You are on page 1of 50

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

አምስተኛ ክፍል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት


ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም
አቀፍ) የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተዘጋጀ 2015 ዓ.ም
ያግኙን

Email
office@eotc-gssu.org
YouTube
https://www.youtube.com/channel/
UC83LE1vp0FBsV2TEfcpSmUg
Facebook
http://facebook.com/EOTC.GSSU
Telegram
https://t.me/EOTCNSSU
Website
https://eotc-gssu.org/a/
Twitter
https://twitter.com/tibeb_felege

Copyright ©
2015
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ
አስኪያጅ እና የባህርዳር ሁገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ቀለሜንጦስ በሰንበት ትምህርት ቤቶች


ማደራጃ መምርያ የበላይ ሊቀጳጳስና የሰሜን ሸዋ ሀገረ
ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ማውጫ
መግቢያ
ምዕራፍ አንድ
፩. መንፈሳዊ ሰው-------------------------------------- ፯
፩.፩ በመንፈሳዊ ሕይወት ጸንተን ለመኖር ምን እናድርግ..... ፱
፩.፪. መንፈሳዊ ሰው በቤተሰቦቹ መካከል---------------------- ፲፪
፩.፫. መንፈሳዊ ሰው በአካባቢው-------------------------------፲፬
፩.፬. መንፈሳዊ ሰው በትምርት ቤቱ--------------------------፲፮
፩.፭. መንፈሳዊ ሰው የትም ቦታ................................... ፲፯

ምዕራፍ ሁለት
፪.፩. ክፉውን በክፉ አለመመለስ ---------------------፳፩
፪.፪. ሰላማዊ ሰው ስለመሆን--------------------------፳፫
፪.፫. ሰላማዊ ሰው አለመሆን በማኅበራዊ ሕይወት የሚያስከትለው
ችግር..................................................................... ፳፭
፪.፬ ደስታና የደስታ ምንጮች-----------------------------፳፯

ምዕራፍ ሦስት
፫.፩. ዓለማዊነት እና መገለጫዎቹ---------------------፴፩
፫.፪. የስጋ ሥራ እና ውጤቱ---------------------------፴፪
፫.፫. ከዓለም ርኩሰት ራስን ለእግዚአብሔር ስለመለየት-... ፴፫

ምዕራፍ አራት
፬.፩. የጥበብ ምንነት ጥቅምና ምንጭ------------------፴፱
፬.፪. ጥበብ ስጋዊ እና ጥበብ መንፈሳዊ-----------------፴፱
፬.፫. ከጠቢብ ሰው የሚገኙ ነገሮች----------------------፵


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

መግቢያ

የክርስቲያን ሥነ ምግባር መሠረቱ ፈሪሐ እግዚአብሔር ነው፡፡


በእግዚአብሔር መንፈስ የተቃኘው ልበ-አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ
እና ልጁ ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር ሊኖረው
ስለሚገባው መልካም ግንኙነት ሲያስረዱ የዕውቀት መጀመሪያ አድርገው
ያስቀመጡት ፈሪሐ እግዚአብሔርን (እግዚአብሔርን መፍራትን) ነው፡፡
(መዝ. ፻፲፥፲ ምሳ ፩፥፯)

እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በቁጣው ይቀስፈኛል፤ በኃያልነቱ


ያጠፋኛል ከሚል የሥጋትና የጭንቀት መንፈስ ሳይሆን ይህን ዓለም
ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ማስገኘቱን፤ የፍጥረት ሁሉ ጌታ
መሆኑን፤ ሰውን ከፍጹም ፍቅሩና ከፍጹም ፈቃዱ የተነሣ በመልኩ
በምሳሌው መፍጠሩን፤ የፍጥረት ሁሉ መጋቢነቱን አምኖ መውደድ
ሲሆን እንዲሁም ለሕጉ ለትእዛዙ መገዛትና በሕጉ በትእዛዙ መመራት
ነው፡፡

በክርስትና እምነት የሕይወት መንገድነት ተጉዞ ዕረፍተ ነፍስን፤ ርስተ


መንግሥተ ሰማያትን መውረስ የሚሻ ሁሉ የክርስትናው ራስና ፈጻሚ
የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሥጋ
በቆየባቸው ወራት የነበረውን ኑሮ ልብ ብሎ ሊያስተውል ይገበዋል፡፡
በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ የእርሱ ገንዘብ መሆኑ
የሚታወቅበትን ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሌለው ሰው ቢኖር የእርሱ
እምነት ጥቅም የሌላት ሙት ናት፡፡ ያዕ.፪፥፲፬-፲፯

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በጉባኤ ተምረውት፤ በአእምሮ አውቀውት ብቻ


የሚቀር አይደለም፡፡ ይልቁንም ዕለት ዕለት በሕይወት የሚጠቀሙበትና
የሚመሩበት ነው እንጂ፡፡ በወንጌል ”የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ የምድር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
ጨው ናችሁ” ተብሎ ለምእመናን የተነገረው ቃል ምእመናን መልካም
ሥራቸው ለሌላው የሚያበራ፤ በኃጢአት ጣዕሙን ላጣው ዓለም
በበጎ ሥራቸው ጨውነት ጣዕም የሚሆን(የሚያጣፍጥ) ስለሆነ ነው፡
፡ በመሆኑም ክርስቲያን ከራሱ አልፎ ወገኑን በእምነቱና በሥራው ወደ
እግዚአብሔር እንዲያቀርበው ”በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፤” ያለውን
ቃል በወንጌል በተራራ ላይ እንዳለች ከተማ አድርጎ ለሁሉ የሚታይ
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን ገንዘብ በማድረግ መገለጥ አለበት፡፡


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ምዕራፍ አንድ

መንፈሳዊ ሰው

ዓላማ
ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ሲያጠናቅቁ

. ስለ መንፈሳዊነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል


. መንፈሳዊ ሰው በቤተሰቦቹ መካከል የሚጠበቅበት ነገር ምን እንደሆነ
ይገነዘባሉ
. መንፈሳዊ ሰው በአካባቢው የሚየሚጠበቅበት ነገር ምን እንደሆነ
ይገነዘባሉ
. መንፈሳዊ ሰው በትምህርት ቤት የሚጠበቅበት ነገር ምን እንደሆነ
ይገነዘባሉ
. መንፈሳዊ ሰው በሁሉም ቦታ የሚጠበቅበት ነገር ምን እንደሆነ
ይገነዘባሉ

ማስጀመርያ ጥያቄዎች

፩. መንፈሳዊ ማለት ምን ማለት ነው?


፪. መንፈሳዊነትን ከየት እንማራለን?
፫. መንፈሳዊ ሰው ማን ነው?
፬. መንፈሳዊ ሰው ምን ይጠበቅበታል?


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ቁልፍ ቃላት

መንፈሳዊ ሰው፡- በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ፤ መልካም ሥራቸው


በእግዚአብሔርም ሆነ በሰውም ዘንድ የተወደደላቸውና ለሌሎች ሰዎች
አርአያ የሚሆኑ በቤተ ክርስቲያን ጆሮ ውስጥ ጥዑም ቃና ያላቸው፤
ሕያው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ተንቀሳቃሽ ቤተ ክርስቲያን የሆኑ፤
ዘወትር በጸሎት የሚተጉ ሰዎች ናቸው፡፡

ቤተሰብ ፡- ቁጥሩ ከአንድ በላይ የሆነ በመዋለድ፣ በመቀራረብ፣ በማደጎ


ወይም በሌላ መሰል ምክንያቶች በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው
ቤተሰብ ይባላል፡፡
ቤተሰብ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ሲሆን ጌታችን መልካም ዛፍ
መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ እንዳስተማረን ከጥሩ ቤተሰብም መጥፎ
ልጅ ከመጥፎ ቤተሰብም ጥሩ ልጅ በብዛት አይገኝም፡፡

መንፈሳዊነት፡- መንፈሳዊነት በመንፈስ ቅዱስ መመራት እና የመንፈስ


ቅዱስን ፈቃድ መፈጸም ማለት ነው፡፡


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

፩. መንፈሳዊ ሰው ማለት ምን ማለት ነው?

† መንፈሳዊ ሰው የምንለው
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ቃሉን
ወይም ህጉን በቀንና በሌሊት የሚመለከት የሚአሰላስል፣ የሚያወጣ፣
የሚያወርድ ወይም በራሱን በመንፈስ ቅዱስ መስታወት የሚያይ ሰው
በውኃ አጠገብ እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠሏም
እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል መዝ ፩÷፫-፬ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት በውኃ
አጠገብ የተተከለች ብሎ የመሰለው በቁሙ ተክል ሳይሆን የሚናገረው
ስለ መልካም ሰው (መንፈሳዊ ሰው) ህይወት ነው፡፡

ሰውም ተክል ተክሎ ጠዋትና ማታ ውኃ ካላጠጣውና ካልተንከባከበው፣


ካልኮተኮተውና በስሩ ፍግ ካላፈሰሰበት ሊለመልም ሊያብብ እና ሊያፈራ
አይችልም እንዲያውም ያለው እድል መጠውለግና መድረቅ ተነቃቅሎ
መጥፋት ነው፡፡ የተክሉም ባለቤት ትርፉ ድካም እንጂ ምንም ጥቅም
አያገኝበትም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ከክርስቲያን ቤተሰብ የተወለደ ክርስቲያን
የሆነ ሁሉ በአርባ እና በሰማንያ ቀን በእግዚአብሔር ቤት በአጸደ ቤተ-
ክርስቲያን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማህፀነ ዮርዳኖስ ተወልዶ ዕድሜው
ለትምህርት ሲደርስ ቃሉን እለት እለት ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብሎ
በመማር ይኖርበታል፡፡

እንዲሁም በቤተክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት እየተከታተለ ያደገ


እንደሆነ በመልካም ስነ-ምግባር በቤተክርስቲያናዊ ህግና ስርዓት ወይም
በፍፁም በጎ ሥራ ይገለጣል ለሰውም ለእግዚአብሔርም ይጠቅማል አርአያ
እና ምሳሌ በመሆን በአካባቢው ሁሉ መቅረዝ ላይ እንዳለ መብራት
የሚያበራ መልካም ሰው ይሆናል፡፡ እንግዲህ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ
ዳዊት በውኃ አጠገብ እንደተተከለች ተክል የመሰለው እንዲህ ያለውን
ክርስቲያን እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

መንፈሳዊነት በክርስቲያናዊ አነጋገር፣ አለባበስ፣ አረማመድ፣ ገጽታ ወዘተ


ይገለጻል፡፡ ይህ ማለት ግን መንፈሳዊነት ጅልነት፣ ኋላ ቀርነት ወይንም
ደግሞ፣ ንጽሕናን አለመጠበቅ ማለት ግን አይደለም፡፡ በመንፈሳዊነታቸው
የሚደነቁት የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ጎርጎርዮስ
ዘኑሲስ፣ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ ባስልዮስ ዘቂሳርያ በዘመኑ በነበረው
የግሪክ ፍልስፍና እና ዕውቀት የበለጸጉ ነገር ግን ዕውቀታቸውን እና
ሥልጣኔያቸውን በወንጌል የቃኙ ነበሩ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሃይማኖት ወልዶ በምግባር ኮትኩቶ


ተንከባክቦ ያሳደገው ልጁ ጢሞቴዎስን በመልካም ስነ-ምግባር እራሱን
እንዲገነባ እና ለሌሎችም እንዲተርፍ እንዲህ ሲል መክሮታል
እስጠንቅቆታልም፡፡ “አንተ ግን በተማርክበትና በተረዳህበት ነገር ፀንተህ
ኑር ከማን እንደተማርክም ታውቃለህና ከህፃንነትህም ጀምረህ ኢየሱስ
ክርስቶስንም በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን
ቅዱሳን መፃህፍትን አውቀሀል የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና በበጎ ሥራ
ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ
ሁሉ ለትምህርት እና ለተግሳፅ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ባለው
ምክር ደግሞ ይጠቅማል”፡፡ ጢሞ ፫÷፲፬ እስከ ፍፃሜው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እርሱ ካረፈ በኋላ አገልግሎቱን የሚያስቀጥልለት


መንፈሳዊ ሀብቱን የሚያወርሰው ደቀመዝሙር ጢሞቴዎስ ነውና
እርሱን በመልካም ሥራ እንዲጎለብት ደግሞ ደጋግሞ ምዕመናን ፊት
እራሱን ዝቅ አድርጎ እንዳይመለከትና ተደማጭነቱን እየቀነሰ እንዳይሄድ
በመልዕክቱ አጥብቆ ይመክረው ያስጠነቅቀው ነበር፡፡

በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽህናም ምሳሌ ሁን እንጂ


ማንም ታናሽነትህን አይናቀው እስክመጣ ድረስ በማንበብና በመምከር
በማስተማርም ተጠንቀቅ በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
የተሰጠህን በአንተ ያለውን የፀጋ ስጦታ ቸል አትበል በማለት ይመክረው
እንደነበረ መረዳት ይቻላል፡፡ በ፩ኛ ጢሞ ፬÷፲፬-፲፭

አንድ ክርስትያንን መንፈሳዊ ነው የሚያሰኘው ብዙ መስፈርቶች አሉት፡፡


በእርግጥም አንድን ክርስቲያን ክርስቲያን ነው የሚያሰኘው ዝም ብሎ ወደ
ቤተ ክርስቲያን መመላለሱ ብቻ ሳይሆን በሚኖረው መንፈሳዊ ሕይወትም
ጭምር ነው፡፡ “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ አንተን
በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ” መዝሙረ ዳዊት ፭ ፥ ፯ ፡፡

እንደ አባቶቻችን አገላለፅ መንፈሳዊነት የሚመለከተው የሰውነቱን


ማጎንበስ ወይም መንበርከክ ሳይሆን ሰውነቱን ከመንፈሱ ጋር አብሮ
እንዲሰግድ ነው፡፡ ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን በምንሄድበት ጊዜ
ይህንን ቃል ልናስብና ልንገነዘብ ይገባናል፡፡ ቅዳሴም በምናስቀድስበት
ጊዜ ዲያቆኑ የሚያውጀው አዋጅ አለ፡፡ ይኸውም “ስግዱ ለእግዚአብሔር
በፍርሃት” በፍርሀት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ስገዱ ይላል፡፡ ስለዚህ
ወደ ቤተ ክርስቲያን በምንሄድበት ጊዜ ራሳችንን አውቀን፣ ተዘጋጅተን፣
በድፍረት ሳይሆን በፍጹም ፍቅርና ትህትና ከሆነ የመንፈሳዊነት ብርታት
መገኛ የሆነ አምላክ እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ጽናቱንና ብርታቱን
ሰጥቶን በሃይማኖታችን ጸንተን ራሳችንን ገዝተን እንድንኖር ይረዳናል፡
፡ ራስን መግዛት አንዱ የመንፈሳዊነት መገለጫ ነው፡፡ ራስን መግዛት
ሲባል ምላስን፣ ስሜትን፣ ሃሳብን፣ አካሄድን፣ ሆድን (ምግብን)፣ ፀባይን
የመሳሰሉት ናቸው፡፡

፩.፩ በመንፈሳዊ ሕይወት ጸንተን ለመኖር ምን እናድርግ


ሀ. ቃለ እግዚአብሔርን መማር
መንፈሳዊ ሕይወት ቀስ በቀስ የሚያድግ ስለሆነ በአንዴ ተነስቶ መንፈሳዊ
ሰው መሆን አይቻልም። ያለንን መንፈሳዊ ጸጋም እስከመጨረሻው አጽንተን
የምንጓዝ ምግበ ነፍስ የሆነውን ቃለ እግዚአብሔር ስንሰማና ስንማር

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ነው። ሰው መማሩን፣ መጠየቁን፣ የአባቶችን ምክር መስማት ካቆመ


ለተለያዩ ፈተናዎች እየተጋለጠ መሄዱን ያሳያል። “ሰው ከእግዚአብሔር
አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” /ማቴ ፬፥፬/ ተብሎ
እንደተጻፈ መማር፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን ማንበብ፣ አባቶችን መጠየቅ
በእግዚአብሔር እንድንታመን፤ በቅዱሳን አማላጅነና ተራዳይነት አምነን
እንድንጠቀም፤ የቤተክርስቲያናችንን ታሪክ፣ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ዶግማና
ቅኖና እንድናውቅ ያደርጋል። በዘመናችን የተዘረጋውንም የቴክኖሎጂ
የመረጃ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በመጠቀም ለነፍሳችን የሚያስፈልጋትን
ምግብ መመገብ እንችላለን።

ለ. ትእዛዛተ እግዚአብሔርን መጠበቅ


አባቶቻችን ሃይማኖት ካለ ሥርዓት ዋጋ የለውም፤ ካለምግባር መንግሥተ
ሰማያት ሊያስገባን አይችልም በማለት የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሕግ
መፈፀምና መጠበቅ እንዳለብን በአጽንኦት ይነግሩናል። ምክንያቱም
የእግዚአብሔር ሕግና ትዕዛዝ ሁሉን አሟልቶ የያዘ ነውና። እግዚአብሔር
እንዲህ ይላል “የሚወደኝ ቢኖር ትእዛዜን ይጠብቅ” /ዮሐ ፲፬፥፲፭/፡፡
መቼም እግዚአብሔርን የማይወድ ማንም የለም እርሱን የምንወድ ከሆነ
ደግሞ ትዕዛዙን መጠበቅ ነው።

ሐ. ጾምና ጸሎት
ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር፤ እግዚአብሔርን
ማመስገን፣ መለመን፣ መጠየቅ መማጸን ማለት ነው። እንዲሁም ሰው
ሃሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት፣ እግዚአብሔር የሰውን ልመና
ተቀብሎ ፍቃዱን የሚፈፅምበት ረቂቅ ምስጢር ነው። ጾምና ጸሎት
ሁለቱ የማይለያዩ የእግዚአብሔር የበረከት ስጦታዎች ናቸው። እርሱ
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን ፈተና በጾምና በጸሎት ድል
እንደምንነሳው በገዳመ ቆሮንቶስ ለ፵ ቀንና ለ፵ ሌሊት ጾሞና ጸልዮ
አሳይቶናል። ማቴ ፬፥፩ ከዚህም በተጨማሪ ጾምና ጸሎት ወደ ፈተና


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
እንዳንገባ የምንጠበቅበትና ከፈተናም የምንወጣበት ታላቅ መሳሪያ
መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። “ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም
በቀር አይወጣም” /ማቴ ፲፯፥፳፩/

መ. ትዕግሥት
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ትዕግሥት ከመንፈስ ፍሬዎች
አንዱ ነው። /ገላ ፭፥፳፪-፳፫/ የመንፈስ ፍሬ ብሎ የዘረዘራቸው ምግባረ
ሰናያት እርስ በእርሳቸው ግንኙነት አላቸው። ዕምነት ያለው ሰው
የውሃት፣ ቸርነት፣ በጎነት ሊኖረው ይገባል፤ ፍቅር ያለው ሰው ደስታ፣
ሰላም ከእነዚህም ጋር ትዕግሥትም አለው። ፍቅርና ዕምነት ያለው ሰው
እራሱን መግዛት ይችላል። ፍቅር ይታገሳል እንዲል /፩ቆሮ ፲፫፥፬/። ጠቢቡ
ሰሎሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው” /መክ ፫፥፩/ እንዳለ ጸሎታችን ልመናችን
መልስ የሚያገኝበት፣ የሚያስፈልገን ሥጋዊ ነገር የምንናገኝበት፣ እጅግ
አስቸጋሪ መስሎ የሚታየን የብቸኝነት የስደት ኑሮ የሚያበቃበት ጊዜ
አለና ይህን በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል። “ቢዘገይም በእርግጥ
ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም” /ዕን ፪፥፫/

ሠ. ከክፉ ባልንጀራ መራቅ


በዚህ በምንኖርበት በስደት ዓለም ከማን ጋር መዋል፣ መነጋገር፣
መወያየትና መመካከር እንዳለብን ካለወቅን ልንነሳ በማንችልበት አወዳደቅ
ልንወድቅ እንችላለን። ብዙዎች በጓደኛ ምክንያት ከእምነታቸው፣
ከባህላቸው፣ ወጥተው ማንነታቸውን ለውጠው የክፉ ጓደኛቸውን ገጸ
ባህሪ ተላብሰው እናገኛቸዋለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አትሳቱ፤
ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል። በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም
አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና” /፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፴፫/ እያለ
ምን ዓይነት ጓደኛ መከተል እንዳለብን ይመክረናል። ክፍ ባልንጀራ
የጀመርነውን መንፈሳዊ ሕይወት እስከመጨረሻው እንዳንዘልቅ እንቅፋት
ይሆንብናል።
፲፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ፤ መልካም ሥራቸው በእግዚአብሔርም


ሆነ በሰውም ዘንድ የተወደደላቸውና ለሌሎች ሰዎች በአርአያነት
የሚነሱ፤ በቤተ ክርስቲያን ጆሮ ውስጥ ጥዑም ቃና ያላቸው፤ ሕያው
መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ተንቀሳቃሽ ቤተ ክርስቲያን የሆኑ፤ ዘወትር
በጸሎት የሚተጉ ሰዎች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ከእኛ የሚጠበቁ ነገሮችን


እያደረግን፣ የቀረውን ነገር እግዚአብሔር በቸርነቱ እንዲጎበኘን በጸሎት
እየለመን፣ በመንፈሳዊ ሕይወት እድንጓዝ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን
ማስወገድ ይኖርብናል።

፩.፪. መንፈሳዊ ሰው በቤተሰቦቹ መካከል


የቤተሰብ መገኛው ጋብቻ ነው፡፡ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ የተፈጠረ
አይደለም በማኅበር ይኖር ዘንድ ማኅበረሰቡም የሚጠይቀውን ነገር
ያደርግ ዘንድ ግዴታ አለበት፡፡ እግዚአብሔር ያለበት ትዳር የጥሩ ቤተሰብ
መገለጫ ነው፡፡ የጥሩ ቤተሰብ መገለጫው ደግሞ የበጎ ጥሩ ማኅበረሰብ
መገኛ ነው፡፡ የትኛውም ስብዕና ግንባታ መጀመሪያው ቤተሰባዊ ግንባታ
ነው፡፡ አባቶቻችን ከጥሩ ቤተሰብ በመገኘታቸው ጥሩ ሆነው አድገው
የእግዚአብሔርን ስም የሚያስጠራ ሥራዎችን ሰርተው አልፈዋል፡
፡ ለምሳሌ፡- ይስሐቅን እና አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖትን ማንሳት
ይቻላል፡፡

ቤተሰብ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ሲሆን ጌታችን መልካም ዛፍ


መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ እንዳስተማረን ከጥሩ ቤተሰብም መጥፎ
ልጅ ከመጥፎ ቤተሰብም ጥሩ ልጅ በብዛት አይገኝም፡፡ ስለዚህ ባልና
ሚስት በኑሮአቸው ውስጥ በጎ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ተለማምደው
በእሱ መኖር ከቻሉ የሚወልዷቸው ልጆች ለቤተሰብም ለሃገርም ጠቃሚ
ይሆናሉ ስለዚህም፡
፲፪
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
. መንፈሳዊ ሰው ቤተሰቡን ያዳምጣል ያከብራል
. ከቤተሰቡም ጋር መልካም ንግግር እና ውይይት ያደርጋል
. ከሥራም ሆነ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲመለሱ ወላጆቻቸውን
በሥራ ያግዛሉ
. እናት አባታቸውን ታላላቆቻቸውን እንዲሁም ታናናሾቻቸውን በመታዘዝ
ያከብራሉ
. ከቤተሰብ ጋር እንዲሁም በግል ጸሎት ያደርጋሉ
. መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና በተጨማሪም ደግሞ ከትምህርት ቤት
የሚሰጣቸውን የቤት ሥራ ይሠራሉ ያጠናሉ፡፡

† ልጆች ለወላጆች
ሰው ወደዚህ ዓለም ከመጣበት ከመጀመሪያው ሰዓት አንስቶ ያልተለዩትን፤
በማልበስ፤ በመመገብና በመምከር ያሳደጉትን ስለ ልጆቻቸው ያለማቋረጥ
የሚጨነቁትን ወላጆቹን መርሳት የለበትም፡፡ምክንያቱም አባት እና
እናቱን የሚያከብር ወላጆቹን የሚያስብ ልጅ ዕድሜው ረጅም ኑሮውም
መልካም ይሆንለታል፡፡

“አባትና እናትህን አክብር እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር


ዕድሜህ እንዲረዝም፤ መልካምም እንዲሆንልህ“ እንዲል ዘዳ.፮፥፲፮
የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንኑ ቃል መሠረት በማድረግ
“መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትና
እናትህን አክብር“ ኤፌ.፮፥፪-፫

ስለዚህ መንፈሳዊ ሰው የሥነ ምግባር መጀመሪያ የሆነውን ወላጆችን


የማክበር አገልግሎት መፈጸም ነፍሱንና ሥጋውን በበረከት ማክበር አለበት፡
፡መንፈሳዊ ሰው ወላጆቹ ያደረጉለትን ሁሉ በማስታወስ ፍቅራቸውን፤
ቸርነታቸውን፤ ትዕግስታቸውን፤ ምክራቸውንና ተግሳጻቸውን ለማን
እንደሆነ መመስከር ይጠበቅበታል፡፡ ሌላው ለወላጆች የምናደርገው ነገር
፲፫
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ቢኖር ባለን አቅም መርዳት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ነገር


ግን ለእርሱ ስለሆኑትም ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን
ሃይማኖቱን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው“ ፩ጢሞ. ፭፥፰

፩.፫. መንፈሳዊ ሰው በአካባቢው


መንፈሳዊነት የሚጀምረው ከመኖሪያ ቤታችን ሲሆን በመኖሪያ ቤታችን
ውስጥ ከእናት ከአባት ከእህት ከወንድሞቻችን ጋር መልካም የሆነ
መንፈሳዊ ህይወትን መኖር ስንችል ይህንን መልካም የሆነውን መንፈሳዊ
ህይወታችንን በአካባቢያችንም ልንጠቀምበት ይገባል ምክንያቱም
ማኅበራዊ ኑሮን መኖር የሚጀምረው ከአካባቢው ሰዎች ጋር ነው፡:

ከዚህ አንፃር ጥሩ ማኅበራዊ ኑሮ እሴቶች የሚያስተምር ቤተሰብ በአካባቢው


መሥራትን ፣ ከሰዎች ጋር ሆኖ መወያየትን እንዲሁም በመንፈሳዊያት
ማኅበራት እንደ (የጽዋ ማኅበር፣ ሰንበቴ፣ ዝክር) በሚኖሩበት ሁኔታ ላይ
አስተዋጽኦን ማበርከት ይችላል፡፡
፩. የአካባቢያችንን እና የግል ንፅህና መጠበቅ
፪. በሃዘንና በደስታ መረዳዳት
፫. ለችግሮቻቸው ፈጥነን መፍትሔ መስጠት
፬. ከጎረቤቶቻችን ጋራ የግጭት ምክንያቶችን ማጥፋት
፭. ስንገባ ስንወጣ ለጎረቤቶቻችን ሰላምታ መስጠት
፮. በተቻለ መጠን በሁሉ ነገር በጎ አርአያ መልካም አብነት ሆኖ መገኘት
፯. የአካባቢ ጓደኞቻችንን ቤታችን ጠርተን ጸበል ፀዲቅ ማድረግ ዝክር
ማዘከር
፰. ለወላጆቻችን በአካባቢያቸው ላይ ማህበራዊ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን
ለምሳሌ እድር እቁብ ሄዶ መክፈል…
፱. ሌሎችንም ሆነ እኛን የሚጠቅሙ ነገሮችን ማድረግ ለምሳሌ
አቅመደካሞችን መርዳት
፲. ከአካባቢያችን ካሉ ልጆች ጋ በጋራ ማጥናት እና መጫወት
፲፬
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

የመንፈሳዊ ሰው ሥነ ምግባር ቦታና ጊዜ የሚወስነው ሳይሆን በማንኛውም


ሥፍራ የሚታይና ዘወትር የሚገለጽ የሰው ልጅ በሚኖርበት አካባቢ
በተግባሩ የሚጠላ፤ በሆነው ባልሆነው የሚጋጭ፤ በረባሽነቱ አካባቢውን
የሚያሰለች መሆን የለበትም፡፡

በአንጻሩ በመልካም ተግባሩ የሚታወቅ፤ አርአያ የሚሆን፤ የተቸገረን


በአቅሙ የሚረዳ ኀዘንተኞችን የሚያጽናና፤ የተጣሉትን የሚያስታርቅ
ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡

በክርስትና ትምህርት የሰው ልጅ ከራሱ ይልቅ ለሌሎች እንዲያስብ፤


ለሀገሩ፤ ለሕዝቡ እንዲጨነቅ ይማራል፡፡ ምክንያቱም ከክርስቶስ
የምንማረው ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠትን ነውና፡፡ ክርስትና ማለት
በሁሉ ነገር ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ ጌታችን ከመወለዱ በፊት በሰውና
በእግዚአብሔር፤ በሰውና በመላእክት፤ በነፍስና በሥጋ፤ በሕዝብና አሕዛብ
መካከል ሰላም አንድነት አልነበረም፡፡ ክርስቶስ ሲወለድ ግን ሰላም፤ እርቅ
፲፭
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

በመስፈኑ በእነዚህ ሁሉ መካከል ሰላም ሆኗል፡፡ የማኅበር የአንድነት


ሕይወት ተጀምሯል፡፡

፩.፬. መንፈሳዊ ሰው በትምርት ቤት


መንፈሳዊ ህይወት ቦታ የሚገድበው በቦታ የሚወሰን አይደለም
መንፈሳዊነታችንን ልናሳይበት ከሚገቡን ቦታዎች አንዱ ትምህርት
ቤት ነው፡፡ ማንኛውም ተማሪ በትምህርት ገበታው ላይ ሊያከብራቸው
የሚገቡ የሥነ ምግባር ሕግጋት አሉ፡፡ እነዚህ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣
ዘርና ባህልን ሳይለዩ ሁሉም ሰው የሚስማማባቸውና ሊፈጽማቸው
የሚገባ ሕግጋት ናቸው፡፡ አንድ መንፈሳዊ ሰው በትምህርት ቤቱ ውስጥ
ከሁሉም የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር በፍቅር፣ በትህትና፣ በኅብረትና
በአንድነት ሆኖ ሊማር ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ከመንፈሳዊ ሰው ከጎበዝ
ተማሪ ቅንነት፣ ታታሪነት፣ ታማኝነት እና ታዛዥነት እንደሚጠበቀው
ሁሉ የሚከተሉት ነገሮች በተጨማሪ ይጠበቃሉ፡፡

፩. በምንማረው ትምህርት ላይ ትዕግስት እና ጽናትን ማሳየት


፪. ትምህርትን በንቃት እና በትጋት መከታተል
፫. መምህርን (የእውቀት አባትን እና እናትን) ማክበር
፬. በትምህርት ውጤታማ መሆን
፭. የትምህርትን ሰዓት አክብሮ መግባት እና መውጣት ለትምህርት ቤቱ
ህግና ሥርዓት ተገዢ መሆን
፮. የሚሰጠንን የቤት ሥራ በሚገባ መጠን ሰርተን በሰዓቱ መገኘት
፯. በምንማረው ትምህርት ጎበዝ ብንሆንም አለመታበይ ምክንያቱም
የእውቀት ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑን ዘወትር መረዳት
፰. በምንማረው ትምህርት ራሳችንንም ሰውንም ለመጥቀም መጣር
የምንማረው እና የተማርነው ለሌሎች እንደሆነ ማወቅ
፱. የምንማረውን ትምህርት ማጥናት
፲. የራስን አክብሮ መስራት የሌላን አለመሻት (አለመኮረጅ)
፲፮
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
፲፩. በአለባበስ በአነጋገር በአጠቃላይ በአኗኗር ምሳሌ መሆን
፲፪. ሌሎችን እንደ ራስ መውደድ
፲፫. በራሳችን እንዲሆን የማንፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አለማድረግ

፩.፭. መንፈሳዊ ሰው የትምቦታ


መንፈሳዊ ሰው የትም ቦታ ሲኖር ለምሳሌ በስደት /በባዕድ አገር/
በትምህርትም ሊሆን ይችላል ወይም በሌላ ነገር ሁልጊዜ እግዚአብሔርን
ማሰብ አለበት ምክንያቱም እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ የለም እግዘአብሔር
በሁሉም ቦታ ይገኛል:: በተጨማሪም መንፈሳዊነቱን በጠበቀ ሁኔታ
ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ መንፈሳዊ ሰው
በሃይማኖት ከሚመስለው ሰው ጋር ብቻ አይደለም መንፈሳዊነቱን
የሚገልጸው በሃይማኖት ከማይመስሉንም ጋር መንፈሳዊነታችንን በጠበቀ
ሁኔታ ጥሩ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል፡፡

፲፯
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ሕይወትን በእውነት በአርአያነትና በምሳሌነት


እንዲሁም በምግባር የመግለጽና የመኖር ሕይወት ነው፡፡ ይህንንም
መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት
እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ›› በማለት (፩ኛ ዮሐ.፫፥፲፰)። የቃልና
የአንደበት ሕይወት ሳይሆን የተግባር ሕይወት ነው ኦርቶዶክሳዊነት፡፡
በሃይማኖትና በፍሬ ራስን የመምራት (የመኖር) ሃይማኖትን በምግባር
የመግለጥ እውነትን (ሕይወትን) በተግባር የመግለጥ ዓለምና የዓለም
የሆኑ ነገሮችን የመጥላት ዘወትር ስለ ነገረ እግዚአብሔር ስለ ቅድስና
ሕይወት፤ ስለ ዘለዓለማዊ ጸጋና ክብር እያሰቡ የመኖር ሕይወት ነው፡
፡ ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ሕይወትና እውነት ነው፡፡ ለዚህ ነው
ጌታችን ‹‹እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው›› ያለን
(ዮሐ.፮፥፷፫)፡፡

ማቴ ፭፥፲፮ ላይ ‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን


አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ››
ተብሏልና መንፈሳዊ ሰው በሁሉም ቦታ ላይ መንፈሳዊነቱን ሊያንጸባርቀው
ይገባል፡፡
. መፆም መጸለይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ማገልገል
. ነገረ እግዚአብሔርን ማስተማር
. አነጋገራችንም ሆነ አለባበሳችን መንፈሳዊነታችንን የሚገልጥ መሆን
አለበት
. አመጋገባችንም ሆነ አረማመዳችን መንፈሳዊነታችንን የሚገልጥ ሊሆን
ይገባል፡፡
የማጠቃለያ ጥያቄ
፩. መንፈሳዊ ሰው በቤተሰቦቹ መካከል ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
፪. መንፈሳዊ ሰው በአካባቢው ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
፫. መንፈሳዊ ሰው በትምህርት ቤቱ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
፬. መንፈሳዊ ሰው በሁሉም ቦታ ላይ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል

፲፰
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ምዕራፍ ሁለት

ክፋት

ዓላማ
ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ሲያጠናቅቁ

. ክፋት ምን እንደሆነ እና የሚያስከትለውን ጉዳት ይገነዘባሉ


. ሰላማዊ ሰው ማለት ምን እንደሆነ ግንዛቤ ያገኛሉ
. ስለ ደስታና የደስታ ምንጮች ግንዛቤ ያገኛሉ

ማስጀመርያ ጥያቄዎች

፩. ክፉ ምንድን ነው?
፪. በእናንተ አመለካከት ክፉ የሚባል ሰው ምን የሚሠራ
ነው?

፲፱
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ቁልፍ ቃላት

. ሰላም ፡- አማን፣ ደኅና፣ ጤና፣ ዕረፍት


. ደስታ ፡- ተድላ፣ ድሎት፣ፍሥሐ፣ ምቾት
. ክፋት:- ምቀኝነት፣ ተንኮለኝነት፣ መጥፎ መሥራት


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

፪.፩. ክፉውን በክፉ አለመመለስ

ክፋት ማለት ምቀኝነት፣ በሰው ላይ ተንኮል ማድረግ፣ በእግዚአብሔርም


በሰውም ዘንድ የተጠላ ሥራ መሥራት ማለት ነው። ደስታ የሚገኘው
ከክፋት በመራቅ ነው። የደስታ ምንጩ መልካምነት ነው። መጽሐፍ
ቅዱስ እንዲህ ይላል “እኔ ግን እላችኋለሁ ክፉውን በክፉ አትቃወሙ
ነገር ግን ቀኝ ፊትህን ቢመታህ ግራህን መልስለት”፡፡ /ማቴ ፭፥፴፰/

ክፉን በክፉ አለመመልስ ስንል ሰው ሁሉ ሰውን በሰውነቱ እንዲወድ


የተሰጠው ሕግ በተግባር መተርጎሙን የምናረጋግጥበት የክርስቲያን ስነ-
ምግባር ትልቁ መለኪያ ነው፡፡ /ማቴ ፭፥፴፭ ዘጸ ፩፥፳፫/

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ” ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ


አትሸነፍ (ሮሜ ፲፪፥፳፩)” እንዳለው በጎ ሕሊና ያላችሁ ወገኖች
መልካምነትን፣ ፍቅርን፣ መዋደድን፣ መከባበርን፣ መተዛዘንን፣ ከምንም
በላይ እግዚአብሔርን መፍራትን በተግባር ማሳየት አለብን።

ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር በሥራ መገለጣቸው የሚመዘኑባቸው ቃላተ


ወንጌል አሉ፡፡ እነዚህም፡-
. የተራቡን ማብላት /ማቴ ፭፥፴፭/
. የተጠማን ማጠጣት /ማቴ ፭፥፴፭/
. እንግዳን መቀበል /ማቴ ፭፥፴፭/
. የታረዘን ማልበስ /ማቴ ፭፥፴፭/
. የታመመን መጠየቅ /ማቴ ፭፥፴፭/
. ክፉውን በክፉ አለመመለስ ፡- አይቶ ሰምቶ ነገሮችን ሁሉ በትዕግስት
ማለፍ ማለት ነው፡፡
/ የቁጣን ብልጭታና የበቀልን ስሜት ታግሦ የማሳለፍ ችሎታው እያነሰ
ካልሆነ በቀር አብዛኛውን ጊዜ ከቁጣና ቁጣ ከሚያስከትላቸው ክፉ ነገሮች

፳፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ይልቅ ክፉን በበጎ ለመመለስ መቻል ሚዛናዊ ድልን ያስገኛል፡፡


. አይቶ ሰምቶ ነገሮችን ሁሉ በትዕግስት ማለፍ ራሱን የቻለ መንገድ
ሆኖ በቀልን ለእግዚአብሔር መስጠት ጥሩ የሥነ ምግባር መለኪያ ነው፡፡
. ክፉ ለሚያደርጉ ወገኖች በጎ ምላሽ መስጠት፤ ራስን ከስሕተት ከጥፋት
ማዳን ነው፡፡ ሌሎችንም ከክፉ ተግባር መመለስ የፍቅርን፤ የትዕግሥትንና
የትሩፋትን ሥራ ማስተማር ከክፉ እምነት ወደ በጎ ማስገባት ነው፡፡ ይህ
ደግሞ ለሁለቱም ወገን ዋጋንና ጥቅምን ያስገኛል፡፡

. ”እኔ ግን እላችኋለሁ ክፉን በክፉ አትቃወሙ ነገር ግን ቀኝ ፊትህን


ቢመታህ ግራህን መልስለት--- ” ማቴ.፭፥፴፰
. ሕይወቱ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ክርስቲያን ለክፉዎችና ለበጎዎች
የሚመልሰው መልስ በጎ የሆነውን ሰላምን የሚያሰፍነውንና ፍቅርን
የሚያጸናውን ብቻ መሆን አለበት፡፡ይህም የክርስትና ራስና ፈጻሚ ከሆነው
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ ነው፡፡

. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ በተያዘበት ዕለት


መከራ ላጸኑበት ሁሉ ክፉ አልመለሰላቸውም፡፡ ይንንም ሐዋርያው ቅዱስ
ጴጥሮስ ”እርሱም ኃጢአት አላደረገም ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም
ሲሰድቡትም መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም ”፩ጴጥ.
፪፥፪-፳፫ በማለት መስክሯል

.ሊያስይዘው ጭፍራ አስከትሎ የመጣውን ይሁዳንም ”ወዳጄ ” ብሎታል፡


፡ ከቃሉ ግርማ የተነሳ ተፍገምግመው የኋሊት የወደቁትን አይሁድንም
ሊይዙት ይችሉ ዘንድ አጽንቷቸዋል፡፡ መላእክት እንኳን ሊያዩት
የማይችሉትን ፊቱን በጥፊ የመታውን ተቆጥቶ አላጠፋውም፡፡ ለሁሉም
በጎ ምላሽ ሰጠ እንጅ፡፡ ማቴ. ፳፮፥፶ ዮሐ. ፲፰፥፬-፰

፳፪
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
“የእግዚአብሔር ፍቅር የሁሉም ጥሩነት፣ የሁሉም መልካምነት፣
የሁሉም የሥነ-ምግባር ጥንካሬ ስር ነው።”......መጽሐፋችንም በማቴ5:44
ላይ እንዲህ ይላል፦ «ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ።» የሁለም
ሰው መልካምነት፣ የሁሉም ሰው ቸርነት ስሩና ምንጩ የአምላካችን
የክርስቶስ ቸርነትና ደግነት ነው።«አትበቀሉ፥... በቀል የእኔ ነው፥ እኔ
ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ» በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
ለሮማ ክርስቲያኖች የጻፈው በወንጌል መድኃኒታችን «ክፉውን በክፉ
አትቃወም» በማለት ካስተማረው በመነሣት ነው።

፪.፪. ሰላማዊ ሰው ስለመሆን

ሰላም ‹‹ተሳለመ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጒሙም


መፋቀር፣ መዋደድ ማለት ነው፡፡ ሰላም በሕይወት ስንኖር ልናጣቸው
ከማይገቡ ነገሮች የመጀመሪያው ነው፡፡ ሰላም የፍጥረታት ሁሉ የሕይወት
መርህ ነው፡፡ ሰላም/ፍቅር/ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ነው፡፡ ሰላም የሕይወት
ማጣፈጫ ቅመም ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ለማኅበራዊ ኑሮ
መሠረቱ ሰላም ነው፡፡ ሰላምን በዋጋ መተመን በወርቅ በብር መግዛት
አይቻልም፡፡ ሰው እርስ በእርስ በሰላም በፍቅር በአንድነት የማይኖር ከሆነ
ምስጢረ ሥጋዌን /የአምላክን ሰው መሆን/ ምስጢራዊነት አለመረዳት
ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን ነውና፡፡

ሰላምን የምንሻ ከሆንን ሰላማውያን ከመሆን በተጨማሪ ሌሎችም


ሰላማውያን እንዲሆኑ የምንችለውን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከጥፋት
ልንድን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ከጥፋት ማዳን ይኖርብናል፡፡‹ ‹ሰላምን
ፈልጉ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ›› (ት.ኤር. ፳፱፥፯)
ሰላም በስምምነት በአንድነት በፍቅር የምንኖርበት የዕረፍትና
የተስፋ ስሜት የተሞላበት ህይወት ነው፡፡ ሰላማዊ ሰው ማንም ሰው
ያሳድደኛል ብሎ አያስብም ተረጋግቶ ይኖራል እንጂ፡፡

፳፫
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

የሰው ልጅ ሰላምን የሚመሰርተው


. የሰላም ንጉስ የሰላም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆነ በመረዳት
. በአርቆ አሳቢነት
. በሆደ ሰፊነት
. ከማህበረሰቡ ጋር ተደማምጦና ተስማምቶ በመኖር
. ለእኔ ይቅርብኝ ላንተ ይሁንልህ የሚል ሲሆን

ዓለምን የለወጡ ለጨለማው ዓለም ብርሃን የሆኑ ሰላማውያን ሰዎች


ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌ ቅዱሳን ሐዋርያትን ማንሳት እንችላለን፡፡ ሰላማዊ
የሆኑ ሰዎች የዘወትር ሐሳባቸው ፈቃደ እግዚአብሔር ያለበትንና
ስሙም የሚመሰገንበትን፤ የሰው ልጅ የሚጠቀምበትን፤ ሰላም ዕርቅና
አንድነት የሚወርድበትን፤ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርብና ከእርሱም ጋር
ሊኖር የሚያስችል መልካም ሥራ መሥራትን ይወዳሉ፡፡ በማኅበራዊ
ሕይወትም የሌላውን ድካምና ስህተት ለቅመው ከመክሰስና ከመተቸት
ይልቅ ባለማወቅ ያጠፋውን ወደ ማወቅ አድርሰው ከጥፋቱ ያርሙታል፤
የደከመውን ያበረቱታል፡፡ በሁሉ ክፉውን ወደ መልካም ይለውጡታል፡፡
ሕይወታቸው በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን በሰውም ፊት የተገለጠ
ስለሆነ በኅብረተሰቡም ፊት መልካም የሆነውን ይፈጽማል፡፡ /፪ቆሮ.
፰፥፳-፳፪/

ቤተ ክርስቲያንም ሁልጊዜ በአስተምህሮዋ በቅዳሴዋ ‹‹ሰላም ለኵልክሙ/


ሰላም ለሁላችሁ ይሁን›› እያለች ትሰብካለች፡፡ ሰላም የተጀመረው
በጥንተ ተፈጥሮ ነው፡፡ መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ሁሉም መላእክት
ማን ፈጠረን እያሉ በተረበሹ ሰዓት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በያለንበት
እንጽና /አትረበሹ/ ተረጋጉ በማለት የመጀመሪያውን የሰላም ብሥራት
አብስሯል፡፡ ስለዚህ የሰላም አስተማሪ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አባቶቻችን
ስለ ሰላም ብዙ ጽፈዋል፣ ብዙ መሥዋዕት ከፍለዋል፡፡

፳፬
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
ሰላማዊ መሆን በጎነት ነው፡፡ ጻድቁ ኢዮብ እንዲህ ይለናል፡፡ ‹‹አሁንም
ከእርሱ ጋር ተስማማ ፣ሰላምም ይኑርህ፣ በዚያም በጎነት ታገኛለህ፡፡››
(መ.ኢዮብ ፳፪፥፳፩) ሰላማዊ መሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፡፡ ያለ
ሰላም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከሁሉ ጋር
ወደ ሰላም ሩጡ›› (ዕብ. ፲፪፥፲፬) ሰላማዊ ሰው መሆን ፍላጎትን ማሳኪያ
መንገድ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ትእዛዜን ብትሰማ ኑሮ
ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር ዘርህም
እንደ ባሕር አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፡
፡›› (ት.ኢሳ.፵፰፥፲፰) በማለት እንደተናገረው፣ ሰላማዊ መሆን ለራስም
ለሌሎችም ደስታን መፍጠር ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹የዋሆች ግን ምድርን
ይወርሳሉ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል›› እንዲል፡፡ (መዝ. ፴፮፥፲፩)
ሰላማዊ መሆን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ማምጣት ነው፡፡ ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ
በአንድ ልብ እና በአንድ ሐሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጅ
መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ››
በማለት በአጽንኦት ይመክረናል፡፡ (፩ኛ.ቆሮ. ፩፥፲)

፪.፫. ደስታና የደስታ ምንጮች

ደስተኛ ማለት ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት የሌለበት በደል ኃጢአት


ስለማይሰራ በደስታ በተመስጦ መንፈስ የሚኖር ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ
የደስታ ምንጭ እግዚአብሔር እንደሆነ ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል
ምክንያቱም ደስታ የሌለው ሰው እግዚአብሔር የለውም ቅዱስ ጳውሎስ
እንዳለው “ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ”
የደስታ ምንጭ በሆነው በጌታ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ደስተኝነት የቅድስና
የእውነተኝነት ምልክት ነው፡፡ ሰው በጸሎቱ ከእግዚአብሔር ጋር
በመነጋገሩ ደስ ይለዋል፡፡ ምጽዋት በመስጠቱ ለእግዚአብሔር እንደሰጠ
ቆጥሮ ደስ ይለዋል፡፡ ምግባር ትሩፋት በመስራቱ ግዳጁን እንደተወጣ

፳፭
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ስለሚቆጥር የደስታ ስሜት ይሰማዋል፡፡ ደስታ የመንፈስ ፍሬ እንደሆነ


መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ገላ ፭፥፳፪

ደስታ፡-ማለት ተድላ፣ ድሎት፣ፍሥሐ፣ ምቾት ማለት ነው።(ኪ. ወ.


መዝገበ ቃላት) በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን በደስታ እንዲኖር
ፈጠረው፡፡ እርሱ ሰውን በአትክልት ሥፍራ ውስጥ በኤደን ገነት
አስቀመጠው፡፡ ምቾት ያላቸውን ሀብቶች ሁሉ አቀረበለት፡፡ ለሰው
ሁሉንም ነገሮች ፈጠረለት ሰማይ፤ ብርሃን፤ ወንዞች፤ ፍሬያትን፤
አበቦች፤ -----ወዘተ በዘላለማዊው መንግስት ሊገለጹ የማይችሉ ሌሎች
ደስታዎችን አዘጋጀለት፡፡ ዓይን ያላየውን፤ ጆሮም ያልሰማውን በሰው
ልብም ያልታሰበውን ደስታ አዘጋጀለት፡፡ ፩ቆሮ. ፪፥፱ ከዚህ በላይ
ሰውን በመሞቱ ከወዳጆቹ ከመላእክትና የጻድቃን ነፍሳት ጋር ደስታን
ወደሚያጣጥምበት ወደ ገነት አሸጋግሮታል፡፡

በዚህ ጊዜያዊ ሕይወት እንኳን እግዚአብሔር ለሰው ብዙ ደስታዎችን


አዘጋጅቶ አቅርቦለታል፡፡
ይህም ለሰው በእያንዳንዱ ሳምንት ውስጥ እረፍት ሊወስድና ሊደሰትባቸው
የሚችሉ ቀናትን ሰጥቷል፡፡ በብሉይ ኪዳንም እግዚአብሔር ለሰው ደስታ
የሚውሉ የተቀደሱ በዓላትን ሰጥቷል፡፡ ዘሌ. ፳፫

እውነተኛ ደስታ ለሥጋና ለስሜት የተገባ ሳይሆን ለመንፈስ የተገባ ነው፡


፡ ሰው በመብላትና በመጠጣት ወይም ውብ የሆነ ትዕይንት በማየት
ወይም በመስማት እርካታ ሊሰማው ይችላል፡፡ እነዚህ ሥጋዊ እርካታዎች
ናቸው፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊ መዝሙር ወይም መንፈሳዊ ቃላትን
በመስማት መንፈስ የራሱን ድርሻ ይወስዳል፡፡ እዚህ ላይ ደስታውም
ደግሞ መንፈሳዊ ነው፡፡

፳፮
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

፪.፬ የመንፈሳዊ ደስታ ምንጮች


. ራስን በእግዚአብሔር ሕልውና እና ጥበቃ ውስጥ ማድረግና ከእርሱም
ጋር በመገናኘት መደሰት ነው፡፡ ዮሐ. ፲፮፥፳፪
. በንስሓ እና ኃጢአትን በማስወገድ መንፈሳዊ ደስታ ይገኛል፡፡ ሉቃ.
፲፭፣ መዝ. ፶፩፥፰-፪
. የራስ የሆነ ማንኛውንም መልካም ተግባር በመፈጸም መንፈሳዊ ደስታ
ይገኛል፡፡ ፪ቆሮ. ፱፥፯
. እግዚአብሔርን የሚወድና በእግዚአብሔር የሚወደድ ሰው ሁል ጊዜ
ደስተኛ ይሆናል፡፡
. አገልግሎታችን ስኬታማ በሚሆንበት ጊዜ እንደሰታለን፡፡
. እያንዳንዱ ሰው በድካሙ ፍሬ እና አግዚአብሔር ለእርሱ በሰራለት
ሥራ ይደሰታል፡፡ መዝ.፲፪፥፷፫
. እውነተኛ ደስታን የምናገኘው ከራሳችን ይልቅ በቅድሚያ ለሌሎች ሰዎች
ትኩረት ስንሰጥ ነው! ምክንያቱም “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጡትን
ይወዳል” (፪ቆሮ ፱፥፯)
. ይቅርታ ማድረግ እና ይቅርታን መጠየቅ እንዳለብን በማወቅ! “የጽዮን
ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥
በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም
ይበልሽ ምክንያቱም እግዚአብሔር የተፈረደብሽን ፍርድ አስወግዷልና”
(ት. ሰፎ ፫፥፡፲፬-፲፭)

፳፯
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

የማጠቃለያ ጥያቄዎች
፩. ክፉውን በክፉ መቃወም ማለት ምን ማለት እንደሆነ በዝርዝር
አስረዳ፡፡
፪ ሰላም እንዴት እንደሚገኝ እና ሰላማዊ ሰው ምን እንደሚያስፈልገው
አስረዳ፡፡
፫ ደስታ ማለት ምን ማለት ነው?
፬ የደስታ ምንጮች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር አስረዳ፡፡

፳፰
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ምዕራፍ ሦስት

ዓለማዊነት እና መገለጫዎቹ

ዓላማ
ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ሲያጠናቅቁ

. ስለ ዓለማዊነት መገለጫዎችን በዝርዝር ይገነዘባሉ


. የስጋ ሥራ እና ውጤቱ ምን እንደሆነ ይገነዘባሉ
. ከዓለም ስለመራቅ እና ራስን ለእግዚአብሔር መስጠትን ይገነዘባሉ

ማስጀመርያ ጥያቄዎች

፩. ዓለም ምንድን ናት?


፪. ዓለማዊነት ማለት ምን ማለት ነው?
፫. የዓለማዊነት መገለጫዎች እነማን ናቸው?

፳፱
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ቁልፍ ቃላት

. ዓለማዊነት ፡- ማለት ዓለምን የሚወዱ ከክርስቶስ ይልቅ ራሳቸውን


ለዓለም አሳልፈው የሰጡ መንፈሳዊውን ሳይሆን ሥጋዊ ፍላጎታቸውን
ብቻ ለማሟላት የሚጥሩ ሰዎች ማለት ነው፡፡

. እግዚአብሔርን መውደድ፡- ማለት የቅድስና የእውነተኝነት ምልክት


ነው፡፡ ምክንያም የደስታ ምንጩ እግዚአብሔር ነውና፡፡ ክፋት፣ ተንኮል፣
ምቀኝነት የሌለበት በደል ኃጢአት ስለማይሰራ በደስታ በተመስጦ መንፈስ
የመኖር ውጤት ነው፡፡


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

፫.፩. ዓለማዊነት እና መገለጫዎቹ

ሀ) ዓለማዊነት
ዓለማዊነት ማለት የእግዚአብሔርን ፍቅር ትቶ እግዚአብሔር
እንድንጠቀምባቸው ከፈጠራቸው ፍጥረታት ጋር መጣበቅ ነው፡፡ ስለዚህ
ዓለማዊነት የፍቅርን አቅጣጫ ከእግዚአብሔር ወደ ዓለም ማዞር ነው::
ከዚህም አልፎ ኃጢአትንና ራስ ወዳድነትን ህጋዊ ማድረግም ነው፡፡

ዓለማዊነትን (Secularism) እንደ ርዕዮተ አለም የሚያራምዱ ሰዎች


የእግዚአብሔርን መኖር ላይክዱ ይችላሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የመኖር
ዓላማ ግን የላቸውም፤ ስለ ድኅነትና የዘላለም ህይወት ብለውም ምንም
ዋጋ መክፈል አይፈልጉም፡፡

ዓለማውያን (Seculars) እግዚአብሔርን ከፈለጉት እንኳ የሚፈልጉት


ዘላለማዊ ለሆነ ፍቅር ሳይሆን በዚህ ዓለም የበለጠ ደስተኛ እንዲያደርጋቸው
ብቻ ነው፡፡ ‘የሃይማኖተኞቹ’ ዓለማውያን የእምነት መግለጫ ‘ሃይማኖተኛ
ሆኖ መኖር በዚህ ዓለም የበለጠ ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ይጠቅማል’ የሚል
ነው፡፡’ዓለማዊነት’ ማለት ‘ዘመናዊነት’ ማለት አይደለም፤ ዓለማዊነት
ያልነበረበት ዘመን የለምና፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር
ፈቃድ ርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ
ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን
ዓለም አትምሰሉ፡፡›› (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲፬) በማት ያስተማረው፡፡

ለ) ዓለማዊነት መገለጫዎቹ
ዓለማዊያን ዓለምንና በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን የሚወዱ ናቸው፡
፡ ዓለማዊያን ደስታንና እርካታን ሁሉ ከዓለም ማግኘት ስለሚፈልጉ
ደስታቸው ጊዜያዊ ነው፡፡ ጊዜያዊ ደስታቸውን ለማግኘት ሲሉ ግን
፴፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

የዘላለማዊ ደስታ ባለቤት እግዚአብሔርን ረስተው በኃጢአት ይዘፈቃሉ፡


፡ በመሆኑም ዓለማዊያን ቢያንስ የሚከተሉት መገለጫዎች አሏቸው፡፡
ለምሳሌ
. ሴሰኝነት ወይም ገንዘብን መመኘት ወይም ጣዖትን ማምለክ /ማቴ ፭
፥ ፴፭ (፩ኛ ቆሮ ፮፥፪)
. ውሸት፤ ኃጢአትን መሥራት፤ የማይጠቅሙ ወሬዎች ማውራት /፩ኛ
ጢሞ ፬ ፥ ፯/
. ክፉ ምኞት /፪ኛ ጴጥ ፩ ፥ ፬/
. የስጋ ምኞት የዓይን አምሮት ስለገንዘብ መመካት / ፩ኛ ዮሐ ፪ ፥ ፲፭
– ፲፮/ እና የመሳሰሉት ናቸው

፫.፪. የሥጋ ሥራ እና ውጤቱ


ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር ‹‹የሥጋ ሥራ የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት
፣ ርኩሰት ፣ መዳራት ፣ ጣኦት ማምለክ ፣ ሟርት ፣ ጥል ፣ ክርክር
፣ ቅናት ፣ ቁጣ ፣ አድመኝነት ፣ መለያየት ፣ መናፍቅነት ፣ ምቀኝነት
፣ መግደል ፣ ስካር ፣ ዘፋኝነት እና የመሳሰሉት እንደሆኑ ገልጧል (ገላ
፭፥፲፱/ ፡፡ እነዚህም ብቻ ሳይሆኑ እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ብዙዎች
ሲኖሩ በጥቅሉ ኃጢአት ተብለው ተጠርተዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከእንስሳዊ
ባሕርዩ የተነሳ ኃጢአትን ይጸንሳል፤ ኃጢአትም ሞትን ትወልዳለች፡
፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልዕክቱ እንደነገረን “ከዚህ በኋላ ምኞት
ጸንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች”
ያዕ ፩፥፲፭፡፡ ምክንያቱም የሥጋ ሥራ ውጤቱ ዘላለማዊ ሞት ነው፤/
ሮሜ ፰፥፮/ ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነው/ ሮሜ ፰፥፯/፤
ስለ ሥጋ ማሰብ ዘላለማዊ ፍርድና በዘለዓለማዊ እሳት መቃጠል ነው/
ይሁ ፩፥፯/

፴፪
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

፫.፫. ከዓለም ርኩሰት ራስን ለእግዚአብሔር ስለመለየት


ዓለማዊነት ከክርስትና ጋር ያለው ተቃርኖ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ተስፋፊ
ርዕዮተ ዓለም ራሳችን ለመከላከል ምን እናድርግ?

፩. የክርስትናን መሠረታዊ እሴቶች በደንብ ማወቅ


የክርስትና ታላቁ እሴቱ ድኅነትን ማግኘት ነው፡፡ (ዮሐ.፲፥፲ ) (በርግጥ
ለዓለማዊ ሰው ‘ድኅነት’ የሚለው ሃሳብ ራሱ ግልጽ አይመስለኝም፤
ምክንያቱም መታመሙን እና መዋቲነቱንም አይቀበልምና) ድኅነት
ደግሞ ዘላለማዊ ዋጋ ያለው ጉዞ እንጂ በዚህ ምድር የሚያልፍ ነገር
አይደለም፡፡ የድኅነት የመጨረሻ ዓላማ በታደሰ ህይወት ለፍጥረታቱ
የዘላለም ደስታና ሠላም ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም በአንድነት
መኖር ነው፡፡ (ራእይ. ፳፩፥፫) ድኅነት ማለት በክርስቶስ መድኃኒትነት
ከኃጢአት ህመምና ሞት ተፈውሶ በፀጋ የእግዚአብሔር ልጅ መሆን
ነው፡፡ (ማር. ፪፥፲፯፣ ሮሜ. ፰፥፲፮) የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ደግሞ
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ህይወትነት ተላብሰን የማታልፈው ርስቱን
ወርሰን በደስታ እንኖራለን፡፡ (ገላ. ፫፥፳፯፣ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፬)

ክርስቲያን የሆንነው በዚህ ዓለም በሠላም ለመኖር ስለሚጠቅመን ብቻ


እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ሐዋርያው “ሰው ግን ራሱን ይፈትን”
እንዳለው ዘወትር ራሳችን ልንፈትን ይገባል፡፡ (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፳፰) ይህ
ማለት ክርስቲያን መሆን በዚህ ዓለም በሰላም እና በደስታ ለመኖር
አይጠቅምም ማለት አይደለም፤ የክርስትና ዋናው ዓላማው ድኅነትና
የዘላለም ህይወት ነው ለማለት ነው እንጂ፡፡ ክርስቶስን ለዚህ ምድር ብቻ
ተስፋ የሚያደርጉት ግን ሐዋርያው እንዳለው “ከሁሉ ይልቅ ምስኪኖች
ናቸው፡፡” (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፲፱)

፪. ከኃጢአት ጋር መዋጋት እና ለክርስቲያናዊ ሥራ መትጋት


ኃጢአትን ማስተባበል፣ ቸል ማለትና እና ህጋዊ ማድረግ ዓለማዊነትን
፴፫
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

የመለማመድ ምልክት ነው፡፡ ሁላችንም በመውደቅ በመነሳት እንደምንኖር


እናውቃለን፤ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በኃጢአት እንደሚፈተን እንረዳለን፡፡ (ምሳሌ.
፳፬፥፲፮) ነገር ግን እውነተኛ ክርስቲያን ቢወድቅ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ
ይነሳል፤ መነሳት ቢያቅተው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብርታትን ይጠይቃል
እንጂ ኃጢአቱን ለማስተባበል እና ምክንያት ለመደርደር አይሞክርም፡
፡ ኃጢአትን ማስተባበል እና ህጋዊ ማድረግ ከጀመርን ወደ ዓለማዊነት
እየገባን መሆኑን እና ልቡናችንን እየተቆጣጠረ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡
ዓለማዊነት በዝባዥነት ነው ካልን ለሌሎች መልካም ማድረግ የዚህ
ተቃራኒ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ግብዝነት የሌለበትን ክርስቲያናዊ መልካም
ሥራ ለሌሎች የማድረግ ፍላጎታችን ሲጠፋ ዓለም በልቡናችን ቤት
እየሠራች እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፲፬-፲፯)

፫. ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አለመለየት፤ የግልና የማኅበር ጸሎትን


በትጋት መሳተፍ
ሰው ዓለማዊ (Secular) ሲሆን ከምሥጢረ ንስሐ፣ ቅዱስ ቁርባን
እና ከሌሎች የድኅነት ምሥጢራት ይርቃል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡
ኃጢአትን ያልጠላ እና ባለፈው ህይወቱ ያልተጸጸተ ሰው እንዴት ወደ
ንስሐ ይመጣል? እንዴትስ ከክርስቶስ ጋር በፍቅር አንድ ወደ ሚያደርገው
ቅዱስ ቁርባን ይቀርባል? (ዮሐ. ፮፥፶፮) ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን
ወዶ ለመፈጸም በልብ ውስጥ የቅድስና ናፍቆት እና የእግዚአብሔርን
ፍቅር መሻት ሊኖር ይገባል ማለት ነው፡፡

የግል ጸሎትና የቤተ ክርስቲያን የማኅበር ጸሎቶች (ቅዳሴ፣ ኪዳን፣


ማኅሌት ወዘተ...) በዚሁ መንገድ የሚታዩ ናቸው፡፡ ጸሎትን የሚወድና
የሚያዘወትር ሰው ልቡ ከአምላኩ ጋር የተጣበቀች ናት፡፡ የጸሎት ጥልቅ
ትርጉሙ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ነው፡፡ ዓለማዊነት በልቡ ያደረበት
ሰው ለጸሎት ይቸገራል፤ ልቡ ከእግዚአብሔር ፍቅር ርቋልና፡፡ ይህንንም
አንድ ሊቅ “ከሁሉም ነገር በላይ ዓለማዊነት ተቃርኖው ከአምልኮ ጋር
፴፬
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
ነው” በማለት ገልጾታል፡፡

ሲጠቃለል፡- ዓለማዊነት በልቡና ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር መጥፋት


እና ኃጢአትንና አላፊውን የዚህ ዓለም ተድላ ደስታ መውደድ ነው፡፡ ከላይ
የዘረዘርናቸው የክርስትና መርሆች ራሳችን ለመመርመር ያስችሉናል፡፡
ዓለማዊነት የሥጋ ምኞት የሥጋ ፈቃድ ከእንስሳዊ ባሕሪ የሚመነጭ
የሚገታው የሚከለከለው ሳይኖር እንዲሁ በደመነፍስ በመመራት ነፍስ
ለስጋ ፍላጎትና ፈቃድ እንድትገዛ በማድረግ ራስን ለዓለም ማስገዛት
ነው፡፡ “ከዓለም ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር ነገር ግን
እናንተን ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ ከዓለም ስለአይደላችሁ ስለዚህ
ዓለም ይጠላችኋል፡፡/ዮሐ. ፲፭፥፲፱ “/

የዓለም ሥራ ለኛ ስለማይጠቅመን እግዚአብሔር እራሱ ከዓለም


መርጦናል። እኛ ደግሞ የበለጠ ከዓለም ተለይተን ከእግዚአብሔር ጋር
ለመኖር ከክፉ መጠበቅ /ዮሐ ፲፯፥፲፭/፡ ከሥጋ ሥራዎች እራስን ማራቅ
፡ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን ማጠናከር
ይኖርብናል፡፡

፴፭
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

የምዕራፉ ማጠቃለያ
. ዓለማዊነት በልቡና ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር መጥፋት እና
ኃጢአትንና አላፊውን የዚህ ዓለም ተድላ ደስታ መውደድ ነው፡፡
. ‹‹የሥጋ ሥራ የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት ፣ ርኩሰት ፣ መዳራት
፣ ጣኦት ማምለክ ፣ ሟርት ፣ ጥል ፣ ክርክር ፣ ቅናት ፣ ቁጣ ፣
አድመኝነት ፣ መለያየት ፣ መናፍቅነት ፣ ምቀኝነት ፣ መግደል ፣ ስካር
፣ ዘፋኝነት እና የመሳሰሉት ናቸው (ገላ ፭፥፲፱/
. ምክንያቱም የሥጋ ሥራ ውጤቱ ዘላለማዊ ሞት ነው፤/ ሮሜ ፰፥፮/
ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነው/ ሮሜ ፰፥፯/፤ ስለ ሥጋ
ማሰብ ዘላለማዊ ፍርድና በዘለዓለማዊ እሳት መቃጠል ነው/ ይሁ ፩፥፯/
. ከዓለማዊነት ራሳችንን ለመጠበቅ፡- የክርስትናን መሠረታዊ እሴቶች
በደንብ ማወቅ፤ ከኃጢአት ጋር መዋጋት እና ለክርስቲያናዊ ሥራ
መትጋት፤ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አለመለየት፤ የግልና የማኅበር
ጸሎትን በትጋት መሳተፍና የመሳሰሉትን መፈጸም ይገባል፡፡

የማጠቃለያ ጥያቄ
፩. የዓለማዊነት መገለጫዎች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር ጻፍ፡፡
፪. የሥጋ ፍሬዎችንና የመንፈስ ፍሬዎችን በዝርዝር ጻፉ፡፡
፫. ራስን ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስረዳ፡፡

፴፮
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ምዕራፍ አራት

ጥበብ

ዓላማ
ተማሪዎች ይህንን ምዕራፍ ሲያጠናቅቁ

. ስለ ጥበብ ምንጭ እና የጥበብን ጥቅም ያውቃሉ


. ጥበብ ሥጋዊንና ጥበብ መንፈሳዊን ይለያሉ
. ከጠቢብ ሰው የሚገኙ ነገሮችን በዝርዝር ያስረዳሉ

ማስጀመርያ ጥያቄዎች

፩. ጥበብ ምንድን ነው?


፪. የጥበብ ምንጭ ማን ነው?
፫. የሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብ ምን እንደሆነ ተወያዩ?

፴፯
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ቁልፍ ቃላት

. ጥበብ ፡- ዕውቀት፣ ብልኃት፣ፈሊጥ፣ ፍልስፍና


. ጎልቦ፡- ቆዳን ማለዘብ ወይም ማለስለስ

፴፰
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

፬.፩. የጥበብ ምንነት ጥቅምና ምንጭ

ጥበብ ማለት ዕውቀት፡ ብልኃት፡ ፈሊጥ፡ ፍልስፍና እና የመሳሰሉት


ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ጥበብ ማለት እግዚአብሔርን መፍራት ማለት
ነው፡፡ መዝ ፻፲፩፥፲ ምሳ ፯፥፩ ጥበብ ብልህነት ነው፡፡ ጥበብ የማስተዋል
ውጤት ነው፡፡ የጥበብ ምንጭ ደግሞ እግዚአብሔር ነው ። ማንም ሰው
ጠቢብ ነኝ የሚል ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት አለበት፡፡
ጥበብ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡፡ ጥበብ መንፈሳዊና
ጥበብ ሥጋዊ በመባል፡፡

፬.፪. ጥበብ ሥጋዊ


ጥበብ ሥጋዊ ማለት የሥጋዊ ጥበብ ማለት ነው፡፡ ሥጋዊ ጥበብ የሚባለው
ብረቱን አቅልጦ፣ እንጨቱን አለዝቦ፣ ቁርበቱን ጎልቦ፤ ድንጋዩን ጠርቦ፣
መገልገያ መሳሪያዎችን መሠራትና ለሥጋዊ ኑሮ ስኬታማነት ብልሃትን
በአግባቡ መጠቀም ማለት ነው፡፡

ጥበብ ሥጋዊ ሰዎች ተምረው ወይም እግዚአብሔር በሰጣቸው እውቀት


ሰርተው ራሳቸውንም ሆነ ኅብረተሰቡን የሚያገለግሉበት ጥበብ ነው፡፡
ለምሳሌ፡-
. የስራ አመራር ፪ኛተሰ ፫፥፰-፲
. ግብርና ዘፍ፡- ፵፪፥፳
. ንግድ ሕዝ፡- ፳፯፥፩-፳፭
. ምህንድስና ዘፍ፡- ፮፥፲፫-፲፰…. ወዘተ ብሎ የጥበብ ሥጋዊ ሥራዎችን
መዘርዘር ይቻላል፡፡

. ጥበብ ሥጋዊ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ለኅብረተሰብም ለራስም


ጥቅም አለው፡፡ ነጋዴ ነግዶ፤ ገበሬም አርሶ፤ልብስ ሰፊም ሸምኖ ሕዝብን
ከችግር፣ በልብስ ከመራቆት፣ በብርድና ከመመታትና ገላን ከመሸፈን
፴፱
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ችግር ያድናል፡፡ ራሱም ሥጋዊ አካሉ እንዳያጎሰቁልና አላስፈላጊ ችግር


እንዳይገጥመው ይረዳዋል፡፡ ስለዚህ ጥበብ ሥጋዊ የሞተ የሚሆነው
ከጥበብ መንፈሳዊ የተለየ እንደሆነ ነው፡፡ ሰው የሥጋዊ ጥበብ ኖሮት
መንፈሳዊ ጥበብ ከሌለው እንደ እንስሳ ሥጋውን አደልቡ በነፍሶ ከመሞት
የሚያድነው አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የሥጋ ጥበብ ብቻውን ፈርሶና
በስብሶ ለሚቀረው ሥጋ ብቻ ማሰብን ያመጣልና፡፡ ይህንን ሥጋ በሥጋዊ
መንገድ ለማስደሰት ወይም ለጊዜያዊ ደስታ ሲባል የሥጋ ሥራዎቸን
ማለትም ዝሙት ፣ ርኩሰት ፣ መዳራት ፣ ጣኦት ማምለክ ፣ ሟርት ፣
ጥል ፣ ክርክር ፣ ቅናት ፣ ቁጣ ፣ አድመኝነት ፣ መለያየት ፣ መናፍቅነት
፣ ምቀኝነት ፣ መግደል ፣ ስካር ፣ ዘፋኝነት እና የመሳሰሉት መፈጸምን
ያመጣል፡፡ (ገላ ፭፥፲፱/ እነዚህም የሚፈጽም ደግሞ መጨረሻው ሞት
ነው፡፡ ለዚህ ነው ጠቢቡ ሰለሞን በመጀመሪያ እግዚአብሔርን ሲለምን
‹‹ማስተዋልና ጥበብ ስጠኝ›› ያለው፡፡ ይኸውም መንፈሳዊ ጥበብ ስጠኝ
ማለቱ ነው፡፡

፬.፫.ጥበብ መንፈሳዊ
ጥበብ መንፈሳዊ ማለት መንፈሳዊ ጥበብ ማለት ነው፡፡ የመንፈሳዊ ጥበብ
ምንጩ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥበብ የሥጋን ደካማ ጠባይ
ለማሸነፍና ለነፍስ ባሕርይ ለመገዛት አስተዋይነት መያዝ ነው፡፡ ይኸውም
ጥበብ ሙሉ የሚሆነው የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራትና
እንደ ፈቃዱ ሲኖር ነው፡፡ ሃይማኖት /ይሁ ፩፥፳ ፪ኛጢሞ ፬፥፯/፡ በጎ
ሥነ ምግባር /ዘጸ ፳፥፯ – ፲፯ ያዕ ፪፥፯/፡ እግዚአብሔርን መፍራት /ምሳ
፯፥፯/ እና የመሳሰሉትን ሁሉ ጥበብ መንፈሳዊ ብለን እንጠራቸዋለን ።

፬.፬ ከጠቢብ ሰው የሚገኙ ነገሮች


የማስተዋል ዘዴ፡ ማንኛውንም ነገር ለማግኘት የመመርመር ችሎታ
ያለው ሰው ጥበበኛ ወይም ጠቢብ ያባላል፡፡ከጠቢብ ሰው ብዙ ነገሮች
ልናገኝ እንችላለን ለምሳሌ ያህል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል
. እግዚአብሔርን መፍራት
. ትዕግስት
. ደግነት
. አስተዋይነት
. ሰውን ማክበር
. ተግሳፅን መስማት መዝ ፩፥፭

የምዕራፉ ማጠቃለያ
. ጥበብ ማለት ዕውቀት፡ ብልኃት፡ ፈሊጥ፡ ፍልስፍና እና የመሳሰሉት
ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ጥበብ ማለት እግዚአብሔርን መፍራት ማለት
ነው፡፡ መዝ ፻፲፩፥፲ ምሳ ፯፥፩ ጥበብ ብልህነት ነው፡፡
. ሥጋዊ ጥበብ የሚባለው ብረቱን አቅልጦ፣ እንጨቱን አለዝቦ፣ ቁርበቱን
ጎልቦ፤ ድንጋዩን ጠርቦ፣ መገልገያ መሳሪያዎችን መሠራትና ለሥጋዊ
ኑሮ ስኬታማነት ብልሃትን በአግባቡ መጠቀም ማለት ነው፡፡
. ጥበብ ጥበብ ሥጋዊና ጥበብ መንፈሳዊ በመባል በሁለት ዋና ዋና
ክፍሎች ይከፈላል፡፡ሥጋዊ ጥበብ የሚባለው ብረቱን አቅልጦ፣ እንጨቱን
አለዝቦ፣ ቁርበቱን ጎልቦ፤ ድንጋዩን ጠርቦ፣ መገልገያ መሳሪያዎችን
መሠራትና ለሥጋዊ ኑሮ ስኬታማነት ብልሃትን በአግባቡ መጠቀም
ማለት ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥበብ የሥጋን ደካማ ጠባይ ለማሸነፍና ለነፍስ
ባሕርይ ለመገዛት አስተዋይነት መያዝ ነው፡፡

የማጠቃለያ ጥያቄ
፩. ሥጋዊ ጥበብና መንፈሳዊ ጥበብ የሚባሉት እነማን ናቸው?
፪. ከጠቢብ ሰው ከሚገኙ ነገሮች የተወሰኑትን ጥቀስ፡፡

፵፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አምስተኛ ክፍል

ዋቢ መጻሕፍት

መጽሐፍ ቅዱስ
ወንጌል ቅዱስ- ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ-ታህሣሥ ፳፬/፲፱፻፹፰
ዓ.ም
የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ንባብ እና ትርጓሜ
ፍትሐ ነገሥት-ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት ፲፱፻፺- አዲስ አበባ
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት ፳፻፯ ዓ.ም. እትም (ክሥም ፫፻፭ )-
ማኀበረ ቅዱሳን
በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ ፪ መንፈሳዊ ሰው በቤተሰቦቹ
መካከልየመንፈስ ፍሬዎች (የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያ ፓትርያርክ
ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሦስተኛ እንደጻፉት ኅዳር ፳፻፬ ዓ.ም)
ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፯ኛ ዓመት መስከረም ፳፻፲፪ ዓ.ም.- ማኀበረ
ቅዱሳን
ብሂለ አበው -በመምህር ማሞ ከበደ-መጋቢት ፳፻፬ ዓ.ም- አዲስ አበባ

፵፪
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ
የመንበረ ፓትርያርክ (ዓለም አቀፍ) የሰ/ት/ቤቶች አንድነት
የሰንበት ት/ቤት አመራር እና መምህራን እንዲሁም
ተማሪዎችና ወላጆች በመጽሐፉ ላይ ያላችሁን
ማንኛውም አስተያየት እና ግብዓት በሚከተለው
አድራሻ ላኩልን

office@eotc-gssu.org
https://t.me/GSSUCurriculum_bot

You might also like