You are on page 1of 9

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያዎች መተዳደሪያ መመሪያ

መመሪያ ቁጥር ሳከትሚ 001/2012

ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

የካቲት/2012 ዓ.ም

0
መግቢያ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ 1097/2011 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የከፍተኛ
የትምርት ተቋማት ውስጣዊ ብቃት ለማሻሻል ብሎም የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትምህርት
እየሰሩ ለሚገኙ የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያዎችን በተመለከተ ይህንን መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ
ተገኝቷል፡፡

ክፍል አንድ

አጠቃላይ ድንጋጌዎች
1.1 አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ በመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያዎች
መተዳደሪያ መመሪያ ቁጥር 001/2012 ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል ፡፡

1.2 አውጪው አካል


ይህ መመሪያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር
1152/2011 አንቀፅ 35/2 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሚኒስቴሩ የወጣ ነው፡፡

1.3 ትርጓሜ
በዚህ መመሪያ ውስጥ የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር፡-
I. “ የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያ ’’ ማለት የመማር ማስተማርን የምርምርና ማህበረሰብ
አገልግሎት ስራን በሙያው ለማገዝ የተቀጠረ ሰራተኛ ነው፡፡
II. የተግባር ትምህርት ማለት በቤተሙከራ (በወርክሾፕ) እና በመስክ ትምህርት ለተማሪዎች
የሚሰጥን ትምህርት ያጠቃልላል፡፡
III. ቤተ-ሙከራ ማለት ለተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማህበራዊ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት በአንድ
ክፍል የተደራጁ መሳሪያዎችን በመጠቀም በሳይንሳዊ ምርምር ሙከራዎች የሚደረግበት
ክፍል ነው፡፡
IV. የመስክ ትምህርት ማለት የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የማህበራዊ ሳይንስ እና የቴክኖሎጂ
ትምህርት በተግባር በመታገዝ በመስክ የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡

1
V. ወርክሾፕ ማለት የተለያዩ መሳሪያዎችንና ማሽኖችን በያዘ ክፍል ውስጥ የተግባር
ትምህርት የሚሰጥበት ማለት ነው፡፡

1.4 የጾታ አገላለጽ


በዚህ መመሪያ በወንድ ጾታ የተገለጸው የሴት ጾታንም ይጨምራል ፡፡

1.5 ተፈጻሚነት ወሰን

ይህ መመሪያ በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

1.6 ዓላማ

I. በተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ ያተኮረው የከፍተኛ ትምህርት


ሰፊ የተግባር ትምህርትን የሚያካትት በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ተማሪዎች የተሻለ የተግባር
ትምህርት የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት፡፡

II. የተግባር ትምህርት የሚሰጡ ባለሙያዎች የሚኖራቸውን መብት፣ ተግባር እና ኃላፊነት


ለመወሰን፡፡

III. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚኖረውን የወርክሾፖች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ የኢንዱስትሪ


ትስስሮች፣ የልህቀት ማዕከላት፣ የመስክ የተግባር ትምህርት፣ ምርምሮችና የማህበረሰብ
አገልግሎቶችን ለማሻሻል ውጤታማ ለማድረግና ከስራው ባህሪ አንፃር የባለሙያዎችን
ተጠቃሚነትና መብት ለማረጋገጥ፣

1.7 መርህ
I. በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ የአስራር ስርዓት ለመዘርጋት፣
II. የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፤
III. በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የተግባር ትምህርትንና የምርምር ስራን ጥራት
ማስጠበቅ፡፡

2
ክፍል ሁለት

2. አካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያዎች ተግባርና ኃላፊነት፣መብትና ግዴታዎች

2.1. የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያዎች ተግባርና ኃላፊነት

I. የቅድመ ምረቃ እና የድህረ ምረቃ ፕሮግራም የተግባር ትምህርትን በሙያው መደገፍ፤


II. ተማሪዎች ፕሮጀክት ለመስራት እንደ መነሻ ሃሳብነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ናሙና

ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ያቀርባል፤

III. የተግባር (የቤተ-ሙከራ/የመስክ) ትምህርት በሚሰጥባቸው በቅድመ ምረቃ እና በድህረ ምረቃ

የሚሰጡ ትምህርቶችን ያስተባብራል፤

IV. ለተግባር ትምህርት የሚያገለግሉ የተለያዩ አይነት ማንዋሎችን በጥራት አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ

እንዲውሉ ያደርጋል፣ የተዘጋጁ ማንዋሎችን ይገመግማል፣ ማስተካከያ ይሰጣል፤

V. የቴክኖሎጅ እድገትና መሻሻልን በመከተል የላቦራቶሪ እና የመስክ ትምህርት የላቀ፤ ቀልጣፋና

ውጤታማ ያደርጋል፤

VI. የላቦራቶሪ እና የመስክ ስራ በኃላፊነት ይመራል፣ የተግባር ትምህርት የሚወስዱ

ተማሪዎችንም ያስተባብራል፤

VII. የተለያዩ የላብራቶሪ /የመስክ፣ የወርክ ሾፕ መሳሪያዎችን መግጠም፣ መፍታት፣ ማደራጀት፣

ብቃታቸውን በማረጋገጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፣

VIII. ከሌሎች የሚመለከታቸው መምህራን እና ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር የተለያዩ ላብራቶሪ

(ወርክ ሾፕ ) እንዲደራጁ ያደረጋል፤


IX. የቅድመ እና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በቤተ-ሙከራ /በመስክ የሚወስዱትን የተግባር
/የመስክ ትምህርቶችን ዓለማቀፋዊ ደረጃውን በጠበቀ መልክ እንዲማሩና እንዲመራመሩ
ያመቻቻል፣
X. ከቤተ- ሙከራ/ከመስክ ስራ የሚገኙ ማንኛውንም የልኬት ወይም የምልከታ ውጤቶች ትክክል
መሆናቸውን ያረጋግጣል፤
XI. ቤተ-ሙከራ እና የቤተ ሙከራ መሳሪያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ
ተሟልተው እንዲቀርቡ ሙያዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤

3
XII. አዲስ ቤተ-ሙከራ ለማቋቋም የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ምከረ-ሃሳብ ሰርቶ
ያቀርባል፤ ሲፈቀድም ተከታትሎ ያስፈጽማል፤
XIII. አመታዊ የስራ እቅድ ከመምህራንና ከተመራማሪዎች ጋር በቅንጅት ያወጣል፣ የተግባር

ትምህርት ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል፤


XIV. ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፍ የተግባር ሞዴል ዲዛይን ለፋብሪካዎችና ተዛማጅ ሴክተሮች
እንዲሰራ ፤ሙያዊ ድጋፍም ያደርጋል፣
XV. ጥናትና ምርምር ለሚሰሩ አካላት የላቦራቶሪ እና የመስክ ስራዎችን የማመቻቸት ውጤቶችን

የመተንተን ስራ ይሰራል፤

XVI. ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፍ ቴክኖሎጂ በማላመድ የአሰራር ሲስተሞች በመዘርጋት

ለፋብሪካዎች እና ለመሳሰሉ ተዛማጅ ሴክተሮች ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፣

XVII. ለተግባር (የቤተ-ሙከራ/ወርክሾፕ፣የመስክ) ትምህርትና ምርምር ስራ መማሪያ የሚሆኑ


ማንዋሎችን በየደረጃው ያዘጋጃል በጥናት ያሻሽላል ፤
XVIII. ተማሪዎች ፕሮጀክት ለመስራት እንደ መነሻ ሃሳብነት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የተለያዩ
ንድፈ ሃሳብ ፕሮጀክቶችን የሚሰሩበትን ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
XIX. የተግባር (የቤተ-ሙከራ/ወርክሾፕ፣የመስክ) ትምህርት ወይም ምርምር የስራ ሁኔታውን ከግብ
ለማድረስ አዳዲስ የጥናት ሃሳቦችን ያቀርባል፤
XX. የተማሪዎች የመመረቂያ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ስራዎች ላይ ሙያዊ የድጋፍ ይሰጣል፤
XXI. በተቋሙ ያሉት የምርምር ውጤቶች ከተመራማሪው ጋር በመቀናጀትና ሙያዊ ድጋፍ

በማድረግ ወደ ማህብረሰቡ እንዲወርዱ ያደርጋል፤

XXII. ከቤተ ሙከራ/ወርክ ሾፕ ጋር በተያያዘ በአካባቢ ላይ ከሚደርሱ ተጽዕኖ በጸዳ ሁኔታ

የሚሰራበትን የተለያየ ዘዴዎችን በመቀየስ ተግባራዊ እንዲሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረጋል፤

2.2. የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያ መብቶች

I. የአካዳሚክ ነጻነት ከዩንቨርስቲው ተልዕኮ መሰረት ባደረገ መልኩ ይተገብራል፤

II. የአጭርና የረጂም ጊዜ ትምህርትና ስልጠና የማግኘት መብት ይኖረዋል፤

4
III. በሁለት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና በአካዳሚ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያው መካከል በሚደረግ

ስምምነት መሰረት የመዛወር፤

IV. በዩንቨርስቲው የአካዳሚክ ስራዎችን በሚመለከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማቀድ

እና ስራዎችን የመገምገም ፤

V. በዩኒቨርስቲው በሚወሰኑ ውሳኔዎች ውስጥ እንደማንኛውም የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ የመሳተፍ

መብት ይኖረዋል፤

2.3. የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያ ግዴታዎች

I. በተቋሙ ተልዕኮ፣ እሴቶች እና ሥርዓት መሰረት የተግባር ትምህርት፣ ምርመርና ማህበረሰብ


አገልግሎቶችን የመደገፍ ስራ ይሰራል፣
II. ለተግባር ትምህርት የሚያገለግሉ የተለያዩ አይነት ማንዋሎችን በጥራት አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ
እንዲውሉ የማድረግ፤ የተዘጋጁ ማኑዋሎችን የመገምገም ብሎም ማስተካከያ መስጠት አለበት፤
III. ተማሪዎች ፕሮጀክት ለመስራት እንደ መነሻ ሃሳብነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ናሙና ፕሮጀክቶችን
መስራት አለበት፤
IV. ለተግባር ትምህርት የተገዙ ቁሳቁሶችን ተማሪዎች በጥንቃቄ እንዲጠቀሙ የማድረግ፤
የማስተካካልና ትክክለኛ ያልሆኑትን በማሻሻል፤ በማጠናከር በጥንቃቄ የመያዝና እንደ
አስፈላጊነቱም በጥናትና ምርምር ዙሪያ የተገኙ ውጤቶችና መረጃዎችን ስህተትና ችግር
ያለባቸውን ለይቶ ውጤቱንም ለጥናትና ምርምር ማዕከል ሪፖርት ማድረግ አለበት፤
V. ተማሪዎች ያላቸውን የተግባር እውቀት ክፍተት ለመሙላት ሳይንሳዊ እና ተግባራዊ ድጋፍ ማድረግ
አለበት፤
VI. የተማሪዎችን የተግባር ትምህርት ምዘና ውጤት ምስጥራዊነቱን መጠበቅ፤ የተጀምሩ ወይም
ያላለቁ ስራዎች የተለያዩ አይነት ጥናቶችን እና ተገቢ ባልሆኑ ሰዎች እጅ እንዳይወድቁ በኃላፊነት
መጠበቅ፤
VII. ተማሪዎች የተቋሙን ተልዕኮ መሪ እሴቶችና የከፍተኛ ትምህርት ዓላማዎችን እንዲያውቁ
የማገዝና የመርዳት፤ ሙያዊ ምክር አገልግሎት የመስጠት፣ የተማሪዎችን ቅሬታዎችንና
አቤቱታዎችን የማስተናገድና በአጠቃላይ የሚጠበቅበትን ሙያዊ ስነ ምግባር መወጣት አለበት፤

5
VIII. የከፍተኛ ትምህርት ዓላማዎችንና ተቋሙ የሚመራባቸውን እሴቶች የማክበር፤ የመተግበርና
በሙያዊ ስነ ምግባርና አግባብነት መወጣት ይኖርበታል፤
IX. ልዩ ፍላጎት የሚሹ ተማሪዎችን የመደገፍ እና የማብቃት ሃላፊነት አለበት፤

ክፍል ሦስት

3. የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳቶች የትምህርት እድል፣ የስራ ጫናና ወደ መምህርነት የመሸጋገር መብት

3.1. የትምህርት እድል በተመለከተ

I. ለሁሉም የአካዳሚክ ቴክኒካል ረዳት ባለሙያዎች የትምህርት ደረጃቸውን ለማሳደግ የትምህርት


እድል ያገኛሉ፤

II. ዩኒቨርሲቲዎች በየአመቱ ለአካዳሚክ ቴክኒክ ባሙያዎች ለብቻ የሚያገኙትን የትምህርት እድል
ይወስናሉ ፣ እድሉም በውድድር እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

3.2. የስራ ጫናን በተመለከተ

I. በቀን 8 ሰአት በዩኒቨርስቲው ውስጥ ተገኝቶ የመስራት ግዴታ እንደተጠበቀ ሆኖ በላብራቶሪ/ወርክሾፕ

ከተማሪዎች ጋር የሚቆዩበት ጊዜ 1 ሰአት የአንድ ሰአት ዝግጅት ይጠይቃል በሚል ስሌት ሳምንታዊ

የስራ ጫና 30 ሰአት ይሆናል፡፡

II. የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያ በላብራቶሪ/ወርክሾፕ የሚቆዩበት ጊዜ አንድ ሰአት /Contact hour /

እንደ አንድ የትምህርት ጊዜ /One Credit hour/ ይቆጠራል፡፡

3.3. ወደ መምህርነት የመሸጋገር መብት

I. የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያዎች ወደ መምህርነት የማደግ መብት ይኖራቸዋል፡፡ እድሉ


ሲፈቀድም እርስ በርስ ውድድር ይደረጋል፡፡

II. የሚሰሩበት ትምህርት ክፍል የመምህር ፍላጎት መኖሩ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

6
III. ለመምህርነት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች በሙሉ መሟላታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡

IV. ወደ መምህርነት ለመወዳደር ሁለተኛ ዲግሪ ኖሮት ሁለት አመት በያዘው የትምህርት ደረጃ
በየኒቨርሲቲው ማገልገል አለበት፣ በቺፍ ቴክኒካል አሲስታንት ደረጃ እያገለገለ ያለ መሆን አለበት፡፡

V. ውድድር ተደርጎ በትምህርት ክፍሉና በየደረጃው ባለ ኃላፊ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔው


በአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት አቅራቢነት በፕሬዚዳንቱ ሲፀድቅ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

III.4. በተማሪዎች ምዘና ላይ ስላላቸው ኃላፊነት

I. የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያዎች በላብራቶሪ/ወርክሾፕ ውስጥ በሚከናወን የተማሪ ግምገማ ላይ


ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ውጤቱንም ለኮርስ ባለቤቱ መምህር ያስገባሉ፡፡

II. በላብራቶሪ/ወርክሾፕ ውስጥ በሚከናወን የተማሪ ግምገማ 20 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ የመጨረሻውን
ውጤት የሚሰጠው የኮርሱ ባለቤት መምህሩ ይሆናል፡፡

3.5 የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያ የአመት ዕረፍትን በተመለከተ

የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያ የአመት እረፍት መደበኛ የመማር ማስተማር ዝግ
በሚሆንበት ወቅት ማለትም ሀምሌ እና ነሀሴ ይሆናል፡፡

3.6 የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያ የወጪ መጋራትን በተመለከተ

የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ቴክኒክ ረዳት ባለሙያ የመማር ማስተማሩን ስራ በቀጥታ የሚያግዝ በመሆኑ
በመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው የተጋሩትን ወጪ ከክፍያ ነጻ ሆነው በአገልግሎት
እንዲወጡ ይደረጋል፡፡

III.7. የተሻሩ ህጎች

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከአሁን በፊት የተላለፉ ሰርኩላሮች እና መመሪያዎች በሙሉ ተፈጻሚነት
አይኖራቸውም፡፡

III.8. መመሪያውን ስለማሻሻል

7
ይህ መመሪያ በስራ ላይ ውሎ ለመፈጸም ሲያስቸግርና አዲስ አሰራር በሚያስፈልግበት ወቅት በሚኒስቴሩ
ሊሻሻል ይችላል ፡፡

3.9. መመሪያው ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ

ይህ መመሪያ በሚኒስትሩ/ሯ ተፈርሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

--------------------------------------------
ሂሩት ወልደማርያም /ፕሮፌሰር/
የካቲት 2012 ዓ.ም - አዲስ አበባ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር

You might also like