You are on page 1of 7

ቋንቋ፣ ብሔራዊ ዕሴት እና ትምህርት

………………………
(፩)
ከተባባሪ ፕ/ር አያሌው ሺበሺ ጋር የተደረገ ውይይት
………………………………………
በአንድ ጽሑፍዎ ላይ፣ “የትምህርት ሥርዓታችን በተለያዩ አገሮች የጡት አባትነት ሲካሄድ መቆየቱ ጎድቶናል” ሲሉ
ገልጸዋል። እስኪ ነገሩን ይበልጥ ያብራሩትና እንዴት እንደጎዳን ይግለጹልን?
………………………………………….
ተባባሪ ፕ/ር አያሌው፡- የትምህርት ሥርዓታችን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ተጽዕኖ አልተለየውም። ከ1908 -
1928 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ትምህርት ቤቶች በእርግጥ በጣም ጥቂት ነበሩ። በወቅቱ የትምህርት ሥርዓቱን
ለመምራት የመጣ የተወሰነ አገር ሰው የለም። ግን አብዛኞቹ ከግዕዝ፣ ከአማርኛና ከግብርገብ ትምህርት ውጪ
ያሉትን ትምህርቶች ያስተምሩ የነበሩት መምህራን ከውጭ አገር የመጡ፤ በተለይ ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ጋር
ግንኙነት ያላቸው ነበሩ። እና የዚያም ጊዜ ቢሆን በአገር የበቀለ ትምህርት ነው ማለት አይቻልም።
በጣሊያን ጊዜ የነበረው እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት አይደለም። ጣሊያኖች የነበረውን ዘመናዊ
ትምህርት በእንጭጩ ከቀጩት በኋላ ለራሳቸው የሚበጅ፣ እነሱ የማይሠሩትን ሥራ ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎችን
ለማፍራትና ወታደሮችን ለማስተማር የጀመሩት የትምህርት ሥርዓት ስለነበረ፣ በወቅቱ ኢትዮጵያዊ የትምህርት
ሥርዓት መጠበቅ አይቻልም። ጣሊያን ተሸንፎ ከወጣና የኢትዮጵያ መንግሥት ከተመለሰ በኋላ ደግሞ በተለይ
በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የትምህርት ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ አስተዳደር በሙሉ በእንግሊዞች ሥር
ነበር። የዚያን ጊዜ አጣዳፊው ነገር፤ መንግሥትን መልሶ ለማቋቋም ቢሮክራሲውን የሚያንቀሳቅሱ የውትድርና
ተቋሙን የሚመሩና ሌሎች የሥራ ድርጅቶች የሚፈልጉትን የሰው ኃይል ለማሟላት ነበር ትኩረት የተሰጠው
በወቅቱ።
መምህራኑም ብዙዎቹ በእንግሊዝና እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳ፣ ሱዳን እና ሕንድ ከመሳሰሉ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች
የመጡ ነበሩ። አንዳንዶቹ እንዲያውም በውትድርና የአገሪቱን ነጻነት ለማስመለስ ከረዳው የእንግሊዝ ሠራዊት ጋር
አብረው የመጡ ነበሩ። የትምህርት መዋቅሩም ጠቅላላ የእንግሊዝን የትምህርት ሥርዓት ተከትሎ ነው የሄደው።
በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የነበሩት ዋና ዋና ሹመኞችም እንግሊዛውያን ነበሩ። መጻሕፍቱም ከዚያው ከእንግሊዝ
የመጡ ነበሩ። ይሄ እንግሊዞች እዚህ እስከነበሩት ጊዜ ቀጠለና ኢትዮጵያ “ፓይንት ፎር” የተባለውን ፕሮግራም
ከአሜሪካ ጋር ከተፈራረመች በኋላ የመንግሥት ዕርዳታውም የመንግሥት አመራሩም በአሜሪካ ሲስተም ውስጥ ገባ።
በዚህ ጊዜ ብዙ ለውጦች ነበሩ። ራሱ መዋቅሩ ስምንት ዓመት የአንደኛ ደረጃ ትምህርትና አራት ዓመት የሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት እንዲሆን ተደረገ። በዚህ ጊዜ የቢሮክራሲው፣ የወታደሩና የሌሎች መሥሪያ ቤቶች ፍላጎት በተወሰነ ደረጃ
ተሟልቶ ስለነበረ አንደኛ ደረጃ የሚስተምሩት መምህራን ኢትዮጵያውያን እንዲሆኑ ሙከራ ተደረገ። አጠቃላይ
የትምህርት ሥርዓቱ ግን የአሜሪካንን ሲስተም እንዲመስል ነው የተደረገው። ይሄ እስከ 1966 ዓ.ም. ቀጠለ።
የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በወታደራዊው መንግሥት እስከተተካበት ጊዜ ድረስ መጀመሪያ የእንግሊዞች በኋላ ደግሞ
የአሜሪካውያን ተጽዕኖ ነው የነበረው። በአብዮቱ ዓመታት እንደሚታወቀው አገሪቱ በአጠቃላይ ፊቷን ወደ ምሥራቅ
መለሰች፤ የትምህርት ሥርዓቱም የራሱ ድርሻ ነበረው። በተለይ ከምሥራቅ ጀርመንና ከሶቭየት ኅብረት ጋር በነበረው
ቁርኝት የምሥራቅ ጀርመንን ሞዴል ለመከተል ብዙ ሙከራ ተደረገ። ዋናው በዚህ ጊዜ የነበረው መርህ፣ መንግሥት
ይከተለው በነበረው ርዕዮተ-ዓለም መሠረት፣ ማለትም በማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተምህሮ አንጻር፣ የትምህርት
ሥርዓቱን መቅረጽ ነበር።
ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ምናልባት እንዲህ አንድ አገር በቀጥታ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ሁኔታ ተፈጠረ ማለት
አይቻልም። በእርግጥ የምሥራቁ አዝማሚያ ተቀይሮ የምዕራቡን በአጠቃላይ የመከተል አዝማሚያ ነው ያለው።
በዚህ ሂደት ግን አንድ አገር ሳይሆን ብዙ አገሮች በጋራ በትምህርቱ ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ያም
በመሆኑ ከዚህ አገር ከዚያ አገር ተቀዳ ለማለት ያስቸግራል። የብዙ አገሮች ተጽዕኖ ነው ያለው።
ለማጠቃለል፣ እንደየጊዜው የተለያዩ አገሮች በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ሞክረዋል። እንግሊዞች በነበሩ
ጊዜ የትምህርት ሥርዓቱ በአጠቃላይ የእንግሊዞችን ይመስል ነበር። አሜሪካውያን ሲተኩም የእነሱን መሰለ። ከዚያ
በኋላ ደግሞ አገሪቷ ዐይኗን ወደ ምሥራቅ ባደረገችበት ጊዜ የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ ታስቦ ነበር፤ ግን ተፈጻሚነት
አልነበረውም። የትምህርት ይዘቱን ግን ቀደም ሲል ከነበረው ወደ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ይዘት እንዲያደላ ለማድረግ
ከፍተኛ ተጽዕኖ ተፈጥሯል። ሰዎችም እየተላኩ ይሠለጥኑ የነበረው ወደ ምሥራቅ ጀርመን ነው። እንዲያውም
የትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች ‹‹ከሞትና ከምሥራቅ ጀርመን የሚቀር የለም›› እያሉ የሚቀልዱት ቀልድ ነበር። የክፍል
ኃላፊዎች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ኤክስፐርቶች በሙሉ ለ6 ወር፣ ለ9 ወር፣ ለአንድ ዓመት እየሄዱ እየሠለጠኑ ነበር
የሚመጡት።
እንግዲህ የዚህ ሁሉ አጠቃላይ ሂደት ትምህርቱን በኢትዮጵያ ዕሴቶች ላይ የተመሠረተ አገራዊ እንዳይሆን አድረጎታል።
እነፕ/ር መሳይ ከበደ፣ ፕ/ር ሀብታሙ ወንድሙና ፕ/ር ማሞ ሙጬን ጨምሮ ብዙ ምሁራን በጉዳዩ ላይ በይበልጥ
ትችታቸውን ሰንዝረዋል። “መጀመሪውኑ ሲጀምር ለምን በኢትዮጵያ ዕሴቶች ላይ ተመሥርቶ እንዲጀምር
አልተደረገም?” የሚል ሰፊ ትችት አለ። እንዲያውም ትችቱ የሚጀምረው በ1920ዎቹ ነው። በወቅቱ የትምህርት
ሥርዓቱን እንዲያጠና ተቀጥሮ የመጣ ፕ/ር ኧርነስት ወርክ የሚባል ምሁር ነበር። እና የትምህርት ሥርዓቱን አይቶ
ከፍተኛ ትችት ነበር ያቀረበው። “ልጆቻችሁን የምታስተምሯቸው ምንድን ነው? ከአውሮፓ የተገለበጠ፣ የኢትዮጵያን
ቋንቋ፣ ታሪክና ባሕል ያላገናዘበ ትምህርት ነው እያስተማራችኋቸው ያላችሁት” ሲል ነበር አስተያየት የሰጠው።
እንዲያውም፣ “ልጆቻችሁ ስለአማርኛ ሥነ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍም ሆነ እንደአፄ ሚኒልክ ዓይነት ስመ ጥሩ መሪዎቻችሁ
ምንም አያውቁም፤ ስለ ውጭ ቋንቋ፣ ታሪክና ባሕል ለምሳሌ ስለአውሮፓ ባሕልና እንደጋሪባልዲና ቢስማርክ ዓይነት
የውጭ አገራት መሪዎች ግን አብጠርጥረው ያውቃሉ” የሚለው ከሰጠው አስተያየት ትዝ ይለኛል። ስለዚህ ትችቱ የቆየ
ነው። እኔ እንደማየው በአንድ በኩል መተቸቱ ትንሽ ከባድ ይመስለኛል።
………………………………..
እንዴት?
…………………………………….
ተባባሪ ፕ/ር አያሌው፡- ለምሳሌ በ1920ዎቹ አካባቢ የነበረውን ሁኔታ ብንወስድ፣ ዘመናዊ ትምህርት የወሰዱና
በትምህርት ሥራ የሚሳተፉ በጣት እንኳ የሚቆጠሩ ሰዎች አልነበሩም። የተማሩ ሰዎች በሌሉበት ባሕሉን፣ ታሪኩን
አጥንቶ በኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ላይ የተመሠረተ የትምህርት ሥርዓት መፍጠር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። መጀመሪያ
የተማረ የሰው ኃይል እንዲኖር ያስፈልጋል። በጣሊያን ጊዜ የነበረው ያው የጣሊያን የሥርዓት ትምህርት ነው። ለራሱ
አገዛዝ እንዲበጀው አድርጎ የቀረጸው ነው። በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያዊ ዕሴትን የያዘ የትምህርት ሥርዓት መቅርጽ
የሚጠበቅ አይመስለኝም። ከሁሉ የከፋው ነገር ጣሊያን የመጣሁት የማሠልጠን ዓላማ ይዤ ነው ቢልም፣ የጀመረው
ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት እና ወደ ጦር ካምፕነት በመቀየር ነበር።
እንደሚታወቀው በአገራችን የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት ነው። ጣሊያኖች
በመጀመሪያ ያደረጉት የሚኒልክን ትምህርት ቤት ወደ የአየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያነት መቀየር ነበር። ከዚያ ሁሉ
የከፋው እነዚያን ከጦርነቱ በፊት የተማሩትን ጥቂት ኢትዮጵያውያን ፈጅተዋቸዋል። የታሪክ ባለሙያዎች
እንደሚነግሩን በወቅቱ ከጠቅላላው ሕዝብ ወደ ሃያ አምስት በመቶው አልቋል ነው የሚባለው። ከጣሊያን በፊት
ከተማሩት ኢትዮጵያውያን ውስጥ ደግሞ ሰባ አምስት በመቶዎች ናቸው ያለቁት። ነጻነት ተገኝቶ ወደ አገር ሲመለሱ
መጀመሪያ የመንግሥት መዋቅሩን መፍጠር ስለነበረ ርብርቡ በሕይወት የተገኙት ጥቂት ኢትዮጵያውያን
ቢሮክራሲውን ለማቋቋም ነበር የተመደቡት። እና በትምህርቱ መስክ የተሰማሩ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ
ኢትዮጵያውን አልነበሩም። የትምህርት ሥርዓቱ በውጭ አገር ሰዎች እጅ ነው የነበረው። ከ1933 ጀምሮ እስከ 50ዎች
ባለው ጊዜ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ዳሬክተሮች ሳይቀሩ አብዛኞቹ በትምህርት ሥራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች የውጭ አገር
ዜጎች ነበሩ።
በወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የነበሩት የካሪኩለም ኤክስፐርቶች፣ የፕላን ኤክስፐርቶች ሁሉ የውጭ ሰዎች
ነበሩ። ሁኔታው ይህ በነበረበት ጊዜ ለምን በኢትዮጵያ ዕሴቶች ላይ የተመሠረት ትምህርት አልተቀረጸም ብሎ
ሥርዓቱን መውቀስ አስቸጋሪ ይመስለኛል። ያንን የሚቀርጹ ሰዎች ሥርዓቱ አላፈራም። ይሄ ወቀሳ አግባቡ የሚሆነው
ከ1960ዎቹ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ሲቀርብ ነው። በአሁኑ ወቅት ይሄ ለምን አልተሠራም? ለምን
አልተደረገም? የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው፤ እንጂ በ1930ዎቹ፣ በ1940ዎቹ እስከ 1950ዎቹ አጋማሽ ድረስ
ቢሮክራሲውንና ሌሎች ዘርፎችን የሚመራ የሰው ኃይል ከማፍራት ውጪ የትምህርት ሥርዓቱን የሚመራ የሰው
ኃይል አላፈራንም። በኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ላይ ያተኮረ ትምህርት አለመሰጠቱ፣ ይልቁንም የራሳችንን ቋንቋ
አለመጠቀማችን ግን ካለምንም ጥርጥር ጎድቶናል።
…………………………………….
ለደረሰው ጉዳት ማሳያዎች ምንድን ናቸው?
…………………………………………
ተባባሪ ፕ/ር አያሌው፡- ያፈራነው የሰው ኃይል ስለአገሩ ብዙም የማያውቅ ግን ስለአሜሪካ፣ አውሮፓን፣ ኢሲያ ወዘተ.
አበጥሮ የሚያውቅ፣ ባሕሉንም ታሪኩንም የሚናገር ትውልድ ነው። ይሄ በእንግሊዝኛው “ኤሊኔሽን” (alienation)
እንደሚሉት የተማረውን የሰው ኃይል ከማኅበረሰቡ ጋር ያፈራቀቀ፣ የለየ የትምህርት ሥርዓት ነው የነበረን። ያ ደግሞ
በዕድገታችንም በታሪካችንም ብዙ ጎድቶናል። እንደሚታወቀው ከንጉሣዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ
እስከተሸጋገርንበት ጊዜ ድርስ የተማሪው ኃይል ነው የለውጥ መሪ፣ የለውጥ አንቀሳቃሽነት ሚና የተጫወተው። ያ
ኃይል ግን ስለአገሩ የነበረው ዕውቀትና ግንዛቤ ውሱን ነበር። ስለ ቋንቋው፣ ስለ ባሕሉና ስለ ታሪኩ ብዙ የተረዳ ነበር
ለማለት በጣም ያስቸግረኛል። ያም በመሆኑ ያላደገበትን ርዕዮተ-ዓለም ተከትሎ በመጓዙ በአገራችን ብዙ ጥፋት
ደርሷል።
……………………………………..
አሁንም ቢሆን በዚያው በተለመደው መንገድ ከመሄድ ወጭ የኢትዮጵያን ባሕልና ታሪክ ከግምት የሚያስገባ ሁኔታ
አለ ማለት አይቻልም። በእርስዎ በኩል የሚያዩት ለውጥ ምንድን ነው? በዚህ ሁኔታስ እስከ መቼ እንቀጥላለን?
……………………………………….
ተባባሪ ፕ/ር አያሌው፡- አሁንስ ቢሆን የሚለው ደግሞ አሁን ለየት ያለ ችግር ነው ያለው። የኢትዮጵያዊ ዕሴቶች
ምንድን ናቸው? ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶችና የብዙ ብሔረሰቦች አገር ናት። ከዚያ ውስጥ የጋራውን ባሕል ለይተን
አውጥተን የተከተልን አይመስለኝም። በተለይ በአንደኛ ደረጃ ላይ - የአብዛኛው ሕዝብ አስተሳሰብ የሚቀረጸው ደግሞ
በዚያ ደረጃ ነው - ሥርዓተ-ትምህርቱ አንኳር የሆኑ የጋራ ኤለመንቶች ቢኖሩትም፣ የሚቀረጸው በክልል ደረጃ አንዳንድ
ቦታ እንዲያውም በዞን ደረጃ በመሆኑ፣ የጋራ ዕሴቶችን ለማውጣት በጣም ያስቸግራል። እና ለልጆቻችን ተመሳሳይ
አገራዊ ዕሴት እየሰጠናቸው እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
…………………………………………….
የአገራችን የትምህርት ጥራት በሚያሳስብ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግልጽ ነው። በመንግሥትም በኩል ችግሩን ለመቅረፍ
ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው የሚነገረው። በትምህርት ጉዳይ ላይ ለረዥም ጊዜ ጥናትና ምርምር እንደሠራ ምሁር፣
የእርስዎ ሐሳብ ምንድን ነው? ለጥራቱ መውደቅ ምክንያት ናቸው የሚሏቸው፣ እንዲሁም ጥራቱን ለማሻሻል ይረዳሉ
የሚሏቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
……………………………………………….
ስለትምህርት ሲወራ ጥራትና ብዛት ዋና ዋና የመነጋገሪያ ነጥቦች ናቸው። ያለፋትን ሁለት ዐሥርት ዓመታት
የትምህርት ይዞታ ያየን እንደሆነ ብዛቱን በሚመለከት ያለ ጥርጥር ሰፊ ጥረት ተደርጓል። በመንግሥትም በዓለም
ዐቀፍ ድርጅቶችም ድጋፍ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤ በአንደኛ ደረጃም፣ በሁለተኛ ደረጃም፣ በከፍተኛ
ትምህርትም።
በአንደኛ ደረጃ፣ ትምህርት ማግኘት አለባቸው የሚለውን የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት
እየተደረገ ነው። የተሳትፎ መጠኑም አሁን ከ90 በመቶ በላይ ደርሷል። ይሄ ትልቅ ውጤት ነው። በሁለተኛ ደረጃም
እንዲሁ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ያየን እንደሆነ እንደሚታወቀው በ1983
ዓ.ም. አስመራ ዩኒቨርሲቲን ስንተው አዲስ አበባና አለማያ ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ነበሩ። አሁን ቁጥሩ ወደ 43 ደርሷል።
የተማሪውም ቁጥር በጣም አድርጓል። ያም ሆኖ ከሰሃራ በታች ካለው የአፍሪካ ደረጃ ላይ አልደረስንም።
ይሄንን ጥያቄ ከጥራት አኳያ እንየው፡፡ ጥራትን እንግዲህ ከግብዓትም፣ ከሂደትም፣ ከውጤትም አንጻር መለካት
ይቻላል። ከግብዓት አንጻር መሻሻሎች ይታያሉ። ግብዓት የምለው የተማሪ-መምህር ጥምርታ፣ የተማሪ-ክፍል
ጥምርታ፣ የአስተማሪ የትምህርት ደረጃ ወዘተ. በቁጥር ሊገለጹ የሚቻሉ ነገሮች አሉ። እነሱን ስንመለከት ከጊዜ ወደ
ጊዜ መሻሻሎች እንዳሉ ይገባኛል። ሒደቱ፣ የማስተማር መማር ሒደቱ ላይ ነው ትልቅ ችግር ያለው። ውጤቱ፣ ተምሮ
የመጣው ሰው በተግባርም ‹‹በነቢብም ሲፈተሽ በሚፈለገው ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ነው ወይ?›› ብለን ስንጠይቅም
ትልቅ ችግር አለ። እና ጥራቱ ወርዷል ብቻ ሳይሆን አሁንም እየወረደ ነው። ቀሰቱ አሁንም ቁልቁል ነው የሚያሳየው።
የጥራቱን መውረድ መንግሥትም የሚስማማበት ነው።
ጥራቱን ለማሻሻል ምን እናድርግ? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው። ቀላልና አጭር መልስ ያለውም አይደለም። ለምሳሌ
የፋብሪካን ወይም የኢንዱስትሪን ሥራ የወሰድን እንደሆነ ጥራቱን እንዴት እናሻሻለው? ብለን ብንጠይቅ የተወሰነ
ፕሮግራም ቀረጾ ሂደቱንና ውጤቱን በሚመለከት “ይሄ ይደረግ” ማለት ይቻላል። የትምህርት ጥራትን በሚመለከት
ግን ነገሩ ሌላ ነው። አንደኛ ጥራቱ ለመውረድ ጊዜ ይፈጃል፤ ከወረደ በኋላም ለመመለስ እጀግ በጣም አስቸጋሪ ነው።
መኪና ከፋብሪካው ተበላሽቶ ቢወጣ መልሶ ወደ ፋብሪካው መላክ ይቻላል፤ አሁን ጃፓን እያደረገች እንዳለው።
የማይሆን ነገር ተምሮ የወጣን ሰው እንደገና ተመልሶ ይስተካከላል ማለት ግን የሚቻል አይደለም። ፈተናው ብዙ
ነው፡፡
ለእኔ የመጀመሪያው ነገር እየወረደ ያለውን ሒደት ማቆምና ከዚያ በኋላ ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ነው። ይሄ እንዴት
ይሠራል? አንደኛ ግብዓቱን ማሟላት ነው። ትምህርት ቤቱን፣ መምህሩን፣ መጽሐፉን፣ ቤተ-ሙከራውን የመሳሰሉትን
ነገሮች በወጉ አደራጅቶ እንደየደረጀው መስጠት ነው። ሁለተኛው ሒደቱን ማሻሻል ነው። ሒደቱ እንዴት ነው
የሚሻሻለው? መጀመሪያ እዚያ ላይ የሚመደቡ ሰዎች፣ በማስተማርም በአስተዳደርም ሥራ የሚመደቡ ሰዎች፣
ለደረጃው የሚመጥኑ፣ በሥራው የሚደሰቱ፣ መሰጠቱ (ኮሚትመንት) ያላቸው ሰዎች መሆን አለባቸው። መምህርና
ተማሪ ስለተገናኘ ብቻ ትምህርት ይካሄዳል ብሎ ማመን ያስቸግራል። በሙያው የሚሰማሩት መምህራን ለሥራው
ፍቅር ያላቸው፣ ችሎታው ያላቸው፣ በሥራው የሚያምኑ ሰዎች መሆን አለባቸው።
አሁን ስመለከተው ደግሞ ያሉን መምህራን በሥራቸው ሙሉ በሙሉ ደስተኛ እንዳልሆኑ፣ ይኼ ሙያዬ ነው፣ ሥራዬ
ነው ብለው ያሉ ናቸው ለማለት ያስቸግራል። ብዙ ቅሬታ አላቸው። ቅሬታ የሚፈጥሩባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ።
ዋነኛው ግን አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም የሚያስችል ገቢ አለማግኘታቸው ይመስለኛል። ያንን በአገሪቱ
አቅም መሠረት ቢያንስ ‹‹ምን ልብላ ምን ልጠጣ›› ብለው እንዳይቸገሩ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚያ ላይ ደግሞ
ተከታታይ ሥልጠና መስጠት የግድ ነው። ከሙያው ጋር እንዲተዋወቁ ተከታታይ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ሙያው
ዝም ብሎ ቆሞ የሚጠብቅ ነገር አይደለም፡፡ ያድጋል፤ ይለወጣል። ሥልጠናውም ዝም ብሎ የማዳረስ ነገር ሳይሆን፣
በትክክል የሰዎችን አቅም የሚያሳድግ መሆን አለበት።
በኃላፊነት ቦታ የሚመደቡት የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን፣ የትምህርት ቤት ሱፐርቫይዘሮች፣ አሁን ደግሞ
ኢንስፔክሽን የሚባል ነገር ተጀምሯል፣ ኢንስፔክተሮች በሙያ ብቃታቸው ብቻ መመደብ ይኖርባቸዋል። የወረዳ፣
የዞን፣ የክልል የትምህርት ኃላፊዎች በሙሉ በሙያ ብቃታቸውና ችሎታቸው ብቻ ተመርጠው የሚቀመጡ ሰዎች
መሆን አለባቸው። ዋናው መመዘኛ “የመማር ማስተማሩን ሥራ፣ የትምህርት አመራሩን ሥራ ምን ያህል
ተገንዝበውታል? ለዚያስ ራሳቸውንና ጊዜያቸውን በተገቢ ሁኔታ ለማዋል ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?” የሚለው ነው።
ሌላ መመዘኛ ሊገባ አይገባም። ያን አድርገን ጠንክረን ከሠራን ከችግሩ መውጣት የሚቻል ይመስለኛል
…………………………………….
በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ባለው የ70/30 ፕሮግራም ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
……………………………………….
ተባባሪ ፕ/ር አያሌው፡- ቁጥር ላይ ሳንመጣ ሐሳቡ በመሠረቱ ጥሩ ነው። በዛ ያለውን ወደ ሳይነስና ቴክኖሎጂ፣ አነስ
ያለውን ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ መመደቡ ተገቢ ሐሳብ ይመስለኛል። ለእኛ አገር ይኼ አስተሳሰብም አዲስ አይደለም።
ምናልባት ‹‹ሴክተር ሪቪው›› ስለሚባል ጥናት የምታውቅ ይመስለኛል። የዚያን ጊዜ ሊተገበሩ ታስበው ከነበሩት
ሐሳቦች አንዱ 60/40 የሚል ፕሮግራም ነበር። 60 በመቶው ወደ ሳይንስ፣ 40 በመቶው ደግሞ ወደ ማኅበራዊ ሳይንስ
ዘርፍ እንዲመደቡ ነበር ሐሳቡ። የሩቅ ምሥራቅ አገሮች በተለይ ደቡብ ኮሪያ የተጠቀመችበት ፕሮግራም ነው። የአሁኑ
ሐሳብም የተገኘው ከዚያ ይመስለኛል።
በመሠረቱ ሐሳቡ ምንድን ነው? አገሪቱ ተዳጊ አገር ናት። ለዕድገቱ ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂው መስፋፋት ስላለበት
ለዚያ የሚሆን የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል ከሚል መነሻ ነው። ሐሳቡ ጥሩ ነው ካልን በኋላ ግን 70/30፣ 60/40
ስላልን ብቻ የተሳካ ፕሮግራም ይሆንልናል ብለን ማሰብ ያለብን አይመስለኝም። አንድ መታወቅ ያለበት፣ በሚገባ
እናካሂደው ካልን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ከማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት የበለጠ ወጪ የሚያስወጣ ነው፤ ቤተ-
ሙከራው አለ፣ ቁሳቁሱ አለ። ማኅበራዊ ሳይንሱ ግን ሰላሳም አርባም ሲያስፈልግ ሐምሳም ተማሪ አንድ ክፍል
አስገብቶ ማስተማር ይቻላል፤ ብዙ ወጪ አይጠይቅም። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ግን ብዙ ወጪ የሚጠይቅ
ነው። አንዱ ያ ነው። ሁለተኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ብቻ የሚጀመር ትምህርት
አይደለም። ዝግጅቱ ከአንደኛ ደረጃና ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ መሆን አለበት። በአንደኛ ደረጃ እንኳን የሳይነስና የሒሳብ
ትምህርት ለሁሉም እኩል ይሰጥ ቢባል ብዙም የሚያስቸግር አይሆንም።
ሁለተኛ ደረጃ በምንገባበት ጊዜ ግን የሳይንስ ትምህርቱ የሚጠይቀው ብዙ ነገር አለ። ቤተ-ሙከራ አለ። ቤተ-
ሙከራው የሚጠቀማቸው ኬሚካሎች ወዘተ. አሉ። ያሉን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይሄን ሁሉ ያሟሉ ናቸው
ወይ? በአንድ ት/ቤት ውስጥ አንድ ቤተ-ሙከራ ሊኖር ይችላል። 1500 ወይም 2000 ተማሪዎች ባሉበት ት/ቤት አንድ
ቤተ-ሙከራ ቢኖር ካለ አይቆጠርም። ከተማሪው ቁጥር ጋር የሚሄድ፣ የተመጣጠነ መሆን ይኖርበታል። መጻሕፉቱስ?
አንደኛ በሚገባው ደረጃ የተጻፉ ናቸው ወይ? በሚፈለገው መጠንስ ለተማሪው ይዳረሳል ወይ? ሦስተኛውና ዋናው
ነገር በዚያ ደረጃ ያሉ መምህራን የሳይንስ ትምህርቶችን በሚገባ ሊያስምሩ የሚችሉ ናቸው ወይ? የሚሉት ነጥቦች
መታየት አለባቸው፡፡ ከቁርጠኝነቱ በተጨማሪ ማለት ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ በተለይ በዩኒቨርስቲ ደረጃ የመጀመሪያ ዓመት የዝግጅት ‘ፍሬሽማን’ የሚባል ፕሮግራም ነበር።
ተማሪዎቹ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይታቸው የነበረባቸውን ድክመት የማረሚያና የማስተካከያ ዓመት ነበር።
እሱ በተቋረጠበት ሁኔታ ያሉን ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በሚገባ ያዘጋጁልናል ወይ? በሌላ በኩል፣ ቁጥሩ ላይ
ስንመጣ በአመዛኙ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሄዳቸው የሚጠላ ሐሳብ ባይሆንም ለማኅበራዊ ሳይነሱ 30%
የሚያንስ ቁጥር ነው። ለዕድገታችን የሚያስፈልገው በአብዛኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ነው ቢባልም
ማኅበራዊ ሳይንሱ የማያስፈልግ ዘርፍ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም በሳይንስም፣ በቴክኖሎጂም፣ በሕክምና
ሙያውም ተክኖ የሚወጣ ምሩቅ የማኅበራዊ ሳይንስ ዕውቀቱ አነስተኛ ከሆነ መሐንዲሱም ሐኪሙም ሳይንቲስቱም
የማኅበረሰብ ክህሎቱ ካነሰ ሙያውን ለማራመድ መቸገሩ አይቀርም። ለእነሱም ቢሆን በጣም አስፈላጊ ነው ለማለት
ነው።
ከዚያ በተረፈ እንግዲህ ይኼ ፕሮግራም በመምጣቱ ምን ተፈጠረ? ያልን እንደሆነ አብዛኛው ተማሪ ወደ ሳይንስና
ቴክኖሎጂ ዘረፍ ሲመደብ አንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች ያለ ተማሪ የቀሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ውሰጥ እንደ ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ጂኦግራፊ ያሉ የትምህርት መስኮች ተማሪ እንዳልተመደበላቸው ግልጽ
ነው። ለእኔ ፍልስፍና የሌለበት ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርስቲ አይደለም። የሳይንሶች ሁሉ እናት ነው ፍልስፍና። እንኳን
ለማኅበራዊ ዘርፉ ለሳይንሶቹም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ አስፈለጊ ነው። በአስተሳሰብ ካላደግን በሚያዘው በሚዳስሰው
ቁስ ብቻ ማደግ ለአንድ ማኅበረሰብ ትልቅ ዕድገት ነው ብዬ አላስብም። ማደግም የሚቻል አይመስለኝም። እና ያን
ያመጣጠነና ትኩረቱ ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሆኖ ማኅበራዊ ሳይንሱን የማይገድል መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ በእኔ
እምነት አሁን ካለበት ሁኔታ ማለትም ለማኅበራዊ ሳይንስ የተሰጠውን መጠን/ድርሻ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል።

ቋንቋ፣ ብሔራዊ ዕሴት እና ትምህርት


………………………
(፪)
ከተባባሪ ፕ/ር አያሌው ሺበሺ ጋር የተደረገ ውይይት
……………………………………..
በመምህራን ሥልጠና ረገድ የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲቀያየሩ ይታያል። ለመሆኑ ቀደም ሲል ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው
የመምህራን ልማት ፕሮግራም ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው? ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው ፕሮግራም ቢኖርበት
ነው አዲስ ፕሮግራም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው?
……………………………………….
ተባባሪ ፕ/ር አያሌው፡- የእኛ አገር ትምህርት አንዱ ትልቅ ችግር፣ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ላይ፣ ኢትዮጵያውያን
መምህራንን በተገቢው መጠንና በተገቢው ጥራት አሰልጥኖ ማውጣት አለመቻሉ ነው። በ1940ዎቹና 50ዎቹ የነበሩን
መምህራን የውጭ አገር ሰዎች ነበሩ። በተለይ በ50ዎቹ መጨረሻ እና 60ዎቹ መጀመሪያ ላይ ብዙዎቹ የሁለተኛ ደረጃ
መምህራን ወይ ሕንዶች ናቸው አለበለዚያም ከአሜሪካ የሚመጡ የሰላም ጓድ የሚባሉ ጎርምሶች ነበሩ። አንድም
ቅድም ከራሱ ባሕል ይልቅ ወደ ውጭ አገር የሚያዘነብል ወጣት ማፍራታችን ችግር ነበር ላልነው ነገር ምክንያቶች
እነሱ ናቸው።
የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን ኢትዮጵያውያን ለማድረግ አንድ ትልቅ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትምህርት
ፋኩልቲ ተጀመሮ ነበር። የልዑል በዕደ ማርያም (ላብራቶሪ) ትምህርት ቤት የሚባለውን ማለቴ ነው። 11ኛ ክፍል ላይ
ጎበዝ ተማሪዎችን መልምሎ ለአንድ ዓመት እዚያ ያስተምርና በሳይንስም በማኅበራዊ ሳይንስም ዘርፍ አራት ዓመት
አስተምሮ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ለማድረግ ነበር። ዓላማው በጣም ቆንጆ ነበር። ይሁን እንጂ በተለያየ ምክንያት
ብዙ አልተሳካለትም፤ እንዲዘጋ ተደረገ።
ከዚያ በኋላ በስምንት የትምህርት ዓይነቶች ማለትም እዚህ ስድስት ኪሎ ውስጥ በሚሰጡት አራት ትምህርቶት
ማለትም አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ እና አራት ኪሎ ካሉ አራት ትምህርቶች ማለትም ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣
ሥነ-ሕይወትና ኬሚስትሪ የሚማሩ ሰዎች የተወሰኑ የፔዳጎጅ ትምህርቶችን ወስደው ሲጨርሱ መምህር የሚሆኑት
በዕጣ እንዲወሰን ተደረገ። ማለትም አራት ዓመት ተምሮ አስተማሪ ይሁን ሌላ ሥራ ይግባ አያውቅም። በሰኔ ተመርቆ
በሐምሌ ዕኩሌታ ላይ በሚሰጠው ድልድል ነበር የሚያውቀው። ይሄ ለረዥም ጊዜ ቆየ። አንደኛ የፔዳጎጂ ይዘቱ በጣም
አነስተኛ ነበር። ሁለተኛ መምህር መሆን አለመሆኑ በእጣ ነበር የሚወሰነው። በአስተሳሰብ ሳይዘጋጅ ዝም ብሎ ቆይቶ
ነበር የሚለየው።
እና ወደ 90ዎቹ መጀመሪያ ላይ ‹‹መምህራኑ በትምህርታቸው በጣም ጠንካሮች ናቸው። በሙያው ማለትም
በፔዳጎጂው ግን በጣም ደካሞች›› ናቸው የሚል ሐሳብ መጣ። ስለዚህ ጠንከር ያለ የፔዳጎጂ ዕውቀት እንዲኖራቸው
ተብሎ ነው የመምህራን ልማት ፕሮግራም (Teachers Development Program) የመጣው። በሥራ ላይ
ከሚሰጠው ሌላ የትምህርት ይዘቱንና የፔዳጎጂውን ይዘት ለማመጣጠን ተብሎ ነው ፕሮግራሙ የመጣው።
መሠረታዊ ሐሳቡ ጥሩ ነው። አንድ መምህር የሚያስተምረውን ትምህርት ማወቅ አለበት። ሁለተኛ የሚያውቀውን
የትምህርት ይዘት እንዴት እንደሚያስተምርም ማወቅ አለበት። ስለዚህ ቀደም ሲል የነበረው ነገር ተቀየረና አብዛኛውን
ወደ ፔዳጎጂ ያደላ ሆነ። የትምህርት ይዘቱ ግን ወደ 35 የግንኙነት ጊዜ (‘ክሬዲት አወር’) ወረደ። በዚህ ጉዳይ ላይ የረባ
ሥር የሰደደ ጥናት የተጠና አይመስለኝም። በአብዛኛው የመጣው ቅሬታ ግን እነዚህ የአሁኖቹ መምህራን የማስተማር
ችሎታ ዘዴ እንጂ የሚያስተምሩትን ትምህርት አያውቅቁትም የሚል ነበር። እንደገና አሁንም እንደተለመደው
በሥራው ላይ ያሉ ሰዎች ሳይነጋገሩበት ሳይወያዩበት “አድ-ኦን” (Add-On) የሚባለው ፕሮግራም መጣ። ይኼ
ፕሮግራም ደግሞ ሰዎች የአካዳሚክ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁና ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ
የፔዳጎጂውን ትምህርት ተምረው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚል ነበር።
እንግዲህ ሁለቱም ዓይነት አሠራር አለ። አንድ መምህር የሚሆን ሰው የፔዳጎጂውንም የአካዳሚውንም ትምህርት
አደባልቆ ተምሮ ሲመረቅ ቀጥታ አስተማሪ የሚሆንበት ሥርዓት አለ። የአካዳሚክ ትምህርቱን ጨርሶ ዲግሪውን ካገኘ
በኋላ የሙያውን ትምህርት የሚወስዱበት ሥርዓትም አለ። በተለይ እንግሊዝ አገር “የማስተማር ፓስት ግራጅዌት
ሰርተፊኬት” (Post Graduate Certficate in Teaching) የሚባል ፕሮግራም አለ። መጀመሪያ በአካዳሚክ
ትምህርቱ ይመረቃል። ከዚያ በኋላ የሙያውን ትምህርት ይወስዳል። እና ይሄ “አድ-ኦን” የሚሉት ፕሮግራም እንግዲህ
ከዚህ የተወሰደ ሐሳብ ይመስለኛል። በፊት የተባለው፣ መጀመሪያ ይመረቃሉ ከዚያ በኋላ ለአንድ ዓመት የሙያውን
ትምህርት ይማራሉ የሚል ነበር። ላለፉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት በሁለት ችግር ይመስለኛል ያን ትተው
በክረምት ጊዜ ብቻ እንዲማሩና ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የተደረገው። ችግራቸው አንድም መምህራን እዚህ የሚከርሙ
ከሆነ የመምህራን እጥረት ያጋጥማል ከሚል ይመስለኛል። በሌላ በኩል ደግሞ መምህራኑ ለአንድ ዓመት ዩኒቨርስቲ
ውስጥ የሚቆዩ ከሆነ የሌላውን ተማሪ ቦታ ሊሾሙ ይችላሉ ከሚል ነው። በዚህ ምክንያት ከተቀጠሩ በኋላ ይማሩ
ተብሎ ተሰማርተዋል። የተደረገ ጥናት አላውቅም።
ግን በዚህም ፕሮግራም ቢሆን አመርቂ ውጤት እየተገኘ እንዳልሆነ ነው የምሰማው። አንደኛ፣ አንድ ክረምት ብቻ
የተወሰኑ ትምህርቶች አስተምሮ “ሂድ አስተምር” ማለት “ለሥራው መሠልጠን አያስፈልግም” እንደማለት
ይመስለኛል። ሁለተኛ፣ ሥልጠናውን በትጋት የሚከታተሉት አይመስለኝም። ተመረቅህ፤ አስተማሪ ሆነህ፤ ደሞዝ
ይከፈልሃል ግን የቀረህ ትምህርት አለና ውሰድ መባል በዚህ ሁኔታ ተቀጥሬ ደሞዝ እያገኘሁ ነው፤ ይሄን ብማርና
ሰርተፊኬቱ ቢጨመርልኝ የማገኘው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ለምን ራሴን አደክማለሁ? የሚል ስሜት ይፈጥራል።
እኔ እንግዲህ እዚያ ፕሮግራም ላይ አላስተምርም፡፡ የሚያስተምሩ ጓደኞቼ ግን ቅሬታ ሲያቀርቡ ነው የምሰማው።
በዚህ ዓመት ግን በቀጥታ ወደ ሥራ መሰማራታቸው ቀርቶ ከተመረቁት ውስጥ ተመልምለው ለአንድ ዓመት
እንዲሠለጥኑ ሊደረግ ታስቦ ለየዩኒቨርሲቲዎች የስም ዝርዝር የተሰጠ ይመስለኛል። ከዚህ ሁሉ ሒደት የምንማረው
ዋናው ነገር ለትምህርት ሥራ ወሳኞቹ መምህራን መሆናቸውን ነው። ጥሩ ጥሩ መጻሕፍት ቢጻፉ፣ ጥሩ ጥሩ ሕንጻዎች
ቢገነቡ፣ ቅድም ያልኳቸው ከግብዓት አንጻር የሚታዩ ነገሮች በሙሉ ቢሟሉም ዋናው ግብዓት፣ ዋናው ውሳኝ ነገር
አስተማሪው ነው። ስለዚህ ለዚህች አገር፣ ለወደፊት ልጆቻችን - ለእኔ እንኳን ለልጅ ልጆቼ ሊሆን ይችላል - የሚበጁ
የሚጠቅሙ መምህራን እንዴት እናፍራ? እንዴት እናስተምራቸው? ብሎ ጠይቆ ለአገር የሚበጀውን ተወያይቶ
መርጦ በዚያ መቀጠል ነው የሚሻለው እንጂ አሮጌ ፈረንጅ መጥቶ እንዲህ አድርጉ ባለ ቁጥር መቀያየሩ ለዚህች አገር
የትምህርት ሥርዓት የሚበጅ አይመስለኝም።
…………………………………………………
ብዙ መምህራን የመምህርነት ሥራቸውን እየተው ወደ ሹመትና አስተዳደር ሥራ ሲሰማሩ ይስተዋላል። እንዲያውም
ብዙዎቹ የወረዳ፣ የዞንና የክልል አመራሮች መምህራን እንደሆኑ ነው የሚነገረው። ይሄ ከጥራት አኳያ ይመጣል
የሚባለውን ለውጥ አይጎዳውም?
……………………………………………………
የመምህርነት ሥራ በአገራችን ክቡር የነበረበት ጊዜ ነበር። ቅድም እንዳነሳሁት በ1940ዎቹና 50ዎቹም አንደኛ ደረጃ
ሙያን መምህራን የውጭ ሰዎችን እየተኩ በሄዱበት ጊዜ የመምህርነት ሥራ የተወደደ ነበር፤ የተከበረ ነበር። መቼም
ሳትሰማ አትቀርም “የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ ወሰዳት አስተማሪ” ይባል ነበር። አውራጃ ወይም ወረዳ ከተማ ውስጥ ሱፍ
ለብሶ ከራቫት አስሮ የሚሄድ ሰው ካለ ያለጥርጥር እሱ አስተማሪ ነው። ወረዳ ላይማ ስንሄድ የወረዳው አስተዳደር
150 ብር እያገኘ መምህራኑ 200፣ 250፣ 300 ብር ነበር የሚያገኙት። ቀስ በቀስ ግን የዚያውም ጊዜ ቢሆን ያ ሁኔታ
እየተቀየረ ነው የሄደው። አንደኛ፣ መምህርነት ገጠር የሚሰድ ሥራ ነው። ስለዚህ ብዙም የሚመረጥ አልሆነም።
ሁለተኛ፣ እንደ ባንክ፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌና አየር መንገድ የመሳሰሉት ድርጅቶ በመምህርነት የተሰማሩትን ሰዎች
መቅጠር ደስ ይላቸው ነበር። ስለዚህ የመምህርነቱን ሥራ ትቶ በገፍ የመሄድ ነገር በዚያን ጊዜም ነበር።
በደርግ ጊዜም ይሄው ሁኔታ በሰፊው ነበር። በወቅቱ ብዙ መምህራን በተለያዩ ጎራዎች ተሰልፈው ሕይወታቸውንም
ያጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ከአገር የወጡ አሉ፤ የታሰሩም አሉ። በተለያየ ምክንያት ከሥራ መልቀቅም ነበር። መንግሥት
የግል ፋብሪካዎችን ወርሶ በአዲስ መልክ ሲያቋቁም የአመራሩን ሥራ አንዲመሩ የተመደቡት ብዙዎቹ መምህራን
ነበሩ። በየወረደው በየአውራጃው የፓርቲ ሹሞች ይሆኑ የነበሩት መምህራን ናቸው። አሁንም ያ ታሪክ በሰፊው
እየተደገመ ነው። አስተዳደር ሲባል የወረዳ ትምህርት አስተዳደር፣ የዞን ትምህርት አስተዳደር ወዘተ. መስሎኝ ነበር። ያ
በእርግጥም መሆን ያለበት መምህር የነበረ ሰው ነው። ችግር የሚሆነው ከውጭ (ከሌላ መስክ) አምጥቶ የትምህርት
አስተዳደሩን እንዲመራ ማስቀመጡ ነው። ሊሆንም አይገባም።
እንግዲህ አንድ መምህር ክፍል ውስጥ ጀምሮ ክፍል ውስጥ ቢሞት ጥሩ ነው። እኔም ያንን የማደርግ ይመስለኛል።
በተረፈ ግን የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል ወዘተ. የትምህርት ኃላፊ ቢሆንም ጠቃሚ እንጂ ጉዳት የለውም። ወደ ሌላ የሥራ
ዘርፎች የሚሄዱት መምህራን ካለባቸው ችግር፣ በመምህርነታቸው የሚያገኙት ጥቅም አነስ ያለ በመሆኑና ካለባቸው
ሰፊ ቅሬታ አንጻር ነው። የኑሮ ማምለጫ መንገዱ ከዚያ ወጣ ብሎ ወደ ሌላ ሥራ ወይም ሹመትና አስተዳደር
መሰማራት ስለሆነ ነው። ይሄ እንግዲህ በራስ ሙያ ከመከፋት፣ የሚፈልጉትን ካለማግኘት የሚመጣ ነው። እንጂ
እንደተባለው ወደ ወረዳዎች፣ ወደ ዞኖችና ክልሎች ብንሄድ በየቦታው በተሿሚነትና በአስተዳደር ሥራ የተቀመጡት
ብዙዎቹ መምህራን ናቸው። ከመብዛታቸው የተነሳ በአንድ ቢሮ የሚገኘውን ኃላፊ የት ነበር የምትሠራው? ሳይሆን
የት ነው ያስተማርከው? ምን ደረጃ ነው ያስተማርከው? ብሎ መጠየቅና መልስ ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል። እና
ሙያው መሸጋገሪያ እየሆነ ነው። ሥራውን ያወቀው የበሰለው ለቆ ሲሄድ አዲስ ጀማሪ ማምጣቱ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።
ወጣቶቹም ከነባሮቹ የሚማሩበትና ልምድ የሚቀስሙበት ዕድል እያመለጠ ነው። ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ የሥራ
መልቀቅ ሒደት በመምህራኑ በራሳቸው ፍላጎት የሚካሄድ ይመስለኛል። ያ ፍላጎት ደግሞ ምንጩ የተሻለ ገቢ የተሻለ
ኑሮ ለማግኘት ነው። ሰው እንደመሆናቸው መጠን ይሄንን ቢያደርጉ የሚፈረድባቸው አይመስለኝም።
እንዴት እናቁመው? ይሄ ቅድም ወዳልነው ጉዳይ ይመልስናል። ለራሱ መተዳደሪያ የሚበቃ ገቢ አስካገኘ ድረስ፣
ለሙያው የሚሰጠው ክብር ከፍ እስካለ ድረስ፣ ብዙ ሰው ሥራውን ጥሎ የሚሄድ አይመስለኝም።

You might also like