You are on page 1of 36

ገቢር አንድ

ትዕይንት -አንድ

ባዶ መድረክ

/የግንባር መብራት ቀስ እያለ ሲፈካ ከፊት ለፊት መድረኩ በኢትዮጵያ መልከዓ ምድርና ታሪካዊና ሀይማኖታዊ፤ቅርሶችና አብያተ
ክርስቲያን የደመቀ የተወጠረ ሻራ ይታያል/

በሸራው ላይ የአክሱም ሐውልት እና ቤ/ክርስቲያና የነጃሽ መስጂድ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት የጎንደር /ፈሲል ደስ/ ግንብ
የሐረር ግንብ በጉልህ ወጥተዋል፡፡

መድረኩ መሃል ላይ ዙፋን ለአመል ያህል ዝቅ ያለ ባለ እንጨት ጌጠኛ ወንበር ብቻውን ተቀምጧዋል፡፡

/ከጀርባ በርከት ያሉ ድምፆች እጂግ ጎልተው መሰማት ጀመሩ ድምፆቹ በተለያዩ የኢትዮጰያ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ ተደበላልቀው
ይወርዳሉ!

ድምፆቹ፡--እንዝመት በቃ እንሂድ እንዝለቅ

ምንድነው በትዕግስት መታነቅ

አዝማች ካጣን እኛ እንሔዳለን ?

ስንቄን ማቄን የለም ያለ ሀገር ማን አለ ?

ኑ እንዝመት፤እንዝመት ፤ወደፊት፤ ወደ ፊት፡፡

ወደፊት፡፡

/በዚህን ግዜ ከተመልካች ጀርባ አንድ የጎላ ድምፅ ሲያስገመግም ከጀርባ ይመጣ የነበረው የህዝብ እንዝመት ሁካታ እየረገበ እየረገበ
ይመጣል/

ተራኪ፡-እውነት ነው ነገር ከተበጠሰ

የውጫሌ ውል አንቀፅ አስራ ሰባት ከፈረሰ

ቃል ከደፈረሰ የምን ቸልታ ነው?

/ተራኪው ትረካውን እየወረደው ወደ መድረኩ ይዘልቃል /

ታላቋ ንግስት እቴጌ ጣይቱ

የኢጣልያን የአውሮፓን ልብ ታውቀው ስለነበረከጥንቱ

አንቶኔሊ በድንፋታ እርር ድብን ብሎ ውሉን ሲቀደው

እሷ ግን ጦርነቱን በአደባባይ አወጀችው

‹‹ሒድ አንካሳ ዶሮ ሳይቀድምህ ለንጉሥህ ንገረው

ጦርነቱን ነገ አድርገው ››

ይኃው ቃሏ ሰምሮ አባዳኝው ነጋሪት እያስገሰመ

ቀንድ መልክት እያስለፈለፉ አዋጁን ከአገር አገር አተመመ


ሳይነኩ ነክተው

ለአባዳኝው አባቶች የሰጡትን ምድር ደፍረው

እንቢኝ ያሉት ንፍፍቲያም ጣሊያኞች ሲጎብሩ

ከመረብ ምላሽ ተንደረደሩ

/ፋታ/

ታዲያ ህዝብ ከተነሳ በኃላ ዝግመት

ምን የሚሉት?

ጣሊያኖች የስጋት እሩጫ ሆኖባቸው

መቀሌን አልፍው አምባላጌ ከትመው

እንቅልፍ አልባ መባነናቸውን ተሸክመውት

እዚህ አባዳኝውን መክዳት ?

እረ እንዴት ነው የሚሆነው ወገን እንዴት

እንዴት?

በተወጠረ ስጋትየመጣው ጠላት

እንግዲህ በዋዛ ከቶውንም አይመከት

አመጣጡ ለሞን ነው ሞትን ሊያነግስ

እናት እህት ልጅ አክስቴን ሊያረክስ

በእርግማን የወንድነቱ ጉልበት ሊያልከሰክስ

አባት አያት ወንድም ባልን ሊያዋርድ

ቀሳውስትን መነኮሳትን ባህታዊያንን ረግጦ ሊያርድ

እምነትህን አዋርዶ ሊያላግጥየአምልኮን ሥፍራን ሊድጥ

ታሪክ ሊያፈርስ ሊያወድም ሊያጠፋ ሊደፈጥጥ

አገር ሊያፈራርስአገር ሊድስ

ልብህን ለወገንህ ከሰጠህ

ዳግም ኢትዮጵያን ታያታለህ

አልያ ከለገምህ አብረሃት ትጠፋለህ

አገሬ እንዳትል ሀገር የለህ

ወገን እንዳትል ወገን የለህ


የት ትደርሳለህ ?

አውሮፓ በጣሊያን ዝርያዎቿ ዘልቃ ገብታ

እነ አንቶኔሊን ሳሌምቢኒን ጂያኮምን

ፊልተርን አሰማርታ

የእያንዳንዱን መሳፍንት በር አንኳኩታ

መሰስ ብላ እየገባች ነው ምኒልክን

ልትጥል እንደቴዎድሮስ ዕጣ ፈንታ

ግን ይሆናል እንዴ ጎበዝ? ይሆናል?

ምኒልክ ቢወድቅ ወዴት ይደርሳል?

ምኒልክ እኮ ዛሬ ሀገር ነው ንጉስ

አይደለም

አገር በተወጠረችበት ግዜ ያለ ንጉሥ

አገር አዳኝ እንጂ ገዥ አይባልም

ዛሬ ምኒልክ አውሮፓ ያደመበትን አገር ለማዳን

እረኛ ሆኖ የወጣ ተንከራታች ሟች ወደቂ

እንግልት ነው ለወገን

አገሩ ታሪኳ እንዳይበላሽ ተዳፈነትች እንዳትባል

ወገኑ እንዳይዋረድበት እንደባሪያ እንዳይፈነገል

ሕፃን አዛውንትወንድ ሴት

ፍፅም ደቆ ወድቆ ተንኮትኩቶ እንዳይሞት

ለማዳን የወጣ ጭፍራ እንጂ እባካችሁ

ንጉሥ አትበሉት

ታዲያ ይሔን እረኛ ነው አውሬ በጎች

የሚከዱት?

ከዱት

የነ ሳሌምቢኒን ቃል ሰሙበት

በእነ አንቴኔሊ አንደበት ተረቱበት

በእነ ጂያኮም ስብከት ተጠመቁበት

በእነ ፈልተር መሰሪነት


ልባቸው ተሸረፈበት

ግን ይሆናል?

መቼም አይጥል ነውና ለምኒልክም ወገኑ

ተግ ብሎ ተነስቶለታል ሚታመንበት ሚታመንለት አምላክ

ያውቃል

/ተራኪው በህዝብ መሃል እያንዳንዱን ቃል እየረገጠ አሳምሮ ከነሀዘን ቆዛዜው ቃሉን ውርዶት በስተግራ መድረክ ወደ ውስጥ ዘልቆ
ገባ በተለይ የመጨረሻው ቅዛዜ ላይ ሀዘን ነጋሪ እንጉርጉሮ ዜማ ተከትለው !

ጣዲቄ፡-ከሀሉም ከሁሉም ጤፍ ታንሳለች

ህዝብ፡-ጤየፍ ታንሳለች

ጣዲቄ ፡-ወድቃ በስብሳ ትነሳለች

ህዝብ፡-ትነሳለች

ጣዲቄ፡-ይሄንን እውነት እረሳና

ህዝብ፡-እረሳና

ጣዲቄ፡-የአዳም ዘር ሁሉ ዘነጋና

ህዝብ፡-ዘነጋና

ጣዲቄ፡-ተው አትዘንጋ

ህዝብ፡-ተው አትዘንጋ

ጣዲቄ፡-ተሰርቶልሀል የእሳት አልጋ

ህዝብ፡-የእሳት አልጋ

ጣዲቄ፡-ያን የእሳት አልጋ የእሳት ባህር

ህዝብ፡-የእሳት ባህር

ጣዲቄ፡-እንደምን ብዬ ልሻገር

ህዝብ፡-ልሻገር

ጣዲቄ፡-ተሸገሩትአሉ በሰሩት ምግባር

ህዝብ፡- ምግባር

ጣዲቄ፡-ዘልቀው ተጉዘው በፍቅር

ህዝብ፡-በፍቅር

/ልክ ተራኪው ከገባ በኃላ ምኒልክ አባዳኝው ከበስተቀኝ መድረክ ይገባል/


/አናቱን በሻሽ አስሮ ሙሉ እጀ ጠባብ ለብሷል ሰናደር ጠመንጃ በቀኝ እጁ ይዞ ጥይት ሙሉ ዝናር ታጥቋል ጥልፍልፍ ጫማ
ተጫመምቶዋል፡፡/

ምኒልክ፡-አያቴ ሳህለ ስላሴ ኢትዮጵያን አንድ ሊያደርጉ ሲጓጉ

የሰው እድሜ ልኬት እጥረቱ አፍኗቸው ከሞት ሲጠጋጉ

አባቴ ኃ/መለኮት በአባታቸው እግር ቢተኩም

አንድ አድራጊው ሌላ ሆነና እሳቸውም አልዘለቁም

የዕጣ ፈንታ ተርታዬ ንፁህ እጅ ሲዘረጋልኝ

ከአባ ታጠቅ ዘንድ በክብር ነበር የጣለኝ

ያን ግዜ ነበር የአያቴ ህልም የገባኝ

ኢትዮጵያ ስፊ እንደሆነች እንደፀሀይ የበራልኝ

የግዛት ስፋት ክብር ነው የወገን ክንድ ባለቤት

አልደፈር ባይነት ውርስ የማንነት መለኪያ እውነት

ዛዲያ አባቴ ቴዎድሮስ

እንዲያ በመሳፍንት መዳፍ ቅንጣት ታህል የተበጣጠሰችውን

መልሶ እንደቆዳ ሰፍቶ ስም አሳጣት ያለማትን

በጎንደር ትግሬ ሸዋ ጎጃም ወሎ እንዳልተሰነጣጠቀች

በአባቴ ቴዎድሮስ ዘመን እንደ ጥንትዋ ኢትዮጵያ ተባለች

ያኔ አውሮፓ ደነገጠ

የጥንትዋ ኢትዮጵያ ከተመለሰች ጠፋለሁ ሲል ተናወጠ

መሳሪያ ከመለመን ስሩልኝ ማለቱን

በድንጋጤዋ ስር አውቆበት ማንነቱን

ሥልጣኔ ተመልሶ በኢትዮጵያ ምድር ከበራ

ድፍን አፍሪቃን አንቅታ ከቆመች ከአለም ጎራ

ያን ግዜ እኛ ጉድጓዳችን ይማሳል

አውሮፓ ብሎ የግዛት ምድር ህልም ይሆናል

ሲሉ ተምታተው ታመሱ ይባስ ግራ ገባቸው

ራሴን ልቻል ልስራ ባለ ጠላትነት ሰርፆ በልባቸው

/ፋታ/

ግና ወርደው መቼ ገጠሙት

የገዛ ወገኑን ጠላት እንዲሆነው አጩለት


ወትሮም በኢትዮጵያ ምድር የመሳፍንት ዘመንሲተክሉ

እጁንዘርግቶ ወደ ተከተላቸው ወገን አደሉ

በመድፍ በአረር በነፍጥ እየደለሉ

ከዙላ ተነስተው አለ አንድ ችግር መቅደላድንኳን ተከሉ

እቅዳቸው ተሳካ በወገኑ አስነከሱት

የኢትዮጵያ ዳግማዊ መስራች ራሱን በራሱአስጠፋ

አባቴ ቴዎድሮስ የሀገሩን ፍቅር በሞቱ ገለፀላት

ተደፍራ ከመመልከት

ራሱን በራሱ ለእናቱ በራከት ሰጣት

/ፋታ/

ዛዲያ ያ ሁሉ የግፍ ዘመን ተነግሮ እኔ ዘንድ ሲደርስ

ለምንድነው እንደ አባቴ ቴዎድሮስ በከሀዲ የምታመስ ?

ተነስ ወረሒሉ እንገናኝ ማለቴን

መቁረጥ መነሳቴን

ሲያውቁ ነው የሚሸረሽሩኝ?

የሸር ጥፍራቸውን የሚያሾሉብኝ ?

እንደ አባ ታጠቅ አገር ላቅና ባልኩኝ

ሲበዛ ራሴን እችላለሁን ባስረገጥኩኝ

የገዛ ወገኖቼ የአውሮፓን ቃል ሰምተው ልባቸውንያርቁብኝ?

/በግራ ክንፍ መድረክ እልፍኝ አስከልካይ ይገባል/

እ/.አስከልካይ፡-ጌታዬ. . . ንጉስ ነገስት የተጠሩት ደርሰዋል

/ ምኒልክ በመበሳጨት ወደ ወንበሩ እየተመለሱ /

ምኒልክ ፡-ደርሶ ያልነበረ ልምድ ይግቧ ዛዲያምን ከደጂ ይገትራችኃል ?

/ዙፋኑ አጠገብ /ወንበር/ ሔዶ ቆመ እንጂ አልተቀመጠበትም /

/እፍኝ አስከልካይ እጂ ነስቶ ወጣ /

/ ምኒልክ ቁዝም ብሎ እንደቆመ እልፍኝ አስከልካይ ተመልሶ ሶስት መሳፍንት፤ራስ መኮንን ፤ራስ ወሌንና ዋግ ሹም ከሩን አስከትሎ
ገብቶ ደረደረና እጂ ነስቶ ወጣ /

እነ ራስ መኮንንም እኩል እንደቆሙ እኩል እጂ ይነሳሉ/

/ ምኒልክ መልስ አልሰጣቸውም በመገረም ተመለከታቸው/


/የሁሉም አለባበስና መሳሪያ አያያዝ ልክ እንደ ምኒልክ ነው/

ምኒልክ ፡-ለዘመቻ ለመነሳት ወግ ወጉ ተይዟዋል

ዘመቻ ግን መጃመሪያ እዚህ ስር ይመሰረታል

/ልቡን እየዳበሰ ያሳያቸዋል/

ለመሆኑ . . .

/በስተቀኝ የመድረክ ክንፍ ሌላ እልፍኝ አስከልካይ ሲበር ገብቶ ለጥ ብሎ እጂ ይነሳል/

/ ምኒልክ ዞር ብሎ ይመለከተዋል/

እ/አ ፡-ጌታዬ ንጉሥ ነገስት

ንጉሥ ተ/ሃይማኖትና እና ራስ አሉላ ደርሰዋል

/ ምኒልክ በደስታ ከቦታው ንቅንቅ እያለ/

ምኒልክ፡-ዛዲያ ፍቃድ ትጠይቅለቸዋለህ ? ግቡ በል

እነሱን ከደጂ ማን ያስቆማል ?

/እጂ ነስቶ ይወጣል /

/ ምኒልክ የገቡትን እየተመለከተ/

ይግቡ እንጂ ይግቡ እነሴማ አንዲያቸውን

ልባቸውን ለሀገራቸው ሰጥተዋል

/ሶስቱ ቀዳምት ገበ መሳፍንታት ሽሙጡ ስለገባቸው አንገታቸውን እንደመድፋት አደረጉ/

/ንጉሥ ተ/ሃይማኖት ቀደሞ ራስ አሉላ ከተል ብለው ገቡ /

/ ምኒልክ ከነበረበት እየቀረባቸው የጥብቅ ወዳጂነት ሰላምታ ሰጣቸው/

/ሶስቱ ቀደምት መሳፍንት ለመመልከትም አልደፈሩም/

/እነሱም አለባበስና ነፍጥ አያያዝ እንደ ምኒልክ ነው/

ምኒልክ - እንዴት ከርማችኃል ወንድሞቼ ልበችሁ ሲታመስ በመዝለቁ

በአልኩ ባይ መሳሪያ የጣሊያን ሰይጣን መሞሽለቁ

የእናትንተ ልብ ግን ኢትዮጵያ ለመጥለቁ

ምስክር ሳልሻ ይኃው ከአጠገቤ ደርሳችሁ አየሁት

ለመሆኑ እንዴት ከረማችሁት ?

/ወደ ወንበሩ ተመልሶ ይሔድና ወንበር ላይ ጠመንጃውን እንደሰው አስቀምጦት ተደግፎት ይቆማል/

ንጉስ፡-ጌታዬ ግርማዊ ጃንሆይ


ወትሮም ለኢትዮጵያ ለአንድነቱ የደከመ የጠጠረ ልብበማን ሊሰለብ ?

ጌታዬ የአልጋ ናፍቆት ይዞን አልነበር አገር ስናቀና የኖርን

ግና የቀናች አገር ለመናድ አውሮፓ የክፋት ጥፍሩን ሲያሸልብን

የሰይጣን ምክሩን ሹክ እያለ መሳፍንቱን ሲያሰትብን

ጭራሱኑ ልባቸውን እንዳይሞሸልቅ

ነቅሎ መጣል ይበጃል ከምድራችን ማላቀቅ

እንግሊዝም ሆነች ፈረንሳይም ቤልጂግም ሆነጣሊያን

ከቶውን ለወዳጂነት አይፈልጉን

ምንድነው ጭንቁ ወዲያ የማይወጡልን ?

ምኒልክ ፡-እውነቱን ነው በፍቅር ልጨርሰው ስታገል

ትዕግስት ፍራቻ ይመስል

አጠገቤ የውጫሌን ውል ቀድዶ እብስ ሲል

ያን ግዜ ነበር ሁሉን አብሮ ማስከተል

ይሀው

/ወደ ተጣራጠሩት እየጠቆመ/

ልባቸው በስጋት ተወጥሮ

በስብከት ሰክሮ

ከዘመቻው እንኳን እነሱ እኔ እንድቀር

ገሸሽ እያሉ አሳዩኝ

ሰግተው ወገኔን ሊያሰጉብኝ

/ ምኒልክ ልባቸው ወደ መኮንን እየሄደ/

ምኒልክ ፡-ለመሆኑ እስኪ ልጠይቅህ አንተም መልስ ሳታብል

ከልብህ ሥር አንዳች ድብቅ እውነት ሳትተክል

እኛ ከጥልያን ጋር የተዋዋልነውን ውልእንደምናቀፈርስ

እያወቅህ

አንቀፅ አስራ ሰባትን እንዳጋጨን እየገባህ

አዲስ ውል ከባሪያቴሪ ጋር መዋዋልህ

እርሱ ከጥልያን መንግስት ጋር አጋብቶ

ንጉሥ ሊያደርግህ
ሲያስማማህ

ምን ተስማማህ?

መንገሻ ፡-ውሉ ንጉሥ ነገስትነን ለመሻትም አልነበር

ምኒልክ ፡-ዛዲያ ሌላ ምን ነበር?

መንገሻ ፡-ጥልያን ባህረ ነጋሽ ተቀምጦ

ኢትዮጰያን ቋምጦ

ቁልቁል ይወርዳል በሚል ስጋት

እዛው ለመግታት

ምኒልክ፡-እ. . . ለመግታት

የተዋዋልከው በንጉሥ ነገስትነት?

/ትቶት እየሄደ/

ሀገር መጠበቅ በንጉሥ ያምራል

ሲሉን

እንቅልፍ አጥተን

ሀገር ልንሰፋ

ወሰን ልናሰፋ

የተማርነውን ልንተገብር

ወዳጂነታችን እንዴት እንደሚቋጠር

ከወገኖቻችን ጋር ስንመክር

ለባሪያቴር ልብህን ሰጥተህ ስትዋዋል

ንጉሥ ከመሆን በቀር

ሕልምህስ ምን ነበር?

መንገሻ ፡-አገር ከመጠበቅ በቀር

ምንም አልነበር

ምንልክ ፡-ነው ? አገር ልናቀና ቁልቁል ስንወርድ

አንተ ደግሞ ሽቅብ ልትሔድ

ያልፈቀድንልህን ጦርነት ልትገጥም

ኢትዮጵያን ልታዋርድ በሀገርህ ላይ ስትለግም

ስንሐት ይሉ ደጃዝማች እትጉም


ኃላ ብታጋጩም

እኛን ብቻ ሳይሆን አንተንም ክዶ ከእነሱ ጋር

ከመግጠሙ ፊት

እንዲያ ሲሞግትህ በመልዕክት

በክፋት ተጣብቆብህ

አልላቀቅ ሲልህ

ምን ነበር የመከረህ ?

መንገሻ ፡- . . . ምንም ››

ምኒልክ ፡- እኮ ምንም?

መንገሻ ፡- አዎ ምንም ?

ምኒልክ፡-አንተ የታረቅህ መስለ ግባ አላለህም ?

መንገሻ ፡- በፍቀፁም

ምኒልክ ፡-አንተም እርሱም

ልባችሁ አይታመንም

ቀድመህ ክደህ አይተንሃል መዳፍህ እምነት

አይጨብጥም

እሱስ ማንነቱ ታውቋል

እዚያ ተቀላቅሎ የጥልያንን መሳሪያ ታጥቋል

የአንተስ ልብ አለመሸፈቱ በምን ይታወቃል ?

መንገሻ ፡- ልቤ በሀገሬ መሆኑ ድንጋይ ተሸክሜ ይቅርታ

በመጠየቄ ተረጋግጧል

ምኒልክ ፡-የለም አላግጧል ብትለኝ ይሻላል አላግጧል

ራስ አሉላ ፡-ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

ለእርቀ ሰላም ማውረዱ እኛም ስለመበርንበት

ምኒልክ ፡-አባቴ ራስ አሉላ እሱን ይተውት

ደጃች ስብሃት ይሉት ጉድ

የሴጣን ውልድ

የአጤ ዮሐንስ የወንድም ልጂ መሆንህን

አንስቶ
መተማ ሲወድቁ አልጋ ማውረሳቸውን አውስቶ

ልብህን በአልጋ ናፍቆት አስረትቶ

ጥልያን ቢዘምትም ይረታናል አሰኝቶ

ከጎናቸው ብትቆም ለአጎትህ አልጋ

ያበቃሃል

ምኞታችን ይሰምራል

አላለህም ብሎሃል?

መንገሻ ፡- እረ ጌታዬ ንጉሥ ነገስት

/ ምኒልክ መለስ ብሎ ወደ መንገሻተመልክቶ እያቀና /

ምኒልክ- ፡-ልብህን አትዋሻት

መቼም ሰው ነህና የወንድምልጅ መሆንህን አንስታት

አልጋ ይውረስ መባሉንም አንዘነጋት

/እጁን ወደ ዙፋን እያመለከተ /

ይህቺን አልጋ ብትመኛት

እኛም በምኞትህ አንፈርድበት

/አሁን ወደ እነ አሉላ እየሔደ /

ፍረዱኝ ወዳጆቼ ግና ሽንፈቴን ለምን አሰበው ?

ሽንፈቴ እኮ የእኔ አይደለም የሀገሩ ነው

/ወደ ሕዝብ እያተኮረ እና እጁን አልጋው ላይ ሰንዝሮ /

ይህ አልጋ የተመሰረተው

በአባት በአያቶች አጥንትና ደም እንጂበነገስታት ብቻ ያለው ማነው ?

የአባት የአያት ጭፍራ ባይኖር አልጋውን ማነውሚያፀናው ?

/ወደ መኮንን እያተኮረ /

እውነት ወገን ካለህ አልጋውን ከፈለግህው

ያው

/ትቶት እየሄደ /

ግና ለአልጋ ብለህ አገራችንን አንዘንጋት

እሷ ስትኖር ነው አልጋ ሚፀናባት


/ወደ መንገሻ ፡ እየተመለሰ /

ወገን ሲኖርህ ነው ንጉስ ተብለህ ምትገዛበት

ግና አውሮፓን አምነህ ከተንበረከክላት

ባሪያ እንጂ ጌታ አያደርግህም ይህችን ከልብህ ስር አትማት

አባቴ አባ ታጠቅ ሲያስተምረኝ

በኢትዮጵያ እንጂ ለአልጋ ቁብ እንዳይኖረኝ ነው ያደረገኝ

በኢትዩጵያ ለኢትዩጵያ ነው የቃኝኝ

እኔ ለኢትዩጵያ የምዋደቅ እንድ ጭፍራ ነኝ

/ተመልሶ ወደ ተክለ ሀይማኖት እያቀና /

እስኪ ተክልዬን ተመልከቱት ሲሆን እሱ ነበር ለአልጋ ምኞት የተቀነበበ

እውን ለኢትዮጵያ አልጋ ከእሱ በላይ ማን ይሆን የቀረበ ?

ንጉስ እኮ ነው ተመልከቱት

ምኒልክ ለአገሩ ሲወድቅ እሱም አብሮ ሲወድቅከተረፈ የምትተኩት

የዛሬን መትረፍ ያመጣው

ይኃው ታላቅ ንጉስ ነው

ንጉስ፡-እሯግ . . . እሯግ በማራያም ይዤዎታለሁ ንጉሠ ነገስት

ይሄን ያህልም ልቤን በኩራት አይሙሉት

ምኒልክ፡-ሞልቶ ይፍሰሰ

ኩራትህን የሰጠህ ያለበሰህ ታላቅ ሞገስ

ለሀገር የደከምክለት የታገልክበት እስከ ሆን ድረስ

ተወው ሞልቶ ይፍሰስ

/ወደ አፈሩት መለስ ብሎ እየሄደ /

አያችሁ . . . ሳለምቢኒ እንደ እናንተ መስሎት ቢቀርበው

ተክልዬ ደህና አድርጎ ነበር ልቡን ያሸው

ልክስክስነቱን አጣብቶት በጠጂና በሴትኢጣሊያን አውሮፓን ያዘካዘከው

የእንግሊዝ መሰሪነት

የኢጣሊያን ቡችላነት

የፈረንሳይን የሩቅ ህልም የጀርመንን ዕብሪት

የቤልጂግን የተንኮል ንፊፊት


የአውሮፓን አፍራቃን በቅኝ ለመያዝ መነሻ

የመቀራመቱን መዳረሻ

አሳምሮ ነበር ያዘከዘከው

ሰውም ሳንልክ እዚህ ነበር ያውሮፓን ልብያወቅነው

/ወደ መንገሻ፡እየተመለሰ /

አየህ ቢመኝ እንኳን ሚያምርበት

እሱ ነበር ለአልጋው ቅርብ የአልጋው ባለቤት

መንገሻ ፡- ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

ምኒልክ፡-ተው . . . እቺን የክብር ስም መልስና ዋጣት

ኢጣሊያን እመንና ስሙን አንተው ውረሰው

ባሪያ አያደርገህ እንዳው ያው !

/እጁን ዘርግቶ ያሳየዋል/

እኔን ግን ተወኝ

እኔ ወሰንዋ ላይ ደረቴን ለአረር የምሰጥየኢትዮጵያ ትቢያ ነኝ

ስለዚህ ትቢያ ለመሆን አትታገል አንተ ንጉስ ነህናእንዳትከተለኝ

/ራስ አሉላ በዳኝነት መስመር ውስጥ ለመግባት በላሰብ /

አሉላ፡-መቼም ጌታዬ ንጉሥ ነገስት

ኢትዮጵያ እንዲህ በታመሰችበት ወቅት

የእርስ በእርስ መገፋፋቱ ያመጣልና ክፍተት

ይሀው መሰንጠቅ ጥቅም ነውና ለጠላት

/ ምኒልክ መለስ ብሎ አሉላን በሀዘን እያየ /

ምኒልክ፡-የነገር ርምጃዎ አካሔዶዎን ተረዳሁት

ሁሉም ታውቋል አልፏልና ይተውት እሯ ይተውሊሉኝ አይደለም ራሱ አሉላ

አሁንስ አምኜ እንደተጓዝሁ ሁሉ ዳግም አምኜ ተቀብዬ ስለምን ልቤ በሀሰት ይበላ ?

አሉላ፡-የሐሰትም ሳይሆን የክርስትያንነታችንን ይዘን

እርስ በእርስ ታቦት እንኳን ባናወጣ ሞፈር ይዘን ተማምለን . . .

/ሚኒሊክ አቋርጦ እየገባ /

ምኒልክ ፡-ይሄን የመሀላ ግዝት


ስንት ዘመን ነው ወንዝ በተሻገርን ቁጥር የምናውቃት ?

/ ምኒልክ አሉላ ላይ እመሰከረ ክርክር ይገባል /

እርሶዎ . . . እርስዎ አባቴ ራሱ አሉላ

ስንት ዘመን ነበር ያውቁ የነበር ይህንን መሃላ ?

አሉላ፡-መቼም የጀግና ምህላውእንድዬንነው

ጀግናን ያልተቀበለ ሲያውቀው

ምህላ ሲፈርስበት አንገት ከመቀልበስ ወዲያ ምን ያደርገው ?

ምኒልክ ፡-ይሀው . . . ሯስዎ አመጡልኝ ይሀው

/ትቷቸው ወደ ሌሎቹ ለምስክርነቱ እየሄደ /

ልብ ቢሉልኝማ. . . እሳቸውን ያዋረደ ንጉሥ ወገን የኢዮጵያ አንድነት ሲጣሉት

ሥዑል ሚካኤል ንጉሥ ኢዮሲያስን በሻሽ አንቆ ገሎ የመሳፍንት ዘመንን ሲመሰርቱት

ያኔ ነው ኢትዮጵያ ዳፍንት የተጣባት

እየደከመ የመጣ አልጋ ለአንድነቷ መታገል ሲያቅተው

ሥዑል ሚካኤል ኢትዮጵያዊነትን ደረመሰው

አይደለም አባቴ ራሱ አሉላ አንደበቴ ዕብለት አለው ?

አሉላ፡-አሯ ፍፅም ፍፅም ያውቁታል ልቅም አድርገው

ምኒልክ ፡-አምላክ ይበቃኛል ሲል አባ ታጠቅን ቢያስነሳላት

የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ ሲል ካሳም ምርጫ ዳግም አደመባት

ልብ ባላሉ ልበኞች ስር የክፋት መርዙን በትኖ

ከአውሮፓ ተመስጥሮ የኢትዮጵያ አንድነት ሲያደፈርሳት

ዳግም መስራች አባቷን በራሱ እጂ አስገደለባት

/አሉላ የቅርብ ግዜ ትውስታ መጥቶባቸው እዝን ይላሉ /

አሉላ፡-ይሔ እኮ የእግር እሳት ነበር ጌታዬ ንጉስ ነገስት

ቁጭት ነው በቃጠሎ ቤት መገኝት

ሊያውም እውስጡ ተሞጂሮ መቅረት

ግና እንግሊዝ የባህር በር እንዳይኖረን

የክፋት ጥፍሯን ስታሾልብን

ቱርክና ግብፅን አሽሽታ ኢጣሊያን ስደነቅርብን


የባህር በሩ ሲገርም ዳጋሊናከሰሀጢ ቢመኙብን

የቁጭት መመለሻው ግለት እኔ ላይ ከውስጤ ተግ ቢል

በአገሬ አትምጡብኝ ብል

/አሉላን እየተመለከተ ሟሞገሱ ሲከብደው ወደ ከዳተኞቹ እየዞረና ቃሉን እየረገጠ ያስረዳል /

ምኒልክ ፡-አሉላ ዶጋሊ ሰሐጢ ላይ የምሳቸውን ሲያቀምስ

የኢጣሊያንን የእባብ መንጋ ሲደመስስ

በእንግሊዝ ክስ

ክበብርና ሞገሱን ራስነቱን ገዥነቱን ገፈውት

ከሐማሴን አንስተው ወህኒ ሲወረውሩት

ዶጋሊና ሰሀጢን አልፎ ያሻት በስፍራ እንድትረግጥ

ለኢጣሊያ መንገድ ሲጠርጉላት

ሁሉን አልፋ ዘልቃ ባህረ ነጋሽን ወርሳ ኤርትሪያ ስትል ስም አወጣችላት

/ፋታ/

ኤርትሪያ ማለት

የመጀመራያው የቅኝ ግዛት መሬት

ነው ይሉናል ኢጣሊያኖች ሲተረጉሙት

/ወደ ራስ አሉላ ተመልሶ በጥሞነ ሲያስተውላቸው ቆየና/

ዛዲያ አባቴ እርስዎ ዛሬ ሲቆሙ ለእርቅ ለዳኝነት

ያን ግዜ የእርስዎን ቃጠሎ ማን ነበር ያየልዎት

/አሉላ የትዝብት ሳቅ እየመጣባቸው /

አሉላ፡- ጌታ ንጉስ ነገስት

ያ . . ዘመን የተሸከመ ፍፅም ክፋት ነው ክፋት

የ ኢትዮጵያን ህልም ማጥፋት

አንድነትዋን ደርምሶ መሬት እየቆረጡ መስጠት

ምኒልክ ፡-እሳት ካየው ምን ለየው

ይህኛውስ ወዴት ነው ሚወግነው ?

ለአገሩ ክብር አንድነት ነው የቆመው ?

ወይስ ለስሙ ንግስና ነው የሞገተው ?

/ንጉስ አሉላን እየረዱ ይገባሉ /


ንጉስ፡-ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

ውሉ አልለየም እኮ የትኛው ይደረስበት

አሁን የሽቅብ ይሁንብኝና በትዕግስት

/ ምኒሊክ ሳያስበው ከፍ እያለ ይናገራል /

ምኒልክ ፡-ትዕግስት መጥፋቱን እኮ ደርሰንበታል

ንጉስ፡-ቢሆንም ጌታዬ ንጉሰ ነገስት . . .

ምኒልክ፡-ወዴት ተ/ኃይማኖት

ያንዱ ቢሆን ምን ተዳዬ ሶስቱ እኮተመሳጥረው የወገኑት

/ሶስቱም ወሎ መኮንን ኮሩ እኩል ደነገጡ /

ወሌ፡-እሯግ ሐሰት ነው ንጉሥ ነገስት

/ ምኒልክ ይሔን ግዜ ወደ ወሌ በፍጥነት ይዞራሉ ከመኮንን በላይ በጣም የተናደዱ ይመስላሉ /

ምኒልክ፡-እ . . . አንተማ እህትህ እህቴ እመቤቴ ሚሽቴ በመሆኗሳቢያ

ያ . .ጂያኮም ይሉት ትቢያ

ምኒልክ ጦርነት ላይ ወድቆ ሲሰናከል

ሬሳ ሆኖ ለሀገሩ ሲከነበል

ለእህትህ ሲባል

ዙፋን ጠባቂ ይመስል

ወደ ንጉሰ ነገስት እንድትጠጋጋ ኢጣሊያ መሬቱን ያደላድልልሀል

ሰለዚህ ክዳውና እኛን ተከተል

ሲል አልሰበከህም ሰብኮሃል ?

/ወሌ እውነት ስለሰማ ይመስል እጂግ በጣም ይደናገጣል /

ወሌ ፡- በስመ እግዝያብሔር ይህ ምክር ይቃጣል ?

ጃንሆይ . . . እንዲህ ያለ ቃል

እንዴት ቢደፍር አንደበቱ እኔ ዘንድ ይወጣል ?

/ ምኒልክ መሲደናገጡን ሲመለከት የበለጠ እየረገጠና ስር እየሰደደ /

ምኒልክ- ያወጣል እንዴት አያወጣ አንተ ዘንድ ይቻለዋል

/መልሶ የፍርድ ያለ እንዳይሉት ወደ እነ አሉላ ዞሮ እያስረዳ /

ወዳጆቼ ነጭ እርጉም እፉኝት ነው ቀድሞ ልብ ያያል


ሞራውን ገልጦ ተመልክቶ በምን እንደሚሸርፍ ያጠናል

ውስጥ ውስጡን እንደፍልፈል ይሰረስርሃል

ድክመትህ የት ዘንድ እንደለ ሲመለከት ያደባል

/ንቀት በበዛበት ሁኔታ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ በግልምጫ አድብኖት /

በተለይ እነደሱ በምድር ፍሬ ጭማቂ የወደቀሲያገኝ ይቀለዋል

ሚኒሊክ ሲወድቅ አልጋው ያንተው ነው ሲልበስካር ግለት ያንረዋል

ይሔ ያን ጊዜ ንጉሡን ቀርቶ ሀገር ይሸጣል

/ድንገት ቱግ አለ/

ሽጧታል እንጂ ከዚህ በላይ ለማን ያስማማት ?

ገና ከስንት ውልድ ጀርባ በእህት ሳቢያ ለሚመጣ የዙፋን ውርሰት

አገሩን በክህደት አግማማት

ዛዲያ ከዚህ ጋር ነው የሚዘመት

ንጉስ፡- ይህውልዎ ጌታዬ ንጉሠ ነገስት ግድ የሎትም በኔ ይሁንቦት

ምኒልክ ፡- ተወኝ . . . ተወኝ ወዳጄ ንጉስ ተ/ሀይማኖት

እሱ የሞተው እሺ ያለ ቀን ነው

የካቲካላ እንፋሎት

እንደጉም አእምሮውን የሸፈነው እለት

ያን ግዜ አገሩን ሽጣት

ለጣሊያን ባሪያ ሆኖ ሊገዛላት ማለላት

እንደ ህፃን መጫወቻ የጭቃ ስሪት

በክቶ ወድቆ ከርፍቶ እስሩ ተጋደመላት

/ተንደርድሮ ወደ ወሌ እየገሰገሰ/

እንሒድስ ብንል እንዴት አድርገህ ትዋጋለህ

ልብህ ሰጥተህ ሞተህ

የሕፃን ያህል እየዳህ

ከስካርህ ካልተላቀህ

አሁን አንተም ራስ ተብለህ ትዋጋለህ ? ታዋጋለህ

አሉላ፡- ምንም ቢሆን ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

ስንት ጀግና ይመራበት በነበረው ብልሃት . . .


/ሚኒሊክአሉላን ነጥቆ እየገባ/

ምኒሊክ፡-አባቴ ራስ ብልሀቱንማ ነጠቁት

እሱ ሴራቸውን በጠጂ ሲያወራርድ እነሱ ቀድመው ስለቀጡት

/ትክ ብለው ይመለከቱታል/

አንድ አንጀትም አልነበረ ከእህትህ ጋር የተኛችሁት

ምነው ታዲያ እሷ የአናብስት ሁሉ አናብስት ሆናስትነሳ ምን አለ ብትከተላት

ታናሽ ስለሆነች ናቅሃት ?

የተናቅህስ አንተ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር

አንዱ ኢትዮጵያ አንዱን ኢጣሊያ አድርጎ ይፍጠር

አፈር !

አሉላ፡- ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

ንጉሥ ሲባል ቻይ ነው እንደ አባት

አንዴ በጠፋ ጥፋት

ዳግም ላንመለስበት

የልባችንን የክፋት ሞራ ገልጠንተማምለን

የመጣብንን ጠላት ገፍተን ከባህር ጥለን

ስንመለስ እንወቃቀሳለን

/ ምኒሊክ መለስ ማለት ይጀምራሉ/

ንጉሥ፡-አዎን አሁን የፊት ፊታችንን እንመልከት

ጠላት በስንጥቃችን ሳይገባበት

ዙራያ ገባውን በፍቅር ደፍነንበት

የጀግን ነት ግለት ሙቀት ይዘን እንዝለቅበት

ሶስቱም አጥፍተዋልና ይቅር ብለው ጌታዬንጉሠ ነገስት

/ምኒልክ በጥሞና እያዳመጠ ከተከዘበት ድንገት ቱግ ይላል /

ምኒልክ ፡-ሶስቱም . . . ሶስቱም ብሩን ጨምሮ ነው ሶስቱም ?

/ቱግታው ምንም መልስ እንዳይሰጥ ገታው /

/ዋግ ሹም ብሩ የሚገባበት ጠፋው /

ብሩ የታማኝነት ደም ውርዴ እንደተጣባው አታውቅም

የእምነት ሾተላይ እንደሚመታው ከዘሩ አልጋባችሁም


/ሁሉም ግራ ይጋባል/

አታውቅም ክህደትን እንደወረሰው ከተመዘዘው ዘሩ

ገብረ መድህን አባ ታጠቅን ክዶ ለእንግሊዝ ኢትዮጵያን ስለማስወረሩ ?

እርስ በእርስ ተማምለው

ከካሳ ጋር ቃል ተሳስረው

እንግሊዝ የሚጥልላቸውን የመድፍ የነፍጥና የአራርትራፊ ተማምነው

ሊካፈሉ ተስማምተው

አገሬን በአውሮፓ የክፋት እግር እንዳስረገጧት

በአምቻ ተጋብተው እንደከዷት

/የሚያውቀው ሁሉ አሁን ፀጥ አለ/

/ምኒልክ ወደ ብሩ እየተመለሰ /

ግና ገብረ መድህንስ መቼ ቀረለት

አምቻ ብሎ የተጠጋው ነው ነፍሱን መልሶ የዋጣት

‹‹የገደለው ባልሽ

የሞተው ወንድምሽ

ሃዘንሽ ቅጥ አጣ

ከቤትሽ አልወጣ ››

አታውቅም እንዲህ እያለ ሽዋ በገብረ መድህን አህትላይ ሲተረትባት

እጅ እግሩ ተቆራርጦ ዓይኑ ፈርጦ የውሻ ሞት ሲሞታት ?

/ፋታ ወስዶ/

ግና . . . እኔም ይህንን የክፋት በትር ልጣል ብል

አንተን ከአጠገቤ ባስጠልል

የዘርህን ግፍ ያከምኩ ይመስል

ዋግ ሹም ብዬ ካባ አልብሼ ከፍ አድርጌ ብሰቅል

እነዚህ የዲያቢሎስ ልጆች ከገሃነብም እንደወጡ

ከነ ክፉ መሳሪነታቸው ከልብህ ስር ቢቀመጡ

አገሬን ለነአንቶኔሊ ልትሽጣት ተነሳህ

እመ ብርሀን ትይብህ

/ምኒሊክ ግሽግስ ሲል እርቁ እንዳይስተጓጎል አሉላ በሀዘን እንደጨመተ ወደነ ራስ አሉላ እየዞረ/
ምኒሊክ፡-ጌቶች እነዚህን አጠገቤ በማየታችሁ

አልችል ቢል አንጀታችሁ

ሃዘን በመታው ልባችሁ

ብትማፀኑም እንግዲህ አንዲያ የዞረ ልብ

ደግሞ ለፀፀት ስለማይታሰብ

ተውኝ

ሞት እንዲሁ አይቀር እኔ ደግሞ የክብር ሞት ሟች ነኝ

ኢትዮጵያ ተቆርሳ ስትቀር እኔ ወሰኗ ላይ እቆማለሁ

ዳኝው የምፅዋን ውኃ ካልጠጣ መመለሱ እንዳሁ ቀልድ ነው

/ቆራጥ ውሳኔ/

ስለዚህ ወዳጆቼ የፍቅር ድብቅ ፍርድ መመልከቱ ይቅርብኝ

ከእናንተ በቀር አንዳቸውም እንዳይከተሉኝ

ግና እሬሳዬን ከወሰንዋ ላይ አንስተው ይቅበሩኝ

/ከመሀል ጥግ መድረክ ተንደርድሮ ሊወርድ መራመድ ይጀምራል /

/ሽምግልና የገቡት ሁለቱ ከአቅን አቸው በላይ ስለሆነ ይከተሉታል /

/ሶስቱም እየተንበረከኩ /

ሶስቱም፡- ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

እረ በእመብረሀን ምህረት

/በዚህ መሀከል ከተመልካች ጀርባ ከፍ ያለ የኦሮምኛ ማቅራራት ይሰማል ሁሉም ቀልባቸው ወደዛ ይሳባል /

/ራስ ጎበና በአጀብ እያስፎከረ ይገባል /

/በሕዝብ ተመልካች መሃል ከትጥቁ መሃል ሲደርስ ሚኒሊክ ፈት ለፊት ፉከራውም ተረጋጋና ፀጥ አለ /

ምኒሊክ፡-ጎበና አንተው ነህ ?

ጎበና፡- አዎ ጌታዬ እኔው ነኝ መጣሁልህ

ምኒሊክ፡-ድምፄን ሰምተህ መጣህልኝ

ጎበና፡-ድሮስ የአንተን ድምፅ ሰምቼ ምን እረፍት አለኝ ?

ምኒሊክ፡-ወትሮም መወለድ ቋንቋ ነው ይላል የእኛ ሰው

ይህው ከልጂነት እስከ እውቀት በወንድምነት የጠጣነው

የፍቅር ምንጭ አንጀቴን አራሰው


/ወደ ጎበና እሄደ/

ከልጂነት ዘመን አንስቶ ያደግንበት ምድር

እንደ እናት ስንቆጥር

ለዚህ በቃን ለታላቅነት ክብር

ዛሬ የእኔ ያልኳቸው ጣሊያን ልባቸውን ሲሰልብብኝ

ከድካምህ እረፍ ስልህ አላርፍ ብለህ ደረስክልኝ

ጎበና፡-አገሬን ያወቅኃት በአንተ እናት

ከእንጀራ ጋር የጎረስኳት

ከልቤ ከአካሌ ጋር ያዋኃድኳት

አንተ ወንድሜ ንጉስ ሁነህ ከማንም ፊት አክብረህኝ

ዛሬ የተከበርኩባት ኢትዮጵያ ተደፍራ ምን ዕረፍት ሊኖረኝ ?

የትኛው እንቅልፌ ነው ሃገሬ ባንና ሚያንቀላፋኝ ?

የትኛው እግሬ ነው በተደፈረች ምድር ሚራመድልኝ ?

የትኛው እጄ ነው እንደባሪያ ድርጎ ሚቀበልልኝ ?

ቃልህ ወጥቶ ስትለፈፍ ወገን ሁሉ እንደሰማት

እንሒዳ . . . በል እንሒዳ ወሰንዋ ላይ እንሙት

ምኒሊክ ፡-የጀግና ቃል ይሄ ነው

ለኢትዮጵያ የማይታጠፈው

እንሒዳ . . . በሉ እንሒደው

/ምኒሊክ ድምፁን ከፍ አድርጎ መንገድ ጀመረ /

/በስተግራ በኩል ሌላ በጉራግኛ በኢሮምኛ በሃዲይኛና በሌላ ቋንቋ በተደበላለቀ መልኩ እየተፎከረ በባልቻ መሪነት ሌላ ወገን ገባ

ምኒሊክ፡- …………አንተው ኖረሀል ?

ባልቻ፡-አዎን ጌታዬ እኔ ነኝ ልጂዎ በስምዎ የምምል

በእጆዎ ጎርሼ ያደኩ በጂርወንድ ብለው የሾሙኝ

አዎ ጌታዬ ንጉስ ነገስት ባልቻ ሳፎ ነኝ

ምኒሊክ፡-አገር ስናቀና ባላገኝህ ዝሬ ልጅም አትሆነኝ

እንኳን አገር አቀናሁኝ

ባልቻ፡-እንኳን ኢትዮጵያ አቀኗት


አገሬን በወገን አሰፏት

በልጆዎችዋ እንድትባረክ አደረጓት

ደማቸውን ሊያፈሱ ይኃው ስትደፈር ቆሙላት

ረጂም እድሜና ጤና ለታላቁ ንጉሰ ነገስት

ምኒሊክ፡-እኔም ረጂም እድሜ ለልጆቼ

ለክብር ለኩራት ላበቃችሁልኝ ወገኖቼ

በሉ እንሒዳ . /. . እንግዲህ በጀግንነት የምንተያይ

ወሰኗ ላይ

/ምኒሊክ መንገድ ላይ ሲጀምር ከሕዝብ ተመልካች በስተቀኝ ወገን በኦሮምኛ፤በሲዳምኛ፤በጋሞኛ በወላይትኛ ድብልቅ ያለ ፉከራና
ዘፈን በበርካታ ሰው ድምፀ ይሰማል /

/ጦና ያን ሁሉ ሰው እየመራ ጦርና ጋሻ ይዞ የነብር ቆዳ ……በእርቃለ ገላው ላይ ደርቦ ይገባል /

ምኒሊክ ፡-- አባ ጤና ? ጦና ?

ጦና፡-አዎ ጌታዬ ጦና ነኝ

/ዝቅ ብሎ እጂ ይነሳል /

እንግዲህ የማከብርም ልቤም ከልብዎ የተቋጠረልኝ

/ምኒሊክ በተመለከተው ነገር ተደስቶ ግን ደግሞ አፈር እያለ/

ምኒሊክ ፡-በሀገር ማቅናት ግርግር

ትንሽ ብንቸጋገር

በመሃከል ደም ከመቃባት በቀር

ለካስ ቂምም አልነበር

ጦና፡-የምን ቂም ጌታዬ የእኛ ልብ ቂም አያውቅም

ደግሞ ደግ አባት እንጂ ክፋት ከቶ አላየንም

በዚህ ላይ ቃልም ደርሰን አገሬ ተደፍራለች ሲል

አገር ከሌለች ማን ሊኖር እኛ ታዲያ ቸል የምንል

/ፋታ/

አገር እመቤት ናት ጌታዬ የጀግኖች መፈጠሪያ ምድር

የወገን መኩሪያ መከታ ለውልዷ ታላቋ ክብር

እቺ ሀገር በነጭ ነኝ ባይ እንደ ዘበት አትደፈር

የድል አናብስት ነን የተፈጠርን ከዚህች ምድር


ምኒሊክ፡-በዚህስ እኔም አላውቅ ፍፁም ጥርጥር

ራሱ ወድቆ የሚያቆማት ጀግና እንጂ በባዕድ የሚሰለብ .ከዚህ ምድር አይፈጠር

/ወደነይመለከታል/

በሉ እንሂድ ለጠላት መቀበሪያውን እንቆፍር

ጓንጉል ልክ እንደ ገበና ከደጂ እያስፎከሩ ይገባሉ/

/የጎበና ሰዎች ለቀቁላቸው/

ምኒሊክ በጣም በመገረም ይመለከትና/

ምኒሊክ ፡-ጓንጉል

ጓንጉል፡-አዎን ጓንጉል ነኝ

ምኒሊክ፡ -የጉድ ቀን አይመሽ አሉኝ

አንተ እንዴት እዚህ ልትገኝ?

ጓንጉል፡-ጌታዬ የእኔና የእትስዎ ጠብ የክብር ቢሆንም

ከአገር በላይ ክብር የለም

ዛሬ ሀገሬ በምጥ ተይዛ የሚያዋልዳት ሲፈለግ

እርስዎ ሽቅብ ወጥተው ወገኔ ሁሉ ዘመቻ

መሃል ሲገሰግስ

ገና ለገና ከንጉስ ጋር ኩርፊያ ተፈጥሯል

በሚል ምክንይት

አገሬ ከሞት ጋር ድርድር ስትገባ እንዴት ነው

አላድንሽም ብዬ ምቀርባት

የእኔና የእርስዎ ጠብ ይቅር

በሀገር መደራደር

በሀገር ላይ ጀርባ ማዞር

በሀገር ላይ መኩረፍ ቂም ማሳደር

ራስን እንደ መግደል ራስን እንደ መቅበር

ነውና የሚቆጠር

ጌታዬ ንጉሰ ነገስት

ይፍቀዱልኝና አብሬ ልዝመት

ይፍቀዱልኝና አብሬ ልሙት


አምላክ ፍቃድ ሆኖ በህይወት ከተመለስን

ያን ግዜ ኩርፍያችንን ረስተን

የኢትዮጵያ ልዩነታችንን ፍቅራችንን አድሰን

አብረን እንዘልቃለን

ወይም ደግሞ› . . .

ምኒሊክ ፡- ደግሞን ተው ጓንጉል

ደግሞ አፍራሽ ቃል ነው ከደግሞ ፍቅር ይበልጣል

አብረን እንሙት ብለህ ወደ እኔ ልትዘልቅ

ይኃው ሳህለ ማሪያምም በፍቅር ያቅፍሀል/ ሄዶ ያቅፈዋል/

ጎበዝ ልብን ያጀገነ ቅን

እንዝመት ብሎ ከወገን ሲተቃቀፍ

መሃከላችን ያቀፍናቸው ያመናቸ ከጠላት ጋር ወግነው

ሊጥሉን ካሰቡ እንግዲህ ከመውደቃችን ፊት መተው

እንዲህ ነው ኢትዮጵያ ማለት

የፍቅር የመከበር የመተሳሰሪያ መሬት

በል አሁንም እንደወገንን ጠላቷን ደፍተን

እስከ መቃብሩ እንደርደር

የተቀረው ለነገ ይደር

በሉ እንግዲህ እንዝለቀው

/ሁሉም እያቅራራ መንገድ ተጀመረ/

/በዚህ መሀል ከፍተኛ ድንፅ ተሰማ/

/ሁሉም ፀጥ አለ/

/እቴጌ ጣይቱ ከጀርባ በርካታ ሴቶቸ ን አስከትላ ገባች/

/ፈትል ቀሚስዋንና ሱሪዋን አድርጋ ዝናር ታጥቃ ጠመንጃ ይዛለች/

/የተቀሩትም ሴቶች ከጠመኝጃ በቀር አለባበሳቸው እንደ እሷ ነው

ጣይቱ፡-ወዴት ? ወዴት ወዴት ነው ሰው ሳይዙ ጉዞ

ምን ተይዞ ?

/ሁሉም በአንድነት ወደ ጣይቱ ይዞራል ሁሉም ቅሬታ ተሰምቶታል /


ምኒሊክ፡-የለም እመቤቴ እኔማ አንችን አሳርፌ

/ሳታስጨርስ እገባች/

ጣይቱ፡-የምን ዕረፍት ነው ጌታዬ ዕረፍት ይሉ ነገር

እንዴት ነው የሚሆነወው ሀገር ስትደፈር ?

ምኒሊክ፡-ጎዞው አድክሞ ብንዘልቀው

እመሃል መሰናክልም ቢኖረው . . .

/አሁንም አቋርጣ ትገባለች /

ጣይቱ፡-ጌታዬ መሰናክሉን ይተውት

መሰናከል ከተባለ መሰናክል እንደሆ ሞት

ሞት ደግሞ ተሸክመነው የምጓዘው ፀጋ

ለሀገር መሞት አያዋርድ ያሰጣል እንጂ ታላቅ ዋጋ

/እቴጌ የልብ የልብ ተሰምቷት ፈንጠር እያለችና እያበራታች/

የጣይቱ ክብር የጣይቱ እመቤትነት

የተሰራው በኢትዮጵያ እምብርት

ዳር ሲነካ ዳር መሃል ዳር የሆነ ዕለት

ጣይቱ ባሪያ እንጂ እንዴት ልትደርስ እቴጌነት?

/ትዝብት አዘል ልሳን/

የለም ሴት ነሽ ነፍጥ አታነሸም

ቃታ ስበሽ አትተኩሽም

ጦር ሰብቀሽ አትወረውሪም

ጋሻ መክተሸ ፈለፃ አትጥይም

በፈረስ በበቆሎ ሽምጥ አትጋልቢም

ሮጠሸ ዘለሽ ጠላት አትይዥም

ስለት ሰንዝረሽ ከቶ አትበጥሽም

መድፍ ተኩሰሽ ከልብ አይደርስም

ከሆነ ነገሩ እንቅር ግድ የለም

ግን !

/ፈታ /

አገር ናትና መቅረት መጎለት ከቶ አይታሰብም


የማን አንጀት ነው ታጥፎ የሚተኛ

የማን እግር ነው ሚሆን ዳተኛ

የማን እጂ ነው የሚሆን ለማኝ

የባሪያ ያህል ግፉኝ የሚመኝ

ዛዲያ . . .ባልዋ . ፣ ንጉሷ . . ወንድሟ ወሰን ሲቀበር

ልጇ እህቷ አባቷ ተደፍተው ሲያድሩ በባእድ አራር

ከአገር በላይ ባል የለም

ከአገር በላይ አባት የለም

ከአገር በላይ ልጂ የለም ልጂ የለችም

ከአገር በላይ ንጉሥ የለም

/ፋታ/

አገሬ ስትቆም ኢትዮጵያ ስትቆም ነው

ሌላው አብሮ የሚቆመው

ክብሯ እውነቷ እምነቷ ሲቀጥል ነው

ወገኔ እስትንፋሱ ሚቀጥለው

/ወደ መድረክ ጫፍ እየመጣች/

ጎበዝ

በል ክንድህ እንዳይዝል ጉልበትህ እንዳይታጠፍ

አካልህ የተልባ እግር እንዳይሆን ለሀገርህ ስትል ተሰለፍ

ለራስህ ስትል ተሰለፍ

ሒድና ገስግሰህ ግታው

አመጣጡ ሊያረክስህ ነው

አመጣጡ ሊያፈርስህ ሊጥልህ አንገትህን ሊያስደፋው

ባሪያ አድርጎ ሊሸጥህ በየ አገራቱ ገበያው

መሬትህን ደፍቶ ሊደፋህ

አንገትህን ቆልምሞ እንደ ከብት ሊያርስብህ

ከሰውነት ተራ አውጥቶ እንደ አውሬ ከጫካ ሊያድንህ

ገድሎ በየፈፋው ሊጥልህ

አልገዛ ያለውን ንጉሥህን አዋርዶ ክብርህን ከላይህ ሊገፍህ

ነውና አመጣጡሂድ በለው ውጣ በለው


በእመቤቴ እለምንሀለው

ከማርከው አትማርህ አትማረው

ሂድ . . . . በለው . . . በለው . . . በለው

/በዚህ ግዜ ወ/ሮ ጣዲቄ ቀረርቶ ትጀምራለች/

ጣዲቄ ፡-አትደፈርም ሲል ደፍሮ የሞተላት

ሴቶቹ ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-እምዬ ኢትጵያ ስንት ጀግና እያላት

ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡- እንዴት የሴጣን ልጅ ሊረግጣት ይመኛት

ሴቶቹ፡ ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-እንኳ ጀግና ቀርቶ ነፍጥ የታጠቀው

ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-አራሹም ይዘልቃል ሞፈር የጨበጠው

ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-አገር ያለች እለት ኢትዩጵያ ስትቆም

ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-ያን ጊዜ ይፈታል የታላቅ ጀግና ህልም

-ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-ሸሸተህ ቀርተህ እንዲሁ ምኒሊክ ይቀየም

ሴቶች፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-ሸሽተህ ቀርተህ እንዲሁ ጣይቱ ትቀየም

ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-ሸሽተህ ቀርተህ እንዲሁ በጀግኖ ች ተረገም

ሴቶቹ፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡-ሸሽተህ ቀርተህ እንዲሁ በኢትዮጵያ እንዳትቆም

ሴቶች፡- ዋ . . .ዋ

ጣዲቄ፡- በል ዝለቅ
/ባልቻ ይገባሉ/

ባልቻ፡-እኔ ያንተ ልጅ ያንተ ቡችላ

ተቀባይ፡-በለው

ባልቻ፡፡-ደሙ የጠማኝ ለጠላት ተኩላ

ተቀባይ፡-በለው

ባልቻ፡-ሒይ በለኝና ሒድ ላሳይህ

ተቀባይ፡-እሰይ

ባልቻ፡፡-የጠላት አንገት ልበጥስልህ

ተቀባይ፡-እንዲያ ነው

/ጎበና ይገባል በሌላ ምት/

ጎበና፡-እረግ ጀግና ነኝ የጀግና ውላጂ

የጠላት አንገት ሁሌ አወራራጂ

ደሜ ቁጡ ነው ሲነኩት ሚግል

ካልጠላ በቀር ማይገላገል

እንኳን ተወርዶ እንኳ ታስቦ

ወዲያ መጣል ነው ይህን ተስቦ

/ ጦና ይገባል/

ጦና፡-አትምጣ ሲሉት ከመጣማ አይቀር

አዚህ መቅበር ነው በአገሬው ምድር

ገፉ ገፋና ወዲህሲልኩት

ደሙ ደመ ከልብ ሆነው አገኙት

ልክ እንደፈረስ እንደጋለቡት

ሽምጥ ለቀው ለሞት ዳረጉት

/ጓንጉል ይገባል /

ጓንጉል ፡- ጠላት ዘልቆ በሀገሬ ምድር

የምንስ ቸል ነው የምንስ እረፍት

ኩርፍያን ጥላቻን ወዲያ መጣል

ወሰን ለመውደቅ እንዘልቃለን


የጀግና ጀግና ጀግና ሆነን

የጀግና ጀግና ጀግና አፍርተን

የኢትዮጵያ እውነት እንሰብካለን

/የሴቶች ዕልልታው ይቀልጣል/

/ምኒሊክ ጉዞው ሊጀምሩ ሲሉ ሶስቱም በህብረት ይጮኃሉ/

ሶስቱ፡-እረ ጌታችን ንጉስ ነገስት

በእመብርሀን ፊትዎን ያዙሩት

/ሁሉም ፀይላል/

/ምኒልክ ባሉበት ቆመው ዞረው ያዩዋቸዋል/

ምኒልክ፡-እንግዲያስ

/መለስ ይላሉ /

መጀመሪያ ጂያ ኮምን፤ ባሪያቴሪን፤ አንቶኔሊን ከልባቸው አውጧቸው

በደማችሁ ምላችሁ ብተከተሉኝ ጀግኖቼንናችሁ ድሮምማውቃችው

መንገሻ፡-ይህው ከልቤ ንቅል አድርጌ አወጣሁኝ

ሐሰት ከሆነ የኢትዮጵያ አምላክ ይፍረድብኝ

ወሌ፡-እኔም እመ ብርሀን ትፍረድብኝ

እንደመስቀሉ ይስቀለኝ

እንደ መቀመቅ መቃብር ይሰንጥቀኝ

ብሩ፡-የአገሬ አምላክ . . .

ምኒልክ፡-አንተ › . . አንተ . . . ተወኝ . . .ተወኝ

የአንድ ዚያ ብቻ ስላልሆነ ጓንጉል ስላለ አንተ ተወኝ

ይልቅ ወዲያ ውሰዱልኝ

/ባልቻ ሲያዝ ሁለት ጭፍሮቹ ሲበሩ ወጥተው አንከብብበው ወደ ውስጥ ያስገቡታል/

ምኒልክ፡-እግዝያብሔር ደማችሁንይጠበው

ምሬታችሁን የእንቆቆ ፍሬ ዝፍዝፍ ውኃ ያድርገው

የኢትዩጵያ አምላክ የቀደመ ቅን ልቦናችን ይመልስልኝ

ኑ እናንተ የአሀሬ ጀግኖች ተከተሉኝ

ሁላችንም ወሰኗ ላይ እንገናኝ


/በዚህ ግዜ አማርኛው ከጉራግኛ ጉራግኛው ከኦሮምኛው ኦሮምኛው ከሲዳማ ፤ወላይታ ፤ጋሞው ተቀላቀለና እተፎከረ …..እተዘለለ
በህዝብ በሃል ሚኒልክ መሐል …..ሁሉም ወጥተው አለቁ/

ተራኪ፡-ሄደ የኢትዮጵያ ልጅ ገሰገሰ

ለሀገሩ ለወገኑ ሊሞት እንደጉንዳን ተርመሰመሰ

ሽቅብ ወደ ጠላቱ ተስፈነጠረ

ብርንዶ እንዳየ አሞራ ረሀብ እያጋለው በረረ

ያባዳኝው የጦር አበጋዝ የጀግኖች ጀግና ገበየው

የእናት ሀገሩን ኢትዮጵያ መደፈር አልታይ ቢለው

በጀርባ ሰንጥቆ ገብቶ ጠላትን አፈር ሊያስግጥ

ከጀግኖቹ ልባም ዘማች ጋር ጠላት መሀል ሲገጠገጥ

ጠላት በተኮሰው አረረ ተቃጠለ

ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ በኢትዮጵያ ምድር ተከነበለ

እንዲያ የጎበረው ጠላት

ሊያው በግማሽ የቀን ልኬት

አምባላጌ ተገረሰሰጣሊያን የኮራበት ምሽግ

ጠላት ከሞት ሲሸጋሸግ

ከማርከው አልምርህምን ቃል ያተመው ጀግና

ጠላቱን አምባላጌ ላይ አድቅቆ መቀሌን ዘለቀ እንደገና

/ፋታ/

/ቅዛዜ ልሳን /

አባዳኝው የሰጋው ደረሰ

ወገን በጠላት መድፍ አፈር ለበሰ

እንዳ እየሱስን ታክኮ በገነባው የምሽግ ግንብ

ወገን ወደ ጠላት እንዳይዘልቅ ሲገደብ

ትርፍ እልቂት ሆነና ወገን መርገፍ በዛበት

እልህ የወጠረው የኢትዮጵያ ልጅ ሞት ከአናት ዘነበበት

ድል እንደ ኮኮብ ሰማይ ራቀች

ኢትዮጵያ ተፈታች

በዘዴ የተሞላው ልብዋ ድንቅ ብልሀት ሲፈጥርላት

ጣይቱ ታላቅዋ ንግስት ጠላትን በውሀ ጥም ስትፈታላት


ልጆችዋ ተግተልተትለው ከምሽጉ ሲደርሱላት

ጠላትዋን ረግጣ ቆመች በጣይቱ ታላቅ እምነት

በሴት መላ ድል ሆነ

የጠላት ወረራም መከነ

ጭራውን እንደ ውሻ ቆልፎ ሽቅብ ወደ አድዋ በነነ

አባ ዳኝው ንጉሥ ሳይሆን አዝማች ሆኖ ዘለቀበት

ያውሮጳን አምስት ጀነራሎች ጀግኖች ይዞ ገጠመባት

በጣሊያን ሳቢያ አውሮፓን በአድዋ ከርሰ ከተታት

የጥቁር አለም በራ የድል ቀንዲል ተለኮሰ

የወገኖቹን የብሶት እንባ አባዳኝው በኩራት አበሰ

በቅኝ ግዛት የወደቀው ጥቁር

ቀና ብሎ ተራመደ እድሜ ለኢትዮጵያ ክብር

ከአፍሪቃ እሰከ አውሮፓ ጥግ

ከላቲን እስከ ኢሲያ የድል ብስራት ሲንቦገቦግ

አለምን ልግዛ ያለው ነጭ አፈረ

አንገቱን ቁልቁል ሰበረ

የአለም ህዝብ ደነገጠ

የጥቁር ክብር ከፍ ብሎ ተረጋገጠ

የሰው ልጂ ካዳም በተመዘዘ አንድ ዘር

በአለም ዙሪያ ቢመነዘር

ዞሮ መሰረቱን አይስትም

ይኃው አየን በኢትዮጵያዊነት ሲታተም

ሲል መሰከረ የአለም ሰው

የኢትዮጵያ ጀግና የማይነካ ከመጡበት ሚያደቅ ነው

/ፋታ/

እኛ ኢትዮጵያዊያን

ያአለም ጥቁር ህዝቦች ተገን

ከአፈራችን ሰው ተፈጥሮ

በአለም ህዝቦች የቸርን


የታላቅ ወብዝ ባለቤት

የጥቁር ተገን የሆንን

ከአፍሪቃ ምድር አልፈን

ላቲን ደርሰን

እስያ ገብተን

የነፃነት ቀንዲል የለኮስን

መብት ሆነን የቆምን

እውነት ክብርን የሰበክን

አንዳችም የሰው ምድር ያልረገጥን

ስንደፈር የማንተኛ መፍረስ የማንችል ህዝቦች ነን

ኮምፒውተር ፀሁፍ አስታውሽኝ በነጋ

ተፀፎ ተጠናቀቀቴአትር ክፍል

አሰታውሽኝ በነጋ ቤት

5/4/2014

ሰዓት 11 ፡ 53
ማስታወሻ

ይህንን ድርሰት እንድፅፍ ወንድሜንና የልጄ የአሜን ንጉሡ የክርስትና አባት ኤፍሬም ልሳኑ በሌላ ጀግና ታሪክ ዙራያ አድርጎ
በ 25/3/2014 ዓ.ም ደውሎ አሳሰበኝ፡፡

እግዝአብሔር አምላክ ደግሞ ይህንኛውን ፈቅዶ ሊሰጠኝ ፅፌ ለመስጠት በቃሁኝ፡፡

ድርሰቱ የተፃፈበት ቀን፡- የፊታውራሪ ገብረ ህይወት መኮንን /ገብርዬ /የታላቁ ንጉሰ ነገስት የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን የጦር አበጋዝ
ታሪክ በተከታታይ የቴሌቭዥን ፊልም በ 40 ደቂቃ ልኬት ለ 16 ክፍል በ Dstv chana ለማቅረብ ልፅፍ ግንቦት 26/2013
ዓ.ም ወደ እዚህ ውደ አቶ ሞገስ ጎርፌ ልጃቸው ምስጋና ሞገስ /ሚሹ/ ከሚኖርበት ግቢ ገባሁ፡፡

እዚህ ጊቢ ከሚሹና ከሁለቱ ልጆቹ ፍቅር /እማ/ አሜን /ኤሚ / ምስጋናው እና ከተስፋዬ ከቀመር ጋር በፍቅር ቆየሁ ፡፡
በተለይ በተለይ ሮፌ/ Rofi/ ከተባለ ውሻ ጋርማ የአባትና ልጂ ያህል ሆነን ዘለቅን ፡፡እናም ሁሉም ተጠናቅቆ ልክ በገባሁ በስድስት
ወሩ ኀዳር 26/2014 ዓ.ም በ 27/2014 ሙሉ ለሙሉ ጨርሴ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ስዘጋጂ ተፃፈ፡፡

ይህ ድርሰትየተፈቀደነው፡፡በእግዚያብሔር ፍቃድ ማስታወሻም እንዲሆን በመጨረሻው ቀን ተፃፈ የደብረ ዘይት የሚሹ


፤የእማ፤የኤሚ፤የቀመር፤የተስፋዬ፤የአልማዝ በጣም ደግሞ የምወደው ውሻ ሮፌ /Rofi /ማስታወሻ ይሁንልኝ፡፡

ንጉሡ ጌታቸው

26/03/14

ደብረ ዘይት

You might also like