You are on page 1of 3

ሁለቴ መቸገር

«ከተራበ ይልቅ ለጠገበ አዝናለሁ» ይሉ ነበር አጎቴ፡፡ ለምን ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ «ሰው ተርቦ ከሚደርስበት ጉዳት ጠግቦ የሚደርስበት
ጉዳት ይበልጣል» አሉኝ፡፡ «ሰው ጠግቦ ጉዳት ያደርሳል እንጂ ምን ጉዳት ያደርሳል?» አልኳቸው፡፡ «እርሱኮ ነው ጉዳቱ፡፡ በሰው ላይ
ጉዳት አደርሳለሁ ብሎ የሚመጣበት ጉዳት፡፡ ለተራበ ሰው ውድቀት ማለት ከመጀመርያው ደረጃ እንደ መውደቅ ነው፡፡ የጠገበ ሰው
ውድቀት ማለት ግን ከመጨረሻው ደረጃ አጓጉል እንደ መውደቅ ነው» አሉ፡፡
ይህ የእርሳቸው አባባል የሕንዶችን ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡ ሕንዶች ረሃብም ሆነ ጥጋብ ሁለቱም እኩል ይጎዳሉ ይላሉ፡፡ ረሃብ እና
ጥጋብ ሁለቱም የጤንነት፣ የደኅንነት እና የሰላም ዕንቅፋቶች ናቸው ብለውም ይጨምሩበታል፡፡ ረሃብ እና ጥጋብ ሀገርን እኩል ነው
የሚጎዷት ሲሉም የሚከተለውን ይተርካሉ፡፡
ሕንድ ውስጥ አንድ ትልቅ ሕንጻ የሚያሠራ ሰው ነበረ፡፡ ይህ ሰው ሕንፃውን ለማሠራት ቆሞ እያለ አንድ የኔ ቢጤ ወደርሱ ይመጣል፡፡
ያም የኔ ቢጤ የሳንቲም ድቃቂ የልብስ እላቂ ፈልጎ ሀብታሙን ሰውዬ ይለምነዋል፡፡ ሀብታሙም ሰውዬ «ተመልከት እኔ ሕንፃውን
የሚሠሩልኝ ሰዎች ፈልጌ እዚህ ቆሜያለሁ፡፡ ታድያ አንተ ሠርተህ ለምን አትበላም?» አለው፡፡
የኔ ቢጤውም «መሥራት አልችልም» ሲል መለሰለት
«ለምን?» አለው ሰውዬውም
«ሆዴ ባዶ ነው፤ ጠኔ አሞኛል መሥራት አልችልም» አለው፡፡
ያ ሕንፃ አሠሪ በሁኔታው አዘነና ባለሟሎቹን ጠርቶ ሰውዬውን እስኪበቃው ድረስ አብልተው እንዲያመጡት አዘዛቸው፡፡ እነርሱም
ያንን የኔ ቢጤ ወደ ቤት ወስደው አይቶት የማያውቀውን ምግብ እና መጠጥ አቀረቡለት፡፡ እርሱም እምብርቱ እስኪለጠጥ የቻለውን
ያህል አስገባ፡፡
ባለሟሎቹ መጥገቡን እንዳረጋገጡ ሕንፃው ወደሚሠራበት ቦታ ወሰዱት፡፡ የኔ ቢጤው ግን ወደ ሥራ መሠማራት አልቻለም፡፡ አንድ
ዛፍ ሥር ተቀመጠ፡፡ ባለቤቱም ሲመጣ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘው፡፡
«እህ ጠገብክ» አለው
በዓይኑ ሰውዬውን በእጁም ሆዱን እያሸ በአንገቱ አረጋገጠለት፡፡
«መልካም በል አሁን ተነሣና ወደ ሥራ ተሠማራ፤ ከዚህ በኋላ ለምኖ መብላት የለም» አለው ሕንፃ አሠሪው፡፡
«አልችልም» አለ የኔ ቢጤው፡፡
«በልቼ ጠግቤያለሁ አላልክም»
«ልክ ነው ጌታዬ»
«ታድያ ቅድም ሥራ ስልህ ሆዴ ባዶ ስለሆነ በባዶ ሆዴ መሥራት አልችልም አልከኝ፡፡ አሁን ከጠገብክ ለምን አትሠራም»
«አሁን ደግሞ ሆዴ ከመጠን በላይ በመጥገቡ አሞኛልና ጎንበስ ቀና ብዬ መሥራት አልችልም» አለው፡፡
ርሃብም ያማል፤ ጥጋብም ያማል ያሉት ሕንዶች ለዚህ ነው፡፡
አለመማርም፣ መማርም፣ የሚያማቸው ሰዎች ገጥመዋችሁ አያውቁም፡፡ አንዳንዶቹ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ለምን ያጠፋሉ?
ለምን ሀገር ይጎዳሉ? ለምን ሕዝብ ያስለቅሳሉ? ለምን ፍርድ ያዛባሉ? ለምን በሙስና ይዋጣሉ? ለምን የዘመድ አዝማድ አሠራር
ይዘረጋሉ? ደረቴ ይቅላ፣ ሆዴ ይሙላ ብለው ብቻ ለምን ያስባሉ? እያልን እንጠይቅና ባይማሩ ይሆናል ብለን እናስተሠርይላቸዋለን፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ ደራሲ
ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ
እንዳሉት ለቦታው እና ለሥራው፣ ለኃላፊነቱ እና ለወንበሩ የሚመጥን ዕውቀት ኖሯቸው፣ ዐወቁ፣ መጠቁ፣ ላቁ ያልናቸው ሰዎች
ያልተማሩ ሰዎች የሚያጠፉትን ያህል ሲያጠፉ፣ ከዚያም በላይ ሲብሱ በምን እናስተሥርይላቸው?
መማርም አለመማርም እኩል ነው እንዴ የሚጎዳው?
ተለወጡ፣ አደጉ፣ ተመነደጉ፣ ኢንቨስተር ሆኑ፣ ሠለጠኑ፣ ተሾሙ፣ ተሸለሙ በሚባሉ ወገኖቻችን ላይ ዕድገት ነው የማየው ወይስ
ጥጋብ? የሚለው ጥያቄ እስካሁን መልስ ላገኝለት አልቻልኩም፡፡ ዕድገት የአእምሮ ነው፣ የአመለካከት ነው፣ የልቡና ስፋት ነው፣
የኅሊና ምጥቀት ነው፣ የአስተሳሰብ አድማስ ንጥቀት ነው፣ የኃላፊነት መሰማት ነው፣ ለነገ ጭምር ማሰብ ነው፡፡
ጥጋብ ግን የሆድ ብቻ ነው፡፡ የቅሪላ መነፋት ነው፡፡ ከክብደት እና ከቅላት፣ ከወዝ እና ከስፋት ጋር የሚሄድ ነው፡፡ ዕድገት አገርን፣ ጥጋብ
ሆድን ብቻ ያሳድጋሉ፡፡ መጥገብን ማንም ያውቀዋል፡፡ ይታያል ይዳሰሳል፡፡ ይጨበጣል፡፡ ጥጋብ ታይታ ይበዛዋል፡፡ የመኪና ጋጋታ፣
የግብዣ ቱማታ፣ የጌጣ ጌጥ ሻሻታ ነው ጥጋብ፡፡
አንዳንዱ ወገናችን ተራ ሰው ሆኖ አይሠራም፡፡ ምክንያት ሲሉት ችግሩን ያወራል፡፡ ባለ ሥልጣን ሆኖም አይሠራም፡፡ ምክንያት ሲሉ
ጥጋብ አላሠራው ብሏል፡፡ አንዳንዱ ወገናችን ላጤ ሆኖም ያማርራል፡፡ ምክንያት ሲሉት የሞቀ ቤት፣ የሞላ ትዳር ናፈቀኝ ይላል፡፡
አግብቶ ጠግቦ ያማርራል፡፡ ምነው ሲሉት ትዳር ከውጭ ያሉ እንግባ እንግባ፣ ከውስጥ ያሉ እንውጣ እንውጣ የሚሉበት ነው ይላል፡፡
አሁን በተማረው ወገናችን ያለው ዘንድ ጥጋብ ነው ወይስ እድገት ነው? የተለወጠው ማዕረጉ ነው ወይስ አመለካከቱ፣ የተሻሻለው
ደመወዙ ነው ወይስ ዕውቀቱ? የሠለጠነው በምርምር ነው ወይስ በማጭበርበር ስልት? ጊዜውን የሚያሳልፈው ሥጋ ላይ ነው ወይስ
ንባብ ላይ? ያጠናው ትንተና ነው ወይስ ቅንቀና?
ሕፃን ሆኜ የሰማሁት አንድ ተረት እዚህ ላይ ኖር ሊባል ይገባዋል፡፡ ያኔ ትርጉሙ አይገባኝም ነበር፡፡ ትርጉሙ የገባኝ አሁን ነው፡፡ አሞራ
እና አይጥ ተጋብተው ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ፍለጋ ሲዞሩ አንድ በእህል የተሞላ ስልቻ ያገኛሉ፡፡ ስልቻውን አሞራ
አንጠልጥሎ፣ አይጥም በጥርሷ እየጎተተች ወደ ማደርያቸው ይወስዱታል፡፡
እዚያ ደርሰው ሲፈቱት ለካስ የባቄላ ገለባ የተሞላ ኖሯል፡፡ መቼም በውስጡ አንዳች አይጠፋውም ብለው ፈተሹት፡፡ በመጨረሻም
አንድ ፍሬ ባቄላ አገኙ፡፡ ባቄላውን እንዳገኙ ሁለቱም ክርክር ገጠሙ፡፡ አይጥ «ይህቺ በቄላ ተበልታ ምንም አትጠቅምም፤ ስለዚህ
እንዝራት» አለች፡፡ አሞራ ደግሞ በጣም ርቦት ስለነበር እንደ ጓያ ነቃይ የዕለቱን አሰበና «የለም ለነገ ነገ ያውቃል፣ ዋናው ዛሬ ነው፣
እንብላት» አለ፡፡
በዚህ ክርክር እስካሁን አይጥ እና አሞራ እንዳልተስማሙ ይነገራል፡፡
ምን አይጥ እና አሞራ ብቻ እኛም አልተስማማንም፡፡ የሀገሪቱም ጥያቄ ይኼው ይመስለኛል፡፡ እንብላት እንዝራት? በአንድ
ማኅበረሰብ ውስጥ «እንብላት» የሚለው ከበዛ በሀገሪቱ ውስጥ ዕብጠት እንጂ ዕድገት ሊኖር አይችልም፡፡ ሆዳቸው፣ ኪሳቸው፣
ሀብታቸው፣ ጡንቻቸው፣ ጉንጫቸው፣ አንጎላቸው ያበጠ ብዙ ዜጎችን እናፈራለን እንጂ አእምሮአቸው እና ኅሊናቸው፣ ልቡናቸው
እና ሰብእናቸው ያደገ ዜጎችን በሥዕ ለትም አና ይም፡፡ ዕድገት የአእምሮ፣ ዕብጠትም የጥጋብ ውጤቶች ናቸው፡፡
ሰው ሲርበው በቁጭት እና በእልክ፣ በአልሸነፍ ባይነት እና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መሥራት አለበት፡፡ የሚታገለው ስለበላ፣
ስለሞላለት እና ለትግል የሚሆን ነገር ስላለው አይደለም፡፡ እንዲበላ፣ እንዲሞላለት እና ለተሻለ ትግል የሚሆን ነገር እንዲያገኝ እንጂ፡፡
ሰው ሲበላም በምስጋና እና የተሻለ ነገርን በማለም፣ ርካታው በጥማት፣ ሙላቱም በጉ ድለት እንዳይተካ ነገን ለማስተማመን
መሥራት መታገል አለበት፡፡
ሲያጣ ራበኝ ብሎ፣ ሲያገኝ ጠግቦ መሥመር የሚስተውን ግን ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ እነዚህን ሁለቱንም የያዘች ሀገር ጉዞዋቸውን
በቁሳዊ ርካታ እና በቁሳዊ ድል በሚለኩ ዜጎች ትሞላለች፡፡ ድህነት እና ውርደትን፣ ዕድገት እና ጥጋብን መለየት በማይችሉ ዜጎች
ትሞላለች፡፡ ሀገርን እነዚህ ሲሞሏት ደግሞ ዕውቀት ርካሽ ይሆናል፡፡ ዕውቀት እና ዐዋቂም ዋጋ ያጣሉ፡፡ ማጭበርበር እና መቀላጠፍ
ከመማር እና ከማወቅ በላይ፣ ፖለቲካዊ ጥገኛነት እና መንጠላጠል ከምርምር እና ልሂቅነት በላይ ዋጋ ያወጣሉ፡፡ ፊደል ቆጣሪ እንጂ
የተማረ ብርቅ ይሆንባታል፡፡
እንዲህ ያለች ሀገር የወጣቶቿ አመለካከት «ከሦስት ዲግሪ አንድ ግሮሠሪ» ወደሚለው ያዘነብልባታል፡፡ ዕውቀት አደሮች አልቀው
ሆድ አደሮች ይበዙባታል፡፡
በአንዲት ሀገር ውስጥ እንዝራት የሚሉ ዜጎች ከበዙ ግን ያቺ ሀገር ተስፋ ያላት ሀገር ትሆናለች፡፡ ከዕለቱ የዓመቱን፣ ከዛሬው የነገውን
ማየት የሚችሉ ዜጎች ታፈራለች፡፡ ጥቅምን ከራሳቸው፣ ገንዘብን ከኪሳቸው፣ ዕድገትን ከቤታቸው፣ በላይ አድርገው ማሰብ የሚችሉ
ልጆች አግኝታለች ማለት ነው፡፡
እነዚህን ባገኘች ሀገር ድህነት ቁጭትን እና ንዴትን ይፈጥራል፡፡ ከድህነት ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ሳይሆን ከድህነት ተመራምረው
የሚያመልጡ ዜጎች ሻምፒዮና ይሆኑባታል፡፡ እንዲህ ባለች ሀገር ወይ ዕውቀት ከሀብት ይቀድማል፣ አለያም ዕውቀት ከሀብት እኩል
ይመጣል፣ቢያንስ ደግሞ ዕውቀት ከሀብት ይከተላል፡፡
እንዲህ ባለች ሀገር ዕድገት እንጂ ዕብጠት ስለማይኖር ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ሆዳቸው ኅሊናቸውን ያልተ ጫነባቸው፣ በአመክንዮ
እሺ ብለው በአመክንዮ እምቢ የሚሉ፣ ራሳቸውን በየጊዜው ለአዲስ ዘመን የሚወ ልዱ፣ በልተው የሚጠግቡትን ሳይሆን ዘርተው
የሚያፍሱትን የሚያስቡ ልጆች በደስታ ይኖሩባታል፡፡
ሰው ሲያገኝም ሲያጣም ሆዱ የሚያስቸግረው ከሆነ፡፡ ሲያገኝም ሲያጣም ጥያቄው የሆድ ብቻ ጥያቄ ከሆነ፤ በማይምነት እና
በምሁርነት፣ በሸማችነት እና በነጋዴነት፣ በተራነት እና በባለ ሥልጣንነት፣ በወጋነት እና በታዋቂነት ጊዜም ሆዱ ካስቸገረው፣ ከሆድ
ወደ አእምሮ ለማደግ ካልቻለ ዕብጠት እንጂ ዕድገት ሲያልፍም አልነካካው ማለት ይኼም አይደል፡፡

You might also like