You are on page 1of 16

ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቤተክርስቲያን አንጻር

በሰሎሞን ደጀኔ

ጭምቆ
እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአርአያው ወንድና ሴት አድርጎ ሲፈጥር ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት
ግዙአትም አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ይኽንን ሥልጣን/ኃላፊነት ሲሰጥ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ሥራ ተሳታፊና
የሥራውም ቀጣይ እንዲሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ በሰው ልጅ ሕይወትና በፍጥረት ላይ እንደሚሠራ ሁሉ
በእግዚአበሔር መልክና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ የዚህ የእግዚአብሔር መልክ በእርሱ ይንጸባረቅና መልኩና አምሳሉ
በሙላት ይገለጥ ዘንድ ሊሠራ ግድ ነው፡፡ መልክና አርአያ የሚለው ጥምር ቃል ውጭያዊ ገጽታን የሚገልጥ ሳይሆን
ባሕርይንና ተግባርን የሚመለከት ነው፡፡ ስለሆነም የሚሠራ አምላክ ምሳሌ፣ መልክና አርአያ የሆነ ፍጥረት በመሥራት
ፈጣሪውን ይመስላል፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ ቤተክርስቲያንም በበኩሏ ሥራን በተመለከተ በቀጥታና በተዘዋዋሪ
መልእክቷን ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ እንደዚሁም ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ አኳያ ሥራ የሚኖረውን ድርሻ
ቤተክርስቲያን አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል በመመርኰዝ ድምጿን ታሰማለች፡፡ የአገራችንን የሥራ ባሕል አስመልክቶ
የተለያዩ አመለካከቶችንና ባሕሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁንና በተለይ ከአገራችን መንፈሳዊነት (spirituality) አንጻር
ለሥራ የተሰጠውን ቦታ በአጭሩ መመልከቱ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህንንም ከታሪክ አንጻር በማየት ለዛሬ ምን ዓይነት
አንደምታ ይኖረዋል ብሎ መመርመሩ ከጊዜው ጋር የሚጣጣም ትርጉም እንድናገኝ ይረዳናል፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ነዳያንን
የመርዳትና የመመጽወት መንፈሳዊነትን ትናንት እንዴት ነበር? ዛሬስ ምን ይመስላል? በማለት መጠየቅ ሥራና ምጽዋት
መጠበቅ/መስጠት የሚኖራቸውን ትስስርና ልዩነት ለማወቅ ይረዳናል፡፡

መግቢያ
ሥራ ምንድን ነው? ሥራ ምንም ዓይነት ባሕርይ ቢኖረው የሰው ልጅ የሚያከናውነው ማናቸውም ተግባር ሁሉ -
የጉልበት ይሁን አእምሮአዊ - ሥራ ይባላል፡፡ (Laborem Exercens: Introduction) ሥራ የሰው ልጅ በተፈጥሮው
በውስጡ የተቀመጠ የኅልውናው መለያ የሆነ ባሕርይው ነው፡፡ ሰው ከሌሎች ፍጥረታት የሚለይበት አንዱ ባሕርይው
ሥራን መሥራት መቻሉ ነው፡፡ እንስሳት ራሳቸውን ለማቆየት የሚፈጽሟቸው የአደንና የምግብ ፍለጋ ተግባራት ሥራ ሊባሉ
አይችሉም፤ ምክንያቱም ሥራ - የጉልበትም ሆነ አእምሮአዊ - ከመነሻው በሀሳብና በሰው ልጅ አመክንዮ የተቀረጸ ስለሆነ
ነው፡፡ የእንስሳት ተግባር ግን በደመነፍስ በመመራት ሕይወታቸውን ለማቆየት የሚያደረጉት እንቅሰቃሴ ነው፡፡ ስለዚህ ሥራ
የሰው ልጅ ስብእና አንዱ መለያው ሲሆን ይኽንንም የሚፈጽመው በይነሰብአዊ (interpersonal) እና ማኅበረሰባዊ በሆነ
መቼት ውስጥ ነው፡፡

የሥራ ባሕል በኢትዮጵያ


ቋንቋ የአንድ ሕዝብ ማንነት፣ ባሕል፣ ወግ፣ እምነትና መሰል ባሕርያት የሚገለጡበት መሣሪያ ነው፡፡ በቋንቋ
ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ዘይቤዎች፣ አነጋገሮች ወጎች የሕዝቡን እሴቶች በተወሰነ መልኩ ይገልጣሉ፡፡ታድያ ለያዝነው ርእስ
በተወሰነ መልኩ በቋንቋችን ውስጥ ታምቀው ያሉትን አባባሎቸ በመጀመርያ ብንመለከት በተወሰነ ደረጃ ከታሪክና ከባሕል
አነጻር ለሥራ ባገራችን የሚሰጠውን ዋጋ ልንረዳ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይሄ በምንም ዓይነት ባሕሉን፣ እምነቱንና ሙሉ
ባሕርይውን እንደማይገልጸው ልንገነዘብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም አነጋገሮቹ ዕድሜን ያስቆጠሩ ከሆነ ከአሁኑ ትውልድ ጋር
ያላቸው የትርጉምና ተምሳሌታዊ ዋጋ (symbolic value) ምን ያህል ውስጣዊና ሥር የሰደደ መሆኑ ካልተመዘነ እንደው
መላምታዊና የነሲብ ድምዳሜ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ በታች በሥራ ዙሪያ ከሚታወቁ ምሳሌያዊ አነጋገሮች የተወሰኑትን
ወስደን እንመልከት፡፡
1. ሥራ ካልሠራችሁ የት ይገኝ ምሳችሁ
2. ሥራ ያጣ ገበሬ ጨው የሌለው በርበሬ
1
3. ሥራ ያጣ ጢስ ይሞቃል/ሙቅ ያኝካል/ገንፎ ያላምጣል
4. ሥራ ያጣ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል
5. ሥራ ከመፍታት ልጄን ላፋታት
6. ሥራ ያጣች አፍ ሞት ትጠራለች
7. ሥራ ለሠሪው እሾኽ ላጣሪው/ወሬ ላውሪው
እነኚህ ብሂሎች ወይም ምሳሌያዊ አነጋገሮች በተወሰነ መልኩ ባገራችን ስለሥራ ያለውን አመለካከትና እምነት
ይገልጻሉ፡፡ የመጀመሪያውን ብንመለከት ሥራን ከዕለት ጉርስ ወይም ከመተዳደሪያ ምንጭነት ጋር በማስተሳሰር ካለተሠራ
ምግብ ወይም የመተዳደሪያ ምንጭ ሊኖር እንደማይችል የሚያመለክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጨው የሌለው በርበሬ
ጣዕመ ቢስ እንደሆነና ተፈላጊነት እንደሌለው ሁሉ የማይሠራ ገበሬም እንደዚሁ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ለገበሬ መከበሩ፣
ወጉና ማማሩ መባተሉ፣ ላቡን ማንጠፍጠፉ ነው፡፡ በሌላ በኩል በቁጥር ሦስት የተቀመጡት የተለያየ ማሰሪያ ያላቸው
አባባሎች በሙሉ ሥራ ከመፍታት የሚደረጉ አላስፈላጊና ትርጉም አልባ ተግባራትን በመግለጥ የሥራ ፈትነትን አሉታዊ
ገጽታዎች ያስረግጣሉ፡፡ በቁጥር 4 እና 5 የተጠቀሱትም የሥራ ፈትነትን ጎጂ መልክ የሚገልጹ ሲሆኑ በተለይ በቁጥር 5
የተጠቀሰው አባባል ካለመሥራት መጥፎ ነገርም ቢሆን ለወግ ለማዕርግ ያበቁትን ልጅ እስከማፋታት ድረስ እንኳ ቢሆን
አንድ ነገር ማድረግ ግድ እንደሆነ ያመለክታል፤ ሌሎች በርግጥ ይህንን አባባል ሥራ የፈታ አእምሮ ምን ያህል በመጥፎ
ነገሮች ሊተበተብ እንደሚችልና ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ እንዲሁም 6ኛው ምሳሌያዊ አነጋገር
የሥራ ፈትነት መዘዝ ለራስ ውድቀት ወይም ለሞት እንደሚዳርግ ያስረዳል፡፡ በአንጻሩ 7ኛው ምሳሌያዊ አነጋገር እሾኽ
ለአጣሪው ቤቱን ከሰርጎ ገብ እንደሚከላከልለትና ዋስትናው እንደሚሆነው (በዘመኑ ሁኔታ በማሰብ) ሥራም ለሠሪው
ዋስትናው፣ መቆሚያው፣ መከበሪያው እንደሆነ የሚገልጽ ነው፡፡
እነኚህ ምሳሌያዊ አነጋገሮች በተወሰነ መልኩ የአገራችን ማኅበረሰብ ለሥራ የሚሰጠውን ዋጋ የሚያንጸባረቁ
ቢሆኑም ከአሁኑ ትውልድ ጋር ያላቸውን ግብረገባዊ/ሥነምግባራዊ ቁርኝት (moral/ethical relation) ለመገምገም
አዳጋች ነው፡፡ ከተጠቀሱት አነጋገሮች መካከል የተወሰኑቱ ምናልባትም በዘመናችን ወጣት የሚታወቁም አይደሉም፡፡ ይሄ
ደግሞ የሚያሰማው የእነኚህ አነጋገሮች ግብረገባዊ እሴት (moral value) ካለፈው ትውልድ ወደ አሁኑ በሙላት ሊተላለፍ
እንዳልቻለ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን እነኚህ አነጋገሮች ለአሁኑ ትውልድ ምንም ዓይነት የትርጉም፣ ተምሳሌታዊ ወይም
ግብረገባዊ ዋጋ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ የአነጋገሮቹ መልእክት ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው ትርጉም ያለው በመሆኑ
ለሥራ ሊሰጠው የሚገባውን ዋጋ በሚገባ ያስረዱታል፡፡ በተጨማሪም አነጋገሮቹ የተነሡበትን፣ የተፈጠሩበትን የትናንቱን
ማኅበረሰብ ታሪክና ዘርፈ ብዙ ታሪካዊ እሴቶች እንዲመረምር ሊጋብዙት እንደሚችሉና ከነዚያም ሊማር የሚችለውን
ቁምነገር ማግኘት እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡

ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊነትና ሥራ
እንግዲህ በአነጋገር ዙሪያ ይህንን ያህል ካልን ሥራ ከእምነት ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ቁርኝት እንዳለው በመጠኑ
እንመርምር፡፡ ምንም እንኳ ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ "የማይሠራ አይብላ" ቢልም
በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ የተቸገረን መመጽወት እንደሚገባ የሚያሳስቡ ጥቅሶችን እናገኛለን፡፡ የአገራችንም
መንፈሳዊነት ለነዳያን ምጽዋት መስጠትን የመንግሥተ ሰማያትን በር ቁልፍ ሊያስገኙ ከሚያስችሉ ሠናያት ቀዳሚውን ቦታ
እንደሚይዝ ያስተምረናል ብል የተሳሳተኩኝ አይመሰለኝም፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ አመጣጥ ያለው
ኢትዮጵያዊ መንፈሳዊነት ነው፡፡ መንፈሳዊነት ደግሞ መሠረቱን ሳይለቅ ከጊዜው ጋር ራሱን እያዋሐደ ከዘመን ዘመን
የሚተላለፍ የእምነት ልምምድ ነው፡፡
በቀደሙት ዘመናት የነበረን አኗኗር አሁን ካለን አኗኗር ጋር በበረካታ መልኩ የተለየ ነው፡፡ የከተማ ኑሮ
ባልተስፋፋበት፣ በትናንሽ መንደሮችና በገጠር፥ በእርሻና በከብት እርባታ የሚተዳደር ማኅበረሰብ የሚኖረው አኗኗር፣
በአሁኑ ጊዜ ካለው ከከተማ ቀመሱ ጋር የተለያየ ነው፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ባይወክል፤ የከተማ
ኑሮ በአገራችን በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ በርግጥ አሁንም ቢሆን በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከ20% (United Nations
Population Fund http://www.unfpa.org/profile/ethiopia.cfm, accessed 12 Dec. 2010) አልዘለለም፡፡

2
ይሁንና ይኸው 20% በቀረው 80% ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ በገበያ ዋጋና በሌሎችም መስኮች ላይ
ማየት ይቻላል፡፡ በተለይ የክር-አልባና የሞባይል ስልክ በስፋት በገጠሩ የአገራችን ክፍል መዘርጋቱ ያስከተለው እመርታ
ከፍተኛነቱ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የከተሞች ተመጣጣኝ ያለሆነ ዕድገትና ከገጠር ወደ ከተማ
የሚታየው ከፍተኛ የሕዝብ ፍልሰት፥ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሆነ አመቺና ፍትሐዊ የሆነ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ
ከተሞቹ ሊያስተናግዱት ከሚቸሉት በላይ በመሆኑ በከተሞች ውስጥ በተለይም በትላልቆቹ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የሥራ
አጥነት ችግር ይታያል፡፡ ምንም እንኳን ከገጠር ወደ ከተማ መፍለስ ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለና ነገም የሚኖር ቢሆን፤
በአሁኑ ወቅት ዘመኑ ያፈራው የመገናኛ ብዙኀንና ከላይ የጠቀሰኳቸው የስልክ አገልግሎቶች በገጠሩ የአገራችን ክፍሎች
መስፋፋት የፍልሰቱን ፍጥነት በእጅጉ ጨምሮታል፡፡ በአንጻሩ ከተሞቹ ይኽንን ለማስተናገድ አቅማቸው ገና አልዳበረም፡፡
ይኽንን ያነሣሁት ያለምክንያት አይደለም፡፡
በቀደሙት ዘመናት የሥራ አጥነት ችግር እምብዛም ነበር፡፡ አብዛኛው የኅበረተሰብ ክፍል በጭሰኝነትና በራሱ
ግብርና፣ በአርብቶ አደርነት እንዲሁም ባሕላዊ በሆነ የንግድ ሥራ ነበር የሚተዳደረው፡፡ አስተዳደሩም ዘመናዊ በሆነ
የመንግሥት ሥርዓት የተዋቀረ ባለመሆኑ የመተዳደሪያ ሥራ በግለሰቦችና በባላባቶች ሁኔታ የሚወሰን ነበር፡፡ የኑሮ ደረጃ
ዝቅ ይበል፣ ባልተመቻቸ የኅብረተሰብ ሥርዓት ውስጥ በባላባቶች ተጽእኖ ሥር ይሁን እንጂ፤ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል
ከላይ በጠቀስኳቸው የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ወይም ገባር ሆኖም ቢሆን እየሠራ የዕለት ጉርሱን እያገኘ ይኖር ነበር፡፡
ሥራ አጥነት እንደ አሁኑ ጊዜ ማኅበራዊ ችግር አልነበረም፡፡ ብቃት ኖሮአቸው፣ መሥራት እየቻሉ፣ ወዘተ በፍጹም
የማይሠሩና የሰው እጅ የሚያዩ አልነበሩም ባይባልም እጅግ ጥቂት ነበሩ፤ እንደማኅበራዊ ችግር እስከሚታይበት ደረጃም
አልደረሰም ነበር፡፡ በሥራ አጥነት ምክንያት ኑሮአቸው በችግር ከነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል አብዛኞቹ በደዌና
በአካል ጉዳተኝነት ምክንያተ መሥራት የማይችሉ ነበሩ፡፡ በዚህም መልክ ቢሆን ለመሥራት ካልታደሉት የኅብረተሰብ
ክፍሎች ከፍተኛውን ቦታ ይዘው የሚገኙት በሥጋ ደዌ በሽታ የተጎዱ፣ በተለያየ ሁኔታ የአካል ጉዳተኝነትና የአእምሮ
ዘገምተኝነት ተጠቂዎች ናቸው፡፡ በተለይም በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ከማኅበረሰቡ ተገልለው በግላቸው እንኳ
ለመሥራት እንዳይችሉ ከፍተኛ የሆነ የባሕል ተጽእኖ ይደረግባቸው ነበር፡፡ አሁንም ሙሉ ለሙሉ በመላው የአገሪቱ ክፍል
ችግሩ ተቀርፏል ለማለት አይቻልም፤ ተስፋ ሰጪ ለውጦች ግን እየታዩ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ውስጥ ታድያ ቤተክርስቲያን በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሰዎች
መንፈሳዊና ባሕላዊ ሕንጸት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራት፡፡ እንዲህ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ ለእነኚህ መሥራት ለማይችሉ
የኅብረተሰብ ክፍሎች ምጽዋት መስጠት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልምምድ ውስጥ እንደ ተጨማሪ መንፈሳዊ ነገር ሳይሆን
ዋነኛና መሠረታዊ መንፈሳዊነት ነበር፤ አሁንም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊታይ የሚገባው ከጊዜውና ከማኅበረሰቡ ባሕላዊና
ማኅበራዊ ዐውድ አንጻር ነው፡፡ በዚያን ዘመን ለልመና ወይም ለጥገኝነት የሚዳረጉት ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በአካል
ጉዳተኝነት የሚገኙና በሥጋ ደዌ በሸታ የሚጠቁ ግለሰቦች ሲሆኑ፤ እነኚህም ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ያላቸው አማራጭ
በልመና መተዳደር ወይም በበጎ ፈቃዳቸው ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች መጠጊያ የሚሰጡ ባለጸጎች ዘንድ መጠጋት ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ልመና በዘር የወረስነው ነው የሚሉ ከተወሰኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በስተቀር ዛሬ ጊዜ እንደምናየው
በየጎዳናው፣ በየመንገዱና በየደጀ ሰላሙ የሚለምን የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአደጋ ንብረታቸውን ያጡ፣ ጎተራቸው
የተቃጠለባቸው፣ ሠብላቸውን ዋግ የመታባቸው፣ ተምች የበላባቸው፣ ወዘተ የአካባቢው ኅብረተሰብና ዘመድ አዝማድ
የተቻለውን አዋጥቶ ይደጉማቸዋል፤ በቀረው በጣም ከከፋ ለተወሰነ ጊዜ እየዞሩ እርጥባን ይጠይቃሉ (ቃለመጠይቅ ከአቶ
ደጀኔ ወልደዮሐንስ ጋር ታኅሣሥ 6 ቀን 2003 ዓ.ም)፡፡ ለዚህም ነው የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊነት መመጽወትን እንደ
አስፈላጊ ሠናይና ቁልፍ መንፈሳዊነት የሚቆጥረው - የሚለምነው በጤና ችግር፣ በአስገዳጅ የባሕል፣ የኑሮ ሁኔታ መሥራት
የማይችል ሰለሆነ፡፡ ዛሬ በተለምዶ ለማኝ እንላለን እንጂ ትክክለኛ ስያሜው "የኔ ቢጤ" ነው፡፡ የኔ ቢጤ የሚለው ቃል
የዚያን ተመጽዋች ክቡርነት የሚገልጽ ነው፡፡ ከራስ ጋር ማመሳሰሉ ደረጃው ዝቅ ያለ አለመሆኑንና ዕድል ፈንታው እንጂ
እሱም እንደእኔው ሰው መሆኑን፣ የእኔ ቢጤ፣ የእኔ መሰል መሆኑን፤ ነገር ግን ሊሠራ ባለመቻሉ ሊረዳ ሊደገፍ የሚገባው
መሆኑን የሚያንጸባረቅ ቃል ወይም ስያሜ ነው፡፡
እንግዲህ ባሕላችንና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያቆዩልን ይሄ መንፈሳዊነት በጥልቀት ባለመመርመሩ ምክንያት
በየጎዳናው፣ በየደጀሰላሙ፣ በየገበያ ቦታ ቆሞና ተቀምጦ፣ ወይም በር እያንኳኳ ለሚለምን ሁሉ ኅብረተሰባችን ያለማንገራገር
ይመጸውታል፡፡ ይሄ መንፈሳዊነት ከላይ ከተመለከትነው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊነት ጋር ይጣረሳል፡፡ ማለትም
ቤተክርስቲያን ለነዳያን መስጠትንና ለተቸገሩት መመጽወትን እንደትልቅ ሠናይ የመታስተምረው በዚያን ዘመን ከነበረው
3
ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሁኔታ በመነሣት በተለያዩ አስገዳጅ ሁኔታዎች መሥራት ለማይችሉ
ሰዎች እንጂ በስንፍና፣ በቸልተኝነት፣ በባሕርይ ችግር፣ ወዘተ ለማይሠራና የሰው እጅ ለሚያይ ሁሉ አይደለም፡፡ ይሁንና
ይሄንን መንፈሳዊነት በሙላት ባለመረዳት ዛሬ በየቦታው እጁን ለዘረጋ ሁሉ በመመጽወት የዚህ መንፈሳዊነት ተሳታፊ የሆኑ
የሚመስላቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንንም ለመረዳት በተለይ በእሑድና በንግሥ በዓላት ቀን በየአብያተ ክርስቲያናቱ
ደጃፍ የሚኰለኰለውን የነዳያን ብዛትና ሲገባና ሲወጣ የሚመጸውተውን ምእመን ብዛት መመልከቱ ሁነኛ ማስረጃ
ይሆናል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ልመና ካለመቻል ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ቤተክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ ነበር
መመጽወትን ከፍተኛ ቦታ ከሚይዙ ሠናያት መካከል እንደአንደኛው አድርጋ የምትወስደው፡፡ ታድያ አሁን ባለንበት ዘመን
ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በአብዛኛው ልመና ካለመቻል ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደ አማራጭ፣ አነስተኛ ገቢ ከሚያስገኝ ሥራ
እንደተሻለ የገቢ ምንጭ፣ ወይም በባሕላዊና ማኅበራዊ ተጽእኖ የተናቀና ጥሩ ቦታ ከማይሰጠው ሥራ ይልቅ እንደተሸለ የገቢ
ምንጭ፣ አንዳንዴም እንደ ሁለተኛ ሥራ፣ ብሎም እንደቀላል ገቢ ማግኛ ዘዴ የሚታይበት ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡
ቤተክርስቲያን ታድያ ይህንን ጥልቅ የሆነ ዋጋ ያለው መንፈሳዊነት ምእመናን በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት እጁን ለዘረጋ
ሁሉ በመመጽወት መሥራት የሚችሉ እግዚአብሔር የፈጠራቸው እጆች እንዳይሠሩ እያደረጉ ስለሆነ በአሁኑ ማኅበረሰብ
ውስጥ የዚህ መንፈሳዊነት ሥነምግባራዊና ነገረ መለኮታዊ ዋጋ ምን እንደሆነና በእንዴት ያለ ሁኔታ ለተቸገሩት እጅን
መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ ልታስተምር ይገባል፡፡ ካለፉት ትውልዶች የወረስናቸው መልካም የሆኑት መንፈሳዊ ቅርሶችና
ሠናያት በራሳቸው ጥሩ ሆነው ሳሉ፤ ከዘመናችን ጋር አለማጣጣማችን ከሥራ ይልቅ ልመናን የሚያበረታታ ባሕልን
እንድናሳድግ እያደረገን ነው ብል ከሐቅ መራቅ አይሆንም፡፡
ቤተክርስቲያን መመጽወትን ከፍተኛ ቦታ ስትሰጠው ኅብረተሰቡ ለሥራ የሚሰጠውን ቦታ በሚሸረሽር መልኩ
አልነበረም፡፡ እንዴት? ቢባል በአካል ጉዳት፣ በደዌ ወይም በባሕል ተጽእኖ ምክንያት መሥራት የማይችል ብቻ ነበር
የሚለምነውና፡፡ አሁን ግን ፈርጣማውና ጉልበታሙም፣ ደኅና ልጆች ያሉአቸው አረጋውያንም፣ ኑሮ ትንሽ ጎርበጥ ያለውም፣
ብቻ ዓይነቱ ብዙ ነው የሚለምነው፡፡ የለጋሹም ሁኔታ የዚህኑ ያህል አስገራሚ ነው፡፡ ጫማ የሚጠርገው፣ የመኪና ማቆሚያ
ሒሳብ የምትሰበስበው፣ በየደጃፋችን ከታክሲ ወይም ከመኪና ስንወርድ ከበድ ያለ ዕቃችንን ተሸክሞ ቤት የሚያደርስልን፣
ወዘተ ዋጋው ላይ የጥቂት ሣንቲም ለውጥ ካደረገ/ች ለመደራደር፣ ለመቆጣት የሚፈጥን ብዙ ሰው አለ፡፡ በአንጻሩ ስለ...ብሎ
ለሚለምን ከአፍታ በፊት በጥቂት ሣንቲም ከጫማ ጠራጊ ጋር በቁጣ የተጨቃጨቀው ግለሰብ ጫማ ጠራጊው ከጠየቀው
የዋጋ ልዩነት በላይ ለፈርጣመው `ለማኝ́ ́1 ሲመጸውት መመልከት እንግዳ ገጠመኝ አይመስለኝም፡፡ መመጽወቱ በራሱ ምንም
ክፋት የለውም፤ እንደውም ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ክብር ባለው መንገድ ራሱን ለማስተዳደር ያልቻለን ግለሰብ ችግሩን
በመመልከት ካለው ያካፈለ ሰው የልቡን መነካትና ርኅራሄ የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ልምምድ በትንሹ ሁለት
መሠረታዊ ችግሮች ይታዩበታል፡፡ አንደኛው በመመጽወት ኑሮን ማሻሻል ወይም ማሸነፍ ይቻላል ብሎ ማሰብ
ከአብዛኞቻችን ተሞክሮ አንጻር ስንመለከተው የተሳሳተ በመሆኑ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለበርካታ ዐሠርት ሲመጸወቱ የነበሩ
አገራት እንኳን ለውጣቸው ሽንቁር እንስራ ውስጥ ውኃ ከመሙላት የተለየ እንዳልሆነ በአገራችንና በበርከታ በኢኮኖሚ
ባልበለጸጉ አገራት የምንመለከተው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተመጽዋቹም ቢሆን ራሱን ወደ መቻልና ለሥራም የሚሰጠውን
ግምት የሚያዳክምበት ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ ዋናው ቁምነገር ያ በዘመኑ ሁኔታውን አጢኖ የተወለደ መንፈሳዊነት፥ ጊዜውና ሁኔታው በተለወጠ ጊዜ
ዘመኑን ሊዋጅ ራሱን ካልለወጠ ወይም በጊዜው ዐውድ ካልተጠመቀ ከዘመኑ ጋር ይጣረሳል፡፡ ታድያ ዛሬ ሊሠሩ የሚችሉ
እጆች በየመንገዱ ዳር፣ በየደጀሰላሙ፣ በየገበያው ለመመጽወትና ለጥገኝነት ሲዘረጉ ስናይ ቆም ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ
ያስፈልጋል፡፡ "በመስጠቴ ለዚህ ግለሰብ ሕይወት ምን ፋይዳ አመጣለሁ? ባልመጸውተውስ ከሱም ሆነ ከአምላክ ምን
አጎድላለሁ?" ከላይ የተመለከትነው መንፈሳዊነት አነሣሱ ምን እንደሆነ ከሥር መሠረቱ በማጤን ዛሬ የምናየውን የሥራ
ባሕላችንን የሚሸረሽረውን የልመና ባሕል እጃችንን ለሚሠሩ እጆች እንጂ ለሚለምኑ እጆች ባለመዘርጋት ልጓም ልናበጅለት
እንችላለን፡፡ "ብቻዬን በኅብረተሰቡ ላይ ለውጥ ማምጣት አልችልም" እንዳይሉ አንደኛ ብቻዎን አይደሉም ቢያንስ ይህን
1
የኔ ቢጤ ከሚለው ቃል ይልቅ እዚህ ጋ ለማኝ የሚለውን ስያሜ የተጠቀምኩት ቀደም ሲል ባስቀመጥኳቸው ምክንያቶች ወደ ልመና የመጣው
ግለሰብ በመገፋት ሳይሆን በተለያዩ ምክንያቶች በተወሰነ መልኩ በምርጫ በመሆኑ ስለሆነ ነው፡፡ የኔ ቢጤው ልመና ዕድል ፈንታው ሲሆን ቀን
ሲቀየር ሌላ ዕድል ፈንታም ሊኖረው ይችላል፡፡ ስለ ዕድል በኢትዮጵያ ያለውን አስተሳሰብ ፍልስፍናዊ ትንታኔ Messay Kebede. 1999 ይመልከቱ

4
ጽሑፍ ሲያነቡ ብቻዎን እንዳልሆኑ ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛ ዛሬ ብቻዎን የሚያደርጉትን ነገር የሚመለከት ታዛቢ ነገ የእርስዎ
ደቀመዝሙር ሆኖ ተባባሪዎ ይሆናል፡፡ ሦስተኛ የየትኛውም ርቀት መንገድ የሚጀመረው በአንድ እርምጃ መሆኑን
በመገንዘብ አንድ ብለው የጀመሩት እርምጃ ቀስ ብሎ የተለሙት ርቀት ላይ እንደሚያደርስዎ ራስዎን ሊያሳምኑ ይገባል፡፡
ከአገራችን ባሕልና መንፈሳዊነት አንጻር ስለሥራ ይህንን ያህል ከተባለ መጠነኛ ግንዛቤ ለማግኘት በቂ ይሆናል፡፡
በመቀጠል ደግሞ በአሁኑ ወቅት ያለው ኅብረተሰብ ከሥራ ጋር ያለውን ልምምድ በተወሰነ መልኩ እንመልከተው፡፡

በአሁኑ ወቅት የሥራ ባሕላችንና ሥነምግባራችን ምን ይመስላል?


በጥቅሉ ስለሥራ ይህንን ያህል ካልን አሁን ያለንበት ማኅበረሰብ ለሥራ ያለው አመለካከት ምን ይመስላል? የሥራ
ባሕላችንና ሥነምግባራችንስ ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች በአጭሩ እንመልከት፡፡ "ሥራ ለአህያም አልበጃትም"
ከሚለው ዘመን አመጣሽ የምጸት ብሂል በመጀመር ለሥራ የሚሰጠውን ቦታ እንመልከት፡፡ በየመንገዱ ከባድ ሸክም ተጭና
የምትሄድ አህያን የተመለከተ በእውነቱ ሥራ ለአህያ ምንም እንዳልበጃት እንደውም ዱላ እንዳተረፋት ይገነዘባል፡፡ ሥራዋን
ከተገቢው በላይ የምትወጣውን አህያ ደጋግሞ እየመታ የሚያሰቃያት አህያ ነጂ ወይም የአህያ ባለቤት ያልተገነዘበው ነገር
ቢኖር የመኖሩ ዋስትና የአህያዋ በጤናና በብቃት መኖር መሆኑን ነው፡፡ [ዛሬ በአብዛኛው በታክሲና በሌላ የሕዝብና የጭነት
ማመላለሻ መኪናዎች ላይ ተቀጥረው የሚሠሩ ግለሰቦች የሚያሽከረክሩትን መኪና ከልክ በላይ በማሠራት በተሸከርካሪው
ላይ ጉዳት ሲያደርሱ እናያለን፡፡ የተሽከርካሪው ባለቤት መኪናዋ ካስገባችው ገቢ የሚያገኘው ግማሹን ወይም ከግማሽ በታች
ነው፡፡ አሽከርካሪውና ረዳቱ የሚያስቀሩትን ገንዘብ ጆርናታ ይሉታል፡፡ ከአህያ ነጂው ጋር የሚለያየው አህያዋ ሕይወት ያላት
ፍጡር በመሆኗ በዱላው ምክንያት መሠቃየቷ ነው፡፡] ለሥራውም ሆነ ለአህያዪቱ የሚሰጣቸው ክብር ከፍተኛ ባለመሆኑ
አህያዪቱን በመደብደብ ብዙ ለማሠራት ይሞክራል፡፡ አህያዪቱ ዱላ የተረፋት በሚገባ በመሥራቷ ሳይሆን ለሥራዋ ተገቢ
ምላሽና ሽልማት ወይም ደሞዝ ከመስጠት ፋንታ ከአቅሟ በላይ ከሚጠብቅ አህያ ነጂ የሚመነጭ የግፍና ያለማስተዋል
እርምጃ ነው፡፡ ይልቁንም "ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል፡፡" የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል እንደ መሪ ቃል በመውሰድ
ፍትሐዊ የሥራ ዋጋ መክፈልን በአገር ደረጃ በሕግ እንዲቀረጽ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም ይህንን በአህያዪቱ ላይ
የተፈጸመውን ኢፍተሐዊ የሆነ የሥራ ዋጋ በመመልከት የሚደረስ ብሂል ስላቅ ወይም ምጸት እንደሆነ እንጂ ለተግባራዊ
ንጽጽር የሚሆን ሆኖ አይታየኝም፡፡ በአንጻሩ ምጸትነቱን ባለማስተዋል ይሁን ሀኬተኝነትን ለመሸፈን ይህንን ብሂል መሠረት
በማድረግ ሥራን በትጋት አለመሥራታቸውን የሚገልጹ አንዳንድ ሰዎች ሳያጋጥሙን አልቀሩም፡፡
የአገራችንን ወቅታዊ የሥራ ባሕልና ሥነምግባር ለመዘርዘርና በዚያ ላይ ትንታኔ መስጠት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ
አይደለም፡፡ ይሁንና ጥቂት ነጥቦችን ማንሣቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ላነሣ የምወድደው በቤተሰብ ውስጥም ሆነ
በጓደኞች አካባቢ የትምህርት አቅጣጫን ለመወሰን ልጆቻችንንና ጓደኞቻችንን የምንቀርጽበት አንዱ መሥፈርት ለሥራ ካለን
ግንዛቤ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ እንድንመረምረው ማስፈለጉን ላሳስብ እወድዳለሁ፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ወደ ሦስተኛ ደረጃ
(ኮሌጅ/ዩኒቨርሲቲ) ልጆቻችን/ጓደኞቻችን ለመግባት በሚዘጋጁበት ጊዜ በአብዛኛው የምርጫቸውን አቅጣጫ ልንቀርጽ
የምንፈልገው የሚማሩት ትምህርት ከሚኖረው የሥራ ገበያ ጋር የተቆራኘ ብቻ ሳይሆን ሊያስገኝ ከሚችለው ዳጎስ ያለ የገቢ
ምንጭ አንጻርም ነው፡፡ በተለምዶም "ይሄንን መስክ ብትመረጥ በጣም ያበላል፡፡" በማለት አቅጣጫውን ወደ ተወሰነ መስክ
እንዲያደርግ እንገፋፋዋለን፡፡ ዝንባሌና ስጦታ በዚህ ዓይነት አካሄድ ቦታ አይኖራቸውም፡፡ የሥነጽሑፍ ስጦታና ዝንባሌ
ያለውን ወጣት ገና ለገና ጥሩ ገቢ ያስገኛል በማለት ወደ ምሕንድስና የትምህርት መስክ እንዲገባ ብናደርገው ምናልባት
ያልነውን ጠቀም ያለ ገቢ ሊያገኝ ይችላል፤ ነገር ግን ጸጋዬ ገብረመድኅንን የሚያስንቅ ጸሐፊና ባለቅኔ እንዳይፈጠር ምክንያት
እንሆንም ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ አገርና ወገን ሊያገኝ የሚችለውን እሴት ማጣት ማለት ነው፡፡ የመንግሥትም የ70/30
ፖሊሲ በዚህ አንጻር ሲታይ ገበያ ተኮር እንጂ ሁለንተናዊ የሰውን ዕድገት መሠረት ያደረገ እንዳለሆነ ይታያል፤ በመሆኑም
መብትንና ፈቃድን የሚገድብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በርግጥ ለፍቶና ደክሞ ያስተማረ ወላጅ እንዲሁም ዐይኑን ጨምቆና
ራሱን አስሮ የተማረ ወጣት ዳጎስ ያለ ገቢ ያለው ሥራ ለማግኘት ቢጓጓ በራሱ ምንም ስህተት የለበትም፤ ነገር ግን ሥራን
እንደገቢ ማስገኛ መሣሪያ ብቻ መቁጠሩ የሥራን ክቡርነት ይቀንሳል፡፡ በዚህ መልኩ ሥራን የምንመለከት ከሆነ በተዘዋዋሪ
አነስተኛ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን እንንቃቸዋለን ወይም ዝቅተኛ ዋጋ እንሰጣቸዋለን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን
አስተሳሰብ ይዞ ወደ ሥራ የገባ ሰው ደግሞ የገባበት የሥራ መስክ ተፈላጊነቱ ቀንሶ የሚያገኘው ገቢ ካሽቆለቆለ ያ ግለሰብ
የሥራውን መስክ ሊጠላው ይችላል፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ሥራ የገቢ ማግኛ ዘዴ ቢሆንም በዋነኝነት የሰው ልጅ

5
ስብእናውን የሚያሳድግበት፣ በእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ ተሳታፊ የሚሆንበት፣ ብሎም በምድርና በግዙፉ ዓለም ሁሉ
ላይ የሚሠለጥንበት መንገድ ነው፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ የመንግሥት፣ የግልና የሃይማኖት ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦችን የሥራ ባሕል
በተለያየ አጋጣሚ ተመልክተን የሥራ ሥነምግባራቸው አሳዝኖን ይሆናል፡፡ በአንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ በተለይም
አገልግሎት ሰጪ በሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች ተገልጋዩ በሚፈልጋቸው ሰዓት የሠራተኞች በሥራ
ቦታቸው አለመገኘት፣ አላስፈላጊ በሆነ ምክንያት ተገልጋዩን/ደንበኛውን ማመላለስና ማጉላላት፣ ለተገልጋዩ/ለደንበኛው
በሰጡት የቀጠሮ ሰዓት/ቀን መሠረት ሊፈጽሙ ቃል የገቡትን ሥራ ሳያከናውኑ መቅረት ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ በሰጡት
የቀጠሮ ቀን/ሰዓት እንደማይደረስ እያወቁ ደንበኛው/ተገልጋዩ ምንም ግልጋሎት ላያገኝ እንዳይመጣ በስልክ ሆነ በሌላ
መንገድ አለማሳወቅና ማድከም፣ ወዘተ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ቢሮዎች ለደንበኞች አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው ከሥራ
መግቢያ ሰዓት ግማሽ ሰዓት በኋላ ሲሆን ከአንድ ሰዓት አገልግሎት መሰጠት በኋላ በሻይ ዕረፍት ይቋረጣል፡፡ ምንም እንኳን
የሻይ ዕረፍት አይኑር ባይባልም (በአንዳንድ ድርጅቶች እዚያው የሥራ ቦታቸው ላይ ነው የሚቀርብላቸው) አብዛኛውን ጊዜ
ከግማሽ ሰዓት እስከ 45 ደቂቃና ከዚያም በላይ በዚህ ምክንያት መቃጠሉ ግን ድርጅቱም ሆነ የሚመለከተው ሠራተኛ
ለደንበኛው/ለተገልጋዩ የሚሰጠውን ክብር ማነስ ከማመልከቱም ባሻገር ለሁለቱም ወገን የጊዜና የገንዘብ ብክነት ከፍተኛ
አስተዋፅኦ አለው፡፡
በሌላ በኩል የቅርብ ቁጥጥር በሌለባቸው አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በሥራ ገበታ ላይ በሰዓቱ አለመገኘት
ወይም ከሥራ ገበታ ተነሥቶ ወደ ግል ጉዳይ ወይም እንዲሁ ወጣ ማለት የተለመደበት ሁኔታ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ
መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ የሰዓት መቆጣጠሪያ ፊርማ ባለባቸው ድርጅቶች ውስጥ በሥራ ቦታ አለመገኘት ያልተለመደ
ነገር አይደለም፡፡ በርግጥ እነኚህ ሁሉ የተጠቀሱት ችግሮች አሉ ማለት ሥራቸውን በተገቢ ሁኔታ የሚሠሩ ሰዎች የሉም
ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ በበርካታ ድርጅቶች ውስጥ የሚታዩ ሲሆን ቤተክርስቲያን ውስጥም ሆነ ሌሎች
ክርስቲያናዊ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦች ከዚህ የጸዱ አይደሉም፡፡ እንደውም ቤተክርስቲያን አካባቢ ችግሩ
በአንጻራዊነት ሲታይ የሚጎላ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በጸሎት፣ በበዓላትና በመሳሰሉት በማመካኘት ከሥራ ገበታ
መነሣት ወይም ከቶውኑ አለመገኘት ከሥራ ሥነምግባር አንጻር እንደ ስህተት የሚቆጠር አይመስልም፡፡ ይሄ ደግሞ
ከመለማመድ የመጣ በመሆኑ ለማረቅም እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡
ከላይ የዘረዘርናቸው ደንበኛን/ተገልጋይን ተገቢና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዳያስተናግዱ ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ
ነጥቦች አንዱ ግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖር ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግል እንዲሁም በቤተክርስቲያን ድርጅቶች
ውስጥ ምንም እንኳን በሥራ ዙሪያ ስብሰባዎች ቢካሄዱም አለቆችም ሆኑ ጭፍሮች በሙሉ ግልጽነት በድፍረት የመነጋገር
ልምምዱና ባሕሉ የላቸውም፡፡ እንደውም ከሠራተኞች መካከል በግልጽ የሚናገር ካለ፣ "ምን አገባኝ ብሎ ነው እንደዚህ
የሚለው አሁን? አርፎ አይቀመጥም ይልቅ!" በማለት ሌሎች ሠራተኞች ያጉተመትሙበታል፣ የሚቀርቡትም ይነግሩታል፡፡
ይሄ ደግሞ የሚያመለክተው አለመተማመንን ነው፡፡ መተማመን በሌለበት ቦታ ደግሞ ፍሬአማ የሆነ ሥራ መሥራት
አይቻልም፡፡ ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ ነገር ግን በላቀ ሁኔታ ሊሠራ ሲችል ሠራተኛው ሊሠራ ከሚችለው አቅም በታች
ይሠራል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ ደንበኞች/ተገልጋዮች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ተቀብሎና አርሞ ወደ
ተሻለ ደረጃ ለመድረስ አዳጋች ይሆናል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ ኃላፊነትን የመጋራትና ውክልናን የመስጠት ባሕል አለመዳበር በሥራ ሥነምግባራችን
ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያደርጋል፡፡ ኃላፊነትን ካለመጋራትና ከግልጽነት ማነስ ጋር ተገናኝቶ የሚፈጠር አንድ ችግር አለ፡፡
ይኸውም በሠራተኞች መካከል መፈራራት፡፡ መፈራራት ባለበት ደግሞ ምንም ዓይነት መዘዝ የማይኖራቸውን ተግባራት
እንኳን በቀጥታ የሚመለከተው የሥራ ኃላፊ ከሌለ ለማከናወን የትኛውም ሠራተኛ አይደፍርም፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ
ባለጉዳይ ብዙ ጊዜ የሚጉላላበት ሁኔታ አለ፡፡ ነህምያ ከንጉሡ ፈቃድ አግኝቶ የኢየሩሳሌምን ቅጽር ለማደስ በተነሣበት ጊዜ
በመጀመሪያ ያደረገው ሁኔታውን በዝርዝር በማጥናት ይቆጩ ዘንድ ለወገኖቹ መንገር ነበር፡፡ ከዚያም ኃላፊነትን
ተከፋፍለው ቅጽሪቱን አደሱ፡፡ ይህንን በሚያደርግበት ጊዜ በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ ነገር ግን በጽናት በመጓዝና
በተገቢ ሁኔታ ኃላፊነትን በማከፋፈል ከዳር ሊያደርሰው ችሏል፡፡ ዛሬ በበርካታ ድርጅቶች አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ
ኃላፊነትን ማካፈልና ማስተላለፍ ባሕሉና ልምዱ ስለሌለ ውሳኔ ለማግኘት ብዙዎች የሚንከራተቱበት፣ ጉዳያቸው እልባት
ሳያገኝ ተስፋ ቆርጠው የሚተዉበት፤ በዚሁ ምክንያት ላላስፈላጊ ወጪ የሚዳረጉበት ወዘተ ሁኔታ በጣም ይታያል፡፡
ፓስተሮች ኃላፊነት ባለማጋራታቸው እነሱ ትተው ሲያለፉ ቤተክርስቲያናቸው ትከስማለች፡፡ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሹሞች
6
ለሥራ ጉዳይ፣ ለስብሰባ፣ ለሥልጠና፣ በጤና ችግር ወዘተ ለተወሰኑ ቀናት ወይም ሳምንታት በሥራ ገበታቸው ላይ
በማይገኙበት ጊዜ ቀላል ጉዳዮች እንኳን ውሳኔ ሰጪ አጥተው የሚጓተቱበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡ በቅርብ ያለ
ባልደረባቸውን ወይም ብቃት ያለውን ሌላ ሠራተኛ ኃላፊነት ስለማይሰጡ ባለጉዳይ ያለአግባብ ጊዜውና ገንዘቡ
ይባክንበታል፡፡ በቀጥታ በኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጠው ሠራተኛ በቦታው ከሌለ በምክትሉም ሆነ በሌሎች ከሥራው ጋር
ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሠራተኞች ውሳኔ እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ደንበኞች ላልተፈለገ እንግልት
ይዳረጋሉ፤ እንዲሁም ሥራ ይበደላል፡፡ ይሄ ደግሞ ኃላፊነትን ለማጋራት ካለመፈለግ፣ ኃላፊነትን በራስ ዙሪያ ብቻ
ለመሰብሰብ ካለ ጥማት፣ በሥራ ባልደረቦች ላይ እምነት ካለመኖር፣ ከራስ ሌላ ለሥራው ብቃት ያለው ሰው የለም/ላይኖር
ይችላል ከሚል ስጋት የተሞላበት ወይም የግብዝነት አስተሳስብ፣ በራስ የመተማመን ሁኔታ አነስተኛ ከመሆን የሚፈጠር
ነው፡፡
"ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤"
(ማር 6፡7) ጌታ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ጠርቶ ይህንን ኃላፊነት ሲሰጣቸው በአንድ በኩል አብረውት ባሳለፉት ጥቂት ቆይታዎች
ከእርሱ የተለማመዱትን የእምነት ጉዞና ትምህርት በተግባር የሚፈትኑበት የልምምድ ጊዜ ሊሰጣቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል
ደግሞ ሥልጣኑንና ኃላፊነቱን በማጋራት የሥራውን ቀጣይነት መልክ ለማስያዝና አገልግሎቱን ለማስፋት ነው፡፡ ከሥራ
አንጻር ስንመለከተው ደግሞ ሁለት መሠረታዊ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በእርሱ ብቻ ይከናወኑ የነበሩ
ተግባራትን (የፈውስ፣ ነጻ የማውጣት፣ የማስተማር፣ ወዘተ) ለዐሥራ ሁለቱ በመስጠት አገልግሎቱን ከእሱ ብቻ ያገኙ
የነበሩት አሁን ቢያንስ ከዐሥራ ሁለት ሰው ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መጉላላት ይቀንሳል፣ በርካታ
የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊደረሱ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው ግን ተተኪ በማፍራት የጀመረው
ሥራ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ማስቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ዓይነት ልምምድና ባሕል እጦት ጋር በተያያዘ
በአገራችን የምናየው ችግር አለ፡፡ ከትናንሽ አንሥቶ እስከ ትላልቅ በሙያ ወይም በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች
ከአብራካቸው የወጡ ልጆቻቸውን ይሁን በሥራው ዘርፍ ከእነርሱ ጋር ሆኖ የሚሠራን ግለሰብ ኃላፊነትንና ሥልጣንን
በመስጠት የማለማመድ ባሕል ካለመኖሩ የተነሣ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው የጀመሩትን፣ ለፍተውና ደክመው ዘመናቸውን
ሙሉ ሠርተው ያቆሙትን ደርጅት በዕድሜ ይሁን በጤና ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ሥራቸው አብሮ እንዲሞት
ሲያደርጉት ይታያል፡፡ ተረካቢ ባለመዘጋጀቱ ለሽያጭ ይዳረጋል ወይም ከስሮ ይዘጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለዕደጥበብና ለእጅ ሙያና ለንግድ በባሕላችን ይሰጣቸው የነበረው ቦታ ዛሬ ላለን አመለካከት
የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡ አባቶቻችን ፋቂ፣ ቀጥቃጭ፣ መጫኛ ነካሽ በማለት አንቋሽሸውና አናንቀው ሲጠሩ
መስማታችን በተወሰነ መልኩ ለሙያው ያለንን አመለካከት አሉታዊ ያደርገዋል፡፡ ይሄ በራሱ ዝንባሌና ችሎታው ቢኖረን
እንኳን ወደነዚህ ሙያዎች እንዳንገባ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡ በርግጥ ባለፉት ጥቂት ዐሠርት ዓመታት በሁሉም
መስክ ባይሆን በተወሰኑ የዕደጥበብ ሙያዎችና በንግድ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች ከፍተኛ የሆነ የኑሮ መሻሻል
በማሳየታቸው በኅብረተሰቡ ውስጥ ለሙያ ዘርፎቹ ያለው አመለካከት በአብዛኛው እየተቀየረ ነው፡፡ ይሁንና አሁንም
መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ አብያተ ክርስቲያናት ሰፊ ሚና ሊጫወቱ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ምእመኖቻቸውን ብቻ ሳይሆን መላውን ኅብረተሰብ የመገናኛ ብዙኀንን በመጠቀም ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይም የንግዱን የሥራ ዘርፍ በተመለከተ ከሥነምግባር አኳያ ትልቅ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡
የንግዱን ኅብረተሰብ መድረስን ጨምሮ ኅብረተሰቡ ስለንግድ ያለውን አመለካከትና አስተሳሰብ በሥነምግባር ለማነጽ
ቤተክርስቲያን ራሷን ልታስታጥቅ ይገባል፡፡ በመንገድ ላይ አንድን ሰው አስቁመን ስለንግድ ሙያ ብንጠይቀው በአብዛኛው
የምናገኘው መልስ፥ "በአጭር ጊዜ የሚከበርበት (ሀብት የሚገኝበት) የሙያ ዘርፍ ነው፡፡" ይሆናል፡፡ በአንድ በኩል፥ "ነጋዴ
ሌባ ነው፡፡" የሚለው አባባል በጣም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህንኑ አባባል የሚጠቀመው ግለሰብ ደግሞ ራሱ ነጋዴ መሆን
የሚፈልግበት ሁኔታም ይታያል፡፡ ማንም መቼም ሌባ መሆን የሚፈልግ የለም፡፡ ታድያ ለምንድን ነው ነጋዴ ሌባ ነው
የሚለው ሰው ራሱ ነጋዴ መሆን የሚፈልገው? እዚህ ላይ ነው መሠረታዊ ችግሩ፡፡ እያንዳንዱ ሙያ ለባለሙያውና
ለማኅበረሰቡ የሚያበረክተው ማኅራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ዋጋ አለው፡፡ ነገር ግን ሙያው በራሱ ሥነምግባርና ሙያዊ
የዕድገት ለውጥ ባሕል (dynamics)ካልተመራ ማኅበረሰቡ ለሙያው የሚኖረው አመለካከት አሉታዊ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ
ነው ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቃል ስታስተምር ወይም የምሥራቹን ቃል ስታውጅ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለሥርዓተ
አምልኮና ለጸሎት ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ሳይሆን፥ "ሕያውና የሚሠራ ነው፤ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ ስለታም ነው፤
ነፍስንና መንፈስን፥ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ የሚቆራርጥ ነው፤ በልብ ውስጥ የተሰወረውንመ ሐሳብና ምኞት
7
መርምሮ የሚፈርድ ነው፡፡" (ዕብ 4፡12) እንደሆነም ማስተማር ይኖርባታል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቃሉ በዕለት ተዕለት
ሕይወት ላይ ለውጥ በማምጣት በሥራ ገበታ ላይ ከሥነምግባርም ሆነ ከውጤታማነት አንጻር ልቆ መገኘትን ማምጣት
ይኖርበታል፡፡ በተለይም ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ የሥነምግባር ጉዳይ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ የንግድን ሥራ
በእግዚአብሔር ቃል የማረቅ አገልግሎት ቤተክርስቲያን ላይ ተጥሏል፡፡ ይህንን ዓይነት ለውጥ በሰዎች ላይ ማምጣት
ካልቻለ ቃሉ በመንገድ ዳር እንደወደቀው ዘር ወፎች በልተውታል፤ ወይም በጭንጫማ መሬት ላይ እንደወደቀው ዘር ገና
እንደበቀለ ፀሐይ ሲያገኘው እንደጠወለገው ነው፤ አልያም በእሾኽ ቁጥቋጦ መካከል እንደወደቀው ዘር ነው፣ ጥቂት
እንደበቀለ እሾኹ አንቆ ያለፍሬ ቀጨው፡፡ (ማር 4፡3-7)
እንደዚሁም በተለምዶ በጎዳና ቋንቋ ቢዝነስ የሚለው ቃል ከተሰጠው አሻሚና ሰፊ ትርጉም የተነሣ የተለያዩ
የማጭበርበርም ሆነ በሙስና የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ እንዲካቱተ የተደረገ ይመስላል፡፡ ቢዝነስ መሥራት ማለት ዛሬ ጊዜ
ሕገ ወጥ በሆኑ ወይም በኅቡእ ገንዘብ የማግኛ ዘዴ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሙስና ወይም በተጭበረበሩ
ሰነዶች ከማምረቻ ወይም ከመንግሥት የማከፋፈያ ድርጅቶች ዕቃዎችን አውጥቶ መሸጥ ቢዝነስ ነው፡፡ እውቅናና ሕጋዊ
ፈቃድ ሳይኖር በአንድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ውስጥ ጉዳይ ማስፈጸም ቢዝነስ ነው፡፡ እጥረት ያለባቸው ምርቶች
በሙስና ይሁን በሌላ ወረፋ በማሳጠር ተጠቃሚው ያለአግባብ ቅድሚያ እንዲያገኝ ማድረግ ቢዝነስ ነው፡፡ በሙሉ በዝርዝር
ቢጻፍ በርካታ ገጾች የማይበቁት የቢዝነስ ዓይነቶች አሉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ እነኚህን ከዘረዘርን ለአንባቢው ግንዛቤ በቂ
ይመስለናል፡፡ እንግዲህ ሥራ ወይም ቢዝነስ ይህን መሰል አንደምታ ያለው ከሆነ ኅብረተሰባችን ውስጥ ስለሥራ ሊፈጠር
የሚችለውን ሥነምግባራዊ እይታ መገመት አያዳግትም፡፡ ይህንን መሰል አስተሳሰቦች ያለምንም መከልከል በሚስተናገዱበት
ማኅበረሰብ ውስጥ የሚያድጉ ሕጻናትና ልጆች ለሥራ የሚኖራቸው ሥነምግባራዊ ዋጋ በዚሁ መልክ እየተቀረጸ ሄዶ
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ይህን መሰሉ አሠራር የተለመደ ስህተት መሆኑ ቀርቶ እንደ ብቸኛና ተገቢ የአሠራር መንገድ
ይወሰዳል፡፡ በዚህ ረገድ አብያተ ክርስቲያናት የፋና ወጊነት ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቋንቋችን በእምነት
ሊቀረጽ ይገባል፡፡ ቢዝነስ ወይም ሥራ በማናቸውም መልኩ የዚህ መሰል ተግባራት የሚወከሉበት ቃል መሆን የለበትም፡፡
በአንድ ቋንቋ አንድ ቃል ወይም አባባል በማኅበረሰቡ ውስጥ ቦታ የሚያገኘው አባባሉን የሚናገረው ክፍል ስለተጠቀመበት
ብቻ ሳይሆን ሰሚው ክፍልም ተቀብሎት ያንን ሲያስተጋባ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በማስተማርም ሆነ
ቃሉ/አባባሉ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ትክክለኛ የሆነ አጠቃቀም እንዳልሆነ ምላሽ በመስጠት በመጀመሪያ ደረጃ ቃሉን
ማምከን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
አንዳንዶች እዚህ ላይ ተግባሩ ካለ የአባባሉ መቀየር ምን ትርጉም አለው? ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ቋንቋ የሰውን
አስታሳሰብ በመቅረጽ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ስላለው የቃሉ/የአባባሉ መቀየር በራሱ በተወሰነ መልኩ ሥነምግባራዊ ተጽእኖ
ማሳደሩ አይቀሬ ነው (Fairclough 2001)፡፡ ለምሳሌ፡- "ጉቦ ሰጥቼ ይህን ያክል ከረጢት ሲሚንቶ ላስፈቅድልህ፤ አንተ
ለኔ ይሄን ያክል ክፈለኝ፡፡" ከሚል ይልቅ "በቢዝነስ ይህን ያክል ከረጢት ሲሚንቶ እንድታገኝ አደርግሃለሁ፤ አንተ ደግሞ
ትንሽ አስብልኝ፡፡" የመጀመሪያው አባባል ግልጽ በሆነ ቋንቋ ስህተት የሆነ አካሄድ ተከትሎ ጉዳዩን እንደሚያስፈጽምለት
ስለተነገረው ተጠያቂው ግለሰብ ፈቃደኛ ለመሆን ወደኋላ ሊል የሚችልበት ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ በሁለተኛው አባባል ግን
ተሸፋፍኖ በመቅረቡና ተናጋሪው የተጠቀመው ቃል ምንም ዓይነት እኩይ ወይም አሉታዊ ሥነምግባርን የሚያመለክት
ባለመሆኑ ተጠያቂው ግለሰብ ፈቃደኛ ሆኖ ሊተባበር የሚችልበት ሁኔታ ከመጀመሪያው ይልቅ ከፍ ያለ ነው፡፡ በዚህ ረገድ
ደግሞ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ድርጅትም ሆነ እንደ ግለሰብ አማኞች ተባባሪ የሚሆኑበት ሁኔታ አልታየም ማለት
አይቻልም፡፡ ይሁንና የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት በማድረግ ለምእመናኖቻቸውም ሆነ ለመላው ኅብረተሰብ የሥራን
ሥነምግባር በስፋት በማስተማር፤ እንደዚህ ያለው ኢግብረገባዊ የሆነ የአነጋገር ዘይቤም ራሱ ተቀባይነቱ እንዳይስፋፋ
በቃልና በተግባር በማስተማር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ተግባሩ ላይ
ጥቂትም ቢሆን ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ሥራን ከመጽሐፍ ቅዱሰና ከቤተክርስቲያን (ማኅበራዊ) አስተምህሮ አንጻር እንመልከት፡፡
መጽሐፍ ቅዱሰ ስለሥራ በተለያየ ሁኔታ ያስረዳናል፡፡ ቤተክርስቲያንም ይህንኑ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት አድርጋ በሥራ
ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ፣ ግብረገባዊና የመሳሰሉት ትርጉሞችና ዋጋዎች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ድምጿን
ስታሰማ ቆይታለች ዛሬም እያሰማች ነው፣ ነገም ታሰማለች፡፡

8
ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስና በቤተክርስቲያን እይታ
የሰው ልጅ እግዚአብሔር ከከለከለው፥ ክፉና ደጉን ከምታስለየው የእውቀት ዛፍ ከበላ በኋላ "በወዝህ ትበላለህ"
የሚለውን ጥቅስ በመመርኰዝ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥራን ከሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅ በኋላ በርግማን እንደመጣ
ይወስዳሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በመጀመሪያ የሰውን ልጅ በመልኩና በአርአያው ፈጥሮ በፍጥረት ሁሉ ላይ በሾመው
ጊዜ እግዚአብሔር የፈጠረውን ውብ የአትክልት ቦታ (ገነት) እንዲከባከበው መመሪያ ሰጥቶት ነበር፡፡ ይህንኑ ትእዛዝ
ለመፈጸም የሰው ልጅ ሊሠራ ግድ ነው፡፡ ክብካቤ ራሱ ሥራ በመሆኑ ሥራ ከሰው ልጅ ውድቀት ቀዳሚ መሆኑን
ያስገነዝበናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ "ምድርንም ሙሉአት ግዙአትም" ብሎ ሥልጣንን ሲሰጠው ምድርን ለመግዛትና
በፍጥረትም ሁሉ ላይ ባለሥልጣን ለመሆን ወይም ለመሠልጠን ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ካልሠራ በፍጥረት ላይ
ሊሠለጥን፣ ምድርንም ሊገዛት አይቻለውም፡፡ አሁንም ይኸው ጥቅስ ሥራ ከሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅ ቀዳሚ እንደሆነ
የሚያሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ ከውድቀት በኋላ ሥራ በድካምና በመከራ የታጀበ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት
የመጀመሪያው ሰው ኃጢአት የእግዚአብሔርን እምነት በማጉደል ለሱ ሙሉ ለሙሉ ታዛዥ በመሆን ክቡር የሆነ ፍጡር
መሆኑን መቀበል ትቶ የፍጥረት ሁሉ ሙሉ ባለቤት ለመሆን መመኘቱ፣ እንዲሁም በሁሉ ላይ ፍጹም የሆነ የበላይነትንና
ሥልጣንን በመሻቱ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ በአምላኩ ሥራ ተሳታፊ እንዲሆን እንጂ ራሱን
ከፈጣሪው ጋር እንዲያስተካክል አልነበረም (Pontifical Council for Justice and Peace. 2005: 256/114)፡፡ ሥራ
ደግሞ የአምላክ አንዱ መገለጫው ስለሆነ በመልኩና በአርአያው የተፈጠረው የሰው ልጅም አምላኩን የሚመስልበት አንዱ
ባሕርይው ሥራ ነው፡፡ በመሆኑም ከመውደቅም በፊት ሆነ ከመውደቅ በኋላ ሥራ ይህንን ጠባዩን አልቀየረም፡፡
ሥራ ሁለት ገጽታ አለው፡፡ አንደኛው ገሐዳዊ (objective) የሚባለው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ባሕርያዊ
(subjective) ነው2፡፡ ገሐዳዊ የምንለው ተጨባጭ የሆነውን ይህንን ወይም ያንን ሥራ ነው፡፡ እሱም በሥልጣኔ ዕድገት፣
በግለሰቡ ችሎታ፥ ብቃትና ጉልበት፣ በምርት ሂደትና መጠን፣በሚከፈለው የሥራ ዋጋ ወይም ደሞዝ እና በመሳሰሉት
ይወሰናል፡፡ በዚህ መልኩ ሥራ ተለዋዋጭ ጠባይ አለው፡፡ እንደአካባቢው/እንደአገሩ ባሕል፣ የዕድገት ደረጃ፣ የፖለቲካና
የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ ተጨባጭ ሥነምግባራዊና (ethical) ግብረገባዊ (moral) እሴት፣ ማኅበራዊ ሁናቴ ይኸው ገሐዳዊ
የሥራ ገጽታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ አንድ ገበሬ በተወሰነ የቆዳ ስፋት ባለው መሬት ላይ ሊያመርት የሚችለው የእህል መጠን
ገበሬው በሚጠቀምበት የእርሻ መሣሪያ፣ በሚጠቀመው የእርሻ ዘዴ (በዝናብ/በመስኖ)፣ ማዳበሪያ፣ በአሠራር ዘይቤው፣
ወዘተ ይወሰናል፡፡ እንደዚሁም የአንድ አገር የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ለሕዝቡ የሥራ ባሕል መዳበርም ሆነ መኮሰስ
ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ሊያበረክቱ በሚችሉት አስተዋፅኦ ሳይሆን ለሹሙ፣ ለአለቃቸው፣
ለፖለቲካው ወዘተ ታማኝ ስለሆኑ ብቻ የኃላፊነት ቦታ የሚያገኙ ከሆነ ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የሚኖረው የሥራ
ተነሣሽነትና የሥራ ሥነምግባር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡
በአንጻሩ ሰው በቀዳሚነት ማሰብ የሚችል ፍጡር በመሆኑ ምክንያት በማናቸውም መልኩ ራሱንና አካባቢውን
ለመግዛትና ስብእናውን ለማጎልበት የሚያደርጋቸውን ተግባራት ባሕርያዊ ሥራ ብለን እንጠራዋለን፡፡ የመጀመሪያው ወይም
ገሐዳዊ የሥራ ገጽታ የሰውን ልጅ ጥገኝነት፣ ተሰባሪነት፣ ጎደሎነት (contingent) የሚያንጸባርቅ ሲሆን የሥራውም ዓይነት
እንደጊዜው፣ እንደባሕሉ፣ እንደፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና እንደቴክኖሎጂ የዕድገት ደረጃው ይዘቱና ቅርጹ ይለያያል፡፡ በሌላ
በኩል ባሕርያዊ የምንለው ግን በስብእናውና ሰው በመሆኑ የስብእናውም አንዱ መገለጫ በመሆኑ የሚያከናውናቸው
ማናቸውም ተግባራትን ያካተተውን ነው፡፡ በዚህ በሁለተኛው መልኩ ሥራ ከሰው ልጅ ስብእና ጋር የተሳሰረ በመሆኑ
ሠራተኛው ግለሰብ በሚያመርተው ምርት፣ በሚሠራው የሥራ ዓይነት፣ በቴክኖሎጂ ዕድገቱ፣ በኢኮኖሚያዊ ተጽእኖው፣
ወዘተ የሚወሰን ሳይሆን በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ክቡር ፍጡር በመሆኑ ብቻ የሚወሰን ነው፡፡ የጉልበትም ሆነ
የአእምሮ፣ ውስብስብ በሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚከወንም ሆነ በኋላ ቀር መሣሪያ ወይም በእጅ የሚሠራ፤ መልኩን
አይቀይረውም፡፡ ሥራ በመሆኑና የሰው ልጅ የስብእናው መገለጫ በመሆኑ ብቻ ባሕርያዊ ያሰኘዋል፡፡ ይሄኛው ገጽታ ነው
በአምላኩ መልክና አርአያ መፈጠሩን የሚያመለክተው፡፡ የሚሠራ አምላክ በመልኩ፣ እንደምሳሌው የፈጠረው ፍጡር
በመሥራት አርአያ አምላክነቱን ይገልጻል፡፡

2
ስለሥራ ገሐዳዊና ባሕርያዊ ገጽታዎች ር.ሊ.ጳ. ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ Laborem Exercens ስለ ሰው ልጅ ሥራ በሚል ርእስ በጻፉት
ሐዋርያዊ መልእክት ውስጥ በሰፊው አብራርተውታል፡፡ ይሄም መጣጥፍ በአብዛኛው መሠረት ያደረገው ይህንኑ ሐዋርያዊ መልእክት ነው፡፡
9
በዚሁ በባሕርያዊ መልኩ ምክንያት ነው ሥራ እንደ ሸቀጥ ወይም እንደ ማናቸውም የንግድ ዕቃ ሊታይ
የማይችለው፡፡ ሥራን በምርት ሂደት ውስጥ እንደ አንዱ የምርት ምንጭ አድርጎ መቁጠር የሥራን ክቡርነት ይቀንሰዋል፡፡
ክቡር በሆነ ፍጡር የሚከወን በመሆኑና የስብእናም መገለጫ በመሆኑ ብቻ ሥራ ክቡር ነው፡፡ የክብረቱም ብቸኛ መለኪያ
ራሱ የሰው ልጅ ነው (Laborem Exerense 6)፡፡ ስለሆነም የሥራውን ዓይነትና ጠባይ የሥራን ክቡርነት ከፍ ወይም ዝቅ
ሊያደርገው አይችልም፡፡ ዓይነቱን፣ ጠባዩን ወይም የሚያስገኘውን ደሞዝ በመመዘን ለሥራ የተለያየ የክብር ደረጃ መስጠት
መጽሐፍ ቅዱሳዊም ክርስቲያናዊም አይደለም፡፡ ሥራ ከሰው ልጅ የሚመነጭ ተግባር ሲሆን ሥራ መኖሩም/መሠራቱም ሆነ
የመጨረሻ ግቡ የሰው ልጅ ነው፡፡ ሥራ ለሰው ልጅ እንጂ ሰው ለሥራ አልተፈጠረም፡፡ (Pontifical Council for
Justice and Peace. 2005: 272)
ባሕርያዊ ሥራ ከገሐዳዊ ሥራ ቀዳሚ ነው፤ ምክንያቱም ሰው በመሆኑና የስብእናው መገለጫና መጎልበቻ ይኸው
ባሕርያዊ ሥራ በመሆኑ ሲሆን ገሐዳዊው ደግሞ ባሕርያዊ የሆነው ሥራ በተጨባጭ መልኩ የሚገለጥበት ወይም
የሚተረጐምበት ነው፡፡ በባሕርያዊው ምክንያት ነው ገሐዳዊው ሥራ ሊፈጠር የቻለው፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ከሌላኛው
ተለይቶ ሊኖር አይችልም፡፡ በሁለቱም መልኩ ሥራ የሰው ልጅ ክቡርነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን ክቡርነቱም የሚጨምርበት
ሂደት ነው፡፡ (Laborem Exercens: 39)
ሥራ ጥልቅ የሆነ ማኅበራዊ ገጽታ አለው፡፡ በማናቸውም መልኩ የአንድ ሰው ሥራ ከሌሎች ሰዎች ጋር የተሳሰረ
ነው (Centesimu Annus: 31)፡፡ በተለይም በአሁኑ ዘመን ዓለም እንደ ትንሽ መንደር የተወሰኑ ቁልፎችን በመንካት
ወይም በጠቅጠቅ የግንኙነት ፍጥነቶች በሚያስገርም መልኩ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው መድረስ በሚቻልበት ጊዜ፤
ሥራ አንድ ግለሰብ ለብቻው የሚሠራው ሳይሆን ከሌሎች ጋርና ለሌሎች መሥራት ነው ሊባል ይቻላል (Pontifical
Council for Justice and Peace 2005:273) ፡፡ የግለሰቦች፣ የድርጅቶችና የአገራት፥ አህጉር አቀፍ፣ በይነ-አህጉራዊ
(intercontinental) እና ሉላዊ የሥራና የንግድ ትስስር ሥር በሰደደበት በአሁኑ ዘመን ሥራ ከአንድ ግለሰብ ጋር ብቻ
የተቆራኘ ጉዳይ ሊሆን አይቻለውም፡፡ በርግጥ መቼም ሥራ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ ሆኖ አያውቅም ምክንያቱም ሰው
በተፈጥሮው ማኅበራዊ ፍጡር ነውና፡፡ የሰው ልጅ ስብእና በይነ-ሰብአዊና ማኅበራዊ በሆኑ መንገዶች ብቻ ነው ሊያድግ
የሚችለው ምክንያቱም ሰው የቅድስት ሥላሴ ባሕርይ አለውና፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የትስስርና የግንኙነት
ፍጹም ምሳሌ ናቸው፡፡ ሰው አምላኩን የሚመስለው ከብጤው ጋር በሚያደርገው መስተጋብራዊ ትስስር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ
አንዱ መንገድ ሥራ ነው፡፡ የሚያርስም ሆነ የሚነግድ፣ የምርምር ሥራ የሚሠራም ሆነ የቀን ሥራ የሚሠራ፣ የሚሥልም ሆነ
የሚጽፍ፣ ሁሉም የሥራ መስክ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖር መስተጋብር ነው የሚከወነው፡፡
ሥራ ለሰው ልጅ ግዴታውም ነው፡፡ ምክንያቱም 1. ፈጣሪ ያዘዘው ትእዛዝ በመሆኑ፤ 2. ስብእናውን ለመጠበቅና
ለማሳደግ ስለሚያስፈልገው (Laborem Exercens: 72, 73)፡፡ እርስ በርስ ካለን ትስስር አንጻር ሥራ ግብረገባዊ
ግዴታም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በቀዳሚነት የራስን ቤተሰብ ይመለከታል፤ ብሎም ባልንጀራን፣ የሚኖርበትን ማኅበረሰብና
አገርን፣ ቀጥሎም መላውን የሰው ልጅ ይመለከታል፡፡ ሰው ያለፉት በርከታ ትውልዶች ሥራ ወራሽ ብቻ ሳይሆን የዛሬው
ትውልድ ባለቤትና የነገው ትውልድ ቀራጺ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሚያዝዘው መሠረት ሥራ ለእንጀራና ራስን
ለማኖር ብቻ ሳይሆን ባልንጀራን ለመሸከም፣ ለመቀበል፣ ለመደገፍ ጭምር ነው፡፡ "ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ
አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታረዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፣ ታስሬ ወደ እኔ
መጥታችኋልና፡፡" (ማቴ 25፡35-36) ማንም "የወንድሜ ጠባቂ እኔ ነኝን?" (ዘፍ 4፡9) ለማለት አይችልም፤ ምክንያቱም
የወንድሙ ሥቃይ በአምላኩ ፊት ከመጮሁ በላይ "ምድርን ሙሉአት ግዙአትም" ተብሎ የተሰጠው ትእዛዝና ሥልጣን
የጋርዮሽ መልእክት ነውና ከመለኮታዊ ግብረገብ አንጻር አንዱ ሌላኛውን ለችግሩና ለመከራው ጥሎ የዚህ በረከት ነጻ
ተካፋይ ሊሆን አይችልም (Pontifical Council for Justice and Peace. 2005 274)፡፡
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የመፈጠሩ መለያ አንዱና ዋነኛ ማረጋገጫው ሥራ ነው፡፡ "በሥራው
የሰው ልጅ በምድር ላይ የበለጠ ባለሥልጣን እየሆነ ይሄዳል፡፡ እንዲሁም በገሐዱ ዓለም ላይ ሹም መሆኑን እያረጋገጠ
ይሄዳል፡፡ ይሁንና በዚህ ሁሉ ሂደትና ሁኔታ ውስጥ በቀዳሚነት እግዚአብሔር ባበጀው ሥርዓት ውስጥ መጽናት ዋነኛ
መሠረቱ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ያበጀው ሥርዓት ደግሞ በማናቸውም ሁኔታ በማይለወጥና በማይሻር መልኩ የሰው ልጅ

10
በእግዚአብሔር መልክ ከመፈጠሩ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡" (Laboreme Exercens: 15 የራሴ ነጻ ትርጉም) ይህም
የሚያሳየው የሰው ልጅ የምድርም ሆነ የማናቸውም ግዙፉ ዓለም ባለቤት ሳይሆን ባለአደራ እንደሆነ ነው፡፡
በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ በመፈጠሩ ምክንያት ብቻ የሰው ልጅ ክቡር ነው፡፡ ይሄን ክቡርነት በትምህርት
ልንመስለው እንችላለን፡፡ የአንድ አገር ትምህርት ከትውልድ ወደ ትውልድ እያደገና እየጎለበተ የሚሄድ ዘርፍ ነው፡፡ ከ50
እና60 ዓመት በፊት እንጠቀምባቸው የነበሩትን የትምህርት ዘዴዎችና መሣሪያዎች ዛሬ አሻሽለን ወይም እንዳለ ቀይረን ነው
የምንጠቀመው፡፡ እንዲሁም ያኔ እንደ አዳዲስና ትልቅ ግኝት እናስተምራቸው የነበሩት ዛሬ ተሽረው በምትካቸው ከነሱ
የላቁና የረቀቁ ግኝቶች በተማሪው መጻሕፍት ውስጥ ተካትተው እናገኛለን፡፡ የሰውም ልጅ ክቡርነት እንደዚሁ በየጊዜው
እያወቀውና እያሳደገው ወደ ፍጽምና የሚያደርሰው፣ በሂደት የሚገለጥ እንጂ እንደ ቆመ ምሰሶ የተተከለ ፅንሰ-ሐሳብ
አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን ክቡርነቱ ከእውቀቱና ከዕድገቱ ጋር የሚያድግ ነው ማለት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ እውቀቱን
በማሳደግና ለአምላኩ ታዛዥ በመሆን ክቡርነቱን በበለጠ እያወቀና እየጨበጠ ይሄዳል፡፡ ከዚህም የተነሣ ለሕይወቱ
የሚሰጠው ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለዚህም ነው ከጥንታውያንና ከኋላ ቀር ማኅበረሰቦች ይልቅ ዘመናዊና የሠለጠኑ
ኅብረተሰቦች ለሰው ልጅ ሕይወት የበለጠ ዋጋ የሚሰጡት፤ ሕይወቱንም ለመጠበቅ በርካታ ሕግጋት ቀርጸው በተቻለ አቅም
እንዲጠበቅ የሚያደርጉት፡፡ ሥራ ደግሞ የሰው ልጅ የክቡርነቱን አንዱን መልክ በየጊዜው የሚያውቅበት መሣሪያው ነው፡፡
የሰው ልጅ በሥራ ተፈጥሮን መለወጥና እንደአስፈላጊነቱ ለራሱ መገልገያ ቢያደርግም ዋነኛ የሥራ ፍሬ ግን ሰው የበለጠ
ሰው የሚሆንበት፣ የበለጠ አምላኩን የሚመስልበት ሂደት መሆኑ ነው፡፡ "አባቴ እስከዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ"
(ዮሐ 5፡17)
ወደ 3 እግዚአብሔር መልክ የተፈጠረው የሰው ልጅ ከአምላኩ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ
እንዲሠለጥንባቸው፣ በፍትሕና በቅድስና እንዲያስተዳድር ኃላፊነትን ተቀብሏል፡፡ ይሄም ኃላፊነት ራሱንም ሆነ
የሚያስተዳድራቸውን ፍጥረት የሁሉ ፈጣሪና ጌታ ከሆነው ከአምላኩ ጋር እንዲያስተሳስር ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ በሰው
ሥልጣን ሥር መሆኑ በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንዲከብር ነው (Gaudium et Spes)፡፡ ምክንያቱም ሰው
በፍጥረት ላይ በሠለጠነ፣ በፍትሕና በቅድስና ፍጥረትን ሁሉ ባስተዳደረ መጠን በእግዚአብሔር ሥራ በይበለጥ በመሳተፍ
ለስብእናው መለኮታዊ መልክ እየሰጠ ስለሚሄድ በኃጢአት ቆሽሾና ጎድፎ የነበረው ስብእናው እግዚአብሔር በመጀመሪያ
ሲፈጥረው የነበረውን አምላካዊ መልኩን እየመለሰ ወደ ምሉእነት እንዲቀርብ ስለሚያደርገው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሰው ልጅ
እግዚአብሔር አምላክ የጀመረውን የፍጥረት ሥራ ተረክቦ በመቀጠል ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀለት የፍጽምና
መድረሻ (divine destiny) እንዲደረስ የመለኮታዊ ሥራ ባለድርሻ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ፈጥሮ በምድር ላይ
ሲያኖረው በሥራው የሱ ሥራ ተሳታፊ እንዲሆን ነው፡፡ የእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ በስድስቱ ቀን የተጠናቀቀ ሳይሆን
ዛሬም ዓለምን ያጸናትና ያቆማት በዚሁ በፍጥረት ሥራው (creative act) ነው፡፡ ስለዚህም ማናቸውም የሰው ልጅ
የሚሠራው ሥራ የዕለት እንጀራን ከማስገኘት ባሻገር በዚህ በመለኮታዊ የፍጥረት ሥራ (creative act) ላይ ተሳታፊ
የመሆን ጉዳይ ነው (cf. Laborem Exercens: 114)፡፡ ይኸው የዕለት እንጀራን ለማግኘት የሚከወን ሥራ ለራስና
ለቤተሰብ የመኖሪያ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር ኅብረተሰቡንና መላውን የሰው ዘር በተወሰነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
እንደ ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ሥራ ለሰው ልጅ መሠረታዊ መብት ነው (Laborem Exercens 9,
18. Gaudium et Spes 26)፡፡ ለስብእናውም ክቡርነት ወሳኝነት ያለው መልካም መሣሪያ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የሥራን
ዋጋ ስታስተምር የሰው ልጅ የሥራ ባለቤት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ሥራ ራሱ በባሕርይው ለሰው ልጅ አስፈላጊ መሆኑን
ጭምር ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡ ሥራ በመጀመሪያ ደረጃ ቤተሰብን ለማኖርና ለማስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ ለሰው ልጅ
የንብረት ባለቤትነት (right to property) ሥራ መሠረቱ ነው፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ እ.ጎ.አ 1891 ከወጣው Rerum
novarum ከተሰኘው የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 13ኛ ሐዋርያዊ መልእክት ወዲህ የተለያዩ ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት በሐዋርያዊ
መልእክቶቻቸው፣ በነገረ መለኮታዊ ጽሑፎቻቸው፣ በሕዝባዊ ንግግሮቻቸው፣ በሠነዶቻቸው ወዘተ ውስጥ ይህንን ርእሰ

3
በእግዚአብሔር መልክ ከማለት ፋንታ ወደ እግዚአብሔር መልክ የሚለውን የተጠቀምኩት እግዚአብሔርን የመምሰሉ የሰው ባሕርይ በሂደት
የሚያድግ መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ `ወደ́́ ́ የሚለው መስተዋድድ የበለጠ ስለሚገልጸው ነው፡፡ በአንጻሩ `እንደ ́ ወይም `በ ́ የሚለው መስተዋድድ
ሁነትን የሚገልጽ እንጂ ሂደትን ስለማያመለክት ነው ̀ወደ́́ ́ የሚለውን ያልተለመደ ቃል የተጠቀምኩት፡፡

11
ጉዳይ ዳስሰዋወል፡፡ ይሁንና ለዚች መጣጥፍ በርእሰ ጉዳዩ ላይ በስፋት ማብራሪያ የሰጡትን ጥቂት ሐዋርያዊ መልእክቶችና
ሠነዶችን ብቻ ነው የመረጥነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለሰው ልጅ የጋራ-ጥቅም (common good) ሥራ መሠረቱ ነው (Laborem Exercens:
73)፡፡ በተለይ ደግሞ ቤተሰብን ከማኖርና ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ ሥራ መሠረታዊ የገቢ ምንጭና (means of
subsistence) ልጆችን ለማሳደግ ወሳኝ የሆነ የሰው ልጅ መብት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ የምታስተምረው
ቤተሰብን ለመመሥረት ሥራ ወሳኝነት እንዳለው ነው (Laborem Exercens: 42)፡፡ ምክንያቱም ለቤተሰብ መቆም
የሚተዳደርበት የገቢ ምንጭ መኖር አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ የሚቻለው በሥራ ነው፡፡ የቤተሰብ ሕይወትና ሥራ እርስበርስ
የተሳሰሩ ናቸው፡፡ አንዳቸው በሌላኛው ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ፡፡ ከሥራ የሚገኘው የገቢ መጠን አነስተኛ ወይም ከፍተኛ
መሆን፣ በቀን ውስጥ ረጅም ወይም አጭር ሰዓት መሥራት፣ ሁለትና ሦስት ሥራዎችን በተለያዩ ቦታዎች መሥራት፣ የሥራና
የመኖሪያ ቦታ ርቀት መጠን፣ ወዘተ በቤተሰብ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያደርጋሉ፡፡ ከነኚህ አንዳቸው ሚዛናዊ ባለሆነ
ሁኔታ በሠራተኛው ላይ ጫና የሚፈጥሩ ከሆነ በወላጅና በልጆቸ፣ በትዳር ግንኙነት ላይ ተጽእኖ በማሳደር ለቤተሰብ ኑሮ
መጽናት ወይም መናጋት፣ ለቤተሰብ ሰሳም ማጣት ብሎም መፍረስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን ለሁሉም
ሰው የተደላደለ ወይም በተለምዶ አነጋገር አልጋ ባልጋ የሆነ የሥራና የኑሮ ሁኔታ መፈጠር አለበት ወይም ይቻላል ለማለት
አይደለም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ኅብረተሰብ ጥረት ማድረግ ያለበት፥ ሥራ በመጀመሪያ ደረጃ ከግለሰብና (person not
the individual)4 ከቤተሰብ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በተቻለ መጠን የሥራና የሠራተኛ ፖሊሲዎች ይህንን ከግምት ያስገቡ
እንዲሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቤተክርሰቲያን ፖሊሲዎችንና አፈጻጸማቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከነገረ መለኮትና ከሥነምግባር
አንጻር ልትተችባቸውና ምእመናንንና መላውን ኅብረተሰብ ልታሳውቅ ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ደግሞ ከመንግሥት፣ ከፖሊሲ
አርቃቂ አካላትና ከአጽዳቂው አካል (የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት) ጋር የማያቋርጥ ንግግርና ውይይት ማድረግ
ይጠበቅባታል፡ በአንድ አገር ውስጥ ቤተክርስቲያን አገልግሎቷ ቃለ እግዚአብሔርን ማወጅ ብቻ ሳይሆን እንደነቢይ ሆና
ጥበብ በተሞላበት መንገድ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለሕዝብና ለመንግሥት፤ የሕዝብን ቅሬታና ቁስል ደግሞ ለመንግሥትና
ለባለሥልጣናት ማሰማት ጭምር ነው፡፡
የሥራ ባለቤት የሰው ልጅ ስለሆነ አቅሙ ለሥራ ለደረሰና መሥራት ለሚችል ሰው ሁሉ እንደብቃቱ መጠን ሥራ
ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ በርግጥ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ በተሟላ ሁኔታ አይገኝም (Pontifical Council for
Justice and Peace. 2005: 288)፡፡ በርግጥ እንደ አገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዕድገት ሁኔታ የሚወሰን ጉዳይ ነው፡፡
ነገር ግን በመርህ ደረጃ አንድ አገር (መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰብ) ጥረት ማድረግ ያለባቸው አቅማቸው ለሥራ የደረሱ
ግለሰቦች ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሥራ መስክ እንዲሰማሩ ማመቻቸት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ካለው የትምህርት ዘርፍ
ስርጭት፣ ዕድገትና አቅርቦት ጋር በተዛማጅ የሚሄድ ነው፡፡

ሥራና መብት፣ ግብረገብ


ፍትሐዊ ደሞዝ የሥራ ተገቢ ፍሬ ነው (Pontifical Council for Justice and Peace 2005:302)፡፡
ሠራተኛ ደግሞ ፍትሐዊ /fair/just ደሞዝ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ፍትሐዊ ደሞዝ ማለት ሠራተኛው በሥሩም የሚተዳደሩትን

4
እዚህ ላይ በአማርኛ person ለሚለውና individual ለሚለው ቃል የተለያየ ስያሜ ስለሌለን ልዩነታቸውን በአጭሩ ማብራራቱ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
person የሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ግለሰብን የሚያመለክት ሲሆን ምንነቱ ራሱ በትስስርና በግንኙነት የሚገለጽና የሚወሰን ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ person
የሚለውን ቃል ግለሰብ ብለን እንተረጉማለን፡፡ ግለሰብ ደግሞ ያለግንኙነትና ትስስር እርሰበርሱ የሚጣረስ ጽንሰ-ሐሳብ ነው፡፡ individual የሚለው
ቃል በተለያየ አገባብ የተለያየ ትርጓሜ ሊሰጠው ቢችልም ከግለሰብ ጋር በተያያዘ መልኩ ሲሆን ግለሰቡ እንደ አንድ ነጠላ ሰው፣ ከማንም ጋር
ባልተገናኘና ባልተሳሰረ መልኩ የሚያመለክት ስያሜ ነው፡፡ ይህ ቃል በየትኛውም ሁኔታ ሰውን በምሉእነቱ ሊያመለክት አይችልም ምክንያቱም ሰው
በባሕርይው የግንኙነት/የትስስር (relational) ፍጡር ነው፡፡ የፈጠረው አምላክ፣ ቅድስት ሥላሴ፣ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱሰ የግንኙነትና የትስስር
ፍጹም ምሳሌና መገለጫ በመሆኑ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረው የሰው ልጅም የግንኙነትና የትስስር ባሕርይ ወይም ተፈጥሮ አለው፡፡ (ይህንን ርእሰ-ጉዳይ
በበለጠና በጥልቀት ለመረዳት C. LaCugna 1991 ይመልከቱ)፡፡

12
ሁሉ አካላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊና መንፈሳዊ ሕይወቱን መልካም በሆነ መንገድ ለማነጽ የሚያስችለው ሊሆን ይገባል፡፡
ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ አስተምህሮዋ የደሞዝን አወሳሰን በተመለከተ ተገቢ/ፍትሐዊ ደሞዝ በቀጣሪና በተቀጣሪ መካከል
ብቻ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም ብላ ነው የምታስተምረው፡፡ የአንደ ሠራተኛ ምንዳ አንድን ሰው/ቤተሰብ ለማኖር በቂ
ከመሆን ሊያንስ (level of subsistence) አይገባም፡፡ ይህንን አሚነ መሠረት ያገናዘበ ፖሊሲ በአገር ደረጃ ሊቀረጽ
ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ቤተክርስቲያን የደሞዝ ደረጃ በአሠሪና በሠራተኛ ብቻ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም የምተለው፡፡
በእያንዳንዱ አሠሪና ሠራተኛ ውል ላይ ጣልቃ የመግባት ጉዳይ ሳይሆን ስብእናን በማያኮሰምን መልኩ መሠረታዊ
መርሕዎች በፖሊሲ ደረጃ ከተቀረጹ፣ የዝቅተኛ ደሞዝ ወሰን ከተደነገገ በአሠሪና በሠራተኛ መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች
በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ስለሚሆኑ ኢሰብአዊ የሆኑ የጉልበት ብዝበዛዎችን ለመከላከል በከፍተኛ ደረጃ ይረዳል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለን፣ "ቀጥረህ የምታሠራው ሰው ደሞዝ ለአንድ ሌሊት እንኳ በአንተ ዘንድ አይደር"
(ዘሌ. 19፡13) እንዲሁም "እስራኤላዊውም ሆነ ከአገርህ ከተማዎች በአንዱ የሚኖር የውጪ አገር ተወላጅ ድኻና ችግረኛ ሆኖ
የተቀጠረውን ማናቸውንም ሰው አትበዝብዘው፡፡ እርሱ ድኻ በመሆኑ ያን ገንዘብ ለማግኘት በብርቱ ጒጒት ስለሚጠብቅ
በየቀኑ (በወቅቱ) የሠራበትን ገንዘብ ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት ስጠው፤ ባትከፍለው ግን ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ
ያሳጣሃል፤ አንተም በደለኛ ሆነህ ትገኛለህ" (ዘዳ 24፡14-15)፡፡ በአዲስ ኪዳንም ይህንኑ መሰል ቃል እናገኛለን፡፡ ያዕቆብ
በጻፈው መልእክት ላይ እንዲህ ይላል፣ "ይሁን እንጂ በእርሻችሁ ሲያጭዱ ለዋሉት ሠራተኞች ዋጋቸውን ስላልከፈላችሁ
እነሆ፥ የተቃውሞ ጩኸታቸው ይሰማል…" (ያዕ 5፡4)፡፡ ለሠራተኛ ደሞዙ የምድርን ሀብታትን ለመጠቀም ያስችለዋል፡፡
የአንድ አገር ምጣኔ ሀብታዊ (economic) ጤናማ ደረጃ የሚለካው በምታመርተው የምርት መጠን (GDP) ብቻ
ሳይሆን በምን ዓይነት ሁኔታ እንደምታመርተውና ባላትም ፍትሐዊ የሀበት ስርጭት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ የሀብት ስርጭት
እያንዳንዱ ግለሰብ ለስብእናው ዕደገትና የፍጽምና ጉዞ የሚያስፈልገውን ሁሉ እንዲያገኝ የሚያስችለው ሊሆን ይገባል፡፡
የእያንዳንዱ ዜጋ ብቃት ብቻ ሳይሆን ፍላጎት (need) ከግምት ያስገባ የሀብት ስርጭት ማኅበራዊ ፖሊሲ ሲኖር ጤናማ
ምጣኔ ሀብታዊ ደረጃ አላት ሊባል ይችላል (Pontifical Council for Justice and Peace 2005:302)፡፡
ሴቶች በሥራ የመሳተፍ መብታቸው በማናቸውም መልኩ ከወንዶች እኩል ሊሆን ይገባል፡፡ የድርጅቶች መዋቅር
ደግሞ የሴቶችን ሁኔታ ከግምት ያስገባ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይ ከእርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ የጤና ክትትል አስፈላጊ
በመሆኑ ይህንን ያገናዘቡ ፖሊሲዎች መቅረጽ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነታቸው ከአስተዳደር አንሥቶ መላውን ሠራተኛ
በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማሠልጠንና የግንዘቤ ማስጨበጫ ዐውደጥናቶችን በሥራ ገበታ ላይ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ቅድመ- እና ድኅረ-ወሊድ በሴቶች ላይ መጠነኛ የሥነልቦና ለውጥ ስለሚኖር በሥራ አካባቢ ይህንንም የሚያሰተናግድ
ማኅበማዊ ድጋፍ ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ ተባእታዊ (patrarchial) ባሕል ሥር በሰደደበት በኛ ማኅበረሰብ ውስጥ የሴቶችን
በተለይም በከፍተኛ የሙያ (ፕሮፌሽናል) ቦታዎችና የአመራር ቦታ ላይ እንዳይደርሱ የሚደረጉ ግልጽና ስውር አሠራሮችን
ከሥር መሠረታቸው ልንነቅላቸው ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ሲባል ግን ሴቶች ወንዶችን ይምሰሉ ወይም እንደ ወንድ ይሁኑ ማለት
አይደለም፡፡ ነገር ግን ስብእናቸውን የሚያሳድጉበትን፣ ሙያዊ ብቃታቸውንና ለማኅበረሰቡ ሊያበረክቱ የሚችሉትን መንገድ
በሴትነታቸው ብቻ የሚከለክሉ ወይም እንቅፋት የሚሆኑ መዋቅሮችና አስተሳሰቦች ማኅበራዊ ኃጢአት/መዋቅራዊ ሕጸጽ
(social sin/structure of sin) ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ማኅበራዊ የሚያሰኘው ኃጢአቱ በባልንጀራ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ በርግጥ
ማናቸውም ኃጢአት ሌላው ቀርቶ ማንም ሌላ ሰው የማያውቀው የግለሰቡ የውስጥ ምሥጢር የሆነ ኃጢአትም ቢሆን
ማኅበራዊ ገጽታ ስላለው ከማኅበራዊ ኃጢአትነት ነጻ አይደለም፡፡ ልዩነቱ ግን ይሄኛው በቀጥታ ባልነጀራን (ሴቶችን)
የሚመለከት በመሆኑ ማኅበራዊ ባሕርይው ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚተባበር ሁሉ
ደግሞ ይሄው መዋቅራዊ ሕጸጽ እንዲቀጥል አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ይሄ ደግሞ የሰዎች በኃጢአት የመተሳሰርና የመተባበር
ግንኙነት (communion of sin) ይባላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ኃጢአት የሚያስፈልገው የግለሰቦች መለወጥና
(personal conversion) የማኅበረሰብአዊ መለወጥ (social conversion and structure of conversion) ነው፡፡
(በማኅበራዊ ኃጢአትና መዋቅራዊ ሕጸጽ ጉዳዮች ላይ የዳግማዊ ዮሐንሰ ጳውሎስን ድኅረ-ሲኖዶሳዊ ሐዋርያዊ ማነቀቂያ
መልእክት 1984: Reconciliation and Penance እና 1987፡ Sollicitudo rei Socialis ይመልከቱ)
ቋንቋችን ሳይቀር በሴቶች ላይ አሉታዊ አባባሎችን በመያዙ አስተሳሰባችን በዚያ እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ
ወሳኝ፣ ቆራጥና ቆፍጣና የሆነችን ሴት “ወንድ ናት” ማለት የተለመደ ነው፡፡ የወንጌል ሰባክያን ሳይቀሩ ይህንን መሰል ቃላት
በመጠቀም ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲኖረው የሚያደርጉበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይሄ ደግሞ ከላይ
እንደተመለከትነው ማኅበራዊ ኃጢአት ወይም መዋቅራዊ ሕጸጽ ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ ማኅበራዊ ኃጢአት ለመውጣት
13
እያንዳንዱ ግለሰብ ውስጣዊ እሱነቱን በእግዚአብሔር ቃል መለወጥ ቋንቋውን ሳይቀር በእግዚአብሔር ቃል ማረቅ
ይኖርበታል፡፡ ይሄ መለወጥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ይመለከታል፣ ከተፈጸመው ኃጢአት ጋር ያለንን ግንኙነት
እና መዘዙን ያካትታል፤ ስለሆነም ከባልንጀራችን ጋር ያለንን ግንኑነትም ይመለከታል፡፡፡ ባልንጀራ በዚህ አንጻር ግለሰብ
ሊሆን ይችላል ወይም ማኅበረሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ (Sollicitudo rei socialis 38) ከላይ ያነሣነው ከሴቶች ጾታዊ በደል
አንጻር ስለሆነ ይሄ ለውጥ ከሴት እኅቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ያካተተ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
ከሥራ ጋር በተያያዘ ሌላው ሳይነሣ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የሕጻናት/የልጆች ጉልበት ብዝበዛ ነው፡፡
እንደኢትዮጵያ ባሉ ደኻ አገራት የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ቤተሰብን ከመደጎም ጋር በመያያዙ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ኢ-
ግብረገባዊ ተግባርና ማኅበራዊ ችግር አይቆጠርም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ስለ ሕጻናት/ልጆች ሥራ ሌላኛውን ጽንፍ የያዘ
አቋም ያላቸው ግለሰቦች/ወላጆችም እንዳሉ አልፎ አልፎ ማየታችን አልቀረም፡፡ የዚህ አስተሳሰብ አራማጅ የሆኑ ወላጆች
ልጆች በቤት ውስጥም ምንም ዓይነት ሥራ እንዲሠሩ ስለማይፈልጉ የልጆቻቸው ሰብአዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ
ያሳድራሉ፡፡ እንደዚሁም ልጆቻቸው ስለሥራ የሚኖራቸውን አስተሳሰብ ራሳቸውንም ሆነ ማኅበረሰቡን በማይጠቅም ብቻ
ሳይሆን በሚጎዳ መልኩ እንዲቀረጽ ያደርጋሉ፡፡ በርግጥ ዋነኛ ርእሰ ጉዳያችን ይህንን መዳሰስ ስላለሆነ ሐሳቡን ጠቆም
ካደረግን በቂ ይሆናል፡፡ ሕጻናት/ልጆች በትመህርት ቤት እንጂ በፋብሪካና በእርሻ ቦታ ሊውሉ አይገባም፡፡የሕጻናትን ጉልበት
ብዝበዛን ድኽነት በማናቸውም መልኩ እንደ ትክክለኛም ሆነ እንደአስፈላጊ እኩይ (necessary evil) እንዲታይ ሊያደርገው
አይገባም፤ አይችልም፡፡
ሌላውና በአገራችን በአብያተ ክርስቲያናትም ጭምር ትኩረት የተነሣው ጉዳይ የአካል ጉዳተኞችና የአእምሮ
ዝግመት ተጠቂዎች ሁኔታ ነው፡፡ የሥራ ዕድል በመክፈት ቀርቶ የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን ለመግፋት በሚያደርጉት
እንቅስቃሴ የተመቻቸ ነገር ከቶውኑ አያገኙም፡፡ የአብያተ ክርስቲያናት የሥርአተ አምልኮ ቦታ፣ የሥራ ቦታ፣ የገበያ
ማዕከላት፣ ቀበሌዎች፣ ፍርድቤቶች፣ ሐኪም ቤቶች፣ ወዘተ ለአካል ጉዳተቸኞችና ለአእምሮ ዝግመት ተጠቂዎች የሚመች
አሠራር የላቸውም፡፡ አሠሪዎች የሥራ ማስታወቂያ አውጥተው ለቃለመጠይቅ አመልካቾች በሚመጡበት ጊዜ
ከተወዳዳሪዎቹ አንዳቸው የአካል ጉዳተኛ ከሆነች ብቃት እንኳ ቢኖራት ከሌሎች ይልቅ የመውደቅ ዕድሏ ሰፊ ነው፡፡
ያለምንም ድጋፍ መሥራት የሚችሉ ምንም ዓይነት የአካልና ብአእምሮ ጉዳት ለሌለባቸው ሰዎች ብቻ የሥራ ዕድል መስጠት
የኅብረተሰቡ አካል የሆኑትንና የስብእናችን ተጋሪ የሆኑትን የአካል ጉዳተኞችና የአእምሮ ዝግመት ተጠቂዎችን መኖር መካድ
ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞችና የአእምሮ ዝግመት ተጠቂዎችም እንደማንኛውም ዜጋ በሥራ መስክ የመሳተፍ መብት አላቸው፡፡
በተቻለ መጠን ተገቢ ሥልጠና አግኝተው መሥራት እንዲችሉ ለአካል ጉዳተኞችና ለአእምሮ ዘገምተኞች ሁኔታዎች
ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ አብያተ እምነቶች በተናጠልና በጋራ ሕዝቡን በመድረስ በኩል ብዙ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡
ከሥራ ከቶውኑ ሊነጣጠል የማይችለውና ስለሥራ በሚታሰብበት ጊዜ እምብዛም ትኩረት የማይሰጠው ጉዳይ
ዕረፍት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በስድስት ቀን የፍጥረት ሥራውን ፈጽሞ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ (ዘፍ 2፡2)፡፡
በመልኩና በአምሳሉ የተፈጠረው የሰው ልጅም ከሥራው ሊያርፍ ያስፈልገዋል (Laborem Exercens: 114, 115)፡፡
ሥራ መብት እንደሆነው ሁሉ ዕረፍትም የሰው ልጅ መብት ነው፡፡ ከቤተሰቡ ጋር ጊዜ እንዲኖረው፣ በማኅበራዊ፣ ባሕላዊና
ሃይማኖታዊ ዘርፎች ውስጥ መሳተፍ ይችል ዘንድ የሚሠራ ሰው ሁሉ የዕረፍት ጊዜያት ያስፈልጉታል (Gaudium et
Spes: 67)፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የሰንበት ሕገ ድንጋጌ ለዚህ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በእሑድ፣ እንደ ፋሲካና የጌታ ልደት
ዓይነት ትላልቅ በዓላት ዕለት ክርስቲያኖች መሠረታዊው የሆነውን ለእግዚአብሔር የሚገባ ሥርዓተ አምልኮና ክብር
እንዳይፈጽሙ እንቅፋት ከሚሆን ሥራ መታቀብ ይኖርባቸዋል (የካቶሊክ ቤ/ክ ትምህርተ ክርስቶስ 2185)፡፡ እንዲሁም
ምርትን ከፍ ለማድረግና የአገርን ዕደገትና ግንባታ ለማፋጠን በሚል ሰበብ ግለሰቦችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማስገደድ
ለእግዚአብሔር የሚገባውን ሥርዓተ አምልኮ እንዳይፈጽሙ ከላይ በተጠቀሱት ወሳኝ የዕረፍትና ለፈጣሪ የተሰጡ ቀናት
እንዲሠሩ ማድረግ በአንድ በኩል ሥነምግባራዊ አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሕገመንግሥት ያጸደቀውን
የሃይማኖት ነጻነት የሚጻረር ነው፡፡ ይልቁንም በእንደዚህ ዓይነት የተቀደሱ ቀናት የፍቅር ሥራን መሥራትና ለነፍስና ለሥጋ
አስፈላጊውን ዕረፍት መስጠት ይገባል፡፡ የፍቅር ሥራ የምንላቸው የታመሙትንና የታሰሩትን መጠየቅና በእግዚአብሔር
ቃልና ፍቅር ማጽናናት፣ አቅመ ደካሞችን መጎብኘት፣ ለደሞዝ ሳይሆን ለጸጋ በረከት የሚሆኑ ይህንን መሰል ሥራዎችን
መሥራት ናቸው፡፡

14
መደምደሚያ
ሥራን በተመለከተ በአገራችን ከአነጋገር፣ ከመንፈሳዊነትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ያለውን ባሕልና ልምድ በአጭር
ባጭሩ ቃኝተናል፡፡ እንዲሁም ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስና በቤተ ክርስቲያን (ማኅበራዊ) አስተምህሮ እይታ ምን ማለት
እንደሆነ ጥቂት ነጥቦችን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ምን ልንማር እንደሚገባ በዚህች ክፍል በጣም በአጭሩ
እንመለከታለን፡፡
ሥራ የሰው ልጅ ስብእናው የሚያድገበትና በበለጠ አምላኩን የሚመስልበት ተግባር ስለሆነ ክቡር ነው፡፡ ስለሆነም
በማናቸውም የሥራ መስክ የተሰማራ ግለሰብ ሥራውን እንደ የገቢ ምንጭ መሣሪያነት ብቻ ሊያየው አይገባም፡፡ የሕይወት
ትርጉም ጣእም የሚታወቀው አንዱ በሥራ ስለሆነ በደስታና በፍቅር ሰው ሁሉ ሥራውን ሊሠራ ይገባል፡፡ በሥራ ደስታና
ፍቅር ከሌለ በኑሮ ደስተኛ መሆን አይቻልም፡፡ የሥራህን ተገልጋይ (ደንበኛ/ባለጉዳይ) ሥነምግባር በተሞላና ተገቢ በሆን
መንገድ ልታስተናግድ የምትችለው ለሥራህ ፍቅር ሲኖርህና በሥራህ ደስተኛ መሆን ስትችል ብቻ ነው፡፡ አሁን አንተ
ያለህበት የሥራ ቦታ ላይ ሌላ ሰው ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህቺን ቦታ ለአንተ አዘጋጅቶ በመስጠቱ፣
የአእምሮና የጉልበት ብቃት ሰጥቶህ በዚህ ሥራ ላይ እንድትሰማራ ስላደረገህ በማመስገን ልትሠራ ይገባል፡፡ ይህ ዓይነቱ
አመለካከት ደግሞ ለፍሬአማነት፣ ለኑሮ ጣእም፣ ለተሻለ ዕድገት ከፍተኛ የሆነ የመንፈስና የሥነልቦና አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
በተለይም ብዙዎች በጤና ችግር፣ በኑሮ ጉስቁልና፣ በተለያዩ ሌሎች ምክንያቶች አእምሮአዊ፣ አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ ወይም
ሌላ ብቃት አጥተው መሥራት እየፈለጉ መሥራት የማይችሉ እንዳሉ በማሰብ መሥራት መቻል በራሱ ልዩ ጸጋ እንደሆነ
እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡
ሥራን ለራስ ብቻ እንደተሰጠ ነገር አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ ሥራ ስብእናን ለማሳደግ፣ ቤተሰብን ለማቆም፣
ማኅበረሰቡን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለመጥቀም ለሰው ልጅ የተሰጠው መሣሪያ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ
ሥራን እንደማኅበራዊ ዘርፍ በማሰብ ሰፋ ያለ ሥነምግባራዊ ዋጋ ልንሰጠው ይገባል፡፡ እንደማኅበራዊ ዘርፍነቱ ሥራ
ሌሎችን/ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ለእኔ የተሰጠኝ ኃላፊነት ነው ብሎ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የራሴ እንደመሆኑ
መጠን ደግሞ የገቢ ምንጭ የማገኝበትና ቤተሰቤን የማስተዳድርበት መሣሪያዬ ነው፡፡ እነኚህ ሁለቱ በመደጋገፍ የሚሄዱ
ከሆነ አገልግሎት መስጠት ላይ ደንበኛ/ባለጉዳይ የሚጉላላበት ሁኔታ እንዳይኖር ጥረት እንዳደርግ ስለሥራ ያለኝ
አመለካከት ይወስነዋል፡፡ ምክንያቱም እይታዬ ሥራ ማኅበረሰቡን እንዳገለግልበት የተሰጠኝ ኃላፊነት እንጂ ራሴን ብቻ
የምጠቅምበት መሣሪያ ስላልሆነ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የእኛ ሥራ ለራሳችን የገቢ ምንጭ ከመሆን ባሻገር በተለያየ ምክንያት ለመሥራት ያልታደሉ
ባልንጀሮቻችንን ለመደገፍም ጭምር ከእግዚአብሔር የተሰጠን የኃላፊነት ቦታ ነው፡፡ የኛ ሥራ የተቸገሩትን ለማንሣት
አገልግሎት የማይውል ከሆነ የአቤል የደሙ ድምፅ በእግዚአበሔር ፊት እንደጮኸ ሁሉ ከግራና ከቀኛችን ያሉ የተቸገሩ
ነፍሳት የእንባቸው ድምፅ በእግዚአብሔር ፊት ይጮኻል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለአገልገሎት በሚዘዋወርበት ጊዜ በሚያገለግላቸው ሰዎች ጥገኛ ላለመሆንና ሸክምም
እንዳይሆንባቸው ያለመቋረጥ ይተጋ እንደነበር ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ እናገኛለን፡፡ "ወንድሞች [እኅቶች]
ሆይ! እንዴት እንደ ሠራንና እንደ ደከምን ታውቃላችሁ፡፡ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ በምናበሥርበት ጊዜ
በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን በመሥራት እንደክም ነበር፡፡" (1 ተሰ 2፡9) ጳውሎስና አብረውት የነበሩት
አገልጋዮች ከሚያገለግሏቸው ሰዎች ከመጠበቅ ይልቅ ሥራ በመሥራት ለዕለት ጉርሳቸው ይተጉ ነበር፡፡ እንግዲህ
እንደሐዋርያና እንደመጋቢ የማግኘት ባለመብት ሆነው ሳሉ አርአያ ለመሆንና ለጥገኝነት ልማድ ላለመሰጠት ነበር
እነጳውሎስ የሚሠሩት፡፡ ታድያ ዛሬ የሚለምኑ ጤናማ እጆች ወደ ሥራ እንዲገቡ የጳውሎስን ፈለግ በመከተል
ቤተክርስቲያን ምእመኖቿንና መላውን ኅብረተሰብ ያለማቋረጥ ልታስተምር ይገባል፡፡
እንግዲህ የሰው ልጅ በምድርና በግዙፉ ዓለም ላይ የሚሠለጥንበት፣ ወደ አምላኩ የሚቀርብበት፣ አምላኩንም
በበለጠ የሚመስልበት ስጦታ፣ እርስ በርሱም በተለያየ መልክ የሚተሳሰርበት ሠንሠለት፣ ከጥገኝነት ነጻ የሚወጣበት
የባሕርይው መገለጫ ሥራ ነው ብለናል፡፡ እንደ አገራችንም ብሂሎች ሥራ ለሠሪው ተገኑ እንደሆነና ካልሠራም የመኖሩ
ትርጉም ስለሚጠፋ ጌታችን ራሱ እንደሚለው፡- "አባቴ እስከዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ" (ዮሐ 5፡17) እኛ ደግሞ
እንሠራለን የሚለውን ቃል እንደ ሕይወት ቃልና መመሪያ ወስደነው ልንመራበት ይገባል፡፡

15
ሥራ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተቀበለው የባሕርይው መገለጫ በመሆኑ፤ ከሥራ የራቀች ነፍስ ስብእናዋን
ታጎድላለች፡፡ በሥራ ፈትነት ምክንያት የሰው ልጅ የማይፈልጋቸውንና በእግዚአብሔርና በሰው ፊት የማይወደዱ ጠባያትን
ይለብሳል፣ እኩይ ተግባራትንም ይፈጽማል፡፡ ከዚህና ከዚህ መሰሉ ሁኔታ በመነሣት ነው ከላይ እንደተመለከትነው አበው
ሲተርቱ፣ "ሥራ ያጣች አፍ ሞትን ትጠራለች" ያሉት፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን እናቶቻችን ይህን መሰሉን ቁምነገር በምሳሌና
በብሂል ስላስተላለፉልን የዛሬው ትውልድ ደግሞ እነዚህን ትልቅ የቁምነገር ፍሬ ያረገዙ አባባሎች በማሰላሰልና
ትርጒማቸውን ከጊዜው ጋር እንዲዛመድ በማድረግ ተወልደው ሕይወት እንዲዘሩ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የአሁኑ
ትውልድ እነኚህ መልእክት አዘል ብሂሎችን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በማዋሐድ የሕይወት መመሪያ ቢያደርጋቸው በአንድ
በኩል ከታሪክና ከባሕል ጋር ያለውን ግብረገባዊ፣ ታሪካዊና አገራዊ ትስስር ያጸናበታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እነኚሁ
አባባሎች እንደ ቅርስ ሳይሆን ዛሬም ትርጉማቸውን በእግዚአብሔር ቃልና በጊዜው ዐውድ በመቅረጽ ትውልዱ ተጠቃሚ
እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ እንዲህ በሎ ነበር፡- "ደግሞ ከእናንተ
ጋር ሳለን ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና፡፡ ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ
ዘንድ ስለሚሄዱ ስለአንዳንዶች ሰምተናልና፡፡ እንደዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን
በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን፣ እንመክራቸውማለን፡፡ እናንተ ግን፥ ወንደሞች [እኅቶች] ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት
አትታክቱ፡፡" (2 ተሰ. 3፡10-12)
እንግዲህ እንደ ክርስቲያንነታችን ምሳሌ በመሆን በተሰለፍንበት ሁሉ የሥራ መስክ በትጋትና ሥነምግባር
በተሞላበት መንገድ በመሥራት ለሌሎች አርአያ መሆን ከእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚጠበቅበት ፍኖተ ሕይወት ነው፡፡
ቤተክርስቲያንም በተለይ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት በማድረግ እንዲሁም መልካሙን የአበው ምሳሌ በማጣቀስ ሕዝበ
ክርስቲያኑን በሥራ ሥነምግባር ያለማቋረጥ ልታንጽ ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያንም አገርም የሚያድጉት ታታሪና በሥነምግባር
የታነጹ ዜጎችን ማፍራት ሲችሉ ነው፡፡ ስለሆነም የሁላችን መሪ ቃል፡- "አባቴ እስከዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ"
ስለዚህ እኛም እንሠራለን የሚለው መሆን ይኖርበታል፡፡

__________________________
ዋቢ ጽሑፎች:
Catechism of the Catholic Church (1994). Ottawa: Publication Service of CCCB.
Fairclough, N. (1992). Discourse and Social Change. Cambridge: Polity Press
Fairclough, N. (2001) Language and Power. Edinburgh: Pearson Education.
Hollenbach, D. (2002). The Common Good and Christian Ethics. Cambridge: Cambridge University Press.
John Paul II (1981). Encyclical Letter Laborem Exercens www.vatican.va
John Paul II (1987). Encyclical Letter Sollicitudo rei Socialis www.vatican.va
John Paul II (1991). Encyclical Letter Centesimu Annus www.vatican.va
LaCugna, C (1991). God for Us: The Trinity and the Christian Life. San Francisco: Harper
Leo XII (1891). Encyclical Letter Rerum Novarum www.vatican.va
Messay Kebede (1999) Survival and Modernization, Ethiopia’s Enigmatic Present: A Philosophical Discourse,
Asmara: Red Sea Press.
Pius XI (1931). Encylical Letter Quadragesimo Anno. www.vatican.va
Pontifical Council for Justice and Peace (2004). Compendium of the Social Doctrine of the Church. Washington,
DC: USCCB.
Second Vatican Ecumenical Council (1966). Pastoral Constitution of the Church Gaudium et Sepes www.vatican.va

16

You might also like