You are on page 1of 3

Lij Tedla Melaku Worede

January 6 at 6:29 PM · 

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና ኢማም አሕመድ አል ግሀዚ (አሕመድ ግራኝ)


ዘለግ ያለ ትንታኔ በመሆኑ በጥንቃቄ ይነበብ። የመጀመሪያው ክፍል ታሪካዊ አውዱን በተመለከተ ያቀረብኩት ሐተታ ሲሆን
የመጨረሻው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት እይታ ላይ ያተኩራል። ልንባብ እንዲቀል ስል ከወትሮዬ ያጻጻፍ ስልት ወጣ ብዬአለሁ።
ታሪክ ላይ አፄ ልብነ ድንግል እና የምስራቁ የአደል መንግሥት መሪ የነበረው ሃደሬ-ሶማሌው አሕመድ አል ግሀዚ (አሕመድ
ግራኝ) ያካሄዱት ጦርነት ከመሰረቱ ፖለቲካዊ እንጅ ሃይማኖታዊ ጦርነት እንዳልነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ያትታሉ። የዚህም
ማስረጃ አሕመድ ግራኝ አፄ ልብነ ድንግል ሴት ልጃቸውን ከዳሩለት ውጊያውን እንደሚተው የላከላቸው መልዕክት ነው - "The
Historical Geography of Ethiopia: from the first century AD to 1704" የተሰኘ ምሑራዊ ምንጭ እንደሚነግረን
አሕመድ አል ግሀዚ አፄ ልብነ ድንግልን "ሴት ልጅህን ከዳርከኝ ሰላም እሰጥሃለሁ፣ አልወጋህም" የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበር
መሆኑ ነው።
ይህን በአግባቡ ለመረዳት ያፄ ልብነ ድንግል ቅም አያት የነበሩት አፄ ይኩኖ አምላክ በዘመናቸው ከነበረው የግብፅ ሡልጣን ጋር
የተጻጻፉትን ደብዳቤ እና የምሥራቁ ሶማሌ መንግሥት (Sultanate) (በኋላ አሕመድ ግራኝ የተነሳበት) ከሰሎሞናዊ ነገሥታት ጋር
የነበረውን የጠላትነት ምክኒያትና መነሻ እና መሰረቱ ምን እንደነበረ (ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስለመሆኑ) የሚከተለውን ማስረጃ
በጥንቃቄ መረዳትን ይጠይቃል።
ከጽሑፉ መጨረሻ ታች በጠቀስኩአቸው ምሑራዊ ምንጮች ላይ (ሞርድካይ አቢር) እንደተገለጸው፣ የመካከለኛው ዘመን
የሰሎሞናዊ ነገሥታት አባት የሆነው አፄ ይኩኖ አምላክ የሐበሻ ሙስሊሞች ጋር በጎ ግንኙነት እንደነበረው እንመለከታለን።
በሞርድካይ አቢር በቀረበው የተጠና ታሪካዊ ሐተታ የሰሎሞናዊ ክርስቲያን ነገሥታት እንቅስቃሴ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ
የነበርና ከሐበሻ ሙስሊሞች ጋር በጎ ግንኙነትን የመሰረተ ነበር። አፄ ይኩኖ አምላክና እርሱን የተኩት ሰሎሞናዊ ነገሥታት የሐበሻ
ሙስሊሞች የንግድ መስመሮችን እንዲቆጣጠሩ በማድረጋቸው በኢትዮጵያ ሰሎሞናዊ መንግሥት ሙስሊሞችና በምሥራቅ
(ሶማሌ) ሡልጣኔት ሙስሊሞች መካከል መቃቃር ተፈጥሮ ነበር ሲል ያስረዳል (Mordechai Abir, "Ethiopia and the Red
Sea: The rise and decline of the Solomonic dynasty and Muslim-European rivalry in the region, Chapter
II)።
የዚህም ምክኒያት የመንግሥታቸው ማዕከል በሸዋ እና በቤተ አምሓራ የነበር ሰሎሞናውያን ነገሥታት የቀይ ባሕር የንግድ
መስመሮች በሐበሻ ሙስሊሞች እንዲያዙ በማድረጋቸው የምሥራቁ ሡልጣኔት ሙስሊሞች ከሰሜኑ ሐበሻ ሙስሊሞች ጋር
መቃቃር ውስጥ የገቡ መሆናቸውን ይገልጻል። ከዚያም አልፎ አፄ ይኩኖ አምላክ ለግብጽ ሡልጣን በላከው ደብዳቤ በርሱ
ሰሎሞናዊ መንግሥት ውስጥ ለሚኖሩ ሙስሊሞች ጠባቂ (ባለ አደራ) መሆኑን እና በርሱ መንግሥት ውስጥ ሐበሻ ሙስሊሞች
ከሐበሻ ክርስቲያኖች ጋር እኩል መብት ያላቸውና በሰሎሞናዊ መንግሥት ባለ አደራነት መብታቸው ተጠብቆ የሚኖሩ መሆኑን
የሚገልጽ መሆኑን ያትታል።
የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ሰሎሞናዊ ነገሥታት ያካሄዱአቸው ጦርነቶች በሐበሻ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠሩ አልነበሩም።
ያካሄዱአቸው ጦርነቶች ለፖለቲካዊ የበላይነት ከተዋጉአቸው የምሥራቅ ግዛት ኃይሎች ጋር እንጅ በራሳቸው ሉዓላዊ ግዛቶች
(dominions) ውስጥ ያለውን ሕዝበ ሙስሊም አልነበረም። እነርሱም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማ የነበራቸው፣ እንዲሁም
በወረራና በጥቃት ምክኒያት የተካሄዱ መሆናቸው በነዚህ ሰነዶች ይገለጻል። ይህን የማይረዱ ግን ሰሎሞናዊ ነገሥታት በራሳቸው
ሕዝብ ላይ ጥቃት ያደረሱና ሙስሊም የሆኑን ኢትዮጵያዊያን ለይተው ያጠቁ አስመስለው በማቅረባቸው ሕዝባችን በገዛ ታሪኩ
ላይ ጥያቄ እንዲያነሳና ጥርጣሬ እንዲያድርበት አድርገዋል። ከስብረዲን ጋር፣ ከሐቀዲን ጋር፣ እንዲሁም ከአሕመድ አል ግሀዚ
(አሕመድ ግራኝ) ጋር የተደርጉ ጦርነቶች ለፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ተፎካካሪ ከሆነ ኃይል ጋር የተደረጉ እንጂ የርስ በርስ የሃይማኖት
ጦርነቶች አለመሆናቸው ይሚገለጽ ሐቅ ነው።
አፄ ልብነ ድንግልን የሙስሊም ጠላት አድርገው ማቅረብ የሚፈልጉ አንዳንድ ታሪክን በትክክል ያላዩ ሰዎች ብዙዎችን አሳስተዋል።
አፄ ልብነ ድንግል ጦርነት የገጠመው ሃይማኖትን ለፖለቲካዊ ዓላማ አውለው ከዐረብና ከቱርክ ኃይላት ጋር በማበር የሐበሻውን
መንግሥት የወረሩን ጠላቶች ነው። ጦርነቱ ሃይማኖታዊ ቅርፅ የያዘው በዐረብ ፋቂሕ ዜና መዋዕል እንደተዘገበው አሕመድ ግራኝ
በሐበሻው መንግሥት ላይ ጅሃዳዊ ጦርነት በማወጁ እና ሠራዊቱ ቤተ ክርስቲያንን ኢላማ አድርጎ በማሳደዱ ነበር፤ ሆኖም ግን
አሕመድ ግራኝ በእሳት አቃጥሎ ያወደመው ቤተ መንግሥቶችን፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የሥልጣኔ ቅርሶችን ጭምር ነው።
በዛሬ ትመና በቢሊዮኖች ዋጋ የነብረውን የወርቅ ሐብት በቱርኮቹና በዐረቦቹ አስዘርፎ አከፋፍሎአቸዋል (በዐረብኛ የተጻፈውን
ፉቱሕ አል ሐበሻ ተመልከት)። ዓላማው የሐበሻውን ሥልጣኔ አመድ ማድረግ እንጅ ሃይማኖታዊ ተጋድሎ አልነበረም።
አሕመድ ግራኝ ሶማሌ እንደነበር ከሚጠቁሙ ተ አማኒ ምንጮች አንዱ (“The Portuguese Expedition to Abyssinia
1541-1542 as narrated by Castanhoso” p. xxxiii) አሕመድ አል ግሀዚ ዐረብ አልነበረም፣ የኢብራሒም አል ግሀዚ ልጅ፣
ከሶማሌዎች ዘምድና ያለው ነው ይላል።
“ፉቱሕ አል ሐበሻ” ለሚለው የግራኝ ዜናመዋዕል በዐረብኛ [በዘመኑ የሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ፖለቲካዊ ማዕከል የነበረውን]
የቤተ አምሓራን መንግሥት ቅኝ መግዛት እንደነበር ማሳያው:
በclassical ዐረብ ሥነ ጽሑፍ "ፉቱሕ" ("the openings") የሚለው ቃል ሃይማኖታዊ ባልሆነ ወይንም secular በሆነ ትርጓሜ
የመጀመሪያዎቹን (ሃይማኖትን ያመካኙ) የዐረብ ቅኝ ግዛቶችን (Arab Conquests) የሚያመላክት ቃል ነው:
- "ፉቱሕ አል ምስር" (የግብጽ ቅኝ ግዛት)፣
- "ፉቱሕ አል ሻም" (የሶርያ ቅኝ ግዛት)፣
- "ፉቱሕ አል ኢራቅ" (የኢራቅ ቅኝ ግዛት)፣
- "ፉቱሕ አል ቡልዳን" (የምድሮች ቅኝ ግዛት)፣
- "ፉቱሕ አል ሐበሻ" (የሐበሻ ቅኝ ግዛት)።
የቃላቱን አውድ ለመገንዘብ ያኽል የ “ፉቱሕ አል ሐበሻ” የእንግሊዝኛ ትርጉም "Conquest of Abyssinia" የሚለው ለዚኽ ነው
። ዋና ዓላማውም ሐበሻን በዐረብ ማቅናት ወይንም ቅኝ መግዛት ማለት ነው።
ካፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን ጀምሮ የነበረው በሐበሻው ሰሎሞናዊ መንግሥት እና በምሥራቁ ኤሚሮች መንግሥት መኻከል የነበር
ግጭት አራት ነገሥታትን ተሻግሮ እስከ አፄ ልብነ ድንግልን ዘመን ድረስ ደረሰ። ባፄ ልብነ ድንግል ዘመን ማሕፉዝ የሚባለው
የምሥራቅ ኤሚር ሠራዊቱን አስከትሎ የልብነ ድንግልን ማዕከለ መንግሥት ወርሮ አጠቃ። አፄ ልብነ ድንግል ጦርነቱን ተዋግቶ
ኤሚር ማሕፉዝን ገድሎ ድል በማድረጉና ሠራዊቱን እስከ መጣበትን መዳረሻው ሐረር ድረስ አሳዶ ስለ ፈጀው ወናግ ሰገድ
የሚለውን የአርበኝነት ሥም ይዞ በጀግንነት ወደ ዙፋኑ መመለሱ ተጽፎአል። አህመድ ግራኝ የኤሚር ማሕፉዝን ሽንፈት ተከትሎ
አለ የተባለን የሶማሌ፣ የዐረብና የቱርክ ሠራዊት ካደራጀ በኋላ ለበቀል ልብነ ድንግልን ለመግደልና መንግሥቱንም ለማጥፋት
እንደተነሳ በዘመኑ በእነ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ተመዝግቦአል (“Layers of Time: A History of Ethiopia” p. 84; ተመልከት)።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አሕመድ አል ግሀዚን አስመልክቶ በሰጠው ቃለ ምልልስ የልብነ ድንግልን እና የአሕመድ ግራኝን ጦርነት
ሃይማኖታዊ ዓላማና ርዕዮተ ዓለም ያለው ብቻ አድርጎ ማቅረቡ አውዱን በተመለከተ የግጭቱ መነሻ ካፄ ይኩኖ ኣምላክ ዘመን
ጀምሮ መሆኑን፣ የግጭቱ መንስዔም የቀይ ባሕርን የንግድ መስመሮች ለመቆጣጠር በተደረገ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሽኩቻ
መሆኑን ፈፅሞ የዘነጋ ነው።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አፄ ልብነ ድንግልን የኢትዮጳይን ሙስሊሞችን ለማጥፋት የተነሳ አስመስሎ አቅርቦታል። ይህ ፈፅሞ
ውሸት ነው። አፄ ልብነ ድንግል የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ለምጥፋት ቢያልም ኖሮ ከጉያው ሥር በ ሐበሻው መንግሥት ውስጥ
የሚኖሩትን ሙስሊሞች ትቶ ምሥራቅ ድረስ ካሉት ሙስሊሞች ጋር ጦርነት አይገጥምም ነበር። አፄ ልብነ ድንግል እና ዘር
ማንዘሮቹ በሙሉ ግን ጦርነታቸው የነበረው ከምሥራቁ የሶማሌ አደል መንግሥት ጋር እንጅ ከሐበሻው ሙስሊም ጋር
አልነበረም። የታሪክ ድርሳናቱም ይኽን ይመሰክራሉ።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አሕመድ ግራኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መድፍ ያስተኮሰውን የቱርክ ሰራዊት ላመጣበት
አድናቆቱን ሲገልጽ የሰጠው ማስተባበያ ልብነ ድንግልም የፖርቱጋል ሠራዊት አምጥቶ ነበር የሚል ነው። ነገር ግን ልብነ ድንግል
የፖርቱጋሉን ሠራዊት በሕይወቱ ሳያየው ነው ያለፈው። የፖርቱጋሉ ሠራዊት እንዲመጣ የተጠራው አሕመድ ግራኝ ቀድሞ
የትሩክና የዐረብ ጦርን ከሙሉ ትጥቅ ጋር ታግዞ የሐበሻውን መንግሥት የወረር በመሆኑ ነው። የፖርቱጋሉ ሠራዊትም ለሐበሻው
መንግሥት ሊደርስለት የቻለው አፄ ልብነ ድንግል ከሞተ በኋላ ልጁ አፄ ገላውድዎስ እርሱን በተካው ጊዜ ነው።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አሕመድ ግራኝ ቱርኮችን ስላባረረ አደንቀዋለሁ፣ አፄ ገላውድዎስ ግን ፖርቱጋሎችን ስላላባረረ አሕመድ
ግራኝ እንደሚያይል ገልጾአል። ነገር ግን፣ የቱርኩ ሠራዊት በመምጣቱ ሲሐብ አልድ ዲን አብድአል ቃድር በፉቱሕ አል ሐበሻ
እንደጻፈው አፄ ናኦድ ያሠራትን የወርቅ ቤት ክርስቲያን መካነ ሥላሴን ሳይቀር ከሩቅ ስትታይ እንደ እሳት የምታበራ፣ ከቅርብ
ደግሞ በቱርክና ዐረብ በዓለም ዙሪያ በሕንድም፣ በሮምም፣ በቢዛንቲንም እንዲህ ያለ ድንቅ ሕንፃ ታይቶ አይታወቅም
የተባለላትን ጭምር የመናፍቅ ቤተ እምነት በማለት በእሳት አቅልጦ እንዳጠፋት፣ መላውን የሰሎሞናዊ ነገሥታት የሐበሻ
መንግሥት በእሳት እንዳጠፋው፣ በጎንደር እንዳሉት ዓይነት በሸዋው የበራራ መንግሥት የነበሩን ቤተ መንግሥቶች ጨምሮ
እንዳጠፋቸው የመናዊው ሲሓብ አል ዲን በዓይኑ ዓይቶ ጽፎአል። አቢያተክርስቲያናት ብቻም ሳይኾኑን የሐበሻን መንግሥት
ሥልጣኔውን እንዳጠፋው በፉቱሕ አል ሐበሻ ዐረብ ፋቂሕ እያንዳንድዋን የአሕመድ ግራኝን ጀብዱ መዝግቦአል። ፖርቱጋሎች
ይህን መንግሥት ለማዳን ባጋዥነት የመጡ እንጅ ልብነ ድንግል ሙስሊሞችን ለማጥቃት ያግዙት ዘንድ የጠራቸው አልነበሩም።
በመጨረሻም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መስዋዕትነት ከፍለው እና ሕይወታቸውን ገብረው እሱ ለዚህ የበቃባትን ቅድስት ቤተ
ክርስቲያን ያተረፉለትን እነ አፄ ገላውድዎስን ዝቅ አድርጎ ቤተ ክርስቲያንዋን ከመስራቁ የሶማሌ መንግሥት ተነስቶ እስከ መኻል
አገር ድረስ ወረራ በማካኼድ እስከ መጥፋት ላደረሳት ለአሕመድ አል ግሀዚ በሰማይ ፊት ምስክርነት ሲሰጥ ሳየው ዐረቦቹ
ዘመዶቻችን እንደሚሉት "አኺሩል ዘመን!" ማለቴን ገልጬ ልዝጋ።
ልጅ ተድላ መልአኩ ወረደ
_____________
በመጀመሪያው ክፍል ላይ ለቀረቡ ማብራሪያዎች ተጠቃሽ ምንጮች
George Wynn Brereton Huntingford, "The Historical Geography of Ethiopia: from the first century AD to
1704"
Mordechai Abir, "Ethiopia and the Red Sea: The rise and decline of the Solomonic dynasty and Muslim-
European rivalry in the region"

You might also like