንም
ትንሽ ጠለቅ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል፥ ይጠቅማል፥
A Simple Algebra of Social-Dynamics –
The Role of the Youth
A social collective is populated by different multiplicities of actors, with
different preferences of interests and attractors of meanings. If all actors
are collectively designated as agency, we can call them „The Human
Agency”. This Agency can be divided ( to make the social analysis and its
dynamics as simple as possible) into three big [...]
Read More…
III/ ሦስተኛ
________________________________________
የኢትዮጵያም 21ኛው ክፍለ፥ዘመን ለውጥ መሠረታዊ መሆን አለበት፣
ይህ ይሆን ዘንድ ምን ዓይነት መሰረታዊ ግንዛቤ ማድረግ ያስፈልጋል?
መሠረታው ሃሳቦች፥
A Short Note on Ethiopian Political Change in Systemic Thinking
Social relations and the nature of conflict in a community (family,
community or state etc.) are, according to Alexander Wendt,
characterized by the sense of perception as enemies (Hobbesian), rivals
(Lockean) & friends (Kantian). But I would add “the other”, which has

~ 24 ~

to be utterly “new” or should look like substantially different from the
perspective of all [...]
Read More…
________________________________________
IV/ አራተኛ
በመጨረሻም ከሁሉም ይልቅ ስረ፥መሠረታዊ የሆነው፣
አስርቱ ፍሬ ነገሮች፣ ስለሥልጣንና
የሥልጣነ ቢስነት/ የደካማነት ውስጣዊ ተንቀሳቃሽ ግንኙነት
Ten Theses on the Inner Dynamics of Power and Powerlessness

1.
በህግም ሆነ በመዋቅር ክልል ውስጥና ከዚያም ባሻገር፣
በግላዊ መስተጋብር ውስጥ፣ ሌላኛው
በ እ ኔ ላ ይ ሥልጣን የሚኖረው፣ እኔ ለ እ ር ሱ ለመስጠት የፈቀድኩለትን
ያህል ብ ቻ ነ ው!
2.
የባለሥልጣኑንም ሆነ የደካማውን/ ሃይለ ቢስነት፣ ክብርንና
የሥልጣኑን አንጻራው ተጽዕኖ በብዛት የሚመጥነው፣ ራሳችን
የምንሰጠው ከፍተኛ ዋጋ ነው።
3.
በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ፣ ማጎንበስ አለብን ብለን የምናምንለት
ከፍተኛ ሥልጣን
በአብዛኛውን ጊዜ በተጨባጭየሚመነጨው፣
ሥልጣንን ከመቀበል የገዛ ፈቃደኝነት ወይንም የተለምዶ ሃይል ነው።
4.
ደካማነት/ ሃይለቢስነት መጀመሪያ የሚከሰተው በራሳችን ጭንቅላት ውስጥ ነው፤
እራሳችን በራሳችንና፣ በአስተሳሰብ ዘይቤያችን ነው፣

~ 25 ~

እራሳችንን ተገዢ አድርገን የጥንካሬያችን እንቅፋት የምንሆነው።
5.
ይበልጡን ግዜ በብዛት የምናስበው በክፉና እራሳችንን ሽባ
በሚያደርግ መንገድ ነው።
ለለውጥ ያሉትን በቂ ደግ እድሎችንና አጋጣሚዎችን አናይም!
6.
እያንዳንዱ ለውጥ የሚጀምረው በራሳችን ውስጥ ነው።
7.
እያንዳንዱ ለውጥ የሚጀምረው በራሴ የሃላፊነት ክልል ውስጥ ነው
8.
ብዙውን ግዜ ንቁና አዲስ ነገር በሚፈጥሩ ጥቂት ሰዎች ዘንድ
ያለውን ጠንካራ ሃይል ፤
እንዲሁም በማህበራዊ ሥረ መሠረት ደረጃ ያለውን የመተባበር ሃያልና ድፍረት ብዙውን ግዜ
ኣሳንሰን እናያለን።
9.
የሚረባ ፍሬ ነገር የሚገኘው ፣ ሃይልን በመረዳት ሲገለገሉበት፣ ሌላውን ለመቆጣጠር በሚሻ መልኩ
ሳይሆን ፤
ነገር ግን ለጋራ ፍላጎትና ለመልካም ህይወት፣ ለተቻለው ብዛት ሁሉ፣
በጋራ ጥረት ሃይልን ሲገነቡበት ነው።
ይህ ነው፣ የራሳችንና የሚገባንን ፍላጎት ከማህበራዊ ና
ከፖለቲካዊ ትብብር ጋር የምናቀናጅበት፣
ዴሞክራሲያዊው መንገድ።
10.
ሃይለ ደካማነትን ለማሸነፍ ዕውቀት፣ትዕግስትና (በራስ)
መተማመንን ይጠይቃል።
*

*1) Reprinting & Translation of these extracts granted in this form by

Copyright © 2005 by Professor Dr. Gerd Meyer

~ 26 ~