You are on page 1of 2

ካልነሳ፣ የሞተው: መከራን የተቀበለው በምትሐት እንጂ በእውነት ካልሆነ፤ እኔ በምን ምክንያት ስለእርሱ እታሰራለሁ፣

ራሴንስ ለተራቡ አናብስት ለመስጠት ስለምን እቸኩላለሁ? እንዲህ ከሆነ ሞቴ ከንቱ ነዋ!ክርስቶስን በመከራው
ለመምሰል መከራን የምቀበል እኔ ሐሰተኛ ነኛ! እንዲህም ከሆነ ‘እነርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ ሰውም ለአንድያ ልጁ
እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል’ያለ ነቢዩ ከንቱ ተናገራ!
(ዘካ.12:10):: እነዚህ ሰዎች ከሰቃልያን አይሁድ የማይተናነሱ የማያምኑ ናቸው፡፡ እኔስ አለኝታየን በማስመሰል፣
በምትሐት በሞተልኝ ላይ አላደርግም፤ በእውነት ነው እንጂ፡፡ ድንግል ማርያምም በእውነት እግዚአብሔር የተዋሐደውን
ሥጋ በማኅፀኗ ተሸከመች፡፡ እግዚአብሔር ቃልም እንደእኛ ሕማም ሞት የሚስማማው ሥጋን ተጋርዶ በእውነት
ከድንግል ተወለደ፡፡ ሰውን ሁሉ በማኅፀን የሚስል እርሱ በእውነት በማኅፀን ኖረ፤ ከድንግልም ያለ ሩካቤ ለራሱ ሥጋን
አዘጋጀ፡፡ እንደእኛ ዘጠኝ ወር በማኅፀን አደረ፣ እንደእኛ በእውነት ተወለደ፣ እንደእኛ በእውነት ጡትን ጠባ፣ በላ ጠጣ፡፡ 30
ዘመናት ከሰው ጋር ከተመለለሰ በኋላ በዮሐንስ እጅ በምትሐት ሳይሆን በእውነት ተጠመቀ፣ ሦስት ዓመት ወንጌልን
አስተማረ፣ ታምራት አደረገ፣ ፈራጅ ሲሆን በአይሁድ በሐሰት ተፈረደበት፣ በገዥው በጲላጦስ ተገረፈ፣ በጥፊ ተመታ፣
በማስመሰል: በማታለል ሳይሆን በእውነት ተሰቀለ:: በእውነት ሞተ፣ ተቀበረ፣ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ … ” (Epistle
to the Trallians, chapter 10)፡፡

ዳግመኛም እግዚአብሔር “ስለ እኛ ሞተ” የሚለውን ይዘው “መለኮት በባሕርዩ ታመመ ሞተ” ላሉ መናፍቃንም ምላሽ
ሲሰጥ፥

“እኛ ግን የባሕርይ አምላክ ክርስቶስ ሰው እንደ መሆኑ በሥጋ እንደ ታመመ፤ በመለኮት እንዳልታመመ እናምናለን፤ በሥጋ
ሞተ፤ በመለኮት አልሞተም፡፡… መለኮት ሞተ ካልክ ሦስቱ ሞቱ እንዲያሰኝብህ፤ የጌታችንንም ሥጋ በመቃብር ውስጥ
እንደ ሙታን በድን እንዳደረግኸው አታውቅምን?” (ሃይ.አበ. ምዕ.11፣ ክፍል 11፣ ቍ.10-13)፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሐደው ሥጋ እንደ ተነሣ፣ አሁንም በተዋሐደው ሥጋ በአባቱ ቀኝ በጌትነቱ
ተቀምጦ እንዳለ፣ ዳግመኛም በሚመጣበት ጊዜ በክበበ ትስብእት እንደሚመጣ፤ መለኮት እና ሥጋ ከተዋሕዶ በኋላ
መቼም መች መለያየት እንደሌለባቸው በስፋት መስክሯል፤ እንዲህ ሲል፡-

“ክርስቶስ ሲወለድ: ሲሰቀል ብቻ ሳይሆን ከትንሣኤም በኋላ በተዋሕዶ ነው፤ አሁንም እንዲሁ ነው፡፡ ወደ ጴጥሮስ እና
አብረውት ወደ ነበሩት መጥቶ እንዲህ አላቸው፥ ‘እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥
መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው’ (ሉቃ.24፥39)፡፡ ቶማሰንም እንዲህ አለው ‘ጣትህን
ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን’ (ዮሐ.20፥27)::
ወዲያውም እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ አመኑ፡፡ ቶማስም ‘ጌታዬ አምላኬም’ አለው ((ዮሐ.20፥28) … በተዋሐደው ሥጋ
በምስጋና፥ በክብርና በሥልጣን ሊመለስ፤ በተዋሐደው ሥጋ ወደ ላከው ወደ አብ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፡፡ መላእክትም
እንዲህ አሏቸው ‘ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ
ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል’ (ሐዋ. 1፥11):: መናፍቃን እንደተናገሩት
በመጨረሻ ያለ ሥጋ የሚመጣ ከሆነ ዐይንም ሁሉ የወጉትም እንዴት ያዩታል? እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ባወቁትስ ጊዜ
እንዴት ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ (ራእ.1፥7):: መናፍስት በተፈጥሯቸው አካልም፣ ምስልም፣ ምልክትም፣ ቅርፅም
የላቸውምና …” (Epistle to the Smyrneans, chapter 3)::

በዚህ ዓይነት ለመናፍቃን ምላሽ እየሰጠ በማሳፈር እና ምእመናንን ከክፉ ትምህርታቸው እንዲጠበቁ በመምከር
ከሐዋርያት ለተረከባት እምነት ጠበቃ ነበረ፡፡

3. ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን

ቅዱስ አግናጥዮስ በላካቸው መልእክታት በሙሉ የሚጠቅሰው ሌላው ጉዳይ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እንዴት
በሥርዐት መተዳደር እንዳለባቸው ነው፡፡ ምእመናን ጳጳሳትን፣ ቀሳውስትን እና ዲያቆናትን እጅግ እንዲያከብሩ
በተደጋጋሚ ይናገራል:: … ምእመንስ ይቅርና፥ ካህናትም እንኳ ቢሆኑ ከጳጳሳት ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ ምንም ነገር
እንዳያደርጉ ያስጠነቅቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሥርዐት በሥላሴ ዘንድ ካለች የፈቃድ አንድነትና ስምምነት ጋር እያነጻጸረ
በቤተ ክርስቲያንም እንደዚህ አይነት ፍጹም የሆነ የልብና የሐሳብ አንድነት እንዲኖር ያስተምራል፡፡

“[አይሁድ ክርስቶስን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቃወማለህ ባሉት ጊዜ] ‘እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ
ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም እውነት ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና’ [ማለትም እኔ ምንም ምን
ከራሴ ብቻ አንቅቼ አላስተምርም: በህልውና እንደሰማሁ አስተምራለሁ እንጂ፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ ልዩ፣ እንግዳ
ሆኖ የእኔ ፈቃድ ሊደረግ አልወድም፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ አንድ ነውና የአባቴ ፈቃድ ሊደረግ እወዳለሁ እንጂ]
እንዳለ (ዮሐ. 5፥30፣ ወንጌል አንድምታ) እናንተም ካህናትም ሆናችሁ ዲያቆናት ወይም ምእመናን ያለ ጳጳሱ ፈቃድ
ምንም ነገር አታድርጉ:: እንዲህ ያለው ተግባር ኀጢአት እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚቃወም ነው” (Epistle to the
Magnesians, chapter 7)፡፡

ካህናትን የሚያቃልሉ፣ ለካህናት የማይታዘዙ ሁሉ መጨረሻቸው ጥፋት እንደ ሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-

“ሁሉም ነገር መጨረሻ ያለው መሆኑንና ትእዛዙን በመጠበቃችን ሕይወት እንደ ተዘጋጀልን፣ ያለመታዘዝ ፍጻሜው ግን
ሞት እንደ ሆነ፣ ሁሉም እያንዳንዱ እንደ ምርጫው ወደየቦታው እንደሚሄድ ተገንዝበን ከሞት ርቀን ሕይወትን
እንምረጥ” (Epistle to the Magnesians, chapter 5)፡፡

You might also like