You are on page 1of 83

፩.

ነገረ ቅዱሳን /ክፍል አንድ/

መግቢያ

፩፡፩  ነገር ማለት፡- በቁሙ ሲተረጐም ቃል ፥ ንባብ ፥ ወሬ ፥ የቃል ፍሬ ፥ ከድምጽ ጋር የሚስማማ ፤ በጽሕፈት


፥ በአንደበት የሚገለጥ ፤ ከልብና ከአፍ የሚወጣ ፥ በአንደበት የሚነገር ማለት ነው። ይኸውም መንገርን ፥
መስበክን ፥ ማስተማርን ፥ ማውራትን ፥ ማብሠርን ፥ ነገርን ሳያቋርጡ እንደ ውኃና ዝናም ማፍሰስን ፥
ማውረድን ፥ ማንጐድጐድን ፤ አሳብን ምሥጢርን በቃል መግለጥን ፥ በንባብ ማስጌጥን ፤ መልክ እያወጡ ፥
ምሳሌ እየሰጡ ማነጽና መቅረጽን የሚያመለክት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « ከጥንት ጀምሮ
እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ » በማለት የዕብራውያን መልእክቱን
የጀመረው ለዚህ ነው። ዕብ ፩፡፩ ። ግዕዙ « በብዙኅ ነገር » ይለዋል፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ሙሴን፦
«እግዚአብሔር አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ እንደጨረሰ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ »
ብሎለታል፡፡ ግዕዙም የሚለው፦ « ጸሐፍ ኲሎ ነገረ ፍጥረት፤ » ነው። ኲፋሌ ፪፥፬። በተጨማሪም
የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት።

-       « ኢትኅፈር ነገረ ጌጋይከ ፤ የኃጢአትህን ነገር መናገር አትፈር ፤ » ሢራ ፬ ፥ ፳፮


-       « መኑ ይክል ነጊረ ምሕረቱ ጥንቁቀ ፤ የምሕረቱን ነገር ጠንቅቆ መናገር የሚቻለው ማነው ? » ሢራ ፲፭ ፥

-       « ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያት ፤ በነቢያት አፍ አስቀድሞ ያናገረው ፤ » ሮሜ ፩ ፥፪
-       « ለምንት ትነግር ሕግየ፤ ለምን አንተ ሕጌን ትናገራለህ ? » መዝ ፵፱ ፥ ፲፭
-       « ፈሪህየ ከመ እንግርክሙ ዘእኄሊ ፤ ዕውቀቴን የማስበውን እነግራችሁ ዘንድ ፈርቼ ዝም አልሁ ፤ » ኢዮ
፴፪ ፥፮
፩፥፪ ፡- ቅዱስ ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥ ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ ማለት
ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል። በአጠቃላይ « ነገረ ቅዱሳን » የሚለው ሲተረጐም፦  የቅዱሳንን ነገር
መናገር ፥ መስበክ ፥ ማስተማር ፥ ማብሠር ፥ መጻፍ ይሆናል።

፪፡- ቅዱስ ማነው?

  ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥
ማዕከለ ዓለም ፥ ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው  የለም፡፡ ነቢዩ
አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው  ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ ፤ » በማለት የነገረን ይኽንን ነው ። ኢሳ ፵ ፥
፳፭ ፡፡

፪፥፩ ስሙ ቅዱስ ነው ፤

  የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « ከስም ሁሉ የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። « ወተወከልነ በስሙ ቅዱስ
በቅዱስ ስሙ ታምነናልና ፤» እንዲል ይህ ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን የምንወጋው ፥
በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን እንደሚከብ
የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነደዳቸው ቅዱስ በሆነው
በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲። በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም « አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ
ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም
እመጣብሃለሁ።» ብሎታል። በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ በሰረገላ ተገፍትሮ የማይወድቀውን
ጐልያድን በእግዚአብሔር ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ።

          በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን


እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ
መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ አርትተውታል። የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም
በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ
፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት
ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ
የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም ጠንቋዩን በርያሱስን
በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲። የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት ፈውሷታል።
የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ።
፪፥፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤

          የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ


፥ አምላክ ፥ ንጉሥ ነው ፤ ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም
አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ
ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥ ሕያው ፥ ኃያል ፥ ረቂቅ ፥ መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው
፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ
፥ ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና አባት ነው።

          ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ


እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ፤ » እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫።
እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት የታደጋቸውን እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን
የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥ ድንቅንም የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤
» እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል።
ኢሳ ፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታትም፦ « ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ
አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ ፮፥፱-
፲፩ ።

ነገረ ቅዱሳን/ክፍል ሁለት/

« ቅዱስ » ለፍጡራን ይቀጸላል ?


እግዚአብሔር ከባረካቸውና ከቀደሳቸው ይቀጸልላቸዋል። እርሱ ሰውን ፥ ቦታን ፥ ንዋያትን ቀድሶ የጸጋው መገለጫ
ያደርጋቸዋል። በዚህን ጊዜ ከዓለማዊ ግብር ተለይተው ለእግዚአብሔር ብቻ ይሆናሉ።

፫-፩ ቅዱሳን ሰዎች


በዚህ ዓለም በሃይማኖት ጸንተው፥ በምግባር ተገልጠው ፥ በገድል የተቀጠቀጡ ነቢያትና ሐዋርያት፥ ጻድቃንና ሰማዕታት፥
ሊቃውንት፥ካህናትና ምእመናን ቅዱሳን ናቸው። ቅዱስ የሚለው ለፍጡር የማይሰጥ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ለእስራኤል
ዘሥጋ በሙሴ በኩል፦ «እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፤» አይላቸውም ነበር። ዘሌ ፲፱፥፪
:: ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ይኸንን ይዞ፦ «ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁ (ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ አድርጋችሁ)
ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገ ለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። አንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ
የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ
ደግሞ ቅዱሳን ሁኑ።» በማለት እስራኤል ዘነፍስ ለተባሉ ለአዲስ ኪዳን ምእመናን አያስተምራቸውም ነበር። ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፫-
፲፮። «ቅዱሳን  ሁኑ፤» የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል አጽንቶ ሲያስተምርም የዓለምን ኅልፈት ከተናገረ በኋላ፦ «ይህ ሁሉ
እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም
በመምሰል እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል»ብሏል። ፪ኛ ጴጥ ፫፥፲-፲፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «በኲራቱም ቅዱስ ከሆነ
ቡሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፥ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎች ደግሞ ቅዱሳን ናቸው፤» ብሏል። ሮሜ ፲፩፥፮፣ ዘኁ~`፲፭፥፳።

ቅዱሳን በሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእይ መጽሐፉ ስለ ሕይወት መጽሐፍ እግዚአብሔር
የተናገረውን ጠቅሷል። ራእ ፳፥፲፪:: ከዚህም ሌላ፦ «ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል፥ስሙንም ከሕይ ወት
መጽሐፍ አልደመስሰውም፥ በአባቴና በመላእክትም ፊት ለስሙ እመሰክራለታለሁ። መንፈስ ለአብያተክርስቲያናት የሚለውን
ጆሮ ያለው ይስማ፤» የሚል አለ። ራእ ፫፥፭። ነቢዩ ኢሳይያስም፥ «በጽዮን የቀሩ ፥ በኢየሩሳሌምም የተረፉ፥ በኢየሩሳሌም
ለሕይወ ት የተጻፉ ሁሉ፥ ቅዱሳን ይባላሉ።» በማለት በመጽሐፈ ትንቢቱ ተናግሮአል። ኢሳ ፬፥፬። እርሱ እንዲህ አድርጎ
ለወንድሞቹ ለቅዱሳ ን ሲመሰክርላቸው፦ የአዲስ ኪዳን ሐዋርያት ደግሞ ለእርሱና ለወንድሞቹ መስክረውላቸዋል።
ይኽንንም የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ፦ «ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ
ሊተረጉም አልተፈቀደም። ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው
በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተናገሩ።» በማለት አስተ ምሯል ፪ኛ ጴጥ ፩፥፳። የያዕቆብ ወንድም ይሁዳም፦ ርትዕት ሃይማኖት
እንደተሰጠቻቸው፥ በእርሷም እስከሞት ድረስ መጽናታቸውን፥ እኛም እነርሱን አብነት አድርገን መጋደል እንዲገባን፦
«ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ ፤ ወዳጆች ሆይ ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን
አንድ ጊዜ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።» በማለት መልእክቱን
አስተላልፏል። ይሁ ፩፥፪-፫። ጻድቁ ካህን ዘካርያስም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት ሲናገር ከጥንት ጀምሮ የነበሩትን ነቢያት
ቅዱሳን ብሏቸዋል። ሉቃ ፩፥፷፱
፬ አስማተ ቅዱሳን፤
ቅዱሳን ሰዎች የሚጠሩባቸው ስሞች፥ የዓለም ሰዎች እንደሚጠሩባቸው አይደለም። የተቀደስ ነው። ስማቸው ከግብራቸው
የተዋሐደ ነው። «ስምን መልኣክ ያወጣዋል፤ » እንደሚባለው ነው። በመሆኑም፦ ዓለማውያን እንደሚሰየሙበት ሥጋዊ፥
ምድራዊ አይደለም። ምናልባት ዓለማውያንም በመንፈሳዊ ስሞች ይጠሩ ይሆናል፥ ነገር ግን ግብራቸው ከስማቸው -
ስማቸው ከግብራቸው አይገጥምም። የቅዱሳን ስሞች ግን፦
፬፥፩ እግዚአብሔር ያወጣው ነው፤
አብርሃም የመጀመሪያ ስሙ «አብራም» ነበር፤ አብራም ማለት ታላቅ አባት ማለት ነው። «ከዚህም በኋላ አብራም የዘጠና
ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ እግዚብሔር
እኔ ነኝ፤ በፊቴ መልካም አድርግ፥ ንጹሕ ሁን፥ ቃል ኪዳኔንም በአንተና በእኔ መካከል አጸናለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ።
አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም አብራምን እንዲህ አለው እነሆ ቃል ኪዳኔን በእኔና በአንተ መካከል አጸናለሁ፥
ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። እንግዲህ ስምህ አብራም አይባልም፥ አብርሃም ይባላል እንጂ፤ ለብዙ አሕዛብ አባት
አድርጌሃለሁና።» ይላል ዘፍ ፲፯፥፩-፭
በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የደቀመዛሙርቱን የቀደመ ስም እየለወጠ አዲስ ስም
ሲሰጣቸው ታይቷል። ይኸውም ከተጠሩበትና ከተመረጡበት ሰማያዊ ግብር ጋር የሚገጥም፥የሚዋሐድ ስም ሲሰጣቸው
ነው። ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ እንደመዘገበው፦ «በየስማቸውም ጠራቸው፤ስምዖንን ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው። የዘብዴዎስ
ልጅ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስንም ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፤ የነጐድጓድ ልጆች ማለት ነው።» ይላል ማር
፫፥፲፮።

፬፥፪ መልአክ ያወጣው ነው፤


«ወአስተርአዮ መልአከ እግዚአብሔር እንዘ ይቀውም መንገለ የማነ ምሥዋዕ ዘዕጣን። የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣን
መሠዊያው በስተቀኝ ተገለጠለት፤» የተገለጠው ለዘካርያስ ነው። በቀኝ መገለጡ የማናዊ ነኝ ሲለው ነው፤ አንድም መንገለ
የማን (ከግራ ወደ ቀኝ) የምትመለሱበት ዘመን ደርሷል፤ አንድም ከግራ ወደ ቀኝ የሚመልስ ልጅ ትወልዳለህ ሲለው ነው።
የቅዱሳን መላእክት ፊታቸው እንደ መብረቅ ስለሆነ ዘካርያስ ፈራ፥ ደነገጠ፥ ተንቀጠቀጠ። ፍርሃት የልቡና ፥ ረዓድ የጉልበት፥
ድንጋጤ የናላ ነው። ከዚያ በፊት በድምፅ ሰምቶት እንጂ በመልክ አይቶት አያውቅም ነበር።

ለመልአክ ፍርሃትን አርቆ መናገር ልማድ ነውና፥ «ኢትፍራህ ዘካርያስ፤ ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤»አለው። ነቢየ እግዚአብሔር
ዳንኤልን፦ «ኢትፍራህ ብእሴ ፍትወት ዳንኤል፤» እንዳለው ማለት ነው። ዳን ፲፥፲፪። ፍርሃትን ካራቀለት በኋላም ልክ
ለነቢዩ በነገረው መልክ «ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቷልና፥ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤
ሰሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ሐሴትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። እርሱ በእግዚአብሔር
ፊት ታላቅ ይሆናልና፤» ብሎታል። ሉቃ ፩፥፰ ።
፬፥፫ የተባረከ ነው፤
እግዚአብሔር አብርሃምን፦ «ከአገርህ፥ ከዘመዶችህ፥ ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።» ካለው
በኋላ ተስፋውን ነግሮታል። ከተስፋውም መካካል «ስምህንም አከብረዋለሁ፤የሚል ይገኛል። ዘፍ ፲፪፥፪። ይህ ልዑለ ባህርይ
እግዚአብሔር የሚያከብረው የሚያሰከብረው ስም በእውነት የተባረከና የተቀደሰ ነው።

፬፥፬ እግዚአብሔር በክብር የጠራው ነው፤


የነቢያት አለቃ ሙሴ የአማቱን የምድያምን ካህን የዮቶርን በጎች ይጠብቅ ነበር። ሙሴ ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረለት፦
የንጉሥ የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ ያለ፥ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር
መከራ መቀበልን የመረጠ፥ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት
አንደሚሆን ያወቀ፥ዋጋውን አሻግሮ የተመለከተ፥ የንጉሡን ቁጣ ሳይፈራ የግብፅን ሀገር በእምነት የተወ፥ ከሚያየው ይልቅ
የማይታየውን ሊፈራ የወደደ ሰው ነው። ዕብ ፲፩፥
ሙሴ በጎቹን ወደ ምድረ በዳ ነዳ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተራራ ወደ ኮሬብ ወጣ። እግዚአብሔርም የደብረ ሲናን ሐመልማል
ተዋህዶ በእሳት ነበልባል አምሳል ተገለጠለት። ሐመልማል የእመቤታችን፥ ነደ እሳት የመለኰት ምሳሌዎች ናቸው። ሙሴ
ነበልባልና ሐመልማል ሳይጠፋፉ ተዋህደው ባየ ጊዜ ተደነቀ። «ቊጥቋጦው ስለምን አልተቃጠለም?ልሂድና ይህን ታላቅ
ራእይ ልይ፤» አለ። እግዚአብሔርም እርሱ ይመለከት ዘንድ እንደመጣ ባየ ጊዜ፦ «ሙሴ፥ ሙሴ ሆይ፥» ብሎ ጠራው ዘጸ
፫፥፩-፬። «ሆይ» የሚለው ቃል ቃለ አክብሮ ነው። ለፍፃሜው ሐመልማለ ሲና በምትባል በእመቤታችን አድሮ ከሥጋዋ ሥጋ
ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ በመወለድ ሐዋርያትን፣ ሰብዓ አርድዕትን እና ቅዱሳት አንስትን ለሰማያዊ ግብር እንደሚጠራቸው
ያመለክታል።
እግዚአብሔር ነቢዩ ሳሙኤልንም በክብር ጠርቶታል። የስእለት ልጅ ነበር፤ ጡት ከጣለበት ጊዜ ጀምሮ ያደገው
በእግዚአብሔር  ቤት በእግዚአብሔር ፊት ነው። ያ ዘመን የእግዚአብሔር ድምፅ ከአገልጋዮችም ከተገልጋዮችም የራቀበት
ዘመን ነበር፤ ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ታጥቆ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። እናቱም ትንሽ
መደረቢያ ሠራችለት፤ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ትወስድለት ነበር። ሊቀ ካህናቱ ዔሊም
መክነው ያገኙትን ልጃቸውን በእምነት ለእግዚአብሔር በመስጠታቸው «በምትክ ዘር ይስጣችሁ፤» ብሎ ባረካቸው።
እግዚአብሔርም በምትኩ ሦስት ወንዶች እና ሁለት ሴቶችን ሰጣቸው። ብላቴናው ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ፊት አደገ ፪ኛ
ሳሙ ፪፥፲፭-፳፮።
የእግዚአብሔር መብራት ገና ሳይጠፋ ሳሙኤል የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ነበር። በዚህን
ጊዜ ነው፥ እግዚአብሔር በታቦቱ አድሮ «ሳሙኤል፥ ሳሙኤል ሆይ፥» እያለ በአንድ ሌሊት አራት ጊዜ መላልሶ የጠራው።
እርሱ ግን እግዚአብሔርን ገና በድምፅ ስላላወቀው ፥ ሊቀ ካህናቱ ዔሊ የጠራው መስሎት፦ «እነሆ፥ የጠራኸኝ፤» እያለ
ተመላልሶ ነበር። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን በክብር እንደጠራው አስተውሎ፦ «ልጄ፥ ሄደህ ተኛ፤ ቢጠራህም፦
አቤቱ ባሪያህ ይሰማል ተናገር በለው።» ሲል መከረው። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በእስራኤል ሊያደርገው ያሰበውን
ምሥጢር ሁሉ ለብላቴናው ነግሮታል። ሳሙኤልም እሰኪነጋ ተኛ፥ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ።
ራእዩንም ለዔሊ መንገር ፈራ። ዔሊ ግን «ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥» በማለት ስሙን በክብር ከጠራ በኋላ «እግዚአብሔር
የነገረህ ነገር ምንድን ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤» አለው። በእግዚአብሔርም ስም አማጸነው። ሳሙኤልም አንዳችም ሳይሸሽግ
ነገሩን ሁሉ ነገረው። በዚህን ጊዜ ዔሊ «እርሱ እግዚአብሔር ነው፥የወደደውን ደስ ያሰኘውን ያድርግ፤» አለ። ፩ኛ ሳሙ ፫፥፩-
፲፰።
ነቢዩ ኤርምያስም፦ «ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፦ ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም የሎሚ በትር
እያለሁ፥ አልሁ። እግዚአብሔርም፥ የተናገርሁትን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ፤» ብሏል። የሎሚ
በትር የተባለች እመቤታችን ናት። ሎሚ መዓዛ አለው ፥ ይህም ለመዓዛ ድንግልናዋ ምሳሌ ነው። ኤር ፩፥፲፩። እግዚአብሔር
ነቢዩ ሕዝቅኤልንም ለነቢይነት በጠራው ጊዜ፦ «የሰው ልጅ ሆይ! በእግርህ ቁም እኔም እናገራለሁ፤ --- የስው ልጅ ሆይ
እኔን ወደ አስመረሩኝ ወደ እስራኤል ቤት እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ዐመፁብኝ። እነርሱ ፊታቸው የከፋ፥
ልባቸው የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው። ---
አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ኲርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥ፥ አትፍራቸው፤
ቃላቸውንም አትፍራ፤--- ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና። --- አንተ የሰው ልጅ ሆይ!
የምነግርህን ሰማ፤ ---- አፍህን ክፈት፥ የምሰጥህንም ብላ። ---- የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፤
ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር። ---- የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ። ---
የሰው ልጅ ሆይ!ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድና ግባ፥ ቃሌንም ንገራቸው።» ብሎታል። ሕዝ ፪፥፩-፲ ፤ ፫፥፩-፬፤
እርሱም፦ «እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ፤» ብሏል። እግዚአብሔር ነቢዩ ሕዝቅኤልን እስከ መጨረሻው
ድረስ ያነጋገረው «የሰው ልጅ ሆይ! » እያለ ነው። ይኸውም በመጨረሻው ዘመን (ዓመተ ዓለም፥ ዓመተ ፍዳ፥ ዓመተ ኲነኔ
ሲፈጸም) በተዋህዶ ሰው ሆኖ እንደሚወለድ ሲገልጥለት ነው።
         
፬፥፭፦ ቅዱሳን መላእክት በክብር የጠሩት ነው፤
ነቢዩ ዳንኤል አይቶት የነበረው ድንቅ ራእይ ይገለጥለት ዘንድ፥ ስለ ራሱም፥ ስለ ወገኖቹም ሱባኤ ገብቶ ነበር። ምክንያቱም
ከራእዩ የተነሣ አያሌ ቀን ታምሞ ነበርና ነው። ማቅ ለብሶ አመድ ላይ ተኛ። ይጸልይና ይለምን (ይማልድ) ዘንድ ፊቱን ወደ
ጌታ ወደ አምላክ አቀና። በትህትና ራሱን ከዓመፀኞች ጋር ቆጥሮ፦ «ጌታ ሆይ! ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል
ኪዳንን እና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፍራ አምላክ ሆይ! ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም
አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል።» አለ። «ጌታ ሆይ! በፍጹም ቸርነትህ ቁጣህንና
መቅሠፍትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌምና ከተቀደሰው ተራራህ መልስ፤ ስለ ኃጠአታችንና ስለ አባቶቻችን  በደል ኢየሩሳሌምና
ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ (በአሕዛብ ዘንድ) መሰደቢያ ሆነዋልና።» እያለ ተማጸነ። «አምላኬ ሆይ! በፊትህ የምንለምን
ሰለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና፥ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህንም ገልጠህ ጥፋታችንን እና
ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። አቤቱ ስማ፥ አቤቱ ይቅር በል፥ አቤቱ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ! ስምህ
በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና ስለ ራስህ አትዘ ግ ይ ።» እያለ ማለደ። በዚህ ዓይነት ኹኔታ ሲጸልይ፥ ሲማልድ
አስቀድሞ በጸሎቱ መጀመሪያ አይቶት የነበረው ገብርኤል እየበረረ ወ ደ  እርሱ መጣ። በማታም መሥዋዕት ጊዜ
ዳሰሰው፤አስተማረው፥ ተናገረውም፤ «ዳንኤል ሆይ! ጥበብና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አ ሁን መጥቻለሁ። አንተ እጅግ
የተወደድህ ሰው ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ቃል ወጥቷል፥ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፥
ራእዩንም አስተውል፤» አለው። ዳን ፰፥፲፭-፳፯።

ነቢዩ ዳንኤል በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥትም ራእይ ተገልጦለት ነበር። በራእዩ ውስጥም ታላቅ
ኃይልና ማስተዋልም ተሰጥቶት ነበር። በዚህም ጊዜ ማለፊያ እንጀራ ሥጋም ሳይበላ፥ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ፥ ዘይትም
ሳይቀባ ሦስት ሳምንት ሙሉ አዘነ፥ ጾመ። አካሉ እንደ ቢረሌ፥ ፊቱም እንደ መብረቅ፥ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥
ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ድምፅ የሆነ በራእይ ተገለጠለት። ብቻውን ስለጾመ ብቻውን
ራእዩን አየ። በአፍ ጢሙም ፍግም ብሎ ተደፋ፥ በጉልበቱ ተንበረከከ፥ ሰገደ። እነሆ እጅ ዳሰሰው፥ እጁንም ይዞ በጉልበቱ
አቆመው። «እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ! እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ
ብለህም ቁም።» አለው። እየተንቀጠቀጠም ቆመ። ደግሞም «ዳንኤል ሆይ!አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም
በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ከአደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ፤»
አለው። አሁንም ፊቱን ወደ ምድር ደፍቶ ሰገደ፥ ዲዳም ሆነ። እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሩን ዳሰሰው፥ ያን ጊዜም
አፉን ከፍቶ ተናገረ፥ በፊቱ ቆሞ የነበረውንም፦ «ጌታ ሆይ! ከራእዩ የተነሣ ሰ ውነቴ ታወከች ፥ ኃይልም አጣሁ። አቤቱ
አገልጋይህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ አንዴት ይችላል? ከአሁንም ጀምሮ ኃይሌ አይጸናም፤ እስትንፋስም አልቀረልኝም፤»
አለው። የስው ልጅ የሚመስለውም ዳሰሰውና አበረታው። ሦስተኛም፦ «እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ! አትፍራ ሰላም ለአንተ
ይሁን፥ በርታ፥ ጽና፤» አለው። እርሱም በረታ። ዳን ፲፥፩-፲፱

፬፥፮፦ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ነው


የቅዱሳን ስማቸው የእግዚአብሔርን ማንነት የሚገልጥና የሚያስተምር ነው። ሳሙ-ኤል ማለት የእግዚአብሔር ስም ማለት
ነው። ኤልያስ ማለት ኃይለ እግዚአብሔር ማለት ነው። ኢሳይያስ ማለት እግዚአብሔር መድኃኒት ማለት ነው። ኢዩኤል
ማለት እግዚአብሔር አምላክ ማለት ነው። ኢያሱ ማለት እግዚአብሔር አዳኝ ማለት ነው። ኤልሳዕ ማለት እግዚአብሔር
ደኅንነት ማለት ነው። ኤርምያስ ማለት እግዚአብሔር ከፍ ያደርጋል ማለት ነው። ሚክያስ ማለት እግዚአብሔርን የሚመስል
ማነው? ማለት ነው። ዳንኤል ማለት እግዚአብሔር ዳኛ ማለት ነው። ዘካርያስ ማለት እግዚአብሔር ያስተውላል ማለት
ነው። አዛርያ ማለት እግዚአብሔር ይረዳዋል ማለት ነው። ሚሳኤል ማለት እግዚአብሔርን የሚመስል ማለት ነው። ሶፎንያስ
ማለት እግዚአብሔር ሰውሮአል ማለት ነው። አብድዩ ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ማለት ነው። ሕዝቅኤል ማለት
እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጣል ማለት ነው። ዮሐንስ ማለት የእግዚአብሔር ጸጋ ማለት ነው። ናትናኤል ማለት
የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው። ቤተክርስቲያን የልጅነትን ጥምቀት በምታጠምቅበት ጊዜ ስመ ክርስትና የምትሰጠው
ለዚህ ነው።

፬፥፯ መማጸኛ ነው።


እግዚአብሔር ከሚለመንባቸው መንገዶች አንዱ በቅዱሳን ስም የሚቀርብ ተማኅጽኖ ነው። የወዳጆቹን ስም እየጠራን
ስንማጸነው ይለመነናል። እርሱ ራሱ ያከበረው የቀደሰው ስም ነውና። በመሆኑም ስማቸው ብቻ ስለተጠራ በረከት አለ። ክፉ
የሚባል ሰው እንኳ በሚወደው በአባቱ፥ በእናቱ፥ በልጁ ስም ሲማጸኑት ይለመናል። ሞተውም ከሆነ «በአባትህ አጥንት፥
በእናትህ አጥንት፥ በልጅህ አጥንት» ይሉታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአተኞችና በደለኞች ብቻ ሳይሆኑ ቅዱሳንም በቅዱሳን ስም ሲማጸኑ፥ የቅዱሳንን ስም መማጸኛ
ሲያደርጉ ታይተዋል። ነቢዩ ኤልያስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ በጸሎት ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ዝናብ ለዘር ጠል ለመከር
ከከለከለ በኋላ፦ እግዚአብሔር «ሂድና ለንጉሡ ለአክዓብ ተገለጥለት፤» አለው። በሰማርያ ራብ ጸንቶ ነበር። አከዓብም
ኤልያስን ባየው ጊዜ «እስራኤልን የምትገለባብጥ (ከባሕር እንደወጣ ዓሣ በውኃ ጥም የምታገላብጠው፥ ወፍራሙን ቀጭን፥
ቀዩን ጥቁር፥ ጥቁሩን ነጭ የምታደርገው አንተ ነህን?» አለው። ኤልያስም «እግዚአብሔርን ትታችሁ በዓሊምን
የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እን ጂ እኔስ እስራኤልን አልገለባብጥም። አሁንም ወደ እስራኤል ሁሉ ልከህ
አራት መቶ ሃምሣ ነቢያተ ሐሰትን፥ አራት መቶ የማምለኪያ ዐፀድ ነቢያትን ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ፤ »
አለው። የንጉሥ ትእዛዝ ነውና እነርሱም ሕዝቡም ተሰበሰ ቡ።

ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሕዝቡ ቀርቦ፦ «እስከ መቼ በሁለት ልብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፥
በዓልም አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤» ብሎ ወቀሳቸው። አንዲት ቃል እንኳ አልመለሱለትም። ቀጥሎም፦
«ከእግዚአብሔር ነቢ ያት አንድ እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ እነርሱ ግን ስምንት መቶ ሃምሣ ናቸው። ሁለት ወይፈኖች ይስጡንና
መሥዋዕት እንሠዋ፤ እነርሱም የአምላካቸውን ስም ይጥሩ፥ እኔም የፈጣሪዬን የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም
በእሳት የሚመልስ እርሱ አምላክ ይሁን፤» አላቸው። ሕዝቡም «ይህ ነገር መልካም ነው፤» አሉ።

ኤልያስ የበዓልን ነቢያት፦«እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፥ የአምላካችሁንም ስም
ጥሩ፥ በበታቹም እሳት አትጨምሩ፤» አላቸው። መሥዋዕታቸውን አዘጋጅተው «በዓል ሆይ፥ ስማን፤» እያሉ ቢጮኹ፥
መሠዊያውን እየዞሩ ቢያነክሱ ሰሚ ጠፋ። ለወትሮው ቀረብ በሎ «አቤት» የሚላቸው ሰይጣን የእግዚአብሔር ሰው ኤልያስ
ስላለ መቅረብም ድ ምፅ ማሰማትም አልቻለም። የራሱን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ክብር የሚፈልግ ኤልያስም፦ «አምላክ
ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፥ ምናልባት ጨዋታ ይዞ ወይም አሳብ ይዞት ወይም ተኝቶ እንደሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል።»
እያለ ይዘብትባቸው ጀመር። በታላቅ ቃል እየጮኹ፥ እንደልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ገላቸውን ቢቧጭሩ፥ እስከ
ሠርክ ድረስ ትንቢት ቢናገሩ፥ የሚመልስና የሚያዳምጥ አልነበረም።
ነቢዩ ኤልያስ እነርሱን፦ «እንግዲህስ ወዲያ በቃችሁ ወግዱ፥ሂዱም፤ እኔም መሥዋዕቴን እሠዋለሁ።» ካላቸው በኋላ፦
በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ አሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ መሠዊያ ሠራ። የፈረሰውንም መሠዊያ አደሰ። በመሠዊያው
ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጉድጓድ ቈፈረ። በመሠዊያው ላይ እንጨት ደረደረ። ወይፈኑንም በብልት በብልት
ቆርጦ በእንጨቱ ላይ አኖረ። ጉድጓዱ ሞልቶ ውኃው በመሠዊያው ዙሪያ እስኪፈስስ ድረስ አሥራ ሁለት ጋን ውኃ
አስፈሰሰበት። በመጨረሻም፦ «አቤቱ የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ ሆይ! ስማኝ፤ ዛሬ በእሳት ስማኝ፤» ብሎ
በቅዱሳን አባቶቹ ስም ተማጸነ። እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወረደች፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ እንጨቱንም፥
ድንጋዩንም በላች፤ (አቃጠለች)፤በጉድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ አፈሩንም ላሰች። ሕዝቡም በግምባራቸው ተደፍተው፦
«እግዚአብሔር በእውነት እርሱ አምላክ ነው፥ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው፤» አሉ። ፩ኛ ነገ ፲፰፥፩-፵።

እስራኤል ዘሥጋ በግብፅ ሳሉ ከባርነት የተነሣ አልቅሰው ጮኸው ነበር፤ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር
ወጣ። እግዚአብሔርም ጩኸታቸውን ሰማ። የጮኹት በአባቶቻቸው በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ስም ነው።
እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይሰሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አስቦ ጐበኛቸው ታወቀላቸውም። ዘጸ
፪፥፳፫-፳፭።

ነቢዩ ኤልያስ በእሳት ፈረሶች በሚሳብ በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ መጠምጠሚያውን ለኤልሳዕ ጣለለት።
በኤልሳዕም ራስ ላይ ዐረፈ። ኤልሳዕም ተመልሶ በዮርዳኖስ ዳር ቆመ። በራሱ ላይ ያረፈችውን የኤልያስን መጠምጠሚያ
ወስዶ ወኃውን መታባት፦ ውኃው ግን አልተከፈለም። ያልተከፈለው ዝም ብሎ በመምታቱ ነው። በኋላ ግን «የኤልያስ
አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? እንዴትስ ነው?» እያለ በመምህሩ ስም እየተማጸነ ቢመታው ዮርዳኖስ ለሁለት
ተከፍሎለታል። ፪ኛ ነገ ፪፥፩-፲፬።

ነገረ ቅዱሳን (ክፍል፫)

                                   ፭ ቤተመቅደስ
 አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት የእግዚአብሔር ቤት ቅዱስ ነው። ይኸውም በሰማይ ባለ ቤተ መቅደስ አምሳል
የተሠራ ነው። እግዚአብሔር ደብረ ሲናን በእሳት መጋረጃ ጋርዶ ለሙሴ ሰማይን ከፍቶ (ምሥጢር ገልጦ) ካሳየው በኋላ፦
«መቅደ ስ ትሠራልኛለህ፥ በመካከላችሁም አድራለሁ። በተራራው እንዳሳየሁህ ሁሉ፥ እንደማደሪያው ምሳሌ፥ እንደ
ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ ለእኔ ትሠራለህ፤ እንዲሁ ትሠራለህ።» ብሎታል። ዘጸ ፳፭፥፲።

          ፭፥፩፦ ደብተራ ኦሪት፤


 
እግዚአብሔር መንፈሱን በባስልኤልና በኤልያብ አሳድሮ ማስተዋልን ዕውቀትንና ጥበብን ሰጥቷቸው ደብተራ ኦሪትን
ሠርተዋል ዘጸ ፴፩፥፩-፲፩። ይህ የድንኳን ቤተ መቅደስ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ተቀብቶ ቅዱስ እንደሚሆንም አስቀድሞ
ለሙሴ የነገረው እግዚአብሔር ነው። ዘጸ ፴፥፳፮። ይህም ይታወቅ ዘንድ ታቦት ባለበት በዚህ ቅዱስ ስፍራ እግዚአብሔር
በደመና ዓመድ ይገለጥ ነበር። ሙሴም ወደ ድንኳን በገባ ጊዜ ዓምደ ደመና ይወርድ ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን
ይናገረው ነበር። ሕዝቡም ሁሉ ዐምደ ደመናው በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ
በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር፤ እግዚአብሔርም፥ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር
ነበር። ዘጸ ፴፫፥፯-፲፩።
፭፥፪፦ ሕንፃ ቤተ መቅደስ፤
ንጉሥ ዳዊት በዘመኑ ሕንፃ ቤተ መቅደስ ለማነጽ ቢፈልግም እግዚአብሔር አልፈቀደለትም። ቢሆንም እንዲያንጽ
ለተፈቀደለት ለልጁ ለሰሎሞን፦ ወርቁን፥ ብሩን ፥ የከበረውን ድንጋይ ፥ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ አደራ ሰጥቶታል።
፩ኛዜና ፳፪፥፩-፲፮። ሰሎሞንም እግዚአብሔር ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት በአሞሪያ ተራራ ዳዊት ባዘጋጀው ስፍራ
በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤት ሠራ። ፪ኛ ዜና ፪-፲፯። ቅዳሴ ቤቱም ሲከበር ንጉሡ
ሰሎሞን ጸሎቱን በእግዚአብሔር  ፊት አቀረበ። እሳት ከሰማይ ወርዶ የሚቃጠለውን ቁርባን መሥዋዕቱን ሁሉ በላ፤ ይህም
የአዲስ ኪዳን መሥዋዕት እሳተ መለኰት የተዋሀደው ለመሆኑ ምሳሌ ነው። የእግዚአብሔርም ክብር ቤተ መቅደሱን
ሰለሞላው ካህናቱ በዚያች ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም። የእስራኤልም ልጆች እሳቱንም ክብሩንም ባዩ
ጊዜ ድንጋይ በተነጠፈበት ምድር ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። «እርሱ ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤»
እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ፪ኛ ዜና ፯፥፩-፫።
 በመጨረሻም እግዚአብሔር ለሰሎሞን በሌሊት ተገልጦ፦ «ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህንም ስፍራ ለራሴ ለመሥዋዕት ቤት
መርጫለሁ። --- አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ
ለዘለዓለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፥ ቀድሻለሁም። ዐይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናል።» በሎታል።
፪ኛ ዜና ፯፥፲፪-፲፮። ቤተ መቅደሱ በፈረሰ ጊዜም እግዚአብሔር  እንደፈረሰ ይቅር አላለም። «ይህ ሕዝብ የእግዚአብሔር ቤት
የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም ይላል። በውኑ ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ እናንተ ራሳችሁ በተሸለሙ ቤቶቻችሁ ለመኖር ጊዜው
ነውን?» በማለት በነቢዩ በሐጌ አድሮ ወቀሳቸው። ያጡትንም ጸጋ ሲነግራቸው፦ «እስኪ በልባቸሁ መንገዳችሁን አስቡ።
ብዙ ዘራችሁ፥ ጥቂትም አገባችሁ፤ በላችሁ፥ ነገር ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ፥ ነገር ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ፥ ነገር
ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዙን የተቀበለም በቀዳዳ ከረጢት ሰበሰበ።»ብሏቸዋል። ከዚህም አያይዞ፦ “በልባችሁ መንገድ
አስቡ ፥ ወደ ተራራው ውጡ ፥ እንጨትንም ቁረ ጡ ፥ ቤትንም ሥሩ ፥ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል ፥ እመሰገናለሁም ።”
ሲል አዟቸዋል ። ሐጌ ፩ ፥ ፪-፫ ። በመጨረሻም  “በርቱና ሥሩ ፥ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ ፤ . . . ከፊተኛው ይልቅ የዚህ
የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል ፤ . . . በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ ፤ . . . ይህን ቤተ መቅደስ ከፍ ለማድረግ
ለምትሠራ ሰውነት ሁሉ ሰላምን እሰጣለሁ ።” የሚል ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል ። ሐጌ ፪ ፥ ፩ - ፱

፭፥፫ ፦ የአዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ፤


አዲስ ኪዳንን በደሙ ያጸና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በምሴተ ሐሙስ ፦ “ስትዩ እምኔሁ
ኩልክሙ ፥ ዝ ውእቱ ደምየ ዘሐዲስ ሥርዓት ፥ ዘይትከዓው በእንተ ብዙኃን ለኅድገተ ኃጢአት ። ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ
፤ ኃጢአትን ስለማስተስረይ ፥ ስለብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው ።” ያላችው ለዚህ ነው። ይኸውም የአዲስ
ሕግ የወን ጌል ፥ የአዲስ ርስት የመንግሥተ ሰማያት መጽኛ ነው ማለት ነው ። በመሆኑም ሕገ ወንጌል ባለማለፍ ጸንታ
የምትኖረው በሥጋውና በደሙ ነው ። የማታልፍ ርስት መንግሥተ ሰማያትም የምትወረሰው በሥጋውና በደሙ ነው ።
“የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋውን ካልበላችሁ ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ ፥ ለእናንተ ሕይወት የላችሁም ብዬ
በእውነት እነግራችኋለሁ። ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የማታልፍ መንግሥተ ሰማይን ይወርሳል። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ፥
ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ። ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ከእኔ ጋር ተዋሕዶ ይኖራል፥ እኔም አድሬበት (እሳት ብረትን
እንዲዋሀደው በጸጋ ተዋህጄው) እኖራለሁ ።” እንዳለ ። ዮሐ ፮ ፥ ፶፫ -፶፮። ይህም ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ነው
። የሚሰናዳው ፥ የሚፈተተውና የሚታደለው በአዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ በቤተክርስቲያን ነው ። ከዚህም ጋር እግዚአብሔር
፦ በመዝሙር፥ በቅዳሴ፥ በማኅሌት ይመሰገንበታል ። በአጠቃላይ አነጋገር በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ
የሚታደልባቸው ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይፈጸምበታል ። እነዚህም ጥምቀት ፥ ሜሮን ፥ ቁርባን ፥ ክህነት ፥
ተክሊል ፥ ንስሐ ፥ ቀንዲል ናቸው ።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በአርባ ቀኑ በሕገ ኦሪት የተጻፈውን ሥርዓት ይፈጽሙለት
ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ወስደውታል ። ሉቃ ፪ ፥ ፳፪ -፳፬ ። ዓሥራ ሁለት ዓመት በሞላው ጊዜም እንደ አስለመዱ ወደ
ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ጠባቂዋ፥ ዘመዷ፥ አረጋዊ ፥ ጻድቁ ዮሴፍ በየዓመቱ
ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር ። በዓሉን ካከበሩ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም
ቀርቶ ነበር። ያገኘው ሁሉ በፍቅር ይነጣጠቀው ስለነበር እመቤታችን እና ጠባቂዋ ዮሴፍ የሆነውን አላወቁም። በደረሱም
ጊዜ ዕለቱን ፈልገው ስለአላገኙት እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በሦስተኛው ቀን በሊቃውንት መካከል ተቀምጦ
ሲሰማቸው ሲያሰማቸው፥ ሲጠይቃቸው ሲመልስላቸው አገኙት። ጥያቄውን እና ምላሹን የሰሙት ሁሉ ያደንቁት ነበር።

እናቱ እመቤታችን፦ «ልጄ ለምን እንዲህ አደረግኸን? እኔና አረጋዊው ዮሴፍ ስንፈልግህ ሦስት ቀን ደከምን።» አለችው።
«ወይቤሎሙ ለምንት ተሐሥሡኒ እያእመርክሙኑ ከመ ይደልወኒ አሀሉ ውስተ ዘአቡየ ቤት። ለምን ትፈልጉኛላችሁ?
በአባቴ ቤት ልኖር እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?» አላቸው። በዚህም ቤተመቅደሱን የአባቴ ቤት አለው። ሉቃ ፪፥፵፩-፵፱።
በዕለተ ሆሣዕናም ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ፦ «ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ
አደረጋችኋት።» በማለት ሻጮችንና ለዋጮችን አስወጥቷቸዋል። ሉቃ ፲፱፥፵፭=፵፮።

ቅዱሳን ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሰዓት ጠብቀው ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ ይጸልዩ፥ በዚያም ተአምራት
ያደርጉ ነበር የሐዋ ፫፥፩-፲ ይኸውም በየትም ሥፍራ ከሚጸለይ ጸሎት በቤቱ የሚጸለይ ጸሎት ስለሚበልጥ ነው።
እግዚአብሔር አንድ ጊዜ፦ «አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዐይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ።» ብሏልና።
፪ኛ ዜና፥፲፭ ። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ቤተ መቅደስ በተመስጦ ይጸልይ የነበረው ለዚህ ነው። ይኸንንም፦ «ወደ ኢየሩሳሌም
ከተመለስሁ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ።» በማለት ገልጦታል። የሐዋ ፳፪፥፲፯። ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ የቤተ
መቅደሱ ክብር በሰማይ ስለተገለጠለ ት፦ «በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ
ታየ፤» ብሏል። ራእ ፲፩ ፥፲ ፱። በተጨማሪም፦ «ከዚህ በኋላ አየሁ፥ የምስክሩ ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ።» በማለት
ነገሩን አጽንቶታል።
እንግዲህ በብሉይ ኪዳንም በአዲስ ኪዳንም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ቅዱስ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ንጉሡ ሰሎሞን፦
«የእግዚአብሔር ታቦት የገባችበት ስፍራ ቅዱስ ነው።» ያለው ለዚህ ነውና። ፪ኛ ዜና ፰ -፲፩ ። ከሁሉም በላይ ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አካሉን በቤተ መቅደስ መስሏል። ቤተ መቅደሱን ከሻጮችና ከለዋጮች ባጸዳ
ጊዜ ደቀመዛሙርቱ፦ «የቤትህ ቅናት በላኝ፤» የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ አሰቡ። መዝ ፷፰፥፱። አይሁድ ግን፦ «ይህን
የምታደርግ ምን ምልክት ታሳየለህ?» አሉት። ኢየሱስም፦ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ፤»
ብሎ መለሰላችው። አይ ሁድም፦ «ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፥ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ
ታነሣዋለህን?» አሉት። እርሱ ግን ይህን የ ተናገረው ቤተ መቅደስ ስለተባለ ሰውነቱ ነበር። ዮሐ ፪፥፲፮-፳፩።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እኔ ክርስቶስን መስየዋለሁ፤»፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩ እንዳለ፦ ክርስቶስን መስለው የተገኙ ቅዱሳንም
አካላቸው በቤተ መቅደስ ተመስሏል። ይኸንንም፦ «የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ
እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።» በማለት ገልጦታል።

፭፥፬፦ ስግደት በቤተ መቅደስ፤


በብሉይም በአዲስም እንደተገለጠው የእግዚአብሔር ቤት ቅዱስ ነው። እንደማንኛውም ቤት ስለአልሆነ ቅዱስ ተብሎ
ይቀጸልለታል። በመሆኑም ከሩቅ መሳለም ከቅርብ መስገድ ይገባል። «ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፥ ስለ ምሕረትህና ስለ
እውነትህም ስምህን አመሰግናለሁ።» እንዲል፤ መዝ ፻፴፪፥፪። «በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፤» የሚልም አለ።
መዝ ፳፰፥፪። በተቀደሰ ስፍራ መስገድ እንዲገባ መንገዱን ያሳየ እግዚአብሔር ነው። በደብረ ሲና ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ፦
«ወደዚህ አትቅረብ፥ አንተ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ።» ብሎታል። በዚህም
ለምድሪቱ ቅድስት ብሎ እንደቀጸለላት እናስተውላለን። ዘጸ ፫፥፭። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለኢያሱ ወልደ ነዌ
በተገለጠለት ጊዜ፦ «አንተ የቆምህበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ፤» በማለት ነግሮታል። እርሱም
መሬቱን ቅዱስ ብሎታል። ቂያ ፭፥፲፭። ሙሴም ኢያሱም በቅድስናው ስፍራ ጫማቸውን አውልቀው ሰግደዋል።
የአዲስ ኪዳን ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስም በበኲሉ፦ ጌታ ክብረ መንግሥቱን፥ ግርማ መለኰቱን የገለጠበትን፤ ምሥጢር
ሥላሴ በገሀድ የታየበትን፤ ሙሴ ከመቃብር ተነሥቶ ኤልያስ ከሰማይ ወርዶ የጌታን የባህርይ አምላክነት የመሰከሩበትን
ተራራ ደብረ ታቦርን «ቅዱስ» ብሎታል። «የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን  ኃይሉንና መምጣቱን ስናስተምራችሁ
የተከተልነው የፍልስፍና ተረት አይደለምና፥ የእርሱን ገናንነት እኛ ራሳችን አይተን ነው እንጂ። ከገናናው ክብር፦ በእርሱ ደስ
የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ
አድርጓልና። (ከእርሱ ጋር ትክክል የሆነ ክብሩን፥ ምስጋናውን ፥ የባህርይ አባቱ አብ ልጄ በማለት መስክሮለታልና)። ይህንም
ቃል እኛ በተቀደሰው ተራራ (በደብረ ታቦር) አብረነው ሳለን ከሰማይ እንደወረደለት ሰምተነዋል።» በማለት ከነምክንያቱ
አብራርቷል። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፮።

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፬


፮፦ ቅዱሳት ንዋያት፤
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በውስጥ በአፍአ የምንገለገልባቸው ንዋያት (እቃዎች) የተቀደሱ ናቸው። ለዓለ ማዊ ወይም
ለሥጋዊ አገልግሎት አንጠቀምባቸውም። ለእግ ዚአብሔር የተለዩ ናቸው። «በቀማሚም ብልሃት እንደተሠራ ቅመም
የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል። የምስክሩንም ድንኳን፥ የምስ ክሩንም ታቦት፥
ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም፥ ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን
መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ። ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፤ ቅድስተ
ቅዱሳንም ይሆናሉ፥ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤» ይላል። ዘጸ ፴፥፳፭-፳፱። በአዲስ ኪ ዳንም አዲስ ቤተ መቅደስ
ተሠርቶ የሚከብረው ፥ ቅዱሳት ንዋያትም የሚከብሩት ፥ ቅብዐ ሜሮን እየተቀቡ ነው። በመሆኑም፦ ታቦቱ ፥ መንበሩ ፥
ጻሕሉ ፥ ዐውዱ ፥ አጎበሩ ፥ እርፈ መስቀሉ ፥ ጽዋው ፥ መቊረርቱ ፥ ብርቱ ፥ ከበሮው ፥ ጸናጽሉ ፥ መቋሚያው ፥ ጃንጥላው
፥ ድባቡ ፥ ምንጣፉ ፥ መጋረጃው ፥ መነሳነሱ ፥ መቅረዙ ፥ አትሮንሱ ፥ ሙዳዩ ፥ መሰቦ ወርቁ ሁሉም የተቀደሱ ናቸው።

፯፦ ቅዱሳት አልባሳት፤
በእግዚአብሔር ቤት ካህናት ለብሰውት የሚያገለግሉበት አልባሳት ሁሉ የተቀደሱ ናቸው። በሥጋዊ ልብስ እግዚአብሔር
አይገለገልም። ለእግዚአብሔር የተለዩ መንፈሳውያት አልባሳት አሉ። «አንተም ወንድምህን አሮንን  ከእርሱም ጋር ልጆቹን
ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን ፥ የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፥
አብድዩንም፥ አልዓዛርንም፥ ኢታምርንም፥ አቅርብ። የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለመለያ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን
ሥራለት። አንተም የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። እነርሱም ካህን ሆኖ
እንዲያገለግለኝ ለአሮን ለቤተ መቅደስ የሚሆን የተለየ ልብስ ይሥሩ። የሚሠሯቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ
እንግድዐ፥ ልብሰ መትከፍ፥ ቀሚስም፥ ዥንጉርጉር እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያ፥ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት
ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፥ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም
ይውሰዱ።» ይላል። እግዚአብሔር ለሙሴ የነ ገረው አሠራሩን ጭምር ነው። ዘጸ ፳፰፥፩-፲፬። በነቢዩ በሕዝቅኤልም አድሮ፦
«ወደ ውጭውም አደባባይ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን (ልብሰ ተክህኖውን) ያውልቁ፤ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት
ያኑሩት፤ ሕዝቡን በልብሳቸው እንዳይቀደሱት ሌላውን ልብስ ይልበሱ።» ብሏል። ይህም ልብስ ተክህኖ ለብሶ ዓለማዊ ቦታ
መገኘት እንደማይገባ ያስረዳል። ሕዝ ፵፬፥፲፱። በመ ሆኑም፦ ቀሚሱ ፥ ካባ ላንቃው ፥ መጎናጸፊያው ፥ ቀጸላው ፥ ሞጣህቱ
፥ አክሊላቱ ፥ ቆቡ ፥ ማኅፈዳቱ ሁሉም የተቀደሱ ናቸው።

፰፦ጻድቅ
 ጻድቅ፦ እውነተኛ ማለት ነው። በመሆኑም ጻድቅ እግዚአብሔር ነው። «በእውነትህ ቀድሳቸው፥ ቃልህ እውነት ነው፤»
እንዲል ፥ እውነት የባህርይ ገንዘቡ ነው። ዮሐ ፲፯ ፥፲፯። እርሱ የእውነትና የሕይወት መንገድ ነው። ዮሐ ፲፬፥፮። ጸጋንና
እውነትን የተመላ ነው። ዮሐ ፩፥፲፩። «ኦሪት በሙሴ ተሰጥታን ነበርና፥ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን፤ »
የተባለው ለዚህ ነ ው። ዮሐ ፩ ፥፲፯ ይኸንን በተመለከተ በመጽሐፈ ዕዝራ፦ « አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ ፥ አንተ ጻድቅ
ነህ፤ » የሚል አለ። ዕዝ ፱፥፲፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ግዳጁን አንደጨረሰ፥ የሚያርፍበት ዕድሜ እንደደረሰ፥
መልካሙን ገድል እንደተጋደለ፥ ሩጫውን እንደፈጸመ፥ ሃይማኖቱንም እንደጠበቀ ከተናገረ በኋላ፦ «እንግዲህስ የጽድቅ
አክሊል ይቆየኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱ
ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።» ብሏል። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፮-፰

፰፥፩፦ ጻድቃን፤
አካኼዳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ያደረጉ፥ ሃይማኖት ይዘው ፥ ምግባር ሠርተው የተገኙ ሰዎች ጻድቃን ይባላሉ። እነኚህም
በነገር ሁሉ እውነተኞች ሆነው የተገኙ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ስለ ኃጥአን እና ስለ ጻድቃን በተናገረበት አንቀጽ፦
«ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ እርሱ በደልን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአት በደል ናትና። (ጥቃቅኑን ኃጢአት የሚሠራ ወደ
ታላላቁም ኃጢአት ተስቦ ይበድላል፥ ሁለቱም ከመንግሥተ ሰማያት በማውጣት አንድ ናቸው)። እርሱም ኃጢአትን
ያስወግድ ዘንድ እንደተገለጠ ታውቃላችሁ፥ በእርሱም ኃጢአት የለም። በእርሱ የሚኖር ሁሉ አይበድልም፥ (አንድ ጊዜ
ቢበድል ሁለተኛ፥ በሥጋ ቢበድል በነፍስ፥ በሐልዮ ቢበድል ፥ በነቢብ በገቢር አይበድልም)፥ የሚበድልም ሰው አያየውም፥
አያውቀውምና። (አያምነውምና፥ አይወደውምና)። ልጆቼ ሆይ ማንም አያስታችሁ፤ (ጥቃቅኑ ኃጢአት ወደ ታላላቁ ኃጢአት
አያደርሷችሁም፥ ጥቃቅኑና ታላላቁ ከመንግሥተ ሰማያት በማውጣት አንድ አይደሉም፥ በማለት ማንም አያታላችሁ)፤ እርሱ
ጻድቅ እንደሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፫፥፬-፯።
 በብሉይ ኪዳን፦ «የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው፤ ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ፥ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ
አሰኘው፤» ተብሎ ለኖኅ ተጽፎለታል። ዘፍ ፮፥፱። እግዚአብሔርም፦ «በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።»
ሲል መስክሮለታል። ዘፍ ፯፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ተነሥቶ፦ «ኖኅም ሰለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ
ፈራ፥ ቤተሰቡንም ያድን ዘንድ ክፍል ያላትን መርከብ ሠራ፥ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ
ወራሽ ሆነ።» በማለት ተናግሮለታል። ዕብ ፲፩፥፯።

ቅዱስ ዳዊት ጻድቃንን በተመለከተ ብዙ ተናግሯል። በተለይም የጸጋቸውንና የክብራቸውን ብዛት ሲናገር፦ «ጻድቅሰ ከመ
በቀልት ይፈሪ። ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል።»ብሏል። መዝ ፺፩፥፲፪ ዘንባባ አድጐ ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ እንደሚል ፥
የጻድቅም ጸጋው ክብሩ ከፍ ያለ ነው፥ ሰማያዊ ነው። የዘንባባ ፍሬው ብዙ እንደሆነ የጻድቅም ጸጋው ክብሩ ብዙ ነው፤
ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ ዘንባባ የደስታ ምልክት ነው። አብርሃም ይስሐቅን፥ ይስሐቅ ደግሞ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፤
እስራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት ከግብፅ በወጡ ጊዜ ዘንባባ ይዘው አመስግነዋል። ጻድቃንም የደስታ ምልክት ማለትም
ሰውንም እግዚአብሔርንም ደስ ያሰኙ ናቸው። ዘንባባ የድል ምልክት ነው። ዮዲት የእስራኤልን ጠላት ሆሎፎርኒስን
በገደለችው ጊዜ የእስራኤል ሴቶች ተሰብስበው መርቀዋታል፥ በዓልም አድርገውላታል። እርሷም ለእያንዳንዳቸው ዘንባባ
አድላቸዋለች። ዮዲ ፲፭፥፲፪። ጻድቃንም ፍትወታት እኲያትን፥ ርኲሳት መናፍስትን ድል ያደረጉ ናቸው። ዘንባባ የሰላም
ምልክት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ዘንባባ
ይዘው ተቀብለውታል። ዮሐ ፲፪፥፲፫። ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ቢቻላችሁ በእናንተ በኲል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።» እንዳለ
ሮሜ ፲፪፥፲፰ ጻድቃንም ለጠላቶቻቸውም ጭምር የሰላም ሰዎች ነበሩ። ሰላምን ሲሹ ሰላምን ሲከተሉ የኖሩ ናቸው። መዝ
፴፫፥፲፬።
 ቅዱስ ዳዊት መንግሥተ ሰማያት የጻድቃን መሆኗንም ተናግሯል። ምክንያቱም የጸጋና የክብር መጨረሻ መንግሥተ ሰማያት
ናትና። «አርኀዉ ሊተ አናቅጸ ጽድቅ፥ እባእ ውስቴቶን ወእግነይ ለእግዚአብሔር። ዛ አንቀጽ እንተ እግዚአብሔር፥ ጻድቃን
ይበውኡ ውስቴታ። የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፥ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግን ዘንድ። ይህች የእግዚአብሔር
ደጅ ናት፥ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።» ብሏል። መዝ ፻፲፯፥፲፱። ይህም ከዚያ ገብቼ ለእግዚአብሔር እገዛ ፥ እር ሱንም
አገለግል ዘንድ ፥ የኢየሩሳሌምን አንድም የቤተ መቅደስን አንድም የገነትን ደጆች ክፈቱልኝ። ይህች የኢየሩሳሌም አንድም
የቤተ መቅደስ አንድም የገነት ደጆች የእግዚአብሔር ናት። (የእግዚአብሔር በረከትና ሕይወት የታዘዘባት ናት)። ጻድቃን
ይወርሷታል፥ ማለት ነው። በሌላ አንቀጽም፦ «ጻድቃንሰ ይወርስዋ ለምድር፥ ወይነብሩ ውስቴታ ለዓለም ዓለም። ጻድቃን
ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ። » ብሏል። ምድር ያለውም፦ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር የተባለችውን፥
ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ያያትን መንግሥተ ሰማያትን ነው። ራእ ፳፩፥፩።

  ወልደ ዳዊት ንጉሥ ሰሎሞንም በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ስለ ጻድቃን ብዙ ተናግሯል።


-       ስለ በረከት፦ «በረከተ እግዚአብሔር ውስተ ርእሰ ጻድቃን። የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ነው።»

-       በመታሰቢያቸው እለት ልዩ ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ፦ «ዝክረ ጻድቅ ምስለ ውዳሴ። የጻድቅ መታሰ ቢያ ከምስጋና ጋር


ነው።»

-       ስለ አንደበታቸው « ነቅዓ ሕይወት ውስተ አፈ ጻድቃን፤ የሕይወት ምንጭ በጻድቃን አፍ ነው፤ (የሕይወት መገኛ የሚሆኑ
ሕግጋተ እግዚአብሔር በእነርሱ አፍ ሲነገር ይኖራል።)

-       ስለ ደመወዛቸው፦ «ግብረ ጻድቃን ሕይወቱ ይገብር፤ የጻድቃን ሥራ ሕይወትን ያደርጋል፤ (የድካማቸው ዋጋ ሕይወት
ነው፤)»

-       ስለነገራቸው ጽሩይነት፦ «ብሩር ርሱን ልሳነ ጻድቅ፤ የጻድቅ ምላስ (ነገራቸው) የተፈተነ (የነጠረ) ብር ነው፤»
-       ሀብተ ትንቢት እንደተሰጠቸው፦ «ከናፍረ ጻድቃን የአምራ ነዋኃ፤ የጻድቃን ከንፈሮች የሩቁን ያውቃሉ፤ (መጻእያትን
ይናገራሉ)፤»

-       በረከታቸው ሁሉን ባዕለጸጋ እንደምታደርግ፦ «በረከተ እግዚአብሔር ውሰተ ርእሰ ጻድቃን ፥ ይእቲ ታብእል፤


የእግዚአብሔር በረከት በጻድቃን ራስ ላይ ሆና ባለጠጋ ታደርጋለች፤»

-       ስለ ምኞታቸው፦ «ፍትወቱ ለጻድቅ ሥምርት በኀበ እግዚአብሔር። የጻድቅ ምኞቱ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደች
ናት፤»

-       ከኃጢአት ፈጽመው ተለይተው እንደሚኖሩ፦ «ጻድቅሰ ተግሂሦ ለዓለም ይድኀን፤ ጻድቅ ግን ተሰውሮ ለዘለዓለም


ይድናል፤»
               
-       ደስታ እንደማይለያቸው፦ «ትጐነዲ ተፍሥሕት ምስለ ጻድቃን፤ ተድላ ደስታ ከጻድቃን ጋር ትኖራለች፤»

-       በምንም እንደማይናወጡ፦ «ጻድቅሰ ለዓለም ኢይኤብስ፤ ጻድቅ ሰው ለዘላለም አይናወጥም፤ (አይበድልም)፤»


-       ጥበብ መንፈሳዊ ከአንደበታቸው እንደማይለይ፦ «አፈ ጻድቃን ይነብብ ጥበበ፤ የጻድቃን አፍ ጥበብን ይናገራል፤»

-       ስለ ዕውቀታቸው፦ «ወከናፍረ ጻድቃን ያውኀዝ ሞገሰ፤ የጻድቃን ከንፈሮች ሞገስን ያፈስሳሉ፤ (የተወደደ ዕውቀትን
ይናገራሉ)፤» በማለት ተናግሯል። ምሳ ፲፥፩-፴፪።

በአዲስ ኪዳን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ስለ ካህኑ ዘካርያስና ስለ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ጽድቅ በወንጌሉ መጀመሪያ መስክሯል።
«በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአቢያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ። ሚስቱም ከአሮን ልጆች ወገን
ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ። በእግዚአብሔር ሥርዓትና በትእዛዙ ሁሉ
ያለ ነውር የሚሄዱ ነበሩ ልጆችም አልነበራቸውም፥ ኤልሳቤጥ መካን ነበረችና፥ ዘመናቸውም አልፎ ነበር።» ብሏል። ሉቃ
፩፥፭-፯። የሊቀ ካህናቱ የአሮን ሚስት ስሟ ኤልሳቤጥ ትባል ነበር። እርሷ ሳለች ኦሪት ተሠርታለች። በኋለኛዋ ኤልሳቤጥ ግን
አልፋ ወንጌል ተሠርታለች። በኤልሳቤጥ የተሠራች ሕግ በኤልሳቤጥ አለፈች ለማለት ኤልሳቤጥን ጠቅሷል። ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ ደግሞ፦ «የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ፤» ብሏል። ሮሜ ፰ ፥ ፴። ከሁሉም በላይ ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፦ «ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።» በማለት ስለ
ጻድቃን ተኗግሯል። ማቴ ፲፥፵፩።

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፭፤


                        ፩፦ እግዚአብሔርን፤ መምሰል፤ (በተፈጥሮ)፤

«ወይቤ እግዚአብሔር ንግበር ስብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ፤ እግዚአብሔር፦ ዓርብ በነግህ ፥ በእኛ አምሳል፥ በእኛ
አርአያ ሰውን እንፍጠር አለ፤» እንዲል፦ የሰው ልጅ የተፈጠረው በእግዚአብሔር አርአያ፥ በእግዚአብሔር አምሳል ነው፤ ይህም
ታላቅ ቅድስና ነው። «እግዚአብሔርም አለ፤» የሚለው፦ ሥላሴ፦ በመለኰት፥ በሥልጣን፥ በባህርይ፥ በፈቃድ፥ በህልውና
አንድ መሆናቸውን ያስገነዝበናል። «በመልካችን፥ በምሳሌያችን እንፍጠር፤» የሚለው ደግሞ የስም፥ የአካል፥ የግብር
ሦስትነታቸውን ያስተምረናል። ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸውና። አንድነታቸው ሦስትነታቸውን አይጠቀልለውም፥
ሦስትነታቸውም አንድ መሆናቸውን አያጠፋውም። «ምሥጢረ ሥላሴ፤» እንዲል፦ የሥላሴን ነገር ምሥጢር የሚያሰኘው
ይህ ነው። ዘፍ ፩፥፳፮። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴ አዳምን፦

፩-፩፦ አዋቂ አድርገው ፈጥረውታል፤

 እግዚአብሔር አዳምን በነግህ የፈጠረው፥ የንጋት  (የማለዳ) ተከታይ ብርሃን ስለሆነ ነው። ብርሃን የዕውቀት ምሳሌ ሲሆን
ጨለማ ደግሞ የድንቊርና ምሳሌ ነው። ይህም የሚያመለክተው ልበ ብርሃን (አዋቂ) አድርጐ እንደፈጠረው ነው። አባታችን
አዳም እናታችን ሔዋን ከጐኑ ስትፈጠር ማዕከለ ንቃሕ ወንዋም (በመንቃትና በማንቀላፋት መካከል) ነበር። ይህም፦ ፈጽሞ
አልነቃም ፈጽሞም አልተኛም ማለት ነው። በመሆኑም የተሰማውም የታየውም ነገር የለም። ነገር ግን፥ ሔዋን ከወዴት
እንደመጣች አውቆ፦ «ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፥ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።»
ብሏል። ዘፍ ፪፥፳፫። «ሕዝብ ዚይነብር ውስተ ጽልመት፥ ርእየ ብርሃነ ዓቢየ፤ በጨለማ ላሉ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤
(በድንቊርና፥ በቀቢጸ ተስፋ፥ ለነበሩ ሰዎች ዕውቀት ተሰጣቸው)፤» የሚለው ኃይለ ቃልም የሚያስተምረን ብርሃን የዕውቀት
ምሳሌ መሆኑን ነው። ኢሳ ፱፥፩፣ ማቴ ፬፥፲፬። ጻድቁ ካህን ዘካርያስም፦ «ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን
ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤» ብሏል። ሉቃ ፩፥፸፰
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይብራ፤ ያለ እግዚአብሔር፦ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን
ዕውቀት በልባችን አብርቶልናልና፤» ብሏል ፪ኛ ቆሮ ፬፥፱።

፩፥፪፦ የጸጋ አምላክ ፣ ንጉሥ አድርገው ፈጥረውታል፤


አምላክ ማለት ገዥ ማለት ነው፤ አምላክነት የባህርይ ገንዘቡ የሆነ፥ የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
«የጸጋ» ማለት ግን «የሥጦታ» ማለት ነው። «የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን
ሁሉ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ፤» እንዲል፦ ለአዳም ከሰማይ በታች ያለውን ፍጥረት ሁሉ እንዲገዛ ሥልጣን
ሰጥቶታል ዘፍ ፪፥፳፮። አዳምም እንደ ገዥነቱ ለሰማይ አዕዋፋት ለምድር እንስሳትና ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አውጥቶላቸዋል።
ዘፍ ፪፥፲፱። እግዚአብሔር ባወቀ ይሰግዱለትም ነበር። እንኳን እርሱ ፀሐይ እንኳ የተፈጠረው ቀንን እንዲገዛ ነው፥ ጨረቃና
ከዋክብት ደግሞ ሌሊትን እንዲገዙ ነው። መዝ ፻፴፭፥፰።

አዳም ከእግዚአብሔር ከተጣላ በኋላ የማይታዘዙት ሆነው ነው እንጂ ከዚያ በፊት ፍጥረታት ሁሉ ይታዘዙለት ይገዙለት ነበር።
ይህ ጸጋ በቅዱሳን ሕይወት ላይ ታይቷል። ለጻድቁ ለኖኅ እንስሳቱ፥ አራዊቱ፥ አዕዋፋቱ፥ ሁሉም፦ «እሺ በጀ፤» ብለው ወደ
መርከብ ገብተውለታል። ዘፍ ፮፥፳። ለሊቀ ነቢያት ለሙሴ ባሕረ ኤርትራ ታዝዛለታለች። ዘጸ ፲፬፥፳፩ ለኢያሱ ወልደ ነዌ
ፀሐይና ጨረቃ ተገዝተውለታል፤ ፀሐይ ሰዓቷን ጠብቃ የማትጠልቅ ሆነች፥ ጨረቃም ዘገየች። ኢያ ፲፥፲፪። ለነቢዩ ለኤልያስም
ሰማይ ስለተገዛችለት ዝናም ለዘር፥ ጠል ለመከር የማትሰጥ ሆናለች። ፩ኛነገ ፲፯፥፩፣ ያዕ ፭፥፲፯። ሠለስቱ ደቂቅ እሳቱን
ገዝተውታል። ዳን ፫፥፳፯ ለነቢዩ ለዳንኤል ደግሞ አናብስት ተገዝተውለታል። ዳን ፮፥፳፪።

፩፥፫፦ ካህን አድርገው ፈጥረውታል፤

አዳም በገነት እያለ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት፥ አምልኮቱን የሚፈጸምበት በዓት (ቦታ) ነበረው። ሀብተ ክህነት
ተሰጥቶት ስለነበር፦ መሥዋዕት ያሳርግ ነበር። ለዚህም ምስክሩ የነቢያት አለቃ ሙሴ በምድር ቤተ መቅደስ አንዲሠራ
በተነገረው ጊዜ፦ ሥርዓቱን ሁሉ ልክ በሰማይ ቤተ መቅደስ እንዳየው አይነት እንዲያደርገው በማስጠንቀቂያ ጭምር መታዘዙ
ነው። ዘጸ ፲፭፥፲። በሰማይ መሠዊያና መሥዋዕት ፥ ጸሎትና ምልጃም እንዳለ በራእይ ዮሐንስ ተገልጧል። «አምስተኛውንም
ማኅተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለጠበቁት ምስክር የተገደሉትን ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ።
በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ «ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት
ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ለእያንዳንዱም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤» ይላል። ራእ ፮፥፱። በተጨማሪም፦ «ሌላ
መልአክም መጣ፤ በመሠዊያው ፊትም ቆመ፤ የወርቅ ጥናም ይዞ ነበር፤ በዙፋኑ ፊት ባለው በወርቁ መሠዊያም ላይ፥ ለቅዱሳን
ሁሉ ጸሎት እንዲያሳርገው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት
ዐረገ።» የሚልም አለ። ራእ ፰፥፫። ስለዚህ አዳምም በገነት መሥዋዕት የሚያሳርግበት የመሠዊያ ቦታ ነበረው መባሉ ትክክል
ነው። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ፥
አፌንም ዳሰሰበትና፦ እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረ የለህ፥ አለኝ።» ብሏል።
ኢሳ ፮፥፮።

በሌላ በኩል ደግሞ ቀዳማዊ አዳም ለዳግማዊ አዳም፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ በመሆኑ ከዚያ አንፃር የምንረዳው ብዙ ነገር
አለ። ቀዳማዊ አዳም ከድንግል መሬት እንደተገኘ፥ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወልዷል፤ እርሱም
የባህርይ ንጉሥ ነው። ፩ኛ ጢሞ ፩፥፲፯። ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፩። እንደ መልከ ጸዴቅክህነትም የዘለዓለም ካህን ነው ዕብ ፭፥፮፤ ፱፥፲፩።
እንግዲህ አዳም ለክርስቶስ ምሳሌ ሊሆን የቻለው በጸጋ ካህንም ንጉሥም በመሆኑ ነው። መቅድመ ገድለ አዳም ላይ፦ «ዐርብ
ዕለትም ስድስተኛ ቀን ሆነ፤ ፀሐይ ከወጣ በኋላ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አዳምን ፈጠሩት፤ በፊታቸውም ቆመ፥ የሕይወት
እስትንፋስም እፍ አሉበት፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሀብተ ክህነትን፣ ሀብተ መንግሥት፥ሀብተ ትንቢትን ሰጡት።» ይላል።

፩፥፬ ፦ ነቢይ አድርገው ፈጥረውታል፤

ከላይ እንደተገለጠው፦ አባታችን አዳም፦ ሀብተ ትንቢት ተሰጥቶት ስለነበር ፦ የራቀው ቀርቦ ፥
የረቀቀው ጐልቶ እየተገለጠ ለት ትንቢት ይናገር ነበር። በገድለ አዳም እንደተጻፈው ከመሞቱ በፊት ለልጁ
ለሴት፦ «ልጄ ሆይ! በኋላኛው ዘመን ጥፋት ይመጣል ፥ ፍጥረትን ሁሉ ያሰጥማል ፥ ከስምንት ሰው በቀር
የሚቀር የለም። ልጄ ሆይ ! ከልጆቻችሁ የሚቀሩት እኒህ በዚህ ዘመን ከዚህ ቤት ሥጋ ዬን ከእነርሱ ጋር
(ከወርቁ ፥ ከከርቤው ፥ ከዕጣኑ ጋር) ይወስዱታል።» እያለ ነግሮታል። ይህም የኖኅን ዘመን ጥፋት
የሚያመለክት ነበር።

፪፦ ሰባቱ ባህርያት ፤

 «ሰብእ» ማለት ሰባት ማለት ነው። እንዲህም የተባለበት ምክንያት ከሰባቱ ማለትም ከአራቱ ባህርያተ ሥጋና
ከሦስቱ ባህርያተ ነፍስ ስለተፈጠረ ነው። የሰው ልጅ የተፈጠረባቸው አራቱ ባህርያተ ሥጋ የተገኙት፦ አፈር
ከዱዳሌብ ፥ ውሃ ከናጌብ ፥ ነፋስ ከአዜብ ፥ እሳት ከኮሬብ ነው። ሦስቱ ባህርያተ ነፍስ ደግሞ ለባዊነት
(ማሰብ) ፥ ነባቢነት (መናገር) ፥ ሕያውነት (ዘለዓለማዊነት) ናቸው። ሰባት ፍጹም ቁጥር እንደሆነ ሁሉ
ከሰባቱ ባሕርያት የተፈጠረ የሰው  ልጅም ፍጹም ሆኖ ተፈጥሯል።

፫ ፦ በአራቱ ባሕርያተ ሥጋ እግዚአብሔርን መምሰል፤

 እግዚአብሔር አዳምን ከአራቱ ባህርያተ ሥጋ የፈጠረው ፦ በአምላካዊ ባህርዩ ውስጥ አራት ነገሮች እንዳሉ
ለማጠየቅ ነው። እነኚህም፦ ባለጠግነት ፥ ሩኅሩኅነት (ቸርነት) ፥ ከሃሊነት (ሁሉን ቻይነት) ፥ እና ፈታሒነት
(ፈራጅነት ፥ ዳኝነት) ናቸው። በዚህም መሠረት ፦ መሬት የባለጠግነቱ ፥ ውኃ የርኅራኄውና የቸርነቱ ፥ እሳት
የከሃሊነቱ ፥ ነፋስ ደግሞ የፈታሒነቱ ምሳሌ ናቸው።

፫፥፩ መሬት፤

             ባዕለጸጋ የሆነ እግዚአብሔር የመሬትን ብልጽግና አብዝቷል። ቅዱስ ዳዊት፦ «ምድርን ጐበኘሃት ፥
ብልጽግናዋንም እጅግ አበዛህ ፤»  ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፷፬፥፱። በተጨማሪም  ፦ « እግዚአብሔር ይሁብ
ምሕረቶ ፥ ወምድርኒ ትሁብ ፍሬሃ ፤ እግዚአብሔር በጎ ነገርን ይሰጣል ፥ ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች፤»
በማለት ተናግሯል። መዝ ፹፬፥፲፪። ይህም የሁሉ ነገር አስገኝ እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ ፥ ከመሬ ትም
ያልተገኘ ፥ የማይገኝም ነገር የለም ፥ ለማለት ነው። በመሆኑም የሰው ልጅ በመሬትነት ባህርዩ ፥ በባህርዩ
ባዕለጸጋ የሆነውን እግ ዚአብሔርን ይመስለዋል።

፫፥፪ ፦ ውኃ፤

  ውኃ፦ ለእግዚአብሔር ርኅርኄና ቸርነት ምሳሌ ነው። የውኃ ባህርይ እድፍ ማስወገድ ፥ ቆሻሻ ማጥራት
ነው። እግዚአብ ሔርም አይሠሩ ሥራ ሠርተው ፥ በድለው ፦ « አላበጀንም ፥ ማረን ፥ ይቅር በለን፤» ካሉት፦
ሁሉን ይቀበላል ፥ ሁሉን ይምራል፤ ከኃጢአ ታቸው ያነጻቸዋል ፥ ከበደላቸው ያጥባቸዋል። ይኽንንም
የሚያደርገው በውኃ በተመሰለ ርኅራኄውና ቸርነቱ ነው። ቅዱስ ዳዊት ይኽ ንን አውቆ፦ «አቤቱ ፥ እንደ
ቸርነትህ መጠን ማረኝ ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ ፥ ከኃጢ
አቴም አንጻኝ ፤» ብሏል። መዝ ፶፥፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን
መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም
አመንዝሮች ወይም ቀላጮች (ወንድ ከወንድ፥ ሴት ከሴት የሚያመነዝሩ) ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት
የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች
የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶች እንደዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል ፥ ተቀድሳችኋል ፥ ጸድቃችኋል፤» ብሏል። ፩ኛ
ቆሮ ፮፥፱። በመሆኑም የውኃነት ባሕርይ ያለው የሰው ልጅ በርኅራኄውና በቸርነቱ በንስሐ ውኃ ከኃጢአት
የሚያነጻውንና ከበደል የሚያጥበውን እግዚአብሔርን ይመስላል።

፫፥፫፦ እሳት፤

 እሳት፦ ለእግዚአብሔር ከሃሊነት(ሁሉን ቻይነት) ምሳሌ ነው። እሳት በተነሣ ጊዜ እርጥቡንም ደረቁንም
ያቃጥላል፥ እንዲያ ውም ገደልና ባሕር ካልከለከለው በስተቀር የብዙ ቀን መንገድ እየተጓዘ ማንኛውንም ነገር
አቃጥሎ ወደ አመድነት መለወጥ ይችላል። እግዚአብሔርም ቸርነቱና ርኅራኄው ካልከለከለው በስተቀር
ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፥ የሚሳነው ነገር የለም ዘፍ ፲፰፥፲፬ ፣ ሉቃ ፩፥፴፯።

            እግዚአብሔር ለሙሴ በደብረ ሲና በእሳት አምሳል ሐመልማሏን ተዋሕዶ ተገልጦለታል። ዘዳ ፫፥፪።


እሳቱ ያላቃጠላት ሐመልማል የእመቤታችን የቅድሳት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ምክንያቱም
እመቤታችንም በተለየ አካሉ በማኅፀኗ ያደረው እሳተ መ ለኰት አላቃጠላትምና ነው። ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፦
«እግዚአብሔር አምላክህ የሚበላ (የሚያቃጥል) እሳት ፥ ቀናተኛም አምላክ ነውና።» በማለት ወገኖቹን
እስራኤልን አሰጠንቅቋቸዋል። ዘዳ ፬፥፳፬። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ « እነሆ ፥ እግዚአብሔር፦ መዓቱን በቊጣ ፥
ዘለፋ ውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፤ » ብሏል። ኢሳ ፷፮፥፲፭። ብርሃነ ዓለም
ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና፤» በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል።
ዕብ ፲፪፥፳፱። በመሆኑም የእሳትነት ባህርይ ያለው የሰው ልጅ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን ይመስለዋል።
፫፥፬፦ ነፋስ፤

ነፋስ ፦ ለእግዚአብሔር ፈታሒነት(ፈራጅነት ፥ዳኝነት) ምሳሌ ነው። ገበሬ አዝመራውን አጭዶ ፥ ከአውድማ
ላይ ወቅቶ ፥ በመንሽ ባነሣው ጊዜ ፥ በነፋስ ኃይል፦ ፍሬው ከገለባ ፥ ገለባውም ከፍሬው ይለያል። ጌታም
በፈታሒነቱ ጻድቃንን ከኃጥአን ፥ ኃጥአ ንንም ከጻድቃን ይለያል። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስ፦
«መንሹም በእጁ ነው ፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራ ይከታል፥ ገለባውን ግን
በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፫፥፲፪ ፣ ሉቃ ፫፥፲፯። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ፍርድ ቀን በተናገረ ጊዜ ፦ «እረኛም፦ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ
እርስ በእርሳቸው ይለያ ቸዋል፤ በጎቹን በቀኙ ፥ ፍየሎቹን በግራው ያቆማቸዋል።» ብሏል። ማቴ ፳፭፥፴፪።
ጻድቃን በስንዴና በበጎች ሲመሰሉ ኃጥአን ግን  በገለባና በፍየሎች ተመስለዋል። እንግዲህ የሰው ልጅ በነፋስነት
ባህርዩ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እንደሚመስለው በዚህ እናስ ተውላለን።

በሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ እግዚአብሔርን መምሰል፤

 ነፍስ፦ ለባዊት ናት ፥ ልብ ታደርጋለች ፥ ታስባለች ፤ ነባቢትም ናት ፥ ቃል አላት ፥ ትናገራለች ፤ ሕያዊትም


ናት ፥ ለዘለዓለም ትኖራለች። ለባዊነት የሚለው ቃል በቁም ሲተረጐም፦ ልባም ፥ ልብ አድራጊ ፥ ተመልካች
፥ አስተዋይ ፥ ብልኅ ፥ ዐዋቂ ፥ ጠንቃቂ ማለት ነው። በመጽሐፈ ሲራክ ፦ «ነገርን ዐዋቂዎች ራሳቸው
በልቡናቸው ይራቀቃሉ ፥ የተረዳ ምሳሌም ይናገራሉ፤ » የሚል ተጽፏል። ሲራ ፲፰፥፳፰። በመጽሐፈ ጥበብ
ደግሞ ፦ «ሰው ወዳጅ ፥ የጥበብ ወዳጅዋ ፥ ዐዋቂ ፥ እውነተኛ ፥ ግዳጅ የሌለበት ፥ ትዕግሥተኛ ፥ ሁሉንም
የሚችል ፥ ሁሉንም የሚጐበኝ ፥ ንጹሓትና አስተዋዮች ፥ ረቂቃትም በሆኑ ነፍሳት የሚያድር ነው፤» የሚል
አለ። ጥበብ ፯፥፳፫።

            ነፍስ ከሥጋ ከተለየች በኋላ አስባ እንደምትናገር (ነባቢት እንደሆነች) ሕያውም ሆና እንደምትኖር፦
ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ያየውን ፦ «ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የተገደሉትን ሰዎች ነፍሳት
ከመሠዊያው በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅ እየ ጮኹ፤» በማለት ተናግሯል። ራእ ፮፥፱። ይኽንንም ጌታም
በወንጌል ፦ « ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ ፥ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል ፤ ሕያው የሆነም
የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤» በማለት አስቀድሞ ለእኅተ አልዓዛር ማርታ ነግሯት ነበር። ዮሐ
፲፩፥፳፭።

            እንግዲህ ለባዊነት የሚለው ልብን ፥ ነባቢት የሚለው ቃልን ፥ ሕያዊት የሚለው ደግሞ ሕይወትን
እንደሆነ አይተናል። በም ሥጢረ ሥላሴ፦ አብ ልብ ፥ ወልድ ቃል ፥ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት እስትንፋስ
ናቸው። አብ የራሱንም ሆኖ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ፤ ወልድ የራሱንም ሆኖ የአብ የመንፈስ
ቅዱስ ቃላቸው ነው ፤ መንፈስ ቅዱስም የራሱንም ሆኖ የአብ የወልድ ሕይወ ታቸው እስትንፋሳቸው ነው።
ልብን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ ፦ «የእግዚአብሔርን ልብ ያወቀው ማነው? » በማለት ተናግሯል። ኢሳ
፵፥፲፫ ፣ ሮሜ ፲፮፥፴፬ ። ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ሦስቱንም ልብ ፥ ቃልና እስትንፋስን በተመለከተ
«የእግዚአብሔር ይቅርታው (የአብ ቸር ነቱ) ምድርን ሞላ። በእግዚአብሔር ቃል (በወልድ) ሰማዮች ጸኑ ፥
(ባለማለፍ ጸንተው የሚኖሩት ሰባቱ ሰማያት ተፈጠሩ) ፥ ሠራዊ ታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ ፤
(በመንፈስ ቅዱስ) ፤» በማለት ተናግሯል። መዝ ፴፪፥፭። በመሆኑም፦ ነፍስ በለባዊነት አብን ፥ በነባቢነት
ወልድን ፥ በሕያውነት መንፈስ ቅዱስን ትመስላለች።

እግዚአብሔርን መምሰል፤ (በጸጋ በመክበር)

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፡- ፮

እግዚአብሔርን መምሰል፡- (በጸጋ በመክበር፤)

          እግዚአብሔርን የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው እንደሌለ ቅዱሳት መጻሕፍት በመተባበር


ይመሰክራሉ። እግዚአብሔርን በባህርይ የሚመስለው፥ በሥልጣን የሚተካከለው የለምና። በመሆኑም ቅዱሳን
በጸጋ ከብረው እርሱን መሰሉት ማለት ተካከሉት (ተስተካከሉት) ማለት አይደለም። ለምሳሌ፡- አዳም በሥላሴ
መልክና አርአያ በመፈጠሩ፡- ሥላሴን ተካክሎ ተፈጠረ፥ አያሰኝም። ምክንያቱም በምንም መንገድ ቢሆን
ፍጡር ፈጣሪን ሊተካከለው አይችልምና ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን
መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ፤» በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። ኢሳ ፵፥፳፭።

          በጸጋ እግዚአብሔር የከበሩ ቅዱሳን በብዙ ነገር የጠራቸውን እግዚአብሔርን መስለውታል። ይኸውም
ራሳቸውን በመካዳቸው (ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው) በማስገዛታቸው ነው። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «እኔን መከተል የሚወድ (ሊመስለኝ የሚፈቅድ) ቢኖር ራሱን ይካድ፤»
ያለው ለዚህ ነውና። ማቴ ፲፮፥፳፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- በዚህ ቃለ ምክር ዘክርስቶስ በመጓዙ፡- «እኔ
ክርስቶስን መስያለሁ፤» ለማለት በቅቷል። ፩ኛ ቆሮ ፲፩፥፩። በሮሜ መልእክቱም፡- «እግዚአብሔር
የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል
በኲር ይሆን ዘንድ (ለቅዱሳን ለበጎ ምግባር ሁሉ አብነት ይሆናቸው ዘንድ) አስቀድሞ ያወቃቸውንና
የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን (ኢየሱስ ክርስቶስን) ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቷቸዋል። ያዘጋጃቸውን እነርሱን
ጠራ፥ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፥  ያጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፳፰።
ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ደግሞ፡- «እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን
ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋውንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም
የሚገዛለት (የሁሉ ገዥ) ነው።» ብሏል።

ወልድ (የባህርይ ልጅ)፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ፥ የማርያም ልጅ ነው። «እግዚአብሔር
አለኝ፥ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔም ዛሬ ወለድሁህ፤» እንዲል፡- ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ተወልዷል። መዝ
፪፥፯። ይኸንንም በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር፡- «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤» በማለት
የባህርይ አባቱ አብ መስክሮለታል። ማቴ ፫፥፲፯፣ ፲፯፥፭። እርሱም አባቴ እያለ ለባህርይ አባቱ ለአብ
መስክሮለታል። ዮሐ ፲፩፥፵፩፣ ፲፬፥፪፣፳። በመሆኑም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ የባህርይ ልጅ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፡- «የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን
እንደሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» ያለው
ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፥ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፥ ከአንቺ
የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል።»  እንዲል በመንፈስ ቅዱስ ግብር
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም፡- ያለ አባት ተወልዷል። ሉቃ ፩፥፴፭፤፪፥፮። ይኸንንም ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ፥ (አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም)፥
እግዚአብሔር ልጁን(አብ ወልድን)ላከ፤ ከሴትም (ከሴቶች ሁሉ ተለይታ ከተባረከችው ከድንግል ማርያም)
ተወለደ።» በማለት መስክሯል። ገላ ፬፥፬። በመሆኑም ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባህርይ አንድ
ባህርይ (በተዋህዶ አንድ አካል አንድ ባህርይ) የሆነውን ኢየሱሰ ክርስቶስን የባህርይ አባቱ አብ «ልጄ» እንዳለው
ሁሉ እመቤታችንም «ልጄ» ብላዋለች። ሉቃ ፪፥፵፰።

ውሉድ (የጸጋ ልጆች)፤

          ቅዱሳን ልጅነታቸውን አጽንተው የጠበቁ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ይኸንንም ወንጌላዊው ቅዱስ
ዮሐንስ፡- «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው።
እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ
አልተወለዱም።» በማለት ተናግሮታል። ዮሐ ፩፥፲፪። ከሁሉም በላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ፡- «እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ፡- አባታችን ሆይ፥ በሰማያት የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ፥
በሉ።» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፮፥፱። በተጨማሪም «ለሰዎች በደላቸውን ይቅር ብትሉ፥ ሰማያዊው
አባታችሁ ይቅር ይላችኋልና። ነገር ግን ለሰዎች በደላቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም በደላችሁን የቅር
አይላችሁም።» በማለት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ለደቀመዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል።
ማቴ፮፥፲፬። በእርግጥ በአብ፥ በወልድ፥ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች
ሆነናል። ማቴ፳፰፥፲፱፣ ዮሐ ፫፥፫፤ ነገር ግን፡- «ኃጢአትን የሚሠራትም ከሰይጣን ወገን ነው፥ ጥንቱን
ሰይጣን በድሏልና፤ ስለዚህ የሰይጣንን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር
የሚወለድ ሁሉ ኃጢአትን አይሠራም፤ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ኃጢአትንም ሊሠራ አይችልም፤
ከእግዚአብሔር ተወልዷልና። በዚህም የእግዚአብሔር ልጆችና የሰይጣን ልጆች ይታወቃሉ፤ ጽድቅንም
የማይሠራ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ አይደለም፤ ወንድሙንም የማይወድ እንዲሁ ነው።» የሚለውን
ለመፈጸም እንቸገራለን። ፩ኛ ዮሐ ፫፥፭።

          አካላው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢባል የባህርይ ነው። ይህም ማለት፦ ተቀዳሚ
ተከታይ የሌለው የአብ የባህርይ ልጅ ነው፥ማለት ነው። በመሆኑም፦ አብ አባት በመሆን ወልድን
አይበልጠውም፥ አይቀድመውም። ጌታችን በወንጌል፦ «እኔና አብ አንድ ነን፤» እንዳለ፥ በመለኰት፥ በባህርይ፥
በሥልጣን፥ በፈቃድ አንድ ናቸው። ዮሐ ፲፥፴። በተጨማሪም «እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ
እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ።» እንዳለ በህልውና አንድ ናቸው። ዮሐ ፲፬፥፲፩። የቅዱሳን
«የእግዚአብሔር ልጆች» መባል ግን የጸጋ ነው። በመሆኑም በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው፡-
«የእግዚአብሔር ልጅ» የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስን መስለውታል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የትንሣኤው ዕለት፥ ለመግደላዊት ማርያም በተገለጠላት ጊዜ፡- «ወደ አባቴ፥ ወደ አባታችሁ---
አርጋለሁ፤ ብሏል፥ ብለሽ ለደቀመዛሙርቴ ንገሪ፤» ያላት ለዚህ ነው። ምክንያቱም «ወደ አባቴ» ማለቱ እርሱ
ለአብ የባህርይ ልጅ በመሆኑ ነው።  «ወደ አባታችሁ» ማለቱ ደግሞ እነርሱ የጸጋ ለጆች በመሆናቸው ነው።
እንደዚያ ባይሆን ኖሮ፡- ጠቅለል አድርጎ «ወደ አባታችን» ባለ ነበር። ዮሐ ፳፥፲፯።

የባህርይ አምላክ፤

  አምላክ፥ ማለት፥ ፈጣሪ፥ ገዥ፥ ፈራጅ፥ ዳኛ፥ ሠሪ፥ ቀጭ፥ ፈላጭ ቆራጭ ማለት ነው። ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- የፈጠረውን ፍጥረት የሚገዛ የባህርይ አምላክ ነው። ይህም
ገዥነት የባህርይ ገንዘቡ የሆነ ማለት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- «በመጀመሪያ ቃል (ወልድ) ነበረ፤ ቃልም
በእግዚአብሔር ዘንድ (በአብ ህልው ሆኖ፥ ከአብ ተካክሎ፥ በዘመን ሳይቀዳደሙ፥ በሥልጣን ሳይበላለጡ፥
በቅድምና) ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። (ፈጥሮ የሚገዛ ነው)፤  ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር
ዘንድ (በመንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ተካክሎ፥ በዘመን ሳይቀዳደሙ፥ በሥልጣን ሳይበላለጡ፥
በቅድምና) ነበረ። ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ (የሚታየውም የማይታየውም፥ የሚያልፈውም የማያልፈውም
ሁሉም በእርሱ አምላክነት ተፈጠረ)፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም። (እርሱ ሳይኖር፥ ያለ
እርሱ አምላክነት የተፈጠረ ፍጥረት የለም)» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፩። በመልእክቱም ላይ፡- «እርሱም
እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው፤» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡-
«ከእነርሱም (ከቤተ አይሁድ) ክርስቶስ በሥጋ መጣ፤ (ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ
በተዋህዶ ሰው ሁኖ ተወለደ)፤ እርሱም ከሁሉ በላይ ሁኖ (የፈጠረውን ፍጥረት እየገዛ) ለዘለዓለም የተባረከ
(የተመሰገነ) አምላክ ነው፤» ብሏል። ሮሜ ፱፥፭።

የጸጋ አማልክት፤

   ቅዱሳን የጸጋ ገዢዎች ናቸው። ጸጋ ማለት፡- ሀብት፥ መልካም ስጦታ፥ ዕድል ፈንታ፥ ትምርት፥ ስርየት፥
ይቅርታ፥ብዕል፥ ክብር፥ ሞገስ፥ የቸርነት ሥራ፥ ያለዋጋ የሚሰጥና የሚደረግ ማለት ነው። እንደሚታወቀው፥
አባታችን አዳም የተፈጠረው የጸጋ አምላክ (ገዥ) ሁኖ ነው። ይኸውም፡- «እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን
በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥
በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፤» በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ታውቋል። ዘፍ ፩፥፳፮።
እርሱም እንደ ገዥነቱ ለእያንዳንዳቸው ስም አውጥቶላቸዋል። ወደ ገዢያቸው ወደ አዳም ሰብስቦ
ያመጣቸውም እግዚአብሔር ነበር። ዘፍ ፪፥፲፱።

          እግዚአብሔር በግብፅ ሀገር ለወዳጁ ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ፡-«እነሆ፥ እኔ ለፈርዖን  አምላክ


አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።» ብሎታል። ዘዳ ፯፥፩። ይህም በእርሱ ላይ
አሰለጥንሃለሁ ሲለው ነው። አንድም፦ አምላክ የወደደውን እንደሚያደርግ ሁሉ አንተም የወደድከውን
አድርገው ሲለው ነው። በመሆኑም ሙሴ የጸጋ አምላክነቱን (ገዥነቱን) በግብፃውያን ላይ በወረደ አሥር
መቅሰፍት አረጋግጧል። እነዚህም፡- የግብፅ ውኃ ወደ ደምነት ተለውጧል፥ የግብፅ ምድር በጓንጉቸሮች
ተሸፍኗል፥ በሰውም በእንሰሳም ላይ ቅማል ፈልቷል፥ ተናካሽ ዝንቦች ወርረዋቸዋል፥ የቤት እንሰሳት
አልቀዋል፥ ሻህኝ ቁስል ወጥቶባቸዋል፥ ኃይለኛ በረዶ ወርዶባቸዋል፥ የአንበጣ መንጋ ታዝዞባቸዋል፥ ሦስት
ቀንና ሦስት ሌሊት ጨለማ ሆኗል፥ ከንጉሡ ጀምሮ የሕዝቡም የበኲር ልጆቻቸው የእንስሳቱም ሳይቀር
ሞተውባቸዋል፤

 ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ለቅዱሳን ስለተሰጠ የጸጋ አምላክነት ሲናገር፡- «እኔ ግን እላለሁ፥ አማልክት ናችሁ፥
ሁላችሁ የልዑል ልጆች ናችሁ፤» ብሏል። መዝ ፹፩፥፮። ጌታችን በወንጌል ይኽንን ጠቅሶ አስተምሯል።
«ዳግመኛም አይሁድ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፡- ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ
አሳያኋችሁ፤ ከእነርሱ በየትኛው ሥራ ምክንያት ተወግሩኛላችሁ አላቸው። አይሁድም፡- አንተ ሰው ስትሆን
ራስህን እግዚአብሔር ታደርጋለህና፥ ስለ መሳደብህ ነው እንጂ ስለ መልካም ሥራህስ አንወግርህም አሉት።
ጌታችንም ኢየሱስ መልሶ፡- እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ፥ ተብሎ በኦሪታችሁ ተጽፎ የለምን? የእግዚአብሔር
ቃል የመጣላቸውን እነዚያን አማልክት ካላቸው፥ የመጽሐፉ ቃል ይታበል ዘንድ አይቻልም። እኔ
የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብላችሁ፥ አብ የቀደሰውንና ወደ ዓለምም የላከውን እንዴት ትሳደባለህ ትሉኛላችሁ?
የአባቴን ሥራ ባልሠራ (አምላክ ብቻ ሊሠራው የሚችለውን ሥራ ባላደርግ) በእኔ አትመኑ። ከሠራሁ ግን፥
እኔን እንኳን ባታምኑ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ታውቁና ትረዱ ዘንድ ሥራዬን እመኑ፤»
ብሏቸዋል። ዮሐ ፲፥፴፩። ቅዱስ ዳዊት፡- «የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ምድርንም ጠራት፤»
በማለት የተናገረውም ቅዱሳን በጸጋ አማልክት በመሆናቸው ነው። መዝ ፵፱፥፩።

የባህርይ ንጉሥ፤

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ንጉሥ ነው። ቅድመ ዓለም፥ ማዕከለ ዓለም፥
ድኅረ ዓለም ንጉሥ ነው። ቅዱስ ዳዊት፡- «ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁና፤» እያለ
ይማጸነው ነበር። መዝ ፭፥፪። ዘለዓለማዊነቱንም፡- «እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤» በማለት መስክሯል።
መዝ ፱፥፴፮። በማዕከለ ምድር በቀራንዮ፥ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ዓለምን እንደሚያድን ሲናገርም፡-
«እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ፤» ብሏል።መዝ
፸፫፥፲፪። ክብር ምስጋና የሚገባው ንጉሥ መሆኑንም፡- «እግዚአብሔር ነገሠ፥ ክብርንም ለበሰ፤» በማለት
ተናግሯል። መዝ ፺፪፥፩ ። ከዚህም ሌላ፡- «እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆችም
ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥
እግዚአብሔር ነው፥ በሰይፍ ኃያል። እናነት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆችም ይከፈቱ፥
የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማነው? የጭፍሮች አምላክ እግዚአብሔር፥ እርሱ የክብር ንጉሥ
ነው።» የሚል አለ። መዝ ፳፫፥፯። ነቢዩ ኢሳይያስም፡- «እነሆ ጻድቅ ንጉሥ ይነግሣል፤ --- ንጉሥን በክብሩ
ታዩታላችሁ፤» ያለው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢሳ ፴፪፥፩፣ ፴፫፥፲፯። ጊዜውም ሲደርስ የባህርይ ንጉሥ
ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ዙፋኑ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ነግሦአል፥ ተገልጧል። ነቢዩ
ኤርምያስ ደግሞ፡- «እነሆ ለዳዊት የጽድቅ ቁጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እንደ
ንጉሥ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል፤» ብሏል። ኤር ፳፫፥፭። ይኽንን
ትንቢት ሲጠባበቁ የኖሩ ሰዎችም፡-ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አያነጠፉ፥ የዛፍ ቅርንጫፎችን እየጐዘጐዙ፥
ዘንባባ ይዘው፥ ሆሣዕና የዳዊት ልጅ፥ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፥ ሆሣዕና በአርያም፤» እያሉ
ተቀብለውታል። ማቴ ፳፩፥፰። መንግሥቱም የምታልፍ፥ የምትጠፋ፥ ምድራዊት ሳትሆን፥ የማታልፍ፥
የማትጠፋ ሰማያዊት ናት። ይኸንንም «የእኔ መንግሥት ከዚህ አይደለችም፤ መንግሥቴስ በዚህ ዓለም
ብትሆን ኖሮ ለአይሁድ እንዳልሰጥ አሽከሮቼ (መላእክት) በተዋጉልኝ ነበር፤ አሁንም መንግሥቴ ከዚህ
አይደለችም፤» በማለት ለጲላጦስ ነግሮታል። ዮሐ ፲፰፥፴፮። ይኸንን በተመለከተ፡- ሐዋርያው ቅዱስ
ጴጥሮስ፡- «እንዲሁ ወደ ዘለዓለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት
በምልዐት ይሰጣችኋል፤» ብሏል፤ ፪ኛ ጴጥ ፩፥፲፩።

ነገሥታት ዘበጸጋ
 ቅዱሳን የጸጋ ነገሥታት ናቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «የነገሥታት ንጉሥ፤»
ተብሎ የተጠራው በእነርሱ ላይ ነው። የኸንንም ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- «የነገሥታት ንጉሥ--- የሚል ስም
አለው፤» በማለት በራእይ መጽሐፉ ነግሮናል፡ ራእ ፲፱፥፲፮። በወንጌል እንደተጻፈ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን፡-
«በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤» ማለቱም የሚያመለክተው በጸጋ ነገሥታት መሆናቸውን ነው።
ምክንያቱም በዙፋን የሚቀመጥ ንጉሥ ነውና። ማቴ ፲፱፥፳፰። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በበኩሉ፡-
«ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኲል በሕይወት
ይነግሣሉ፤» ብሏል። ሮሜ ፭፥፲፯። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ «ከዚህም በኋላ ዙፋኖች ተዘርግተው፥
የሰው ልጅም (በተዋህዶ ሰው የሆነው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) በላያቸው ተቀምጦ አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ
ምስክርና (በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስላመኑ፥ ስሙን ስላስተማሩ፥ በስሙ ስለተጠሩ) ስለ እግዚአብሔር ቃልም
(በአካላዊ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ስላመኑ አንድም ቃሉን ስላስተማሩ) ለተገደሉት ነፍሳት ቅን ፍርድ
ተፈረደላቸው፤ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን፥ በግምባራቸውና በእጃቸው ላይ ምልክቱን
ያልጻፉትንም አየሁ፥ እነርሱም ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ኖረው (የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት ሆነው)
ይነግሣሉ።» ብሏል። ራእ ፳፥፬። በመሆኑም የባህርይ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን በጸጋ ነገሥታት
አድርጎ ራሱን አስመስሏቸዋል።

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፦ ፯

፩፦ የባህርይ ጌታ፤

          ጌታ፦ የግብር፣ የክብር፣ የማዕረግ ስም ነው። ትርጓሜውም፦ ገዥ፥ ሹም፥ ባለቤት፥ መምህር፥ ታላቅ፥ ማለት ነው።
በመሆኑም፦ የፍጥረት ገዥና አዛዥ የሆነው፦ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ጌታ ነው። (ጌትነት የባ
ህርይ ገንዘቡ ነው)። ቅዱስ ዳዊት፦ «የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል።» እንዳለ፦ ቅዱሳን መላእክት ለጌትነቱ
ተንበርክከዋል። መዝ ፺፮፥፯፤ ዕብ ፩፥፮። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊም፦ «እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱ ለት፤»
እንዳለ፦ የሰው ልጆችም ለጌትነቱ ተንበርክከዋል። ማቴ ፳፰፥፱። ነፋሳት ባሕርና ማዕበላትም ለጌትነቱ ተገዝተዋል። ደቀ
መዛሙርቱም ይህን አይተው፦ «ባሕርና ነፋሳትስ እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማነው?» እያሉ አድንቀዋል። ማቴ ፲፥፳፮።
አጋንንትም፦ «የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? (አንተን የምንቃወምበት ምን ኃይል፥ ምን ሥልጣን
አለን?) ጊዜው (ዕለተ ዓርብ፥ ዕለተ ምጽአት) ሳይደርስ ልታሠቃየን (ልትፈርድብን) ወደዚህ መጣህን? . . . ከሰው ልቡና
ካወጣኸንስ በእሪያዎቹ መንጋ እንድናድር ወደዚያ ስደደን።» እያሉ፥ እየለመኑት ለጌትነቱ ተገዝተዋል። ማቴ ፰፥፳፱።
በተሰቀለበት ዕለት ደግሞ ምድር በመነዋወጥ፥ መቃብራት በመከፈት፥ ታላላቅ ዐለቶች በመሰነጣጠቅ ፥ ፀሐይ በመጨለም፥
ጨረቃ ደም በመምሰል፥ ከዋክብት በመርገፍ ለጌትነቱ ተገዝተዋል። ማቴ ፳፯፥፵፭፣ ማር ፲፭፥፴፫፣ ሉቃ ፳፫፥፵፬፣

ጌታችንን፦ ለምጻሙ ሰው፦ «ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤» እያለ ቀርቦ ሰግዶለታል። ማቴ ፲፥፪ ከደቀመዛሙርቱ
ጋር በታንኳ በባሕር ላይ በሚጓዝበት ጊዜም ብርቱ ማዕበል በመነሣቱ፦ «ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን፤» ብለውታል። ማቴ
፲፥፳፱። ከነዓናዊቷም ሴት ስለ ልጇ በማለደችው ጊዜ፦ «ጌታ ሆይ እርዳኝ፤» እያለች ሰግዳለታለች። ማቴ ፲፭፥፳፭። ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌትነቱን ክብር በደብረ ታቦር በገለጠ ጊዜ፦ ፊቱ እንደ ፀሐይ በርቷል፥ ልብሱም
እንደ ብርሃን ነጸብራቅ ሆኗል። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን አይቶ፦ «ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው።» ብሏል። ማቴ
፲፯፥፬። ከተራራው በወረደ ጊዜም፦ አንድ ሰው በጉልበቱ ተንበርክኮ እየሰገደ፦ «ጌታ ሆይ ልጄን ማርልኝ» ብሎታል። ማቴ
፲፯፥፲፭።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈሪሳውያንን እና ሰዱቃውያንን፦ «ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል?
የማንስ ልጅ ነው?» ብሎ ጠይቋቸው ነበር። እነርሱም፦ «የዳዊት ልጅ ነው፤» አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ ዳዊት፦ «ጌታ
ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፦ አለው፤ ሲል እንዴት በመንፈስ (በትንቢት) ጌታ
ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል?» አላቸው። እንዲህ ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ አንዳችም
ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም። ከዚያ ቀንም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። «ጌታ፥ ጌታዬን፤»የሚለው ትርጉሙ፦
«ጌታዬ እግዚአብሔር አብ፥ጌታዬ እግዚአብሔር ወልድን፤» ማለት ነው። መዝ ፻፱፥፩፣ ማቴ ፳፪፥፵፩። ቅድስት ኤልሳቤጥ፦
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎበኘቻት ጊዜ፦ «የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆናልኛል?»
ያለችው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ጌታ በመሆኑ ነው። ሉቃ ፩፥፵፫። ቅዱስ ቶማስም በእጆቹ ከዳሰሰው በኋላ፦ «ጌታዬ
አምላኬም፤» ብሎታል። ዮሐ ፳፥፳፰። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ «የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ለሚጠሩት ሁሉ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰላምና
ጸጋ ለእናንተ ይሁን።»  ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፩፥፪ በተጨማሪም «ሁሉ በእርሱ የሆነ፥ እኛም በእርሱ የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ
ክርስቶስ አለን፤» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፰፥፮ ከዚህም ሌላ አንድ ጌታ ሲሆን፥ ልዩ ልዩ አገልግሎት እንዳለ ተናግሯል። ፩ኛ ቆሮ
፲፪፥፭። ይህ ሐዋርያ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱም፦ ኢየሱስ ክርስቶስን፦ «የጌቶች ጌታ፣» ብሎታል። ፩ኛ ጢሞ ፮፥፲፭።
ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ «የጌቶች ጌታ የሚል ስም አለው፤» ብሎናል። ራእ ፲፱፥፲፩። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ፦ «የጌቶች ጌታ፤» የተባለው፦ ቅዱሳን በጸጋ ጌቶች በመሆናቸው ነው።

፪፦ የጸጋ ጌቶች (አጋዕዝት ዘበጸጋ)፤


 ቅዱሳን ስለተሰጣቸው ጸጋ ከፍ ያለ ክብርና ማዕረግ ስላላቸው ጌቶች ናቸው፥ ጌቶችም ተብለው ይጠራሉ። ይህ ጸጋ፥ ክብርና
ማዕረግ ከእግዚአብሔር ነው። ይኸንን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ «ሰውነቴ በእግዚአብሔር ትከብራለች፤»
ብሏል። መዝ ፴፫፥፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «ያጸደቃቸውንም እነዚህን አከበራቸው፤» ብሏል። ሮሜ ፰፥፴።
በመሆኑም ቅዱስ የሚለው ለቅዱሳን እንደሚቀጸልላቸው ሁሉ፦ ጌታ፦ የሚለውም ይቀጸልላቸዋል። ጌታዬ አብርሃም ፥ ጌታዬ
ሙሴ ፥ ጌታዬ ዮሴፍ ፥ ጌታዬ ጳውሎስ ፥ እንላቸዋለን። ጌታ፦ ያሰኛቸውም የማይሰፈረው ፥ የማይቆጠረው የእግዚአብሔር ጸጋ
ነው።

                                  ፪፥፩፦ ጌታ አብርሃም፤

 እግዚአብሔር፦ አብርሃምን መርጦ እንዳከበረው የምታውቅ ሣራ፦ «ጌታዬ» ኢያለች ትጠራው፥ ትታዘዘውም ነበር። ወደ
ድንኳናቸው በእንግድነት የገቡ ቅድስት ሥላሴ፦ «የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም
ልጅን ታገኛለች፤» ብለው ለአብርሃም ቃል ሲገቡለት ሰምታ፦ «እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሏል፤»
ብላለች፤ ዘፍ ፲፰፥፲፪። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ላይ ተመሥርቶ፦ «ቀድሞም እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ
የተቀደሱ ሴቶች እንዲሁ ለባሎቻቸው በመገዛት ራሳቸውን ያስጌጡ ነበር። እንዲሁም ሣራ ለአብርሃም ትታዘዘው ነበር፤
ጌታዬም ትለው ነበር፤ እናንተም ከሚያስደነግጥ ነገር ምንም ሳትፈሩ በበጎ ሥራ ልጆችዋ ሁኑ።» በማለት አስተምሮበታል። ፩ኛ
ጴጥ ፫፥፭።

አብርሃም በከነዓን ሲኖር ኬጢያውያንም በሰሜኑ ክፍል በዚያ ይኖሩ ነበር። እነዚህም ከከነዓን የተገኙ ወገኖች ናቸው። ዘፍ
፲፥፲፭። ከነዓን የካም ልጅ፥ የኖኅ የልጅ ልጅ ነው። የአብርሃም ሚስት ሣራ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ሲሆናት፦ በቈላ
አውራጃ ባለች አርባቅ በምትባል ሀገር ሞተች። ይህችውም በከነዓን ውስጥ ያለች ኬብሮን ናት። አብርሃምም፦ ለሚስቱ ለሣራ
ፈጽሞ ሲያለቅስላት ከቆየ በኋላ የኬጢን ልጆች፦ «እኔ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ዘመን ስኖር መጻተኛ ነኝ፤ እንደ እናንተ
እናንተን መስዬ እኖር ዘንድ የመቃብር ቦታ በዋጋ ሽጡልኝ፤» አላቸው። እነርሱም፦ «ጌታችን ሆይ፥ የምንነግርህን ነገር ስማ፤
ከእግዚአብሔር ታዝዘህ የመጣህ ንጉሣችን አንተ ነህና፤ እኛ ከምንቀበርበት ከወደድኸው ቦታ ሬሣህን ቅበር፤ ይህን እንዳታደርግ
ከእኛ ወገን የሚከለክልህ የለም፤» አሉት። አብርሃምም የኬጢን ልጆች እጅ ከነሣ በኋላ፦ «ሬሣዬን ከፊቴ አርቄ እንድቀብር
ከወደዳችሁስ ስሙኝ፤ ለሰዓር ልጅ ለኤፍሮንም ስለ እኔ ንገሩት፤ በእርሻው ዳርቻ ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን
ይስጠኝ፤ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን በሚገባ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፤ ከእርሱም እገዛለሁ፤» አላቸው። ኤፍሮንም
በኬጢ ልጆች መካከል ስለነበር፦ «አይደለም፥ ጌታዬ ቀርበህ ስማኝ፤ እርሻውን በውስጡም ያለውን ዋሻውን ሰጥቼሃለሁ፤
በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሣህን ቅበር።» አለው። ኤፍሮን ለጊዜው አልቀበልም ብሎ ቢያስቸግረውም፥ አብርሃም፦
አራት መቶ ምዝምዝ ብር መዝኖ ሰጥቶታል፥ ርስት ሆኖ ስለጸናለትም ሣራን በዚያ ቀብሯል። (ይህች ስፍራ ለእመቤታችን
ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት)። ዘፍ ፳፪፥፩-፳።
፪፥፪፦ ጌታ ዮሴፍ፤

 ዮሴፍ፦ የያዕቆብ አሥራ አንደኛ ልጅ፥ የራሔል የበኲር ልጅ ነው። ዘፍ ፴፥፳፪። ከጠባዩ መልካምነትና ከዝናው፥
ከፈጸመውም ትልቅ ሥራ የተነሣ ከያዕቆብ ልጆች ሁሉ የተከበረ ሆነ። ያዕቆብም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወድደው
ነበር። እርሱ በሽምግልናው የወለደው ስለሆነ፥ በብዙ ኅብር ያጌጠች ቀሚስ አለበሰው። በዚህም ምክንያት ወንድሞቹ ጠሉት።
በሰላም ይናገሩት ዘንድ አልቻሉም። ዮሴፍ ህልም የማየት ጸጋም ስለነበረው፦ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክ ብትም
ሲሰግዱለት ማየቱን፦ በወንድሞቹ ፊት በመናገሩ አባቱ ገሠጸው። ቀጥሎም፦ «ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድን ነው? በውኑ
እኔና እናትህ፥ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?» አለው። ወንድሞቹም ቀኑበት፤ አባቱ ግን ይህን ነገር
በልቡ ይጠብቀው ነበር። በመጨረሻም ዮሴፍን ወንድሞቹ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች ሸጡት። የዮሴፍንም ልብ ስ በደም
ነክረው፥ ከሜዳ እንዳገኙት አድርገው፥ ክፉ አውሬም እንደበላው አስመስለው፥ ለአባታቸው ሰጡት። ያዕቆብም፦ «ይህ የልጄ
ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍን ቦጫጭቆታል፤» እያለ ብዙ ቀን አለቀሰ። «ወደ ልጄ ወደ መቃብር እያዘንሁ
እወርዳለሁ፤» ብሎም ሐዘንን እንቢ አለ። ዘፍ ፴፮፥፩

፪፤፪፥፩፦ ዮሴፍና በረከቱ፤

 ዮሴፍ ወደ ግብፅ እንደወረደ፦ በፈርዖን ቤተ መንግሥት፥ በመጋቢዎች ላይ አለቃ የሆነ ጲጥፋራ የተባለ ሰው ገዛው።
እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ስለነበር ሥራው ሁሉ ተከናወነለት። ጌታውም እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ፥ ሥራውንም ሁሉ
አይቶ በቤቱ ላይ ሾመው። ዮሴፍ በሁሉ በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ። እግዚአብሔርም ስለ ዮሴፍ ቤቱን ባረከው። በረከት
በቤትም በውጪም ተትረፈረፈ። ከዚህ የተነሣ ጌታው ሀብቱን ሁሉ እንዲያስተዳድር ለዮሴፍ አስረከበው።

፪፤፪፥፪፦ ዮሴፍና ፈተናው፤

          ዮሴፍ መልኩ ያማረ፥ ፊቱም እጅግ የተዋበ ነበር። ከዚህ በኋላ የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት። ባለቤቷ በሌለበት
ጠብቃ፦ «ከእኔ ጋር ተኛ፤» አለችው፥ እርሱ ግን ለጌታውም ለእግዚአብሔርም ታማኝ ሆኖ እንቢ አለ። «እንዴት ይህን ክፉ
ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?» አለ። በየዕለቱም ትነዘንዘው ነበር። ይባስ ብላ ልብሱን
ይዛ፦ «ከእኔ ጋር ተኛ፤» አለችው። እርሱም ልብሱን ትቶላት ሸሸ። እርሷም በብስጭት፦ «ሰው አለመኖሩን አይቶ ሊደፍረኝ
ነበር፥ ነገር ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ ስለጮኽኩኝ ልብሱን ትቶብኝ ሸሸ፤» ብላ ለባለቤቷ ከሰሰችው። በዚህም ምክንያት ወደ
እስር ቤት ተወረወረ። እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ። ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው።
የሚያደርገውንም ሁሉ በእጁ ያቀናለት ነበር። ዘፍ ፴፱፥፩-፳፫።

፪፤፪፥፫፦ ዮሴፍና ጥበቡ፤

          ዮሴፍ የእስረኞችን ህልም ይፈታላቸው ነበር። ዮሴፍ እንደተረጐመላቸው፦ የፈርዖን ቤተ መንግሥት የጠጅ አሳላፊዎች
አለቃ፥ በሦስት ቀን ውስጥ ወደ ሹመቱ ተመለሰ። የእንጀራ አሳላፊዎች አለቃ ግን በሦስት ቀን ውስጥ ሰቅለው ገደሉት። ዮሴፍ፦
ወደ ሹመቱ የሚመለሰውን ሰው። «ነገር ግን በጎ በተደረገልህ ጊዜ አስበኝ፥ በግፍ ታስሬያለሁና ለፈርዖን ነግረህ አስፈታኝ፤»
ብሎት ነበር፥ እርሱ ግን ረሳው። ዘፍ ፵፥፩-፳፫። ሁለት ዓመት ሙሉ አላስታወሰውም ነበር።

          ከሁለት ዓመት በኋላ ፈርዖን ህልም አይቶ መንፈሱ ታወከችበት። የግብፅ ጠቢባንም ሊተረጉሙለት አልቻሉም።
በዚህን ጊዜ የጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አስቦ ለፈርዖን ነገረው። ፈርዖንም ዮሴፍን ከግዞት ቤት አውጥቶ፦
«ሕልሜን ተርጉምልኝ፤» አለው። ዮሴፍም፦ «እግዚአብሔር ከገለጸለት ሰው በቀር መተርጐም የሚችል
የለም፤» ካለው በኋላ ተረጐመለት። በመጨረሻም፦ ፈርዖን፦ « እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና ከአንተ
ይልቅ ብልህና አዋቂ ሰው የለም። አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፤ ህዝቡም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔም ከዙፋኔ
በቀር ከአንተ የምበልጥበት የለም።» ብሎ በሁሉ ላይ ሾመው። የዮሴፍ ዕድሜ ገና ሠላሳ ነበር። በእናት በአባቱ
ቤት አሥራ ሰባት ዓመት ፥ በጲጥፋራ ቤት አሥር ዓመት ፥ በእሥር ቤት እንደ መጽሐፈ ኲፋሌ ሦስት ዓመት
በጠቅላላው ሠላሳ ይሆናል። ዘፍ ፵፩፥፩-፵፮።

፪፡፪፥፬፦ ዮሴፍ ግብፃውያንን እንደታደጋቸው፤

          ዮሴፍ የፈርዖንን ህልም በፈታለት መሠረት ፥ የሰባቱ ዓመት የጥጋብ ዘመን ሲጀምር ፦ የግብፅ አገር
ያስገኘችውን እህል ሁሉ ነዶውን እያስከመረ ፥ የሚነቅዘውን እያስፈጨ ፥ ጡብ እያስጣለ ፥ የማይነቅዘውን
በሪቅ ፥በጎተራ አኖረ። የግብፅ ሰዎች መስፈር መቊጠር እስኪሳናቸው ድረስ እህሉን እንደ ባሕር አሸዋ ብዙ
አድርጎ ሰበሰበ። በዚህን ጊዜ ሁለት ልጆች ተወለዱለት። የበኲር ልጁን ምናሴ አለው። መርስኤ ሐዘን ማለት
ነው። ሁለተኛውንም ኤፍሬም አለው። ዕበይ (ክብር) ፍሬ ማለት ነው።

የጥጋቡ ዘመን ሲያልፍ ሰባቱ የረሃብ ዘመን ጀመረ። በግብፅ ሀገር ሁሉ ረሃቡ ታዘዘ። ሕዝቡም እህል
እንዲሰጣቸው ንጉሣቸውን ቢጠይቁት ወደ ዮሴፍ አሰናበታቸው። ዮሴፍም እየሰፈረ ይሸጥላቸው ነበር።
የግብፅ ሀገር ሰዎች ሁሉ እህል ሊሸምቱ ዮሴፍ ወደአለበት ይመጡ ነበር። ዘፍ ፵፮፥፵፯-፶፯።

፪፡፪፥፭፦ ዮሴፍና ይቅርታው፤


ሽማግሌ ከመንደር ዳር ፥ ከድንበር መቀመጥ ልማድ ነውና ፥ ያዕቆብ ከዚያ ተቀምጦ ሳለ፦ ነጋድያን ከግብፅ
እህል ሸምተው ሲመለሱ  ጠይቆ ስለተረዳ ልጆቹን ወደዚያ ሰደዳቸው። እነርሱም በከነዓን ረሃብ ጸንቶ ነበርና
፥ ነገ ፥ ተነገ ወዲያ ሳይሉ ወዲያው ተነሡ። ከዚያም ሲደርሱ የሸጡት ወንድማቸው መሆኑን ሳያውቁ
ለዮሴፍ ሰገዱለት። በዚህም የዮሴፍ ሕልም ተፈታ ፥ የእግዚአብሔርም ዓላማ ተፈጸመ። ዮሴፍም
እንደማያውቃቸው ሆኖ ፦ « ሰላዮች ናችሁ፤» አላቸው። እነርሱም እውነቱን ነገሩት። አውቆ በአስተርጓሚ
ያናግራቸው ነበር። ነገራችሁ እውነት የሚሆነው « ቢኒያም» ያላችሁትን ወንድማችሁን ስታመጡት ነው ፥
እስከዚያው ብሎ ስምዖንን አቆይቶ ፥ ለእነርሱ እህል በየስልቻቸው ሞልቶ የከፈሉትንም ገንዘብ በምሥጢር
በውስጥ አድርጐ ሰደዳቸው። የሆነውንም ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት። ቢኒያምን ይዘው በተመለሱ ጊዜ፦ ዮሴፍ
የእናቱን ልጅ በማየቱ ወደ እልፍኙ ገብቶ አለቀሰ። ተመልሶም፦ መልካም ግብዣ አደረገላቸው። በመጨረሻም
ራሱን ገለጠላቸው። «አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትፍሩ ፥ እግዚአብሔር ለሕይወት ከእናንተ በፊት
ልኮኛልና። . . . እግዚአብሔርም  በምድር ላይ እንድትድኑና እንድትተርፉ እመግባችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት
ላከኝ፤ » አላቸው። ሁሉንም ሳማቸው አንገታቸውንም አቅፎ አለቀሰ። ዘፍ ፵፫፤፵፬፤፵፭። ከዚህ ሁሉ በኋላ
ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ፥ የዮሴፍን መገኘት ነግረው ፥ አባታቸውን ያዕቆብንና ቤተሰቡን ይዘው ወደ ግብፅ
ተመለሱ። የልጆቹ ሚስቶች ሳይቆጠሩ ወደ ሰባ ነበሩ ። ኑሮአቸውንም በዚያ አደረጉ። ዘፍ ፵፮ ፥ ፩-፴፬።

፪፡፪፥፮፦ የያዕቆብ ሞት፤

          ያዕቆብ፦ ልጆቹን ሁሉ ጠርቶ መረቃቸው ፥ በኋለኛውም ዘመን ስለሚገጥማቸው ነገር ሁሉ


ነገራቸው። ከዚያ በፊት ሁለቱን የዮሴፍን ልጆች እጁን አመሳቅሎ ባርኳቸው ነበር። ይህም በአዲስ ኪዳን
ዘመን በመስቀል ለመባረካችን ምሳሌ ነው። ዘፍ ፵፰፥፵፬። አብርሃምና ሣራ ፥ ይስሐቅና ርብቃ በተቀበሩበት
ስፍራም እንዲቀብሩት ካዘዛቸው በኋላ ሞተ። የልቅሶውም ወራት  ከተፈጸመ በኋላ እንዳዘዛቸው አደረጉ።
ዮሴፍም ፈርዖንን አስፈቅዶ ከወንድሞቹ ጋር አባቱን ቀብሮ ተመለሰ። ይህም ሰው ሲሞትብን ወደ ቤተ
ክርስቲያን ወስደን ለመቅበራችን ምሳሌ ነው። ዘፍ ፵፱ ፤፶።

፪፡፪፥፯፦ ዮሴፍ ወንድሞቹን ማረጋጋቱ፤

          ከቀብር በኋላ ፥ የዮሴፍ ወንድሞች ፦ « ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል ፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ
ብድራትን ይመልስብን ይሆናል ፤» አሉ ። መልእክተኛም ልከው ፦ «አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ
አዝዞናል፦ ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ እባክህን የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል ፥ እነርሱ
ከፍተውብሃልና ፤ አሁንም እባክህን የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።» አሉት። ዮሴፍ ይህን
ሰምቶ አለቀሰ። ወንድሞቹም፦ እግዚአብሔር በጌትነት ጸጋ እንዳከበረው አምነው ፦ በፊቱ ከሰገዱለት በኋላ
፦ «እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን፤» አሉት። ዮሴፍም ፦ «እኔ በእግዚአብሔር ፈንታ ነኝን? እናንተ ክፉ ነገር
አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው።
አሁንም አትፍሩ። እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። » አላቸው። አጽናናቸውም ፥ ደሰ
አሰኛቸውም። እነርሱም፦ የግብፅን ምድር ከረገጡበት ጊዜ ጀምሮ የሚያነጋግሩት «ጌታችን ሆይ፤» እያሉ
ነበር። ዘፍ ፵፪ ፥፲ ። ይሁዳ፦ ወደ እርሱ ቀርቦ ፦ «ጌታዬ ሆይ ፥ እኔ ባሪያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን
እንድናገር  እለምንሃለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና።» እያለ የተማጸነበት ጊዜ
ነበር። ዘፍ ፵፬ ፥፲፰። (የዮሴፍን ታሪክ በመጠኑ ዘርዘር ያደረግነው ፥ ለወጣቶችም ሆነ ለሌሎችም አርአያና
ምሳሌ ስለሆነ ነው።)

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፰

         ሙሴ ከነገደ ሌዊ ሲወለድ፦ እስራኤል በግብፅ በባርነት ነበሩ። ዘጸ ፪፥፩። ይህ ጊዜ እስራኤላውያን


እናቶች ወንድ ልጅ ከወለዱ እንዲገደል በግብፅ ንጉሥ የታዘዘበት ጊዜ ነበር። ሙሴ ሲወለድ ብርሃን ተሥሎበት
ነበርና፦ አዋላጆቹ ራርተው ይህንስ የፈጠረው ይግደለው ብለው ትተውታል። እንድም፦ ቅዱስ ጳውሎስ
እንደመሰከረው « ሙሴ ከተወለደ በኋላ ወላጆቹ ያማረ ሕፃን (በፊቱ ላይ ብርሃን የተሣለበት) መሆኑን
አይተው ፦ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት ፥ የንጉሡንም አዋጅ አልፈሩም።» ዕብ ፲፩፥፳፫። ከሦስት ወር በኋላ
ግን ወንድ መሆኑ በልቅሶው በሳሉ ስለሚታወቅ ፦ በሳጥን አድርገው፥ እግዚአብሔር ያነሣዋል ብለው፥ ከአባይ
ወንዝ ዳር በቄጤማ ውስጥ አስቀመጡት። ቀን ቀን እኅቱ ትጠብቀዋለች ፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ እናቱ
ስታጠባው ታድራለች። ዘጸ ፪፥፩-፫።

፫፥፩፦ የእግዚአብሔር ሥራ በሕፃኑ ላይ፤

          ተርሙት የምትባል የፈርዖን ሴት ልጅ፦ ልትታጠብ ፥ አንድም ፦ ከብሽ የሚባል ደዌ ነበረባትና


ልትጠመቅ ፥ አንድም፦ ነጋዴ ወዳጅ ነበራትና እርሱን ለመቀበል ፥ አንድም፦ አዞ ጉማሬ ታመልክ ነበርና
ስለዚህ ፥አንድም፦ የውኃ ዋና ልትማር ወደ ወንዝ ወረደች። ደንገጡሮቿ በወንዝ ዳር ይመላለሱ ነበር። እነርሱ
ሳያዩ እርሷ ሳጥኑን አሻግራ በቄጤማ ውስጥ አየች። ደንገጡሯንም ልካ አስመጣችው። ነጋዴ የረሳው ዕቃ
መስሏት ነበር። በከፈተችው ጊዜ ግን የሚያለቅስ ሕፃን ሆኖ አገኘችው ፥ እግዚአብሔር ልቧን ስላራራው
አዘነችለት። ምነው የኔ ልጅ በሆነ ብላም ተመኘች። ደንገጡሯም ምኞቷን ሰምታ ፥ «እመቤቴ፦ አሁንስ
ወለድኩ ብትዪ ይሆን የለምን፤» አለቻት። እርሷም ፦ «ማርገዜ ሳይታወቅ ወለድኩ ብል ማን ያምነኛል?»
አለች። ደንገጡሯም ፦ «የነገሥታት ልጆች በእልፍኝ ትኖራላችሁ ፥ መውለዳችሁ ነው እንጂ ማርገዛችሁ
ይታወቃልን?» ብላ መለሰችላት። በዚህን ጊዜ በስውር ትጠብቀው የነበረች እኅቱ ማርያም፦ «ሕፃኑን
ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን?» ብትላት ፈቃደኛ ሆነች። ሄዳም
እናቱን አመጣች። የፈርዖንም ልጅ፦ እናቱን ፦ « ይህን ልጅ ተንከባክበሽ ፥ ጠብቀሽ አሳድጊልኝ፤ እኔም
የአሳዳጊነት ዋጋሽን እሰጥሻለሁ።» አለቻት። የትም ብንወድቅ ፥ የትም ብንጣል እግዚአብሔር እንዲህ
ያነሣናል። ዘጸ ፫፥፬-፮።

፫፥፪፦የሙሴ አስተዳደግ፤

 በስመ ሞግዚት ልጇን መልሳ ያገኘች የሙሴ እናት በጥሩ ኹኔታ አሳደገችው። ስታሳድገው እንዲያው (ጡት
በማጥባት ፥ ፍትፍት በማጉረስ ብቻ) አይደለም። «ተስፋ ያልተነገረላቸው የእነዚህ የቈላፋን (የኢግዙራን)
ልጅ አይደለህም። ተስፋ የተነገረላቸው የአብርሃም ፥ የይስሐቅ ፥ የያዕቆብ ልጅ ነህ፤» እያለች አሳድጋዋለች።
አባቱም ሁልጊዜ ዜና አበውን ይነግረው ነበር። በዚህም አጠቃላይ ማንነቱን ማለትም ፦ ሃይማኖቱን ፥
ሥርዓቱን ፥ ባሕሉን ፥ ታሪኩን ፥ ተስፋውን፥ አውቆ አደገ። ከዚህ በኋላ ወስዳ ለፈርዖን ልጅ አስረከበችው።
እርሷም፦ «እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና፤» ስትል ሙሴ አለችው። የንጉሥ የልጅ ልጅ ተብሎ በምቾት አደገ።
ምቾቱ ግን ማንነቱን አላስረሳውም። ዘጸ ፫፥፯-፲።

፫፥፫፦ ሙሴና ወገኖቹ ፤

 ሙሴም የአርባ ዓመት ጐልማሳ ከሆነ በኋላ ወንድሞቹ እስራኤል ወደ አሉበት ወደ ራምሴ  በሄደ ጊዜ
ግብፃውያን የሚሠሩባቸውን ግፍ አይቶ ፈጽሞ አዘነ። ብዙ ሰው ግን እርሱ ከተመቸው ማንም ትዝ
አይለውም። ሙሴ አንድ የግብፅ ሰው ፦ የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታው አየ። የመታው በመስኖ
ውኃ ምክንያት፦ አንድም ዕብራዊው ያጠመደውን ዓሣ ልውሰድብህ ብሎት ፥ አንድም ዕብራዊው በዘረጋው
ጃንዲ በበጠበጠው እንዶድ ልጠብበት ብሎ ነው። ከዚህም አልፎ በገላህ ፥ በደምህ ባጥብ በገዛ ባሪያዬ ማን
ከልክሎኝ ብሎታል። በዚህን ጊዜ ሙሴ፦ ግብፃዊውን ገድሎ በአሸዋ ውስጥ በመቅበር ለወንድሙ
ተበቅሎለታል። ይህም ክርስቶስ የዲያቢሎስን ሥራ ገድሎ አዳምን ነፃ ለማውጣቱ ምሳሌ ነው። ብዙ ሰዎች
ወንድማቸው ሲበደል አይተው እንዳላዩ፥ ሰምተው እንዳልሰሙ፥ ይሆናሉ። ወይም የኃይል ሚዛኑን አይተው
ከበዳይ ጋር ይሰለፋሉ። ዘጸ ፪፥፲፩።

፫፥፬፦ የሙሴ ስደት፤

በበነጋው በራምሴ ፥ በጋምሴ ያሉትን ዘመዶቹን ጠይቆ ሲመለስ ሁለት ዕብራውያን ሲጣሉ አገኘ፤ ሙሴም
በዳዩን ቀርቦ፦ «ለምን ወንድምህን ትመታዋለህ?» አለው። ያም ሰው፦ «በእኛ ላይ ፈራጅ ዳኛ አድርጎ የሾመህ
ማነው? ወይስ ትናንት ያን ግብፃዊ እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትወድለህን?» አለው። ሙሴ
ግብፃዊውን የገደለው በሥውር ቢሆንም፦ « አመስጋኝ አማሳኝ፤» እንዲሉ፦ ያ ያዳነው ሰው ፦ « ትናንት
ወንድሜ ሙሴ ባያድነኝ ኖሮ ግብፃዊው ገድሎኝ ነበር።» ብሎ ሲናገር ሰምቶ ነው። የሙሴን ምክር የገዛ ወገኑ
አለመቀበሉ ፥ ክርስቶስን የገዛ ወገኖቹ አይሁድ ላለመቀበላቸው ምሳሌ ነው። « ወደ ወገኖቹ መጣ ፥ ወገኖቹ
ግን አልተቀበሉትም፤» ይላል። ዮሐ ፩፦፲፩።

ሙሴም ያደረገው ነገር ሁሉ እንደተሰማበት አውቆ ፈራ፥ ፈርዖንም ይህን ነገር ሰምቶ ሊገድለው ወደደ።
በዚህ ምክንያት ወደ ምድያም አውራጃ ተሰደደ። በመንገደኛ ልማድ ፦ ጥሬ ቆርጥሞ ፥ ውኃ ጠጥቶ ለመሄድ
ከውኃ ዳር ተቀምጦ ሳለ፦ የዮቶር ሰባት ሴት ልጆች በጎቻቸውን ማጠጣት ጀመሩ። በዚህን ጊዜ ሌሎች
እረኞች መጥተው ተጋፉአቸው። ሙሴ ይህን አይቶ ዝም አላላም። ሁልጊዜም ለተገፉት መቆም ልማዱ
ስለሆነ «ግዳይ ላፈለመ ፥ ውኃ ለቀደመ ነው ፤» ብሎ ሴቶቹን ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ
ቤታቸው ሲመለሱ ፥ ፈጥነው የተመለሱበትን ምክንያት አባታቸው ቢጠይቃቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩት።
እርሱም ፦ « እንዲህ ያለውን ሰው፦ ለምን ትታችሁ መጣችሁ? አሁንም ጥሩትና እህል ይቅመስ፤ » አላቸው።
በዚህን ጊዜ ፦ ሲፓራ የተባለች ልጁ፦ «አሁንም አላጣውም ፥ ልሂድ ፤» ብላ ይዛው መጥታለች። ይህም
የወደፊት ባሏ የሚሆን ነውና ፈቃደ እግዚአብሔር አነሣሥቷት ነው። መልአከ እግዚአብሔርም እየመራ ከዚያ
አድርሷታል።

ሙሴ አንድ ቀን አድሮ በበነጋው ፦ « ልሂድ አሰናብተኝ፤» ቢለው፦ እርሱም «የት ትሄዳለህ?» አለው።
ሙሴም፦ «እግሬ ካደረሰኝ ፤» አለው። እርሱም፦ «ውኃ ቢቀዱት ቢቀዱት ፥ መንገድ ቢሄዱት ቢሄዱት
ያልቃልን ? ለኔ ወንድ ልጅ የለኝምና ከእነዚህ ከልጆቼ አንዲቱን አግብተህ ፥በጎቼን እየጠበቅህ ፥ ተቀመጥ፤»
ብሎት፥ በዚህ ተዋውለው ፥ሚስት ልትሆነው ሲፓራን ሰጥቶታል። ዘዳ ፪፥፭-፳፪።

፫፥፭፦ የእግዚአብሔር ጥሪ፤

ሙሴ በጎቹን አሳማርቶ ሳለ፦ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል አምሳል ሐመልማሏን ተዋሕዶ በደብረ ሲና
ተገለጠለት። «ሙሴ ፥ሙሴ ሆይ፤» ብሎ፦ በክብር ጠርቶ አነጋገረው። የቆመባት ምድር የተቀደሰች በመሆኗ
ጫማ ሳያወልቅ እንዳይቀርብ ከመንገር ጋር፦ «እኔ የአባቶችህ አምላክ፦ የአብርሃም አምላክ ፥የይስሐቅም
አምላክ ፥ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤» አለው። የሕዝቡን መከራ አይቶ ፥ጩኸታቸውን ሰምቶ ፥ ሥቃያቸውን
አውቆ ሊያድናቸው ፥ ማርና ወተት ወደሚያፈስሰው ምድር ሊያገባቸው እንደወረደ ፥ ለዚህም ሥራ እርሱን
እንደመረጠው ነገረው። ሙሴ ዓለምን ንቆ በመመነኑ ፥ ከጌትነት ወደ ባርነት ፥ ከአለቅነት ወደ አሽከርነት
በመውረዱ እግዚአብሔርን አገኘ። ከራሱ ምቾት ፥ድሎት ይልቅ የወገኖቹን መከራ በማስበለጡ
እግዚአብሔርን በእሳት ምሳሌ አየው። እመቤታችንን ደግሞ ባልተቃጠለችው የሲና ሐመልማል ምሳሌ
አያት። የምድራዊ ንጉሥ የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ በማለቱ የሰማያዊ ንጉሥ ልጅነቱ ጸናለት።
የምድራዊት እመቤት ልጅ መባልን በመናቁ፦ የራቀው ቀርቦ ፥ የረቀቀው ጎልቶ እመቤቱን በበረሃ ውስጥ
በለመለመች ዕፅ ምሳሌ አገኛት። ይኽንን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስ ፦ «ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ
ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር
መከራ መቀበልን መረጠ። የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅ የሚበልጥ ባለጠግነት
መሆኑኑ አውቋልና ፥ ዋጋውንም ተመልክቷልና። የንጉሡንም ቊጣ ሳይፈራ ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤
ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዷልና።» ብሏል። ዕብ ፲፩ ፥፳፬-፳፯። እኛ ግን እግዚአብሔርን፥
እመቤታችንንም ለማየት የምንፈልገው ፥ ቤተ ክርስቲያንንም ለማገልገል የምንሮጠው፥ በሥጋ ፍላጐት
ተውጠን ነው። ዘጸ ፫፥፩-፲።

፫፥፮፦ የሙሴ ትህትና፤

 ሙሴ ለዚህ ታላቅ ሹመት እግዚአብሔር ሲመርጠው ይገባኛል አላለም፦ «ይኽን አደረግ ዘንድ እኔ ማነኝ? እኔ
ምን ቁም ነገር ነኝ?» አለ። እግዚአብሔርም፦ «በእውነት እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤» አለው። ሕዝቡ፦ «ማን
ላከህ?» ሲለውም ፦ ምን ማለት እንዳለበት ለንጉሡም ምን መንገር እንዳለበት ነገረው። ከዚህም ጋር
ተአምራታዊ ኃይልና ምልክት ሰጠው። ይህ ሁሉ ሆኖም፦ «ጌታ ሆይ ፥ እማልድሃለሁ፤» ትናንት ፥ ከትናንት
ወዲያ ባሪያህን ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ (አንደበተ ርቱዕ) ሰው አይደለሁም። እኔ አፌ ኰልታፋ ፥
ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ፤» አለ። እግዚአብሔርም፦ «ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር
አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ።
(ልብ አስደርግሃለሁ)።» አለው። ሙሴም፦ «ጌታ ሆይ ፥ እማልድሃለሁ፤ ወደ ንጉሥ ቤት የሚላክ ነገር
አከናውኖ የሚናገር ሰው ነው። እኔ ነገር አከናውኖ መናገር አይቻለኝምና ሌላ ሰው ፈልገህ ላክ፤» አለው።
እግዚአብሔር በሙሴ ላይ እጅግ ተቆጥቶ፥ ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ እንደሚነግርልህ
አውቃለሁ፤ እነሆም፥ እርሱ ሊገናኝህ ይመጣል፤ በአየህም ጊዜ ልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትነግረዋለህ፤
ቃሌንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ አንደበትህንና አንደበቱን አረታለሁ፤ የምታደርጉትንም አለብማችኋለሁ።
(ልብ እንድትሉ አደርጋችኋለሁ)። እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይነጋገራል፤ እርሱ አፍ  ይሆንሃል፤ አንተም
በእግዚአብሔር ዘንድ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግባት በትር በእጅህ ያዝ፤» አለው።
በመንፈሳዊውም ሆነ በሥጋዊው ዓለም  ከላይ እስከታች ለሥልጣን ብለን ለምንጋደል ሰዎች ይህ የሙሴ
ሕይወት ለእኛ ታላቅ  ተግሣፅ  ነው። ዘጸ ፫፥፲፩ ፣ ዘጸ ፬፥፩-፲፯።

፫፥፯፦ የሙሴ ወደ ግብፅ መመለስ፤

ሙሴ ወገኖቼን ልጠይቅ ብሎ ዮቶርን ተሰናበተው ፥ እርሱም «በደኅና ሂድ፤» አለው። ከብዙ ዘመንም
በኋላ ሙሴን ያሳደደው የግብፅ ንጉሥ ሞቶ ሌላ ተተክቶ ነበር። እግዚአብሔርም፦ «ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች
ሁሉ ሞተዋልና ወደ ግብፅ ሂድ፤» አለው። ይህም የእግዚአብሔር መልአክ ዮሴፍን፦ «የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ
ሙተዋልና ፥ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ፤» ላለው ምሳሌ ነው።

ሙሴ ጉዞ የጀመረው ሚስቱንና ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ነበር። በመንገድ ላይ በአደረበት ስፍራ የእግዚአብሔር


መልአክ አገኘውና ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ አንዱን ልጁን የእኔ ፈንታ ነው ፥ ብሎ ሲገርዘው ፥ ሁለተኛውን
ግን የእናቱ ፈንታ ነው ፥ ብሎ ትቶት ነበር። ሚስቱ ሲፓራም፦ በባልጩት (በድንጋይ ምላጭ) ፈጥና የልጅዋን
ሸለፈት ከገረዘች በኋላ፦ «ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን፤» ብላ ለመልአኩ ሰገደች። ሙሴም
መልአኩን፦ «ምን አጠፋሁ?» አለው። መልአኩም፦ «ከግብፅ ያሉትን አውጣቸው፤ ብትባል ፥ ከዚህ ያሉትን
ይዘህ ትሄዳለህ ? » አለው። ሙሴም፦ «እኔማ ማን ይመግባቸዋል ብዬ ነው?፤» አለ። መልአኩም፦ « እስኪ
ከዚህ ባሕር እጅህን ስደድ ፤ » አለው። እጁን ቢሰድድ ደንጊያ ይዞ ወጣ። መልአኩም፦ «ስበረው፤» አለው።
ቢሰብረው፦ አንድ እውር ትል መንታ ቅጠል ያላት እንጨት በቅሎለት  አንዲቱን እስኪበላ አንዲቱ
እያደገችለት አየ። መልአኩም፦ «ይህን የሚመግብ ማነው?» አለው። ሙሴም፦ «እግዚአብሔር» አለ።
መልአኩም፦ «ይህን የመገበ ይመግባቸዋልና ፥ ትተሃቸው ሂድ፤ » አለው። እርሱም ትቷቸው ሄደ። የእኛም
ወላጆች ፦ «እውር አሞራ የሚመግብ አምላክ ያውቅልኛል፤» ይላሉ።

አሮንም ከከተማው ወጥቶ እግዚአብሔር ሙሴን አግኘው ባለው ቦታ በእግዚአብሔር ተራራ አግኝቶት እጅ
ነሣው፥ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ። ሙሴም ሁሉንም ለአሮን ነገረው።  « ከሽማግሌ ምክር ፥ ከጎበዝ ውረር
፤» እንዲል፦  የእስራኤልን ሽማግ ሌዎች ሰብስበው ነገሯቸው ፥ ሕዝቡም ፍጹም እስ.ከያምኑ ድረስ
ተአምራት አደረጉላቸው። ዘጸ ፬፥፲፰-፴፩።

፫፥፰፦ ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት፤

          ሙሴና ኦሮን፡- እግዚአብሔር ልኳቸዋልና፡- ሳይፈሩና ሳያፍሩ በንጉሡ ፊት ቆሙ። የእግዚአብሔርንም


መልእክት ነገሩት። እርሱ ግን፡- «የእስራኤልን ልጆች እለቅቅ ዘንድ፥ ቃሉን የምሰማው እርሱ እግዚአብሔር
ማነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅም፤» አለ። «የሦስት ቀን መንገድ ተጉዘው
አምልኮታቸውን እንዲፈጽሙ እግዚአብሔር ጠርቷቸዋል፤» ቢሉትም፡- አልሰማም። «ለምን ይህን ሕዝብ
ሥራ ታስፈቱታላችሁ፥ ሥራ የላችሁምን? ይልቁንስ ወደ ሥራችሁ ሂዱ፤» አላቸው። በሕዝቡም ላይ
ከቀድሞው የበለጠ የሥራ ጫና እንዲደረግባቸው፥ መከራም እንዲጸናባቸው ሹማምንቱን አዘዛቸው።
ሕዝቡም መከራው እንዲቀልላቸው ወደ ፈረዖን አቤት ብለው (አቤቱታ አቅርበው) መልስ በማጣታቸው
ሙሴንና አሮንን ተጣሏቸው። እነርሱ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር አመለከቱ። ዘጸ ፭፥፩-፳፫። እግዚአብሔርም
ሙሴን ፡- «በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋልና፥ በተዘረጋችም ክንድ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸውልና፥ አሁን
በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ፤» አለው። በሙሴና በአሮን እጅም እግዚአብሔር ተአምራትን አደረገ።
ግብፃውያንንም በአሥር መቅሠፍታት ገረፋቸው። ዘፍ ፯፤፰፤፱፤፲፤፲፩፤

፫፥፱፦ እስራኤል ከግብፅ መውጣታቸው፤

          እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን ስለ ፋሲካ ነገራቸው። እነርሱም ለሕዝቡ፡- ሁሉም በየቤቱ የፋሲካ
ጠቦት እንዲያዘጋጁ፥ ከሚያዝያ አሥር እስከ አሥራ አራት አስረው ካቆዩት በኋላ በሠርክ እንዲያርዱት፥
ከደሙም ወስደው የቤቱን መቃንና ጉበኑን እንዲቀቡት፥ የየቤቱ የሰው ቁጥር ሰባት ወይም አሥር ወይም
አሥራ ሁለት እንዲሆን፥ ሥጋውን ከመራራ ቅጠል ጋር የተጠበሰውን እንዲበሉ፥ እለቱን እንዲጨርሱ እንጂ
ለነገ ብለው እንዳያሳድሩ፤ ወገቦቻቸውን ታጥቀው፥ ጫማቸውን ተጫምተው፥ በትራቸውን ጨብጠው፥
በችኰላ እንዲበሉ ነግረዋቸዋል።

ታስሮ የቆየው ጠቦት በአይሁድ እጅ ተይዞ ለታሰረ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። በሠርክ መሠዋቱ፦ ክርስቶስ
በመስቀል ላይ ለመሠዋቱ ምሳሌ ነው። የጠቦቱ ደም የቤቱ ጉበንና መቃን መቀባቱ፦ የክርስቶስ ደም በመስቀል
ላይ ለመፍሰሱ ምሳሌ ነው። የየቤቱ የቤተሰብ ቁጥር መወሰኑም ምክንያት አለው። ይኸውም፦ ሰባት ቁጥር
በዕብራውያን ፍጹም ቁጥር በመሆኑ ፍጹም እምነትን፥ አሥር ቁጥር ሙሉ ቁጥር በመሆኑ ሙሉ እምነትን፥
አሥራ ሁለት ቁጥር ለጊዜው አሥራ ሁለቱን ነገደ እስራኤል፥ ለፍጻሜው ግን አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት
ያመለክታል። ሥጋውን በእሳት ጠብሰው መብላታቸው፡- የክርስቶስ ሥጋና ደም እሳተ መለኮት የተዋሀደው
ለመሆኑ፥ ከመራራ ቅጠል ጋር መብላታቸው ደግሞ አሥራ ስምንት ሰዓት ጾመን ለአፋችን መረር ሲለን
ለመቁረባችን ምሳሌ ነው። ለነገ አታሳድሩ መባላቸው፦ ሥጋውና ደሙ ተሠውቶ፥ ተፈትቶ ላለማደሩ ምሳሌ
ነው። ወገብ መታጠቅ ለልብ ንጽሕና፥ ጫማ ለምግባር፥ በትር ደግሞ ለመስቀልና ለእመቤታችን ምሳሌዎች
ናቸው። ሕዝቡም የተባሉትን ፈጽመው ከባርነት ቤት ከግብፅ ወጥተዋል። ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ
የግብፃውያንን በኵር ሁሉ ሲገድል የጠቦቱን ደም በየበራቸው እያየ እስራኤላውያንን አልፏቸዋል። ይህም
በሥጋ ወደሙ የታተሙ ምእመናን መቅሠፍት፥ ሞተ ነፍስ እንደሌለባቸው ምሳሌ ነው። ከግብፅ
መውጣታቸውም፡- በኋለኛው ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣታቸው ምሳሌ ነው። ዘጸ
፲፪፥፩-፶፩።

 የእግዚአብሔር መልአክ ከፊት ከፊታቸው እየሄደ ቀን ቀን በደመና ዓምድ፥ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በብርሃን
ዓምድ መርቷቸዋል። በሙሴ በትር ኃይለ እግዚአብሔር ተገልጦ ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ተሻግረውል፥
ፈርዖንን ግን እስከነ ሠራዊቱ አስጥሞላቸዋል። ይህም በክርስቶስ ቤዛነት ነፍሳት ባሕረ እሳትን
ለመሻገራቸው፥ ዲያብሎስና ሠራዊቱ ደግሞ ድል ለመሆናቸው ምሳሌ ነው። ዘጸ፲፫፥፲፯-፳፪፤ ፲፬፥፩-፴፩።
በመንገዳቸውም መና ከሰማይ እየወረደ፥ ውኃ ከዐለት እየፈለቀ ተመግበውል። ዘጸ ፲፮፥፩። በሌላ በኵል
ደግሞ በደመና ተጋርደው ባሕረ ኤርትራን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው። መናውና ውኃው የሥጋውና
የደሙ ምሳሌ ነው። ዐለቱ ደግሞ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ይኸንንም ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ፡- «ወንድሞቻችን ሆይ፥ አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው
እንደሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ። ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ
ተመገቡ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት
ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።» በማለት ተርጉሞልናል። ፩ኛ ቆሮ ፲፥፩። «ከሚከተላቸው ድንጋይ፤»
መባሉም ይዘውት ይጓዙ ስለነበረ ነው። ሙሴ በበትር ሲመታው በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ፡- በአሥራ
ሁለት በኵል እንደአጋተ የላም ጡት፦ ወተት የመሰለ ውኃ ይወጣው ነበር። ይኸንን የምድረ በዳ ድንጋይ
የበረከት ምንጭ ያደረገ አምላክ፡- እመቤታችንን፥ ቅዱሳንን፥ ታቦቱን፥ ሥዕሉን፥ መስቀሉን፥ ሌሎቹንም
የበረከት ምንጭ አላደረጋቸውም ማለት አይገባም። እነዚያ ድንጋዩን ተሸክመው፥ አክብረው፥እንደተጓዙ፦
እኛም ጌታ የሰጠንን የበረከት ምንጮቻችንን ሁሉ ተሸክመን፥አክብረን እንጓዛለን፥ እንኖራለን።

፫፥፲፦ ሙሴና የእግዚአብሔር ክብር፤

          እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ፡- «እኔ በፊትህ እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ፤ . . . ይህን ያልኸኝን ነገር
አደርግልሃለሁ፤ በፊቴ ሞገስን አግኝተሃልና ከሁሉ ይልቅ አውቄሃለሁና፤  . . .  እኔ በክብሬ በፊትህ አልፋለሁ
. . .  እጄን በላይህ እጋርዳለሁ።» ይለው ነበር። በደብረ ሲና የሰጠው ጽላትም ተሰብረውበት ስለ ነበር፡-
ፈቅዶለት እንደገና ሠርቶ አስባርኳል። ፊቱም እንደ ፀሐይ አብርቷል። ዘጸ ፴፫፥፲፪፤፴፬፥፩። በዚህም
እግዚአብሔር ክብሩን ለሙሴ አሳይቷል፥ ክብሩን በሙሴ ላይ ገልጧል። በአጠቃላይ አነጋገር፡- የክብሩ
መገለጫ፥ የበረከቱ መስጫ አድርጐታል። እንኳን እርሱን በትሩን እንኳ የኃይሉ መገለጫ አድርጐታል። ታቦቱ
ያለበትን የመገናኛውን ድንኳንም የእግዚአብሔር ክብር ተለይቶት አያውቅም። «ድንኳኑና በምሥዋዑ ዙሪያ
የቅጽሩን ዓምዶች አቁሞ መጋረጃውን ጋረደ፤ የቅጽሩንም በር እግዚአብሔር እንዳዘዘው አድርጎ ጋረደው።
ሙሴም እንዲህ አድርጎ ሥራውን ሁሉ ሠርቶ ጨረሰ፥ ድንኳኒቱንም ብሩህ ደመና ሸፈናት፥ የእግዚአብሔርም
ብርሃን ሰፍሮባት ታየ። ሙሴም ወደ ደብተራ መግባት ተሳነው። ደመናው ከድንኳኒቱ ላይ ከተነሣ በኋላ ግን
የእስራኤል ልጆች በየነገዳቸው ይጓዙ ነበር። (ነገደ ቢኒያም ሁለቱን ነገድ ይዘው በፊት ይጓዛሉ፥ ቀጥለው ነገደ
ሮቤል ሁለቱን ነገድ ይዘው ይጓዛሉ፥ ሌዋውያን ካህናትም ታቦትንና ንዋየ ቅዱሳቱን ይዘው በመካከል ይጓዛሉ፥
ከዚያ ቀጥለው ነገደ ምናሴ ሁለቱን ነገድ ይዘው ይጓዛሉ)። ደመናው ከድንኳኑ ካልተነሣ አይጓዙም ነበር፤
ምክንያቱም አለመነሣቱ አትጓዙ ሲል ነውና። ተጉዘው በሚሰፍሩበት ሁሉ ደመናው እስራኤል እያዩት ቀን
በድንኳኑ ላይ ሰፍሮ ይውልና ሌሊት ዓምደ እሳት ሁኖ ሲያበራላቸው ያድር ነበር።» ይላል። ይህም የአዲስ
ኪዳን ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ክብር ለመመላቷ፥ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ለመሆኗ ምሳሌ ነው።

፫፥፲፩፦ አሮንና ማርያም፤

          ሙሴ የኢትጵያን ሴት አግብቶ ነበርና፡- «እኛን ከአረማውያን አትጋቡ እያለን እርሱ ግን ያገባል፤» እያሉ
ወንድሙ አሮንና እኅቱ ማርያም አሙት። «በውኑ እግዚአብሔር ሙሴን ብቻ ተናገረውን? እኛንስ የተናገረን
አይደለምን?» ተባባሉ። ሙሴ ግን በዚህ ዓለም ካለው ሰው ይልቅ ፈጽሞ ደግ ሰው ነበር። እግዚአብሔርም፡-
ሙሴንና አሮንን ማርያምንም፡- «ሦስታችሁም ፈጥናችሁ ወደ ደብተራ ኦሪት ኑ፤» አላቸው እነርሱም
ፈጥነው ሄዱ። እግዚአብሔርም በዓምደ ብርሃን ወደ ደብተራ ኦሪት ወርዶ አሮንን እና ማርያምን
ስለጠራቸው ሁለቱም ቀረብ አሉ። እርሱም፡- «ነገሬን ስሙ፥ ከእናንተ ለእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሰው ቢኖር
በራእይ እገለጽለታለሁ፥ በሕልምም እነጋገረዋለሁ። ነገር ግን የምናገረው እነደታመነ ወዳጄ እንደ ሙሴ
አይደለም፤ እሱ በወገኖቼ በእስራኤል ሁሉ የታመነ ነውና፤ ተገልጬ ቃል በቃል እነጋገረዋለሁ እንጂ በራእይ
ወይም በሕልም የምነጋገረው አይደለም፥ የእግዚአብሔርነቴን ጌትነትም ያየ እሱ ነው። ወዳጄ ሙሴን
ማማትን ለምን አልፈራችሁም?» አላቸው፤ ተቆጥቶባቸውም ሄደ። (እግዚአብሔር ፈርዶ ያመጣው መከራ
በእነርሱ ላይ ተደረገ)።

፫፥፲፪፦ አሮን ወደ ሙሴ፤ . . .  ሙሴ ወደ እግዚአብሔር፤

          ደመናውም ከደብተራ ኦሪት ተወገደ፤ (ራቀ)፤ ማርያምን ወዲያው ለምጽ ያዛት፥ ሁለንተናዋም እንደ
በረዶ ነጭ ሆነ። አሮንም ወደ ማርያም ተመልሶ ቢያይ ለምጽ ይዟት ቢያገኛት አዘነ፥ ደነገጠ። ሙሴንም፡-
«ጌታዬ ሆይ፥ እባክህ እሺ በጄ በለኝ፥ እንደበደልን አላወቅንምና በእኛ ዕዳ አታድርግብን፤ ከእናት ማኅፀን
እንደወጣ ጭንጋፍ፡- በሞት የተለቀምን አንሁን፤» አለው። ወንድሟን አምታለችና የማርያም የሰውነቷ
እኵሌታ በለምጽ ነደደ። ሙሴም፡- «አቤቱ፥ እሺ በጀ በለኝና ማርያምን ከለምጽ አድናት፤» ብሎ ወደ
እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- «አባቷ ምራቁን በፊቷ ቢተፋባት እንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ
ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ትመለስ፤» አለው።
ማርያምም ከሰፈር ወጥታ ሰባት ቀን ተቀመጠች። ሕዝቡም እርሷ እስክትነጻ ድረስ አልተጓዙም። ዘኁ
፲፪፥፩-፲፭። በዚህም እነ አሮን በጸጋ የከበረ ሙሴን «ጌታ» ብለው እንደጠሩት እናስተውላለን።

ነገረ ቅዱሳን ክፍል ፱

፩፦ ጌታ ጳውሎስ፤

 ቅዱስ ጳውሎስ የስሙ ትርጓሜ ብርሃን ማለት ነው፥ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለ ሀገረ ገዥ የገዛ ስሙን ሰጥቶት
ነው፥ የቀደመ ስሙ ሳውል ነበር። ይህ ሀገረ ገዥ አስተዋይ ሰው ስለነበር፡- የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ
ወድዶ፥ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ አስጠራቸው። ኤልማስ የተባለው ጠንቋይ ግን አገረ ገዥውን ከማመን
ለማጣመም ፈልጐ ተቃወማቸው። ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስ ባደረበት ሰውነት ሆኖ፡- «አንተ ተንኰል ሁሉ፥
ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታ መንገድ ከማጣመም
አታርፍምን? እነሆ የጌታ እጅ (ሥልጣን) በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ፥ እስከጊዜውም ፀሐይን
አታይም፤» አለው። ያንጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ
አገረ ገዥው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።  የጠንቋዩን ዓይነ ሥጋ በተአምራት
ሲያጠፋበት፥ የእርሱን ደግሞ ዓይነ ኅሊናውን ሲያበራለት አይቶ ጳውሎስ (ብርሃን) የሚለው ስም ለአንተ
ይገባሃል አለው። የሐዋ ፲፫፥፮።

   ጳውሎስ ማለት ንዋይ ኅሩይ (ምርጥ ዕቃ) ማለትም ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ስለ ጳውሎስ ለሐናንያ በመሰከረለት ጊዜ፡- «ይህ በአሕዛብም፥ በነገሥታትም፥ በእስራኤልም ልጆች
ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤» ብሎታል። የሐዋ ፱፥፲፭። ምርጥ ዕቃ የተባለው
መዶሻ ነው። እርሱም ሰባት የማዕድን አይነቶችን ቀጥቅጦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስም
እግዚአብሔርን እና ሰውን፥ሰውን እና መላእክትን፥ ሕዝብን እና አሕዛብን፥ ነፍስን እና ሥጋን አስታርቆ አንድ
ያደርጋል። አንድም ምርጥ ዕቃ የተባሉ ወርቅና ብር ናቸው። ወርቅና ብር ለንዋያት ሁሉ ጌጥ እንደሆኑ፡-
እርሱም የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ነው። አንድም፡- ጳውሎስ ማለት፡- አመስጋኝ፥ ደስታ፥ ምዑዝ ነገር የሚናገር፥
ልሳነ ክርስቶስ፥ ሰላም፥ ፍቅር ማለት ነው።

፩፥፩፦ የልጅነት ጊዜው፤

          ቅዱስ ጳውሎስ የተወለደው በጠርሴስ ነው፤ የሐዋ ፳፩፥፴፱። በዚያ ዘመን አምስት መቶ ሺህ ሰው
ይኖርባት ነበር። ድንኳን መስፋትን የተማረው በዚያ ነው። የሐዋ ፲፫፥፫። የሮም ዜግነትን የወረሰው ከአባቱ
ነው። የሐዋ ፳፪፥፳፮። አባቱ የሮም ዜግነት ይኑረው እንጂ፡- ከብንያም ወገን የሆነ ፈሪሳዊ ነበረ። የሐዋ
፳፫፥፮። በፊልጵስዩስ መልእክቱ፡- «በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥
ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁኝ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።»
ያለው ለዚህ ነው። ፊል ፫፥፭። ከታላቁ መምህር ከገማልያል እግር ስር ሆኖ ሕገ ኦሪትን እና የአይሁድን ወግ
ጠንቅቆ ተምሯል። የሐዋ ፳፪፥፫።

፩፥፪፦ የቅዱስ ጳውሎስ አጠራር፤

          የተጠራው ከደማስቆ ጐዳና ነው። በደማስቆ ላሉ ምኵራቦች የተጻፈ የትእዛዝ ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ
ተቀብሎ፥ ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰረ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ይተጋ ነበር። (ለሕገ ኦሪት ቀንቶ
ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር)። ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ፡- ድንገት በእርሱ ዙሪያ ብርሃን አንጸባረቀ፥
በምድርም ላይ ወደቀ። «ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?» የሚለውን ድምፅ ሰምቶም፡- «አንተ ማን
ነህ?» አለ። እርሱም፡- «አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም በአንተ
ይብስብሃል፤ (ሰይፍ የረገጠ ሰው ይጎዳል እንጂ ሰይፉ ይጐዳልን? ልክ እንደዚህ አንተ ትጐዳለህ እንጂ እኔ
አልጐዳም፤ እንዲህ እንደ ተደላደልህ እንደተቀማጠልህ አትቀርም፥ የኔን ነገር ስታስተምር ኔሮን ቄሣር በሰይፍ
አስመትቶ ይገድልሃል)፤ አለው። እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፡- «ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?»
አለው። ጌታም «ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል፤» አለው።

          ሳውል፡- ሦስት ቀን ማየት ተሳነው፥ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። ጌታም ለሐናንያ በራእይ
ተገልጦ፡- «ሳውልን አግኘው፥ እርሱ ይጸልያል፥ ሐናንያ የሚባል ሰው እጁን ሲጭንበት ሲፈወስም አይቷል፤»
አለው። ሐናንያም፡- «ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ፥ ስለዚህ ሰው ከብዙዎቹ
ሰምቻለሁ፤ ስምህን የሚጠሩትን ለማሰር ከካህናት ሥልጣን አለው።» አለ። ጌታም፡- «በሁሉ ፊት ስሜን
ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፥ አትፍራ፤» አለው። በመጨረሻም ሐናንያ ሳውልን አግኝቶት
ሲጸልይለት እንደ እንጨት ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ላይ ወደቀለት። የሐዋ ፱፥፩-፲፰ ።

፪፦ በብዙ መከራ ወንጌልን ሰበከ፤

          «እጅግም ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ። አይሁድ


አንዲት ስትቀር አምስት ጊዜ አርባ አርባ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤
መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ ስዋኝ ዋልሁ። በመንገድ ዘወትር መከራ
እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ ተቀበልሁ፤ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ ዘመዶቼም አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ
አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልሁ፤ በበረሃም መከራ ተቀበልሁ፤ በባሕርም መከራ ተቀበልሁ፤ ሐሰተኞች
መምህራን መከራ አጸኑብኝ፤ በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም ዕንቅልፍ በማጣት፥ በመራብና በመጠማት፥
አብዝቶም በመጾም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርሁ።» ብሏል።፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፳፫-፳፯።

፪፥፩፦ አደራ ይከብደው፥ ኃላፊነት ይሰማው ነበር፤

-       «ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፤» ፩ኛ ቆሮ ፱፥፲፮


-       «ለግሪክ ሰዎችና (ለአረማውያንና) ላልተማሩ፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ሁሉ አስተምር ዘንድ ዕዳ
አለብኝ። ይልቁንም በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ወንጌልን ላስተምራችሁ እተጋለሁ።» ብሏል። ሮሜ ፩፥፲፬

፪፥፩፦ የሚያስጨንቀው የቤተክርስቲያን ጉዳይ ነበር፤

-       «የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብደኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።» ብሏል። ፪ኛ
ቆሮ ፲፩፥፳፱።

፪፥፫፦ ትሑት ነበር፤

-       «ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ። ተቀበረ፤ እንደተጻፈም በሦስተኛው ቀን ተነሣ። ለጴጥሮስ ታየው፤


በኋላም ለአሥራ አንዱ ደቀመዛሙርት ታያቸው። ከዚህም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ
ጊዜ ታያቸው፤ . . .  ከዚህም በኋላ ለያዕቆብ ታየው፤ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታያቸው። ከሁሉም በኋላ
ጭንጋፍ ለምመስል ለእኔ ታየኝ። ከሐዋርያት ሁሉ እኔ አንሳለሁና፤» ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፬-፰።
-       «ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ ሁሉ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር
ከዘለዓለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት፥ ምን እንደሆነ እገልጥ ዘንድ፥ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ
ለማንስ ለእኔ ተሰጠ።» ብሏል።  ኤፌ ፫፥፰።

፪፥፬፦ ትእግሥተኛ ነበር፤

-       «እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ


እጃችን እየሠራን እንደክማለን፥ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን
እንማልዳለን፥ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ፥ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፬፥፲፩።

                                              ፪፥፭፦ ታማሚ ነበር፤

-       «ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ፥ የሥጋዬ መውጊያ፡- (የጎን ውጋትና የራስ ምታት)፡-  እርሱም
የሚጐስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፥ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት
ጊዜ ጌታን ለመንሁ፤ እርሱም ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፯።

፪፥፮፦ ድንግላዊ ነበር፤

-       «ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላለሁ። (እንደኔ ከሴት
ርቀው፥ ንጽሕና ጠብቆ ቢኖሩ ይሻላቸዋል ብዬ እነግራቸዋለሁ)።» ብሏል።  ፩ኛ ቆሮ ፯፥፰።

፪፥፯፦ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ይነጠቅ ነበር፤

-       «እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ
ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤
ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰው ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ።» ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፲፪፥፫።

፪፥፰፦ ተአምራትን ያደርግ ነበር፤

-       በልስጥራን አንካሳውን አርትቷል። የሐዋ ፲፬፥፰። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጐበዝ በመስኮት ተቀምጦ
ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር። ጳውሎስም ነገር ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ
ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ቅዱስ ጳውሎስም በጸሎት አስነሣው። የሐዋ ፳፥፱። በልብሱም ይፈውስ
ነበር። የሐዋ ፲፱፥፲፩።
፪፥፱፦ ዕለተ ሞቱን ይናፍቅ ነበር፤

-       «በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል
ነውና፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ይህንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ
እንደገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ
ዘንድ፥ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቆይ አውቃለሁ።» ብሏል። ፊል ፩፥፳፫።

፪፥፲፦ ዕለተ ሞቱን ያውቅ ነበር፤

-       «ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፡- በየከተማው መከራና እስራት ይጠብቅሃል ብሎ ይመሰክርልኛል። ነገር ግን


የእግዚአብሔርን የጸጋውን ወንጌል እንዳስተምር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልሁትን ሩጫዬን
እንድጨርስና መልእክቴንም እንድፈጽም ነው እንጂ ለሰውነቴ ምንም አላስብላትም። አሁንም እነሆ፥
የእግዚአብሔርን መንግሥት የሰበክሁላችሁ እናንተ ሁላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቴን እንደማታዩኝ እኔ
ዐውቄአለሁ።» የሐዋ ፳፥፳፫።

-       «ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና


እግር ብረትን ብቻ አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም የቆረጥሁ
ነኝ፤» አለ። የሐዋ ፳፩፥፲፫። መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ባወቃት ዕለት፡- ሐምሌ አምስት ቀን በሰማዕትነት
አርፏል። ያረፈውም፡- የጠራው ጌታ፥ አስቀድሞ እንደነገረው በሰይፍ ተመትሮ ነው።

፫፦ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በእስር ቤት፤

 እየጠነቆለች ለጌቶቿ ብዙ ገንዘብ የምትሰበስብ አንዲት የቤት ሠራተኛ ነበረች። ቅዱስ ጳውሎስን እና
ሲላስን እየተከታተለች፡- «የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው፤»
ብላ ትጮህ ነበር። ይህንንም እጅግ ብዙ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን፡-
«ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤» በዚያም ሰዓት ወጣ። ጌቶቿም፡-
የትርፋቸው ተስፋ እንደወጣ ባዩ ጊዜ፡- ጳውሎስን እና ሲላስን በሹማምንት ፊት ጐተቱአቸው፤ ወደ
ገዢዎችም አቅርበው፡- «እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች
ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ፤» በማለት ክሱን ፖለቲካዊ
አደረጉት። ሕዝቡም ተባበራቸው፥ ልብሳቸውንም ገፍፈው በበትር ደብድበው ወደ ወኅኒ ጣሏቸው።

በወኅኒም ከግንድ ጋር አጣብቀው አሰሯቸው። መንፈቀ ሌሊትም ሲሆን እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ
አመሰገኑ፥ እስረኞቹም ያዳምጡአቸው ነበር። በዚህን ጊዜ የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ የምድር
መንቀጥቀጥ ሆነና ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ፥ የሁሉም እስራት ተፈታ። ጠባቂውም ከእንቅልፉ ሲነቃ እስረኞቹ
ያመለጡ መስሎት፡- ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ። ቅዱስ ጳውሎስ ግን፡- «ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ
ነገር አታድርግ፤» ብሎ ጮኸ። መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ለጳውሎስና ለሲላስ
ሰገደ፤ ወደ ውጭም አውጥቶ፡- «ጌቶቼ ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» አላቸው። እነርሱም፡-
«በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተሰዎችህ ትድናላችሁ፤» አሉት። ወንጌልንም አስተማሩት፤
በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው፥ ስብራታቸውን አሰረላቸው፥ ከቤተሰቦቹም ሁሉ
ጋር ተጠመቀ፥ ማዕድም አቀረበላቸው፤ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሴት አደረገ።
የሐዋ ፳፥፲፮-፴፬።

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲

እግዚአብሔርን መምሰል፦ በጸጋ በመክበር፤

፩፦ ፀሐይ፤

    ፀሐይ ቀንን እንዲገዛ የተፈጠረ ነው።  « ለፀሐይ ቀንን ያስገዛው ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ፤ » ይላል። መዝ
፩፻፴፭ ፥ ፰። የፀሐይ ተፈጥሮ ከእሳት ስለሆነ ትሞቃለች ፥ ትደምቃለች። ብርሃኗም ከጨረቃ ብርሃን ሰባት
እጥፍ ነው። ሄኖ ፳፩ ፥ ፶፮ ። እግዚአብሔር ማክሰኞ ማታ ለረቡዕ አጥቢያ ፦ « ለይኩን ብርሃን ውስተ ጠፈረ
ሰማይ ፤ ብርሃን በሰማይ ጠፈር ይሁን ፤» ባለ ጊዜ ጸሐይ ጨረቃ ከዋክብት ተፈጥረዋል። ዘፍ ፮ ፥ ፲፮ ።
በዚህን ጊዜ መላእክት በታላቅ ድምጽ አመስግነውታል። « ወአመ ተፈጥሩ ከዋክብት ሰብሑኒ ኲሎሙ
መላእክትየ በዓቢይ ቃል ፤ ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምጽ አመሰገኑኝ ፤» እንዳለ ።
ኢዮ ፴፰ ፥ ፯ ።
የተፈጠሩበት ዓላማም በዚህ ዓለም እንዲያበሩ ፥ (ጨለማን እንዲያርቁ) ፥ በመዓልትና በሌሊት መካከል
ድንበር ሆነው እንዲለዩ ፥ ማለትም መለያ ምልክት እንዲሆኑ ፥ አንድም ለሰው ልጅ ምሳሌ እንዲሆኑ ነው።
ፀሐይ መውጣቷ የመወለዳችን ፥ በጠፈር ላይ ማብራቷ በዚህ ዓለም የመኖራችን ፥ መግባቷ ( በምዕራብ
መጥለቋ ) የመሞታችን ፥ ተመልሳ በምሥራቅ መውጣቷ የመነሣታችን ምሳሌ ነው። ከዚህም ሌላ ፦ ክረምት
፥ በጋ ፥ ጸደይ ፥ መጸው ብሎ አራት ክፍለ ዘመን ለመቊጠር ፥ ለሳምንት ሰባት ቀን ብሎ ለመቊጠር ፥
ሦስት መቶ ስድሳ አምስቱን ቀን ዓመት ብሎ ለመቊጠር ምልክት ይሆኑ ዘንድ ፀሐይን ጨረቃን ከዋክብትን
ፈጠረ።
፩፥፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፀሐይ ነው ፤

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፀሐይ ተመስሏል። « ወይሠርቅ ለክሙ ለእለ ትፈርሁ
ስምየ ፀሐየ ጽድቅ ፤ ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ይወጣላችኋል ፤ ( ፀሐየ ጽድቅ
ክርስቶስ ይወለድላችኋል ) ፤ ይላል። ሚል ፬ ፥ ፪። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ በቅዱሱ ተራራ በደብረ ታቦር
በነቢያትና በሐዋርያት ፊት ገጹ እንደ ፀሐይ በርቷል። « ወአብርሃ ገጹ ከመ ፀሐይ ፤ ፊቱ እንደ ፀሐይ ብሩህ
ሆነ ፤ ( ጌትነቱን ገለጸ ) ፤ » ይላል። ማቴ ፲፯ ፥ ፪ ።
ፀሐይ በጠፈረ ሰማይ ሆና እንደምታበራ ፥ በሰማይ የሚኖር እርሱ ብርሃናችን ነው። « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ
፥ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም። ( ወደ ከህደት አይሄድም )።
ብሏልና ። ዮሐ ፰ ፥፲፪ ፣ ፱ ፥ ፭ ። ፀሐይ በመዓልትና በሌሊት መካከል እንደምትለይ ፥ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ
ክርስቶስም ፦ ጻድቃንን ከኃጥአን ፥ ኃጥአንን ከጻድቃን ይለያል። « የሰው ልጅ ( ወልደ ዕጓለ እመሕያው
ክርስቶስ ) በጌትነቱ ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ ፥ ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን
ይቀመጣል። አሕዘብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ ፥ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እየራሳቸው
ይለያቸዋል። በጎችን ( ጻድቃንን ) በቀኙ ፍየሎችንም (ኃጥአንን) በግራው ያቆማቸዋል። » ይላል ። ማቴ ፳፭
፥ ፴፩። ፀሐይ የዕለታት ፥ የአራቱ አዝማናትና የዓመታት መለያ እንደሆነች ፦ እነዚህን ለይቶ ባርኮ የሰጠን
ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። « ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ፥ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም ፥
ወይረውዩ አድባረ በድው ፤ የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ ፥ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ ፥
የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ ፤ » ያለው ለዚህ ነው። መዝ ፷፬ ፥ ፲፩ ። አክሊል ያለው ፍሬ የሚሸከመውን
የስንዴ ዛላ ነው። አክሊል የሚቀመጠው በራስ ላይ እንደሆነ ሁሉ ፍሬው ፥ ዛላው ከላይ ነውና።

፩ ፥ ፪፦ ቅዱሳን ፀሐይ ናቸው፤


ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዓለም ለይቶ የጠራቸውን ፥ ጠርቶም የመረጣቸውን
ደቀመዛሙርቱን ፦ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ  ፥ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ መሰወር አይቻላትም። »
ብሏቸዋል። ማቴ ፭ ፥ ፲፬። እርሱ ፦  « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፤ » ማለቱ የባህርዩ ሰለሆነ ነው ፥ የእነርሱ
ግን የጸጋ ነው። በጸጋ ያከበራቸውም እርሱ ነው። በተጨማሪም ፦ « ያንጊዜም ጻድቃን በአባታቸው
መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ ፤ ( ከፀሐይ ሰባት እጅ ያበራሉ ) ፤ » ብሏል። ማቴ ፲፫ ፥ ፵፫ ። በመሆኑም
ቅዱሳን ባሉበት ቦታ ሁልጊዜ ብርሃን ነው። ጨለማ ይወገዳል
፪፦ ኮከብ፤
  ኮከብ፦ በቁሙ ሲተረጐም ፦ የብርሃን ቅንጣት ፥ የጸዳል ሠሌዳ ፥ ብርሃን የተሣለበት ፥ የሰማይ ጌጥ ፥
የጠፈር ፈርጥ ፥ ሌሊት እንደ አሸዋና እንደ ፋና በዝቶ የሚታይ ፥ የሚያበራ ፥ የፀሐይ ሠራዊት ፥ የጨረቃ
ጭፍራ ማለት ነው። የተፈጠረውም ሌሊቱን እንዲገዛ በሌሊት እንዲሰለጥን ነው። መዝ ፩፻፴፭ ፥ ፱ ።
ከዋክብት በሰዎች ዘንድ የማይቆጠሩ ናቸው። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቁጥራቸው ይታወቃል ፥
በየስማቸውም ይጠራቸዋል። መዝ ፩፻፵፮ ፥ ፬ ።

፪፥፩፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ኮከብ ነው፤


«ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤»
        የእስራኤል ልጆች ከባርነት ቤት ከግብፅ ወጥተው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር ወደ ከነዓን
በሚጓዙበት ጊዜ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በዮርዳኖስ ማዶ ባለው በሞዓብ ሜዳ ሰፈሩ። በዚህም ምክንያት
ሕዝቡም  ንጉሣቸው ባላቅም ፈሩ፥ደነገጡ ፥ ተንቀጠቀጡ። ምክንያቱም የእስራኤል አመጣጣቸው
እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን እንደ ቅጠል እያረገፈላቸው ነበርና ነው። ከመደንገጣቸውም የተነሣ፦ «በሬ
የለመለመውን ሣር እንደሚጨርስ ይህ ጭፍራ በዙሪያችን ያለውን ሁሉ ይጨርሳል፤» አሉ። ይህንንም
የተባባሉት ከምድያም ሽማግሌዎች ጋር ነው።

ንጉሡ ባላቅ፦ በወገኖቹ ልጆች ሀገር ወንዝ ወደሚኖር ፥ በለዓም ወደተባለ ሟርተኛ ዘንድ፦ መልእክተኞችን
ልኮ፦«እነሆ ከግብፅ የወጣ ወገን በበዛቱ ምድርን ሸፈናት፥በአቅራቢያዬም ሰፍረው አሉ። ከእኔ ይበረታሉና
እነሱን መውጋት እችል እንደሆነ፥ከአገሬም አስወጥቼ እሰዳቸው እንደሆነ፥ አሁን መጥተህ ረግመህ አጥፋልኝ፤
አንተ የመረቅኸው ምሩቅ እንዲሆን፥ የረገምኸውም የተረገመ እንዲሆን አውቃለሁና፤» አለ። የሞዓብና
የምድያም ሽማግሌዎችም፦ ከመልእክቱ ጋር የሚያሟርትበትንም ገንዘብ ይዘውለት ሄዱ። እነርሱም፦
«በዚህች ሌሊት እደሩና እግዚአብሔር የሚለኝን ነገር እነግራችኋለሁ፤» ብሏቸው በዚያው አደሩ።

 በለዓም ለወትሮው፦ ልብሱን ጥሎ፥ ዕርቃኑን ሆኖ፥ ከአሸዋ ላይ ወድቆ ሲያሟርት፥ ሰይጣን በጣዖቱ አድሮ
ይናገረው ነበር፤ ዛሬ ግን እስራኤልን የሚረዳ ነውና እግዚአብሔር ተገልጦለት፦ «ከእነርሱ ጋር አትሂድ፤
የተባረከ ነውና ሕዝቡን አትርገም፤»አለው። በለዓምም፦ «ከእናንተ ጋር እሄድ ዘንድ እግዚአብሔር
አላሰናበተኝምና ወደ ጌታችሁ ሂዱ፤» ብሎ ለመልእክተኞቹ ነገራቸው። እነርሱም ተመልሰው ይኽንኑ ለባላቅ
ነገሩት።

 ባላቅ፦ ከዚህ ቀደም የተላኩት፦ በቁጥር ባይበዙ፥ በማዕረግ ባይከብሩ ነው ብሎ ከቀደሙት የበዙና የከበሩ
መልእክተኞችን ላከ። ከእርሱም ደርሰው፦ «የሶፎር ልጅ ባላቅ፦ እባክህ ወደ እኔ መምጣትን ቸል አትበል፤
ክብርህን እጅግ ታላቅ አደርገዋለሁና፥ የተናገርኸውንም ሁሉ አደርግልሃለሁና፥ ና፥ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ ፥
ብሏል፤» አሉት። በለዓምም መልሶ የባላቅን አለቆች፦ «ባላቅ ቤት ሙሉ ወርቅና ብር ቢሰጠኝ
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቸል ማለት አይቻለኝም፤ አሁንም እናንተ የዛሬን ሌሊት እደሩና እግዚአብሔር
የሚናገረኝን እነግራችኋለሁ፤» አላቸው። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ወደ በለዓም መጥቶ፦ «እሊህ
ሰዎች ይጠሩህ ዘንድ መጡን? ተነሥተህ ተከተላቸው፤ ነገር ግን የምነግርህን ነገር ለመናገር ተጠበቅ እንጂ
መከተሉንስ ተከተላቸው፤» አለው።

 በለዓምም ማልዶ ተነሥቶ፦ አህያውን ጭኖ ከባላቅ መልእክተኞች ጋር ሄደ፤ ወደ ክብረ በዓል የሚሄድ ደብተራ
ቅኔውን እያሰበ እንደሚሄድ እርሱም፦ «እግዚአብሔር ቀድሞ አትሂድ አለኝ ፥ አሁን ደግሞ ሂድ አለኝ፤
አሁንም፦ ቀድሞ አትርገም ያለኝን መልሶ እርገም ይለኝ ይሆናል፤» ብሎ መርገሙን እያሰበ ሲሄድ
እግዚአብሔር ተቆጣ፤ የእግዚአብሔር መልአክም ሊያሰናክለው ተነሣ። በለዓም የተቀመጠባት አህያ የተመዘዘ
ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ አይታ ከመንገድ ፈቀቅ አለች ፥ እርሱ ግን ምሥጢሩን ስላላወቀ ደብድቦ
ወደ መንገድ መለሳት። የእግዚአብሔርም መልአክ በቀኝና በግራ የወይን አጥር ባለበት ቆመ። አህያይቱም
የእግዚአብሔርን መልአክ ባየች ጊዜ በአጥሩ ተጠግታ ስታልፍ የበለዓምን እግሩን ላጠችው ፥ እርሱም ዳግመኛ
ደበደባት። የእግዚአብሔርም መልአክ በቀኝና በግራ መተላለፊያ በሌለበት በጠባብ ስፍራ ቆመ። ያችም አህያ
የእግዚአብሔርን መልአክ ባየችው ጊዜ በለዓምን እንደተሸከመች ተንበረከከች (ሰገደች)። እርሱም ለሦስተኛ
ጊዜ ይደበድባት ጀመር። እግዚአብሔርም የአህያይቱን አፍ ከፈተ ፥ በሰው አንደበት እንድትናገርም አድርጎ፦
«ሦስት ጊዜ የመታኸኝ ምን አድርጌብህ ነው?» አለችው። በለዓምም «ስለዘበትሽብኝ ነው፤ በእጄስ ሰይፍ
ቢኖር አሁን በገደልሁሽ ነበር፤ (ሰይፍ ቢኖር በቆረጥሁሽ ፥ ጦር ቢኖር በወጋሁሽ ነበር፤) አላት። አህያይቱም፦
«ከወጣትነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ የምትቀመጥብኝ አህያህ አይደለሁምን? በውኑ አንተን ቸል ያልሁበት ፥
በአንተም እንዲህ ያደረግሁበት ጊዜ ነበርን?» አለችው። እርሱም፦ «እንዲህ አላደረግሽብኝም፤» አላት። ከዚህ
የምንማረው፦ «ቅዱሳን መላእክትን አላከብርም ፥ ለእነርሱም አልሰግድም፤» ማለት ከእንስሳዋ አንሶ
መገኘትን ነው።

 እግዚአብሔር የበለዓምን ዓይኖች ከፈተለትና የእግዚአብሔርን መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ፥ ከመንገድ
ላይ ቆሞ አየ። በግንባሩም ወድቆ ሰገደለት። የእግዚአብሔርም መልአክ «አህያይቱ ሦስት ጊዜ ከፊቴ ዘወር
ባትል ኖሮ አንተን በገደልኩህ ነበር፥ መንገድህ በፊቴ የቀናች አይደለችምና አለው። በለዓምም፦ «በድያለሁ፤
አንተ በመንገድ ላይ በፊቴ እንደቆምህብኝ አላወቅሁም፤ እንግዲህ አሁን አትወድድ እንደሆነ እመለሳለሁ፤»
አለ። መልአኩም፦ «ከሰዎቹ ጋር ሂድ፤ ነገር ግን የምነግርህን ቃል ብቻ ለመናገር ተጠንቀቅ፤» አለው። በለዓም
መልአኩን አይቶ ያከበረው ፥ የሰገደለትም እግዚአብሔር ከገለጠለት በኋላ ነው። በመሆኑም ክብረ መላእክት
ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አለመሆኑን እንረዳለን። ስለዚህ ማንም ቢሆን እግዚአብሔር ካልገለጠለት
በስተቀር ቅዱሳንን አያከብርም።

በለዓም አስቀድሞ እግዚአብሔር ፥ በኋላም መልአከ እግዚአብሔር እንደተናገረው ከባላቅ መልእክተኞች ጋር


ሄደ። ባላቅም መምጣቱን ሰምቶ በአርኖን ዳርቻ ወዳለችው ወደ ሞዓብ ከተማ ሊገናኛቸው ወጣ። ባገኘውም
ጊዜ፦ «አንተን ለመጥራት የላክሁብህ አይደለምን? ለምንስ ወደ እኔ አልመጣህም? አንተን ለማክበር እኔ
አልችልምን?» አለው። በለዓም ግን፦ «እነሆ፥ ወደ አንተ መጥቼአለሁ፤ አሁን አንዳች ነገር ለመናገር
እችላለሁን? እግዚአብሔር በአፌ የሚያደርገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ፤» ሲል መለሰለት። ከባላቅም ጋር
ሄደ ፥ ወደ ቅጽር ግቢውም ገቡ። ባላቅም በሬዎችንና በጎችን አርዶ ወደ በለዓም ፥ ከእርሱም ጋር ወደአሉት
አለቆች ላከ። በበነጋውም ባለቅ በለዓምን ይዞ ወደ በአል ኮረብታ አወጣው፤ በዚያም ሆኖ የሕዝቡን አንድ
ወገን አሳየው። ዘኁ ፳፪፥፩-፵፩።

 በለዓም፦ ባላቅ ባዘጋጀለት ሰባት መሠዊያ ላይ ሰባት ወይፈኖችን እና ሰባት በጎችን ከሠዋ በኋላ፥ ባላቅን፦
«በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፤ እኔ እግዚአብሔር ቢገልጥልኝ፥ ቢገናኘኝም እሄዳለሁ፤ የሚገልጥልኝንም
እነግርሃለሁ፤» አለው። እግዚአብሔርም ለበለዓም ታይቶ ፥ ቃሉን በአፉ አኖረ፤ በለዓምም እግዚአብሔር
በነገረው መሠረት ወደ ባላቅ በተመለሰ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እርሱ መጥቶ፥ በምሳሌ ይናገር
ጀመር። «እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? እግዚአብሔር ያልተጣላውን እንዴት እጣላለሁ?»
ብሎ እስራኤልን መረቃቸው። ባላቅም፦ «ያደረግህብኝ ምንድን ነው? ጠላቶችን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤
እነሆም መባረከን ባረክሃቸው፤» አለው። በለዓምም፦ «በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ
የምጠነቀቅ አይደለምን?» አለ።

            ሁለተኛም፦ «በዚያ እነርሱን ወደማታይበት ወደ ሌላ ቦታ እባክህ ፥ ከእኔ ጋር ና፤ ከእነርሱ አንዱን


ወገን ብቻ ታያለህ፤ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያ እነርሱን ርገምልኝ፤» አለው። እንዲህም ማለቱ በለዓም
ብዛታቸውን አይቶ የፈራ መስሎት ነው። በሜዳ ወደ ተገነባ ግንብ ራስ ላይም ወሰደው ፥አዞረውም፤ ሰባት
መሠዊያዎችን ሠራ ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን ፥ አንድም አውራ በግ አሳረገ። በለዓምንም፦
«በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቈይ፤ እኔም እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንደ እሄዳለሁ፤» አለው። እግዚአብሔርም
በለዓምን አግኝቶ ተነጋገረው ፥ ወደ ባላቅም እንዲመለስ አዘዘው። ተመልሶም በምሳሌ እየተናገረ እስራኤልን
መረቃቸው። ባለቅ ቢቸግረው፦ «ከቶ አትርገማቸው ፥ ከቶም አትባርካቸው፤» አለ። በለዓም ግን፦
«እግዚአብሔር የተናገረኝን ቃል አደርጋለሁ ብዬ አልነገርሁህምን?» አለው። ባላቅም በለዓምን፦ «ና፥ ወደ ሌላ
ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚያ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድድ ይሆናል፤» ብሎ
በምድረ በዳ ወደ ተከበበው ወደ ፌጎር ተራራ ወሰደው። እንደተለመደው ሰባት መሠዊያዎችን ሠራ ፥ ሰባት
ወይፈኖችና ሰባት በጎችም መሥዋዕት ሆነው ቀረቡ። ዘኁ ፳፫፥፩-፳፱።

            በለዓም፦ እስራኤልን መባረክ በእግዚአብሔር ፊት መልካም እንደሆነ ባየ ጊዜ ፥ እንደ ልማዱ


ለማሟረት ወደ ፊት አልሄደም፤ ነገር ግን በምሥራቅ በኲል ወደአለው ምድረ በዳ ፊቱን መለሰ። ዓይኑንም
አንሥቶ እስራኤል በየነገዳቸው ሲጓዙ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ። (ለጊዜው አደረበት፥ አፉን
ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ አናገረው)። በምሳሌም እየተናገረ እስራኤልን መረቃቸው፦ «እንደ አንበሳና እንደ አንበሳ
ደቦል ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? (በልቶ፦ እንደ አባት አንበሳና እንደ ግልገል አንበሳ ይተኛል፤ ማን
ይቀሰቅሰዋል? የሚመርቁህ ሁሉ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ፤» አለ። ባላቅም
ተቆጥቶ እጁን አጨበጨበ፥ በለዓምንም፦ «ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም ፈጽመህ
መረቅሃቸው፤ ይህ ሦስተኛህ ነው፤ አሁንም ወደ ስፍራህ ሂድ፤ እኔ አከብርሃለሁ ብዬ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን
እነሆ ፥ ክብርህን ከለከለ፤» አለው።

  በለዓም የእግዚአብሔርን ቃል መተላለፍ እንደማይቻለው ከተናገረ በኋላ አሁንም በምሳሌ ይናገር ጀመር።
በትንቢቱም፦ «አየዋለሁ ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እባርከዋለሁ ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ
ይወጣል፤» አለ። ለጊዜው ከእነርሱ ነገሥታቱ ዳዊት ሰሎሞን ይወለዳሉ ሲል ነው። ለፍጻሜው ግን ከእነርሱ
የባሕርይ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚወለድ ነው። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦
«በክርስቶስ እውነት እነግራችኋለሁ፤ ሐሰትም አልናገርም። ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል፤
በጊዜው ሁሉ ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለ። በሥጋ ዘመዶቼና ወንድሞቼ ስለሚሆኑ እኔ
ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ።እኒህም ልጅነት፥ ክብር ፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው ፥ ተስፋም
የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ
ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን፤»  ብሏል። ሮሜ ፱፥፩-፭

            ከዚህ ታሪክ የምንማረው ፦ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ማዋረድ ፥ የመረቃቸውንም መርገም


የማይቻል መሆኑን ነው። ንጉሡ ባላቅ የእስራኤል መመረቅ አበሳጭቶታል። ዛሬም እግዚአብሔር ያከበራቸው
ቅዱሳን ስማቸው ሲጠራ፥ በመዝሙርና በእልልታ ሲመሰገኑ፥ ገድላቸው ሲነበብ፥ ተአምራቸው ሲነገር፥
አማላጅነታቸው ሲመሰከር የሚበሳጩ ሰዎች አሉ። የሚገርመው ነገር፥ እነዚህ ሰዎች ስማቸውን
እየጠራችሁ ብታመሰግኗቸው፥ ከሰውም በላይ አድርጋችሁ ብታከብሯቸው በደስታ ይሰክራሉ። ንጉሥ
ባላቅም የጠላው የእስራኤልን ክብር ነው፥ ለራሱ ሲሆን ግን በግድም ቢሆን አክብሩኝ ይላል።

፪፥፪፦ «ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናል፤» ማቴ ፪፥፪።

            በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ክፍል በቤተልሔም ጌታችን ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ ፥ ሰብአ
ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። አመጣጣቸውም፦ «ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ
መጥተናልና ፥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?» እያሉ ነበር።

            (ታሪክ)፦ እስክንድር የሚባል ንጉሥ እስክንድርያ የምትባል ሴት አግብቶ፦ አትሮብሎስን እና


ሕርቃሎስን ይወልዳል፤ በሚሞትበት ጊዜ ለሚስቱ፦ «ታናሹን አንግሠሽ፥ ታላቁን ካህን አድርገሽ ኑሪ፤»
ብሏታል። ይኽንንም ያደረገው አድልቶ ሳይሆን፦ ታናሹ ልጅ ሕርቃሎስ፦ «ብልህ ነው ፥ ሰው ማስተዳደር
ያውቃል፥ ብሎ ነው። እርሷም እንደነገራት አድርጋ ስትኖር፦ ሄሮድስ ወልደ ሐንዶፌር የእስራኤልን መንግሥት
በማናቸውም ምክንያት ይፈላለገው ነበርና፦ ከታላቁ ከአትሮብሎስ ጋር መላላክ ጀመረ። በመልእክቱም፦
«ታላቅ ሳለህ ታናሽ፥ አዋቂ ሳለህ አላዋቂ ያነገሡብህ በምን ምክንያት ነው? ጦርም አንሶህ እንደሆነ፥ ከእኔ
ወስደህ፥ እሱን ገድለህ ንገሥ፤» እያለ ገፋፋው። እርሱም እውነት መስሎት ጦር ተቀብሎ መጥቶ ፥
ወንድሙን ገድሎ ነገሠ።

            ሟች ሕርቃሎስ፦ አርስጥአሎስ የሚባል ልጅ ነበረውና በጥበብም ቢሉ፥ ተዋግቶም ነው ቢሉ


የአጐቱን ጆሮውን ቆረጠው። እንዲህም ማድረጉ እስራኤል አካሉ የጐደለ ስለማያነግሡ ነው። በዚህ መካከል
ሴረኛው ማርያ የምትባለውን እኅታቸውን አግብቶ ነገሠ። ምንም እንኳን እርሱ በጥበብ ፥ በተንኰል የነገሠ
ቢመስለውም መንግስት ከቤተ ይሁዳ አልወጣም። ምክንያቱም፦ የእስራኤል አባታቸው ያዕቆብ፦ «መንግሥት
ከይሁዳ አይጠፋም ፥ ምስፍናም ከአብራኩ ፥ ለእርሱ የሚጠብቀውን እስኪያገኝ ድረስ፤ የአሕዝብ ተስፋቸው
እርሱ ነውና፤» በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበርና ነው። ዘፍ ፵፱፥፲። ወንጌላዊው ማቴዎስ ሄሮድስን ያነሣው
በላዩ ላይ ሰማያዊ ንጉሥ ተወለደ ለማለት ነው። ሰብአ ሰገልም ይዘውት የመጡት ወርቅ ዕጣንና ከርቤም
የራሱ የሆነ «የት መጣ?» አለው።

            በገድለ አዳም እንደተጻፈው፦ እግዚአብሔር፦ ወርቅ ያመጣውን መልአክ ፥ ዕጣን ያመጣውን


መልአክና ከርቤ  ያመጣውን መልአክ የመጋባትን ተግባር ያስረዱት ዘንድ ወደ አዳም ላካቸው። እነርሱም
አዳምን፦ «ወርቅን ውሰድ፥ ለማጫ ይሆናት ዘንድ ለሔዋን ስጣት ፤ እርሷና አንተ አንድ አካል ትሆኑ ዘንድ
ቃል ኪዳንም አድርግላት፤ የእጅ መንሻ ዕጣን ከርቤም ስጣት፤» አሉት። እርሱም የተባለውን ፈጸመ። አዳም
ሔዋንን ያገባው ከገነት በወጣ በሁለት መቶ ሦስተኛው ቀን ነው።

            ይህ፦ ወርቅ ፥ዕጣንና ከርቤ፦ ሲወርድ ፥ሲዋረድ ከአባታቸው እጅ ገብቷል፤ ዠረደሸት የሚባል ፈላስፋ
አባት ነበራቸው፤ በቀትር ጊዜ ከነቅዓ ማይ(ከውኃ ምንጭ) አጠገብ ሁኖ ፍልስፍና ሲመለከት፦ ድንግል በሰሌዳ
ኮከብ ተስላ፥ ሕፃን ታቅፋ አየ። ወዲያውም በሰሌዳ ብርት ቀርፆ አኖረው፤ በሚሞትበት ጊዜም፦ «እንዲህ
ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ስጡ፤» ብሏቸው ነበር። እንዳለውም
ጊዜው ሲደርስ ኮከቡ ታየ፤ ያም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ ደርሶ እስኪቆም ድረስ
ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም አይተው ደስ አላቸው። ወደቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር አገኙት፤
ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው ወርቅና ዕጣን፥ ከርቤም እጅ መንሻ አቀረቡለት። በዚህ
ዓይነት ሰብአ ሰገልን የመራ ኮከብ ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

፪፥፫፦ «የሚያበራም የአጥቢያ ኮከብ እኔ ነኝ፤» ራእ ፩፥፲፮

            የአጥቢያ ኮከብ የሚባለው በማለዳ የሚወጣው ኮከብ ነው። ይኸውም የጨለማውን ጊዜ ማለትም
የሌሊቱን መገባደድ የሚያመለክት ነው። በራእይ ዮሐንስ እንደተገለጠው፦ «የሚያበራም የአጥቢያ ኮከብ እኔ
ነኝ፤» ያለው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲህ ያለበትም ምክንያት፦
«ኮከብ ይሠርቅ እምያዕቆብ፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤» ተብሎ የተነገረልኝ እኔ ነኝ፥ ለማለት ነው።
            ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በተዋሕዶ ሰው የሆነው አምስት ሺህ አምስት
መቶ ዘመን ሲፈጸም ነው። ይህ ዘመን የፍዳ፥ የኲነኔ፥ የጨለማ ዘመን ነበር። በመሆኑም ጨለማውን
ለማገባደድ የአጥቢያ ኮከብ እንዲታይ፥ የጨለማ ዘመን የተባለውን ዘመነ ፍዳ፥ ዘመነ ኲነኔ አስወግዶ ዘመነ
ምሕረትን ለመተካት የአጥቢያ ኮከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ታይቷል፥ (ተገልጧል)። ይህ የአዲስ ኪዳን ዘመን
የአጥቢያ ኮከብ የታየባት ሰማይም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት።

፪፥፬፦ ከዋክብት፤

            በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው እርሱን እንዲመስሉ በእግዚአብሔር የተወሰነላቸው ቅዱሳንም


ከዋክብት ናቸው። ኮከብ ብርሃን የተሣለበት ሰሌዳ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ
የተሣለባቸው፥ የተቀረጸባቸው የብርሃን ሰሌዳ ናቸው። ይኽንን በተመለከተ ነቢዩ ዳንኤል፦ «ወእለሰ ለበዉ
ይበርሁ ከመ ብርሃነ ሰማይ ፥ ወእምነ ጻድቃን ብዙኃን ከመ ከዋክብተ ሰማይ እስከ ለዓለም፤ ጥበበኞችም እንደ
ሰማይ ፀዳል፥ ከጻድቃንም ብዙዎች እንደ ከዋክብት ለዘለዓለም ያበራሉ።» በማለት በትንቢት መጽሐፉ
ተናግሯል። ዳን ፲፪፥፫። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «ካልእ ክብሩ ለፀሐይ፥ ወካልእ ክብሩ ለወርኅ፤
ወካልእ ክብሮሙ ለከዋክብት፤ ኮከብ እምኮከብ ይኄይስ ክብሩ። የፀሐይ ክብሩ ሌላ ነው ፥ የጨረቃም ክብሩ
ሌላ ነው፤ (የፀሐይ ክፍለ ብርሃን ከጨረቃ ክፍለ ብርሃን ልዩ ነው፥ የጨረቃ ክፍለ ብርሃንም ከፀሐይ ክፍለ
ብርሃን ልዩ ነው)፤ የከዋክብትም ክብራቸው ሌላ ነው፤ (የከዋክብትም ክፍለ ብርሃናቸው ልዩ ልዩ ነው)፤ ኮከብ
ከኮከብ በክብር ይበልጣልና። (ከአንዱ ኮከብ ክፍለ ብርሃን የሌላው ኮከብ ክፍለ ብርሃን ልዩ ነው፥
ይበላለጣሉ)።» እያለ የተናገረው ስለ ቅዱሳን ነው። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፵፮።

            ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በመጋዝ ተተርትረው ፥ በሰይፍ ተመትረው፥ በእሳት ተቃጥለው፥


በሠረገላ ተፈጭተው ፥ ያለፉትን ሰማዕታት በፀሐይ ፥ በዓት ወስነው፦ ድምፀ አራዊትን ፥ጸብአ አጋንንትን ፥
ግርማ ሌሊትን ሳይሰቀቁ የኖሩትን መነኰሳትን በጨረቃ ሰብአ ዓለምን (በዓለም እየኖሩ የጸኑትን) በኮከብ
መስሎ ተናግሯል። አንድም ሁሉ በሁሉ አለ ብሎ ፥ ከሰማዕታት፦ እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፥ እንደነ ቅዱስ
ቂርቆስ፥ እንደነ ቅዱስ መርቆሬዎስ ያሉትን በፀሐይ፤ በተዋረድ ከዚያ ዝቅ ያሉትን በጨረቃ፤ ከዚያም ዝቅ
ያሉትን በኮከብ መስሏል። ከመነኮሳትም፦ እንደነ እንጦንስ ፥ እንደነ መቃርስ፥ እንደነ አቡነ ተክለሃይማኖት
ያሉትን በፀሐይ፤ በተዋረድ ከዚያ የሚያንሱትን በጨረቃ፤ ከዚያም የሚያንሱትን በኮከብ መስሏል። ከሰብአ
ዓለምም፦ እንደነ አብርሃም ፥ እንደነ ኢዮብ ያሉትን በፀሐይ፥ በተዋረድ ከዚያ የሚያንሱትን በጨረቃ፤
ከዚያም የሚያንሱትን በኮከብ መስሏል። እግዚአብሔር፦ አብርሃምን፦ «ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት
አበዛልሃለሁ፤»ያለው ከእርሱ ወገን ስለሚወለዱ ቅዱሳን ነበር። ዘፍ ፲፭፥፭።

፫፦ ብርሃን፤
 እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ፩ኛ ዮሐ ፩፥፭። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤
(ኅልፈት ጥፋት የለበትም)፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል። (አይደፈርም)፤ አንድ ሰው እንኳ
አላየውም፤ (መለኰታዊ ባሕርዩን መርምሮ የደረሰበት የለም)፤ ሊያየውም አይቻለውም፤ (ባሕርዩን መርምሮ
ሊደርስበት የሚችል የለም)፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤» ያለው እግዚአብሔርን ነው። ፩ኛ
ጢሞ ፮፥፲፮።

 ብርሃናትን፦ ፀሐይ ፥ ጨረቃ ፥ ከዋክብትን የፈጠረ እርሱ ነው። ዘፍ ፩፥፫። እነዚህ የሚያልፉ ብርሃናት
ናቸው፤ ይኽንንም፦ «ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን
አትሰጥም ፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።» በማለት ጌታችን በወንጌል
ነግሮናል። ማቴ ፳፬፥፳፱። በመጽሐፈ ሲራክ ላይ ደግሞ፦ «ከፀሐይ የሚበራ ምን አለ? እርሱም እንኳን
ያልፋል።» የሚል ተጽፏል። ሲራ ፲፯፥፴፮።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት
ብርሃንን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም።» በማለት እርሱ ብርሃን እንደሆነ ነግሮናል። ዮሐ
፰፥፲፪። «በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ፤» በማለትም፦ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዓይነ ስውር ሆኖ
የተወለደውን ብላቴና ፈውሶታል። ዮሐ ፱፥፭። በዚህም አማናዊ ብርሃንነቱን አሳይቷል። ነቢዩ ኢሳይያስ፦
«በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።» በማለት ትንቢት
የተናገረው ለእርሱ ለጌታችን ነበር። ኢሳ ፱፥፪ ፣ ማቴ ፬፥፲፬።

፫፥፩፦ ብርሃናት፤

            በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው እርሱን እንዲመስሉ የተወሰነላቸው ቅዱሳንም ብርሃን ናቸው።


ይኽንንም፦ ራሱ ብርሃነ ዓለም አምላክ ፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤»
በማለት በወንጌል ተናግሯል። ማቴ ፭፥፲፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «እንደ እግዚአብሔር ልጆች
ንጹሓንና የዋሃን ትሆኑ ዘንድ፥ በማያምኑና በጠማሞች ልጆች መካከል ነውር ሳይኖርባችሁ በዓለም እንደ
ብርሃን ትታያላችሁ፤» ብሏል። ፊል ፪፥፲፭። ራሱንም ጨምሮ ሲናገር ደግሞ፦ «በጨለማ ውስጥ ብርሃን
ይብራ ፥ ያለ እግዚአብሔር፦ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን ዕውቀት ብርሃን በልባችን አብርቶልናልና፤»
ብሏል። ፪ኛ ቆሮ ፬፥፮። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ብርሃን ለጻድቃን ፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ፤» ያለው ለዚህ
ነው። መዝ ፺፮፥፲፩። ነቢዩ ኢሳይያስም፦ «እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ በመቅሰፍቱ
የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት ፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን ፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን
ብርሃን እጥፍ ይሆናል፤» ያለው ስለ ቅዱሳን ነው። ኢሳ ፴፥፳፮።

ነገረ ቅዱሳን ክፍል፦ ፲፩


 እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው፤ የሚታየውን እና የማይታየውን፥ የሚያልፈውን እና የማያልፈውን ፈጥሮ
የሚገዛው፥ የሚያስተዳድረው፥ በሥርዓት የሚመራውና የሚመግበው ሁሉን ቻይ በመሆኑ ነው። ዘፍ ፩፥፩-
፴፮። በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑ ሥላሴ፦ በአብርሃም ድንኳን በእንግዳ አምሳል በተገኙ ጊዜ፦ «እንደ
ዛሬ ጊዜ ተመልሼ በረድኤት ወደ አንተ በመጣሁ ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤» ብለውት ነበር። ሣራ
በድንኳኑ ደጅ ከአብርሃም ኋላ ቆማ ሳለች ይኽንን ነገር ሰማች። አብርሃምና ሣራ የጐልማስነታቸው ወራት
አልፎባቸው ፈጽመው አርጅተው ነበር። በሴቶች የሚሆነው ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም፦ «ሲያረጁ
አምባ ይዋጁ፤» እንዲሉ፦ «እስከዛሬ ድረስ ገና ቆንጆ ነኝን?» ብላ፥ አንድም «ጌታዬ አርጅቷል እኔ ገና ነኝን?»
ብላ፥ አንድም «ጌታዬ አላረጀምን? ብላ» ተጠራጥራ ሳቀች። ሥላሴም፦ አብርሃምን፥ «ሣራን ለብቻዋ
በልብዋ ምን አሳቃት? እስከ ዛሬ ገና ነኝን?» ብላ፥ አንድም «ጌታዬ አርጅቷል እኔ ገና ነኝን? በእውነትስ
እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅቷል። እነሆ ፥እኔም አርጅቻለሁ ብላለችና። በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው
ነገር አለን?» ብለውታል። ዘፍ ፲፰፥፲። እግዚአብሔር ሣራን በቸርነት፥ በረድኤት ጐበኛት፤ «ልጅ
ትወልጃለሽ፤» ብሎ እንደተናገረ አደረገላት። ሙቀት ልምላሜ ከተለያት በኋላ እግዚአብሔር በተናገረው
ወራት ለአብርሃም በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ወለደችለት። ዘፍ ፳፩፥፩።

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል፦ ከእግዚአብሔር ተልኮ መጥቶ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር አምላክን
በድንግልና ፀንሳ፥ በድንግልና እንደምትወልድ ለእመቤታችን በነገራት ጊዜ፦ «መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤
የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል። እነሆ
ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን አልሳቤጥም  እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል
የነበረችው ከፀነሰች እነሆ፥ ይህ ስድስተኛ ወር ነው። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።» ብሏታል።
ሉቃ ፩፥፴፭።
ነቢዩ ዳንኤል፦ የባቢሎኑን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ሕልም በፈታለት ጊዜ፦ «ልዑልም የሰዎችን መንግሥት
እንዲገዛ ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ መኖሪያህም
ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደበሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፤ ሰባት ዘመናትም
ያልፉብሃል። የዛፉንም ጉቶ ተዉት ማለቱ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደሆነ እስክታውቅ ድረስ መንግሥትህ
ይቈይልሃል። ንጉሥ ሆይ! ስለዚህ  ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤
በጽድቅና በምጽዋት ትድናለህ፤ በደልህንና ኃጢአትህንም ለድሆች በመራራት እግዚአብሔር ይቅር ይልሃል።»
ብሎት ነበር። ዳን ፬፥፳፭-፳፯። ከዐሥራ ሁለት ወር በኋላም ንጉሡ፦ «የባቢሎን ቤተ መንግሥት መኖሪያ
እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?» ብሎ በትዕቢት ተናገረ። ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ
(ተናግሮ ሳይጨርስ) ድምፅ  ከሰማይ መጣ፦ ነቢዩ ዳንኤል ነግሮት የነበረውን መልሶ ነገረው። በዚያም ሰዓት
ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጉሩም እንደ አንበሳ፥ ጥፍሩም እንደ ንስር ፥እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች
ተለይቶ ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

          ከሰባት ዓመት በኋላ ነቢዩ ዳንኤል፦ የናቡከደነፆር ልቡ በጸጋ እንደተመለሰ አውቆ፦ «ሂዳችሁ
አምጡት፤» ብሎ ሹማምንቱን ልኳቸዋል። እነርሱም ከዛፍ ሥር ቁሞ አግኝተውት አምጥተውታል።
እርሱም፦ «ከእነዚያም ዘመናት በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤
ልዑሉንም ባረክሁ፤ ለዘላለም የሚኖረውንም አመሰገንሁ፤ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘለዓለም ግዛት ነውና።
በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል
እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚቃወማት ወይም ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።» በማለት፦
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ እንደሆነና የሚሳነውም ነገር እንደሌለ መስክሯል። ዳን ፬፥፳፰-፴፭።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱ፦ «እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?»


ብለው አድንቀው በጠየቁት ጊዜ፦ «በሰው ዘንድ ይህ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል፤»
በማለት መልሶላቸዋል። ማቴ ፲፱፥፳፮። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር
እንደሌለ ሲናገር፦ «እንደወደደም በእርሱ የወሰነውን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ገለጠልን። የሚደርስበትንም
ጊዜውን ወሰነ፤ በሰማይና በምድር ያለውም ሁሉ ይታደስ ዘንድ ክርስቶስን በሁሉ ላይ አላቀው። እንደ ፈቃዱ
ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰን በእርሱ ርስትን ተቀበልን።» ብሏል። ኤፌ
፩፥፱-፲፩።

፪፦ «የሚሳናችሁ ነገር የለም፤» ማቴ ፲፯፥፳።

 ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ለነቢያቱ ለሙሴ ለኤልያስ፥ ለሐዋርያቱ ለጴጥሮስ


፥ለዮሐንስና ለያዕቆብ ክበረ መንግስቱን ገልጦ ከደብረ ታቦር ሲወርድ ሕዝቡን ከእግረ ደብረ ሲጠብቁት
አገኛቸው። ያ ሕዘብ፦ የተቀሩትን ደቀመዛሙርት፦ «መምህራችሁ ወዴት ሄደ?» እያሉ ሲያደክሟቸው፥
ሲያዋክቧቸው ቆይተዋል። አንድ ከነገር ያልገባ ሰው፥ ለብቻው ቆይቶ፥ ወደ ጌታ ቀረበና፦ «አቤቱ፥ ልጄን
ማርልኝ፤ ክፉ ጋኔን ጨረቃ ስትወጣ (በየወሩ መጀመሪያ) ያሠቃየዋልና፥ ይዞ ይጥለዋልና፤ ብዙ ጊዜም ወደ
እሳት ይጥለዋል፤ ወደ ውኃም የሚጥልበት ጊዜ አለ። ወደ ደቀመዛሙርትህም አመጣሁት፤ እነርሱም ማዳን
ተሳናቸው።» እያለ ከምልጃ ጋር ሰገደ።
  ከዚህ በኋላ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «የማታምን ጠማማ
(እንቢተኛ፥ አሉተኛ) ትውልድ እስከመቼ ድረስ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከመቼስ እታገሣችኋለሁ? (ዝም
እላችኋለሁ)? አላቸው። ደቀመዛሙርቱ፦ ንጉሥ በሌለበት ከንቲባ መቅጣት እንዲገባው ባለማወቃቸው፦
«አድኑልኝ፤» ቢላቸው፦ «መምህራችን በሌለበት ጊዜ አይቻለንም፤» ብለዋል። ጌታችን፦ «እስከ መቼ ድረስ
በዚህ ምድር ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤» ያላቸው ለዚህ ነው። ምክንያቱም፦ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደ
ቀደመ ክብሩ መመለሱ፥ ወደ ሰማይ ማረጉ አይቀርምና ነው። «እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ፤» ያለበት
ምክንያት ደግሞ፦ «ንጉሥ ባለ ጊዜ ከንቲባ መሥራት መቅጣት እንደማይገባው ባለማወቃቸው፦
«መምህራችን ባለበት እንጂ እርሱ በሌለበት አይሆንልንም፤» በማለታቸው ነው። ይኸውም፦  «እኔ ካለሁማ
እኔው እሠራዋለሁ፤» ሲላቸው ነው። እንዳለውም በሽተኛውን «ወደ እኔ አምጡልኝ፤» ብሎ ጋኔኑን ገሠጸውና
(ፃዕ መንፈስ እርኲስ አለውና) ከእርሱ እንዲወጣ አደረገው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ዳነ።

 የጌታ ደቀመዛሙርት ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀረቡና፦ «ስለምን እኛ ማውጣት ተሳነን?» አሉት። ጌታችንም፦
«ስለ እምነታችሁ መጉደል ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍንጭ ቅንጣት የሚያህል  እምነት ቢኖራችሁ
ይሀን ተራራ ከዚህ ወደዚያ ተነቅለህ ሂድ ብትሉት ይፈልሳል፤ የሚሳናችሁ ነገርም የለም። ይህ ዓይነት ግን ያለ
ጾምና ጸሎት አይወጣም፤» አላቸው። ማቴ ፲፯፥፲፬-፳፪።

 ሰናፍጭ፦ የፍጹምነት ምሳሌ ናት፤ ሰናፍጭ እንደሌላው የእህል ዘር ነቅ የለባትም፥ ወንጌልም ነቅዕ፣ ኑፋቄ
የለባትም፤ ሰናፍጭ ላይዋ ቀይ ውስጧ ነጭ ነው፤ ወንጌልም በላይ ደማችሁን አፍስሱ ትላለች፥ በውስጥ ግን
ብሩኅ ተስፋ ያለት ሕግ ናት። አንድም ሰናፍጭ ጣዕሟ ምረሯን (ምረቷን) ያስረሳል፥ ወንጌልም ተስፋዋ
መከራዋን ያስረሳል፤ አንድም ሰናፍጭ ቊስለ ሥጋን ታደርቃለች፥ ወንጌልም ቊስለ ነፍስን ታደርቃለች፤
አንድም ሰናፍጭ ደም ትበትናለች፥ ወንጌልም አጋንንትን ፣ መናፍቃንን ትበትናለች፤ አንድም ሰናፍጭ
ከምትደቈስበት ተሐዋስያን አይቀርቡም ፥ ወንጌልም ከምትነገርበት (ከምትተረጐምበት፣
ከምትመሠጠርበት) አጋንንት፣ መናፍቃን አይደርሱም ፥ ቢደርሱ ይረታሉ፤ አንድም ሰናፍጭ ከበታችዋ
ያሉትን አትክልት ታመነምናለች፥ ወንጌልም በትርጓሜዋ፣ በሚሥጢሯ የመናፍቃንን ጉባዔ ታጠፋለች፥
ትምህርታቸውንም ከንቱ ታደርጋለች፤ ሰናፍጭ አንድ ጊዜ የዘሯት እንደሆነ በየዓመቱ ዝሩኝ አትልም፥ ተያይዛ
ስትበቅል ትኖራለች፥ ወንጌልም በመቶ ሃያ ቤተሰብ ተጀምራ እስከ ምጽአት ድረስ ስትነገር ትኖራለች።
ሰናፍጭ ስትዘራ ከአዝርዕት ሁሉ ታንሳለች፥ ባደገች ጊዜ ግን ከአዝርዕት ሁሉ ትበልጣለች። ከአዕዋፍ
መጥተው ማረፊያ፥ መስፈሪያ እስኪያደርጓት ድረስ ደግ ዕፅ ትባላለች።  ወንጌልም ስትጀመር በትንሹ በመቶ
ሃያ ቤተሰብ ነበር፥ በጉባዔ በተነገረች ጊዜ ግን ከሕግጋት ሁሉ ትበልጣለች። ሕዝብም አሕዛብም
እስኪያምኑባት ድረስ ደግ ሕግ ሆናለች።
          አምላካችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት
ቢኖራችሁ፤» ማለቱ፥ ጥርጥር የሌለው ፍጹም ሃይማኖት ቢኖራችሁ ሲላቸው ነበር። ተራራ፦ ያለው ደግሞ
ስለ ትዕቢቱ ዲያቢሎስን ነው። «የሚሳናችሁ ነገር የለም፤» ማለቱም፦ «ቸግሯችሁ የሚቀር ነገር የለም፤»
ሲላቸው ነው። አንድም ተራራውም ቢሆን በሚሰጣቸው ሥልጣን በተአምር የሚነሣላቸው ስለሆነ ነው።
ይኸውም ሙሴ ባሕር እንደከፈለው፥ ኢያሱም ፀሐይ እንዳቆመው ዓይነት ማለት ነው።

          ታሪክ፦ በአብርሃም ሶሪያዊ ጊዜ፦ ለሊቀጳጳሱ አንድ አይሁዳዊ ወዳጅ ነበረው፤ ሁለቱም ለንጉሡ
ባለሞሎች ነበሩና በየፊናቸው ንጉሡን ለመጠየቅ ሲሄዱ ከዚያ ይገናኛሉ። የሃይማኖት ነገር አንሥተው
ሲከራከሩም ሁል ጊዜ ሊቀጳጳሱ አይሁዳዊውን ምላሽ ያሳጣዋል። ከዕለታት በአንድ ቀን አይሁዳዊው
ለብቻው ገብቶ በሊቀ ጳጳሱ ላይ ነገር ሠራ። ወደ ንጉሡ ቀርቦ፦ «የእነዚህ የክርስቲያኖች ሃይማኖታቸው
ደካማ ነው፤» አለው። ንጉሡ ግን፦ «እንግዲያስ እየተከራከሩ ለምን ምላሽ ያሳጧችኋል፤» አለው። በዚህን
ጊዜ አይሁዳዊው፦ «ወንጌላቸው፦ የሰናፍንጭ ቅንጣት ያህል ሃይማኖት ቢኖራችሁ ተራራ ማንሣት
ይቻላችኋል ትላለች፤ አድርጉ ቢሏቸው ግን አያደርጉትም፤» አለ። ንጉሡም፦ ሊቀ ጳጳሱን ሲያገኘው ነገሩ
እየጠፋው፥ ነገሩን ሲያስታውሰው ደግሞ ሊቀጳጳሱን እያጣው ብዙ ቀናት አለፉ። በኋላ ላይ ግን ሊቀጳጳሱ
ባለበት ነገሩ ትዝ አለውና ጠየቀው፥ ሊቀጳጳሱም፦ «እውነት ነው፥ በወንጌል ተጽፏል፤» አለው። ንጉሡም፦
«እንኪያስ የዚህ ሁሉ ክርሰቲያን እምነት ቢደመር ከተራራ ይበልጣልና ሠርተህ አሳየኝ፤» አለው።
ሊቀጳጳሱም ንጉሡን፦ «ቀን ስጠኝ ሠርቼ አሳይሃለሁ፤» ቢለው ሦስት ቀን ሰጠው።

          ሊቀ ጳጳሱ ቀጥታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ፥ ከሥዕለ ማርያም ሥር ተንበርክኮ ለእመቤታችን


ለቅድስት ድንግል ማርያም አመለከተ። እመቤታችንም፦ «ልጄ፥ እንዲህ ያለው ላንተ አይደረግልህም፥
የሚደረግለት አለ፥ እርሱም ስምዖን አንድ ዓይና ነው፥ ተርታ ሰው መስሎ ከገበያ እንጨት ሲሸጥ ታገኘዋለህ፥
ሂደህ እመቤታችን ነግራኝ ነው ብለህ ንገረው፥ አለበለዚያ በጀ አይልህም፤» አለችው። ቢሄድ እንደነገረችው
ሆኖ አገኘው፥ እየፈራም ሂዶ፥ በስተኋላው ልብሱን ቢይዝ፥ «የተሰወረውን ጸጋዬን አወቀብኝ፤» ብሎ
ተቆጣው። «በሀገርህ ድኃ አይኖርበትም፤» ብሎ ጮኸበት። በዚህን ጊዜ ሊቀጳጳሱ፦ «እመቤታችን ልካኝ
ነው፤» ብሎ በግልጥ ነገረው።

          በዚህ ጊዜ ስምዖን አንድ ዓይና፦ ለሊቀ ጳጳሱ፦ «የእኔን ማንነት አትግለጥብኝ፤ ሂደህ ክርስቲያኖችን
ከተራራው ፊት ለፊት፥ አሕዛብን ደግሞ ከተራራው ጀርባ እንዲሆኑ አድርገህ፥ ካህናቱን ልብሰ ተክህኖ
አልብሰህ፥ መስቀል ጽንሐ አስይዘህ ቆየኝ፤ አንተ እኔ የምሠራውን ሥራ እያየህ ሥራ፥ ሕዝቡ ደግሞ አንተ
የምትሠራውን እያዩ ይሥሩ፤» አለው። ሊቀጳጳሱም ቀድሞ ሂዶ የተባለውን ሁሉ አደረገ። በመጨረሻ፦ አርባ
አንደ ኪርያላይሶን አድርሰው ሰግደው ሲነሡ ተራራው ብድግ አለ፥ በተራራው ሥርም በወዲያና በወዲህ
ያሉት ተያዩ፥ በዚህ ዓይነት ተራራው እየሰገዱ ሲነሡ ሦስት ጊዜ ብድግ ብሏል። በዚህም፦ «የሚሳናችሁ ነገር
የለም፤» የሚለው ቃለ ወንጌል ተፈጽሞላቸው አሕዛብን አሳፍረዋል። የእምነታቸውም ኃይል ጌታ
እንደተናገረ ጾምና ጸሎት ነበር። እንግዲህ እኛም እንደተሰጠን ጸጋ መጠን በእምነት ከጸናን፥ እምነታችንን
በሥራ ከገለጥን፥ ጾምን ጸሎትን ገንዘብ ካደረግን፥ በሥጋ ከባድ መስሎ የታየን ሁሉ ቀላል ነው።

፪፥፩፦ «አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ፤»

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ረሀብ የሚስማማውን የሥጋን ባሕርይ


በመዋሐዱ በማለዳ ወደ ከተማ ሲወጣ ተራበ። በመንገድም አጠገብ የበለስን ዛፍ አይቶ ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር
ግን ከቅጠል በቀር ምንም ፍሬ አለገኘባትም፤ «እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይኑርብሽ፤» አላት፤
ያንግዜውንም በለሲቱ ደረቀች። ደቀመዛሙርቱም አይተው፦ «ይህች በለስ እንዴት ወዲያውኑ ደረቀች?»
ብለው አደነቁ። ጌታችንም መልሶ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ፥ ባትጠራጠሩም በበለሲቱ
እንደተደረገው ብቻ የምታደርጉ አይደለም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት
ይደረግላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።» ብሏቸዋል። ማቴ ፳፩፥፲፰-፳፪።

          ፍሬ አልባ በለስ የተባሉት፥ ሃይማኖት ከምግባር የታጣባቸው እስራኤል ዘሥጋ ናቸው፤ በለሷን
እንደመቅረብ ከእነርሱ ተወልዷል፥ በመካከላቸው ተመላልሷል፥ የቃሉን ተምህርት አስተምሯቸዋል፥ የእጁን
ተአምራት አሳይቷቸዋል። አንድም ፍሬ አልባ በለስ የተባለች ኦሪት ናት፥ ምክንያቱም ሕይወትን አፍርታ
አልተገኘችምና ነው። በለሷ ወዲያው እንደደረቀች ኦሪትም ፈጥና አልፋለች፤ አንድም ፍሬ አልባ የተባለች
ኃጢአት ናት፤ ጌታችን ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ የበለስ ቅጠሉ ሰፊ እንደሆነ ሁሉ ኃጢአትን ሰፍታ ሰፍና
አግኝቷታል። «በአንፃረ በለስ ረገማ ለኃጢአት፤ በበለስ አንፃር ኃጢአትን ረገማት፤» እንዲል፦ «በአንቺ
ምክንያት በመጣ ፍዳ የሚያዝ አይኑር፤» አላት። በእርሱ በጌታችን የኃጢአት ሥሯ ደረቀ፥ ቅጠሏ ጠወለገ።
በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፥ ቆይቶ ይቆመጥጣል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ያሰኛል፥ በኋላ ግን ይጸጽታል፥
አንድም እንደመምረር ምረረ ገሃነምን ያመጣል። እኛስ ብንጐበኝ የመንፈስን ፍሬ አፍርተን እንገኝ ይሆን?
«የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር ፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ምጽዋት፥ ቸርነት፥እምነት፥ ገርነት፥ ንጽሕና
ነው።» ገላ ፭፥፳፪።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረ፦ ቅዱሳን በዚህ ዓለም በሃይማኖት
ሊሠሩት ያልቻሉት ምንም ነገር የለም። በጾም በጸሎት ተወስነው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደርጎላቸዋል፥
«የሚሳናችሁ ነገር የለም፤ አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኙታላችሁ፤» የተባለው
ተፈጽሞላቸዋል። እንግዲህ ነገረ ቅዱሳንን መጠራጠር በጌታ ተቃራኒ፦ «የሚሳናቸው ነገር አለ፤» ማለት
እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል።

፪፥፪፦ «በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን እርሱም ይሠራል፤»

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ አንዱ ፊልጶስ፦ «አብን


አሳየንና ይበቃናል፤ (መስማቱ ይበቃናል፥ መስማቱ በማየት ይፈጸምልናል፥ ለናፍቆት፣ ለዕሤት ፣ ለደጅ ጥናት
ይሆንልናል)፤» ብሎት ነበር። ጌታችን ግን፦ «ፊልጶስ፥ ይህን ይህል ዘመን አብሬአችሁ ስኖር አታውቀኝምን?
(አላወቅኸኝምን)?  እኔን ያየ አብን አየ፤ እንግዲህ እንዴት አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም
በእኔ አንዳለ (ህልዋን እንደሆንን፥ በህልውና፣ በመለኰት፣ በስልጣን፣ በፈቃድ፣ በባህርይ፣ አንድ እንደሆንን)
አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ (ከራሴ ብቻ አንቅቼ) የተናገርኩት አይደለም፤ በእኔ ያለ
አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ ። (በአብ ልብነት የታሰበ ነው)። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ
እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑ። (ይህን ሥራ አምላክ ቢሠራው አንጂ ዕሩቅ ብእሲ አይሠራውም
ብላችሁ እመኑ)።» አለው።

          ከዚህ በኋላ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ደቀመዛሙርቱን፦ «እውነት እውነት
እላችኋለ ሁ፤ በእኔ የሚያምን (ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ ሰው የሆነ የባሕርይ አምላክ ነው፥ ከባህርይ አባቱ
ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባህርይ፣ በህልውና፣ በሥልጣን በፈቃድ፣ በመለኰት አንድ
ነው፥ ብሎ የሚያምን) እኔ የምሠራውን ሥራ (ያደረግኋቸውን ተአምራት) እርሱም ይሠራል፤» ብሏቸዋል።
ዮሐ ፲፬፥፰-፲፪። ቅዱሳን ሐዋርያትን በመረጣቸውም ጊዜ፦ « ሄዳችሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች
እያላችሁ አስተምሩ። ድውያንን ፈውሱ፤ ሙታንንም አንሡ፤ ለምጻሞችንም አንጹ፤ አጋንንትንም አውጡ፤
ያለ ዋጋ የተቀበላችሁትን ያለ ዋጋ ስጡ፤» ብሏቸው ነበር። ማቴ ፲፥፮-፰። ከትንሣኤው በኋላም፦ «ይህችም
ምልክት በስሜ የሚያምኑትን ትከተላቸዋለች፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋም ( ባላደጉበት፥
ባልተማሩት፥ ተናጋሪም አድማጭም ሕዝብ ባለው ቋንቋ) ይናገራሉ። እባቦችንም በእጃቸው ይይዛሉ፤
የሚጎዳቸውም ነገር የለም፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡም የሚጎዳቸው የለም፤ በድውያን ላይም እጃቸውን
ይጭናሉ፤ ድውያንም ይፈወሳሉ።» በማለት ተናግሮላቸዋል። ማር ፲፮፥፲፮-፲፰።

፪፥፫፦ «ከዚህም የሚበልጥ ይሠራል፤»

 ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ


እርሱም ይሠራል፤» ካለ በኋላ፦ «ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፤» ብሏል። ይህም፦ ፍጡር ከፈጣሪው በላይ
የሚሠራ ሆኖ አይደለም። እርሱ፦ ወንጌልን ያስተማረው፥ ተአምራትን ያደረገው ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር
ነው፥ እነርሱ ደግሞ ብዙ ዘመን ስለሚያስተምሩ ብዙ ተአምራትንም ስለሚያደርጉ ነው። ዕውራንን
በማብራት፥ አንካሳዎችን በማርታት፥ ድውያንን በመፈወስ፥ ሙታንን በማስነሣት፦ በቊጥር የበዙ
ተአምራትን ስለሚያደርጉ ነው። ወንጌልንም በማስተማር ረገድ፥ እርሱ መቶ ሃያውን ቤተሰብ አስተምሯል ፥
እነርሱ ደግሞ በቊጥር ከዚህ የበዙ ደቀመዛሙርትን ስለሚያስተምሩ ነው። «በሐዋርያት እጅም በሕዝብ
ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤ በቤተ መቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ነበሩ።
ሕዝቡም እጅግ ያከብሩአቸው ነበረ። ከሌሎችም ይቀርባቸው ዘንድ አንድ ስንኳን የሚደፍር አልነበረም።
በጌታችንም የሚያምኑ ብዙዎች ይጨመሩ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙዎች ነበሩ።» ይላል። የሐዋ ፭፥፲፪-
፲፫።

፫፦ ጌታችን ያደረጋቸው ተአምራት፤


ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው አያሌ ተአምራትን አድርጓል። እነዚህንም በቃል ተናግረዋቸው፥ በፊደል
ቀርጸዋቸው የሚወስኗቸው አይደሉም። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፦ «ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር
ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ሁሉ ባልበቃቸውም ይመስለኛል፤» ያለው
ለዚህ ነው። ዮሐ ፳፩፥፳፭።

፫፥፩፦ ማየት የተሳናቸውን መፈወሱ፤

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በዓይነ ሥጋ ማየት የተሳናቸውን በተአምራት፥ ዓይነ
ልቡና ቸው የታወረባቸውን ደግሞ በትምህርት አብርቶላቸዋል። ሁለት ዕውራን፥ «የዳዊት ልጅ ሆይ፥
ራራልን፤» ብለው እየጮኹ ተከተሉት። ጌታችንም ለእነርሱ ርቆ መሄድ አይሆንላቸውም በማለት ከቤት ገብቶ
ቆይቷቸዋል። ዓይነ ስዉራኑም፦ ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፥ «ይህን ማድረግ እንዲቻለኝ ታምናላችሁን?»
አላቸው፤ እነርሱም፦ «አዎን ጌታ ሆይ !» አሉት። «እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ፤» ብሎ ዓይኖቻቸውን
ዳሰሳቸው። ያንጊዜም ዓይኖቻቸው ተገለጡ፤ ማቴ ፱፥፳፯-፴። ጌታችን፦ «አዎን እናምናለን፤» እንደሚሉት
እያወቀ «ታምናላችሁን?» ብሎ የጠየቃቸው አላዋቂ የነበረን ሥጋ መልበሱን ለማጠየቅ ነው። አንድም በዓይነ
ስዉራኑ ልብ ያለ እምነት በአንደበታቸው እንዲገለጥ ነው።

  ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከኢያሪኮ በወጣ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር
ነበሩ፤ ብዙ ሰውም ነበረ፤ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስም በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።
የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደሆነም ሰምቶ፥ «የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ፤» ብሎ ጮኸ ። ብዙዎችም ዝም
እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን ድምፁን ከፍ አደረገና፥ «የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ» አለ። ጌታችን ኢየሱስም
ቆመና፥ «ጥሩት» አለ፤ እነርሱም ዓይነ ስውሩን ጠሩት፤ «በርታና ተነሥ፥ መምህር ይጠራሃል፤» አሉት።
እርሱም ተነሥቶ፥ አዳፋውን ልብሱን ትቶ፥ ደኅናውን ለብሶ ወደ ጌታችን ኢየሱስ መጣ። ጌታችን ኢየሱስም
መልሶ፥ «ምን ላደርግልህ ትሻለህ?» አለው፤ ዕውሩም፥ «መምህር ሆይ፥ እንዳይ ነው፤» አለው። ጌታችን
ኢየሱስም፥ «ሂድ፤ እምነትህ አዳነችህ» አለው፤ ወዲያውም አየ፤ በመንገድም ተከተለው። ማር ፲፥፵፮-፶፪።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ አይሁድን፦ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም
ሳይወለድ እኔ አለሁ፤» ብሏቸው ስለነበር፥ ያንን ቃሉን በሥራው ለማስረዳት ከዚያ አልፎ ሲሄድ ዓይነ ስዉር
ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ። ደቀመዛሙርቱም፦ «ኃጥአን ከእናታቸው ማኅፀን ጀምሮ ተለዩ፤» የሚለውን
ይዘው፦ «መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዓይነ ስዉር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ነውን?» ብለው
ጠየቁት። «ብዙ ሕፃናት በወላጆቻቸው በደል ይሞታሉ፤» የሚለውንም ይዘው፦ «ወይስ በወላጆቹ ኃጢአት
ነውን?» በማለት ጣምራ ጥያቄ ጠይቀውታል። ጌታችን ኢየሱስም፦ «የእግዚአብሔር ሥራ (አምጻኤ
ዓለማትነቱ፥ ከሃሊነቱ፥ ጌትነቱ፥ ተአምራቱ፥ መጋቢነቱ) እንዲገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፤
ወላጆቹም አልበደሉም። ነገር ግን ቀን ሳለ (ፀሐይ ዕድሜዬ በመስቀል ሞት ሳይጠልቅ) የላከኝን ሥራ፦
(የአባቴን የፈጣሪነት ሥራ ሠርቼ እናንተን ማሳመን ይገባኛል)፤ ማንም ሥራ ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት
(የመስቀል ሞት) ትመጣለችና። በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን (የሰው ዕውቀቱ) እኔ ነኝ።» አላቸው።
ይህንንም ብሎ በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ የዓይነ ስዉሩን ዓይኖች ቀባው።
«ሂድና በሰሊሆም ጸበል ተጠመቅ፤» አለው። ትርጓሜውም የተላከ ማለት ነው፤ ሄዶም ተጠምቆ እያየ
ተመለሰ። ዮሐ ፱፥፩-፯።

፫፥፪፦ ሕሙማንን መፈወሱ፤

 ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ሁለቱን ዓይነ ስዉራን፦ «እንደ እምነታችሁ
ይሁንላችሁ፤» ብሎ ከፈወሳቸው በኋላ፦ ጋኔን ያደረበትን ድዳ ወደ እርሱ አመጡ። መናገርም መስማትም
አይችልም ነበር። አንድም ድዳ ደንቆሮም የሆነ ጋኔን አድሮበት ነበር። ጋኔኑ «ድዳ» የተባለው ጥንት አመስግን
ሲባል ላለማመስገን ዝም በማለቱ ነው፥ «ደንቆሮ» የተባለው ደግሞ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ባለመስማቱ
ነው። ይህ ሰው ያደረበት ጋኔን በወጣ ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ ተናግሯል፥ ጆሮውም አድምጧል። ማቴ ፱፥፴፪
፣ ፲፪፥፳፪። ጌታችን፦ አንካሶችንም ፈውሶ እንደ እንቦሳ እንዲዘሉ አድርጓል። ማቴ ፳፩፥፲፬። እጃቸው
የሰለለባቸውንም ፈውሷል። ማቴ ፲፪፥፲። ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዓይነ ስዉራን
ሲያዩ አይተው፥ እስኪደነቁ ድረስ፥ የእስራኤልን አምላክ ያመሰግኑት ነበር።
 ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የከነዓናዊቱን ሴት ልጅም ባለበት ሆኖ በቃሉ ብቻ
ፈውሷታል። ይህች ሴት፦ «አቤቱ የዳዊት ልጅ እዘንልኝ፤ ልጄን ክፉ ጋኔን ይዞ ያሠቃያታልና፤» ብላ አብዝታ
በጮኸች ጊዜ እምነቷ፥ ትዕግሥቷ ይገለጥ ዘንድ ዝም አላት። ጩኸቷን ባለማቋረጧም፦ ደቀመዛሙርቱ ወደ
እርሱ ቀርበው፦ «ይህችን ሴት አሰናብታት፤ እኛን እየተከተለች ትጮሃለችና፤» ብለው ማለዱት።
መማለዳቸውም፦ ትምህርት ታስፈታለች፥ አንድም ወይ ተናግረው አያስፈጽሙ፤ ወይ አያሰናብቱ ትላለች
ብለው፥ አንድም ብታሳዝናቸው ነው። እርሱም መልሶ፦ «ከእስራኤል ቤት ወደ ጠፉ በጎች (ትምህርት አብነት
አጥተው ወደ ተጐዱት) ብቻ እንጂ አልተላክሁም፤» አላቸው። እንዲህም ያለው የተነገረውን ትንቢት፥
የተቈጠረውን ሱባዔ የሚያውቁት እነርሱ በመሆናቸው ነው። ሴቲቱም፦ ቀርባ፦ «አቤቱ ጌታዬ እርዳኝ፤» ብላ
ሰገደችለት። እርሱም መልሶ፦ «የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መስጠት መልካም አይደለም፤» አላት።
እንዲህም ማለቱ ይህች ሴት፦ «ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።» ከተባለው
ወገን በመሆኗ ነው። ትርጉሙም የተመረቀው የሴም በረከት ለተረገመው ለከነዓን አይሰጥም ማለት ነው።
ሴቲቱም በፍጹም እምነትና ትህትና፦ «አዎን ጌታዬ ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ
ይበላሉ፤ (ለእስራኤል ደጋጉን ተአምራት ብታደርግላቸው ጥቃቅኑን ተአምራት አታደርግልኝምን)? አለችው።
ከዚህም በኋላ ጌታችን መልሶ፦ «አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ፤» አላት፤
ከዚህችም ሰዓት ጀምሮ ልጅዋ ዳነች። ማቴ ፲፭፥፳፩-፳፰። ጌታችን ይህችን ሴት ሦስት ነገር አግኝቶባታል።
እነርሱም፦ እምነት፥ ትህትና እና ጥበብ ናቸው፤ ልጄን ያድንልኛል ብላ መምጣቷ እምነት ነው፥ በውሻ
ሲመስላት «አዎን ውሻ ነኝ፤» ማለቷ ትሕትና ነው፥ «የልጆችን እንጀራ ለውሾች መስጠት አይገባም፤» ብሎ
በጥበብ ሲናገር፥ እርሷም፦ «ውሾችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤» ብላ በጥበብ
ተናግራለች።
         
          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ለሕዝቡ ቃሉን ነግሮ በፈጸመ ጊዜ ወደ
ቅፍርናሆም ገባ።አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ አገልጋዩም ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር፤ እርሱም በእርሱ ዘንድ
የተወደደ ነበር። የጌታችን የኢየሱስንም ነገረ በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ አገልጋዩን እንዲያድንለት ይማልዱት ዘንደ
የአይሁድን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ላከ። ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስም መጥተው ማለዱት፤ «ፈጥነህ ውረድ፣
ይህን ልታደርግለት ይገባዋልና። እርሱ ወገናችንን ይወዳልና፤ ምኲራባችንንም ሠርቶልናልና፤» ብለው
አጥብቀው ለመኑት። ጌታችን ኢየሱስም ከእነርሱ (ከአማላጆቹ) ጋር ሄዶ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ፥ የመቶ
አለቃው ወዳጆቹን፦ «አቤቱ አትድከም፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና። እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤
ወታደሮችም አሉኝ፤ አንዱን ሂድ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም እንዲህ
አድርግ ብለው ያደርጋል ብሏል፥ ብላችሁ ንገሩልኝ፤» ብሎ ወደ እርሱ ላካቸው። እነርሱም ይኽንን ወስደው
ነገሩት። ጌታችን ኢየሱስም ይህን ከእርሱ በሰማ ጊዜ አደነቀው፤ ዘወር ብሎም ይከተሉት ለነበረው ሕዝብ፥
«እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው ሰው አላገኘሁም፤» አላቸው። የተላኩትም
(አማላጆቹ) በተመለሱ ጊዜ ብላቴናውን ድኖ አገኙት።

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ይህንንም ሰው ሦስት ነገሮች አግኝቶበታል።


እነርሱም፦ እምነት፥ ትሕትና እና ጥበብ ናቸው። የእነርሱን ልመና ተቀብሎ አገልጋዬን ያድንልኛል፥ ብሎ
አማላጆችን መላኩ እምነት ነው፥ «ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና፤ እኔም ወደ አንተ ልመጣ
አይገባኝም፤» ማለቱ ትሕትና ነው፥ «እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤ ወታደሮችም አሉኝ፤ አንዱን ሂድ ብለው
ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤» ማለቱ ጥበብ ነው።

          ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ የመቶ አለቃውን ታሪክ የጻፈው «አቤቱ፥ ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ
በቤት ተኝቶአል፤» ብሎ ራሱ ቀርቦ ተናገረ፥ ብሎ ነው። ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ የጻፈው አስቀድሞ የአይሁድ
ረበናትን፥ በኋላም ወዳጆቹን አማላጅ አድርጎ ልኳል በማለት ነው። ንባቡ የሚጣላ ይመስላል፥ ነገር ግን
ትርጓሜው ያስታርቃቸዋል። ቅዱስ ማቴዎስ እንደተናገረው ራሱ ሄዶ ቢናገር የከነዓናዊቱን ሴት ጩኸት
ሰምቶ ዝም እንዳለ እርሱንም ዝም ብሎታል። በዚህን ጊዜ «እኔ የበቃሁ ባልሆን ነው፤» ብሎ ወደ ቤቱ
ተመልሶ፥ የአይሁድ ሽማግሌዎችን አማላጅ አድርጎ ልኳል። ሁለቱም ታሪክ የተፈጸመ በመሆኑ፥
እግዚአብሔር ባወቀ ወንጌላውያኑ ተከፋፍለው ጽፈውታል። ማቴ ፰፥፩-፲፣ ሉቃ ፯፥፩-፲።

ይቀጥላል . . .

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲፪


ካለፈው የቀጠለ. . . .

፫፥፫፦ ልሙጻንን ማንጻቱ፤

          ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ አያሌ ተአምራትን አድርጓል። «ጌታችን


አየሱስም በምኲራባቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም
ሁሉ እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይመላለስ ነበር። ዝናውም በመላው ሶርያ ተዳረሰ፤ የታመሙትን ሁሉ፥
የተጨነቁትንም፥ ደዌያቸውም ልዩ ልዩ የሆነውን፥ አጋንንትም ያደሩባቸውን፥ ጨረቃ እያየ የሚጥላቸውን፥
ልምሾችንም ሁሉ አመጡለት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው።» ይላል። ማቴ ፬፥፳፫-፳፬። ለምጻሙ ሰው ወደ እርሱ
ቀርቦ፦ «አቤቱ ከወደድህስ እኔን ማንጻት ይቻልሃል፤» እያለ በሰገደለት ጊዜ፦ «እፈቅዳለሁ ንጻ፤» ብሎታል።
ያንጊዜም ከለምጹ ነጽቷል፤ ጌታም፦ ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሂድና ራስህን ለካህን
አስመርምር፤ ምስክርም ሊሆንባቸው ሙሴ እንዳዘዘ መባህን አቅርብ፤» ብሎታል። ማቴ ፰፥፩-፬።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ወደ ኢየሩሳሌሞ ሲሄድ፥ በሰማርያና በገሊላ መካከል
አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ ለምጽ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች ተቀበሉትና ራቅ ብለው ቆሙ።
ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው፥ «ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እዘንልን፤» አሉ። ባያቸው ጊዜ፥ «ወደ ካህና
ሂዱና ራሳችሁን አስመርምሩ፤ (ሳታውቁ በስሕተት፥ አውቃችሁ በድፍረት የሠራችሁትን ኃጢአት ተናዘዙ)፤
አላቸው፤ ሲሄዱም ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደነጻ ባየ ጊዜ፥ «ያዳነኝን ትቼ ወዴት እሄዳለሁ፤» ብሎ፥
በታላቅ ቃል እያመሰገነ ተመለሰ። በግንባሩም ወድቆ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር በታች ሰገደና
አመሰገነው፤ ሰውዬውም ሳምራዊ ነበር። ጌታችንም፦ «የነጹ ዐሥር አልነበሩምን? እንግዲህ ዘጠኙ የት አሉ?
ወገኑ ሌላ ከሆነ ከዚህ ሰው በቀር ለእነዚያ ተመልሶ እግዚአብሔርን ማመስገን ተሳናቸውን?» አለ። እርሱንም፦
«ተነሥና ሂድ፥ እምነትህ አዳነችህ፤» አለው። ሉቃ ፲፯፥፲፩-፲፱።

፫፥፬፦ መጻጉዕን መፈወሱ፤


          ከዚህ በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም የበጎች በር
አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ (የምሕረት ቤት) ይሉአታል፤ አምስት
እርከኖችም (መደቦች፥ ደረጃዎች) ነበሩአት። እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ምሳሌዎች ናቸው።
በዚያም እውሮችና አንካሳዎች፥ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ
ነበር። (በሽተኞቹ፦ ዕውራን፣ አንካሶች፣ የሰለሉ፣ ልምሾ የሆኑ እና የተድበለበሉ አምስት ዓይነት ናቸው)።
እነዚህም የአረጋውያን፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የካህናት እና የመነኰሳት ማለትም የአምስቱ ፆታ ምእመናን
ምሳሌዎች ናቸው። እነዚያ (በሽተኞቹ) ተጠምቀው በጸበሉ ኃይል እንደሚፈወሱ፥ እነዚህ ደግሞ፦ ልጅነትን
በምታሰጥ ጥምቀት ኃይል ሰይጣን የሚያመጣውን ፈተና ድል ያደርጋሉ።

          የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው (በሚባርከው) ጊዜ፥


ከውኃው መናወጥ (ከተባረከ) በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር። መልአኩ
የሚወርደው ውኃውን ለመቀደስና መሥዋዕት ለማሳረግ ነው። ቅዳሜ ቅዳሜ፦ አንድ አንድ በሽተኛ ይፈወስ
ነበር፥ ይህም የማይቀር የማይደገምም ነው። አለመቅረቱ፦ «ተአምራት በአባቶቻችን ዘመን ይደረግ ነበር፥
በእኛ ዘመን ግን ቀረ፤» ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ ነው፥ አለመደገሙ ደግሞ በኦሪት ፍጹም የሆነ ድኅነት
አለመሰጠቱን ለማጠየቅ ነው። መልአኩ የቀሳውስት ምሳሌ ነው።

          በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነ ድውይ ነበረ፥ ደዌ ጠንቶበታል፥ ዘግይቶበታልም።
ጌታም፦ ያን ሰው በአልጋው ተኝቶ ባየ ጊዜ (በደዌ ዳኛ፥ በአልጋ ቊራኛ ተይዞ ብዙ ዘመን እንደቆየ
ስለሚያውቅ) «ልትድን ትወዳለህን?» አለው። መዳን እንደሚፈልግ እያወቀ የጠየቀው፥ አንደኛ፦ አላዋቂ
የነበረን ሥጋ መዋሀዱን ለማጠየቅ ነው፤ ሁለተኛም ለማስፈቀድ ነው። ሳያስፈቅድ ቢፈውሰው ኖሮ፥ በኋላ
በዕለተ ዓርብ የጌታን ፊቱን በጥፊ ጸፍቶ በሚመሰክርበት ጊዜ፦ ምክንያት ባገኘ ነበር። ይኸውም፦ «ምነው
ያዳነህን?» ሲሉት፥ «በቀለብላባነቱ አዳነኝ እንጂ መች አድነኝ ብዬ ለመንኩት፤» ባለ ነበር። ዛሬም
ባለውለታዎቻቸውን በድለው ሲጠየቁ፦ «ለምኜሃለሁ?፥ ለምኜሻለሁ?፥ ለምኜዋለሁ?፥ ለምኜታለሁ?»
የሚሉ አሉ።   

          በሽተኛው፦ የመዳን ጥያቄ በቀረበለት ወቅት፦ «ውኃው በተናወጠ ጊዜ፥ ከመጥመቂያው አውርዶ
የሚያስጠምቀኝ ሰው የለም እንጂ መዳንሰ እወድ ነበር። ነገር ግን እኔ በመጣሁ ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ
ይጠመቃል፤» ሲል መለሰ። እንዲህም ማለቱ፦ አንደኛ፦ ይህ የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ አውርዶ ሊያስጠምቀኝ
ይችላል፥ ሁለተኛም፦ ከተከታዮቹ አንዱን ጉልበታም  ያዝዝልኛል ብሎ ነው። ጌታችን ኢየሱስም፦ «ተነሥና
አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤» አለው። ወዲያውንም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ።
          ደዌ በአራት ምክንያት ይመጣል፤ ፩ኛ፦ ደዌ ዘንጽሕ (የንጽሕና ምልክት የሆነ ደዌ) ነው፥ ይህም፦ እንደ
ቅዱስ ጢሞቴዎስ ያለ ነው። እርሱም መምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ስለ ንጽሕና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት
የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ፤» ብሎታል። ፩ኛ ጢሞ ፭፥፲፭። ፪ኛ፦ ደዌ ዘዕሤት
(ዋጋ ያለው ደዌ) ነው፤ ይህም እንደ ጻድቁ ኢዮብ ነው፤ «ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም
ከእግሩ ጫማ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቊስል መታው፤» ይላል። ኢዮ ፪፥፯። ፫ኛ፦ ደዌ ዘመቅሠፍት ነው፤
ይህም እንደ ሳኦል እንደ ሄሮድስ ነው፤ «የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉ መንፈስም ከእግዚአብሔር
ዘንድ አሠቃየው።» ፩ኛ ሳሙ ፲፮፥፲፬። «ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው፥
በትልም ተበልቶ ሞተ፤» ይላል። የሐዋ ፲፪፥፳፫። ፬ኛ፦ ደዌ ዘኃጢአት እንደ መጻጉዕ ነው። ሠላሳ ስምንት
ዓመት የታመመው በኃጢአቱ ነው።

፫፥፭፦ ሙታንን ማንሣቱ፤

          ኢያኢሮስ የሚሉት አንድ መኰንን ወደ እርሱ መጥቶ፦ «ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን
ጫንባት፤ ትድናለችም፤» እያለ ሰገደለት። ጌታችን ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፤ ደቀመዛሙርቱም
አብረውት ነበሩ። ከመኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችን እና የሚንጫጩትን ሰዎች አየ። «ሹም ሲሞት
ሃምሣ፥ የሹም ልጅ ሲሞት ደግሞ አንድ መቶ ሃምሣ፤» እንዲል ለቀስተኛው ብዙ ነበር። ጌታችንም፦
እንደሚያስነሣት ስለሚያውቅ፥ አንድም በነፍስ ሕያው መሆኗን ለማጠየቅ፥ «ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ
የሞተች አይደለምና ፈቀቅ በሉ፤» አላቸው። እነርሱም፦ «የሞተና ያልሞተ መለየት የማይችለውን ይኽንን
ያስነሣልኛል ብሎ ይዞት መጣ፤» ብለው በኢያኢሮስ ሳቁበት፤ አንድም፦ «መሞቷን አረጋግጠን ሬሣውን
ያጠብን፥ የገነዝንም እኛ ነን፥ እንዴት አልሞተችም ይለናል፤» ብለው በጌታ ሳቁበት። ጌታም ሰዎቹ ከወጡ
በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ብላቴናዪቱም ተነሣች። የተአምራቱም ዝና በሀገሩ ሁሉ ተሰማ። ማቴ
፱፥፲፰፥፳፮።

          የማርያም የማርታ አገር በምትሆን በቢታንያ አልዓዛር የሚባል ሰው ታሞ ነበር። ማርያምም ጌታን
ሽቱ የቀባችው ፥ እግሩን በዕንባዋ ያጠበችው፥ በፀጉሯም ያበሰችው ናት። የአልዓዛር እህቶች ወንድማቸው
በመታመሙ፦ «ጌታ ሆይ፥ ወዳጅህ ታሟል፤» ብለው ወደ ጌታ ላኩ፤ ጌታም እንደታመመ በሰማ ጊዜ፦ «ይህ
ደዌ ለሞት የሚያበቃ አይደለም፥ አንድም ሙቶ ሊቀር አይደለም፥ እግዚአብሔር አብ በልጁ ህልው ሆኖ
እርሱን አንሥቶ ጌትነቱ ይገለጥ ዘንድ ነው፥ አንድም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን
ከሞት አንሥቶ በጌትነት ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፤» አለ። ጌታችን፦ ማርያምን ማርታን እና አልዓዛርን
የፍጹማን ፍቅር ይወዳቸው ነበር። ጌታችን የአልዓዛርን መታመም በሰማበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ፥ ከዚህም
በኋላ ደቀመዛሙርቱን «ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ፤» አላቸው።
ደቀመዛሙርቱም፦ ስለ እንቅልፍ የተናገረ መስሏቸው፥ «አቤቱ፥ ከተኛስ ይነቃል፤ ይድናልም፤ (የታመመ ሰው
የተኛ እንደሆነ ጤና አግኝቶ ይነሣል)፤» አሉት። ጌታችን ግን የተናገረው ስለ ሞቱ ነበር። ከዚህ በኋላም፦
«ታምኑም ዘንድ (አስቀድሞ አውቆ የነገረን የባሕርይ አምላክ ቢሆን ነው ብላችሁ እንድታምኑ) በዚያ
ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ፤» በማለት ገልጦ ነገራቸው። ዲዲሞስ
የሚሉት ቶማስም፦ አይሁድ ጌታን በክፉ እንደሚፈልጉት ስለሚያውቅ፥ ባልንጀሮቹን ደቀመዛሙርት፥
«እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ፤» አላቸው።

          ጌታችን ቢታንያ በደረሰ ጊዜ፥ አልዓዛርን ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው፤ አልዓዛር የሞተው ረቡዕ
ነው፥ ጌታ የደረሰው ቅዳሜ ነው። ቢታንያ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አምስት ከ ሜ ርቆ ከደብረ ዘይት
ወዲያ የሚገኝ መንደር ነው። ብዙ አይሁድ የአልዓዛርን እኅቶች ሊያጽናኗቸው በዚያ ነበሩ፤ ማርታ፦ ጌታችን
እንደመጣ በሰማች ጊዜ፥ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን እንግዶችን ጥሎ መውጣት ስለከበዳት በቤት
ተቀምጣ ነበር። ማርታም፦ ጌታችንን ድውይ መፈወስ እንጂ ሙት ማንሣት የማይቻለው መስሏት፥ «ጌታዬ
ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር
እንዲሰጥህ አውቃለሁ፤» አለችው። ጌታም፦ «አላመንሽም እንጂ ብታምኚ ወንድምሽ ይነሣል፤» አላት።
ማርታም፦ የኋላውን የነገራት መስሏት፥ «ሙታን በሚነሡበት በኋለኛዪቱ ቀን እንዲነሣ አውቃለሁ፤»
አለችው። ጌታም፦ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል፥ (በእኔ ያመነ አይሞትም፥
በሥጋ ቢሞት በነፍስ ይድናል፥ ፈርሶ በስብሶ አይቀርም፥ ትንሣኤ ዘለክብር ይነሣል፥ አንድም በትንሣኤ
ዘጉባዔ የማስነሣ እኔ አሁንም ላስነሣ እችላለሁ)። ይህንን ታምኛለሽን?» አላት። እርስዋም፦ «አዎን ጌታዬ
ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ፤» አለችው።

          ማርታ እምነቷን ከገለጠች በኋላ፥ ወደ ቤት ተመልሳ፥ «መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል፤» ብላ በቀስታ


ለማርያም ነገረቻት። እርሷም ፈጥና ወደ እርሱ ሄደች፥ ጌታችን ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። በቤት
የነበሩት ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሏቸው ተከተሏት። ጌታችን ካለበትም ደርሳ ከእግሩ በታች
ሰገደችለትና፦ «ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤» አለችው። ጌታም ስታለቅስ፥
ከእርሷም ጋር የመጡ አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከና (መፍቀሬ ሰብእ ነውና በሐዘን
ራሱን ነቀነቀና) «የት ቀበራችሁት?» አለ። እንዲህም ማለቱ፦ አላዋቂ የነበረን ሥጋ መዋሐዱን ለማጠየቅ
ነው። አንድም አዳምን፦ አላዋቂ የሆነ የአንተን ሥጋ ለብሼ እፈልግሃለሁ ሲለው፦ «አዳም የት ነህ?» ብሎት
ስለነበረ ያ እንደተፈጸመለት ለማጠየቅ ነው። አንድም፦ «ከሱናማዊቷ ሴት ለምን አነሳችሁ? እርሷ እንኳ ልጇ
በሞተባት ጊዜ አጥባ፥ አጐናጽፋ፥ ከአልጋ ላይ አስተኝታ፥ በሯን ዘግታ ነቢዩ ኤልሳዕን ልትጠራ ሄደች እንጂ
ለመቅበር አልቸኰለችም፤» ሲላቸው ነው። እነርሱም፦ «አቤቱ፥ መጥተህ እይ፤» አሉት። ጌታችንም ዕንባውን
አፈሰሰ። አይሁድም፦ «ምን ያህል ይወድደው እንደነበር እዩ፤» ተባባሉ። ከእነርሱም መካከል፦ «ዕውር ሆኖ
የተወለደውን ዓይን ያበራው ይህ ሰው፥ ይህስ እንዳይሞት ሊያደርግ ባልቻለም ነበር?» ያሉ ነበሩ። እነዚህም
ድውይ መፈወስ እንጂ ሙት ማንሣት የሚቻለው ስላልመሰላቸው ነው።

          ዳግመኛም ጌታችን በልቡ አዘነ፤ ወደመቃብሩም እያለቀሰ ሄደ፥ መቃብሩም ዋሻ ሆኖ በታላቅ ደንጊያ
ተገጥሞ ነበር። ጌታችን ኢየሱስም ሳይደክሙ ዋጋ እንደማይገኝ ሊያስረዳቸው፦ «ድንጋዩን አንሡ፤» ብሎ
ሥራ ሰጣቸው። ማርታም፦ «ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ (ተልቶ) ይሆናል፤» አለችው።
ጌታም፦ «ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልሁሽም ነበርን?» አላት። ድንጋዩንም ባነሡ ጊዜ፥
ጌታችን፦ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ፥ «አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። እኔም ዘወትር
እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤» አለ። ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ያቀናበት ምክንያት፦ «ይህን የማስነሣበት ሥልጣን
ከአንተ ጋር አንድ ነው፤» ሲል ነው። ከዚህም ጋር ወደ አብ የጸለየበትን ምክንያት ሲናገር፦ «ነገር ግን አንተ
እንደላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ፤» ብሏል። አንድም ተአምራት
እንዲደረግላችሁ በምትፈልጉበት ጊዜ ወደ እግዚአብሔር አመልክቱ ለማለት፥ አብነት ለመሆን ነው።
በታላቅም ድምፅ ጮኸ። አልዓዛርን ከመቃብር ውጣ አለው። የሥጋህም የነፍስህም ፈጣሪ እኔ ነኝ ሲል
ነፍሱንና ሥጋውን አዋህዶ አስነሣው። ሞቶ የነበረውም እንደተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደታሰረ፥ ፊቱም
በሰበን እንደተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታም፦ ምትሀት እንደመሰላቸው ስላወቀ ፈጽመው ያምኑ ዘንድ፥ አንድም
ያልጸና መስሏቸው ደግፈውት ነበርና፦ «እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ፤» አላቸው። ከአይሁድም ብዙዎች
አመኑበት፤ ከእነርሱም ወደ ፈሪሳውያን ሄደው የከሰሱት ነበሩ። ዮሐ ፲፩፥፩-፵፮።

፬፦ ቅዱሳን ያደረጉት ተአምራት፤

          የነቢያት አለቃ ሙሴ ተአምራታዊት በትር ነበረችው። እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፥ «ፈርዖን፦


ተአምራትንና ድንቅን አሳዩኝ ሲላችሁ ወንድምህን አሮንን፦ በትርህን ወስደህ በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት
ጣላት፥ በለው፤ እባብም ትሆናለች።» ብሏቸው ነበር። እነርሱም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። የግብፅ
ጠንቋዮችም በትራቸውን እባቦች አደረጉ። አሮን እባብ እንድትሆን የጣላት የሙሴ በትር ግን ሁሉንም
ዋጠቻቸው። ይህን ብቻ ሳይሆን፦ ፩ኛ፦ ውኃውን ወደ ደም ለውጠዋል፤ ፪ኛ፦ የግብፅ ምድር እስኪሸፈን
ድረስ ጓጉንቸሮችን (እንቁራሪቶችን) አውጥተዋል፤ ፫ኛ፦ በሰውና በእንስሳ ላይ ቅማል እንዲፈላ አድርገዋል፤
፬ኛ፦ በግብፅ ምድር ሁሉ ተናካሽ ዝንቦችን አዝዘውባቸዋል፤ ፭ኛ፦ የግብፅ እንስሳት እንዲያልቁ አድርገዋል፤
፮ኛ፦ በሰውና በእንስሳ ላይ ሻሕኝ የሚያመጣ ቊስል እንዲወጣባቸው አድርገዋል፤ ፯ኛ፦ በሜዳ የቀረ ሰውና
እንስሳ እስኪሞት ድረስ በረዶ አውርደውባቸዋል፤ ፰ኛ፦ የአንበጣ መንጋ ታዝዞ ከበረዶ የተረፈውን ሰብልና
ዛፍ አጥፍቷል፤ ፱ኛ፦ ሦስት ቀን እና ሦስት ሌሊት ጽኑ ጨለማ ሆኗል፤ ፲ኛ፦ ከንጉሡ ከፈርኦን ጀምሮ
የሁሉም ሰው የበኲር ልጆች ሞተው ምድሪቱ በጩኸት ተከድናለች። ዘጸ፯፥፲፬-፳፭፤ ፰፥፩-፴፪፤ ፱፥፩-
፴፭፤ ፲፥፩-፳፱፤ ፲፩፥፩-፲። ከዚህም ሌላ ሙሴ፦ ቀይ ባሕርን በበትሩ ለሁለት በመክፈል ውኃው እንደ ግድግዳ
እንዲቆም አድርጓል። ዘጸ ፲፬፥፳፩። እግዚአብሔር ያሳየውን እንጨትም ከመራራው ውኃ ውስጥ በመጣል
እስራኤል ጣፋጭ ውኃ እንዲጠጡ ረድቷቸዋል። ዘጸ ፲፭፥፳፪-፳፮። መና ከሰማይ አውርዶላቸዋል፥ ከደረቅ
ዓለትም ውኃ አፍልቆላቸዋል። ዘጸ ፲፮፥፩-፴፮፤ ፲፯፥፩-፯፤ ሌሎችንም ተአምራት እግዚአብሔር በሙሴ እጅ
አድርጓል።

          ኢያሱ ወልደ ነዌም የዮርዳኖስን ወንዝ ለሁለት ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል። ኢያ ፫፥፩-፲፯።
የኢያሪኮን ታላቅ የግንብ አጥር በጩኸት ብቻ አፍርሷል። ኢያ ፮፥፩-፳፯። ፀሐይ እንዳትጠልቅ ገዝቶ
አቁሟታል። «ፀሐይም በሰማይ መካከል ቆመች፤ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል አልጠለቀችም፤» ይላል። ኢያ
፲፥፲፫።

          ነቢዩ ኤልያስ፦ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ፥ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብ እንዳይዘንብ
አድርጓል፥ ተመልሶም እንዲዘንብ ያደረገው እርሱ ነው። ፩ኛ ነገ ፲፯፥፩ ፤ ፲፰፥፵፪ ፣ ያዕ ፭፥፲፯።
የሰራፕታዋን ሴት ዱቄትና ዘይት ባርኮላት የረሀቡ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ እንዳያልቅ አድርጎላታል፥ ልጇም
ቢሞትባት አስነሥቶላታል። ፩ኛ ነገ ፲፯፥፰-፳፬። በመጐናጸፊያው የዮርዳኖስን ወንዝ ለሁለት ከፍሎ በእሳት
ሠረገላ ወደ ሰማይ ዐርጓል። ኛ ነገ ፪፥፩-፲፬።

          ነቢዩ ኤልሳዕ በመምህሩ በኤልያስ ስም እየተማጸነ በመምህሩ በኤልያስ መጐናጸፍያ ዮርዳኖስን ለሁለት
ከፍሏል። ፪ኛ ነገ ፪፥፲፪-፲፬። ቢጠጡት ይገድል የነበረውን መርዛማ ውኃ ከአዲስ ማሰሮ ውስጥ ጨው
አውጥቶ በመጨመር በእግዚአብሔር ስም ፈውሶታል። ማሰሮ የእመቤታችን፥ ጨው የኢየሱስ ክርሰቶስ፥
የውኃው መርዛማነት የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ምሳሌዎች ናቸው። ከአዲስ ማሰሮ የወጣው ጨው
የውኃውን መርዛማነት እንዳስወገደው፥ ከእመቤታችን የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስም መርገመ ሥጋን
መርገመ ነፍስን አስወግዷል። ፪ኛ፥፲፱-፳፪።

          በቤቴል የሰደቡትንና ያዋረዱትን ብላቴናዎችም ረግሞ የዱር አራዊት ሰብረው አርባ ሁለቱን
እንዲገድሏቸው አድርጓል። ፪ኛ ነገ ፪፥፳፫-፳፭። የደሀይቱን ሴት ዘይት ባርኮላት ዕዳዋን ከፍላ ልጆቿን
ለባርነት ከመሸጥ አድኖላታል። ፪ኛ ነገ ፬፥፩-፯። ሱናማዊቷን ሴት በጸሎት ረድቷት ከሽማግሌ ባሏ ልጅ
እንድትወልድ አድርጓታል፥ አድጐ በሞተባትም ጊዜ በጸሎቱ አስነሥቶላታል። ፪ኛ ነገ ፬፥፰-፴፯።
በተመረዘው ምግብ ውሰጥ ዱቄት ጨምሮ ፈውሶታል። ሃያ የገብስ እንጀራና ጥቂትም የእህል እሸት ባርኮ
መቶ ሰዎች ተመግበውት እንዲተርፍ አድርጓል። ፪ኛ ነገ ፬፥፴፰-፵፬። ሶርያዊው ንዕማንም በዮርዳኖስ
ተጠምቆ ከለምጹ እንዲድን አድርጐታል። ደቀመዝሙሩ ግያዝ ደግሞ «መምህሬ ልኮኝ ነው፤ ብሎ፥ በስሙ
ዋሽቶ ፥ገንዘብና ልብስ በመቀበሉ፥  መንፈሰ እግዚአብሔር ገልጦለት በጠየቀው ጊዜ በመካዱ ረግሞ በለምጽ
አንድዶታል።

          ከደቀመዛሙርቱ አንዱ እንጨት በሚቆርጠበት ጊዜ የምሳሩ ብረት ወልቆ ከዮርዳኖስ ወንዝ ገብቶበት
ነበር። በዚህን ጊዜ፦ «ጌታዬ ሆይ፥ ወየው ወየው የተዋስሁት ነበር፤» ብሎ ወደ እርሱ ጮኸ። ኤልሳዕም
ከእንጨት ቅርፊት ቀርፎ ወደ ባሕሩ ጣለው፥ ቅርፊቱም፦ ወደ ውስጥ ገብቶ ብረቱን ይዞ ወጣ። ብረት
የአዳም፥ ባሕር የሲኦል፥ ቅርፊት የኢየሱስ ክርስቶስ፥ ኤልሳዕ የእግዚአብሔር አብ ምሳሌዎች ናቸው። ነቢዩ
ኤልሳዕ ወደ ባሕር የላከው ቅርፊት ብረቱን ይዞ እንደወጣ፥ የባሕርይ አባቱ ወደ ዓለም የላከው ኢየሱስ
ክርስቶስም፥ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር እንደወረደ፥ በአካለ ነፍስም ወደ ሲኦል ወርዶ አዳምን እና ልጆቹን
አውጥቷል። ፪ኛ ነገ ፮፥፩-፯። ከሰማርያ በስተሰሜን ሃያ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ከተማ በዶታይን ተቀምጦ
በሶርያ ቤተ መንግሥት በምስጢር የሚዶለተውን እግዚአብሔር እየገለጠለት ያውቅ ነበር። ይኽንንም ያወቀ
የሶርያ ንጉሥ በፈረስ በሠረገላ በብዙ ሰራዊትም ባስከበበው ጊዜ የእሳት ሰይፍ ይዘው የሚጠብቁትን መላእክት
አይቷል። የከበቡትንም ዓይናቸውን አሳውሮ ማርኳቸዋል። ፪ኛ ነገ ፮፥፰-፲፱።

          ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ   በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ


ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው አገኙ። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት
ይለምን  ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚሉት መቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር። እርሱም ምጽዋት
ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው። ቅዱስ ጴጥሮስም  ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና፦ «ወደ እኛ
ተመልከት፤» አለው፤ እርሱም  ምጽዋት እንደሚሰጡት ተስፋ አድርጎ  ወደ እነርሱ ተመለከተ፤ ቅዱስ
ጴጥሮስም፦  «ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
ተነሥተህ ሂድ፤» አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤  ያን ጊዜም ቁርጭምጭሚቱ ጸና። ዘሎም ቆመ፤
እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእርሱ ጋር ወደ ቤተመቅደስ ገባ። ይህ ሰው ቅዱስ
ጴጥሮስ እንዳዘዘው ወደ እነርሱ በመመልከቱ በሥጋም በነፍስም ተጠቅሟል። በሥጋ ተፈውሷል፥ በነፍስ
ደግሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት ታድሏል። እኛም በስሙ ተአምር እንዲሠሩ
ሥልጣን ወደተሰጣቸው  ቅዱሳን ብንመለከት የምንጠቀም እንጂ የምንጎዳ አይደለንም። የሐዋ ፫፥፩-
፰።                   

          በሐዋርያት ዘመን ያመኑት ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ
ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ፤ «ይህ የእኔ ገንዘብ ነው፤» የሚል አልነበረም። የሐዋ ፬፥፴፪። ሐናንያና ሚስቱ
ሰጲራ መሬታቸውን ሸጠው ለቤተ ክርስቲያን  ለመስጠት፥ ከአንድነቱ ለመግባት  ከወሰኑ በኋላ ሰይጣን
ልባቸውን ከፈለባቸው፥ አሳባቸውን ሁለት አደረገባቸው። በዚህም ምክንያት ግማሹን በስውር አስቀምጠው፥
ግማሹን ብቻ ይዞ ሐናንያ ቀድሞ ሄደ፥ በሐዋርያትም እግር አጠገብ አስቀመጠ። ይህንንም ያደረጉት  «ሁሉን
ካስረከብን በኋላ ማኅበሩ የፈረሰ እንደሆነ ተመልሰን ምን እንበላለን?» ብለው ተጠራጥረው ነው። ቅዱሳን
ሐዋርያት ቢጠይቋቸው  ተራ በተራ ገብተው፥ ምን ብለው መዋሸት እንዳለባቸው ተማክረዋል።

           ቅዱስ ጴጥሮስም፦  «ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልለው ዘንድ፥ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ


ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ? ጥንቱን ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ይህን ነገር በልብህ
ለምን አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አላታለልህም፤» አለው። ሐናንያም ይህንን ሰምቶ ሞተ። ይህ
ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላ ሚስቱ መጣች፥ የሆነውንም አላወቀችም ነበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስም፦  እስኪ ንገሪኝ
መሬታችሁን የሸጣችሁት ይህን ለሚያህል ነውን? ብሎ በጠየቃት ጊዜ፥  «አዎን፤» ብላ ዋሸች።  እርሱም
መልሶ፦ «እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንፈስ ትፈታተኑት ዘንድ እንዴት ተባበራችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት
ሰዎች እግሮች በበር ናቸው፤ አንቺንም ይወስዱሻል፤» አላት። ያን ጊዜም ከእግሩ በታች ወድቃ ሞተች።
ቅዱሳንን መድፈር አድሮባቸው የሚኖር መንፈስ ቅዱስን መፈታተን ነውና። የሐዋ ፭፥፩-፲። ቅዱስ
ጳውሎስና በርናባስ ጳፉ በምትባል ሀገር ገብተው ባስተማሩበት ጊዜ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለውን ሀገረ ገዢ
ከማመን ለመከልከል፥ በርያሱስ የተባለው ጠንቋይ ተቃውሟቸው ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ግን አድሮበት
በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ትኲር ብሎ ከተመለከተው በኋላ፦ «ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን
ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ (ወንጌልን) ከማጣመም አታርፍምን?
እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤»
አለው። ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ። አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ
ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ። የሐዋ ፲፫፥፬-፲፪።

        በቅዱሳን ሐዋርያት እጅ (ሥልጣን) በሕዝቡ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር። ሐዋርያው
ቅዱስ ጴጥሮስ የአካሉ ጥላ ያረፈባቸውን አያሌ በሸተኞችን ፈውሷል። የሐዋ ፭፥፲፪-፲፮። የአልጋ ቊራኛ
ከሆነ ስምንት ዓመት የሞላውን ኤንያን፦ «ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስህ፥ ተነሥና አልጋህን
አንጥፍ፤» ብሎ ፈውሶታል። በኢዮጴ፦ ጣቢታ የሚሏት ደግ ሴት በሞተች ጊዜ አስከሬኗን አጥበው በሰገነት
ካስተኟት በኋላ ደቀ መዛሙርትን ልከው ቅዱስ ጴጥሮስን አስመጡት። እርሱም፦ «ጣቢታ ሆይ ተነሽ፤»
በማለት ከሞት አስነሥቷታል።የሐዋ ፱፥፴፪-፵፪።

       ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በልስጥራን፥ እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው አግኝቶ፥
«ተነሥና ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም፥ እልሃለሁ፤» በማለት ፈውሶታል። የሐዋ ፲፬፥፰-፲። በምዋርተኝነት
መንፈስ እየጠነቈለች ለጌቶቿ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝ የነበረችውንም ሴት ባገኛት ጊዜ፦ «መንፈስ ርኲስ፥
ከእርሷ እንድትወጣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፤» በማለት ከቊራኝነት አላቋታል። የሐዋ
፲፮፥፲፮-፲፰።
          ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ፦ በዚህ ምክንያት በእግር ብረት ታስረው ተደብድበው ወደ ወኅኒ ቤት
ተወርውረው ነበር። በዚህም እግዚአብሔርን አመሰገኑት እንጂ አላማረሩም። እስረኞቹም ተደንቀው
ይሰሟቸው ነበር። በድንገትም የወኅኒ ቤቱ መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ። የሁሉም
የእግር ብረቶቻቸው በተአምር ወለቁላቸው። የብረት መዝጊያዎችም በተአምር ተከፈቱ። የሐዋ ፲፮፥፳፭-
፳፮። እግዚአብሔርም በቅዱስ ጳውሎስ እጅ ታላላቅ ሥራን ይሠራ ነበር። ከልብሱ ዘርፍና
ከመጠምጠሚያው ጫፍ ቈርጠው እየወሰዱ በድውያኑ ላይ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ይፈወሱ ነበር፤ ክፉዎች
መናፍስትም ይወጡ ነበር። የሐዋ ፲፱፥፲፩-፲፪።

          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ በጢሮስ በሚያስተምርበት ጊዜ፥ ትምህርቱን እስከ መንፈቀ ሌሊት ድረስ
አስረዝሞ ነበር። በዚያም ስሙ አውጤክስ የሚባል ጐልማሳ በመስኮት በኲል ተቀምጦ ሳለ ከባድ እንቅልፍ
አንቀላፍቶ ነበር፤ ከእንቅልፉ ብዛት የተነሣ ከተኛበት ከሦስተኛው ፎቅ ወደ ታች ወድቆ፥ ሬሳውን አነሡት።
ቅዱስ ጳውሎስም፦ ወርዶ በላዩ ላይ ወድቆ አቀፈውና፦ «ነፍሱ አለችና አትደንግጡ፤» ብሎ አረጋጋቸው።
በመጨረሻም ከሞት አስነሥቶታል።

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲፫

ቅዱሳን፦ በቃልም በሕይወትም እስከ ሞት ድረስ እንደመሰከሩለት ሁሉ እግዚአብሔርም ለቅዱሳን


መስክሮላቸዋል፥ ወደፊትም ይመሰክርላቸዋል። (ይፈርድላቸዋል)። ይኽንንም ፦ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፤ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት
እመሰክርለታለሁ። (ዘመን የወለደውን፥ ንጉሥ የወደደውን ሳይል በሰው ፊት ያመነብኝን በሰማያዊ አባቴ ፊት
ልጄ ወዳጄ እለዋለሁ)።» በማለት አረጋግጦልናል። ማቴ ፲፩፥፴፪። የእግዚአብሔር ምስክርነት ከምንም በላይ
የታመነ ነው። በባቢሎን ምርኮ የነበሩ እስራኤላውያን አማላጃቸውን ነቢዩ ኤርምያስን፦ «አምላክህ
እግዚአብሔር ወደ እኛ የላከህን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን ታማኝ ምስክር ይሁን።»
ያሉት ለዚህ ነው። ኤር ፵፪፥፭። ይልቁንም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የባሕርይ
አምላክነቱን ላላመኑ አይሁድ፦ «ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክረው ሌላ ነው፤ (አብ ነው)፤ ስለ እኔ የሚመሰክረው
ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ አውቃለሁ።» ብሏል። ዮሐ ፭፥፴፩።

መናፍቃን፦ ስለ ቅዱሳን መመስከር ከሰው ይመስላቸዋል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የእግዚአብሔርን


ስምና ክብር መሸፈን ነው ይላሉ፥ ነገር ግን አይደለም፤ ስለ ቅዱሳን መመስከር ከእግዚአብሔር ነው።
ገድላቸው፥ ተአምራቸው፥ ትምህርታቸው፥ ቃል ኪዳናቸው፥ የእግዚአብሔር ስምና ክብር የሚገልጥ እንጂ
የሚሸፍን አይደለም። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከቅዱሳን አንዱ ለሆነው ስለ
ቅዱስ ጳውሎስ ሲመሰክር፦ «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእሥራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ
ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፤» ያለው ለዚህ ነው። የሐዋ ፱፥፲፭። በመሆኑም ስለ ቅዱሳን የምንመሰክረው
ምስክርነት የእግዚአብሔርን ስምና ክብር ገልጦ፥ እግዚአብሔርን የሚያስመሰግን ብርሃን ነው። ይኽንንም
ራሱ ጌታችን፦ «መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑት ዘንድ እንዲሁ
ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።» በማለት በወንጌል ተናግሯል። ማቴ ፭፥፲፮። ይህ እግዚአብሔርን
የሚያስመሰግን በሰው ፊት የሚበራ ብርሃን  የቅዱሳን ገድል ነው።

          ስለ ቅዱሳን የሚመሰከረው፦ እግዚአብሔር ጠራቸው፥ እግዚአብሔር መረጣቸው፥ የእግዚአብሔር


መንፈስ አደረባቸው፥ በእግዚአብሔር ስም አስተማሩ፥ በእግዚአብሔር ስም ተአምራትን አደረጉ፥
በእግዚአብሔር ስም መከራን ተቀበሉ፥ ጾሙ፥ ጸለዩ፥ ሰገዱ፥ ወደ እግዚአብሔር አማለዱ፥ በእግዚአብሔር
ስም በእሳት ተቃጥለው፥ በሰይፍ ተመትረው፥ በመጋዝ ተተርትረው፥ ለአራዊት ተሰጥተው፥ ወደ ጥልቅ
ባሕር ተጥለው በሰማዕትነት አረፉ፤ በእግዚአብሔር ስም ከዓለም ተለይተው፥ በረሀ ወድቀው፥ ደንጊያ
ተንተርሰው፥ ጤዛ ልሰው፥ ጸብአ አጋንንትን፥ ድምፀ አራዊትን፥ ግርማ ሌሊትን ሳይሰቀቁ ኖሩ፥ ተብሎ ነው።
እንግዲህ ይህ ምን የተለየ ጥቅስ ያስፈልገዋል? ብሉያቱም አዲሳቱም የሚናገሩት ይኽንኑ ነው። ምክንያቱም፦
እግዚአብሔር የመረጣቸው ነቢያትና ሐዋርያትም ስለ ቅዱሳን ያልተናገሩበት ጊዜ የለምና ነው። ታዲያ ምኑ
ላይ ነው፥ «ማኅበረ አጋንንት» የሚያሰኘው? ስለ ቅዱሳን የመሰከረ የሚመሰክርም እግዚአብሔርንስ ምን
ሊሉት ነው? ለመሆኑ አጋንንት መቼ ነው፥ ስለ ቅዱሳን መስክረው የሚያውቁት? አጋንንት የሚታወቁበት
ግብራቸው ቅዱሳንን መክሰስና በቅዱሳን ላይ መከራ ማጽናት ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ «በሰማይ ሰልፍ
(ጦርነት) ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፤ ዘንዶውም ከነሠራዊቱ ተዋጋቸው።
አልቻላቸውምም፤ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘላቸውም። ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና
ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ
ጋር ተጣሉ። በሰማይም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፥ የአምላካችን ማዳንና ኃይል፥ መንግሥትም፥
የመሢሑም ሥልጣን ሆነች፤ አባቶቻችንን (ቅዱሳንን) በእግዚአብሔር ፊት በቀንና በሌሊት ሲያጣላቸው
የነበረው ከሳሽ ወድቆአልና።»የሚል ተጽፏል። ራእ ፲፪፥፲። ሰይጣን፥ ኢዮብን፦ «በውኑ ኢዮብ
እግዚአብሔርን የሚያመልከው በከንቱ ነውን? አንተ ቤቱን በውስጥም በውጭም፥ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ
አልሞላህለትምን? የእጁንም ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱንም በምድር ላይ አብዝተህለታል። ነገር ግን እጅህን
ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።» እያለ ከስሶታል። ኢዮ ፩፥፱። በትንቢተ
ዘካርያስም ላይ፦ «እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፤ ሰይጣንም
ይከስሰው ዘንድ በስተቀኙ ቆሞ ነበር።» የሚል ተጽፏል። ዘካ ፫፥፩። ሰይጣን እንኳን እኛን ደካሞችን
እግዚአብሔርን አንኳ ከቅዱሳን ጋር ለማጣላት የሚታገል ጉድ ነው።

          ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለው ሀገረ ገዥ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ፥ ቅዱስ ጳውሎስንና


በርናባስን ወደ እርሱ አስጠርቶ ነበር። ጠንቋዩ ኤልማስ ግን አገረ ገዢውን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ
ተቃወማቸው። (ቅዱሳኑን ከሰሳቸው)። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን አድሮበት በሚኖር መንፈስ ቅዱስ ሆኖ
ተመለከተውና፦ «አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያቢሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥
የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም
ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤»አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም
የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚህን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ
አመነ፥» ይላል። የሐዋ ፲፫፥፯-፲፪። ይህ ታሪክ ከቅዱስ ጳውሎስ እና ከቅዱስ በርናባስ ገድል አንዱ ክፍል
ነው። የጻፈውም ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ነው። ከዚህ የቅዱሳን ገድል የምንማረውም በቅዱሳን እጅ
የተደረገውን የጌታን ኃይልና ሥልጣን ነው። በተጨማሪም ቅዱሳንን የሚቃወሙ (የሚከስሱ) ዲያቢሎስና
ልጆቹ መሆናቸውን እንማራለን። ይህ እንዲህ ከሆነ «ማኅበረ አጋንንት» እነማናቸው? ወገኖቼ! እውነቱን
እውነት፥ ሐሰቱን ሐሰት ማለት ይገባል።

          ከዚህ በመቀጠል እግዚአብሔር ስለ ቅዱሳን እንዴት እንደመሰከረላቸው በአጭር በአጭሩ ለማየት


እንሞክራለን።

፩፥፩፦ በእንተ አቤል፤

          አቤል ከወንዱሙ ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን (ከበጎቹ በኲራት፥ ቀንዱ ያልከረከረውን፥
ጠጉሩ ያላረረውን፥ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን ነውር የሌለበት ጠቦት) በበጎ ኅሊና ለእግዚአብሔር አቀረበ።
እግዚአብሔርም ወደ አቤልና መሥዋዕቱ ተመለከተ። ዘፍ ፬፥፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽንን ይዞ፦
«አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፤ በዚህም ጻድቅ እንደሆነ
ተመሰከረለት፤ ምስክሩም መሥዋዕቱን በመቀበል እግዚአብሔር ነው።» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፬።

፩፥፪፦ በእንተ ሄኖክ፤

          ሄኖክ ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ ነው። በሁሉ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶታል፥ ዓለምን ንቆ
ከእግረ ገነት ሰባት ዓመት በጾም በትኅርምት ኖሯል። በዚህ ዓለም የኖረው ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት
ነው። ሄኖክ እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው አልተገኘም፤ አግዚአብሔር ሰውሮታልና። ዘፍ ፬፥፲፰። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ይህንንም ይዞ፦ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለወሰደው
አልተገኘም፤ ሳይወሰድም እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘው ተመስክሮለታል፤» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፭።

፩፥፫፦ በእንተ ኖኅ፤

          ኖኅ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶታል፤ ደስ


ማሰኘቱም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው መሆኑ ነው። እግዚአብሔር አምላክም፦ «የሥጋ ሁሉ
ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር
አጠፋቸዋለሁ። ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤» አለው። መርከቡን ከሠራ በኋላም፦ «አንተ
ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፥ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና፤» ብሎታል። ዘፍ
፮፥፱-፲፫፣ ፯፥፩። በዚህም የኖኅን ጽድቅ እግዚአብሔር እንደመሰከረለት እናያለን። ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስም በዚህ ላይ ተመሥርቶ «ኖኅም ስለማይታየው ነገር የነገሩትን ባመነ ጊዜ ፈራ፤ ቤተሰቡንም ያድን
ዘንድ ክፍል ያላት መርከብ ሠራ፤ በዚህም ዓለምን አስፈረደበት፥ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ
ሆነ፤» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፯። የኖኅ መርከብ የቤተ ክርስቲያንም የእመቤታችንም ምሳሌ ናት።  ኖኅና ቤተሰቦቹ
በመርከቧ እንደዳኑ፥ ቤተ ክርስቲያን በጸጋዋ፥ እመቤታችን በአማላጅነቷ ያድናሉ። አንድም፦ እግዚአብሔር
ኖኅን እና ቤተሰቦቹን መርከቧን ምክንያት አድርጎ እንደ አዳነ፥ እመቤታችንንም ምክንያት አድርጎ ዓለምን
አድኗል። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፥ እመቤታችንን፦ «ለእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መሣሪያ ሆና
ተገኝታለችና፤» የሚሉት ለዚህ ነው፡፡

፩፥፬፦ በእንተ አብርሃም፤

          አብርሃም እግዚአብሔርን ፈልጎ በማግኘቱ፥ «ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ


ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም
ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤»
ተብሏል። ዘፍ ፲፪፥፩-፫። በዚህ ትንቢት መሠረት ከወገኑ የተወለደች እመቤት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ
በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን ለፍጥረቱ ሁሉ የምታሰጥ ሆናለች። ከእርሷ የተወለደ ኢየሱስ ክርስቶስም
በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን በልግስና ሰጥቷል። ዘሩ እንደ ምድር አሸዋ እና እንደ ሰማይ ከዋክብት
እንደሚበዛለትም ተነግሮታል። ዘፍ ፲፪፥፲፮፣ ፲፭፥፭። በአሸዋ የተመሰሉት ከእርሱ ወገን ተወልደው ኃጥአን
የሚሆኑትን ሲሆን፥ በከዋክብት የተመሰሉት ደግሞ ከእርሱ ወገን የሚወለዱ ጻድቃን ናቸው። ሥላሴን
በድንኳኑ አስተናግዷል። ዘፍ ፲፰፥፩-፲፭። የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም
ምሳሌ ናት። የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ሚስቱን ሣራን በወሰደበትም ጊዜ እንዳይቀርባት አድርጎ እግዚአብሔር
ጠብቆለታል፥ ንጉሡንም በሕልም ገሥፆለታል። በመጨረሻም፦ ስለ አብርሃም፦ «አሁንም የሰውየውን ሚስት
መልስ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ
የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ ዕወቅ።» በማለት ለንጉሡ ነግሮታል። ዘፍ ፳፥፩-፯። እግዚአብሔር
የመሰከረው የአብርሃምን ቅድስና ብቻ ሳይሆን ጸሎቱም እንሚያድን ጭምር ነው። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «የአብርሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ
ነበር. . . አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።» እያለ መስክሮለታል።
ይኸውም አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ መልከጼዴቅን በማየቱ ክርስቶስን እንዳየ ተቆጥሮለታልና ነው። ዮሐ
፰፥፴፱፤ ፶፮። ከዚህም ሌላ «ድሀውም (አልዓዛርም) ሞተ፥ መላእክትም በአብርሃም እቅፍ
አስቀመጡት።»በማለት ተናግሮለታል። በዚህም የመንግስተ ሰማያትን ክብር በአብርሃም እቅፍ መስሎታል።
ሉቃ ፲፮፥፳፪። ከዚህም፦ ከቅዱሳን እቅፍ መውጣት ማለት፥ ከመንግሥተ ሰማያት መውጣት እንደሆነ
እንማራለን።

፩፥፭፦ በእንተ አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብ፤

          እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ቃል ኪዳን ለልጁ ለይስሐቅ፥ ለልጅ ልጁ ለያዕቆብም


አጽንቶላቸዋል። በምድር ላይ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ረሀብ በላይ ረሀብ በሆነ ጊዜ፥ ይስሐቅ ወደ
ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቤሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ተገለጠለትና፦ «ወደ ግብፅ
አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ። በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥
እባርክሃለሁም፤ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም
ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥
ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና።» አለው። ዘፍ ፳፮፥፩-፮። ይስሐቅ የአብርሃም የቃል ኪዳን
ልጅ በመሆኑ በአዲስ ኪዳን ዘመን ከውኃና ከመንፈስ ተወልደው (በሥላሴ ስም ተጠምቀው) የእግዚአብሔር
ልጆች ለሚሆኑ ክርስቲያኖች ምሳሌ ሆኗል። ሮሜ ፱፥፮-፱፣ ገላ ፬፥፳፩-፴፩።

          እግዚአብሔር ለያዕቆብም በፍኖተ ሎዛ ጫፏ ሰማይ በደረሰ መሰላል ላይ ተገልጦለታል፦ «የአባትህ


የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተ
እሰጣለሁ፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ
ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። እነሆ፥ አኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥
በምትሄድበትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ
ድረስ አልተውህምና።» ብሎታል። ዘፍ ፳፰፥፲፫-፲፭። እግዚአብሔር የተገለጠባት መሰላል የእመቤታችን
የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት። ምክንያቱም እግዚአብሔር በተዋሕዶ ሰው ሆኖ ተገልጦባታልና ነው።
ጫፏ ሰማይ መድረሱም የወላዲተ አምላክ ክብሯ ሰማያዊ መሆኑን ያጠይቃል። እግዚአብሔር በደብረ ሲና
ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜም፦ «እኔ የአባትህ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም
አምላክነኝ፤» በማለት መስክሮላቸዋል። የደኅና ልጅ አባት በልጁ ተመክቶ የእገሌ አባት ነኝ እንደሚል፥
እግዚአብሔርም በእነርሱ ተመክቶ የእነርሱ አምላክ ነኝ በማለት መስክሮላቸዋል። በአዲስ ኪዳንም ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም፥ አምላክ የያዕቆብም
አምላክ ነኝ፥ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው
እንጂ የሙታን አይደለም።» በማለት ተናግሮላቸዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በብሉይ ኪዳን እና
በአዲስ ኪዳን ላይ ተመሥርቶ፦ «አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስት አድርጎ ይወርሰው ዘንድ ወደአለው ሀገር
ለመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚደርስም ሳያውቅ ሄደ። በእምነትም ከሀገሩ ወጥቶ ተስፋ በሰጠው
ሀገር እንደ ስደተኛ በድንኳን፥ ተስፋውን ከሚወርሱአት ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ኖረ። መሠረት ያላትን
ሠሪዋና ፈጣሪዋ እግዚአብሔር የሆነላትን ከተማ ደጅ ይጠኑ ነበርና።» ብሏል። ዕብ ፲፩፥፰-፲። በዚህም፦
የቅዱሳን በረከት ለልጅ ልጅ እንደሚተርፍ፥ ሕያዋንም እንደሆኑ መስክሮላቸዋል። ከዚህም ሌላ፥ ክርስቲያኖች
በዚህ ዓለም ከቅዱሳን ጋር እንደምንኖር ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያትም ከእነርሱ ጋር እንደምንኖር፥ ጌታችን
መስክሯል። «እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም
ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤» ብሏል። ማቴ ፰፥፲፩።

፩፥፮፦ በእንተ ሙሴ፤

          እግዚአብሔር ሙሴን በጠራው ጊዜ፥ «እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥
የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ፤. . . ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደኅና እንዲናገር
አውቃለሁ፤ እነሆም ዳግም ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም ትናገረዋለህ፥
ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ። እርሱ
ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንሃል፥ አንተም በእግዚአብሔር ፈንታ
ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።» ብሎታል። ዘጸ ፬፥፲፬-
፲፯። ከዚህም በላይ፦ «ረሰይኩከ አምላኮ ለፈርዖን፤ ወአሮን እኁከ ይኩንከ ነቢየ፤ ለፈርዖን አምላክ (የጸጋ ገዥ
አድርጌሃለሁ)፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሁንልህ፤» ብሎታል። ዘጸ ፯-፩።

          የነቢያት አለቃ ሙሴ፥ ኢትዮጵያዊቷን ሴት በማግባቱ፥ ወንድሙ አሮን እና እኅቱ ማርያም አምተውት
ነበር። «በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ የተናገረ አይደለምን?» ማለታቸውን
እግዚአብሔር ሰምቶ፥ ሦስቱንም ወደ መገናኛው ድንኳን ከጠራቸው በኋላ በደመና ዓምድ ወርዶ በድንኳኑ
ደጃፍ ከቆመ በኋላ፥ «ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥
ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ
ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ
ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም።» ብሎ ድምፁን አሰምቶአቸዋል። ዘኁ ፲፪፧፩-፰። በዚህም በቅዱሳን ላይ
በድፍረት መናገር እንደማይገባ አስተምሯል። ማስተማር ብቻም ሳይሆን በአሮን እና በማርያም ላይ
ተቆጥቶባቸዋል። በዚህ ምክንያት ማርያም እኅተ ሙሴ በለምፅ ነድዳለች። አሮንም ወደ ሙሴ ተመልሶ፦
«ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና፤ እባክህ ኃጢአት አታድርግብን።» ብሏል። ዘኁ ፲፪፥፱-፲።
ከዚህም በቅዱሳን ላይ መናገር ስንፍና፥ በደል፥ ኃጢአት መሆኑን እንማራለን። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፦ «እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም
ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴንም ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።
መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ? ብሏል። ዮሐ ፭፥፵፭።

ይቀጥላል. . .   

ነገረ ቅዱሳን፦ ክፍል ፲፬


የእግዚአብሔር ምስክርነት (ለ)

ካለፈው የቀጠለ  . . .

፩፥፯፦ በእንተ አሮን፤

አሮን፦ የሙሴና የማርያም ወንድም ነው፤ ዘጸ ፮፥፳፣ ዘኁ ፳፮፥፶፱። እግዚአብሔር ለሙሴ ተገልጦ፥
ምልክት አስጨብጦ፥ ወደ ግብፅ እንደሚልከው በነገረው ጊዜ፥ « ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ ትናንት፥ ከትናንት
ወዲያ ባሪያህን ከተናገ ርኸኝ  ጀምሮ አፈ ትብዕ (አንደበተ ርቱዕ) ሰው አይደለሁም። እኔ አፈ ኰልታፋ፥
ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ።» ብሎ ነበር። እግዚአብሔርም፦ «ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? ዲዳስ፥
ደንቆሮስ፥ የሚያይስ፥ ዕውርስ የሚያደርግ ማን ነው? እኔ እግ ዚአብሔር አይደለሁምን? እንግዲህ አሁን ሂድ፤
እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ፤ (ልብ እንድትል አደርግሃለሁ)፤»
አለው። ሙሴም መልሶ፦ «ጌታ ሆይ እማልድሃለሁ፤ መናገር የሚችል የምትልከው ሌላ ሰው ፈልግ፤» አለ።
እግዚአብሔርም በሙሴ ላይ እጅግ ተቆጥቶ፦ «ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ እንደሚና
ገርልህ አውቃለሁ፤ እነሆም፥ እርሱ ሊገናኝህ ይመጣል፤ በአየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። አንተም
ትናገረዋለህ፤ ቃሌንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ አንደበትህንና አንደበቱን አረታለሁ፤ የምታደርጉትንም
አለብማችኋለሁ። (ልብ እንድትሉ አደርጋች ኋለሁ)። እርሱ ስለ እናንተ ከሕዝቡ ጋር ይነጋገራል፤ እርሱ አፍ
ይሆንልሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ዘንድ ትሆንለታለህ። ይህችንም ተአምራት የምታደርግበትን በትር
ያዝ፤» ብሎታል። ዘጸ ፯፥፩-፪።

ሙሴ ወደ ፈርዖን በቀረበ ጊዜ፥ ከዚያም በኋላ የአርባው ዓመት የምድረ በዳ ጉዞ እስኪያልፍ ድረስ፥
አሮን፦ ሙሴ በሚሠራው ሥራ ሁሉ የቅርብ ረዳቱ ነበር። የእስራኤል ልጆች ከአማሌቅ ጋር በተዋጉ ጊዜ
አሮንና ሖር ለጸሎት የተዘረጋ የሙሴን እጆች ይደግፉ ነበር። ዘጸ ፲፯፥፱-፲፪። እስራኤል ዘሥጋ በዳታን
በአቤሮን እና በቆሬን መሪነት በሙሴና በአሮን ላይ (የሙሴን ምስፍና፥ የአሮንንም ክህነት በኃይል ለመንጠቅ)
በተነሡ ጊዜ እግዚአብሔር ተቆጥቶባቸው ነበር። ከእስራኤልም ልጆች በምክር የተመረጡ፥ ዝናቸውም
የተሰማ ሁለት መቶ ሃምሣ የማኅበሩ አለቆች ከዓመጻኞቹ ጋር ተሰልፈው ነበር። ሙሴንና አሮንንም፦
«ለአናንተ ይበቃችኋል፤ (እናንተ ከሌላው ሕዝብ በምንም አትለዩም)፤ ማኅበሩ፦ (ሕዝቡ) ሁሉ እያንዳንዳቸው
ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና፤ በእግዚአብሔርስ ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?»
አሉአቸው። ሙሴ ግን በፍጹም ትኅትና በግንባሩ ከፊታቸው ተደፍቶ ለመናቸው፥ ፍርዱንም ከእግዚአብሔር
እንዲጠብቁ (ቅዱሳን የሆኑትንና ያልሆኑትን እንዲያሳያቸው) ወደ እርሱ አሰናበታቸው። ቆሬንና ሁለቱ መቶ
ሃምሣዎቹ ሰዎች ሊያጥኑ በድፍረት ወደ ታቦተ ጽዮን በገቡ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንደተለበለበ ግንድ
ሆኑ፥ ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ። ዳታንና አቤሮን ቤተሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች
ሁሉ፥ ከብቶቻቸውንም ሁሉ መሬት ተከፍታ ዋጠቻቸው። እነርሱም፥ ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ
በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፤ በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ
ከጩኸታቸው የተነሣ፥ «ምድሪቱ እንዳትውጠን» ብለው ሸሹ።

በነጋውም የእስራኤል ልጆች የተደረገውን ተአምራት አይተው ከክፋት ከመመለስ ይልቅ፦ «እናንተ
የእግዚአብ ሔርን ሕዝብ ገድላችኋል፤» ብለው በሙሴና በአሮን (እግዚአብሔር በመረጣቸውና
በመሰከረላቸው ቅዱሳን) ላይ አጉረመ ረሙ።» በዚህን ጊዜ፥ እግዚአብሔር በደመና ዓምድ ወረደ፥
በመገናኛው ድንኳን ላይ ክብሩን ገለጠ። ሙሴንና አሮንንም፦ «ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም
በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ፤» አላቸው። እነርሱም እግዚአብሔርን ስለ ሕዝቡ ሊማ ልዱት በግንባራቸው ወደቁ።
መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፥ ነገር ግን በሙሴ አማላጅነት፥ በአሮንም ማዕጠንት ቆመ። በቆሬ
ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት አሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ይህ ሁሉ የሆነው
እግዚአብ ሔር ለቅዱሳኑ ሲመሰክርላቸው ነው። ዘኁ ፲፮፥፩-፶። ከዚህም ሌላ፦ በእግዚአብሔር ትእዛዝ
በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ልክ ወደ ቤተ መቅደስ ከገቡት አሥራ ሁለት ደረቅ በትሮች መካከል፥ በሙሴ
ጸሎት የአሮንን በትር እንደትለመልም፥ እንድታብብና ለውዝ እንድታፈራ በማድርግ መስክሮላቸዋል።
ሙሴም በትሮቹን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አወጣቸው፤ እነርሱም አዩ፤
እያንዳንዱም ደረቅ በትሩን ወሰደ። እግዚአብሔርም፦ «ማጉረምረማቸው፤ ከእኔ ዘንድ እንዲጠፋ፥ እነርሱም
እንዳይሞቱ ለማይሰሙ ልጆች ምልክት ሆና ትጠብቅ አንድ የአሮንን በትር በምስክሩ ፊት አኑር፤» አለው።
ዘኁ ፲፯፥፩-፲፪። ሳይተክሏትና ውኃ ሳያጠጧት ለምልማ፥ አብባና አፍርታ የተገኘች፥ በቤተ መቅደስም
የኖረች የአሮን በትር፥ እንበለ ዘርዕ ፀንሳ አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ
ናት።

፩፥፰፦ በእንተ ኢያሱ ወአልዓዛር፤

እግዚአብሔር፦ የነቢያት አለቃ የሆነውን ሙሴን ወደ ናባው ተራራ ጠርቶት በዚያ እንደሚሞት
በነገረው ጊዜ፥ ያሳሰበው ትልቅ ነገር ቢኖር፥ ከእርሱ በኋላ ማን እንደሚተካው ነበር። በመሆኑም፦ «የሥጋና
የነፍስ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር፥ በዚህ ሕዝብ ላይ የሚሆነውን ይሹም፤ በፊታቸው የሚወጣውንና
የሚገባውን፥ የሚያስወጣቸውንና የሚያስገባቸውንም፥ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ
እንዳይሆን።» በማለት ለእግዚአብሔር ተናገረ። በዚህም ለሕዝቡ ከፊት መሪ፥ ከኋላ ተከታይ እየሆነ፥
የሚያወጣቸውንና የሚያገባቸውን (መልካም እረኛ) እንዲመርጥላቸው እግዚአብሔርን ጠየቀ።
እግዚአብሔርም የወዳጁን ልመና ተቀብሎ፥ «መንፈስ ቅዱስ ያለበትን (ያደረበትን) የነዌን ልጅ ኢያሱን
ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ (ሹመው)፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት አቁመው፤ በማኅበሩም ፊት እዘዘው፤ ስለ
እርሱም በፊታቸው እዘዝ። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ ስጠው። (ክብርህን፥ ጸጋህን፥
ሹመትህን አሳድርበት)። በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ፍርድ ይጠይቅለት፤
(በካህኑ በአልዓዛር ፊት ቁመው በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚናገረውን ፍርድ ይጠይቁለት)፤ እርሱ ከእርሱም ጋር
የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፤ በቃሉም ይግቡ። (ኢያሱና የእስራኤል ልጆች ሠራዊቱም ሁሉ
በአልዓዛር ቃል ይግቡ፥ ይውጡ)፤» አለው።

አልዓዛር የስሙ ትርጓሜ «እግዚአብሔር ረድቶናል፤» ማለት ነው።ከአባቱ ከአሮንና ከተቀሩት ሦስት ወ
ንድሞቹ ጋር በክህነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር የመረጠው ሰው ነው። ስማቸውም፦ ናዳብ አብዩድ እና ኢታ
ምር ይባላል። እግዚአብሔር ሙሴን፦ «አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች 
መካከል ለይተህ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤» ያለው ለዚህ ነበር። ዘጸ ፳፰፥፩። በመጨረሻም
፦ «በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም፤» ብሎታል። ዘጸ ፴፥፴።  

            ተቀድሶ መርከስ፥ ከብሮ መዋረድ፥ ተቀብቶ ተርታ መሆን ስለሚያጋጥም፥ ናዳብና አብዩድ ሥርዓተ
ቤተ መቅደስን በመተላለፋቸው፥ የእግዚአብሔርን ቤት በመድፈራቸው፥ ከሰማይ በወረደ እሳት ተቃጥለው፥
በእግዚአብሔር ፊት ሞተዋል። ዘሌ ፲፥፩-፪። አልዓዛር ግን አሮን ከሞተ በኋላ በምትኩ ሊቀ ካህናት ሆኗል።
ዘኁ ፫፥፴፪። እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን፥ በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ በሖር ተራራ፦ «አሮን ወደ ወገኑ
ይጨመር፤ (በሞት ከሞቱት ወገኖቹ ጋር ይቀላቀል)፤ በክርክር ውኃ ዘንድ ስለአሳዛናችሁኝ እኔ ለእስራኤል
ልጆች ወደሰጠኋት ምድር አትገቡም። አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ በማኅበሩ ፊት ወደ ሖር ተራራ
አምጣቸው፤ ከአሮንም ልብሱን አውጣ፤ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኖቹ ይጨመር፤
በዚያም ይሙት።» ብሎት ነበር። ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ። ዘኁ ፳፰፥፳፪-፳፱።

ኢያሱ፦ የስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር አዳኝ (መድኃኒት) ማለት ነው። ከግብጽፅ የወጣው ገና ታናሽ
ብላቴና እያለ ነው። አያቱ ኤሊሳማ የኤፍሬም ነገድ አለቃ ነበረ። ፩ኛ ዜና ፯፥፳፮-፳፯፣ ዘኁ ፩፥፬-፲።
ኢያሱ፦ በሙሴ ትእዛዝ ከአማሌቃውያን ተዋግቶ አሸንፏል፤ የረዳውም የሙሴ ጸሎት ነው። ዘጸ ፲፯፥፰-፲፫።
(አማሌቃውያን፦ ከአማሌቅ የተገኙ ነገዶች ናቸው፥ ከእስራኤል አገር በስተደቡብ በኲል ይኖሩ ነበር። ከሙሴ
እስከ ሕዝቅያስ ዘመን ድረስ እስራኤልን ይቃወሙ ነበር። ዘጸ ፲፯፥፰፣ መሳ ፫፥፲፫፣፮፥፫። ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፫፣
፩ኛ ዜና ፬፥፵፫። አማሌቅ የዔሳው የልጅ ልጅ ነው። ኢያሱ፦ በሙሴ እግር እግዚአብሔር እስኪተካው ድረስ
የሙሴ አገልጋይ ነበር። ዘጸ ፳፬፥፲፫፣ ፴፪፥፲፯፣፴፫፥፲፩፣ዘኁ ፲፩፥፳፰። ሙሴ ምድረ ርስትን እንዲሰልሉ
በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከላካቸው አሥራ ሁለቱ ሰዎች መካከል አንዱ ኢያሱ ነበር። ኢያሱና ካሌብ
እግዚአብሔር ምድረ ርስትን እንደሚያወርሳቸው በእምነት በመናገራቸው የተስፋው ወራሾች ሆነዋል። ዘኁ
፲፫ እና ፲፬። በመጨረሻም በሙሴ እግር ተተክቶ የእስራኤል መሪ ሆኗል። ዘኁ ፳፯፧፲፭_፳፫፤ ዘጸ
፫፧፳፱፣፴፩፥፳፫።

እግዚአብሔርም፦ «በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ


ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም። ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን
ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ በርታ፤ አገልጋዬ ሙሴ እንደአዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ
ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል። የዚህ
ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም
አንብበው፣ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል፤ አስተዋይም ትሆናለህ። እነሆ አዝዝሃለሁ፤ በምትሄድበት
ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።» ብሎታል። ኢያ
፩፥፭-፱። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ተገልጦለታል። ኢያ ፭፥፲፫። በመጀመሪያ እግዚአብሔር፥
ሁለተኛም የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ያበረታቱት ኢያሱ በታቦተ እግዚአብሔር ላይ በተገለጠ ኃይለ
እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ ለሁለት ከፍሎታል፥ የኢያሪኮንም ግንብ አፍርሷል። ኢያ ፫፥፩-፲፯፣ ፮፥፩-
፳፯። ከኢያሪኮ ነገሥታት ጋር በሚዋጉበትም ጊዜ፥ «በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፤ በኢሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤»
አለ። እግዚአብሔርም አደረገለት። ኢያ ፲፥፲፪-፲፫።

ከታሪኩ እንደምንረዳው፥ በመስፍኑ በሙሴ እግር ኢያሱን የተካ፥ በካህኑ በአሮንም ፈንታ ልጁን
አልዓዛርን የተካ እግዚአብሔር ነው። መተካት ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ኢያሱ፦ «መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው
ነው፤» በማለት መስክሮታል። ስለ አልዓዛርም፦ «ኢያሱና የእስራኤል ልጆች ሠራዊቱም ሁሉ በአልዓዛር ቃል
ይግቡ፥ ይወጡ፤ (ይታዘዙለት)፤» በማለት መስክሮለታል። ከዚህም ክህነት ከፍ ያለ ሥልጣን መሆኑን
እንማራለን። አስተማሪውም እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም፦ የዚህ ዓለም መሳፍንት «በዚህ ውጡ፥ በዚህ
ግቡ፤» እያሉ እንደ ጠፍ ከብት ሲነዱን፥ እንደ በግ ሲጐትቱን ልናፍር ይገባናል። ከሁሉም የሚያሳፍረው
መነዳታችንና መጐተታችን በፈቃዳችን መሆኑ ነው።

፩፥፱፦ በእንተ ባስልኤል ወኤልያስ፤

እግዚአብሔር ሙሴን፦ «እይ! ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠር
ቼዋለሁ።  በሥራ ሁሉ ያስተውል ዘንድ በጥበብም፥ በማስዋልም፥ በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ
(መንፈሰ ረድኤትን) ሞላሁበት፤ (አሳደርሁበት)፤ የአናጺዎች አለቃ ይሆን ዘንድ ወርቅንና ብርን፥ ናስንም፥
ብጫና ሰማያዊ፥ እጥፍ ሆኖ የተፈተለ ነጭና ቀይ ሐርን ይሠራ ዘንድ፤በሥራውም ሁሉ የሚደረገውን
የድንጋይ ማለዘብ፥ ከእንጨትም የሚጠረበውን ይሠራ ዘንድ። እኔም እነሆ፥ ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን
ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ። (ኤልያብን ለባስልኤል አጋዥ አድርጌ ሰጠሁት)፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ
በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ዕውቀትን ሰጠሁ ። የምስክሩን ድንኳን፥ የቃል ኪዳኑንም ታቦት፥ በእርሱም
ላይ ያለውን መግጠሚያም ይሠሩ ዘንድ)፤ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፤ (ንዋየ ቅዱሳቱን) የዕጣን መሠዊያውን፥
ገበታውንም፥ ዕቃውንም፥ ከዕቃውም ሁሉ የነጻውን መቅረዝ፥  (ዕጣን የሚታጠንበት ማዕጠንቱን ፋና
የሚበራበት መቅረዙን ከጠራ ወርቅ ይሠሩ ዘንድ፤ አዕፁቋን ምንባረ ፈትሏንም ይሠሩ ዘንድ)፤ ለሚቃጠል
መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ (ስብ የሚጤስበት ምሥዋዓ  ብርቱን መሣሪያውንም
ሁሉ ይሠሩ ዘንድ)፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም፥ (ኲስኲስቱን ከነመቀመጫው)፥ በክህነት አኔን
የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥ የሚቀቡትንም የቅብዐቱንም ዘይት፥
ለመቅደሱ የሚያጥኑትን ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ ፤» ብሎታል። ዘጸ ፴፮፥፩-፲፩። በዚህም
ለባስሌኤልና ለኤልያብ፦ መንፈሰ ረድኤትን እንዳሳደረባቸው፥ ጥበብን እንደሰጣቸውና እውቀትንም
እንደገለጠላቸው መስክሮላቸዋል።

You might also like