You are on page 1of 3

ሀገር ማለት ሰው፤ ሀገር ማለት መሬት ነው። ያለሰውም ያለመሬትም ሀገር የለም። ሰው "ሀገሬ" የሚለው መሬትና

'የሀገሬ ልጅ" የሚለው ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የፖለቲካ ንክኪ ትሩፋቶች ናቸው። መሪዎች ለጀግና
መንፈሳቸው አልያም ለሀገር ወዳድ ባሕርያቸው ሲሉ አንዱን ሲያስገብሩ፣ ግዛታቸውን ሲያሰፉ፣ ሕዝብ ሲቀይጡ፣ ሀገር
ሲደባልቁ ይኖራሉ፤ በዚህም ሕዝብ "አሜን" ብሎ የተቀበለው ከብዙ ሕዝብና ከሰፊም ሆነ ጠባብ መሬት የተሠራ ሀገር
ይገነባሉ።

እኔ ወጣት ነኝ። ከወጣትም ኢትዮጵያዊ ወጣት። እስከዛሬ ቢልልኝ የተሻለ ሀገር ላይ መኖር ይገባኝ ነበር። የሀገሮች ብቻ
ሳይሆን የሀገሬን የሥልጣኔ ታሪክ እርዝማኔን ላሰበ 'መሉ በኩልሄ' በሆነ ሀገር መኖር እችል ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም።
የቀደሙ መሪዎች በጣሉልኝ ድንጋይ ተረማምጄ ዛሬ ላይ ደርሻለሁ። ሀገሬን ስለሠራት ትናንት፣ ስላቆማት ዛሬ፣
ስለሚያቆያት ነገ አብዝቼ አስባለሁ። የሀገሬ የስሪት መነሻ ጥንታዊ ፖለቲካ፣ የመቆየቷ ሙጫ የዘመነ የፖለቲካ ተግባቦት
እንደሆነም እረዳለሁ።

ለፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ለማሰብ ከነቃሁበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መልካም የሚባልን ነገር ሰምቼ
አላውቅም። የፖለቲካ ጉዞው የትም ፈቅ አለማለቱ የፖለቲካ ጉዞ የሚባልነገር ስለመኖሩ ሁሌ ጥርጣሬ ውስጥ እንድገባ
ያደርገኛል። በኢትዮጵያዊነቴ ማግኘት የሚገባኝን ማግኘት እንዳልችል ሆኜ የኖርኩት በዘመኔ አንድ መንግሥት ብቻ
ማየቴ ነው ብዬ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አስብ ነበር፤ ነገር ግን ችግሩ የአስተዳደር ሳይሆን የአስተዳዳሪዎቹ እንደሆነ ውል
ያለኝ በቅርብ ጊዜ ነው። (ምክንያቴን አብራራለሁ።)

20 ዓመት ሊምላኝ ከወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶኛል። ለፖለቲካ ንቁ የሆንኩበት ጊዜ ግን ምናልባትም ከጥቂት ዕድሜ እኩዮቼ
የቀደመ ሳይሆን አይቀርም። ስለሀገሬ ፖለቲካ ባየሁትና ባስተዋልኩት ጉዳይ ሁሉ ግን አንድም ቀን ተደስቼ አላውቅም።
የ'ዴሞክራሲያዊ ሀገር' ፖለቲከኝነት ግቡ ዴሞክራሲና ሰላም፣ መርኁ ሕዝብን ማገልገል ነው። (ይመስለኛል) የሀገሬ
አስተዳዳሪዎች ግን ከፖለቲካ ዳዴዬ ጀምሮ ስለዴሞክራሲ መርኅና ግብ ግድ ሲሰጣቸው ታዝቤ አላውቅም። መሪዎች
የመግዛት እንጂ የማስተዳደር ፍላጎት ስለሌላቸውም ዴሞክራሲን በአደባባይ ወጥተው ሲሸኟት ሕቅ እንኳን
አላላቸውም።

እስከዛሬ አብዛኛው የፖለቲካ ሊቅና "ሊቅ ነኝ" ባይ የሚስማማበት (በልቡናም ቢሆን) ጉዳይ በፖለቲካ ጎሬ ተጠልለው
ሕዝቡን የሚበሉት ጅቦች የጨለማው ሥርዓት ውጤት እንደነበሩ ነው። አሁን ግን የተግባቦታችንን መነፅር መቀየር
ያለብን ይመስለኛል። ጅቦቹ የጨለማው ውጤት ሳይሆኑ ጨለማውን ጅቦቹ ራሳቸው ነው የሠሩት። የዴሞክራሲያዊና
ሰብዓዊ መብቶች አለመከበር ዋነኛ ምክንያቱ የሥርዓቱ መጨለም ሳይሆን ጅቦቹ በልካቸው ጨለማውን መስፋታቸው
ነው።

እንዲህ ዝብርቅርቅ ጽሑፍ ወዳስጻፈኝ ጉዳይ ልግባ። ሰሞኑን በሀገሬ ታሪክ ውስጥ የማይታሰብ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ
አንገት ያስደፋ ትልቅ ክስተት ተፈጠረ። (ዝርዝሩ ይቆየን) የሰሞኑንው ግድያ (ፍጅት የሚለው ቃል ካላነሰው) በሀገሬ
ገዢዎች ላይ የነበረኝን ሊከስም ያለ ተስፋ ከቶውኑ አጠፋው። ገዢዎቻችን የከረፋውን የፖለቲካ ዓለም ጊዜው
አስተምሯቸው (ምንም እንኳን 25 ዓመት ለመማር በቂ ቢሆንም) ትንሽ በመልካም መዐዛ ያውዱት ይሆናል የሚል
የተሟጠጠ ተስፋዬን ርኅራኄ አልባ ሥራቸው ወደማይመለስበት መቀመቅ ከተተው።

ሀገሬ ዘመናዊ የፖለቲካ መዘውርን ከጨበጠች ከአርባ ዓመት ትንሽ ፈቅ ብትልም በዘመናዊ የፖለቲካ ስልት ተቃኘን ያሉት
ሁለቱም መንግሥታት (ደርግና ኢሕአዴግ) ለተቀናቃኝና ተቃራኒ ሐሳቦች ክፍት ሆነው አያውቁም፤ ነገር ግን ደርግ
ከኢሕአዴግ የሚሻልበት አንድ ጉዳይ ቢኖር ከፖለቲካ ተቋማትና ፖለቲከኞች ውጪ ሕዝብን በጠላትነት አለመፈረጁ
ነው። አፈ-ሙዝ ባገነነው የኢሕአዴግ መንግሥት ግን የጠላትነት ሚዛን ልክ የሚለካው በፖለቲከኝነት ክብደት ሳይሆን
በሕዝብነት ብቻ እንደሆነ ሰሞኑን ባደረገው ጉዳይ ተረዳሁ። ምን አስተዳደር ቢከፋ የሥልጣን ሥጋቶቹን ያጠፋ ይሆናል
እንጂ እንዴት "100% መረጠኝ" ያለው ሕዝብ ላይ ጦርነት ያውጃል? እንዴትስ በአፍ የተወረወረ ሐሳብ ላይ አፈ-ሙዝ
ያዛል?

የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ የሚበዛው ክፍል የሚቀዳው በጦርነት ከፈሰሰ የወንድማማቾች ደም ነው። መሪዎች በዘረጉት
የፖለቲካ (ጥንታዊም ቢሆን) ጥላ ሥር ተከልሎ፤ ነገር ግን ከመሪዎች ሐሳብ፣ እምነት ጋር የማይጣጣም ወይም መሪውን
የመግፋትና የመግዛት ፍላጎት ያለው ሌላ መሪ (በንጉሠ-ነገሥታቱ ሥር ያለ ንጉሥ) ካለ እሱንና ተከታዮቹን ጦር
አዝምተው ያጠፏቸዋል። ችግሩ የእምነት ከሆነ ደግሞ ሰይፍና ካራ መዘው እምነት ያስቀይራሉ "አሻፈረኝ" ያለውን
ይገድላሉ። የዚህ ዓይነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በገቢር ካለፈች፣ ታሪኩም ነበር ሆኖ ከቀረ ቆየ። (የቆየ መሰለ) በዘመናዊ
ኢትዮጵያ ግን የሚያስገድል ጉዳይ ቢኖር የሥልጣን ጥመኝነት አይሆንም። ሕዝብ መሆን በቂ ነው። ከሕዝብም ድምፅ
ያለው ሕዝብ።

ዶክተር መረራ ጉዲና "የኢትዮጵያ ታሪክ ፈተናዎችና የሚጋጩ ሕልሞች" የሚለው መጽሐፋቸው ላይ "የምኒሊክ ቤተ-
መንግሥት ገብቶ ከታሪክ የተማረ መሪ አይቼ አላውቅም።" ይላሉ። እውነታቸውን ነው። ይኸው የዘመናት የመገዳደል
ታሪካችን ጭራሹኑ ተሻሽሎ የመግደል ታሪክ ብቻ ሆኗል፡፡ (¡) በዘመናዊ ፖለቲካ የመገዳደልን 'ሀ ሁ' ያስተማሩን የ'ያ
ትውልድ' አባላት (የኛዎቹ መሪዎችም ጭምር) የደም ዕዳቸውን እንዳወራረዱ እየታወቀ የዚህኛውቹ ትውልድ 'ገዳዮች'
ምነው ልብም አንልም አሉ? ትናንት የቆመው ለወሬና ለትረካ ብቻ እንዳልሆነ ለማወቅ ሀገር አስተዳዳሪነት አይደለም
ተራ ሰው መሆኑ አይበቃም? ለምንስ ከተሠራ ታሪክ መማር ስንችል ታሪክ ተሠርቶብን መማርያ እንሆናለን?

እስቲ የኢትዮጵያን ታሪክ ለአፍታ ዞር ብለን እንየው። ከቴዎድሮስ ጀምሮ ያለችው ዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪኳ ተገልብጦ
ቢታይ ልክ የሚሆን ይመስላል። ቴዎድሮስ - ዮሐንስ - ምኒሊክ - ልጅ ኢያሱ - ዘውዲቱ - ኃይለ ሥላሴ - መንግሥቱ -
መለስ - ኃይለ ማርያም ከሚለው የዘመን ቅደም ተከተል (Chronological order) ይልቅ ኃይለ ማርያም - መለስ -
መንግሥቱ - ኃይለ ሥላሴ - ዘውዲቱ - ልጅ ኢያሱ - ምኒሊክ - ዮሐንስ - ቴዎድሮስ የሚለው የዘመን አካሄድ በአንጻራዊነት
የተሻለ ስሜትን ይሰጣል። ከአሁን ወደ ድሮ ስንቆጥር የኢትዮጵያ ታሪክ እያማረ ይሄዳል፡፡ አባቶቻችን ሕዝባዊ
ወንድማማችነትን አክብረው፣ ሀገርና ድንበሩን አስከብረው የኖሩ ነበሩ። ትናንትናችን ውስጥ ሕዝባዊ ተግባቦቱ
(Harmony) ያማረ፣ ሕዝቡ የሚወደው መሪ፣ መሪውም የሚወደው ሕዝብ ነበረው። እንደ ባለሙያ ጠላ ከጣፈጠ ታሪክ
የተረፈን አተላው ብቻ ነው፡፡ "The cigar has been smoked out, and we are the ashes." ("ሲጋራው ተጭሶ አልቆ
እኛ አመዶቹ ነን።") እንዲል Anthony Trollope መሪዎቻችንም እንደዛው ናቸው። የትናንት ሲጋራ አመዶች።

.
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ "አጤ ምኒሊክና ኢትዮጵያ" በሚል በ 20 ኛው ክ/ዘመን መባቻ ላይ ባሳተሙት መጽሐፍ
እንዲህ የሚል ቃል ሠፍሮ እናገኛለን። "አእምሮ ባላቸው ሕዝቦች ዘንድ ግን መንግሥት ማለት ማሕበር ማለት ነው።
ንጉሣቸውም የማሕበራቸው አለቃ ማለት ነው። ስለዚህ ንጉሡ የፈቀደውን ያደርግ ዘንድ አይችልም። ሥልጣኑ የሕዝቡ
ማሕበር በደነገገው ሕግና ወግ የተወሰነ ነው።" ነጋድራስ ይህን ያሉት የሠለጠነ የመንግሥት አስተዳደር ለዚህች ሀገር
ይመኙ ስለነበር ነው። ይህን ምኞታችንን ተሸክመን ይኸው አንድ ምዕተ ዓመት ተሻገርን። ዓለም ትቶን ነጎደ። እኛ ግን
ካለንበት ፈቅ ሳንል ጭራሹኑ እየበሰበስን አለን። ታድያ እስከ መቼ እንዲህ እንቀጥላለን? ከመሪዎች ሆድ የዘለለ ፖለቲካ
መቼ ይኖረናል? የምንወደው መሪ መቼ ይሆን የሚመጣው? ከኢዮብ ትዕግሥት ተምረን ይህ ሁሉ ጠበቅን። ጠቢቡ
ሰለሞን " ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ።" ያለንን
አድምጠን ይህ ሁሉ ታገሥን፤ ግን እስከመቼ? እኔንጃ!

ሰላም በዓለሙ ላይ ሁላ ይስፈን!

You might also like