You are on page 1of 4

የተሰደዱ ስሞች

በአዲስ አበባ ሲኤም ሲ አካባቢ በሚገኝ አንድ የግል ትምህርት ቤት የዐጸደ ሕፃናት በር ላይ ቆሜያለሁ፡
፡ እንዴው አንዳች ነገር ገፋፋኝና በየበሩ የተለጠፈውን የተማሪዎች ስም ዝርዝር መመልከት ጀመርኩ፡፡
ቢያንስ በአንድ ክፍል በር ላይ እስከ ሃያ የሚደርሱ ተማሪዎች ስሞች ተለጥፈዋል፡፡

የአንድ የአምስት ክፍል ተማሪዎችን ስም ዝርዝር ስመለከት ከኢትዮጵያውያን ስሞች መካከል የተሰደዱ
መኖራቸውን አየሁ፡፡ እነ ትርንጎ፣ ብርቱካን፣ ትጓደድ፣ ድንበሯ፣ ቻላቸው፣ እያቸው፣ ስማቸው፣ ውዴ፣
ሙሉነሽ፣ አየነው፣ ገበያው፣ ሙሀባው፣ አብዱል መጂድ፣ አብዱል ቀኒ፣ ገብረ መስቀል፣ ገብረ
እግዚአብሔር፣ በላቸው፣ ደርበው፣ ጥሩ ወርቅ፣ የትም ወርቅ፣ የሚሉ ጥንታውያኑ ስሞች በዝርዝሮቹ
ውስጥ የሉም፡፡

እነ ማርታ፣ ማኅሌት፣ አርሴማ፣ ጀሚላ፣ ሣራ፣ ማክዳ፣ አቤሜሌክ፣ ባሮክ፣ ሰሎሞን፣ ሐዊ፣ ሀቢብ፣
አዜብ፣ ግሩም፣ አትናቴዎስ፣ ቢንያም፣ የሚሉ ስሞች የዘመኑ ሻምፒዮ ናዎች ሆነው ይታያሉ፡፡

ስም የአንድ ነገር መለያ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሰዎች ስሞች የአንድን ሕዝብ እምነት፣ ባህል፣ ማንነት፣
ፍልስፍና፣ ርእይ፣ ታሪክ፣ ገጠመኝ፣ ይገልጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብረ መስቀል፣ ወልደ መስቀል፣ ወለተ
መስቀል የሚሉ ስሞችን ስንሰማ የአውጭዎችንም ሆነ የወጣላቸውን ሰዎች እምነት ክርስቲያን መሆናቸውን
የሚያሳዩ ሲሆን በሌላም በኩል ደግሞ አብዱል ቀኒ፣ አብዱል ሰመድ፣ መሐመድ፣ ከድጃ፣ የሚሉ ስሞችን
ስንሰማ ደግሞ ባለቤቶቹ የእስልምና እምነት ተከታዮች መሆናቸውን ይጠቁመናል፡፡

ስሞች ታሪካዊ ክስተቶችን እና የታሪክ ሂደቶችንም ያሳያሉ፡፡ ጉም፣ አስጎምጉም፣ ለትም፣ ተላተም፣ አይዙር፣
ድድም፣ ውድድም፣ የሚሉትን ስሞች ስንሰማ የአኩስም ዘመን ትዝ እንደሚለን ሁሉ ስቡሐይ፣ ሐርበይ፣
መይራረ፣ ጠጠውድም፣ ይምርሐነ፣ ላሊበላ፣ የሚሉትን ስንሰማ ደግሞ የዛግዌ ዘመን ይታወሰናል፡፡ በአብዮቱ
ዘመን የተወለዱ ልጆች አብዮት፣ ገሥግሥ፣ መንግሥቱ፣ ድላቸው፣ ትቅደም፣ የሚሉ ስሞችን ወርሰው
ቀርተዋል፡፡ እንዲያውም የአባትዬው ስም የሚገጥም ሆኖ ሲገኝ ገናናው መንግሥቱ፣ አንዳርገው
መንግሥቱ፣ ምናለ መንግሥቱ፣ አሸናፊ መንግሥቱ፣ መሪነህ መንግሥቱ እየተባሉ ተጠርተው ነበር፡፡

ነጻ ፕሬስ እንደ ልብ የማይገኝበት እና በቃላዊ ፕሬስ ሃሳብን መግለጥ በተለመደበት የኢትዮጵያ ማኅበረ
ሰብ ውስጥ ብሶት፣ ምሬት እና ጭቆና ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ በሚወጡ ስሞች ነው፡፡ ለልጆች፣
ለውሾች እና ለበሬዎች በሚወጡ ስሞች አማካኝነት የዘመኑን ብሶት እና ምሬት ወላጆች ይገልጣሉ፡፡

ባሕርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይሠራ የነበረ አንድ አባት በደርግ ዘመን ለጦርነት፣ ለድርቅ፣ ለርዳታ፣
ለፓርቲ፣ ወዘተ የሚከፈለው መዋጮ በዛበት፡፡ የሰውዬው ስም «በዛብህ» ይባል ነበር፡፡ እናም ልጆቹን
ተቆራጩ፣ መዋጮው፣ ቅጣቱ ብሎ አወጣላቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ሰውዬው ሦስቱንም ልጆች ከሚስቱ
ሳይሆን ከሦስት የተለያዩ ሴቶች ነበር የወለደው፡፡ የልጆቹ እናቶች በየአሥራ አምስት ቀኑ የልጆቻቸውን
ተቆራጭ ሊወስዱ ይመጡ ነበር፡፡ ተቆራጭ የሚወስዱት ሴቶች ይሰለፉና የልጆቻቸው ስም በጩኸት
እየተጠራ ነበር የሚሰጣቸው፡፡
እናም በየአሥራ አምስት ቀኑ «ተቆራጩ በዛብህ፣ መዋጮው በዛብህ፣ ቅጣቱ በዛብህ» እየተባለ ሲጠራ
ሰው ሁሉ በሳቅ ይፈነዳ ነበር፡፡ አንዳንድ ካድሬዎች ሰውዬውን ጠርተው የልጆቹን ስም እንዲቀይር
አስፈራርተውት ነበር፡፡ እርሱ ግን ወይ ፍንክች ማለት ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ነገር ለሰው ሁሉ ተናገረ፡፡
ሁኔታው ስላላማራቸው ሴቶቹ ስማቸው ሳይጠራ ቢሮ ገብተው እንዲወስዱ አደረጉ፡፡

ገበሬው

ሁለት ውሾች አሉኝ የማሳድጋቸው

አንዱ ሰምቶ ማለፍ ሌላው መቻል ናቸው

ብሎ ለውሾቹ በሰጠው ስም የኑሮ ፍልስፍናው ታግሎ ማሸነፍ ሳይሆን ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፍ እና
መከራውን ሁሉ ችሎ ማሳለፍ መሆኑን ገልጦበታል፡፡

አባቱ በሰው እጅ የተገደለ እንደሆነ በሰሜኑ ባህል ልጅ ተወልዶ የአባቱን ደም ይመልሳል ተብሎ
ይታሰባልና እናቱ ደምመላሽ ብላ ትሰይመዋለች፡፡ ለልጇ አድጎ መሥራት ያለበትን የቤት ሥራ
እየሰጠችው፡፡ የአባቱ ርስት እና ሀብት ተወርሶ እናቱን የሚቆጫት ከሆነ ደግሞ አንተ እደግና አስመልሰው
ስትል አስመላሽ ትለዋለች፡፡ ልጂቱ ቆንጆ ሆና ያያት ሁሉ ይጠልፍብኛል ብላ ካሰበች ለልጅቱ ሳይሆን
ለቤተሰቡ ማንቂያ እና ማስጠንቀቂያ የሚሆን ስም ትሰጣታለች፡፡ «ዘቢደር» ስትል፡፡ ይህቺን ልጅ
ለመጠበቅ ዘመድ ወዳጅ ሁሉ ዘብ ይደር ማለቷም አይደል፡፡

ልጅ እምቢ ብሏቸው ከርመው እንዴው ባልታሰበ ጊዜ ያኙት እንደሆን ሰማኸኝ፣ አገኘሁ፣ ስጦታው፣
ተገኘ፣ እያሉ ሁኔታውን ያስታውሱበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ስም የሚያወጡት ለራሳቸው ነው
ወይንስ ለልጆቻቸው? ያሰኛል፡፡

እናት ጀግና የፈለገች እንደሆነ፣ ለልጇ ያላትን ምኞት የምትገልጠው በምትሰጠው ስም ነው፡፡ የበላይ
ዘለቀ እናት ልጇን በላይ ዘለቀ ብላ ስትጠራው ስሙን ከአባቱ ጋር አስማምታ ነው፡፡ ልጇ የሁሉም
የበላይ ሆኖ ለማየት ምኞት ስለነበራት፡፡ በላይም ይህንን አልዘነጋውም፡፡ እርሱ አብረውት ለዘመቱት
አርበኞች የማዕረግ ስም ሲሰጥ ለራሱ አልሰየመም ነበር፡፡ በኋላም ነጻነት ተመልሶ ሠራዊቱን ንጉሡ
የርሱን የመዓርግ ስም ሲጠይቁት «እኔንማ እናቴ አንድ ጊዜ በላይ ብላኛለች» ብሎ ነበር የመለሰው፡፡

የግጥም ችሎታቸውን በልጆቻቸው ላይ ያስመሰከሩ ወላጆችም

ፀሐይ ወጥታ እስክትገባ

አትጠገብ የኔ አበባ

የሚል ስም ለልጃቸው አውጥተዋል፡፡ ይህ ስም እንዴት መታወቂያ ላይ እንደሚጻፍ ማሰብ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ለልጆቻቸው ስም ማውጣትን አንደ ትልቅ ተልዕኮ ነው የሚያዩት፡፡ የቤተሰቡን ምኞት፣


ሃሳብ፣ እምነት እና አመለካከት፣ በልጁ እንዲቀረጽ የተፈለገውን ነገር ሁሉ ይይዛልና፡፡ ለዚህም ነው
«አበሻ ሚስቱ ስታረግዝ እርሱ እንቅልፍ አይወስደውም» የሚባለው፡፡ ለምን? ቢሉ ስም ፍለጋ፡፡
በአሁኑ ዘመን በተለይም በከተማ አካባቢ ያሉ ብዙ ወላጆች የሚመርጧቸው ስሞች ቢቻል ከአምስት
ፊደል ያልበለጡ፣ በብዙ ሰዎች ዘንድ ያልተለመዱ፣ ትርጉም ያላቸው፣ በእንግሊዝኛ ሲጻፉ ከ «ኤ» እስከ
«ኤፍ» ድረስ ባለው መሥመር የሚካተቱ ዓይነት ናቸው፡፡ አንድ ወላጅ ለልጃቸው ለምን ከ«ኤ» እስከ
«ኤፍ» የሚካተት ስም አውጣልኝ እንዳሉ ስጠይቃቸው «ልጄ መጨረሻ ሲሰለፍ ማየት አልፈልግም»
ብለውኛል፡፡ አንዱ ጓደኛዬ ደግሞ እናቱ ለልጁ ያወጡላትን «ፈሰሰ ወርቅ» የሚለውን ስም ለምን
እንደቀየረው ስጠይቀው «እንዴ ምን ብዬ ላቆላምጣት ነው?» ብሎ አስቆኛል፡፡ ይህም አለ ለካ፡፡

በአሁኑ ዘመን አጫጭር ስሞች ተወዳጅ ከመሆናቸው የተነሣ ረዣዥም ስሞችን ማሳጠርም እየተለመደ
ነው፡፡ ቤተልሔምን «ቤቲ»፣ መስተዋትን «መስቲ»፣ አደራጀውን «አዱ»፣ ወልደ መስቀልን «ወልዴ»፣
አምኃ ሥላሴን «አምኃ»፣ ደብረ ወርቅን «ደብሬ»፣ ፈትለ ወርቅን «ፈትለ»፣ ሣህለ ማርያምን «ሣህሉ»፣
አብዱል ሁሴንን «አብዱ»፣ ብለን ያሳጠርናቸው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እነዚህም አጠሩ
ተብለው ቲቲ፣ ኪኪ፣ ሊሊ፣ ሚሚ፣ ቺቺ፣ ጂጂ፣ ቲጂ፣ ሶል፣ ዳን፣ ጃክ፣ የሚሰኙ ስሞች እየተዘወተሩ
ነው፡፡

ወላጆች ለየት ያለ ስም ለልጆቻቸው ያወጡ ቢመስላቸውም በብዙ ሀገሮች እጅግ የሚወደዱ እና


ተደጋግመው የሚወጡ ስሞች ግን አሉ፡፡ ለምሳሌ በሊቢያ «መሐመድ» የሚለው ለወንዶች፣ «አያ»
የሚለው ደግሞ ለሴቶች መጠርያነት በመዋል ቀዳሚ ስሞች ናቸው፡፡ ወደ ሞሮኮ ስንሻገር ደግሞ
ለወንዶቹ እንደ ሊቢያ «መሐመድ» ቀዳሚውን ይይዝና ለሴቶቹ ግን «ፋጢማ» የሚለው ስም ለብዙዎች
መጠርያነት በመዋል ተዘውታሪ ሆኗል፡፡

በእሥራኤል ለወንዶቹ «ኖዓም» የሚለው ስም በብዛት ጥቅም ላይ ሲውል፣ «ኖዓ» የሚለው ደግሞ
የሴቶች መጠርያ በመሆን ቀዳሚውን ቦታ ይዟል፡፡ በደቡብ ኮርያ «ሚንጁን» የሚለውን ስም ብዙ
ወንዶች ይጠሩበታል፤ ሴቶቹ ደግሞ «ሴዩአን» የተሰኘውን ስም በብዛት ተጠርተውበታል፡፡ በኦስትሪያ
«ሉቃስ» በብዛት የወንዶቹ መጠርያ ሲሆን፣ «ሣራ» ደግሞ ለሴቶቹ በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
በጣልያን «ፍራንቼስኮ»፣ በቤልጅየም «ኖኅ»፣ በዴንማርክ «ዊልያም»፣ በጀርመን «ሊኦን»፣ በግሪክ
«ጆርጂዮስ»፣ በሩስያ «አሌክሳንደር»፣ በስፔን «ዳንኤል»፣ በስዊዘርላንድ «ናታን»፣ ለወንዶቹ በስፋት
ጥቅም ላይ የዋሉ ስሞች ናቸው፡፡

ለሴቶቹ ደግሞ በጣልያን «ጊዩልያ»፣ በግሪክ «ማሪያ»፣ በሩሲያ «ኤለና»፣ በስፔን «ሉቺያ»፣
በስዊዘርላንድ «ኤማ» እና «ሌና»፣ በዴንማርክ «ኢዳ»፣ በቤልጂየም «ኤማ» እና «ማሪዬ»፣ በጀርመን
«ሚያ» እጅግ የብዙዎቹ መጠርያዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ወደ አሜሪካ ስንሻገር በሜክሲኮ «ሳንቲያጎ»፣ በዩናይትድ ስቴትስ በነጮቹ ዘንድ «ያዕቆብ»፣ በአፍሪካ
አሜሪካውያን ዘንድ «ጃይደን»፣ በአሜሪካ ሕንዶች ዘንድ ደግሞ «ዴቨን» ለወንዶች መጠርያነት በብዛት
እያገለገሉ ናቸው፡፡ ለሴቶቹ ደግሞ በሜክሲኮ «ማርያ» እና «ፌርናንዳ»፣ በነጭ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች
ዘንድ «ኢዛቤላ»፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድ «ማዲሰን»፣ በአሜሪካ ሕንዶች ዘንድ ደግሞ «አንያ»
ተመራጭ ስሞች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያውያን ዘንድስ ተመራጭ የሆኑት ስሞች እነማን ናቸው? ስሞቻችንስ ለምን እያጠሩ እና
እየተለወጡ መጡ? በቀጣይ እንመለስባቸዋለን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

You might also like