You are on page 1of 2

(Last post on Personal Shadow)

ግለሰብዓዊነት
----
በካርል ዩንግ ፍካሬ–ልቡና ህልዮት ውስጥ ግለ–ሰብዓዊነት የግለሰብን የሰብዕና ልቀት የሚያሳይ ቃል ነው።
ግለሰባዊነት በሂደት የምንጎናፀፈው ማንነት ሲሆን በልቦናችን የምንፈጥረው የንቅና ኢንቅ የሆነው ከፍል ውህደት
ነው። ይህ ውህደት ሰዎችን ወደ ምልዓት እንደሚመራቸው ዩንግ ያስረዳናል። የግለሰባዊነት ሂደት ራስን ከማወቅና
"ሙሉ ሰው" ከመሆን ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን። ዩንግ በራሱ በፍካሬ ልቡና ሐቲቶቹ ላይ
እንዳሰፈረው ግለሰባዊነት (individuation) ማለት ሊነጣጠል የማይችል ውህደት ያለው (individual) መሆንን
እንደሚያመለክት ያስረዳናል። እናም ግለሰባዊነት (individuation) ወደ ገዛ ራስ መምጣት፣ ራስን ማወቅ የሚል
ትርጓሜ ሊሰጠው እንደሚችል ይገልፅልናል። ታዲያ ሂደቱን ከሚያግዙ ስልቶች ውስጥ ዋነኛው ባለፉት ክፍሎች
ያነሳነናቸው ጥላን በመግለጥ የተደበቀውን ማንነት የማወቅ ልምምዶች ናቸው።
ውጫዊው አለም የተገነባው ከውስጣዊ ውህደታቸው በጎደሉ ሰዎች ነው። ይሄን ማረም የምትችለው ወደ ራስህ
ውስጥ ለመጓዝ የወሰንክና ተጋፍጠኸው በድል የተመለስክ እለት ነው። ታዲያ አሁን የምናወጋውን ያህል ቀላል
ምልልስ አድርገህ እንዳታስበው። እጅግ በጣም ዋጋ የሚያስከፍል ልምምድ ነው። እርግጥ ነው በህይወት ውስጥ
ታላላቅ የሚባሉት ነገሮች በሙሉ ዋጋ ያስከፍላሉ። ዩንግ በራሱ ከላይ ያነሳነውን የፍካሬ ልቡና ዘ—ፍጥረት ለመፃፍ
ከ 16 አመታት በላይ ለፍቷል። 1913 አካባቢ የራሱን ጥላ ሲጋፈጥ በነበረው ልምምድ ሰዎች ወደ እብደቱ እንዳመራ
ሲገምቱ ዩንግ ደግሞ " ድብቅ ማንነትህን ለመጋፈጥ ውስጥ ባለ ልምምድ ሰዎች እብድ ሊሉህ እንደሚችሉ ማመን
ይኖርብሃል" በሚል ተናግሮ ነበር። ነገር ግን እያንዳንዱን ተሞክሮዎቹን በቃላትና በስዕል እያደረገ መዝግቦ " ቀዩ
መፅሃፍ" የሚል ስያሜ ሰጥቶት ነበር። የቤተሰቦቹ ፈቃድ ስላልነበረ ለመታተምም እጅግ ዘግይቷል።
ምናልባትም ከሞተ ከምእተ-አመት በኃላ ነበር የታተመው። ለምን? ምክኒያቱም ዩንግ ራሱን በመጋፈጥ ያገኘውን
ሃቅ በሙሉ አስፍሮ ነበር። ከነዚያ መሃል ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ሊቀበሏቸው የሚከብዱ፣ ቤተሰብን የሚያዋርዱ
ማንነቶችን የገዛ ጥላውን በመግለጥ ውስጥ ተጋፍጦ አንድም ሳያስቀር ፅፎ ስለነበር ነው። የቤተሰቦቹ በዚያ መልኩ
መዘግየትና ዩንግ የገለፀውን ማንነት ለመቀበል መቸገር ምናልባትም ዛሬ ሁላችን በራሳችን የራሳችንን ፀሊም ገፅ የኔ
ነው ብለን ለመቀበል እንደምንቸገረው እጅግ የተለመደ ባህሪይ ነው።
ችግር የሚሆነው አለምን በሽፋን/ማስክህ መቀላቀልህና ድብቁ የማታውቀው ማንነትህም ተከትሎ በውሳኔና
በትልምህ፣ ባህሪና በግብርህ ሁሉ ጣልቃ በመግባት የምንኖርባትን አለም ማበላሸቱን ሲቀጥል ነው። የደረስንበትን
የትርምስና ያለመግባባት ቀውስ ስታስተውል የምታስቀምጣቸው ውጫዊ ምክኒያቶች ቢረቡ ኖሮ ዛሬ አለም
ፀጥታዋ የሚማርክ ተምነፀታዊ ምድር በሆነች ነበር።
በአለማችን ላይ እጅግ ቀላሉ ነገር የሰዎችን ድክመትና ጥንካሬ እያነሱ መተንተን መንስኤና ውጤት በማቆራኘት
ታሪክ መስራት ነው። ሁላችንም ያንን ለማድረግ በማንኛውም ጊዜ ተነሳሽነቱ አለን። የምንጓዘውም ርቀት
ረጅምና አድካሚ ቢሆንም እንኳ እንደታላቅ ግብር እንደሰትበታለን። በዚህ ድርጊት አንዳች አይነት ለውጥ
አለማችን አስተናግዳ አታውቅም። ትልልቅ ለውጦች ከባባድ ልምምዶችን ይጠይቃሉ። ምድራችን
ያስተናገደቻቸው ታላለቅ የሚባሉ ለውጥና ግኝቶች ዳራ ስር ያለ አንድ ከባድ ልምምድ አለ:— ጥላን በመግለጥ
ከገዛ ድብቅ ማንነት መተዋወቅና ከስነልቡናዊ መበታተን ወደ ውህደት በመምጣት ራስን ማውቅ!
---
ተከታታይ ክፍሎቹን በድጋሚ በማንበብ ልምምዱን ላንተ እንተዋለን። አበቃን።
(ተጨማሪ የንባብ ጥቆማ /ዋቢ ከፈለክ )
----
• Jung, C.G.(1912). Psychology of the Unconscious
• Jung, C.G. (1969). The Archetypes and the Collective Unconscious, Collected Works, Volume 9,
Part 1, Princeton, N.J.: Princeton University Press. ISBN 0-691-01833-2. par. 259
• Carl Jung (1963). Memories, Dreams, Reflections. Random House p. 101. ISBN 0-679-72395-1.
• Carl Jung (2009). The Red Book: Liber Novus (manuscript produced circa 1915–1932)

You might also like