You are on page 1of 5

ቀን 16/10/2014 ዓ.

የሣሙና ኑሮ- ሥነ-ግጥም ላይ የተደረገ (የመመረቂያ) ሂሳዊ ዳሠሣ

ደራሲ፡- ዶ/ር ሙሉጌታ ስመወርቅ

አቅራቢ፡ ዳኜ አበበ

ቦታ፡- አአዩ-የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም-ራስ መኮንን አዳራሽ/ገነተ-ልዑል

መግቢያ፡- የደራሲ ዶ/ር ሙሉጌታ ስመወርቅ ‹‹የሣሙና ኑሮ›› የግጥም ስብስቦች በ221 ገጾች ተቀንብበው የተሰደሩ ሲሆን
ብዛታቸውም 163/147 (?) ናቸው፡፡ የሣሙና ኑሮ የግጥም ስብስብ ከዚህ ቀደም በ2004 ዓ.ም ኒዮርክ ውስጥ ታትሞ ለንባብ
የበቃ ሲሆን እነሆ በ2014 ዓ.ም በድጋሜ ኢትዮጵያ ውስጥ ታትሞ ለንባብ ቀርቧል፡፡

የግጥሞቹ አጠቃላይ እይታ፡

1. ግጥሞቹ በቀላሉ ተነበው፣ ውስጠ-ምስጢራቸው እንዲሁ በገደምዳሜ የማይገኝ፣ ግልብነት የሌላቸው፣ ይልቁንም
እሳቤያቸውን ለማግኘት፣ ለመደርደር ተዳጋጋሚ ንባብን የሚጠይቁ እንዲሁም የማይሰለቹ የስንኝ ጉድኝት
የተሞላቸው ናቸው፡፡
2. የግጥም ይዘቶችን/የአጻጻፍ ይትብሃሎችን/ርዕሠ-ነገሮችን ከደራሲው የሙያ መስክ አንፃር ስንመዝናቸው (በነርቭ ስነ-
ህይወት ጥናት እና በስነ-አእምሮ-Neurobilogy and Neural science and behavior በእርግጥ ገጣሚ፣
ደራሲ እና ሙዚቀኛም እንደሆነ ከሕይወት ታሪኩ ለመረዳት ችያለሁ) አዲስነት የማይታይባቸው፣ ይህም ማለት
ደራሲው ተሰጥኦ ብቻ ሳይሆን ለሥነ-ጽሑፍ ብልሃት ቅርበት እንዳለው የሚመሰክሩ (እጅጉን የዳበረ ልምድ)፣
ከእነዚህም መካከል- የቃላት ሃብታምነትን የተጎዳኙ፣ ረብ ባላቸውና በዘይቤ በበለፀጉ የትኩስ አስተሳሰቦች
ማቅረቢዎች የተሸመኑ፣ እንደ ሙዚቃ የሚንቆረቆሩ የስንኝ ተጣምሮዎችን ማየት ይቻላል፡፡
3. ብዙዎቹ አያዎነት የሚበዛቸው፣ ገድሎ ማዳንን ወይም አድኖ መግደልን ስልት የተከተሉ ይመስላሉ፡፡ በመሆናቸውም
አጀማመርና አፈጻጸማቸው አይገመቴነት ይልቁንም ሳቢነት እንዲኖራቸው እና ደግመን ደጋግመን እንድናጠይቅ
ዕድልን የሚሰጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡
4. የደራሲውን ታዛቢ ጠያቂነት፣ የሚያጎሉ በርካታ ስንኞች ስምረትና ስክነትን የተሞሉ ናቸው፡፡ በተለያየ አውድ ውስጥ
የሚስተዋሉ የዘመን ብስልና ጥሬ ማህደሮችን ይነቅሳል፡፡
5. ደራሲው አሁን ያለበትንና ያደገበትን ብሎም ከዚህ ቀደም ያለፈበትን፣ እያለፈ ያለበትን እንዲሁም ማሕበራዊ
በመሆናችን ከተፈጥሮ ጋር በምናደርገው ግብግብ ብዙዎቻችን የምንጋራቸው፣ ማሕበረሰባዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ፣
ሀገረ-በቀልነታቸውንም ያልሳቱ የእጅ ቀለሞችን በጉልህ ያጋራናል፡፡
6. በዲያስፖራነት ስሜት የተቃኙ፣ የተቀረጹ ቢኖሩም ስለሀገር (ኢትዮጵያችን) ምንም አልሰራሁልሽ ተምኔት የተከነዱ
በሳል ብዕሮች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ አኳያ አንድ በውጪው ዓለም ለብዙ ጊዜያት እንደቆዬ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን፣

1
ከባሕልና ቋንቋዋ ጋር በአዕምሮው ተሸክሞ ይዟት እንደሚዞር ግጥሞቹ በግልፅ ይሰብኩናል ሳይሆን እንድንኖራቸው፣
እንኖራቸው ዘንድ የተፈረዱብን ሁሉ አብረውን ተቃኝተዋል፡፡
7. ስለፍቅር ተብሰልስሎት ጊዜ የተሰጣቸው ብዙ ሥነ-ግጥሞች ቢሆኑም፣ አቀራረባቸው በተለመደው ግልብ የፍቅር
ማንበሪያ ዘዴዎች ሳይሆን እራሱ ፍቅር በቃላት ግዘፍ-ነስቶ የቀረበበት መንገድ፣ (ብዙ የፍቅር ግጥሞች) እያደሩ
እንደምድጃ ፍም እሳት ረመጨት የሚፋጁ፣ እንደ አበባ የሚፈኩ፣ ውስጠ-ግለት ተኮር የሆኑ ናቸው፡፡
8. ማሕበራዊ እውነታን የሚያሄሱ፣ በተለይም እንደ ሼክስፒሩ ሃምሌት ‹‹መሆን አለመሆን›› ሥነ-ሰብዓዊ የትውልድ
መንታ መንገዶች ላይ የተዋደዱ ተጣምሯዊ ግዴታዎችን የሚሞግቱ ተሰናስሎዎችም ቀርበውበታል፡፡
9. ትናንት እና ዛሬን ያየበት መነፅር፣ በትናንተ ትዝታችን የተጠፈነግንበትን የግዴታ አዙሪት የ‹‹እያረሩ መገላበጥ›› አባዜ
‹‹ካምና ተበድሮ›› ሲል፣ የትናንት መልካምም ይሁን መጥፎ ልማድ እንዴት ተሻጋሪ እንደሆነ አዕምሯችን ላይ
ይስልብናል፡፡ (57)
10. አንዳንድ ጊዜ በግጥም መካከል የተሰኩ ፍልስፍናዊ እይታዎች እንደ ግጥም ቤት የማይመቱ ግን ሙዚቃዊ ቃና
ያላቸው አጫጭር አባባሎች፣ የበለጠ ምርምርን ይጠይቃሉ፤ ለእኔም ለፍቺ የጠነከሩ፤ ምናልባት አንድ ላይ ቢሰበሰቡ
ብዬ አሰብኩና፤ በሌላኛው ጎን ስናዬው ደግሞ በየግጥሞቹ መካከል መሰካታቸው እንደ እፎይታና ውበት ጎልተው፣
ቆም እያልን እንድናጤናቸው ያስገድዱናል፡፡ ምሳሌ- ( ገጽ-58፣ 66፣71፣ 81፣ 91፣ 94፣ 108፣111፣ 119፣ 129፣
134፣ 146፣ 172፣ 186፣ 193፣ 221)
11. ሊቀ-ማዕምሩን የ‹‹ከወዴት አለ ሚናህ›› ጥሪ፣ መለከት የሚያስተጋቡ (67-አሁን ላይ ሆነን በሚከንፈው የጊዜ ሃዲድ
ቁልቁል እንደ ንሥር ብንመለከተው የበለጠ ውርጅብኝ ሆኖ በተጻፈ የሚያሰኝም ጭምር ነው)፡፡ ኅሊናዊ ማዕምርነት
እና ሆድ አደርነት የሚነጻጸሩበትም ነው፡፡
12. ዋነኛ የመጽሐፉ ጭብጥ፣ መልዕክት-የሌሎች ግጥሞችም ማጠንጠኛ- የሣሙና ኑሮ (68፣ 112-ኮሜዲ ኑሯችን)
13. ‹‹አካፋን አካፋ፣ ዶማን ዶማ›› ስትለው አካፋ ለምን አካፋ፣ ዶማም ለምን ዶማ ተባልሁ ብሎ ያጎብርብታል፣ አይነት
ግጥሞች ተቀምረዋል፡፡
14. በየኑሮ ሣሙና- ያልተዳሠሠ የሕይወት ምህዳር፣ የጊዜ ማዕቀፍ የለም፡፡ ትናንት፣ ዛሬ፣ ነገም ጭምር! በዚህም አኳያ
ማህበረ-ፖለቲካዊ፣ ትምህርታዊ፣ ርዕዮታዊ አንዋራት ተቃኝተው ተሰድረዋል፡፡ (70)
15. አፈ-ቃላዊ ተረቶች እንዴት ተቃንተውና ተሳብረው እንደሚቀርቡ እና ከሀገራችን ታሪክ ጋር የተሳሰሩብት አውድ
የሚደንቅ ነው፡፡ (ይህም- ጎባጣ ተረቶች በሚል---72-3)
16. በተለይም ጠንካራና ምርምርን የሚጠይቁ ግጥሞች-ከዘመኑ የአገጣጠም ስልት ወጣ ብለው ቅመሱኝ፣ ድገሙኝ፣
ሰልሱኝ የሚሉ ናቸው፡፡ ቋጠሯቸው ጠንከር ያሉ ናቸው፡፡ ምሣሌ፡- (77-78 እና 79) በጥቂቱ!
17. ቋንቋን ምርኩዝ አድርገን ሀገራችንን ምጥ ላበዛንባት እኛ፣ ከፍጥረተ-አዳም ጋር አገናኝቶ የሚለውም አለው!
ይጠይቃልም፤ ይፈላሰፋልም! በተለይ ቋንቋ እና ሃይማኖት ከሰውት ከበለጠ፣ ሰዎች አይደለንም፣ እንደሚል
ወስጄዋለሁ፡፡ (82፣ 83)

2
18. ስለኢትዮጵያዊነት ብዙ ቦታ ላይ የተቀነቀነ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊነት የተገለጠበት መንገድ በተለይ ከገጽ 85-88
እጅግ ልዩ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንዴት ይገለጻል፣ ስንል ለአሁኑ ውጥንቅጥ መልስ፣ በተለይ ደራሲው ምን ያህል
አገሩን አዝሎ፣ አዕምሮው ውስጥ ሰንቅሮ ይዟት እንደሚዞር ያሳየናል፡፡ (ከላይኛው ጋር እሚዋሀድ)
19. የስደት አገር (አሜሪካ) የፓርኪንግ ሥራን አስቸጋሪነት ወይም ከቀልብ ሳይሆኑ ኑሮን በተለያዬ ሰው ስሜት ሥር ሆኖ
በማስተናገድ መግፋት ምን ያህል አስከፊነት ያለው አውድ እንደሆነ በቴአትር ጨዋታ መልኩ ለማሳየት የተሞከረበት፣
የጊዜ አጠቃቀሙ ኑሮው ልክ እንደ እሳት ዳር ቢራቢሮ የሚቃዥ እረፍት የለሽ መሆኑ የታየበት (95-101)
20. አጭር ታሪክ መሰል (አጭር ልቦለድ) ትዝብት፣ ወጎች፣ ምሉዕነት ያለው ሀሳብ ማስተላለፍ፣ በተለዬ ስልት የቀረበበት
(106፣ 163-5፣ 173-4/ጣፋጭ ወግ)፣ በጣም ተጨማሪ ወጎች-በጣም አጫጭር (218 እና 19 እጅግ አጭርና
ጣፋጭ)
21. ጣምራ ትርጉም ጠሊቅ ስሜት ያላቸው ግጥሞች- ለሚስት፣ ለሀገር፣ ለእናት (132-133)፣ ስለ ትዳር፣ ሴትና ወንድ
ግንኙነት፣ አዲስ የሥነ-ግጥም ማቅረቢያ ዘዴን ተጠቅሟል (181- አጋብቶ ያኑረን)
22. ስለ ፍቅር የተጻፉ ግጥሞች ሥር-ተከል፣ አዲስ በቀል፣ ልዩ ዕይታና ማዕቀፍ ያላቸው መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡
ምናልባትም የደራሲውን የፍቅር ጉዞ ውስብስብነት… (153፣ 167)፣ ብዙዎች ተምሳሌታዊ ናቸው፣ ስለ ፍቅርም
ጭምር የተጻፉት (ምሳሌ 113-16)
23. ስለ ስደት ኑሮ፣ ምጸትና ስላቅ እንዲሁም ሁነቶች ምሬት (189-9) ‹‹ያገር ጅብ መልዓክ ነው?›› በሚል አያዎነት
ቀርቧል፡፡
24. ስለ ሰውነት፣ ሰብዓዊነት የተዘመረበት! (በተለይ ገጽ 192) ‹‹ለእኔ አገሬ ሰው ነው››
25. ረጅም ግጥሞች፣ ከእነዚህ ሁሉ-ሁለት ናቸው፤ (195-200፣ 208-14) በተለይ ሁለተኛው፣ ትውልድን የወቀሰበት፣
የጠየቀበት፣ ያነጻጸረበት፣ ፈረንጅ የሳቀብን የደራሲው ትዝብት (አሁናዊ) በእጅጉ የታየበት፣ የንሥር እይታ ‹‹ፍርምባ
በቆሎ›› (208-2014)

ማጠቃለያ-ከሥነ-ጽሑፍ እና ሥነ-ግጥም ባህርያት አኳያ በጥቂቱ

1. የኑሮ ሣሙና የሥነ-ግጥም ስብስብ፣ ዮሐንስ አድማሱ እንዳለው አንድም ‹‹የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነ-ጥበብ ኃይል
ግዘፍ ነስቶ፣ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው›› ወይም ብዙዎች እንደሚሉት “originality, quality,
creativity and pleasure” ተጣምረው የገኑበት የሥነ-ግጥም ስብስብ ነው፡፡ እንደ ካልደን የሥነ-ጽሑፍ ምደባ
በ“Textual meaning and referential meaning” እጅግ የዳበረ የግጥም ሰብስብ ነው፡፡
2. ከሁንተናዊ ባህርይ አንፃር “Timelessness, Eternity, Universality, and Permanence” ባህርያት ግልፅ
መለያዎች አሏቸው፡፡
3. ከተለያዩ የሥነ-ግጥም ትርጓሜዎች አኳያ (የሣሙና ኑሮ) የዊልያም ዎርድስዎርዝ ‹‹ምት ያለውና ምናባዊ የሆነ
የብርቱ ስሜት መግለጫ…በለሆሳስ የታወሱ ጠንካራ ስሜቶች ከውስጥ ገንፍሎ መውጣት›› እንዲሁም ከሀገር

3
በቀሎቹ የሥነ-ጽሑፍ ባለቅኔዎች መካከል ‹‹የግጥም ፋንታ የሰው ልጅ የኑሮ ዓላማውን ለማሳካት የሚያደርገውን
ግላዊ መፍጨርጨር…ከዚህ ዓለም ችላ ባይነት ጋር አያይዞ ማብላላት ይመስለኛል፡፡ ማብላላት፣ ማፋጨት፣ እያፋጩ
ተቃራኒዎችን ማጣመድ፣ ተመሳሳዮችን ማለያየት፤ ከግጭታቸው ላንዳፍታ እንደበራሪ ኮከብ የሚታይ ግልጥ
መፍትሔን ማዋለድ… እንደ እብነ በረድ የሚዳሰስም ባይሆን ባጭሩ የስንኞች መገናኘት፣ የድምፅ ስልት አወራረድ፣
ከቃላቱ የሚፍለቀለቁት ስዕሎች አመጣጥ፣ ወረቀት ላይ ታትሞ የሚታዬው የግጥሙ ጠቅላላ ቅርፅ፣ የመስመሮች
እጥረት የሚያስከትለው ቁልቁል የስሜት ጥድፊያ ወይንም የመስመሮች መራዘም የሚፈጥረው ከባድ ተጎታችነት
የስሜት የሃሳብና የዜማ መወሳሰብ›› ሲል ብያኔ ያሳረፈው ሰለሞን ደሬሳ እና ‹‹የአካባቢ ልዩ ኃይሎች በመንፈስ ላይ
በሚያሳድሩት ተፅእኖና በሚያስከትሉትም የኅሊና ጭንቀት፣ የተለዬ ሐሳብ በልቦና ውስጥ ይፀነሳል፡፡ ያም ሐሳብ
ሲብላላና ሲጋጋል ከቆዬ በኋላ በልዩ ልዩ መልክ በአንደበት በኩል ይፈነዳል›› ሲል የገለፀው ኃይሉ ገ/ዮሐንስ
እንዲሁም ‹‹ማራኪና ምርጥ በሆኑ ቃላት ምታዊ ድርደራ የሰውን ልጅ ውስጣዊ ስሜት ጠልቆ በመግባት፣ ህልሙንና
ሰብዕናውን ለመግለፅ…የእውነት ነጸብራቅ፣ የሕይወት ሃያሲና ተምሳሌትም ነው፡፡ የጠራ መንፈስ የሚገለጥበትም
ነው…›› የሚሉት የአያልህ ሙላቱ ሃሳቦች ኩልል ብለው ተንፀባርቀውበታል፡፡
4. ከተጨባጭነትም አኳያ ‹‹ከጠጣርነታቸውና እምቅነታቸው የተነሳ በአንባቢ አዕምሮ ውስጥ የሚጭሯቸው ስሜቶችና
የሃሳብ ብልጭታዎች የማይመጠኑና የማይገመቱ ናቸው›› ከምናባዊነታቸውም አንፃር፣ በተፃፉት ቃላት ኃይል
አስገዳጅነት፣ በተለይም የደራሲው ስሜት የሚሰማን፣ እውነቱ ገዝፎ የሚታየን፣ በሕመሙ የምንታመም፣ በደስታው
የምንስቅ፣ በስቃዩ የምናነባ ተደራሲያን እንሆን ዘንድ በእጅጉ ይጋብዛሉ፡፡ በሦስተኛነት በተለይም በባለሙያ እጅ
ሲቆላ እንደሚፈካ ፈንዲሻ፣ በኑሮ ሣሙና የግጥም ስብስቦች ውስጥ፣ የታመቀ ኃይል ያላቸው ቃላት ሲፈቱ እጅጉን
ይፈካሉ፣ ያብባሉ፣ ይደምቃሉ፤ የተደበቀ ውበታቸውም ሲገለጥ፤ እምቅና ቁጥብነታቸው ይታያል፡፡ በተጨማሪም
‹‹ቅኔ ቋንቋን የተመረኮዘ ሙዚቃ ነው፡፡ ቃላት በስሜት እየፈሉ፣ ከነጠሩ በኋላ የሚያስገኙት የሃሳብ አረቂ ነው፡፡
እርግጥ ሙዚቃ ከሥዕልና ከቅኔ በጣም የረቀቀ ቢሆንም፣ በጣፋጭና የድምፅ ስልቱ አድማጭን እያሳሰበ ማስደሰቱንና
ሃሳብ መቀስቀሱን አይተውም›› እንዳለው ገ/ክርቶስ ደስታ፣ የግጥሞቹ መሰረቶች የሆኑት-እንጉርጉሮ፣ ዝማሬና
ተብሰልስሎት እንደ ወራጅ ውሃ ይፈሱበታል፡፡ በመሆኑም ስሜታችንን አነቃቅተው በውስጣችን አንዳች ሰብዓዊ
ስሜት ያሰርፁብናል፡፡ ሳሙኤል ታይለር ሥነ-ግጥምን ሲገልጽ ‹‹የተመረጡ ቃላት በተመረጠ ቦታቸው ሲሰደሩ
ነው›› እንዳለው ያላቸው ጣዕም ልዩ ነው፡፡
5. ከውስጣዊ ባህርይ አኳያም ቢሆን፣ ምት፣ ምጣኔ፣ የቃላት ምርጫና ዘይቤ (ምስል ፈጣሪነት) ልክና መጠን የጸኑ
ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በተለይም ከእማሬ ይልቅ ፍካሬ ቃላት ተደራቢ ትርጉማቸው የጎላ፣ የተለዬ ግብ መቺነትን
የሚያራምዱ ሲሆኑ የቃላተ-ምሁር አጠቃቀም ስልት በብዛት ተግባር ላይ ውሏል፡፡
6. ስብስቦቹ በተባ ሃሳብ ተመስርተው፣ ለስሜት ቅርብ የሆኑ ምናባዊ ምስሎችን በመግለጽ በሰላ ብዕር የተቀናበሩ
በግልጽ የቋንቋ አጠቃቀም ብልሃቶች የተዋቀሩ ሥነ-ግጥሞች ስብስብ ነው፡፡
26. በአጠቃላይ፣ የተዋጣለት እርማት፣ አወቃቀር፣ አካዳሚያዊ እውቀትን ያማከለ የቃለ-ጽሑፍ ክህሎት፣ ሃሳብን ያዘሉ
ስንኞች ሽብልቅ ትዕይንትና ህብረት የሚታይበት፣ እንዲሁም ስሜትን ለማንጸባረቅ (ለማለት) ሳይሆን ጥጣሬ፣ ፍካሬ

4
የተሞላቸው፣ በእውቀት (ሳይንሱን) ከልምድና ተግባቦት የዘገኑ፣ ውስጠ-ምርምርን፣ ትኩረትን፣ ድጋሜ ተጢኖን
የሚሹ በምልዓት የፈኩ፣ ሲተነተኑ እንደፈንዲሻ የሚዋቡ ሆነው በትጋት የተዋቀሩ ናቸው፡፡ (ምሳሌ-121)

አመሰግናለሁ!

You might also like