You are on page 1of 26

ማውጫ

1 መግቢያ 2

2 ትውልድ እና ዕድገት 4
2.1 የዘር ሐረግ . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 4
2.2 ጽንሰትና ልደት . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 4
2.3 ዲቁና፣ ቅስና እና ምናኔ . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 5

3 ገድላቸው 7
3.1 ምንኲስና እና ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 7
3.2 የሞረት አይሁድና ማኅሌተ ጽጌ . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 8
3.3 ኢትዮጵያን መዘዋወራቸው . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 8
3.4 ዕረፍታቸው . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 10
3.5 ቃልኪዳናቸው . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 11
3.6 ገድላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 12

4 ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች 15

5 የገድላቸው መጽሐፍ 20

6 ገዳሞቻቸው 22
6.1 ምሑር ኢየሱስ ገዳም . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 22
6.2 ደብረ ብሥራት ገዳም . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . 23

1
ምዕራፍ 1

መግቢያ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርት በምትሆን ወንጌል

እኔን የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ... ነፍሱን ሊያድን
የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፣ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል

− ማቴ 16፥24-25

ባለው መሠረት ብዙ ቅዱሳን ጻድቃን መከራ መስቀሉን ተሸክመው ወንጌልን በመስበክና ክርስትናን
በማስፋፋት እግዚአብሔርን አገልግለውታል። ይህንን ቃልም ተስፋ በማድረግ ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣
ድንጋይ ተንተርሰው፣ ድምጸ አራዊቱን፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ጸበ አጋንንቱን ሁሉ ታግሰው በየዱሩ በየገደሉ
በመንፈሳዊ ሥራ ተጠምደው ይኖራሉ።
በሃገራችን ኢትዮጵያ ከተነሡ እኚህን ከመሰሉ ቅዱሳን ጻድቃን መካከል አንዱ አቡነ ዜና ማርቆስ
ናቸው። ”ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ሰማይ ከዋክብት ለዘለዓለም ይደምቃሉ” (ዳን
12፥3) የሚለውን አምላካዊ ቃል ተስፋ አድርገው በመላዋ ሃገራችን ወንጌልን እየሰበኩ፣ ጣዖታትን
እያፈረሱ፣ አብያተ ክርስቲያናትን እየተከሉ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ቆይተዋል። በዚህም እንደ
ወንድማቸው እንደ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አዲስ ሐዋርያ እስከ መባል ደርሰዋል።
አቡነ ዜና ማርቆስ ለፈጣሪያቸው ሕይወታቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ያለ ምቾት፣
ያለ ሐኬት በርዳታ፣ በማስተማር፣ በሰማዕትነት፣ በድንግልና፣ በተባሕትዎና በምንኲስና 140 ዘመን
ፈጣሪያቸውን አገልግለዋል። ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ገድላቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በደብረ ብሥራት
ገዳም በሰላም ዐርፈዋል።
ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በአፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት በማዕረገ ቅዱሳን
እንዲታሰቡ፣ መታሰቢያ በዓል እንዲደረግላቸው፣ በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ፣ ገዳማትም
እንዲቆረቆሩ፣ መጽሐፍ እንዲጻፍላቸው በፈቃደ እግዚአብሔር በጉባኤ ወስነዋል። ገድላቸውንም አሰረፍኖታቸውን

2
ምዕራፍ 1. መግቢያ

የተከተሉ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ከዋሉበት እየዋሉ፣ ካደሩበት እያደሩ እግዚአብሔር በእርሳቸው ላይ


ያደረገውን ድንቅ ሥራ ሁሉ ዐይተውና ሰምተው ጽፈውታል።
ቅዱሳን ከሚጻፍላቸው ገድል ባሻገርም እምነታቸውን፣ ትምህርታቸውንና ተጋድሎአቸውን በተአምራት
ይመሰክርላቸዋል። ተአምራቱም በሕይወታቸው ብቻ ሳይወሰን ከሞቱም በኋላ ዐጽማቸው በተከሰከሰበት፣
ወዛቸው በተንጠፈጠፈበት፣ ደማቸው በፈሰሰበት፣ ወዘተ ሁሉ ሳይቋረጥ ይኖራል። አቡነ ዜና ማርቆስም
በዚህ መሠረት በእርሳቸው ስም የሚያደርገው ተአምራት ከዐረፉ ጀምሮ መቃብራቸው ባለበት፣ ገድላቸው
በሚነበብበት፣ ስማቸው በሚጠራበት ቦታ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራል። እኛም ይህንን ይዘን ’አምላከ
ዜና ማርቆስ’ እያልን በስማቸው እግዚአብሔርን እንማጸናለን፣ መታሰቢያቸውን እናደርጋለን።

የጻድቁ አባታችን ጸሎት ረድኤት አይለየን። አሜን።

3
ምዕራፍ 2

ትውልድ እና ዕድገት

2.1 የዘር ሐረግ


አቡነ ዜና ማርቆስ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ የዘር ሐረጋቸው ከእስራኤል ነገድ ነገደ ሌዊ ነው።
ከአዳም ጀምሮ 62ኛ ትውልድ ሲሆኑ፣ ወደ ኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ከመጣው ሊቀ ካህኑ
አዛርያስ ሲቆጠር ደግሞ 28ኛ ትውልድ ናቸው።1

ሌዊ → ቀዓት → እንበረም → አሮን → ይታምር → ጌዴዎን → አልዓዛር → አቤሜሌክ


→ ናታን → አብያታር → ሳዶቅ → አዛርያስ → ሳዶቅ ሌዊ (እግዚእ መሐር) → ሕዝበ
ረዓይ (አባ በግዑ) → ሕዝበ ዋሂ → ኦኪን → ስምዖን → እንበረም (በአብርሐ ወአጽብሐ
ዘመን) → ንጉሥ ሕዝባም → ሕዝበ ባርክ → አጽቀ ሌዊ → ይግናህ መስቀል → ይግናዕ
ዳዊት → ዘልዑል → ሚናስ (የንጉሥ ላሊበላ መምህር) → ሕይወት ብነ በጽዮን →
አባ አይድላ → ሕይወት ብነ ጽዮን ዳግማዊ → በኩረ ጽዮን → ሕዝበ ቀድስ → ብርሃነ
መስቀል → ሕይወት ብነ → ሴት → ወረደ ምኅረት → ዘካርያስ → ዮሐንስ (ቴዎድሮስ)2
→ ዜና ማርቆስ

2.2 ጽንሰትና ልደት


የአቡነ ዜና ማርቆስ አባታቸው አባ ዮሐንስ (ቴዎድሮስ) እና እናታቸው ማርያም ዘመዳ (ዲቦራ)
ከእመቤታችን ስዕል ፊት ዘወትር ልጅ እንድትሰጣቸው ይለምኑ ነበር። የእመቤታችንን እና የወንጌላዊ
1
ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ − በገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምዕራፍ 8 ግን ከአዳም ጀምሮ የሚቆጠረውን ትውልዳቸውን
ከ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር እኩል 61 ያደርገዋል። እንደገናም ገድለ ተክለ ሃይማኖት ”ከአዛርያስ ጀምሮ ቢቆጠሩ 27
ትውልድ ይሆናል” ይላል።
2
እንደ ገድለ ዜና ማርቆስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የአቡነ ዜና ማርቆስ የአጎት ልጅ ናቸው። ገድለ ተክለ ሃይማኖት ግን
”ወረደ ምኅረት ጸጋ ዘአብን ወለደ” ይላል።

4
ምዕራፍ 2. ትውልድ እና ዕድገት

ቅዱስ ማርቆስን መታሰቢያ በየወሩ ያደርጉ ነበር።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ወደ ዲቦራ መጥቶ በራእይ ተገልጦ ገድሉ
ትሩፋቱ ክብሩ እንደራስ ጠጉሩ የበዛ የተባረከ ፍሬ በማኅፀኗ እንደሚያድር አበሠራት። ለባሏ አባ ዮሐንስም
በቤተ መቅደስ የእመቤታችንን ስዕል ሲያጥን ተገልጦለት፦ ’ለድኆች በምታደርገው መራራት፣ ምጽዋት
ቡሩክ የሆነ ልጅ ይወለድልሃል፤ ስሙም ዜና ማርቆስ ይባላል’ ብሎ አበሠረው።

5
ምዕራፍ 2. ትውልድ እና ዕድገት

በዚሁም አባታችን አባ ዜና ማርቆስ የካቲት 24፣ 1333 ዓ.ም. አካባቢ3 ቀን ተፀንሰው በካህናተ
ሰማይ መታሰቢያ ዕለት ኅዳር 24 በጽላልሽ ዞረሬ፣ ቡልጋ፣ በኢቲሳ ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ተወለዱ።
የስማቸውም ትርጓሜ በቅዱስ ማርቆስ ብሥራት (ዜና) የተገኘ፣ የተወለደ ማለት ነው። በተወለዱ ጊዜም
ሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ ሩፋኤልና ቅዱስ ዑራኤል ልክ እንደ ነቢይ ኤልያስ የብርሃን ልብስ አልብሰው
በክንፋቸው ጋርደዋቸዋል። ገና ጡት ሳይጠቡም፣ እናታቸው ሳታውቅ በግብጽ የቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ
መቃብር ባለበት ወስደው እንዲባረኩ አድርገው መልሰዋቸዋል።
በተወለዱ በሦስተኛው ቀንም ከእናቱ ዕቅፍ ወርዶ በሥላሴ ስም አምናለሁ ብሎ ሦስት ጊዜ ሰግዷል።
ዐርብ እና ረቡዕ በሚሆኑ ቀናትም የእናታቸውን ጡት ባለመጥባት ጾምን ይጾሙ ነበር። በ40ኛው ቀንም
ለመጠመቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተገኘበት ጊዜ አጥማቂው አጎቱ ቀሲስ እንድርያስ ጸሎት
በማድረግ ላይ እያለ የመጠመቂያው ውኃ እጅግ ይፈላል፤ በዚህ ጊዜ ቀሲስ እንድርያስን ጨምሮ ሁሉም
ደንግጠው ጥለው የሸሹ ቢሆንም መልአኩ አረጋግቶ መልሷቸዋል። እንዲያውም አጥማቂው ራሰ በራ
የነበረው የ72 ዓመት የዕድሜ ባለጠጋ ቀሲስ እንድርያስ ከውኃው ራሱ ላይ ቢያፈስ ጠጉራም ሆነ።

2.3 ዲቁና፣ ቅስና እና ምናኔ


አቡነ ዜና ማርቆስ በአምስት ዓመታቸው ወደ መምህር ሄዶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከነትርጓሜአቸው
ለ3 ዓመታት ተምረው ጨርሰዋል። በዚሁ በ8 ዓመቱ በጊዜው በሃገራችን ከነበሩት የግብጽ ሊቀ ጳጳስ
አባ ጌርሎስ ዘንድ ሄደው ዲቁናን ተቀብሏል።
ዕድሜአቸው ለአቅመ አዳም እንደደረሰም ወላጆቻቸው ጸሎት ቢያደርጉ የእግዚአብሔር መልአክ
ተገልጦላቸው ማርያም ክብራ የተባለች የ10 ዓመት ውብ የባለጠጋ ልጅ እንዲያጩ አዘዛቸው። በዚሁም
ማርያም ክብራ ታጭታ ሠርግ ተደርጎ፣ በጫጉላ ቤት የሙሽሮችን ወግ እንዲያደርሱ በዚያው ተዉአቸው።
አባታችን ዜና ማርቆስ ግን ለማርያም ክብራ የዚህ ዓለም ነገር እንደ ጥላ እንደሚያልፍና የራሳቸውን
ነፍስ ድኅነት ለመሻት እንደሚሄዱ ነገሯት፤ እርሷም ትተዋት እንዳይሄዱ የእሳቸውን ፍኖት ለመከተል
አብራቸው ለመሄድ እንደምትፈልግ ነግራቸው በሌሊት አብረው ጫጉላ ቤቱን ትተው ወጡ።
በመላእክቱ በቅዱስ ሩፋኤል እና ቅዱስ ዑራኤል መሪነት ዜና ማርቆስ ወደ በረሃ፣ እርሷ ደግሞ ወደ
ደናግላን ገዳም የአባ ማማስ ደብር ገቡ። ማርያም ክብራ በዚያው ገዳም በተጋድሎ ለ7 ዓመት ከመንፈቅ
ከኖረች በኋላ ጥር 21 ቀን ሦስት አክሊላትን ተቀዳጅታ በሰላም ዐርፋ በሁለት አናብስት ተቀብራለች።
በኋላ ደግሞ ወደ እስክንድርያ፣ ግብጽ ሄደው ከአቡነ ብንያም ጋር ተገናኝተው፣ ምንኲስና እና ቅስና
ማዕረግ አግኝተው ተመልሰዋል።

3
ገድላቸው ’ግርማ አስፈሪ ሲነግሥ ያን ጊዜ አባታችን ዜና ማርቆስ 40 ዓመት ሆኖት ነበር’ ስለሚልና ግርማ አስፈሪ (ውድም
አስፈሪ) በ1374 ዓ.ም. ስለነገሠ ነው

6
ምዕራፍ 3

ገድላቸው

3.1 ምንኲስና እና ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር


አቡነ ዜና ማርቆስ እናትና አባታቸው ካረፉ በኋላ ሃብትና ንብረታቸውን ለነዳያን ሰጥተው ወግዳ
በተባለች ሃገር ወዳለች ዋሻ ገብተው በተጋድሎ መኖር ጀመሩ። ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም
ወደዚያች ዋሻ መጥተው ዜና ማርቆስን እያገለገሉ ይኖሩ ጀመር። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የሐዋርያትን እግር በማጠብ የትሕትና ሥራ እንደሠራ ለአቡነ ዜና ማርቆስና ለኢትዮጵያውያን መነኮሳት
ሁሉ የቆብ አባት ሲሆኑ ለእነርሱ የትሕትና ሥራን ያሳዩ ዘንድ አገልጋይ ሆኑ።
በአንዲት ቀንም አባ ተክለ ሃይማኖት በመፍጨት ሥራ ላይ እያሉ አባታችን ዜና ማርቆስ ለእንግዶች
እንጀራ እና ወጥ እያዘጋጁ ነበር። የእንግዶችን እግራቸን እያጠቡም እያሉ ወጡ ሲገነፍል ድንገት ድስቱን
ቢይዙ ግለቱ እጃቸውን አሳረረው፤ በዚያም እግዚአብሔርን እንዲፈውሳቸው ጮኸው ተናገሩ። ይህንን
ጩኸታቸውን የሰሙት አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በጌታችን ስም እፍ ቢሉበት እጃቸው ተፈውሷል።
ሁለቱ ቅዱሳን አባቶች በአንድነት በተጋድሎ ብዙ ከኖሩ በኋላ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል
መቃብራቸው ወደምትሆን ግራርያ የምትባል ሃገር አቡነ ተክለ ሃይማኖትን እንዲሄዱ ነገራቸው። አቡነ
ዜና ማርቆስንም የእነ እንጦንስና መቃርስ ሰይጣንን ድል የሚነሡበትን የመላእክት አስኬማ አልብሰው
ተሰናብተዋቸው ሄዱ። ዜና ማርቆስ ግን አስቀድመው በመንዝ ሃገር በአባ ገብረ ናዝራዊ ገዳም ከአባ
ገብረ ናዝራዊ ምንኲስናን ተቀብለው ነበር። እኚህም አባ ገብረ ናዝራዊ አስቀድመው ከጻድቁ አባታችን
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኲስናን የተቀበሉ ነበሩ።

ቅዱስ ሚካኤል → አባ እንጦንስ → አባ መቃርስ ትልቁ → አባ ጳኲሚስ → አባ


ቴዎድሮስ → አባ አረጋዊ → አባ ክርስቶስ ቤዛነ → አባ መስቀል ሞዐ → አባ ዮሐኒ →
አባ ኢየሱስ ሞዐ → አባ ተክለ ሃይማኖት → አባ ዜና ማርቆስ

የቆብ አባትነት ከአባ እንጦንስ ጀምሮ

7
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከደብረ ብሥራት ለመሄድ በተነሡ ጊዜ በዚያ የነበሩ
ዛፎች፣ እንጨቶችና ደንጊያዎች ሁሉ አብረዋቸው ለመሄድ ተነሡ። እርሳቸው ግን ሁሉንም በዚሁ
በደብረ ብሥራት እንዲጸኑ ገዘቷቸው፤ እንዲያውም ያቺን ደብረ ብሥራት ገዳምን ሳይሳለም ማንም ወደ
እርሳቸው ሃገር እንዳይመጣ አዘዋል

3.2 የሞረት አይሁድና ማኅሌተ ጽጌ


አባታችን ዜና ማርቆስ ከንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ ጋር ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አይሁድ
ካሉበት ሃገር ሄደው ምኩራባቸው ገቡ። በዚያም አንድ አይሁድ አግኝተው ስለ ብሉያት ትንቢት
በእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መፈጸሙን ሲነግሩት
ቆዩ። አይሁዳዊውም መልሶ የክርስቲያኖች መመኪያ የሆነች የእመቤታችንን ሥዕለ አድኅኖ በይፋት በረሃ
አግኝቶ ፈጣሪን ያህል ጌታ እንዴት ከሰው እንደሚወለድ ሲያወጣ ሲያወርድ አይሁዳዊ ጓደኛው መጥቶ
ሥዕሏን ቢመታው ወዲያው እንደተቀሰፈ እንዲሁም መልአክ በወፍ አምሳል ተገልጦ ዜና ማርቆስ የተባለ
መነኮስ እስኪመጣ ድረስ በአንተ ጥበቃ ትቆይ ብሎ እንዳዘዘው ነገራቸው። አባታችን ዜና ማርቆስም
ማንነታቸውን ገልጠውለት አሳምነው አጠመቁት፤ ስሙንም ጽጌ ብርሃን አሉት።
ሥዕሏንም በጥቅምት 1 ቀን በያሬዳዊ ዜማ እያሸበሸቡ ጣፋጭ በሆኑ ሽቱዎች መዓዛዋን አሳምረው
በደብረ ብሥራት ገዳም በስተምሥራቅ በሚገኝ ሜዳ ላይ የሥዕል ቤት ሠርተው በዚያ አኖሯት። መታሰቢያ
በዓሏንም ጥቅምት 3 ቀን አደረጉ። አባ ጽጌ ብርሃንም (አባ ጽጌ ድንግልም ይባላሉ) በመዝሙረ ዳዊት
ብዛት ልክ 150 ማኅሌተ ጽጌ የደረሱ ናቸው። 150 መዝሙረ ጽጌአትን የደረሰው የደብረ ሐንታው አባ
ገብረ ማርያምም ወደዚሁ የዜና ማርቆስ ገዳም ደብረ ብሥራት መስከረም መባቻ ላይ በመምጣት ከእነ
አባ ጽጌ ብርሃን ጋር አሳልፎ በኅዳር 8 ይመለስ ነበር። በወርሃ ጽጌ ሥዕሏ ፊት እያሸበሸቡ ሲዘምሩ
እመቤታችን ከሰማይ ወርዳ አባታችን ዜና ማርቆስንና በዚያ ያሉ ልጆቻቸውን ትባርካለች። አቡነ ዜና
ማርቆስም ሥዕሏን በንጹሕ ዕጣን እያጠኑ ይዞሯታል፤ በማዕጠንቱም ጢስ ድውያን ሁሉ ወዲያውኑ
ይፈወሱ ነበር።

3.3 ኢትዮጵያን መዘዋወራቸው


አባታችን ዜና ማርቆስ በኢትዮጵያ ሁሉ ያሉ ቅዱሳት ገዳማትን ጎብኝተዋል። በኪደተ እግራቸውም
መላዋን ኢትዮጵያን ባርከዋታል። በዚህ ጉዞአቸውም 4 ደቀ መዛሙርትን ያፈሩ ሲሆን በ200 አናብስት
እና በ200 አናብርት ታጅበው ይንቀሳቀሱ ነበር። ጉብኝታቸውም፦

አዳል → ምሑር → ጉራጌ → ሞረት → ዋልድባ ገዳም አባ ሳሙኤልን አግኝተው →


ተከዜ ወንዝ → ዐድዋ ላይ አባ ኢይስያስ → የ7 ቀን ምሕላ በቅዱስ ያሬድን መቃብር

8
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

አድርገው ቅ/ያሬድ፣ አባ ሕርያቆስና ቅ/ኤፍሬም ተገልጠውላቸው ባርከዋቸዋል → አክሱም


ጽዮን → ይምርሐነ ክርስቶስ ገዳም → የቅዱስ ላሊበላ ገዳም → ነአኩቶ ለአብ የተሰወረባት
ቦታ → ንጉሥ ገብረ ማርያም የሠራት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሮሓ → ጣና
ቂርቆስ ውስጥ አባ ያፍቅረነ እግዚአና በአባ ዘካርያስ ተባርከዋል → ጎጃምን ተዘዋውረዋል
→ ሸዋ ተመልሰው → ብሔረ ሕያዋንን ጎብኝተው በቅዱሳኑ ተባርከዋል → ዝቋላ አቡነ
ገብረ መንፈስ ቅዱስ ኮከበ ገዳም

ሥዕል - የአቡነ ዜና ማርቆስ ጉዞዎች በከፊል ከአሁኗ ኢትዮጵያ አንጻር

ጻድቁ አባታችን በጾም በጸሎት እጅግ ይተጉ ነበር፤ በዓመትም 3 ጊዜ ብቻ፦ በጌታችን ልደት፣
ጥምቀትና ትንሣኤ ካልሆነ በቀር እህልና ውኃ አይቀምሱም ነበር። ከ40 ዓመት ዕድሜአቸው በኋላ
በጸሎታቸው አጋንንት ታስረው ነበርና በመላዋ ኢትዮጵያ መናፍቃን አልተነሡም፤ ቀዳሚት ሰንበት እንደ

9
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

ክርስቲያን ሰንበት አትከበር ከሚሉና ንስሃ አያስፈልግም ከሚሉ በቀር። እኚህንም አባታችን ረተዋቸዋል4 ።

ተራ ሃገር ንጉሥ ያመኑ ሰዎች ጣዖት የተተከሉ


አብያተ
ክርስቲያናት
1 ምሑር አውጊት (ገብረ 2,075 ማኮስ 56 ታቦታት
መንክራዊ) (ቅ/ማርያም፣
ቅ/ማርቆስ፣
መስቀል፣
ቅ/ሩፋኤል፣
...)
2 ጉራጌ ቆልብ ግባ 12,000 ገርዳን -
3 ሞረት ድልአሰገድ - አጃጅ አርባቱ እንስሳ
4 የሞረት እስላሞች - 7,950 - -
5 አዳል አብድል ማል 802,000 ጽፍሮን -
6 በሃገረ ደንስ - ብዙ አይሁድ - ቅ/ማርያም፣ አባ
ኖብ፣ ቅ/ጊጋር፣
ቅ/ሚካኤል
7 ጎጃም ደየላፊት 1218 - -
8 እመሒና ገብረ ማሕየዊ - ዘንዶ -
9 እንደጊብጦን አሽሪፍ (ሠርፀ - - -
ማርያም)

ሠንጠረዥ 3.1: ጻድቁ አባታችን ከአምልኮ ጣዖት ወደ ክርስትና የመለሱባቸው ቦታዎች

3.4 ዕረፍታቸው
ጻድቁ አባታችን ዜና ማርቆስ በመጨረሻው ዘመናቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ
ቃልኪዳኖችን ከሰጣቸው በኋላ ገነትንና ሲዖልን አስጎበኛቸው። ከ10 ወራት በኋላም እንደሚያርፉ
ነግሮአቸው ወደ ገዳማቸው ደብረ ብሥራት መለሳቸው።
ጻድቁ አባታችንም በገዳማቸው ላሉ መልእከተኞች ከመስከረም እስከ ታህሣሥ ወር መግቢያ የመንፈስ
4
’ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች’ የሚለውን ምዕራፍ ተመልከት።

10
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

ልጆቻቸው ሁሉ እንዲመጡ ላኩ። በታህሣሥ ወር የመጀመርያዋ ቀንም 8000 ልጆቻቸው በዚያች ገዳም
በተሰበሰቡ ጊዜ 8 እንጀራ ብቻ የነበራቸው የገዳሙ ደቀ መዛሙርት ተጨነቁ። በዚህ ጊዜ አቡነ ዜና
ማርቆስ 8ቱን እንጀራ ባርከው፣ ቆራርሰው ሰጧቸው። በዚህም 8 ሺሁም ልጆቻቸው በልተው ጠግበው
108 መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ ተርፎ ተመልሷል።
ከዚህም በኋላ በደንስ በረሃ ያገኟት የእመቤታችን ሥዕል ባለበት ቤተ ክርስቲያን መሥዋዕት እንዲያዘጋጁ
ልጆቻቸውን አዘዟቸው። ራሳቸው ሠራዒ ካህን ሆነው ቅዳሴ በሚቀድሱበት ጊዜም 8000 ልጆቻቸው
ሥጋ ወደሙ ሳይቀበሉ መሽቶ ሊነጋ ነውና ፀሐይ እንድትቆም ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ። በዚህ ጊዜ
ፀሐይ መሥዋዕተ ሠርኩ እስኪያልቅ ድረስ በሰማይ ቆመች።
ልጆቻቸውንም ሁሉ ሲመክሩ ከቆዩ በኋላ በታህሣሥ 3፣ ዐርብ ቀን ዐረፉ። የክብር ባለቤት ጌታችን
እና እናቱ እመቤታችን፣ ሠራዊቶቻችውም መላእክት ወርደው ክብርት ነፍሱን አሳረጓት። በዚያም እስከ
ታላቁ ወንዝ ዠማ ድረስ መልካም ጣፋጭ መዓዛ ለ40 ቀናት ያህል ሸተተ።
የዐርብ ከሰዓት ቅዳሴ ሊጀምር ሲልም የግብጹ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ5 ከግብጽ በእሳት ሠረገላ ተጭነው
በዚያች ቤተ ክርስቲያን ደርሰው ሠራዒ ካህን ሆነው ቀድሰዋል። በኋላም ለዜና ማርቆስ ደቀ መዛሙርት
እንደነገሯቸው በግብጽ አይሁድ፣ ክርስቲያኖችና እስላሞች ክርክር ገጥመው ሳሉ ፀሐይ በመቆሟ የመቆሟ
ምክንያት እንዲገለጥ ጸሎት ሲያደርጉ ከሰማይ ድምጽ መጥቶ ”ክቡር አባ ዜና ማርቆስ እጅግ ብዙ
ለሆኑ ልጆቹ ቅዱስ ቊርባንን እስከሚያቀብሏቸው ድረስ እንዳትጠልቅበት አቁሟታልና የፀሐይ መቆሟ
ስለዚህ ነው” አሏቸው። በዚህም የተነሣ በዚያ የነበሩ እስላሞችና አይሁዶች አምነው እንደተጠመቁም
ተናግረዋል። እኚህ የግብጽ ሊቀ ጳጳስ አባ ዮሐንስ በዚያው በደብረ ብሥራት ለአንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ
ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።

3.5 ቃልኪዳናቸው
እግዚአብሔር ጻድቃን፣ ቅዱሳን ወዳጆቹን በአጸደ ሥጋ ለሠሩት ተጋድሎ ገነት፣ መንግሥተ ሰማያትን
በማውረስ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል። ነገር ግን ይህ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ልጆች ስም የሚበልጥ የመታሰቢያ
ስም በቤቱና በቅጥሩ ይሰጣቸዋል። ነገር ግን የቅዱሳን ዋጋ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ በስማቸው አምኖ
የሚማጸነውንና የታመነውን ነፍሱን በማዳን ሌላ የተጋድሏቸውን ዋጋ ይከፍላቸዋል። ቅዱሳን የራሳቸው
ነፍስ በመዳኗ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ነፍስ መዳን አብዝተው የሚሹ ናቸውና።
ጻድቁ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ በተለያየ ጊዜ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን
ተቀብለዋል፤

• በጣና ሐይቅ ደሴት ላይ ባለችው የዙር አባ ቤተ ክርስቲያን ሠራዒ ካህን ሆነው ሥጋ ወደሙ
5
አራቱ ኃያላን - በግብጻውያን የሊቃነ ጳጳሳት ዝርዝር መሠረት በዚህ ወቅት የነበሩት አቡነ ዮሐንስ 12ኛ /1480-83
እ.ኤ.አ/ ወይም ደግሞ አቡነ ዮሐንስ 13ኛ /1484-1524 እ.ኤ.አ/ ናቸው።

11
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

በሚፈትቱበት ጊዜ ጌታችን ለመታረድ የቀረበ ነጭ በግ ሆኖ ተገለጠ። በዚያም ቤተ ክርስቲያን


በኪዳነ ምኅረት መታሰቢያ ዕለት የካቲት 16 እና አባታችን ዜና ማርቆስ በተፀነሰባት በየካቲት
24 ሥጋ ወደሙ ለሚቀበሉ በኃጥያት ሆነው ከመሞት እንደሚድኑ በዚያው ዕለት ቃልኪዳን
ተቀብለዋል። ይህንን ቃልኪዳን በተቀበሉባት የካቲት 19 ዕለት እመቤታችን በርግብ አምሳል
ወርዳ ባርካቸዋለች፤ ከዚያም በኋላ ጻድቁ አባታችን ኑሮአቸው እንደ ሰማያውያን መላእክት ሆኖ
መብል እና መጠጥ መሻት ጠፍቶላቸዋል።

• ለእመቤታችን እና ለጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ኢትዮጵያን ዐሥራት አድርጎ
እንደሰጣቸው፤ ለአቡነ ዜና ማርቆስ ደግሞ የሞረት እና የመርሐ ቤቴ ሃገርና ሕዝብ በሙሉ
ዐሥራት አድርጎ ጌታችን ሰጥቷቸዋል።

• በፅንሰታቸው፣ በልደታቸውና በዕረፍታቸው ዕለታት፣ እንዲሁም በየወሩ በ3ኛው ቀን


መታሰቢያቸውን ለሚያደርጉ ሁሉ ከመከራ ሥጋ፣ ከመከራ ነፍስ እንደሚድን ቃልኪዳን
ገብቶላቸዋል።

• ቤተ ክርስቲያናቸው በታነጸበት የላም ሞት፣ በሰው ላይ ቸነፈር፣ በእህል ላይ ድርቅ፣ የሕፃናት


በሽታ አይደርስም፤ አንበጣ፣ ኩብኩባ፣ ጃርትም ቢሆኑ አይመጡም።

• የክብር ባለቤት ጌታችን ደግሞም ’ለማንም ያልሰጠሁትን ቃልኪዳን ልስጥህ’ በማለት በጻድቁ
ቃልኪዳን ያመነ፣ እርሳቸውን የሚወድ ኀጥያተኛ ሰው ሁሉ ከ80-160 ዘመን ለንስሐ
እንደሚሰጠው እንጂ በሞት እንዳይወሰድ ቃል ገብቶላቸዋል።

• በገዳማቸው ደብረ ብሥራት ባለች የእመቤታችን ሥዕል ፊት የእመቤታችንን ስም ጠርቶ


የሚጸልየውን ሁሉ ከገሃነመ እሳት እንደሚጠበቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል።

3.6 ገድላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ


እግዚአብሔር ልጆቹን በቀጥታ በመገለጥ እንደ ሐዋርያትና ነቢያት የሚጠራ ሲሆን፣ በነቢያት አድሮ
ትንቢትና ተግሳጽ እያናገረ፣ በሐዋርያት አድሮ ወንጌልን እየሰበከ፣ እያጻፈ በተዘዋዋሪ ይጠራል። ገድላት፣
ድርሳናት፣ መዝሙራት፣ ጸሎታት፣ ወዘተ እግዚአብሔር በተዘዋዋሪ መንገድ ከሚጠራባቸው መንገዶች
ጥቂቶቹ ናቸው።
ገድለ ዜና ማርቆስን የመሰሉ አዋልድ መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወለዱ ራሳችውም ቅዱሳን የሆኑ
መጻሕፍት ናቸው፤ የጻፏቸውም ሆኑ የተጻፈላቸው ቅዱሳን ናቸውና። ልክ ዛሬ የአንድ አባት ልጅ፣
የሥጋው ቁራጭ የአጥንቱ ፍላጭ ተብሎ ቁርጥ አባቱን ይመስላል እንዲባል − ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወለዱ
ገድላት፣ ድርሳናትም ይዘታቸው የአባታቸውን መጽሐፍ ቅዱስን ይመስላል። ልጅም አባቱን በመልካም

12
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

ሥራው መስሎት ስሙን እንዲያስጠራ ሁሉ ገድላት፣ ድርሳናትም የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ይተነትናሉ፣
ያብራራሉ፣ እንዲሁም በቃል ያለው በተግባር ሲፈጸም ያሳያሉ።
ይሁንና ይህ ገድለ ዜና ማርቆስና ሌሎችም ገድላትና ድርሳናት እውነትን በተቀሙና አእምሮአቸው
በጠፋባቸው ሰዎች እየተነቀፉ እና እየተወገዙ ይገኛሉ። በመሆኑም በዚህ ክፍል የአቡነ ዜና ማርቆስ
ገድል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ያለውን ዝምድና በጥቂቱ ለመዳሰስ እንሞክራለን።

• በቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ ብሥራት መፀነሳቸው − የእግዚአብሔር መልአክ ለማኑኤ እና ሚስቱ


ተገልጦ፣ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ አብሥሯቸዋል። ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለካህኑ
ዘካርያስ እንዲሁ ወንድ ልጅ እንደሚወልድ አብሥሮታል።

• በልደታቸው በብርሃን (መላእክት ክንፍ) መጠቅለላቸው − ነቢዩ ኤልያስ በልደቱ በእሳት


ተጠቅልሎ እንደተገኘ።6 በገለአድ አውራጃ ውስጥ ባለች በቴስብያ ነቢዩ ሲወለድ መላእክት
በጨርቅ ፈንታ በእሳት ጠቀለሉት። እናትና አባቱም ደስታቸው ሁሉ ወደ ፍርሃት እስኪለወጥ፣
ጌታ በጨርቅ በተጠቀለለበት ከራሱ ልደት የነቢዩን ልደት እስኪያስበልጥ ድረስ መላእክቶቹን
ላከለት። የሁሉ ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ በጨርቅ ብቻ የተጠቀለለ ነውና።

• ጣዖቱን ማኮስን ወደ መሬት መቅበራቸው − ሊቀ ነቢያት ሙሴ አንድ ግብጻዊ እስራኤላዊውን


እጅግ ሲበድለው ዐይቶ ኃያል በነበረች ክንዱ መትቶ ገድሎ አሸዋ ውስጥ ቀብሮታል፤ በዚህም
ግብጻዊው የዲያቢሎስ፣ ዕብራዊው የአዳም፣ ሙሴ የጌታ ምሳሌዎች ናቸው። (ዘፀ 2፥12)

• የሞረቱን የድል አለሰገድ ሠራዊት ምድር አፏን ከፍታ መዋጧ − ዳታንና አቤሮንን መሬት አፏን
ከፍታ መዋጧ። ዳታን፣ አቤሮን እና ቆሬ በሙሴ ላይ ባመጹ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት
ተሰንጥቆ እነርሱን ከነቤተሰቦቻቸው እና ዕቃዎቻቸው በሙሉ ውጣቸዋለች። (ዘኁ 16፥32)

• በአዳል ከዐርብ እስከ ሰኞ ጨለማ መሆኑ − በግብጽ በፈርዖን መደንደን የተነሣ ጨለማ እንደሆነ።
የግብጽ ፈርዖን ልቡ ደንድኖ እስራኤልን ከባርነት አልለቅም ባለ ጊዜ 9ኛው መቅሰፍት ድቅድቅ
ጨለማ ለ3 ቀናት በግብጽ ምድር መሆን ነበር። ሙሴም እጆቹን ባነሣ ጊዜ በግብጽ ጨለማ ሲሆን
ማንም ለ3 ቀናት ያህል ወንድሙን አላየም፣ ማንምም ከቦታው አልተንቀሳቀሰም። (ዘፀ 10)

• መላዋ ኢትዮጵያ በኪደተ እግራቸው መቀደሷ − ቀጶዶቅያ በቅዱስ ጴጥሮስ መመላለስ


እንደተባረከች

• 200 አናብስትና 200 ነብሮች ላይ መጓዛቸው − እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ከፈጠራቸው


በኋላ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት፣ ግዟትም፣ የባሕር ዓሣዎችንና የሰማይ ወፎችን፣ በምድር
ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዟቸው” (ዘፍ 1፥26-28) ብሎ በምድር ያሉ ፍጥረታትን ሁሉ
6
ድርሳነ ኤልያስ ዘወርኀ ታህሣሥ

13
ምዕራፍ 3. ገድላቸው

እንዲገዙ ሥልጣንን ሰጥቶአቸል። በመሆኑም አዳም አንበሶችንና ነብሮችን ጨምሮ አራዊትን ሁሉ


የማዘዝ ሥልጣን የነበረው ሲሆን ሕገ እግዚአብሔርን አፍርሶ ከገነት ከተባረረ በኋላ ይህንን ጸጋ
አጥቶታል። ከአዳም በኋላ ግን እግዚአብሔር ባለሟል ለሆኑት ቅዱሳን ልጆቹ ሁሉ ይህንን ጸጋ
ሲያድላቸው ኖሯል። ለምሳሌ ነቢዩ ኤልያስን ቁራዎች ይታዘዙት እንደነበር መጽሐፈ ነገሥት
መዝግቦታል፦ ”ቁራዎችም በየጥዋቱና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር” (1ነገ 17፥6)

• ፀሐይን ማቆማቸው − በሙሴ እግር የተተካ ኢያሱ ወልደ ነዌ ፀሐይን በገባዖን ሰማይ እንዳቆመ።
አሞሬዎናውያንን ከእስራኤል ጋር ተዋግተው ድል ቢነሡ ሲሸሹ በበረዶ ተመትተው ካለቁ በኋላ
እስራኤል ጠላቶቻቸውን ፈጽመው ሳያጠፉ እንዳይመሽ ኢያሱ ለእግዚአብሔር ጸሎት አደረገ፤
በዚያም ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ቆሙ። እግዚአብሔርም የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ
ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም እስኪባል ድንቅ ተአምራት ተደረገ። (ኢያ
10፥9-14)

• ሙታንን ከሞት ማስነሣታቸው − ነቢዩ ኤልያስ የሰራፕታዋን ሴትዮ ልጅ እንዳስነሣ (1ነገ 17፥17-
24) የኤልያስ ደቀ መዝሙር ነቢዩ ኤልሳዕም እንዲሁ የሱናማዊቷን ልጅ ከሞት እንዳስነሣ (2ነገ
4፥32-37)። በሐዲስ ኪዳንም እንዲሁ ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታን፣ ቅዱስ ጳውሎስ አወጣኪስን
ከሞት ማስነሣታቸው (ሐዋ 9፥3፤ ሐዋ 20፥7-12)

14
ምዕራፍ 4

ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች

መላእክት ከሰማይ ወረዱና


በክንፎቻቸው ጋረዱት፣ እንዲህም አሉ፦
እውነት በእውነት የድካሙ ፍሬ ተካዩ
የሆነ አምላካችንን ደስ ያሰኘ፣ ብፁዕና
ቅዱስ ወንጌላዊ ዜና ማርቆስ ያማረና
የተወደደ የዘይት ዕንጨት ነው።
በተጋድሎውና በምንኲስናው ወንጌልን
በኢትዮጵያ ሃገሮች ሁሉ ዞሮ በመስበክ
ማከማቻዎቹን ሁሉ ፍሬው ሞልቷልና።

ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ምዕራፍ 18

አቡነ ዜና ማርቆስ ጠቅለል ባለ መልኩ ለቤተ ክርስቲያናችን ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች፦

• በመላው ኢትዮጵያ በመዘዋወር ወንጌልን ሰብከዋል፣ በኪደተ እግራቸው ሃገሪቷን በሙሉ ባርከዋል፤
በዚህም በቤተ ክርስቲያን አባቶች ሐዲስ ሐዋርያ ተብለዋል።

• በተዘዋወሩባቸው የሃገራችን ክፍሎች ሕዝቡን ከአምልኮ ጣዖት ወደ ክርስትና መልሰዋል

• በሞረት፣ በተጉለትና በአዳል ያሉ እስላሞችን ፊት ለፊት በመከራከር ብዙ የዕድሜ ዘመናቸውን


አሳልፈዋል። የገድላቸው መጽሐፍ፣ ተአምር 8 ላይ ወንጌልን ከሚያውቁ እስላሞች ጋር፣ በተለይ
በዮሐንስ ወንጌል ላይ ተመሥርቶ፣ ያደረጉትን ሰፊ ክርክር መዝግቦት ይገኛል። በኋላም የሞረት
እስላሞች ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና እደመጡ ይናገራል።

• አጋንንትን በጸሎታቸው በማሰር ምንፍቅና እንዲጠፋ አድርገዋል፤ እንዲያውም ከሁለት ቦታዎች

15
ምዕራፍ 4. ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች

በቀር በመላው ኢትዮጵያ ምንፍቅና ጨርሶ እንደጠፋ ገድላቸው ይናገራል7 ።

• በአፄ ሰይፈ አርዕዝ ዘመነ መንግሥት ባደረጉት የቀዳሚት ሰንበት ክርክር፣ በሸዋ እንዲሁም
በኢትዮጵያ በአዋጅ የቀዳሚት ሰንበት መታሰቢያ እንዲከበር አስደርገዋል።

• በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ አይሁድን ወደ ክርስትና አምጥተዋል። በተለይም የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ


አባ ጽጌ ብርሃን (አባ ጽጌ ድንግል) በጻድቁ አባታችን ስብከት ወደ ክርስትና መጥተዋል። በዚያም
የእመቤታችን የወርኀ ጽጌ የምስጋና ሥርዓት ለ40 ቀናት እንዲደረግ ሥርዓቱን ሠርተውታል።

• በደቡቡ የሃገራችን ክፍል፣ በተለይም በምድረ ጉራጌ ክርስትናን አስፋፍተዋል፤ በዚሁ በደቡቡ
ክፍልም ታላቁን የምሑር ኢየሱስ ገዳም ገድመዋል።

• በጉራጌ ማኅበረሰብ እጅግ የሚታወቀውን በእንሰት ላይ የተመሠረተ የምግብ ዝግጅት አቡነ ዜና


ማርቆስ ባርከው እንደሰጡ8 ይነገራል።9

• ፀሐይን በማቆም ተአምራቸው በግብጽ የነበሩ እስላሞችና አይሁድ ወደ ክርስትና መጥተዋል10

• ወንጌልን ጠንቅቀው የተማሩ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ሃይማኖታቸውን ኢየሩሳሌም ድረስ


በመሄድ አንዲመሰክሩ ሆኗል። የመቃብራቸው አፈር በተለይ ኢየሩሳሌም ድረስ ከተጓዙት
መነኰሳት ጋር አብሮ በመሄድ በተለያየ ጊዜ ተአምራቱን ያደርግ ነበር። በዚህም የተነሣ የገድላቸው
መጽሐፍ ይህንን አስፍሮ ይገኛል፦

በዓለም ሁሉ ያላችሁ የክርስቲያን ወገኖች ወንድሞቻችን በትውልድ ሃገሩም በሸዋ


ምድር የምትኖሩ ስሙ፤ አባታችን ዜና ማርቆስ የሥሉስ ቅዱስን ሃይማኖት ያስተማረ
በሕይወቱ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ከዕረፍቱ በኋላም
አስተማረ።
− ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ተአምር 18
7
በዚሁ ምዕራፍ ’ከመናፍቃን ጋር ያደረጉት ክርክር’ የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።
8
ጎጎት የጉራጌ ብሔረሰብ ታሪክ የሚል መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ፦ ”የእንሰት ተክል አመጣጥ በማኅበረሰቡ ዘንድ
ብዙ አፈታሪኮች መካከል በሰፊው የሚነገረው ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጋር ተያይዞ የሚነገረው ነው። ይኸውም አቡነ ዜና ማርቆስ
ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተነስተው ክርስትናን ለማስፋፋት ወደ ምህር ቤተ ጉራጌ በመጡበት ጊዜ ይዘውት እንደመጡ ይነገራል።
በሌላ በኩል ደግሞ አቡኑ ሃይማኖታቸውን የተቀበለው የምሑር ሕዝብ ድርቅና ሌሎች አደጋዎችን የሚቋቋም የምግብ ተክል
እንዲያገኝ ባደረጉት ጸሎት በእግዚአብሔር ፍቃድ አንዲት ላም ከጣለችው እበት ላይ የበቀለ መሆኑን ይነገራል ... ይህንን
አፈታሪክ መቀበል እጅግ ያዳግታል” ይላል።
9
ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ ንባብና ትርጓሜ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
10
”ዕረፍታቸው” የሚለውን ንዑስ ክፍል ተመልከት

16
ምዕራፍ 4. ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች

ከመናፍቃን ጋር ያደረጉት ክርክር


ጻድቁ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ በሕይወት እያሉ ካደረጓቸው ሃይማኖታዊ ክርክሮች ዋነኛው ስለ
ቀዳሚት ሰንበት አከባበር እና ስለ ንስሐ በንጉሡ አፄ ሰይፈ አርዕድ ፊት ያደረጉት ነው11 ። አፄው ልክ
እንደ አባቱ ዓምደ ጽዮን በዝሙት ንዳድ የረከሰ ሆኖ ሳለ ጻድቁ አባታችን በንስሐ ሊመልሱት ወደ ቤተ
መንግሥቱ ሲመጡ በክፉ መካሪ ሆን ብሎ የሃይማኖት ተቃዋሚአቸውን ፈልጎ አምጥቶ አከራከራቸው፤
አስቀድሞ ግን ሃሳቡ ምንም ቢከራከሩ፣ ፍርድ ለባላጋራቸው ሰጥቶ እርሳቸውን ለማሰደድ ነበር።
በክርክሩም አቡነ ዜና ማርቆስ ቀዳሚት ሰንበት ከክርስቲያን ሰንበት እኩል ሆና የምትከበር እንደሆነች
አስረድተዋል። ከኦሪት በአሥርቱ ትዕዛዛት ያለውን ጨምሮ በነቢያት የተነገረውን ሁሉ፣ ’ሰንበታት’
ሰለመባላቸው፣ ዓመተ ኀድገትን ጨምሮ ስለ ቀዳሚት ሰንበት ክብር የተነገረውን አቀረቡ። በወንጌልም
ጌታችን ኦሪትንና ነቢያትን ሊሽር እንዳልመጣ፣ ቀዳሚት ሰንበትን አክብሮ የማዳን ሥራውን በዐርብ
ፈጽሞ በቅዳሜ በመቃብር እንዳረፈባት፣ ሐዋርያትም መሥዋዕት በሁሉም አጽዋማት በነግህ እንዲደረግባት
ማዘዛቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
ብዙ ’ኀጥያት ለሠራ ሰው ንስሐ የለውም’ ለሚለውም መልስ በዚያው ሰጥተዋል። ያስሩና ይፈቱ ዘንድ
በቅዱስ ጴጥሮስ ለሁሉ ካህናት ሥልጣንን እንደሰጣቸው፣ ሐዋርያትም በሲኖዶሳቸው ስለንስሃ የደነገጉትንና
ሊነገር የማቻል ኀጥያት የሠራች ሴት ኀጥያቷ በቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ እንዴት እንደተሠረየላት ተርከው
አስረድተዋል።
በዚያም ባላጋራቸው ካህን ውስጡን ካቶሊክ ኖሮ አላምንም በማለቱ ቢያወግዙት እርሱንና ከርሱ ጋር የነበሩ
40 ካህናትን ከሰማይ የወረደ እሳት በልቷቸዋል። ንጉሡም በዚህ ደንግጦ በፊታቸው ሰገደ፤ ንስሐም ገባ።
በመላው ኢትዮጵያ በአዋጅ ነጋሪ ቀዳሚት ሰንበትን በታላቅ ክብር እንዲያከብሩ፣ የሰንበትን መታሰቢያ
ትዕዛዝ ሰጠ፤ የማያከብሩም ገንዘቡ ሁሉ እንዲወረስ ደነገገ።

ደቀ መዛሙርቶቻቸው በኢየሩሳሌም ያደረጉት ክርክር


ጻድቁ አባታችን ከላይ እንደጠቀስነው በሕይወት እያሉ ብቻ ሳይሆን ከዕረፍታቸውም በኋላ ወንጌልን
ሰብከዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አስደናቂ ታሪክ በገድላቸው መጽሐፍ ተመዝግቦ የሚገኘው 60
ገጾችን የሚፈጅ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ወደ አክሱም ጽዮን ብሎም በግብጽ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረጉት
ጉዞ ነው።
ታሪኩ በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ልጅ ልጅ አፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት ከደብረ ብሥራት ገዳም 12 መነኰሳት
የ9ኙ ቅዱሳን መካናትን፣ አክሱም ጽዮንን እንዲሁም ኢየሩሳሌምን ለመሳለም የጻድቁ አባታችንን አቡነ
ዜና ማርቆስ መቃብር አፈር ይዘው መንገድ መጀመራቸውን በመናገር ይጀምራል። አፈሩንም ይዘው
11
ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ ተአምር 5

17
ምዕራፍ 4. ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች

እስከ አክሱም ጽዮን በሄዱበት ቦታ ሁሉ ክፉ ዘንዶን አጥፍቶ፣ ሙታንን አስነሥቶ፣ በውኃ በጥብጦ
የጠጣ ድውይ መኮንን አውሬ አስወጥቶለት፣ የአፈሩ ዝና በመላው ትግራይ እስኪናኝ ድረስ ተአምራትን
አደረገ። በደብረ ዳሞ ገዳምንም በብርሃን ገመድ መነኰሳቱን አውጥቶ ብርሃኑን በሌሊት ቢሰጥ የገዳሙ
መነኰሳት ገዳማችን በእሳት ተቃጠለ እስኪሉ ድረስ ድንቅ የብርሃን አምድን ይተክል ነበር።
በግብጽም በደረሱ ጊዜ በጊዜው ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት አባ ማቴዎስ ዘንድ ሊገቡ ባሉ ጊዜ ረድኦቻቸው
በበትር እንደሚመታቸው እያስፈራራ አባረራቸው፤ እነርሱም በዚያው በረሃ ወርደው ጸሎት ሲይዙ
የጻድቁ አባታችን የዜና ማርቆስ ክብር ይገለጥ ዘንድ በሌሊት የያዙት አፈር ከምድር ወደ ሰማይ የብርሃን
አምድ ተከለ። ይህንንም በሌሊት ሊቀ ጳጳሱ እንዲሁም የግብጹ የእስላም ንጉሥ ቢያዩ መነኰሳቱ ካሉበት
ወርደው ነገሩን ሰምተው አደነቁ። ሊቀ ጳጳሱም በፍቅር በአንድነት ወደ ኢየሩሳሌም አብረዋቸው ሄዱ።
በኢየሩሳሌምም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መቃብር ተሳልመው፣ ዐቢይ ጾምን በአንድነት ጾመው
ሲፈጽሙ በሃገሩ የተዘጋጀ የፋሲካ ማዕድ ለሊቀ ጳጳሱ ሰቅርብ የአቡነ ዜና ማርቆስ ልጆች የሆኑ
ኢትዮጵያውያን መነኰሳትን ግን በውጭ ተዉአቸው። እነርሱ ግን ሳይከፋቸው ሊቀ ጳጳሱ መብሉን
ፈጽሞ እስኪመለስ ድረስ ይጠብቁ ነበር። በዚያ በዕለተ ትንሣኤ ጾማቸውን ያገኛቸው ዮሐንስ የተባለ
የሮማውያን መምህር አዝኖላቸው እንዲመገቡ ወደቤቱ ወስዶ ፍሪዳ አርዶ ቢያቀርብላቸውም በሃይማኖት
ጠብ አለንና አንበላም አሉት።
በዚህም የተናደደው ዮሐንስ ሃገራቸው ሩቅ መሆኑን አውቆ ማንም አይጠይቀኝም በማለት አስደብድቦ
ጨለማ ቤት ወስጥ እንዲሞቱ ዘጋባቸው። በዚያም ጸሎት ሲያደርጉ ያ ይዘውት የመጡት አፈር እንደልማዱ
በሌሊት የብርሃን አምዱን ተክሎ በመላዋ ከተማዋ ታየ። የግብጹ ሊቀ ጳጳስም ከእርሳቸው ጋር የመጡ
ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ተናግረው ተንኰለኛው ዮሐንስን አንዲያዝ፣ መነኰሳቱ እንዲፈቱ አደረጉ።
የከተማዋ ገዢዎችም ያደረሰባቸውን አይተው ሞት ቢፈርዱበትም የጻድቁ አባታችን መነኰሳት ግን እርሱ
በሞት ፈንታ የሃይማኖት ክርክር ጉባኤ እንዲዘጋጅና ዮሐንስ ቢረታ የእነርሱን እምነት እንዲቀበል ጠይቀው
ሁሉም ተስማማ።
በዚህም ከመነኰሳቱ የደብረ ብሥራት መምህር የነበረ አባ በኃይለ ማርያም ቋንቋ ሳያግደው ባሻቸው ቋንቋ
መከራከር እንደሚችል ተናግሮ የአስቄጥስና የቊስቋም ገዳማት አበምኔቶች፣ የአትሪብ ሃገር፣ የመርያ፣
የግብጽ፣ የአርመን ሊቀ ጳጳሳት፣ የቆጵሮስ፣ የሥሩግ፣ የሶርያ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የአይሁድና የዓረብ አለቆች
ሁሉ በተገኙበት ጉባኤው ተደረገ።
አስቀድሞም ዮሐንስ እንደ ዘመናችን መናፍቃን እመቤታችን ማርያምን አምላክን ወለደች የሚል ጥቅስ
እንደሌለ ነግሮ አባ በኃይለ ማርያምን የአምላክ እናት ለምን እንደሚላት ጠየቀው። አባ በኃይለ ማርያምም
ከኦሪት፣ ከወንጌል፣ ከመጻሕፍተ አበው፣ ከጉባኤያት ቀኖናዎች፣ ከቅዳሴአት እየጠቀሰ በዕብራይስጥና
በዓረብኛ ሰፊ መልስ ሰጠው። ሙሉ መልሱ በገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ እስከ 30 ገጾች ድረስ ወስዶ
ሰፍሯል።
በዚህ ትምህርቱም የተንባላት፣ የአይሁድም ሆነ የዓረብ አለቆች በሙሉ በአቡነ ዜና ማርቆስ አምላክ

18
ምዕራፍ 4. ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸው አስተዋጽዖዎች

እናምናለን አሉ። የአይሁድ እና የተንባላት አለቆችም ያዩትን ተአምራት ሁሉ አጽፈው 150 በወርቅ
የተንቆጠቆጡ የሐር ልብሶችን ጨምረው ወደ ኢትዮጵያ በ60 ፈጣን መልእክተኞች ላኳቸው። በደብረ
ብሥራት የነበረው አባ ቃለ ዐዋዲም በገድሉ መጽሐፍ ጨምሮታል። መነኰሳቱም ከሁለት ዓመታት በኋላ
በሰላም ወደ ደብረ ብሥራት ተመልሰው መልእክተኞቹ አስቀድመው ያመጡት ጽሑፍ ላይ እንዳለው
የሆነውን ሁሉ ለደብሩ መነኰሳት ነገሯቸው።

19
ምዕራፍ 5

የገድላቸው መጽሐፍ

እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በነቢያት፣ በኋላ በሐዋርያት ቀጥሎም በሐዋርያት እግር በተተኩ ቅዱሳን
አባቶች አማካኝነት ”ኑ እንዋቀስ፣ ንስሐ ግቡ” እያለ እኛን ልጆቹን በቀጥታ ሲጠራን ቆይቷል። ገድላትም
እግዚአብሔር ልጆቹን በተዘዋዋሪ ከሚጠራባቸው መንገዶች አንዱ ነው፤ ገድሉን ሰምተው፣ አንብበው
ወደ ንስሐ እና ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ብዙዎች ናቸውና።
ከቤተ ክርስቲያናችን አብዛኛዎቹ ገድላት አጻጻፍ ወጣ ያለ የአጻጻፍ መንገድ የሚከተለው ገድለ አቡነ
ዜና ማርቆስ በብዙ ጸሐፍት እንደተጻፈ ይነገራል። በገድሉ ላይ እንደምናገኘው በመጀመርያ የአቡነ ዜና
ማርቆስ ደቀመዛሙርት አባ አካለ ክርስቶስ፣ አባ ዮሴፍና አባ ገብረመስቀል ያዩትንና ከአቡኑ እኅት
ማርያም ክብራ የነገረቻቸውን አካትተው ጽፈውታል። በኋላም በደብረ ብሥራት በተደረገለት ተአምራት
ዓይኑ የበራው ጸሐፌ መንክራት ዮሐንስ እና በኋላም በአባ ገብረ መርዓዊ አማካኝነት ተጽፏል።
የአቡነ ዜና ማርቆስ የአጽማቸው ፍልሰት በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በተደረገ ጊዜ የሆነውን
በገድላቸው ላይ የጻፉት ደግሞ አባ ገብረ መስቀል፣ አባ እንድርያስ እና አባ ገብረ ሚካኤል ሲሆኑ
በግራኝ አሕመድ ወረራ ጊዜ የደብረ ብሥራት አበምኔት የነበረው አባ ቃለ ዐዋዲ ተአምራቱን በማጠቃለል
ጽፈውታል።
ሌላው ገድሉን እጅግ ለየት የሚያደርገው ነገር ተአምራቱን የጻፉት አባ ቃለ ዐዋዲ ተአምራቱን በሁለት
ከፍለው መጻፋቸው ነው። ቀዳማይ ክፍል የሚለው አቡነ ዜና ማርቆስ በሕይወት እያሉ የተደረጉ
ተአምራትን ሲይዝ ካልዕ ክፍል የሚለው ደግሞ ከዕረፍታቸው ጀምሮ የተደረጉ ተአምራትን መዝግቦ
ይገኛል።
ሌላው አስደናቂ ነገር ገድሉ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለሃገራችን ለኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት የሚጠቅሙ
ልዩ ልዩ መረጃዎችን ይዞ መገኘቱ፤ በጊዜው የነበረውን ጠቅላላ ታሪክ መዝግቦ መገኘቱና ለተለያዩ
ጸሐፍት የታሪክ ምንጭ ሆኖ ማገልገሉ ነው።

ገድለ ዜና ማርቆስ በተደጋጋሚ ሊነበብ፤ ከልዩ ልዩ ነገሮች አንፃር ሊተነተን የሚገባው


ገድል ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገድላት እንዴት ተጻፉ፣ ምንጫቸው ምን ነበር?

20
ምዕራፍ 5. የገድላቸው መጽሐፍ

ማን ጻፋቸው? እንዴት ሊጠበቁ ቻሉ? ከታሪክ ጋር ያላቸው ተዛምዶ? ወዘተን ለመሳሰሉ


የዘመኑ ጥያቄዎች መልስ ከሚሰጡት ገድላት አንዱ ነው። ገድለ ዜና ማርቆስ አንዳንድ
ወገኖች ገድልን በተመለከተ ያላቸውን ደከም ያለ አስተሳሰብ ሊያርምላቸው የሚችልና
ጥናታቸውን ከንቀት ሳይሆን ከአክብሮት እንዲጀምሩ የሚያደርግ ነው።

− ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ከያዛቸው ወሳኝ ኲነቶች መካከል፦

• በጊዜው ከግብጽ ተሹመው የመጡ የግብጽ ሊቃነ ጳጳሳትን ዘርዝሮ ይዟል። በተለይም የአባ
ጌርሎስ፣ አባ ዮሐንስና አባ ማቴዎስ ታሪክን በዝርዝር ያትታል።

• ከአቡነ ዜና ማርቆስ ውጭ የሌሎች አበውንም ታሪክ ይናገራል። ከእነዚህም መካከል የአቡነ ተክለ
ሃይማኖት፣ አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ፣ አባ ሕፃን ሞዓ፣ አባ አኖሬዎስ ታላቁ እና አባ ቀውስጦስ
ዘመሐግልን ታሪክ መዝግቦ ይገኛል።

• እንደ እነ አፄ ይኩኖ አምላክ፣ አፄ አምደ ጽዮን፣ አፄ ሰይፈ አርዕድ እና አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ያሉ


የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክም በስፋት መዝግቦ እናገኛለን።

• የሸዋንና የጉራጌ ሃገረ ስብከትና ክርስትና መስፋፋት የዘግባል

• የሸዋ ገዳማውያን ጎጃም፣ ትግራይ፣ ኤርትራ፣ ግብጽና አንዳንድ ጊዜም ኢየሩሳሌም ያሉ አብያተ
ክርስቲያናትን ለመሳለም የሚያደርጉትን ጉዞ መዝግቦ እናገኛለን።

• የዘመኑን የእስላምና ክርስቲያን ማኅበረሰብ ግኑኙነት ይተርካል

• ስለ ቤተ እስራኤል እና የማኅሌተ ጽጌ አጀማመር

• የተአምረ ማርያም ከአፄ ዘርዐ ያዕቆብ በፊት መጻፉን እና ተያያዥ ታሪኮቹን

• የአሕመድ ግራኝ ዘመቻንና በሸዋ የደረሰውን ጥፋት

• በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት የሰንበት ክርክር አጀማመር

21
ምዕራፍ 6

ገዳሞቻቸው

6.1 ምሑር ኢየሱስ ገዳም


ምሑር ኢየሱስ ገዳም ከአዲስ አበባ ከተማ 200 ኪ.ሜ. ወይንም ከወልቂጤ ወደ ሰባት ቤት መንገድ
55 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኝ ገዳም ነው። ገዳሙ በከምባታ፣ ሃዲያ እና ጉራጌ
ሃገረ ስብከት ውስጥ የሚካተት ሲሆን በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን
በአቡነ ዜና ማርቆስ ተቆርቁሯል።
አስቀድሞ ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሄሮድስ ዘመን የተወደደ ልጇ ጋር በስደት ወደ
ኢትዮጵያ ስትመጣ ካረፈችባቸውና ከባረከቻቸው ቦታዎች ውስጥ አንዱ ነው። በ9ኛው መ/ክ/ዘ ደግሞ
ድብር ተተክሎበት እንደነበርና በኋላ ግን የአካባቢው ሕዝብ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ርቆ ጣዖት ማምለክ
እንደጀመረ ይነገራል።
ጻድቁ አባታችን ዜና ማርቆስ ከበዓታቸው ከገዳመ ደንስ ተነሥተው ወደ ሰባት ቤት ጉራጌ፣ ምሑር
አውራጃ በሄዱ ጊዜ የአካባቢው ሰው ማኮስ የተባለውን ጣዖት ያመልኩ ነበር። ጣዖቱን በአደባባይ
አፍርሰው ወንጌልን ሰብከው ሕዝቡን ወደ አምልኮ እግዚአብሔር ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ሰይጣን
የሕዝቡን ልቦና አደንድኖ፤ ይባሱን አውጊት የተባለው ገዢያቸው አስከፊ ግርፋት አደረሰባቸው።
እርሳቸው ግን ይህንን መከራ በአኮቴት እየተቀበሉ ለ3 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን ሰብከዋል።
በኋላም በወንጌል ይህ ሕዝብ ምልክት ይሻል እንደተባለ ጻድቁ አባታችን ምድሩን ወደ ሰፊ ባሕር ቀይረው
በተአምራቱ ሕዝቡን አሳምነዋል። በቅዱስ ሩፋኤልም ወደ ሃገረ እስክንድርያ ተወስደው ክህነት ከተቀበሉ
12
በኋላ 20,075 ሰዎችን አጥምቀው ተመልሰዋል።
በኋላ ግን ያ በጨለማ ይኖር የነበረ ሕዝብ ብርሃን በርቶለት፣ ጣዖቱ ጠፍቶለት ምሑር ኢየሱስ ገዳም
ተገደመለት። በዚያው እስከ 156 ያህል አብያተ ክርስቲያናት ተተክለውበት ነበር። ከእነዚህም ውስጥ
በእመቤታችን፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በቅዱስ ማርቆስና በቅዱስ ሩፋኤል ስም
12
ዲቁና እና ቅስና የሚለውን ምዕራፍ ተመልከት

22
ምዕራፍ 6. ገዳሞቻቸው

የተተከሉት ተጠቃሾች ናቸው።


በዚህ ሁኔታ እስከ አፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆይቶ ከዚህ በኋላ ክብሩን እያጣ ሲለማም
ሲጠፋም ቆይቷል። በአፄ ምኒልክ ዳግማዊ ደግሞ በገዳሙ መነኩሴ አባ ጥጋቡ ጥያቄ መሠረት ታድሶ
ርስት መሬት እንዲሰጠው ትዕዛዝ ቢሰጡም ባልቻ አባነፍሶ ይህንን ተቃውመው እንዳይሰጠው አድርገው
ነበር። ከዚህም በኋላ ደጃዝማች ባልቻ በጽኑ ደዌ ተይዘው፣ በሕልም ሲሰቃዩ ይቆያሉ፤ ምክንያቱንም
ሲጠይቁ የከለከሉት ርስት እንዲህ ያለ ሕማም እንዳመጣባቸው ሲነገራቸው የራሳቸው የሆነ 100 ጋሻ
መሬት በርስትነት ለገዳሙ ሰጥተው ጤንነታቸውም ተመልሷል። በመሬት ላራሹ አዋጅ ግን ይህንን
ርስታቸውን ተቀምተው የገዳሙ አብዛኛው መነኮሳት የተበተኑ ሲሆን በብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እና
በደቀመዝሙራቸው ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አስተባባሪነት ወደነበረ ክብሩ እንዲመለስ ተደርጓል።

6.2 ደብረ ብሥራት ገዳም


የደብረ ብሥራት ገዳም በሰሜን ሸዋ ሃገረ ስብከት በሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኝ ገዳም ሲሆን...
ግራኝ አሕመድ ወደ ሸዋ እየገፋ በመጣ ጊዜ በጊዜው የገዳሙ አበ ምኔት የነበረው አባ ቃለ ዐዋዲ በገዳሙ
ይገኙ የነበሩ ከ1600 በላይ መጻሕፍትንና 57 ታቦታት ወደ ተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች አዘዋውረዋቸዋል።

• 200 የሚሆኑ መጻሕፍትን ከ16 ታቦታት ጋር ወደ በዚያው በደብረ ብሥራት፣

• 7 የገድላቸውን ቅጂዎችና 1000 የሚደርሱ መጻሕፍትን በምሑር ኢየሱስ ገዳም፣ በጋይ ዋሻ፣
በወተጌ ባለች ዋሻ፣ በእንቡ ልቡልና ዞረት የሚገኝ ዋሻ፣ በሸር ካቢ ዋሻ ደብቀው

• 400 የሚደርሱ መጻሕፍትን ከ1200 ደቀ መዛሙርቱ ጋር እና 547 መነኰሳት ጋር ወደ በጌምድር


ተሰድደዋል።

በገዳሙ የነበሩ 1600 በላይ መጻሕፍት፣ 1200 ተማሪዎች እና 547 መነኰሳት መኖራቸው በጊዜው
ገዳሙ ምን ያህል የሊቃውንት መፍለቂያ እና የገዳማውያን መናኽርያ እንደነበር ይጠቁማል። የገዳሙ
13
ሊቅ አባ በኃይለ ማርያም በሙሉ ልብ በኢየሩሳሌም ስለ ሃይማኖቱ መከራከሩ ገዳሙ የነበረበትን
የመንፈሳዊ ትምህርት ደረጃ ያሳያል። ታቦታቱም በብዛት መገኘታቸው በአካባቢው የነበሩ አብያተ
ክርስቲያናት ታቦታቸውን ከዚሁ ገዳም የሚያገኙ በመሆኑ ነው።
ይህ ታላቅ ገዳም ግን ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ የአካባቢው ተወላጆች የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ከገዳሙ
መነኮሳት ጋር ባደረሳቸው ግጭት የገዳሙ ይዞታ የነበሩ መሬቶች እየተወረሱ ይገኛሉ። እንዲያውም በኅዳር
ወር፣ 2006 ዓ.ም. እስከ 80 የሚደርሱ መነኮሳት፣ አበ ምኔቱን ጨምሮ ተበትነው በድነባ ቅድስት
በኣታ ለማርያም ገዳም ለመጠለል ተገድደው ነበር። እስከ 16ኛው መ/ክ/ዘ የሊቃውንት መፍለቂያና
13
ማጣቀሻ

23
ምዕራፍ 6. ገዳሞቻቸው

የመናንያን መናኸርያ የነበረው ይህ ታላቅ ገዳም ዛሬ እንዲህ ያለ አሳሳቢ አደጋ የተጋረጠበት በመሆኑ
የመላውን የቤተ ክርስቲያናችን ትኩረት ይሻል።

24
ሥዕለ አድኅኖአቸው

በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችን መሠረት የጻድቁ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ ሥዕለ አድኅኖ የምሑር ሃገረ
ገዢ በጦር ሲወጋቸውና ከተወጉበት ብርሃን ሲወጣ ተደርጎ ይሳላል። ሥዕሉም በደብረ ብሥራት ገዳም
ይገኛል።

የጻድቁ አባታችን ዜና ማርቆስ በረከት፣ ረድኤት ይደርብን


ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር

25
ማጣቀሻዎች

[1] ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ፤ ደብረ ብሥራት አቡነ ዜና ማርቆስ አንድነት ገዳም፣ ሳቤላ ማተሚያ፣
2005 ዓ.ም.

[2] ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ አራቱ ኃያላን፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሜጋ ማተሚያ፣ 2006 ዓ.ም.

[3] ገድለ ተክለ ሃይማኖት፤ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ 2004 ዓ.ም.

[4] ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ ገድለ ዜና ማርቆስ የያዛቸው መረጃዎችና ሁነቶች፤ የኢትዮጵያ ፊሎሎጂ
ማኅበር ባዘጋጀው 3ኛ ዓመታዊ ዐውደ ጥናት ላይ የቀረበ፣ 2001 ዓ.ም.

[5] አበበ ጋሻዬ ፈንታ፤ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ 2009
ዓ.ም.

[6] ሐመር ዘኦርቶዶስ ተዋሕዶ፣ 5ኛ ዓመት ቁጥር 5፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ 1990 ዓ.ም.

[7] መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ድርሳነ ኤልያስ ነቢይ፤ 2005 ዓ.ም.

[8] ገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ ንባብና ትርጓሜ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣
በቀበና ምስራቀ ፀሐይ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፤
https://www.youtube.com/watch?v=_ExXx8qZYVk፤ [ተንቀሳቃሽ ምስል] ነሐሴ፣ 2005
ዓ.ም. የተሰቀለ

[9] አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ጥር 24፣ 2006 ዓ.ም.

26

You might also like