You are on page 1of 2

የአማራ ክልል አጠቃላይ ገጽታ

የአማራ ክልል በሰሜናዊ የኢትዮጲያ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ክልል ሶስት በመባል ይታወቃል፡፡ የአማራ
ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ከ9-14 ዲግሪ ሰሜን ኬክሮስና ከ36-40 ዲግሪ ምስራቅ ኬንትሮስ ሃሳባዊ መስመሮች መካከል የሚገኝ
ሲሆን የክልሉ የአየር ንብረት 2.35 በመቶ ውርጭ፣ 24.15 በመቶ ደጋ፣ 46.61 በመቶ ወይና ደጋና 26.71
በመቶ ቆላ ነው፡፡ የክልሉ የመልክዓ ምድር ገፅታ ሜዳማ፣ ሸለቋማ፣ ኮረብታ፣ አምባና ተራራማ ሲሆን
አማካይ ከፍታው ከ500 ሜትር እስከ 4620 ሜትር ይደርሳል፡፡

በአገራችን በከፍታው የሚታወቀውና እንደ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉ ብርቅዬ
አራዊቶች የሚገኙበት የራስ ዳሽን ተራራ የሚገኘው በዚሁ ክልል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ
ተግባራት ሊውሉ የሚችሉ የበርካታ ወንዞች /አባይ፣ ተከዜ፣ አንገረብ …/ እና ሃይቆች /ጣና፣ ሎጐ፣
ዘንገና፣ አርዲቦ …/ ባለቤትም ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አመሰራረት ፓርላሜንታዊ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ክልል ምክር ቤቱ
294 መቀመጫ ወንበሮች ያሉት ሲሆን ከፆታ አንፃር 201 ወንድና 93 ሴት የምክር ቤት አባላት ያሉት
ምክር ቤት ነው፡፡ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት የብአዴን አባላት ናቸው፡፡ የአማራ ክልል በ12 የአስተዳደር
ዞኖች /ሦስቱ የብሔረሰብ ዞኖች ናቸው/፣ በሦስት የሜትሮፖሊ ታንያን ከተሞች (ባሕር ዳር፣ ጎንደርና ደሴ
ከተሞች) የተዋቀረ ሲሆን 38 የከተማ አስተዳደሮች፣ 139 ወረዳዎችና 3,461 ቀበሌዎች አሉት፡፡ ክልሉ
ከአማራ ብሔር በተጨማሪ የአዊ፣ የኦሮሞ፣ የዋግ ኽምራና የአርጐባ ብሔረሰቦች ይኖሩበታል፡፡

ርዕሰ ከተማ

: ባህር ዳር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ ከተማ ነች፡፡

የስፍራው አቀማመጥ
:የአማራ ክልል በምራብ እና በሰሜን ምእራብ ከሱዳን፤በሰሜን ከትግራይ፤ በምስራቅ ከአፋር፣ በምራብ እና
በደቡብ ምዕራብ ከቤኒሻንጉል-ጉምዝ ክልልእና በደቡብ ከኦሮሚያ ጋር ጋር ይዋሰናል፡፡

የቆዳ ስፋት
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 170‚752 ስኩ.ኪ.ሜ የሚገመት የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡ ይህም ክልሉ
ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት 15 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልሎች በመቀጠል የሀገሪቱን
3ኛውን ትልቁን የቆዳ ስፋት ይይዛል፡፡

ስነ-ህዝብ

የኢትዮጲያ ስታስቲክ ኤጀንሲ በ2007 በተገኘው የህዝብ ቆጠራ መሰረት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ
መንግስት የህዝብ ብዛት 17,221,976 ሲሆን ከዚህም ውስጥ 8,641,580 ወንዶች እና 8,580,396
ሴቶች ናቸው፡፡ 84 ከመቶ የሚሆነው በገጠራማው የክልሉ ቦታዎች ይኖራል፡፡ በሀይማኖት ረገድም
81.5ከመቶ የኦርቶዶክስ ክርስትያን፣ 18.1 ከመቶ የእስልምና ፣ 0.2 ከመቶ የፕሮቴስታንት የተቀረው
0.1ከመቶ የሌሎች እምነት ተከታይ ነው፡፡ በብሄር ስብጥር አኳያም 91.2 ከመቶ አማራ፣ 9.1 ከመቶ አዊ፣
3 ከመቶ ኦሮሞ፣1.3 ከመቶ አገው /ካሚር 0.4 አርጎባ ፤1.2 ከመቶ ቅማንት፤ 0.6 ከመቶ ትግራዋይ
ብሄረሰቦች ይኖራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በግእዝ ፊደላት የተቀረፀው የአማረኛ ቋንቋ የክልሉ የስራ ቋንቋ ሲሆን
85.5 ከመቶ በክልሉ ይነገራል

ዋነኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች


በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኘው ህዝብ 85 ከመቶየሚሆነው ህዝብ ኑሮውን የግብርና ስራ
ላይ ያደረገ ነው፡፡ በክልሉ በቆሎ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽንብራ፤ዳጉሳ፤ አተር እና ባቄላ እንዲሁም የተለያዩ
የቅባት እህሎች በከፍተኛ ደረጃ የሚመረቱ ሰብሎች ናቸው፡፡ ሰሊጥ ለገበያ የሚቀርብ ምርት ነው፡፡

You might also like