You are on page 1of 9

ኒኮላ ቴስላ

አንድ ሰው ነበር ቴስላ የሚሉት…


(ግሩም ተበጀ)

ራዕዩን መቀበል ለተሳነው ዓለም በሕይወቱ የኋለኛው ዘመን ባሰፈረው ማስታወሻው ላይ፣ “ይህ ዘመን የናንተ ሊሆን ይችላል፣
መጪው ዘመን ግን የኔ ነው” ሲል ጽፏል…

እንደ እንከን አልባ ፈጠራዎቹ ሁሉ ይሄም ትንቢቱ መሬት ጠብ ያላለበት ይህ ታላቅ ሰው … በተለይም እ.አ.አ ከ1990ዎቹ
ወዲህ ጊዜው ደረሰ መሰል ዓለም ከእንቅልፉ ባንኖ ከስንት አንዴ ብቅ የሚል ታላቅ ሰው መሆኑን እየተረዳ መጥቷል፡፡
… በዚህ ታላቅ ሰው የሕይወት ታሪክ ዙሪያ የተጠናቀረ አንድ ዘጋቢ ፊልም የዚህ ሰው ጥፋት ምናልባትም ከጊዜው ቀድሞ
መወለዱ ነው ይላል…
በቢሊየን የሚቆጠር የዓለማችን ሕዝብ በየቀኑ እንደዋዛ ከሚጠቀምባቸው አብዛኞቹ የኤሌክትሪክና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች
ጀርባ የአንድ ሰው የፈጠራ ምናብ ገንኖ እንደሚወጣ ሲታሰብ አጀብ አያስብል ይሆን…

የዚህን ታላቅ ሰው ሥራዎች የገመገሙ ባለሞያዎች እንደሚሉት ግን ከሞተ 70 ያህል ዓመታት አልፈውትም እንኳ ለዓለማችን
ያለማቸውን ረቂቅ ቴክኖሎጂዎች ለመቀበል ዓለም ገና አሁንም ዝግጁ አይመስልም…

ዛሬ ታሪኩን በጥልቀት የምንዳስሰው ሰርቢያ - አሜሪካዊው አሌክትሪካል መሐንዲስና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ታላላቅ ፈጠራዎች
ባለቤት...
ኒኮላ ቴስላ !

ኒኮላ ቴስላ የተወለደው በያኔዋ ኦስትሮ - ሐንጋሪ በዛሬዋ ክሮሺያ ውስጥ ባለች ስሚሊጂን በተባለች መንደር ውስጥ እ.አ.አ
በ1856 ሐምሌ 9 ለ 10 አጥቢያ ከሌሊቱ 6 ሰዓት በመብረቅ ብርሃን በደመቀ ነጎድጓዳማ ሌሊት ነበር፡፡ ይሄው የልደት ጊዜው
ምልኪ ነው መሰል ቴስላ የመላ ሕይወቱ ሥራ በአጠቃላይ ከአሌክትሪክ ጋር የተቆራኘ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በፈጠራ መብት ባለቤትነት ከተመዘገቡለት 300 ያህል ፈጠራዎቹ አብዛኞቹ በአሌክትሪክ ዙሪያ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ
ሆኖም ግን ቴስላ ስለኤሌክትሪክ ምንም አላውቅም ባይ ነው፡፡
ስለ አሌክትሪክ ምንነት የሰው ልጅ ያወቀ 'ለት ያ ዕለት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ቀን ይሆናል
ሲል ጽፏል፡፡ በ17 ዓመቱ ኦስትሪያ፣ ግራትዝ ወደሚገኘው ፖሊቴክኒክ ገብቶ በወቅቱ ገና አዲስ ከነበረው የአሌክትሪክ ዓለም
ጋር የተዋወቀው ቴስላ በቤተ ሙከራ ውስጥ የማያት እያንዳንዷ የአሌክትሪክ ብልጭታ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥልቅ የማወቅ
ስሜቶችና የፈጠራ መነሳሳቶችን በአእምሮዬ ውስጥ ታጭር ነበር ሲል ያስታውሳል፡፡
ቴስላ አስገራሚ የማስታወስ ችሎታውንና የፈጠራ ክህሎቱን ከእናቱ እንደወረሰ ይናገራል፡፡ ደከመኝ የማያውቁት፣ ከውድቅት
እስከ ሌሊት ሲባትሉ የሚውሉት የቴስላ እናት ቴስላ እንደሚለው ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ በርካታ ሚካኒካዊ ቁሶችን
ፈብርከዋል፡፡ ቴስላ፣ እናቴ ዘመናዊ ትምህርት ብትቀስምማ ማንም የሚስተካከላት አይኖርም ነበር ይላል፡፡
ካህኑ የቴስላ አባትም ታዲያ የዋዛ ሰው አልነበሩም፡፡ ስብከታቸው የምዕመናኑን ልብ የሚያማልል የሚባልላቸው፣ ብሉይ
(Classic) የሥነ - ጽሁፍ ሥራዎችን በስፋት ያነበቡ … ኧረ እንዲያውም … በዚሁ ዙሪያ የማስታወስ ብቃታቸውን
አስመልክተው፣ ቴስላ፣ አባቱ በተለይም አንዳንድ ብሉይ የሥነ - ጽሁፍ ስራዎች ከምድር ገጽ ቢጠፉ እንኳ መልሼ እጽፋቸዋለሁ
ይሉ እንደነበር ጽፏል፡፡
እኒህ ካህን አባቱ ታዲያ ለዚህ ሳይንስና ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራ በልቡ ለጸነሰ ልጃቸው ከመጀመሪያው አንስቶ ያቀዱለት ሙያ
የራሳቸውኑ የቤተክህነት አገልጋይነት ነበር፡፡ ነፍሱ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂያው ፈጠራ የተሰጠው ታዳጊው ቴስላ ታዲያ ይህ
የታለመለት የሕይወት አቅጣጫ ከእሱ የውስጥ መሻት ጋር ስለማይጣጣም ሁሌ እንደተረበሸ ነው፡፡
ቴስላ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በተለይ በሒሳብ ትምህርት ክፍል የኢንቴግራል ካልኩለስ ጥያቄዎችን በጭንቅላቱ ሰርቶ
በመመለስ አስተማሪዎቹ አንዳች ማጭበርበሪያ የሚጠቀም እስኪመስላቸው ድረስ ያስደንቃቸው ነበር፡፡ ውስብስብ ሒሳባዊ
እና ቴክኒካዊ ሁነቶችን በጭንቅላቱ በጥልቀት በማስብ መከወን የቴስላ የፈጠራ ሕይወቱ ሁነኛ ሥልቱ ሆኖ እስከመጨረሻው
ዘልቋል፡፡
ቴስላ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ሳይንቲስትም ሆነ ኢንጂነር አንድን ነገር በተግባር ከመሥራቱ በፊት በምናቡ የሚሰራውን ሥራ
በተደጋጋሚ መላልሶ በማየት፣ በምናቡ በመሞከር፣ በመፈተሽ ስህተቶቹን አስተካክሎ ጨርሶ 100 % እርግጠኛ ሲሆን ብቻ
ነው ወደ ተግባራዊ ሥራው መሄድ ያለበት ሲል ይመክራል፡፡ በምናብ ያለው የፈጠራ እሳቤ ወይም ምስል ሳይዳብር ወደ ተግባር
መሮጥ በከንቱ ጉልበትን ከማባከኑም በላይ የምናብና የፈጠራ ብቃትን ያዶለዱማል ሲል ያስጠነቅቃል፡፡
ቴስላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እ.አ.አ በ1873 አጠናቅቆ ወደ ትውልድ መንደሩ እንደተመለሰ፣ አባቱ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ
ሊልኩት እየተዘጋጁ ባሉበት፣ በአደገኛ ሁኔታ በኮሌራ ተይዞ ለወራት የአልጋ ቁራኛ ሆነ፡፡ ሞት አፋፍ በደረሰው ልጃቸው ጉዳይ
የሚይዙ የሚጨብጡትን ያጡት አባት አንድ ቀን ተስፋ ቆርጠው ቴስላ ወደተኛበት ክፍል ሲገቡ፣
“ወደ ቴክኒክ ኮሌጅ ብትልከኝ እኮ እድን ነበር…” አልኳቸው ሲል ቴስላ ያስታውሳል፡፡
የዚህ በቴክኖሎጂያዊ ፈጠራ ፍቅር ልቡ የጠፋ ልጃቸው ክፉ ሕመም ቀልባቸውን የነሳቸው አባት እዚያው በዚያው፣
“አንተ ዳን እንጂ … አለ ወደተባለ ምርጥ የቴክኒክ ኮሌጅ ልኬ ነው የማስተምርህ” ሲሉ ተናገሩ፡፡
ቴስላ፣ “እነዚህን ቃላት ከአባቴ ስሰማ … ሁሉም ሰው ጉድ እስኪል ድረስ … እዚያው በዚያው … ድኜ ከአልጋዬ ተነሳሁ”
ይላል፡፡ በቃ ይኸው ነው ! አንተ ዳን እንጂ ወደ ቴክኒክ ኮሌጅ እልክሃለሁ የተባለው ሕመምተኛው ወጣት ልክ እንደ አልአዛር
እዚያው በዚያው ከሕመሜ ድኜ ተነሳሁ ይላል፡፡
ቴስላ ድኖ እንደተነሳ የኦስትሮ ሐንጋሪ ጦር ወጣቶችን ለተዋጊነት እያደነ የነበረበት ወቅት ነውና ከአደኑ ሽሽት ዓመት ያህል አዳኝ
መስሎ ጫካ ውስጥ ከራርሞ፣ ኋላ ላይ አሜሪካ ሲገባ የቅርብ ጓደኛው የሆነውን የማርክ ትዌይንንና የሌሎችንም ደራሲዎች
ሥራዎች ሲያነብ ቆይቶ፣ በጫካው ሕይወቱ አካልና መንፈሱን አጎልብቶ እ.አ.አ በ1875 ነጻ የትምህርት እድል አግኝቶ ኦስትሪያ፣
ግራትዝ ውስጥ ወዳለው የኦስትሪያ ፖሊ ቴክኒክ ተቋም ገባ፡፡
የሚያልመው የቴክኒክ ተቋም ውስጥ የገባውን ቴስላን ማን ይቻለው፡፡ በሁሉም ትምህርቶች ከፍተኛውን ውጤት አስመዘገበ፡፡
የጥናት ትጋቱን ያዩ አስተማሪዎቹ ይሄ ልጅ በዚሁ ከቀጠለ ለሕይወቱ ያሰጋዋል ሲሉ ለአባቱ ደብዳቤ ጻፉ፡፡ ቴስላ የእረፍት
ቀናትም ሆነ በዓላት ሳይገድቡት ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት አንስቶ ያለ እረፍት እስከ ምሽቱ 5፡00 ሳይታክት ይሰራ፣ ያነብ፣ ያጠና
ነበር፡፡
ቴስላ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ፣ ከፈጠራዎቹ ሁሉ በዘመናዊው የሰው ልጅ ስልጣኔ ላይ ወደር የለሽ ተጽእኖውን ያሳደረው
የታላቁ ፈጠራው ሐሳብ ተጠነሰሰ፡፡ ቴስላ በወቅቱ የነበሩትን የAC የኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮችን ፈጽሞ አዲስ በሆነ ስልት ማሻሻል
ይቻላል ሲል ለመምህሩ ለፕሮፌሰር ፖሽል ተናገረ፡፡ ቴስላ እንዴት አድርጎ እንደሚያሻሽለው ሐሳቡ አልመጣለትም፡፡ ብቻ ግን
በወቅቱ አለ የተባለው የAC ጄኔሬተር ጨርሶ መስተካከል እንደሚችልና እሱ ራሱም እንደሚያስተካክለው አምኗል፡፡ የቴስላን
ሐሳብ የሰሙት ፕሮፌሰሩ፣ “ቴስላ ታላላቅ ተግባራትን ማከናወን ይችል ይሆናል፤ ይሄን ያለው ግን መቼም ሊሆን የማይችል
ነው - ፈጽሞ !!” ሲሉ ለተማሪዎች ተናገሩ፡፡

የዚህ ጄኔሬተር እንደ አዲስ የማሻሻያ እንቆቅልሽ በነፍሱ የሚላወስበት ቴስላ በ2ኛ ዓመት ትምህርቱ ማብቂያ ግድም ግን የነጻ
ትምህርት እድሉ ተቋርጦ የወጣለት ቁማርተኛ ሆኖ አረፈው፡፡ በቀጣዩ ዓመት መላውን ለመኖሪያና ለትምህርት የተሰጠውን
ገንዘብ በቁማር ተበልቶ ባዶውን ቀረ፡፡ ቴስላ የሕይወት ታሪኩን ባሰፈረበት መጽሐፍ ላይ ይህን ጊዜ አንስቶ ሲጽፍ፣ …በዚሁ
የቁማር ሱስ ሳቢያ አባቱ ምን ያህል እንደተፀየፈውና፣ የማንኛውም ሰው መዳን በዚያው ሰው እጅ ውስጥ መሆኑን የምታውቀው
እናቱ ‘በቶሎ ያለንን ገንዘብ በሙሉ በቁማር ተበልተህ ብታጠናቅቀው ይሻለናል’ ብላ የቤተሰቡን የመጨረሻ ጥሪት
እንደሰጠችው ያወሳል፡፡

በዚህ ገንዘብ “የተበላሁትን ገንዘብ ካስመለስኩ በኋላ እዚያው በዚያው ይሄንን የቁማር ሱሴን ቆርጬ ጣልኩት” ይላል፡፡ …
የሲጋራ ሱሴንም ልክ እንደዚሁ ነው ከላዬ ላይ ቆርጬ የጣልኩት የሚለው ቴስላ፣ ሌሎች ሰዎች ሱሳቸውን ርግፍ አድርገው
ሲተዉ እንደሚሆኑት ፍላጎትን የመሰዋት ሳይሆን ሱሶቼን አሽቀንጥሬ መጣሌ አንዳች ኃይልም አጎናፅፎኛል ይላል፡፡ ልቤን
ሲያደክማት ታዝቤ ያቆምኩት ቡና ብቻ አስቸግሮኝ ነበር ሲል ፅፏል፡፡
ቴስላ ከዚህ በኋላ አስቸጋሪ ጊዜ አሳለፈ፡፡ የፖሊ ቴክኒክ ተቋም ትምህርቱን አቋረጠ፡፡
ትምህርቱን ማቋረጡን ቤተሰቦቹ እንዳይሰሙ በመስጋት ከቤተሰቦቹ ጋር ያለውን ግንኙነት አቋረጠ፡፡ ሌላ ዩኒቨርሲቲ እንዲገባ
ሁለት አጎቶቹ በቂ ገንዘብ አዋጥተው ቢሰጡትም በተለያዩ ምክንያቶች በዛ ዩኒቨርሲቲ መቀጠል ሳይችል ቀረ፡፡
በመቀጠል፣ እ.አ.አ በ1881፣ ቤተሰቦቼ ለእኔ ሲሉ ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል እናም ሸክማቸውን ቀለል ላድርግላቸው በሚል
ቴስላ ቡዳፔስት፣ ሐንጋሪ ሄዶ እዚያ ያለ የቴሌግራፍ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠረ፡፡ የቀጣሪውን ድርጅት አለ የተባሉትን
የኤሌክትሪክና ቴሌግራፍ ቁሳቁሶች ሁሉ ጠጋገነ፣ በፈጠራ መብት ባለቤትነት ያላስመዘገባቸውን ሁለት ወሳኝ የስልክ ቴክኖሎጂ
ቁሳቁሶችን ፈበረከ፡፡

ቴስላ እዚህ እያለ አደገኛ የሆነ የነርቭና የአንጎል ነውጥ (Nervous Breakdown) አጋጠመው፡፡ ይህን ፈፅሞ አገግሜ ይሻለኛል
ብሎ ያልገመተውን ሕመሙን አስመልክቶ በግለ ታሪኩ ላይ ያሰፈረው እንዲህ ይላል፣ “ከልጅነቴ አንስቶ የስሜት ሕዋሳቶቼ
ንቃት … የማየትና የመስማት ብቃቴ እጅጉን የሰላ ነበር፡፡ ሰዎች ከርቀት የማያዩትን ነገር አያለሁ፡፡
ልጅ ሳለሁ፣ የእሳት ቃጠሎ ገና ሲጀምር ያለውን አብዛኛው ሰው ሊሰማው የማይችለውን አነስተኛ ድምጽ ሰምቼ በርካታ ጊዜያት
በውድቅት ሌሊት ጎረቤቶቻችንን ከእሳት አደጋ ታድጌለሁ … በዚህ የሕመሜ ወቅት ያጋጠመኝ የስሜት ሕዋሳቶቼ ንቃት ግን
ከዛኛው በብዙ እጥፍ የበለጠ ነበር ! ቤት ውስጥ ተቀምጬ ከሦስት ክፍሎች አልፎ ባለው ቤት ውስጥ ያለው የግድግዳ ሰዓት
የሰከንድ ቆጣሪ ድምጽ በጉልህ ይሰማኛል፡፡ በኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ያለ ሰረገላ ሲጓዝ የሚያሰማው ንዝረት እኔን ቤት ውስጥ
ተቀምጬ ይነዝረኛል፡፡

በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚጓዝ ባቡር ንዝረት ሳቢያ አልጋዬ በጣሙን ሲርድ ይሰማኛል፡፡ … በጨለማ ውስጥ የስሜቴ
ንቃት የሌሊት ወፍን ያህል ሆነ፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከ4 ሜትር ርቀት ላይ ግድግዳ መኖሩን በዓይኖቼ መሐል ግንባሬ
ላይ በሚሰማኝ ስሜት አማካኝነት ማወቅ እችላለሁ፡፡”
ቴስላ ከዚህ እንግዳ የሆነ የነርቭና የአንጎል መዋዠቅ ቀስ በቀስ እያገገመ መጣ፡፡

በዚህ ወቅት፣ አንዲት ዕለት አመሻሽ ላይ፣ ከአንድ ጓደኛው ጋር በከተማዋ ፓርክ ውስጥ በሚናፈሱበት ጊዜ … በቃሉ
ከሚያውቀው የጀርመናዊው ባለቅኔ የገተ ዝነኛ ድርሰት ከሆነው ፎስት ውስጥ ያሉትን ተወዳጅ የግጥም ሐረጎች በቃሉ ሲያነበንብ
የፖሊ ቴክኒክ 2ኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ሊፈታው ያሰበው የAC ሞተርን የማሻሻል እንቆቅልሽ መልስ እንደ አንዳች ራዕይ በምናቡ
ላይ ወረደ፡፡ ቴስላ፣ ወዲያውኑ በእንጨት አሸዋው ላይ በምናቡ የመጣለትን የተሻሻለውን የAC ሞተሩን ገፅታ ስሎ ለጓደኛው፣
“ተመልከት … ሞተሬን ተመልከት” አልኩት ይላል፡፡

ይህ ፈጠራ በዘመናዊው ዓለም ላይ ጉልህ ተጽእኖ ካሳደሩ ታላላቅ ፈጠራዎች ሁሉ በግንባር ቀደምትነት ይነሳል፡፡
በቀጣዩ ዓመት ቴስላ ፈረንሳይ፣ ፓሪስ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካዊው የበርካታ ፈጠራዎች ባለቤት የቶማስ ኤዲሰን ኩባንያ
የሆነው Continental Edison Company ውስጥ ተቀጠረ፡፡ በዚሁ የፓሪስ ቆይታው የኩባንያውን የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች
እንደ አዲስ ሲያሻሽል ቆይቶ የፓሪሱ የኤዲሰን ኩባንያ ኃላፊ ቻርለስ ባችለር ያንተ ዓይነቱ ባለ ብሩህ አእምሮ (Genius) ቦታው
እዚህ ሳይሆን እዚያው ኤዲሰን ጋር አሜሪካ ነው ብሎ ለኤዲሰን የሚሰጥ ደብዳቤ አስይዞ ኒውዮርክ ያለው የኤዲሰን ኩባንያ
ውስጥ ይሰራ ዘንድ ወደ አሜሪካ ሰደደው፡፡

ባችለር በቴስላ አስይዞ ለኤዲሰን የላከው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፣ “ውድ ኤዲሰን፣ ሁለት ታላላቅ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ አንደኛው
አንተ ነህ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ይህ ወጣት ነው፡፡” ኤዲሰን ያለምንም ማቅማማት፣ ይህን ቤሳ ቤስቲን ሳይዝ ለፈጠራ የነደደ ልቡን
ይዞ አሜሪካ የገባውን ወጣት ወዲያውኑ ቀጠረው፡፡

ቴስላ ወደ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊት … በጀርመንና በፈረንሳይ ሳለ … የAC ጄኔሬተሩን ለማምረት የሚረዳው ድርጅት
ወይም ባለሐብት ፈልጎ ለማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ እነሆ አሁን ግን አሜሪካ ገብቶ በሚያደንቀው በቶማስ ኤዲሰን ድርጅት
ውስጥ ተቀጥሯልና … የAC ጄኔሬተሩን ለማምረት ይረዳው ዘንድ ቴስላ በታላቅ ጉጉት የAC ጄኔሬተር ፈጠራውን ለኤዲሰን
አሳየው፡፡

ኤዲሰን ግን ይሄን የቴስላን ፈጠራ ጨርሶ አልወደደውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኤዲሰን ከጥቂት አመታት በፊት አንስቶ በራሱ
የDC የኤሌክትሪክ ጄኔሬተሮች አማካኝነት ለኒውዮርክ ከተማ ኤሌክትሪክ እያመረተ በማቅረብ ላይ በመሆኑና ይህ የቴስላ
ፈጠራ ተቀናቃኝ የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ነው፡፡

ምንም እንኳ የቴስላ AC ጄኔሬተር ከኤዲሰን የDC ጄኔሬተር እጅጉን የተሻለ ቢሆንም የገነባውን ቢዝነስ የሚያፈርስበትን ይህን
የቴስላን ፈጠራ መቀበል ለኤዲሰን ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ ይልቁንም ኤዲሰን የራሱን የDC ጄኔሬተሮች ቴስላ
እንዲያሻሽልለት ፈልጓል፡፡ “የDC ጄኔሬተሮቼን ካሻሻልክልኝ 50 000 ዶላር እከፍልሃለሁ” አለኝ የሚለው ቴስላ፣ ከጠዋቱ 4፡
30 እስከ ቀጣዩ ቀን ንጋት 11፡00 ሰዓት … በአጠቃላይ በቀን ከ19 ሰዓት በላይ እየሰራ የኤዲሰንን የDC ጄኔሬተሮች ካሻሻለለት
በኋላ ክፍያውን ሲጠይቅ የኤዲሰን ምላሽ፣ ‘አይ ቴስላ … ለካንስ የእኛን የአሜሪካኖች ቀልድ አታውቅምና…’ የሚል ስላቅ
ሆነ፡፡

ኤዲሰን በ50 000 ዶላሩ ፋንታ ደሞዝህን ልጨምርልህ ቢለውም በጉዳዩ የበሸቀው ቴስላ አንዳችም ቃል ሳይተነፍስ ባዶ እጁን
ከኤዲሰን ድርጅት ለቅቆ ወጣ፡፡ ከዚህ በኋላ ቴስላና ኤዲሰን ክፉኛ የሚጠላሉ ቀንደኛ ተቀናቃኞች ሆኑ፡፡ እ.አ.አ በ1931፣
ቶማስ ኤዲሰን ሲሞት ሁሉም ማለት ይቻላል ስለታላቁ ሳይንቲስት በጎ ቃላት ተናግረዋል - ከአንድ ሰው በስተቀር … ቴስላ!
የኤዲሰንን ሞት አስመልክቶ በኒውዮርክ ታይምስ ላይ የሰፈረው ሰፊ ዘገባ ቴስላ ስለ ኤዲሰን የተናገረውን ይዞ ወጥቷል፡፡
ቴስላ፣ ስለ ኤዲሰን እንዲህ ሲል ተናግሯል፣ “…አንዳችም የትርፍ ጊዜ መዝናኛ hobby የሌለው፣ ንጽሕናውን እንኳ
የማይጠብቅ … የፈጠራ ስልቱም በጣሙን ኋላቀርና በአታካች ሙከራ የተሞላ ከመሆኑ የተነሳ ግኝቶቹ በአብዛኛው በአጋጣሚ
የሚገኙ ተራ የእድል ውጤቶች ናቸው፡፡ ጥቂት ንድፈ ሐሳብና ሒሳብ ቢጠቀም ኖሮ 90 % ልፋቱ ይቀርለት እንደነበር ስታዘብ
ያሳዝነኝ ነበር…” ከኤዲሰን ጋር ተጣልቶ ባዶ እጁን ከሥራው ለቅቆ የወጣው ቴስላ በቀጣይ ጊዜያት በርካታ ውጣ ውረዶችን
አሳለፈ፡፡ ለዕለት ጉርሱ ሲል በቀላል የኤሌክትሪክ ጥገናና በጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች ውስጥ ተሰማራ፡፡ ቴስላ፣ እነዚህን ጊዜያት
የመራር እንባና የመከራ ጊዜያት ነበሩ ሲል ጽፏል፡፡
ቀስ በቀስ ቴስላ እያንሰራራ መጣ !

በሽርክና ከሌሎች ሰዎች ጋር ኩባንያ አቋቋመ፡፡ ቤተ ሙከራ ከፈተ፡፡ የAC ጄኔሬተሩን በናሙና መልክ ሰራ፡፡ የAC ጄኔሬተሩን
ብቃት የተገነዘቡ የኤሌክትሪክ መሐንዲሶች ጆርጅ ዌስቲንግሐውስ የተባለው የWestinghouse Electric and
Manufacturing Company ባለቤት የቴስላን የAC ጄኔሬተር የፈጠራ መብት (ፓተንት) እጁ እንዲያስገባ መከሩት፡፡
ኩባንያው የቴስላን የAC ጄኔሬተርና ተዛማጅ የፈጠራ መብቶች በ1 ሚሊየን ዶላር ክፍያና ኩባንያው የሚያመርታቸው የAC
ጄኔሬተሮች ከሚያመርቱት ከእያንዳንዱ የፈረስ ጉልበት 2.5 ዶላር ቴስላ እንዲከፈለው ተዋዋሉ፡፡
ቴስላ … አሁን ሕልሙ የሰመረለት ባለፀጋ ሆኗል … ለሌሎች ታላላቅ ፈጠራዎቹ የሚሆን ጥሪትም ቋጥሯል……ይህንኑ
ተከትሎ ግን አንድ አስገራሚ ጦርነት ተቀሰቀሰ…ይህ ጦርነት የኮረንቲዎቹ ጦርነት (War of currents) ይሰኛል...
…ለመሆኑ ይሄ የኮረንቲዎቹ ጦርነት ምን ይሆን ? ተፋላሚዎቹስ እነማን ይሆኑ ? አሸናፊውስ?

የኮረንቲዎቹ ጦርነት (War of currents)…

ከቶማስ ኤዲሰን የDC የኤሌክትሪክ ማመንጪያና ማሰራጫ ስርዓት የተለየውን የቴስላን የAC የኤሌክትሪክ ማመንጪያና
ማሰራጪያ ሥርዓት ሊተገብር የተነሳው ዌስቲንግሐውስ፣ ከቶማስ ኤዲሰን ኩባንያ ጋር የየኔ ቴክኖሎጂ ይበልጣል የመረረ ቅራኔ
ውስጥ ገባ፡፡ በመጨረሻ … በአሁኑ ወቅት በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘው የቴስላ የAC የኤሌክትሪክ ማመንጪያና
ማስተላለፍያ ስርዓት አሸናፊ ሆኖ እስኪወጣ ድረስ የቴስላና የኤዲሰን የኤሌክትሪክ ቴክኖሎጂ ስርዓቶችን በባለቤትነት የያዙት
ኩባንያዎች ቢዝነሳቸውን ላለማጣት ታላቅ ትንቅንቅ ገጠሙ፡፡ … ይህ ትንቅንቅ የኮረንቲዎቹ ጦርነት (War of currents)
በሚል ይታወቃል፡፡

ኤዲሰን የተቀናቃኙን የቴስላን የAC የኤሌክትሪክ ማመንጪያና ማሰራጪያ ሥርዓት ለማጣጣል ከፍተኛ የሚዲያና የቅስቀሳ
ዘመቻውን አጧጧፈው፡፡ የቴስላ የAC ሥርዓት ለሕይወት አደገኛ ነው፣ የሚያመነጨው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ቮልትም
ሕይወትን ያጠፋል በማለት ኤዲሰንና ረዳቶቹ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አደባባዮች የተለያዩ እንስሳትን (ውሻ፣ ፈረስ … ዝሆን
ጭምር) መግደሉት ተያያዙት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.አ.አ በ1893 በቺካጎ የተካሄደውን የዓለም የንግድ ትርዒት በኤሌክትሪክ ብርሃን ለማድመቅ የወጣውን
ጨረታ የቴስላን የAC ሞተሮች የፈጠራ መብት የገዛው ዌስቲንግሐውስ ኤሌክትሪክ አሸነፈ፡፡
ቴስላ፣ ይህ ክስተት የፈጠራውን ብቃት የማሳያ ሁነኛ አጋጣሚ መሆኑን ተረድቶታል፡፡ በጨረታው መሸነፉ ያንገበገበው
የኤዲሰንን ኩባንያ አዋሕዶ ግዙፍ ኩባንያ የሆነው General Electric ኩባንያ የኤዲሰንን በግለት የሚሰሩ የኢንካንዲሰንት
አምፖሎች ለዌስቲንግሐውስ አልሸጥም አለ፡፡ ሁኔታውን የተረዳው ቴስላ ችግሩን በቶሎ ለመቅረፍ ከኤዲሰን የተለየና የተሻለ
ሌላ ዓይነት የአምፖል ፈጠራውን ይዞ በጊዜ ለንግድ ትርዒቱ ለመድረስ በቃ፡፡

የንግድ ትርዒቱን የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መርቀው ሲከፍቱት የቴስላ የAC ሥርዓት ብቃት በጉልህ ታየ…
በዚሁ ስኬቱ ሳቢያ ከናያጋራ ፏፏቴ ኃይል አመንጭቶ የማከፋፈል ኮንትራት የቴስላን የACና ተዛማጅ ፓተንቶች ለገዛው
ለዌስቲንግሐውስ ኤሌክትሪክ ተሰጠው፡፡ የቴስላ ሥርዓት በተሳካ ሁኔታ ከናያጋራ ፏፏቴ ኃይል አመንጭቶ ማከፋፈል ጀመረ፡
፡ በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ጥቅም ላይ የዋለው የኤሌክትሪክ ማመንጪያና ማከፋፈያ ሥርዓት መነሾው ይህ በናያጋራ
እውን የሆነው የቴስላ የAC የኤሌክትሪክ ማመንጪያና ማከፋፈያ ሥርዓት ነው፡፡ በዚሁ … በቴስላ የAC እና በኤዲሰን የDC
የኤሌክትሪክ ማመንጪያና ማከፋፈያ ሥርዓቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው የየኔ ሥርዓት ይበልጣል የኮረንቲዎቹ ጦርነት አሸናፊ
ማን እንደሆነ ታወቀ - የቴስላ የAC ሥርዓት በድል አድራጊነት በላጭ ሆኖ ወጣ፡፡
ይህ ድል ግን ለአሸናፊው ለዌስቲንግሐውስ ኤሌክትሪክ መራር ጣፋጭ ድል ሆነ፡፡ በሁለቱ የኤሌክትሪክ ሥርዓቶች መካከል
በተነሳው የኮረንቲዎቹ ጦርነት እና በሌሎችም ወጪዎች ሳቢያ ዌስቲንግሐውስ ኤሌክትሪክ የፋይናንስ አቅሙ ክፉኛ ተዳክሟል፡
፡ ስለዚህም ዌስቲንግሐውሶች የACውን ፈጣሪ ቴስላን፣ ኩባንያው እንዳይከስር ከፈለግክ በአንድ የAC ሞተር የፈረስ ጉልበት
ልንከፍልህ የተስማማነውን የ2.5 ዶላር ክፍያ ተውልን ሲሉ ጠየቁት፡፡
ቴስላ ይህን የAC ሞተሩን እውን ለማድረግ የረዳውን ኩባንያ ለመታደግ በፈረስ ጉልበት 2.5 ዶላር ክፍያ የሚያስገኘውን
የኮንትራት ውሉን ቀደደው፡፡

ዓለም ዛሬ ላይ ቴስላን የሚያስታውሰው በአብዛኛው በዚህ የAC ሞተር ፈጠራው ይሁን እንጂ ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው
ፈጠራዎች ባለቤትም ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ጥቂት የማይባሉት የቴስላ ፈጠራዎች በሌሎች ተሞጭልፈው የሌሎች እንደሆኑ
ተደርገው ሲነገሩ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

x-rayን አገኘ በሚል እ.አ.አ በ1901 በፊዚክስ የመጀመሪያውን የኖቤል ሽልማት የተሸለመው ጀርመናዊው ዊልሄልም
ሮንትንገን x-rayን ከማግኘቱ ከ8 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1887 ቴስላ በx-ray ጨረሮች ፎቶግራፍ አንስቷል፡፡
እ.አ.አ በ1893ቱ የቺካጎ የዓለም የንግድ ትርዒት ወቅት ደግሞ በጊዜው ከነበረው ከኤዲሰን የኢንካንዲሰንት አምፖል አንጻር
አነስተኛ ኃይል የሚወስደውን፣ ረጅም ጊዜ ሳይበላሽ የሚቆየውን፣ የበለጠ ብርሃናማ የሆነውንና ኃይል ቆጣቢ የሆነውን
ለዘመናችን የፍሎረሰንት አምፖሎች እንደመጠንሰሻ ተደርጎ የሚቆጠረውን የፎቶፎስፈረሰንስ አምፖል ፈጠራውን ለዓለም
አበረክቷል፡፡

ከዚህ ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ እ.አ.አ በ1891 ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የአሜሪካ የኤሌክትሪክ
መሐንዲሶች ኢንስቲትዩት ጉባዔ ላይ ቴስላ ከአንዳችም የኤሌክትሪክ ገመድ ጋር ያልተያያዙ ሁለት የፎቶፎስፈረሰንስ
አምፖሎችን በሁለት እጆቹ በመያዝ ሲበሩ አሳይቶ ታዳሚውን ጉድ አስብሏል፡፡ ይህ ገመድ አልባ በሆነ መልኩ የኤሌክትሪክ
አምፖሎችን የማብራት ጉዳይ፣ ለጊዜው የኤሌክትሪክ መሐንዲሶች ጭምር ምትሃት እንጂ የቴክኖሎጂ ብቃት አይመስልም ነበር፡
፡ እ.አ.አ በ1898 ቴስላ አነስተኛ በእጅ የምትያዝ የመሬት መንቀጥቀጥ የምትፈጥር መሳሪያ ፈብርኳል፡፡ በዚያው ዓመት በዛን
ዘመን ፈፅሞ የማይገመተውን በርቀት መቆጣጠሪያ (Remote Control) የምትንቀሳቀስ አነስተኛ ጀልባ ሰርቶ አጅብ አስብሏል፡
፡ እ.አ.አ በ1901 የፀሐይንና ከሕዋ የሚመጡ ጨረሮችን ተቀብሎ ወደ ሌላ ኃይል የሚለውጥ ፈጠራውን በፈጠራ ባለመብትነት
ያዝመዘገበው ቴስላ፣ እ.አ.አ በ1917፣ ማለትም ከራዳር
መፈጠር 17 ዓመታት ቀደም ብሎ የራዳርን አሰራር
አመላክቷል፡፡
እኒህ ሁሉ ፈጠራዎች ግን ቴስላ ሊያሳካ ከሚሻው ከአንድ
የቴክኖሎጂ ሕልሙ አንጻር ምንም ማለት አይደሉም፡፡
በተለይም ከAC የኤሌክትሪክ ሥርዓቱ መተግበር ስኬት
በኋላ የቴስላ የቀን ተሌት ሐሳቡ ይህ ነው - የኤሌክትሪክ
ኃይልን ያለ ገመድ ከቦታ ቦታ ማስተላለፍ ! ይህን በዚህ
በኛ ዘመን እንኳ ለማሳካት ፈታኝ የሆነውን ቴክኖሎጂያዊ
ሁነት ማሳካት ይቻላል ባዩ ቴስላ በዚህ ዙሪያ ምርምሩን
ለማካሄድ ከኒውዮርክ ወደ ኮሎራዶ ያቀናው እ.አ.አ
በ1899 ነበር፡፡
በኮሎራዶ ቆይታው ቴስላ ቤተ ሙከራና ረጅም ማማ
በመገንባት መሬትንና የከባቢ አየርን ኤሌክትሪክ
አስተላላፊ ክፍል በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይልን ያለ
ገመድ ረጅም ርቀት ማስተላለፍ የሚቻልበትን መንገድ
ሲያጠና ከረመ፡፡ ከ1 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ርቀት ላይ
የተቀመጠን አምፖል ከኤሌክትሪክ ገመድ ጋር ሳይገናኝ
ማብራት ቻለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ቴስላ፣ ከምድር
ውጪ ካሉ ፍጡራን የተላከ ነው ያለውን እንግዳ የሆነ
የሬዲዮ ሞገድ መቀበሉን ተናገረ፡፡ አሁን ላይ …
ሳይንቲስቶች ቴስላ ከሕዋ አካላት የሚለቀቅ የሬዲዮ ሞገድን በመቀበል የመጀመሪያው ሰው ሳይሆን አይቀርም ባይ ናቸው፡፡
ቴስላ፣ ከኮሎራዶ ሙከራው የኤሌክትሪክ ኃይል ያለ ገመድ ረጅም ርቀት ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ማስተላለፍ ይቻላል
የሚለው መላ ምቱ እንደሚሰራ ተረድቷል፡፡ መረዳቱን በገቢር ለማረጋገጥ ግን ከኮሎራዶው የበለጠ ግዙፍ ማማና የኤሌክትሪክ
ሙሌት ተሸካሚ ድፍን የብረት ጉልላት መገንባት እንዳለበት ተገንዝቧል፡፡ ይህንኑ ለመተግበር እ.አ.አ በ1900 ወደ ኒውዮርክ
ተመልሶ ዋርደንክሊፍ የተባለ 54 ሜትር ርዝመት ያለው ግዙፍ ማማ ማስገንባት ጀመረ፡፡
በዚሁ ማማ አማካኝነት በመላው ዓለም የፅሁፍ መልዕክት፣ ድምፅና ምስሎች መላክ እንደሚቻል ይህም በሚሊዮኖች ዶላር
የሚቆጠር ትርፍ እንደሚያስገኝ ከቴስላ የሰማው ጄ ፒ ሞርጋን የተባለው ባለሐብት ከትርፉ ለመቋደስ በማሰብ 150 000 ዶላር
ለፕሮጀክቱ አዋጣ፡፡

አናቱ ላይ 55 ቶን የሚመዝን ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ብረት ጉብ ያለበት የዚህ ግዙፍ ማማ ግንባታ ግን ቴክኒካዊ እክሎች
ያጋጥሙት ጀመር፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ እ.አ.አ በዴሴምበር 12፣ 1901 ጉግሎኒ ማርኮኒ አንዲት የእንግሊዝኛ ፊደል የያዘች
የቴሌግራፍ መልዕክት በገመድ አልባ ስልት አትላንቲክን አሻግሮ የመላኩ ዜና ተሰማ፡፡

እዚህጋ ማርኮኒ ገመድ አልባ የቴሌግራፍ መልዕክቱን ለመላክ 17 የተመዘገቡ የቴስላን ፈጠራዎች መጠቀሙን ልብ ይሏል፡፡
ዜናው የደረሰው ቴስላ … ማርኮኒ በእሱ ፈጠራዎች ላይ ተመርኩዞ መሥራቱን ጠቅሶ፣ ማርኮኒ በሥራው ቢቀጥል ተቃውሞ
እንደሌለው ገለፀ፡፡ የቴስላ ፈጠራ ዕውን ሲሆን ሚሊየን ዶላር አፍሳለሁ በሚል ተስፋ 150 000 ዶላር ለቴስላ የሰጠው ጄ ፒ
ሞርጋን ግን ይህን ጉዳይ በዋዛ የሚያልፈው አልሆነም፡፡

ጄ ፒ ሞርጋን፣ “ይሄው ማርኮኒ ገመድ አልባ የቴሌግራፍ መልዕክት ላከ … አንተ ያልከኝ ገመድ አልባ መልዕክት፣ ድምፅና
ምስል መላኪያ የት አለ ?” ሲል ቴስላን አፋጠጠው፡፡ ይሄኔ ቴስላ የሚገነባው ሰማይ ጠቀስ ማማ እውነተኛ ዓላማ ለመናገር
ተገደደ፡፡ ቴስላ ለሞርጋን፣ “እየገነባሁት ያለሁት ማማ ዓላማ ተራ መልዕክትና ምስል መላኪያ ሳይሆን ከፍተኛ መጠን ያለው ነጻ
የኤሌክትሪክ ኃይል በመላው ዓለም ማስተላለፍ ነው” ሲል እውነታውን አፈረጠው፡፡
የቴስላ ሕልም እንደሰማይ የራቀበት ሞርጋን፣ አንዴ የከሰርኩትን ከስሬያለሁ ብሎ ይመስላል ፊቱን ከቴስላ ወደ ማርኮኒ አዙሮ
የማርኮኒን የገመድ አልባ ቴሌግራፍ ፈጠራ በገንዘብ መደገፍ ጀመረ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ተጨማሪ ገንዘብ ለቴስላ
የዋርደንክሊፍ ማማ ግንባታ እንዲሰጥ የተጠየቀው ሞርጋን ከዚህ በኋላ ሰባራ ሳንቲም አልሰጥም ሲል መለሰ፡፡
ቴስላ የሕይወቱ ታላቅ ግብ የሆነውን ይህን ፈጠራውን እውን ማድረጊያ ተጨማሪ ገንዘብ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ከAC ሞተሩና
ተዛማጅ የፈጠራ መብቶች ሽያጭ ያገኘው ገንዘብም በዚሁ ማማ ግንባታና ለሙከራው ማካሄጃ ወጪ ሆኖ ተሟጠጠ፡፡
በስተመጨረሻ፣ እ.አ.አ በ1904 በገንዘብ ድጋፍ እጥረት ቴስላ በማማው ላይ የሚያደርገውን ሙከራ ሙሉ ለሙሉ ለማቋጥ
ተገደደ፡፡ ከዓመታት በኋላ … ቴስላ ሙከራውን ለማካሄጃ የተበደረውን ብድር ለመክፈል የማማው ብረት እየተነቃቀለ ተሸጠ፡

በዚህም ታላቁ የፈጠራ ሰው ለዓለም ሊያበረክተው ያሰበው ረቂቅ ራዕዩ እንደ ጉም በነነ፡፡ ይህን በከንቱ ተደናቅፎ የቀረ ታላቅ
ሕልሙን አስመልክቶ ቴስላ፣ “…ይሄ እኮ ሕልም አይደለም …ይሄ እኮ ቀላል፣ ሳይንሳዊ የኤሌክትሪክ ምህንድስና ውጤት
ነው …ይህ ተጠራጣሪ፣ ድንጉጥና የታወረ ዓለም” ሲል ቁጭቱን ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የገመድ አልባ ቴሌግራፍ ፈጠራውን አሜሪካ ውስጥ በፈጠራ መብት ባለቤትነት ለማስመዝገብ ጥያቄ
አቅርቦ ቀድሞ ከተመዘገበው የቴስላ ፈጠራ ጋር ተመሳሳይ ነው በሚል ውድቅ ሆኖበት የነበረው ማርኮኒ እ.አ.አ በ1904
ተሳካለት፡፡ የአሜሪካው የፓተንት ቢሮ የቀድሞ ውሳኔውን ሽሮ የቴስላን ፈጠራዎች በመኮረጅ የተሰራውን የማርኮኒን ሥራ
መዘገበው፡፡ ከዚህ በኋላ እንኳንስ የፈጠራ ሐሳቡን መተግበሪያ ገንዘብ ቀርቶ ኑሮውንም በወጉ የሚደጉምበት ገንዘብ ያልነበረው
ቴስላ፣ ከሰው ተነጠለ፡፡ ቴስላ ከዚህ ጊዜ በኋላ በአብዛኛው የሚታየው እውነተኛ፣ ታማኝ ጓደኞቼ ናቸው የሚላቸውን እርግቦች
ሲመግብ ነበር፡፡

ጭራሽ እ.አ.አ በ1909፣ የቴስላ ፈጠራዎችን በመኮረጅ ገመድ አልባ የቴሌግራፍ መልዕክት መላክ ለቻለው ለጉግሎኒ ማርኮኒ
የፊዚክስ የኖቤል ሽልማት ሲሰጥ፣ ቴስላ በሸቀ፡፡ የጉዳዩ ምፀት ያለው ደግሞ እዚሁ ላይ ነው … እ.አ.አ በ1943፣ ቴስላ ከሞተ
ከ5 ወራት በኋላ፣ የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማርኮኒ ሥም ተመዝግቦ የነበረውንና ኖቤል ሽልማት የተሸለመበትን የሬድዮ
ፈጠራ መብት ሰርዞ የሬድዮ እውነተኛው ፈጣሪ ቴስላ ነው ሲል ብይኑን ይፋ አደረገ፡፡
የገንዘብ ችግር የፀናበት ቴስላ፣ ከማርኮኒ ኩባንያ አይነት ግዙፍ ኩባንያ ጋር የሕግ እሰጣገባ ውስጥ መግባት ትርፉ ድካም መሆኑን
ሲረዳ ተወው እንጂ፣ ማርኮኒ ፈጠራዬን ሰርቋል በሚል በፍርድ ቤት ክስ መስርቶም ነበር…ከጥቂት ዓመታት በኋላ … አንድ
ጋዜጣ ታላቁ ሳይንቲስት ኒኮላ ቴስላ የ935 ዶላር ታክስ አልከፈልክም በሚል ፍርድ ቤት መቅረቡን የሚገልጽ ዘገባ ይዞ ወጣ፡፡
ቴስላ በቃለ መሐላ ለፍርድ ቤቱ አንዳችም ገንዘብ እንደሌለውና ለዓመታት በብድር የሚኖርበትን ሆቴል ክፍያም እንዳልከፈለ
ተናገረ፡፡
ሁኔታውን የተረዳው የአሜሪካ የኤሌክትሪክ መሐንዲሶች ኢንስቲትዩት የተከበረውን የኤዲሰን ሜዳልያ ሊሸልመው ጥሪ
አቀረበለት፡፡ ቴስላ ግን በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ምሽት አልተገኘም፡፡ በዛን ምሽት ቴስላ በኒውዮርክ የሕዝብ ቤተመጻህፍት
አካባቢ እርግቦችን እየመገበ ነበር፡፡ ሸላሚዎቹ የዛኑ ምሽት እርግብ ከሚመግብበት ቦታ አግባብተው አምጥተው ሽልማቱን
አበረከቱለት፡፡ በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ ቴስላ የኤሌክትሪክ ኃይል ያለ ገመድ ማስተላለፍ የሚያስችለውንና የፀሐይን ብርሃን
ወደ ኃይል የሚቀይር ፈጠራውን ማጠናቀቁን ለታዳሚው ተናገረ፡፡

እ.አ.አ በ1934 ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ቴስላ በኮሎራዶ ቆይታው የሞት ጨረር (Death ray) የተባለ አደገኛ የጦር መሳሪያ
መሥራቱን የሚገልጽ ዘገባ ይዞ ወጣ፡፡ ዘገባው፣ የጦር መሳሪያው በ400 ኪሎ ሜትሮች ክልል ውስጥ የሚገኙ የጠላት
ወታደሮችንና አውሮፕላኖችን ዶግ አመድ እንደሚያደርግ ይገልጻል፡፡ ቴስላ በዘገባው ላይ ምንም ምላሽ አልሰጠም፡፡
… ወቅቱ የአልበርት አይንስታይን ዝና እጅጉን የገነነበት ጊዜ ነበር፡፡ ቴስላ የአይንስታይንን ሳይንሳዊ ስኬት አስመልክቶ፣ “የዛሬ
ዘመን ሳይንቲስቶች ከእውነታ ጋር ፈጽሞ ተለያይተዋል፡፡ ሥራቸው ከእውነታ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሒሳባዊ
ፎርሙላዎችን መደርደር ብቻ ሆኗል … አይንስታይን ሳይንስን ወደተሳሳተ መንገድ መርቶታል” ሲል የሰላ ወቀሳውን ሰነዘረ፡፡
የአቶሚክ ኃይልንም (Atomic Energy) አስመልክቶ የሰው ልጅ በአተም ቅንጣት ውስጥ ያለውን ኃይል ካወጣ ከሚያገኘው
በረከት ይልቅ እልቂቱ ይብሳል ሲል አስጠነቀቀ፡፡
ናዚዎች በጀርመን ሥልጣን ይዘው አውሮፓም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እሳት መለብለብ ስትጀምር ቴስላ የሞት ጨረር
(Death ray) የተሰኘውን አደገኛ የጦር መሳሪያውን ለአሜሪካ፣ ብሪታኒያና የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ለመሸጥ ፍላጎት
እንዳለው ገለጸ፡፡ “መቼም የማይጠፋ የጦርነት ጥላቻን ከአባቴ ነው የወረስኩት…” የሚለው ቴስላ፣ “ጦርነት ሊጠፋ
የሚችለው ጠንካራውን ደካማ በማድረግ ሳይሆን፣ ሁሉንም ሀገራት ራሳቸውን ከወረራ መከላከል እንዲችሉ በማስታጠቅ ነው”
ይላል፡፡ ለዚህም ጦርነትን ያጠፋል ላለው ስልት ደግሞ ያሰበው የሞት ጨረር ፈጠራውን ነው፡፡ ይህን የጦር መሳሪያ የታጠቀ
የትኛውም ሐገር የሚቃጠበትን ወረራ ማክሸፍ ይችላልና…

ቴስላ ይህን የጦር መሳሪያ ለብሪታኒያ በ30 ሚሊየን ዶላር ለመሸጥ ድርድር ጀምሮ ነበር፡፡
መሳሪያውን ከመስጠቴ በፊት ገንዘቡን በቅድሚያ ክፈሉ ባለው ቴስላና፣ መጀመሪያ መሳሪያውን ስጠን ባሉት የብሪታኒያ
ተደራዳሪዎች መካከል መግባባት ላይ መድረስ ስላልተቻለ ሽያጩ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ፣ ብሪታኒያ የሞት ጨረር
(Death ray) ለመስራት ሳይንቲስቶቿን አሰባስባ ብትሞክርም ሊሳካላት አልቻለም፡፡ ናዚዎች ዮጎዝላቪያን ሊወሩ ባኮበኮቡበት
ጊዜም ቴስላ ለትውልድ ሐገሩ የጦር መሳሪያውን ለመሸጥ ሞክሮ ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡
የኋላ ኋላ የአሜሪካ መንግሥት በቴስላ የሞት ጨረር የጦር መሳሪያ ላይ ፍላጎት አሳድሮ ነበር፡፡ በሁለት የአሜሪካ መንግሥት
መሐንዲሶች ጥቆማ ላይ በመመርኮዝ እ.አ.አ በ1943፣ ጥር 8 ቀን የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኋይት ሐውስ
ሊመክሩ ቀጠሮ ይዘው ነበር፡፡ ከዚህ ቀን አንድ ቀን ቀደም ብሎ ግን ለዓመታት በኖረበት የኒውዮርከር ሆቴል ክፍል ውስጥ
ታላቁ የፈጠራ ሰው ኒኮላ ቴስላ በ86 ዓመቱ እስከወዲያኛው አሸለበ፡፡

ቴስላ እንደሞተ አደገኛ የጦር መሳሪያ መስሪያ ግኝት ላይ ደርሷል የሚል ወሬ ተነዛ፡፡ የአሜሪካ የፌድራል ምርመራ ቢሮ (FBI)
ወዲያውኑ የቴስላን የምርምር ወረቀቶች ሰብስቦ በሚስጥር በማይክሮ ፊልም ቀዳቸው፡፡ በነዚህ የቴስላ ወረቀቶች ላይ
በመመርኮዝም ሳይንቲስቶቿ የሞት ጨረር እንዲሰሩላት አሜሪካ አንድ ፕሮጀክት ጀመረች፡፡ FBI በማይክሮፊልም የቀዳቸው
የቴስላ ወረቀቶች ተሰብስበው ወደ ትውልድ ሐገሩ የያኔዋ ዩጎዝላቪያ ተላኩና በዚያው የቴስላ ሙዚየም ተከፈተ፡፡
በቴስላ ታሪክ ላይ የአሜሪካው የሚዲያ ተቋም PBS የሰራው አንድ ዘጋቢ ፊልም፣ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች በቴስላ ወረቀቶች
ላይ በመመርኮዝ የሞት ጨረር ለመስራት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም ይላል፡፡ ቴስላ ባሰበው መልኩም ባይሆን HAARP
የተሰኘ አንድ ፕሮጀክት በሳተላይት አማካኝነት የኤሌክትሪክ ኃይልን ከአንድ የዓለማችን ክፍል ወደ ሌላኛው ለማስተላለፍ
ተሳክቶለታል፡፡ ቴስላና ረቂቅ የፈጠራ ምናቡ የሚያስደምማቸው በርካቶች ዛሬ ላይ ከሚያነሷቸው ነጥቦች ዋንኛው በአጭር
የተቀጨው የዋርደንክሊፍ ማማ ሥራ ቢሳካ ኖሮ ኢንተርኔትን ጨምሮ የዛሬዎቹን የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ብዙ አስርት አመታት
ቀደም ብለን እናገኛቸው ነበር ነው…
ምንም እንኳ ነጻ የኤሌክትሪክ ኃይልንና መልዕክትን በመላው ዓለም የማስተላለፍ ሕልሙ አለመሳካት የቴስላን ስሜት ክፉኛ
ቢያነክተውም፣ ቴስላ በኋለኛው ዘመኑ በጻፈው ፅሁፉ እንዲህ ሲል ይፅናናል፣ “…የሳይንስ ሰው የተራቀቁ ሐሳቦቼ ዛሬውኑ
እውን ካልሆኑ ማለት የለበትም፡፡ የእሱ ሥራ ለነገ ዘር መዝራት ነው … ከእሱ በኋላ ወደፊት ለሚመጡት መሰረት መጣል …
መንገድ ማሳየት…” እንዲያ ከሆነ በዕርግጥም ቴስላ ተሳክቶለታል፡፡ በዚህ ዘመን በመላው ዓለም ላሉ የቴስላና የፈጠራዎቹ
አድናቂዎች ደግሞ በዕርግጥም እንዳለው ይህ ዘመን የቴስላ ሆኗል…

You might also like