You are on page 1of 3

አለቃ ተክሌ

አለቃ ተክሌ የታዋቂው ሊቅ የአለቃ ገብረ ሐና ልጅ ናቸው፡፡ ዝማሜው ከእርሳቸው የቀደመ ታሪክ ቢኖረውም ያሳወቁት እና
ወንበር ዘርግተው ያስተማሩት እርሳቸው በመሆኑ «የተክሌ ዝማሜ» እየተባለ በስማቸው ይጠራል፡፡

የአለቃ ተክሌ እና የዝማሜው መገጣጠም ግን የሚከተለውን ይመስላል፡፡

በፍትሐ ነገሥት ዐዋቂነታቸው የዐፄ ቴዎድሮስ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት አለቃ ገብረ ሐና በቀልደኛነታቸው ምክንያት ከዐፄ
ቴዎድሮስ ጋር ሊስማሙ አልቻሉም ነበር፡፡

በኋላ ደግሞ ካህናት በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ ባመፁ ጊዜ በአድማው ካሉበት ካህናት መካከል አንዱ ገብረ ሐና መሆናቸው
ስለታወቀ ዐፄ ቴዎድሮስ በአለቃ ገብረ ሐና ላይ አምርረው ሊቀጧቸው ዛቱ፡፡ አለቃም ሸሽተው ጣና ሐይቅ ሬማ
መድኃኔዓለም ገዳም ገቡ፡፡ በዚያም ባሕታዊ ጸዐዳ ገብረ ሥላሴ የተባሉ የአቋቋም ሊቅ አገኙ፡፡ ሁለቱም ተወያይተው በጎንደር
አቋቋም ስልት የመቋሚያውን የአካል እንቅስቃሴ ጨምረው ዝማሜውን አዘጋጁት፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ለዝማሜው መነሻ
ያደረጉት በጣና ዳር የበቀለውን ደንገል እየተባለ የሚጠራ ሸንበቆ መሰል ተክል እንቅስቃሴ ነው ይላሉ፡፡ ባሕታዊ ጸዐዳ
«ከእንግዲህ እኔ ወደ ዓለም አልመለስም፤ አንተ ይህንን ስልት አስተምር» ብለው አለቃ ገብረ ሐናን አደራ አሏቸው፡፡

ይህንን በአፈ ታሪክ ሲነገር የነበረ ታሪክ ወደ ካቶሊክነት የተቀየረውና ከአንቶኒዮ ዲ አባዲ ጋር በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ስለ
ሆነው ሁሉ ደብዳቤ ይለዋወጥ የነበረው፣ የዋድላው ሰው ደብተራ አሰጋኸኝ ጥር ስድስት ቀን 1858 ዓ.ም ለአንቶኒዮ ዲ አባዲ
በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ በማለት ፍንጭ ይሰጥበታል፡፡ «አለቃ ገብረ ሐናን ንጉሥ መቱዋቸው በሽመል፡፡ ወደ ትግሬ ወደ
ላስታ ተሰደዱ፡፡ እጅግ ተዋረዱ፡፡ እኔም በዋድላ አገኘኋቸው ወደ ቆራጣ ሄዱ፡፡» (Sven Rubenson ed.Acta
Aethiopica: Tewodros and His Contemporaries, p 259)

አለቃ ይህንን ዝማሜ በጎንደር በኣታ ማስተማር ጀምረው ነበር ይባላል፡፡ ነገር ግን ጎንደሬ ሚባለውን መቋሚያ ስልት ከጥንት
ጀምረው የሚያውቁት የጎንደር ሊቃውንት ለቀበሏቸው አልቻለም፡፡ በተለይ ይህ የአለቃ ገብረ ሐና አቋቋም ለተመስጦ እንጂ
ለፕሮቶኮል ስለማይመች ከጎንደር ሊቃውንት ጋር ነጋ ጠባ ክርክር ሆነ፡፡ አለቃ ገብረ ሐናም ይህንን አቋቋም እንዳያስተምሩ
ተከለከሉ፡፡ አለቃ ቢጨንቃቸው ቤታቸውን ዘግተው ለልጃቸው ለተክሌ አስተማሩት፡፡ ተክሌ በአቋቋሙ መካኑን ሲያውቁ
ከእስልምና ወደ ክርስትና ተመልሰው የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንት በመብራት እየፈለጉ ወደሚሾሙት ወደ ወሎው ራስ
ሚካኤል ሀገር ላኩት፡፡

አለቃ ገብረ ሐና ደርቡሽ ጎንደርን ሲወርር ልጃቸውን ወደ ወሎ ልከው እርሳቸው ዘጌ ገዳም ገቡ፡፡ በኋላም ዐፄ ምኒልክ
ደርቡሽን ለመውጋት ወደ ፎገራ መምጣታቸወን ሲሰሙ ከተደበቁበት ወጥተው ንጉሡን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ
ተመለሱ፡፡ ምኒልክም እንደገና የራጉኤል አለቃ አደረገው ሾሟቸው፡፡ ልጃቸው ተክሌ ወሎ ንጉሥ ሚካኤል ዘንድ እያሉ
የተንታ ሚካኤል በዓል ሲከበር ከአባታቸው የተማሩትን ዝማሜ በተመስጦ አቀረቡት፡፡ ንጉሥ ሚካኤልም በዚህ ተደንቀው
በዚያው በተንታ እንዲያገለግሉ አደረጉ፡፡ የተክሌ ዝማሜ በይፋ የተጀመረው ያኔ ነው ይባላል፡፡ በኋላ ራስ ጉግሣ /1792 -
1818/ ዝናውን ሰምተው ንጉሥ ሚካኤልን በማስፈቀድ ወደ ደብረ ታቦር አምጥተው ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሾሟቸው፡፡

አለቃ ተክሌም በደብረ ታቦር ኢየሱስ ተቀምጠው ትምህርቱን አስፋፉት፡፡ በምስክርም አለቃ ብሬን፣ አለቃ መኮንንን፣ አለቃ
ዓለሙንና አለቃ ይትባረክን መርቀዋል፡፡ አለቃ ተክሌ ያረፉት ራስ ጉግሣ ወሌ በሌሉበት በመሆኑ ራስ ጉግሣ መርዶውን
ሲሰሙ «ምን ተክሌ ሞተ ትሉኛላችሁ፤ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ፈረሰ በሉኝ እንጂ፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ቢፈርስ አሁን ካለው
በበለጠ አድርጌ ልሠራው እችላለሁ ተክሌን ግን ከወዴት አገኘዋለሁ?» በማለት ተናግረዋል ይባላል፡፡ አልቃሽም፡

«ተክሌ ገብረ ሐና ተቀበረ ጣቱ


መንክረ ክስተቱን የዘመመበቱ»
                               ብላ ገጥማለች፡፡

ታላቁ ራስ ጉግሣ ደብረ ታቦር ኢየሱስን በጣም ስለሚወዱ «ላቂያዬ» ብለው ይጠሩት ነበር ይባላል፡፡ የደብሩንም አገልጋዮች
ብዛት ወደ 318 ከፍ እንዲል አድርገውት ነበር፡፡ በራስ ጉግሣ ወሌ ወደ 150 ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ የታላቁ ራስ ጉግሣ፣
የራስ ዓሊ፣የራስ ይማም፣የራስ ዶሪ፣ የራስ ማርዬ፣ የራስ እንግዳ፣ የንጉሥ ወልደ ጊዮርጊስ ባለቤት የወ/ሮ የሺ እመቤት ቀብር
የተፈጸመው እዚህ ነው፡፡

በ 15 ኛው አለቃ ዘመን ዐፄ ኃይለ ሥላሴ የደብሩ አለቃ «መልአከ ታቦር» ተብሎ እንዲጠራ ፈቀዱ፡፡ የተክሌ አቋቋም
ትምህርት ቤት በጥር አምስት ቀን 1993 ዓ.ም የአካባቢው ምእመናን፣ የሀገሩ ተወላጆችና በጎ አድራጊዎች ባደረጉት
አስተዋጽዖ በአዲስ መልክ ተሠርቶ ተመርቋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለአለቃ ተክሌ አንዳች መታሰቢያ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይም ብዙ በደከሙበት በደብረ ታቦር መንገድም
ይሁን ትምህርት ቤት፣ አደባባይም ይሁን ድልድይ በስማቸው መሰየም ይገባዋል፡፡

Posted by danielkibret at 5/20/2010 11:24:00 PM

2 comments:

KESDROS ZE MISRAK said...

It is so nice. I am sure most of us don't know this great person. But concerned bodies
should give emphasis for such peoples and give some memorial work in their name... D/n
Daniel i hope you will tell us something about TENTA MICHEAL in other time. I know
it is a great place with lots of spritual and cultural value around that area

May 21, 2010 12:38 AM

Anonymous said...

Dear Daniel

Thank you so much for sharing us that one enciant histrory of our church,

But I have one comment for you


"" «ተክሌ ገብረ ሐና ተቀበረ ጣቱ
መንክረ ከሰተን የዘመመበቱ»

May 21, 2010 6:56 AM

You might also like