You are on page 1of 22

ብልጽግና ወይስ ህልውና?

ለኢትዮጵያ ህዝቦች የቀረበው አጣዳፊ አጀንዳና የአማራ ህዝብ ጥያቄ

በይርጋ ገላው1

ይህ ጽሁፍ አንድ ሰፊና ሁለት አጠር ያሉ ክፍሎች አሉት። ክፍል አንድ በሰፊው የሚያትተው በአማራ
ህዝብ ላይ የሚደርሰውን የማንነት ጭቆና ልዩ ባህርያትና የፖለቲካውን መልስ ይሆናል። በተለይም አማራ
የሚወቀስበት የአንድነት ፖለቲካ የተሳሳተ አቋም በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰውን ኪሳራ ለማሳየት ይጥራል።
ሁለተኛው ክፍል ከአማራ ህዝብ ላይ የተጋረጠው የህልውና አደጋ ከሌሎችም ህዝቦች የህልውና አደጋ ጋር
የተያያዘ መሆኑን በማሳየት ከማንኛውም የፖለቲካ አማራጭ በፊት የህልውና ጥያቄወች መልስ ማግኘት
እንደሚገባቸው ያስረዳል። የህልውና አደጋን ለማስቀረት መደረግ ካለባቸው ቅድመሁኔታወች አንዱ
የአማራን ወይም የሌላውንም ማንኛውም ህዝብ ማንነት የብሄር ጠላት አድርጎ መሳል በህግ የተከለከለ
እንዲሆን ማድረግና የፍትህና የእርቅ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ያስረዳል። በሶስተኛው ክፍል
በሃገራችን ዛሬ የሚታየው ጦርነት በጥቂቶች ብልጽግናና በብዙሃኑ ህልውና መካከል የሚደረግ ጦርነት
መሆኑን ያስረዳል። የአማራ ህዝብ እንዲሁም ሌሎች የሃገራችን ህዝቦች ካንዣበበባቸው የህልውና አደጋ
ለመዳን ማድረግ ስለሚገባቸው ጉዳይ አጭር ገለጻ ያደርጋል። በጽሁፉ ያነሳኋቸው ነጥቦች እስከዛሬ በቂ
ውይይት ያልተደረገባቸው ስለመሰለኝ እየደጋገምሁ ለማብራራት ሞክሬአለሁ።

ክፍል 1፡ የአማራ ህዝብ የህልውና አደጋ ምንጭ የሆኑ ትርክቶች ላይ የቀረበ ሂሳዊ ቅኝት2

መግቢያ

በዚህች ጽሁፍ ላይ የማተኩረው በአማራ ማንነታቸው ምክንያት ሰብዐዊ መብታቸው የሚጣስ ሰወች ላይ ያሉ እሳቤወችን
ለመሞገት ነው። በግሌ የብሄርተኝነትንም ይሁን የአሃዳዊ አንድነትን ፖለቲካ የምቃወምባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉኝ።
የሃገራችንን የፓለቲካ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ስሪት የማየው በገጠርና በከተማ የህይወት ተቃርኖ ላይ የተመሰረተ
ሃገርበቀል የልሂቃን ቅኝ አገዛዝ እንደሆነ አድርጌ ነው። ይህንን ሃሳቤን ኔቲቭ ኮሎኒያሊዝም (Native Colonialism)
በተሰኘ መጽሃፍ ጽፌአለሁ፣ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃኖችም ምልከታየን ለማጋራት ሞክሬአለሁ፤ ወደፊትም የምለው
ይኖረኛል። አሁን የማተኩረው ግን በዚህ ላይ አይደለም። አሁን የማተኩረው በማንንት ላይ የሚደርሰው ጥቃት የፖለቲካ
ጉዳይ ብቻ ተደርጎ በመታየቱ በጥቃቱ ሰለባወች ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ ላይ ብሄርተኝነትን ሽፋን ያደረገ ወንጀልና
አፓርታይድን የሚመስል የአድልወ ስርአት እየፈጠረ መሆኑን ለማሳየት ነው።

1
ይርጋ ገላው አውስትራሊያ በሚገኘው የከርትን ዩንቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ሲሆን በግጥም ስራወቹም ይታወቃል። አስተያየትወን
በኢሜይ አድራሻው መላክ ይችላሉ። Yirga.woldeyes@curtin.edu.au
2
ይህ የክፍል 1 ጽሁፍ በፍትህ መጽሄት 3አመት ቁጥር 131፣ 2013 በአጭሩ ታትሟል

1
በዚህ ጽሁፍ ላይ በምሳሌነት የማነሳውን በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በሌሎች ማንነቶች ላይ ከሚደርሰው
ጥቃት ለየት የሚያደርገው ጉዳይ አለ። አማራ የህዝብ መጠሪያ ብቻ አይደለም። ወደኋላ አካባቢ እንደማሳየው፣ ላለፉት
30 አመታት አማራነት የተወሳሰበ ትርጉም ያለው ማንነት እንዲሆን ተደርጓል። ጉራጌም ይሁን ኦሮሞ፣ ትግሬም ይሁን
አማራ፣ ገበሬም ይሁን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ቄስም ይሁን ሼክ፣ ኦህዴድም ይሁን ብዐዴን፣ ኢዜማም ይሁን ባልደራስ፣
የኦሮሞን ወይም የትግራይን የብሄር ትርክት ከተቃወመ፣ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አራማጅ ከሆነ ወይም
የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ከሆነ ‘ዐማራ” የሚለው ስያሜ እንደየሁኔታው ሊጫንበት ይችላል። ለምሳሌ ፕሮፌሰር አሰፋ
ጃለታ በህዳር ወር በጻፉት ጽሁፍ ላይ በአማራ ልሂቃን ተጽዕኖ ይመራሉ ብለው የዘረዘሯቸው የፖለቲካ ሃይሎች
ኦህዴድን፣ ኢዜማን፣ ባልደራስን፣ አብንንና የአማራ መንግስትን ያጠቃልላሉ። ይህ የሚያሳየን ከፖለቲካ ውጭ የሆነው
ድሃ የአማራ ተወላጆች ከነዚህ የተለያየ የፖለቲካ አቋምና ፍላጎት ካላቸው ሃይሎች ጋር ተደምረው በጨፍላቂነት፣
በነፍጠኛነት፣ በአሃዳዊነትና በዱሮ ስርዐት ናፋቂነት እየተፈረጁ እንደፖለቲካ ጠላት በመቆጠር ላይ መሆናቸውን ነው።

ይሄው ምሁር ጠቅላይ ሚንስትሩን ሳይቀር ‘አማራ ሆነዋል ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፡

Abiy’s father is Oromo. But he was raised by his Amhara mother, a fact that he
has used extensively. Considering his cruelty against the Oromo who embraced
him at the beginning, most Oromos now think that his close affinity with his
mother shaped his values, philosophy, ideology, and culture.3

ጸሃፊው የሚሉት ‘ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአባታቸው ኦሮሞ ናቸው። ታዲያ በኦሮሞ ላይ ጨካኝ የሆኑት ለምንድን
ነው ለሚለው ጥያቄ ብዙ ኦሮሞወች የሚሰጡት መልስ የአብይ እሴቶች፣ ፍልስፍናወች፣ ርዕዮተለአለምና ባህል አማራ
በሆነችው እናታቸው በኩል ያገኙት ስለሆነ ነው የሚል ነው። ይህ የሚያሳየን አንድ በኦሮሞ ጥናት ትልቅ ስም ያላቸው
ምሑር “most Oromos” ብለው ስለብዙ ኦሮሞወች አስተሳሰብ የሰጡን ሰእል ምን እንደሚመስል ነው፡፡ ይህም፣ ወልዳ
የምታሳድግ እናት ሳትቀር አማራ ከሆነች ልጇን በኦሮሞ ላይ ጨካኝ የሚያደርግ እሴት ልታወርሰው ትችላለች ብለው
እንደሚያስቡ ነው። በበኩሌ ይህ የልሂቃን እንጅ የተራው ኦሮሞ ህዝብ እምነት ነው ብየ አልገምትም። ሆኖም ይህ አይነት
እሳቤ ጋር በተያያዘ የአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎች ምን ተደረገ የሚለውን እንይ። ኢሃዴግ በ1983 ዓ.ም. ስልጣን ከያዘ
ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የአማራ ማንነት ያላቸው በርካታ ሰወች
የአሰቃቂ ግድያ ሰላባ ሆነዋል። ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሰባዊ ክብራቸው ተደፍሯል፤
ስነልቦናቸው፣ ቤተሰባቸው፣ ስራቸው፣ ተስፋቸው ተሰባብሯል።

ይህ ጥቃት ፖለቲካዊ ምክንያት ቢኖረውም እንደከባድ ወንጀል ተውስዶ አጥፊወች አልተቀጡም፣ ተጠቂወች ፍትህ
አላገኙም። ሌላው ቀርቶ የመንግስት ዋና አጀንዳ አልሆነም። ምድሪቱ በአማራ ላይ ወንጀል ፈጽሞ በነጻነት መኖር
የሚቻልባት ሃገር ሆናለች። ይህም በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጸም ወንጀል ከህግ ቁጥጥር ውጭ ነው የሚል አደገኛ
አንድምታ ፈጥሯል። ይህ በአማራ ማንነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደምሳሌ ባነሳሁት የአማራ ማንነት ላይ ብቻ ሳይሆን

3
ይህ ጽሁፍ በታዋቂ ሚዲያወች ታትሟል፤ አንዱን እዚህ ላይ ይመልከቱ።
https://theconversation.com/what-lies-behind-the-war-in-tigray-150147

2
በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጸም የሚችልበትን ቅድመሁኔታ የሚያመቻች ነው። ይህም _ ፖለቲካ _ ራሱ ማንነትን ፈጥሮ፣
እራሱ ወንጅሎ፣ እራሱ ፍርድ የሚሰጥበት አደገኛ ስርአት የመላ ሃገሪቱ የፖለቲካ ባህል ሆኖ ማደጉን ያሳየናል። እንዲህ
አይነት ስርአት ብዙ ቦታ ላይ ተከስቷል። በአይሁዶች፣ በጥቁሮች፣ በፍልስጥኤማውያን፣ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች፣
በኩርዶች፣ በዳርፉር ሱዳኖች ወዘተ፣ አስከፊ የንጹሃን መብት የተጣሰባቸው ቦታወች ሁሉ ዋና የሚያመሳስላቸው ጉዳይ
በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥላቻና ውንጀላ ሰለባ መሆናቸው ነው። ከሰወች ማንነት ላይ ያልመረጡትንና ያልተስማሙበትን
ትርጉም ጭኖ፣ ከሌሎች የሚለያዩበትን የፖለቲካ አጥር ሰርቶ፣ ንጹሃንን የሚያስፈጅና የሚጨቁን ፖለቲካ ከአፓርታይድ
አይነት አድሏዊነት እስከ ርዋንዳ አይነት አጠቃላይ ዘር የማጥፋት ወንጀል ድረስ የሚደርስ ክፋት ለመፈጸም አመቺ ነው።
ይህ ስራት ደም በማፍሰስ የመሳሰሉ ወንጀሎች እየዳበረ ከሄደ በኋላ በማንነት የሚጠቁ ሰወችን በሃሳብ መርዳት ወይም
መወዳጀት ሳይቀር ወንጀለኛ እስከማድረግ ያደርሳል። ተጠቂወቹን ለመጠቃታቸው ምክንያቱ የራሳቸው ጥፋት ነው ብሎ
ያሳምናል። በውይይት በምክክር ሊቀለበስ አይችልም።

የማንነት ጥቃትን እንደከባድ ወንጀል ለማስተናገድ መደረግ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በዚህ ጽሁፍ ላይ
የማተኩረው መደረግ የሌለባቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሆናል። ከእነዚህም ውስጥ “አማሮች ላይ የመብት ጥሰት
የሚደርሰው በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ነው” የሚሉትንና “ግድያው በዜግነት እንጅ በብሄር ማንነት ሊጠራ አይገባውም”
የሚሉት ይገኙበታል። ዋናው ክርክሬ እነዚህ እሳቤወች የሰብዐዊ መብትን ጥያቄ ከርዕዮተአለም ጥያቄ ጋር በማደበላለቅ፣
ዘር ተኮር ጥቃትን ተራ ወንጀል አስመስሎ በማቅረብ፣ የመንግስትን አለማቀፋዊ ሃላፊነት በማሳነስ፣ ወንጀል የፖለቲካ
አላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሆኖ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። በተጨማሪም አሁን ስራ ላይ ባለው የፖለቲካ
አደረጃጀትና መዋቀር ውስጥ ዜግነት ብቻውን ስለማይከበር የአማራ ህዝብ ከህግ ከለላ ውጭ ራቁቱን እንዲቀር
ያደርጉታል። በመደምደሚያየም የሃገራችንን እጣ ፈንታ ወደተሻለ አማራጭ ለማምጣት፣ በርዕዮተአለም ሳቢያ በአማራ
ላይ የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብቶች ጥሰት በስሙ መጥራትና ማውገዝ እጅግ ትንሹ ግን የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
ብዙ ህዝብ ተፈናቅሎ፣ ተርቦና እየተገደለ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ ከፖለቲካ ይልቅ ለህዝቦች ህልውና ቅድሚያ የማይሰጥ
ስርዐት በፍጹም ለህዝብ ደንታ ቢስ ነው። በዚህ አይነት ስርአት ውስጥ ህግ ፖለቲካውን ስለማይገዛው የዜግነትም ሆነ
የብሄርተኝነት ፖለቲካ ለአማራ ህዝብ ዋጋ የለውም። ተፈጥሯዊ ሰብዐዊ መብትን ከፖለቲካ ርዕዮተአለም በመለየት
የህልውና ጥያቄ ከህግ በላይ ሆኖ ቅድሚያ ካልተሰጠውና በመብት ረጋጮች ላይ ህጋዊ ተጠያቂነት ካልተረጋገጠ፣ አግላይና
አክራሪ የሆነው የብሄርተኝነት ትርክት ወንጀሉ ተደብቆለት ስለሚቀጥል፣ በሂደት የመንግስት ግልጽ ባህሪ ሆኖ በፖሊሲ
ጭምር መገለጹ እንደማይቀር የበርካታ ሃገሮች ልምድ ያሳየናል።

ታሪክ ወይስ ርዕዮተአለም፡- አማሮች የሚገደሉት በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ነውን?

አንዳንድ ሰወች በአማራ ማንንት ላይ የሚደርሰው በደል “‘በተሳሳተ የታሪክ ትርክት” የተፈጠረ ነው ብለው ሲናገሩ
ይደመጣሉ። ከዚህ በመነሳትም ታሪክን ለማረም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ጥረት መጥፎ ባይሆንም ‘የታሪክ ስህተት’
የሚለው አቀራረብ ችግሩን በቀላሉ ሊታረም የሚችል እንደሆነ አድርጎ ስለሚያቀርብ አዘናጊ እንጅ ገላጭ ምክንያት
አይደለም። ምክንያቱም የታሪክ ስህተት ቢሆን ኖሮ የሚፈታበት ቦታ ዩንቨርስቲ ውስጥ ወይም የታሪክ ጥናት ክርክር
መድረክ ላይ ይሆን ነበር። ችግሩ የፖለቲካ እምነት (ርዕዮተአለም) ጉዳይ እንጅ የታሪክ አረዳድ ስህተት አይደለም።
በታሪክ አረዳድና በርዕዮተአለም መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት በደንብ መገንዘብ ስለሚያስፈልግ ስለርዕዮተአለም ትንሺ
ልበል።

3
ርዕዮተአለም፣ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንደአንድ የማህበረሰብ አባል በመቁጠር ሃገር የምንገነባበት፣ ወይም
የምናፈርስበት፣ ወይም በጋራ እንድንኖር የሚያደርገን የፖለቲካ እምነት ነው። ዋና አላማው አንድ የሚያደርገን ቋሚ
የፖለቲካ እምነት መፍጠር ስለሆነ፣ ትኩረቱ እውነተኝነት ላይ አይደለም። ርእዮተአለም በውሸት ወይም ፈጠራ ላይ
የተመረኮዘ ትርክትን እንደመነሻ ሊወስድ ይችላል። ለምሳሌ በነገስታቱ ዘመን ህዝቡ በተሰጠው የስልጣን ተዋረድ መሰረት
ጌቶቹን እያከበረ ለመኖር መሪወቹ ከፈጣሪ እንደተቀቡ አድርጎ ማመን ነበረበት። ይህ እምነት እውነት ቢሆንም ወይም
ባይሆንም ለብዙ ሺ ዘመናት ሃገር ገንብቶ ለመኖር የሚያስችል ውጤት ነበረው። በዚያ ዘመን ይህንን እምነት የሚቃወም
እንደ ከባድ ወንጀለኛ ይቆጠር ነበር። ርዕዮተ አለም ከሀይማኖት የሚለየው ትኩረቱ ፖለቲካ ላይ ስለሆነ ብቻ ነው።
ርዕዮተአለም የማህበረሰብ የጋራ እምነት ስለሆነ፣ ለርዕዮተአለሙ ታማኝ የሆኑ ሰወች ታማኝነታቸውን የሚያስመሰክሩት
የርዕዮተአለሙን ጠላቶች አምርረው በመታገል ወይም በማጥፋት ነው። በ1966ቱ አብዮት በነገስታቱ መለኮታዊ ስልጣን
ላይ የተመሰረተው ርዕዮተአለም ተሻረ። ከዚያ በኋላ፣ እስካሁን የምንጣላበት ዋና ምክንያት ሁላችንንም የሚያስማማ የጋራ
ርዕዮተአለም መፍጠር ባለመቻላችን ነው።

ታሪካችን ውስጥ ጥፋትም በጎነትም ሞልቷል፤ ነገስታቱ መላእክትም ሰይጣናትም አልነበሩም፣ እንደእኛ ሰወች ነበሩ።
ሆኖም ፖለቲከኞች ከታሪክ ውስጥ የሚፈልጉትን መርጠው ወይም ፈጥረው የፖለቲካ እምነት ወይም ርዕዮተአለም
ይሰራሉ። ርዕዮተአለም ፖለቲካዊ ሃይማኖት ነው። በውስጡ አክራሪም ለዘብተኛም አማኞች ስለሚሳተፉበት
እንደመሪወቹ ለዘብተኛም ጽንፈኛም ባህሪ ይንጸባረቅበታል። የርዕዮተአለም አላማ የዱሮውን ታሪክ ለመቀየር ሳይሆን
መጭውን ጊዜ ለመቆጣጠር የሚያስችል የተደራጀ ሃይል ማሰባሰብ ነው። እስካሁን ባለው ልምድ፣ ይህንን የተደራጀ ሃይል
የሚያሰባስብበት ዋናውና አቋራጩ መንገድ ተከታዮቹን ሊያስተባብር የሚችል የጋራ ጠላት በመፍጠር ነው። በፖለቲካው
አለም ውስጥ ሰወች የጋራችን የሚሉት ዋና እውነታ የጠላታቸው ማንነት ሲሆን፣ ይህ ጠላታቸው የፖለቲካ አብሮነታቸውን
ለማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነገር ይሆናል። ይህ የጋራ ጠላት ከተፈጠረ በኋላ ተከታዮቹ የራሳቸውን የፖለቲካ ሰብዕና፣
ታሪክና አጠቃላይ የማንነታቸውን ትርጉም ሁሉ መገንባት የሚጀምሩት ጠላት ካሉት ማንነት በሚያርቅና በሚቃረን
አግባብ ይሆናል። አንድነታቸውን፣ ቆራጥነታቸውንና ታማኝነታቸውን የሚያረጋግጡት የጋራ ጠላት ያሉትን በመፈረጅ፣
በማግለል፣ ባለመተባበር፣ በማጥላላት፣ በመስደብ፣ በመግደል፣ በማፈናቀል ሊሆን ይችላል። ይህንን የሚያደርጉት
በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ሳይሆን በራሳቸው የውስጥ ፖለቲካ ፍላጎት በመመራት ሆን ተብሎ በተመረጠና በተቀናባበረ
ትርክት ይሆናል። ስለዚህ ታሪካዊ ትርክትን እንደግባት ቢጠቀምም፣ ርዕዮተአለም ተከታዮቹን በስሜት ለማታገል
የሚፈጠር የፖለቲካ እምነት ስለሆነ የታሪክ ማስረጃ በማቅረብ እምነቱን ማስቀየር አይቻልም። ዛሬ አማራ ተብለው
የሚሞቱት ሰወች ከነገስታቱ ዘመን ጋር የሚያገናኛቸው ምንም አይነት የስልጣን ወይም የኢኮኖሚ ትስስር እንደሌለ
ገዳዮቹም አይጠፋቸውም።

ከዚህ አንጻር፣ በአማራ ላይ የሚደርሰው ጥቃት የታሪክ ስህተት ሊባል የማይገባበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከኢሃዴግ
የስልጣን ዘመን ጀምሮ፣ የአማራን ህዝብ ብቻ ነጥሎ ከነገስታቱ ዘመን ጋር ያገናኘው የጨቋኝነት ትርክት የብሄር ፖለቲካ
ዋና ማደራጃ ርዕዮተአለም አካል ሆኗል። ርዕዮተአለም ደሞ ከላይ እንዳልሁት በባህሪው ከታሪክ ይልቅ ለሃይማኖት
ይቀርባል። በታሪክ ትንታኔ አይቀየርም። ምክንያቱም ዋናው አላማው ትናንትን ሳይሆን ነገን ለመቆጣጠር የሚያስችል
ስርዐት ለመፍጠር ሃይል ማሰባሰብ ነው። በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ርዕዮተአለም ከተፈጠረ በሗላ፣ አማራወች
“አጥፍታችኋል” የሚባሉትን ሁሉ አሜን ብለው ቢያምኑ እንኳን፣ ጥላቻው የባህል የፖለቲካ፣ የተቋማትና የህግ መሰረት
ከያዘ በኋላ ርዕዮተአለሙን ማፍረስ ማለት የተፈጠረውን የሃይል ስብስብ የመበተን ያህል ከባድ ይሆናል። ምክንያቱም
በብሄር ማንነት ብቻ የተደራጀ ፖለቲካ የብሄር ጠላት ያስፈልገዋል። በመደብ ማንነት የተደራጀ ፖለቲካ የመደብ ጠላት

4
ያስፈልገዋል። በጥቂት ግለሰቦች ስብከት፣ የታሪክ ማስረጃ በመደርደር፣ ወይም ለችግሩ እውቅና በመንፈግ ሊቀየር
አይችልም። የአንድ ፖለቲካ ለዘብተኛነትና አክራሪነት የሚለካው ‘ጠላት’ ብሎ የፈረጀውን አካል በሚያስተናግድበት
አግባብ ነው። ጠላቱን ሊደራደረውና ሊወዳደረው ከተነሳ (በሰለጠኑት ሃገሮች እንደሚታየው) የሚያስፈልገው የሃሳብ
ትግል ነው። የሚገድል፣ የሚያፈናቅል ከሆነ (በእኛ ሃገር እንደሚታየው) የሚያስፈልገው የህልውና ትግል ነው።

ከላይ እንዳልሁት ጠላትን በመፍጠርና በማጥቃት ግለቱን ጠብቆ የሚጓዝ ርዕዮተአለም በህይወት ለመቀጠል ሲል የራሱን
ለዘብተኛ አባላት ጨምሮ ማንኛውንም ተቃዋሚ ሰው በጠላትነት መፈረጁንና ማጥቃቱን ይቀጥላል።። በዚህ ሂደት
መጨረሻም ራሱን በራሱ የሚያጠፋበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በአክራሪ ርዕዮተአለም ሽፋን የሚፈጸመውን ወንጀል
በህግ መዳኘት ካልተቻለ የሚፈሰው ደምና የሚፈጸመው ወንጀል እንደጀግንነትና ድል ስለሚቆጠር የብዙ ሰወችን ጭፍን
ድጋፍ ያገኛል። ድጋፍ ባያደርጉም ዝም የሚሉ ሰወች በዝምታቸው ወንጀሉ የተለመደና መፍትሄ የለሽ ሆኖ በህዝብ
እንዲታይ ያደርጉታል። ይህ የቅቡልነት ሂደትም (ኖርማላይዜሽን) ዛሬ በሁሉም አለም ላይ በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው
የዘር መድሎ ትክክል ባይሆንም የተለመደ ሆኖ እንደቀረው ሁሉ፣ በአማራ ላይ የሚደርሰውም ጥቃት ትክክል ባይሆንም
ሊወገድ የማይችል ድርጊት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጉታል።። በተለይም በሃገርቤትና በውጭ ወንጀሉን የሚያድበሰብሱ
ወይም ምክንያታዊ የሚያስመስሉ ትርክቶች (አሁን እንደሚታየው) ከተሰራጩ፣ መንግስት የርዕዮተአለሙን አክራሪ ባህሪ
ከመቀየር ይልቅ የራሱን ባህሪ ለአክራሪወቹ በሚመች መንገድ ማስተካከል ይጀምራል። ጥቃቱን በመፍቀድና በማስፈጸም
ደጋፊ ያበዛበታል። ለአክራሪወቹ አባላት ስልጣን ማደል ይጀምራል። በሂደትም አክራሪነትን የሚደግፉ ሰወች ስልጣን ላይ
ይበዙና በመንግስት ፖሊሲና ተቋማት ውስጥ የአክራሪወቹ አድሏዊ ፍላጎቶች በስውር ብቻ ሳይሆን በግልጽ መንጸባረቅ
ይጀምራሉ። ያኔ የጥላቻ ርዕዮተአለም የሙስናና የህገወጥነት ጭምብል ይሆናል። እዚህ ላይ የአለማቀፉ የገንዘብ ስርዐት
ባህርይም ለዚህ አስተዋጾ ያደርጋል።

አንዳንድ የሃገራችን የፖለቲካ ልሂቃን የምዕራቡን አለም ዲሞክራሲና የሊበራሊስዝም ፖለቲካ እንደጥሩ ልምድና አራያ
መከተላቸው ትክክል አይደለም። የካፒታሊዝም ስርዐት በተለይም አሁን ያለው የኒዮሊበራሊዝም ወይም
ቴክኖፊውዳሊዝም ስርዓት ካፒታል ወይም ካፒታል የሚፈልገው ክህሎት የሌላቸውን ሰወች እንደሸክም እንጅ እንደሰው
አይቆጥራቸውም። ለካፒታሊዝም ጥቅም የማይሰጡ ሰወች የያዙትን የተፈጥሮ ሃብት ለካፒታል አስረክበው እንዲለቁ
ይፈልጋል። ሰወቹን ግን አይፈልጋቸውም። ይህ የካፒታሊዝም ባህሪ አፍሪካ ውስጥ የእርስበርስ ግጭትን (ዋርሎርድ
ፖሊቲክስ) ለራሱ መጠቀሚያ ለማድረግ ያልማል። ለምሳሌ አፍሪካውያን አብዛኛው ህዝባቸው ለካፒታሊዝም የሚጠቅም
ስላልሆነ የሰለጠነው አለም የስጋት ምንጭ ናቸው ብለው ማመን ከጀመሩ ቆይተዋል። ትኩረታቸው የራሳቸውን ጥቅም
የሚያስከብር የጸጥታ ፖሊሲ መከተል ሲሆን ለዚህ አላማቸው ከእርዳታ መስጠት እስከ ጦር ሰፈር ምስረታ ድረስ
ይሰራሉ። ባራክ ኦባማ በአህጉሪቱ አፍሪኮም በሚል አደራጅቶት የሄደው 36 የጦር ሰፈር ሰብዐዊ መብትን ለመጠበቅ
አይደለም። በቅርቡ የአለማችን አንደኛ የመሬት ከበርቴ የሆነው ቢልጌት የአፍሪካ ህዝብ መብዛት የአለም ህዝብ የስጋት
ምንጭ መሆኑን በግልጽ ሲናገር ሰምተናል። ቻይና የአፍሪካን ጥሬ እቃ እንዳታጣ ለመሪወቹ የፈለጉትን ሁሉ ታደርጋለች።
ሰሞኑን ራሺያ 10 የሚደርሱ የጦር ካምፖችን ለመመስረት በመሯሯጥ ላይ ናት። ሌሎችም እንደ ህንድ፣ ቱርክ፣ ሳኡዲ
ወዘተ አፍሪካን ለመቀራመት ይሯሯጣሉ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን አፍሪካ ዛሬ ያለችው በበርሊን ኮንፈረንስ ዘመን ከነበረችው
ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ነው። ከዱሮው የነጮች የቀጥታ ቅኝ አገዛዝ ከአሁኑ የሚለየው የአሁኑ ድርብ ቅኝ አገዛዝ በመሆኑ
ነው። ድርብ ቅኝ አገዛዝ የሚፈጠረው ነጮችና የአፍሪካ ልሂቃን የጥቅም ትሥስር በመፍጠር የሁለቱንም ጥቅም
በሚያስጠብቅ ደረጃ ህዝቡን ሲመዘብሩትና ሲያሰቃዩት ነው። ነጮቹ የሚፈልጉት ህዝቡ የተፈጥሮ ሃብቱን ለመጠቀም
በሚያስችለው አግባብ እንዳይደራጅ ማድረግ ነው። በህግ ማስከበር ስም ረግጦ በማስተዳደርና በመግዛት ለእነሱ ኢኮኖሚ

5
ተፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶችን በልማት ስም እነሱ ለሚያትሙት ወረቀት (ገንዘብ) የሚለውጥ ከህዝባዊነት ይልቅ
ቡድናዊ ማንነት ያለው ስራት ይፈልጋሉ። ከአፍሪካ የሚፈልጉት መሬቷን፣ ውሃዋን፣ ማእድኗን፣ ከህዝቧ ነጻ አድርጎ
የሚያስረክባቸው አሽከር መንግስት ነው። በተለይም የሰው ጉልበት የማይፈለግበትና ሁሉንም ስራ በቴክኖሎጂ መስራት
የሚቻልበት ጊዜ ላይ ስለደረስን፣ በዚህ ዘመን በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ ድሃውን ህዝብ ከተፈጥሮ ሃብት እየነጠለ
መሬቱን ለካፒታል የሚያቀርብ፣ ለትርፍ የተቋቋመ የኮርፖሬሽን አይነት ቅርጽ ያለው ወንጀለኛ መንግስት በእጅጉ
ይመቻቸዋል። ይህ መንግስት ቢዝነስ እንዲሰራ የሚፈልጉት ከግል ኩባንያወቻቸው ጋር ነው። ይህን የሚያደርጉበት አንዱ
ምክንያት ራሳቸውን ከወንጀሉ ነጻ በማድረግ ለሰብዐዊ መብት የቆሙ ለመምሰልና አገልግሎቱን ሲጨርስ በሌላ መንግስት
ለመተካት ነው። በኩባንያወቻቸው አማካኝነት የተፈጥሮ ሃብታችንን ሲጠቀሙ በመንግስታቸው በኩል ደግሞ ያገኘነውን
የውጭ ምንዛሬ በእዳ ክፍያ ሰበብ መልሰው ይወስዱታል። ይህንን ዘዴ በኮንጎ፣ በአንጎላ፣ በቻድ፣ በዛምቢያ፣ በናይጀሪያ፣
በሱዳን፣ ወዘተ በግልጽ እየተገበሩት ነው። የእነዚህን አሳሳቢ ሁኔታወች ከእኛ ሁኔታ አንጻር በዝርዝር ለማቅረብ ሌላ ርዕስ
ያስፈልጋል። ማለት የፈለግሁት ግን እስካሁን ባለው ልምድ፣ የውጭ መንግስታት ዋና ፍላጎት የራሳቸውን ጥቅም
የሚያስከብር ስርዐት እንዲኖር ማድረግ ብቻ ስለሆነ አክራሪ ብሄርተኝነት ከነሱ ጥቅም ጋር ካልተጋጨ በደስታ አብረውት
ይሰራሉ። እንደውም የህዝቡን አጀንዳ ከኢኮኖሚ ላይ ሳይሆን ከፖለቲካው ላይ እንዲያተኩር ስለሚያደርግ
የብሄርተኝነትን ፖለቲካ ይወዱታል።

ከላይ እንደገለጽሁት በማንነት ላይ የሚፈጸም ግድያንና መፈናቀልን የሚያህል ከባድ ወንጀል የለም። መንግስት ለማንነት
ጥቃት የሚሰጠው መልስ የራሱን የመንግስትን ማንነትና ባህሪ የሚያሳይ ነው። በማንነታቸው የተጠቁ ሰወች ከአካላዊ
ጥቃቱ በላይ በቃላት የማይገለጽ የስነልቦና ስብራትና ውርደት ይሰማቸዋል። የተጠቁት በማንነታቸው ስለሆነ ማንነታቸው
ዋጋ እንዳለውና እንደሚከበር የሚያሳይ እርምጃ ካልተወሰደ ዋጋቢስነትና ውርደት ይሰማቸዋል። በተለይ ጥቃቱ ሆን
ተብሎ እንደእንስሣ እንደሆኑ በመቁጠር በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈጸመ ከሆነ ሰው መሆናቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ
አካሚ ድጋፍና እንክብካቤ ያሻቸዋል። መንግስት ይህንን የሚያደርገው የተጠቃው ማንነት የእኔም ማንነት ነው ብሎ
ሲያምን ነው። ስለሆነም በማንነታቸው የተጠቁ ሰወችን ጉዳይ ቁጥር አንድ አጀንዳ ካላደረገው የተጠቂወቹ የመኖር መብት
በመንግስት አይጠበቅም ማለት ነው። ይህም ተጠቂወቹ ዝቅተኛነታቸውን እንዲቀበሉ፣ አጥቂወቹ ታሪክ ሰሪ እንዲባሉ
የሚያደርግ አደገኛ መልዕክት ያስተላልፋል። በሂደትም የመንግስት ስርዐት ዋና ባህሪ ለፍትህና ለህጋዊነት ዋጋ የማይሰጥ
ስለሚሆን በዚያው ልክ ዜጎችም ለመንግስትና ለህጋዊነት ዋጋ የማይሰጡ መሆን ይጀምራሉ። በንጹሃን ሰወች ላይ
የሚዘገንን ጥቃትን የሚፈቅድ ወይም የሚታገስ ህሊና ያላቸው ባለስልጣኖች ወደፊት የፖለቲካ ወይም የጥቅም
ባላንጣወቻቸውን ይቅር ይላሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው። እስካሁን ባቀረብሁት ገለጻ አማራነትን በታሪክ አተረጓጎም
ስህተት የተፈጠረ ማንነት አድርጎ ከማየት ይልቅ የብሄርተኝነት ልሂቃን የርዕዮተአለም ጠላት አድርገው በመሳል
የተከታዮቻቸው ማታገያ ያደረጉት ማንነት መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ የሚመጥን ምላሽ ላይ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህን
ምላሽ ወደፊት ከማየታችን በፊት ለሃሳብ ጥራት ይረዳል የምላቸውን ጥቂት ነጥቦች ላንሳ።

በአማራነታቸው የተጠቁ ሰወች ‘ዜጎች’ ናቸው ወይስ ‘አማሮች’?

ሰብዐዊነት የተፈጥሮ ስጦታ ነውና ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል ነው። መንግስት የተፈጥሮ መብቶችን ለያንዳንዱ ግለሰብ
የሚያስጠብቅበትን ህግ ታሳቢ በማድረግ በተለምዶ ‘የዜግነት መብት’ ብለን እንጠራቸዋለን። ዋናው ቁምነገሩ ሰው
በተፈጥሮ ያገኛቸውን መብቶች መንግስት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን ሃላፊነት የሚወስድ መንግስት
የሌላቸው ሰወች፣ ዜግነት አልባ (ስቴትለስ) ሊሆኑ ይችላሉ። በማይንማር 600000 የሚደርሱ ሮሂንጋ የሚባሉ ጎሳ

6
አባላትን መንግስት የእኔ ዜጎች አይደሉም ስላላቸው ዜግነት አልባ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ በህንድም ተከስቷል። የሞዲ
መንግስት ስልጣን ላይ ሲወጣ ህንድ የሂንዱይዝም እምነት ተከታዮች ሃገር ናት በማለት እስላሞችን ሃገር አልባ
የሚያደርግና ለጅምላ ግድያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ፖለቲካ ይዞ ብቅ ብሏል። ይህ አስተሳሰብ የኢኮኖሚ ጥቅም
ያስገኘላቸው የሂንዱ ተከታዮች ሞዲን በከፍተኛ ሁኔታ በመደገፍ ላይ ናቸው። ፍልስጤማውያንም የራሳቸው ምድር ላይ
ምድር አልባ ሆነው ብዙ ዘመናት እየገፉ ነው። እስራኤል የአይሁዶች ብቻ ሃገር ናት የሚለው የጽዮናዊያን ፖለቲካዊ
አመለካከት ለእስራኤላውያን ጥቅም ስላለው አድሏዊ ስርአቱን ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፈዋል። አንድን ህዝብ ሃገር
አልባ የሚያደርግ በዘር ማንነት ላይ የተገነባ ርእዮተአለም የፖለቲካ ስልጣን ካገኘ የማንነቱ ተከታዮች ስለሚደግፉት
ተጠቂውን ህዝብ የሚታደገው ምንም አይነት አለማቀፍ የፍትህ አካል የለም።

ወደሃገራችን ስንመለስ በህግ “ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የተባለ ስለሌለ በማንነት የሚጠቁ ሰወች ችግር ለጊዜው የዜግነት
ችግር አይደለም። አማራም ይሁን ትግሬ፣ አፋርም ይሁን ኦሮሞ ወዘተ ሁሉም ዜጎች በሁሉም የሃገሪቱ ቦታ ያለዐድልዎ
የመኖር መብት እንዳላቸው በህገመንግስቱ ተደንግጓል። ሆኖም ወደተግባራዊነቱ ስንመለስ፣ ይህ የግለሰቦች መብት
ከብሄሮች ሉዐላዊነት ስር ወድቋል። ህገመንግስቱን ተከትሎ በተደራጀው የብሄርተኝነት ርዕዮተአለም ሳቢያ፣ በአማራ
ህዝብ ላይ እንደዜጋ ሳይሆን እንደአማራነት የተፈጠረ ማፈናቀልና ግድያ ተፈጥሯል። ግድያው አንድ ወቅት ብቻ የተከሰተ
ሳይሆን፣ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ እጅግ ዘግናኝ ግፎች የተፈጸሙበትና በበርካታ ቦታወች የተከሰተ ነው። በበደኖ፣
በአርባ ጉጉ፣ በገለምሶ፣ በጋራ ሙለታ፣ በወተር፣ በሃብሩ፣ በአጋሮ፣ በአሰቦት፣ በሸቤ፣ ወዘተ በገደል በመወርወር፣ በቢላዋ
በመታረድ፣ በእሳት በመቃጠል፣ በጥይት በመደብደብ አማራ ማንነት ባላቸው ላይ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሟል። የአገዳደል
ዘዴው ራሱ በማንኛውም ንጹህ ዜጋ ላይ የሚፈጸም የተለመደ አይነት ወንጀል አይደለም። የነፍሰጡር ሴትን ሆድ ቀዶ
ልጁን በማውጣት ለእናት መስጠት፣ በእሳትና ዱላ ደብድቦ መግደል፣ ህጻናትን ማረድ፣ አስከሬን ጎዳና ላይ መጎተት
የመሳሰሉ የጭካኔ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ማስረጃወች ያስረዳሉ። ከግድያው ጀርባ በአማራነት ላይ የተዘራውን ጥላቻ
ምክንያታዊ የሚያስመስሉ የትምህርት፣ የጥናት፣ የሃይማኖት፣ የሃውልት፣ የስነቃል፣ የሙዚቃና የትጥቅ እንቅስቃሴወች
አሁንም አሉ። በዚህ አውድ የሚፈጸምን በደል ‘በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስ በደል’ ብሎ መጥራት የመሳለቅ ያህል ነው።
እዚህ ላይ አንዳንድ ሰወች በየዋህነት ‘ግን ምን ችግር አለው ዜጋ ቢባሉ” ስለሚሉ አንዳንድ ነጥቦችን ማየት ያስፈልጋል።

አንዱ ምክንያት በብሄር ማንነታቸው የሚገደሉ ሰወችን ባልተገደሉበት ምክንያት ዜጋ ብሎ መጥራት ማለት ገዳዮቻቸው
ተራ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ እንጅ የዘር ጥቃት ያደረሱ እንዳልሆኑ የሚያደርግ ከለላ መስጠት ነው። የሰብአዊ መብት
ድንጋጌወች ሁሉ የዘር ተኮር ጥቃትን ከዜጎች ተራ ጥቃት የተለየ ትኩረት የሚሰጧቸው ብሄርተኝነትን ለማስፋፋት ፈልገው
አይደለም። ጉዳዩ ከተራ ወንጀል በተለየ መልኩ አለማቀፍ ትኩረትና መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ አርቲስት ሃጫሉ
ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ ሁኔታውን አጣርቶ የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ ላይ ግድያውን በሰብዐዊነት
ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል እንደሆነና የዘር ማጥፋት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ያለውን ስጋት አስታውቋል። ይህ
አይነት ወንጀል አለማቀፍ ወንጀል ነው። ወንጀሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ካለን የአመለካከት ልዩነት ጋር አይያያዝም።
ወንጀሉ አንድን ማንነት የፖለቲካ ጠላት አድርጎ በመሳል፣ ከፖለቲካ ውጭ የሚኖሩ ድሃ ገበሬወችን ለግልጽ ጥቃት
የሚያጋልጥ፣ ሰላማዊ ዜጎች በወገኖቻቸው ላይ ግፍ እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ኢ-ሰብአባዊነት ነው። ምንም አይነት አላማ
ቢኖረው፣ ይህ አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰወችን ማጥቃትከጀመረበት ከዚያች ሰአት ጀምሮ ከፖለቲካ አውድ
ወጥቶ ወደአሸባሪነትና ኢሰባዊነት አውድ እየተሸጋገረ ነው ማለት ነው። ይህ የአሸባሪነት የሽግግር ሂደት ዝም ከተባለ፣
በገዳዮቹና በተገዳዮቹ ብቻ የሚቆም የዜጎች ጠብ ሳይሆን ኦሮሞና አማራ በሆኑ ሰወች መካከል ሁሉ ከትውልድ ትውልድ
የሚተላለፍ ጥላቻን የሚያሰራጭና፣ የህዝቦችን ተስፋ እስከመጨረሻው ከንቱ ሊያስቀር የሚችል አደገኛ መርዝ ይሆናል።

7
ይህን ወንጀል ለማስቆም የመጀመሪያው ተግባር የወንጀሉን የፖለቲካ ጭምብል አውልቆ አረመኔያዊ ድርጉቱን ለህዝብ
በግልጽ ማሳየት ይሆናል። ከዚያም የመገናኛ ብዙሃን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ሰወች ታሪክ ለህዝብ በክብር በማሳወቅ፣
ሽማግሌወችና የሃይማኖት መሪወች የእርቅና ምክክር ስራቶችን በህዝብ ፊት እንዲፈጽሙ በማድረግ፤ የህዝብ ለህዝብ
ውይይት በመክፈት፣ በመንግስት በኩል አጥፊወችን በህግ በመቅጣት፣ ተጎጅወችን በማቋቋምና በመካስ፣ እንዲሁም
እርዳታ በማሰባበር የተጎዱትን ለማቋቋም ጠንክሮ መስራት አለበት። ይህ ጥረት በሃገሪቱ የሰላምና የትብብር ተስፋ
መፍጠር ይችላል። ይህን ካላደረገ ግን ጥቃቱን ይደግፈዋል ወይም አይቃወመውም፣ ወይም እንደአንድ ተፈጥሯዊ አደጋ
ያየዋል ማለት ነው።

የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት የምንከተለው ስርዐት ለመብት የማይመች መሆኑ ታውቆ አስፈላጊ መሻሻሎች
እንዳይደረጉ ያደርጋል። መቸም በህይወት ከመኖር መብት የሚበልጥ መብት ያለ አይመስለኝም። የመንግስት ዋና ሃላፊነት
ህይወትን መጠበቅ ነው። የህገመንግስቱ አቀራረብ ብሄርተኝነትን እንደሉዐላዊ የጋራ መብት ስለሚቆጥር፣ መንግስት
የግለሰብ መብትን አስከብራለሁ የሚለው በብሄርተኝነት መዋቅር ውስጥ አልፎ ነው። ይህ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም
የመንግስትን ሃላፊነት ግን አያቀልለትም። መንግስት የተፈጥሮ መብት በብሄር ልዩነት እንዳይረገጥ የማድረግ አለማቀፋዊ
ግዴት አለበት። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በስሙ የማንጠራው ከሆነ ግን ይህንን ግዴታ ከመንግስት ትከሻ ላይ
እናወርድለታለን። ጉዳዩ የስርዐት ችግር ወይም በፖለቲካ ስም የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ሳይሆን የጥቂት ሰወች ህገወጥነት
ችግር ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሌላ አባባል የብሄር ፌደራሊዝሙ አተገባበር የፖለቲካ ወንጀልን
ከህግ ቁጥጥር ውጭ አድርጎ እንዲቀጥል ያደርጋል:: ከዚህ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከተደራጀ ገዳይ ሃይል በስተጀርባ ማን
እንዳለም ለማወቅ አይቻልም። የአሜሪካን ጨምሮ በርካታ መንግስታት ከተጠያቂነት ለመሸሽ ህገወጥ ቡድኖችን
አስታጥቀው ብዙ ወንጀል ስለሚያስፈጽሙ፣ ህዝብ መንግስትን እንዳይጠራጠር ከተፈለገ ጥርት ያለ መረጃ መስጠትና
ቁርጠኛነቱን በተግባር ማሳየት አለበት።

የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት ጽንፈኝነትን የበለጠ ያባብሳል። ዘር ተኮር ጥቃት በአለማቀፍና ሃገራቀፍ ደረጃ
በስሙ ካልታወቀ መንግስትም ይሁን ጽንፈኞች እርምጃቸውን ለማስተካከል የሚያስገድድ ጫና እንዳይደርስባቸው
ምክንያት ይሆናል። እንደውም በተቃራኒው ጽንፈኞች ያለማንም ተከራካሪ ትርክታቸው ትክክለኛ የፖለቲካ ምክንያትና
የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ነጻ እድል ያገኛሉ። ዘርንና የፖለቲካ እምነትን በሚያደባልቅ ሁኔታ ኦሮሞም
ይሁን ጉራጌ፣ ትግሬም ይሁን አማራ ብቻ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑትን ሁሉ ‘አማራ’
በሚል ስም በመፈረጅ፣ ለጠላታቸው የብሄር ማንነት በመስጠት፣ የራሳቸውን የብሄር ትግል በህዝቦች የማንንት ልዩነት
ላይ ይመሰርታሉ። የጥቃታቸው ሰለባ የሚሆኑትን ሰላማዊ ሰወች ከፖለቲካ ጠላቶቻቸው ጋር አንድ ማንነት እንዳላቸው
አድርገው ከፈረጁ በኋላ ወንጀልን የተቀደሰ የነጻነት ትግል አካል አድርገው ለማቅረብ ይመቻቸዋል። በዚህ ሂደት
ህጻናትንና እናቶችን ጭምር የገደሉ ሰወች የፈጸሙትን አረመኔአዊ ተግባር የማንነታቸው አካል አድርገው ስለሚያዩት
የበለጠ ጥፋት ለመፈጸም የሚያነሳሳ ስነልቦናዊ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ይህ ሰላማዊ ህዝቦችን ለከባድ ወንጀል የሚያጋልጥ
አሰራር በግልጽ ካልተነገረና የህዝብ ተቃውሞ ካልገጠመው በሃገር ብቻ ሳይሆን በውጭም ብዙ አድማጭ ያገኛል።
ምክንያቱም አብዛኛው የአለም ህዝብ አፍሪካውያንን የብሄር ዘረኞች አድርጎ ስለሚያይ የኢትዮጵያን ነባር ገጽታ በቀላሉ
ወደሌላው የአፍሪካ የጎሳ ዘረኝነት ታሪክ ለመቀየር ከባድ አይሆንበትም።

በማንነት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በግልጽ አለመታገል የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በዜግነት ወይም
በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን የሚሉ ልዩ ልዩ ፖለቲከኞች ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ የሆነው የአማራ ህዝብ በነሱ

8
የፖለቲካ አቋም ምክንያት የሚደርስበትን ጉዳት ተገንዝበው በማንንት ላይ የሚፈጸምን ወንጀል ከፖለቲካ በመለየት
ለአለም ለማሳወቅ ሲጥሩ አይታዩም። ይባስ ብለው በአማራ ማንነት የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብት ጥቃት በግልጽ
ባለመናገር ራሳቸውን ከብሄር ፖለቲካ የነጹና ገለልተኞች የሆኑ አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። ይህም
በማንንት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል የህግ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሆኖ እንዲጥል አስተዋጾ ያደርጋል። እነዚህና
ሌሎችም ምክንያቶች በማንንት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን እንደፖለቲካ መሳሪያ የሚጠቀም ባህልን ያጠናክራሉ። ይህ
ሁኔታ ወደፊት ከቀጠለና በማንነት ላይ የሚደርሰው ወንጀል እንደተድበሰበሰ ከቀረ፣ መንግስት ራሱ በአክራሪነት
የተፈጠረውን የፖለቲካ ሃይል የራሱ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት ሃገሪቱ የከፋ የአድልወ ስርዐት
ውስጥ ልናገኛት እንችላለን። ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ በተለይም ከመንግስት የሚጠበቀው የመጀመሪያው እርምጃ በማንነት
ሳቢያ የሚደርሰውን ግድያና መፈናቀል በስሙ በመጥራትና፣ በህግ እንዲዳኝ እንጅ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዳይሆን
ማድረግ ነው።

በማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት በስሙ መገለጽ ያለበት ከተጠቃው ማንነት ጋር የሚያያዝ መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው።
በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በስሙ አለመጥራት የሚጠቃውን የአማራ ማንነት ለመታደግ ምንም ነገር
እንዳይደረግ ያደርጋል። በህይወት የመኖር መብት ከሁሉም መብቶች ስለሚበልጥ የመንግስት ቀዳሚ አስፈላጊነት ይህንን
መብት ማስከበር ነው። መንግስት የሰወችን በህይወት የመኖር መብት አሁን ባለው የብሄርተኝነት መዋቅር ውስጥ ማረጋገጥ
ካልቻለ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከግለሰቦች ጋር እንደብሄር የፈጸመውን ህገመንግስታዊ ጋብቻ አፍርሶ እንደዜጋ መዋዋል
ይሆናል። (እርግጥ ይህን እሚያደርግ ከሆነ የዜግነት መብቶች የብሄር መብትን እንዳይረግጡ ማድረግም ይኖርበታል)።
ያኔ ሰወች በብሄር ስማቸው ቢገለጹ ወይም ባይገለጹ ላያከራክር ይችላል። አሁን ግን ዜግነት በራሱ በቂ ሆኖ በማይከበርበት
ሁኔታ፣ የብሄር ጥቃትን በስሙ አለመጥራት፣ አማራወችን ያለህገመንግስት ከለላ ራቁታቸውን ማስቀረት ይሆናል። መርሳት
የሌለብን እውነታ፦ የተጎጅወቹን ጥቃት የብሄር ማንነታቸው ምክንያትየደረሰ ነው ብሎ አለመጥራት ህይወታቸውን
ከብሄር ፖለቲካ ነጻ አያደርገውም። ይልቁንም፣ በህይወታቸውና በኑሯቸው ላይ የተፈጸመው ወንጀል የፖለቲካ አጀንዳ
ማራገቢያ ሆኖ ይቀጥላል። (በነገራችን ላይ ዜግነትም ይሁን ብሄርተኝነት ከባዕዳን የቀዳነው ትርከት እንጅ ከሃገራችን ህዝብ
ባህልና ልምድ የወረስናቸው ሃሳቦች አይደሉም። ሁለቱም ሳይኖሩ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ኑራለች። ይህንን ለመተንተን ግን
ሌላ ሰፊ ርእስ ያስፈልጋል።)።

አንዳንዶች አማራወች ተበደሉ ብሎ መናገርን ለአንድ ብሄር መቆም እንደማለት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ይህ አተያይ ግን
የተበዳዮቹን ሰብዐዊ መብት በራስ ርዕዮተአለም ብቻ ከማየት የሚነሳ ስህተት ነው። የዘር ፖለቲካን አልቀበልም የሚለው
እሳቤ ችግር የለበትም፡፡ በእኔ እምነት የብሄርም ይሁን የአንድነት ፖለቲካ ከህዝብ ውስጥ በፈለቁ ፍላጎቶችና እሳቤወች
ካልተመራ አብዛኛውን ድሃ ህዝብ አያገለግልም። ያም ሆነ ይህ፣ ፖለቲከኞች የአንድነትም ይሁን የብሄርተኝነት ፖለቲካን
የማራመድ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰላማዊው የአማራ ህዝብ ጥቃት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ጥያቄ
የርዕዮተአለም ሳይሆን የመብትና የገሃዱ አለም ጥያቄ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ትግሬም ይሁን
አማራ፣ ኦሮሞም ይሁን ኮንሶ እንደዜጋ ብቻ ሳይሆን፣ እንደብሄር ማንነቱም እንድንቆምለት የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሯል።
የቱንም አይነት የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ ቢኖረን፣ የማንነት መብት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህግ ጉዳይ ስለሆነ ይህ
መብት ሊከበር ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ህገመንግስቱ የብሄር ማንነትን በህግ መከበር እንዳለበት መብት አድርጎ ከደነገገ
በኋላ አፈጻጸሙን ግን አማራነትን ተከባሪ ሳይሆን ተጠቂ እንዲሆን በሚያደርግ የፖለቲካ አውድ ላይ ጥሎታል። መንግስት
ይህ የፖለቲካ አውድ የህግ መብትን እንዳይጥስ የማድረግ ግዴታ አለበት። ይህን ካላደረገ መንግስት የአማራን ማንነት
በህግ የፈጠረው ለማስከበር ሳይሆን ለማስጠቃት አልሞ ነው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።

9
እዚህ ላይ ራሳቸውን የኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃ አድርገው የሚያዩ ሰወችን አቋም መቃኘት ያስፈልጋል። እነዚህ ሃይሎች፣
የብሄር ፖለቲካ ቀርቶ ሁሉም ሰወች ዜጋ ሆነው በእኩልነት ይኑሩ፣ ህገመንግስቱም የብሄር ፖለቲካን ያስወግድ ሲሉ
ይደመጣሉ። በመሰረቱ ይህ የህገመንግስት ይቀየር የሚል ትግል አስፈላጊ የሚሆነው በህገመንግስቱ ትግበራ ምክንያት
በአማራወች ላይ የደረሰውን መዋቅራዊ ጭቆና አስቀድሞ ወይም በአንድ ላይ ለመፍታት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ
መፍጠር የሚቻል ከሆነ ነው። የህገመንግስቱ መነሻ ምንም እንኳን አማራን ጨቋኝ አድርጎ በማየት የተፈጠረ ቢሆንም፣
በአሁኑ ጊዜ ራሱ አማራ በተጨቋኝነት ውስጥ የሚገኝ ማንነት ሆኗል። ስለዚህ ህገመንግስቱ ይቀየር የሚለው ትግል
ዘረኛው የአድልወ መዋቅር ይወገድ ከሚለው ትግል ሳይነጠል መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው። ከዚህ በኋላ ህገመንግስቱን
መቀየር ላይ ያነጣጠረ ትግል ብቻውን የእኩልነት ጥያቄን መፍታት እንዳይችል የሚያደርግ መዋቅራዊ እውነታ ተፈጥሯል።
ይህ መዋቅር (structure) በጦር ሰራዊቱ፣ በኢኮኖሚውና በሰራተኛው አወቃቀር ላይ ስር ሰዶ ከተጠናከረ በኋላ፣
በኢኮኖሚ፣ በሚሊተሪ፣ በስልጣን ክፍፍል የአንድ ወይም የጥቂት ብሄር አባላት የበላይነት ከተረጋገጠ በኋላ፣
የህገመንግስቱ ብቻውን መቀየር ለአማራ ህዝብ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል። እርግጥ ከአማራ ውስጥ የስልጣን ተቋዳሽ
የሚሆኑ ሰወች ይኖራሉ፤ እርግጥ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች በሁሉም ቦታ የመስራት መብት እናገኛለን በሚል ሊደሰቱ
ይችላሉ። ሆኖም በአማራው ላይ ህቡእ የዘር ጭቆናና ግልጽ የመደብ ጭቆና ተነባብሮ ሊጫንበት ይችላል።

በማንኛውም ሁኔታ በዘር ልዩነት ሳቢያ የተፈጠረው መዋቅር እንዳለ የሚቀጥል ከሆነ፣ የአማራ ህዝብ ጠቡ ከህገመንግስቱ
ጋር ሳይሆን ህገመንግስቱን ከሚያስቀጥለው መዋቅር ጋር መሆን አለበት። በብሄር ማንነቱ ምክንያት የተገለለና የሚጨቆን
ማህበረሰብ ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን ማንነቱን የሚያከብርለት ህገመንግስት ካለ ያንን መብት ለራሱ ጥቅም ሊገለገልበት
ይገባል። እዚህ ላይ የዘረኝነትን ትግል እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ነጮች ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ ህገመንግስት
ነበራቸው። በዚያ ህግ ተጠቅመው መጀመሪያ የኢኮኖሚዉን፣ የወታደሩን፣ የቢሮክራሲውንና የማህበራዊውን ዘርፍ ሁሉ
በነጭ የበላይነት አስተሳሰብ ከሞሉት በኋላ ራሳቸውን ልክ እንደነጻነት፣ ዲሞክራሲያዊነትና እንደእኩልነት ጠበቃ
ለማቅረብ ሲሉ ዘረኝነትን የሚቃወሙ ሆነው ቀረቡ። ዘረኝነት ማህበራዊ፣ ባህላዊና መዋቅራዊ መሰረት ከያዘ በኋላ
ከህጋቸው ቢሰርዙትም ለጥቁሮችና ለሌሎች ንኡሳን ግን ያመጣላቸው ለውጥ ኢምንት ነበር። ዛሬ እንደአሜሪካ ባሉት
ሃገሮች ውስጥ ዘረኝነት በህግ ቢታገድም የባህል፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሰረቱ ሳይናድ እየቀጠለ ነው። የባህልና የሰብአዊ
መብት ድንጋጌወችም አንዱ ችግርም ይህ ነው። ሰብአዊ መብት “አንተም ሰው ነህ እኔም ሰው ነኝ፣ ስለዚህ አንተም እኔም
እኩል ተፈጥሯዊ መብት አለን” ይልሃል። ግን ይህን ሲልህ እሱ ሚልየነር ነው አንተ ደግሞ ቤት አልባ ነህ። እኩል ያልሆኑ
ሰወችን እኩል እንደሆኑ አስመስሎ የበላይነትን ማስቀጠል የቻሉበት ዘዴ ነው።በስልጣን መዋቅርና በኢክኖሚ እኩል
ያልሆኑ ሰወችን በህጉ መሰረት እኩል ናችሁ ብትላቸው ለድሆቹ ምን ይጠቅማል? የእኩልነት ህግ ፍትሃዊነትን መሰረት
ካላደረገ የጭቆና ጭምብል ይሆናል። ህገመንግስቱ ከፍትሃዊነት ጋር አብሮ ካልተሻሻለ የኢፍትሃዊነት ጭምብል ሆኖ
መቀጠሉ አይቀርም። ስለዚህ፣ ህገመንግስቱ ሲወገድ ወይም ሲሻሻል እስካሁን ይዞት የመጣው አድልዎ፣ ግፍና ጭቆናም
አብሮት መወገድ ወይም መስተካከል አለበት። ቢያንስ ቢያንስ አማራውን የሚያገል አስተሳሰብና መዋቅር በከፍተኛ ደረጃ
ከተፈጠረ በኋላ አሁን በህገመንግስቱ መሻሻል የአማራ ችግር ይፈታል ወይስ ይባባባሳል ብሎ በጥንቃቄ ማሰብ
ያስፈልጋል።

ለማጠቃለል፣ የአማራም ይሁን የአፋር፣ የትግሬም ይሁን የኦሮሞ፣ የጉራጌም ይሁን የኮንሶ ማንኛውንም ማንነትን መሰረት
ያደረገ ጥቃት በሚፈጸምበት ጊዜ በኢትዮጵያ አንድነት አምናለሁ የሚል ሰው “የማምነው በዜግነት እንጅ በብሄር አባልነት
አይደለም” በማለት ወይም በሌላ ምክንያት ጥቃቱን ተራ ጥቃት አድርጎ መመልከት የለበትም። በብሄርተኝነት የሚያምንም

10
ሰው “የማምነው በብሄርተኝነት እንጅ በዜግነት አይደለም” ብሎ ጥቃቱን ዝም ሊል አይገባውም። ይህንን ማድረግ ፖለቲካ
ከህግ ቁጥጥር ውጭ እንዲሰራ መተባበር ነው። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከፖለቲካ አጀንዳነቱ በፊት ከፍተኛ የሆነ
አለማቀፍ ወንጀል ነው። የማንነት ውንጀላ በህግ ካልታረመ ማንኛውንም ሰው በሰበብ ባስባቡ ሰለባ ስለሚያደርግ
ማህበረሰባችንን በፍርሃት አስሮ የሚያኖር ሰንሰለት ይሆናል። ብዙ ፖለቲከኞች ያላቸው አቋም “ያንተ መብት በእኔ
የፖለቲካ እሳቤ ካልተቀረጸ አያገባኝም” የሚል አይነት ነው። ይህ ማለት ከሰው ህይወት የራስን ርዕዮተአለም ማስቀደም
ይሆናል። በሌላ አባባል የወንጀሉን ግዝፈት ተቀብሎ በስሙ መጥራትና ማውገዝ የመፍትሄ ፍላጎት ምልክት ነው።

የአማራ ማንነት የፖለቲካ መጫወቻ ለምን ሆነ?

አንዳንዶች ለዚህ የሚሰጡት መልስ አማራወች ማንነታቸውን ስለማይቀበሉ ነው የሚል ነው። አማራነትን እንደፖለቲካ
ማንነት ብንቀበለውም ባንቀበለውም፣ መብት የሚከበረው የፖለቲካ እምነት እየታየ ስላልሆነ፣ የአማራ ማንነት በህግ
ከሌሎች ማንነቶች እኩል መጠበቅ አለበት። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በርካታ የአማራ ተወላጆች አማራነትን እንደማንነት
ለመቀበል ለምን እንደሚከብዳቸው እንመልከት።። በእኔ እምነት ብዙ ሰወች አማራን የፖለቲካ ማንነት አድርገው
ላለመቀበል በቂ ምክንያት ነበራቸው። ይህም የአማራነት ፖለቲካዊ ትርጉም ከጥንት ጀምሮ በኖሩበት ባህልና እሳቤ
ሳይሆን በሌሎች የፖለቲካ ትርክት ተወስኖ የተጫነባቸው ማንነት (politically imposed identity) ስለሆነ ነው። ማንነት
የተወሳሰበ ጽንሰሃሳብ ስለሆነ አጭር ታሪክ ቀመስ ገለጻ ላቅርብ።

ማንነትን ራሳችን መርጠን ስንሆነውና ሌሎች “ እንዲህ ናችሁ” ብለው ሲጭኑብን አቀባበላችን ይለያያል። ለምሳሌ የሰው
የቆዳ ቀለም (ጥቁር ወይም ነጭ የመሆን ጉዳይ) በአይን የሚታይ ልዩነት ቢሆንም፣ በ17ኛው ክፍለዘመን ከስልጣንና
ከፖለቲካ ጋር እስከሚገናኝ ድረስ አስፈላጊ ማንነት አልነበረም። አሜሪካ በእንግሊዝ ቅኝ ስትያዝ እዛ የተወሰዱት ድሃ
ነጮችና ከባርነት የተለቀቁ ጥቁሮች ተመሳሳይ ህይወት ነበራቸው። ነጭ ወይም ጥቁር መሆናቸው ከየት እንደመጡ
የሚያሳይ እንጅ የበላይነትና የበታችነት ምልክት አልነበረም። በ1675-6 ናትናኤል ቤከን በሚባል ሰው አነሳሽነት ድሃ
ነጮችና ጥቁሮች ተባብረው አንድ ፐርሰንት በሚሆኑት የእንግሊዝ ከበርቴወች ላይ አመጹ (Becon’s Rebellion)። በዚህ
ስጋት የገባቸው የእንግሊዝ ገዥወች፣ ነጮቹንና ጥቁሮቹን ከፋፍለው ለመግዛት ዘረኝነትን በቆዳ ቀለም ላይ እንዲመሰረት
ወሰኑ። ለድሃወቹ ነጮች ምንም ተጨማሪ ጥቅም ሳይሰጡ ጥቁሮቹን ለይተው ከነጮቹ የበታች አደረጓቸው። ጥቁሮች
መሳሪያ እንዳይዙ፣ በነጮች ላይ የመመስከር መብት እንዳይኖራቸው፣ ከሰው ይልቅ ለዝንጀሮ የሚቀርብ ማንነት ያላቸው
ተደርገው እንዲሳሉና ህይወታቸው ከነጮች እንዳይቀላቀል የሚያደርግ አስገዳጅ ህግ ወጣ። የነጭና ጥቁር ጋብቻ
ተከለከለ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥቁር ማለት የቆዳ ቀለም ሳይሆን የማንንት ምንጭ ሆነ። ጥቁሮቹ ጥቁርነታቸውን ራሳቸው
አልፈጠሩትም። ነገር ግን ጥቁር አይደለሁም ቢሉ በነጮች ‘ጥቁር” ከመባልና ከመጨቆን ስለማያመልጡ ያላቸው አማራጭ
የጥቁር ማንነትን ተቀብለው ትርጉሙን በራሳቸው ታሪክ መቀየር ነበር። ስለዚህ የጥቁር አፍሪካውያንን ህዝቦች ጥንተ
ታሪክ ማጥናትና የማንነታቸው ምንጭ ለማድረግ ጥረት አደረጉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያኒዝም ያሉትን ንቅናቄ የጥቁር ማንንት
የማስከበሪያ መንገድ አድርገውት ይከተሉት ነበር። እዚህ ላይ ልብ እንበል። ማንኛውም ልዩነት ከፖለቲካና ከስልጣን ጋር
ካልተያያዘ የግለሰቦች ጉዳይ ስለሚሆን ማንነት ብለን ብንጠራው ወይም ባንጠራው ብዙ ችግር የለውም። ማንነት
የፖለቲካና የስልጣን ምንጭ ከሆነ ግን የማይከበር ማንንት ያለው ሰው ከባድ ጉዳት ላይ ሊወድቅ ይችላል። ለምሳሌ
ለብዙወቻችን የአፍንጫ እርዝመት አስፈላጊ አይደለም። አንድ ወቅት ግን ርዋንዳ ውስጥ ቤልጀሞች ቱትሲወቹን
ከሁቱወቹ የለዩት የህዝቡን አፍንጫ በሴንቲሜትር በመለካት ነበር። ረዘም ያለ አፍንጫ ያላቸውን ቱትሲ ብለው ስልጣን
ሰጡዋቸው፤ አጠር ያለ አፍንጫ ያላቸውን ሁቱ ብለው ተገዢ አደረጓቸው። በአፍንጫ ልዩነት ሰበብ የፖለቲካና የጥቅም

11
ልዩነት ተፈጥሮ ከቆየ በኋላ አንዱ ተነስቶ “በቃ እንርሳው፣ የአፍንጫ ልዩነት እኮ ማንነት አይደለም” ቢል ሰሚ አያገኝም።
ማንነት የባህል ጉዳይ ቢመስልም የስልጣንና የጥቅም ደረጃ መመጣጫ ከሆነ ችላ ሊባል አይችልም። ቱትሲና ሁቱ
መጀመሪያ ትርጉም በሌለው የአፍንጫ እርዝመት ቢለያዩም፣ ባሳለፉት የፖለቲካ ህይወት ሳቢያ እስከመተላለቅ ደረሱ።

የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ልምድ ወዘተ ከህዝቦች ጋር ሁሌ የሚኖር ማንንት ነው። ይህን ማንንት ከፖለቲካና ከስልጣን ጋር
ካልተያያዘ ሰወች በነጻነት ሊቀይሩት፣ ሊደበላለቁ ይችላሉ። ሆኖም ፖለቲከኞች ይህንን ልዩነት ሰወችን ጠላትና ወዳጅ
አድርገው ለመክፈል ሲጠቀሙበት ያኔ የጠላት ማንነት የተጫነባቸው ሰወች የተጫነባቸውን የማንነት ትርጉም
እስኪቀይሩት ድረስ መቀበል ይከብዳቸዋል። አማራወች ከጥንት ጀምሮ በኖሩበት ባህልና እሳቤ ሳይሆን በብሄር ፖለቲካ
ልዩ ትርጉም የተሰጠው ማንነት ተጭኖባቸዋል። ብዙወቹ ከቋንቋቸው ጋር በማያያዝ አማራነታቸውን ይሁን ብለው
ቢቀበሉም ፖለቲካው ለአማራነታቸው የሰጠውን ትርጉም ግን ሊቀበሉት የሚከብድ ነበር። ለምን?

ኢሃዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት አማራ የተባሉ ሁሉ ራሳቸውን የጨቋኙ ብሄር አባል ሆነው አገኙት። ይህ የማንነት ፍረጃ
ለማንም ምክንያታዊ ሰው ግራ የሚገባ ነው። ምክንያቱም በ17 አመቱ የደርግ አገዛዝ ዘመን፣ የነገስታቱ ስርዐት (የብሄርም
ይሁን የመደብ) የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሰረቱ (በመሬት ላራሹና በሌሎችም) ከስር ከመሰረቱ ተነቅሎና በአዲስ የልሂቃን
መደብ ተተክቶ ነበር። ኢሃዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ ሁሉም ድሃ ኢትዮጵያውያን በአንድ መደብ ላይ ነበሩ፡፡ ያኔ በሃገሪቱ
ላይ ጉልበትና ሃብት የነበራቸው የዘውዱ ስርዐት ናፋቂወች ሳይሆኑ የዘውዱን ስርዐት ያጠፉት ወታደሮች ነበሩ። ይህም
ማለት ህወሃት ጫካ ሲወጣ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በተመለከተ ያረቀቀው የብሄር ትንታኔ (ስህተትም ሆነ አልሆነ)
ወደስልጣን ሲመጣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አውዱ ጠፍቶ ነበር ያገኘው። ሆኖም ከላይ እንዳልሁት ርዕዮተአለም
የፖለቲካ ሃይማኖት ነውና፣ ህወሃት ሃይማኖቱን ለመቀየር አልሞከረም። አማራነትን ከነገስታቱ ዘመን የጨቋኝነት መደብ
ጋር አስተሳስሮት ቀጠለ። ጨቋኝ በሌለበት ነጻ አውጭ ስለማይኖር ህወሃት ራሱን ነጻ አውጭ አድርጎ ለማስቀጠል
የአማራን የጨቁኝነት ትርክት ይዞት ቀጠለ። የህወሃት አስተሳሰብ በኢሃዴግ ውስጥ ስለተተገበረ ባለፉት 30 አመታት
አማራ በብሄሩ ጨቋኝ ለመሆን የሚችልበት መሰረት ሊኖረው ይቅርና፣ በብሄሩ ጥቃት የሚደርስበት ማንነት ወደመሆን
ተቀየረ። በዚህ ሳቢያ ብዙ አማርኛ ተናጋሪወች የአማራነትን ትርጉም ለመቀበል ሲከብዳቸው በአንዳንድ ክልሎች ዘንድ
ግን አማራነትን የሚያገሉ ህጎች፣ እምነቶችና አደረጃጀቶች ተፈጠሩ። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ያለፉት 47 አመታት ምን
ያህል የዱሮውን የዘውድ ስርዐት እንዳጠፉትና በአዲስ የልሂቃን ስርዐት እንደቀየሩት እየታወቀ፣ አሁንም አማራ ከነገስታቱ
ዘመን ጋር የተሳሰረ ማንነት ሆኖ ተፈጠረ። ከዚህም ይባስ ብሎ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ፣ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን
የነገስታቱን ታሪክ ከብሄር ጭቆና ወደ ጥገኛ ቅኝ አገዛዝ ታሪክ ስለቀየሩት አማራነት ከቅኝ ግዛት ሰፋሪነት ጋር የተያያዘ
አዲስ ማንነት ሆኖ ብቅ አለ። እዚህ ላይ በብሄር ጭቆናና በቅኝ አገዛዝ ጭቆና ያለውን አንድ ልዩነት ማጤን ይገባል።

የብሄር ጭቆና በአንድ ሃገር ውስጥ ካሉ ብሄሮች መካከል አንዱ ብሄር ሌላውን የሚጨቁንበት ስራት ሲሆን የቅኝ አገዛዝ
ጭቆና ግን ምንም አይነት የዘርና የባህል ግኑኝነት በሌላቸው ባእዳን መካከል የሚፈጠር፣ የአንድ ሃገር መንግስት በሌላ
ሃገር መንግስት ላይ የሚጭነው ጭቆና ነው። ለምሳሌ ሻዕቢያ አላማው ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ስለነበረ
የተከተለው ትርክት ኢትዮጵያ ኤርትራን ቅኝ ገዝታለች የሚል ለበር። አሁንም አንዳንድ የኦሮሞና የትግራይ ብሄርተኞች
ከብሄር ጭቆና ወደ ቅኝ አገዛዝ ጭቆና የሚያደላ ትርክት የሚከተሉት አዲስ መንግስት የመመስረት አላማን ምክንያታዊ
ለማስመሰል ይመስላል። የቅኝ ግዛት ትርክት በነጭ አውሮፓ ሰፋሪወችና በጥቁር አፍሪካ ኗሪወች መካከል የነበረውን
የዘርና የስልጣን ልዩነት መሰረት አድርጎ የሚተነተን ስለሆነ ትርክቱ ሙሉ ተቀባይነት ካገኘ የመገንጠልን ጥያቄ የነጻነት
(ዲኮሎናይዜሽን) ጥያቄ የማድረግ ሃይል አለው። በኦሮሚያ የዚህን ትርክት መስፈርት ለማሟላት በደርግ ዘመን ከልዩ ልዩ

12
ቦታ ለሰፈራ የሄዱ ድሆችን ልክ በቅኝ ግዛት ዘመን ከአውሮፓ ወደአፍሪካ እንደሄዱት አይነት ተደርገው እንዲቆጠሩ
የሚያደርግ የርእዮተአለም ግንባታ ሲደረግ ቆይቷል። አንዳንድ ‘ልሂቃን’ በኦሮሚያ የሚኖሩ አማሮችን ባልተፈጠሩበት
ዘመን የነበሩ ‘የሚኒልክ ሰፋሪወች’ የሚሏቸውና አንዳንድ የትግራይ ልሒቃን ሳይቀሩ ትግራይ በአማራ ቅኝ አገዛዝ
የተጨቆነች ናት የሚሉት፣ የቅኝ አገዛዝ ጭቆና ትርክት ሁለት የጥቅም አማራጭ ስላለው ነው። አንደኛ የመገንጠልን
ተገቢነት ስለሚያስከትል ነው። ሁለተኛ ቅኝ ገዥ ተብሎ የተፈረጀው አካል የያዘው መሬትና ሃብት በቅኝ አገዛዝ የተያዘ
ነው በሚል ሰበብ ሃብትና መሬቱን ከመቀማት ጀምሮ ከሃገር እስከማባረር የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ስለሚመች ነው።
ከዚህም በላይ ፍራንትዝ ፋኖን የአልጀሪያን ቅኝ አገዛዝ አይቶ፣ ቅኝ የተገዙ ሰወች የሃይል ጥቃትን በመፈጸም ወደተከበረ
ማንነታቸው ይመለሳሉ ብሎ ያቀረበውን ሃሳብ ለመጠቀም አመች ይሆናል። ከዚህ አንጻር ከብሄር ጭቆና ወደቅኝ አገዛዝ
ጭቆና የተቀየረው ትርክት በአማራ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የህልውና ስጋት መፍጠሩ የሚገርም አይደለም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ የአማራ ማንነት እየሰፋ የብሄር ፖለቲካን የሚቃወሙ ወይም አንድነትን የሚደግፉ የሌላ ብሄር
ተወላጆች ወይም ከአማራ ዘር የተደባለቁ ሁሉ የሚፈረጁበት ማንነት ሆኗል። አማራነት አማራ ባልሆኑ የፖለቲካ ቡድኖች
የሚፈጠር ብቻ ሳይሆን አማራ እየተባሉ ነገር ግን አማራነትን የሚቃወሙ ሃይሎች ሁሉ የወል ስያሜ ወደመሆን
ተሸጋገሯል። አንዳንዴም አማራነት በኦሮሞ ውስጥ ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ታማኝ አይደሉም ተብለው የሚጠረጠሩ
ግለሰቦች መፈረጃ እስከመሆን የደረሰበት ሆኔታ ይታያል። በዚህ ሁሉ ሂደት የአማራ ህዝብ የራሱን ማንነት በራሱ ፍላጎትና
ልምድ እንዳይፈጥር ከፍተኛ እክል ገጠመው። ለምሳሌ የአንድነት ሃይል የሚባሉት በአክራሪ ብሄርተኞች ‘አማራ’ እየተባሉ
የሚጠሩ ቢሆንም የአማራን ህዝብ በማንነቱ መደራጀት ግን አጥብቀው የሚቃወሙ፣ አልፎ አልፎም ‘ብቸኛው የኢትዮጵያ
አለኝታ’ እያሉ የፖለቲካ መሳሪያ ሊያደርጉት የሚሞክሩና በማንነቱ ጥቃት ሲደርስበት ግን በዝምታ የሚያዩ ሆኑ። እነዚህ
ሰወች በሃገሪቱ የፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ ውስጥ የአማራን ህዝብ ድርሻ ይዘው ለአማራ ህልውና የማይቆሙ ወይም የጥቃት
ምክንያት የሚሆኑ መሆናቸው ያሳዝናል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን የአማራ ማንነት በፖለቲካ መነጽር የሚታይና ብሄርተኞች
ብቻ ሳይሆሙ የአንድነት አቀንቃኞችም በየራሳቸው ምክንያት የማያከብሩት ማንነት ሆኖ እንደቆየ ነው።

ብሄርተኝነትን እንጸየፋለን የሚሉ ልሂቃኖች ብሄር ተኮር የሆነውን ጥቃት በቂ እውቅና ባለመስጠት የሞራል ልዕልና
ለማግኘት ወይም የሃላፊነትን ስሜት ለማስቀረት ሲሞክሩ ይስተዋላል። የሞራል ልዕልና የምለው የብሄር ተኮሩን ግድያ
“የዜጎች ግድያ ነው” ስንለው ገዳይም ሟችም የእኛው እኩል ዜጎች ናቸው ብሎ ለማመን ይመቸናል። ከዛም ገዳዩንም
ተገዳዩንም ዜጋ ካደረግናቸው በኋላ ችግሩ እኛን በማይመለከተን ጥፋት የተፈጠረ እንደሆነ አድርገን በማቅረብ ከሃላፊነት
ነጻ የመሆን ስሜት ይሰማናል። በዚህም የሞራል ልዕልና በመታገዝ የመብት ጥሰቱን የብሄር ፖለቲካን አደገኛነት ለማሳያነትና
ደጋፊ ለማብዛት እንጠቀምበታለን፡፡ ወገንተኝነት የሚጠይቀውን ከተጠቂወቹ ጎን የመሰለፍ ሃላፊነትንም በማስቀረት
ራሳችንን መካከለኛ፣ ገላጋይና የመፍትሄው ቁልፍ አድርገን እናቀርባለን። ‘አማራነት መሞቻ ሳይሆን መከበሪያ ይሁን’
ከማለት ይልቅ “ብሄርተኝነት ይጥፋ” በማለት የእነሱን የማንነት መብት ጥያቄ ወደእኛ የርዕዮተአለም ጥያቄ እንቀይረዋለን።
ይህ አስተሳሰብ ውስጡ ምን ያህል ከዘር እሳቤ የጸዳ እንደሆነ ማወቅ ያዳግታል። ምክንያቱም ይህን የሚሉ ሰወች የእኔ
ብሄር ተጎዳ ባይሉም የእኔ ዜጋ ተጎዳ ብለው ግድያውን ለማስቆም ከብሄርተኞች የተሻለ ጥረት ሲያደርጉ ስለማይታይ
ነው። የብሄር ፖለቲካ አይመለከተኝም የሚሉ ሰወች አንዳንድ ነጮች በዘረኛ ስርዐት ውስጥ እየኖሩ ‘I donot see colour’
እንደሚሉት አይነት ናቸው። ፖለቲካየን ያበላሽብኛል፣ የዜግነት ፖለቲካየን የአክራሪ አማራ ጭምብል ያስመስልብኛል
ማለት እኮ፣ የእኔ የፖለቲካ እምነትና ህይወት ከሰው ህይወት በላይ ነው እንደማለት ነው። ይህ እሳቤኮ በራሱ አክራሪ
ፖለቲካኝነት ነው። ከራሳቸው አይን ላይ የብሄር መነጽር ሰክተው የማንነት ተጎጅወችን ባያዩ ኖሮ ሞታቸውን ከብሄር
ፖለቲካ ጋር ባላገናኙትም ነበር።

13
የአንዳንዱ ሰው ምክንያት ደግሞ የማንነት ስነልቦና ቀውስን ለማስቀረት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በአማሮች ላይ
የሚደርሰው የግድያ አይነት እጅግ የሚዘገንን ስለሆነ ራሱን ‘ጀግና ነኝ’ የሚል ሰው ወይም ‘የኔ ብሄር አረመኔ አይደለም’
የሚል ሰው አገዳደሉ የውርደት ስነልቦናን የሚጭንበት መስሎ ይሰማዋል። ጥቃቱ በእኔ ማንነት ላይ የተፈጸመ ነው ብሎ
ቢቀበል ለጥቃቱ የሚሰተው መልስ አሁን ከሚችለው በላይ የገዘፈና ከራሱ ሰብእና ጋር የማይሄድ ሆኖ ይታየዋል። ይህ
ጥቃት እኔ ላይ ደረሰብኝ ወይም የእኔ ብሄር አደረሰው ብሎ ከሚያስብ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ መካዱ ወይም
ማድበስበሻውን መቀበሉ አቋራጭ አማራጭ ይሆንለታል። ታዲያ እየቆየ ሲሄድ ይህ እሳቤ የሰው ህይወትን ዋጋ ከብሄር
ማንነት በታች አሳንሶ የሚያስቀር የፈሪወች ጭምብል ከመሆን አያልፍም። ራስንም አያድንም።

አንዳንዶች “አማራ እንዲህ ሆነ የማንለው ብሄርተኝነትን ላለማስፋፋት ነው” ይላሉ። ይህ ከላይ እንዳልሁት ህግንና
ፖለቲካን ከማደበላለቅ የሚነሳ ስህተት ነው። እንደውም የአማራን ሰቆቃ ማደፋፈን የብሄር ፖለቲካን የበለጠ አስፈላጊና
ብቸኛ አማራጭ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሰላማዊው የኦሮሞ ህዝብ በአማራ ወገኑ ላይ የሚደርስበትን ጥቃት ተገንዝቦ
ድርጊቱን ለማስቆም እንዳይነሳ ያደርገዋል። ይልቁንም፣ ድርጊቱ በጽንፈኞች ብቻ ትርጉም እንዲሰጠው ስለሚያደርግ
ከፖለቲካ ውጭ የሆኑ ሰወች ህልውናቸውን ለማስቀጠል የሚችሉበት ብቸኛ የፖለቲካ መደራጃ መንገድ የብሄር ፖለቲካ
ብቻ እንዲመስላቸው ያደርጋል።

አንዳንዶች አማራ እንዲህ ሆነ የማንለው ጉዳዩ እንዲረግብ ለትዕግስት ተብሎ ነው ይላሉ። እኔም ግጭት እንዳይባባስ፣
ዕልቂት እንዳይከሰት የሚደረግን ጥንቃቄ እደግፋለሁ። ግን ሰላማዊና ጠንካራ ጥረት ከተደረገ እኮ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ
የቤንሻንጉል ወዘተ ውስጥ በድርጊቱ የሚያዝኑና ክፋቱን ለማስቆም የሚፈልጉ ብዙ ሰወች አሉ። እነዚህ ሰወች
የሚያሰባስባቸው መድረክና የጋራ አጀንዳ ይፈልጋሉ። በህልውና መብት ላይ የተመሰረተ ንቅናቄ ይህን እድል ሊፈጥር
ይችላል። ሰወች በማንነታቸው አይገደሉ የሚል ሃገራዊ ንቅናቄ ካልተፈጠረና የደረሰው ዘግናኝ ሰቆቃ ተቃራኒ የክፋት
ትርክቶችን ማሸነፍ ካልቻለ፣ ሃገሪቱን ወደተሻለ ሁኔታ መመለስ አይቻልም። “አንድ አማራ እስኪቀር ድረስ ኢትዮጵያ
ትቀጥላለች” እያሉ አማራነትን የመስዋዕት በግ አድርጎ ማቅረብ ከዚህ በኋላ አዋጭ እሳቤ አይደለም። ኢትዮጵያ
የአማራነትን መብት የምትጠብቅ ሃገር እንድትሆን መጣር እንጅ አማራን የምታስገድል ጭራቅ ሆናም ቢሆን መቀጠል
የምትችል አድርጎ መሳል አይገባም። የፖለቲከኞች ክፋት ባይጨመርበት ኖሮ አማራነትን ከማንኛውም ማንነት ጋር
በተቃራኒ እንዲቆም የሚያደርገው ምንም አይነት ነባራዊ ሁኔታ አይፈጠርም ነበር። የማንንት ግድያ፣ ዘረፋና ማፈናቀል
ከባድ ወንጀል ስለሆነ፣ በማለባበስ፣ በስሙ ባለመጥራት፣ እንዲቆም ባለመታገልና እውነተኛ እርቅ ባለመፍጠር ችግሩ
አይቆምም። አማራወቹ የሚገደሉት በተሳሳተ የታሪክ ትርክት አይደለም። ትርክቱ ተሳሳተም አልተሳሳተ አሁን የፖለቲካ
ርዕዮተአለም ሆኗል። ርዕዮተአለም ደግሞ የሚታረም ስህተት ሳይሆን ብዙ ህይወት የሚበላና በቀላሉ የማይቀየር እንደሆነ
ከመንጌ ዘመን ጀምሮ እናውቃለን።

መደምደሚያ

ስለሰብዐዊነት የሚናገሩ ሰወች ሰብዐዊነት በቃላት የሚደረደር ትርጉም የለውም ይላሉ። የሰው ልጆች ሰብዐዊነታቸውን
የሚያውቁት ሰብዐዊነት በተጣሰ ጊዜ በሚወስዱት እርምጃ ነው። ይህም እርምጃ ሰብዐዊነታቸው የተጣሰባቸው ሰወች
ማንነት የእኔም ማንነት ነው በሚል እሳቤ መመራት አለበት። እኛ ግን ሰብዐዊ መብታቸው በአማራነት ስም የተጣሰባቸው
ሰወች ማንነት የእኛ ማንነት እንዳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ አድርገን በማየት ስንሸሽ ነው የኖርነው። በማንነታቸው

14
ስቃይና ሞት የደረሰባቸውን አማራወች ዝም ማለታችን በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው። ድርጊቱን የምናየው
ከተጎዱት ሰወች ማንነት አንጻር ሳይሆን ከሁኔታወች ወይም ከውጫዊ ሰውነቶች ላይ ስለሆነ የትኛውም አይነት
ምክንያታችን መነሻው ራስ አምላኪነት (ሰልፍ ሴንተርድነስ) ነው።

በማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት ሃገራዊና አለማቀፋዊ የመብት ንቅናቄ የመፍጠር አቅም አለው። በብሄር ማንነት ሳቢያ
የሚደርስ ጥቃት ካልታወቀና በግልጽ ካልተወገዘ ለአጥፊወቹ የፖለቲካ ትርፍ ስለሚያስገኝ የስርዐቱ ባህሪ ይሆናል፤
አላማቀፍ ትኩረት ስለማያገኝ፣ ወንጀል መሆኑ ተረስቶ ወደ ፖሊሲ ሊቀየር ይችላል። ጥቃቱ በደም መፋሰስ ምክንያት
ከትውልድ ትውልድ ወደሚሸጋገር ጠብ ያመራል። በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል በጥልቀት ይስፋፋል። በአማራ ማንነት ላይ
የተፈጸመው ጥቃት በግልጽ ባለመታወቁና በሃገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ሚና ያላቸው ሁሉ አምርረው ስላልታገሉት ለዚህ
ውጤት አስተዋጾ አድርጓል።

የርዕዮተአለም ትግሉንና የህልውና ትግሉን መለየት ይገባል። የፖለቲካ ርእዮተአለም የሰው ህይወት አገልጋይ እንጅ፣ ሰው
ህይወት የርእዮተአለም አገልጋይ ሊሆን አይገባም። ብሄር እንደ ርዕዮተአለም ሲታይና ብሄር እንደ ህጋዊ መብት ሲታይ
የተለያዩ ናቸው። እንደ ርዕዮተአለም የብሄርን ፖለቲካ አልከተልም ማለት ይቻላል፡፡ እንደህጋዊ መብት አላከብረውም
ማለት ግን የመብቱን ባለቤት ያለህግ ከለላ ራቁቱን ማስቀረት ነው። ህጉ እስካልተቀየረ ድረስ በአማራነት ምክንያት
የሚሆነው አያገባኝም ማለት የምኖረው በህልም ፖለቲካ ውስጥ ነው እንደማለት ነው። በእኔ ላይ እስካልደረሰ ድረስ
በሌሎች የሚሆነው አያገባኝም እንደማለት ነው።

በማንነታቸው ለሚጠቁ መቆም ከእስከዛሬው የበለጠ አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላም ነጥብ አለ። ዛሬ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትና
የእስልምና ሃይማኖት ነባር ፍቅር እንዲበጠስ፣ የሃገሪቱ አዲስ ትውልድ ከዱሮው ባህል እንዲቆራረጥ የሚያደርግ የባህል
ጥፋት እየተፈጸመ ነው። ብዙወቹ የሃገራችን ህዝቦች የጋራ እሴቶች “የአማራ ባህል” በሚል ተፈርጀው እንደ ፖለቲካና
የስልጣኔ ጠላት እየታዩ ነው። በአንዳንድ ቦታወች ጥምቀትን መሰል በዐላት ማክበር ተከልክሏል። በልዩ ልዩ ቦታ ያሉ
የአማራ ተወላጆች በቋንቋቸው እንዳይማሩ፣ የፖለቲካ መብት እንዲያጡ ተደርጓል። ይህ በደል እየባሰ ሄዶ ወደግድያና
ወደቤተክርስቲያን ማቃጠል ከተሸጋገረ ሰነባብቷል። ህገመንግስቱ ሳይቀየር፣ በደሉ እየከፋና ወደዘር ማጥፋት እየዞረ
ባለበት ሰዐት ለሚጠቃው ብሄር መብት መከበር ቅድሚያ አለመስጠት፣ በአማራነት ስም ለሚጠፋው የኢትዮጵያ ነባር
ሃይማኖትና ባህል ደንታ ቢስ መሆን ነው። አማራ እንዳልባል በሚል አይመለከተኝም ብሎ ዳር መቆም ውድመቱ
እንዲሳካና እንዲቀጥል የተመቸ ሁኔታ መፍጠር ወይም የመተባበር ምርጫ ነው። በየትኛውም አለም የማንነት ጥቃት
ሲፈጸም ትልቅ ተቃውሞ የሚያስነሳውን ያህል በእኛ ሃገር ውስጥም ተቃውሞ እንዳይፈጠር የዘመኑ የፖለቲካ ድርጅቶች
ሁሉ አስተዋጾ አድርገዋል። ሰላማዊ ሰልፍ ያልጠሩ ወይም ጠንካራ መግለጫ እንኳን ያልሰጡ ብዙ ናቸው።

በኦሮሞና በትግራይ ብሄርተኞች ‘አማራ’ የሚባሉት የአንድነት ፖለቲካ አራማጆች ለአማራ የማንነት መብት መቆም ኪሳራ
ነው ይላሉ። እነሱ ቢከስሩም የሚከስሩት የፖለቲካ ስልጣንን ነው። በብሄራቸው ምክንያት አማራ የሚባሉት ድሆች ግን
እያጡ ያሉት ህይወታቸውን ነው፡፡ የአማራ ማንነታቸው በህጉ መሰረት እንዲከበር ባለማድረግ፣ በአማራ ማንነት
የሚደራጁትን በማጣጣልና በማሸማቀቅ ህዝቡን ለከፋ አደጋ ከማጋለጥ ሊቆጠቡ ይገባል።

አንድነቶች ኢትዮጵያዊነትን ለከተማ ልሂቃን በሚስማማ አኳኋን ብቻ ተርጉመው፣ የአማራን ህዝብ ጭፍን ደጋፊያቸው
ለማድረግ ይሰራሉ። የኦሮሞ ፖለቲከኞችም የአንድነትና የከተማ ልሂቃንን ከድሃው የአማራ ህዝብ ባለመለየትና እንደጠላት

15
በመፈረጅ የአንድነቱ ሃይል ደጋፊ አካል አድርገው ያዩታል። ብዙወቹ ብሄርተኞችም ሆኑ አንድነቶች ለብዙሃኑ ድሃ ህዝብ
መብት በተለይም ለገጠሩ ህዝብ ህልውና የሚጨነቁ አይመስልም። ለዚህ ማሳያ ምሳሌ የሚሆነን ህወሃት መሩ ኢሃዴግ
እንዲወድቅ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የመሬት ወረራ ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ የገጠር ይዞታ ባለቤቶች መሬታቸውን
በልማት ስም አጥተዋል፤ አሁንም እያጡ ነው። እንደዜጋም ሆነ እንደብሄር የእነዚህ ሰወች ከመሬት መነቀል እንዲቆምና
መሬታቸው እንዲመለስላቸው በቆራጥነት የተከራከረ ፓርቲ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን እንደመጡ ሁሉንም
የህብረተሰብ ክፍል ሲያወያዩ ገበሬውን ግን ሰብስበው አላወያዩም። በማዳበሪያ፣ በመሬት ዋስትና ወዘተ ጉዳዮች
እንደአንድ ችግር እንዳለበት ማህበረሰብ ተቆጥሮ የሚያወያየው አላገኘም።፡ እርሳቸው ስራ በዝቶባቸው ነው ቢባል እንኳን
“ይህንን ለምን አላደረጉም?” ብሎ የጠየቀ ጋዜጠኛ እንኳን የለም። ገጠሩ የሃገሪቱን ብዙሃን ህዝብ የያዘ ቢሆንም
በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ውስጥ የገጠሩ ህይወት መሻሻል ዋና የመንግስት አጀንዳ አይደለም። ሌላው ቀርቶ ገጠሬነት
የቴሌቪሽን ድራማወች መቀለጃና መዝናኛ ከመሆን ያለፈ ክብር የለውም። ባለሃብት ብር ይዞ ከመጣ ኢምንት የካሳ ክፍያ
ተሰጥቶት ገበሬው ከመሬቱ እንደቆሻሻ ተጠርጎ ይጣላል። የማንነቱና የህልውናው መደምሰስ ማንንም አያስጨንቅም።
ገጠሩ የጦርነትና የረሃብ ቀጠና ቢሆንም ከተማውን እስካልረበሸ ድረስ በቂ ትኩረት አያገኝም። በአጭሩ ገጠሩ
ለፖለቲከኞቻችን ባዶ ቦታ (Terra Nullius) ነው። ለገጠሩ ህይወት ህልውና የማይጨነቀው ፖለቲካና መንግስት፣
ለገጠሩ ህይወት ቅርብ ለሆነው የከተማ ድሃም ብዙም አይጨነቅም። ዛሬ ለከተማው ድሃ የህልውና ፈተና የሆነው ኑሮ
ውድነትም እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት አይቸረውም።። ይህ የሚያሳየን የልሂቃን ፖለቲካ ከድሃው ህዝብ ህይወት ሙሉ
በሙሉ የተነቀለ መሆኑን ነው። ለህዝብ ህይወት እቆማለሁ የሚል ፖለቲካ በቅድሚያ ከብዙሃኑ ህይወት ልምድና ፍላጎት
ውስጥ ራሱን መትከል ነበረበት።

የልሂቃኑ ፖለቲካ ራስ ወዳድነት መገለጫ የሆነ በቅርቡ አንዳንድ የአንድነት ፖለቲካ አራማጅ ነን የሚሉ ሰወች
የሚያራግቡት መፈክር አለ። ይህም "ብቻየን እስክቀር ድረስ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" የሚል ነው። "ብቻየን እስክቀር ድረስ
ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" የሚሉት ልሂቃን የግላቸውን ህይወት እንደ ኢትዮጵያ እያዩ፣ የሚፈራርሰውን የህዝብ ህይወት ግን
እንደመስዋዕትነት የሚቆጥሩ፣ በሃገር ወዳድነት ስም ራሳቸውን ብቻ የሚወዱ ሰወች መሆናቸውን ሊረዱት አልቻሉም።
ይህ አባባል “ኢትዮጵያ ወንጀለኞች የሚፈነጩባት፣ ህጻናትና ሴቶች በዘግናኝ ሁኔታ የሚታረዱባትና ሚሊዮኖች
ተፈናቅለው ሜዳ ላይ የተጣሉባት የገሃነም ምድር ብትሆንም እኔ እስካለሁ ድረስ በህይወት አለች” የሚሉ ሰወች አባባል
ነው። እነዚህ ሰወች የፖለቲካ እምነታቸውን ከሚቀይሩ ይልቅ ወይም “እንደሚጠቁት እኔም አማራ ነኝ” ብለው ለለውጥ
መስዋእትነት ከሚከፍሉ ይልቅ ህዝብ ቢያልቅ የሚመርጡ ይመስላሉ። የአማራን የህይወት ህልውና ጥያቄ ወደ ሃገር
የህልውና ጥያቄ ይቀይሩታል። ከኢትዮጵያ ታላቅ ባህሏ መርከስ፣ ከህዝቦቿ መረበሽ፣ በደም ከጨቀየ ምድሯና፣ በእንባ
ከሚታጠብ አካሏ ሁሉ በላይ ጎልቶ የሚታያቸው የራሳቸው የፖለቲካ እሳቤ ትክክልኛነትና የሚያመጡት የሰላምና
የብልጽግና ህልም ነው። ኢትዮጵያዊው ሁሉ በዘር ተከፋፍሎ በሚረገጥበትና ደም እንደውሃ በሚፈስበት ጊዜ ራሳቸውን
ከዘር ፖለቲካው በማግለል በሌለ መዋቅርና ስርአት የህልማቸውን ሃገር እያሰቡ ይቆዝማሉ። "ብቻየን እስክቀር ድረስ
ኢትዮጵያ ትቀጥላለች" ማለት ኢትዮጵያውያን ቢያልቁም እኔ ብቻየን በአስከሬን ምድር ላይ እኖራልሁ እንደማለት ነው።
አባቶቻችንና እናቶቻችን ጥንት ይሉ የነበረው ግን እንዲህ ነበር፦ “እኔ እስካለሁ ድረስ አንድም ኢትዮጵያዊ አይሞትም፤
ምክንያቱም እኔ በህይወት ቁሜ ኢትዮጵያውያን እያለቁ በማየት ብቻየን መኖር አልሻምና”።

ሰው ኢትዮጵያዊ የሚሆነው በሚሰራው ፖለቲካዊ ስራ እንጅ በሚያስበው ፖለቲካዊ ሃሳብ አይደለም። ሃገርንና ህዝብን
ለማዳን የሚያስችል ፖለቲካዊ ስራ ለመስራት ደግሞ ከተዋረደውና ከሚጠቃው የትኛውም ማንነት ጋር አብሮ መቆም
ያስፈልጋል። አማራ መሆን ማለት በአማራነታቸው ለሚጨፈጨፉት ሰወች መትረፍና ፍትህ ማግኘት ተግባራዊ ስራ

16
መስራት ማለት እንጅ የልሂቃንን የፖለቲካ ትርክት መላበስ አይደለም። አማራ በሚለው ማንነት ውስጥ የተሸፈኑት ሰወች
ወንጀለኞች ሳይሆኑ ንጹሃን መሆናቸውን ለማሳየት ራስን በዚያ ማንነት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል።

ክፍል 2- የአማራ ጥያቄ ለምን የህልውና ጥያቄ ሆነ

የህልውና ጥያቄ ሰው የመሆን ጥያቄ ነው።


እንደግለሰብም ይሁን እንደቡድን የምንተዳደረው በተቋማትና በህግጋት ስለሆነ፣ ሰዋዊ ማንነታችንና ሰብዓዊ መብታችን
የሚከበረው በህግ አይን እንደሰው ስንታይ ብቻ ነው። ተቋማትና ህግጋት ደሞ እያንዳንዳችንን የሚያዩት, የሚዳኙት፣
ሰው ሰውን እንደሚያየው ሳይሆን በፖለቲካው መነጽር በኩል ተመርተው ነው። ስለዚህ ተቋማትና ህግጋት አማራን
እንዴት ያዩታል ብለን እንጅ እኔ ራሴን እንዴት አያለሁ ብለን ማሰብ የለብንም። የስርአቱ ህግ ከእኔ ላይ የጫነውን የአማራ
ማንነት እንዴት ነው የሚያየው ብለን እንጠይቅ። እዚህ ላይ ልብ እንበል። አማራነትን ወደድነውም ጠላነውም በኢትዮጵያ
ህገ-መንግስት እስከተገዛን ድረስ ይህ ህግ እንዴት እንደሚያየን እያሰብን በስራቱ አይን ራሳችንን ካላየን ችግሩን መገንዘብ
አንችልም። የህግ አላማ ሰውን መጠበቅ ነው። ሰው በተፈጥሮ የተሰጠውና በህግ የማይገሰስ ሰብአዊ ማንነት አለው። ህግ
የሚወጣው ይህንን የተከበረ ሰብአዊነት ለመጠበቅ ስለሆነ ይህንን ሰባዊነታችንን ለመጠበቅ የስራቱ ህግ በቅድሚያ መከበር
እንዳለበት ሰው ያየናል ወይስ አያየንም ብለን መጠየቅ አለብን።

ከህገመንግስቱ ጀምሮ ባሉት ህጎችና ተቋማት አይን ሲታይ አማራ የሚለው ማንነት የንጹህ ሰው ማንነት ሳይሆን የወንጀለኛ
ማንነት እንዲሆን ተደርጓል። ስለዚህ በፖለቲካ ስርአቱ አይን ካየነው አማራ “ሰው” አይደለም። የፖለቲካ ስርዓቱ ወይም
መንግስቱ አማራን የሚያየው ይቅር የማይባል ወንጀል የፈጸመ ማንነት አድርጎ ነው። ስለዚህ ጠላት አድርጎ የፈረጀውንና
የማያከብረውን ማንነት በህግ ሊያስጠብቀው አይችልም። በሌላ አባባል፣ ፖለቲካው የአማራን ማንነት የቀረጸው ህጉ
የሚጠብቀውና የሚንከባከበው ማንነት እንዳይሆን አድርጎ ነው። ለንጽጽር -አሜሪካ ውስጥ “ሰው ሁሉ እኩል ነው”
የሚለው ህግ የወጣው ገና ባርነት ባልጠፋበት ዘመን ነው። ያኔ በባርነት የተያዙት ጥቁሮች በሰው አይን ሲታዩ ሰው
ቢሆኑም በህጉ አይን ሲታዩ ግን ሰው አልነበሩም። ስለዚህ ህጉ እስኪቀየር ድረስ የሰው ልጆች የእኩልነት መብት በአሜሪካ
ውስጥ መኖሩ ወይም አለመኖሩ በእነሱ ላይ ለውጥ አልነበረውም። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታም የሃገሪቱ ህግ
ለአማራ ማንነት ጥበቃ መስጠትና ዋስትና መሆን አይችልም። በስርዓቱ ፖለቲካ አይን ሲታይ አማራ ሰው ስላልሆነ በአማራ
ማንነት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ህጉ እርምጃ አይወስድም፤ ከወሰደም የይስሙላ ብቻ ይሆናል። ህጉ ለአማራ ማንነት
ጥበቃ ስለማያደርግም በማንነቱ ሳቢያ የሚጠፋው አማራ ሰው ሳይሆን ነፍጠኛ፣ ሰፋሪ፣ ጃውሳ፣ ወዘተ ስለሆነ በፖለቲካው
በኩል አማራን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ የተነሳ ሃይል ቢኖር ህጉ ምንም አያደርግም። እንደውም ለከፋ ጥቃት ምቹ ሁኔታ
ይፈጥራል።

አንድ ማንነት በፖለቲካ ውሳኔ ጠላትህ ከተደረገ፣ በጠላትህ ላይ የምትሰራው ክፋት ለወዳጅህ የምትሰራው ጽድቅ ተደርጎ
ይቆጠራል። ለብሄርህ ያለህን ጥልቅ ፍቅር የምትገልጽበት ዋናው መንገድ የብሄርህን ጠላት አምርረህ በማጥቃት ይሆናል።
ልክ እንደ መስቀል ጦርነት አዋጅ ጠላትን የገደለ የክርስቶስ ወታደር እንደሚባለው ሁሉ የብሄርን ጠላት የገደለም
ተመሳሳይ ክብር ይሰተዋል። እንደቆራጥ የህዝብ ልጅ ይታያል። ይህ ማለት የአማራ ህልውና በብሄርተኛ ፖለቲካወች
ውሳኔ ላይ ብቻ የተንጠልተለ ይሆናል ማለት ነው።

17
አሁን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲወች ወይም የመንግስት ህጎች ለአማራ ማንነት አገልግሎት የላቸውም። በርካታ አማራወች
አሁን በሰላም የሚኖሩት ፖለቲካዊው ሃይል ህልውናቸውን ለመንጠቅ የሚፈልግበት ምክንያት እስኪፈጠር ድረስ ብቻ
ነው። የዜግነት ፖለቲካ ወይም የብሄርተኝነት ፖለቲካ ሁለቱም አሁን ባለው ሁኔታ የአማራን ህዝብ የህልውና ጥያቈ
አይፈቱም! በቅድሚያ የህልውና ጥያቄ ራሱን ችሎ መፈታት አለበት። ምክንያቱም የዜግነትና የብሄር መብቶች የአማራን
ህዝብ እንዳያገልግሉ ተደርገዋል። እነዚህ የመብት ምርጫወች ከማንነት ፍረጃ ነጻ ለሆነ ብሄር፣ ወይም ዜጋ ብቻ
የሚያገልግሉ ናቸው። በማንነቱ ምክንያት ጠላት የተደረገ ህዝብ የመብት ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም። ባለው የብሄርም
ሆነ የዜግነት መብት ለመገልገል በቅድሚያ ከተጫነበት የጠላትነት ትርክትና ጥቃት ነጻ መሆን አለበት። ይህንን ነጻነት
ለማግኘት ግን መለመን ሳይሆን መታገል ነው ያለበት። ምክንያቱም ህልውና ስጦታ አይደለም። ህልውና ተፈጥሯዊ ነው።
የህልውና ጥያቄ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ ጥያቄወች በላይ ነው። ሰው ሆኖ የመኖር ጥያቄ ነው። ማንነቴን የጥቃት ኢላማ
አድርጎ ራሱን የሚያደራጅ የፖለቲካ ሃይል ሊኖር አይገባም የሚል ጥያቈ ነው። በአማራ ማንነት ላይ ለደረሰው ግፍ ፍትህ
ይሰጥ የሚል ጥያቄ ነው። ይህ ሳይሆን እንደሰው መከበር ይቅርና መኖርም አይቻልም።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ዜጎች ወይም ብሄሮች ጥቃት አለባቸው። በአማራ ላይ የሚደርሰው ግን ከሁሉም
ይለያል። በህገመንግስት የተፈቀደ ነው። በታሪክ ውስጥ ለነበረው “የተዛባ ግኑኝነት”፣ ጭቆና፣ ዘርማጥፋት ወዘተ ሁሉ
ተከሳሽ ሆኖ፣ ፖለቲካዊ ፍርድ ተላልፎበት ወንጀለኛ የተደረገ ማንነት አማራ ብቻ ነው። ጎሳቸውን ወደሀገር ለመቀየር
ያለሙ ፖለቲከኞች ከአማራ ማንነት ላይ ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር የጥላቻ ትርክት ጭነውበታል። ይህ የሆነው
ከአማራ ህዝብ ላይ ብቻ ነው። ቢሆንም የአማራነት ትርጉሙ ሌሎችም ላይ እንዲጫን በሚያደርግ ሁኔታ ሰተቀረጸ ከስራቱ
ጋር የሚጣሉ፣ ወይም ተቃውሞ የሚያነሱ ብቻ ሳይሆን መጠቃታቸው ጥርፍ የሚያስገኝ ከሆነ ሁሉም የሃገራችን ህዝቦች
ተጠቂ መሆናቸው አይቀርም። ስራቱ የኢትዮጵያዊነትን እሴቶች በሙሉ ቀስ በቀስ ከሁሉም ህዝቦች ውስጥ ማጥፋቱን
ይቀጥላል።

ስላዚህ፦
በህጉ አይን ራቁቱን የቀረና የማይከበር ማንነት ያለው ህዝብ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት ስርአቱና ህጉ እንደሰው
እንዲያየው የሚያደርግ ወይም የሚያስገድድ የህልውና ትግል ማድረግ ነው። ሰብዓዊ ህልውና በመንግስት የሚጠበቅ
እንጅ ከመንግስት የሚሰጥ ስላልሆነ ህልውናን ለማስከበር የማንንም ፈቃድ ማግኘት አያስፈልግም። መንግስት ለህልውና
መልስ የሚሰጠው ጸረ-ህልውና ዘመቻውን በመተው ነው። ለጥቃት ሰለባወች ፍትህ በመስጠት ነው። በሰላማዊ መንገድ
የቀረበን የህልውና ጥያቄ በሃይል ለመፍታት መሞከር ግን የህልውና ጠላት መሆንን ማረጋገጥ ነው።

የአማራ ህዝብ መሪ አለው። የአማራን ህዝብ የሚመራው የህልውናው ጥያቄ ነው። ከተፈጥሯዊ ማንነቱ ላይ ያላግባብ
የተጫነን ወንጀል ለማስወገድ የቀረበ ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ በልሂቃን ትርክትና አመራር ተቀናብሮ ሳይሆን በአማራ
ማንነት ከደረሱ ጥቃቶች በተወለደ የህይወት ልምድ የሚመራ ትግል ነው። ህዝባዊ የሚያደርገው ልዩ ባህሪም ይህ ነው።
የአማራ ያልሆነውንም ጭምር በአንድ ላይ ለመነሳት ለመተባበር የሚያስችል ሰው የመሆን ጥያቈ ነው። ሁሉም
ፖለቲከኞችና የሁሉም ብሄር አባላት በቅድሚያ ሊስማሙበት የሚገባ ጥያቄ ነው። ይህ እንዳይሆን መሰናክል የሚሆኑ
የፖለቲካ ሃይሎች የእነሱ አጀንዳ የአማራን ህዝብ ጥያቄ እንደማይፈታ ሊገነዘቡት ይገባል። አማራ በህገመንግስቱ
በተሰጠው ማንነት ተደራጅቶ ይታገል ማለት የተጫነበትን የጨቋኝነት ትርክት ይዞ ይቀጥል ማለት ነው። ይህ ደግሞ
የጥቃት ኢላማ ሆኖ ይቅር ብሎ መፍረድ ነው። ብሄርተኞች ይህንን የጥፋተኝነት ማንነት ይዞ እንዲቀጥል ለምን ይፈልጋሉ?
ምክንያታቸው ከራሳቸው ፖለቲካዊ ህልውና ጋር የተያያዘ ነው።

18
የብሄር ነጻ አውጭወች ጨቋኝ የሚሉት ብሄር ከሌለ የነጻነት ግንባር ሆነው መቀጠል አይችሉም። ብሄራቸውን ነጻ
እናወጣለን የሚሉት ከአማራ ጭቆና ነው። የአማራ ጭቆና ቢኖርም ባይኖርም፣ የነጻነት ግንባር ሆነው የሚቀጥሉት አማራ
የሚባል ጨቋኝ ሃይል እንዳለ አድረገው ተከታዮቻቸውን በማሳመን ነው። ስለዚህ የአማራን ህዝብ እንቅስቃሴ
የሚከታተሉት ትርክታቸውን እውነት የሚያስመስል የፖለቲካ ስህተት አማራወች ላይ በመፈለግ ላይ ነው። ያለ አማራ
ጭቆና ትርክት እነሱ የብሄር ነጻ አውጭ ሆነው መቀጠል ስለማይችሉ የአማራን ህዝብ ጠላት አድርጎ የሚያስቀጥል ሃሰተኛ
ትርክት የግድ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ሁኔታ ለሁሉም ብሄሮችና ህዝቦች አደገኛ ነው። የአማራ ህዝብ ከምድረ ገጽ ቢጠፋም
እንኳን መቀጠሉ አይቀርም። ምክንያቱም የዚህ ዘረኛ ፖለቲካ እስትንፋስ የሚቀጥለው ማንኛውንም የፖለቲካ ባላንጣውን
“አማራ” እያለ በመፈረጅ ነው።

በሃገራችን የብሄር ፖለቲካን መከተል ያስፈልጋል ከተባለ በቅድሚያ ሁሉንም ብሄሮች እኩል የሚያይ ህግ ያስፈልጋል።
የአማራን ማንነት እንደሌላው ማንነት እኩል የሚያከብሩ ህጎችና የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር አለባቸው። ማንነትን
የፖለቲካ ጠላት አድርጎ መሳል በህግ መከልከል አለበት። አውሮፓውያን አይሁዶችን ማንነት ያጠቁበት ትርክት
አንቲሰመቲዝም በህግ እንደተከለከለው በአማራም ላይ የሚቀርቡት የማንነት ፍረጃወች መታገድ አለባቸው። ይህን
ለማድረግ ክርክር አያስፈልግም። በታሪክ ውስጥ ምንም ይደረግ ምን፣ ዛሬ ላይ ሰው መግደል ፍትሃዊ አይደለም።
አረመኔአዊነትና ጸረህዝብነት ነው። በተጨማሪም በአማራ ማንነታቸው ምክንያት የተገደሉ፣ የተፈናቀሉ፣ የታሰሩ፣
ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ መብታቸውን የተነፈጉ ሁሉ ፍትህ ማግኘትና ተመሳሳይ የማንነት ጥቃትን የሚያስቀር የህግ ጥበቃ
እዲኖራችው ማድረግ ይገባል። ይህ ካልሆነ አሁን ያለው የብሄር መብት ለአማራ ህዝብ መጥፊያ እንጅ መዳኛ ሊሆን
አይችልም።

ስለዚህ፦
• በቅድሚያ ሃገር አቀፍና ህዝባዊ የህልውና ንቅናቄ ይፈጠር ዘንድ ሁሉም ሰወች ወይም ህዝቦች በአንድ ላይ
ከፖለቲካቸው በፊት የህልውና ጥያቄን ያለልዩነት ማንሳት ይገባቸዋል። ምክንያቱም ከላይ ስለአማራ የዘረዘርሁት
ሁሉ በሌሎቹም ላይ ይሰራል። የፖለቲካው ሃይል በጠላትነት ፈርጆ እነሱንም ሊያጠፋቸው ይችላል። ይህ ሁኔታ
ስርአቱ በዘር ማጥፋት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያደርገዋልና።
• የሁሉንም ህዝቦች የህልውና ትግል መደገፍ ያለብን የሌሎቹን ህዝቦች ማንነት ጠላት አድርገው እስካልተነሱ
ድረስ ብቻ ነው። ህዝብን በማንኛውም ምክንያት ጠላት አድርጎ የሚነሳ ፖለቲካ ጸረ ህዝብ ነው። ይህ በህግ
እንዲታገድ መደረግ አለበት።
• ህጉ እንደሰው የማይጠብቀው ማንነት የተጫነበት ሰው ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት አለው። ህጉ
ማንነቱን እስኪያስከብርለት ድረስ፣ ራሱን ከመጥፋት ለማትረፍ የሚያደርገውን ተጋድሎ መደገፍ አለብን።
ይህንን የምናደርገው ህግ ለመጣስ ሳይሆን ህጉን ፍትሃዊ ለማድረግ ነው። ህጉ ፍትሃዊ ካልሆነ ሁላችንንም
ያጠፋናል።
• በአማራ ላይ የሚደርሰውን ማንነት ተኮር ጥቃት መቃወም ካልቻልንና እንደህልውና ጥያቄ ካልወሰድነው
በአማራ ላይ የሚፈጸመው ጭካኔ እኛኑ በፍርሃት ያስረናል። እኛም ነገ ብንቃወም እጣ ፈንታችን በጭካኔ መገደል
መታረድ ሊሆን እንደሚችል እንድናስብ ያደርገናል። መቸም ቢሆን ነጻ ሆነን መኖር

19
የአማራ ህዝብና የሌሎችም ህዝቦች የህልውና ጥያቄ የሚስተናገደው ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ የሆነ የፍትህ ስራ መተግበር
ሲቻል ነው። በእጃችን ላይ ላሉት ጉዳተኞች ፍትህ ሳናረጋግጥ የፖለቲካውን ቁስል ማከም አንችልም። ከዚህ ጋርም የህዝብ
ለህዝብ የእርቅ ፕሮግራም ማዘጋጀት ይገባል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታወች ከተሳኩ በኋላ አማራም ይሁን ጉራጌ፣ ጋምቤላም
ይሁን አፋር፣ ኦሮሞም ይሁን ኮንሶ፣ ሁሉም ህዝቦች በእኩልነት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ህይወት ሊሻገሩ ይችላሉ። ከዚህ
በኋላ በዜግነትም ይሁን በብሄርተኝነት ፖለቲካ መሳተፍ የትኛውንም ህዝብ የህልውና አደጋ የማይጋብዝ ይሆናል።
ብዝሀነት የሃገራችን ውድ ማንነት ስለሆነ በየትኛውም የፖለቲካ ስርአት እናስከብረው የሚለው ጥያቄ የፖለቲካ ምርጫችን
አካል ይሆናል።

ክፍል 3- የህልውና ትግል የሁሉም የሃገራችን ህዝቦች አጀንዳ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

የሃገራችንን ህዝቦች የሚያስተሳስሯቸው ገመዶች ከእለት እለት እየተቆራረጡ በመውደቅ ላይ ናቸው። ይህን አደጋ
ለመቀልበስ ችግሩን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል። የችግሩ ፈጣሪወችና አስቀጣዮች ናቸው የምላቸው በሀገሪቱ ውስጥ
ያሉት የብሄርተኝነትና የአሃዳዊነት (ዜግነት) እሳቤን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ሃይሎች ናቸው። ሁለቱም እሳቤወች (እንደ
እኔ የሃገርበቀል ቅኝ አገዛዝ እሳቤወች ናቸው) ህዝቡ ከነባር ማንነቱና እሴቱ ውስጥ መፍትሄ እንዳያፈልቅ አድርገውታል።
ይህን ያደረጉት በቅድሚያ የህዝቡን የህልውናና የፍትህ ጥያቄ መሰረት ያደረገ ትግል ምካሄድ ከቻሉ ብቻ ነው።

ጎሳቸውን ወደሀገር ለመቀየር ያለሙ ፖለቲከኞች ባህልን፣ ታሪክንና፣ ቋንቋን የብሄረ-መንግስት መመስረቻ መሳሪያወች
አድርገዋቸዋል። የፖለቲካ መሳሪያ የሆነ ነገር ደግሞ የጥቅም ማስከበሪያና የጠላት መመከቻ ወደመሆን ስለሚቀየር
መንፈሳዊ ክቡርነቱ እየረከሰ ወደ ስልጣን አገልጋይነት ይወርዳል። ከሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌወች ይልቅ የፖለቲካ
ልሂቃን የእምነቱና የባህሉ ጠበቃ ነን ብለው እንዲነሱ ያስችላቸዋል። የባህል፣ የእምነትና የቋንቋ ጠበቃወቹ ፖለቲከኞች
ስለሚሆኑ፣ እነሱን ተው ማለት የሚወክሉትን ማንነትን የመቃረን ሙከራ ተደርጎ መተርጎም ይጀምራል። ፖለቲካዊ
ማንነትና የቋንቋና የባህል ማንነት ሲደበላለቁ የሚከበርና የሚታፈር ነገር እየጠፋ ይሄዳል። በባህልና እምነት ውስጥ ያሉት
ህዝብን የሚያፋቅሩ፣ የሚያስተዛዝኑ፣ የሚያከባብሩ እሴቶች ሁሉ እየተሰባበሩ ይወድቃሉ። በዚህ ሳቢያ ሁሉም ህዝብ
(ፖለቲከኛ የሆነውም ያልሆነውም) ተጎጅ ይሆናል።

በብሄር ፖለቲካ ምክንያት ሁላችንም የማንነት ጥቃት ሰለባወች ሆነናል። ብዙ ትግሬወችና ኦሮሞወች ምንም
ያላደረጋቸውን የአማራ ህዝብ እንዲጠሉ ተደርገዋል። የአማራ ጥላቻ የፖለቲካ ማንነታቸው አካል ሆኗል።፡አማራወችም
በሚደርስባቸው በደልና ጥላቻ ሳቢያ የጠሏቸውን እንዲጠሉ ማድረግ የሚችል የበደል ጥግ ተከምሮባቸዋል። በዚህ አውድ
ውስጥ ጦርነት፣ ግድያና ማፈናቀል ሲደርስ መታረቂያ የሚሆን ድልድይ (ሶስተኛ ጎራ) እንዲጠፋ ተደርጓል። ይህ ድልድይ
ከጥንት ጀምረን የወረስነው በሁሉም ብሄርና እምነት ውስጥ ያለውና ለሺ ዘመናት እንደሀገር ያኖረን የፍትህ፣ የርህራሄ፣
የመተማመን፣ የይሉኝታ፣ ወዘተ እሴት ነው። የዚህ ድልድይ መፍረስ ህዝባችንን በተለይም ወጣቱን የጉልበት እና የገንዘብ
አምላኪ እያደረገው ይሄዳል። ስልጣንና ወንጀል ያለሃፍረት የገንዘብ መሰብሰቢያ ይሆናሉ። ታዲያ ይህንን የሃገር ህልውና
መሰረት የሆነውን ድልድይ እያፈረሰው ያለው ምንድን ነው? ከህዝባዊነት ወደ ገንዘብብ አምላኪነት እየወሰደን ያለው ማን
ነው? ይህንን የህዝብ ድልድይ ለማፍረስ ፖለቲከኞች እንዴት ያለ ዘዴ ተጠቀሙ?

ዘዴው የፖለቲካ ስነልቦና እጥበት ነው። በመጀመሪያ አማራ የሚባለውን ከጨቋኝነት፣ ከዘራፊነት፣ ከነፍጠኝነት ጋር
አስተሳሰሩት። የኦርቶዶክስን እምነት፣ ነባሩን የእስልምና እምነትና የሃገሪቱ የነጻነት ምልክት የሆነውን ባንዲራ የአማራነት

20
መገለጫ እንዲሆን አደረጉት። ኢትዮጵያዊነትንም ጨምረው አማራ የሚለው ማንነት መገለጫ እንዲሆን አደረጉት።
በፖለቲካ ትርጉሙ የማንነታቸው ጠላት እንዲሆን የተደረገው አማራ ባንዲራቸውን ይዞና የዱሮውን ታሪክ ጠብቆ
እንዲያዩትና፣ ኢትዮጵያዊነት የአማራነት መገለጫ ብቻ ሆኖ እንዲታይ አደረጉት። በዚህ ጊዜ ከአማራ ውጭ ያሉት ህዝቦች
በተለይም የኦሮሞ ህዝብ የራሳቸው አባቶችና እናቶች ከሌሎቹ ጋር መስዋእትነት የከፈሉለት ባንዲራና የነጻነት ታሪክ
በቀላሉ የአማራ የመጨቆኛ መሳሪያ እንደነበረ አድርገው እንዲያዩት ይወተወቱ ጀመር። የዛሬው ህይወታቸው በትናንቱ
የአማራ ጭቆና የተፈጠረ እንደሆነ አድርጎ የሚስል የፖለቲካ ባህል እንዲፈጥሩ ተደረገ። ይህ ባህል በሙዚቃቸው፣
በስነቃላቸው፣ በትምህርታቸው እያደገ ሂዶ፣ ወደዘር መጠፋፋት የሚያደርስ ግጭት ውስጥ ለመንደርደር የማያመነታ
ትውልድ ፈጠረ።

የሃገራችን ጦርነት አማራ በሚል በተወከለው የኢትዮጵያ ነባር ማንነትና ብልጽግና በሚል በተወከለው የአሜሪካውያን
ካፒታሊስት ማንነት መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው። የዘመናችን ግጭት ለህልውና በሚደረግ ትግልና ለብልፅግና
በሚደረግ ጥቃት መካከል የሚካሄድ ጦርነት ነው። የህልውና አላማ ይዘው የሚታገሉት የሃገራችን ድሆች ናቸው።
ብልፅግናን አልመው የሚታገሉት የሃገራችን መሪወችና ከጀርባቸው ያሉት ጥቅመኞች ናቸው። የኢትዮጵያ ነባር እምነቶች
ከአማራ ላይ ብቻ ስለተጫኑ ነው እንጂ ሁሉም ህዝቦች የህልውና ጥቃት ላይ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ነን እስካሉ ድረስ፣
ባንዲራዋን እስካከበሩ ድረስ፣ ኦርቶዶክስ እስከሆኑ ድረስ፣ እስልምናቸው፣ ፖለቲካቸው ኢትዮጵያን እስካከበረ ድረስ
አማራ ተብለው ይፈረጃሉ። ስለዚህ ለማንም ብለው ሳይሆን ለራሳቸው ህልውና ሲባል ይህንን የግፍ ስራት ሊያስቆሙት
ይገባል። ለአማራ ህዝብ መቆም ለህዝባችን እሴቶች መከበር መታገል እንጅ አንድ ብሄር በሌላው ላይ እንዲጫን መታገል
አይደለም። ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ አይደለችም። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራ የአማራ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያና
ባንዲራዋ የህዝቦቿ የጋራ ታሪክ መገለጫወች ናቸው። ብልጽግና ግን የድሃ ኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነት አይደለም።
ብልጽግና ድሃ ሳያፈናቅል ሃብት ማፍራት አይችልም። ብልጽግና የሰውን ልጅ እኩል ማየት አይችልም። አንዱ እንዲበለጽግ
አንዱ መደህየት አለበት። የገንዘብ ምንጩ የድሃ ህዝባችን እልቂት ነው። ልብ እንበል። ሃብት የሚባለው ብር ሳይሆን
መሬት ነው። ገንዘብ በባለስልጣን የሚታተም ነው።፡መሬት ግን ከፈጣሪ ለህዝባችን የተሰጠን የህልውና መሰረት ነው።
መኖሪያና መቀበሪያ ነው። በጉልበትና በስልጣን የፈለገውን የሚያደርግ መንግስት ገንዘብን እያተመ የፈለገውን ማክበር
ያልፈለገውን ማደህየት ይችላል። ይህንን ለማድረግ እንዲመቸው የጋራ እሴቶቻችንን አስቀድሞ በማጥፋት ላይ ነው።
አላማው እንዳንተባበር፣ እንዳንደማመጥ፣ አብረን ድናንቆም ባለፈው እንጂ በመጭው ጊዜ ላይ እንዳናተኩር ማድረግ
ነው። ብልጽግና የሚያትመውን ገንዝብ ተጠቅሞ ሃብታችንን ለመቀማት እኛን በጠላትነት መፈረጅ አለበት። ለዚህ ነው
የምንገዳደለው። ሃገራችንን፣ ሃብታችንን፣ የወደፊት ልጆቻችንን፣ አለም ያደንቀው የነበረውን ማንነታችንን ኁሉ የአንድ
ብሄር ማንነት መገለጫ አድርጎ ሲያጠፋው ከዳር ቆመን እንድናይ እያደረገን ያለው ለዚህ ነው። እስከዛሬ ድረስ ዳር ቆመን
ማየታችን ያሳዝናል። አሁንም ግን ተስፋ አለ። ሁላችንም ከተባበርን ይህንን ጥፋት አንድ ጥይት ሳይተኮስ ቢያንስ ድርጊቱን
እንዲቀይር ማስገደድ እንችላለን።

አረመኔ ስርአት ውስጥ ተጠቃሚወቹ ጥቂቶች ናቸው። ብዙ ሚሊየን ህዝብን መጨቆን የሚችሉት ጉልበታቸው ከእኛ
ስለሚበልጥ ሳይሆን እኛን የክፋት ስራቸው ተባባሪ በማድረግ ነው። ልዩ ልዩ የስነልቦና ጦርነት በማካሄድ የእኛ ፍላጎት
ሊሳካ የሚችለው በእነሱ ፍላጎት መሳካት በኩል እንደሆነ አድርገን እንድናምን በማድረግ ነው። ሌላው ዘዴ አእምሮአችንን
በፍርሃት በመቆለፍ ነው። አሰቃቂ ግድያና ጥቃት የሚፈጽሙት ፍርሃት ትልቅ የጭቆና መሳሪያ እንደሆነ ስለሚያውቁ
ነው። ጉራ ግማሽ ሃይል ነው እንደሚባለው ህዝቡ የእነሱን ጉልበት የማይደፈር አድርጎ እንዲያምን በማድረግ ብቻ
የአሸናፊነት ስዕል በህዝቡ ስነልቦና ውስጥ ያገኛሉ። ትላልቅ የሚመስሉ ፕሮጀክቶቻቸውና የውትድርና ትርኢታቸው

21
የነልቦና ጦርነት መሳሪያቸው ነው። የተሸናፊነትና የተስፋ ቆራጭነት ስሜት ማስረጽ የስልጣናቸው ማስጠበቂያ መሳሪያ
ነው። ሌላው ዘዴያቸው፣ ፖለቲካን የግለሰቦች ጉዳይ አድርጎ ማሳየት ነው። ትኩረታችንን ጥቂት ባለስልጣናት ካደረጉትና
ከሰሩት ላይ እንዲውል በማድረግ ስርአቱ የሚፈጽመውን መዋቅራዊ ጭቆና እንዳናውቀው ያደርጉናል። ስለግለሰቦች
ስናወራ እነሱ በተደራጀ ሃይል የፈለጉትን ይፈጽማሉ። ህዝቡ በቀላሉ የሚረዳው ሃሳብ የግለሰቦችን ስራ በመስማት ስለሆነ
እንደ አንቂና መሪ አድርጎ የሚያየውም ስለግለሰቦች ወሬ የሚያወሩለትን ስለሆነ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ባህል ስርአቱን
ለመቀየር የሚያስችል የፖለቲካ አጀንዳ እንዳያድግ ያደርገዋል። አሉባልታና ወሬን ከፖለቲካ መለየት ስለሚከብድ ብዙወች
ፖለቲካን ዋጋ ቢስ አድርገው እንዲያዩትም ያደርጋል።

የሁላችንም ስነልቦና የስልጣናቸው መገልገያ መሆኑ ያበቃ እለት፣ መፍራት አቁመን መታገል ስንጀምር፤ ያኔ የእነሱ
95%በላይ የስልጣንና የሃይል ምንጭ ይደርቃል። የሚያዙት ትእዛዝ አይፈጸምም። የሚናገሩት ንግግር አይሰማም።
ከተጨቋኞቹ የሃገራችን ህዝቦች ልብ ውስጥ ሲወጡና እኛ በልዩ ልዩ ባህልና ቋንቋ የበለጸግን ኢትዮጵያውያን በፍቅር
ስንተያይ ያኔ የብልጽግና ፖለቲካ ራሱን ለማትረፍ ለህዝብ ፍላጎት እጅ ይሰጣል ወይም በህዝብ ግፊት ይወገዳል። በላቲን
አሜሪካ ብራዚል ገጠር ውስጥ የሚኖሩት ዛፓቲስታወች ያደረጉት ይህንን ነው። እንደአንድ ሃሳብና ድምጽ ተስማመተው
ከመንግስት ጋር መተባበርን አቆሙ። ሁሉም ተመሳሳይ ያለመታዘዝና ያለመተባበር እርምጃ በመውሰዳቸው መንግስት
የቱን አስሮ የቱን እንደሚፈታ ጨነቀው። የሚገዛለት ሲያጣ ከፍላጎታቸው ጋር ለመስማማት ተገደደ። ዛሬም ህዝቡ ይህንን
አማራጭ ሊከተል ይችላል። በአማራነት ስም የሁላችንም ሰብዓዊነት ሲወድም ዝም አንበል። ለህልውናቸው የሚታገሉትን
የአማራ ህዝብ ልጆች ማገዝ ነገም ለእያንዳንዳችን ህልውና የሚታገል ህዝብ ለማትረፍ ያስችለናል። የአማራ ህዝብ ትግል
እንደጠላት ሳይታይ፣ ከሁሉም ህዝቦች ጋር እኩል የሚኖርባት ኢትዮጵያን ማየት ነው። ይህ ካልሆነ የአማራ ህዝብ
ህልውናውን ለማስቀጠልና እንደሰው የሚያየው ስርአት ለመፍጠር ባለው ህግና ስርአት ያልተገደበ ሁለንተናዊ ጥረት
የማድረግ ተፈጥሯዊ ፈቃድ አለው።

22

You might also like