You are on page 1of 12

አሌክስ አብርሃም

ከጥቁሩ መስተዋት ኋላ
(አሌክስ አብርሃም)

ከሰሞኑ የሆነች ስራ ልሰራ ከአንድ ኤምባሲ ጋር ተስማማሁና በአምባሳደር ሂሳብ ፍልስስ አልኩላችሁ ! እውነቱን ልንገራችሁ የሆነ
ድልቅቅ ያለ ምቾት አይመቸኝም ! ኧረ አይመችም !! ሲጀመር የሹፌሩ ሽር ጉድ ማለት አልደላኝም ….

እንግዲህ አሰሪወቸ መኪና እቤቴ ድረስ ይልኩልኛል አሳቻ ቦታ ላይ ያለ መኪና ማቆሚያ አካባቢ እንዲጠብቀኝ ለሹፌሩ ነግሬዋለሁ
…. እኔ ያ መከረኛ አከራየ ደግሞ ይሄን መኪና አይቶ ኪራይ እንዳይጨምር ፈርቸ ነው ሹፌሩ ግን ትህትና መስሎት የመኪናዋ
አፍንጫ የቤቴን ደረጃ እስኪነካ አስጠግቶ ያቆምልኛል ! ኧረ እንደውም መኪናዋ ደረጃ መውጣት ብትችል እቤቴ ሳያስገባት አይቀርም
!

ሹፌሩ ፂሙን ሙልጭ አድርጎ ከመላጨቱ ብዛት የቆዳውንም ቀለም የተላጨ ነው የሚመስለው …. በአክብሮት ቦርሳየን ተቀብሎ በር
ሲከፍትልኝ ከገባሁ በኋላ በስርአት በሩን ሲዘጋና ‹‹ወዴት እንሂድ›› ሲለኝ ግራ ይገባኛል ሂድና አንገቱን ይዘህ አምጣው ተብሎ
ተልኮ ወዴት እንሂድ ይለኛል ! በዚህ ጊዜ ጠጋ በል እዛ ሶስተኛ ወንበር ላይ የሚለው እረዳት ትዝ ይለኛል !

ታምኑኛላችሁ ገና በሁለተኛው ቀን ድምፄ ትእቢት ትእቢት ሸተተ ‹‹እ…..ወደኤምባሲ›› እለዋለሁ ! መኪናዋ መስተዋቷ ጥቁር
ስለሆነ ወደውጭ ብቻ ነው የምታሳየው….. እና ከውስጥ ወደውጭ ህዝቡን ስመለከተው በጠራራ ፀሃይ ሳይቀር ጥላ ቦታ ላይ የቆመ
ስለመሰለኝ ለታክሲ የተሰለፈው ህዝብ እንደወትሮው አላሳዘነኝም !

በዛ ላይ ወንበሩ እንደአልጋ የሚደላ ባለማቀዝቀዣ የእኔን ቤት የሚያክል ስፋት ያለው መኪና ውስጥ(ትንሽ አጋንኛለሁ እንዳልሰማችሁ
እለፉኝ) ፈልሰስ ብየ እንዴት ነው ለዚህ ህዝብ የማዝነው ….እንደውም ሰው የተሰለፈው ቸግሮት ሳይሆን ጥጋብ ፍንቅል አድርጎት
ስራ ደብሮት ይመስላል እኔ ጠግቢያለኋ ! ይገርማችኋል አዚህ እኔ ያለሁበት ቦታ ሁናችሁ ብታስቡት እች አገር 11 ምናምን በመቶ
ማደጓ እውነት ነው ትላላችሁ !

አንድ አገር ላይ ሁለት አለም ውስጥ ነን ህዝቡና እኔ ! መለያ መስመራችን ጥቁር መስተዋት ነው ! ህዝቡን ከውስጥ ወደውጭ አጥቁሮ
ያሳየኛል መስተዋቱ ….አይ መስተዋቱ!! ሽማግሌወች ርጉዝ ሴቶች ተማሪወች መቆማቸው ቢታያችሁም ምቹ ወንበር ላይ
ተቀምጣችሁ ስትመለከቱ የማንም መቆም ከብዶ አይታያችሁም !

ኤምባሲ ውስጥ ምሳ ተብሎ ጠረንጴዛውን የሞላ ምግብ ሲቀርብ ወንድምና እህቶቸ ጋር አንድ ሰሃን ከበን የምንራኮተው ነገር ትዝ
ይለኝና አይ ኤምባሲዮን እላለሁ !

መቸም ባለስልጣናት ባለሃብቶች ይህን ጥቁር መስተዋት አልፈው የህዝቡን ህመም መታመም የህዝቡን ስቃይ መሰቃየት ከቻሉ ያኔ
ነው መልካም አስተዳደር ከመጋረጃዋ ወጣች የሚባለው !

ሹፌሩ ላፕቶፔን ተቀብሎ ወደውስጥ ሲመራኝ ውስጥ አንዲት አይኗንም አፏንም በስሌት የምታንቀሳቅስ ረዥም ወጋግራ የምታህል
ሴትዮ እጀን ጨብጣኝ ከመጋጠሚያው እስኪላቀቅ እየወዘወዘች ‹ደህና በመምጣቴ በጣም ደስ እንዳላት ›› በፈገግታ ስትነግረኝ ፊቷ
ላይ ግን ከውሻሸት ፈገግታዋ በላይ የሚታየኝ ‹‹ስራህን ጨርሰህ ከዚህ አካባቢ ጥፋ አንተ አመዳም ›› የሚል ስሜት ነበር !

ፈገግታዋ ለሚመጣው ወርም ይከስማል ብየ አላሰብኮም ነበር ….ወዲያው ዞር ብየ ስመለከታት ግን ጆሮዋ ጥግ ደርሰው የነበሩት
ከንፈሮቿ ግጥም ብለው ተዘግተው ለሌሎች እንግዶች ፈገግታ ስታጠራቅም አየኋት !

ኤዲያ በዚህስ ኢትዮጲያዊ ይምጣብኝ ወዳጁን ሲያገኝ እንግዳም ሲመጣበት በሳቅ ፍርስስስስ የሚለው ….አንድ አበሻ ጋር ተገናኝተህ
እኮ ካለፍክ በኋላ ሁሉ ፒያሳ ፈገግ ያለልህ የአገርህ ሰው መርካቶ ድረስ ፈገግታው አይከስምም እዛም እቃ ሲወደድበት ነው ኮስተር
1
አሌክስ አብርሃም

የሚለው !

ደግሞ የገረመኝ ኤምባሲው ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጲያዊያን ፍርሃት ! ድሮ እንትን መስሪያ ቤት እጁን ኪሶቹ ውስጥ ከቶ ሲያፏጭ
የምታውቁት እንትና ወይም እዚህ ፒያሳ እና ካሳንችስ ጦር ድምፅዋ ሲያደነቆራችሁ የኖረች እከሊት ኤምባሲ ውስጥ ተቀጥረው
ስታገኟቸው አንገታቸውን ደፍተው በጥፍራቸው ሲራመዱ ትታዘባላችሁ ! ስርአት ጥሩ ነው ያን ያህል ተሸማቆና ነፍስን አስጨንቆ
የሚመጣ ደሞዝ ግን ባፍንጫየ ይውጣ! እውነትም ኤምባሲ ሌላ አገር ማለት ነው ! መሃል አገራቸው ላይ ስደት በአጥር ታጥሮ !

ወቸ ጉድ ኤምባሲዮን ! ማነህ ወዳጀውሃ አምጣልኝ እስኪ ስትሉት ውሃ የለም ጌታየ አሁን ሄደችብን የማትባሉበት ቦታ ካጋጠማችሁ
እሱ ኤምባሲ ሳይሆን አይቀርም ! አንድ ሚስጥር ላማክራችሁና ልጨርስ ‹‹ እዚቹ ጥገኝነት ልጠይቅ እንዴ ››

ማመልከቻየ እንዲህ ይፃፋል ‹‹ ኢቤ.ተ. ነ.ግ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት ሃላፊ ነበርኩ መንግስት ገና ለገና ስልጣኔን ይቀማኛል ብሎ
እያሳደደኝ ነው እንደውም በአሸባሪነት ሊከሰኝ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ነግሮኛል እባካችሁ ፍራሸን አምጥቸ እዚች አረፍ ልበል ›› አሪፍ
አይደል !! ኢ.ቤ.ተ.ነ.ግ ማለት የኢትዮጲያ ቤት ተከራዮች ነፃ አውጭ ግንባር ማለት እንደሆነ ማንም ያውቃል (ሃሃሃ

2
አሌክስ አብርሃም

እስኪ ዛሬ ሰይጣንን እናብሽቀው


(አሌክስ አብርሃም)

ምን መሰላችሁ ሰይጣን አለ !! እንዳትሸወዱ ሰይጣን በደንብ አለ ! እግዚአብሄር የለም ከማለት የከፋው ሃሳብ ሰይጣን የለም ብሎ
ማሰብ ነው …..ወዳጅህን የለም ብትል ወዳጅህ በመከራህ ባትጠራውም እየቆመ ….በደስታህ አብሮህ እየተደሰተ እሱ ራሱ በስራው
መኖሩን ያስረግጥለሃል ! ሰይጣን ግን የለም ስትለው እንደሌለ ሊያሳምንህ ልክ መሆንህን ሊያረጋግጥልህ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል !
ስታመን እና የለም ብለህ ዘና ስትል ሂወትህን በሚያናጋ ኩርኩም ነፍስህን ያፈልሳትና መኖሩን ያሳይሃል !! ከዛ አንተ ስታለቅስ
ስታዝንና ስትጎሳቆል ሰይጣን ጋንገም እስታይል ይጨፍርበሃል ! (እንዲህ ነው የኛ ስታይል እያለ)

ደግሞ ሰይጣንን በብልጠት አታመልጠውም ! ለምን መሰለህ…. የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ የሰወችን ባህሪ ጥንቅቅ አድርጎ
አውቆታል !!! አንተ ቢበዛ የአምሳና የስልሳ አመት የንባብ የሂወት ተሞክሮ ነው ያለህ ! ገፋ እናድርገው ግዴለም የመቶ አመት ……
ሰይጦ ግን የብዙ ሽ አመት የስራ ልምድ አለው ሲቪውን በመቶሽ መርከብ ጭኖ ውድቀትህን ሊያፋጥን በተከፈተ የክፋት መስሪያ ቤት
ሊቀጠር ይችላል …….

በዚች ምድር ላይ ሰወችን እንዴት መጣል እንደሚቻል የሚያትቱ ሚሊየን መፀሃፎችን መድረስ የሚችል ከሰይጣን ሌላ ማን ሊኖር
ይችላል …… ከፈለገ …‹‹አንድ ትሪሊየን ሰወችን የማሳሳቻ ጥበቦች ›› የሚል መፅሃፍ መፃፍ ይችላል ሰይጣን ! ያውም በተግባር
የተፈተኑ እርኩስ ጥበቦች ፡፡

እና ሰይጣን ጋር በሰው ጥበብ ልትታገል ከሞከርክ ድመት በግልገል አይጥ እንደምትጫወተው እንደዛ ይጫወትብሃል እያነሳ
ያፈርጠሃል ….. መጨረሻ ይበለሃል !! ከፈጣሪህ ተጠጋ የሰይጣንን ልብ የሚያርድ ሃይል ያስታጥቀሃል ! አሁን ሰይጦ ቀጥ ብሎ
አያይህም ያውቃላ ማን አብሮህ እንደቆመ !

በጣም ርቦህ በመስተዋት ውስጥ የተቀመጠ ዳቦ ብታይ እና እጅህን ብትዘረጋ ምን ታገኛለህ ? መስተዋት ! እንደዛ ይሆናል ሰይጣን
…… ሲያምርብህ ስትረጋጋ ሲመችህ በፈጣሪህ ግርዶሽ ውስጥ አሻግሮ እያየህ ሊበላህ እየቋመጠ የሰይጣን ወስፋቱ ይጮሃል ! ሃሃሃ
ፈጣሪ አትሳደብ የኔ ልጅ ይልሃል እንጅ ሰይጣንን ወስፋታም ልትለው ሁሉ ትችል ነበር !

ሰይጣን የፈለገ ጥበበኛ የፈለገ ብልጥ ቢሆን ክፋቱና መጥፎ ስራው ሁሉ በሁለት መንገድ የተወሰነ ነው ! ያዝማ ማስታወሻ
1 ኛ በል …..አልክ ? …..በጣም ጥሩ ! አንደኛ …..ሰይጣን የተፈቀደልህን በጎ ነገር ባልተፈቀደልህ መጥፎ ቦታ ያስቀምጥለሃል ! ይሄ
ማለት ምን መሰለህ አይጥ ቲማቲም ብትበላ ችግር አለው ? ዳቦ ብትበላስ ? በሶ ብትቀማምስ ሽሮ ብትልስ ? አየህ ቲማቲሙም
ዳቦውም በሶውም አይገድላትም አንተ ግን እነዚህን የተፈቀዱላትን ጣፋጭ ምግቦች ገዳይ ወጥመድ ላይ ታስቀምጥላታለህ ….‹‹በቀን
ሶስት ጊዜ መብላት ሰብአዊ (አይጣዊ) መብቴ ነው ›› ምናምን ብላ ቂን ቂን ስትል ወጥመድህ …… አግሬን በሰበረው እጀን
በቆረጠው የለም ከተያዝክ ተያዝክ ነው ተጨማሪ ዱላ ይከተላል ሁሉ ተይዘሃላ !

ሰይጣንም አንተንና አንችን እንደዛ ነው የሚያደርጋችሁ (እኔም አለሁበት ታዲያ ) አንተ አይጥ ተራበች ብለህ አዝነህ ምግብ
እንደማትሰጣት ሁሉ ሰይጣንም ምርጥ ምርጥ ነገር ሲሰጥህ ላንተ አዝኖ አይደለም …. የሰይጣን አይጥ ሲያደርግህ ነው !

ሁለተኛው መሸወጃው ምን መሰለህ …..ያልተፈቀደልህን ነገር የተደቀደልህ ቦታ ያስቀምጥልሃል ! አሁን ፌስ ቡክ መጠቀም ፈጣሪን
አያስከፋውም አይደል ….. የተፈቀደልህ ቦታ ነው ማለት ነው …በተፈቀደልህ ቦታ የወሲብ ፊልሞችን ….ዘረኝነትን ስድብን
ጎጠኝነትን ያስቀምጥልህና ወደመሃበረ ርኩሳን ጉባኤ በክብር ይጠራሃል ዘው ብለህ ስትገባ ወላ ስምህን ቀይረህ ወላ ፎቶህን ደብቀህ
በሩቁ አያዩኝም ምን ያመጣሉ ብለህ ሌሎችን ስትዘልፍ ከአጠገብህ በክፉ በደጉ ያልተለየ ፈጣሪህ ያዝናል ከፈጣሪህ ፎቶህን አትደብቅ
3
አሌክስ አብርሃም

ስምህን !

እንግዲህ አሁን እችን ስላወራን ሰይጣን እንዴት እንደሚበሳጭ ባየህ ….ኤልፓ ላሉ ጓደኞቹ ደውሎ ይሄን ፅሁፍ ሳይፖስተው በፊት
መብራቱን አጥፉት እያለም ሊሆን ይችላል ! ግን እግዚሃር ይወደን የለ …ይሄማ ቶሎ ይፖሰት ብሎ ሰይጣንን ኩም !! ኔትወርኩንም
ፍጥን !!

ሰይጣን ደግሞ ምንም ቢልህ አትስማ እሽ ….የመጨረሻ እንደሰባራ ቅል ያቀለሃል አትስማው ‹‹ ቅል ራስ ›› ቢልህ አትስማው …
የሆንሽ አስቀያሚ ቁጭራ ቢልሽ ዝም በይው …ታዲያ ሲቆልልሽም አትስሚው …አንች እኮ ውብ ነሽ ቢሰገድልሽ ሲያንስሽ ሲልሽ
እንዳትሰሚው ሊያጋጭሽ ነው ! ይብቃው ይሄ አመዳም ! በሌላ ቀን ደግሞ እናበሳጨዋለን እኛ እደሆንን በእግዜሩ መስተዋት
ተከልለናል ምን ያመጣል …..! ሰላም እደሩ ! ሰይጣንን ልክ ልኩን ነገርነው አይደል …..እንዳንሸወድ እ …መናገር ብቻ ሰይጣንን
አያርቀውም እንደውም ይመቸዋል ተናግራችሁ ከመጋረጃ ኋላ ሌላ ከሆናችሁ ቲያትር ነው የሚመስለው ! በቃልም በስራም ልክ
ማግባት ነው ይሄን የማይረባ

4
አሌክስ አብርሃም

ሰው ሁኖ . . .
(አሌክስ አብርሃም )

ሰው ሁኖ 1

ልጁ እየሰበከኝ ነው . . . የሚሰብከኝ ለነፍሴ እንዳይመስላችሁ ብር ከፍየ የሆነ የቢዝነስ ሶሳይቲ አባል እሆናለሁ አምስት ሽ ብር ከፍየ!
እኔ ደግሞ በተራየ ሰወችን ሰብኬ አምስት ሽ ብር ሳመጣ ብር ይከፈለኛል ‹ ኮስት ኔት › አይነት . . . እና ሰው እየሰበካችሁ የወርቅ
ሰአት ቦርሳ ምናምን እየተሸለማችሁ ብርም እያተረፋችሁ ምናምን እያለ የሚቀጥል በትርፍ ጊዜ የሚሰራ የቢዘነስ ስራ ነው ! ውስብስብ
ስለሆነ ነው በደንብ ያልገለፅኩት . . .
ወደዋና ወሬ ስመጣ … ልጁ ሲሰብከኝ እንዲህ አለ

‹‹አብርሽ ግዴለህም ድፈር …በመጀመሪያው አመት መኪና በቀጣዩ ሌለ መኪና ትገዛለህ ! እንደውም አንተ ፌስቡክ ላይ ብዙ ሰው
መጋበዝ ትችላለህ . . .ምን አላት አምስት ሽብር . . . መቸም ሰው ሁኖ አምስት ሽ ብር የሌለው የለም !

ሰው ሁኖ 2

አንዲት ታዋቂ የአገራችን ድምፃዊት አሜሪካ ቆይታ መመለሷ ነበር .ቃለ መጠይቅ ይደረግላታል ….እናም ጋዜጠኛው ‹‹ ለመጀመሪያ
ጊዜ አሜሪካ እንዴት ሄድሽ ›› ድምፃዊቷ መለሰች
‹‹ያው እንግዲህ ሰው ሁኖ አሜሪካ የማይሄድ የለም . . . ››

ሰው ሁኖ 3

ዩኒቨርስቲ እያለን ነው የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) በአካባቢው ለሚሰራቸው የልማት ስራወች ብር የማሰባሰቢያ ፕሮግራም
አዘጋጀና ተማሪወችን ሰብስቦ አወያየ እናም ሰብሳቢው እንዲህ አሉ
‹‹መቸም ሰው ሁኖ የትውልድ ቦታውን ለማልማት የማይተባበር የለም . . .ትምህርት ቤት ውሃ መብራት ሲገባ የማይተባበር የለም
… ›› ካሉ በኋላ ከኪሳቸው ብዙ ትኬት በብር መያዣ ላስቲክ የታሰረ አወጡና ለተሰብሰቢወቹ እያሳዩ ‹‹ይሄ ሎተሪ ነው
እያንዳንዳችሁ 25 ብር እየገዛችሁ ልማቱን በመደገፍ እድላችሁን ትሞክራላችሁ ሃያ አምስት ብር ምናላት …›› ተማሪው በተቃውሞ
ተንጫጫ
‹‹እንዴ ባለፈው አስር ብር አዋጣን አይደል እንዴ ተማሪ እኮ ነን ከየት እመጣለን ››

ሰብሳቢው ቆጣ ብለው መለሱ ‹‹ታጋይ ወንድሞቻቻን እንኳን 25 ብር ለህዝብ ሂወታቸውን ሰውተው ለዚህ ሰላም አብቅተውናል እና
25 ብር ምኑ ቁም ነገር ሁኖ ነው …›› አንዱ እጁን አወጣ
እሽ እዛ ጋ . . .

‹‹ እንግዲህ ታጋይ ወንድሞቻችን ለህዝባቸው ሂወታቸውን ሰጥተዋል እውነት ነው . . .እኛም ለህዝባችን 25 አንሰጥም ብለናል ይሄም
እውነት ነው . . .መቸስ ሰው ሁኖ ሂወት የሌለው የለምና ታጋዮች ሂወት ሰጡ ግን ሰው ሁሉ ሃያ አምስት ብር የሌውምና ሰው ሁሉ
ያለውን ነገር ሰው ሁሉ ከሌለው ነገር ባያወዳድሩት መልካም ነው ››

አዳራሹ በሳቅና ጭብጨባ ተሞላ . . .ሰው ሁኖ ትዝታ የሌለው የለምና እኔም ትዝ ብሎኝ አወራኋችሁ !

5
አሌክስ አብርሃም

ከ ‹‹ፈሮግራምህ›› ውልፍት የለም ! ( የህዝብ ወግ)


(አሌክስ አብርሃም )

(ይህ ፅሁፍ ባለፍ ገደም ‹ብልግና› ቢጤ ስላለበት የማይስማማው ሰው እንዳያነበው እመክራለሁ )

አንሾ ባልታወቀ ምክንያት የምትወደው ባሏ አባተ ጋር ትጣላለች እናም ኮብልላ ወላጆቿ ቤት ታድራለች ! በበነጋታው የአገር
ሽማግሌወች ባልና ሚስትን ሊያስታርቁ ሽምግልና ይቀመጣሉ !
‹‹ ችግርሽ ምንድነው ?››
‹‹ምንም››
‹‹እንዴት ያለምንም ችግር ትዳርሽን ታፈርሻለሽ ?››
‹‹ በቃ አልፈልግም ››
‹‹እኮ ለምን ?›› አሉ ሽማግሌወች በማግባባት ሴትዮዋ ስትፈራ ስትቸር አንዲት ነገር ተናገረች ‹‹ አሱ ሰው አይደለም ዝንጆሮ ነው ››
ሽማግሌወቹ ገባቸው ! ባሏ እንደዝንጆሮ ወሲብ ያበዛል አልቻለችውም ማለት ነበር ትረጉሙ…. እናም ሽማግሌወቹ ጉዳዩን በዝርዝር
እንድታስረዳቸው ጠየቁ… እ,ሷም አንዴ ከአፏ ወጥቷልና በዝርዝር ጉዳዩን ታስረዳ ጀመረ !

‹‹ እንደው በኔ የደረሰ አይድረስባችሁ ባለቤቴ ሳያገባኝ በፊት ጎበዝ ገበሬ …. አገር ያወቀው ጀግና ነበር ታውቃላችሁ መቸስ
….ከተጋባን ጀምሮ መሬቱ ሁሉ ጦም አደረ በሬወቹ እንደተጠመዱ ትቷቸው ይመጣና እኔን ይጠምደኛል …. ሌሊት ወገቤ አያርፍ
እግሬ አይገጠም ጧት በግድ ተነስቸ ያዘጋጀሁትን ቁርስ ቀመስ አድርጎ ይተውና ወደመደቡ መጎተት ነው ….ውሃ ቀድቸ ስመለስ
እንስራየን አውርዶ ወዲያ ይወረውርና ‹ያዥ እንግዲህ › ነው … አልቻልኩም በዛብኝ ምነው ሸዋ ! ›› አለችና ሽማግሌወቹ ፊት
አለቀሰች ! ሽማግሌወቹም ችግሯን ስለተረዱ እዛው ተቀምጦ ጉዱን የሚሰማውን ባሏን ጠሩና መከሩት

‹‹አባተ ››
‹‹አቤት አባቶቸ ›› አለ እየተቅለሰለሰ
‹‹እንግዲህ የተባለውን ሰምተሃል እውነት ነው ሃሰት ? ››
‹‹ኧረ ሃቅ ነው አባቶቸ ….›› ሲል አመነ
‹‹ ጥሩ እንግዲህ ጥፋት አይተንብሃል በል አሁን የምንመክርህን ስማ ›› አሉና ሽማግሌወቹ ተመካክረው በአንድ ወግ አዋቂ ሽማግሌ
በኩል እንዲህ አሉት

‹‹ እንግዲህ አባተ <እንትን > እንደሆነ ዝም ብለው ቢውሉበት ቁርስ አይሆን ምሳ ርስት አይሆን ሃብት …. እየናፈቀ ሲገኝ ነው ደጉ
…ይሄው አረጀንበት ከልጅነት እስከእውቀት ኖርንበት እሱ እንደሆን እያደር አዲስ ነው ከምን እንደሰራው አንድየ ይወቀው …..እና
አሁንም አንተም ሚስትህን አንሻን እንዳታማርራት በ ‹ፈሮግራም › እንዲሆን ወስነንበሃል ›› ሲሉ አስረዱተረ

‹‹ እሽ አባቶቸ እንዳላችሁ ….ግ…..ን ‹ፈሮግራሙ› እንዴት እንዴት ነው ›› አለ አባተ

‹‹ እንግዲህ ፈሮግራሙ እንዲህ ነው …. ቀን ቀን እቤት ድርሽ ሳትል እርሻላህ ላይ ትውልና ማታ ጀምበር ሲያዘቀዝቅ ከብቶችህን
አስገብተህ ስታበቃ አንሾም ናፍቃህ ትውል የለም …..አንደዜ ! ….ደሞ ራት ተተበላ በኋላ ኩራዝ ጠፍቶ ጋደም ስትሉ ….አንደዜ !
ወደንጋጋቱ ላይ ዶሮ ሲጮህ ደሞ አንደዜ ! ሶስት ሃቅህ ነው !›› አሉት

አባተ ቅር እያለው እንዲህ አለ ‹‹ እንደ…..ው ኣባቶቸ ምክራችሁ ጥሩ ነበር ግ…..ን እነደው …. ለጠራራውም ለውሃ ጥሙም ቀን
ላይ አንደዜ ብትጨምሩልኝ ›› ሲል ጠየቀ

6
አሌክስ አብርሃም

አንሾ በተራዋ ‹‹ የዶሮ ጩኸቱን ብታነሱልኝ ምናለ …. ሁለቴ ካገኘ ምን አነሰው ›› ስትል ቅሬታዋን አቀረበች ! ሽማግሌወቹ ግራ
ቀኙን አድምጠው ‹‹ አንሾ አንችም አትሰስች ….አንተም ከ ‹ፈሮግራምህ› ውልፍት የለም ! ከተሜው ሁሉ እንዲሁ ነው የሚያረግ
›› አሉና በውሳኔያቸው ፀኑ !

አንሾና አባተም እርቅ አውርደው ወደቤታቸው ሄዱ ! ልክ እቤታቸው ሲደርሱ ጀምበር አዘቅዝቆ ስለነበር አባተ እየተጣደፈ አንሾን
ወደመደቡ ጎተታት …. አንሾም ተጣልተው ስለቆዩ ናፍቋት ስለነበር አልከፋትም ኧረ እንደውም ደስ አላት !
‹‹ አንድ በል ቁጥር እነዳትስት ›› አለች ቀሚሷን እያጠለቀች ! አፍታ ሳይቆይ አባተ አንሾ አማረችው ! አለፍ ስትል ሳብ አደረገና እነሆ
! ሁለት ! ገና እራት ሳይቀርብ አንሾ ጉድ ጉድ ስትል ጠይም ፊቷ በምድጃው እሳት ወጋገን ወርቅ መስሎ ታየው አባተ አላስችል አለው
በቃ ሳብ አደረጋና ሶስተኛውን ሃቁን አነሳ !

እራት ቀርቦ በሉና ጋደም እንዳሉ አባተ የአንሾ አርቲ እና አሽኩቲ ጠረን አቅሉን ነሳው ! ሽማግሌወች የወሰኑለትን ኮታ ደግሞ
ጨርሷል እናም በጨለማው ውስጥ ቀስ ብሎ እንዲህ አለ ‹‹አንሾ ››
‹‹ምን ፈለክ…..የዛሬውን ድርሻ ሶስትህን ጨርስሃል ነገር ትፈልገኝና ውርድ ከራሴ ›› አለች አንሾ በቁጣ
‹‹ እንደው አፈር ትሆንልሽ …..ተነገው አንድ አበድሪኝ አንሾዋ ›› አላት ያልሆነ ቦታ እየደባበሳት .....አንሾ አሰብ አደረገች እሽ
እንዳትል ኩራቷ ያዛት እምቢ እንዳትል የአባተ እጅ ቀልቧን ወስዶታል እናም እንዲህ አለች ‹‹ ምን የነገውን አበዳደረህ የትላንቱስ
ሶስቱ መች ተነካ ›› ትላንት ተጣልተው አብረው አላደሩም !!

ወደቁም ነገራችን ስንመለስ በባልና በሚስት መሃል ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄው ሶስተኛ ወገን ሳይሆን ፍቅር ራሱ ነው !

7
አሌክስ አብርሃም

ነዳጅ ካለ እሳት አለ !
(አሌክስ አብርሃም)

የሰፈራችን ታዋቂ ሰካራም ጋሽ አዳሙ ልክ ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ በተለመደ ጎርናና ድምፁ ምሽቱ ላይ የሰፈረውን የፀጥታ ድባብ
እየደረማመሰው መጣ !

‹‹ እያንዳንድሽ …..ተኝተሸል ! እዚህ አናትሽ ላይ ባለ ሃያ ምናምን ፎቅ ህንፃ አቁመሽ ‹‹የአፍሪካ ህብረት እናት ነኝ መዲና ነኝ ››
ስትይ ከርመሽ አሁን አፍሪካ ልጆቿን ነዳጅ በወለደው ወጠጤ ስትነጠቅ ካለሃሳብ ለሽሽ ብለሻል ! ሌላው ሌላው ቢቀር ፆሎት እንኳ
አታደርሽም ? ተነሽ ! ….እኔ አዳሙ ብቻየን ለድፍን አፍሪካ መንገብገቤ ምነው …አፍሪካ የእኔ ብቻ ናት ? ላፍሪካ መጨነቅ ያለብኝ
እኔ ብቻ ነኝ ….ተነሽ ! እያንዳንድሽ ተነሽ ብያለሁ ተነሽ …›› ሁላችንም በየቤታችን ፊታችን በፈገግታ ተሞልቶ ጋሽ አዳሙ
የሚለውን ለመስማት ጆሯችን ይቆማል ……

ጋሽ አዳሙ መዝፈን ይጀምራል


‹‹አፍሪካ …አፍሪካ አፍሪካ አገራችን
አፍሪካ …አፍሪካ አፍሪካ አፍሪካ አገራችን ….ዘፈን ብቻ ! …..አንዱ ፈረንጅ ‹‹ አፍሪካ ለአለም ያበረከተችው ዘፈን ብቻ ነው ››
አለ አሉ ….ለቅሶውን ረስቶት እኮ ነው ! … እናት አፍሪካ ይሄውእኔ ልጅሽ አገሬው ሁሉ ተጋድሞ ሲያንኮራፋ ለጨለማዋ አህጉር
ጨለማ ላይ ቁሜ እጮሃለሁ …. መንደርተኛውማ በየቤቱ ሃያአምስት ሻማ አምፑሉን በለጭ አድርጎ የታል ጨለማው ይላል …
ይሄው ! ወንድ ከሆነ ከግድግዳው አልፎ አገር ምድሩን የሞላውን ጨለማ አይመለከትም ? ይሄው እንኳን ሰው ውሻው ተኝቶልሻል
››

ዝም ይላል ጋሽ አዳሙ … ‹‹በቃ ወደቤቱ ገባ›› ብለን ጆሯችንን ከሰቀልንበት ወረድ ስናደርግ ‹‹ ተነሽ ›› ብሎ ይጮሃል ! ‹‹
እያንዳንድሽ አሁን በቀደም ስጮህ ስወተውት ‹‹የጠፋው አውሮፕላን የት ሄደ ›› ስል ሁልሽም በየቤትሽ ‹‹ ይገኛል ባክህ አሜሪካ
ታገኛዋለች..የተባበሩት መንግስታት ያገኘዋል ›› እያልሽ ጭጭ ….አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት እንኳን አውሮፕላን የዩክሬን
አንድ አውራጃ ተገንጥሎ ሲጠፋ ፈልገው አላገኙትም !

ሁለት መቶ ሰው እልም ድርግም !ሰው አይደሉም እንዴ የጠፉት ? አታዝኑም ? እግዚኦኦኦኦኦኦኦ አትሉም ? የግድ አውሮፕላኑ ውስጥ
አማራ መኖር ነበረበት? ትግሬ መኖር ነበረበት ? ኦሮሞ መኖር ነበረበት? ደቡብ …ቤንሻንጉል …ጋምቤላ …አፋር …. ….አባትህ
እናትህ እህትህ መኖር ነበረባቸው ……? ይሄው አሁንማ እንኳን አውሮፕላኑ ፈላጊወቹም ድምፃቸው ጠፋ !! ፈላጊውን ለመፈለግ
ፈላጊ እንላክ እንዴ …..ሃሃሃሃሃ ኮሚቴውን ለማፍረስ ኮሚቴ ይቋቋም አሉ ያ ሰውየ ››

ዝም ብሎ ይቆይና ይናገራል ጋሽ አዳሙ ….‹‹ጭጭ ትያለሽ በየቤትሽ …የአፍሪካ መዲና በራስሽ ጭንቀት ተወጥረሽ ዝም ! እስቲ
ስላፍሪካም አንዳንዴ ጩኺ … ስለአለም ጩሂ …..የአውሮፕላኑ ሲገርመን ይሄው በቀደም ነዳጅ የወለደው ቦኮሃራም የተባለ ወጠጤ
ሁለት መቶ ምናምን ሴት ህፃናትን ጠልፎ እየሸለለ እየፎከረ እልም ! አውሮፕላኑ እልም ሁለት መቶ የምድራችንን ዜጎች ይዞ
….ቦኮሃራም እልም ሁለት መቶ ምናምን የነገ አበባወችን ይዞ …..እዚሁ ናይጀሪያ …..እኛ የአፍሪካ መዲኖች የአፍሪካ እናቶች ‹‹
በለው ወሰዳቸው ›› እያልን ጭጭ ! ወይስ ህንፃው ብቻ ነው ንብረታችን …. በየጊዜው የሚደረገው ስብሰባ ነው ሃብታችን …

….. እያንዳንድሽ አፍሪካ መሰብሰቢያዋ ስታደርግሽ እኮ ለመሪወቿ ውስኪ መራጫ እንድትሆኝ አልነበረም ….ሚስኪን ህዝቧ ሲነካ
እንድትጮሂላት ነበር ሲራብ እንድትናገሪ በግፍ ሲገደል ልሳን እንድትሆኝ …አንች በባርነት አልተያሽም ጀግና ነሽ ብላ ነበር አክብራሽ
መናሃሯ ያደረገችሽ ….አንች እዚህ ቤትሽን ዘግተሸ የሱዳን ህዝብ ስደት የናይጀሪያ እንቦቀቅሎች ዜና ሲነበብ ጓዳሽ ውስጥ

8
አሌክስ አብርሃም

እያንጎዳጎድሽ ‹‹ ሰው ለሰው ሲጀምር ጥሩኝ›› ትያለሽ ሰው እየታረደ ሰው እየታፈነ ሰውለሰው ! ቱ ተረታም ሁሉ ››

የጋሽ አዳሙ ድምፅ እየራቀ ይሄዳል ‹‹ነዳጅ የወለደው ቦኮሃራም አንድ ፍሬ ልጆች ከትምህርት ቤት ዘግኖ እንደድንች
እቸረችራቸዋለሁ ሲል አለም ወሬ ብቻ ! አንድ ጢያራ ሙሉ ሰው እልም ድርግም ሲል አለም ወሬ ብቻ ! ኤዲያ … አለም ጨለማ
አፍሪካ ጨለማ …እና ብጠጣ ይፈረድብኛል ….እጠጣለሁ ! ጉበትህ ጨጓራህ ይሉኛል …ልጥፋ እንኳን እኔ ይሄው ስንት ሚስኪን
ጠፍቷል ….

እኔ መንገድ ላይ ድፍት ብየ ብቀር ሬሳየን ቤተሰቦቸ ፈልገው ያገኙታል …. የኔ ፍቅር የኔ ወላንሳ ካሜሪካ ትሻላለች …የኔ ውብ
ሚስት ከአፍሪካ ህብረት ትሻላለች እንኳን ከናካቴው ጠፍቸ ትንሽ ሳመሽም ፈልጋ ወዲያው ነው የምታገኘኝ ….የኔ ባህር ሰርጓጅ
መርከብ በቢራ ውቂያኖስ ስሰጥም ፈልጋ ነው የምታወጣኝ …ወላንሳየ ….የኔ ሰው አልባ አውሮፕላን ያለሁበትን አረቂ ቤት በአይነ
ቁራኛ የምትጠብቅ ሚስቴ …

የኔ ሚስት ፍቅር እንጅ ነዳጅ አልወለዳት ……ሃሃሃሀሃ ነዳጅማ ቤታችን ቢፈልቅ አብሮ እሳት ይፈልቅ ነበር ….
ወላንስየ የኔ ሚስት መጣሁልሽ ….ላንች ስል ይሄው በጧቱ ገና ከምሽቱ አራት ሰአት ከተፍ ! ሃሃሃሃሃሃሃ በእግሬ ነው የመጣሁት
ባውሮፕላን ብመጣ እጠፋለሁ ብየ የኔ ቆንጆ ….አይዞሽ ቦኮሃራምም ቢሆን ጫፌን አይነካም ….ፈላጊ ሚስት ያለውን ሰው ይፈራል
….ሃሃሃሃሃሃ ነዳጅ የወለደው ሲጠልፍ ብሶት የወለደው ሲያስር አለም መስመሩ ተቀላቀለ እኮ ….ሃሃሃሃሃሃ ……
ነዳጅ ካለ እሳት አለ …..ብሶት ካለ ……ሃሃሃሃሃሃሀሃ

9
አሌክስ አብርሃም

እግረመንገዱን…
ሽመሉ ቃንቄ በድሬቲዩብ
(በአሌክስ አብርሃም)

አንዲት ሴት ወይዘሮ ይዘው የመጡትን የሚጠገን ዣንጥላ ‹‹አልሰራም›› በማለቱ ሴትዮዋ ጋር ሲነታረክ ነበር

‹‹ለምን አትሰራም ›› አሉ ሴትዮዋ ተበሳጭተው

‹‹ ሬዲዮ እያደመጥኩ ነው እሜቴ›› ሴትዮዋ በብስጭት ተንጨረጨሩ


‹‹ያው መንገድ ተሰራ ትምርት ቤት ተቋቋመ ነው …በልማታዊ ዜና የእኔ የእታለማሁ ዣንጥላ እንደተሰበረ ይቅር እንዴ››

‹‹ ለልማት እንኳን የእርሰወ ዣንጥላ አገር ምድሩ ፈርሷል …ምናለ ለልማቱ ሲሉ ፀሃይ ለትንሽ ቀን ቢያንቃቃወ ዝናብ
ቢያበሰብስዎ ››
‹‹የሚያንቃቃ ያንቃቃህ እቴ ወፈፌ ››ብለው እየተቆናጠሩ ሄዱ ሽመሉም ወደሬዲዮው ዞረ ….

10
አሌክስ አብርሃም

‹‹ መልካም ነው …እጅግ ጥሩ ሃሳብ ነው …›› ሲል ሁለት እጆቹን ወደመንገዱ ዘርግቶ ጮኸ ሽመሉ ቃንቄ ….የሰማው ዜና
ሳይገርመው አልቀረም ! ግድግዳው ላይ ወደተሰቀለችው ሬዲዮ ጠጋ አለና ድምፅ ጨመረባት . . . .

‹‹ . . . ኔትወርክ ጥራት ደረጃን የሚለኩ ተንቀሳቃሽ ሮቦቶች ሥራ ላይ ሊውሉ ነው ተባለ ….ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ስልክ
አገልግሎት ጥራትን በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የሚፈትሹ በተሽከርካሪ ላይ የሚገጠሙ ተንቀሳቃሽ ሮቦቶችን ሥራ ላይ
ሊያውል እንደሆነ ያስነበበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡ >>

‹‹ወገኖቸ … እንደኔ እንደኔ ቸልተኛና ግዴለሽ ሃላፊወችን የሚተካ ሮቦት ስራቸውን በአግባቡ የማይወጡ ሙያተኞችን
የሚተኩ ሮቦቶች ቢመጡልን ይሻል ነበር . . ሰው ነው ችግራችን ….በተለያየ አካባቢ እየዞረ ችግሩን የሚያስታውቅ ሮቦት
ከማስመጣት በሬዲዮ በስልክ ከተለያየ አካባቢ ችግሩን የሚናገረውን ህዝብ መቸ ሰማችሁት . . . አይ ቴሌ ! ›› ሲል ሽመሉ
ሬዲዮው ላይ አተኮረ ዜናውም ቀጥሏል

‹‹…..በአዲስ አበባ በመከናወን ላይ የሚገኘው የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ሥራ ላይ የሚውሉት
የኔትወርክ ጥራት መፈተሻ ሮቦቶች፣ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የሚያጋጥሟቸውን የኔትወርክ ጥራት ጉድለቶች በትክክል
መገንዘብ የሚችሉ መሆናቸውን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም አድማሱ ጠቅሶ ዘገባው
አመልክቷል፡፡ >>

‹‹አሄሄ …ህዝብ የሚከፍላቸው ሃላፊወችማ ጆሯቸው ላይ ለሽሽ ብለው ተኝተዋል አይሰሙም እንዲህ የህዝብ ብሶት
የሚሰማ ሮቦት አምጡልን እንጅ . . . ባይሆን ሮቦቱንም አባል ሁን እንዳትሉት ….አዎ ነፃ እና ፍትሃዊ የማንኛውም ፖለቲካ
ፓርቲ አባል ያልሆነ ሮቦት ይምጣልን ! አቢዮታዊ ዲሞክራሲ ሮቦት አምጥታችሁ ሮቦቱ ስራውን እየተወ ሮቦት ባልደረቦቹ
ጋር ስብስባ ታጉሮ እንዳያጉላላን አደራ ነጣ ሮቦት ይምጣልን ›› አለ ሽመሉ ቃንቄ

‹‹ሽመሉ ቃንቄ ጀመረው ›› ይላል ጎረቤቱ

‹‹ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የሚያጋጥማቸውን የጥራት መጓደል፣ መቆራረጥ፣ የራስን ድምፅ መልሶ መስማትና የመሳሰሉትን
አሁን በሥራ ላይ ያለው ሲስተም አይገነዘብም የተባለ ሲሆን . . . >> እያለ ዜናው ቀጠለ ‹‹እኛም ያልነው ይሄንን ነው ህዝቡ
ብሶቱን ሰሚ ካለ ብሎ ይጮሃል ! ህዝቡ ግን መልሶ የሚሰማው የራሱን ጩኸት ነው …አዎ መንግስትም እንደቴሌው
ሲስተም የህዝቡን ሲስተም አይገነዘብም ….በነካካ እጃችሁ መንግስትንም የሚተካ የህዝብ ብሶት የሚሰማ ሮቦት አምጡልን !

በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እነዚህን ሮቦቶች በማንቀሳቀስ እርስ በርስ ጥሪ እንዲለዋወጡ በማድረግ
የሚያጋጥማቸውን የኔትወርክ ጥራት ጉድለት መለየትና በፍጥነት ችግሩን የመቅረፍ ሥራ ለማከናወን እንደሚስችሉ
ተገልጿል፡፡ ‹‹ሮቦቶቹ የት ቦታ የድምፅ ማስተጋባት እንደገጠማቸው የት ቦታ ድምፃቸውን መልሰው እንዳዳመጡ፣ የት ቦታ
ያደረጉት ጥሪ እንደተቋረጠ ወይም እንዳልደረሰ መመዝገብ ይችላሉ፤›› ተብሏል፡፡ ››

የምን ነገር መደጋገም ነው …ተናገርን እኮ ከሮቦቶቹ በፊት ህዝቡ ራሱ የት ቦታ ፍዳውን እንደሚበላ የትቦታ የሞላውን ካርድ
ሳይነጋገር እንደሚነጠቅ እራሱ …ህዝቡ ይናገር አልነበረም እንዴ ? ምናለ ባታምታቱን …አሁንም ሮቦቱ ቀድሞ
ይመርመር… ይጠና …

አንደኛ እንዳአንዳንድ የመስሪያ ቤቱ ባልደረቦች የሻይ የሚቀበል ከሆነ ሮቦቱ አይምጣብን …

ሁለተኛ …ሁለተኛው አስተያየት ተብሎ ይመዝገብልኝ . . . ሮቦቱ እግረመንገዱን የህዝቡን የኑሮ ችግርም እየመዘገበ
ለሚመለከተው ቢልክልን መልካም ነው . . .የትቦታ ህዝቡ በቤት ኪራይ ተንገበገበ ? የት ቦታ በምግብ እጦት ተሰቃየ ?
የትቦታ የመልካም አስተዳደር ችግር አንገፈገፈው ? የሚለውን ይመዝግብልን …ይችን ከሰራልን ሮቦቱ ለምርጫ ቢወዳደር
እንኳን 99.9 በመቶ በነቂስ ወጥተን እንመርጠዋለን ! በቃ!!

11
አሌክስ አብርሃም

12

You might also like