You are on page 1of 3

የተሰደዱ ስሞች

(ክፍል ሁለት)
ሁለት)
ባለፈው እትም በልዩ ልዩ የዓለም ከፍሎች ተዘውታሪ የሆኑትን ስሞች አንሥተን ነበር የተሰናበትነው፡፡
የኢትዮጵያውያንን ተዘውታሪ ስሞች በተመለከተ በቂ የሆነ መረጃ ማግኘት ቸግሮኛል፡፡ ምናልባት
የስታትስቲክስ መሥሪያ ቤታችን ከሕዝብ ቆጠራ ያገኘውን መረጃ ተጠቅሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ
በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉትን የሴት እና የወንድ ስሞች እንዲነግረን አደራ እያልኩ መጠነኛ ፍንጭ
የሚሰጡንን ብቻ እንጥቀሳቸው፡፡

አንድ «ስቱደንት ኦፍ ዘወርልድ» የተሰኘ ድረ ገጽ በመረጃ መረብ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በጥቅም


ላይ የዋሉትን የኢትዮጵያውያንን ስሞች በመሰብሰብ በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል ያላቸውን የወንድ እና
የሴት ስሞች እስከ አንድ መቶኛ ደረጃ ዘርዝሯቸዋል፡፡

በዚህ ድረ ገጽ ዝርዝር መሠረት በስፋት ጥቅም ላይ በመዋል ከአንደኛ እስከ አሥረኛ ያለውን ደረጃ
የያዙት የሴቶች ስሞች «ኤደን፣ ሣራ፣ ቤቲ፣ ሕይወት፣ ቤዛ፣ ሜሮን፣ ትእግሥት፣ ቃል ኪዳን፣ ሩት እና
ሰላም» ናቸው፡፡ የወንዶቹን ስናይ ደግሞ «ዳንኤል፣ ሰሎሞን፣ ብሩክ፣ ዳዊት፣ ሄኖክ፣ ሳሙኤል፣ ያሬድ፣
አቤል፣ ሀብታሙ እና አሸናፊ» ናቸው፡፡

የእነዚህ ስሞች አካሄድ የሚያሳየን አንድ ነገር አለ፡፡ የኢትዮጰያውያን ወላጆች በተለይ ደግሞ ከተምቾ
ወላጆች የስም አወጣጣቸው መቀየሩን፡፡ በጋዜጦች ላይ የሚወጡ የስም ለውጥ ማስታወቂያዎችም ከዚህ
ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ያሳዩናል፡፡ በአብዛኛው ስሞቻቸውን የሚቀይሩት በቀድሞ ዓይነት ስሞች
የሚጠሩት ናቸው፡፡ የሚቀይሩት ደግሞ በዘመናችን መለመድ ወደ ጀመሩት ከላይ ወደ ጠቀስናቸው
ዓይነት ስሞች ነው፡፡

በአሁኑ ዘመን ያለው የስም አወጣጥ መንገድ የአራት ነገሮች ተጽዕኖ ይታይበታል፡፡ የመጀመርያው
ሃይማኖት ነው፡፡ በክርስቲያኖች ዘንድ አጠር ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች እየተዘወተሩ ሲመጡ
በሙስሊሞችም ዘንድ አጫጭር እስላማዊ ስሞች እየተለመዱ ናቸው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የእንግሊዝኛ ስሞች ተጽዕኖ ነው፡፡ አሜሪካኖች ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ
ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ የእንግሊዝን ስሞች እየቆራረጡ በማሳጠር አሜሪካዊ ስሞችን መፍጠር ነው፡፡
እነዚህ አሜሪካውያን ስሞች በኢትዮጵያውያን ስሞች ላይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተጽዕኖ
አድርገዋል፡፡ እነ ዘውዱ «ዜድ»፣ እነ ክንዴ «ኬነዲ»፣ እነ ማርያማዊት «ሜሪ»፣ እነ ቢንያም «ቢኒ»
የሆኑት በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ አንዳንድ ስሞች የዘመናዊነት
መገለጫዎች እየተደረጉ መታየታቸው ነው፡፡ ትርንጎ ከመባል «ሜሪ»፣ ወዳጄነህ ከመባል «ሳሚ»፣ ድፋባ
ቸው ከመባል «ዲ»፣ አስቻላቸው ከመባል «አስቹ»፣ ቴዎድሮስ ከመባል «ቴዲ»፣ ዘውዱ ከመባል
«ዜድ» ሲሳይ ከመባል «ሲስ»፣ ዘመናዊነትን እያሳዩ መጥተዋል፡፡

በውጭ ዓለም በሚኖረው ዳያስጶራ ዘንድ ደግሞ ለፈረንጆቹ ለአጠራር እንዲያመች ተብሎ ስሞች
እንዲያጥሩ እየተደረገ ነው፡፡ በተለይም በሥራ ቦታ እና በትምህርት ቤት አካባቢ በአበሻዊ ስሞች
መጠራት ፈረንጅ ቀጣሪዎችን እና መምህራንን ስለሚያስቸግር ስሙን ጎርዶ ለአጠራር የሚያመች ስም
ማውጣት እንደ ቀላል መንገድ ተወስዷል፡፡ አንዲት እኅት ፍሬ ወርቅ የሚለውን fire work ብላ በመጻፏ
ስሟ «ፋየር ዎርክ» ተብሎ መቅረቱን አጫውታኛለች፡፡

ስም የአንድ ሕዝብ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ፍልስፍና እና አመለካከት የሚያሳይ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን
የሆኑ ስሞቻችን ባይዘነጉ መልካም ይመስለኛል፡፡ አጫጭር እና ያልተለመዱ፣ ትርጉም ያላቸው እና
ለአጠራር የሚቀሉ ዓይነት ስሞችንም ቢሆን ከኛው ውስጥ መርጦ ማውጣት የሚከብድ አይመስለኝም፡፡

በብዙ ሀገሮች የስም ማውጫ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በዚያች ሀገር በሚገኙ ሕዝቦች
ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የሚወጡትን ስሞች ከተቻለ ከነ ትርጉማቸው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕ
ፍት አያሌ ጥቅሞች አሏቸው፡፡ የመጀመርያው ጥቅማቸው የቅርስ መዛግብት መሆናቸው ነው፡፡ በዚያች
ሀገር ታሪክ ውስጥ ለልዩ ልዩ ነገሮች መጠርያ ሆነው ከጥቅም ውጭ የሆኑትን ስሞች በቅርስነት
ይይዙልናል፡፡

ለምሳሌ በሀገራችን እየተረሱ የመጡ የፈረስ ስሞች፣ የንግሥና ስሞች እና የመዓርግ ስሞች አሉ፡፡ እነ
ደጃዝማች፣ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች፣ ራስ፣ ቢትወደድ፣ ፊታውራሪን የመሰሉት የመዓርግ ስሞች በአሁኑ
ዘመን በሹመት እየተሰጡ ባለመሆናቸው የመረሳት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ወደፊት ልጆቻችን የጥንት
መዛግብትን ሲያነብቡ እነዚህን ስሞች የሚተረጉምላቸው መዝገበ ቃላት ይፈልጋሉ፡፡ ከፖሊስ ቤት
አገልግሎት የተሠረዙት እነ መቶ አለቃ፣ አሥር አለቃ፣ ሻለቃ፣ ሻምበል ወደፊት ከመረሳታቸው በፊት ከነ
አገልግሎታቸው እና ታሪካቸው የሚመዘግባቸው ይሻሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ እየጠፉ እና እየተቀየሩ የሚገኙ የአካባቢ ስሞች አሉ፡፡ መንግሥታት እና ሥርዓተ
ማኅበሮች በተቀያየሩ ቁጥር የመለወጥ አደጋ ከሚያጋጥማቸው ቅርሶች መካከል የአካባቢ ስሞች ዋነኞቹ
ናቸው፡፡ እነዚህ ስሞች ጥቅም ላይ ውለው በነበሩበት ዘመን የተጻፉ አያሌ መዛግብት አሉ፡፡ እነዚህን
መዛግብት በሚገባ ለመረዳት እነዚህ ስሞች ከነአካባቢያዊ ምልከታቸው ተመዝግበው መቀመጥ አለባቸው፡፡

ማኅበረሰቡ ለአንዳንድ ነገሮች ከዘመኑ ክስተት ጋር የተያያዘ የመታሰቢያ ሰም የሚሰጥበት ጊዜ አለ፡፡


ምኒሊክ ብርጭቆ የሚባለው ብርጭቆ አሁን ይኑር አይኑር እንጃ፡፡ ተፈሪ ሚዛን የሚባል ዛፍ ላይ
የሚንጠለጠል ትልቅ ሚዛን ትዝ ይለኛል፡፡ በደርግ ጊዜ ከሶቪየት ኅብረት የሚገቡ «ሞስኮብ» እየተባ
የሚጠሩ የክፍለ ሀገር ሚኒባሶች ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በገባ ሰሞን የመጡት ዲኤክስ መኪኖች
«ወያኔ ዲኤክስ» ሲባሉ፣ አባ ዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት በሆኑበት ዘመን የመጡት ነጫጭ
ሚኒ ባሶች ደግሞ «አባ ዱላ» ተብለው ተሰይመዋል፡፡ ወደ ሀገር ባህል ልብስ ቤት ብንገባ ደግሞ ኦባማ
ቀሚስ፣ ቢዮንሴ ቀሚስ እየተባሉ የሚጠሩ የሐበሻ ቀሚሶችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ስሞች ዘመንን ከነ
ክስተቱ የሚያስታውሱ በመሆናቸው ቢቻል ከነ ፎቶ ግራፋቸው ቀርሶ የሚያስቀምጣቸው መዝገብ ይሻሉ፡፡

ሁለተኛው የመዝገበ ቃላቱ ጥቅም ደግሞ የወላጆችን ጭንቀት መፍታቱ ነው፡፡ ወላጆች ከምኞታቸው፣
ከሃሳባቸው፣ ከአመለካከታቸው እና ከእምነታቸው ጋር የሚሄድ ተወዳጅ ስም ማውጣት ፍላጎታቸው ነው፡
፡ ችግሩ ይህንን ስም ከየት እንደሚያገኙት አለማወቃ ቸው ነው፡፡ ይህንን መሳይ የስም መዝገበ ቃላት
ቢኖረን ግን ወላጆች እና አሳዳጊዎች በቀላሉ የሚፈልጉትን ዓይነት ስም ለማግኘት ይችሉ ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን ሕፃናትን ወስደው የሚያሳድጉ የውጭ ሀገር ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከጠየቁኝ ነገር
አንዱ ኢትዮጵያውያን ስሞችን የሚያገኙበትን አማራጭ እንድነግራቸው ነው፡፡ ለልጆቻቸው የቤት ውሻ
ይሰጧቸዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጰያዊ የሆነ የውሻ ስም ይፈልጋሉ፡፡ እነ መቻልን፣ እነ ገሥግሥን፣ እነ
ደምሳሽን በምን ይወቋቸው፡፡ እነዚያ ሕፃናት ልጆች ያድጉና እነርሱም ለልጆቻቸው ስም ይፈልጋሉ፡፡
ያደጉት በምዕራቡ ማኅበረሰብ ውስጥ በመሆኑ ከአበሻው ጋር ብዙም ቀረቤታ የላቸውም፡፡ ልጆቻቸውን
የሀገራቸውን ቋንቋ ማስተማር ቢያቅታቸው እንኳን የሀገራቸውን ስም መስጠት ግን ይፈልጋሉ፡፡ ግን ከየት
ይምጣ?

ሦስተኛው ጥቅሙ ደግሞ የማናውቃቸውን የሀገራችንን ስሞች ለማወቅ እና ለመጠቀም ማስቻሉ ነው፡፡
በየብሔረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ፣ ትርጉማቸው እጅግ አስደናቂ የሆኑ፣ ሃሳባችንን እና እምነታችንን
ሊገልጡልን የሚችሉ ስሞች አሉ፡፡ ያልተጠቀምንባቸው ባለማወቃችን ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን
ስሞች የምናገኝበት መዝገብ ቢኖረን ኖሮ የማንተዋወቅ ሕዝቦች ለመተዋወቂያ ምክንያት ይሆነን ነበር፡፡

ባሁኑ ዘመን ስም የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መንገዶች፣ ሕንፃዎች፣ መንደሮች፣ መኪኖች፣


ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ሱቆች፣ ሌሎችም ስም እየወጣላቸው ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግን ከሥራቸው እና
ከሃሳባቸው ጋር ተስማሚ የሆኑ ስሞችን ማውጣት ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሠር
ተው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመርተው የእንግሊዝኛ ወይንም የፈረንሳይኛ ስም የሚይዙ ምርቶች፣ አገልግ
ሎቶች እና ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ሀገርኛ ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ አማራጮችን
ማቅረብ ይመስለኛል፡፡

በሀገራችን ባለቤት አልባ ውሾች ብቻ አይደለም ያሉት ባለቤት አልባ ሥራዎችም አሉ፡፡ ከነዚህ አንዱ
ኢትዮጵያውያን ስሞችን መቀረስ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች ገንዘብ ተከፍሏቸው ለሰዎችም ሆነ ለድርጅቶች
ተፈላጊ ስሞችን የሚያወጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ መቼም ድርጅትን ኤም ኤን ኢንተርናሽናል፤ ቢ ቲ
ትሬዲንግ፤ ሲ ፊ አስመጭ እያሉ ከመጥራት ከፍሎ ሸጋ ሸጋ ስም መውሰድ የተሻለ ነው፡፡

እናም ከጥንት መዛግብት፣ ከጥንት ጋዜጦች፣ የሰዎችን እና የድርጅቶችን ምዝገባ ከሚያካሂዱ መሥሪያ
ቤቶች፣ ከመቃብር ሥፍራዎች፣ መታወቂያ እና ፓስፖርት ከሚሰጡ ተቋማት፣ ሀገር ዐቀፍ ፈተና ከሚሰጡ
ድርጅቶች ወዘተ መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎችንም በመጠየቅ ስሞችን የመሰብሰብ፣
የመመዝገብ እና የመቀረስ ሥራ መሥራት ታሪክን፣ ባህልን፣ ፍልስፍናን እና ማንነትን የመጠበቅ እና
የመጠቀም አንዱ አካል ተደርጎ የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡

You might also like