You are on page 1of 5

yÄNx@L :Y¬ãC

Daniel kibret’s Views


www.danielkibret.com

ጥርስ ወይስ እጅ - ማን ይቅደም ?


አሜሪካ ቨርጂንያ አሌክሳንድርያ ውስጥ ከሚኖር አንድ ወዳጄ ጋር ወደ አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል
ሄድን፡፡ ይህ ወዳጄ እዚያ ነው የሚሠራው፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ እርሱ በሚሠራበት የእንግዶች
ማስተናገጃ ቦታ (ፍሮንት ዴስክ ይሉታል) አንድ የርሱ ጓደኛ እየሠራ ነበር፡፡ ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡ እኔም
ወዳጁ መሆኔን ነገረው፡፡ ያም ጓደኛው ሻሂ እንድንጋበዝለት ለመነን፡፡ እኛም ባንድ አፍ ብለን ሶፋው ላይ
ዘና አለን፡፡

ያኔ ነው ይህ ወዳጄ ስለ ጋባዡ ጓደኛው የነገረኝ፡፡ ይህ ጓደኛው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነው፡፡ እዚህ


ከትምህርት በሚተርፈው ጊዜ ነው የሚሠራው፡፡ ሌሎችም በዚህ መልኩ የሚሠሩ አሉ፡፡ የዚህኛውን ልዩ
የሚያደርገው ግን ይህ ጓደኛው የሆቴሉ ባለቤት ልጅ መሆኑ ነው፡፡

ይህንን ስትሰሙ «ምን ዓይነት ገብጋባ አባት ነው፡፡ ያንን የመሰለ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል እያለው
ለልጁ የሚፈልገውን ነገር ካላደረገለት ምኑን አባት ሆነው? ይኼ ጋብሮቮ መሆን አለበት፤ እኔ እርሱን
ብሆን ኖሮ ልጄን አንቀባብሬ ነበር የማሳድገው፣» ሳትሉ አትቀሩም፡፡ እስኪ ለመፍረድ አትቸኩሉ፡፡

አባትዬው ልጁን ማሳደግ እንጂ መግደል አልፈለገም፡፡ ምነው «ባለጌን ካሳደገ የገደለ ጸደቀ» ትሉ የለም
እንዴ፡፡ ባለጌ ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ጥሮ ግሮ በወዙ ለማደር የማይፈልግ፣ ተንጠላጣይ ማለት
አይደለም፡፡ ታድያ አንድ ልጅ የሥራን ጥቅም እና ጠባይ ካላወቀ፣ በራሱ ካልተማመነ፣ ታግሎ ማሸነፍን
ገንዘብ ካላደረገ፣ ከሥር እስከ ላይ ያለውን የዕድገት መሰላል ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ካልተገነዘበ
ከመባለግ ውጭ ምን አማራጭ አለው?

አባትም ያደረገው ይኼንኑ ነው፡፡ የአባቱን ሀብት እንደሆነ መቼም ያገኘዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ማግኘት
ያለበት ልምድ እና ዕውቀት አለ፡፡ ከዕውቀት በፊት የተገኘ ገንዘብ መሬቱ ሳይገኝ የተቦካ ሲሚንቶ ማለት
ነው፡፡ ሁለቱም ይበላሻሉ፡፡

ሠርቼ አገኘሁ እና በዕድሌ አገኘሁ ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በዕድል የተገኘ በዕድል ይጠፋል፡፡
በጥረት የተገኘ ግን ቢጠፋም በጥረት ይተካል፡፡ ዓሣውን አትስጠው ዓሣ የሚያወጣበትን ጥበብ ስጠው

dkibret@gmail.com
yÄNx@L :Y¬ãC
Daniel kibret’s Views
www.danielkibret.com
ይባል የለ፡፡ ዓሣውን ብቻ ብትሰጠው ነገም ሌላ ሰው ዓሣ እንዲሰጠው ይጠብቃል፡፡ የዓሣ ማውጫውን
ጥበብ ከሰጠኸው ግን ማንንም ሳይለምን ራሱ ዓሣ ያጠምዳል፡፡

ኣባትም ሊያደረግ የፈለገው ይኼንን ነው፡፡ ሀብቱን አይደለም ሊሰጠው ያሰበው፤ ሀብቱን ያገኘበትን መን
ገድ እንጂ፡፡ እንዴት ሀብታም መሆን እንደሚቻል ማስተማር ነው የፈለገው፡፡ የሥራን ክቡርነት፣ ጥበብ
እና ታላቅነት ጭምር ነው ሊሰጠው ያሰበው፡፡ የኢትዮጵያን ብሮች ስናያቸው በሁሉም ላይ ሠራተኛ ሰዎች
አሉ፡፡ ሞሰብ የምትሰፋ፣ ሞፈር ቀንበር አገናኝቶ የሚያርስ፣ ከብቶች የሚጠብቅ፣ ምርመራ የሚያደርግ፣
ቡና የሚለቅም፣ በትራክተር የሚያርስ፡፡ ገንዘብ በሥራ ብቻ ሊገኝ እንደሚገባው እየነገረንኮ ነው፡፡

ጓደኛዬ እንደነገረኝ ከሆነ የባለቤቱ ልጅ እኩል ከእነርሱ ጋር ተወዳድሮ ነው የተቀጠረው፡፡ በሥራ ቦታ


ላይ እነርሱ እና በእርሱ መካከል ያለው ልዩነት እርሱ አባቱ በመሆኑ ምክንያት በባለቤቱ ስም መጠራቱ
ብቻ ነው፡፡ አንድም ቀን የሆቴሉ ባለቤት ልጅ መሆኑን ተናግሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም ስለ ተሰጠው ቲፕ እና
በአለቃው ስለ መመስገኑ አውርቶ ያውቃል፡፡ አቤት እኛ ሀገር ቢሆን ኖሮ አልኩ፡፡ እንኳን የባለቤቱ ልጅ፤ የባለቤቱ
ልጅ ጓደኛ፣ የጓደኛውም ዘመድ፣ የዘመዱም አማች ጉራው አያስቀምጥም ነበር፡፡

ሰዓት ማክበር፣ ለአለቃው መታዘዝ፣ የእንግዶችን ሻንጣ መቀበል፣ ሲቀር ማስፈቀድ፣ ሲታመም የሐኪም
ፈቃድ ማምጣት፣ ከዚያም በላይ ከእንግዶች ቲፕ መቀበል እርሱንም ይመለከታል፡፡ የባለቤቱ ልጅ
ቢሆንም አባቱ ለቀጠረው አለቃው ግን ይታዘዛል፡፡ የባለቤቱ ልጅ ቢሆንም የሥራ ሥነ ምግባሩ እንደ
ሠራተኞች እንጂ እንደ ልጅነቱ አይደለም፡፡ እንደ ሌሎቹ ሠራተኞች እኩል ነው ደሞዝ የሚከፈለው፡፡

ይኼኔ ነው የሀገሬ ባለ ሀብቶች እና ነጋዴዎች ትዝ ያሉኝ፡፡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች
እያለን «የሀብታም ልጆች» የሚባሉት ጓደኞቻችን እንዴት ይቀብጡ እንደ ነበር ትዝ ይለኛል፡፡
ከዐቅማቸው በላይ የሚሆን ገንዘብ ነበራቸው፡፡ ከትምህርት ይልቅ ለመዝናናት ጊዜ ነበራቸው፡፡ በተለይ
ወንዶቹ የፈሰሰ ውኃ የማያቃኑ ነበሩ፡፡ ወላጆቻቸው ሀብታሞች መሆናቸውን እንጂ ሀብታቸው እንዴት
እንደመጣ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡

በሆቴል ንግዳቸው የታወቁት በቀለ ሞላ በአንድ ወቅት «የርስዎ ልጆች በትንሽ በትልቁ ብዙ ገንዘብ
ይሰጣሉ፣ እርስዎ ግን ቁጥብ ነዎት» ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ «እኔ የድኻው የሞላ ልጅ ነኝ፤ እነርሱ
ግን የሀብታሙ የበቀለ ልጆች ናቸው» ያሉት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡

በመጠኑም ቢሆን በገበሬው እና በከተማው የጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ካልሆነ በቀር ልጅን ሥራ
እያስለመዱ ማሳደግ በሌሎቻችን ዘንድ ነውር ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚህም ምክንያት በሞያቸው እና

dkibret@gmail.com
yÄNx@L :Y¬ãC
Daniel kibret’s Views
www.danielkibret.com
በዕውቀታቸው፣ በልምዳቸው እና በሥራቸው ከመተማመን ይልቅ በወላጆቻቸው ሀብት የሚኮሩ የሀብታም
ልጆችን አፍርተናል፡፡ ሳይሠራ የሚገኝ ገንዘብ ለልቅነት የተጋለጠ ነው፡፡ እንዴት እንደመጣ የማታውቀውን
ገንዘብ እንዴት እንደወጣም አታውቀውም፡፡

በሀብታም ልጆች እና በድኾች ልጆች የስርቆት ዐመል መካከል ልዩነት አለ፡፡ የድኻ ልጅ የሚሰርቀው
ከእጥረት በመጣ ልማድ ነው፡፡ አላገኘውም ብሎ ስለሚያስብ ሰርቆ ለማግኘት ያስባል፡፡ በዚያውም
ይለምድበታል፡፡ የሀብታም ልጆች ግን ከቅብጠት የመጣ ነው፡፡ ብዙ ማውጣት የለመደ እጅ እጥረትን
አይቋቋምም፡፡ ብዙ ማውጣት በቀላሉ የማይከደኑ ብዙ ቀዳዳዎች መክፈት ነው፡፡ እነዚህ ክፉ የለመዱ
ቀዳዳዎች ደግሞ እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አይሄዱም፡፡ ገቢ ገቢን ወጭም ወጭን ይጠራዋል፡፡ ቀላይ
ቀላይን ትጠራለች አይደል መጽሐፉ የሚለው፡፡ እነዚህ ከእድሜያቸው እና ከዕውቀታቸው በፊት ገንዘብ
ያገኙ ልጆች ይበልጥ ለማውጣት በሚያደርጉት ጥረት የወላጆቻቸውን ሀብት እስከመስረቅ፣ ባስ ሲልም
ንብረታቸውን እስከመሸጥ፣ የከፋም ከመጣ ወላጆቻቸውን ገድለው ሀብት እስከመውረስ ይደርሳሉ፡፡

ልጆችን ቅንጦትን ሳይሆን ሥራን ነው ማስለመድ ያለብን፡፡ ሰውን ድሎት እንጂ ሥራ አይጎዳውምና፡፡
በቤታችን ውስጥ እስኪ ለልጆቻችን ሥራ እናከፋፍላቸው፡፡ ለምሳሌ ሳሎኑን ለአንዱ ልጅ፣ መኝታ ቤቱን
ለአንደኛው፣ ግቢውን ለሌላኛው በኃላፊነት እንስጥ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ያለ ቦታቸው የተቀመጡትን
ዕቃዎች ማስተካከል፣ መደረግ ያለበትን ለወላጆች ማመልከት፣ ቆሻሻዎችን መሰብሰብ፣ ጠረጲዛዎችን
መወልወል ወዘተ የእነርሱ ሥራ ይሁን፡፡

የሳሎን ኃላፊ፣ የመኝታ ቤት ኃላፊ፣ የግቢ ኃላፊ የማዕድ ቤት ኃላፊ እያላችሁ መድቧቸው፡፡ የኃላፊነትን
ስሜት አሁን ይልመዱት፡፡ አወዳድሯቸው፡፡ ተግባሩን በሚገባ የተወጣውን ሸልሙት፡፡ ስለ እነርሱ ሥራ
እንግዶች ፊት ተናገሩላቸው፡፡ ከፍ ሲሉ ደግሞ በቤቱ ውስጥ ያሉትን ጉዳዮች አካፍሏቸው፡፡ ለምሳሌ የም
ግብ ጉዳዮች፣ የጽዳት ጉዳዮች፣ የክፍያ ጉዳዮች (ስልክ፣ መብራት፣ የቤት ኪራይ፣ ሌላም መከፈሉን መከ
ታተል)፣እያላችሁ፡፡ ታድያ ለእነዚህ ሥራዎች መደበኛ ክፍያ መድቡ፡፡ በሳምንት ስንት ትከፍሏቸዋላ ችሁ?
ይወቁት፡፡ ያንን ገንዘብ እናንተ ጋ አስቀምጡላቸው፡፡ መዝናናት ሲፈልጉ፣ ወጣ ያለ ነገር መግዛት ሲፈልጉ
ሠርተው ካጠራቀሙት ወጭ ያድርጉ፡፡ ያኔ ሠርቶ ማግኘትን ይለምዳሉ፡፡ እናንተ ደግሞ በሚገባ ኃላፊ
ነታቸውን ሲወጡ ካጠራቀሙት ላይ ጨመር አድርጉላቸው፡፡ በመሥሪያ ቤትስ ቦነስ አለ አይደል እንዴ፡፡

አንድ ሰው አለ፡፡ «ስንት ልጆች አሉህ?» ተብሎ ሲጠየቅ «ለሥራ ያልደረሱ፣ ለመብል ያላነሱ አምስት
ልጆች አሉኝ» ይል ነበር፡፡ የኛ ልጆች ለመብል ያላነሡ ለሥራ ያልደረሱ እንዳይሆኑ ከፈለግን በኛው

dkibret@gmail.com
yÄNx@L :Y¬ãC
Daniel kibret’s Views
www.danielkibret.com
ድርጅት ተቀጥረው ይሥሩ፡፡ መማር ያለባቸው በጥገኝነት አይደለም፡፡ እየሠሩ ነው፡፡ የሚቻል ከሆነ
ከትምህርት ቤት ውጭ ባለው ሰዓታቸው በእናንተ ድርጅት ውስጥ የተመደበ ሥራ ይኑራቸው፡፡ ያ
ካልተቻለ ደግሞ ቅዳሜ እና እሑድ በተወሰነ ጊዜ ይሥሩ፡፡

ስትመድቧቸው ልጄ እዚህ ጋ ይሥራ አትበሉ፡፡ አወዳድሯቸው፡፡ ተወዳድሮ ማሸነፍን ይልመዱ፡፡ የብዙ


ባለጸጎች ልጆች ወላጆቻቸውን ድንገት ሲያጡ ድርጅታቸወን የሚያደርጉት ይጠፋቸዋል፡፡ ሀብቱን እንጂ
ጥበቡን አልወረሱምና፡፡ ድርጅቱን ከውጭ እንጂ ከውስጥ አያውቁትም፡፡ አሸነፍኩ፣ ድል አደረግኩ እንዲሉ
ይወዳደሩ፡፡ በአንዳንድ ድርጅቶች ባለ ሀብቶች ልጆቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ይመድ
ባሉ፡፡ ምደባቸው ግን በዝምድና እና በችሮታ እንጂ በማወዳደር እና በዕውቀት ስላልሆነ ለድርጅቱም
ለድርጅቱ ኃላፊዎቸም ችግር ይሆናሉ፡፡ በሥራ ያሾፋሉ፣ ባልሠሩበት ሀብት ይመካሉ፣ የባለሀብቱ ልጅ
ወይንም ዘመድ በመሆናቸው ይታበያሉ፣ በሥራ ያሾፋሉ፤ አለቆቻቸውን ይንቃሉ፤ የእዝ ሠንሠለቱን ጥሰው
ከበላዮች ጋር ይገናኛሉ፡፡ ይኼ ማበላሸት እንጂ መጥቀም አይደለም፡፡ ነገ በራሳቸው ሲቆሙ እንዲህ ያለ
አሠራር አይገጥማቸውም፡፡ እናም ያልተማረው ትምህርት ፈተና ላይ እንደመጣበት ተማሪ ይደነጋገራሉ፡፡

እየሠሩ ያደጉ ልጆች የሥራን ጠባይ ብቻ ሳይሆን የሠራተኛንም ጠባይ ያውቃሉ፡፡ የሠራተኛን ጉዳት፣
ሕመም፣ ችግር እና ውጣ ውረድ ይረዳሉ፡፡ ሠራተኛ ምን ይፈልጋል? ምን ያማርረዋል? ምን ያበረታ
ታዋል? ይረዱታል፡፡ ያለፉበት ነውና ነገ ኃላፊ ሲሆኑ ለሠራተኛው ይራራሉ፡፡ እንዴት ገንዘብ እንደሚገኝ
ከሕይወት ልምዳቸው አይተዋልና በገንዘብ አይቀልዱም፡፡ ከታችኛው የሥራ ክፍል ጀምረው ድርጅቱን
እስከ ማስተዳደር ስለሚደርሱ እያንዳንዷን የሥራ ዝርዝር ያውቋታል፡፡

ከሁሉም በላይ በራስ የመተማመናቸው ስሜት ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የተረጅነት ሳይሆን ታግሎ የማሸነፍ
ሞራል አላቸው፡፡ በሥራ እንጂ በዘር ማንዘር መመካትን ያርቃሉ፡፡ የእገሌ ልጅ ነኝ ከማለት ይልቅ
እንዲህ የሠራሁ ነኝ ማለት ያስደስታቸዋል፡፡ የእሳት ልጅ ዐመድ ሳይሆኑ የእሳት ልጅ ትንታግ ይሆናሉ፡፡

በተለይም በዳያስጶራ የሚኖሩ የሀገሬ ልጆች ታናናሾቻቸው እያበላሿቸው ነው፡፡ የርዳታን እንጂ የሥራን
ስሜት አላሳደሩባቸውም፡፡ አንድ ልጅ ያለኝን ልንገራችሁ፡፡ የኮሌጅ ተማሪ ነው፡፡ እኅቱ ከአሜሪካ ለኮሌጅ
ትከፍልለታለች፡፡ በየወሩ ደግሞ ለኪሱ መቶ ዶላር ትልካለች፡፡ ሦስት ጊዜ ኮሌጅ ቀየረ፡፡ ሁለተኛ እና
ሦስተኛ ዓመት ሲደርስ ነው የሚቀይረው፡፡

እኅቱ ግራ ገባትና እባክህ አናግረው አለቺኝ፡፡ አናገርኩት፡፡ ወዲያ ወዲህ ብሎ ምክንያት ሊሰጠኝ ሲሞክር
እርሱ ተማርኩበት ወደሚላቸው ሁለት ኮሌጆች ኃላፊዎች መደዋወል ጀመርኩ፡፡ «እውነቱን ልነገርህ?»

dkibret@gmail.com
yÄNx@L :Y¬ãC
Daniel kibret’s Views
www.danielkibret.com
አለኝ፡፡ ተደላደልኩ፡፡ «አሁን እኅቴ በየወሩ መቶ ዶላር ትልክልኛለች፡፡ በኢትዮጵያ ስትመታው አንድ ሺ
ሰባት መቶ ብር ይሆናል፡፡ ግብር ምናምን የለበትም፡፡ እኔ ተምሬ ብመረቅ ግን አንድ ሺ ሁለት መቶ
ብር አካባቢ ነው የምቀጠረው፡፡ በዚያ ላይ ግብር አለበት፡፡ እኅቴም ሥራ ያዘ ብላ ታቆማለች፡፡ ታድያ
እኔ ኮሌጅ ተምሬ ከምመረቅ ባልመረቅ የተሻለ አገኛለሁኮ» ነበር ያለኝ፡፡ ሳስበው እውነቱን ነው፡፡

መጀመርያውኑ ከወላጆቹ ጋር ለሚኖር ያንን ያህል ወጭ ለሌለበት ወጣት አንድ ሺ ሰባት መቶ ብር በየ


ወሩ መስጠት «ጥፋ» ብሎ መፍረድ ነው፡፡ እኅቱ ገንዘብ መርዳት ከፈለገች እንኳን አንዳች ነገር እየሠራ
ብትከፍለው መልካም ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሳምንት የተወሰነ ሰዓት አገል
ግሎት እንዲሰጥ አድርጋ በእነርሱ ሪፖርት መሠረት በደመወዝ መልክ ብትሰጠው እንዴት በተሻለ ነበር፡፡

አንድ ሊቅ «ሰው ሲወለድ ከጥርሱ በፊት እጅ ነው የሚፈጠርለት፡፡ ይህም መሥራት ከመብላት በፊት
መቅደም እንዳለበት ሊያሳየን ነው» ብለዋል፡፡ ከእጅ በፊት ጥርስ የተፈጠረላቸው ሰዎች ግን አሉ፡፡
መብላት እንጂ መሥራት የማይችሉ፡፡ የአንዳንዶች ደግሞ ከዚህ የባሰ ነው፡፡ ጥርስ ማውጣት ሲጀምሩ
እጆቻቸው ሽባ ይሆናሉ፡፡ ቀድመው የተፈጠሩትን እጆች ሽባ የሚያደርጋቸው ደግሞ እጆቹ የበቀበሉበት
ማኅበረሰብ ነው፡፡

dkibret@gmail.com

You might also like