You are on page 1of 5

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

መዝሙርና ምሥጢራዊ ሥርዓቱ


መዝሙር ወይም ዜማ የተጀመረው በአራቱ ሰማያት ማለትም በሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ በኢዮር፣ በራማና በኤረር ያሉ

መላእክት እግዚአብሔር ፈጣሪያቸውን ያለ ዕረፍት ሲያመሰግኑት ነው። ይህንንም ሲያረጋግጥ ነቢዩ ኢሳይያስ፦ “እግዚአብሔርን

በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ሊይ ተቀምጦ አየሁት የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር

አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር።

የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ። ቤቱንም ጢስ ሞላበት” ይላል (ኢሳ ፮፤ ፩-፭)። ይህም በመላእክት

የተጀመረው ጣዕመ ዜማ በእነሱ አሰሚነት ለሰው ልጆችም ተላልፏል። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሥልጣነ

እግዚአብሔር እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አገዛዝ ነፃ ባወጣበት ጊዜ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ በደረቅ ምድር ቢያሻግራቸው ሙሴና

ተከታዮቹ በተለይም እኅቱ ማርያም በከበሮ ድምጽ እየታጀቡ እግዚአብሔርን በጣዕመ ዝማሬ አመስግነዋል፤ የመዝሙርም በይፋ

መጀመር የታወቀው በዚሁ ጊዜ ነው (ዘጸአ ፲ ፭፤፳፪)። ደግሞም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ባየው ራእይ ምዕ ፲ ፬፤፩-፮ በምድር

የተዋጁት አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ወገኖች ማንም ያልዘመረውንና ሊዘምረው የማይችል ጣዕሙ ልዩ የሆነ አዲስ መዝሙር

በመድኃኒታችን ዙፋን ፊት በኪሩቤልና ሱራፌል መካከል እንደዘመሩ ይገልጻል።

የመላእክት ጣዕመ ዝማሬ ለሰው ልጆች የታደለ ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ፈጣሪዋን

ስታመሰግን ትኖራለች። ይህም የምንዘምረው መዝሙር የቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው። ይህም ዜማ አርያም ይባላል። አርያም ማለትም

ልዑል፣ ከፍተኛ ማለት ነው። ቅዱስ ያሬድ የዜማ መጀመሪያውን አርያም ብሎ የሰየመው በሰማይ ካሉ መላእክት ሰምቶ መዝሙር

ስለጀመረ ነው። ይህም ሊታወቅ “ቀዲሚ ዜማ ተሰምዓ በሰማይ” እያለ ይሔድ እንደነበር ሊቃውንት ይተርካሉ። ይህ ታላቅ ሊቅ

በመንፈሳዊነት ተመስጦ ሰማየ ሰማያት ተነጥቆ ከመላእክት ያገኘው የዜማ ዓይነቶች ሦስት ናቸው፦ እነዚህም ፩) ግዕዝ ፪) ዕዝል ፫)

አራራይ ይባላሉ። እነዚህ ሦስቱ የዜማ ስልቶችም ምሳሌና ትርጉም አላቸው። ይኸውም ግዕዝ ማለት ርቱዕ ነው። አብን “ርቱዕ ሎቱ

ነአኩቶ” ማለት ክብርና ምሥጋና ለእርሱ ይሁን ለማለት ነው። ዕዝል ጽኑዕ ማለት ነው። ወልድ ጽኑዕ መከራ ተቀብሎ አዳምን

እንዳዳነው ለማመልከት ነው። አራራይ ማለትም ጥዑም ማለት ነው። ጥዑም ሀብተ መንፈስ ቅዱስን እንደ ተጎናጸፍን ለማስረዳት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የቅዱስ ያሬድ ዜማ በቂና ምሳሌ ያላቸው ፰ አበይት ምልክቶች አሉት። እነዚህም ዜማውን ለሚማር ደቀመዝሙርና

ለሚዘምረው ሁለ ፈረንጆች ኖታ እንደሚሉት በምልክትነት ሲያገለግሉ ምሳሌያቸውና ምሥጢራቸው ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ

ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለኛ የተቀበለውን መከራ የሚያስታውሱ ናቸው። እነዚህም፦


 
፩) ይዘት-በአይሁድ ጭፍሮች ለመያዙ

፪) ሂደት - ታሥሮ ለመጎተቱ

፫) ጭረት- ለግርፋቱ ሰንበር

፬) ድፋት - አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል) ለመድፋቱ

፭) ደረት - ሲሰቅለት በመስቀሉ ላይ አንጋለው ከደረቱ ላይ እየረገጡት ለመቸንከሩ

፮) ርክርክ - ለደሙ ነጠብጣብና ለችንካሮቹ ምልክት

፯) ቁርጽ - በጦር ተወግቶ ፈጽሞ መሞቱ ለመታወቁ

፰) ቅንዓት - አይሁድ በቅናት ተነሣሥተው ለመግደላቸው ምሳሌ ናቸው።

ስምንት መሆናቸውም ስምንቱ ማኅበረ አይሁድ ተባብረውና መክረው በብዙ ሥቃይ ለመግደላቸው ምሳሌ ነው። እነዚህስ ማንና ማን

ናቸው ቢሉ፦

፩) ጸሐፍት

፪) ፈሪሣውያን

፫) ሰዱቃውያን

፬) ረበናት (መምህራነ አይሁድ)

፭) መገብተ ምኲራብ (የምኲራብ ሹማምንት)

፮) መልሕቅተ ሕዝብ (የሕዝብ ሽማግሌዎች)

፯) ሊቃነ ካህናት

፰) መጸብሐን (ቀራጮች) ናቸው።

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የማኅበር ጸሎት ሲደርስ በጣዕመ ዜማ (መዝሙር) ማመስገንና መጸለይ የተለመደና

የተወደደ ሥርዓት ነው። ይህ ሁለ ሲከናወን ለምሥጋናውና ለጸሎቱ ማጎልመሻ ሆነው የሚቀርቡት ንዋያተ ቅድሳትና የጸሎቱ ቅደም

ተከተሉ ራሱ በቂ ምክንያትና ምሳሌ ያለው ሆኖ መገኘቱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ልጆች ሁለ በጣም ያኮራናል። ይህንንም

ለመረዳት በጸሎተ ቅዳሴ እንዲሁም በማኅሌት የምሥጋና መዝሙር በሚቆምበት ጊዜ የሚፈጸመውን ከልብ መመልከትና ማገናዘብ

ይገባናል።

የቤተ ክርስቲያናችን የመዝሙር መሣሪያዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለማችን ካሉ የእምነት ድርጅቶች ልዩ የሚያደርጓት ባሕርያት መካከል

አንዱ የመዝሙር ሥርዓቷ ነው። ቅዱሳን አባቶች ፈጣሪያቸውን በያሬዳዊ መዝሙር እያመሠገኑ እስከነመሣርያው ጠብቀው
 
አቆይተውልናል። እኛም በዚህ ዘመን ያለን ምዕመናን ከአባቶቻችን የተረከብነውን መዝሙርና ሥርዓት ማወቅና በአግባቡ መጠቀም

ይኖርብናል። ታድያ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘውን የዜማ ስሌት በተሟላ ምሥጢርና ምሳሌ ለመዘመር፦

፩) የመዝሙር መሣርያዎችን ማወቅና መጠቀም፣

፪) የቅዱስ ያሬድን የዜማ ምልክቶችና የድምጽ አሰባበሩን ማጥናት፣

፫) የአቋቋሙንና የንቅናቄውን ሥነ ሥርዓት ማወቅ ይኖርብናል።

ለአሁኑ የመዝሙር መሣርያዎችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎቻቸውን እንመለከታለን። ቤተ ክርስቲያናችን በአጠቃላይ

የምትጠቀምባቸው አምስት የመዝሙር መሣሪያዎች አሉ። እነርሱም ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ፣ በገና፣ መለከት በመባል የሚታወቁ

ሲሆኑ ከነዚህም በተጨማሪ ክራርና መሰንቆ ከበገናው ዘርፍ በመመደብ ያገለግላሉ። እነዚህ መሣሪያዎች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት

ከፍተኛ ጥቅም ስለሚሰጡ ንዋያተ ቅድሳት (የተቀደሱ የቤተ ክርስቲያን ገንዘቦቿ) ተብለው ይጠራለ። እነዚህን የመዝሙር መሣሪያዎች

በአግባቡ ማወቅና መጠቀም የክርስትናችን መገለጫ በመሆኑ እስከነጥቅማቸውና ምሳሌያቸው እንመለከታለን።

ከበሮ ፦ በብለይ ኪዳን ዘመን እሥራኤላውያን ፈጣሪያቸውን ለማመስገን ይጠቀሙበት የነበረ የመዝሙር መሣርያ ነው። ለ፬፻፴

ዓመታት በግብጽ ስደት ይኖሩ የነበሩ ሕዝበ እግዚአብሔር የተባሉት እሥራኤላውያን በነቢዩ ሙሴ አማካይነት የኤርትራን ባሕር

ከተሻገሩ በኋላ በከበሮ በመታጀብ “ንሴብሖ ለእግዚአበሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ” ( ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን)

እያሉ አመስግነዋል። ከበሮ የምትመታውም የአሮንና የሙሴ እኅት ማርያም ነበረች (ዘጸአ ፲ ፭፣፳-፳፩)። በተጨማሪም ንጉሥ ዳዊት

እግዚአብሔርን በከበሮ እንድናመሰግን ያስተምረናል (መዝ ፻፶፣፬)። በዘመነ ሐዲስ የተነሡ ቅዱሳን አባቶች ከበሮን ከመድኃኒታችን

ኢየሱስ ክርስቶስ የሕማማቱ ሰሞን ጋር በማገናዘብ መንፈሳዊ ትርጉም ሰጥተውታል።

ይኸውም ፦

ሀ) ከበሮ በአንድ በኩል ሰፊ ሲሆን በአንደኛው ጠባብ ሆኖ ግራና ቀኝ ይመታል። ትንሽ ጎኑ አይሁድን ሲያመለክት ትልቁ የኢየሱስ

ክርስቶስ ምሳሌነው። ፍቺውም አይሁድ ታናናሾች ሆነው ሳለ ታላቁን ፈጣሪ መድኃኔዓለምን መደብደባቸው ነው።

ለ) በከበሮው ዙርያ የተጠላለፈው ቆዳ አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገረፉት ጊዜ በሰውነቱ ላይ የወጣው ሰምበር ምልክት

ሲሆን የከበሮው መያዣ ደግሞ የጅራፉ መታሰቢያ ነው።

ሐ) ከበሮው የሚለብሰው ጨርቅ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገነዘበትን ንጹሕ በፍታ ያመለክታል (ማቴ ፳፯፣፶፱)። ዮሴፍና

ኒቆዲሞስ መድኃኔዓለምን ከመስቀለ ላይ በማውረድ በንጹሕ ጨርቅ ሸፍነው በአዲስ መቃብር አኑረውታል። እንግዲህ ቅዱሳን
 
አባቶቻችን በማኅሌት በወረብ ጊዜ ከበሮ የሚመቱት የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጥፊ መመታቱን መደብደቡን

ባጠቃላይም ሕማሙን በማሰብ መሆኑ ከበሮን መንፈሳዊ ትርጉም ይሰጠዋል።

ጸናጽል ፦ በብለይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እሥራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቀሙበት የነበረ መሣሪያ ነው (፪ኛ

ሳሙ ፮፣፭)።

ሀ) ያዕቆብ በሎዛ መንገድ ላይ ያየው መሰላል ምሳሌ ነው (ዘፍጥ ፳፰)። ያዕቆብ ብዙ መንገድ ተጉዞ ሎዛ በተባለች መንገድ ላይ ዕረፍት

አደረገ፤ ከድካሙም የተነሣ አንቀላፋ። በህልሙም መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክላ በዚያች መሰላል ላይ መላእክት ሲወጡባትና

ሲወርዱባት ተመለከተ፤ በመሰላሉም ጫፍ ላይ እግዚአብሔር ተቀምጦባት አየ። እንግዲህ ጸናጽል፤ ያዕቆብ ያየው መሰላል ምሳሌ ሲሆን

በጸናጽሉ ላይ ያሉት አምስት ቅጠልች የመላእክቱ ምሳሌ ናቸው። ይኸውም የቅጠልቹ ድምፅ በሰማያት ያለ መላእክት እግዚአብሔርን

ሲያመሰግኑ የሚያወጡት ታላቅ ድምፅ ምሳሌ ነው። የቅጠሎቹ አምስት መሆን ቤተ ክርስቲያናችን በአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ላይ

የተገነባች መሆኗን ያመለክታል።

ለ) የጸናጽል ሁለቱ ዘንጎች (ማለትም በግራና ቀኝ ያሉት) ጋድም ይባላሉ። ሁለቱ ጋድሞች የሁለቱ ኪዳናት ምሳሌዎች ናቸው፤ ብሉይና

ሐዲስ ኪዳን።

ሐ) ቅጠሎቹ የተንጠለጠለባቸው ሁለት ዘንጎችም ምሳሌ አላቸው። ይኸውም በሁለቱ ዐበይት ትዕዛዛት ዐሠቱ ቃላት የመጠቃለላቸው

ምሳሌ ነው። ለዚህም ቅዱስ መጽሐፋችን “በእነዚህ በሁለቱ ትዕዛዛት ሕጉም ሁለ ነቢያትም ተሰቅለዋል።”(ማቴ ፳፪፣፵) ሕጉም ሁሉ

ያላቸው ዐሠርቱን ትዕዛዛት ነው።

መ) ያዕቆብ በሎዛ መንገድ ላይ ተኝቶ በህልሙ ያያት መሰላል የእመቤታችን ምሳሌ መሆኗን የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት

ያስተምሩናል። ስለሆነም ጸናጽሉን ለእመቤታችን ምሳሌ ያደርጉታል። በዚህም መሠረት ሁለቱ ዘንጎችና ጋድሞች የአማላጅነቷ

ምሳሌዎች ናቸው። ሁለቱ ዘንጎችና ጋድሞች የመሰላል ቅርጽ የያዙ ናቸው። የመሰላል ጥቅም ወደ ላይ ለመውጣትና ወደ ታች

ለመውረድ እንደሆነ ሁሉ በእመቤታችን መሰላልነት (አማላጅነት) ወደ እግዚአብሔር እንደርሳለን፣ ከጌታም ምሕረትን እናገኛለን።

እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከጠፋበት ለማዳን በወደደ ጊዜ ወደዚች ምድር ለመምጣት ሰው መሆን ነበረበት። ሰው የሆነውም

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተዋሐደው ሥጋና ነፍስ ነው። እንግዲህ የማይታየው ፈጣሪ የሚታይ በሆነ ጊዜ

የእመቤታችንን ሰውነት መሰላል አደረገው ማለት ነው። የጸናጽሉ ቅጠሎች የቅድስናዋ፣ ንጽሕናዋ፣ ትኅትናዋ፣ ድንግልናዋ፣ ትዕግሥቷ

ምሳሌዎች ሲሆኑ የዘንጎቹ ሁለት መሆን እመቤታችን በሥጋም በነፍስም ድንግል እንደሆነች ያመለክታል። ካህናት አባቶቻችን ጸናጽል

በቀኝ እጃቸው ይዘው ደፋ ቀና ሲያደርጉትና ወደ ቀኝና ግራ ሲያወዛውዙት መስቀል መሥራታቸው ነው። ይህም የጌታችንን ሕማሙን

መከራውን ለማሰብ ነው። በተጨማሪም ጸናጽል ወደ ታች መጣሉና ወደ ላይ መነሣቱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

ወደዚህ ዓለም መምጣቱንና ማረጉን ደግሞም ለክብር እንደሚመጣና ቅዱሳኑን በክብር ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ እንደሚወስዳቸው

ያጠይቃል።
 

መቋምያ ፦ መቋምያ የክርስቶስ መስቀል ምሳሌ ነው። በመጀመሪያ የሠሩት በግብጽ ገዳም ይኖሩ የነበሩ አባ እንጦንስ (St. Anthony)

የተባለ መነኩሴ ናቸው። ይህንንም ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ ላደረገው ጉዞ መታሰቢያ ይሁን ብለዋል። ስለሆነም በማኅሌት ጊዜ

ካህናት መቋምያ ይዘው ወደ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ ማወዛወዛቸው የክርስቶስን መንገላታት ለማሰብ ነው። ይህንም አርአያ

በማድረግ በጎጃም ክፍለ ሀገር መሬት ዋፈ በምትባሌ ሥፍራ ይኖሩ የነበሩ መምህር አጽቀ ድንግሌ የሚባለ የአጼ ልብነ ድንግል ወንድም

በተደገፉት ቁጥር እንዲወጋቸውና የክርስቶስን መከራ እንዲያስታውሱ ፲ ፭ ሾክ የፈሰሰበት መቋምያ አሠርተው ነበር ይባላል።

በገና ፦ በገና ዐሥር አውታር (ጅማት) ያለው የመዝሙር መሣርያ ነው። በዘመነ ብለይ ኪዲን ለመዝሙር መሣሪያነት ያገለግል ነበር

(፩ኛ ዜና ፲ ፭፣፳፩)። ንጉሥ ዳዊትም በገና እየደረደረ በሚዘምርበት ወቅት አጋንንት ያደሩባቸው ሳይቀሩ ይፈወሱ ነበር። ለዚህም

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፤ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤

ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፤ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር (፩ኛ ሳሙ ፲ ፮፣ ፳፫)። የበገና አውታሮች ዐሥር

መሆናቸው ለምንድነው ተብሎ ቢጠየቅ ምሳሌነት አለው። ፍጹም የሆነው አምላካችን ፍጹማን የሆኑ ዐሥር ትዕዛዛትን ለሕዝበ

እሥራኤል እንደሰጠ የሚያጠይቅ ነው። በተጨማሪም ዐሥሩ ቆነጃጅት ትዝ ይሉናል(ማቴ ፳፭፣ ፩-፲ ፫)። አምስቱ ልባሞችና አምስቱ

ሠነፎች በአንድነት ዐሥሩ ቆነጃጅት ይባላለሉ። እነርሱን ስናስብ የእኛም ዕጣ ከየትኛው እንደሆነ እንድናስብና ማስተካከል ያለብን ነገር

ካለ እንድናስተካክል ይረዳናል።

በዚሁ በበገና ዘርፍ ክራርና መሰንቆም ይገኙበታል።

መለከት ፦ ከከብት ቀንድ ወይም ከብረት የሚሠራ ለመጥሪያ (አዋጅ መንገርያ) በተጨማሪም ለመዘመርያ የሚያገለግል ነው (ዘኁል፲፣

፩-፲)። ምሳሌነቱም በተለይ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መንግሥቱ ሲመጣ ቅዱስ ሚካኤል መለከት እንደሚነፋ፤

የሞቱት ሁለ በአንድ ሊይ እንደሚሰበሰቡና እንደየሥራቸው እንደሚቀበሉ ያሳያል (፩ኛ ተሰሎ ፬፣፮)። እኛም መለከት ሲነፋ የክርስቶስን

ዳግም ምጽአት እያስታወስን በንስሐ እንድንኖር ያደርገናል።

ክርስቲያኖች ፦ የመዝሙር መሣርያዎቻችንን ማወቅ እንድንጠቀምባቸው ይረዳናል። ዛሬ ብዙ ወገኖቻችን ወደ ሌላ የሄዱት ይህን

ባለማወቃቸው የራሳቸው የሆነ ያለ ስለማይመስላቸው ነው። ይህን ማሳወቅ የሚገባን እኛው ነን። በተለይም ለማኅሌቱ አገልግሎት

የምንጠቀምባቸውን ከበሮ፣ ጸናጽል እና መቋምያ ከያሬዳዊው ዜማ ጋር በማቀናበር መዘመር ይጠበቅብናል።

ለዚሁም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን በረከት በሁላችን ላይ ጸንቶ ለዘለዓለሙ

ይኑር አሜን።
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚኒያፖሊስ፣ ሚኒሶታ መስከረም ፳፻፫ ዓ.ም.

You might also like