You are on page 1of 52

አይበገሬው ጀግና ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ!

ጊዜው ጥር 28 ቀን 1933 ዓ.ም. ነው። የበጌምድር አርበኞች ብቻ ሳይሆኑ ወንድ የተባለው ሁሉ


አርበኞቹን ተከትሎ ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ዘምቷል።
በደብረታቦር አውራጃ፣ ፋርጣ ወረዳ፣ በክምር ድንጋይ ምክትል ወረዳ፣ መገንዲ ጊዮርጊስ ደብር፣
ጋይድባ በተባለች መንደር አንዲት እናት ምጥ ተይዘዋል። ወይዘሮ ዘውዲቱ ተሰማ ይባላሉ። አርበኛው
ባለቤታቸው ፊታውራሪ መለሰ ከተማ ቀርቶ ከብቶቹን እንኳን ከበረት የሚያወጣ ወንድ ባልነበረበት
ሰዓት ነው ምጥ የተያዙት። ወንድ ልጅ በወለዱ በሦስት ዓመቱ በሞት ያጡትና በሐዘን የተኮማተሩት
ወይዘሮ ዘውዲቱ “ምነው አምላኬ የወሰድክብኝን ልጄን ብትመልስልኝና ብትክሰኝ” እያሉ
ከምጣቸው ጋር አብረው ይማፀናሉ። ተማፅኖአቸው ከንቱ አልቀረም፤ ወንድ ልጅ በሌለበት ሠፈር
ወንድ ልጅ ወለዱ። እልል አሥር ተባለ። ወይዘሮ ዘውዲቱም የእግዚአብሔርን ቸርነት በማየት
የልጃቸውን ስም ማንተፋርዶ መለሰ አሉት። ከዚህ በፊት የሞተባቸውን መስፍን መለሰ የተባለ ወንድ
ልጃቸውን ከጌታ ጋር ማን ተፋርዶ (ማን ተሟግቶ) መለሰልኝ ማለታቸው ነበር።
ፊታውራሪ መለሰም ከዘመቻው በድል ሲመለሱ ወንድ ልጅ ተወልዶ ስላገኙ ደስታቸው ከመጠን ያለፈ
ነበር። ህፃኑ ማንተፋርዶ ለቤተሰቡ ብርቅ ልጅ በመሆኑ ዘመድ አዝማዱ ሁሉ ብዙ ስም ነበር
ያወጣለት። አያቱ እማሆይ አዱኛ አገኝ ሲሉት፣ አንድ አክስቱ ደግሞ ቢክስ ብለው ጠሩት። ፈንታነሽ
እምሩ የተባሉ ሌላ አክስቱ ደግሞ አንድነህ አሉት። አባቱና የክርስትና አባቱ ግን የክርስትና ስሙን
በመውሰድ ኃይለ - እንድርያቆስ አሉት። ኅፃኑ ማንተፋርዶ በአጠቃላይ ከዘመድ አዝማዱ 14 ስሞች
ወጥተውለት ነበር። ሆኖም ግን የአባትና የክርስትና አባት ስም እየጎላ መጥቶ ማንተፋርዶ እየቀነሰ
ኃይለ - እንድርያቆስ እየገነነ መጣ። ይህም በጊዜ ሂደት እንድርያቆስን ገድፎ ኃይሌ እየተባለ መጠራት
ጀመረ። የያኔው ህፃን ኃይሌ መለሰ፣ የዛሬው ብርጋዴር ጀኔራል ኃይሌ መለሰ አጭር የሕይዎት ታሪክ
በዚህ መልኩ ይጀምራል።
ፊታውራሪ መለሰ ከተማ የወላጅ አባታቸው ስም ከተማ ሳይሆን ወረታ ነበር። የእናታቸውን የእማሆይ
አዱኛ ከተማን አባት ስም ወርሰው ነው መለሰ ከተማ የሚባሉት። አባታቸው ወረታ ኃይሉ ከጋይንት
(ስማዳ) ለሥራ ጉዳይ ወደ ደብረታቦር/ፋርጣ አውራጃ መጥተው ነው አዱኛ ከተማን በማግባት መለሰን
የወለዱት።
ፊታውራሪ መለሰ በአካባቢው በጣም የታወቁ አርበኛና አንደበተ - ርቱዕ የአደባባይ ሰው ነበሩ።
ፊታውራሪ መለሰም ሆኑ ወይዘሮ ዘውዲቱ ተሰማ የመጀመሪያ ባልና ሚስት አልነበሩም። ሁለቱም
የመጀመሪያ ትዳራቸውን ከፈቱ በኋላ ነበር የተጋቡት። ወይዘሮ ዘውዲቱ ከመጀመሪያ ትዳራቸው
አንለይ ተሰማ የተባለ ወንድ ልጅ ነበራቸው። የሁለቱ የጋራ የመጀመሪያ ልጃቸው ብዙዬ መለሰ
ስትሆን፣ ከእርሷ ቀጥሎ የተወለደው መስፍን መለሰ ነበር። ግን ወዲያው በህፃንነቱ አልፏል። ጄኔራል
ኃይሌ የወይዘሮ ዘውዲቱና የፊታውራሪ መለሰ ሦስተኛ ልጅ ናቸው። ከጄኒራል ኃይሌ ቀጥለው
የተወለዱት ወይዘሮ ጠየቁ እና ዘመቱ መለሰ ናቸው። ፊታውራሪ መለሰና ወይዘሮ ዘውዲቱ ለተወሰነ
ጊዜ ተለያይተው ስለነበር ፊታውራሪ መለሰ ከሌላ ሴት ወይዘሮ ጦቢያ፣ ሙሉጌታና ብርቄ መለሰ
የተባሉ ልጆች ወልደዋል። ሆኖም ግን ተመልሰው ታርቀው እስከ ዕለተ ሞታቸው አብረው ኖረዋል።
ህፃኑ ኃይሌ የተወለደው ታላቅ ወንድሙ መስፍን ከሞተ በኋላ በመሆኑ እናትና አባቱ በስስት
የሚመለከቱት ህፃን ነበር። በመሆኑም ምንም እንኳን ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት መድገም በአካባቢው
ካሉ መምህር ቢማርም ከዓይናቸው ርቆ በመሄድ ዘመናዊ ትምህርት እንዲማር ደብረታቦር ሊልኩት
ግን አልደፈሩም። ምክንያቱም ኃይሌንም ልክ እንደመስፍን የሚያጡት ስለመሰላቸው ከአጠገባቸው
እንዲርቅ አልፈለጉም። በጊዜ ሂደት ግን የኃይሌን ልብ የሚያሸፍት አንድ ክስተት ቤተሰቡ ውስጥ
ተፈጠረ። ከፊታውራሪ መለሰ ቤት ሆኖ ከኃይሌ ጋር ቄስ ትምህርት ቤት አብሮ ይማር የነበረው

1
የፊታውራሪ መለሰ የቅርብ ቤተሰብ የሆነው መልኬ መንግሥቴ ደብረታቦር ዘመናዊ ትምህርት ቤት
ገባ። ታናሼ መልኬ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሲገባ እኔ ለምን አልገባም እያለ ቅሬታውን ደጋግሞ
በማሰማቱ ምንም እንኳን ብርቅየ ልጃቸው ከዓይናቸው በመራቁ ሥጋት ውስጥ ቢገቡም፣ እንዲከፋው
ደግሞ ስላልፈለጉ ፈቀዱለትና ደብረታቦር ከሚገኘው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት
ቤት ገባ።
ወጣቱ ኃይሌ ስድስተኛ ክፍል ላይ እያለ አባቱ ፊታውራሪ መለሰ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የኃይሌ
ትምህርት አደጋ ላይ ወደቀ፤ ማቋረጥ ተገደደ። ምክንያቱም በቆላ በደጋው ያለውን እርስትና ቤተሰቡን
የማስተዳደሩ ሃላፊነት ከኃይሌ በስተቀር ከማንም ትከሻ ላይ የሚወድቅ አልነበረምና። የዚያን ዘመን
የአካባቢው የመሬት ሥሪት ደግሞ የርስት ይዞታ በመሆኑ አንደበተ ርቱዕና ተሟጋቹ ፊታውራሪ መለሰ
አስከብረውት የነበረውን እርስት ሁሉ የእርሳቸውን መሞት አይቶ 7 ትውልድ እየቆጠረ “እወለዳለሁ”
የሚለው ሁሉ ሊቧጨቀው ተነሳ። የአባትን እርስት አሳልፎ መስጠት እንደጥቃት የቆጠረው ወጣቱ
ኃይሌ ከአባትና እናቱ ጋር ተሟግቶ የጀመረውንና የሚወደውን ትምህርት አቋርጦ የመጣውን ጥቃት
ለመቋቋምና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ወሰነ። ለትምህርቱ መቋረጥ ሌላው ገፊ ምክንያት ደግሞ አባቱ
በአርበኝነታቸው ተሰጥቷቸው የነበረው የነጭ ለባሽነት ሹመት መና ሊቀር መሆኑ ነው። በወቅቱ
የአርበኛ ልጆች አባቶቻቸው በሞት ሲያልፉ የአባቶቻቸውን ሹመት የመውረስ መብት ስለነበር ወጣቱ
ኃይሌም የአባቴ ሹመት ይገባኛል አለ።
በመሆኑም አባቱ ፊታውራሪ መለሰ በአርበኝነታቸው ይዘውት የነበረውን የነጭ ለባሽ ሻምበልነት
ማዕረግ “በአርበኛ ልጅነቴ የአባቴን ሹመት የማግኘት መብት አለኝና ይሰጠኝ” ብሎ በመጠየቅ
የነጭ ለባሽ ሻምበል ሆነ። (በወቅቱ የነጭ ለባሽ ሻምበል ሥራ ፀጥታ ማስከበር እና ሕዝቡ
ለመንግሥት አሥራት እንዲከፍል ማድረግ ነበር)። ተወላጅ ነኝና መሬት ይገባኛል ከሚለው ጋር ሁሉ
በለጋ እድሜው ከደብረ ታቦር ጎንደር ድረስ ሳይቀር በእግር እየተጓዘ በመሟገት የአባቱን እርስት
በማስከብር ላይ እያለ ቤተሰቡን በማስተዳደር ታላቅ ድጋፍ ያደርጉለት የነበሩት እናቱ ወይዘሮ ዘውዲቱ
ተሰማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩት። ይሄ ለኃይሌ ከባድ መከራ ነበር። አሁን ወጣቱ ኃይሌን አራት
ነገሮች ወደ አዕምሮው እየመጡ ይረብሹት ጀመር። እነርሱም፦
1. የማያባራው የመሬት ይገባኛል ሙግት፣
2. ቤተሰቡን በማስተዳደር በኩል ታላቅ እረዳት የነበሩትን እናቱን በሞት ማጣቱ እና በዚያ በኩል
የተፈጠረው ክፍተት፣
3. የቤተሰብን ሁኔታ ለማስተካከል ብሎ ለጊዜው ያቋረጠውን ትምህርት መቼ ነው መልሼ
የምጀምረው የሚለው የኅሊና ሙግት እና
4. ይህንን ሥራ (የነጭ ለባሽነቱን ሥራ እና የግሉን ውጣ ውረድ) እስከመቼ ነው ይዤ
የምቀጥለው የሚሉት ነበሩ።
እነዚህን ተግዳሮቶች በአዕምሮው እያወጣና እያወረደ ባለበት ሰዓት የኃይሌን ሕይዎትና ሞያ የሚቀይር
አንድ ክስተት 1960 ላይ ተፈጠረ። የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በየቦታው ከሚያቋቁማቸው የብሔራዊ
ጦር ሻለቆች ውስጥ 11 ኛው ሻለቃ ወረታ ላይ እንዲቋቋም ተወሰነና ለእጩ መኮንንነትና ለተራ
ወታደርነት ምልመላ መጀመሩን ደብረ ታቦር በነጭ ለባሽነት ሥራ ጉዳይ ላይ እያለ ይሰማል።
በአጋጣሚም መልማዮቹም ደብረታቦር መጥተው ስለነበር ወዲያው አገኛቸውና በእጩ መኮንንነት
ለመመልመል ፍላጎቱን ገለፀላቸው። መልማዮቹም የአርበኛ ልጅ መሆኑ፣ ነጭ ለባሽ ሻምበል ሆኖ
የሚሠራው ሥራ እና በወቅቱ ስድስተኛ ክፍል ድረስ መማሩ ቅድሚያ አሰጥቶ እንደሚያስመርጠው
ነግረው በደስታ መለመሉት።
2. ወታደራዊ ሕይዎት፣

2
ወረታ በሚገኘው 11 ኛ ሻለቃ በሔራዊ ጦር ካምፕ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃና መሠረታዊ የእግረኛ
ጦር ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ደብረዘይት ለምለም ጣቢያ ወደሚገኘው 4 ኛ ሻለቃ የብሔራዊ
ጦር ዋና ማሰልጠኛ በእጩ መኮንንነት ለመሰልጠን ተጠሩ። ይህ የብሔራዊ ጦር እጩ መኮንንነት ኮርስ
ለ 6 ወራት የሚስጥ ሲሆን፣ ከ 12 ቱም የብሔራዊ ጦር ሻለቆች የተውጣጡ 81 ሰልጣኞች የተሳተፉበት
ነበር። ኮርሱም በበላይነት ይመራ የነበረው በኢትዮጵያ የሠራዊት ስልጠና ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ
ጊዜ መሳተፍ በጀምሩት የእሥራኤል የጦር መኮንኖች ስለነበር በጣም ጠንከር ያለና እጅግም ጠቃሚ
ኮርስ ነበር። የወታደራዊ ሕይዎትን ሀ ብለው የጀመሩት እጩ ሞኮንን ኃይሌ ከ 12 ቱም ሻለቆች
ከተውጣጡት 81 እጩ መኮንንኖች ውስጥ 3 ኛ በመውጣት ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
የደብረዘይቱን ኮርስ አጠናቀው ወደ እናት ክፍላቸው 11 ኛ ሻላቃ (ወረታ) እንደተመለሱ የሆለታ ገነት
የመኮንኖች ማሰልጠኛ ጦር ትምህርት ቤት ከአየር ኃይል የጥበቃ ክፍል፣ ከክብር ዘበኛ፣ ከጦር ሠራዊት
አራቱም ክፍለ - ጦሮች፣ ከአየር ወለድና ከብሔራዊ ጦር የተውጣጡ 202 የጦር መኮንኖችን ለማሰልጠን
ስላቀደ፣ ለብሔራዊ ጦር ጠቅላይ መምሪያ 10 እጩ መኮንኖችን መርጦ እንዲልክ ደብዳቤ ጻፈለት።
የብሔራዊ ጦር ጠቅላይ መምሪያም ክ 12 ቱም ሻለቆች 31 ተወዳዳሪዎችን በመጥራት ደብረዘይት
በሚገኘው 4 ኛ ሻለቃ ማሰልጠኛው አማካኝነት በመግቢያ ፈተና አወዳድሮ 10 ከፍተኛ ውጤት ያመጡ
እጩ መኮንኖችን ሲመርጥ፣ እጩ መኮንን ኃይሌ 2 ኛ በመውጣት ነበር ግንቦት ወር 1962 ላይ ወደ
ሆለታ ገነት የመኮንኖች ትምህርት ያመሩት። ሆኖም ግን የመግቢያ ፈተናውን ካለፉ በኋላ ሆለታ
እስከሚገቡ ጊዜ ድረስ አንድ ወር ዘግይተው ስለነበር ከወር በፊት ቀደም ብለው የገቡት ከደረሱበት
ለመድረስ ብዙ እንደለፉና እንደተቸገሩ ይገልፃሉ።
እንደ ብሔራዊ ጦሩ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሁሉ፣ የሆለታውም በኢትዮጵያ ሠራዊት ስልጠና
ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ በጀመሩት የእሥራኤል መኮንኖች በበላይነት የሚመራ ስለነበር
ስልጠናው በጣም ጠንከር ያለ ነበር። ለእንደ እጩ መኮንን ኃይሌ መለሰ ከብሔራዊ ጦር ለመጡት
ደግሞ የሆለታው ኮርስ ይበልጥ ፈታኝ ነበር። ይህም የሆነው በኮርሱ ውስጥ የሚሳተፉት ከአየር ኃይል
የጥበቃ ክፍል፣ ከክብር ዘበኛ፣ ከአየር ወለድና ከምድር ጦር አራቱም ክፍለጦሮች የተውጣጡ
ተወዳዳሪዎች ስለነበሩበት ነው። ይሁን እንጅ ትምህርቱን ከስድስተኛ ክፍል ያቋረጠው፣ የነጭ ለባሽ
ሻምበል የነበረውና ከሁሉም ጦር በዝቅተኛ ደረጃ ከሚታየውና የገበሬ ጦር ነው ተብሎ ከሚታመነው
ከበሔራዊ ጦር የመጣውና ከኮርሱ ተሳታፊዎች በአንድ ወር ወደ ኋላ ዘግይቶ ይተቀላቀለው እጩ
መኮንን ኃይሌ መለሰ ኮርሱን ሲጨርስ ከጠቅላላው 202 ተወዳዳሪ 1 ኛ በመውጣት ሁሉንም
አሰልጣኞችና የጦር አዛዦች አስደመማቸው። የመከላከያ ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና መምሪያ
“ከእናንተ ተወክሎ የመጣው ልጅ እጩ መኮንን ኃይሌ መለሰ ከጠቅላላው ሰልጣኝ አንደኛ ወጥቷልና
እንኳን ደስ አላችሁ” ብሎ ለበሔራዊ ጦር ጠቅላይ መምሪያ ደስታውን ከመግለፁም በላይ በምረቃው
ቀን በክብር እንዲገኙ ጥሪ አስተላለፈ።
ሆኖም ግን ምረቃው እንደ ነገ ሊሆን እንደ ዛሬ ችግር ተፈጠረ። “ንጉሡ ነገ ሲመርቁ ከብሔራዊ
ጦር የመጣ እጩ መኮንን አንደኛ ወጥቷልና ሽልማት ስጡልን ስንል፣ ንጉሡ ‘በቃ ጦር ሠራዊቱ
ሞቷል ማለት ነው?’ ብለው ሊቆጡ ስለሚችሉ፣ የደረጃ ማቀያየር ማድረግ አለብን” ተባለና ሁለተኛ
የወጣውን አንደኛ፣ አንደኛ የወጣውን ደግሞ ሁለተኛ በማድረግ አስተዳደራዊ እርምጃ ወሰዱ። የካቲት
3 ቀን 1963 ዓ.ም. ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ በአስተዳደራዊ ውሳኔ
“አንደኛ ለወጣው” .... የመኮንንነት ቀበቶ ሲያስታጥቁ፣ “ሁለተኛ ለውጣው” እጩ መኮንን ኃይሌ
መለሰ ደግሞ ልዩ የብዕር ሽልማት ሰጡ። ጉዳቸውን ያላወቁት አንድ ከፍተኛ የመከላከያ ጄኔራል፣
ከብሔራዊ ጦር የመጣው እጩ መኮንን ኃይሌ መለሰ “2 ኛ ወጥቶ” ከጃንሆይ ሲሸልም ስላዩ
በመገረም በፎቶው ላይ አፋቸውን ይዘው ይታያሉ።

3
እጩ መኮንን ኃይሌ መለሰ የካቲት 3 ቀን 1963 ዓ.ም. ከሆለታ የጦር መኮንኖች ት/ቤት ከ 202 ተመራቂዎች ውስጥ “2 ኛ”
በመውጣት ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እጅ ልዩ የብዕር ሽልማት ሲቀበሉና ከብሔራዊ ጦር የመጡት ኃይሌ ይህንን
ደረጃ በማግኘታቸው አንድ ከፍተኛ መኮንን በመገረም አፋቸውን ይዘው ይታያሉ።

ብሔራዊ ጦርን ወክለው ከምረቃው ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ጦር የትምህርትና የስልጠና


መምሪያ ሃላፊ ኮሎኔል ማሩ ጋተው ግን በስልክ የተነገራቸው ተገልብጦ እጩ መኮንን ኃይሌ መለሰ
ሁለተኛ ሆኖ ሲሸለም ስላዩ ንጉሠ ነግሥቱ ከሚገኙበት የምሳ ግብዣ ላይ አልገኝም ብለው በንዴት
እየጦፉ ወደ አዲስ አበባ ወዲያውኑ ተመልሰዋል። ይህንን ፍርደ - ገምድል ውሳኔ ያልተቀበሉ ሻለቃ
(በኋላ ጄኔራል) ስዩም መኮንን የተባሉ የትምህርት መኮንን ደግሞ ተመራቂዎች ለመመረቅ ጠዋት
ከተሰለፉበት የሰልፍ ሜዳ ድረስ በመምጣት እጩ መኮንን ኃይሌን፦ “አንደኛ ሆነህ እያለ፣ በአንደኛነት
ባትሸለምም፣ እኔ ባስተማርኩህ የሁኔታ ማረጋገጥ ትምህርት ግን አንደኛነትክን ማንም አልወሰደብህም፤
አሁንም አንደኛ ነህ” ብለው ሞቅ አድርገው በመጨበጥ ደስታቸውን ገለፁላቸው።
ከሆለታ ገነት የመኮንኖች የጦር ትምህርት ቤት በምክትል መቶ አለቃነት የተመረቁት ኃይሌ መለሰ
ከምረቃ በኋላ ደብረዘይት በሚገኘው 4 ኛ ሻለቃ የብሔራዊ ጦር ማሰልጠኛ የትምህርት መኮንን ሆነው
ተመደቡ። በደብረ ዘይት ኑሯቸውን ከመጀመራቸው በፊት በቀጥታ ወደ ደብረ ታቦር በመምጣት
ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ደብረዘይት አመሩ።
ከየካቲት 1963 አስከ የካቲት 1965 ዓ.ም. ደብረ ዘይት 4 ኛ ሻለቃ ብሔራዊ ጦር ውስጥ ስመ - ጥር
የትምህርት መኮንን ሆነው ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ፊቼ መናገሻ ወደሚገኘው 2 ኛ ሻለቃ
በሔራዊ ጦር ተቀየሩ። ም/መ/አ ኃይሌም ፊቼ መናገሻ ለ 6 ወራት ያክል በትምህርት መኮንንነት
ካገለገሉ በኋላ ሀምሌ 7 ቀን 1965 ዓ.ም. አዲስ አበባ ወደሚገኘው የብሔራዊ ጦር ጠቅላይ መምሪያ
የትምህርት መኮንን ሆነው ተዛወሩ። መቶ አለቃ ኃይሌ መለሰ (አሁን ሙሉ መቶ አለቃ ናቸው) ሆለታ
ባመጡት ውጤት የጦሩን ስም ስላስጠሩ በጠቅላይ መምሪያው ከጦሩ አዛዥ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ
ጀምሮ እስከ ታች ባሉት የጠቅላይ መምሪያው አባላት ዘንድ በጣም የተከበሩና ተወዳጅ መኮንን ነበሩ።
ጠቅላይ መምሪያው ውስጥ ለአንድ ዓመት ያክል እንዳገለገሉ የደርግ መሥራች የነበሩት ሻለቃ (በኋላ

4
ኮሎኔል) አጥናፉ አባተ የብሔራዊ ጦር ሁለት ተወካዮች እንዲልክ ለጠቅላይ መምሪያው በጻፉት
መሠረት መቶ አለቃ ኃይሌ መለሰና ሃምሣ አለቃ ጌታቸው ተቀባ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም. በጦሩ
ተመርጠው ያኔ የደርግ ጽ/ቤት ወደነበረበት 4 ኛ ክፍለጦር ተላኩ።

3. የደርግ አባልነት ዘመን


ጄኔራል ኃይሌ መለሰ የደርግን ዘመን በሁለት ከፍለው ነው የሚያዩት። 1 ኛ. ከሰኔ 21 ቀን 1966 እስክ ጥር
26 ቀን 1969 ድረስ ያለውን ሲሆን፣ 2 ኛ ደግሞ ከጥር 26 ቀን 1966 እስከ ደርግ ፍፃሚ (ግንቦት 20
1983) ያለውን ጊዜ ነው።
ከሰኔ 21 ቀን 1966 እስከ ጥር 26 ቀን 1969 ያለው የደርግ የውስጥ አሠራር ዴሞክራሲ የሰፈነበት፣ አንድ
የደርግ አባል በማዕረጉ ሳይሆን እንደ አንድ የደርግ አባል እኩል ድምፅ የነበረው፣ የሕዝብን ጥያቄ
ለመመለስ ከልብ የሚጥር ነበር። ከጥር 26 ቀን 1969 (እነ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ከተገደሉ) በኋላ ያለው
ደርግ ግን እኩልነት የሰፈነበት ሳይሆን የአንድ ሰው አምባገነንነት የሰፈነበት ስብስብ አድርገው
ይመድቡታል።
1968 ዓ.ም. ላይ ደርግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል (“ሁኔታውን ካረጋጋሁ በኋላ በሕዝብ ለተመረጠ
መንግሥት አስረክቤ ወደ ካምፔ እመለሳለሁ”) በመሻር የፖለቲካ ድርጅት (አብዮታዊ ሠደድ) አቋቁሞ
ለስልጣን ለመወዳደር መዘጋጀት ጀመረ። ይህ ድርጊት ለባለማተቡ ኃይሌ መለሰ አልተዋጠላቸውም።
በመሆኑም “ለሕዝቡ ቃል የገባነው የተነሳውን አመፅ አረጋግተን ወደ ካምፓችን ለመመለስ ነው።
አሁን ግን የፖለቲካ ድርጅት ስናቋቋም መንግሥት ለመሆን እየፈለግን ነው ማለት ነው። ይህ
ድርጊታችን ትናንት ለሕዝብ ከገባነው ቃል ጋር እንዴት አብሮ ይሄድልናል? አይጣረስም ወይ?” የሚል
ጥያቄ በማንሳት በደርግ ስብሰባ ላይ ተሟግተዋል። ሆኖም ግን በስብሰባው ላይ ተሟግተው ማሸነፍ
ያልቻሉት ሻምበል ኃይሌ በዚህ ብቻ ሳያበቁ ቃላቸውን ጠብቀው ወደ ካምፓቸው ለመመለስ ደብዳቤ
ለደርግ ጽ/ቤት ጻፉ። የደብዳቤው ይዘትም የሚከተለውን ይመስል ነበር፦ “1 ኛ ለሕዝብ ቃል የገባነው
በውቅቱ የተፈጠረውን ሕዝባዊ አመፅ አረጋግተንና በሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግሥት አስመርጠን
ወደ ካምፓችን እንደምንመለስ ነበር። አሁን ግን ያንን የገባነውን ቃል አጥፈን መንግሥት ለመሆን
እየፈለግን ነው። 2 ኛ/ የመንግሥት በትረሥልጣኑን ይዘን እንቀጥል ብንል እንኳን እኛ ወታደሮች እንጅ
ሀገር የመምራት ልምዱ፣ ችሎታውና አቅሙ ያለን ሰዎች አይደለንም። ስለዚህ እኔ በዚህ መቀጠል
ስለማልፈልግ ወደ ክፍሌ እንድመለስ ይፈቀድልኝ” የሚል ነበር። ጥቂት የቅርብ ጓደኞቻቸውም
ይህንን ፈለግ ተከተሉ። ሆኖም ግን የደርግ ሊቃነ መናብርቱ አጠቃላይ ስብሰባ ጠርተው፦ “መንግሥት
አውርደን መንግሥት ሳንተካ ብንለቅ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ስለምትወድቅ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማቅረብ
አይቻልም” የሚል ውሳኔ ተወሰነባቸው።
ከደርግ ለቅቆ ወደ ካምፕ መመለሱ ሳይሳካላቸው ሲቀር ትግላቸውን በሌላው ምዕራፍ ቀጠሉ። ደርግ ከኅዳር እስከ
ታህሣሥ ወር 1969 ዓ.ም. ድረስ የደርግ አሠራርን የሚወስን (በየክፍለ ሀገሩ፣ በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና
በየኮሚሽኖቹ መድቦ ለማሠራት) እንዲሁም የሊቀመንበሩን ስልጣን ለመገደብና በደርግ ውስጥ እየተፈጠረ ስለመጣው
ልዩነት ፍፁም ነፃና ዴሞክራቲክ ውይይት ለአንድ ወር አድርጎ ነበር። በዚህ ውይይት ወቅት ሻምበል ኃይሌ
የሻለቃ መንግስቱን ስልጣን ለመገደብ ከሚታገሉት ዋና ዋና የደርግ አባልት ውስጥ አንዱ ሆነው ወጡ። በዚህ
ስብሰባ ፍፃሜ የእነተፈሪ በንቲ ቡድን (ሻምበል ኃይሌም ያሉበት ቡድን) የእነኮሎኔል መንግሥቱን ቡድን
በድምፅ ብልጫ በማሸነፍ መንግሥቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ብቻ እንዲሆኑ ሲያደርግ፣
ለኮሎኔል አጥናፉ ግን መከላከያውንና ደህንነቱን በሥራቸው አድርገው እንዲያዙ ስልጣን ሰጥቷቸው
ነበር። የያኔው ሻምበል ኃይሌ መለሰ ደግሞ የጎንደር ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ ተጠሪ ሆነው ተመደቡ።
ሆኖም ግን ይህ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጎንደር ውስጥ ተማሪዎች ፒያሳ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ

5
ሲያደርጉ በወታደሮች በመገደላቸውና የጎንደር ሕዝብ ያምፃል ተብሎ ስለተፈራ ሻምበል ኃይሌ
ራሳቸውን ጨምሮ 9 የደርግ አባላትና 2 ከፍተኛ የሕዝብ ድርጅት ባለስልጣናት የተካተቱበት ቡድን
በሃላፊነት መርተው በመሄድ ሕዝቡን እንዲያረጋጉ ተላኩ።
ቡድኑ ጎንደር ደርሶ ሕዝቡን በማረጋጋት ላይ እያለ አንድ ቀን በአራት አጀንዳዎች ላይ ውይይት
ማድረግ ይጀምራሉ። አጀንዳዎቹም፦
1. የጎንደር ሕዝብ በቀይ ሽብር መመታት አለበት፣
2. የጎንደርን ሕዝብ ትጥቅ እናስፈታ፣
3. ከሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ የመጡት ዶ/ር ዓለሙ አበበ እና አቶ ሸዋንዳኝ በለጠ
ከዘጠኙ የደርግ አባላት ጋር አብረው ድምፅ ይስጡ፣
4. ሻምበል ኃይሌ በማዕከልነት ጎንደር ከተማ ሆነው ያስተባብሩ እንጅ በየአውራጃዎቹ ከእኛ ጋር
መሄድ የለባቸውም የሚሉ ነበሩ።
አጀንዳዎቹ ከሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ ተወክለው ከመጡት ባለስልጣናት የመነጩ
ይመስላሉ። በአጀንዳ 1፣ 2 እና 4 ሻምበል ኃይሌ 8 ለአንድ በሆነ ድምፅ ሲሸነፉ፣ በአጀንዳ 3 ብቻ አንድ
ሰው አብሯቸው ድምፅ በመስጠቱ 7 ለሁለት ተሸንፈዋል። በአጀንዳ አንድ ላይ ሻምበል ኃይሌ
በምክንያት አስደግፈው የጎንደር ሕዝብ በቀይ ሽብር መመታት የለበትም የሚል አቋም ሲይዙ 8 ቱ
የደርግ አባላት ግን መመታት አለበት ብለው ከእርሳቸው ተቃራኒ ሆነው ቆሙ። የጎንደር ሕዝብ ትጥቅ
መፍታት አለበት በሚለው ሁለተኛው አጀንዳም እርሳቸው መፍታት የለበትም ሲሉ ስምንቱ የደርግ
አባልት ግን መፍታት አለበት ብለው በድምፅ አሸነፏቸው። ይሁን እንጅ ምንጊዜም ለዕውነት የቆሙትና
የመርህ ሰው የሆኑት ሻምበል ኃይሌ ብቻቸውን በመቆማቸው ሳይደናገጡና ማንም ሊያግባባቸው
ቢሞክር ከአቋማቸው ፍንክች አላሉም። ሻምበል ኃይሌ መለሰ በድምፅ ብልጫ ቢሸነፉም፣ የአሠራር
መርሃቸውን በመከተል እንደ አንድ የቡድን መሪ የስብሰባውን ውሳኔ ለሻለቃ መንግሥቱ ሪፖርት
አደረጉ። ሻለቃ መንግሥቱም “እኛ ትዕዛዝ እስከምንሰጥ ድረስ ጉዳዩ በይደር ይቀመጥ፣ ተፈፃሚ
እንዳይሆን፤ ቃለ ጉባኤውን ግን ቶሎ ላኩልን” አሉ። ጉዳዩ በጣም ከፍተኛ ሚስጥር በመሆኑ
ሚስጥርነቱን ለመጠበቅ ሲባል በፋክስና በፖስታ ከመላቅ ይልቅ ቃለ - ጉባኤው በአንድ የደርግ አባል
እጅ ተላከ። ሻምበል ኃይሌ የመሩት ቡድን ጎንደር ውስጥ በዚህ ዓይነት ውጥረት ላይ እንዳለ የእነ
ሻለቃ መንግሥቱ ቡድን “ለምሳ አስበውን የነበሩትን፣ ለቁርስ አደረግናቸው” ብሎ እነ ጄኔራል ተፈሪ
በንቲን መግደሉን ማታ በዜና አስነገረ። ሻምበል ኃይሌና መርተውት የሄዱት ቡድንም ጎንደር ላይ
እያደረገ ያለውን ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ አቋርጦ በ 24 ሰዓት ውስጥ ደርግ ጽ/ቤት ሪፖርት
እንዲያደርግ የቴሌግራም መልዕክት ደረሰው።
ሻምበል ኃይሌ አሰላለፋቸውን ስለሚያውቁ እነጄኔራል ተፈሪ በተመቱ ጊዜ እዚያ ስብሰባ ላይ ቢኖሩ
ኖሮ እንደማይተርፉ እርግጠኛ ነበሩ። አሁንም ቢሄዱ እጣፈንታቸው የእነተፈሪ እጣፈንታ እንደሚሆን
ስላመኑ ወደ አዲስ አበባ ላለመሄድ ወሰኑ። በዚያ እናት ልጇን በማታምንበት ወቅት፣ ሻምበል ኃይሌ
መለሰ በወቅቱ የጎንደር ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ የነበሩትን ኮሎኔል እምሩ ወንዴን አምነው “ወደ አዲስ
አበባ ሄጄ እጄን ሰጥቸ መሞት አልፈልግምና በግዛትዎ ያሸፍቱኝ” አሏቸው። ይህንን ሁኔታ ከ 18
ዓመታት በኋላ እ.አ.አ. የካቲት 12 ቀን 1995 ዓ.ም. ኮሎኔል እምሩ ሱዳን ሆነው ጄኔራል ኃይሌ ደግሞ
ጎንደር ውስጥ ለውያኔ እጄን አልሰጥም ብለው ሸፍተው በነበረበት ሰዓት በጻፉላቸው ደብዳቤ እንዲህ
ያስታውሱታል፦
እጅግ በጣም ለማደንቅህና ለምወድህ የወንዜ ልጅ ወንድሜ ብ/ጄ ኃይሌ መለሠ፣
እጅጉን እንደምን አለህልኝ? ለሕይወትህ እሳሳለሁ። ምሽግ ሆኖ ሸፍኖ ለያዘህም
ሕዝባችን፣ ወገናችን ያለኝ አድናቆት ወሰን የለውም። ይህንን ደብዳቤ መጻፍ ስጀምር

6
ብዙ ነገሮች መጡብኝ። ታስታውስ እንደሆን እነተፈሪ ባንቲ በተመቱ ጊዜ አዲስ አበባ
አልሄድም፣ አሸፍተኝ ብለህ በዚያ በሳቱ መተማመን ጭንቅ በነበረበት ጊዜ እኔን
የወንዝህን ልጅ ወንድምህን አምነህ ያካፈልከኝ ምስጢር አንዱ ነው። አዲስ አበባ
ታጠቅ የጦር ሠፈር ተገናኝተን ደግሞ የምወጣበት ቀን እየቀረበ ነው ብዬ በማንሳት
በመተማመን የተወያየነው ሌላው ነው።
ሆኖም ግን በኮሎኔል እምሩ በኩል የሞከሩት ሙከራ ያልተሳካላቸው ሻምበል ኃይሌ የበለሳ ሰው የሆነና
የብሔራዊ ጦር ባልደረባ የነበረውን ጓደኛቸውን መ/አለቃ (አሁን ሻምበል) ጌታቸው ወረደን ፈልገው
ወደበለሳ የሚያሸጋግራቸው ሰው እንዲፈልግላቸው ጠየቁት። መ/አለቃ ጌታቸውም ይህንን ሥራ
በብቃት ያከናውንልኛል ብሎ ያመነበትን ፒያሳ (ጎንደር) የሚኖር አንድ ዮሐንስ የተባለ ጓደኛውን
ለማግኘት ሞክሮ ወደ ባህርዳር ሄዷል ስለተባለ ጥረቱ ሳይሳካ ቀረ። ይህ ሁሉ ጥረታቸው
ያልተሳካላቸው ሻምበል ኃይሌ ከቡድናቸው ጋር በበነጋታው ወደ አዲስ አበባ መብረር ነበረባቸውና
በረሩ።
አዲስ አበባ ደርሰው ደርግ ጽ/ቤት ሪፖርት ከማድረጋቸው በፊት እቤት በመሄድ ባለቤታቸውን ወይዘሮ
የሻለም አየለንና እንደ ልጃቸው የሚያሳድጉትን የእህታቸውን ልጅ መኝታ ቤት አስገብተው በጥሬ
ገንዘባቸው የገዟትን ነጥብ 35 ኮልት ሽጉጥ በመስጠት፦ “ላልመለስ እችላለሁና ይህንን ሽጣችሁ
ለመጓጓዣ በመክፈል ቤተሰቡን ይዛችሁ ወደ ዘመዶቻችሁ ደብረ ታቦር እንድትሄዱ” አሏቸው።
ባለቤታቸውና የእህታቸው ልጅ በእንባ ሲታጠቡ እርሳቸው ግን ምንም አልመሰላቸውም ነበር።
እነርሱን ተቆጥተውና አፅናንተው እናት ክፍላቸው ብሔራዊ ጦር የሰጣቸውን ሽጉጥ ታጥቀው ወደ
ደርግ ጽ/ቤት ሄዱ።
የተፈራው ሳይሆን ቀርቶ ማታ ተመልሰው በሕይዎት ሲመጡ ቤተሰቡ የተሰማው ደስታ በጣም
ከፍተኛ ነበር። ሆኖም ግን ቀደም ብሎ የጎንደር ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ አባል ሆነው ተሹመዋል
የሚለው ደብዳቤ ታጥፎ ለሌላ ሰው ተሰጠ። ከጎንደር እንዲነሱ የተደረጉት በሥራ ጉብኝታቸው ወቅት
8 ለ 1 በተሸነፉበት አቋማቸው (የጎንደር ሕዝብ በቀይ ሽብር ይመታ በሚለውና ትጥቁን መፍታት
አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ በሁለቱም ብቻቸውን በመቆማቸው) ነበር። ከቡድኑ አባላት ውስጥ
ለመንግሥቱ ሪፖርት ሲያደርጉ “ሻምበል ኃይሌ የጎንደር ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ አባል ሆኖ ከቀጠለ
ኢሕአፓና ኢድህ በቅርቡ ጎንደርን ይቆጣጠራሉ፤ ኃይሌ ለጎንደር ሕዝብ ስስ ልብ ነው ያለው፤ ‘እኔ
ወደዚህ የመጣሁት የጎንደርን ሕዝብ በቀይ ሽብር ለመምታትና ትጥቅ ለማስፈታት አይደለም’
ይላል” የሚል ሪፖርት እንተደረገባቸው ታውቋል። በዚህም ምክንያት በአዲሱ የደርግ አሠራር የጎንደር
ክፍለህገር ቋሚ የደርግ አባል ሆነው ተሸመው የነበረው ታጥፎ እርሳቸው ወደ ንግድና ቱሪዝም ቋሚ
የደርግ አባል ሆነው ሲሾሙ፣ በንግድና ቱሪዝም ቋሚ የደርግ አባል ሆነው ተሾመው የነበሩት ሰው
ደግሞ ወደ ጎንደር እንዲዛወሩ ተደረገ።
ሻምበል ኃይሌ በንግድና ቱሪዚም ቋሚ የደርግ አባልነት የሦስት ወራት የሥራ ጊዜያቸው ወቅት
በየአቅጣጫው በመዋከብ ላይ ለነበረው ሠራተኛ እፎይታን ከመስጠት ጀምሮ ከመታሠርና ከመገደልም
የታደጓቸው ሰዎች እንደነበሩ ጄኔራል ኃይሌ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልፀዋል። አንድ
ቀን ቢሮዋቸው ውስጥ ሆነው ሥራቸውን እየሠሩ በነበሩበት ጊዜ ከቢሮዋቸው በር ላይ መሯሯጥና
መጯጯህ ይሰማሉ። ወቅቱ ስጋት የበዛበት ጊዜ ስለነበረና አደጋው በእርሳቸው ላይ ያነጣጠረ
ስለመሰላቸው ዑዚያቸውን ይዘው ሲውጡ አምስት ዲሞትፈር የታጠቁ የቀበሌ ታጣቂዎች አንድን
ሰው ጉሮሮውን አንቀው መተንፈሻ አሳጥተውት ያገኛሉ። ሻምበል ኃይሌም “ምን አደረጋችሁ?
ልቀቁት” ይላሉ። ሁሉን አድራጊ የነበሩት ሰዎች ይህንን የመሰለ ጥያቄ በዚያ ሰዓት ይቀርብልናል
ብለው አልጠበቁም ነበር። በዚህም ምክንያት ከሻምበል ኃይሌ ጋር ተፋጠጡ። ወዲያው ስድስተኛ ሰው
ሆኖ ሰውየውን ከሚያዋክቡት ሰዎች አንዱ ከተሳዳጁ ጋር የንግድና ቱሪዝም መሥሪያ ቤት አባል የነበረ

7
ሰው ለሻምበል ኃይሌ “ምን አደረጋችሁ?” ጥያቄ “ቅጥር ነብሰ-ገዳይ ነው” የሚል ምላሽ ሰጠ።
ሻምበል ኃይሌም ቀጠል አድርገው “አንተ እኔ እዚህ መሥሪያ ቤት እንዳለሁ ታውቃለህ አታውቅም?”
ብለው ሲጠይቁት እንደሚያውቅ ተናገረ። “ታዲያ ካወቅህ ይህ ሰው ቅጥር ነብሰ ገዳይ መሆኑን
መጥተህ ያልነገርከኝ ለምንድነው?” ሲሉት መልስ አልነበረውም። ስለዚህ ተጠርጣሪውን የኢሕአፓ አባል
ቢሯቸው ውስጥ ቆልፈው ለደርጉ የጥበቃ ሃላፊ ለነበሩት ያኔ ሻለቃ (በኋላ ጄኔራል) ጌታቸው ሺበሽ
ስልክ ደውለው ሁኔታውን ገለፁላቸውና ወደ ደርግ ጽ/ቤት ይዘውት እንዲመጡ ተስማሙ። ሻምበል
ኃይሌም ተጠርጣሪውን ከጎናቸው አድርገው እርሳቸው እያሽከረከሩ ለሻለቃ ጌታቸው ሺበሽ
አስረከቡት። ከጊዜ በኋላ ተጠርጣሪውም ተመርምሮ ከተጠረጠረበት ወንጀልና የኢሕአፓ አባልነት ነፃ
በመሆኑ ሊፈታ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪም በየቦታው የመምሪያ ሃላፊዎችና ማናጀሮች የኢሕአፓ
አባላት ናቸው እየተባሉ በዕውነትም ሆነ በሀሰት መወንጀሉ በዝቶ ነበር። ሻምበል ኃይሌም ችግሩ
በተፈጠረበት ቦታ ሁሉ እየሄዱ የሀሰት ከሣሾችን ማሥረጃ አቅርቡ ሲሏቸው ምንም ማስረጃ ማቅረብ
አልቻሉም። “ማስረጃ ከሌላችሁ፣ በሀሰት ውንጀላ ሰው አናስርም፤ አንገድልምም” እያሉ ብዙዎችን
ነፃ አወጧቸው። የሻምበል ኃይሌ ፍትሃዊና ሰብዓዊ ድርጊት አብዛኛውን ሠራተኛ በጣም
ቢያስደስተውም፣ ጥቂት የሀሰት ወንጃዮችን ግን አላስደሰተም። በመሆኑም ሻምበል ኃይሌ ገና ሦስት
ወሩ እንደሠሩና በአብዛኛው ሠራተኛ እንደተወደዱ ወደ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ተቀየሩ። የንግድና ቱሪዝም
ሚኒስቴር ሠራተኛ ግን በመቀየራቸው ቢያዝንም ሚኒስትሩ ዶ/ር አሻግሬ ይግለጡ በተገኙበት በጥሩ
ሁኔታ ደግሶና ሸልሞ ሸኛቸው።
አሁንም ለሦስት ወራት ያክል ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ውስጥ እየሠሩ እያለ የሶማሊያ መንግሥት
ምሥራቅና ደቡብ ኢትዮጵያን በ 1969 መጨረሻ ላይ ወረረ። የደርግ ሥራ አስፈፃሚም መላው የደርግ
አባላትን ጦር አሰልጥነውና መርተው ሀገርን ለመከላከል እንዲዘምቱ ፈቃደኛነታቸውንና ብቃታቸውን
ቃለ-መጠይቅ በማድረግ አጣራ። ቆፍጣናው ሻምበል ኃይሌ በደርጉ ሥራ አስፈፃሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ
የሰጡት መልስ፦ “እኔማ አይሆንም ተባልኩ እንጅ ቀደም ብየም ቢሆን ወደ ክፍሌ ተመልሼ በሞያዬ
እናት ሀገሬን እንዳገለግል ጠይቄ ነበር። ስለዚህ ትናንት ለጠየቅሁት ጥያቄ አሁን መልስ ሳገኝ በደስታ
ነው የምቀበለው። አሁኑኑ ለመዝመት በጣም ፈቃደኛ ነኝ” ብለው መለሱ። ወዲያው 69 ነኛ
ሚሊሺያ ብርጌድ የተባለ ሕዝባዊ ሠራዊት ታጠቅ ጦር ሠፈር ውስጥ አሰልጥነው እንዲዘምቱ ተደረገ።
4.የኦጋዴን ዘመቻ
ሻምበል ኃይሌ መለሰ አሰልጥነው ይዘው የዘመቱት ጦር ከገበሬው የተውጣጣ 2245 የሰው ኃይል
የነበረው የሕዝባዊ ሠራዊት ጦር ነበር። የሻምባል ኃይሌ 69 ነኛ ብርጌድ 4 ሻለቆች ሊኖሩት ሲገባ 3
ሻለቆችን ብቻ ነበር ይዞ የዘመተው። ይህም የሆነው ከ 69 ነኛ በፊት የዘመተው 68 ኛ ብርጌድ የሰው
ኃይል ስላልተሟለለት አንድ ሻለቃ ጦራቸውን ለ 68 ኛ ብርጌድ እንዲሰጡና ለእርሳቸው ደግሞ ሌላ
ሻለቃ ጦር እንደሚተካላቸው ቃል ተገብቶላቸው ነበር። ይሁን እንጅ በነበረው አጣዳፊ ሁኔታ ይህ
ለ 68 ኛ ብርጌድ የሰጡት አንድ ሻለቃ ጦር ሳይተካላቸው በሦስት ሻለቆች ብቻ የተዋቀረውን
ብርጌዳቸውን ይዘው መሥከረም ወር 1970 ላይ ወደ ውጊያው ግንባር ገቡ።
69 ነኛ ብርጌድ የመጀመሪያውን ከባድ ውጊያ ያደረገው ድሬዳዋ አጠገብ ፉላ ቦራ ድልድይን ላለማስያዝ
በተደረገው ውጊያ ላይ ነበር። ሻምበል ኃይሌ መለሰ ስለ ምሥራቁ የጦር ግንባር ተጋድሏቸው
በማስታወሻቸው ካሠፈሯቸው ዕውነታዎች ውስጥ የፉላ ቦራዋ ክስተት እንዲህ ትነበባለች፦
“ድሬዳዋ ላይ እያለን የሶማሊያ ጦር ከፋቱሌ ኤረር ጉታ የሚያልፈውን የባቡርና
የመኪና መንገድ ፉላ ቦራ ላይ ሊዘጋ ነው ስለተባለ እንድንከላከል ተዕዛዝ ተሰጠኝ።
በሁርሶ በኩል አልፈን የተሰጠን የግዳጅ ቦታ ለመያዝ ስንቃረብ፣ ፉላ ቦራ ላይ
የሶማሊያ ጦር አድፍጦ ጠበቀን። የመድፍ፣ የታንክና የላውንቸር ተኩስ አወረደብን።

8
የሚሊሺያው ጦር ከትምህርት ውጭ የተግባር ውጊያ ሲገጥም ገና የመጀመሪያው
ስለሆነ የከባድ መሣሪያው ተኩስ እረበሸውና ተንበራገገብኝ። አንድ የሬዲዮ መገናኛ
ሠራተኛና ከሦስት የማይበልጡ ወታደሮችን እንደያዝኩ በሶማሊያ ጦር ተከበብኩ።
የከበበንን ከፍተኛ የሶማሊያ ጦር ተከላክለንና ሰብረን የምንወጣበት አንዳችም አቅም
አልነበረንም። እንደ አንድ የደርግ አባልና የብርጌድ አዛዥ መኮንን ደግሞ እጄን ለጠላት
ሰጥቼ መማረክ ፈፅሞ የማይታሰብ ነበር። ስለዚህ በእንዲህ ያለው ችግር ጊዜ
እንድጠቀምበት የተሰጠኝን ፈንጅ አውጥቸ በእጄ ይዤ እራሴን ለማጥፋት ስል፣
በጌታቸው ተቀባ የሚመራው 2 ኛ ሻላቃ ጦር ከዚህ መጣ ሳይባል በሶማሊያው ጦር
ላይ ሠፈረበት። የእኔም ሕይዎት ከሞት አፋፍ ተመለሰች።”
ከዚህ በኋላ 69 ነኛ ብርጌድ የሶማሊያ ጦር ሊያንበራግገው ቀርቶ ተኩሱን እንደሙዚቃ እየቆጠረው
ስለመጣ የእርሱን ክንድ ሊመክት የሚችል የሶማሌ ጦር አልነበረም። ድሬዳዋንና አካባቢውን ተከላክሎ
ማዳን ብቻ ሳይሆን የማጥቃት አድማሱን በማስፋት ፉላ ቦራን፣ ቢዮ ባይህን፣ አራቢን፣ ጎሎልቻን፣
ደንበልን፣ ጭናቅሰንን፣ ካራማራን፣ ጂጂጋን (የካቲት 22 ቀን 1970)፣ ደገሐቡርንና መጨረሻም ላይ
መጋቢት 1 ቀን 1970 ዓ.ም. ቀብሪዳህርን ከሶማሊያ ወራሪ ጦር ነፃ አውጥቶ በመቆጣጠር የምሥራቁን
ግንባር ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ ያደረገ ጀግና ብርጌድ ነው።
“የኢትዮጵያ ሠራዊት ከድል ወደ ውድቀት 1967 – 1983 ዓ.ም.” በሚል ርዕሥ ለዶክትሬት ዲግሪው
ማሟያ ጥልቅ ጥናት ያደረገውና በኋላም ወደ መጽሐፍነት የለወጠው ዶ/ር ፋንታሁን አየለ የ 69 ነኛ
በርጌድን ተጋድሎ በደንብ ገልፆታል። በቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ዙሪያ ብዙ ሰነዶችን
ያገላበጠውና የጦርነት ቦታዎችን እየተዘዋወረ የጎበኘው ዶ/ር ፋንታሁን ካራማራን ለማስለቀቅ እነማን
እንደተሳተፉ ሲገልፅ፦ “...አንደኛው ፓራኮማንዶ ብርጌድ፣ 69 ነኛ እና 75 ኛ ሚሊሺያ ብርጌዶች፣
የ 74 ኛ ብርጌድ 2 ሻለቆች፣ ከ 60-70 ታንኮችን ከታጠቀው የኪዩባ ብረት ለበስ ብርጌድ ጋር በመተባበር
ካራማራ ተራራ ላይ በመሸገው የሶማሊያ ጦር ላይ ከሰሜን አቅጣጫ ማጥቃት ሰነዘሩበት”1 ይላል።
በመቀጠልም ዶ/ር ፋንታሁን እንዲህ ይላል፦ ከሰሜን አቅጣጫ ከሶማሊያ ምሽግ ላይ ማጥቃት
ከሰነዘሩ የሚሊሺያ ክፍሎች መካከል በኢትዮጵያና በኪዩባ አዛዦች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈው
69 ኛው ሚሊሺያ ብርጌድ ይገኝበታል። በሻ/ል (በኋላ ብ/ጄ) ኃይሌ መለሰ የሚመራው ይህ ብርጌድ
በገጠመው ከባድ ዝናብና ጭቃማ መንገድ ሳይበገር በእግር አድካሚ ጉዞን በመጓዝ ካራማራ ተራራ ላይ
በመሸገው የሶማሊያ ጦር ላይ ጥቃት ሊሰነዝር ችሏል።2
ከላይ እንዳየነው በምሥራቁ ጦር ግንባር በተካሄደው ውጊያ እንደ ነፃነት ምልክት የምትታየው
ካራማራም የተለቀቀቺው በበላይ አዛዦች ዘንድ ሁልጊዜም ለከባድ ግዳጅ በሚመረጠውና ሻምበል
ኃይሌ መለሰ በሚመሩት ስመጥሩው 69 ነኛ ብርጌድና ሌሎች የጦር ክፍሎች ከሰሜን በኩል በሰነዘሩት
ጥቃት ነው። ከዚያም 69 ነኛ ብርጌድ በፍጥነት ተወርውሮ የካቲት 22 ቀን 1970 ዓ.ም. ጂጂጋን
ተቆጣጠረ። ይህ ሻምበል ኃይሌ ይመሩት የነበረው የ 69 ነኛ ብርጌድ በምሥራቁ ጦር ግንባር
ባስመዘገበው ታላቅ ተጋድሎ በኢትዮጵያውያንም ሆነ በኪውባውያን አዋጊ ጄኔራሎች የተመሠከረለት
ብርጌድ ነበር።
“ጦርነቱን ለመጀመር ስንሰለፍ አንድ መኪና አልነበረንም። በኋላ ግን ከሶማሊያ ጦር
የማረክነው የመኪና ብዛት የአንድን ክፍለጦር ሙሉ ድርጅት ሊያጓጉዝ የሚችል ነበር።
ባዙቃ ለዓይነት እንኳን አንድም አልነበረንም፤ ግን ከወራሪው የሶማሊያ ጦር በመማረክ

1
ፋንታሁን አየለ “የኢትዮጵያ ሠራዊት ከድል ወደ ውድቀት (1967 – 1983) ገጽ 162-163.
2
ዝኒ ከማሁ ገጽ 163

9
መኪና ላይ እንደፍልጥ ከመርነው። ውጊያውን ስንጀምር መትረጌስ በቁጥር ብቻ ጥቂት
ነበሩን። በኋላ ግን እርሱንም እንደ ፍልጥ መኪና ላይ ከመርነው። ስንጀምር የስንቅ
ችግር ነበረብን። በኋላ ግን የምናባርረውን የሶማሊያን ስንቅ ስለተረከብነው
የተትረፈረፈ ስንቅ ነበረን” ይላሉ የኦጋዴኑ አንበሣ ብርጋዴር ጄኔራል ኃያሌ መለሰ።

የምሥራቁ ጦርነት ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ የሞያቸውን ብቃት ያሳዩበትና ጀብድ
የፈፀሙበት የጦር ግንባር ነበር። በሥራቸው የነበሩ የ 69 ነኛ ብርጌድ አባላት ጄኔራል ኃይሌን እንደ
አባት በስስት ነበር የሚያዩዋቸው። እርሳቸውም እንዲሁ እንደልጆቻቸው በፍቅር ነበር የሚያዩዋቸው።

ሻምበል ኃይሌ መለሰ በደገሐቡር (1970)

የምሥራቁ ጦርነት በድል ሲጠናቀቅ ሻምበል ኃይሌ መለሰ በተፋጠነ እድገት ወደ ሻለቃነት አድገዋል።
በመቀጠልም የባህርዳር አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ። በእናት ሀገር ጥሪው ጊዜ ከ 109 ኙ የደርግ
አባላት ውስጥ ጦር ይዘው ያዘመቱት 45 የደርግ አባላት ነበሩ። ጦርነቱ እስከሚያልቅ ድረስ ያዋጉት ግን
3 ብቻ ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ የ 69 ነኛ ብርጌድ አዛዡ ሻለቃ ኃይሌ መለሰና የዚሁ ብርጌድ 2 ኛ
ሻለቃ አዛዥ የነበሩት ሃምሳ አለቃ ጌታቸው ተቀባ ሲሆኑ፣ በአጋጣሚ ሁለቱም ከብሔራዊ ጦር ነበሩ።

5. ሻለቃ ኃይሌ መለሰ፦ የባህርዳር አውራጃ አስተዳዳሪ


ነሐሴ 1970 ላይ ሻለቃ ኃይሌ መለሰ የባህርዳር አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ።

10
ሻለቃ ኃሌ መለሰ ባህርዳር ለ 5 ዓመታት ብዙ ሕዝብ ጠቀም ሥራዎችን የሠሩት ብቻቸውን ሳይሆን
ባላቸው አስተዳደራዊ ጥበብ በከተማው ውስጥ የነበሩ ምሑራንን ከጎናቸው አሰልፈው በእነርሱ
ዕውቀትና ጉልበት በመጠቀም ነበር። በመሆኑም በ 5 ዓመታት የሥራ ዘመናቸው ውስጥ ከሠሯቸው ዋና
ዋና ሥራዎች ውስጥ፦
1. ባህርዳር ላይ የነጭ ሽብርና የቀይ ሽብር ተካሂዶ ስለነበር ሕዝቡ ተሸማቆ ነበር
የሚኖረው። የቀበሌ አብዮት ጥበቃዎች ዲሞትፈራቸውንና ቺኮዛቸውን
እንደታጠቁ መጠጥ ቤት በመግባት በሕዝብ ሥነልቡና ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ

11
ነበር። በመሆኑም የሻለቃ ኃይሌ የመጀመሪያው ሥራ እንዲህ ተደናግጦና
ተሸማቅቆ የነበረውን ሕዝብ አንፃራዊ ሠላም መስጠትና እፎይ እንዲል ማድረግ
ነበር። ለዚህም ማንም የአብዮት ጥበቃ አካል ጠመንጃ ታጥቆ ቡና ቤት
እንዳይገባና ለሥራም ቢሆን ከሌሊቱ 6 ሰዓት በፊት ጠመንጃ መያዝ እንደሌለበት
ጥብቅ ትዕዛዝ በመስጠት ለተጨነቀው ሕዝብ እፎይታን አመጡለት። ይህ ሥራ
በሕዝብ ይወደድ እንጅ እንደፈለጉ ሕዝብን እያስፈራሩ ነግሠው በነበሩ የቀበሌ
የአብዮት ጥበቃ ጓዶችና ካድሬዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም ነበር።

2. ሌላው ዋና ሥራ በከተማው ውስጥ የነበሩትን ሥራ አጦች በማሰባሰብ “አባይና


ጣና ራስ አገዝ ሠፈራ” በማቋቋም የሠሩት ሥራ ነው። በዚህ ፕሮግራም
ውስጥ የታቀፉት አባወራዎች ከ 450 እስከ 500 ይደርሱ ነበር። ለመሆኑ ለእነዚህ
ሰዎች ምን ተደረገላቸው?
ሀ/ አባይ ማዶ (ከቀበሌ 11 አለፍ ብሎ) የሠፈራ መንደር ተመሥርቶ ቤት
ለእያንዳንዳቸው ተሰጣቸው፣
ለ/ የቤተመንግሥት የአትክልት ቦታ የነበረውን እያለሙ ለከተማው ሕዝብ
አትክልት በማቅረብ እንዲጠቀሙ ተሰጣቸው፣
ሐ/ ምርታቸውን የሚያጓጉዙበት መለስተኛ የጭነት መኪና ከዕርዳታ ማስተባበሪያ
ኮሚሽን በሻለቃ ኃይሌ ጠያቂነት ተግኝቶ ተሰጣቸው፣
መ/ የክብር ዘበኛ የኪነት ቡድን ባህርዳር ላይ የተገኘበት የገንዘብ ማሰባሰቢያ
ባዛር ተዘጋጅቶ የመቋቋሚያ ገንዘብ ተሰባሰበላቸው።
3. በአጠቃላይ ባህርዳር በቆዩባቸው 5 ዓመታት ውስጡ ብዙ ሕዝብ ጠቀም የልማት
ሥራዎችን ሠርተው በ 1975 ዓ.ም. በሌ/ኮሎኔልነት ማዕረግ የሸዋ ክፍለ ሀገር
ወታደራዊ ኮሚሣር ሆነው ሲሾሙ በክብርና በፍቅር ተሸኝተዋል።

12
ሌ/ኮሎኔል ኃይሌ መለሰ በ 1975 ዓ.ም. የሸዋ ኮሚሣር ሆነው በመሾም ባህርዳርን ሲለቁ
ከባህርዳር ሕዝብ የተበረከተላቸውን ሽልማት የክፍለ ሀገሩ ኢሠፓ 1 ኛ ጸሐፊ የነበሩት
ሜ/ጄ/ ዘለቀ በየነ ሲያበረክቱላቸው

6. ከሚያዚያ 1975 እስከ ግንቦት 1980 የሸዋ ክፍለ ሀገር ወታደራዊ ኮሚሣር
ሌ/ኮሎኔል ኃይሌ መለሰ በ 1975 ዓ.ም. የሸዋ ክ/ሀገር ኮሚሣር ሆነው ሲሾሙ አንድ ያልተለመደ ነገር
አደረጉ። መንግሥት ለሌሎቹ ባለስልጣናት እንደሚያደርገው ደረጃቸውን የሚመጥን አንድ ኪራዩ
በመንግሥት የሚከፈልና ያኔ ኪራዩ በወር 250 ብር የሆነ ቪላ ቤት ፈለገና እዚያ እንዲገቡ
ያመቻችላቸዋል። አስተዋዩና አርቆ አሳቢው ሌ/ኮሎኔል ኃይሌ ግን የጊዜው ምቾት ሳያታልላቸው
የወደፊቱን አርቆ በማየት “ወደፊት አንድ ነገር ብሆን ልጆቸ በጡረታየ ሊከፍሉት የሚችሉት ድሮ
በ 1969 ዓ.ም. ወደ ምሥራቅ ጦር ግንባር ስዘምት በአደራ ለዘመዶች ሰጥቼው የነበረ ቤት አለና እዚያ
እገባለሁ። ይህንን ግን አመሰግናለሁ፤ አልፈልገውም” ብለው መለሱ። በአደራ ሰጥተዋቸው የነበሩት
ሰዎች ደግሞ የራሳቸውን ቤት ሠርተው በማጠናቀቅ ላይ ስለነበሩ እስከሚወጡ አንድ ሰርቪስ ቤት
ሰጧቸው። ሌ/ኮሎኔል ኃይሌ 13 ቤተሰብ ይዘው ከዚያች ሰርቪስ ቤት ለአንድ ወር በትዕግሥት ጠብቀው
በወር 80 ብር ይከራይ ወደ ነበረውና በ 1969 በአደራ ሰጥተውት ወደ ነበረው በቀበሌ ሥር
ወደሚከራየው የጭቃ ቤታቸው ተመለሱ። እስከአሁን ድረስ ያ እኔ በሌለሁበት ጊዜ ቤተሰቤ በጡረታየ
ሊከፍሉት ወደሚችሉበት ቤት ነው መግባት የምፈልገው እንዳሉት ቤተሰባቸው ከ 1975 ዓ.ም. ጀምሮ
እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ እዚያች የቀበሌ ቤት ያለምንም የኪራይ ጫና ይኖራሉ። እዚያ መንግሥት
መርጦላቸው ከነበረው በኪራይ ቤቶች ድርጅት ሥር ወደነበረው ቪላ ቤት ገብተው ቢሆን ኖሮ የደርግ
መንግሥት በ 1983 ከስልጣን ሲወርድ የቤተሰቡ እጣ ፈንታ ምን ይሆን ነበር? ቤቱ የኪቤአድ ቤት
ስለነበር በቀጥታ ኪቤአድ ያስወጣቸው ነበር። ከዚያ በኋላ የቀበሌ ቤት ማግኘት ስለማይችሉ የግለሰብ
ቤት እየተከራዩ በዘመኑ የማይቀመስ የቤት ኪራይ ይሰቃዩ ነበር። በአርቆ አስተዋይነታቸውና ለምቾት
ቦታ የማይሰጡ ልዩ ሰው በመሆናቸው፣ ቤተሰባቸውን ይሄውና ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ከማይቀመሰው
የቤት ኪራይ ጫና ታድገዋቸዋል።

ሳይፈልጉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት አቋርጠውት የነበረውንና የሚወዱትን ትምህርታቸውን ከ 6-8


ካዛንቺስ በሚገኘው ምሥራቅ ጎሕ፣ ክ 8-11 ደግሞ ካቴድራል ትምህርት ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ
በመከታተል አጠናቀዋል።

13
ለአምስት ዓመታት በሽዋ ክ/ሀገር ኮሚሣርነት ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ካገለገሉ በኋላ በግንቦት ወር
1980 ዓ.ም. የትግራይ አማፂያን (ሕዎሓት) ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር በተቃረበት ሰዓት
የኢትዮጵያ መንግሥት ሻምበል ለገሰ አስፋውን የትግራይ ክ/ሀገር ራስ ገዝ አስተዳደር የበላይ
አስተዳዳሪ አድርጎ ሲሾም ኮሎኔል ኃይሌን ደግሞ የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ በመስጠት የትግራይ

ክፍለ ሀገር ራስ ገዝ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾማቸው።

ኮሎኔል ኃይሌ መለሰና ቤተሰባቸው በወር 80 ብር ከተከራዩት የቀበሌ የጭቃ ቤታቸው ጋር።

14
ኮሎኔል ኃይሌ መለሰ የሸዋ ኮሚሣሪያትን የሥራ አፈፃፀም ሁኔታ በቻርት አስደግፈው በመግለፅ ላይ
እያሉ

7. ከግንቦት 1980 አስከ ታህሣስ 1981 (ለ 8 ወራት) የትግራይ ክፍለሀገር አስተዳዳሪ


ሰው የሚፈለገው የጨነቀለት ነውና ትግራይ ውጥረት ላይ ባለችበት ሰዓት ኮሎኔል ኃይሌ በግንቦት ወር
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እቤታቸው እያሉ ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም አንድ አስቸኳይ ደብዳቤ
በቤተመንግሥት ተላላኪ አማካኝነት መጣላቸው። ደብዳቤውን ከፍተው ሲያነቡት በብርጋዴር
ጄኔራልነት ማዕረግ የትግራይ ራስ ገዝ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል የሚል ነበር።
ያልጠበቁት ሹመት ነበር። አጠገባቸው የነበሩት የቤተሰብ አባላት “ምንድ ነው?” ሲሏቸው ሁልጊዜም
ትሁት ናቸውና፦ “ኃላፊነቱን መወጣት ከቻልኩ በብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ የትግራይ ራስ ገዝ ዋና
አስተዳዳሪ ሆኜ ተሹሜያለሁ” አሏቸው።
ብ/ጄኔራል ኃይሌ የትግራይ ራስ ገዝ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በተሾሙበት ሰዓት አብዛኛው
የትግራይ አውራጃዎች በወያኔ ተይዘው የነበረበት ጊዜ ነው። በመሆኑም ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ በሕይወት
ካልተመልስኩ ብለው በማሰብ ቤተሰቦቻቸውን ሲሰናበቱ ለልጆቻቸው እንዲህ ብለው ተናዘዙ፦

“በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክ/ሀገር ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ከመቀሌ በስተቀር


አብዛኛው ቦታዎች በወያኔዎች ሥር ናቸው። በመሆኑም ልመለስም፣ ላልመለስም
እችላልሁ። ስለዚህ ልጆቼ የመጨረሻ ቃሌን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ። ልጆቼ
ከአባታችሁ የቤት ውርስ ጠብቃችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል፤ ቤት የለኝም። መኪና

15
ጠብቃችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል፤ መኪናም የለኝም። ገንዘብም ጠብቃችሁ ከሆነ
ተሳስታችኋል፤ ገንዘብ የለኝም።

ይሁን እንጅ እኔ ላወርሳችሁ የምችለው ሁለት ጥሩ ነገሮች አሉኝ። እነርሱም፦


1. የዚያ የሌባ ልጅ የማያስብላችሁና ምንጊዜም አንገታችሁን ቀና ብላችሁ
እንድትሄዱ የሚያስችላችሁ ፍፁም ያልተጉደፈደፈ ሰብዕናየን እና
2. እየተዘዋወርኩ በሠራሁባቸው ቦታዎች ሁሉ የያዝኳቸውንና ወደፊትም
ሁኔታውና አቅሜ በፈቀደ መጠን የምይዛቸውን ማስታዎሻዎች ናቸው”
አሏቸው።

ብ/ጄ/ ኃይሌ መለሰ የትግራይ ክ/ሀገር ዋና አስተዳዳሪ በክ/ሀገሩ የኢሠፓ ስብሰባ ላይ እያሉ

ምንም እንኳን ጊዜው የጦርነትና የወከባ ቢሆንምና ለአጭር ጊዜ ቢቆዩም ለትግራይ ሕዝብ
የሚገባውን ፍትሃዊ አስተዳደር ለመስጠት እንደሞከሩ አብረዋቸው የሠሩት የአካባቢው ተወላጆች
ይመሠክሩላቸዋል። ብ/ጄ/ ኃይሌ ትግራይ ለ 8 ወራት ከሠሩ በኋላ የደቡብ ጎንደር ክ/ሀገር የኢሠፓ
አንደኛ ጸሐፊ ሆነው በጥር ወር 1981 ዓ.ም. ተሾሙ።

8. ከጥር 15 ቀን 1981 እስከ የካቲት 1983 የደቡብ ጎንደር ኢሠፓ 1 ኛ ጸሐፊ

16
የኢሕዲሪ መንግሥት 14 ክፍላተ ሀገራት የነበረውን የሀገሪቱን አስተዳደር ወደ 30 ሲያሳድግ ጄኔራል
ኃይሌ መለሰም የትውልድ ክልላቸው ደቡብ ጎንደር የኢሠፓ 1 ኛ ጸሐፊ ሆነው ተሾሙና የካቲት 15 ቀን
1981 ዓ.ም. ሥራ ጀመሩ። በመንደር ምሥረታና በእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት ኢፍትሃዊ አሠራር
የተማረረውና ልቡ የሸፈተው ሕዝብ አሁን ባለቀ ሰዓት ለምን መጣህብን አላቸው። ሩኅሩሁና የፍትህ
ሰው የሆኑት ጄኔራል ኃይሌ የአካባቢው ሰላም ማጣት ለሕዝባቸው ማድረግ በሚፈልጉት መጠን
ባያደርጉለትም፣ በተለይ ግን በመንደር ምሥረታውና የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት ይፈጠሩ የነበሩ
ችግሮችን ለመቅረፍ ሞክረዋል።
ጄኔራል ኃይሌ በአንፃራዊ ሁኔታ በሰላም ደቡብ ጎንደርን ያስተዳደሩት ለ 19 ቀናት ማለትም ከጥር 15
ቀን እስከ የካቲት 4 ቀን 1981 ዓ.ም. ብቻ ነበር። የካቲት 4 ቀን 1981 ዓ.ም. ጋይንት አውራጃ ውስጥ
የትውውቅ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ እያሉ የወያኔ ቃኝ ጦር ተከዜን ተሻግሮ መና መቀጠዋ
ውስጥ መታየቱን መረጃ ደረሳቸው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ከመና መቀጣዋ አልፈው ይበልጥ ወደ
ደብረታቦር በመቅረብ የካቲት 19 ቀን 1981 ዓ.ም. ከደብረ ታቦር 25 ኪሎሜትር ርቃ ከምትገኝ አይዴ
ማሪያም ከምትባል ቦታ ድረስ መጥተው የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማህበር ንብረት የሆኑ 18 በሬዎች
እና 60 በጎችን ዘርፈው ሄዱ።
ጄ/ኃይሌ በሦስት ሳምንት ውስጥ 3,500 (ሦስት ሺህ አምስት መቶ) ሕዝባዊ ሠራዊትና ባለግል
መሣሪያዎችን አዘጋጅተው አካባቢውን ከወንበዴዎች ለማፅዳት በሦስት አቅጣጫ ማለትም በዕብናት፣
ፊት ለፊት በሐሙስ ወንዝና ከምሥራቅ አቅጣጫ በመና በኩል ጦር በመላክ ተከዜን ተሻግሮ
መቀጠዋ ላይ ሠፍሮ የነበረውን የወያኔ ጦር ድባቅ መቱት።
የወያኔ ጦር ሰሜን ወሎን ከተቆጣጠረ በኋላ የጋይንት አውራጃን ዋና ከተማ ነፋስ መውጫን ለመያዝና
ክዚያም አልፎ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለውን ጉናን ለመቆጣጠር አልሞ ቢመጣም ጀግናው የጋይንት
ሕዝብ 18 ቀን ያለማቋረጥ በጀግንነት ተዋግቶ ጨጭሆ ላይ እንዲገታ ስላደረገው መሥከረም 11 ቀን
1982 ዓ.ም. ጨጭሆን ተቆጣጠረና እዚያ ላይ መሸገ። ጄኔራል ኃይሌም በክፍለ ሀገሩ ውስጥ የነበሩ
የተወሰኑ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶችን ይዘው በግንባር በመሰለፍና ሕዝቡን በማስተባበር ተዋግተዋል።
በፊት ተከዜን ተሻግሮ መቀጠዋ የገባውን የወያኔ ኃይል አይቀጡ ቅጣት በመቅጣታቸውና በኋላም
በጨጭሆ የመጣውን ኃይል ሕዝብን አስተባብረው ጨጭሆ ላይ ገድበው በማስቀረታቸው የተደሰቱት
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወዲያው የካቲት 25 ቀን 1981 ዓ.ም. “... የወንበዴዎቹን ወረራ
ለመግታት የአካባቢውን ሕዝብ ይዘው የሚያደርጉትን ትግል አደንቃለሁ። ወደፊትም የሕዝቡ ትግል
የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በመንግሥት በኩል የሚያስፈልግዎት ድጋፍ ሁሉ እንደሚሰጠዎት
ላረጋግጥ እወዳለሁ” የሚል የማበረታቻ የቴሌግራም መልዕክት ለጄኔራል ኃይሌ ላኩላቸው።
ከኮሎኔል መንግሥቱ ቴሌግራም በኋላ ሻለቃ ተካልኝ ባልቻ (በኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ የጠቅላላ
ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑ ባለስልጣን) ለጄኔራል ኃይሌ መለሰ ስልክ ደውለው ያሏቸው ግን ከኮሎኔል
መንግሥቱ ፍፁም ተቃራኒ ነበር። ከሰሜን ጎንደር ጠይቀው ባገኙት መረጃ መሠረት ደቡብ ጎንደር
ውስጥ በቂ መደበኛ ሠራዊት እንዳለና ያንን ይዘው መዋጋት እንዳለባቸው እንጅ ሌላ ጦር ወደ ክልሉ
እንዲመጣላቸው መጠየቅ እንደሌለባቸው የሚገልፅ ነበር። ሌላው ለጄኔራል ኃይሌ የተገለፀላቸው ወደ
ደቡብ ጎንደር የመጣው የወያኔ ኃይል ለማሳሳት የመጣ አነስተኛ ኃይል እንጅ ዋናው የወያኔ ሠራዊት
ወደ ደቡብ ጎንደር እንዳልመጣ ነው። በጉዳዩ ያዘኑት ጄኔራል ኃይሌ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ደቡብ
ጎንደር ተጨባጭ ሁኔታ መጠየቅ የነበረባቸው እርሳቸው እንጅ የሰሜን ጎንደር ባለስልጣናት ሊሆኑ
አይገባም ነበር ካሉ በኋላ፤ ደቡብ ጎንደር ውስጥ አንድም መደበኛ የኢትዮጵያ ወታደር እንደሌለ ገለፁ።
ግን የሚያዳምጣቸው አልነበረም። በዚያን ወቅት ሰሜን ጎንደር ውስጥ 3 እግረኛ ክፍለጦሮችና አንድ
ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ያለውጊያ ተቀምጦ ነበር። ከላይ እንደተገለፀው ደቡብ ጎንደር ግን እንኳን አንድ

17
ክፍለ ጦር አንድም መደበኛ ወታደር አልነበረም። በአንፃሩ ደግሞ ወያኔ ሰሜን ወሎን አጠቃላ ከያዘች
በኋላ ደቡብ ጎንደርን በመቆጣጠር ሰሜን ጎንደርን ወረታ ላይ ለመቁረጥ አቅዳ ጨርሳለች። ደቡብ
ጎንደር ውስጥ ስትራቴጂክ የሆነውን የጨጭሆን በር ከመስከረም 11 ቀን ጀምሮ ተቆጣጥራ ዋናውን
ወታደራዊ ግዥ መሬት ጉናን ለመያዝ ደግሞ እያኮበኮበች ነው።
ደቡብ ጎንደር ላይ በሀሰት “በቂ ኃይል አለ” ያሉ ሰዎች ወያኔ ያለምንም ኃይል ደቡብ ጎንደርን
እንዲቆጣጠርና ብሎም ወደ አዲስ አበባ በፍጥነት እንዲገሰግሥና የሀገሪቱን ውድቀት እንዲያፋጥን
አስተዋፅዖ አድርገዋል። ካርታ ማንበብ የሚችል አንድ ወታደራዊ ጠበብት ወያኔ ሰሜን ወሎን ከያዘ
በኋላ ተንደርድሮ ደቡብ ጎንደርን በመያዝ ሰሜን ጎንደርን ወረታ ላይ ይቆርጣል እንጅ እንደገና ወድኋላ
ሄዶ ሰሜን ጎንደር ላይ ኃይሉን ያባክናል ብሎ አይገምትም። ወያኔ በትክክል ያደረገውም ይሄንኑ ነው።
ያለ የሌለ ኃይሉን አስተባብሮ ደቡብ ጎንደርን ተቆጣጥሮ ሰሜን ጎንደርን ወረታ ላይ ቆረጣት።
መጨረሻ ላይ ጎንደር ከተማ የተያዘችው ባህርዳር ከተያዘች ከ 17/18 ቀን በኋላ ነው።
በማዕከላዊ መንግሥት ተስፋ ያልቆረጡት ጄነራል ኃይሌ 12 ሺህ ሕዝባዊ ሠራዊት አስለጥነው
ለማስታጠቅ መንግሥትን ትጥቅ እንዲልክላቸው ሲጠይቁ የተሰጣቸው መልስ፦ “መላ የጎንደርን
ሕዝብ አስታጥቀህ በመንግሥት ላይ ልታሳምፅ ነው ወይ?” የሚል ነበር። በሽታው ሥር ሳይሰድ
አስቀድሞ በቀላሉ መከላከል ሲቻል የወያኔ ኃይል ብዙውን የደቡብ ጎንደር ቦታ ከተቆጣጠረ በኋላ
ትናንት 12 ሺህ ሕዝባዊ ሠራዊት ለማስታጠቅ ፈቃደኛ ያልነበሩ የበላይ አመራሮች ጄኔራል ኃይሌን
ለ 25 ሺህ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚሆን መሣሪያ እንሰጥሃለን ውሰድና አስታጥቅ አሉት። እጅግ በጣም
የዘገየ ወሳኔ ነበር።
የኋላ ኋላ ( በ 1982 ) ወያኔ ኃይሉን ጉና ላይ ካጠናከረ በኋላ 603 ኛ ኮር የማዘዣ ጣቢያውን ከጎንደር
ወደ ደብረታቦር አዞረና እየሱስ ተራራ ላይ አደረገ። ታኅሣስ 16 ቀን ጄኔራል ኃይሌ የየአውራጃዎቹን
ሕዝባዊ ሠራዊት ጦር በየምድብ ግንባራቸው እየተዘዋወሩ ሲጎበኙና ሲያነቃቁ ውለው ለምሳ እቤት
ሲገቡ የታናሽ እህታቸው ልጅ ከገጠር መጥታ እርሷ በምትኖርበት አካባቢ (ደህረይና እየሱስ) ከፍተኛ
የወያኔ ሠራዊት ሲያልፍ እንዳየች ነገረቻቸው። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ አባቷ አቶ ጋሸው አሰፋ
ደብረ ታቦር ከጄኔራል ጋር ስንብቶ ሲመለስ እርሱም እጅግ ከፍተኛ ሠራዊት እንዳዬ ተናገረ። ይህ
አባትና ልጅ የሚገልፁት ጦር ከጉና ተነስቶ ደብረታቦርን ወደ ግራ በመተው ሊማዶ ማሪያም ወደ
ተባለች ቦታና ወደ ሰሜናዊ ምዕራብ አቅጣጫ እየተጓዘ ነው። በግመልና በጋማ ከብቶች ከባድ
መሣሪያዎችን ጭኗል። ወዲያው ደግሞ አንድ ዋለ ዳምጤ የተባለ የገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር ከፍተኛ
የወያኔ ጦር ከጉና ተነስቶ ደብረታቦርን ወደቀኝ እየተወ ወደግራሪያ እየተጓዘ እንደሆነ ለጄኔራል ኃይሌ
ሪፖርት ያደርጋል። ጄኔራል ኃይሌ እነዚህን ሁለት ሰዎች (ሲቷን በመተው) ያዩትን እንዲያስረዱ እየሱስ
ተራራ ላይ ወደአለው ወታደራዊ ማዘዥ ጣቢያ (Command Post) ወሰዷቸው። የኮሩ አዛዥ
አልነበሩም። የነበረው የ 603 ኛ ኮር የወታደራዊ ደህንነት ሃላፊ ሻለቃ ነበር። ይህ የወታደራዊ ደህንነት
ሃላፊ ሻለቃ ከድንኳኑ ወስጥ ነበር። ጄኔራል ኃይሌ ሻለቃው መጥቶ እንዲያናግራቸው አንዱን
አጃቢያቸውን ላኩበት። “አሁን አስቸኳይ ሪፖርት እየጻፍኩ ነው፤ አልመጣም” የሚል ምላሽ ሰጠ።
አስቸኳይ ወታደራዊ መረጃ እንዳላቸውና መጥቶ እንዲያናግራቸው አሁንም ላኩበት። አሁንም
አልመጣም። በዚህ ላይ እንዳሉ የኮሩ የፖለቲካ ሃላፊ የሆነው ኮሎኔል መጣ። ጄኔራል ኃይሌ ከሁለቱም
ሰዎች የሰሙትን ነገሩት። ኮሎኔሉ ይሄ ሊታመን የማይችል ወሬ ነው። ፋርጣ ቁስቋምንና ደረሂናን
እንዲጠብቅ 11 ኛ ብርጌድን እዚያ አስቀምጫለሁና ስጋት ሊገባን አይገባም። ምናልባት አንተም ያየኸው
የወገንን ጦር ሊሆን ይችላል ብሎ የአቶ ጋሻውን መረጃ አጣጣለው። አቶ ጋሻው ግን በትክክል ያየሁት
የወያኔን ጦር ነው። በትግርኛም እየጨፈሩ ወደሊማዶ ሲሄዱ አይቻለሁ አለ። ምን ያህል ይሆናል
ሲባል አቶ ጋሻው፣ ከ 2500 እስከ 3000 ይሆናል አለ። የአቶ ጋሻውን የዓይን ምሥክርነት አምኖ መቀበል
ሲገባው የኮሩ የፖለቲካ ክፍል ሃላፊው ኮሎኔል ቁጥሩን እንዴት ልትቆጥረው ቻልክ ብሎ ሊያፋጥጠውና

18
ሊያጣጥለው ሞከረ። በአቶ ዋለ ዳምጤ አማካኝነት በግራሪያ በኩል የመጣውንም መረጃ እንዲሁ
መቀበል አልፈለገም። ሁለቱንም እንደዚያ አጣጥሏቸው ወደ ድንኳኑ ሄዶ ገባ።
ኮሎኔሉ ገበሬዎቹን እያነጋገረ ባለበት ሰዓት ጀግናው ጄኔራ ኃይሌ ወታደራዊ ስሌት በመሥራት “ይህ
ደብረ ታቦርን ወደግራ ትቶ ወደሰሜን ምዕራብ ሄደ የተባለ ጦር አጥብቦ ከቆረጠን በሊማዶ አድርጎ
የእርብን ወንዝ በመሻገር በአየር ማረፊያና በሰላምኮ ጊዮርጊስ በኩል ይመጣል። አስፍቶ ከቆረጠን
ደግሞ አለምሳጋና አመድበር ላይ ይቆርጠናል” አሉና የጦር ሜዳ መነፅራቸውን ወደ አየር ማረፊያ
ሲደቅኑ ከእርብ ወንዝ እየተርመሰመሰ የሚወጣ ወታደር ያያሉ። ዓይናቸውን ማመን አቅቷቸው
ኮሎኔሉን በማስጠራትና ያዩትን እንዲያይ በማድረግ የማን ጦር እንደሆነ ጠየቁት። የወያኔ ጦር መሆን
አለበት ሲሉት፣ ኮሎኔሉ ግን “በፍፁም ይሄ የወገን ጦር ነው” አለ። በዚህ ሰዓት ቅድም ሲጠራ
አልመጣም ብሎ የነበረው የኮሩ ወታደራዊ ደህንነት ሃላፊ ሻለቃም መጣና “ይህ የወገን ጦር ነው”
አለ። ጄኔራል ኃይሌም ለኮሎኔሉ “እዚያ ያስቀመጥከው ጦር አለህ?” አሉት። እርሱም ከአሰብ ትናንትና
የገባው ሜካናይዝድ ጦር መሆን አለበት አለ። እርሱ ከሆነ ታዲያ ለምን ከወንዝ ይወጣል ሲሉት
ልብሱን ሊያጥብ ሄዶ እየተመለሰ ይሆናል አለ። በሬዲዮ አግኘውና የወገን ጦር መሆኑን አረጋግጥ
ሲሉት ገና አዲስ የመጣ ስለሆነ የመገናኛ ኮድ አልተለዋወጥንምና በአካል ሄጄ ላረጋግጥ ብሎ ኮሎኔሉ
ሄደ።
ሆኖም ግን ኮሎኔሉ አየር ማረፊያ ከመድረሱ በፊት በሁለቱም መኮንኖች “የወገን ጦር ነው”
የተባለው ጦር ተኩስ ከፍቶ ግስጋሴውን ወደከተማው አደረገው። ኮሎኔሉም ወዲያው ተመለሰ። ወደ
ግራሪያ አለፈ የተባለውም የወያኔ ጦር ከኮማንድ ፖስቱ ጀርባ ተኩስ ከፈተ። በጉና ግንባርም እንዲሁ።
የወያኔ ዓላማ አስቀድማ ኮማንድ ፖስቱን በመምታት ጉና ግንባር ላይ ያለው ጦር ያለአስተባባሪ
እንዲበተን ነበር።
ሁለት የጦር ጄቶችና ሁለት ሄሊኮፕተሮች ተጠርተው ድብደባ ጀመሩ። ግን እየመሸ ስለነበር ብዙ
አልቀጠሉም። በዚህ ሰዓት የኮሩ አዛዥ ጎንደር ስብሰባ ዋልኩ ብለው በሄሊኮፕተር እየሱስ ተራራ ላይ
አረፉ። ሁኔታው ተገለፀላቸው። እርሳቸው ግን ነገሩ አቃልለው በማየት፦ “ወያኔ ዛሬ አለቀላት ማለት
ነው። ኤም አሥራ አራቴን አምጣ፤ አንድ በአንድ እለቅማታለሁ” አሉ። የማይሆን ነገር። ጄኔራል
ኃይሌ ግን ሰሚ ባያገኙም የሚከተለውን ምክረ - ሃሳብ ሰጡ፦
1. ወያኔዎች አስቀድመው የኮሩን ማዘዣ ጣቢያ በመምታት ግንባር ላይ ካለው ጦር
ጋር ግንኙነት እንድናቋርጥ ነው ያቀዱት። ስለዚህ በፍጥነት ማዘዣ ጣቢያ
(ኮማንድ ፖስት) እንቀይር።
2. በእስቴ ግንባር ያለው ጦር ወደ እኛ ይምጣና በግራሪያ በኩል ከመጣው የወያኔ
ጥር ጋር ይፋለም፤
3. በጉና ግንባር ካለ ከፍተኛ ጦር ውስጥ የተወሰነ ኃይል ወደኋላ ይመለስና ከተማ
ውስጥ ከገባው የወያኔ ሠራዊት ጋር በመፋለም ከተማውን ከመያዝ ያድን። ወያኔ
ብዙ ኃይል የላከችው በከተማዋ ግራና ቀኝ እንጅ ፊት ለፊት ከማደናገሪያ ኃይል
ውጭ ብዙ ኃይል አይኖራትም። የእኛ ጦር ደግሞ የተከማቸው ፊት ለፊት በጉና
ግንባር ነው። ከዚህ ኃይል ውስጥ የተወሰነ ኃይል ወደ ከተማው ይመለስና
በከተማው ዙሪያ ካለው ሕዝባዊ ሠራዊትና ሌላው ጦር ጋር ተባብሮ ከተማውን
ከመያዝ ያድን ብለው ወተወቱ። ግን ማን ሰምቷቸው።
ለዚህ ድንቅ ወታደራዊ ምክረ - ሃሳብ የኮሩ አዛዥ የሰጡት ምላሽ፦ “ኃይሌ በእኔ ይሁንብህ፤
ወያኔ አሁን በቃ ያልቅላታል፤ ምንም አይመጣም ጫማህን አውልቅና ተኛ” አሉና ወደ
ድንኳናቸው ሄዱ። ኮሩ ያንን ያክል ጊዜ እየሱስ ተራራ ላይ ሲቆይ ምንም የሠራው ምሽግ
አልነበረም። የኮሩ የፖለቲካ ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል በተገኘው ተፈጥሯዊ ምሽግ በድንጋዩም

19
በቁጥቋጦውም ሥር ምሽግ ማስያዝ ጀመሩ። የጄኔራል ኃይሌ አጃቢዎች ጄኔራል ኃይሌን መሃል
አድርገው በሰሜን በኩል ምሽግ ያዙ። ኮሎኔሉ የክልሉን ሲቪል ከፍተኛ አመራሮች (የፓርቲና
የአስተዳደር) እንደ ወታደሩ ሁሉ የመከላከያ ወረዳ ሰጥተው “እዚህ ሁናችሁ ተከላከሉ”
አሏቸው። ይህንን ያዩት አስተዋዩና ሩህሩሁ ጄኔራል ኃይሌ ግን እነዚህን ሲቪል አመራሮች
እራሳቸው ሄደው በሦስት ዙር ግንብ ከታጠረው የእየሱስ ቤተክርስቲያን ከውስጠኛው ግንብ ውስጥ
ሆነው እንዲከላከሉ ቦታ ሰጧቸው።
ጄኔራል ኃይሌ በወቅቱ (ጊዜ በነበራቸው ሰዓት) “ማዘዣ ጣቢያ እንቀይር” ሲሉ አልሰማም ያሉት
የኮሩ አዛዥ ማዘዣ ጣቢያው በተኩስ ሲናጥ ማዘዣ ጣቢያ እንቀይር አሉ። አሁን ደግሞ እምቢ
ባዩ ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ሆኑ። “በዚህ ሰአት ማዘዣ ጣቢያ ለመቀየር ዘግይተናል። አሁን ማድረግ
ያለብን እዚሁ ምሽጋችንን አጠናክረን መከላክል ብቻ ነው” ብለው እምቢ አሉ። ሁሉም ተረባርቦ
ጄኔራል ኃይሌን ለማሳመን ጥረት አደረገ። ጄኔራል ኃይሌ እንዲህ ከዘገዩ በኋላ ቦታ መልቀቁን
ባያምኑበትም ለብዙኃኑ ሲሉ እየመረራቸውም ቢሆን ተስማሙና ማዘዣ ጣቢያ ለመቀየር ወይም
ለመሸሽ ንቅናቄ ተጀመረ።
ሆኖም ግን መውረጃ በሮቹ የተኩስ ዒላማ ውስጥ ገብተው እየተተኮሰባቸው ስለነበር ያለው
አማራጭ በምዕራባዊ ደቡብ መሞከር ነበር። ነገር ግን ይህ አቅጣጫ ደግሞ መውረጃ መንገድ
የሌለው አደገኛ ገደል ነበርና ብዙ ሰው ገደል እየገባ አለቀ። በዚህም ምክንያት ጨለማው ገፍፎ
ትንሽ የብርሃን ወጋገን እስከሚታይ ድረስ የሆነ ቦታ ላይ ጥግ ይዘው ቆይተው አንድ አካባቢውን
ያውቃል በተባለ የግብርና ሠራተኛ መሪነት ገደሉን እየቧጠጡና እርስ በእርስ እየተደጋገፉ ወርደው
ረባዳው ቦታ ላይ ደረሱ። ጉዞ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሆነ። ጠዋት ከወህኒ ፖሊስ ጀርባ ግርቢ
አካባቢ እንደደረሱ ጄነራል ኃይሌን የሚያውቁ ገበሬዎች ከየቤታቸው እንጀራውንና ጠላውን
በማምጣት አስተናገዷቸው። ከዚያ ቁርስ በኋላ ሄሊኮፕተር ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ይዛ ለመሄድ
አረፈች። ጄኔራል ኃይሌም አብረው ገቡ። ሄሊኮፕተሯ ወረታ ስትደርስ ግን ሞገደኛውና የመርህ
ሰው የሆኑት ጄኔራል ኃይሌ እዚህ ወረታ አውርዱኝ ብለው ወርደው ሕዝብ ማስተባበር ጀመሩ።
የኮሩ አዛዥ ግን በሄሊኮፕተሯ ወደ ጎንደር ሄዱ።
ሐሙሲት ላይ የማዘዣ ጣቢያ ተቋቁሞ የጄኔራል ማደሪያ እዚያ ሆነ። የኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊው
ማለትም የፓርቲ ሥራ ወይም የሲቪል ሥራ እንጅ ጦሩን የማዘዝ ስልጣንም ሆነ መበት የሌላቸው
ጄኔራል ኃይሌ ቀን ከወረታ ሐሙሲት እየተዘዋወሩ ሕዝብ ሲያስተባብሩ እየዋሉ ሌሊት ደግሞ
(ድንኳን ስለሌላቸው) መኪናቸው ውስጥ ያድሩ ነበር። አጃቢዎቻቸው ደግሞ መኪናቸውን ከበው
ባዶ መሬት ላይ ያድሩ ነበር። የኮሩ አዛዥ ጄኔራል ግን ባህርዳር እየሄዱ ጣና ሆቴል ነበር
የሚያድሩት።
በዚህ ሁኔታ ለ 11 ቀናት ከተቆየ በኋላ፣ መንግሥትም ከኤርትራ ጥሩ ልምድ ያለውን 15 ኛ ነብሮ
ክፍለጦርን፣ ከሌላ ቦታ ደግሞ የስፓርታ ጦር ሦስት ብርጌዶችን በማምጣት የመልሶ ማጥቃት
እርምጃ ወሰደ። ወያኔ ወረታ አካባቢ በነበረው የስፓርታ ጦር ላይ በአንድ ሌሊት ብቻ 25 ጊዜ
ማጥቃት ሰንዘረች። ስፓርታ ግን የሚበገር አልሆነላትም። 15 ኛ ነብሮ ክፍለጦርም ኤርትራ ውስጥ
ያለውን ልምድ በመጠቀም ለወያኔ የቆረጣ ውጊያ አልተመቸም፤ ስትቆርጠው አዙሮ እየቆረጠ
ወገብ ዛላዋን ቆረጣት። የወያኔ ጦር የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ። በእስቴና ግራሪያ ግንባር 7 ኛ
ክ/ጦር፣ ፊት ለፊት በአመድበርና በአለምሳጋ ግንባር የስፓርታ ጦርና 15 ኛ ነብሮ ክ/ጦር፣ በውዶ እና
በእርብ ግንባር 25 ኛ ክ/ጦር መፈናፈኛ ሲያሳጡት አየር ኃይል ደግሞ ከአየር ላይ እሣት ያወርድበት
ነበር። ይህንን የመሰለውን የተቀነባበረ ምት መቋቋም ያልቻለው የወያኔ ጦር በታሪኩ ለመጀመሪያ
ጊዜ ያለ ትዕዛዝ በየአቅጣጨው ነፍሴ አውጭኝ ብሎ እንዲያፈገፍግ ተገደደ። የወገን ጦርም መልሶ
ደብረታቦርን ተቆጣጠረ። ጦሩ ከተማውንና አካባቢውን እንደ ተቆጣጠረ ወዲያው ጥሪ ተደረገና

20
ጄኔራል ኃይሌ ቴዎድሮስ አደባባይ ለሕዝብ ንግግር አደረጉ። ሕዝቡን ፀንቶ በመታገሉ አመስግነው፣
አሁንም እስከ መጨረሻው ድል እንዲታገል ጥሪ አቀረቡ። ያለዕቅድና ትዕዛዝ በየአቅጣጫው
የሚሸሸውን የወያኔ ሠራዊት አሳድዶ በመያዝ እጁን ለመንግሥት ሲያስረክብ፣ መሣሪያውን ደግሞ
ለራሱ እንደሚሸልሙት ቃል ገቡለት። በዚህ ንግግር የተበረታታው ወጣትና የአካባቢው ገበሬ
ያለዕቅድ እግሬ አውጭኝ እያለ የሚፈረጥጠውን የወያኔ ሠራዊት በገፍ እየማረከ ወደ ደብረታቦር
ሲያመጣ ቃል በተገባለት መሠረት መሣሪያውን ለእራሱ እንዲያደርግ ተመረቀለት።
ደብረታቦር እንደተለቀቀች የጄኔራል ኃይሌ ቢሮ ውስጥ ጠረጴዛቸውን አልብሶት የተገኘው የወያኔዎችን
የዘመቻ ዕቅድ የሚያሳይ ካርታና የመጠቀሚያ የሚስጥር ቃሎችን አጠቃልሎ የያዘ ሰነድ ነበር።
ሁለቱም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የመረጃ ሠነዶች ለወገን ኃይል የሚሰጧቸው ብዙ ጠቀሜታዎች
ነበሩባቸው። ሠነዶቹ፦
 የፊት ለፊትና የደጀን ኃይላቸው ብዛትና አቀማመጥ፣
 የአጋዥ መሣሪያዎች ዓይነትና አቀማመጥ፣
 የማጥቂያ ስልታቸውና የሚጠቀሙበት መሬት (አቅጣጫ)፣
 የጊዜ ሰሌዳና የሚያካትተው ድርጊት፣
 ወታደራዊ የመገናኛ መሣሪያዎች፣ የሚስጥር ቃሎችና ምልክቶች፣
 ውጊያውን ወደፊት ለመቀጠል ያላቸው የድርጅታዊ ብቃት ወ.ዘ.ተ. የሚገልፁ ጠቃሚ
ወታደራዊ መረጃዎችን
እንኳን ሳይይዙ ያለትዕዛዝና ቁጥጥር ተበትነዋል። አዛዡም ሆነ ረዳቶቹ የሚመሩትን ጦር ማስተባበር ቀርቶ በእጃቸው
አንጠልጥለው ለመሮጥ የሚችሉትን ያን የመሰለ ከፍተኛ የሚስጥር ሠነድ እንኳን ለመያዝ ፋታ አጥተው ሁሉም በተናጠል
ነፍሴ አውጭኝ ብለው እንደሮጡ የሚያረጋግጥ መረጃ ነበር። ጄኔራል ኃይሌም የመረጃዎቹን ወታደራዊ ጠቀሜታ በመረዳት
ፈጥነው እንዲጠቀሙባቸው ለብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ ሲልኩ፣ ለኮሩም አዛዦች አሳውቀዋቸው ነበር። እነርሱ
ግን ያንን የመሰለ መረጃ መጠቀም ይቅርና ምን እንደሚመስል እንኳን ዘወር ብለው ያዩት አይመስሉም። ይህም ጄኔራል
ኃይሌን በጣም ካሳዘኑ ድርጊቶች አንዱ ነበር።
ምንም እንኳን በደብረታቦር ነፃ መውጣት ጄኔራል ኃይሌ በጣም ቢደሰቱም በሚከተሉት ነገሮች ግን
እጅግ በማዘናቸው የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች ደጋግመው ለሚመለከተው አካል አቀረቡ። ይሄውም
ከተማዋን ከወያኔ ነፃ ያደረገው ሠራዊት፦
1. ወያኔ እንደዚህ ያለዕቅድና ማዕከላዊ ትዕዛዝ በሚፈረጥጥበት ጊዜ የወገን ጦር
ሊያሳድደውና ወደፊት ገፍቶ የአካባቢው ገዥ መሬት የሆነውን የጉና ተራራንና
ከዚያም አልፎ በጣም ስትራቴጂካዊ የሆነቺውን የጨጭሆን በር እንዲይዝ ጥያቄ
አቀረቡ፤
2. ጦሩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጂቶችን መዝረፉን እንዲያቆም ጠየቁ።
3. ጦሩ በከተማው ሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን አሰቃቂና አስነዋሪ ድርጊት
እንዲያቆም አምርረው ጠየቁ።
እነዚህና መሰል ጥያቄዎችን ለኮሩ አዛዥ በተደጋጋሚ ከማቅረባቸውም በላይ ለጦሩ ኢታማዦር ሹምም
አቅርበው ነበር። የተሰጣቸው ምላሽ ግን የሚያሳዝን ነበር፤ “ጦር ባለበት ቦታ ሁሉ እንዲህ ዓይነት
ችግሮች የተለመዱ ናቸው” የሚል ምላሽ ነው። ጄኔራል ኃይሌ እንዳሉት ጦሩ ወደፊት ገፍቶ
እየተበታተነ የነበረውን የወያኔን ጦር መደምሰስ ሲገባው ከወር በላይ ሕዝብን እየረበሸ ከተማ ውስጥ
ተቀመጠ። “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንደሚባለው፣ ከጦሩ ጋር አብሮ ለተዋደቀውና ከወያኔ ጋር ደም
ለተቃባው የደብረታቦር ሕዝብ ይህንን የመሰለ ዘግናኝ፣ ኢሰብአዊና ከባህሉና ከሃይማኖቱ ውጭ የሆነ
ግፍ ሊፈፀምበት አይገባም ነበር። የኮሩ አዛዦች፣ ጦሩ ይህንን የመሰለ ዘግናኝ ግፍ በከተማው ላይ

21
እንዲፈፅም በማድረግ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ የፈለጉ ይመስል ነበር። አለበለዚያማ ጦሩን
መቆጣጠር እየቻሉ ለምን ከቁጥጥር ወጥቶ ሕዝብን ሲያስቸግር እንዳላየ ያዩት ነበር።
ምንም እንኳን ጄኔራል ኃይሌ ደጋግመው ወያኔ በተዳከመበት ሰዓት የእኛ ጦር እንዲያጠቃ
ቢወተውቱም ጦሩ ሕዝብን ከመረበሽ በስተቀር ምንም ውጊያ ሳያደርግ ከወር በላይ ተቀምጧል።
በአንፃሩ ወያኔ ግን ከሰሜን ጎንደር አሉላ የተባለውን ክፍለ ጦር አንድ ወር ሙሉ በእግር አጓጉዛ፣
ከደቡብ ወሎና ከሰሜን ሸዋም ጦር ቀንሳ በማምጣት ጉና ላይ የተበታተነባትን ጦር አጠናከረች። ይሄ
ብቻ አይደለም ወያኔ ያደረግችው። ደብረታቦር ላይ ክፉኛ የተመታው የወያኔ ሠራዊት እኛ
“እንድንዋጋ የተመለመልነው ትግራይን ነፃ ለማውጣት ነው። አሁን ግን እያለቅን ያለነው በሰው ሀገር
ነው። ትግራይን ነፃ በማውጣት ተልዕኳችንን ፈፅመናልና ከእንግዲህ ወዲያ አንዋጋም፤ በቃን” ብሎ
ብዙው ሠራዊቷ አመፆባት ነበር። እነመለስ የትግራይ ሽማግሌዎች እግር ላይ ወድቀው በመለመን
አሳመኑ። ሽማግሌዎችም የተበተነውን ጦሩ በየአካባቢው እየተዘዋወሩ በማሳመን ሞት አፋፍ ላይ ደርሶ
የነበረውን ወያኔ መልሶ እንዲያንሰራራ አደረጉት። ወያኔ በመፈርጠጥ ላይ እያለ የወገን ጦር እግር
በእግር ተከታትሎ ድባቅ መትቶት ቢሆን ኖሮ የወያኔ ኅልውና የሚያከትመው ያኔ በደብረታቦሩ ውጊያ
አይቀጡ ቅጣት ከደረሰበትና ያለ ትዕዛዝ ከፈረጠጠ በኋላ ነበር። ግን ከወያኔ ጋር ልዩ ስምምነት
ያላቸው የሚመስሉት የጦር መሪዎቻችን የጄኔራል ኃይሌን የእንዋጋ ውትወታ ሊሰሙ አልቻሉም።
በዚህ ድርጊት ሌት ተቀን ሲበግኑ የነበሩት ጄኔራል ኃይሌ የካቲት 7 ቀን 1982 ዓ.ም. አንድ ታላቅ መርዶ
ሰሙ። ኮሎኔል መንግሥቱ የኮሩን ከፍተኛ የጦር አመራሮች፣ የአካባቢውን የፓርቲ አንደኛ ጸሐፊዎችንና
የክፍላተ ሀገራት አስተዳዳሪዎችን ቤዛዊት ቤተመንግሥት (ባህርዳር) ስብሰባ ጠርተው ደብረታቦርን ነፃ
ለማውጣት ታላቁን ሚና የተጫወተውንና ወያኔን ያሽመደመዳትን 15 ኛ ነብሮ ክፍለጦርን ወደ ኤርትራ
(ያኔ ምፅዋ ተይዞ ስለነበር) አዛውሬዋለሁ አሉ። ጄኔራል ኃይሌ ይህንን ውሳኔያቸውን ለመቃዎም
እጃቸውን ደጋግመው ቢያነሱ (ኮ/ል መንግሥቱ ለምን እንደሆነ ገብቷቸዋልና) ዕድል ነፈጓቸው።
አስቀድሞም የጄኔራል ኃይሌን ቅስም ሰብሮ ዝም ለማሰኘት በሚመስል መልኩ ኮሎኔል መንግሥቱ፦
“እኔ ጎንደርን ከኤርትራ እኩል አላይም” አሉ። ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ዕድል የተነፈጉት
ቆፍጣናው ጄነራል ኃይሌም ተቃውሟቸውንና ንዴታቸውን ለመግለፅ ሲሉ ኮሎኔል መንግሥቱ
ኃይለማሪያም በጋበዙት የእራት ግብዣ ላይ አልገኝም ብለው ሳይሄዱ ቀሩ።
15 ኛ ነብሮ ክፍለጦር ወደ ኤርትራ ከተወሰደ በኋላና ወያኔም የጉና ተራራን በሰው ኃይልና በፈንጅ
ካጠናከረች በኋላ ፊት ለፊት ማጥቃት ተጀመረ። የማጥቃት እቅዱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት
ምንጊዜም ሰሚ የማያገኙት ጄኔራ ኃይሌ መለሰ የፊት ለፊት ማጥቃቱን ዘዴ ተቃውመው ነበር።
ምክንያቱም ወያኔ መሽጎ ያለው ወታደራዊ ገዥ መሬት ከሆነው ጉና ተራራ ላይ ነው። ለእኛ ከታች
ወደ ላይ ለማጥቃት በጣም ከባድ ነው። ከዚህ በፊት በዚሁ የፊት ለፊት ማጥቃት ስልት ሁለት ጊዜ
ተሞክሮ በእኛ ሽንፈት ተጠናቋል። አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ለምን እንደግመዋለን? ከዚያ ይልቅ፦
1. ከእስቴ ተነስቶ በጥናፋ በኩል ጉናን ከደቡብ መሥራቅ የሚመታ፣
2. በሐሙስ ወንዝ አልፎ በመና በኩል በመዞር ወደ ጋይንት በመውጣት ወያኔን ከኋላ መቁረጥ፣
3. ፊት ለፊት በክምር ድንጋይ አድርጎ ወያኔን ማስጨነቅ ይቻላል የሚል የውጊያ ዕቅድ አቀረቡ።
የኮሩ አዛዥ “ጦሬን እንዲህ አድርጌ በታትኜ አላስመታም” ብለው እምቢ አሉ። ሰብሳቢው
ኤታማዦር ሹሙ ሲሆኑ ሌሎችም ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ነበሩ። የጄኔራል ኃይሌን ዕቅድ አንድ
ጄኔራል ብቻ ሲደግፉት ሌሎቹ የኮሩን አዛዥ ዕቅድ ደገፉ። ኤታማዦር ሹሙም የኮሩን አዛዥ ዕቅድ
ደገፉና በኮሩ አዛዥ ዕቅድ መሠረት ፊት ለፊት ውጊያው ተጀመረ። ባለብሩህ አዕምሮው ጄኔራል ኃይሌ
ያሉት አልቀረም ወያኔዎቹ ገዥ መሬት ስለያዙና የወገን ጦር ደግሞ በቀላሉ ለመመታት አመች ወይም
ሙት መሬት ላይ ሆኖ ስለሆነ ውጊያ ውስጥ የገባው ማጥቃቱ በሽንፈት ተጠናቀቀ።

22
ወያኔዎች ጉና ላይ የተቃጣባቸውን ምት ካከሸፉ በኋላ ቀጣዩ ውጊያቸው መከላከል ሳይሆን ማጥቃት
ነበር። ደብረታቦርን ለሁለተኛ ጊዜ ለማያዝ በየካቲት 20 ቀን 1982 ማጥቃት ሰነዘሩ። የኮሩ አዛዥ
የኮሩን ከፍተኛ አመራሮች ሰብስበው ደብረታቦርን እንልቀቅ እና ወደ ኋላ እናፈግፍግ አሉ። ጄኔራል
ኃይሌም በአጋጣሚ ከኮሩ ማዘዣ ጣቢያው ተገኝተው ስለነበር “ይሄ ሁሉ ሠራዊት፣ ስንቅና ትጥቅ
እያለን፣ እንዴት ለቅቀን እንሸሻለን?” ብለው ተሟገቱ። የኮሩ ምክትል አዛዥም የጄኔራል ኃያሌን ሃሣብ
በመደገፍ፦ “ቢያንስ ለ 15 ቀን የሚበቃ ስንቅና ትጥቅ አለን። ስለዚህ ማፈግፈግ የለብንም” አሉና
ማፈግፈጉ ተሠረዘ። ሆኖም ግን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ባልታወቀ ሁኔታ የጦሩ የመሣሪያና የስንቅ
ማካማቻ ተቃጠለ። በእግዚአብሔር ተአምር ሆኖ ነው እንጅ የደብረታቦር ሕዝብ በዚያ ከፍተኛ
የመሣሪያ ማከማቻ ፍንዳታ ማለቅ ነበረበት። ወዲያው የመሣሪያ ዲፖው መቃጠሉን ያየ ሠራዊት
ሽሽት ጀመረ። ማዘዣ ጣቢያ ላይ የነበረውም ኃይል የኮሩን አዝዥ ጨምሮ ወዲያውኑ ሽሽት ጀመረ።
ሆኖም ግን ዓለምሳጋ ላይ የተበላሸ ታንክ መንገድ ዘግቶ አላሳልፍ ስላለ እና መኪኖችና ታንኮች ሁሉ
ሄደው ሄደው ስለተከማቹ ወያኔ ብዙ ሰው ፈጀ። ጦሩ እራሱን እንኳን እየተከላከለ ስልታዊ ማፈግፈግ
እንዲያደርግ አልተደረገምና በዙ ሰው አለቀ፤ ብዙ ንብረትም ወደመ።
ደብረታቦር ይያዝ እንጅ እብናት፣ አዲስ ዘመን፣ ፎገራና ደራ ስላልተያዘ ጄኔራል ኃይሌ ጽ/ቤታቸውን
ደራ ሐሙሲት ላይ አድርገው ባህርዳርና ሐሙሲት እያሉ ለአንድ ዓመት ሕዝቡን በማደራጀትና
ሕዝባዊ ሠራዊቱን በማጠናከር ላይ ታች ሲሉ ቆዩ። በዓመቱ የካቲት 1983 ዓ.ም. ወያኔ ቀሪውን የደቡብ
ጎንደር ግዛትና ባህርዳርን ለመያዝ ጦርነት ከፈተ። በዚህ ጦርነት በሐሙሲት ግንባር ላይ ጄኔራል ኃይሌ
4 ቦታ ላይ ቆሰሉ። ከእርሳቸው ጋር በአንድ ጂፕ መኪና የነበሩ ሁለት አጃቢዎቻቸው (የአጎታቸ ልጅ
የነበረው አሥር አለቃ መንግሥቱ በላይ እና ወታደር ፀጋየ) ተሰው። የሁለቱን አስከሬን ገብርኤል
ቤተክርስቲያን ከቀበሩ በኋላ ቤዛዊት ቤተመንግሥት ላይ የመልሶ መቋቋም አደረጉ። ከፍተኛ ጦርና
መኪና ግን አባይ ድልድይ ላይ እንዳያልፍ ታግዶ ተከማችቷል። ወያኔዎች ለወታደሮቻቸው ድልድዩ
ስለሚፈርስ እንዳይጠጉ ሲመክሩ የተጠለፈ የመገናኛ መልዕክት ያስረዳል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን
ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። በዚያ ሁኔታ እንዳለ የአባይ ድልድይ በፈንጅ ፈረሰና ብዙ ሰው
አለቀ። ብዙ አስከሬንም ውሃው ላይ ተንሳፍፎ ይታይ እንደነበር ጄኔራል ኃይሌ በማስታዎሻቸው ላይ
ከትበውታል።
እነ ጄኔራል ኃይሌም ከቤዛዊት ቤተመንግሥት በስተደቡብ (አባይ ሰፋ ብሎ በሚፈስበት ቦታ ላይ)
አባይን በእግራቸው ተሻግረው ወደ ባህርዳር ሄዱ። ባህርዳር ሲገቡ ሁሉም በየጎሬው ተሸጉጦና
የሚፈረጥጠውም ፈርጥጦ ማንንም ባለስልጣን አላገኙም። ሆኖም ግን ወያኔ በራሷ ምክንያት ባህርዳር
ባለመግባቷ የተደበቁት ባለስልጣናት በበነጋታው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። ጄኔራል ኃይሌም የመጀመሪያ
ህክምና እርዳታ ካገኙ በኋላ በቁርጥ ቀን ጓደኛቸው፣ ውለታው ተዘርዝሮ በማያልቀውና ለጄኔራል
ኃይሌ አድርጎ በማይረካው ዘሪሁን መኮንን አማካኝነት አቶ ተስፋሁን አበበ የሚባሉ ዘመድ የራሳቸውን
መኝታ ለቀውላቸው እንዲያድሩ ተደረገ። በበነጋታው የምዕራብ ጎጃም ፓርቲ ጽ/ቤት ሄደው እነ
በጋሻው አታላይንና የሰሜን ጎንደሩን አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው እንቁባህሪን አገኙ። ለሁለቱም ከዚህ
በፊት ያነሱላቸውን ምክረሃሳብ ደግመው አነሱላቸው። ምክረ - ሃሳቡም እንዲህ የሚል ነበር፦“ጉዳዩ
ተበላሽቷልና ወደሕዝባችን ገብተን እንሸፍት። በጋሻው ከዚህ በፊት የወሎ ቦረና ተወላጅ ነኝ
ብለኸኛል። ስለዚህ አንተ አሁን በኢልማና ዴንሣ አድርገህ ሞጣ አድርሰኝ። እኔ ደግሞ ስማዳ የአያቴ
ሀገር ስለሆነ በስማዳ አድርጌ ቦረና አሸጋግርሃለሁ። ሽፈራውም የትውልድ ሀገርህ በለሳ ስለሆነ በለሳ
ግባ። ከዚያ ግንኙነት እየፈጠርን የሽምቅ ውጊያ እናድርግ” ይሏቸዋል። ሁለቱም ይህንን ሃሳብ
አልተቀበሏቸውም።

በጋሻውና ሽፈራው የእንሸፍት ሃሳባቸውን ባይቀበሏቸውም፣ ቆፍጣናውና ቆራጡ ጄኔራል ኃይሌ ግን


ወደ ክልሌ ተመልሼ ከሕዝቤ ጋር ይህንን መከራ አብሬ እጋፈጣለሁ እንጅ በሰላም ጊዜ ሳስተዳድረው
ቆይቼ አሁን በችግር ጊዜ ብቻውን ትቼው አልሄድም ብለው ወደ ሕዝባቸው የሚመለሱበትን መነገድ

23
ማፈላለግ ይጀምራሉ። በጪስ አባይ በኩል ሞከሩ አልተሳካላቸውም። ቀበሌ 11 አንድ ሰው አግኝተው
አንድ ሺህ ብር እንደሚሰጡትና መንገድ ሊያመቻችላቸው ከተስማሙ በኋላ ጠፋባቸው። ወደ
ክልላቸው ደቡብ ጎንደር ለመመለስ እየባዘኑ እያለ እንደገና ሦስት ቦታ ላይ ይቆስላሉ። ከፊተኛው ጋር
7 ቦታ ላይ መቁሰላቸው ነው። በእግዚአብሔር ተዓምር ግን እነዚህ 7 ቦታዎች በሙሉ ሥጋ ለሥጋ
በመሄዳቸው ለጊዜው ከመቁሰል በስተቀር በሕይዎታቸውም ሆነ በአካላቸው ላይ ፍፁም ጉዳት
አላመጡም።
ከጄኔራል ኃይሌ በላይ ስልጣን የነበራቸውና ስልጣናቸውንና ሞያቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙበት
ሁኔታዎችን መለወጥ ይችሉ የነበሩት ቱባ -ቱባ ባለስልጣናት መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ፣
ከዚያም በላይ ትከሻቸው ላይ የጫኑትን ማዕረግ ትርጉምና ሃላፊነት በመዘንጋት ግማሹ ሄሊኮፕተር፣
ግማሹ ፓጀሮ፣ ሌላው ደግሞ ላንድ ክሩዘር በማስነሳት ወደ አዲስ አበባ እግሬ አውጪኝ አሉ።
ከእነዚህ ሁሉ ባለስልጣናት ይልቅ አዲስ አበባ ሄዶ ለመታክም ከበቂ በላይ ምክንያት የነበራቸው በ 7
ጥይት የቆሰሉት ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ነበሩ። ሆኖም ግን እኒህ ቆራጥ ጀግና፦ “ዳሩን ጠንክረን
ካልጠበቅነው፣ መሃሉ ዳር አይሆንም ያለው ማነው? በዚህ ዓይነት ሁኔታ አዲስ አበባስ አትደፈርም
ያለው ማነው? አዲስ አበባ ስትያዝስ ወዴት ነው የሚሸሸው? ይህ ትከሻየ ላይ የጫንኩት ማዕረግም
እጄን አንከርፍፌ ለጠላት እንድሰጥም ሆነ ሕዝቤን ለጠላት አጋልጨ ሰጥቼ እንድሸሽ አይፈቅድልኝም።
ከሁሉም በላይ ደግሞ እኒያ ጊዜ የማይሽራቸው የቆራጥነት ተምሳሌት የሆኑት ታላቁ ንጉሥ አፄ
ቴዎድሮስ ለጠላት እጅን አንከርፍፎ መስጠትን አላስተማሩኝም። ስለዚህ ከዚህ በኋላ በፍፁም ለሽሽት
እግሬን አላነሳም። በማንኛውም መልኩ አስተዳድረው ወደ ነበረው ሕዝቤ ተመልሼ ችግሩን
እካፈላለው። ቢችል ያግዘኝና ተጋግዘን ጠላታችንን እናሸንፋለን። ባይሳካልኝም እንደ እንቧይ
ከበቀልኩበት ምድር እረግፋለሁ እንጅ የትም አልሄድም” ብለው ወሰኑ።
እስክንድር ነጋም የሌሎች የደርግ አባላትን የመጨረሻ ሰዓት ውሳኔ ከጄኔራል ኃይሌ መለሰ ጋር
አወዳድሮ እ.አ.አ ታህሣሥ 24 ቀን 2010 ላይ በማህበራዊ መገናኛ የሚከተለውን ጽፎ ነበር፦

No amount of violence, however, was able to prevent the downfall of the


Derg. The end came after seventeen long years, in May 1991; ironically,
courtesy of not the political groupings it had feared but from the midst of
the political underdogs. Stunned by a defeat that was never supposed to
happen, Derg officials, whose larger than life reputations had become part
of the public legend, stood humbly in line to give themselves up to the
victors. No sight— before or since—amazed the public more. Only one of
the 109 members of the Derg, General Haile Melese, defied the new regime
by melting into his home region— rural Gonder—and trying to organize an
armed resistance. (Hampered by old age and lack of external support, he
was doomed almost from the start. He now lives in New Zealand. His valor,
however, still stands in sharp contrast to his comrades.)

ነፃ ትርጉም፦ ይሁን እንጅ፣ ምንም ዓይነት የጭካኔ መጠን የደርግን መውደቅ


ሊያስቀርው አልቻለም። የደርግ ሥርዓትም ከ 17 ዓመታት በኋላ በግንቦት ወር 1983
ዓ.ም. አበቃለት። የሚገርመው ነገር ደግሞ ደርግን ያሽነፉት የሚፈራቸው ሳይሆኑ፣
የሚንቃቸው/አልባሌ ኃይሎች መሆናቸው ነው። ይመጣል ብለው በጭራሽ
ባልጠበቁት ሽንፈት ነበር ክው ያሉት፣ እነዚያ ለሰማይ ለመሬት የከበዱ የደርግ
ሹማምንት፣ ላሽናፊወቻቸው እጃቻውን ለመስጠት ተረባረቡ። እንዲህ ያለ ውርደት
ከዚያ በፊትም ሆነ ወዲህ አይቶ ያማያውቀው ሕዝብ ጉድ አለ! አዲሶቹን ገዢዎች
ሳይቀር ባስደመመ መልኩ፣ ከአንድ መቶ ዘጠኙ የደርግ አባላት ተነጥለው፣ ጀነራል

24
ኃይሌ መለሰ የተስኙ ጀግና ብቻ አሻፈረኝ ብለው ጠላታችውን በትጥቅ ትግል
ለመፋለም፣ ወደ ትውልድ መንደራቸው ወደ ጎንደር በማቅናት፣ ዱር ቤቴ አሉ።
ይሁንና፣ ዕድሜያቸው በመግፋቱና የውጭ እርዳታም ባለማግኝታቸው፣ ገና ከጅምሩ
ውጥናቸው ሁሉ መና ሆኖ ቀረ። እኒህ ሰው ባሁኑ ሰአት ኑሯቸውን በኒውዚላንድ
አድርገዋል። ያም ሆኖ፣ ጀግንነታቸው ከሌሎቹ ጓዶቻችው በተለየ ሁኔታ ሲያንፀባርቅ
ይኖራል።

(እዚህ ላይ እስክንድር ከጠቀሳቸው የጄኔራል ኃይሌ ሁለት ችግሮች ውስጥ የውጭ ወይም የድርጅታዊ
ዕርዳታ አለማግኘት እንጅ የዕድሜ መግፋት ችግር አልነበረባቸውም። ያኔ ገና 50 ዓመታቸው ስለነበር
ለውጊያ የሚቸገሩ ሰው አልነበሩም። በሽፍትነት ዘመናቸውም ሰባቱንም የደቡብ ጎንደር አውራጃዎች
በእግራቸው እየተጓዙ ነበር ሲያደራጁ የቆዩት።)

ይህንን ቆራጥ ውሳኔ የወሰኑት አይበገሬው ጀግና የቴዎድሮስ ልጅ ደማቸውን እያዘሩ በእግራቸው
በቁንዝላ በኩል ተጉዘው ዘጌ ይገባሉ። ዘጌ ላይ በአንድ የተባረከና ሀገር ወዳድ በሆነ ቤተሰብ
እንክብካቤ ሲደረግላቸው አደሩ። በበነጋታውም ታንኳ ባለመገኘቱ ለማደር ተገደዱ። በሁለተኛው ቀን
ታንኳ ስለተገኘ የዚህ ምስጉን ቤተሰብ አባላት ታንኳውን አዝጋጅተው ወደ ደራ (ቆራጣ ወለተጴጥሮስ)
እንዲሻገሩ አመቻቹላቸው። እነዚህ ምስጉን የዘጌ ቤተሰቦች ይህንን የመሰለ እንክብካቤ ያደረጉላቸው
የጄኔራል ኃይሌን ማንነት አውቀው ሳይሆን በኢትዮጵያዊ ወታደርነታቸው ብቻ ነበር። ጣናን ጨርሰው
ደራ እንደደረሱ ለታንኳ ቀዛፊዎቹ የሚገባቸውን ዋጋ ከፍለው ጉዟቸውን ቀጠሉ።
ደራ ላይ አንድ የአካባቢው ገበሬ ማኅበር ሊቀመንበር አገኙና ተባበሯቸው። ቤቴ በድንገት ሊፈተሽ
ስለሚችል ማረፊያ ላዘጋጅላችሁ ብለው በአካባቢው ካለ ትምህርት ቤት እንዲያድሩ አደረጉ። እኚሁ
የገበሬ ማህበር ሊቀመንበር የተወሰኑ የሽምቅ ተዋጊዎችን አምጥተው አገናኟቸው። ጄኔራል ኃይሌም
“ተመልሸ መጥቻለሁና ተፈላልገን እንገናኝ” የሚል መልዕክት ለሰባቱም አውራጃ ሽምቅ ተዋጊ
መሪዎች በእነዚያ ሽምቅ ተዋጊዎች አማካኝነት አስተላለፉ።
ከዚያ በኋላ ሌሊት ሌሊት እየተጓዙ ቀን ቀን ጫካ ውስጥ በመዋል 15 ቀን በእግራቸው ተጉዘው
እብናት ገቡ። እብናት ሲገቡ (መመለሳቸውን በሚስጥር የሰሙ አንዳንድ የሽምቅ ተዋጊዎች ወሬውን
ስለነዙት ወሬው ተራብቶ ነበረና) ሕዝቡና የሽምቅ ተዋጊው በሰልፍ ነበር የተቀበላቸው። እርሳቸውም
ለሕዝቡ በይፋ ንግግር አደረጉ። “ትግላችንን አጠናክረን የሽምቅ ውጊያ ማድረግ አለብን” ብለው
መልዕክት አስተላለፉ። እዚያው እብናት ላይ የሊቦን፣ የፋርጣን፣ የፎገራንና የጋይንትን የሽምቅ ተዋጊ
ሃላፊዎች አግኝተው የሽምቅ ውጊያውን እንዴት መቀጠል እንዳለባቸው መመሪያ ሰጡ። ለደራና
ለእስቴ ሽምቅ ተዋጊዎችም እንዲያደርሱ መልዕክት ላኩ።
ከዘጌ እስከ እብናት የቁስል ማድረቂያቸው የዳጉሣ አረቄ ነበር። እብናት ላይ ግን ክሊኒኩ ይሠራ
ስለነበር (በወያኔ ገና አልተያዘምና) ለቁስላቸው ህክምና አገኙ። ይፋ ወጥተው እብናት ላይ
በመታየታቸው አካባቢው በወያኔ ሊወረር ስለሚችል ወደ መልዛ እንዲወጡ የአካባቢው ሽማግሌዎች
መከሯቸውና ወደ መልዛ ሄዱ።
ባህርዳር በወያኔ ጦር ከተያዘች ከ 17 ቀናት በኋላና ጄኔራል ኃይሌ እብናት ከገቡ በኋላ ተቆርጣ
የሰነበተችው ጎንደር ተያዘች። በዚህም ምክንያት ብዙ ወታደር ከጎንደር ወደ በለሳና እብናት መጣ።
ጄኔራል ኃይሌም እነዚህን ወታደሮች የትም እንዳይሄዱና እንዲታገሧቸው ጠይቀው እስከዚያው ድረስ
የተፈናቀሉትን ወታደሮች እንዲመግብላቸው ሕዝቡን ለመኑ። ሕዝቡም አላሣፈራቸውም፤ እሺ ብሎ
ተባበራቸው። እርሳቸው ሕዝቡን ትብብር ከጠየቁ በኋላ፣ ለኮሎኔል መንግሥቱ 13 ነጥቦችን የያዘ ጥያቄ
በአንድ ገበሬ የእጄ ጠባብ ትከሻ ላይ ከውስጥ ሰፍተው ላኩ። ለኮሎኔል መንግሥቱ ከተጠየቁት 13
ጥያቄዎች ውስጥ የተወሰኑት፦

25
1. ጎንደር ሲያዝ ከ 400 የሚበልጡ ወታደሮች ወደ በለሣና እብናት መጥተው በእርሳቸው ጠያቂነት
ለጊዜው ሕዝቡ እየቀለባቸው እንዳለና ይህም ሠራዊት ከክልሉ የሽምቅ ተዋጊ ጋር በአንድ ላይ
ሆኖ ትልቅ ኃይል ሊሆን ስለሚችል፣ ለሠራዊቱ ቀለብ፣
2. መድሃኒት፣
3. 77 ወታደራዊ የርቀት የመገናኛ ሬዲዮ፣
4. የሽምቅ ውጊያውን የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ
5. የወያኔን እንቅስቃሴ ለመገደብ ሰሜን ወሎንና ደቡብ ጎንደርን የሚያገናኘውን ድልድይ ማፍረስ
አስፈላጊ ስለሆነ እርሱን ለማፍረስ የሚጠቅም ተገቢ ደማሚት፣
6. እነዚህን ሁሉ በሄሊኮፕተር ቢልኩላቸው ሊደርሳቸው እንደሚችል፣
7. ጄኔራል ኃይሌ ከጎንደር አካባቢ መንገዱን ሲቆርጡላቸው እነርሱ (የመንግሥት ጦር) ደግሞ
ከወለጋና ከቡሬ አካባቢ ጀምሮ ወደሰሜን ጥቃት በመሰንዘር መሃል ላይ አስገብተው
እንዲጨፈልቋቸው የሚጠይቅ ነበር።
ይህንን መልዕክት እንዲያደርሱ የተላኩት ገበሬ መልዕክቱን ለማድረስ በዳንግላ መሥመር ሲጓዙ፣
መንገዱ በኢሕአፓዎች ተዘግቶ ስላገኙት ከዚያ ተመልሰው በደሴ በኩል ተጉዘው አዲስ አበባ ደረሱ።
የደሴው መንገድ እራሱ ግማሹ በወያኔ (ሰሜን ወሎ)፣ ደቡብ ወሎ ደግሞ በመንግሥት እንደተያዘ
ስለነበር በመሀከል የነበሩ የተወሰኑ ቦታዎችን በእግር መጓዝ ግድ ነበር። ከደሴ በኋላ ግን አውቶብስ
ይዘው አዲስ አበባ ደረሱ። አዲስ አበባ ደርሰው አብሯቸው የመጣ አንድ መምህር በተሰጠው ስልክ
ደውሎ የቤተሰብ አባላትን አገኝቶ ከማን እንደተላከ አስረዳና በቀጠሮ በአካል ተገናኙ። ዋናው
መልዕክተኛ ገበሬው ነበሩና ስለጄኔራል ኃይሌ በጭንቀት ላይ ለነበረው ቤት በዝርዝር በማስረዳት
ለቤተሰቡ እፎይታን ሰጡት። ደብዳቤውን አድርስ ለተባልኩት ኮሎኔል መንግሥቱ እንጅ ለማንም
አላሳይም ያሉትን መልዕክተኛ አግባብቶ በጅ ገልብጦ ኮፒ በማስቀረት ደብዳቤው በነበረበት ሁኔታ
መልሶ ከሸሚዛቸው ውስጥ ተሰፋላቸው። በበነጋታው ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሚሠራ መላክ ማንጠግቦ
ለሚባል የጀኔራል ኃይሌ ጓደኛ ጉዳዩን በማስረዳት መልዕክተኛውን ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ጋ
እንዲያገናኝ ተደረገ። ፕሬዚዳንት መንግሥቱ መልዕክቱ እንደደረሳቸው እጂግ በጣም ነበር የተደሰቱትና
“የጠየቀውን ሁሉ እልክለታለሁ፤ ነገ ይምጡና እንነጋገራለን” ብለው ሸኟቸው። በበነጋታው ግን
ኮሎኔል መንግሥቱ ሌላ ሰው ሆነው ነው መልዕክተኛውን ገበሬ የተቀበሏቸው። ጄኔራል ኃይሌ
ለጠየቁት ለአንዱም ምላሽ አልሰጡም። “ሄሊኮፕተሮቻችን እየወደቁ ስላለቁብን፣ አሁን ዕቃዎቹን
የምንልክበት ሄሊኮፕተር የለንም። ሌላው ጉዳይ ደግሞ እርስዎ በጉዞ ላይ ብዙ ስለቆዩ አሁን ጄኔራል
ኃይሌ እርስዎ ጉዞውን ሲጀምሩ ከነበረበት ቦታ ላይሆን ይችላል እና እርስዎ ከሄዱ በኋላ
እንልክለታለን” ብለው በመሽንገል ልዩ ጸሐፊያቸው ለሰውየው ብቻ 500 ብር የመጓጓዣ
እንዲሰጣቸው በማዘዝ አሰናበቷቸው። የጄኔራል ኃያሌ ቤተሰብ ግን ለሰውየው የተሰጣቸውን 500 ብር
ሳይነካ፣ ደሴ ድረስ የአውሮፕላን ቲኬት በመቁረጥና ለባለቤታቸው መድሃኒት ይፈልጉ ስለነበር ያንንም
በመግዛት ሸኛቸው።
የተላኩት መልዕክተኛ ምንም ነገር ከኮሎኔል መንግሥቱ ባያመጡላቸውም፣ ቆፍጣናውና አንድ ለእናቱ
ጀግና ትግላቸውን አላቆሙም። ሰባቱንም አውራጃዎች በእግር እየተዘዋወሩ የሽምቅ ውጊያውን
አስተባበሩና እቅድ አውጥተው ደብረታቦርን ጨምሮ በ 10 ከተሞች ላይ በአንድ ሌሊት፣ በአንድ የተወሰነ
ሰዓት ወረራ ፈፅሞ የሽምቅ ውጊያውን ይፋ ለማድረግ አቀዱ።
ለምሳሌ የደብረታቦሩን ብንወስድ፣ ደብረታቦርን በአራት አቅጣጫ ከብቦ የሚያጠቃ ሲሆን፣ አምስተኛው
አካል መሃል ከተማ ውስጥ ሆኖ የወያኔ ወታደሮች ላይ ተኩስ በመክፈት በአራት አቅጣጫ ለከበበው
ጦር በሚከፍተው ተኩስ ምልክት ሰጭ ከመሆኑም በላይ የወያኔ ጦር እንዳይረዳዳ በመካከላቸው ሽብር
የሚፈጥር ነበር። ለማጥቃት የተመረጠበት ቀን ግንቦት 22 ለ 23 1986 ዓ.ም. አጥቢያ ከሌሊቱ 6 ሰዓት
ላይ ነበር። ጄኔራል ኃይሌ ለዚሁ ጉዳይ ሲሉ ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ጃን ሜዳ አካባቢ ነበሩ። ቀኑ

26
ግንቦት 22 ለ 23 አጥቢያ ሌሊት እንዲሆን የተመረጠበት ምክንያት ወያኔ ግንቦት 20 ን በሰላም
አሳልፌያለሁ ብሎ ሲስዝናና አዘናግቶ ለመምታት ነበር።
ባለመታደል ግን ከከተማው መሃል ሆኖ የተኩስ ምልክት ሊሰጥ የነበረው አምስተኛው ኃይል ምንም
ምልክት ባለመስጠቱ ደብረታቦርን በአራት አቅጣጫ ከብቦ ያደረው ጦር ሲጠባበቅ ቆይቶ በየቦታው
ተመልሷል። በዚያ ቀን ደብረ ታቦር ጥቃት እንደሚፈፀም መረጃ የደረሳቸው የወያኔ ባለስልጣናት ወደ
ባህርዳር ሸሽተው ነበር። አንዳንድ ወታደሮችም የሲቪል ልብስ በመግዛት ተመሳስሎ ለማምለጥ
የሞከሩም ነበሩ። በኋላ ጄኔራል ኃይሌ ደረስኩበት እንደሚሉት ግን ከሽምቅ ተዋጊው ውስጥ የቀድሞ
ጦር መኮንኖች አብረው ስለነበሩና እነርሱ ደግሞ አስቀድመውም የኢዴመአን (ወያኔ ያደራጀው
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አንድነት ንቅናቄ) አባል ስለነበሩ ወይም በኋላ ተመልምለው
ስለገቡ እነርሱ አሰናክለውታል ብለው ያምናሉ።

27
የደብረታቡርን ከበባ አቃቤ ሕግን ዋቢ በማድረግ የጦቢያ ጋዜጣ እንደዘገበችው

ከዚህ ሙከራ በኋላ መረጃው ያለው ወያኔ የበቀል ዱላውን በተለይ በጄኔራል ኃይሌ ቤተሰቦች፣ በሽምቅ
ተዋጊዎች፣ ሕዝብ ሊያስተባብሩ ይችላሉ ባላቸው ግለሰቦችና በአጠቃላይ በደቡብ ጎንደር ሕዝብ ላይ
አወረደው። በወቅቱ ይወጡ የነበሩ ነፃ ጋዜጦች ሁሉንም ባይሆን ብዙውን ዘግበውታል። የመዐሕድ
ልሳን የነበረው አንድነት ጋዜጣ “ሰቆቃዎ ዐማራ” በሚለው አምዱ ሁልጊዜ የደቡብ ጎንደርን ዐማራ
ሰቆቃ ይዘግብ ነበር። ሌሎችም ነፃ ጋዜጦች እንዲሁ በየጊዜው ይዘግቡት ነበር። የጄኔራል ኃይሌ
ቤተሰብ የተባሉና በተለይ በሽምቅ ውጊያው ያግዙ የነበሩ ሰዎች ሰውነታቸው እየተቆራረጠ በገደል
ተጣሉ። ሁለት እህቶቻቸው (ወይዘሮ ዘመቱ እና ጦቢያ መለሰ) ታሥረው ፍዳቸውን አዩ።
ዘመቱንና ጦቢያን በጣም ይከታተሏቸው ነበር። እነርሱ ናቸው መድሃኒት፣ ስንቅና ልብስ እየላኩ ቆርጦ
እንዲዋጋ ያደረጉት በማለት በየምክንያቱ ቤታቸውን ይፈትሻሉ። በጥቅምት ወር 1984 ዓ.ም. ላይ
ጄኔራል ኃይሌ ወባና ወረርሺኝ (ተስቦ) በሽታ ታምመው ለ 50 ቀን ደብረታቦር ከተማ ገብተው

28
ይታከማሉ። ወያኔ እርሳቸውን ለመያዝ ገጠሩን ልቡ እስኪጠፋ እያሰሰ ነው። ከተማውንም ቢሆን
ያስሳል በተለይ የነዚያን መከረኛ እህቶቻቸውን ቤት። ጄኔራል ኃይሌ ምናቸው ሞኝ ነው አንድ ቁጥር
ተጠርጣሪ ከሆኑት ከእህቶቻቸው ቤት ተኝተው 50 ቀን የሚታከሙት!? እርሳቸው የነበሩት (ቀኑ ይበልጥ
አስተማማኝ ሲሆን ከምንገልጠው) ከሌላ አሳቻ ቤት ነበር። እህቶቻቸው ግን መፈተሻቸው አልቀረም
ነበር። በፍተሻው ወቅት የነበረው ቃለ መጠይቅና ገራሚ መልስ እንደሚከተለው ተቀምጧል፦
1. ወያኔዎች ወደ ወይዘሮ ጦቢያ መለሰ ቤት ሄደው፦ “ልብስና ስንቅ ትልኪያለሽ፤ ከአንቺ ቤት
መጥቶ ሰንብቶ ተመልሷል መባልን ሰምተናልና የት ነው ያለው?” ብለው ይጠይቋታል። ወይዘሮ
ጦቢያም ስትመልስ፦ “ከቤቴ የመብላት የመጠጣቱ ጉዳይ እንኳን ወንድሜ እናንተም
እየመጣችሁ ትበላላችሁ፤ ትጠጣላችሁ። አልመጣም እንጅ ከመጣ እሰየ፣ አበላዋለሁ፤
አጠጣዋለሁ፤ አሳርፈውማለሁ። ወንድሜ እኮ ነው! በአገር አለ ካላችሁና ካገኛችሁት እባካችሁ
ናፍቆኛልና አሳዩኝ። እኔስ ፈልጌ ፈልጌ ላገኘው አልቻልኩም፤ የወንድም ናፍቆቱ ሊገድለኝ
ነው። የት እንዳለ አላውቅምና እባካችሁ ካገኛችሁት ለእኔም አገናኙኝ” አለቻቸው።

2. ወደ ወይዘሮ ዘመቱ መለስም ቤት ሄደው የቤቷን ክፍሎች ከከፈተሹ በኋላ ቁምሳጥን ይከፍቱና
መፈተሽ ይጀምራሉ። በዚህ ድርጊት የተበሳጨችውና እንደስድብ የቆጠረቺው አንበሳይቱ
የአንበሳው እህት፦ “የእኔ ወንድም ወንድ ነው፤ እንደ ልብስ ቁምሣጥን ውስጥ ተጣጥፎ
የሚቀመጥና እንደሴት ማጀት ውስጥ የሚውል አይደለም። ጀግና ስለሆነ የሚውለው ጀግኖች
ከሚውሉበት በረሃ ነው። ጀግና ከሆናችሁ ካለበት በረሃ ሄዳችሁ ፈልጉት። እኔን ሴቲቱን እዚህ
አታስቸግሩኝ” ብላ አሳፈረቻቸው።
ከግንቦት 1986 ቱ ሙከራ በኋል በጄኔራል ኃይሌ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው እልቂትና
እሥራት በጣም እየከፋ መጣ። በዚያ ላይ ከኋላ ሆኖ በገንዘብም ሆነ ለሽምቅ ውጊያ በሚያስፈልጉ
ቁሳቁሶች የሚያግዛቸው አካል አልነበረም። ስለዚህ የከፋኝ ጦር ይንቀሳቀስበታል ወደተባለው ሰሜን
ጎንደር ደባርቅ ድረስ ሰው ልከው አስፈለጉ፤ ግን ማንም የሚያገናኛቸው ሰው አጡ። በሌላ ጊዜ
ራሳቸው ጎንደር የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ተጠቅመው ለማፈላለግ ጎንደር ከእነ አጃቢውቻቸው ጎንደር
ተጓዙ። ይህንን ሲያደርጉ የተሣፈሩት የተለያየ ቦታ ላይ ተከፋፍለው ነበር። ጎንደር ገብተው አበቄለሽ
ይመር ጠጅ (ቡና) ቤት አልጋ ያዙና ዘመዳቸውን ፍለጋ ወጡ። ይሁን እንጅ ይህ የፈለጉት ዘመዳቸው
አውራ ጎዳና ሰለሚሠራ ለመስክ ሥራ ወጥቶ አላገኙትም። ትንሽ ሴት ልጁን ብቻ ነበር ያገኙት።
ግድግዳ ላይ ከተሰቀለ ፎቶ የባለቤቱን የፀጉር አሠራር አይተው ልጂቱን ስለ እናቷ ሲጠይቋት የሺሬ
ሰው ነች ስላለቻቸው ዘመዳቸውን ቢያገኙትም ብዙ እንደማይረዳቸው ገባቸውና ተመልሰው አልጋ
ወደያዙበት ወደ አበቄለሽ ሆቴል ሄዱ። ጎንደር መንገድ ላይ ፀዳል ብርሃኑ (ደብረታቦር የታወቀ ነጋዴ)
እና ሌላ አንድ ነጋዴ ቆመው እያወሩ አግኝተው ፊት ለፊት እያዩአቸው ጄኔራል ሲያውቋቸው እነርሱ
ግን ጄኔራል ኃይሌን አላወቋቸውም ነበር። ከፋኝን የማግኘቱ ሙከራ ሳይሳካ ሲቀር ወደ ደቡብ እነ
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፣ እነ ጄኔራል ዘለቀ በየነ እና ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የሚመሩት ጦር
በኬንያ አለ እየተባለ በጋዜጦች ስለሚዘገብና ስለሚወራ ከዚያ ኃይል ጋር ተቀላቅሎ ወይም ከነርሱ ጋር
ተነጋግሮና በጋራ የሚሠራበትን ሁኔታ አመቻችቶ ወደ ክልላቸው ለመመለስ በማሰብ ወደኬንያ አመሩ።
ጉዞ ወደ ኬንያ
ከደቡብ ጎንደር ኬንያ ለመድረስ ሁለት አማራጮች ነበራቸው። 1/ ከደብረታቦር በደጀን በኩል፣ 2/
ከደብረታቦር በደሴ በኩል። የደጀኑ መሥመር እርሳቸው ባህርዳር ለብዙ ጊዜ በአውራጃ አስተዳዳሪነት
በመሥራታቸው ልታወቅ እችላለሁ ብለው ስለሰጉ የደሴውን መሥመር መረጡ። ወረታ ላይ ተሣፍርው
ወደ ደሴ ሲጓዙ ብዙውን ጊዜ አውቶብሱ ወረታ ላይ ምሣ በልቶ ደብረታቦር ሰው ለማውረድና
ለመጫን ይቆማል እንጅ ለምሳ አይቆምም ነበር። ያኔ ግን አስቀድሞ ሐሙሲት ቁርስ በልቶ ስለነበር

29
ምሣ ደብረታቦር እንዲሆን ተወሰነና አብዛኛው ሰው ወረደ። ጄኔራል ኃይሌ ምን ይሁኑ? ጥቂት
ካልወረዱ ሰዎች ጋር እዚያው አውቶብስ ላይ ለ 1 ሰዓት ተኩል ያክል መጽሐፍ እያነበቡ ቁጭ አሉ።
በዚህ መካከል ግን አንድ ጉድ ተፈጠረ።
ዱሮ ዳግማዊ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያሉ አብሯቸው ይማር የነበረ ገብሬ የሚባል
ሰው (ትንሽ የአዕምሮ መዛባት ደርሶበት) ትምህርቱን አቋርጦ በልመና እና ሻል ሲለውም የቀን ሥራ
እየሠራ የሚኖር ሰው ነበር። ይህ ሰው ደህና ሆኖ ሲያወራ ከጄኔራል ኃይሌ ጋር አብሮ እንደተማረ
ያወራል። ጄኔራል ኃይሌ የሸዋ ኮሚሣር እያሉ አማታቸው ስላረፉ ደብረታቦር ለለቅሶ መጥተው ሳለ
ከገብሬ ጋር ተገናኝተው ስለድሮ ትምህርት ቤታቸው ከማውራታቸውም በላይ ጄኔራል ኃይሌም
ለመርዳት ሞክረው ነበር። አሁን ደግሞ ጄኔራል ኃይሌ ያስተዳድሩት በነበረው ሀገር ላይ ሽፍታ
ሆነው፣ ገብሬ ደግሞ አውቶብሱ ከመናኸሪያው ሲቆም የዕለት ጉርሱን ለመለመን ከዚያ አውቶብስ
ውስጥ ሲገባ ይገናኛሉ። ሆኖም ግን እነፀዳል ብርሃኑ ጎንደር ላይ አግኝተዋቸው ያላወቋቸውን ጄኔራል
ኃይሌን ገብሬ በሽተኛው ይለያቸዋል ማለት ዘበት ነው። ገብሬ ግን የዋዛ አይደለምና ጠጋ ብሎ
ከጄኔራል ፊት በመቆም ዓይኑን ተክሎ ሊንቀሳቀስ አልቻለም። ከዚያ ጠጋ አለና ቀስ ባለ ድምፅ
“አንተ፣ ደህና ነህ!?” አላቸው። እርሳቸውም ደህና ነኛ አሉትና መዘከር ያለባቸውን ተዘክረውት
“ዝም በል” በሚል ምልክት አመልካች ጣታቸውን አፋቸው ላይ አድርገው አሳዩት። ገብሬም “ግድ
የለህም፤ እሺ” ብሎ ከአውቶብሱ ወረደና መንገዱ ላይ ቆሞ አውቶብሱ እስከሚንቀሳቀስ ዓይኑን
ጄኔራል ኃይሌ ላይ ተክሎ ሲጠብቅ ቆየ። አውቶብሱ ሲነሳ እጁን አውለብልቦ ተሰናበታቸው።
አይገርምም?
ደብረታቦርን እንዲህ ፊልም እንጅ ዕውነት በማይመስል መልኩ አልፈው ነፋስ መውጫ ደረሱ። አዳር
እዚያ ነበር። ዱሮ ባለስልጣን እያሉ ነፋስ መውጫ ሲያድሩ ከሚያድሩበት ሆቴል ይዘው አደሩ።
እዚያም ሆነው አንዳንድ ለትግል ያግዛሉ ያሏቸውን ሰዎች ማታ ላይ ወጥተው ለማፈላለግ ሞክሩ፤
ግን አልተሳካላቸውም።
በዚህ መልኩ ተጉዘው በደሴ አድርገው አዲስ አበባ ገቡ። አዲስ አበባ ሲገቡ፣ እዚያ የሚጠብቃቸው
አካል በጎጃም መሥመር የሚገቡ መስሎት በዚያ በኩል ነበር የሚጠብቅ። ከዚያ በላም በረት በኩል
እንደገቡና ሊገናኙ የታቀደበት ቦታ ላይ እንደሌሉ ከተቀባዩ ቡድን ጋር ተለዋውጠው ተቀባዩ ቡድን
ላምበረት ቶሎ ፈጥኖ ደረሰ። ይህ አካል ለዚሁ ጉዳይ ሲል ሚኒባስ ታክሲ ተከራይቶ የታክሲ ሥራ
የሚሠራ መስሎ ነበር የሚንቀሳቀሰው። ስለ ጄኔራል ኃይሌ አዲስ አበባ መምጣትና አጠቃላይ ቅንብሩ
ከቤተስብ ውስጥ ልጃቸው መላከፀሐይ ኃይሌና እንደልጃቸው ያሳደጉት የታላቅ ወንድማቸው ልጅ
አሰፋ አንለይ ብቻ ያውቃሉ። ከጓደኞች ውስጥ ደግሞ ሻለቃ ክፍሌ ወልደሰማያትና ለዚሁ ጉዳይ ታክሲ
ተከራይቶ የታክሲ ሾፌር የሆነው ኮሎኔል ሰውነት ብቻ ያውቃሉ። አሰፋ እንደታክሲ ወያላ ሆኖ
ይሠራል።
ላምበረት ላይ ተቀብለው የተከራዩት ቤት አስገቧቸው። ጄኔራል ኃይሌ አዲስ አበባ ውስጥ 20 ቀን
ሲቆዩ ከፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ለመገናኘት ሞክረው አልተሳካላቸውም። ፕሮፌሠር አሥራት
ታሥረው ነበር። ሌሎቹም ሊገኙ አልቻሉም። ስብሰባቸውን ሚኒባሳቸው ላይ እያደረጉ ለሃያ ቀናት
ከቆዩ በኋላ ወደ ኬንያ የሚያልፉበትን መሥመር አዘጋጅተው ጉዞ ተጀመረ። ጂኔራል ኃይሌ ወደ ኬንያ
በሚሸኙበት ቀን ሚኒባሷ ኮንትራቷ አልቆ ለባለቤቷ ተመልሳለች። በመሆኑም ጄኔራል ኃይሌ የሚሸኙት
በጓደኛቸው በሻለቃ ክፍሌ መኪና በራሱ አሽከርካሪነት ነው። ወደ ለገሐር ለመሄድ በቤተመንግሥት
በኩል ሲያልፉ ይህች ነገረኛና አዋሻኪ መኪና ወያኔዎች ስንት አድነው ያላገኛቸውን ጀግና ጄኔራል
ወስዳ ለመለስ ዜናዊ ጠባቂ ነፍሰበላ ወታደሮች አስረከበች። ልክ ቁሚ እንደተባለች ቤተመንግሥቱ በር
ላይ ስትደርስ ቀጥ አለች። ነፍሰበላዎቹ የቤተመንግሥት ጥበቃ ወታደሮች እሣት ጎርሰው እሣት
ለብሰው መጥተው “ለምን እዚህ ቆማችሁ? መቆም ክልክል ነው ብለው አምባረቁባቸው። የሃምሣ

30
ሰው ግምት ይፋቴው ሻለቃ ክፍሌ ምንም ሳይደናገጥ ተረጋግቶ፦“ተበላሽታብን ነው እንጅ ሆን ብለን
አይደለም” አላቸው። ምንም ማድረግ ያልቻሉት ወታደሮች መኪናዋን እየገፉ ከዚያ አካባቢ
ማስለቀቅ ነበረባቸው። “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም” እንደሚባለው ደፋሩና ቆራጡ ጄኔራል
ኃይሌ ከውስጥ ጉብ ብለው በመለስ ወታደሮች እየተገፉ ነው። ትንሽ ከተገፋች በኋላ ይህች ነገረኛ
መኪና ድሮም ለተንኮሏ ነበር መሰል ቆማ የነበረው ተረክ ብላ ተነሳች። ሻለቃ ክፍሌም ለገሀር ወስዶ
አሳፈራቸውና ተመለሰ። አሰፋ ለገሀር ሆኖ ይጠብቅ ነበርና የተወሰነ መንገድ ድረስ አብሮ ተጉዞ
ሸኛቸውና እርሱም ተመለሰ። ጄኔራል ኃይሌ ከአንድ አጃቢያቸው ጋር ብቻ ወደ ኬንያ ጉዟቸውን
ቀጠሉ።
የቁርጥ ቀን ጓደኛቸው ሻለቃ ክፍሌ ባመቻቸላቸው መሠረት ለተወሰነ ወራት ጂንካ አካባቢ ከቆዩ በኋላ
የመንገድ መሪ አዘጋጅተው ጉዟቸውን ወደ ሞያሌ አመሩ። የሀገር መውደድ ልክፍት የተጠናወታቸው
ጄኔራል ኃይሌ አሁንም ሞያሌ ላይ ችግር ገጠማቸው። ብዙ የቀንድ ከብቶች በኮንትሮባንድ ወደ ኬንያ
ሲገቡ ያዩና በሁኔታው አዝነውና ተቆርቁረው እነዚህን የቀንድ ከብቶች ፎቶ ማንሳት ይጀምራሉ።
የሞያሌ ፖሊሶች “የኬላ ጥበቃችንን እንዴት ፎቶ ታነሳለህ?” ብለው ችግር ፈጠሩባቸው። እንደምንም
ተገላግለው አለፉና ናይሮቢ ደረሱ። እዚያ እንደደረሱ አንድ የተባረከና ዘረብሩክ የሆነ ዘመድ ቤት
ተከራይቶና ቀለባቸውን ችሎ ለተወሰነ ጊዜ ያዛቸው።
ስለሀገራቸው ሲያስቡ እረፍት የሌላቸው ጄኔራል ኃይሌ ይሄን ብዙ የተወራለትን የጥቁር አንበሣ ጦርና
የመድህንን ሠራዊት አስተባባሪዎች ለማግኘት ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ። ጄኔራል ዘለቀ በየነን አገኙና
በእርሳቸው አማክኝነት ኮሎኔል መንግሥቱን በስልክ አገኙ። ፕሬዚዳንት መንግሥቱን ስለትግልና
ስለተባለው ጦር ሲያነሱላቸው፣ መንግሥቱ፦ “እንዳልንቀሳቀስ ዝሆኑ [የአሜሪካ መንግሥት
ማለታቸው ይመስላል] ተጭኖኛል። በአሁን ሰዓት ምንም ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ ለአንተም
የምመክርህ አርፈህ እራስህን ደብቀህ እንድትቀመጥ ነው” አሏቸው። ይህ ምክር ግን ለጄግናው
ጄኔራል ኃያሌ የሚዋጥ አልነበረም። ሀገር በጠላት እጅ ወድቃ ከአደር አደር እየጠፋችና ወገን
ያለርህራሔ እየተጨፈጨፈ እንዴት ራሳቸውን ደብቀው ለመቀመጥ ይቻላቸዋል? በፍፁም፤ ምክሩን
አልተቀበሉትም። ሌላው በጭውውታቸው ውስጥ ኮሎኔል መንግሥቱ ለጄኔራል ኃይሌ ያነሱላቸው፦
“ያኔ ሀገር ቤት እያለን ሁልጊዜ አምርረህ ስትናገር፣ ከሥራ ጫና የመነጨ ይመስለኝ ነበር። ለካ ልክ
ነበርክ። ብዙዎቹ ባለስልጣናት እኮ በሳምሶናይታቸው ወርቅና ብር አጭቀው ሲጓዙ ነው የተያዙት”
ብለው የጄኔራል ኃይሌ ምሬት ትክክል እንደነበር ቢዘገይም አመኑላቸው። የመድህኑም ጦር ቢሆን
እንዲሁ ይወራለታል እንጅ በተግባር ምንም ሊያገኙ አልቻሉም። ተስፋ ያጡት ጄኔራል ኃይሌ
የራሣቸውን ሴል ከጄኔራል ዘለቀ በየነና ሌሎች መሰል ሰዎች ጋር ሆነው ለማቋቋም ሞከሩ።

31
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ከወያኔ ጋር የተጣላው የሱዳን መንግሥት ወያኔን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት፣
ለወያኔ እጅ ሳይሰጡ በጎንደር በረሃዎች እንደሚንቀሳቀሱ ያውቅ ስለነበር ጄኔራል ኃይሌን አፈላልጎ
እንዲያገኙለት ሱዳን ውስጥ ለብዙ ዓመታት የኖሩትን ኮሎኔል እምሩን ይጠይቃል። ኮሎኔል እምሩ
ደግሞ ቀደም ሲል በጄኔራል ኃይሌ ወንድም አማክኝነት ገና ጄኔራል ኃይሌ ሀገር ቤት በትግል ላይ
እያሉ ከጄኔራል ኃይሌ ጋር ግንኑነት ፈጥረው ስለነበር የሱዳን መንግሥት ጥያቄ እንዳቀረበላቸው
አሁንም ለዚያ ወንድማቸው አሳወቁት። ይህ ሰው በዚያን ጊዜ ለንደን ነዋሪ ሲሆን፣ ጄኔራል ኃይሌም
ወደኬንያ የወጡበት ሰዓት ነበርና ደብዳቤውን ለጄኔራል ኃይሌ በመላክ ለወደፊቱ ሁለቱ ቀጥታ
እንዲገናኙ ሁኔታዎችን አመቻቸላቸው። የሁለቱ ግንኙነት ደህና ከተጀመረ በኋላ እጅግ በጣም
ተጓተተ። በዚህ ላይ እያሉ በጄኔራል ዘለቀ በየነ አማካኝነት ከዶ/ር ሪክ ማቻር ጋር ግንኙነት ተፈጠረና
በዚያ በኩል ንግግር ተጀመረ። (ጄኔራል ዘለቀ በየነ የምዕራብ እዝ አዛዥ እያሉና እነሪክ ማቻር ደግሞ
ያኔ ተቃዋሚ እያሉ ጋምቤላ ካምፕ ነበራቸውና ይተዋወቃሉ።) ዶ/ር ሪክ ማቻር በኬንያ የሱዳን
ሚሊታሪ አታሸ ጋር አገናኟቸውና ጉዳዩ በፍጥነት በዚያ በኩል አለቀ። እዚያው ኬንያ ውስጥ
አምልጠው የወጡ የደርግ ባለስልጣናት ወደተለያዩ ምዕራባውያን ሀገራት ለመውጣት መንገዳቸውን
ሲያመቻቹ አባታቸው ፊታውራሪ መለሰ የፋሺስት ወራሪ ጠላትን እየተፋለሙ ባሉበት የአርበኝነት ጊዜ
ተወልደው በትግል ያደጉት ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራ ኃይሌ መለሰ ግን ገና ከድካማቸው ሳያገግሙ

ለሌላ ዙር ትግል ወደ ሱዳን ሊገቡ ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ። ኃይለ - እንድርያቆስ ሆነው ክርስትና
የተነሱት ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ኢብራሂም መሐመድ በሚል የሽፋን ስም፣ ሥራ መምህርና ዜግነት
ሱዳናዊ የሚል የመጓጓዣ ሠነድ ተዘጋጅቶላቸው ሱዳን እ.አ.አ. ጥር 6 ቀን 1997 ሱዳን ገቡ። ጆሞ

32
ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ሄደው የሸኟቸው ሜጀር ጄኔራል ዘለቀ በየነና ሻምበል ይትባረክ
መንግሥቴ ነበሩ።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ እንደ ኢብራሂም መሐመድ

ጄኔራል ኃይሌ መለሰ በሱዳን


ሱዳን እንደደረሱ የሱዳን ምንግሥት ለሁለት ወራት ቅድሚያ የተከፈለበት Green Village Hotel የተባለ
ሆቴል ውስጥ አሳረፋቸው። ሆኖም ግን ጄ/ል ኃይሌ “ይህ ኑሮ ለእኛ የቅንጦት ኑሮ ነው። እኛ ግን
የመጣነው የምቾት ኑሮ ለመኖር ሳይሆን ለትግል ነው” በማለት ለሁለት ወር እንዲቆዩበት
የተከፈለላቸውን የቅንጦት ሆቴል በሳምንት ውስጥ ለቀው በመውጣት ከኮሎኔል እምሩ ጋር መኖር
ጀመሩ።
የጄኔራል ኃይሌ ወደ ሱዳን መሄድ ሱዳን ባለው ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ደስታንና
የትግል መነሳሳትን ፈጠረ። ሁሉም በግንባር ተሰልፎ ለመዋጋትና ነፃነቱን በደሙ ለማግኘት መቁረጡን
በተደረጉት ስብሰባዎች ሁሉ ቃል ገባ። የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስም ሆነ ጠንካራ ግንባር ፈጥሮ
ትግሉን ለመጀመር ሲባል የከፋኝ አንዱ ክንፍ መሪ ከሆኑት ከኮሎኔል እምሩ ወንዴና ከሌሎች ድርጅት
መሪዎች ጋር ውይይት ተጀመረ። ሆኖም ግን ከኮሎኔል እምሩ ቀና ምላሽ ሊገኝ አልተቻለም። ኮሎኔል
እምሩ የጋራ ግንባር ብሎ ነገር የለም፤ ሁሉም ድርጅቶች ጄኔራል ኃይሌን ጨምሮ ከፋኝን ይቀላቀሉ
አሉ። ጄኔራል ኃይሌ ደግሞ “እኔ የራሴ ድርጅት ስለአለኝ የከፋኝ አባል መሆን አልችልም። ሆኖም
ግን በአንድ ክፍለሀገር ብቻ ከታጠረ ድርጅት ይልቅ ሁሉንም ያቀፈና ለኢትዮጵያ የሚመጥን የጋራ
ግንባር ፈጥረን አብረን መሥራት እንችላለን። እርሰዎ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆነው ያሰባስቡናል፤ እኔ
ደግሞ እታች ሆኜ ወታደራዊ ሥራውን እየተንቀሳቀስኩ እሠራለሁ” ቢሉ፣ ኮሎኔል እምሩ አልሰማም
አሉ። እንዲያውም ከአንድም ሦስት ጊዜ 5 ደርጅቶች ሆነው ግንባር ሊፈጥሩ ሰነዱ ሁሉ ከተረቀቀ
በኋላ ኮሎኔል እምሩ በማፈንገጣቸው ያዘጋጁትን ሰነድ ቀድደው ጥለዋል።
ኮ/ል እምሩ እምቢ ቢሉም ሌሎች አምስት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት አርበኞች
የሕብረት ግንባር (ኢ.ዴ.አ.አ.ሕ.ግ) የሚባል ግንባር መጋቢት 28 ቀን 1989 ዓ.ም. ፈጠሩና ትግሉ ቀጠለ።

33
በወሩ እነ ቴዎድሮስ (አሁን ኮማንደር መስከረም) አታላይ ከፋኝን ይዘው (ከኮሎኔ እምሩ በማፈንገጥ)
ግንባሩን ተቀላቀሉ። ቀጥሎ ሰባተኛ ሆኖ የተቀላቀለው ማዘር ላንድ የተባለው ድርጅት ነበር። የድርጅቱ
አባላትም ጄኔራል ኃይሌን ሊቀ መንበር አድርገው ሲመርጡ፣ አቶ ቱሐት ፖልን ደግሞ ምክትል ሊቀ
መንበር አድርገው መረጡ።

ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ዴሞክራሲያዊ የኅብረት ግንባር (ኢ.ዴ.አ.አ.ሕ.ግ)
ሊቀመንበር (1989 ዓ.ም. በሱዳን)

ግንባሩ ከተፈጠረ በኋላ በውስጥም ሆነ በውጭ ያለው አመራር በደንብ እየተጠናከረ እያለና አመርቂ
ሥራ እየተሠራ ባለበት ወቅት በመሠሪዎች ተጠልፎና ወያኔም በሱዳን መንግሥት ላይ ባሳደረው
ተፅዕኖ ገና በተቋቋመ በአንድ ዓመቱ አራት የግንባሩ አመራር አባላትና መሪው ጄኔራል ኃይሌ ቅዳሜ
ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት እ.አ.አ. ሚያዚያ 5 ቀን 1998 ታሠሩ። የሱዳን መንግሥት ጄኔራሉን የከሰሱበት
(በሰንድ የተደገፈ ክስ ባይመሠርትባቸውም)፦
1. የሱዳን መንግሥት ሳይፈቅድ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተህ ተዋግተህ ትመጣለህ፣
2. መሣሪያ እየገዛህ ታጠራቅማለህ
3. በሲአያኤነትና በሞሳድነት ትጠረጠራለህ
4. አንዳንድ አባሎችህም ዲክታተር ነው ይሉሃል
ጄኔራል ኃይሌንም ሆነ የታሠሩ የግንባሩን አባላት ለማስፈታት በውጭ ያለው የግንባሩ አባላትና
ደጋፊዎች ዓለም - አቀፍ ግብረኃይል አቋቁመው ዘመቻ ጀምሩ። ከጄኔራል ኃይሌ ጋር የታሠሩት አራቱ
የአመራር አባላት ማለትም፦
1. መሠረት ቀለመወርቅ
2. የኔነህ ጎሽነህ
3. ራጉኤል ሺፈራው
4. አዲሱ እ.አ.አ. ኅዳር 16 ቀን 1998 ተፈቱ።
ውጭ ያለው የግንባሩ አባላትና ደጋፊዎች የነዚህን ሰዎች መፈታት ሲሰሙ ጄኔራል ኃይሌም ይፈታሉ
የሚል ተሰፋ በውስጣቸው አሳድረው ነበር። የሱዳን መንግሥት ጄኔራል ኃይሌን “ልንፈታህ ፈቃደኞች
ነን። ቤትም እንሰጥሀለን። ሆኖም ግን ይህንን የምናደርገው የፖለቲካ ሥራህን አቁመህ በቅርብ
ከምትጠይቅህ ከወይዘሪት ሁሉአገርሽ በስተቀር ከማንም ጋር ሳትገናኝ ከተቀመጥክ ብቻ ነው”
አሏቸው። ሆኖም ግን ጄኔራል ኃይሌ ሞገደኛና እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጄኔራል በመሆናቸው የሱዳን
መንግሥት ላቀረበላቸው ጥያቄ አልንበረከክም አሉ። እንዲያውም ይህንን አባባል እንደ ታላቅ ስድብ
ነበር የወሰዱት። ወይ የሰው ልክ አለማወቅ! ሰውየው እኮ ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ናቸው። ለዚህ ስድብ
ጀግናው ጄኔራል ኃይሌ መለሰ የመለሱት፦“እኔ እኮ ወደዚህ የመጣሁት የፖለቲካ ሥራ ልሠራ፣
ወታደራዊ ማሰልጠኛ ቦታ ልትሰጡኝና አስፈላጊውን ሁሉ ልታሟሉልኝ ተስማምተን ነው እንጅ
ከማንም ሰው ሳልገናኝ ከቤት ተዘግቸ ልቀመጥ አይደለም። ሆኖም ግን አሁን ቃላችሁን አጥፋችሁ
በሀገራችሁ ውስጥ ሆኜ የፖለቲካ ሥራ እንዳልሠራ ከወሰናችሁ፣ ከእስር ፍቱኝና ሀገራችሁን
ለቅቄላቸሁ ወደሀገሬ ልግባ” አሏቸው። ይህ ዓይነቱ አቋም ግን በሱዳን መንግሥት ዘንድ ተቀባይነት
አላገኘም። ስለዚህ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ሊፈታቸው አልፈለገም።
ማርች 6 ቀን 1999 ለጄኔራል ኃይሌ ዓለማቀፍ አስፈች ግብረኃይል አስደንጋጭ ዜና ደረሰው። ጂኔራል
ኃይሌ የታሰሩበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የረሀብ አድማ መጀመራቸውንና ስንቅ እየያዘች
የምትጠይቃቸውን ልጅ “ሁለተኛ ስንቅ ይዘሽ እንዳትመጭ፣ ከእንግዲህ እንኳን ስንቅ ልታመጭልኝ
ቀርቶ ከነአካቴውም እንዳትጠይቂኝ” ብለው የያዘችውን ስንቅም ሳይቀበሉ አሰናበቷት። በጣም

34
አስደንጋጭ ዜና ነበር። ግብረኃይሉ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ በሱዳን ኢምባሲዎች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ
እንዲደረግ ወሰነ። ማታውኑ ወረቀት ተዘጋጅቶ በበነጋታው እሁድ ቤተክርስቲያናት ወረቀቱ ተበተነ።
በውጭ ሀገር የጄኔራል ኃይሌ አስፈች ግብረኃይሉ ዘመቻውን በየአቅጣቻው አጧጧፈው። በስልክ፣
በፋክስ (ያኔ ፌስ ቡክና ሌላ ማህበራዊ ሚዲያ አይታወቅም ነበር) እና በሰላማዊ ሰልፍ የሱዳን
ኤምባሲዎችን ፋታ ነሳቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ክፍል ዓለም አቀፍ ግብረኃይሉ ባቀረበለት ተደጋጋሚ ጥያቄ
መሠረት የሱዳንን መንግሥት ጄኔራል ኃይሌን እንዲፈታ ወይም ካሠረበት ቦታ እንዲያሳየው ቢጠይቀው
የሱዳን መንግሥት “ጄኔራል ኃይሌ የሚባል ሰው አላሰርኩም፤ እንዲህ የሚባል ሰውም ሱዳን ውስጥ
የለም” ብሎ ምላሽ ሰጠ። እንዲህ ዓይነቱ የክህደት ምላሽ የዘመቻውን አስተባባሪዎች ይበልጥ ስጋት
ላይ ጣላቸው። ምክንያቱም የሱዳን መንግሥት የጄኔራል ኃይሌን መታሠር ከካደ አንድም አሳልፎ
ለወያኔ ሊሰጣቸው ነው፤ አለበለዚያም ሊገድላቸው ነው በማለት ኮሚቴው ሥጋት ውስጥ ወደቀ።
በመሆኑም ዘመቻውን ይበልጥ በማጠናከር በዓለም ዙሪያ የሱዳን ኤምባሲዎችን በሰልፍ፣ በፋክስና
በስልክ አጨናነቃቸው። ኮማንደር አስፋ ሰይፉ ወዲያውኑ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰው
ልጆች መብት ካውንስል ዓለም - አቀፍ ግብረ ኃይሉ ያለውን ስጋት በመግለፅ አመለከቱና እ.አ.አ ጥር
15 ቀን 1999 ምላሽ አገኙ። ሁለት ሰዎችን የያዘ መርማሪ ቡድን እ.አ.አ. የካቲት 2 ቀን 1999 ይሄዳል
ተባሉ። በጎን ደግሞ ሁሉአገርሽ ሱዳን ላለው የተባበሩት የስደተኞች ክፍል በግንባር ቀርባ እኔ ጄኔራል
ኃይሌ የታሠሩበትን እሥር ቤት አውቀዋለሁና ማሳየት እችላለሁ አለች። የቢሮ ሃላፊዋ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ
አሁን መተማመኛ ስላገኙ የሱዳን መንግሥት የሚሰጣቸውን የውሸት ምላሽ ማመን አቁመው ተፅዕኖ
ማድረግ ጀምሩ።
ዓለም አቀፍ ግብረኃይሉ ሁሉአገርሽን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባት በጥብቅ አስገነዘባት። ይሄውም
ምንም እንኳን ጄኔራል ኃይሌ አትምጭብኝ ቢሏትም፣ በየቀኑ እየሄደች ከእሥርቤቱ ዘበኞችም ቢሆን
ደህንነታቸውን እየጠየቀች ጤንነታቸውን ሪፖርት እንድታደርግ ነበር። እርሷም ጥያቄውን ያለምንም
ማቅማማት ተቀብላ ተግባራዊ አደረገችው፤ በየቀኑ እየሄደች ሪፖርት ማድረጓን ቀጠለች። ዓለም -

35
አቀፍ ግብረኃይሉን በጣም ያሳሰበው ነገር ጄኔራል ኃይሌ ከፍተኛ የጨጓራ በሽታ ስላለባቸው የረሃብ
አድማውን ላይቋቋሙት ይችሉ ይሆናል የሚል ሥጋት በውስጡ ስላደረበት ነበር።
እ.አ.አ. ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 1999 በለንደን ሱዳን ኤምባሲ በር ላይ የተካሄደው የመጀመሪያው
ሰላማዊ ሰልፍ
የተፈራው አልቀረም፤ በጣም እየታመሙ መጡ። በመሆኑም ወንድማቸው ካለበት እንግሊዝ ሀገር
አስመጥቶ ለማሳከምና (እግረመንገዱንም ከእሥር ለማስወጫ እንዲጠቅም በማቀድ) ከአንድ የግል
ሆስፒታል ጋር ውል ተዋዋለ። 10 ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲያስዝ ተጠየቀ። አሥር ሺህ አይደልም
አንድ ሺህ ፓውንድ አካውንቱ ውስጥ አልነበረውም። ባንኩን እንዲያበድረው ሲጠይቀው ተስማማ፤
አሥር ሺህ አበድሮት በሰባት ዓመት ክፍያ 21 ሺህ ፓውንድ አድርጎ እንዲከፍል ተጠየቀ። ዓይኑን
አላሸም፤ ተስማማ። በበነጋታው ቀጥረውት ሲሄድ ግን “የተስማማነው ለቤት እድሳት እንጅ ለህክምና
አይደለም” አሉት። ወንድሙን አምጥቶ ለማሳከምና ሕይዎታቸውን ለማትረፍ የጓጓው ወንድማቸው
ወሽመጡ ተቆረጠ። ግን ከተወሰነ ውይይት በኋላ ተፈቀደለትና ባንኩ 10 ሺህ ፓውንዱን ወደግል
ሆስፒታሉ አካውንት አስተላለፉለት። የግል ሆስፒታሉም የአሠራር ሂደቱን ጠብቆ ለእንግሊዝ ውጭ
ጉዳይ ሚኒስቴር ለጄኔራል ኃይሌ መለሰ ቪዛ እንዲሰጥለት ደብዳቤ ጻፈ። የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ
ሚኒስቴር “ሱዳን ውስጥ ኢምባሲ ስለሌለን [ከኦሳማ ቢላደን ጋር ተያይዞ በነበረው ችግር]
ከሚቀርባቸው ጎረቤት ሀገር ሄደው ያመልክቱ፤ ያ ማለት ግን ኢንተርቪው ተደርገውና ጉዳያቸው
አሳማኝ ሆኖ ሲገኝ እንጅ በቀጥታ ቪዛ ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም” የሚል ምላሽ ስጥቶ አሁንም
የወንድማቸውን ተስፋ እንደገና አጨለመው። ሱዳን እሥር ቤት ውስጥ ያለ እሥረኛ እንዴት ብሎ
ጎረቤት ሀገር ሄዶ የእንግሊዝን ቪዛ ይጠይቃል? ጉዳዩ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” ዓይነት
ውሳኔ በመሆኑ የተያዘው ገንዘብ እንዲመለስ ተደረገና አምጥቶ ማሳከም የሚለው አጀንዳ ተዘጋ።
ዓለም አቀፍ ዘመቻው ግን በተጠናከረ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው።

ማርች 17 ቀን ሁለተኛው ሰላማዊ ሰልፍ ለንደን ላይ ተደረገ። በአሜሪካና በሌሎች ሀገሮችም ሰልፉና
ዘመቻው ቀጥሏል።በዚህ ቀን ጄኔራል ኃይሌ ያለምግብ 12 ኛ ቀናቸው ነበር። በ 8/06/1991 ዓ.ም. ከጄነራል
ኃይሌ የተጻፈ ማስታወሻ ማርች 18 ቀን 1999 ለንደን ለዓለም አቀፍ ግብረኃይሉ ደረሰው። መልዕክቱ
“እስከመጋቢት 27 ቀን እጠብቃችኋለሁ። እስከዚያ ካልተሳካላችሁ እራሴን አጠፋለሁ” የሚል
መልዕክት። በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ መልዕክት ነበር።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ደጋፊዎቻቸውና የሃይማኖት አባቶች ጄኔራል ኃይሌ የረሀብ አድማውን አቁመው
ምግብ እንዲበሉ እንዲማፀኗቸው ጥሪ ቀረበና ብዙዎች የሃይማኖት አባቶችና ደጋፊዎቻቸው ጻፉ። ይህ
ዘመቻ ውጤታማ ነበር። ምክንያቱም ጄኔራል ኃይሌ የሕዝቡን ተማፅኖ አይተው ጥያቄያቸውን
መቀበላቸውን የሚገልፅ ምላሽ በጽሑፍ ሰጡ። የተወሰነ እፎይታ ተገኘ። ዘመቻው ግን እንደቀጠለ
ነው።
በመጨረሻ ይህንን የተቀነባበረ ዘመቻ መቋቋም ያልቻለው የሱዳን መንግሥት የተፋውን በመላስ፣
“የሰላማዊ ሰልፍ ዘመቻችሁን አቁሙልኝና ተቀባይ ሀገር ካገኛችሁ ጄኔራል ኃይሌን እለቅላችኋለሁ”
ብሎ ማሠሩን ከማመኑም በላይ ለመልቀቅ ፈቃደኛነቱን ለመጀመሪያ ጊዜ እየመረረውም ቢሆን ገለፀ።

36
በየሀገሩ ያለው ሀገር ወዳድ ሁሉ ሀገር ፍለጋ ተያያዘው። ነብሳቸውን ይማርና ፕሮፌሠር ጆን ስፔንሰር
ራሳቸው እኔ ከጋና ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላለኝ ጋናን ለማሳመን እሞክራለሁ ብለው ጥረታቸውን

ቀጠሉ። ፕሮፌሰር ጆን ስፔንሰር ጄኔራል ኃይሌን “ታላቁ ሰው” ነበር የሚሏቸው።


ብርጋዴር ጄኔራ ኃያሌ መለሰ በሱዳን እሥር ቤት

የካናዳ፣ የኖርዌይና የስዊድን የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቴዎች፣ ሌሎቹም ሁሉ ጄኔራል ኃይሌን የሚቀበል


ሀገር በማፈላለግ ተረባረቡ። የጄኔራል ኃይሌ ዓለም አቀፍ አስፈች ግብረኃይል አባላት በጠቅላላ፣
በተለይ ደግሞ ሊቀመንበሩ ኮማንደር አሰፋ ሰይፉና ጸሐፊው ወንድሙ መኮንን በዚህ ዘመቻ ላይ
የሠሩትን ሥራ ለመግለፅ በቂ ቃላት አይገኝለትም። ኮማንደር አሰፋ አሜሪካ ለእረፍት ሄደው እንኳን
አላረፉም ነበር። ኤልያስ ክፍሌና ነዓምን ዘለቀ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲባዝኑ እንቅልፍ የሚተኙ
አይመስሉም ነበር።
ሀሙስ ሃምሌ 29 ቀን 1999 (እ.አ.አ.) የወያኔ መንግሥት እና የሱዳን መንግሥት ስደተኞችን ለመለዋወጥ
የሚያስችል ስምምነት ተስማሙ የሚል ዜና ለዓለም አቀፍ ግብረኃይሉ ደረሰው። በዜናው መሠረት
የኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው እንዲሰጡት ከጠየቃቸው 97 ስደተኞች ውስጥ ቁጥር አንድ ተብለው
የተጠቀሱት ጄኔራ ኃይሌ መለሰ ነበሩ። ይህ በእንዲህ እያለ፣ በአጋጣሚም ይሁን ወይም በሌላ ጉዳይ፣
እስከዛሬ የጄኔራል ኃይሌን መታሠርና ሕይዎታቸው አደጋ ላይ መሆኑን ተደጋግሞ ሲጻፍለት ምንም
ምላሽ ያልሰጠው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለጄኔራል ኃይሌ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ግብረኅይሉን ራሱ
ደውሎ ጠየቀ። እስከ ዛሬ ለተጻፉለት ደብዳቤዎች ሁሉ ምንም ምላሽ ያልሰጠው አምነስቲ
ኢንተርናሽናል፣ በአሁኑ ሰዓት ማለትም የሱዳን መንግሥት ጄኔራል ኃይሌ በተራ ቁጥር አንድ
የተጠቀሱበትን 97 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ ለመስጠት በተስማማት

37
ሰዓት ደውሎ መጠየቁ የጄኔራል ኃይሌ ሕይዎት አደጋ ላይ ቢሆን ነው ብሎ ግብረኃይሉ እንዲያስብ
ተገደደ።
የሱዳን መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኢትዮጵያውያን የሚደርስበትን ተፅዕኖ ለማለዘብ ሲል
እፈታለሁ ይበል እንጅ ሊለቃቸው አልቻለም። ከላይ እንደተገለፀው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም
አሳልፎ ለመስጠት እየተደራደረ እንደሆነ ስለተሰማ የዓለም አቀፍ ግብረኃይሉ የሱዳን መንግሥት
እያታለለን ነው ብሎ ማሰብ ጀመረ። የሱዳንን መንግሥት ጨዋታ ያላስደሰታቸው ጠርጣራውና ቆራጡ
ጀግና ጄኔራል ኃይሌም አስደንጋጭ ኑዛዜያቸውን ለቤተሰብ አሳወቁ። ኑዛዜው የሚከተለው ነበር፦
1. ታምሜ ሆስፒታል ቢያስገቡኝና ኦፕራሲዮን ልናደርገው ነውና ፈርሙ ብትባሉ እንዳትፈርሙ፤
2. በህክምና ላይ እንዳለ ሞተ ብለው አስከሬን ተቀበሉና ቅበሩ ቢሏችሁም እንዳትቀበሉና
እንዳትቀብሩኝ፤
3. ከበር ላይ አምጥተው አስከሬኔን ቢጥሉላችሁም አንስታችሁ እንዳትቀብሩኝ።
4. ከወያኔ ጋር ተስማምተው በማስፈቀድ ሀገር ቤት ወስዳችሁ ቅበሩ ቢሏችሁም ፈፅሞ
እንዳታደርጉት፤ የትም ይጣሉኝ። እነርሱ አግባብተዋችሁና እናንተም ተደናግጣችሁ ይህንን
ብታደርጉ ኑዛዜየን እንደጣሳችሁ ይቆጠራል።
5. በመድሃኒት ወይም በመርዝ አለበለዚያም ከእሥር ቤት ሾልኮ ሲጠፋ አግኝተን ገደልነው ብለው
ሊገድሉኝ እንደሚችሉ መገመትና ለዚህም አዕምሯችሁን ዝግጁ እንድታደርጉ ያስፈልጋል።
በጭካኔ አንገታቸውን ቆርጠው ሲያዞሩት የነበረው የአፄ ዮሐንስ ጭንቅላት የኋላ ኋላ
ከእግዚአብሔር ዘንድ ቅጣትን እንዳስከተለባቸው ሁሉ የእኔም በግፍ የተገደለና የተጣለ እሬሣ
ጊዜውን ጠብቆ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምላሽ ማስገኘቱ አይቀርም ይላል አስደንጋጩ ኑዛዜ።
ቀሪ ቤተሰብ የሟችን የመጨረሻ ፍላጎት ወይም ኑዛዜ የመፈፀም የሞራልና የባህል ግዴታ አለበት።
ይህንን ዓይነቱን እጅግ ከባድ ኑዛዜ ግን ተግባራዊ ማድረግ ይቅርና መስማቱ ራሱ ምን ያህል
እንደሚከብድና በቤተሰብ አዕምሮ ላይ የሚፈጥረውን ህመምና መረበሽ በቃላት መግለፅ በጣም
ይከብዳል። ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ እንዲህ ዓይነት ቆራጥነት የተሞላበት ጨካኝ ውሳኔ
በራሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ሲወስኑ ይሄ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከዚህ በፊትም እሥሩ ጠንክሮ
የመፈታቱ ሁኔታ አጠራጣሪ እየሆነ ሲመጣና እንዲያውም አሳልፈው ለወያኔ ሊሰጡኝ ይችላሉ
የሚለው ሃሳብ በአዕምሯቸው ከተፀነሰ ቀን ጀምሮ እዚያው እሥር ቤት እያሉ ሕይዎታቸውን
ለማጥፋት ውሳኔ አደረጉ። ለዚህም የሚረዳቸው የመጀመሪያው ዕቅድ ለብቻቸው ከታሠሩበት ክፍል
ውስጥ የኤሌክትሪክ መሥመሩን ልጠው ዝግጁ በማድረግ የሱዳን ጠባቂ ወታደሮች ለፍተሻ ሲገቡ
እንዳያዩት ሸፍኖ ማስቀመጥ ነበር። ሁለተኛው ዝግጅት ራሳቸውን የሚያጠፉበት መርዝ በጠያቂያቸው
በሁሉአገርሽ አብርሓ አማካኝነት እንዲገባላቸው መጠየቅ ነበር። ሁሉአገርሽ እንዴት ራሱን
የሚያጠፋበት መርዝ እሰጣለሁ ብላ ሃሳባቸውን ባለመቀበል ወደ ለንደን ስልክ ደውላ ወንድማቸውን
ምክር ትጠይቃለች። “አዎ ልትሰጭው ይገባል” ይላታል። ያገኘችው መልስ ያልጠበቀችው ምላሽ
ስለነበር ይበልጥ ደነገጠች። “ወያኔ የጀግናው ወንድሜን እጅ ከሚይዘውና አዋርዶ ከሚገድለው ራሱን
በክብር ማጥፋት አለበት። ይህ ተፈፃሚ የሚሆነው ግን መጨረሻ ሰዓት ላይ በእርግጠኝነት ሱዳኖች
አሳልፈው ሊሰጡት ወስነው እጁን ሊይዙ ሲመጡ መሆኑን በአፅንዖት ልትነግሪውና በዚያ ላይ ፍፁም
መግባባትና ስምምነት ሊኖር ይገባል” ብሎ አብራራላት። ይህም ሆኖ ግን አልተቀበለችውም። ምንም
እንኳን ባታምንበትም እንደምንም አግባብቶ ተግባራዊ እንድታደርግ አደረጋት። ይህንን ሲያደርግ ግን
ከላይ እንደተገለፀው መቼ መጠቀም እንዳለበት መልዕክቱን ሁሉ በአፅንዖት ለጄኔራል ኃይሌ ግልፅ
እንድታደርግላቸው ተደርጎና መተማመን ተፈጥሮ ነው።
ይህ በንዲህ እያለ አይበገሬውና ቆራጡ ጄግና ጄኔራል ኃይሌ ለሱዳን መንግሥት እንደታሣሪ ሳይሆን
እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ጄኔራል ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄውም፦ “ከሀገራችሁ እንድኖር አለመፈለግ

38
መብታችሁ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ አንድም ፍቱኝና ሀገራችሁን ለቅቄላችሁ ወደ ሀገሬ ራሴ ልግባ፤
አለበለዚያም ወደ ሌላ የአፍሪካ ሀገር እንድሄድ ይፈቀድልኝ” የሚል ነበር። ለሱዳን መንግሥት ይህንን
ሲጠይቁ፣ ውጭ ላለው ደጋፊያቸው ያስተላልፉትም ፅኑዕ መልዕክት ደግሞ ከትግሉ መራቅ
ስለማይፈልጉ ሀገር ፍለጋው አፍሪካ ውስጥ እንዲሆን የሚያሳስብ ነበር። ባለመታደል የጄኔራል ኃይሌን
እልህና ወኔ በውል የተረዳ የሚመስለው የሱዳን መንግሥት ደግሞ ከጄኔራል ኃይሌ ሃሳብ በተቃራኒ
“ጄኔራል ኃይሌ አፍሪካ ውስጥ ማንኛውም ሀገር ውስጥ ለመኖር ከመረጡ፤ ከእሥር አልፈታም።
ምክንያቱም ወደ ትግላቸው ለመግባት የሱዳንን ድንበር ሊጠቀሙ ስለሚችሉና ይህም ከኢትዮጵያ
መንግሥት ጋር ሊያጋጨኝ ስለሚችል የሀገር ፍለጋችሁ ከአፍሪካ ውጭ ይሁን” አለ። ስለዚህ በዚሁ
የሀገር መረጣ ላይ ጄኔራል ኃይሌ አፍሪካ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር የሚሉትን ሃሳብ እንዲቀይሩ ማሳመን
ግድ ነበር።
መጨረሻ ላይ ከብዙ ውጣ ውረድና መጉላላት በኋላ በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ቢሮ
ሃላፊ ወይዘሮ ኤልዛቤት ጠያቂነት ኒውዚላንድ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነች። የዓለም አቀፍ የጄኔራል
ኃይሌ አስፈች ግብረኃይል ሊቀመንበር ኮማንደር አሰፋ ይህንን ዜና ሲሰሙ በጣም አዝነው፦ “ይሄ
ራሱን የቻለ ግዞት ነው (This byitself is a solitary confinement)” ብለው አዘኑ። ሆኖም ግን ሌላ ምንም
አማራጭ ሀገር ስላልተገኘ መሄድ ነበረባቸው። ወያኔም እጃቸውን አስረክቡኝ ማለት ጀምሮ ስለነበር
የሱዳን መንግሥት በጄኔራል ኃይሌ አስፈች ዓለም - አቀፍ ግብረኃይል፣ ውጭ ባለው የድርጅታቸው
አባላትና ደጋፊዎቻችው ሰልፍና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ክፍል መፈናፈኛ ባያጣ ኖሮ
ሃሳቡን ቀይሮ ለወያኔ ለማስረከብ ውስጥ ለውስጥ እየተደራደረ እንደነበረ ተደርሶበታል። ግን የአምላክ
ፈቃድ ሆኖ ከብዙ መጉላላትና ውጣ ውረድ በኋላ መስከረም 20 ቀን 1999፣ 1 ዓመት ከ 6 ወራት
የታሠሩባትን እሥር ቤትና ሱዳንን ለቅቀው ወደ ኒውዚላንድ ሄዱ። የሱዳን መንግሥት መጨረሻ ሰዓት
ላይ እንኳን ከተከራዩት ቤት ሄደው አንድ ሰነድና ተቀያሪ ልብስ እንኳን እንዲይዙ ሳይፈቅድ ከእሥር
ቤት በወታደር አጅቦ ቀጥታ አውሮፕላን ላይ ነበር ያሣፈራቸው።
ኒውዚላንድ እንደሚሄዱ ታውቆና የበረራው ዝርዝር ሲደርሳቸው ጄኔራል ኃይሌ ካይሮ ላይ ለብዙ
ሰዓታት እንደሚቆዩ ይረዳሉ። ለንደን የሚገኘው ወንድማቸው ሲደውልላቸው ሞገደኛው ጄኔራል
ያቀረቡለት ጥያቄ በዚያ ሰዓት 1 ዓመት ከስድስት ወር እሥርቤት ሲማቅቅ ከቆየ ሰው ይቀርብልኛል
ብሎ ያልጠበቀው ጥያቄ ነበር። “ጎረቤት ሀገር (ካይሮ) ለብዙ ሰዓታት እንደትራንዚት እቆያለሁና ከዚያ
ላይ ጠፍቼ ትግሉን መቀጠል እፈልጋለሁ። ስለዚህ አንደኛ እንድቀር የግንባሩን የውጭ አመራር ፈቃድ
ጠይቅልኝ፣ ሁለተኛ እንድቀር ከተፈቀደልኝ ከዚያ ስወጣ የሚያገኘኝ ሰው አመቻቹልኝ” አሉ።
ወንድማቸው ባልጠበቀው ጥያቄ ተደናግጦና ትንሽ እንኳን እንዲያገግሙ ፈልጎ “ትንሽ አርፈህና
አገግመህ ወደ ትግሉ ትመለሳለህ። ለጊዜው ግን ብታርፍ እፈልጋለሁ” ሲላቸው የመለሱለት መልስ
ለማመን የሚከብድ ነበር። “እንዴት ወገን እየታረደና ሀገር በጥቁር ጣሊያኖች እየጠፋች እያየሁ
ማረፍ ይቻለኛል? ሀገርና ሕዝብ በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ምንስ ዓይነት የሚያርፍ ኅሊና ይኖረኛል ብለህ
እረፍ ትለኛለህ?” በማለት ያነሳውን ጥያቄ እንዲስብ አደረጉትና በሃሳባቸው እንዲስማማ አደረጉት።
ባዘዙት መሠረት የግንባሩን የውጭ አመራር አካላት በተናጠል እየደወለ ጄኔራል ኃይሌ ያነሱትን ጥያቄ
አቀረበላቸው። አንድም ሰው አልተስማማም። ሁሉም እንደተመካከረ ሰው ወደ ኒውዚላንድ ሄደው
ለጊዜውም ቢሆን ማረፍ እንዳለባቸው አቋማቸውን በማያወላውል ሁኔታ ገለፁ። ይህ ውሳኔም
ለጄኔራል ኃይሌ እንዲደርሳቸው ሲደረግ ሐዘናቸው እጅግ ከፍተኛ ነበር፤ ግን መቀበል ግዴታቸው ነበርና
ውሳኔውን ተቀብለው ወደ ኒውዚላንድ በረሩ።
ኒውዚላንድ መጀመሪያ ኦክላንድ በኋላም ዋና ከተማው ዌሊንግተን በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ
የተደርገላቸው አቀባበልና እንክብካቤ በጣም የሚያስደስት ነበር። ኒውዚላንድ ላይ ለ 16 ዓመታት ከኖሩ
በኋላ በመታመማቸውና የቤትሰብ የቅርብ ክትትል ስላስፈለጋቸው ታህሳስ 2015 አውስትራሊያ
የሚኖረው ልጃቸው አቶ መላከፀሐይ ኃያሌ ወሰዳቸውና መደረግ የሚገባውን እንክብካቤ እያደረገ

39
ይዟቸው ቆየ። ሆኖም ግን የበሽታቸው ሁኔታ የባለሙያን የቀን ተቀን ክትትል ማድረግ እያስፈለገ
በመምጣቱ የሽማግሌዎች መጦሪያ ቤት (Nursing Home) አስገብቷቸው እዚያ በጥሩ ሁኔታ ሲረዱ
ቆይተዋል። ጄኔራል ኃይሌ ለእርሳቸው የዕለት ተዕለት ክትትል ተብሎ የሽማግሌዎች ቤት ይግቡ እንጅ
የልጃቸው የመላከፀሐይና የባለቤቱ የወይዘሮ መሳይ ንጉሤ የዕለት ተዕለት ክትትልና እንክብካቤም
አልተለያቸውም ነበር። በአጋጣሚም ሆኖ እዚያው የሽማግሌዎች መጦሪያ ቤት ውስጥ ብዙ
ኢትዮጵያውያን ይሠሩ ስለነበር ሁሉም (ፈረንጆቹ ሳይቀሩ) ልጆቻቸው በሚጠሩበት መጠሪያ
“አብዬ” እያሉ ነበር የሚንከባከቧቸው።
በምዕራብ አውስትራሊያ ፐርዝ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እ.አ.አ. የካቲት 22
ቀን 2020 ለጄኔራል ኃይሌ መለሰ የላቀ የአርበኝነትና ወታደራዊ አግልግሎት ዕውቅና ለመስጠት የደመቀ
በዓል አዘጋጅተው አንፀባራቂ ታሪካቸውን ከመዘከራቸውም በላይ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት
አድርገውላቸዋል።

40
በአውስትራሊይ፣ ፐርዝ ከተማ ለብርጋዴር ጄ/ኃይሌ መለሰ የላቀ ወታደራዊ አገልግሎት እውቅና
በተሰጠበት ቀን

41
42
ጄ/ል ኃይሌ በፐርዝ ነዋሪዎች የተሸለሟቸው ዋንጫዎችና ሜዳሊያዎች
ጄኔራል ኃይሌ ኒውዚላንድና አውስትራሊያ አካላቸው በስደት ይኑር እንጅ ልባቸው ሁልጊዜ ኢትዮጵያ
ውስጥ ነበር። አንድ ቀን ተመልሼ ወገኔን ነፃ ለማውጣት እየታገልኩ የሀገርንና የወገንን ጠላት ጥየ
ማለፍ አለብኝ የሚለው ዕምነታቸው ከአዕምሯቸው ጠፍቶ አያውቅም ነበር። በዚህ ምክንያት አንድ
ጊዜ ኒውዚላንድ እያሉ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት “እባክዎት የእርስዎ ተመልሶ መግባት ለሀገር ነፃነት
ይጠቅማልና ገብተው ያዋጉልን” የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። ለመስማማት ዓይናቸውን አላሹም።
ግን የጤንነታቸውን ሁኔታ በደንብ የሚያውቁ የልብ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ተፅዕኖ በማድረግ
አስቀሯቸው። ለጓደኞቻቸውም ሆነ ቤተሰቦቻቸው አንድ ዋና የተቃውሞ ምክንያት የሆናቸው ጄኔራል
ኃይሌ ከሚወስዷቸው መድሃኒቶች ውስጥ አንዱ ሁልጊዜም ፍሪጅ ውስጥ መቀመጥ ያለበት መድሃኒት
መሆኑ ነው። በረሃ ገብቶ የሚዋጋ ሰው ፍሪጅ ከየት አግኝቶ ለሕይዎቱ ወሳኝ የሆነውን መድሃኒት
ያስቀምጣል? ቆራጡ ጄኔራል ግን ይሄንን እንደ ችግር አላዩትም ነበር። የእርሳቸው የዘወትር ፍላጎት
ሀገር ላይ ስለሀገር ሲሉ መስዋዕትነትን መቀበል ብቻ ነበር። ምንጊዜም በሀገር ፍቅር የሚናውዙት
ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ሁልጊዜ ከአፋቸው የማይጠፋ አባባላቸው “ሀገሬ ላይና በወገኔ መሀል ሆኜ
ለወገኔ እየታገልኩ እንደ እንቧይ ከበቀልኩበት መሬት ላይ መርገፍ ነው የዘወትር ፍላጎቴ” የሚል
ነበር።
አዎ፣ ምንም እንኳን የእርሳቸው የዘወትር ፍላጎት ባይሳካም፣ የመጨረሻ ህልፈተ ሕይዎታቸው
ከምንምና ከማንም አብልጠው በሚውዷት እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ብለው
በተናዘዙት መሠረት ወደ ኢትዮጵያ እ.አ.አ. ሀሙስ ኅዳር 19 ቀን 2020 ከአውስትራሊያ ተነስተው አርብ
ኅዳር 20 ቀን 2020 አዲስ አበባ 12:40 ሰዓት ላይ ደረሱ። በዚያው ቀን 17:30 ላይ ከአዲስ አበባ ተነስተው
18:30 ላይ የባህርዳር አውራጃ አስተዳዳሪ እያሉ ሥራውን ባስጀመሩት የባህርዳር አውሮፕላን ጣቢያ
ለመድረስ በቁ።
እግዚአብሔር ፈቅዶላቸው ምኞታቸው ሙሉ በሙሉ ባይሳካም፣ በከፊል ለማሳካት ሲባልና ሀገር ቤት
ካሉ ልጆቻቸው፣ እህቶቻቸውና ወንድሞቻቸው ጋር የመጨረሻውን ስንብት እንዲያደርጉ ውጭ
የሚገኙ ቤተሰቦቻችው ወደ ኢትዮጵያ ባስገቧቸው በ.... ውስጥ ከሞት በእግዚአብሔር ተዓምር ብዙ
ጊዜ የተረፉት ጀግናው ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለሰ እግዚአብሔር የፈቀደላቸውን እዚህች ምድር
ላይ የመቆየት ዕድሜ ጨርሰው በተወለዱ .... ዓመታቸው ....... ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ እ.አ.አ. በ 1997 ከኢትዮጵያ ሪጂስተር ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ላይ “የደርግ
አባል ሆነው በሠሩባቸው ጊዜያት “በወንጀልና በዘር ማጥፋት” ክሶች በወንጀለኝነት እንደሚፈለጉ
የወያኔ መንግሥት በይፋ ገልፆ ነበር።ስለዚህ ያሎት አስተያየት ምንድነው?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው
እንዲህ የሚል መልስ ሰጥተው ነበር፦
በመሠረቱ እኔ በግል ሃላፊነቴ ገበያ ላይ የማይገኝ የሰው ሕይዎት፣ ቀርቶ ተሠርቶ የሚገኝ ሀብትና
ንብረት ወስደህብኛል ብሎ የሚጠይቀኝ አንድም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ሥራየንና ተዘዋውሬ
ያገለገልኩትን ሕዝብ ምሥክር አድርጌ እቆማለሁ። እንዲያውም ለልጆቼና ለቅርብ ወገኖቸ
የማወርሳቸው አንጡራ ሀብትና ቋሚ ቅርስ ብትኖረኝ ይህቺው ያልተጉደፈደፈች ስምና ተግባሬ ናት።

በደርግ መንግሥት የጋራ አመራር ሀላፊነቴ ግን ከእኔ በበለጠ የእናት ሀገሬና ወገኔ ጠላት የሆኑት ሻዕቢያ
- ወያኔዎች ለማጥፊያ የፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ በሰጡት ትርጉም ሳይሆን በጅምላው የሆይ - ሆይታ
አሠራር በደረሰው እልቂትና መታመስ ሀገሬንና ወገኔን አልበደልኩም አልልም። ሌላው ቢቀር እኛ
ያዋከብነውና ያሳዘንነው አልበቃው ያለ ይመስል የታሪካዊ ጠላቶቻችን ቅጥረኛ ሆነው ለዘመቱበት
ዳግማዊ ጥቁር ጣሊያኖች አሳልፈን መስጠታችን ከዚያ በፊት ከፈፀምነው ወንጀል ሁሉ በላይ የከበደ
በመሆኑ ሕዝባዊ ችሎትም ሆነ የመክሰሻና የመቀጫው አንቀፅ ገና አልተዘጋጀለትም (አልተቀረፀለትም)።

43
ይኼም ሆኖ ግን ደርግ የገደላቸው፣ አሥሮ ያሰቃያቸውና ያሳደዳቸው ሰዎች በዘርና በሃይማኖት ለይቶ
ሳይሆን የሀገሪቱን አንድነት፣ የሚያራምደውን ሥርዓትና የያዘውን ሥልጣን ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን
ሁሉ ነው። በዚህ ወንጀሉም ጠያቂ፣ ምሥክርና ፈራጅ ሆኖ የሚጠይቀው የጉዳቱም ሆነ የጉዳዩ ባለቤት
የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጅ ጠላቶቹ አይሆኑም። እኔም በጋራ የአመራር ሀላፊነቴ በአደረስኩት
በደል በሕይዎት ካለሁ ቁሜ፣ ከሌለሁም ስምና ታሪኬ ቀርቦ ሊፈረድበት ይገባል።

አዎ ጄ/ኃይሌ አሁን በሕይዎት ቆመው ከሚወዱት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ፍርዳቸውን መቀበል
አይችሉም። ግን ስማቸውና ታሪካቸው ለሕዝብ ፍርድ እንዲቀርብ ቃል በገቡት መሠረት ይሄውና
ስማቸውና ታሪካቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍርድ ቀርቧል።
ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ሀገራቸውን ከምንም ነገርና ከማንም
አብልጠው የሚወዱ ቆራጥ አርበኛ፣ እጅግ ትሁት፣ ሰው አክባሪ፣ ለጋስ፣ አንደብተ ርቱዕ፣ ከዘመኑ
ትውልድ ለየት ያሉና የተባ ብዕር የነበራቸው ሰው እንደነበሩ ይመሠክሩላቸዋል። እስኪ ለምሳሌ ያክል
የአንዳንዶቹ እንዴት እንደሚገልጿቸው በአጭሩ እንመልከት፦

1. አቶ ዓለማየሁ ደሴ፣
ጄኔራል ኃይሌ ሁሉም ዓይነት ጥሩ ሰው ነው ማለት ይቻላል። ዕውነተኛ ነው፤ ትሁት ነው፤ ለሰው
አዛኝ ነው፤ ታዛዥ ነው፤ ዝቅ ብሎ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም ነገር ካለና እርሱ የሚያደርገው ከሆነ
ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ሲጣጣር የማውቀው ሰው ነው። ኅሊናው ንፁህ ሰው ነው። የማያውቀውን
ነገር ዝቅ ብሎ ከሚያውቁ ሰዎች ለመማር የሚችል ሰብዕና ያለው ሰው ከመሆኑም በላይ የሚጣጣሩ
ሰዎችንም ለመርዳት የታደለ ሰው ነው። ተፈጥሮው ንፁህ ነው፤ ኅሊናው ንፁህ ነው።
ኃይሌ የደርግ አባል ሲሆንም ንፁ ደሃ ነው፤ ምንም የሌለ ሰው ነው፤ ከኢትዮጵያዊነቱ፣ ክንፅህናው፣
ከዕምነቱና ከቅን ሃሳቡ በስተቀር ምንም ያልነበረው ሰው ነበር። ንፁህ ሰውና ደሃ ሆኖ ጀምሮ
ሲጨርስም ማለትም አባል የነበረበት መንግሥት ሲፈርስም ያው ንፁህ ደሃ ሆኖ የጨረሰ ሰው ነው።
ምንም እንኳን እንደዛሬው በሚሊዮን ባይዘረፍበትም እንደ ኃይሌ የደርግ አባላት የነበሩ ብዙ ሰዎች
ምን ሆነው ጀምረው ምን ሆነው እንደጨረሱ እኔ በግሌ የማውቃቸው ጓደኞች ስላሉኝ
አውቃቸዋለሁ። ኃይሌ ለሀገሩ ሲባክን እንደሌሎቹ አንድ ልጅ እንኳን ወደ ውጭ ሀገር ልኮ
አላስተማረም። ሌሎቻችን መንግሥት ባወጣው መመሪያ ተጠቅመን በ 30 ብር ቦታ ተመርተን ቤት
የመሥራት ዕድል ሲኖረን ኃይሌ ለሀገሩ አንድ ጊዜ ምሥራቅ፣ ሌላ ጊዜ ሰሜን እና ምዕራብ ሲባክን
ለልጆቹ ጎጆ እንኳን ሳይቀልስ የቀረ ሰው ነው።
ኃይሌ ባህርዳር ሲሄድ ባህርዳር በከፍተኛ ሁኔታ በቀይ ሽብር ከተመታች በኋላ በመሆኑ ሕዝቡ
ተሸብሮና ተጨንቆ የነበረበት ሰዓት ነው። በመሆኑም ለኃይሌ ሕዝቡን ማረጋጋት በጣም ከባድ ነበር።
ግን ኃይሌ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ሰዎችን መቅረብ ስለሚችል ሕዝቡን ማረጋጋቱ ተሳካለት። ሥራ ፈቱ
ብዙ ነበር፣ ባዶ መሬትም ነበር፣ ባለሙያዎችም (ከዚያ በፊት ማንም ያልተጠቀመባቸው) ነበሩ። ምንም
እንኳን ገንዘብ ባይኖርም እነዚያን ክሮች በማገናኘት አረም በቅሎበት የነበረውን መሬትና ባለሙያ
ምሁራንን ተጠቅሞ ሥራ አጦችን ባለሥራ በማድረግ ዳቦ እንዲያገኙ በማድረግ የተሳካለት ሰው ነው።
ይህንን የምመሠክርለት ደግሞ እኔ የጎረቤት ሀገር አውራጃ አስተዳዳሪ የነበርኩት ሰው ብቻ ሳልሆን
ያስተዳደረው የባህርዳር ሕዝብም ጥሩ አድርጎ የሚመሠክረው ሐቅ ነው። ሁላችንም ሃላፊዎች ሆነን
ሠርተናል ግን የኃይሌን ሩቡንም መድረስ የሚያስችል ተፈጥሮ የለንም። ኃይሌ ቀና ብሎ ነው
የጀመረው፣ ቀና ብሎ በኩራትና በንፅህና ነው እዚህ የደረሰው። ኃይሌን በጣም ልናከብረውና ከፍ
አድርገን ልናስበው የሚገባ ሰው ነው። ኃይሌ እንደማንም ዘራፊ ሌባ አይደለም፤ ንፁህ ኢትዮጵያዊ

44
ነው። ኃይሌን በማወቄ በጣም ደስተኛና የምኮራ ሰው ነኝ። በጣም እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ማንም
ኃይሌን የሚያውቅ ሰው ቢገልፀው ከእኔ ይበልጥ ሊገልፀው እንደሚችል ነው።

2. አቶ ተክለማርያም መንግሥቱ (የደቡብ ወሎ ኢሠፓ አንደኛ ጸሐፊ የነበሩ)፣

ብዙ ሰው እንደሚያውቀው ጄ/ኃይሌ 120 ተብለው ከሚታወቁት የደርግ አባላት ውስጥ አንዱ ነበር።
ጄ/ል ኃይሌ ከ 120 ዎቹ አንዱ ቢሆንም እንደ ብዙዎቹ የደርግ አባላት በተለያዩ ቦታዎች ተመድቦ
እየተዘዋወረ ሲሠራ የነበረ ታላቅ ሰው ነው። ጄ/ል ኃይሌ በጣም ደግ፣ በጣም የረጋ፣ መልካም
አስተዳደግና ፈሪሃ እግዚአብሄር ያለው ታላቅ ሰው ነው። በወታደር ሞያው በጣም የተከበረ ሰው ነው።
በካራማራ ግንባር በተደረገው ጦርነት አንዱን ክንፍ የመራው እርሱ መሆኑን በቅርቡ አንዳንድ
መዛግብት ባገላበጡ ጄ/ል መኮንኖች ሲጠቀስ ሰምቻለሁ። ያ ብቻ ሣይሆን በመጨረሻም ደቡብ ጎንደር
አንደኛ ጸሐፊ ሆኖ በነበረበት ጊዜ በዚያ ግንባር ከወያኔ ጋር ሲደረግ በነበረው ፍልሚያ ከፍተኛ ሥራ
ሲፈፅም የኖረ፣ ሆኖም ግን ችግሩ አጠቃላይ ሀገር አቀፍ ችግር በመሆኑና ወያኔም በዚያ በኩል ኃይሉን
አጠናክሮ በመምጣቱ በአንድ ሰው ድካም ብቻ ምንም ለውጥ ለማምጣት የማይቻል ቢሆንም እርሱ
ግን እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ በዓላማ ፅናት ሲዋጋ ቆይቷል።
ከዚያም የወያኔን ድል አድራጊነት ሳይቀበል ለፍልሚያ ራሱን አዘጋጅቶ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክሯል።
ግን አጠቃላይ ክሥረቱ ሀገር አቀፍ ስለሆነ አልተሳካለትም። በኋላም በሆነ መንገድ ራሱን አዘጋጅቶ
ተመልሶ የወያኔን የበላይነት ለመፋለም ወደሱዳን እንደገና ተሰደደ። ግን ወያኔ በጥብቅ ይፈልገው
ስለነበር ሱዳንም ላይ ሥራውን መሥራት ሆነ መኖር አልቻለም። ወያኔ ከሚደግፉት አረቦች ሀገራትና
ከሱዳን ጋር ተባብረው እሥር ቤት እንዲገባ አድርገዋል። ከዚያም በብዙ ጥረት ቢፈታም ከእሥር
ባላነሰ ሁኔታ (ሆን ብሎ በተደረገ ሁኔታ) በጣም ሩቅ ሀገር (ኒውዚላንድ) እንዲሰደድ ተደርጓል።
እግዚአብሔር አድልቶ መልካም ባህሪ የሰጠው ሰው ነው። ጄ/ል ኃይሌ ገርና ቆራጥ ሰው ነው።
ለሚያምንበት ነገር ወደ ኋላ የማይል ሰው ነው። የእርሱን የዓላማ ፅናትና ላመነበት ነገር ወደ ኋላ
የማይል ሰው መሆኑን ያየሁበት አንድ ትዝ የሚለኝ ነገር በአንድ ወቅት በኮ/ል መንግሥቱ ሰብሳቢነት
በጦሩነቱ ምክንያት ችግር ያለባቸው ክ/ሀገራት አንደኛ ጸሐፊዎች ተሰብስበን ነበር። ኃይሌ ወያኔ
ጎጃምን ለመቆጣጠርና ወደ መሀል ኢትዮጵያ ለመዝለቅ የግድ ደቡብ ጎንደርን መውረር ስላለባት
ከፍተኛ ኃይሏን ያሠማራችበት ክ/ሀገር የደቡብ ጎንደር አንደኛ ጸሐፊ ስለነበር የክልሉን ችግር ሰፋ
አድርጎ አዘጋጅቶ ነበር። ሪፖርት ማድረግ ሲጀምር ግን እራሳቸው ያዘጋጁትን ሰምተናቸው እንድንሄድ
እንጅ እኛ ከቦታው ላይ ያለነው ሰዎች እቦታው ላይ የገጠመንን ችግር ሪፖርት ስናደርግ ለማዳመጥ
ዝግጁ ያልሆኑት ኮ/ል መንግሥቱ የኃይሌን ደጎስ ያለ ሪፖርት ለማዳመጥ ትዕግሥት አልነበራቸውም።
“ኃይሌ ይሄንን እኮ እናውቀዋለን፤ ይሄ ሁሉ ምን ይሠራል?” ሲሉት፦ “የተጠራነው ችግራችንን
ሪፖርት አድርገን መፍትሄውን አብረን ለመፈለግ ካልሆነ ለምን ተጠራን? ያለውን ችግር ማስረዳት
ካልቻልኩና ችግሩንም አስቀድማችሁ የምታውቁት ከሆነ፣ ደቡብ ጎንደር ምንም ችግር የለበትም።
የእኔም መናገር አስፈላጊ አይሆንም” ብሎ ወረቀቱን አጣጥፎ በንዴት እየተፈናጠረ ሄዶ ከወንበሩ ላይ
ተቀመጠ። ሁላችንም ያኔ ኮ/ል መንግሥቱ ይቆጣሉ ብለን ተደናግጠን ነበር። ግን ምንም አላሉም።
ይህንን ያነሳሁት ኃይሌ ላመነበት ነገር ምንም ነገር ከማድረግ ወድ ኋላ የማይል ቆራጥ ሰው መሆኑን
ለመግልፅ ነው።

3. ዶ/ር ጌትነት ትዕዛዙ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥነ - ትምህርት ኮሌጅ መምህር)፣

45
ጄ/ኃይሌ የሀገራቸው ፍቅር የሚያንገበግባቸው፣ ሀገራቸውና ሕዝባቸው እንዲያድጉ ሌት ተቀን ሲተጉ
የኖሩ፣ ከሙስና የፀዱ ቆፍጣና ወታደር ናቸው። በእኔ አስተያየት ለልጆቻቸውም የሚያወርሱት
ብቸኛው ነገር ይህንን ከሙስና የፅዳ ባህላቸውንና ከብረ-ኅሊናቸውን ነው።
ስለ ጄ/ ኃይሌ ሲነሣ በጣም የሚገርመኝና የሚያስደንቀኝ ግን ከተፈጥሮ የተቸራቸው ጥበብ ወይም
እንግሊዞቹ Natural wisdom የሚሉት ነገር ነው። ማንኛችንም እንደምናውቀው ጄ/ል ኃይሌ በቀልም
ትምህርት ያንን ያህል አልገፉም። ይሁን እንጅ ከአብዛኞቻችን የተሻለ የማመዛዘን፣ የማስተዋልና አርቆ
የማሰብ ችሎታና ተሰጥዖ የነበራቸው ሰው ናቸው።
ስለጄ/ ኃይሌ ሳስብ ሌላው የሚገርመኝና የሚያስደንቀኝ ነገር ደግሞ ለሰው ልጅ ያላቸው አክብሮትና
ትህትና ነው። እግር ጥሎህ ከጄ/ ኃይሌ ቢሮ ብትገባ በዚያ ዘንጣፋ ቁመታቸው ብድግ ብለውና ጠብ
እርግፍ ብለው ያስተናግዱሃል። ለእርሳቸው ተማርክ አልተማርክ፣ ትልቅ ሆንክ ትንሽ፣ ሃብታም ሆንክ
ደሃ ለእርሣቸው ቁባቸው አይደለም፤ ሰው መሆንህ ብቻ በቂ ነው። ለትምህርት የሚሰጡትም ከፍተኛ
ዋጋ በጣም ያስደንቀኛል።

4. ዶ/ር ፋንታሁን አየለ (ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት
ላይ የዶክትሬት ዲግሪውን የሠራና መጽሐፍ የጻፈ)፣

ጄ/ል ኃይሌ መለሰ በ 1970 የ 69 ነኛ ሚሊሺያ ብርጌድ አዝዥ ነበሩ። የወራሪውን የሶማሊያ ኃይል ድባቅ
መትቶ ከኦጋዴን መሬት ለማባረር በተደረገው ፍልሚያ የ 69 ነኛውን ሚሊሺያ ብርጌድ ያክል
መስዋዕትነት የከፈለ የሠራዊት ክፍል የለም። ያ ብርጌድ በመልሶ ማጥቃት ዘመቻው 81% የሰው
ኃይሉን መስዋዕት አድርጓል። ጄ/ኃይሌ ያንን ብርጌድ ለድል ያበቁ ወታደራዊ መሪ ናቸው።
በኋላ በ 1982 የወያኔ ጦር በለስ ቀንቶት ከትግራይ ውጭ በወሎና በጎንደር ማጥቃት ሲጀምር፣ ጄ/ኃይሌ
ዋናው የጠላት ማጥቃት የወረታ - ወልድያ መሥመር እንደሚሆን አስቀድመው የተገነዘቡና
ማስጠንቀቂያ የሰጡ ቢሆንም ሰሚ ባለመኖሩ በዚያ መሥመር ወያኔ ሁለት ጊዜ ማጥቃት ሠንዝሮ
በመጀመሪያው በመልሶ ማጥቃቱ ቢመታም በሁለታኛው ግን ሰፊ ዝግጅት አድርጎ ያንን ቁልፍ
መሥመር ሊቆጣጠር ችሏል።
በአጠቃላይ ጄ/ኃይሌ በወታደራዊ አመራርና በአስተዳደር የተመሰገኑ ሲሆን፣ ለሀገራቸው ያላቸው ጥልቅ
ፍቅር በጣም የተለየ ነው።
5. አቶ አቢዩ ደስታ፣

አሁን ያለንበት ወቅት ለጄ/ ኃይሌ የሚመጥን አይደለም። እርሳቸውን መሰል ሰዎች በጣም
ጥቂት ሰዎች ናቸው። በዚህ ዘመን ጀ/ኃይሌን የመሰሉ ሰዎች ማግኘት በጣም ከባድ ነው።
በተለይ ጄ/ኃይሌ የተለዩ፣ በጣም ቆፍጣና እና ጀግና ወታደር ናቸው። እጅግ ሲበዛ ደግና ለሰው
ተጨናቂ ሰው ናቸው። ጄ/ኃይሌ የተሰጣቸውን ግዳጅ ብቻ ሳይሆን ከተሰጣቸው ግዳጅ በላይ
በመሄድ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጎድተው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ያገለገሉ ጀግና
ናቸው።

ጄ/ኃይሌ የፍትሕ ሰው ናቸው። አብረውኝ ሲታገሉ የተሰው የትግል ጓዶች ሳይረዱ እኔ


ስለተረፍኩ ብቻ የእኔ ልጆች ተለይተው ሊረዱ አይገባም ብለው ልጆቻቸውን በስደት

46
ወደሚኖሩበት ሀገር አልወስድም ብለው በልጆቻቸው ላይ የጨከኑ የዘመናችን ልዩ ሰው
ናቸው። ይሄ አቋማቸው ለእኔ ልዩ ቦታ እንድሰጠው አድርጎኛል።

ጄ/ኃይሌ ላይ ያየሁት የሀገርና የወገን ፍቅር ከሌላ ከማንም ሰው ላይ አላየሁትም ብል አጋንኜ


የተናገርኩት አይደለም። ጄ/ኃይሌ የኢትዮጵያን ችግር ከነመፍትሄው የሚያውቁ ሰውና በቻሉት
ሁሉ በተግባር ለማሳየት የሞከሩ ሰው ናቸው።

6. አቶ ደጀኔ ይግዛው፣
ብዙ ሕዝብ ያላወቃቸው ሕዝባዊ ሰው፣
የአሥረኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው የመተዋወቅ ዕድል የገጠመኝ። በሂደት የቤተሰብ ያህል ቅርበት ተፈጥሮ፣ እንደልጅ፣ እንደወንድም፣ እንደጓደኛም
ሆኜ ሰብእናቸውን  በጥልቅ ለመገንዘብ ቻልኩ። እውነት መራራ፣ ጎሠኝነት፣ በስልጣን መባለግና ውሸት "ጣፋጭ" በሆኑብት አስቸጋሪ ዘመን፣ ከፍ
ያለ ሥልጣን ላይ ሆኖ ኅሊናን ሳይበክሉ መኖር ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል። በሠሩባቸው የሥልጣን እርከኖች ሀሉ የተራውን ሕዝብ ብሶት በማዳመጥ
ችግሩን ለመፍታት፣ ፍትሕ እንዲያገኝ ለማድረግ፣ ከሥልጣን ማማ ላይ ሆኖ ለተራውና ለምስኪኑ ሕዝብ   የእርሳቸውን  ያህል የቀረበና ያገለገለ
ባለሥልጣን ነበር ብሎ ማመን ይከብዳል። ያ የሕዝብ ወገናዊነት፣ አገልጋይነት፣ ቅርበትና  በሕዝብ  ተወዳጅነታቸው ግን በበላዮቻቸው ቢቻል
የሚያሸልም፣ ቢያንስ የሚያስመሰግን መሆን ሲገባው፣ የተገላቢጦሽ እየሆነ ብዙ ይፈተኑና ያዝኑ እንደነበር አልረሳውም። ሕዝብ ሲወዳቸው ሲያዩ
የሚከፉ አለቆች ወደሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ያስደርጉ ነበር። የሚገርመው ግን  "ሥልጣን የተሰጠኝ ሕዝብ ላገለግል እንጅ ለበላይ አለቃ የግል
ጥቅምና ፍላጎት አገልጋይ አሽከር ለመሆን አይደለም" በማለት  ችግሩን ፊት ለፊት  የሚጋፈጡ ጀግና ናነበሩ።  ማስመሰልን፣ መለማመጥን፣ ከእውነት
ማፈንገጥን፣ ጉቦኝነትን... ከቆሻሻ አስበልጠው ይፀየፏቸዋል። በወታደራዊው ማዕረግ እስከ ጀኔራልነት ማዕረግ፣ በሲብል አስተዳደር እስከ ክፍለ ሀገር
አስተዳዳሪነት ያገለገሉ የመንግሥት ከፍተኛው አካልና የደርግ አባልም የነበሩ ሲሆን፣ አንዲት ጎጆ እንኳን አልቀለሱም። የሚገርመው ወደ አዲስ አበባ
ተዛውረው ሲመጡ፣ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ለሥልጣን ደረጃቸው ሲል ትልቅ ቤት  ሲያቀርብላቸው፣ "ይህንን ከተከራየው ልጆቼ ሽሮ በልተው
መኖር አይችሉም፤ በሥልጣኑ ስም ሳይሆን በሚከፈለኝ ደመወዝ መጠንና ነገም እኔ ባልኖር ልጆቼ በጡረታየ ሊከፍሉት የሚችሉት የቀበሌ ቤት
ፈልጉልኝ " ብለው፣ እስከመጨረሻው በቀበሌ ቤትና ባለሥልጣን በማይኖርበት ተራ ሰፈር በድህነት ነበር የኖሩት።  በእርሳቸው ደረጃ የነበሩ ብዙ
ባለሥልጣናት በምርጥ ቤትና ቦታ ተንደላቀው ሲኖሩና በልዩ ወታደሮች ሲታጀቡ እርሳቸው መደበኛ አጃቢ አልነበራቸውም። (በደርግ ጊዜ የነበረው
ሙስና የመጠጥና ምግብ  ጉቦ፣ ከመንግሥት በጀት አምታቶና ከነጋዴ ተሻርኮ በሚገኝ ገንዘብ አንድ ቪላ ቤት ከመሥራት  ያለፈ አልነበረም።
እንደአሁኑ ፎቅ መደርደር፣ አውሮፕላንና መርከብ  ሠርቆ ሸጦ መክበር፣ በቢሊዮንና በሚሊዮን አገርንና ሕዝብን  መዝረፍ  የማይታሰብ ነበር።) 

ጄ/ኃይሌ ሕዝብን በማገልገልና በሕዝብ ነበር የሚተማመኑ። "ለሕዝብ ከሠራን አጃቢያችን ሕዝብ ነው፤ ሕዝብን ከበደልን፣ ምርጥ አጃቢ ቢኖረንም
ከሕዝብ አመፅ አያድነንም" ይሉ ነበር።  የእርሳቸውን ያህል  ለተራው ሕዝብ እጅግ ከፍተኛ  ክብርና ፍቅር ያለው ባለሥልጣን እስከአሁን
አላየሁም። አንደበታቸው ቁጥብ፣ ሰውን ተናግረው ከሚያስቀይሙና ሰው ሲበደል ከሚያዩ፣ ራሳቸው ቢበደሉ የሚመርጡ፣ አለቃን በአግባቡ ማክበር
እንጅ ለአለቃ ማጎብደድን የማይቀበሉ፣ "እውነት መራራ ብትሆንም ኅሊናን  ነፃ ታወጣለች፤  ኅሊናን ማቆሸሽ በቁም መሞት ነው"  ብለው
የሚያምኑ  ልዩ ሰው ነበሩ። በውስጣቸው የሚንቦገቦገውን የጄ/ኃይሌ መለሰን  ኢትዮጵያዊነትና የሀገር ፍቅር  ለመግለጽ ቋንቋ  ላግኝ አልቻልሁም።
ለኢትዮጵያ ክብር ራሳቸውን ለመሰዋት እንደጣሩና እንደተመኙ ነው ለዚህ የበቁት። በሕይወቴ ሙሉ የማከብራቸው፣ ለሀገራቸውና ለኅሊናቸው
ነፃነት ራሳቸውን ስውተው የኖሩ፣ ስማቸውን እንጅ ምንነታቸውን ሕዝብ ያላወቀላቸው ሕዝባዊ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ጀግና ናቸው።
(ብዙ የሚያውቁትን ሰው በጥቂት ቃላት መግለጽ ምን ያህል ከባድ ነው!?) 

7. አቶ ወንድሙ መኮንን (ባኪንግሐም ዩኒቨርስቲ መምህር)፦


በርግጠኝነት የማውቀው ስለጀኔራል ኃይሌ ለመመሥከር ብቃት እንደሌለኝ ነው። ስለጄኔራል ኃይሌ
መለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅሁት ኢትዮጵያን ሬጂስተር በሚባል መጽሔት ላይ ቃለ ምልልሳቸውን
ካነበብኩ በኋላ ነበር። እንዳነበብኩ ያነበብኩትን ባለማመን “ምን? ለመሆኑ ደርጎች ከመካከላቸው
ወንድ አለባቸው እንዴ!?” ነበር ያልኩት።
ያ ሁሉ ውስኪ ተራጭ፣ ጮማ ጎማጅ፣ መሪው ኮብልሎ ዚምባብዌ ሲገባ ጦሩ ተበተነ። መሬት
የማይበቃቸው የነበሩት የደርግ ባላስልጣናት አንዳችም ድምፅ ሳያሰሙ ልክ እንደበግ ተግተልትለው
ያለአንዳች ኮሽታ እጃቸውን ሲያስረክቡ እንዴት ላክብራቸው? በአንፃሩ ሞራሉ የወደቀን ጦር ሲመሩ
የነበሩት ከፍተኛ መኮንኖች አንዳንዱ ላለመማረክ ጥይቱን ጠጥቶ ሲወድቅ፣ ሌላው በጠላት ጥይት
ተነድሎና ተገድሎ የተቀረው ሲማረክ፣ የተረፈው ደግሞ ወደ የመንና ሱዳንም ተሰዷል። ታዲያ
የእንዲህ ዓይነቱ የጀግኖች ጀግና ከእነዚህ መሀል ሲገኝ እንዴት አያስገርምም!? እንዴት አያስደንቅም!?

47
ጄኔራል ኃይሌ ታማኝ ወታደሮቻቸውንና ቃታ መሳብ የሚችለውን የቤተሰባቸውን አባላት ሳይቀር
አሰልፈው ታሪክ የሠሩ ጀግና ናቸው። እንደ ጄኔራል ኃይሌ ያሉ 10 ጄኔራሎች፣ 10 የጦር መሪዎች
ቢኖሩን ኖሮ ወያኔ በፍፁም ኢትዮጵያን እረግጣ መግዛት ባልቻለች ነበር። እኒህን ጀግና ወያኔ ምን
ብትለፋ፣ ብታደፍጥ፣ ፊትለፊት ብትዋጋ ልታቸንፋቸው አልቻለችም። እጃቸውን መያዝ አልቻለችም።
ከርሳቸው ጋር የተሰለፉት በጀግንነት እየተዋጉ እስከ መጨረሻይቱ እስትንፋሳቸው ሲዋጉ፣ የወደቁት
ወድቀው ታሪክ እየሠሩ አለፉ። ታዲያ ምን ያደርጋል? ጥይቱም ያልቃል፤ ማን ጥይት ያቀብላቸው?
ተዋጊውም ይቆስላል፤ ማን መድሃኒት ያምጣላቸው? በወደቁት ጀግኖች እግር ተተክቶ ማን ይዋጋ?
ዕርዳታ ከየት ይምጣ? ጦሩ እየተመናመነ፣ የውጊያ ብቃቱም እየተዳከመ ሄደ። ዘመዶቻቸውም አለቁ።
የቴዎድሮስ ልጅ እጅ ግን አልተያዘም፤ ኃይሌ የሚሰጥ እጅ አልነበራቸውም፤ እንደ እሣት ይፋጃላ!
አይያዙም! አይደፈሩም! አይነኩም!
ሁሉም ነገር የማያዋጣ ሲሆን ኬንያም ኡጋንዳም አካባቢ ወያኔን የሚፋለም ኃይል እንዳለ መረጃ
ሲደርሳቸው ይህንን ኃይል ይዘውት ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ ወደዚያ ለማቅናት ወሰኑ። በየት በኩል
ይለፉ? እዚህ ላይ ነው የሚገርመው። ጀግግናው ኃይሌ ከባላገሩ ጋር ተመሳስለው በቀጥታ ወያኔ
ትፈነጭበት በነበረው አዲስ አበባ ሰንጥቀው በሞያሌ በኩል ኬንያ ገቡ። ለሕይዎታቸውም አልራሩም።
ጀግና ይሉሃል ይሄ ነው። እዚያ ደርሰው የተበታተነውን ኃይል በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ ሱዳን በመብራት
ፈልጋ የመጓጓዣ ሠነድ በማዘጋጀት ወደ ካርቱም ጋብዛ ወሰደቻቸው። እንግዲህ በጂኦግራፊ ስታዩት
ሱዳን ለጎንደር ቅርብ በመሆኗ ሳይውሉ ሳያድሩ ተዋጊ ኃይላቸውን አሰልጥነው፣ አጠናክረውና
አደራጅተው ኢትዮጵያን ከወያኔ እጅ ፈልቅቀው ሊያወጡ ሱዳን ገቡ። ህልማቸው ግን አልተሳካም።
እርግጥ ወያኔን ሊፋለሙ የተዘጋጁ ኃይሎች ቢኖሩም፣ ሱዳን ግን የፈለገቻቸው ወያኔን እንዲወጉና
የኢትዮጵያን ክብር እንዲያስመልሱ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ዋጋ ልታገኝባቸው፣ ልታተርፍባቸው የምትችል
ሸቀጥ አድርጋ ከወያኔ ጋር ለመደራደሪያነት አቀረበቻቸው። አሥራም ቁጭ አደረገቻቸው። ወያኔ ስንት
ዓመት ሙሉ ለፍታ መማረክ ያቃታትን ጀግና ለመንጠቅ አሰፍስፋ ስትደራደር ተደረሰባት። አገኘሁ
እዚህ ለንደን ውስጥ ያለነውን ወንድሞቹንና ቆራጥ ኢትዮጵያውያንን ለንደን ውስጥ ደባውን
እንድናጋልጥ አደራጀን። ጀግናችንን አናስበላም በሚል መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴያችንን
አቀጣጠልነው። ኢ.ኢ.ድ.ን. የሚባል (Ethiopian Electronic Distribution Network) የሚባል መድረክ ላይ
እሳተፍ ነበር። በዚያ መድረክ ላይ ያሉ የትግል ጓደኞቸ በሙሉ ከአሜሪካ እስከ ጃፓን ያሉ ይህንን
እንቅስቃሴ ሲያውቁ ተቀላቀሉ። ትግሉን አቀጣጠሉት። በተለይ የኢትዮጵያን ረጂስተር አርታዒ
የነበረው ነዓምን ዘለቀ (የእውቁ የባህር ኃይል ኮማንደር ዘለቀ ልጅ) ያደረገውን ተጋድሎ አልረሳውም።
የኢትዮጵያን ሪቪው አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌም ያደረገው አስተዋፅዖ ቀላል አልነበረም። ሁሉም በያለበት
የሱዳንን ኤምባሲ አጨናነቁት። ከዚያ በፊት የሱዳን ኤምባሲ ኮሽታ የማይሰማበት ነበር። ያሉበት
እንኳን የማይታወቅ የነበሩ ሱዳኖች በጄኔራል ኃይሌ ምክንያት ድንብርብራቸውን አወጣነው። በዓለም
መንግሥታት ፊት ራቁታቸውን አስቀረናቸው። በዓለም አቀፉ ግብረኃያል ጥረት ሱዳን እንደቋመጠች
ቀረች፤ ጀግናችን ጄኔራል ኃይሌ ተፈቱና ኒውዚላንድ ገቡልን። ያ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ነበር፤
ለእርሳቸው ግን ድል አልነበረም፤ እርሳቸው እንደሽንፈት ነው የቆጠሩት። ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ
ሲሄዱ በድሎት ለመኖር አልነበረም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦራቸውን ገንብተውና አደራጅተው ወደ
ኢትዮጵያ ለመመለስ ነበር እቅዳቸው። ወደ ሱዳን ሲሄዱም እዚያ አካባቢ የበለጠ ኃይል ስለነበር ያንን
ኃይል እየመሩ በሚያውቁት አካባቢ፣ በጎንደር በኩል ገብተው ወያኔን ሊመነግሉ ነበር። ወደ ኒውዚላንድ
ሲሄዱ ግን ኒውዚላንድ ከኢትዮጵያ በጣም ሩቅ ስለሆነች፣ አሥረን ከትግሉ እንዳስወጣናቸውና
ዕቅዳቸውን እንዳከሸፍንባቸው ነበር የተሰማቸው። ተመልሰው የመዋጋት ዕቅዳቸው ስለተቀጨባቸው
ሁልጊዜ እንደተናደዱብን ነው የኖሩት። በውስጣቸው የሐገራቸውንና የሕዝባቸውን ህመም በሆዳቸው
ይዘው “እህ እህ እህ” እንዳሉ እንደበገኑ ነው የኖሩት።

48
በመጨረሻ በግሌ ማለት የምፈልገው አለኝ። አባቴ መኮንን አየነው የበላይ ዘለቀ አንጋች ነበር።
ከአምስቱ ዓመታት አራቱን ገና የ 14 ዓመት ልጅ ሆኖ ጣሊያንን ሲፋለም፣ በረሃ ለበረሃ ሲንከራተት፣
አለቃውን ሲከተል ነበር የኖረው። ታዲያ ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ሳያወራኝ ውሎ አድሮ
አያውቅም ነበር። ያንን እርሱ ሲያወራኝ የነበረውን ቆራጥነት፣ ጀግንነት፣መስዋዕትነት፣ አይበገሬነት፣
ኢትዮጵያዊነት በአንድ ላይ ተጠቃሎ ያገኘሁት ጄኔራል ኃይሌ መለሰ ውስጥ ነው።
8. አቶ ኆኅተብርሃን ጌጡ
ተወለደና ሞተ የማይባል ሕያው ታሪክ ያለው ጄኔራል ኃይሌ መለሰ!
ከጄኔራል ኃይሌ መለሰ ጋር አጋጣሚዎች ፈቅደው ትውውቅ ከፈጠርንበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ
ጊዜያት በአካል የመገናኘት ዕድል አግኝቼ ነበር። እርሳቸዉን ከማወቄ በፊት በውትድርናው ዓለም
ተሰማርተው ስለሚገኙ ሰዎች የነበረኝ አመለካከት ጭራሽ ከማስበው ፈጽሞ የተለየ ሆኖ ነው
ያገኘሁት። እርሳቸው ላይ ያየሁት የውትድርና ሕይወት የመለዮ ልብሳቸውንና ከፍተኛ ወታደራዊ
ማዕረጋቸውን ብቻ ነው።
ልጅም ሆነ ሸመገለ፣ ገበሬም ሆነ ሊቀ ጠበብት፣ ባለ ሥልጣንም ሆነ ተራ ዜጋ ለሰው ልጅ በሰውነቱ
የሚሰጡትን አክብሮት ለተመለከተ ያለ ምንም ማጋነን፣ ይች ዓለም ለእኒህ ሰው የምትገባቸው
አይደለችም ብሎ መናገሩ አይቀርም። ለሰዎች ካላቸው አክብሮት በላይ ደግሞ አስደማሚዉ
ባሕርያቸው ሰዎችን የማዳመጥ ተሰጣኦዋችው ነው። ትዕግሥትን እንደ ሸማ ተላብሰውታል። ይህን
ደግሞ ሰው ታድሎ እንጅ፣ ታግሎም አያገኘውም።
ሙሉ ሕይወቱን ለሀገሩ የሰጠ ሰው ተወለደና ሞተ ስለማይባል ሞቶም ታሪኩ ሕያው ነው። ከልጅነት
እስከ ዕውቀት፣ ከወጣትነት ሕይወት እስከ ሽምግልና ሕይወቱ፣ ከሀገር ውስጥ እስከ ጎረቤት ሀገሮች
ጭምር በመንከራተት ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ጄኔራል ኃይሌ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።
ልጆቻቸዉም የሚወርሱት ይህንኑ አኩሪና ሕያው ታሪካቸውን ነው። ሰው በቁሙም የሀገር ዘራፊና
ባንዳ እየተባለ ሲዘለፍ፣ ሞቶም ቤተሰቡ የሚወርሰው ይህን ዓይነቱን አንገት አስደፊ ታሪክ ሲሆን
ቤተሰብ ጭምር ሞተ ማለት ነው። ባለሥልጣን እና በዉትድርናዉም ዓለም ባለ ከፍተኛ ማዕረግ
ደራቢ ሆኖ፣ትናንትም ሆነ በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን እንዲህ ዓይነት ሞት አለመሞት ፀጋ ነው። ሥም
ከመቃብር በላይ ሲሆን ሞትም ክብር አለው። ጄኔራል ኃይሌን እኛ እንርሳቸው ብንል እንኳ ገድለ
ካራማራ ሲዘክራቸው ይኖራል። በመጨረሻው ሰዓት ሰዉን ማሞገስ እንደ ልምድና ባሕል ብቻ
ወስደነው ሳይሆን፣ ጄኔራል ኃይሌ መለስ ተወለደና ሞተ ብቻ የማይባሉ ሕያው ታሪክ ካላቸው ጥቂት
ኢትዮጵያዉያን መካከል አንዱ መሆናቸውን እውነታ ምስክርነት እንድንሰጥ ግድ ስለሚለን በመሆኑ
ነው።
(በዚህ አጋጣሚ የማውቀውን ግን ደግሞ ሳልናገር ማለፍ የሌለብኝ መልዕክት ቢኖር፣ በማናቸውም
የጄኔራል ኃይሌ መለስ ጉዳይ የራሱን ሕይወት እየበደለ፣ ቤተሰቡን እየተወ ለእርሳቸው ሲል የከፈለዉን
መስዋዕትነት የቤተሰባቸው አባል የሆነውን አቶ አገኘኸዉ መኮንን ምስጋና ሲያንሰዉ እንጂ የማይባዛበት
ሰዉ መሆኑን ነው።)
ጄኔራ ኃይሌ መለሰ የ 7 ልጆች አባትና የ 10 የልጅልጆች አያት ነበሩ።
የተሸለሟቸው ሜዳሊያዎችና ሽልማቶች፦
1. የሕብርተሰባዊት ኢትዮጵያ ታላቅ የክብር ኮከብ ኒሻን 1 ኛ ደረጃ፣
2. የየካቲት 66 አብዮት ኒሻን 1 ኛ ደረጃ
3. አውስትራሊያ የፐርዝ ነዋሪዎች የሸለሟቸው፦

49
3.1 2 ኒሻኖች
3.2 2 ዋንጫዎች
በመጨረሻም፦ እኛ የጄኔራል ኃይሌ ቤተሰቦች፣ ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ በትግል ጊዜያቸው ዓላማቸው
እንዲሳካ ከጎናቸው ቆማችሁ በጊዜ፣ በገንዘብና በጉልበት ላገዛቹሃቸው ዕውነተኛ የትግል ጓዶቻቸው፣
በኋላም ሱዳን ውስጥ ለ 1 ዓመት ከ 6 ወር በታሠሩበት ጊዜ ለማስፈታት ያላሳለሰ ጥረት አድርጋችሁ
ላስፈታችኋቸው የጄኔራል ኃይሌ መለሰ አስፈች ዓለም ዓቀፍ ግብረኃይል አባላትና ደጋፊዎቻቸው፣
ጄኔራል ኃይሌ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ያደረጉትን ትግል ዕውቅና ለመስጠት የደመቀ በዓል
ከማክበራችሁም በላይ ለጀግና የሚገባውን ሽልማት ላደረጋችሁላቸው በአውስትራሊያ ፐርዝ ውስጥ
ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቻችን፣ እንዲሁም በኅልፈተ ሕይዎታቸው ጊዜ ኮጎናችን
ሆናችሁ ሐዘናችንን ላፅናናችሁን ወገኖቻችን ሁሉ እጅግ ከፍ ያለ መስጋናችን ለማቅረብ እንወዳለን።

ጌታ ሆይ፣ የፅኑ አማኝህን የኃይለ-እንድርያቆስን ነብስ በአፀደ ገነት አሳርፍልን።

50
የልቤን መሻት ያክል ባላደርግልሽም፣ የደማሁልሽ፣ የቆሰልኩልሽና እጅግ ብዙ የተንገላታሁልሽ እናት ሀገሬ
ኢትዮጵያ ለዘላለም ኑሪልኝ። እንደገና የመወለድ እድል ቢኖረኝ አሁንም ወታደር ሆኘ ላገለግልሽና
ያልጨረስኩትን የቤት ሥራ ለመጨረስ የጋለ ፍላጎት ነበረኝ። ምንጊዜም ደህና ሁኝልኝ ኢትዮጵያዬ!

51
52

You might also like