You are on page 1of 29

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ትናንት እና ዛሬ።

ይህ ጽሁፍ ከዚህ በፊት የታላቁ ሊቅ ለጌታው አለቃ ኅሩይ መጽሐፍ «ፍኖተ እግዚአብሔር » ሲታተም
እንደ መግቢያ ሁኖ እንዲያገለግል ሁኖ ወጥቶ ነበር። አሁንም የጥንት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በነገረ
ሥጋዌ፣ በትምህርተ ሥላሴ እና በሌሎችም ርሶች የጻፋቸውን ጽሁፎች፣ የተከራከሩባቸውን ርዕሰ ነገሮች
ለታሪክና ለትምህርት እንዲሆኑ በዚህ አምድ ስለምናቀርብ እንደ መግቢያ ሁኖ ቀርቧል።

ትናንት

በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር የኢትዮጵያን የአምልኮተ እግዚአብሔር መነሻ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በቅድሚያ
እንመለከታለን

ቅድመ ልደተ ክርስቶስ

ኢትዮጵያ በጥንተ ተፈጥሮ ስትፈጠር እና በዕለተ ሰኑይ (ሰኞ ቀን) እግዚአብሔር የምድርን መልክ
ሲያስተካክል፡ መጋቢ ወንዞችንም ለመግቦተ ምድር ሲሠራ፡ የዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት ዋዜማ ያልበደለው
(ከበደል በፊት የነበረው) የሰው ልጅ መኖሪያ እንድትሆን የተከላትን ገነትን ከሚያጠጡት ወንዞች ሁለተኛው
ግዮን እንዲከብ አድርጎ ነበር በዕረፍት ውኃ ዳር ያሰማራት:: "ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔደን ይወጣ
ነበር፤ የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው:: እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል::" ዘፍ ፪:፲-፲፫ ብሎ
የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ እንደጻፈልን:: ይህም ኢትዮጵያ እግዚአብሔር የዕረፍት ውሃ መፍሰሻ የበረከት
ምድር ሕዝቦቿም በምህረቱ የተከበቡ በረድኤቱ ጥላ ሥር ያደሩ በጎረገነት (በገነት አጠገብ) የሚኖሩ
መሆናቸውን ያሳያል:: መጽሐፈ ኢዮብ በከበረ ማዕድኗ ያደነቃት ኢትዮጵያን፡ (ኢዮብ ፳፰፥፲፱) ቅድመ
ልደተ ክርስቶስ በአምልኮተ እግዚአብሔር መኖሯንና በእግዚአብሔር ፊት የተዘረጋ የአምልኮ እጅ እንዳላትና
እንደሚኖራት ዳዊትም ተናግሮላታል፡ ዘምሮላታል::

ዳዊት "ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር" አለ፤ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር


ትዘረጋለች” ማለት ነው።(መዝ ፷፯:፴፩) ይህም ትንቢቱ በኢትዮጵያዊት ንግሥተ ሳባ እና በልጁ በሰሎሞን
ዘመነ መንግሥት መፈጸሙን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል:: "የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም
የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች...የሳባ ንግሥትም የሰሎሞንን
ጥበብ ሁሉ… ለእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም:: ንጉሡንም
አለችው...አንተን የወደደ በእስራኤል ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን::" አለች (፩ኛ
ነገሥት ፲:፩-፲)

"ነፍስ አልቀረላትም” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የንግሥቲቱ የልብ እና የአእምሮ እጆች ለአምልኮተ


እግዚአብሔር፤ ለጸሎት እና ለትምህርት መዘጋጀታቸውን ነው:: ንግሥቲቱን ከማረካት ዋነኛውና ተቀዳሚው
ነገር ያየችው የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥርዓትና መሥዋዕት ነበር:: ይህ ባሕርይ እስከ ዛሬ ድረስ
በኢትዮጵያውያን ባሕርይ ይታያል:: ኢትዮጵያውያን ከምንም በፊት፡ ከምንም በላይ የምንወደው፡
የሚማርከን ነገር አምልኮተ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን በግልፅ እናያለን:: “ኢትዮጵያ” የሚለው ስሟም
በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ ይነበባል1

በንግሥተ ሳባ ጉዞ የተመሠርተው ትምህርተ ኦሪት እስከ ሐዲስ ኪዳን ቀጥሎ ክርስቶስ በእስራኤል
በሚሰበክበት ጊዜ፡ ኢትዮጵያም ለአምልኮተ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌም ትገኝ ነበረ፡፡ ጃንደረባው መንፈስ
ቅዱስ በላከው በፊልጶስ የሚያነበው ብሉይ ኪዳን ተተርጉሞለት፣ በክርስቶስ አምኖ፣ የሐዲስ ኪዳን ሰው
ሁኖ፣ እንደገና ተወልዶ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቆ፣ ከግላ ኦሪት (ከኦሪት ጨለማ) ተላቆ፣ ተደስቶ፣ ወደ
ኢትዮጵያ እንደተመለሰ በመጀመሪያው የሐዲስ ኪዳን የቤተክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍ ሉቃስ ጽፎት
እናነባለን:: ቃሉም እንዲህ ይላል "ሕንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቧም
ሁሉ ላይ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበረ:: ሲመለስም በሰረገላ
ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር:: መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኘው
አለው... በውኑ የምታነበውን ታውቀዋለህን? አለው:: እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻላል?
አለው... ጃንደረባውም... እባክህ ነቢዩ ይህን ስለማን ይናገራል አለው... ፊሊጶስም አፉን ከፈተ ከዚህም
መጽሐፍ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት:: ጃንደረባውም እነሆ ውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ
ምንድር ነው? አለ ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዷል አለው:: ኢትዮጵያዊውም "ኢየሱስ
የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ አለ... አጠመቀው ደስ ብሎትም መንገዱን ይሄድ ነበርና" የሐዋ
፰:፳፮-፵ ብሎ ጽፎልናል ቅዱስ ሉቃስ::
1
ዘ ኁ ፲ ፪ :፩ :: ፪ ኛ ነ ገ ሥት ፲ ፱:፱:: ፪ ኛ ዜና መዋ ፲ ፪ :፫ :: ፪ ኛ ዜና መዋ ፲ ፬ :፱-፲ ፫ :: ፲ ፮ :፰:: ፳፩ :፲ ፮ ::
፰:፲ ፱:: አስ ቴር ፩ :፩ :: ኢዮ ፳፰:፲ ፱:: መዝ ፷፯ :፴፩ :: ፹፮ :፬ ::ኢሳ ፲ ፰:፩ :: ፳:፫ -፭:: ፴፯ :፱::
፵፫ :፫ :: ፵፭:፲ ፬ ኤር ፲ ፫ :፳፫ :: ፴፰:፯ :: ፴፰:፲ ፪ :: ፴፱:፲ ፮ :: ፵፮ :፱:: ሕዝ ፳፱:፲ :: ፴:፵:: ፴፰:፭::
ዳን ፲ ፩ :፵፫ አሞጽ ፱:፯ ና ሆም ፫ :፱ ::ሶ ፎን ያ ስ ፪ :፲ ::፪ ፫ :፲ :: ዕ ዝራ ካዕ ል ፫ :፪ :: ዮዲት ፩ :፲ አስቴር ፫ :፩
የ ተወሰኑትን ከትልቁ መጽሐፍ ቅዱስ ይመልከቱ::
ከዚህ ታሪክ የኢትዮጵያ አስተምህሮ መሠረት የሆኑ አምስት ነገሮችን እንገነዘባለን፣ እነዚህም

1. ይህ ሰው ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱን፣

2. አንባቢ መሆኑን፣

3. ጠይቆ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ለመረዳት መምህርና የመንፈስ ቅዱስም ምሪት ወሳኝ
መሆኑን፣

4. ሲገባው በሃይማኖት መታዘዙን፣

5. ተጠምቆ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በሆነው ደስታ ተሞልቶ ወደ ሀገሩ መመለሱን ያስገነዝበናል::


ለመጀመሪያ ጊዜ በጃንደረባው ወደ ኢትዮጵያ የገባው የክርስትና አስተምህሮ በአክሱም ዘመነ
መንግሥት አካል ገዝቷል::

የአክሱም ዘመነ መንግሥትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ

በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተሰበከውና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስትና በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን


ተከናውኖ አስተምህሮው ተስፋፍቶ በሊቀ ጳጳሳት፣ በኤጲስ ቆጶስ፣ በቀሲስ፣ በዲያቆን የአገልግሎት የሥራ
መዋቅር ተጠናክሮ ቀጠለ::

በቅዱስ አትናቴዎስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ለመሆን የበቃው በዘሩ ግሪካዊ እንደሆነ
የሚነገርለትና በአክሱም አድጎ ለዚህ ክብር የበቃው ፍሬምናጦስ የወንጌልን ብርሃን በኢትዮጵያ እንዲበራና
የአረማዊነትም ጨለማ ፈጽሞ እንዲገፈፍ በማድረጉ "ከሣቴ ብርሃን” ተባለ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ
የተገኘውን ሰላም በመስበክ ርቀው የነበሩትን ወደ ክርስቶስ በማቅረብ "የክርስቶስን ሰላም" ሰዎች እንዲያገኙ
በማድረጉ "ሰላማ" ተባለ::

ይህ አባት የኢትዮጵያን ቋንቋ፣ ባሕል፣ ልማድ ጠንቅቆ ያወቀ፡ በዜግነቱም ኢትዮጵያዊ ስለነበረ፡
በቤተ መንግሥትም ፍጹም ተቀባይነት ስለነበረው ወደ እስክንድርያ ሂዶ ተሹሞ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ መሠረት ለመጣልና ለማሻሻል ትልቅ ጥረት
አድርጓል::
በአክሱም ዘመነ መንግሥት በአባ ሰላማ የአገልግሎት ዘመን የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች

፩. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን "ማኅበረ ጽዮን" ተብላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአክሱም ጽዮን
ቤተ ክርስቲያን ተቋቋመች:: በነገሥታቱ ቅንነትና ድካም አሥራ ሁለት በሮች ያሏት የአክሱም ጽዮን ቤተ
ክርስቲያን ታንጻ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ሥርዓተ አምልኮውን በአንድነት እንዲያካሂድ የእግዚአብሔርንም
ቃል እንዲማር ተደርጓል::

፪. በጃንደረባው የተሰበከው የክርስትና ሃይማኖት በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንዲከናወን፤ ሕዝቡ


እንዲጠመቅ፤ እንዲቆርብ እና ሌሎችንም ሥርዓቶች እንዲያገኝ ተደርጓል::

፫. የቀደመው ሳባዊ ፊደላችን አሁን ያለውን መልክ እንዲይዝ እና ከልዩ ልዩ ቋንቋ ወደ ሀገራችን ቋንቋ ወደ
ግዕዝ ቅዱሳት መጽሐፍት እንዲተረጎሙ አድርጓል::

፬. ቀድሞ በአክሱም በነበረው የብሉይ ኪዳን አምልኮተ እግዚአብሔር ያገለግሉ የነበሩ የብሉይ ኪዳን
ሊቃውንት ክርስትናን ተቀብለው "ኦሪትሰ መርሐ ኮነተነ ለኀበ ክርስቶስ እንከሰ ኢንፈቅድ መርሐ" “ኦሪት
ወደ ክርስቶስ መርታ አድርሳናለች ከዚህ በኋላ መሪ (ሞግዚት) አያሻንም” ብለው እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፡
የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓትና አስተምህሮ ወደ ሐዲስ ኪዳን እንደለወጡት፡የቀደመውንም ዕብራዊ
ትርጓሜ ስልት በማስፋት አማናዊውን ከምሳሌ፣ አካሉን ከጥላ፣ ኦሪትን ከወንጌል፣ ሕገ ጸጋን ከሕገ መንፈስ፣
ሙሴን ከክርስቶስ፣ ግዝረትን ከጥምቀት፣ መርገመ ኦሪትን ከበረከተ ወንጌል፣ መንፈሰ ረድኤትን ከመንፈሰ
ልደት፣ ለይተው እንዲያስተምሩ በትርጓሜ እንዲራቀቁ በምስጢር ባሕር እንዲጠልቁ የእነ አትናቴዎስን እና
የሌሎችንም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዲያውቁ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱንም በአስምህሮዋ
እንዲያልቁ፣ እንዲያሳድጉ እያስተማረ እየሾመ ኃላፊነት እየሰጠ እንዲመሩ አድርጓቸዋል::

፭. ያመነው የተጠመቀው ሕዝብ በልዩ ልዩ ቦታ ሰፍሮ ስለሚገኝ፡ በምስጢራተ ቤተክርስቲያን የተከናወነውን


ሃይማኖቱን እንዲጠብቅ ፡የመጻሕፍትን ትርጓሜ በተማሩት ቀሳውስት በኩል መጠበቅ ማስጠበቅ ጀመረ::
ሰውንም በግል ሕይወቱ እየተከታተሉ ለማስተማር የሚያስችል የጠበቀ ስልትና ሥርዓት ቀየሰ::
፭.፩. አበ ንስሐ/የንስሐ አባት ሥርዓት ተሠራ

ይህም አንድ ቄስ የተወሰኑ ምእምናንን በትምህርት እንዲያሳድግ፣ በምክር እንዲያንጽ፣ በመንፈሳዊ


ሕይወታቸው እንዲያድጉ እንዲያስተምር፣ ወደ ዓለም እንዳይመለሱ እንዲጠብቅ የሚያስችል፣ የተጀመረው
የክርስትና ጉዞ መንገድ ላይ እንዳይቀር ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው የአገልግሎት ስልት ነው::

፭.፪ የክርስትና አባትና የክርስትና እናት ሥርዓትን ሠራ

ይህም በአገልግሎቱ ምእምናን እንዲሣተፉ የሚያደርግ፡ በሃይማኖት የጸኑ ፡በእውነት ያመኑ፡ ቃሉን ያጠኑ
ክርስቲያኖች፡ በሕጻንነቱ በውኃ የተጠመቀው ሕፃን ሃይማኖቱን ለመመስከር አፍ ስላልፈታ እና ስለማያውቅ
ስለ እርሱ ጸሎተ ሃይማኖትን ደግመው ፡ሃይማኖቱን ሊያስተምሩት ተስማምተው "እክህደከ ሰይጣን"
"ሰይጣን ክጀሀለሁ" አአምን ብከ ክርስቶስ አምላኪየ”፡ "ክርስቶስ አምላኬ ሆይ አምንብሃለሁ" ብለው፡ ስለ
እርሱ እጣቱን ይዘው መስክረው፡ አድጎ እንደ እነርሱ በእግዚአብሔር ቃል ጎልምሶ እስኪመሰክር ድረስ
በሚደረገው ልጆችን በሃይማኖት የማሳደግ ሥርዓት ላይ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው ሠርቷል:: ዛሬ ዛሬ ግን
በሰዎች ዘንድ የሥጋ ዝምድና መንገድ ሆኖ የክርስትና አባትም ሆነ የክርስትና እናት የክርስትና ልጃቸውን
“የዳቦና የቃል ልጅ” አድርገው ከትምህርት ማነስ የተነሳ ሥርዓቱን ያለ አግባብ ለሥጋ ዝምድና ሲጠቀሙበት
ይታያል::

በአጠቃላይ አባ ሰላማ መጻሕፍትን በመተርጎም ቀሳውስትን በመሾም ወንጌልን በመስበክ ከቤተ መንግሥት
ጋር ተስማመቶ በመሥራት የቤተ ክርቲያኒቱን አስተምህሮ መሠረት የጣለ ታላቅ ሊቅ፣ የሰላም አባት፣ ከሣቴ
ብርሃን ሆኗል:: ከዚህ በኋላ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ተጠያቂዎች መምህሮቿ እነማን እንደሆኑ እና
እንደነበሩ የአስተምህሮ ምንጮቿም እነማን እንደሆኑ ወይም ማን እንደሆነ የአስተምህሮ ስልቶቿም ምን ምን
እንደሚመስሉ ከላይ ከባለቤቱ ጀምረን በቅደም ተከተል እንመለከታለን::
የቤተ ክርስቲያን መምህራን እነማን ናቸው?

፩. ኢየሱስ ክርስቶስ

ቤተ ክርስቲያን "ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ" ተብሎ በኢሳያስ ፶፬:፲፫ እና በኤርምያስ


፴፩:፴፫-፴፬ ዮሐ ፮:፵፭ የተነገረው ቃል የተፈጸመላት፣ በትዕግስት ሰው በኢዮብ መጽሐፍ "እንደ እርሱ ያለ
አስተማሪ ማነው" ተብሎ እንደተጻፈ ወደርና ምሳሌ ከሌለው መምህር ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተማረች፡
ዛሬም የምትማር፡ የክርስቶስ ተማሪ ናት። በነቢዩ በሕዝቅኤል ትንቢት በ፵፯ኛው ምዕራፍ እንደተመለከትነው
ከመቅደሱ የሚመነጨው የሕይወት ውኃ የእግዚአብሔር ቃል በአበውም በነቢያትም በካህናትም
በነገሥታትም ዘመን የነበረው ከወገብ ያላለፈ ነበር:: ነገር ግን በአራተኛው ክፍለ ዘመን በክርስቶስ ዘመነ
ሥጋዌ በክርስቶስ የተሰበከው ወንጌል ሁለንተናን የሚቆጣጠር ሰው/ፍጡር/ ሊሻገረው የማይችል ወደ
ዓለም ሁሉ የሚደርስ፣ ለዓሣዎች ሕይወት የሚሰጥ፣ ተክሎችንም የሚያለመልም፣ የረከሰውን የሚቀድስ፣
የወደቀ የተባለውንም የሚያነሣ፣ ሕዝቅኤልን ያስደነቀ፣ በሐሳብ የነጠቀ፣ ልዩ ትምህርትን ቤተክርስቲያን
በክርስቶስ ከክርስቶሰ ተምራለች። መድኃኒታችን "መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተ ሁላችሁ ወንድማማች
ናችሁ... አለቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነው ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ" ማቴ ፳፫:፰-፲ ብሎ
ለሐዋርያት እንደ ፈሪሳውያን እውነተኛውን መምህር እርሱን ዘንግተው በትዕቢት እንዳይያዙ ባስተማረበት
አንቀጽ(ጉባኤ) እንደተናገረ፡እርሱ መምህራችን ሊቃችን ነው:: በመጽሐፈ ኪዳንም ቤተክርስቲያን
"ወመምህር ዘይትቃወም ለነ" "ተከራክሮ የሚረታልን መምህራችን እርሱ ነው" ትላለች:: በመሆኑም
የቤተክርስቲያን መምህር ክርስቶስ ነው:: ከእርሱ ያላገኘችውን፣ እርሱ ያላስተማረውን አትቀበልም
ያስተማራትንም አትረሳም አትጠራጠርም::

፪. ሐዋርያት

ከእውነተኛው መምህር የተማሩ፣ መምህራቸው እንዲያስተምሩ የፈቀደላቸው፣ ከመለኮታዊው መምህር


የወንጌል ጉባኤ የዋሉ (እንደ አባቶቻችን አባባል) ምሥጢር ያደላደሉ፣ አስተምሩ ደቀ መዛሙርትን አፍሩ
ተብለው የተላኩት ሐዋርያት መምህሮቻችን ናቸው። ሐዋርያት ክርስቶስን በዓይናቸው አይተውታል፡
በእጃቸው ዳሰውታል:: ታምራቱን ኃይሉን አይተዋል፣ ትምህርቱን ሰምተዋል፣ በረከቱን ተቀብለዋል፣
እንዲያስተምሩም ከእርሱ ተልከዋል። ስለዚህ ሐዋርያት የቃሉ አገልጋዮች ሁነው ኑረው አደራቸውን ለሌሎች
ሐዋርያውያን አበው ልጆቻቸው "ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ" "አደራ የሰጠኝን ወንጌል እኔም ሰጥቸሃለሁ" እያሉ
ወንጌሉን የማስተማር ኃላፊነት አደራን ሰጥተዋል:: ቤተክርስቲያንን በወንጌል ቃል ከማይጠፋው ዘር
ወልደዋታል:: ፩ቆሮ ፬፡፲፭፤ማቴ ፪፰፡፩፰፤ማር ፲፮፡፲፬

፫ ሐዋርያውያን አበው

እነዚህ ደግሞ ሐዋርያትን ያዩ፣ ከሐዋርያት የተማሩ፣ አደራቸውን ተወጥተው ስማቸው "ሐዋርያውያን
አበው" እስኪባል ድረስ ሐዋርያትን መስለው እና አኽለው ወንጌልን ሰብከው ያለፉ ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ
ለልጁ ለጢሞቴዎስ የተናገረውን ቃል ተገንዝበው "ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን...
ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ" እንዳለ አስተውለው ደቀ መዛሙርትን ተክተው ሌሎችን
አደራ ብለው ወደ ጌታቸው የሄዱ ሲሆኑ ከሐዋርያት ቀጥሎ መምህሮቻችን ናቸው:: ፪ጢሞ ፪፡፪

፬ ሰማዕታት እና ሊቃውንት

ጌታችን "እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ


ስበኩ" ያለው ቃል የማይታበል በመሆኑ እንደ ሐዋርያትና እንደ ሐዋርያውያን አበው በብዙ መከራ በዘመነ
ሰማዕት ሰማዕታት፡ በዘመነ ሊቃውንት ሊቃውነት ወንጌልን ሰብከዋ። ሰማዕታት በደማቸው በሕይወታቸው
ወንጌልን በአሕዛብ ምድር ዘርተዋል። "የሰማዕታት ደም የቤተክርስቲያን ዘር ሆነ" እስኪባል ድረስ ለወንጌል
ሰርተዋል። ሊቃውንትም በልዩ ልዩ ዘመንና ወቅት አሕዛብ ካነደዱት እሳት፡ ከመዘዙት የሰይፍ ስለት፡
ከተራቡ አናብስት፡ ከጦር አንደበት የተረፈችውን ቤተ ክርስቲያን ሰይጣን በኑፋቄ ትምህርት ሊበርዝ
መናፍቃንን ሲያስነሣ መጽሐፍ አልበው፣ ኃይለ ቃሉን ጠቅሰው፣ ተከራክረው ረትተው፣ የቤተክርስቲያንን
እውነተኛ ትምህርት የጠበቁና ያስጠበቁ መጻሕፍትን የጻፉ፣ በስንዴ መካከል የተዘራውን እንክርዳድ ለይተው
ያሳዩ ሊቃውንት መምህሮቻችን ናቸው።

፭ መምህራን

ዛሬም ጉባኤ ቤት የዋሉ፣ ምሥጢር ያደላደሉ፣ በእኛ ቤተክርስቲያን ታሪክ በተነሡትና በታወቁት
ኃያላን የጠፋውን ፈልገው፣ የተቃጠለውን እንደገና ጽፈው እና አጽፈው፣ ለትምህርተ መለኮት መነሻ መድረሻ
የሆኑትን ቅዱሳት መጻሕፍት ከዓላውያን ነገሥታት ጠብቀው ያቆዩን፣ ቀለም በጥብጠው ብራና ፍቀው
ወንጌልን ጽፈው የሰጡን፣ መጻሕፍቱንም "ወኢነኃድጎ ዘእንበለ ትርጓሜ" "ያለ ትርጓሜ የምናልፈው ሊኖር
አይገባም" ብለው መጻሕፍቱን በረቀቀ የትርጓሜ ስልታቸው አራቅቀው አንብበው ተርጉመው ያስረከቡንና
አሁንም ለደቀ መዛሙርቶቻቸው በማስረከብ ላይ ያሉት ምሁራን አባቶቻችን እና መምህሮቻችን ናቸው::
የድጓው፣ የአቋቋሙ፣ የቅኔው፣ የቅዳሴው መምህራንን ሁሉ ያጠቃልላል:: በሌላ መንገድ በቲዎሎጂ ዕውቀት
በሰፊው የተማሩ በዘመናችን ተጠናክረው በሚታዩት የቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት ተቋማት ማወቅ
የሚገባቸውን ያህል ተገንዝበው የወጡ፡ ሊቃውንትም ምሁራነ ወንጌል ናቸው:: ከዚህ ውጪ ግን በግሌ
በራሴ ተገለጠልኝ ላስተምር የሚሉ ወንጌልን ከፖለቲካና ከሥጋ ሥራ ጋር የሚቀላቅሉ የወንጌልን ጉባኤ
“አባላ” የሚመቱ “ጥቅም” ሐዋርያ፣ ቅዱስ ያሰኛቸው ወንጌልን መብያ መዝረፊያ የሥጋ የሥራ መስክ
ያደረጉ፡ በዘመናችን እንደ አሸን የፈሉ ማኅበራትና ድርጅቶች ግን የቤተ ክርስቲያን ተማሪዎች እንጂ አስተማሪ
ሊሆኑ አይችሉም:: ወንጌሉም አልተሰጣቸውም። ለዚያም ነው መልእክታቸው ሁከትና ረብሻ
አገልግሎታቸውም ገንዘብ እንጂ ነፍስ የማያተርፍ የሆነው::

የቤተክርስቲያን የአስተምህሮ ምንጮች

፩ ቅዱሳት መጻሕፍት

በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን ውስጥ የተቆጠሩ ብሉይና ሐዲስ ተብለው የሚጠሩ በቀኖና
ተቆጥረው ተለይተው እስትንፋሰ እግዚአብሔር ቃለ እግዚአብሔር ትምህርተ እግዚአብሔር መሆናቸውን
ቅዱሳን አበው ሊቃውንት አረጋግጠው ቆጥረው ከመጻሕፍተ ኑፋቄ ለይተው የሰጡን መጻሕፍት
የአስምህሮአችን ምንጮች ናቸው:: መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ይከፈላል::ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን በመባል
እነዚህን የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ከሌሎች የመናፍቃን መጻሕፍት ለይቶ ለብቻቸው ለማሳየት
ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጥረት አድርጋለች:: ያልሠራችው ጉባኤ ያልከፈተችው መድረክ አልነበረም፤ ምክንያቱም
ግኖስቲኮችም ሆኑ ቢጽ ሐሳውያን እንዲሁም የዓለም ጠቢባን የቤተ ክርስቲያንን አስምህሮ ለመበረዝ የሰውን
ልጅም ከእውነተኛው ትምህርተ አምልኮ ለመለየት፡ በሐዋርያት ስም በአርድእት ስም በወንጌላዊያን ስም
የራሳቸውን ድርሰት "የቶማስ ወንጌል" "የማርቆስ ወንጌል" "የጴጥሮስ ወንጌል" ወዘይመስሎ እያሉ
ሰይመው አዳዲስ ነገር በኑፋቄ በርዘው ስላሰራጩ፡ እነዚያን የኑፋቄ መጻሕፍት ከእውነተኞቹ ቅዱሳት
መጻሕፍት በቀኖና ለይተው ሊቃውንት ለቤተ ክርሰቲያን አስረክበዋል:: ዛሬም ምንጩ እንዳይደፈርስ እንደ
ዓይን ብሌን ልንጠብቃቸው ይገባል:: ከእግዚአብሔር የተሰጡን የሕይወት መመሪያዎቻችን ናቸውና፤
እነዚህም የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው::

፪ መጻሕፍተ ሊቃውንት

ከዘመነ ሐዋርያት ቀጥሎ የተነሡ ሐዋርያውያን አበው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያትና ከአርድእት
ያገኙአቸውን መጻሕፍት ተርጉመዋል አብራርተዋል:: በሌላም በኩል በቅዱሳን ሐዋርያትና አርድእት ስም
የተጻፋትን የሐሰት ወንጌላት አጋልጠዋል:: እንዲሁም መጻሕፍት ቅዱሳትን አጣምመው እየተረጎሙ ሐሰትን
ኑፋቄን ክህደትን ያስተማሩትን የመንፈስን ሰይፍ ታጥቀው በእግዚአብሔር ቃል ተዋግተዋል:: በውስጥ
ይህንን የመሰለ ተጋድሎ ከማከናወናቸውም በተጨማሪ በውጭ ካሉት ዓላውያን ነገሥታት እሳቱን ስለቱን
ታግሰው የሕይወት የአካል ዋጋ ከፍለው ተጋድሎአቸውን አጠናቅቀዋል::

የውጭና የውስጥ ባላጋራ ያልበገራቸው ሐዋርያውያን አበውን መልእክት፣ ትምህርት፣ ትርጓሜ፣


መልስ የያዙት መጻሕፍተ ሊቃውንት ለዛሬው ትውልድም ሆነ ወደፊት ለሚነሳው ትውልድ እጅግ
አስፈላጊዎች ናቸው:: በመጻሕፍት ቤት በትርጓሜ ማዕከላት እነዚህ መጻሕፍት ዋጋቸው እጅግ የከበረ ነው::
ቤተ ክርሰቲያን ምሥራቅ እና ምዕራብ ተብላ በሥልጣን ጥመኞችና ቅን ሐሳብ በጎደላቸው መሪዎች ምክንያት
በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስክትከፈል ድረስ የተጻፉት መጻሕፍተ ሊቃውንት እውነተኞችና የቡድን
መልእክት ያላዘሉ በመሆናቸው በዓለም ሁሉ ባለች ቤተ ክርሰቲያን ዘንድ ተቀባይነታቸው እንደተጠበቀ
ነው:: መጽሐፍተ ሊቃውንት የሚባሉም በሃይማኖተ አበው የተጠቀሱት ሊቃውነት እነ ቅዱስ ቄርሎስ፣
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ባስልዮስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ወዘይመስለዎሙ
የጻፏቸው መጽሐፍት የተረጎሟቸው ትርጓሜያት ሲሆኑ በቤተ ክርሰቲያን "ሃይማኖተ አበው" ተብሎ
በሚጠራው መጽሐፍ “እስተጉቡዕ” (ስብስብ) ሆኖ የዋና ዋናዎቹ ሊቃውንት አስተምህሮ ተጠቅሷል:: በቤተ
ክርስቲያናችንም ሥርዓተ-ትምህርት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት በትርጓሜ ሊሰጡ የሚገባቸውን
መጻሕፍትን ለጉባኤ ቤት ሲመርጡ ብሉይ ኪዳንንና ሐዲስ ኪዳንን መደበኛ አድርገው ከአስተማሩ በኋላ
የሊቃውንቱንም መጻሕፍት በትርጓሜ ያስጠናሉ:: ከነዚህም የታወቁት የሊቃውንት መጻሕፍት "ሃይማኖተ
አበው" "ቄርሎስ" "ተረፈ ቄርሎስ" "ድርሳነ ዮሐንስ አፈወርቅ" "ቅዳሴያት" "ውዳሴ ማርያም" እንዲሁም
ሌሎች በጉባኤ ቤት ብሔራዊ በሆነው የትርጓሜ ስልት ተጠንተው ለትምህርት ለተግሣጽ ለቤተ ክርስቲያን
ዕድገት መልዕክት ሲተላለፍባቸው ኖሯል ይኖራልም:: የመጻሕፍተ ሊቃውንት የአስተምሮአቸው ዋና
ማዕከል "ምሥጢረ ሥላሴ" "ምሥጢረ ሥጋዌ" "ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን" እና ሌሎችም ዋና ዋና የሆኑ
አናቅጸ ሃይማኖት ናቸው::

፫. መጽሐፈ መነኮሳት

መጽሐፈ መነኮሳት ሦስት ክፍል ያለው የትምህርት እና የሕይወት መልዕክት መዝገብ የሆነ መጽሐፍ ሲሆን
ሦስቱም መጻሕፍት "ማርይስሐቅ" "አረጋዊ መንፈሳዊ" "ፊልክስዩስ" በሚል ስያሜ ይታወቃሉ:: እነዚህ
መጻሕፍት ከመጻሕፍተ ሊቃውንት ትንሽ ለየት ያለ ይዘት አላቸው:: መጻሕፍቱ የሰው ልጅ በሰይጣን
ተፈትኖ እንዳይወድቅ የሰይጣንን የፈተና ስልት በማሳየት እንዴት የመንፈስን ሰይፍ ታጥቀን ልንዋጋው
እንደሚገባ የሚያስተምሩ ሲሆን "ማር ይስሐቅ" የአበውን ትግላቸውን "ፊልክስዩስ" ታሪካቸውን "አረጋዊ
መንፈሳዊ" ደግሞ ክብራቸውን የሚያስተምሩ መጻሕፍት ናቸው:: መጻሕፍቱም የተጻፉት ከጨለማው ገዥ
ጋር ተዋግተው ድል በነሱ እውነተኞች አበው ትምህርት እና ትምህርት ላይ ተመሥርቶ ነው::

፬. መጻሕፍተ አምልኮ፣ የዜማና የቅዳሴ መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ ቅዳሴ፣ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት

እነዚህ ቤተ ክርስቲያን ለሥርዓተ አምልኮ የምትገለገልባቸው የአምልኮ መጻሕፍት ናቸው:: በውስጣቸውም


ጠቃሚ ጸሎትና የመጻሕፍት ትርጉም አላቸው:: "መጽሐፈ ቅዳሴያት" ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው
በጉባኤ ቤትም በትርጓሜ ደቀ መዛሙርት የሚያጠኑት ለሥርዓተ አምልኮውም በዜማ በቅዳሴ ቤት የሚጠኑ
ሲሆኑ የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት ደግሞ ራሱ ቅዱስ ያሬድ በቀየሰው የዜማ ስልት በሺህ የሚቆጠሩ
ሊቃውንት የተፈጠሩበት ዛሬም ብዙ ደቀ መዛሙርት የሚያጠኑት የሚማሩት የቤተ ክርሰቲያን ልዩ ጸጋ ልዩ
የትምህርት የአምልኮተ እግዚአብሔር የዜማ መጻሕፍት ናቸው:: ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው መጻሕፍት
ትውፊተ አበውን ጨምሮ ምንጫቸው መነሻቸው አባታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው:: ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ
አስተምህሮ የላቸውም:: ደረጃቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ በታች ነው:: ተጠሪነታቸውም ለመጽሐፍ ቅዱስ
ነው:: መጽሐፍ ቅዱስ ርእሰ መጻሕፍት መክብበ መጻሕፍት ነው::
የአስተምህሮ ስልቶች

፩. ትርጓሜ

ቤተ ክርሰቲያን የራሷ የሆነ የትርጓሜ ስልት አላት:: ዘሩን ሳይለቅ ቃሉን ሳያስተባብል ከተጻፈው ሳያጎል
ሳይጨምር የተሰወረውን የሚገልጥ የረቀቀውን የሚያጎላ ያልታወቀውን የሚያሳይ የተደበቀውን
የሚያመለክት የአመለካከት አድማስን የሚያሰፋ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ የትርጓሜ ስልት አላት:: በዚያ
የትርጓሜ ስልትም ከተራ ቁጥር ፩-፫ የጠቀስናቸውን መጻሕፍት ተርጉማለች:: ዛሬም ሊቃውንት በጉባኤ ቤት
ያንኑ ትርጓሜ እያስተማሩ ይገኛሉ:: በእርግጥ ትርጓሜው ለአሁኑ ትውልድ ዘወር ያለ በመሆኑ መሠረተ
ሐሳቡን ሳይለቅ እንደገና መተርጎም ይኖርበታል! ከዘመን ብዛት የተነሣ ለትርጓሜው ትርጓሜ እስኪያስፈልግ
ድረስ ሥራው ጥንታዊ ነውና::

የትርጓሜ ታሪክ:- ይህንን በተመለከተ "ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት" በሚል ርዕስ (ሊቀ ሥልጣናት ሃብተ
ማርያም ወርቅነህ አሁን አቡነ መልከ ጼዴቅ) ገጽ ፪፻፲፫ ላይ እንደተገለጠው ትርጓሜ በሀገራችን መቼ
እንደተጀመረ ወስኖ እርግኛ ሆኖ ለመናገር የሚያስችል መረጃ የለም:: ነገር ግን የመጻሕፍተ ኦሪት ትርጓሜ
በንግሥተ ሳባ በቀዳማዊ ምንይልክ ዘመን ከኦሪት ሊቃውንት ጋር እንደገባ በትውፊት መነገሩ እንደተጠበቀ
ሁኖ ትርጓሜ መጻሕፍት በኢትዮጵያ የተጀመረው በአክሱም ዘመነ መንግሥት መሆኑን የሚጠቁሙ
መረጃዎች አሉ:: ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የተለያዩ የሊቃውንት የትርጓሜ መጻሕፍት ወደ ሀገራችን ገብተው
ዛሬም በየገዳማቱ ግእዝ በግእዝ ተጽፈው ይገኛሉ:: ከውጭ የመጡት የተተረጎሙት ትርጓሜያትም
ለኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትርጓሜአቸውን እንዲያሰፉት እና እንዲያደላድሉት ረድተዋቸዋል::

የትርጓሜው ሥራ ሳያቋርጥ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ከቆየ በኋላ አካል
ገዝቶ መልክ አግኝቶ ለመታወቅ የቻለው በጎንደር ዘመነ መንግሥት ነው::
ትርጓሜ በጎንደር ዘመነ መንግሥት

በግራኝ መሐመድ ወረራ የተበዘበዘችው፣ ሊቃውንቶቿን ያጣችው፣ መጻሕፍቷ የተቃጠሉባት፣ ልጆቿ


የታረዱባት፣ እሳት በአካሏ ላይ የነደደባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቁስሏ የደረቀው፣
ውበቷ የተመለሰው፣ የተቃጠለው መጽሐፏ መልሶ ስለ አንድ ፈንታ ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ሆኖ የተጻፈው፣
ሁለተኛ በሊቃውንት ኃይል የጎለመሰችው፣ የፈረሰው መልሶ የተገነባው፣ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰበሰቡት
ሊቃውንት በጎንደር ዘመነ መንግሥት ባደረጉት ተጋድሎ እና በነገሥታቱ ትልቅ ጥረት ነው:: ይህን
በተመለከተ ጥንታዊ ትምህርት በኢትዮጵያ የሚለው የአቡነ መልከ ጼዴቅ መጽሐፍ "በጎንደር ዘመነ
መንግሥት ጊዜ ጥበባት ሁሉ መልክ እንዲያገኙ እንደተወሰነ የመጻሕፍትም ትርጓሜ መልክ አግኝቶ አደባባይ
ወጥቶ ብዙ ደቀ መዛሙርት አግኝቶ ይህን የአሁኑን ፍለጋ ይዞ ለመስፋፋት በቅቷል... ብዙ መምህራንም
ተነሥተዋል ብዙ ደቀ መዛሙርትም አውጥተዋል:: መመህራኑም ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ሀገር
ሊቃውንትም ይገኙበት እንደነበር የታወቀ ነው"2 ይላል:: በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ
ጸሐፊዎች ዘንድ እንደተገለጸው የጎንደር ዘመነ መንግሥት ወርቃማው የቤተክርስቲያን ዘመን ነበር::
ትርጓሜው፣ ዜማው፣ ሥርዓተ ማኅሌቱ መልክ የያዘው በዚያ ዘመን ነበርና:: ትርጓሜው ሁለት ክፍል አለው
እሱም ነጠላ እና ብዙ አወራረድ ያለው የአንድምታ ትርጓሜ ነው:: የአንድምታ ትርሜም በአራቱ ጉባዔያት
“ሐዲሳት”፤ “ብሉያት” “ሊቃውንት” እና “መነኮሳት” ተብሎ የተወሰነው በአጤ ኢያሱ አድያም ሰገድ ዘመነ-
መንግሥት ነበር።

፪. በርዕስ ማስተማር

በቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ ዋና ዋና የትምህርት ርዕሶች መርጦ በነዚያ ርዕሶች ላይ መጻሕፍትን
ጠቅሶ አስማምቶ የማስተማር ዘዴ ከጥንት ጀምሮ ነበር:: ለምሳሌ " አምስቱ አዕማደ ምሥጢር" በዚያ
መንገድ የተዘጋጀ ጥንታዊ የትምህርተ ሃይማኖት ማስተማሪያ መሆኑ የታወቀ ነው:: ከአምስቱ አዕማደ
ምሥጢር በተጨማሪ የሥነ ፍጥረት ትምህርት፣ አሠርቱ ቃላት፣ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በርዕስ ይሰጡ የነበሩ
ትምህርቶች ናቸው:: ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም በዚሁ ስልት የተዘጋጁ ናቸው::

2
ጥን ታዊ ሥርዓተ ትምህርት በሊቀ ሥልጣና ት ሃ ብተ ማርያ ም ወርቅነ ህ
፫. ዜማ

ቤተክርስቲያን በክፉ ዘመን መምህራኑም ሲያልቁ መከራውም ሲበዛ እምነቷን፣ ሥርዓቷን፣ ሰማያዊ ዋጋዋን፣
ክብሯን፣ አጠቃላይ አስተምህሮዋን በቅዱስ ያሬድ የዜማ ስልት አጥንታ በየዋሻው እየዘመረች መከራው
ሲያልፍላት ጠላት ዘወር ሲልላትም በከበሮና በመቋሚያ በጸናጽል እያደሰች እራሷን በዜማ ስታስተምር
ኖራለች ትኖራለች። የተመስጦ፣ የአምልኮ ሕይወት ባይኖራት ኑሮ እስከ ዛሬ መኖሯ ያጠራጥር ነበር:: ከሰላም
ዘመን በክፉ ዘመን ዜማ ትልቅ ሚና አለው። በዮዲት ጉዲት፣ በግራኝ፣ በድርቡሽ መከራ የበዛባት ዕረፍት
አጥታ የኖረች ቤተክርሰቲያን በዜማ (እንጉርጉሮ) ፈጣሪዋን ስታመሰግን ሃይማኖቷን ስታስብ፣ ስትማር፣
ስታስተምር ኖራለች:: የቅዱስ ያሬድም የዜማ መጻሕፍት መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ ትምህርተ
ሃይማኖትም የሥነ ምግባሩም ትምህርት ጸሎቱም በዜማው መጽሐፍ የተካተተ በመሆኑ ያሬዳዊት
የኢትዮጵያ ቤተ ክርሰቲያን በመዝሙሯ ስትማር ስታስተምር ኑራለች ትኖራለች::

፬. ቅኔ

ስያሜው:- ቃሉ የግዕዝ ነው:: በርባታ ስያሜውም ጥሬ ዘር ይባላል:: ትርጉሙ ቃል በቃል "መገዛት" ማለት
ነው:: ግብሩን በተመለከተ ከፈታነው ደግሞ ቅኔ ማለት "መገዥያ፣ ማምለኪያ፣ ማመስገኛ" ማለት ነው::
በአቀራረቡና በሌሎች አገሮች ካሉት ተመሳሳይ የግጥም ስልት ካላቸው ቅኔ መሰል ግጥሞች አንጻር ሲፈታ
ደግሞ ቅኔ ማለት በጠቅላላ አቀራረቡ ሲታይ "ግጥም" ማለት ነው:: በቅኔ ምስጋና፣ ክብር፣ ደስታ፣ ኀዘን፣
ተገፍዖ፣ ተዋርዶ እና ታሪክ በአጠቃላይ በዓለም የሚታይና የሚከናወን ሕይወታዊ ገጽታ በባለ ቅኔዎች
ይገለጽበታል::

ቅኔ ልዩ የሆነ የምሥጢር ጎዳና፡ የፍልስፍና፡ የትምህርት፡ የርቃቄ መነሻ፤ የአእምሮ ማጎልመሻ፡ ወደ


ሀገረ መጻሕፍት የሚያደርስ ምሕዋር፡ መገስገሻ፣ የጥበብ፡ የአእምሮ መንፈላሰሻ፡ ልዩ ሀብት ነው::
ኢትዮጵያዊ ቅኔ በመላው ዓለም ከሚገኙት የቅኔ የግጥም ባሕርያት የተለየ ባሕርይና ቅርጽ መልክ ያለው
የዕውቀት ጎዳና መሆኑን ነጩም ጥቁሩም ሊቅ ተስማምቶበታል:: ይህን በተመለከተ መላከ ብርሃን አድማሱ
ጀንበሬ የክቡር አቶ አለማየሁ ሞገስን “ሰዋሰወ ግእዝ” በመጥቀስ “ዝክረ ሊቃውንት” በተሰኘው
መጽሐፋቸው እንዲህ ነበር ያሉት “ቅኔ በሌላ ሀገር የማይገኝ ግእዝ ወልዶ ያሳደገው በሽምግልናው ለአማርኛ
ያስተዋወቀው... የሕሊና ስሜት፣ የአእምሮ ትፍሥሕት የድካም መድኃኒት፣ የኀዘን ማስረሻ፣ የፍልስፍና
ማጎልመሻ ሲሆን ከልዑል እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠ መድኃኒት ነው:: ልዩ ልዩ ልሳናትን
ስንማር ምንአልባት እርሱን የመሰለ ጥበብ እንዳለ ለማለት በተቻለን መጠን ይልቁንም የግሪክና የእንግሊዝኛ
ባለቅኔ የሚባሉትን የቅኔያችንን ጣዕም ጠልቆ ያልቀመሰ የሚያደንቀውን እና የሚያጋንነውን ግጥም ሁሉ
ብናነብ እንደ ኮረንቲ ሽቦ ተጣምሮ የሚሄደውን የቅኔያችንን ምሥጢር... አገኛለሁ ማለት ከመሬት ቁጭ ብሎ
በቀኝ እጅ ሰማይን ደግፎ በግራ እጅ ከዋክብትን መግፋት ሆነብን"3 ብለዋል። ሊቁ እንዳሉ የኢትዮዽያ ቅኔ
ከፈረንጆች "poem” ፍጹም ልዩ ነው:: አንድ የኢትዮዽያን ቅኔ ያጠኑ ሮማዊ ሊቀ ጳጳስ ስለ ቅኔያችን ሲናገሩ
"የኢትዮጵያ ቅኔ ካልተማሩት በቀር ስለ እርሱ መናገር ይከብዳል። ስለ ቅኔ ላልተማረው ሰው ማስረዳት
አይቻልም" ነበር ያሉት። እውነት ነው መንገዱ የዕውቀት መንገድ ነውና።

የቅኔ ደራሲ:- የቅኔ ጀማሪ ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ አበው ተስማምተዋል:: የቅዱስ ያሬድ በስድ ንባብም
በግጥምም መንገድ (መልክ) የተዘጋጁ በይዘታቸው "ጽድቅ" የሆኑ ቅኔያቱ በድርሰቶቹ መካከል እንደጌጥ
አልፎ አልፎ ይታያሉ:: ቅኔዎቹም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመጻሕፍት የተጠቀሱ፣ ከአሁኑ ቅኔ የተለየ
መልክ ያላቸው፣ የቅኔን ስያሜ ያስገኙ ቤት ያልመቱ ሰምና ወርቅ ወይንም ልዩ ልዩ የሆኑትን የቅኔ ጎዳናዎች
ያልተከተሉ ቅኔዎች ናቸው:: በታሪክ ጥንታዊ በአካሄድ ዘመናዊ የሆነውን ቅኔ ደራሲ በተመለከተ አንዳንዶች
"ዮሐንስ ገብላዊ" የሚባለው ሊቅ ነው የደረሰው ሲሉ ሌሎች ደግሞ "ደቀ እስጢፋ" ነው የደረሰው ይላሉ::
ያም ሆነ ይህ ቅኔ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው:: ሁለቱም ሰዎች በታሪክ እንደሚነገርላቸው ዕውቅ "የቅኔ" እና
"የአገባብ" ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ነበሩ::

የቅኔ መንገድ ፦ ቅኔ ልዩ ልዩ መንገዶች አሉት:: ሁሉንም ለመዘርዘር ቢያዳግትም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ "ሰምና
ወርቅ" "ሰም ገፊ" "ውስጠ ወይራ" "አገናኝ" "አታላይ" "ጽድቅ" "አንጻር" "ሙሻ ዘር" "ንጽጽር" "ኅብር"
"ጸጸት" "ሞይት" "ዝምዝም ወርቅ" "የወርቅ ተነጻጻሪ" "የወፍ እግር" "ስም ጥቅል" "ኃዳሪና ማኅደር"
"ሠረዝ" "ድርብ ሠረዝ" "ጉት" "ፍና ተሳልቆ" "ውስጠ ዘ" እና ሌሎችም ብዙ የቅኔ መንገዶች አሉ:: ታላቁ
የቤተክርስቲያን ሊቅ የቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ
"ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት" በሚለው መጽሐፋቸው አንድ መቶ አሥራ ሰባት የቅኔ መንገዶችን

3
መላ ከ ብርሃ ን አድማሱ በዝክረ ሊቃውን ት መጽሐቸፋው የ አለማየ ሁ ሞገ ስን መጽሐፍ በመጥቀስ የ ጻፉት
ከነቅኔያቸው ሌሎች ዘጠና አራት የቅኔ መንገዶችን በስማቸው ብቻ ጠቅሰው በአጠቃላይ የሁለት መቶ አሥራ
አንድ ቅኔ መንገዶችን ለትውልድ አስተዋውቀው ጽፈዋል:: ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት ገጽ ፻፹፪-፪፻፯
ይመልከቱ::

የቅኔ ዓይነቶች /ክፍሎች/

ጉባኤ ቃና ዕዝልና ግእዝ

ዘአምላኪየ

ሚበዝኁ

ዋዜማ

አጭር ዋዜማ

ሥላሴ

ዘይዕዜ

ሣህልከ

መወድስ (ፍታሕ ሊተ)

መወድስ (ኩልክሙ)

ሕንፄሃ

ግእዝ ክብር ይዕቲ

ዕዝል ክብር ይዕቲ

ዕጣነ ሞገር ግእዝ


ዕጣነ ሞገር ዕዝል ናቸው::

አዲስ ቅኔ፦ ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ታስቦ ወይም ተቆጥሮ ወይም ተዘርፎ ይቀርባል እንጂ ያደረ ቅኔ የደረቀ ቅኔ
ወይም ክልስ ቅኔ ወይም የተውሶ ቅኔ የለም። ቅኔ ሁልጊዜ አዲስ ከአንድ ጊዜ በላይ ተደግሞ ለምስጋና
የማይቀርብ ሁልጊዜ ትኩስ በሊቃውንት አእምሮ የሚመነጭና የሚፈልቅ የምስጋና ቃል ነው። ከላይ
እንዳልኩት ቅኔ አይደገምም አይከለስም አይሰለስም፣ ቅኔ ሁልጊዜ አዲስና ትኩስ ነው። ባለቅኔውም
በእግዚአብሔር ፊት አዲሱን ምሥጋናውን ከማቅረቡ በፊት ስለቅኔው ከጓደኛው ከመምህሩ ጋርም ቢሆን
አይወያይም ቅኔውንም ለማንም አይነግርም። ለእግዚአብሔር ቅኔው ከመቅረቡ በፊት የቅኔ ሰዎች ቅኔአቸውን
እንደሚደብቁ መናገሬ ነው እንጂ በደል ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶቹስ ደህና የቅኔ ሰው
አማክረው፣ አስተካክለው እንደ አቤል መስዋዕት የተዋበውን ቅኔ ያቀርባሉ።

በቅኔ ሃይማኖትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ተዘክሮተ ሞትን፣ ትምህርተ ሕይወትን፣


አዝማነ መንግሥተ ሰማያትን፣ ጸሎትን፣ ተመስጦን አባቶቻችን ሲያስተምሩ ኑረዋል:: ዛሬም አሉ
ያስተምራሉ:: በአጠቃላይ በቅኔ የፈለጉትን ማለት ይቻላል:: ሊቃውንት በቅኔ ብሶታቸውንም ይገልጹ ነበር::
ቅኔን ለምሥጋናም፣ ለዘለፋም፣ ለተግሣጽም፣ ለተምኔትም፣ ለአቤቱታም መግለጫ አድርጐ መጠቀም ይቻላል
ተችሏልም:: አሁን ለምሳሌ ያህል በቅኔ እንዴት አባቶቻችን ሲያስተምሩ ሲመክሩ ስለ ሃይማኖታቸውም
ሲከራከሩ ሐሳባቸውንም ሲገልጹ እንደኖሩ ከጥንት ቅኔዎችና በቅርቡ ከተደረጉት ቅኔያት አንዳንዶችን
ለምሳሌ ለአንባቢያን አቀርባለሁ::

ቅኔ አንድ:- ስለዚህ ዓለም ጥበብ ከንቱነት

መወድስ ዘዐቃቤ ስዓት ከብቴ

ምንት ውእቱ ፍድፋዴ ዚአሃ ለምክሐ ጠቢባን ጥበብ እስመ በጥበብ ወምክር::
ኢይጸአዱ ጸሊም ወኢይነውኅ ሐፂር

ወለአብድ ዘይጸንህዋ ፪ቱ አጽራር

ሞት ወመቃብር፣ ይጸንህዎ ከማሁ ለጠቢብ ወማእምር

ከመሰ ኢንሰጠም በዕመቀ ብሂል ባሕር

ተኅስር የዋሃት ወጥበብ ታከብር

እንዘ ርግብ የዋህ በዓለ አክናፍ ወእግር

የሐውር በእግር ጠቢብ አርዌ ምድር

ቅኔ ሁለት:- የሃይማኖት አቋም መግለጫ ሊሆን ይችላል።

ቅባት፣ ጸጋ እየተባባሉ ሊቃውንት በሃይማኖት በተለያዩበት ዘመን አንድ ባለቅኔ ቅባትን በመቃወም ያደረገው
አንጻራዊ ቅኔ::

ዋዜማ ቅኔ

መንበረ ኪሩባዌ እመ በቅባት ወረሰ ፍሬ ከርሥኪ ዕፁብ

ዘቤተ ድንጋሌ ማርያም ርግብ

እስመ ከማሁ ኩልነ ሱቱፋነ ቅብዐት ሕዝብ

እስፍንተ ይጸውር መንበሩ ለአብ

ወእስፍንተ ያገምር ኪሩብ


ትርጓሜ

የድንግልና ቤት ርግብ ማርያም ሆይ የማሕፀንሽ ፍሬ ክርስቶስ የኪሩቤልን ዙፋን በመንፈስ ቅዱስ


ቅባትነት ካገኘ ሁላችንም በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተናልና የአብ ዙፋን ስንቱን ይችላል ኪሩብስ ስንቱን
ይሸከማል ብሎ ነበር 4

ቅኔ ሦስት:- ስለ ሥነ-ምግባር ስለ ፍቅር ጠቃሚነት

ሥላሴ ቅኔ ዘመምህር አባ ዓለሙ በላይ ዘደሴ መድኃኔዓለም

ለሰብእ ይደልዎ ሐመረ ጳውሎስ ተፋቅሮ

ማዕዶተ ቀላይ ይግበር እንዘ ያስተጻንእ ኃይሎ

እስመ ሞት ማዕበለ ሥጋ ዘያስጥም ሀሎ

ወሐመረ ጳውሎስ ፍቅር ኢይትገፈታዕ በዐውሎ

እስመ በመልኅቅነ ተጋድሎ

ንሰወቅ ንሕነ ሰብአ ተሣህሎ

ወምስሌነ ዘናአዱ ኩሎ::

ቅኔ አራት:- የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ በቅኔ መግለጽ ይቻላል::

ቅኔ ዘመምህር ልዑለ ቃል አካሉ (ለልደት በ፲፱፻፺፪ ዓ.ም)

ዕጣነ ሞገር:-

ንጽሐ ጠባይዕ ኤልያስ ዘሕገ ተፈጥሮ አቀብከ

ወእም ኀበ ኤልዛቤል ሔዋን ተገፋዕከ

4
ታላ ቁ ሊቅ ብጹዕ አቡነ ጎ ርጎ ርዮስ ከጻፉት፣ የ ኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያ ን ታሪክ በገ ጽ ፻ ፷፬ ይመልከቱ)
ብላእ ወተሴሰይ ለቁመተ ሥጋ መናከ

አምጣነ ርኁቅ ፍኖትከ

ወኅዙነ ልብ ኤርምያስ ለመርስዔ ኀዘን ዘብከ

ንሣእ ጽዋዐ ሕይወት ዘተቀድሀ ለከ

አሰረ ነጋሲ:-

ልደተ ሥጋ ሕፃን ማሕየዊ ወዘሕሊና ሰብእ ማህረከ

በአማን ክቡር ወባዕለ ጸጋ አቡከ

ድኅረ ፍጻሜሁ ለልደትከ

በሐሊብ ጥዑም እስመ ሐፀነከ

ወመዓረ ረሰየ ምግበከ

ቅኔ አምስት:- መምህራን በቅኔአቸው ኀዘናቸውን ይገልጹ ነበር

የታወቁት ሊቅ የኔታ ገብረ ጊዮርጊስ ዓይናቸውን ታመው በ፲፱፻፵፯ ዓ.ም በእስቴ መካነ ኢየሱስ ሳሉ የዘረፉት
ቅኔ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ደቀ መዝሙራቸው ስለነበሩ በቃላቸው ይዘው ያጻፉኝን ቅኔ እንደምሳሌ
አቀርበዋለሁ::

መወድስ ቅኔ ዘየኔታ ገብረ ጊዮርጊስ

በመኑ አቀልል ክበደ ተገፎዖ ጽዋዐ ሕማም ወሞት ትህልፍ እምኔየ

አምጣነ ክህደኒ ሥልሰ ሐዋርያ ብርሃን ዓይንየ

ወሕፀተ ባሶር ሠረገላ መጽአ ከመ ይቅትለኒ ስናክሬም ደዌየ

ሠራዊተ ባቢሎን አመ ርእየ


እስመ ጸበበቶ ምድር ለኤርምያስ ሕሊናየ::

ለዓለም

ኃይልየሂ ወልደ እሴይ ለእመ ረስአ ወበልየ

ነግሠ በፈቃዱ አዶንያስ ሕማምየ

ወአመ ትትገፈታዕ ሥልሰ ኢየሩሳሌም ሥጋየ

ተንሥአ ለተሰዶ እንባቆም ልቡናየ::

በመግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ቅኔ በቅጥነተ ሕሊና በርቀት ባለቅኔውን አክሎ ለተመለከተው ሰው


ማራኪ የሚመስጥ ረቂቅ የጥበብ ጐዳና ሲሆን፡ ለሌላው ተርጉሞ ለማስረዳት ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ
ብዙ ሐተታ የሚያሻው በቅርብ የማይገኝ የምሥጢር ሩቅ ስለሆነ ለባለቅኔዎች እንጂ ለሌሎች በቀላሉ
የሚደረስበት አይደለም:: ባለቅኔዎች አባቶቻችን ቅኔ እያሰቡ የት እንዳሉ በተመስጦ ያሉበትን ይረሱ ነበር::
ቅኔ እያሰቡ በላያቸው ላይ ዝናብ ቢወርድ አይሰሙትም ሰውም በፊታቸው ቢያልፍ ዓይናቸው እያየ
አያዩትም ነበር:: ምክንያቱም በቅኔ ሐሳብ ይነጠቁ በምሥጢሩም ይጠልቁ ይራቀቁ ስለነበር ነው::

እውቁ ኦርቶዶክሳዊ ሊቅ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ስለዚሁ ነገር ሲጽፉ እንዲህ ነበር ያሉት:: "ቅኔ
ሕዋሳተ አፍዓን ሕዋሳተ ውስጥን ለሕሊና አስገዝቶ በተወሰነ ቁርጥ ሐሳብ የሚታሰብ ስለሆነ ቅኔ ተብሏል::
ይኸውም ሊታወቅ በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተነካ ሰው ቅኔ በሚያስብበት ጊዜ በፊቱ የሚደረገውን ነገር እያየ
አያይም፣ እየሰማ አይሰማም:: ከዚህም የተነሳ በጎንደሮች መንግሥት የቁስቋሙ አለቃ በእልፍኝ ውስጥ
ምንጣፍን አስነጥፎ መጻሕፍቱን በፊቱ ደርድሮ ለበዓለ ቁስቋም የሚቀኜውን ቅኔ ሲያወጣና ሲያወርድ ንጉሡ
ዘው ብለው ቢገቡ ልቡ ተመሥጦ ሊያያቸው ባለመቻሉ ቁጭ እንዳለ ቀረ:: ንጉሡም ነገሩ ደንቋቸው
ፍጻሜውን ለማየት እሱን አልፈው ከአልጋው ላይ ተቀምጠው ሁኔታውን ይመለከቱ ጀመር:: ብዙ ሰዓት
ካለፈ በላ አእምሮው ሲመለስ ንጉሡ ተቀምጠው ቢያይ ደንግጦ ተነሥቶ እጅ ነሣ:: ንጉሡም ምነው ምን
ሆነህ ነው ቢሉት ጃንሆይ ቁስቋምን ያህል ደብር አምነው ሹመውኛል ለበዓል የተሰበሰበው ሰው አለቃው
ምን ይናገር ይሆን እያለ ዓይን ዓይን ሲያይ ያልሆነ ነገር ቢሰማ ደብሩን አዋርዳለሁ ጃንሆይን አሳማለሁ እኔም
አፍራለሁ ብየ ቅኔ እቆጥር ነበር አለ ይባላል'' ብለዋል:: በመሆኑም ቅኔ ልዩ የጥበብ፣ የትምህርት፣ የተመሥጦ
ሀብት ስለሆነ ትውልዱ ሊያጠናው ያሉት አባቶች ሳሉ በስሙ ሊያውቀው በመልኩ ሊያየው በእጁ ሊዳስሰው
በዐይነ አእምሮው በፍጹም ልቡም ሊከተለውና ሊያጠናው የሚገባው ልዩ የኢትዮጵያውያን ሀብት ነው::

፭.ቅዳሴ

ቅዳሴያችን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ጸሎት፣ ምስጋና፣ ንስሐ፣ ሞተ ክርስቶስ፣ ትንሣኤ ክርስቶስ፣ የክርስቶስ
ዳግም ምጽአት የሚሰበክበት፤ የምሥጢረ ቍርባን ማክበሪያ የሃይማኖት መማሪያና መተግበሪያ ልዩ
የትምህርት ስልት ነው:: ሥርዓቱ አንድ እና ቋሚ ሆኖ ሁልጊዜ ሳይሰለች አምላካችንን የምናመልክበት
መንገድ ነው::

፮. ሕንፃ ቤተክርስቲያን

ሕንፃ ቤተክርስቲያን ሲሠራ አቀማመጡ፣ አከፋፈሉ፣ በሮቹ፣ አወቃቀሩ፣ ጉልላቱ፣ መስቀሉ፣ አጫዋቹ፣ የሰጎን
እንቁላሉ፣ ደጀ ሰላሙ፣ ቤተልሔሙ፣ ዐውደ ምሕረቱ፣ ምሥራቅ ምዕራቡ፣ ሰሜን ደቡቡ፣ እንዲያስተምር
ተደርጎ ነው የተተከለው።

፯. ሥዕል

ሥዕላት በቀድሞው ዘመን ሕዝቡ ሁሉ በማያነብበት በማይጽፍበት ዘመን በቤተ ክርስቲያኑ ግድግዳ ላይ
ዙሪያውን በልዩ ሥነ ሥዕል ተሥለው የክርስቶስን ነገር ከልደቱ እስከ ዕርገቱ፤ እስከ ዳግም ምጻቱ ወንጌልን
ሲሰብኩ፣ ሞተ ሰማዕታትን በማሳየት የቤተክርስቲያን ታሪክ ሲያስተምሩ፣ የመላእክትን ተራዳኢነት ሲያሳዩ፣
በአጠቃላይ መጠን ሰፊ ትምህርት ሲሰጡ ኖረዋል ይኖራሉ:: በመሆኑም ከአስተምህሮ ሥልቶቻችን
ጥንታውያኑና የተዋጣላቸው መምህራንም ማስተማሪያዎችም ናቸው:: ሰው ዝም ሲል እንኳ ሥዕል ዝም
አይልም:: ፈጣሪዋ ሰማይን ዘርግቶ ምድርን አጽንቶ በሥራው ያስተማራት ቤተክርስቲያን እሷም በሥዕል
ስታስተምር ኖራለች::

፰. የቃል ትምህርት

ከቤተ ክርስቲያናችን የአስተምህሮ ስልቶች አንዱ የቃል ትምህርት ነው:: በቤተክርስቲያን የሚያገለግሉ
ሊቃውንት ሕይወት እንደሚመሰክረው አባቶቻችን በሕፃንነታችን ሁሉን በቃላችን ስለሚያስጠኑን በቀላሉ
ስናድግ ትምህርተ ሃይማኖቱን፤ ሥርዓተ አምልኮውን፤ ለማከናወን እንድንችል አድርገዋል:: "በክፉ ዘመንም
ሊቃውንት መጻሕፍቱ ሁሉ ተቃጥለው ሊቃውንቱ ሁሉ ሙተው ያለቁ እንደሆነ ትውልዱ ባዶውን
እንዳይቀር ብለው ብሉዩን ሐዲሱን ንባቡንም ትርጓሜውንም በቃላቸው ይዘው የተገኙ አባቶች እንደነበሩ
ይታወቃል:: እኔ እንኳን በቅርቡ የማውቃቸው አንድ አባት መጻሕፍተ መነኮሳትን ንባቡን ከነትርጓሜው
በቃላቸው ይዘውት አይቻለሁ:: የጥናት ሰዎችም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን
የጥናት ስልት ብለው ዋጋ ሰጥተው፤ ግሩም የአስተምህሮ ስልት መሆኑን አረጋግጠዋል::

፱. ጸሎት

ጸሎት ከመንፈሳዊ ሕይወትነቱ በተጨማሪ የተማሩት እንዳይጠፋ፣ የያዙት እንዳይዘነጋ፣ የሚያደርግ


የአስተምህሮ ስልት ነው:: ብዙ አባቶች ዳዊቱን፣ ወንጌሉን፣ ቅዳሴውን፣ ኪዳኑን፣ ውዳሴውን የሚጸልዩት
በቃላቸው ነው:: ያም የሆነው ስለተማሩት ነው:: ጸሎቱም ቃለ እግዚአብሔር ስለሆነ ትምህርት ነው::

፲. ምዕላድ

ምዕላድ ማለት የተሰበሰበ ማለት ሲሆን እንደ አምስቱ አዕማደ ምሥጢር እንደ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ
ክርስቲያን ሁሉ በሊቃውንት ግዕዝ በግዕዝ ወይም በግዕዝና በአማርኛ በልዩ ልዩ ርእሶች ላይ የሚያተኩር ሆኖ
የሚዘጋጅ የሃይማኖት ማስተማሪያ ነው:: ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ የረቀቀው ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ
ሥጋዌ የተራቀቀባቸው ከጥንት ጀምሮ ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ ምዕላዶች መኖራቸው ይታወቃል:: ለምሳሌ
የነአቃቤ ሰዓት ከብቴ ምዕላድ፣ የነጌታ ትልቁ ኅሩይ ምዕላድ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ:: እነዚህንና ሌሎችንም
ምዕላዶች እንዳገኝ በቅደም ተከተል እናቀርባቸቃለን።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ ያጋጠሙ ፈተናዎች/ችግሮች

፩. ግብፃዊ ጳጳስ:- ቀደም ሲል እንዳየነው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ


ጳጳስ በዜግነቱ ኢትዮጵያዊ በዘሩ ግሪካዊ የነበረው አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድሪያ
ፓትርያርክ ተቀብቶ ተሹሞ መጥቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን በቅንነት ሲያገለግል ከኖረ በኃላ አረፈ:: ቤተ
ክርስቲያን ያለ እረኛ መኖር ስለሌለባት ሊቀጳጳስ መሾም አስፈላጊ ነበር:: ግብፃዊያን አባ ሰላማ በአትናቴዎስ
ተሹሞ እንደሄደ ሁሉ ለኢዮጵትያ ጳጳስ እኛ እየሾምን እየተሾምን መሄድ አለብን ብለው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክ
ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዕድገት መሰናክል የሆነ ሐሳብ አመንጭተው ያን ሐሳባቸውን የሠለስቱ ምዕት
ለማስመሰል በፍትሐ ነገሥት ውስጥ ሥርዋጽ አስገብተው "ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ወገን ጳጳስ አይሹሙ"
ብለው ጽፈው ያን በማሳየት ሠለስቱ ምዕት ወስነዋል እና እናንተ ልትሾሙ አይገባም ብለው ማስተማር
ጀመሩ::

በመሠረቱ አቡነ አትናቴዎስ የሾማቸው አባ ሰላማ የኢትዮጵያን ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ልማድ፣ ባሕል
የሕዝቡን የኑሮ ሂደት ጠንቅቀው ያወቁ በዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑ በቤተ መንግሥቱም ተቀባይነት
ያላቸው ከቤተ መንግሥት የተላኩ በመሆናቸው ከአንተ የተሻለ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ የሚችል
ሰው አላገኝም:: አንተ ስለሀገሯ ስለሕዝቧ ስለምታውቅ፣ የቋንቋም ችግር ስለሌለብህ፣ አንተን ነው የምሾምህ
ብሎ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ሰላማን ሹሞ ላከልን እንጂ፣ ሰላማ የተሾመው ኢትዮጵያውያን ጵጵስና ሊቀ
ጵጵስና የማይገባቸው ሆነው አይደለም አባ ሰላማም በቀለም ነጭ ስለሆኑ አልነበረም::

ግብፃዊያን ግን አንደኛ በሥልጣን ጦር ተወግተው ሁለተኛ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ


ቤተክርስቲያን ዕድገት ይልቅ ጳጳስ እየላኩ የሚሰጣቸውን የዕንቍ፣ የወርቅ፣ የብር የከበረ ማዕድን እጅ መንሻ
ሽተው ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ሕዝባቸውን ሊመሩ ሲገባ ቤተ ክርስቲያኒቱን ፩ሺህ ፮፻ ዓመት አስረዋት
ኖረዋል። ግብፃዊ ጳጳስ የኢትዮጵያን ቋንቋ አያውቅም ልዩ ሥልጠናም አልተሰጠውም በመሆኑም
በሊቃውንቱ መካከል ችግር ቢፈጠር እውነቱን ለመረዳት አይችልም ሁልጊዜ ከሁለተኛ ሰው ሰምቶ ነው
የሚፈርደው። ለምሳሌ አንድ ታሪክ ብጠቅስ አንድ ሰው ጳጳሱ ወደ ሚገኝበት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ቅስና
ሊቀበል ሄደ በእግሩ ወር ሁለት ወር ፈጅቶበት ስንቁን ጨርሶ ደክሞ ከታሰበው ቦታ ደረሰ ዲያቆኑ ቅስና
ከሚሰጥበት ቦታ ተገኝቶ ቅስና ለመቀበል ተመዝግቦና ፈተናውን ሁሉ አልፎ ሲዘጋጅ አቡነ ቀሲሱ (የጳጳሱ
ረዳት ቀሲስ) ሦስት ብር ክፈልና ነው የምትቀስሰው አለው:: ሦስት ብር የለኝም ከሩቅ አገር ነው የመጣሁት
ሁለት ብር ስላለኝ እርሱን ልስጥህና ጉዳየን ፈጽሜ ልሂድ አለው:: አይሆንም ብሎ (ባንዳው አቡነ ቀሲስ)
ከለከለው:: ለጳጳሱ አቤት ለማለት ቀርቦ በምን ቋንቋ ያስረዳው? ሁለት እጣቶችን እያሳየ "ሁለት ብር ብቻ
ነው ያለኝ ብሎ ጮኸ" ጳጳሱ መንገድ ላይ ነበርና ምንድን ነው የሚለው ብሎ ሲጠይቅ ባንዳው (አቡነ
ቀሲሱ) "ሁለት ሚስቶች አሉኝ ቅስና ይሰጠኝ" ነው የሚለው አለ:: በዚህ ጊዜ በመንገድ እየተንገላታ ቤተ
ክርስቲያኑን በሙሉ ሥልጣን ለማገልገል የመጣው ኢትዮጵያዊ ያለ ቅስና ተመለሰ:: (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
ሃ.አ.ዘቀ. ወዘ.ደኀ) ይህ በቋንቋ ችግር ምክንያት የነበረውን የተዘበራረቀ ሕይወት ያሳየናል:: በመሆኑም
የሕዝቡን ቋንቋ የማያውቅ፣ የበጎችን ድምጽ የማያውቅ እረኛ፣ በጎችም ድምፁን የማይለዩት (የማይሰሙት)
እረኛ በመሆን እሱም በጎቹን ሊሰማቸው በጎችም ድምፁን ሊሰሙት አልቻሉም ነበር። ዓይን እያለው ቤተ
ክርስቲያኑን የማያይ፣ ጆሮ እያለው ቤተ ክርስቲያኑን የማይሰማ ጳጳስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተምህሮ ዕድገት
ላይ ከባድ ፈተና ነበር::

ጳጳሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ጠባቂ እንደመሆኑ የየአንዳንዱን ሊቅ ሐሳብ ተረድቶ በሊቃውንቱ
መካከል ያለውን (የሚኖረውን) ክርክር ሊዳኝ ሊቃውንቱም በአንድነት እንዲሰሩ ሊያደርግ አልቻለም:: ጳጳሱ
ይሠራ የነበረው ለግብጽ መንግሥት እንጂ ለእግዚአብሔር መንግሥት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተክርስቲያን አልነበረም::

፪. የቤተክርስቲያን ያልሆኑ መጻሕፍት በቤተ ክርስቲያን ስም መወሳት ፦አንዳንድ መጻሕፍት ከዓርበኛ


ከግሪክኛ እየተተረጎሙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሳያዩአቸው ገብተው የሰውን መንፈሳዊ ሕይወት መበከል
ጀመሩ:: የቤተ ክርስቲያኒቱ እረኛ፤ ለመጻሕፍት ቅዱሳት ቀኖናዊነት ለመሥራት እና ሌሎችንም መጻሕፍት
ከቅዱሳት መጻሕፍት ለይቶ ለማሳየት የሚያስችል ጉባዔ ሊሰራ ሊያወያይም ባለመቻሉ የመተት፣ የነውር፣
የነቀፋ መጻሕፍት፤ ከላይ “በስመ አብ” ብለው የሚጀምሩ፤ ከውስጥ ግን መርዝ የተመሉ፤ መልእክታትን
የያዙ መጻሕፍት በበር ሳይሆን በመስኮት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ ሰይጣን ጥረት አድርጎ ነበር:: ለምሳሌ
በዚህ ዘመን በጋዜጣ ላይ እንደ ጸሎት መጻሕፍት ይቆጠር የነበረ አንድ ባለ ጠልሰም ጹሑፍ ሲጠና፣ በስመ
አብ ብሎ ጀምሮ ጠልሰሙ የዐረበኛ ሲሆን መልእክቱ ደግሞ ክርስቶስን ከመሐመድ የሚያሳንስ፣ መጽሐፍ
ቅዱስን የሚወቅስ፣ ቁርአንን የሚቀድስ ሆኖ ተገኝቷል:: ገና ነገ የሚገለጥ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነገር
በግብጻዊው እረኛ ዘመን ወደ ቤተክርስቲያን ገብቷል:: ይህን ለማስተካከል ሙሉ ሥልጣን ያለው ቅዱስ
ሲኖዶስ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል::

፫. የነገሥታቱ ጣልቃ ገብነት:- ጳጳሱ ኢትዮጵያዊ ባለመሆኑ ቤተ ክርሰቲያን የራሷን መንፈሳዊ አስተዳደር
ልታደራጅ አልቻለችም:: እንደ ጥገኛ ሆና ነው የኖረችው ነገሥታቱም ጳጳሱን በገንዘብ ገዝተው (ብዙ ገጸ
በረከት ከፍለው) ስለሚያስመጡት እንደፈለጉ ያዙታል:: እሱም ደንታ የለሽ ሆኖ ቤት ተዘግቶበት ይኖራል::
ነገሥታቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂዎች ሲሆኑ መኳንንቱና መሳፍንቱ የወንጌልን ሥራ ማስኬጃ
የራሳቸው መጠቀሚያ እያደረጉት፤ ካህናቱም እንጀራቸው ከሕዝባውያኑ እጅ በመሆኑ የማይገሥጹ፤
መስለው እንዲኖሩ የሚገደዱ ሆኑ:: ቀና ብለው እንዳያዩ እራሳቸው (ጳጳሱ) ጤነኛ አልነበረም እናም ያዋቂ
አላዋቂ ሆነው እያዘኑ ኖሩ::
፬. በሀገሪቱ በተደጋጋሚ የተፈጠረ ጦርነት :- የዮዲት ወረራ፣ የግራኝ አህመድ ወረራ እና ቃጠሎ የቤተ
ክርስቲያንን የአስተምህሮ መረጃዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን አቃጠለ፣ መምህራኑን አረደ፣ ቤተክርስቲያንን
አቃጠለ፣ ሕዝቡን ገደለ፣ የተረፈውን አሳደደ። ከዚህም በተጨማሪ በካቶሊኮችም ምክንያት በሊቃውንቱ
መካከል የተፈጠረው ውዝግብ እና በነሱስንዮስ ዘመን የነበረው ውሽንፍርም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ
መዳከም ይልቁንም ለሊቃውንቱ ፍቅር ማጣት፣ ለስሕተት ትምህርት በር ከፋች በመሆን የቀናውን
የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ተዋግቷል:: ከዚህ ላይ ጠቅሼ በቀላሉ የማልጨርሳቸው ፈተናዎች የቤተ
ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ ተፈታትነውታል::

የቤተ ክርስቲያኒቱ የወንጌል መድረክ ለምን በአብነት የትርጓሜ ትምህርት ቤቶች ብቻ ተወሰነ

፩. በውጭና በውስጥ በተነሡ ጠላቶች ምክንያት

፩.፩ በሀገራችን በጉባኤ ሕዝብ ሰብስቦ ማስተማር መቼ እንደቆመ አይታወቅም:: ምናልባት ከዮዲት ወረራ
በኋላ ሊሆን ይችላል:: ሊቃውንቱም ያተኮሩት ወደ ቅዱስ ያሬድ ዜማ ነበር:: እርሱም ከዚህ በፊት
እንደተመለከትነው ለቤተ ክርስቲያኒቱ በክፉ ዘመን መጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድረጓል:: በጎላ በተረዳ
የታወቀውን ዘመን ከጠቀስን ግን ከአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በኋላ በሊቃውንቱ መካከልም የአስተሳሰብ
ልዩነት "ጸጋ" "ቅባት" "ካራ" በሚል መሰዳደብ እየዳበረ ስለመጣ ሚስዮናውያንም ከፋፋይ አስተምህሮ
እንዲኖር ጥረት ስላደረጉ እና የሊቃውንቱን አእምሮ ለመበረዝ እርስ በርሳቸው እንዲነቃቀፉ ስላደረጉ ሁሉም
ምሥጢር የመሰለውን በልቡ ይዞ መቀመጥ ግድ ሆነበት። አንዱም ከእርሱ የተለየ አመለካከት እንዳለው
የሚገምተውን ሊቅ የስድብ ስም ስለሚሰጠው በቅንነት መወያየት፣ መተማመን፣ መደማመጥ እየጠፋ
በመምጣቱ ሁሉም ያገኘውን ደቀ መዝሙር ቤቱን ዘግቶ ማስተማርን መረጠ::

፩.፪ ግብፃዊው ጳጳስ ከብዙኃኑ ጋራ በቋንቋ ስለማይግባባ ቤቱን ዘግቶ መዋሉ እንደ ቅድስና እና ብህትውና
ስለታየለት ወጥቶ ከማስተማር ይልቅ ቤት ውስጥ ተዘግቶ መዋል እንደ አቡኑ “ቅዱስ” የሚያሰኝ መስሎ
ስለታየ አስተምሮ ከመነቀፍ ቤትን ዘግቶ “ቅዱስ” መባል የተሻለ መስሎ በመታየቱ ብዙዎቹ የያዙትን ይዘው
ተቀመጡ። ይህ ሁኔታ ግን ሁሉንም አይወክልም።

፩.፫ ያልተማሩት የተማሩትን ወደ ነገሥታቱ እንዳይቀርቡ አስቀድመው መምህር እገሌ አለቃ እገሌ "ጸጋ"
ነው "ካራ" ነው "ቅባት" ነው እያሉ ስም በማጥፋት እነሱ የሊቃውንቱን ቦታና መድረክ ሳይማሩ መቆጣጠር
ስለቻሉ ሊቃውንቱ በቀደሙት ነገሥታት ፊት ስማቸው ከጠፋ፣ አንድ ነገር ተናገረ ከተባለ ነገሥታቱ "ከፍ
ብለው አንገት ዝቅ ብለው ባት" በሰይፍ የሚቀጡ (የሚቆርጡ) ስለሆኑ፣ በሥጋት ምክንያት ሁሉም ሊቅ
አስተምህሮውን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በቤቱ ብቻ እያራቀቀ በደናቁርቱ እየሳቀ፣ በነገረ ሠሪዎቹ እየተሳቀቀ
መኖር ግድ ሆነበት::

፩.፬ ዛሬም ቢሆን የተማረውን የሰው ኃይል በሚገባ የመጠቀም፤ የተማረን የመስማት፤ ለተማረው ተገቢውን
ሥልጣንና ቦታ የሥራ ድልድል የመስጠት ችግር ያለባቸው አገሮች ይጠቀሱ ቢባል በተራ ቁጥር አንድ
ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚጠቆሙ ይመስለኛል:: በሕዝባችን አስተሳሰብ የዳበረው
መጥፎ ባሕርይ የአንድ ሰው መማር፣ ማወቅ፣ ማግኘት መክበር የሀገር በረከት መሆኑን፤ ያ ሰው ብቻውን
ለምንም ሊጠቀምበት ሀብቱን ዕውቀቱን እንደማይችል፣ የተማረው ሀገር ሊያገለግል፣ ያገኘው የከበረው
ከወገኑ ጋራ ሊጠቀምበት፣ ዕውቀቱንም ሆነ ሀብቱን ለሀገር ጥቅም ሊያውለው (ኢንቨስት ሊያደርግ) መሆኑን
አንገነዘብም:: የተማረውን ማሳደድ፣ ተገቢ ቦታ መንሣት፣ እንደ ባላንጋራ ማየት፣ መቅናት፣ መመቅኘት
የባሕርያችን ሊመስል ምንም አልቀረውም:: እንደ ኢትዮጵያውያን ያለ የተባረከ አእምሮ ያለው በተሰማራበት
ግብ ሳይመታ የማይመለስ ጎበዝ ሕዝብ አልነበረም:: ነገር ግን ተባብሮ መሥራት የወንድምን የእኅትን
ተስጥኦ፣ ጸጋ፣ ዕውቀት፣ ሀብት፣ የሀገር ዕውቀት ሀብት ጸጋ አድርጎ ማሰብ ግን አልተሰጠውም:: በዚህ
ምክንያት ቤተክርስቲያንም በሊቃውንቶቿ ለመመራት የሚነግሯትንም ለመስማት እንዳትችል በዕውቀታቸው
በጸጋቸው እንዳትጠቀም የመንግሥት ግብረ በላዎች፣ አድር ባዮች ሊቃውንቱን ሲያሳድዱ፣ ስም ሲያጠፉ፣
ሲያስገድሉ ኖረዋል:: ዛሬም ያ ክፉ ባሕርይ ቀጥሎ የቤተ ክርስቲያኒቱን መድረክም ሆነ የትምህርት ዕድል
ነፍስ እያጠፉ ገንዘብ የሚያተርፉ ግለሰቦች በማኅበር ተደራጅተው ሲያማስኑት ይታያሉ::

ነገሥታት ሊቃውንቱ እንዲያስተምሩ መመሪያ የሰጡበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ብንጠቅስ፦ አፄ ቴዎድሮስ:-


ወንጌል እንዲስፋፋ ቤተ ክርስቲያን እንድትጠነክር በደቡብ በምሥራቅ በምዕራብ ኢትዮጵያ ወንጌልን ካህናቱ
ወጥተው እንዲሰብኩ መመሪያ ሰጥተው ነበር:: ነገር ግን የመድረኩ ትምህርት ከተቋረጠ ብዙ ጊዜ ስለሆነው
ካህናቱ በከተማ ተቀምጠው የጣመ የላመ እየተመገቡ በከተማ መቀመጥን ስለመረጡ በንጉሡ ላይ የስም
ማጥፋት ዘመቻ ስላደረጉባቸው፤ ንጉሡ በግዛቴ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ እግዚአብሔርን የማያውቅ
በክርስቶስ ሳያምን የሚሞት፤ እንዳይኖር ሁሉም ለዘለዓለማዊ ሕይወት እንዲበቃ፣ የጠላት መሣሪያ የሚሆን
እንዳይኖር ሂዳችሁ ካልሰበካችሁ በማለትና በሌሎችም ጠንካራ መመሪያዎቻቸው ምክንያት ከካህናት ጋራ
በመጣላት ካህናቱን እስከ መቅጣት የደረሱበት ጊዜ እንደነበር የታሪክ ሰው ሁሉ ያውቀዋል::
፪. ያልተማሩ ሰዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን መድረክ

መቆጣጠር

ሊቃውንቱ በስም አጥፊዎች ምክንያት ከቤት ሲውሉ ሕልም አለምን ራዕይ አየን በሚሉ
ከእውነተኞች የባህታዊያን ሕይወት የተለየ፤ አስመሳይ ሕይወት ባላቸው "ጉባኤ ቤት ባልዋሉ ምሥጢር
ባላደላደሉ" ሲፈልጋቸው እሳት ከሰማይ ይወርዳል፣ ምድርም በውኃ ይሰጥማል የሚሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን
ትምህርተ ሃይማኖት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያልተማሩ ሰዎች በግላቸው ተነሥተው ተከታይ በማግኘት የቤተ
ክርስቲያኒቱን መድረክ ያዙት:: የተማሩትም “እንደልቡ ሐዋርያ” የሆነውን ሰው ትምህርት በደቀ
መዛሙርቶቻው በኩል እየሰሙ በመገረም በዝምታ ያሳልፉት ጀመር:: ጳጳሱም ግብጻዊ ነው:: ሊቃውንቱም
እርስ በርስ መስማማት እንዳይችሉ ጥቃቅኑን ነገር አክብደው እንዲያዩት ጠላት በመካከላቸው ጥልን
ዘርቶባቸዋል:: ይህንን ሁሉ ተቋቁመው ለማስተማር በሚሞክሩበትም ጊዜ “የእነ እንደልቡ ሐዋርያ”
ትምህርት እና የሊቃውንቱ ትምህርት ስለማይመሳሰል ሕዝቡ ብዙውን ጊዜ የሰማውን የእነ “እንደልቡ
ሐዋርያን” ትምህርት ሲቀበል የሊቃውንቱን ለመቀበል ጊዜ የሚወስድበት ወይንም ሊቃውንቱ
ትምህርታቸው ልክ አይደለም የእነርሱ ትምህርት ከባድ ነው ኑፋቄ ነው "የጸጋ" "የቅባት" "የካራ" ነው
እየተባለ ይጥላላ ጀመር::

በመሆኑም እስካሁን ሕዝባችን ከሲኖዶስ ድምጽ፣ ከሊቃውንቱ ትምህርት፣ ከሲኖዶሱ ውሳኔ ይልቅ አክብሮ
የመቀበልና የመስማት ባሕርይው የሚያመዝነው፤ የሊቃውንቱን ስም የሚያጠፉትንና የሲኖዶስ ውሳኔ
የሚቃወሙትን፤ ጳጳሳቱን ሊቃነ ጳጳሳቱን የሚከፋፍሉትን “የእነ እንደልቡ ሐዋርያትን” ድምጽ ነው:: አሁን
አሁንማ ሲኖዶሱንም ሊቃውንቱንም “የእነ እንደልቡ ሐዋርያት ትምህርት” ጫና ሊፈጥርበት ሙከራ
እያደረገ ነው:: ሕዝቡ ካልተቀበለን ምን ልናደርግ እንችላለን በሚል እንደ ወቅቱ እንደ ሰዉ ፍላጎት
በመራመድ በድፍረት ማስተማርን እንደ ሰይፍ እየፈሩት ነው:: ያሳዝናል::

www.kidusyared.org
ዛሬ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዛሬ ከትናንት ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል? አንድ አንድ የቀደመው


ደካማ ባሕርይ ዛሬ ቢታይም ነገር ግን ትልቅ ለውጥ ይታያል:: ይልቁንም በአስተዳደር ራስን በመቻል በኩል
ዕድገቱም ከፍተኛ ነው::

፩. ቤተ ክርስቲያን ከልጆቿ መካከል ሊቃነ ጳጳሳትን ለመሾም በቅታለች:: በመሆኑም መጻሕፍትን ሊመረምሩ
የሚታረመውን ሊያርሙ፣ የሚሻሻለውን ሊያሻሽሉ፣ የተረሳው እንዲታወስ የጠፋው እንዲፈለግ እና እንዲገኝ
ሊያደርጉ ሙሉ ሥልጣን አላቸው::

፪. የራሷ የሆነ የተጠናከረ አስተዳዳራዊ መዋቅር ዘርግታለች:: በመሆኑም ችግሮች ለመፍትሔ የመቅረብ
ዕድል አግኝተዋል:: ምንም መፈራራት የበዛበት የቀድሞው የክፍፍል እርሾ ቅሪት የሚታይበት ቢሆንም
ቢያንስ ሊቃውንቱ ቋንቋቸውን በሚሰሟቸውና ሐሣባቸውን በሚረዷቸው አባቶቻቸው ፊት አቤት ለማለት
በቅተዋል::

፫. መምህራን በመድረክ ላይ ማስተማር ጀምረዋል:- በጣም ደስ የሚለው ሌላው ነገር፤ በቅዱስ ሲኖዶስ
መመሪያ የሚሄዱ፤ በማዕከላዊ አሠራር የሚያምኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ ያጠኑ፣ ጉባኤ ቤት የዋሉ፣
ምሥጢር ያደላደሉ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት ተቋማት የሠለጠኑ ሰባክያነ ወንጌል መምህራነ ወንጌል
በመድረክ ቁመው ወንጌል መስበኩን በተጠናከረ መልኩ ይዘውታል:: ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ሰፍቶ
ሕዝብ በዝቶ የሕይወትን ቃል ሲማር እያየን እየሰማን ነው::

አሁንም ቢሆን ታዲያ በመምህራኑና በአንድ አንድ በግላቸው ማስተማር በጀመሩ እንዲሁም ጥቅም ሐዋርያ
ባሰኛቸው በማኅበር ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያንን ሳያውቋትና ሳይገነዘቧት አስተምህሮዋንም ሳያስተውሉ
ቋንቋዋንም ሳይረዱላት፣ በኃይልና በስሜት ራሳቸውን መምህራን ካሰኙ አስመሳይ ሰዎች ጋራ የአስተሳሰብ
የትምህርት አቀራረብ የብስለት ልዩነት መኖሩ ግልጽ ነው:: በመሆኑም “የጎበዝ አለቃ ሰባኪዎች” መምህራኑ
ያስተማሩትን በቀላሉ ካልገባቸውና መምህራኑም “የግልገል ፈሪሳውያኑን” አስተሳሰብ ወደ ግራ ትተው
በዚያው ገፍተው ካስተማሩ ቦታ የሚያጡ ስለመሰላቸው የአባቶቻቸውን ጨዋታ ደግመው ለመጫወት ስም
ማጥፋትን ያዘወትራሉ::
፬. ቅዱስ ሲኖዶስ በቀኖና መጻሕፍቱን ለመጠበቅ ሊቃውንቱን እያወያየ የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና
ሥርዓት እንዲያስጠብቅ፤ አስተምህሮዋን እንዲያልቅ እንዲያራቀቅ ለማድረግ ዕድሉም ሥልጣኑም
ውሳኔውም ምርጫውም በእጁ ሆኗል::

፭. ዛሬ ለኢትዮጵያ ቤ/ክ አስተምህሮ እና አስተዳደር ፈተና የሚሆነው እና የሆነው ለትለቁ የቤተ ክርስቲያን
አገልግሎት የሚሾሙት ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ ይልቁንም ጳጳሳት መንፈሳዊነት እና የዕውቀት መመዘኛ
ማሽቆልቆል ነው። ጳጳሷ መንፈሳዊ እና በዕውቀት ያልበሰለ ከሆነ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮዋም ሆነ በበጎ
ምሳሌነቷ ወደፊት መራምድ አይሆንላትም። ስለዚህ በሥልጣነ ክህነት አሰጣጥ መመዘኛ ላይ ሊታሰበብት
ይገባል።

መጋቤ ሐዲስ መምህር ልዑለቃል አካሉ ዓለሙ

www.kidusyared.org

You might also like