Professional Documents
Culture Documents
ገድለ ቅዱስ ቴዎድሮስ
ገድለ ቅዱስ ቴዎድሮስ
መግለጫ
በቤተ ክርስቲያናችን የትምህርተ ሃይማኖት መሠረት የሆኑ ፵፮ የብሉይ ኪዳን ፣ ፴፭ የሐዲስ ኪዳን ፤ በድምሩ
፹፩ አሥራው መጻሕፍት አሉን ። ደግሞ የረቀቀውን የሚያጎሉ ፡ ሀይለ ቃል የሚተረጉሙና የሚያብራሩ
መጻሕፍተ ሊቃውንት ፤ መጻሕፍተ መነኮሳት የሚባሉ አሉ ።
ከነዚህም ቀጥሎ ጌታ ለቤተክርስቲያን ፤ በቤተ ክርስቲያንም አማካኝነት ለምዕመናን የሠጣቸውን
ፀጋዎች የሚገልጹ ገድል ፣ ተዐምር ፣ ድርሳን የሚባሉ መጻሕፍት አሉ ።
ገደል ማለት ምዕመናን ጌታን ተከትለው በስሙ የተቀበሉትን መከራ የሚገልጽ ሲሆን ፤ ተዐምር ደግሞ
በተጋድሎ ውስጥ ሳሉ አምላካቸው ያመኑትንና የተማሩትን ትምህርት እውነተኛነት ለመግለጽ ያደረገላቸውን
ተዐምራት የሚተርክ ነው።
ድርሳንም እንደዚሁ አንድ የእግዚአብሔር ሰው የፈጸመውን አገልግሎቱን በአጠቃላይ የሚገልጽ የዜና
ሕይወቱ መግለጫ ነው ።
ለእነዚህ ሁሉ መሠረታቸው ግን በሉቃስ ም ፲፬ ቁ ፳፮ ፡ ዕብራም ፪ ቁ ፬ እና ፱ ፤ እንዲሁም በልዩ ልዩ
የወንጌል ምዕራፎች የተገለጹት ናቸው ።
ከዚህም በላይ የገድል ፤ የተዐምርና የድርሳን መሠረታቸው የሐዋርያት ሥራ የሚባለው መጽሐፍ
ሲሆን ምንጫቸው በአጠቃላይ ያው ወንጌል ነው ።
ገድልንም ፣ ተዐምርንም ፣ ድርሳንንም የሚነቅፉ ቢኖሩ ሁኔታውን በትክክል ያልተረዱ ሰዎች ናቸው ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግን “እናንተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ ፤ እኔን የተቀበለ
የላከኝን ተቀበለ” (ማቴዎስ ም ፲ ቁ ፵) በሚለው መሰረት ፤ እሱን አምላክ ብላ እንደተቀበለች ፤ እሱን ያመኑ
፤ ስለእሱ ዞረው ያስተማሩ ፤ በአደባባይ የመሰከሩ ፤ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ እሱን ያገለገሉ ፤ በቀን በሌሊት
እሱን የሚያመሰግኑ ፤ ሐዋርያትን ፣ ነቢያትን ፣ ሰማዕታትን ፣ ጻድቃንን መላዕክትን በስሙ ትቀበላለች ።
ቅድስናቸውንም ታውቃለች ። ስለእነሱም የተጻፈውን ዜና ሕይወት ትቀበላለች ። ምዕመናንም እነሱን
እንዲመስሉ ፤ እነሱን መስለው እንዲያገለግሉ ፤ እነሱ ከደረሱበት ማዕረግም እንዲደርሱ ፤ በአምላካችን ስም
የፈጸሙት ተጋድሎ ወይንም ገድል ፤ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ተዐምራት ፤ የተሰጣቸውን ጸጋ ፣ ክብርና
ቃልኪዳን ለምዕመናን ታስተምራለች ። ይኽም የቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ ገድል የተዘጋጀው በዚሁ
መሠረት ነው ።
ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ ፵ ዘመን በፈጀው ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ በሚታወቀው ድዮቅልጥያኖስ
ባስነሳውና በፈጸመው በሰማዕታት የተጋድሎ ዘመን ውስጥ በመጀመሪያ የሚገኝ ሰማዕት ነው ። የምሥራቁ
ንጉስ ድዮቅልጥያኖስ ክርስቶስን ክዶ ፤ ለጣኦት ሰግዶ ፤ ቤተክርስቲያንን ዘግቶ ፤ የጣኦት ቤት ከፍቶ
በክርስቲያኖች ላይ የመከራ አዋጅ በአወጀ ጊዜ የመጀመሪያውን የመከራ ጽዋ ከጠጡትና ድል ካደረጉት
የአንጾኪያ ሰማዕታት ውስጥ ተቀዳሚዎቹ የቤተ መንግሥት ተወላጆች ነበሩ ። ቅዱስ ቴዎድሮስ በአንጾኪያ
ቤተ መንግሥት ሶስተኛ የትውልድ ዘርፍ ያለው የመኮንን ሲድራኮስ ልጅ ሲሆን አንዱ ከአባቱ ወገኖች ፣
ሁለተኛው ከእናቱ ወገኖች የተሰየመ ሁለት መጠሪያ ስም ያለውና ቴዎድሮስ በናድልዮስ በመባል የሚጠራ ነው
።
በዘመኑ በቴዎድሮስ ስም የሚጠሩ ሞክሼዎች ሶስት ሲሆኑ አንዱ ሊቀጳጳሳቱ ፣ ሁለተኛው ሊቀ
ሠራዊቱ ሲሆኑ ሶስተኛው እራሱ ቴዎድሮስ በናድልዮስ ነው ።
ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ በዘመኑ በሃይማኖቱና በሰይፍ ሀገሩን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር ከሰውም
የተመረጠ ሐያል ሲሆን ለሀገሩ ለአንጾኪያና ለክርስትና ሃይማኖት ብዙ ሥራ ሠርቷል ። ገድሉም ይኸውና
ለምዕመናን እንዲያመች በአማርኛ ተተርጉመሞ ቀርቧል ።
ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ ድዮቅልጥያኖስን ከመንግሥት አውርዶ ገላውድዮስን በማንገስ አመ
ፀኞችንም በመቅጣት በጊዜው ታላቅ ሥራ ሠርቷል ። ግን የእግዚአብሔር መልአክ ጊዜው ምዕመናን
በሰማዕትነት ሊከብሩበት ፤ የእግዚአብሔር ሃያልነቱና ከሐሊነቱ በልዩ ልዩ የሰማዕትነት አደባባይ እንዲገለጥ
ለድዮቅልጥያኖስ የፈቀደለት መሆኑን ስለገለጸለት ሰይፉን አስቀምጦና ውትድርናውን ትቶ በፈቃደ
እግዚአብሔር ወደ ሰማዕትነት ገብቷል ። በድንግልና ፤ በበጎ ምግባር ፤ በእውነተኛ ሃይማኖት ፤ በሰማዕትነት
ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ እንደ አምላኩ ተሰቅሎ ፤ በ ፻፶፫ ችንካሮች ተቸንክሮ ድል የነሳ ሃያል ሰማዕት
ሲሆን ንጉስ ቁስጥንጢኖስ የሮምን መንግሥት ለመያዝ ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋ በነበረበት ጊዜ በመንፈስ መጥቶ
የረዳው ፤ ጠላቶቹ በብዛት ከበው ባስጨነቁት ወቅት ከጠላቶቹ እጅ ያዳነውና ኋላም በዚያ ሥፍራ ላይ
የቁስጥንጥንያን ከተማ እንዲመሰርት ያዘዘው ፤ የጌታን መስቀል ለማውጣት እንዲተጋ መምሪያ የሰጠው ሃያሉ
ሰማዕት ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ ነው ።
ንጉሥ ቁስጠንጢኖስም በቁስጥንጥንያ ካሰራቸው አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በቅዱስ ቴዎድሮስ ስም
ያሰራው ስለሆነ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኋላ በስሙ ቤተክርስቲያን የተሰራለት ሃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ቴዎድሮስ
እረፍቱ ጥር ፲፪ ሲሆን የሞክሼው የሊቀ ሠራዊት ቴዎድሮስ ደግሞ ሐምሌ ፳ ቀን ነው ።
ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ እጅግ የተፈራ ሰው ስለነበረ ንጉሱ ድዮቅልጥያኖስ ውሎ ሲያድር ሌላውን
ሕዝብ እንዳያነሳሳበትና እንዳይቀሰቅስበት ስለፈራ በአስቸኳይ እንዲሞት በሰጠው ፍርድ ጥር ፲፪ ቀን ተሰቅሎ
ሲሞት ለአንጾኪያ ሰማዕታት ሁለተኛው ነበር ። በመጀመሪያ የሞተው ከቤተ ዘመዶቹ አንዱ የነበረውና
ለአንጾኪያ ሰማዕታት ቀዳሚ ሰማዕት የሆነው በንጉሡ ቀኝ ቆሞ ሳለ የንጉሱ የድዮቅልጥያኖስ የክሕደት
ደብዳቤ እንደደረሰው ደብዳቤውን በመቅደዱ ድዮቅልጥያኖስ ራሱ ሰይፉን መዝዞ በገዛ እጁ ጥቅምት ፱ ቀን
የገደለው የሰማዕትነትን አክሊል የተቀበለው ቀዳሚ ሰማዕት እስጢፋኖስ ነው ። እንግዲህ ሁለተኛው ጥር ፲፪
ቀን በሰማዕትነት አክሊል የተከለለው ቅዱስ ቴዎድሮስ ነው ። ቁስጠንጢኖስንም የረዳው በሰማዕትነት ከሞተ
በኋላ ነው ።
በመግቢያው እንደገለጽነው ሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስቶስንና ቅዱሳኑን ተቀብላ መታሰቢያቸውን
በየመልኩ የምትፈጽም በመሆኗ ከተቀበለቻቸው ሰማዕታትም አንዱ ቅዱስ ቴዎድሮስ ነው ። በኢትዮጵያ
በቅዱስ ቴዎድሮስ ስም የተሰሩ ብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ሲኖሩ አንዱ የየረር ተራራን ተንተርሶ በሚገኘው
ቀድሞ ባዶቄ ፤ አሁን ግምቢ እየተባለ ከሚጠራው ተረተር ላይ የሚገኘው ነው ። በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ታሪክ
ያላቸውና በትንቢትም የሚጠበቁ ሥፍራዎች አሉ ። ከነዚህም አንዱ የረር ቴዎድሮስ ሲሆን በየረር ዙሪያ ብዙ
ሥውራን ቅዱሳን ሰዎች ይኖሩበታል ። ኋላም ቴዎድሮስ የሚባል ሃይማኖታዊ ደገኛ ንጉሥ ቴዎድሮስ
ይነግስበታል እየተባለ ስለሚተረክ ቀደም ሲል በሰማዕቱ በቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ ስም ቤተክርስቲያኑ
የተሰራው በዚህ ምክንያት ነው ይባላል ።
ቤተ ክርስቲያኑ የተቆረቆረው በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን ነው ። ጽላቱ የመጣው ከወደ ቡልጋ
እንደሆነ ይነገራል። አምጭዎቹ ቅድመ አያቶቻችን የመጀመሪያውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ታቦተ
ሕጉን በተለያየ ሥፍራ በመቃኞ እያረፉ ቢሞክሩም ፈቃደ እግዚአብሔር የሆነላቸው ብዙ ዓመታት የሃይማኖት
ተጋድሎ ከፈጸሙ በኋላ ጥንተ ስሙ ባዶቄ ይባል ከነበረው የአብርሃና አጽብሃ ቤተ መንግሥት ከነበረበት
ኮረብታ (የዛሬ መጠሪያው ግምቢ ከሚባለው) ላይ ጸንቶላቸው ቤተ ክርስቲያኑን በቅዱስ ቴዎድሮስ ስም
አንጸው ጽላቱን አሁን ከሚገኝበት ሥፍራ ካሳረፉ ይኸው ከ፻ ዓመታት በፊት ሕዝቡን አስተባብረው ያሰሩት
አባ መዝገቡ የሚባሉ ደገኛ አባት ነበሩ ። ከቤተ ክርስቲያኑ በስተምስራቅ ፪፻ ሜትር ከሚሆን እርቀት ላይ
ከንግሥት ዘውዲቱ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ከመሬቱ ውስጥ የከበሩ ማዕድናት ውጤቶችና ንዋዬ ቅድሳት
ለነገስታቱ በጊዜ ቀርበዋል ። ሥፍራው ለጎብኚዎችና ተማራማሪዎች አሁንም ምቹ ነው ።
የቀደሙ አባቶቻችን ልዩ ልዩ መጽሐፍትን ከልዩ ልዩ ቋንቋ እየተረጎሙ ወደ ኢትዮጵያ ሲያስገቡ
ከመረጧቸው አንዱ ገድለ ቅዱስ ቴዎድሮስ ነው ። መተርጎሙም እንዲያው ለለከንቱ አይደለም ። ከቅዱሳኑ
ገድልና እምነት ጽናት ፤ እግዚአብሔር ካረገላቸው ተዐምራት ምዕመናን እንዲማሩና ለሃይማኖታቸው ፣
ለሀገራቸው ፣ ለክብራቸው ፣ ለመብታቸው ፣ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ እየታገስ ሥጋዊና መንፈሳዊ ክብር
፣ ሥጋዊና መንፈሳዊ መብት ፣ ታሪክ ያጎናጸፋቸውን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውንና ኢትዮጵያን
ሀገራቸውን እንዲጠብቁ ነው ። እኛም ግዕዝ እየደገደገ በመሄዱ ገድለ ቅዱስ ቴዎድሮስን ብዙ ሕዝብ
በሚሰማው በአማርኛ ቋንቋ ተርጉመን አቅርበነዋል ። ሀሳባችን ግን አሁንም ምዕመናን ከኃያሉ ሰማዕት
ከቅዱስ ቴዎድሮስ በናጽልዮስ ገድልና ትዕግሥት ትምህርት እንዲቀስሙ ፣ ከልዑል እግዚአብሔር አምላክ
በተቀባው ቃልኪዳን እየተማጸኑ ስሙን በመጥራት መታሰቢያውን በማድረግ እንዲጠቀሙ ነው ። እንግዲህ
ተተርጉሞ ግዕዝ ከአማርኛው ጋር በንጽጽር ታትሞ የቀረበ ስለሆነ ይህን አገልግሎት ለመፈጸም ላስቻለ
አምላካችን ምሥጋና እያቀረባችሁ የሰማዕቱን የቅዱስ የቴዎድሮስን ስምና የአምላኩን ስም እየጠራችሁ
አምላከ ቴዎድሮስ እርዳን እያላችሁ እየተማጸናችሁ ሐብቱን ፣ ፀጋውን ፣ በረከቱን ለማግኘት እንድትጥሩበት
ይሁን ። አምላከ ቅዱስ ቴዎድሮስ ይህን መጽሐፍ ለማስተርጎም ፣ ለመፃፍ ፣ ለማሳተም ደከሙትን ፤
ገንዘባቸውን ዕውቀታቸውን በዚሁ ሥራ ላይ ያዋሉትን ምዕመናንና ምዕመናትን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ
ይባርክ ። ሀገራችንን ኢትዮጵያን ፣ ኦርቶድክሳዊ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን በምህረቱ ይጠብቅ አሜን።
አለቃ አያሌው ታምሩ
ጥር 1988
አዲስ አበባ