You are on page 1of 15

ነገረ ቤተ ክርስቲያን

ምዕራፍ አንድ ቤተ ክርስቲያን

1.1 የቤተ ክርስቲያን ትርጉም

ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስም መነሻ ቃሉ ግእዝ ሲሆን “ቤተ” እና ክርስቲያን የሚል ሲሆን “ቤተ” ማለት አደረ፣
ወገን፣ ነገድ፣ ዘር፣ ጉባኤ፣ ማኅበር፣ ቤተሰብ ማለት ነው። ይህም በግሪክ አቅሌስያ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ቤት የሚለው ቃል ወገን፤ ነገድ፤ ዘር፤ ትውልድ፤ ጉባኤ፤ ማኅበር ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ
ቃላት መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ማደሪያ፣ የክርስቲያን ወገን፣
ነገድ፣ ዘር፣ የክርስቲያን ጉባኤ፣ ማኅበር፣ ቤተሰብ ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን በግእዝ ቋንቋ ዘይቤና ምሥጢር
ሦስት ዓይነት ትርጉም አለው። የመጀመሪያው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን፣ ሁለተኛው እያንዳንዱ ክርስቲያን እና
ሦስተኛው የክርስቲያኖች ኅብረት/ጉባኤ ማለት ነው።

ሀ. ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን

“ቤተ” ና “ክርስቲያን” አንድ ላይ ሲሆን የክርስቲያኖች ማደሪያ፣ የክርስቲያኖች ቤት የሚለው ትርጉም በመስጠት
ቤቱን መሰብሰቢያውን ሕንፃውን ያመለክታል። ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ስለ በደላቸው ምሕረት
ለመለመን፣ ሕይወት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት፣ በተለይም ደግሞ ለኃጢአት ሥርየት የተሠዋውን
የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመቀበል የሚሰበሰቡበት ቤት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል። ከጌታ ትንሣኤ በኋላ ደቀ
መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም ከተማ የማርቆስን እናት የማርያምን ቤት እንደ ቤተ ክርስቲያን ይጠቀሙበት ነበር።
የመጀመሪያው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የተሠራችው በፊልጵስዩስ ከተማ ነው። አሁን ላይ በዓለም ሁሉ ታንፃ
ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ሥርዓትና አገልግሎት ይገለገሉበታል። በሀገራችን ኢትዮጵያም እጅግ አስደናቂ ሕንፃ አብያተ
ክርስቲያናት ታንፀው ምእመናን በያሉበት ሁሉ መንፈሳዊ ሥርዓት ያደርሱበታል። ስለዚህ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን
የመጀመሪያው የቤተክርስቲያን ትርጉም ነው።

ለ. እያንዳንዱ ክርስቲያን

በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል እያንዳንዱ ክርስቲያን ያመለክታል። ይህም “ቤተ” ማለት ወገንን
የሚያመለክት በሚሆንበት ጊዜ ነው። ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ ሌዊ፣ ቤተ እሥራኤል ወዘተ… እንደሚባለው ሁሉ
የክርስቶስ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ተብለው ይጠራሉ። በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን
ስጦታን ስለሚያገኙ የተቀደሱና የከበሩ ናቸው፦ ዳግም ኃጢአትን ሠርተው ራሳቸውን እስካላሳደፉ ድረስ (ይህም
ቢሆን በንስሐ በተመለሱ ጊዜ ይነዳሉ/ይታደሳሉ)። የክርስቶስ ማደሪያው ናቸውና ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ።

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 1


ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን፦ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም
መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን
ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ” ያለው። 1ኛ ቆሮ 3፡16-17

ሐ. የክርስቲያኖች ኅብረት/ አንድነት

ሦስተኛውና የመጨረሻው ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፣ አንድነት ወይም ጉባኤ ማለት
ነው። በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ቃል ተደጋግሞ ተጽፎ እናገኛለን። በአብዛኛውም የሚያመለክተው የክርስቲያኖች
ማኅበር ነው። ለምሳሌ ጌታ ስለ ይቅርታ ሲያስተምር “ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ
ውቀሰው… ባይሰማህ ግን አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፣ እነርሱንም ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፣
ደግሞም ቤተ ክርስቲያን ባይሰማት እንኳ እንደ አረመኔና ቀራጭ ይሁንልህ” በማለት ገልጿል። ማቴ 18፡15-17
እንደዚሁም ቅዱስ ጴጥሮስ “ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ
ያቀርቡላችኋል” በማለት ባስተላለፈው መልእክት ላይ የገለጸው በባቢሎን ያለችውን የክርስቲያኖች ማኅበር ወይም
ጉባኤ የሚያመለክት ነው። 2ተኛ ጴጥ 4፡13 በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ሲባል ከላይ እንደተገለጸው ሕንፃ ቤተ
ክርስቲያን ወይም እያንዳንዱ ክርስቲያን ወይም የክርስቲያኖች ኅብረት ማለት ስለሆነ እንደየአገባባቸው መረዳት
ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሲባል ሕንፃውን ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን ወይም በአእምሯችን ቶሎ
የሚመጣው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው።

1.2 የቤተ ክርስቲያን ስያሜ

በግእዝ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ የተተረጎመው በጽርዑ ኤክሌስያ ከሚለው ቃል ጋር አንድነት አለው። ፍቺውም
“የተጠሩ ወይም የምርጦች ሸንጎ” ማለት ሲሆን የኅሩያነ (የተመረጡ) እግዚአብሔር ጉባኤ ማለት ነው። ስለዚህ
የጉባኤው አባላት ያመለክታል ማለት ነው። በግእዙ ቤተ ክርስቲያን ሲል የክርስቲያኖች ወገን ማለት ስለሆነ
የኤክሌስያን ምሥጢራው ትርጉም ይዟል ማለት ነው። በሐዲስ ኪዳን “ቤተ ክርስቲያን” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ
ጊዜ የተጠቀመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በማቴ 16፡18 እንዲህ ይላል፦ “እኔም እልሃለሁ፥
አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” እንዲሁም
ማቴ 18፡15-17 “ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን
ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም
ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥
እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ የተጠቀመውና የሰጠን ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምእመናን (ደቀመዛሙርት)ም ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን የተባሉት በአንጾኪያ
ሲሆን ትርጉሙሙ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር (ተከታይ) ማለት ነው። “… ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ
ክርስቲያን ተባሉ” እንደተባለ። የሐ ሥራ 11፡26

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 2


1.3 ቤተ ክርስቲያን በዓለመ መላእክት

እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፦ ሀልዎተ እግዚአብሔር የሚያምኑ፣ በፍቅርና አንድነት ስብሐት
እግዚአብሔር የሚያደርሱ ግዕዛን ያላቸው ፍጥረታት አንድነት (ኅብረት) ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዚህም
የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፥ አንደኛዋና የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው
ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል
ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ደግሞ
በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡

በሥነ ፍጥረት ትምህርት እንደምንማረው መላእክት እግዚአብሔር ሰማይን በፈጠረበት ዕለት፣ በዕለተ እሁድ
የተፈጠሩና በሰማያት እግዚአብሔርን ዘወትር ያለ ማቋረጥ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ በአንድነት የሚያመሰግኑ
ረቂቃን መንፈሳውያን ፍጥረታት ናቸው። በአምልኮት፣ በስብሐተ እግዚአብሔርና በመሳሰለው ሁሉ አንድ
በመሆናቸው ይህ አንድነታቸው (ኅብረታቸው) ቤተክርስቲያን ይባላል።

ከመላእክት አለቆች ወገን የነበረው ሳጥናኤል ከአምልኮተ እግዚአብሔር በተናወጸበት፣ ጥርጥርና ክህደትን ባመነጨበት
ጊዜ ከመላእክት አንድነት (ከቤተ ክርስቲያን) ተለየ፤ በክህደት የተባበሩት መላእክትም እንዲሁ ንጽሕት ከሆነችው
ከመላእክት ማኅበር አብረውት ተለዩ። ከዚያን ጊዜ በኋላም ርኩሳን መናፍስት (ሰይጣናት) ተብለው በመጠራት
ከክብራቸው ተዋርደው ወደ ምድረ ፋይድ ወረዱ። እስከ ዓለም ፍጻሜም ድረስ የክፋት ምንጭ በመሆንና ሰውን
አሳስተው ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዲለይ ለማድረግ በመውጣትና በመውረድ ይኖራሉ። ያልካዱትና የጸኑት
ከቅዱስ ገብርኤል ጋር “ባለንበት እንጽና” ያሉት ቅዱሳን መላእክት ይባላሉ። ስለዚህ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን
(የቅዱሳን መላእክት ኅብረት) የተገለጠችው በዓለመ መላእክት የሰው ዘር ሳይፈጠር በነበረው ዘመን ነው። በመሆኑም
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው መላእክት ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

1.4 ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን

በዚህ ንኡስ ርእስ ብሉይ ኪዳን ሲባል ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መወለድ ያለውን ዘመን ነው።
እግዚአብሔር አምላክ ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ በተለየ ሁኔታ የሰውን ልጅ በራሱ አርአያና ምሳሌ አድርጎ በመፍጠር
ከባረከው በኋላ ለቀሩት ፍጥረታት የበላይ ገዢ እንዲሆን ሾመው፤ ሰው በተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ክፉና ደጉን
የሚለይበት ሙሉ አእምሮ ያለው ሲሆን ፈጣሪውን ከሚያስታውስባት አንዲት ትእዛዝ ተሰጥታው ነበር። ይኸውም
“ከዐፀ በለስ እንዳትበላ” የሚል ነው። ነገር ግን አዳም ከሚወደው ከእግዚአብሔር ይልቅ የሚያሳስተውን የእባብ ምክር
ሰምቶ ዕፀ በለስን በመብላት ሞትን መረጠ። ከእግዚአብሔር የተሰጠው የልጅነት ጸጋ በማጣቱም ከክብሩ ተዋርዶ፣
ከገነት ወጥቶ በነፍሱ በሲዖል እንዲቀጣ እስከዚያውም ድረስ ወደ ምድረ ፋይድ ወርዶ ጥሮ ግሮ በወዙ ይበላ ዘንድ
ተፈረደበት። ይህንን ቅጣት ከርሱ የተወለዱ ልጆችና የልጅ ልጆቹ ሁሉ በውርስ ተካፈሉት፣ የሰው ልጆችም ኃጢአት
እየጨመረ በመሄዱ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች የነበረው ግንኙነት እየደከመ ሄደ። ነገር ግን አዳም ንስሐ በመግባቱ
እግዚአብሔር የገባለት ቃል ኪዳን በማሰብ የሰው ዘር ፈጽሞ እንዳይጠፋ በየወቅቱ ለበረከት የሚሆኑ አንዳንድ
ሰዎችን አተረፈ። ከአዳም እስከ ኖኅ ባለው ዐሥር (10) ትውልድ ውስጥ ሰባተኛው ትውልድ ወይም ሄኖክ አካሄዱን
ከእግዚአብሔር ጋር በማድረጉ ሲዖልን እንዳያይ ሳይሞት ተሰወረ።

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 3


ከኖኅ ዘመን በኋላ እንዲሁ በሴም በኩል ዐሥር ትውልድ ቆጥረን አብረሃምን እናገኛለን። አብረሃም በፍጹም ልቦናው
እግዚአብሔርን በማምለኩ ከዘመዶቹ እንዲለይና ወደ ማያውቀው ሀገር እንዲሄድ በእግዚአብሔር ተጠራ። አብረሃምም
ሳያቅማማ በእምነት የታዘዘውን በመፈጸሙ እግዚአብሔር ማርና ወተት የምታፈልቀውን ምድረ ከነዓንን ከእርሱ
በኋላ የልጅ ልጆቹ ሁሉ ይወርሷት ዘንድ ሰጠው።

ይስሐቅና ያዕቆብም የአባታቸውን የአብረሃምን ፈለግ በመከተላቸው እግዚአብሔር ባረካቸው። እንዲህ እንዲህ እያለ
ከአዳም እስከ ክርስቶስ ልደት በየትውልዱ ደጋግ አባቶች እየተነሱ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር እያደረጉ
በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረውን ግንኙነት ፈጽሞ እንዳይጠፋ አድርገውታል። አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያንም
በብዙ ምሳሌ ለእነዚህ ደጋግ አባቶች ትገለጥ ነበር።

1.5 ቤተ ክርስቲያን በሐዲስ ኪዳን (አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን)

እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተዋጅታና አማናዊት ሆና እስክትገለጥ ድረስ በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት
ዘመን ብዙ ምሳሌዎች ነበሯት፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የሰውን ልጅ ወደቀደመ
ክብሩ ይመልሰው ዘንድ መከራ መስቀልን በፈቃዱ ተቀበለ። በመስቀል ላይ ሆኖ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር
በላቸው” በማለት እርቅን አወጀ፤ በዚሁ ዕለት ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሐዲስ ኪዳንን ሠራልን። በሞቱም
የሞትን ኃይል ሽሮ ለሰው ልጆች ሁሉ ዘለዓለማዊ ክብርን አደለን። አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ሁኔታ
ተሠራች። በምን መሠረት ላይ እንደተሠራችም ሲያመለክት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል “… አንተ
ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለው፣ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም።” በመሆኑም
ማናዊቷን ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ሁኔታ በዕለተ ዓርብ በደሙ መሠረታት። ማቴ 16፡18፤ ሐዋ. ሥራ 20፡22
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት (ማለትም ቅ.
ጴጥሮስ በመሰከረው እምነት) ላይ ነው። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ደቀመዛሙርትም
ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያን የተባሉት በአንጾኪያ ነው።

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 4


ምዕራፍ ሁለት የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎችና ቅጽል ስሞች

2.1 የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች

እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን እንደ እንግዳ ደራሽ በድንገት የተቋቋመች አይደለችም፡፡ ይህች አውነተኛይቱ ቤተ
ክርስቲያን እንደ ወሃ ደራሽ በድንገት የደረሰችም አይደችም፡፡ አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን እንደ ወፍ ዘራሽ በድንገት
የተመሠረተችም አይደለችም፡፡ ዓለም ከተፈጠረበት ዘመን ከተቆጠረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምሳሌዎች እተመሰለች
(በምሳሌዎች እየተገለጸች) በጥላ ውስጥ የነበረችና የኖረች ናት እንጂ፡፡

የክርስቶስ ሐዋርያት ክርስቲያን ተብለው (ሐዋ 11፡26)፣ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያንም በክርስቶስ ደም ተዋጅታና
(ሐዋ 23፡20) አማናዊት ሆና እስክትገለጥ ድረስ በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት ዘመን ብዙ ምሳሌዎች ነበሯት፡፡ እነዚህ
ምሳሌዎች ለእውነኛይቱ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንጂ ለሌሎች ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ብለው ለሰየሙት
ድርጅቶች አይደሉም፡፡

2.1.1 የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች በብሉይ ኪዳን

ሀ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በኖኅ መርከብ ትመሰላለች (ዘፍ 7፡1)

በማየ አይህ /በጥፋት ውሃ/ ጊዜ ነፍሳት ከሞተ ሥጋ የዳኑባት ያቺ የኖኅ መርከብ የእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን
ምሳሌ ናት፡፡ ምሳሌነቷም እንደሚከተለው ነው፡፡ ያቺ የኖኅ መርከብ ሦስት ክፍል ነበራት፡፡ ቤተ ክርቲያንም ቅድስት
፣ መቅደስ፣ ቅኔ ማኅሌት የሚባሉ ሦስት ክፍሎች አሏት፡፡ የኖኅ መርከብ በውስጧ የነበሩት ነፍሳት ሁሉ ከጥፋት
ውሃ ድነዋል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም በክርስቶስ አምነው ተጠምቀው ሥጋ ወደሙን የተቀበሉ ከሞተ ነፍስ ይድናሉ፡፡
በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን በኖኅ መርከብ ስትመሰል ዓለም ደግሞ በጥፋት ውኃው ትመሰላለች፡፡ በቤተ
ክርስቲያን በጥምቀት ገብተው እንደ ሕጉና ሥርዓቱ የሚኖሩ ሲድኑ እምቢ ብለው በዓለም የቀሩት ደግሞ በኃጥአት
ምክንያት (በጥፋት ውኃ) ይጠፋሉና ምሳሌው ገላጭ ነው፡፡

ለ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች (ዘፍ 18፡1)

አብርሃም ሥላሴን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለባት ያቺ የአብርሁም ድንኳን (ኀይመተ አብርሃም) የእውነተኛይቱ
ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡

አብርሃም ሥላሴን በእንግድነት በቤቱ ድንኳን ስር እንደተገኙ በቤተ ክርስቲያን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያድራሉ፡፡
በአብርሃም ድንኳን ውስጥ አብርሃም ምሥጢረ ሥላሴን እንደተማረ በቤተ ክርስቲያንም ምሥጢረ ሥላሴ
ይነገራልና፡፡
በአብርሃም ድንኳን ድሀ ሀብታም፣ ነጭ ጥቁር፣ የተማረ ያልተማረ፣ ኃጥእ ጻድቅ ሳትል እንግዳ እንደተቀበለች ቤተ
ክርስቲያንም ያለ አድሎ ሁሉን በእኩል አይን ትቀበላለች፡፡ በአብርሃም ድንኳን ምግበ ሥጋ ይመገቡባት እንደነበር
በቤተ ክርስቲያንም ሥጋ ወደሙና ቃለ እግዚአብሔር እንመገባለን፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ቤተ ክርስቲያን
በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 5


ሐ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በያዕቆብ ሐውልት ትመሰላለች (ዘፍ 35፡13-15)

“… ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም


በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል
ብሎ ጠራው።›› ዘፍ 35፡9-15

ቤቴል ማለት የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ያቺ ሀውልት እግዚአብሔር ከያዕቆብ ጋር የተነጋገረባት ስፍራ
የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ለያዕቆብ ተገለፀለት፡፡ በቤተ ክርስቲያንም አምኖ ለቀረበ
እግዚአብሔር በረድኤት ይገለፅለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር ያዕቆብን ባርኮታል፡፡ በቤተ ክርቲያንም ተግቶ የጸለየ
እግዚአብሔር በረከትን ያበዛለታል፡፡ በቤቴል እግዚአብሔር የያዕቆብን ስም ለውጦ እስራኤል ብሎታል፡፡ ሰውም ወደ
ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ አዲስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ተቀብሎ አዲስ ማንነትን (ክርስትናን) ይዞ በአዲስ ስም
(በክርስትና ስም) ይጠራል፡፡ እግዚአብሔር በቤቴል ያደረገው ሁሉ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ለሚደረገው ምሳሌ ነው፡፡

መ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ሲና ትመሰላለች (ዘፀ 34፡1)

ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት
/ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ክርስቲያኖች በጾምና በጸሎት ተግተው ሲጸልዩ
ሰማያዊ ክብርን (ቃል ኪዳንን) ያገኛሉና ቤተ ክርስቲያን በሲና ተራራ ተመስላለች፡፡ በደብረ ሲና ሙሴ ከእግዚአብሔር
ጋር ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ በቤተ ክርስቲያንም በጾምና በጸሎት የተጉ አባቶች ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራሉና
ምሳሌነቱ ትክክለኛና ተገቢም ነው፡፡ ሙሴ ከደብረ ሲና ተራራ ሲወርድ ፊቱ እያበራ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያን የኖረ
ሰው ከዚህ ዓለም ተለይቶ ሲሄድ በመላእክት ታጅቦ እንደዚህ እያበራ ነውና ምሳሌነቱ ጽኑዕ ነው፡፡

ሠ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በደብተራ ኦሪት ትመሰላለች (ዘፀ 40፡1)

‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ


ትተክላለህ። በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ። ገበታውንም አግብተህ
በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ። ለዕጣንም የሚሆነውን
የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ። ለሚቃጠል
መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ።›› ዘፀ 40፡1-6 ይህች
በብሉይ ኪዳን የነበረች ደብተራ ኦሪት ምሳሌነቷ በሐዲስ ኪዳን ላለችው አማናዊት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ረ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን በሰሎሞን ቤተመቅደስ ትመሰላለች (1ኛ ነገ 9፡1)

‹‹ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥
እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው፡- በፊቴ የጸለይኸውን
ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና
ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ።›› 1ኛ ነገ 9፡1-8

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 6


ይህችም ቤተ መቅደስ ለአማናዊቷ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን
የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ›› እንዳለ በዚያች ቤተመቅድስ
እግዚአብሔርና ሰው ተገናኝተዋልና የአማናዊት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በዚህች ቤተመቅደስም ክርስቶስ ተገኝቶ
ባርኮ ከወንበዴዎች አፅድቶ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ያለው የአማናዊት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ስለሆነች ነው፡፡

2.1.2 የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች በሐዲስ ኪዳን

ሀ. እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ደብረ ታቦር (የታቦር ተራራ) ትመሰላለች

በአዲስ ኪዳን ከተገለጹት የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች መካከል አንዱ ደብረ ታቦር (የታቦር ተራራ) ነው፡፡ ‹‹ከስድስት
ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው።
በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ
ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።” ማቴ 17፡1-8

በአባቶች አስተምህሮ የታቦር ተራራ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› የሚለው ምሳሌው ቤተ
ክርስቲያን በስድስተኛው ሺህ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደምትመሠረት የሚያሳይ ነው፡፡ በደብረ ታቦር ሦስቱን
ደቀመዛሙርት ብቻ ይዞ መውጣቱ ምሥጢረ ክህነት ለሁሉም ሳይሆን ለካህናት ብቻ የሚፈፀም ምሥጢር መሆኑን
ለማሳየት ነው፡፡ ብርሃነ መለኮቱንም የገለፀላቸው ለእነዚህ ብቻ ነበር፡፡

በደብረ ታቦር ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ገለጸ፡፡ በቤተ ክርስቲያንም እንደዚሁ የክርስቶስ ማደሪያው ናት፡፡ በደብረ
ታቦር ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን ሙሴ ከብሔረ ሙታን ሐዋርያቱ ደግሞ በአካለ ሥጋ ያሉት በአንድነት ከአምላካቸው
ጋር ተገኝተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንና በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖች ከአምላካቸው ጋር
ያላቸው አንድነት ናትና የደብረ ታቦር ምሳሌ ጠንካራ መሠረት ያለው ነው፡፡

ለ. ተጨማሪ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ በኢየሩሳሌም ምድር በእግሩ ተመላልሶ ወደ መንግሥተ
ሰመያት መርታ የምታስገባ ሕገ ወንጌልን በአምላካዊ ቃሉ አስተምሯል። ጌታችን ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ
ስለ ቤተ ክርስቲያን በምሳሌነት የሚጠቀሱት ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

1. የዓሣ ማጥመጃ መረብ (ማቴ 13፡47)


2. ታላቅ የስንዴ አዝመራ (ማቴ 13፡24)
3. የሰናፍጭ ቅንጣት (ማቴ 13፡31)
4. የከበረ ዕንቁ (ማቴ 13፡45)
5. የሠርግ ቤት (ማቴ 22፡1-3)
6. ሙሽራ (ኤፌ 5፡21-33 እና ራእ 21፡9-14)

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 7


2.3 የቤተ ክርስቲያን መጠሪያዎች (ቅጽል ስሞች)

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንን በተለያዩ ስያሜዎች በተለያዩ ዘመናት ሲገልጿት ኖረዋል፡፡ እነዚህ
ሊቃውንት ያስቀመጧቸው የቤተ ክርስቲያን ስያሜዎች በመጻሕፍት የተገለፀውን እውነትና በትውፊት የተቀበሉትን
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በማድረግ የተሰጡ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ዓላማቸውም የቤተ ክርስቲያኒቱን ምንነታና
ማንነት በአጭር ቃላት በገላጭ ቋንቋ ለማስተማርና ለማስረዳት ነው፡፡ እነዚህም ስያሜዎች ከትውልድ ትውልድ
በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሲተላለፉ ቆይተው ከእኛ ዘመን ደርሰዋል፡፡

አንዳንድ ወገኖች እነዚህ ስያሜዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ አይደሉም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን
ስያሜዎች ያስቀመጡልን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ የተማሩ፣ የክርስቶስን ወንጌል
በጥልቀት ያወቁ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንም የጠነቀቁ፣ ከማወቅም በላይ በሕይወታቸው የኖሩ ናቸው፡፡
ያስቀመጡልን ስያሜዎችም መጽሀፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔርን
ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።››
እንዳለ እኛ እነርሱን አብነት አድርገን የምንኖር ክርስቲያኖች እነርስ ያስቀመጧቸውን ስያሜዎች ተጠቅመን ስለ
ቤተክርስቲያን እናስተምራለን፡፡

ሀ. የክርስቶስ ሙሽራ

እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የዓለምን ኃጢአት በቤዛነቱ ያስወገደ የእግዚአብሔር በግ፣ በተዋህዶ የከበረ ወልደ አብ፣
ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ ትባላለች፡፡ ይህም በቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅና በጥልቀት የተቀመጠ
ነው፡፡«ሙሽራ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ድምፁን ለመስማት አጠገቡ የሚቆሙ ሚዜ ግን የሙሽራውን ድምፅ
ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፡፡ እርሱም አሁን ተፈጽሟል፡፡ እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ላንስ ይገባል፡፡»/ዮሐ
3. / ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በሙሽራ በሙሽሪት እና በሚዜ መስሎ የተናገረው የክርስቶስን፣ የቤተ ክርስቲያንን
እና እንደ ራሱ ያሉ አገልጋዮችን ነገር ነው፡፡ በክርስቶስ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት በሙሽራ
እና በሙሽሪት /በባል እና በሚስት/ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር የሚያመሳስሉት በርካታ ነገሮች አሉ፡፡

ሙሽሪትን /ሚስቱን/ የሚመርጣት፣ የሚያጫት ሙሽራው /ባል/ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንንም የመረጣትና ሙሽራው
እንድትሆን ያደረጋት ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ባል ሚስቱን መጠበቅ፣ መንከባከብ ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ
መውደድ ይጠበቅበታል፤ ክርስቶስም ስለ ቤተክርስቲያን ይህንን አድርጓል፡፡ ሚስት ራሷን ለባሏ ራሷን ማስገዛት
አለባት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ለክርስቶስ እንዲሁ ማድረግ አለባት፡፡ ሙሽሪት በሰርጓ ቀን ራሷን አስውባ ትቀርባለች፤
ክርስቶስም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ራሱ ያቀረባት ሙሽራው ያደረጋት በሥጋውና በደሙ አንጽቶ፤ ነውሯን አስወግዶና
አስውቦ ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ በሁለተኛው የቆሮንቶስ መልእክቱ «እናንተ እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ
ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ» /11-2/ ብሎ ጽፏል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ነባቤ መለኮትም በራእይ መጽሐፉ
ሰማያዊት ቤተ ክርስቲያን የሆነች አዲሲቷን ኢየሩሳሌምን የበጉ ሙሽራ ይላታል፡፡ «ቅድሰቲቱ ከተማ አዲሲቱ
ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» /21-1-9/፡፡

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 8


ከዚህም አንፃር ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ እንደሆነች አባቶቻችን ያስተማሩት በምድር የምናያት ቤተ
ክርስቲያን በሰማይ ያለችው የቅድስት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ነው፡፡

ለ. ስንዱ እመቤት

ቤተ ክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት በመሆኗ መንፈሳዊ ምስጢርን፣ ታሪክንና ትውፊትን በማስተባበር ልዩና እንደ
እንቁ የሚያበራ ሥርዓትን ሠርታለች፡፡ በረከት ያለበት የትምህርት ቤት ገበታ፣ ከነፍስ የሚያጣምር፣ በጥቂት ጊዚያዊ
መቸገር ውስጥ የብዙ ዘመን ሀብታም የሚያደርግ፣ ከራስ አልፎ ትውልድ የሚታነጽበት፣ ዘመንን
የሚሻገር/የሚያሻግር ይሄ ይቀረዋል የማይባል የሊቃውንት ዐውድማ የሆኑ አብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም
ስንዱ እመቤትነቷን ታሳያለች፡፡ እነዚህ አብነት ትምህርት ቤቶች ቅዱሳን ኒቢያትና ሐዋርያት የሰበኩትን የጌታችንን
ቅዱስ ቃል ከነትርጓሜው ሳይፋለስና ሳይዛነፍ በዘመናት መካከል እንዲሻገር በማድረግ ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር
ቅዱስ ቃል አጋዥነት የዓለምን ፈተና፣ የመናፍቃንን ክህደት እያሸነፈች እስከ ምጽዓተ ክርስቶስ ድረስ እንድትቆይ
ያግዟታልን።

ሐ. የጸጋው ግምጃ ቤት

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ የጸጋው ግምጃ ቤት ናት፡፡ ይህም የክርስቶስ ጸጋ በሰፊው የሚገኝባትና የሚታደልባት ናት
ለማለት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት ያመኑ፣ ቅዱሣት መጻሕፍትን በተግባር የሚኖሩ ምዕመናንና
ምዕመናት የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ ያለመከልከል የሚቀበሉበት ዘመን ነው፡፡ ከጸጋ ስጦታዎች ዋና ዋናዎቹ
በጥምቀት ከእግዚአብሔር በጸጋ መወለድ፣ በቅብዓ ሜሮን ልጅነትን ማጽናት፣ የክርስቶስ ቅዱስ ስጋና ክቡር ደም
በንስሓ በተዘጋጀ ልቦና ቀርቦ በመቀበል ከክርስቶስ ህያውነት የተነሳ ለዘለዓለም ህያው ሆኖ መኖር ናቸው፡፡ እነዚህ
ሁሉ ጸጋዎች በእምነት ለቀረቡ ሰዎች የሚታደሉት በቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
የጸጋ ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር የጸጋው ግምጃ ቤት ትባላለች፡፡

መ. አካለ ክርስቶስ

ቤተ ክርስቲያን አካለ ክርስቶስ (የክርስቶስ አካል) ትባላለች፡፡ ለምን የክርስቶስ አካል ተባለች ቢባል ይህ በቅዱሳት
መጻሕፍት የተረጋገጠ እውነት ስለሆነ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ
እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ። እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም
ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥
አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።›› ብሎ እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቲያኖችም ኅብረት
የክርስቶስ አካል

ሠ. ባህረ ጥበባት

ባሕረ ጥበባትና ስንዱ እመቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልዩ ከሚያደርጓት ነገሮች
መካከል አንዱ የሒሳብ ስሌት ሰርታ የዘመን መቁጠሪያ ሳይንስን (ባሕረ ሐሳብን) ቀምራ አበቅቴና መጥቅን ለይታ
የአጿማትና የበዓላትን ዕለታት ወስና ለትውልድ ማስተለለፏ ነው፡፡ በመሆኑ ዘወትር በየዓመቱ ሰባቱን የአዋጅ
አጽዋማት ታውጃለች፣

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 9


አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያንን ባለማወቅ ኋላ ቀር አድርገው ቢስሏትም ቤተክርስቲያን ግን የጥበብ ማዕከል ናት፡፡

ረ. መዝገበ ምሥጢር

እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የማትመረመርና ጥልቅ የሆነች ‹‹መዝገበ ምሥጢር›› ትባላለች፡፡ ይህም የምሥጢር
መዝገብ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንብበው የማይጨርስዋት የምሥጢር መዝገብ ናት፡፡ የሰማዩ አምላክ
ምሥጢር የሚነገርባት፣ የድኅነት ምሥጢር የሚከናወንባት ስለሆነች መዝገበ ምሥጢር ትባላለች፡፡ ለዚህም የእምነት
መሠረት በሆኑት አምስቱ አዕማደ ምሥጢር (ምሥጢረ ሥላሴ፡ ምሥጢረ ሥጋዌ፡ ምሥጢረ ጥምቀት፡ ምሥጢረ
ቁርባንና ምሥጢረ ትንሳኤ ሙታን) የጸናች ናትና የምሥጢር መዝገብ መባሏ ተገቢ የሆነ ስያሜ ነው፡፡

ሰ. የድሆች መጠጊያ

በቃል ብቻ ያይደለ በተግባር በተገለጠ እውነት እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡ በዚህ ረገድ
ድህነት ብዙ ዘርፍ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለማስረጃ ያህል ግን የሚከተሉትን እንመልከት፡፡

የእውቀት ድህነት፡- መንፈሳዊ እውቀትን የተራቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ቃለ እግዚአብሔርን ተምረው


ከድህነት ይወጣሉና ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡

የምግባር ድህነት፡- መልካም ምግባርን የናፈቁና በኃጢአት የተዘፈቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ከእስዋ
ተጠግተውና ንስሐ ገብተው ከኃጢአታቸውና ከምግባር ድህነት ይላቀቃሉና ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡

የመንፈስ ድህነት፡- ያላቸውን ትተው ራሳቸውን በመንፈስ ድሀ ያደረጉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ሆነው ‹‹በመንፈስ
ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።›› እንደተባለ መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉና
ቤተ ክርስቲያን የድሆች መጠጊያ ናት፡፡

ሥጋዊ ድህነት፡- በዚች ምድር ላይ ሲኖሩ ምግበ ሥጋን የተራቡ፣ ቀዝቃዛ ውኃ አጥተው የተጠሙ፣ እራፊ ጨርቅ
አጥተው የታረዙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው ጊዜያዊና ዘላቂ ድጋፍ ያገኛሉና ቤተ ክርስቲያን የድሆች
መጠጊያ ናት፡፡

ሸ. ተጋዳይዋና ድል አድራጊዋ

ቤተ ክርስቲያን ስንል የዚህ ዓለም ተጋድሏቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ እግዚአብሔር የሄዱ ቅዱሳን (ሐዋርያት፣
ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣ …) እና ገና በዚህ ዓለም በተጋድሎ ላይ ያሉት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት፡፡ በሰማይ
ያለችው ቤተ ክርስቲያን (ጉባኤ) የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ጨርሰው የሄዱ፣ ድል አድርገው የድል አክሊላቸውን
ለመቀበል እርሱ የወሰነውን ጊዜ የሚጠባበቁ ቅዱሳን ኅብረት ስለሆነች አትናወጽም፤ ስለሆነም ሊቃውንት ይህችን
ቤተ ክርስቲያን ድል አድራጊዋ ቤተክርስቲያን ይሏታል፡፡ ገና በዚህ ዓለም በጉዞና በፈተና ላይ ያለችውን የአንዲቷ
ቤተ ክርስቲያን አካል የሆነችውን ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) ደግሞ ገና በተጋድሎ ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን ይሏታል፡፡

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 10


ምዕራፍ ሦስት የቤተክርስቲያን ባሕርያት

3.1 የቤተክርስቲያን ባሕርያት


የቤተክርስቲያን ባሕርያት (መገለጫዎች) የሚባሉት በኒቅያ ጉባዔ በተደነገገው የሃይማኖት መሠረት ላይ “ወነአምን
በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት (ከሁሉም በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባኤ
በሆነች በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” የሚለው ነው፡፡ እንዲት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን
ዘክርስቶስ የሚያሰኛት በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡት 150 ኤጲስ ቆጶሳት (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን)
በቀኖና ሃይማኖታቸው ላይ እንደገለጡት አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊት (የሁሉና በሁሉ ያለች) እና ሐዋርያዊት ስትሆን
ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን ባሕርያት የሚባሉት አራት ናቸው፤ እነርሱም፦ አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊት እና
ሐዋርያዊት የሚባሉት ናቸው። ከእነዚህ ከአራቱ አንዱን ያጎደለች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ልትሆን አትችልም
አይደለችምም፡፡

3.1.1 አንዲት ናት
ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) ናት፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ አትሆንም፡፡ ከአንድም አታንስም፡፡
አይጨመርባትም፡ አይቀንስባትምም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ …”በዚህ አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሠርታለሁ”
አለ እንጂ “ቤተክርስቲያኖቼን” አላለም፡፡ ማቴ 16፡18 በአንድ መሠረት ላይ አንዱ መሥራች የመሠረታት ስለሆነች
ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በእርሷ ያለውን አንድነትም ያመለክታል፡፡ በቤተክርስቲያን ሦስት አይነት አንድነት
አለ፡፡ የመጀመሪያው በምድር ላይ የምንኖር ክርስቲያኖች (እርስ በእርሳችን) ያለን አንድነት ነው፡፡ ሁለተኛው በአካለ
ሥጋ ያለን ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ያለን አንድነት ነው፡፡ ሦስተኛው አንድነት ሁላችንም (በአካለ
ሥጋ ያለን ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን) ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት ነው፡፡ ይህ አንድነት ነው
እንግዲህ ቤተክርስቲያንን አንዲት ያደረጋት፡፡

እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ እንዳለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ
ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የበቀሉ ቅርንጫፎች ናቸውና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሊሆኑ
ይገባል፡፡ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አለምንም
. . . አንተ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ . . . እኛም አንድ
እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” ዮሐንስ ወንጌል 17 ፥ 20 – 23፡፡ ከሚለው የጌታ አነጋገር የምንረዳው ይህን
አንድነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ
መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ፥ ጌታ አንድ ነው ሃይማኖትም አንዲት ናት ጥምቀትም አንዲት ናት” ኤፌሶን
4 ፥ 4 – 5። በማለት ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ እንዲት መሆንዋን አስገንዝቧል፡፡ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በእብነ
በረድ ትሠራ በጭቃ፤ በሀገር ቤት ትመስረት በውጭ ሀገር እምነትዋ ሥርዓትዋ አንድ ነው፡፡

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 11


ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በዋናነት የሚመለከተው ከአንዱ ክርስቶስ ጋር ያለንን ውህደት ነው እንጂ
አስተዳደራዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድነታችን የአንዱ ግንድ የክርስቶስ ቅርንጫፎች መሆናችንና በአንዱ በክርስቶስ
ሥጋና ደም የምንድን መሆናችን ነው፡፡ ዮሐ 15፡1-10 በዚህ በአንዱ መሠረትነት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች
ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

3.1.2 ቅድስት ናት
ክርስቶስ በቅዱስ ደሙ መሥርቷታል፤ አንጽቷታል፤ ቀድሷታልና ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ኤፌሶን 5 ፥
26፡፡የቤተ ክርስቲያን ቅድስና የተገኘው ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ
ክርስቶስ በመሆኑ ወደ እርስዋ የገቡ ርኩሳን ይቀደሳሉ እንጂ በውስጥዋ ያሉ ሰዎች በኃጢአት በክህደት ቢረክሱ
እርስዋ አትረክስም፡፡ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሠረት በእርሱ ያመኑ በቤተ
ክርስቲያን ጥላ ሥር የተጠለሉ ሁሉ ቅድስናን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ቤተክርስቲያን ቅድስት (የተለየች) ናት ሲንል
አራት ነገሮችን ያመለክታል፡፡

አንደኛ፡ በደሙ የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ነውና ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡ 1ጴጥ 1፡15-16 ሐዋ
23፡20 ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ናትና ቅድስት ናት፡፡ እርሱም መሠረቷ አካሏና ጉልላቷ ስለሆነ ቅድስት
ናት፡፡

ሁለተኛ፡-ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሥራ (አገልግሎት) የሚፈጸምባት የጸሎት ቤት ናትና ቅድስት (የተለየች) ናት፡፡
የተለየችው ለቅድስና ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ያልሆነ ሥራ መሥራት አይገባም፡፡

ሦስተኛ፡- ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑ የሰው ልጆች ምሥጢራትን ተካፍለው (ተጠምቀው ንስሐ ገብተው
ሥጋና ደሙን ተቀብለው) ቅድስና ያገኙባታልና ቅድስት ናት፡፡ የቅድስና መገኛ ስፍራ ናትና ቅድስት ናት፡፡

አራተኛ፡- ቤተ ክርስቲያን ቅድስት የሆነችው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ቅድስት ናት፡፡ ወደ ሰማያዊት
መንግስት የምታደርስ በምድር ላይ ያለች የክርስቲያኖች ቤት ናትና ቅድስት ናት፡፡ በምድር ላይ ለእግዚአብሔር
የተለየች ቅድስት ናት፡፡

አንዳንድ ወገኖች ብዙ ኃጢአት የሚሠሩና በደልን የሚፈፅሙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ስላሉ ቤተ ክርስቲያን
የምትረክስ (ቅድስናዋ የሚቀንስ) ይመስላቸዋል፡፡ እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች በጊዜው በንስሐ ካልተለመሱ ራሳቸው
ይረክሳሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አትረክስም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስናዋ ዘላለማዊና የማይለወጥ ስለሆነ አትረክስም፡፡
ሰው ቢያከብራት ራሱ ይከብራል፡፡ ባያከብራት ደግሞ ራሱ ይረክሳል፡፡ ይህም በአፍኒንና በፊንሐስ እንዲሁም በሐናና
በሰጲራ እንደሆነው ነው፡፡ ሐዋ 5፡1 1ኛ ሳሙ 2፡12 ለምሳሌ በቆሻሻ ላይ የፀሐይ ብርሀን ቢወጣበት ቆሻሻው ይሸታል
እንጂ የፀሐይ ብርሀኑ ምንም አይሆንም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስናም ልክ እንደ ፀሐይ ብርሃን ነው፡፡

3.1.3 ኩላዊት ናት
ቤተ ክርስቲያን ኲላዊት ናት ሲባል የሁሉ (ዓለም አቀፋዊት) እና ከሁሉ በላይ ናት ማለት ነው፡፡ ይህም በጸሎተ
ሃይማኖት “እንተ ላዕለ ኩሉ” በሚለው ይታወቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉ እንደሆነች ሁሉ ደግሞ ከሁሉ በላይ
ናት፡፡ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ወገን ናት የዚህ ወገን አይደለችም የማትባል

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 12


በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎጥና በቀለም እንዲሁም በቦታ የማትከፋፈል የሁሉና በሁሉ ያለች ናት፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ
ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆንዋን እንዲህ ሲል ገልጾታል “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ
ወይም ጨዋ ሰው የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ገላቲያ 3 ፥ 28፡፡

ቤተክርስቲያን የሁሉ ናት (ዓለም አቀፋዊት ናት) ስንል በአምስት ደረጃ ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

በመልክአ ምድር፡- ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሀገር ወይም የዚህ አካባቢ ናት አይባልም፡፡ በክርስቶስ ያመነ የተጠመቀ
ሁሉ (ከማንኛውም የዓለም ክፍል ቢመጣ) የሚገባባትና የሚኖርባት ቤት ናት፡፡

በሰው ፀባይ:- ቤተ ክርስቲያን የዚህ ዘር፣ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የዚህ ጾታ ወይም የዚህ እድሜ ክልል ናት አይባልም፡፡
የሁሉም ናት እንጂ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሰው እምነቱ እንጂ ሰብአዊ ማንነቱ አይጠየቅም፡፡

በጊዜ/በዘመን፡- ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ለነበረው ትውልድ፣ አሁንም ላለው ትውልድ፣ ወደፊትም
ለሚኖረው ትውልድ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ናት ሲባል የሁሉም ትውልድ ናት ማለትም ነው፡፡

በማዕረጋት:- ቤተ ክርስቲያን የፓትያርኩም፡ የጳጳሳቱም፡ የቀሳውስቱም፡ የዲያቆናቱም፡ የምዕመናኑም ናት፡፡ ሁሉም


በቤተክርስቲያን የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡

በሰማይና ምድር፡- ቤተ ክርስቲያን በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉት አንድነት ስለሆነች የሁለቱም ናት፡፡ ቤተ
ክርስቲያን የክርስቶስ ስለሆነች የክርስቶስ ለሆነ ሁሉ ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ናት ሲባል በቃ የሁሉ ናት ተብሎ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የሁሉም ናት ማለት ሁሉም
በቤተ ክርስቲያን የየራሱ የአገልግሎት ድርሻ አለው ማለት ነው፡፡ ፈተና ቢያጋጥማትም የሚመለከተው ሁሉንም
ነው ማለት ነው፡፡

3.1.4 ሐዋርያዊት ናት
ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ነው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብጹዕ ነህ
. . . እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚይች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን አሠራታለሁ የሲዖል በሮችም
አይበረታቱባትም፡፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል
በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል” ማቴዎስ 16 ፥ 15፡፡

ከትንሣኤው በኋላም “ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ ይህንንም ብሎ
እፍ አለባቸውና እንዲህም አላቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይሰረይላቸዋል ይቅር
ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም” ዮሐንስ ወንጌል 20 ፥ 22፡፡

ከላይ በተገለጸው መሰረት ቤተ ክርስቲያንን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንን ሐዋርያት ከጌታ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ
ጳውሎስም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት
አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የሐዋሪያት ሥራ 20 ፥ 28፡፡ በማለት ቤተ ክርስቲያን

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 13


በቅዱስ ሲኖዶስ ልትመራ እንደሚገባ አስገንዝቦናል ሲኖዶስ ማለት የጳጳሳት ጉባኤ መሆኑን ልብ ይልዋል፡፡
ቤተክርስቲያንም ሐዋርያዊት ናት ስንል ሐዋርያዊት የሆነችው በሦስት ነገሮች ነው፡፡

በሢመት ሀረግ፡- ከሐዋርያት አንስቶ ያልተቋረጠ የሢመት ሀረግ መኖሩ ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡
ጌታችን ለሐዋርያቱ የሰጠው የክህነት ስልጣን ሳይቋረጥ በቀጥታ እየተላለፈ መምጣቱ አንዱ የሐዋርያዊትነቷ
መገለጫ ነው፡፡

በትውፊትና በምሥጢር፡- ቤተ ክርስቲያን የሐዋርትን ትውፊት ተቀብላ መተግበሯ ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ እንደ
ሐዋርያት ሲኖዶስ አላት፡ እንደ ሐዋርት ታጠምቃለች፡ እንደ ሐዋርያት ትቀድሳለች፡ ሥጋና ደሙን ታቀብላለች፡፡
ሐዋርያት የሠሩትን እንደ ሐዋርያት አድርጋ ትሠራለች፡፡ ከሐዋርያት የተለየ ሥርዓት ሊኖራት አይችልም፡፡ ይህ
የሐዋርያዊትነቷ ሌላው መገለጫ ነው፡፡

በመጻሕፍት ትርጓሜ፡- ሐዋርያዊ ክትትሉን የጠበቀ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ስላላት ቤተ ክርስቲያን
ሐዋርያዊት ናት፡፡ ሐዋርያት እንደተረጎሙት አድርጋ ትተረጉማለች፡፡ ሐዋርያት እንዳስተማሩት አድርጋ
ታስተምራለች፡፡ ሐዋርያት ያላስተማሩትን አታስተምርም፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት የጀመረችው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመሆኑ ምሥክሩ
መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደረገበትን ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ግብረ
ሐዋርያትን በገለጸበት ጽሑፉ ላይ እንዲህ ተርኮታል፡- አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፥ እንደ ሙሴ ሥርዓት
ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል
ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ግዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት
ወደ ቀሳውስቱም ወደ ኢየሩሳሌምም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ። . . .በሐዋርያት ያደረ ቅዱስ መንፈስ በቅዱስ ጳውሎስም
ያደረ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ለምን ወደ ሐዋርያት መሄድ አስፈለጋቸው? ይህ
ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተገዙ መሆናቸውን
ያሳያል ምክንያቱም ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁና ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው
ናቸውና። ስለዚህ ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል እነርሱ ነበሩ፤ ይህ ሐዋርያዊ ውርስ
ባላት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሲኖዶሳዊት
ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት አይደለችም የምንለው፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ምንረዳው የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ በሐዋርያው
በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት ከ49 – 50 ዓ.ም ባለው ግዜ የተካሄደው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከአሕዛብ ወገን
ክርስትናን በተቀበሉና ከአይሁድ ወገን ክርስትናን በተቀበሉት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለዚያ እልባት
ለመስጠት ነበር ሐዋርያትም ግራ ቀኙን አድምጠው የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተዋል። ሐዋርያትና ቀሳውስት
ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡
ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኃል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል
እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳችውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና
ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን፡፡ ራሳቸውም ደግሞ

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 14


በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል፡፡ ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም
ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል ከዚህም ሁሉ
ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ ጤና ይስጣችሁ፡፡ ” የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 22 – 29፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምድረ ፍልስጤም ወደ ሌሎቹ የሮማ ግዛቶች ግዛትዋን እያሰፋች በመጣች ግዜም መዋቅርዋ፤
ሐዋርያዊ ሠንሰለቱ እንደተጠበቀ ነበር፤ ከቤተ አይሁድም ከቤተ አሕዛብም የመጡ ከሐዋርያት የሰሙ ከሐዋርያት
የተማሩ ሐዋርያውያን አባቶች በሐዋርያት መንበር እየተተኩ ሠንሰለቱ ሳይበጠስ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት የምንለው በሐዋርያው በቅዱስ ፊልጶስ አማካይነት
በ34ዓ.ም ጥምቀትን ተቀበለች፥ በኃላም በአራተኛው ምዕተ ዓመት በሲኖዶስ ሕግ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ሥር
የተዋቀረች በመሆኑ ነው፡፡ የራስዋ መንበር ባለቤት የሆነችውም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በዓመጽ ተገንጥላ
ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት በሥርዓቱ ነው፡፡ ለዚህም አባቶቻችን አያሌ ዘመናት በትእግስት
የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጠንተዋል፡፡ይህም የሐዋርያዊ ውርስ ሠንሰለቱ እንዲጠበቅ የከፈሉት
መሥዋዕትነት ነው፡፡

የሐዋሳ ደ/ም/ቅ/ገ/ገ የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት 15

You might also like