You are on page 1of 24

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

ለመሪነት የሚደረግ ውድድር የምርጫ መሪ ሰነድ


የአንዱዓለም አራጌ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ማውጫ
መግቢያ.......................................................................................................................1
1. የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ..........................................................................1
1.1. ዳራ..............................................................................................................1
1.2. አሁን የምንገኝበት ሁኔታ..........................................................................2
1.2.1. ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ጦስ...................................................2
1.2.2. መሰረታዊ የዜጎች እና የሀገር ደኅንነትን ማስጠበቅ አለመቻል..............2
1.2.3. የሰሜኑ የሀገራች ክፍል ጦርነት................................................................3
1.2.4. ምጣኔ ሀብትን በተመለከተ.......................................................................3
1.2.5. ሀገራዊ ምክክር...........................................................................................4
1.3. ማጠቃለያ...................................................................................................4
2. የፓርቲያችን ወቅታዊ ሁኔታ.....................................................................5
2.1 ዳራ..............................................................................................................5
2.2 አሁን የምንገኝበት ሁኔታ...........................................................................6
2.2.1 ሀገራዊ ዕይታን በተመለከተ.......................................................................6
2.2.2 ድርጅታዊ ጥንካሬ......................................................................................9
2.3 ማጠቃለያ....................................................................................................9
3. እንደ ሀገር ከገባንበት ችግር ለመውጣት ምን መደረግ አለበት?............10
4. ኢዜማ የሚጠበቅበትን ሚና ለመጫወት ሊተገብራቸው የሚገቡ
ለውጦች ምንድናቸው?.............................................................................11
4.1 በሕዝብ ዘንድ ያለን ቅቡልነት/ተሰሚነት ማሳደግ..................................11
4.2 የውስጥ አቅምን ማሳደግ...........................................................................13
4.3 የአባላት ደኅንነትን ማስጠበቅ...................................................................14
4.4 ሀገራዊ ምክክር...........................................................................................14
4.5 የሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ጦርነት................................................................15
4.6 ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት............................................16
4.7 ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ..........................................................................17
4.8 ኢኮኖሚውን በተመለከተ..........................................................................17
ማጠቃለያ...................................................................................................20


መግቢያ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1ኛ መደበኛ ጉባዔውን ሰኔ 25 እና 26 ቀን 2014
ዓ.ም ያደርጋል። በዚህ ጉባዔ ይከናወናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ዐበይት ክንውኖች መካከል
አንዱ ኢዜማን በቀጣይነት የሚመሩ ሰዎች የሚመረጡበት መርሐግብር ነው። ይህ ሰነድ አቶ
አንዱዓለም አራጌ ለኢዜማ መሪ ቦታ በጉባዔው ለመመረጥ የሚያቀርቡት እና ከተመረጡ
የሚተገብሯቸውን አንኳር ተግባሮች የሚዘረዝር ሰነድ ነው። አቶ አንዱዓለም አራጌ በመሪነት
ከተመረጡ አቶ ሐብታሙ ኪታባን ምክትል መሪ ያደርጋሉ።
ይህ ሰነድ ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተደረገውን የሥልጣን ሽግግር
ተከትሎ እስከ አሁን ያለፈችበትን እና የደረሰችበትን ሁኔታ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ኢዜማ
ለመጫወት የሞከረውን ሚና እና ያስገኘውን ውጤት በመቃኘት በቀጣዩ ሦስት ዓመታት
የኢዜማ ዋነኛ አቅጣጫ ሊሆን የሚገባውን መንገድ የሚያመላክት እና ይህንን ለማስፈጸም
ለምን የመሪ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።

1. የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ


1.1. ዳራ
በሀገራችን ሥልጣኑ የተገደበ መንግሥት እንዲኖር ለማድረግ በትውልድ ቅብብሎሽ የረጅም
ጊዜ ትግል ሲደረግ ቆይቷል። ዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ ሥርዓትን በመመሥረት ሕዝቡን
እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ የተደረጉ ትግሎች በብዙ ፈተና ውስጥ ቢያልፉምና
ጥቂት ቢሆኑም፣ መልካም ሀገራዊ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለው ነበር። ከእነዚህ ሀገራችንን
ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመውሰድ በሕዝብ ትግል ከተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎች
መካከል የቅርቡ በ2010 ዓ.ም ቢያንሰ ገዢው ፓርቲ የአመራር ለውጥ እንዲያደርግ ያስገደደው
አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው።

በ2006 ዓ.ም አጋማሽ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ተጀምሮ ሲቀጣጠል የከረመው ሕዝባዊ
ተቃውሞ ሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችን በማዳረስ በገዢው ድርጅት - ኢሕአዴግ ውስጥ
ባሉ ሰዎች መካከልም ቢሆን እንኳን ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲደረግ አስገዳጅ ሁኔታን
ፈጥሮ ነበር። በሕዝብ ግፊት አስገዳጅነት ገዢው ድርጅት በውስጡ ያደረገው የሥልጣን
ሽግግርን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንን የተቆጣጠሩት ሰዎች፣ ከሥልጣን ሽግግሩ
በፊት ሕወሃት መራሹ ኢሕአዴግ ገፍቶት የቆየውን የኢትዮጵያዊነት ትርክት ማቀንቀን የጀመሩ
ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይቅርታ
ጠይቀው ሕዝብን እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር።

1
የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንን የተቆጣጠሩት ሰዎች የገዢው ድርጅት አካል የነበሩ ሰዎች
ቢሆኑም እንኳ፣ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የገቡትን ቃል መሰረት በማድረግ ከፍተኛ ሕዝባዊ
ቅቡልነት እና ድጋፍ አግኝተው ነበር። በጊዜ ሂደት ግን በሀገራችን ሲተገበር የቆየው የዘውግ
ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ የፈጠራቸው ውስብስብ የፖለቲካ እና የደኅንነት ችግሮችን
መፍታት ይቅርና እንዳይባባሱ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። እንዲሁም ሀገራዊ ሁሉን አቀፍ
የአቅም ውስንነትን የተረዳ የአንገብጋቢ የጉዳዮች ልየታ እና የመፍትሄ ዝግጅት ትክክለኛ
ቅደም ተከተል ባለመኖሩ ብሎም ሀገርን ከማሻገር ይልቅ የፖለቲካ ሥልጣን ማስጠበቅን
ቅድሚያ በመስጠታቸው የፈጠሩት የእርስ በርስ ሽኩቻ በሕዝብ ያገኙት ቅቡልነት እና ድጋፍ
በከፍተኛ ሁኔታ ተሸርሽሯል። ድጋፋቸው መሸርሸሩ ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝብ ትግል የተገኘው
ሀገረ-መንግሥቱን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ተስፋ ጭላንጭል ጠፍቶ እንደውም በየአካባቢው
በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚሞቱ ዜጎቻችንን መታደግ እና ሀገራችንን ከመበታተን
ማትረፍ ትልቁ የቤት ሥራ ሆኗል።

1.2. አሁን የምንገኝበት ሁኔታ


1.2.1. ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ጦስ
ባለፉት 4 ዓመታት የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን ሲመሩ የቆዩ ባለሥልጣናት የመገናኛ
ብዙኀን ፊት ቀርበው በተደጋጋሚ ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካን
ሲያወግዙ እና ኢትዮጵያዊነትን ሲያወድሱ ይሰማሉ። ሆኖም አንድ ወጥ አድርገን መሥርተነዋል
የሚሉት ፓርቲ ውስጥ ጭምር ዘውግን መሠረት ያደረገ መከፋፈል መኖሩ፣ በገዢው ፓርቲ
የምርጫ 2013 የመወዳደሪያ ሰነድ በግልጽ በሕገ መንግሥት የተከበሩት የብሔር፣ ብሔረሰቦች
እና ሕዝቦች መብቶች ሳይሸራረፍ ለማስቀጠል እንደሚሠራ ማስቀመጡ፣ እንዲሁም ሰላማዊ
ዜጎች ላይ ማንነታቸውን መሠረት አድርጎ የሚደርሰው አሰቃቂ ጥቃትን ማስቆም አለመቻሉ
በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሊባል የሚችል በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የእርስ በርስ
አለመተማመን እና መፈራራት ተፈጥሯል።

1.2.2. መሠረታዊ የዜጎች እና የሀገር ደኅንነትን ማስጠበቅ አለመቻል


ከላይ እንደተጠቀሰው የተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በተደጋጋሚ
እያደረሱ ይገኛሉ። እነዚህ ጥቃቶች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙባቸው አካባቢዎች የታወቁ
ሲሆን፣ የዜጎችን ደኅንነት እና ሰብዓዊ መብት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ጥቃቶቹ
እንዳይፈፀሙ አስቀድሞ መከላከል አልቻለም። በዚህም ምክንያት ክቡር የሆነው የዜጎች
ሕይወት በየጊዜው የመቀጠፉ ዜና የተለመደ የዕለት ዘገባ እስከመሆን ደርሷል።

ክልሎች አሁንም በልዩ ኃይል ስም ተቋቁመው የታጠቁ ኃይሎችን በስፋት ማሠልጠን


እንደቀጠሉ ሲሆን፤ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እነዚህ ኃይሎች ከሰላም መደፍረስ እና
2
ንፁሃን ላይ ከሚደርሱ አሰቃቂ ጥቃቶች ጋር ስማቸው በተደጋጋሚ ይነሳል። ልዩ ኃይልን
በተመለከተ የመንግሥት ባለሥልጣናት በይፋ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ ቃል
ቢገቡም ምንም ተግባራዊ የሆነ ነገር የለም።

1.2.3. የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት


በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሃት መካከል የተደረገው ጦርነት ሁለቱ ወገኖች በተናጥል
አድርገነዋል ያሉት የተኩስ አቁምን ተከትሎ የረገበ ቢመስልም፣ በየትኛውም ጊዜ ተመልሶ
ሊያገረሽ እንደማይችል ምንም ማረጋገጫ የለም። የፌዴራል መንግሥት በተለይ ከመቀሌ ለቆ
ለመውጣት የወሰነበት ምክንያትን ጨምሮ ከዛ በኋላ ጦርነቱን ሕወሃትን ከማሸነፍ ባለፈ ዘላቂ
ሰላም በማስፈን የአካባቢውን ሕዝብ ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ዕቅድ ይዞ እየሠራ
ስለመሆኑ ምንም ፍንጭ የለም።

ይህ ጦርነት የሀገራችንን ዜጎች ለሞት እና ለመፈናቀል የዳረገ፣ የሀገራችን ምጣኔ ሀብት ላይ


ትልቅ ጫና ያሳረፈ እና በዓለም አቀፍ መድረክ እንደሀገር የነበረንን አቋም በከፍተኛ ሁኔታ
የሸረሸረ ነበር። ይህ ጦርነት መልሶ አገርሽቶ እስካሁን ከደረሰው እልቂት እና ውድመት
ተጨማሪ ኪሳራ ውስጥ እንዳንገባ ሁላችንም የሚጠበቅብንን እንድናደርግ የማስተባበር
ኃላፊነቱን መወጣት የሚገባው መንግሥት፣ ሕወሃት የሚፈጥረውን አስቸጋሪ ሁኔታ አልፎ
ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት እያደረገ ያለው ነገር ስለመኖሩ በተጨባጭ የሚታወቅ
ነገር የለም። በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሌሴንጎን ኦባሳንጆ መሪነት
የሚደረገው እና በየጊዜው ብቅ ጥልቅ የሚለው ሙከራ በተጨባጭ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ
እና መንግሥት በሙከራው ማትረፍ የሚፈልገው ዝርዝር ዓላማ አለመታወቁ ከተስፋ ይልቅ
ጥርጣሬን የሚያጭር እየሆነ ነው።

1.2.4. ምጣኔ ሀብትን በተመለከተ


ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ የመንግሥት ወጪ መጠየቁ
አያጠራጥርም። ከዚህ በተጨማሪም የንግድ እንቅስቃሴን መገደቡ እና ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ
የተጣለብን መዓቀብ (ከAGOA መሰረዝ) የሀገራችን ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ
እርግጥ ነው። ከጦርነቱ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ከዛ በፊት እና
ከዛም በኋላ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች በተጨባጭ ያሉ ችግሮችን በቅደም ተከተል
ለመፍታት ዒላማ ተደርገው በተቀናጀ መልኩ ከሚተገበሩ ተደጋጋፊ ሥራዎች ይልቅ በዘፈቀደ
በባለሥልጣናት መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረቱ ሥራዎች ተግባራዊ በመደረጋቸው፤
የተረጋጋ ምጣኔ ሀብት እንዳይኖረን እንቅፋት ሆኗል። በዚህም ምክንያት የሀገራችን የውጭ
ምንዛሬ ክምችት እና የዋጋ ግሽበት አደገኛ መጠን ላይ ደርሰዋል።

3
1.2.5. ሀገራዊ ምክክር
የሀገራችንን ችግሮች ከመደበኛ የመንግሥት ተቋማት እና ሕግጋት ከፍ ባለ መልኩ ለመመርመር
እና የረጅም ጊዜ የሀገራችንን እጣ ፈንታ በጋራ ለመወሰን የሚያስችል መድረክ እንዲመቻች
በተደጋጋሚ የተለያዩ ኃይሎች ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወቃል። ቀደም ብሎ የተለያዩ ሀገር
በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና
ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን፣ የ2013
ምርጫን ተከትሎ ደግሞ መንግሥት የምክክር መድረክ የሚያዘጋጅ ኮሚሽን ለማደራጀት
ወስኖ ወደሥራ ተገብቷል።

መንግሥት ኮሚሽኑን ለማቋቋም ከወሰነ በኋላ ኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ዝግጅት ጀምሮ
ኮሚሽነሮች እስከመሰየም ድረስ የሄደበት መንገድ፤ በዚህ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው
ፕሮጀክት ተዓማኒነት ላይ ገና ከጅምሩ ጠባሳ ያኖረ ነበር። እስከ አሁን በሌሎች ሀገራዊ
ፕሮጀክቶች (ለምሳሌ ምርጫ 2013) ላይ መንግሥትን የተቆጣጠሩ ሰዎች ያሳዩት ከሀገር
ጥቅም በላይ የሥልጣን ፍቅርን ማስቀደም እና ሁሉንም ለመቆጣጠር የመፈለግ አባዜ ጋር
ተደምሮ፤ ሀገራዊ ምክክሩንም እነሱ የሚፈልጉትን ውጤት ብቻ እንዲያመጣ ለማድረግ ዓላማ
አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ መገመት ከባድ አይደለም።

ሀገራዊ ምክክሩን የሚያስተባብሩ 11 ኮሚሽነሮች የተሰየሙ ሲሆን በኅዳር 2015 ዓ.ም ምክክሩ
እንደሚጀምር ተነግሯል።

1.3. ማጠቃለያ
በአጠቃላይ አሁን ሀገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በሁሉም መስክ ሲታይ እጅግ በጣም
አሳሳቢ ነው። የበለጠ አሳሳቢ የሆነው ነገር ደግሞ፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከገባንበት
ቀውስ የምንወጣበት ሁሉን አቀፍ ራዕይ አዘጋጅቶ በዚያ ዙሪያ ሁላችንንም ማሰባሰብ ይቅርና
ቀውሱን እንኳን እንዳይባባስ ባለበት ማቆም አለመቻሉ ነው። የሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች
ቁመናም ቢሆን የሀገራችን ችግሮች ውስብስብነት እና ጥልቀትን የሚመጥን አይደለም።
በዚህም የተነሳ እንደሀገር አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ ግራ መጋባት ውስጥ ነው ያለነው ማለት
ማጋነን አይሆንም።

4
2. የፓርቲያችን ወቅታዊ ሁኔታ
2.1 ዳራ
ኢዜማ በ2010 ዓ.ም በሕዝብ ግፊት የተፈጠረውን ተስፋ
ተከትሎ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በተለያየ መንገድ
ከሕወሃት መራሹ ኢሕአዴግ ጋር ትግል ሲያደርጉ የነበሩ
ፓርቲዎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ተበታትኖ ከሚደረግ
ፉክክር ይልቅ በመሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ
እስከተደረሰ ድረስ በሰፊ ጥላ ውስጥ ተሰባስቦ አንድ ላይ
መታገል የበለጠ አዋጭ እንደሚሆን ስምምነት ላይ ተደርሶ
ድርጅቶቹ እና ፓርቲዎቹ ራሳቸውን አክስመው ግንቦት 2011
ዓ.ም የተመሠረተ ፓርቲ ነው። የኢዜማ ዋነኛ ምሰሶዎች
ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ፍትህ ሲሆኑ
ፓርቲው የሚያራምዳቸው አቋሞች እና ፖሊሲዎች እነዚህን
ሁለት የፓርቲው ምሰሶዎች በሀገራችን ተተግብረው ማየትን
ዓላማ ያደረጉ ናቸው።

እነዚህን ምሰሶዎች በሀገራችን ለመተግበር ኢዜማ ከመነሻው


አራት ስትራቴጂክ ግቦች ቀርፆ እነዛን ግቦች ለማሳካት
ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። እነዚህም ግቦች፥

• ኢዜማ ተልዕኮውን ማስፈፀም የሚችል ዘመን


ተሻጋሪ፤ ጠንካራ ተጠያቂነት ያለበት
የፖለቲካ ፓርቲ ማድርግ፤
• ኢዜማ ኢትዮጵያን በጠንካራ
የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እድገት ጎዳና
መምራት የሚችልና የኅብረተሰቡን አመኔታ ያገኘ
የመንግሥት ቅርፅ እንዲኖረው ማድረግ፣
• በአገራችን ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣
የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ተቋማዊ
ለማድረግ እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት
ጋር በመተባባር ጉልህ ሚና መጫወት፤
• በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች አብላጫ ወንበር
በመያዝ መንግሥት
ለመመስረት የሚያስችል መቀመጫዎች ማሸነፍ፤
5
ኢዜማ ከምሥረታው ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በተለመደ መልኩ ይደረግ የነበረውን
የተካረረ አካሄድ በመተው፣ የተጀመሩ የተቋማት መልሶ ግንባታ ሥራዎች ውስጥ ለፖለቲካ
ፓርቲዎች በተፈቀደው ልክ በንቃት በመሳተፍ ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማት በሀገር ደረጃ
እንዲኖሩን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

የመንግሥት እና የድርጅት ጉዳዮችን ለይቶ የሚያስተናግድ መዋቅር እና የምርጫ ክልልን


መሰረት ያደረገ አደረጃጀት በሥራ ላይ በማዋል፤ እንዲሁም በምርጫ 2013 ከሞላ ጎደል
የፖሊሲ አማራጮች ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ በማድረግ ዘመናዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ
ተሞክሯል።

በሕዝብ የለውጥ ግፊት ሥልጣን ላይ የወጡት የገዢው ድርጅት ሰዎች፥

1. በተከተሉት የጥገናዊ ለውጥ መንገድ (ከአብዮት በተቃራኒ) ለረጅም ጊዜ


ሲወሳሰቡ ለመጡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ
ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው እና እነዚህን ውስብስብ ችግሮች ተረድቶ
ትክክለኛ መፍትሄ ለመስጠት የአቅም እና የፍላጎት እጥረት እንደሚያጋጥማቸው
በመረዳት፤
2. ከተለመደው የዘውግ ማንነት ላይ ያተኮረ የከፋፍለህ ግዛ ትርክት የወጣ ሀገራዊ
ትርክት በመከተላቸው፣ እነዚህን ሰዎች በጠንካራ ተቃውሞ ከማስደንበር እና ወደ
ጥግ ከመግፋት ይልቅ በትርክት ደረጃ የሚያነሱትን አስተሳሰብ በማበረታታት
ወደ መንግሥታዊ አሠራር እና መዋቅር እንዲያወርዱት ማገዝ እና ዕድል መስጠት
የተሻለ አማራጭ እንደሆነ በማመን፤ እንዲሁም
3. ለረጅም ጊዜ በጉልበት ማስገበርን ልምድ ያደረገ የሀገረ-መንግሥትን ሥልጣን
በእጁ የያዘ ኃይል ጋር የግፍጫ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ዝቅ ሲል የፓርቲያችንን
የውስጥ አቅም ዕድገት የሚገድብ፣ ከፍ ሲል ደግሞ በወቅቱ ከነበረው ሀገራዊ
ሁኔታ አንጻር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥር እና
ለሀገራዊ መረጋጋት ሊፈጥረው የሚችለውን አሉታዊ አስተዋፅዖ ከግምት በመክተት፤
የሚወስዷቸው ትክክለኛ ያልሆኑ እና መውሰድ ሲገባቸው ያልወሰዷቸው እርምጃዎች ላይ
የሰላ ትችት ከመሰንዘር ይልቅ የኢዜማ መርሆዎችን ባገናዘበ መልኩ ለዘብተኛ አቋም ሲወስድ
ቆይቷል። በተለይ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ኃይሎች እና ገዢው ፓርቲ ኢዜማ የተከተለውን
ለዘብተኛ አቋም ከፍርሃት በመውሰድ የፖለቲካ ሜዳውን በከፍተኛ ሁኔታ ተፅዕኖ ስር
ማስገባት ችለዋል። በዚህም ምክንያት ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የፖለቲካ
ምህዳር ውስጥ የተገፋ የዳር ተመልካች የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።
6
2.2 አሁን የምንገኝበት ሁኔታ
ኢዜማ ከላይ ከሰፈሩት ስትራቴጂክ ግቦች አንፃር አሁን ያለበት ሁኔታ ቢገመገም በአመዛኙ
ስትራቴጂክ ግቦቹን ማሳካት እንዳልቻለ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ኢዜማ ራሱን እንደሁነኛ
አማራጭ ማቅረብ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ሀገራችንን ራሱን ችሎ መምራት የሚችል አድርጎ
መሳልም አልቻለም። በሀገራችን ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍንም እዚህ ግባ የሚባል ሚና
መጫወት አልቻለም። በምርጫ 2013ትም የተገኘው ውጤት ሌላኛው የኢዜማ ስትራቴጂክ
ግብ መሳካት እንዳልቻለ ያሳየ ነበር።

2.2.1 ሀገራዊ ዕይታን በተመለከተ


የሀገራችን አጠቃላይ ሁኔታ ላይ በኢዜማ ውስጥ ብዙ ልዩነት ባይኖርም የችግሩ መንስዔ
ትንተና እና መፍትሄ ላይ ግን ጉልህ ሊባል የሚችል ልዩነት አለ። በአንድ በኩል አሁንም ቢሆን
ከመጀመሪያ የያዝነውን ለዘብተኛ አቋም ሊያስቀይር የሚችል በቂ ምክንያት የለም፤ በመሆኑም
በያዝነው መንገድ መቀጠል አለብን የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች አሉ። በሌላ በኩል
ደግሞ እስካሁን ድረስ የወሰድነው አቋም በሀገር ደረጃ የደረሱ ውድመቶችን እና ውድቀቶችን
ማስቆም ያልቻለ ብቻ ሳይሆን የፓርቲውን በረጅም ጊዜም ቢሆን ራሱን እንደ ብቁ አማራጭ
ለማቅረብ የሚችልበትን ዕድል ከጊዜ ወደጊዜ እያቀጨጨ የሄደ በመሆኑ የውስጥ አቅማችንን
እና በሕዝብ ዘንድ ያለንን ተሰሚነት ቀስ በቀስ እየገነባን የምንሄድበት እና በሀገራዊ ጉዳዮች
ላይ ያለንን ተፅዕኖ ማሳደግ ይገባል። ይህንንም ለማድረግ እስካሁን ከመጣንበት አካሄድ የተለየ
መንገድ መቀየስ እና መራመድ ይገባናል የሚል አስተሳሰብ አለ።

እነዚህ ሁለት አንኳር አስተሳሰቦች ሲሆኑ ከነዚህ አስተሳሰቦች ጋር በከፊል የሚስማሙ


እንዲሁም አክራሪ አስተሳሰቦችም አሉ።

በሁለቱ አንኳር አስተሳሰቦች መካከል ያለው ዋነኛ ልዩነት የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን
የያዙ ሰዎች ላይ ያለ ዕምነት ነው። እስካሁን ይዘን በመጣነው አካሄድ መቀጠል አለብን
የሚለው አስተሳሰብ፤ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንን የተቆጣጠሩት ሰዎች አሁንም ቢሆን
የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ፍላጎት እንዳላቸው
የሚያምኑ ሰዎች የሚያራምዱት አስተሳሰብ ነው። በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ ይህን
አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎች በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ኢዜማ የቆመላቸውን ዓላማዎችን
ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ መገንባት ስለማይቻል/ከባድ
ስለሆነ፤ ዓላማዎቹን ለማስፈፀም የመንግሥት አቅም መጠቀም የሚያስችል ጤናማ ግንኙነት
የመንግሥትን ሥልጣን ከተቆጣጠሩ ሰዎች ጋር መፍጠር የተሻለ አማራጭ ነው ከሚል ዕምነት
የደረሱበት ድምዳሜ ሊሆን ይችላል።

7
በሌላ በኩል የእስከ አሁኑ የኢዜማ መንገድ፥
1. በሕዝብ ግፊት የተገኘውን በአንፃራዊነት ሰላማዊ ሊባል የሚችል የለውጥ ተስፋን
ወደ ተግባር ለመለወጥ ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እና እነዚህን ተግዳሮቶች
ለመቋቋም መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች በሚመለከት ምክረ ሀሳብ ቢቀርብም፣
በመንግሥት በኩል ቢያንስ ከምር ተወስደው ስለመመዘናቸው ምንም ማስረጃ
ማግኘት አልተቻለም፤
2. በሕዝብ ግፊት የተገኘውን በአንፃራዊነት ሰላማዊ ሊባል የሚችል የለውጥ ተስፋ
በአግባቡ መመራት ሳይችል ቀርቶ በሕወሃት ጠብ አጫሪነት ቢሆንም በሀገራችን
ከዚህ ቀደም እንደተለመደው የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነትን መሰረት ያደረገ
ደም አፋሳሽ ጦርነትን ለማስቀረት ተፅዕኖ ማድረግ አለመቻሉ፤ ጦርነቱ
ከተጀመረም በኋላ የጦርነቱን ጉዳቶች ለመቀነስ የሚያስችሉ አስቀድመው
ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች በተመለከተ እና በጦርነቱ ምክንያት
የባሰ ጦስ እንዳይመጣ ኢዜማ የሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች
ከመናገር ያለፉ መሆን ያልቻሉ ነበሩ፤
3. በየጊዜው ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሱ አሰቃቂ ጥቃቶችን ለማስቆም ኢዜማ
በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እንዲሁም መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎችን ዘርዝሮ ጥቆማ
ቢሰጥም፣ በመንግሥት በኩል የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ማስቆምም ሆነ
እንዳይከሰቱ አስቀድሞ መከላከል አልተቻለም፤
4. በምርጫ 2013 እንዳየነው ገዢው ፓርቲ ከዚህ ቀደም ሕወሃት/ኢሕአዴግ
ያደርገው እንደነበረው የካድሬ መንጋ በመራጩ ሕዝብ ውስጥ በማሰማራትና
በማስፈራራት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በመግታት ወደ መራጩ ሕዝብ
እንዳይደርሱ በማድረግ፣ በተፎካካሪ እጩዎች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ታዛቢዎች ላይ
ከፍተኛ ተጽእኖ በማድረግ፣ የሀገር እና የመንግሥት ጉዳዮችን ለምርጫ ቅስቀሳ
በመጠቀም፣ በድምጽ መስጫው ቀን ሂደቱ ላይ ተጽእኖ በማሳደር ለነፃ እና ፍትሃዊ
ምርጫ ዝግጁ እንዳልሆነ በግልፅ ሲያረጋግጥ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት
እንቅፋት ሲሆን ማስቆማ አልተቻለም፤
5. ከ2010 ዓ.ም በኋላ ተቋማትን ጠንካራ እና ገለልተኛ አድርጎ ለማቋቋም የወጡ
አዋጆችን ጨምሮ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጡ መብቶችን በመጣስ
የሚወሰዱ ውሳኔዎችን እና እርምጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ እንጂ እየቀነሱ
እንዲሄዱ ማድረግ አልተቻለም፤ እንዲሁም
6. ሀገራዊ ችግሮችን በአግባቡ መዝኖ የመፍትሄ ቅደም ተከተል ማዘጋጀት እና
ለአንገብጋቢ ችግሮች ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ በግብር ይውጣ የሚወሰኑ
ውሳኔዎችን ማስቆም አልተቻለም።

8
በአጠቃላይ በሕዝብ ግፊት የተገኘው የለውጥ ተስፋ የተዳፈነበት እና የአንድ ፓርቲ (አልፎም
የአንድ ግለሰብ) ፈላጭ ቆራጭነት ከዕለት ወደ ዕለት እየጎላ የመጣ ሲሆን፣ ይህንን ለማስቆም
ኢዜማ መወጣት የሚገባውን ሚና በአግባቡ ተወጥቷል ብሎ ማለት አይቻልም። በመሆኑም
አንዴ የያዝነው መንገድ ትክክል ነው መቼም አይለወጥም ከሚል የዕብሪት አስተሳሰብ እና
ደጋግሞ አንድ ዓይነት ነገር በመተግበር የተለየ ውጤት ከመጠበቅ በመውጣት ያለንን አቅም
ሁሉ አሟጠን አዲስ መንገድ በመቀየስ እና በመከተል እየቀጨጨ ያለውን ኢትዮጵያ ውስጥ
እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመመሥረት ተስፋ መልሰን ማለምለም የምንችልበት
የውስጥ አቅም እና ሕዝባዊ ቅቡልነት መገንባት ይገባናል የሚል አስተሳሰብ አለ።

ከላይ የተጠቀሱት የሐሳብ ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ጤናማ ውይይቶች በተለያየ ጊዜ እና


ቦታ የተደረጉ ሲሆን፣ የሐሳብ ልዩነቱን መሰረት በማድረግ ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድም
አንዱ ሌላኛውን ለማፈን ሙከራ መደረጉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

2.2.2 ድርጅታዊ ጥንካሬ


አዲስ ዓይነት መዋቅር እና አደረጃጀት ተግባራዊ ማድረግ ቢቻልም፣ አሁንም ያልደረስንባቸው
እና በጣም ደካማ የሆኑ የምርጫ ክልል መዋቅሮች ብዙ ናቸው። በምርጫ 2013 ምርጫው
ላይ በብቃት መሳተፍ የሚችሉ እና ለማሸነፍ ተስፋ ያላቸው የምርጫ ክልሎችን ለመለየት
በተደረገ ዳሰሳ፤ የኢዜማ መዋቅር የተገኘባቸው የምርጫ ክልሎች 358 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ
226 የሚሆኑት ከፍተኛ የማሸነፍ ተስፋ ያላቸው እንደሆኑ በዳሰሳ ጥናቱ ተደርሶበታል። ይህም
ማለት 189 የምርጫ ክልሎች የኢዜማ መዋቅር ጨርሶ የሌለ፤ እንዲሁም 132 ወረዳዎች
ደግሞ መካከለኛ ወይንም ዝቅተኛ አቅም ያላቸው የኢዜማ መዋቅሮች እንዳሉ ያሳያል። ከዚህ
በተጨማሪ ድርጅታዊ አቅምን በተመለከተ በቀላሉ መረጃ ማግኘት የሚቻልበት ዘመናዊ
እና ቀልጣፋ የመረጃ ሥርዓት ባለመኖሩ የምርጫ ክልል እና አጠቃላይ የኢዜማን ጥንካሬ
ለመከታተል አስቸጋሪ አድርጎታል።

ባለፉት 3 ዓመታት ኢዜማ የሀገራችንን ችግር በመረዳት የሰከነ እና በሐሳብ ላይ ያተኮረ


ፖለቲካ ነው የሚያራምደው የሚል ምስል መፍጠር የተቻለ ቢሆንም፣ በፓርቲው ላይ
የሚሰነዘሩ ትችት እና ነቀፌታዎችን በአግባቡ እና በወቅቱ መመለስ ባለመቻሉ እንዲሁም
በሀገራችን የሚከሰቱ ችግሮች ላይ ፈጥኖ አቋሙን ግልፅ ማድረግ ባለመቻሉ የፓርቲው ምስል
ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ አድርጓል። በባለሙያዎች የተዘጋጁ 42 ፖሊሲዎች አሉ ቢባልም፣
እነዚህ ፖሊሲዎችን በተደራጀ መንገድ ለሕዝብ እንዲደርሱ ለማድረግ አልተቻለም።

9
2.3 ማጠቃለያ
ኢዜማ የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ያግዛል ብሎ
ባለፉት 3 ዓመታት ሲከተለው የቆየው አካሄድ በመርሆዎቹ ላይ በግልፅ የተቀመጡትን
የኢትዮጵያን እና የሕዝብ ደኅንነትን እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን ተጨባጭ
ውጤት ማስገኘት አልቻለም። ውስጣዊ የድርጅት አቅምን በተመለከተም ብዙ ሥራ የተሠራ
ቢሆንም፣ የሀገራችንን ችግር በሚመጥን መልኩ አቅም የገነባ ፓርቲ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ
መናገር አይቻልም።

3. እንደሀገር ከገባንበት ችግር ለመውጣት ምን


መደረግ አለበት?
አሁን ሀገራችን ካለችበት ቀውስ ለመውጣት የቀውሱን ውስብስብነት እና ጥልቀት የሚመጥን
እንዲሁም ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ማሰባሰብ የሚችል የጋራ ራዕይ መቅረፅ
ያስፈልጋል። ይህም የሰከነ የልሂቃን ውይይት ይፈልጋል። ይህንን ውይይት በቅን ልቦና
ለማድረግ ሁሉንም ዓይነት አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን ዕምነት የሚያሳድሩበት
የውይይት መድረክ ያስፈልጋል። ሀገራዊ ምክክሩን ለማስተባበር የተሰየሙት ኮሚሽነሮች
በሂደቱ ጥርጣሬ የገባቸውን ወይንም ተስፋ ያጡ አካላትን በጋራ እና በተናጠል ምክንያታቸውን
ማጥናት እና በሂደቱ ዕምነት እንዲኖራቸው ሊሠሩ ይገባል።

የሀገራዊ ምክክሩ የረጅም ጊዜ ውጤት ያለው ብቻ ሳይሆን ሂደቱ ራሱ ጊዜ የሚፈልግ ነው።


የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እየተካሄደ ጎን ለጎን የዜጎችን ሁለንተዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት
ከሁሉ በላይ ቅድሚያ ሰጥቶት ሊሠራ ይገባል። መንግሥት የሀገር ሀብትን አንገብጋቢ ባልሆኑ
ጉዳዮች ላይ ማባከኑን አቁሞ ትኩረቱን ማስተካከል ይገባዋል። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት
የሕግ የበላይነት የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል።

ኢዜማ ምርጫ 2013ን ተከትሎ የሀገራችን ሽግግር ሂደትን እና ምርጫው ያልፈታቸው ጉዳዮች
ላይ ባደረገው ግምገማ፤ በሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስምምነት ሊደረስባቸው
የሚገቡ 7 አንገብጋቢ ጉዳዮችን ለይቶ ነበር።

1. የሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱን መሰረታዊ ችግሮች በሚመለከት የታዩ ልዩነቶች፣


2. በአሁኑ ጊዜ የሀገርን እና የሕዝብን ደኅንነት ከማስጠበቅና ሀገር ከማስቀጠል አንጻር
እጅግ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን የደኅንነት ተቋማትን በሚመለከት የታዩ ልዩነቶች፣
3. ከቀን ወደ ቀን የዜጎችን ሕይወት ለከፍተኛ ችግርና መከራ እየዳረገ ያለውን፣ የኑሮ
ውድነት፣ የመሠረታዊ የኑሮ ፍላጎት አቅርቦት ችግር እና ሥራ አጥነትን
የሚመለከቱ ችግሮችና የመፍትሄ ሐሳቦች ላይ ያለው ልዩነት፣
4. የሕዝብን ገንዘብና ሀብት ዘርፋና የሙስናን ችግር አረዳድን እና ተግባራዊ
10
የመፍትሄ ሐሳቦችን በሚመለከት የታዩ ልዩነቶች፣
5. የሀገር የመንግሥትና የፓርቲን ፍላጎቶችና
ጥቅም የቀላቀለ አደገኛ አካሄድን
በሚመለከት የታዩ ልዩነቶች፣
6. የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በሚመለከት ሊኖር
የሚገባው የጋራ መግባባት፣
7. የፓለቲካ ፓርቲዎችን በሚመለከት ሊኖር የሚገባው
የጋራ መግባባት፣

የኢዜማ ጠቅላላ ጉባዔ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በመስከረም 2014


ዓ.ም ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት የቀረበው ጥያቄ ላይ
ውሳኔ ሲያስተላልፍ፤ ከላይ የተጠቀሱት 7 ነጥቦችን ከግምት
በማስገባት ነበር። ጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ካስተላለፈበት ጊዜ
አንስቶ እስከ አሁን ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮችን በተመለከተ
መግባባት ላይ መድረስ ይቅርና ምንም ዓይነት ተስፋ ሰጪ
ጅምሮችም አልታዩም።

የሚቀጥሉት 3 ዓመታት ከላይ በተጠቀሱት 7 ዓበይት ጉዳዮች


ላይ እውነተኛ እና ግልጽ ውይይት መደረግ እና ስምምነት ላይ
መደረስ አለበት።

4. ኢዜማ የሚጠበቅበትን
ሚና ለመጫወት
ሊተገብራቸው የሚገቡ
ለውጦች ምንድናቸው?
4.1 በሕዝብ ዘንድ ያለን ቅቡልነት/
ተሰሚነት ማሳደግ

የኢዜማ ዓላማዎችን ለማሳካት ፍላጎታቸውን በእርግጠኝነት


መናገር የማይቻል የሌላ ፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎች ላይ ተስፋ
ከማድረግ ይልቅ፣ የውስጥ አቅማችንን እና በሕዝብ ዘንድ
11
ያለውን ተቀባይነት ማሳደግ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ ይገባል። እስካሁን ድረስ በሕዝብ
ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከጎዱት ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለን ግንኙነት
በሕዝብ ዘንድ የፈጠረው ግርታ ነው።

ከገዢው ፓርቲ ጋር በተያያዘ የሀገር እና የሕዘብ ደኅንነትን ባስቀደመ ሁኔታ የተከተልነው


ለዘብተኛ አካሄድ የሀገርን እና የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ ያደረገው አስተዋፅዖ ውጤታማ
አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢዜማ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እና ተሰሚነት ላይ አሉታዊ
ተፅዕኖ አሳርፏል። በዚህም ምክንያት የቆምንለትን ዓላማ ለማስፈጸም የሚያግዝ ሕዝባዊ
ቅቡልነት አጥተን እንደፓርቲ የምናወጣቸው መግለጫዎች ከዜና ፍጆታነት ማለፍ የማይችሉ
እስከመሆን ደርሰዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ኢዜማ ውስጥ እስካሁን ይዘን በመጣነው አካሄድ እንቀጥል የሚል
አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የኢዜማን የውስጥ አቅም እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ከመገንባት ይልቅ
ሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ እና አብሮ መሥራት የኢዜማን ዓላማዎች ለማሳካት
የበለጠ ዕድል አለው ብለው ያምናሉ። ይህንን ዕምነታቸውን በይፋ ሲያራምዱት ባይሰማም
ትኩረት የሚሰጧቸውን ጉዳዮች በማየት በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

ኢዜማ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እና ተሰሚነት ለማሳደግ በራሱ መቆም የሚችል ፓርቲ
መሆኑን በተግባር ማሳየት እና እስካሁን በዚህ ረገድ የደረሰውን ጉዳት ማረም ይጠበቅበታል።
በመሆኑም ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለን ግንኙነት ጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ላይ ከመመስረት
እና በገዢው ፓርቲ ፊት አውራሪነት ከመመራት ወጥቶ በመርህ እና ግልፅ ስምምነት ላይ
የተመሠረተ እንዲሆን መሥራት ይገባል።

ይህን ለማስፈጸም በአስቸኳይ መሠራት የሚገባቸው ተግባራት፤


1. ገዢው ፓርቲ ከምርጫ 2013 በኋላ በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት
ቦታዎች ላይ የኢዜማ አባል የሆኑ ሰዎችን ለመሾም ባቀረበው ጥያቄ መሠረት
የኢዜማ ጉባዔ የወሰነው ውሳኔ አተገባበርን ገምግሞ የውሳኔ ሐሳብ በማዘጋጀት
ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል፤
2. የገዢው ፓርቲን የአብረን እንሥራ ጥያቄ ስንቀበል ያስቀመጥናቸው 7 ዓላማዎችን
መለካት የሚችሉ መለኪያዎች (indicators) ማዘጋጀት እና ዓላማዎቹ በምን ያህል
ደረጃ እየተሳኩ ስለመሆናቸው ተከታታይ ግምገማ የሚደረግበት የጊዜ ገደብ
ማስቀመጥ፣ እንዲሁም ዓላማዎቹ በሚፈለገው ልክ እየተሳኩ ካልሆነ መወሰድ
ያለባቸውን እርምጃዎች የሚያመላክት የውሳኔ ሐሳብ በቶሎ በማዘጋጀት
12
እንዲፀድቅ እና ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል፤
3. ኢዜማ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው ግንኙነት መመሪያ ይዘጋጃል፤
ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ግንኙነቶች ይህንን
መመሪያ በጥብቅ የሚከተሉ መሆኑን ለማረጋገጥ ክትትል ይደረጋል።
4. አሁን በሥራ ላይ ያለውን ትይዩ ካቢኔ አቅምን እና አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮችን
ባገናዘበ መልኩ መልሶ ማዋቀር እና ለተጋረጡብን አደጋዎች ሁነኛ
መፍትሄ እንዲቀርፁ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል። ትይዩ ካቢኔው ወቅቱን በጠበቀ
ሁኔታ በሀገራዊ አንገብጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ ተግባራዊ መደረግ የሚገባቸውን
እና ሊታረሙ የሚገባቸውን ጉዳዮች ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና
ለሕዝቡ የሚያደርሱበት ግልፅ የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ይደረጋል። በዚህም
መሠረት የትይዩ ካቢኔው የሚከተሉትን ዋነኛ ዘርፎች ይዞ መልሶ
እንዲቋቋም ይደረጋል፤
• የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች
• የኢኮኖሚ ጉዳዮች
• የማኅበራዊ አገልግሎት ጉዳዮች
• የዴሞክራሲ ባሕል እና ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች
• የውጭ ሀገራት እና ተቋማት ግንኙነት ጉዳዮች

4.2 የውስጥ አቅምን ማሳደግ


ከላይ በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ማጠቃለያ ላይ ለማሳየት እንደተሞከረው፣ በሀገራችን ውስጥ
ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች (ኢዜማን ጨምሮ) የሀገራችን ችግር ውስብስብነት እና ጥልቀትን
በሚመጥን ቁመና ላይ አይደሉም። በመሆኑም ኢዜማ የሀገራችንን ችግር በሚገባ የተረዱ እና
ከችግር ለማውጣት የሚችሉ ዘላቂ መፍትሄዎችን ለመቅረፅ እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን
ለማሳመን የሚያስችል የውስጥ እቅም መገንባትን ከሕዝብ ተቀባይነት እና ተሰሚነትን
ከማግኘት ባልተናነሰ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ
የሚከተሉት ሥራዎች በጉባዔ ከሚመረጡ ሌሎች ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት ይከናወናሉ፤

1. ሁሉም የኢዜማ አባላት የኢዜማን ዓላማ እና ኢዜማ ዓላማዎቹን ለማሳካት


ተግባራዊ የሚያደርገውን ስልት በደንብ መረዳት የሚችሉበት ተከታታይ ሥልጠና
በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ይዘጋጃል፤
2. አባላት እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከፍ ላለ የፓርቲው እና ሀገራዊ ኃላፊነት
የሚያበቃቸውን እንዲሁም መሪዎችን መተካት የሚችሉ ተተኪዎችን ማፍራት
የሚያስችል መርሐ ግብር (succession management program) ተቀርፆ
ተግባራዊ ይደረጋል፤
13
3. በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያዊያንን ዒላማ ያደረገ
ምልመላ መደረጉ እና ሁሉም የፓርቲ መዋቅሮች ብቃት ላላቸው አዳዲስ አባላት
ክፍት እና ተደራሽ መሆናቸውን በየጊዜው በሚደረግ ግምገማ ይረጋገጣል፤
4. ሥልጠና እና አቅም ግንባታን በተመለከተ ከሚተባበሩን አጋር ድርጅቶች ጋር ጥሩ
ግንኙነት መፍጠር እና ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራል።

4.3 የአባላት ደኅንነትን ማስጠበቅ


የትኛውም የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት እና ያልተገራ መንግሥት ባለበት ማኅበረሰብ
ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ትግል ከሚገጥመው ተግዳሮት
መካከል ዋነኛው የአባላት ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ፣ መሳደድ፣ እስር እና የተለያዩ
መንገላታቶች ነው። ኢዜማ ከተቋቋመ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አመራር አባላትን ጨምሮ
በሁሉም አካባቢዎች ሕገ ወጥ የሆነ ተግዳሮት ከገዢው ፓርቲ እና ከሌሎች አካላት ሲደርስ
ቆይቷል። ይህ እንዳይቀጥል የሕግ የበላይነትን በተቋም ደረጃ ማረጋገጥ እንዲቻል የሚሠራው
ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአባላትን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚከተሉት ሥራዎች ተግባራዊ
ይደረጋሉ፥

1. የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ


የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ የሚደርሱ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመፍታት
የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሳተፍ እና ሁለቱ ተቋማት
የሚፈጥሯቸው መድረኮች ዋነኛ የችግር መፍቻ መድረኮች እንዲሆኑ ይሠራል፤
2. በፌዴራል እና በክልሎች ከሚገኙ የሰላም አስከባሪ ተቋማት መሪዎች ጋር አንድ
በአንድ ውይይት በማድረግ ችግሮችን አስቀድሞ መከላከል እና ሲከሰቱም
በአስቸኳይ መፍታት የሚቻልበት ሥርዓት እና የግንኙነት መንገድ ይፈጠራል።

4.4 ሀገራዊ ምክክር


ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ያሉ የአመለካከት
ልዩነቶችን ለማጥበብ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ለማቆም ትልቅ ዕድል የሚፈጥር
መድረክ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ይህ የምክክር ሂደት ለሀገር ይጠቅማል ብለን
የያዝናቸውን ዓላማዎች በሥርዓቱ አዘጋጅተን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም የገዢውን
ፓርቲ ሁሉንም ነገር የመቆጣጠር አባዜ እና ሁሉም ነገር እነሱ ወደፈለጉት ውጤት እንዲያመራ
ተፅዕኖ የማድረግ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ሂደቱን ከማንኛውም ያልተገባ ተፅዕኖ
መከላከል የሚያስችል ሥልት ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
ኢዜማ የቆመለትን ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ

14
ፌዴራሊዝም መሬት ላይ እንዲወርድ ቆፍጣና አቋም መያዝ ይገባዋል። እንደምርጫ 2013
የተለሳለሰ አካሄድ ከተከተልን የቆምንላቸውን የዜግነት ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ፍትህ እና
ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም ልናሳካቸው ቀርቶ በሀገራዊ ምክክሩ ያለወኪል በማስቀረት
ጥፋት የምንፈፅም ይሆናል።

ሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ እና ሂደቱ የሀገራችንን ችግር ሊፈታ
የሚችል ፍሬ እንዲያፈራ፣ የሚከተሉት ተግባራት ይከናወናሉ፥

1. ሀገራችን ላለችበት አንገብጋቢ ችግር ያበቋት ጉዳዮችን በግልፅ የሚተነትን እና


የመፍትሄ ሐሳቦችን የያዘ የአቋም ሰነድ ተዘጋጅቶ በሁሉም አካባቢዎች ከሚገኙ
አባላት ጋር ሰፊ ውይይት ይደረጋል፤ አቋሙም ያለምንም ማለሳለስ በሀገራዊ ምክክሩ
ላይ እንዲጸባረቅ ይደረጋል፤
2. የምክክር ሂደቱን ተዓማኒነት ወይንም ውጤታማነት ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራትን
እና ስጋት የሚፈጥሩ አካላትን በመለየት የመከላከያ ሥልት ተነድፎ ተግባራዊ
ይደረጋል፤
3. በትብብር ልንሠራ የምንችላቸውን ባለድርሻ አካላትን እና የትብብር ነጥቦችን
በመለየት ንግግር ይጀመራል።

4.5 የሰሜኑ ሀገራችን ክፍል ጦርነት


በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በሕወሃት እንደ ተፎከረው አንደኛውም ወገን በቀላሉ ድል
የሚቀዳጅበት ሆኖ አልተገኘም። ሀገራችን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለጋ ወጣቶቿን በዚህ
ጦርነት ምክንያት ቀብራለች። በከፍተኛ ምጥ በረጅም ዓመታት ውስጥ ያቆምናቸው ተቋማት
ወደ ትቢያነት ተቀይረዋል። ለልማት ሊውሉ የሚገባቸው በጀቶች ለጦርነት በመዋላቸዉ
የልማት እንቅስቃሴ በእጅጉ ተፋዟል። ጦርነትን ቀርቶ ራሱን መሸከም የማይችለዉ በብድርና
በእርዳታ ተጠጋግኖ የቆመዉ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየወደቀ ነዉ፡፡ በውስጣዊና ውጫዊ
ምክንያቶች የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየጋሸበ ነው።

የሕወሓት ሥነ-ልቦናዊ ዉቅር በእጅጉ የተዛባ መሆኑን ማናችንም የምንስተው ባይሆንም፣


ለጦርነት ከምንዘጋጀው በላይ ለሰላም ከፍ ያለ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው። እንደ ኢዜማ
በጣም ከባዱና ሥልጡን መንገድ ብንመርጥ፤ እርሱንም በደንብ የተደራጁ መፍትሄዎችን
ሰንቀን መግፋት ይጠበቅብናል፡፡ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚገኝ አይደለምና
ተገፍተንም ቢሆን ወደ ጦርነት የምንገባበት ዕድል ቢፈጠር ካለንበት ፖለቲካዊ ከባቢ ዳፋው
ከፍ ያለ መሆኑን ተረድተን ዙሪያ መለስ ዝግጅት ማድረግ የማናሳድረው ሥራችን ሊሆን
ይገባል።
15
ለሰላማዊ መፍትሄ ፍለጋ ከልብ ተጨንቆና ተጠቦ መሥራት እጅግ ሥልጡንና ምስጉን ተግባር
ሆኖ ሳለ ከምኞትና ፍላጎታችን ውጭ በምንገፋበት ወቅት ህልውናችንን በማንመርጠው
መንገድም ቢሆን ለማስጠበቅ በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት ግድ ይላል። ኢዜማ በዚህ
መስመር ላይ ከፍ ባለ ትኩረት መሥራት አለበት። በመሆኑም ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል
ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢዜማ፥

1. መላው ኢትዮጵያዊያን የሀገራችንን አንድነት ለማስጠበቅ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ


ሰጥተን የሚጠበቅብንን እንድናደርግ እና ሀገራችንን ከአደጋ የሚጠብቁ ተቋማትን
በሙሉ ልብ እንድንደግፍ፣ ሰላምን እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚደረጉ
እንቅስቃሴዎችም ውስጥ እንድንሳተፍ በሁሉም የኢዜማ መዋቅሮች በየጊዜው
ማስታወሻ እና ማሳሰቢያ እንዲሰጥ ይደረጋል።
2. ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ያሉ አማራጮችን ለመፈለግ እና ሙከራ
እያደረጉ ከሚገኙ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት የሚሠራ
የከፍተኛ አመራሮች ቡድን ይቋቋማል።
4.6 ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት

ከዚህ በፊት የነበረው አካሄድ በዓላማና በአስተሳሰብ ይቀርቡናል ከምንላቸው ጋር የመቀራረብ


ዝንባሌ በተወሰነ ደረጃ ብናሳይም ብዙም አልገፋንበትም። በሌላ በኩል ከእኛ በተፃራሪ ቆመዋል
ከምንላቸው ጋር ከወዲሁ የመሸሽ እንጂ የመቀራረብ አቅጣጫ አልመረጥንም። የሀገራችን
ችግር መፍታት የምንችለው ከሚመስሉን ጋር በተባበርነው መጠን ብቻ ሳይሆን እንዲያውም
ከፍ ባለ ደረጃ ከማይመስሉንም ጋር ተቀራርበን በልዩነቶቻችን እና በሀገራችን አጠቃላይ እጣ
ፈንታ ላይ መምከር ስንችል ነው።

ልዩነቶቻችን ጨርሰን መፍታት ባንችል እንኳን ውጥረቶችን አርግበን መተማመንን ማጎልበት


ብሎም በሚለዩን ጉዳዮች ላይ ሕዝበ-ውሳኔ እንዲደረግ መስማማት እንችላለን። ስለዚህ
የኢዜማ የውጭ ግንኙነት ሥራ ከገዥው ፓርቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም የፓለቲካ
ኃይሎች ጋር ተቀራርቦ በመምከር ፈር ቀዳጅ ሚና የሚጫወት ሊሆን ይገባዋል። ገዢው ፓርቲ
ሥልጣን ከመያዙ ውጪ ልክ እንደሌሎች ፓርቲዎች ከኛ የተለየ ፍላጎት ያለው መሆኑን ያመነ
ሥልት መተግበር ያስፈልጋል። በመሆኑም፥

1. ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት የሚገዛ መመሪያ ተዘጋጅቶ


እንዲጸድቅ እና ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል፤
2. በመመሪያው መሠረት ከፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት በይፋ ጥሪ እንዲተላለፍ
ይደረጋል። በተለይ ትልቅ ተጽዕኖ አላቸው ተብለው የሚታመኑ የፖለቲካ
16
ፓርቲዎችን በመለየት ለንግግር የመጀመሪያውን እርምጃ እንወስዳለን።
3. የተጀመሩት ንግግሮች ዓላማ እና በየጊዜው የሚደርሱበትን ደረጃ ለአባላት እና
ለሕዝብ በይፋ እንዲገለፅ ይደረጋል።

4.7 ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ


በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ የነበረው የተቃውሞ ጎራ በከፍተኛ ሁኔታ በብሔር መስመር
የተሰነጣጠቀ ሲሆን፣ ለዘመናት ለብሔር ፓለቲካ እጅ አልሰጥም ብሎ የቆየው ሀገራዊ
አስተሳሰብ ያነገበው ዳያስፓራም ልክ እንደ ሀገር ውስጥ ፓለቲካው ሁሉ ወደ ብሔርተኝነት
ጠርዝ እየተገፋ ይገኛል። ከዚህ ሁኔታ የተረፈው ንቁ ዳያስፖራም ቢሆን ከተቃውሞው ጎራ
እየወጣ በገዥው ፓርቲ ካምፕ ውስጥ እየከተመ ይገኛል። የቀረው ደግሞ በድርጅታችን
አካሄድ ባለመደሰት መገለልን መርጧል።

በአሁኑ ሰዓት ኢዜማ ዓለም አቀፍ ድጋፍ አለኝ ብሎ አፉን ሞልቶ የሚናገርበት ደረጃ ላይ
አይገኝም። መዋቅሩ ላይ ለምልክትነት ተንጠልጥለው ከቀሩ ጥቂት አባላቶቻችን በስተቀር
አብዛኛው በተለያየ መንገድ ከመዋቅሩ ውጭ ሆኖአል። ወርሃዊ መዋጮ የሚያዋጡ አባላት
ቁጥር ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከገንዘብ ባለፈ ኢዜማ ሊያገኝ የሚችለውን እና
የሚገባውን ያህል የፓለቲካ ድጋፍ የማግኘት ዕድሉ ወደ ዜሮ ተጠግቷል ቢባል ከእውነት
የራቀ አይደለም። በመሆኑም

1. በውል የታቀደና የተጠና መርሐግብር በማዘጋጀት እየፈረሰ ያለውን የኢዜማ ዓለም


አቀፍ መዋቅር ባለበት ማቆየት፣ ማደስ እና አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራ ይሠራል።
2. የዳያስፖራው ተሳትፎ በዋናነት እንደ ግብዓት የሚጠቀመው የሀገር ውስጥ
እንቅስቃሴውን በመሆኑ፣ ኢዜማ በሀገር ቤት የሚያቅዳቸው ሥራዎች ከዓለም
አቀፍ መዋቅሩ ጋር የተናበቡና የተቀናጁ እንዲሆኑ ያደርጋል፤

4.8 ኢኮኖሚውን በተመለከተ


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግር ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡ ከችግሩ ለመውጣት
የችግሩን ምንጭ መረዳት አስፈላጊ በመሆኑ የችግሩን ምንጭ መርምሮ ሕዝቡ እንዲያውቀው
በማድረግ፤ አማራጭ ሐሳብ በማቅረብና በፖለቲካዊ ግፊት መስተካከል ያለባቸው አካሄዶች
እንዲስተካከሉ እንሠራለን፡፡

የዝርዝር ችግሮች ምንጭ ከሆኑት መካከል የአገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የዓለም
ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ አሰላለፍ ውጤት፣ የሕዝብ ቁጥርና የምርት መጠናቸውን አለመጣጣም፣
የንግድ እና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ሥርዓት ችግር እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት
17
እንደሚጠበቀው አለመሆኑ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ የፖለቲካ
አለመረጋጋት በዋናነት ትኩረት አድርገን የምንሠራበት ሲሆን፣ ሌሎችም ተገቢ የሆነ ትኩረት
ሰጥተን የምንታገልባቸው ይሆናል፡፡

በመሆኑም እንደ አንድ ራሱን ችሎ እንደ ቆመ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፣ ብንመረጥ በኢኮኖሚ
ጉዳዮች ላይ የምናደርገው ትግል የሚከተለውን ይመስላል፤

1. የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አተገባበር ክትትል - መንግሥት እየተከተላቸው


ያሉትን የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ የመፍትሔ ሐሳቦችን በትይዩ ካቢኔ ደረጃ
በመገምገም በየወቅቱ መንግሥት ጠቃሚ የሆኑ እርምጃዎችን እንዲወስድ
አማራጭ ሐሳብ ማቅረብ፤ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን
ሐሳቦች ሲቀርቡ ተቃውሞን በማቅረብ ፖለቲካዊ ግፊትን መፍጠር፡፡
ይህን ማድረግ ይቻልም ዘንድ በትይዩ ካቢኔ ዘርፍ የከፍተኛ የኢኮኖሚ
ባለሙያዎች ምክር ቤት በማቋቋም መሥራት፡፡
2. የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ቅንጅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ - ሰላምና ጸጥታን በማስፈን
ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ማሳለጥ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደረስ
የፖለቲካ ሥራን ምሥራት፣ ለአገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ አካባቢያዊ
አደረጃጀቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ መንግሥት የሚከተላቸውን ፖሊሲዎችና
ስትራቴጂዎች መርምሮ ጥቅምና ጉዳታቸውን በመለየት ለመንግሥት ምክረ
ሐሳብ ማቅረብና ለሕዝብም የማሳወቅ ሥራ እንሠራለን፡፡
3. የገቢ ምርትን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ትኩረት - የቀጠናው እንዲሁም
የዓለምአቀፍ የፖለቲካ አሰላለፍ የሚፈጥረውን ተጽእኖ መቋቋም ይቻል
ዘንድ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሥራ እድልን ለመጨመር ከውጭ የሚገቡ
ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በአጭር ጊዜ ተጨባጭ እርምጃ
እንዲወሰድ የሚያደርግ አዎንታዊ ፖለቲካዊ ተጽእኖዎችን ለማሳደር መሥራት፡፡
4. የመንግሥት ፕሮጀክት ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና አስተዳደር ክትትል - ከቅርብ
ጊዜ ወዲህ በይፋና አስደንጋጭ በሆነ መንገድ የፋይናንስ ምንጫቸው የማይታወቅ፣
የመንግሥት የአሰራር ስርዓት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ እንዲሁም ለአጠቃላይ
ኢኮኖሚው ያላቸው ቅደም ተከተላዊ ፋይዳ ግምት ውስጥ ያልገባ
ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ይገኛሉ። በመሆኑም በመሰል የመንግሥት
ፕሮጀክቶች ዙሪያ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ
ግንዛቤ በመፍጠርና ተጽእኖ በማሳደር ግልጽነት ያለው አሰራር
እንዲተገበርና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ግምት ውስጥ ያስገባ ቅደም ተከተላዊ
አተገባበር እንዲኖር ተጽእኖ ማሳደር።
18
5. የልዩ ድጋፍ አካባቢዎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ - በአገር ውስጥ ባለው
አለመረጋጋት የተነሳ ተጎጂ የሆኑ አካባቢዎች ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣
በአካባቢዎቹ ላይ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችና ኢንቨስተሮች በልዩ ሁኔታ የብድር
አገልግሎት እንዲቀርብላቸው፣ የሰላም መጥፋቱ ተጽእኖን ግምት ውስጥ
ያስገባ ምርት የሚጨምር የድጋፍ ፕሮግራም ተቀርጾ እንዲተገበር ማድረግ፡፡
6. መሠረታዊ የኑሮ ውድነትን ማረጋጊያ ሥራዎችን መሥራት - በከፍተኛ
ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ በምግብና
በመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ የሚተገበር ፕሮግራም
እንዲኖር ግፊት ማድረግ፡፡ በመንግሥት ይሠሩ የነበሩ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች፣
ገዢው ፓርቲ ለፖለቲካ ጥቅም ለማዋል እየተገበረው ያለው አሰራር ላይ
ሕዝባዊ ግፊት ተደርጎ በመሠረታዊ ደረጃ አሰራሩ ላይ መሠረታዊ ለውጥ
እንዲመጣ ማድረግ፤ መጠናቀቅ የሚቀራቸው ቤቶች በፍጥነት ወደ
አገልግሎት እንዲገቡ ማስቻል፤ በቤት ፕሮግራሙ ላይ የተመዘገቡ ዜጎች
በምንያህል ጊዜ ውስጥ የቤታቸው ባለቤት እንደሚሆኑ የሚያሳይ ተጽዕኖ ወለድ
ውሳኔ ላይ መንግሥት እንዲደርስ ማስገደድ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የምግብ አቅርቦትን ለመጨመር የሚረዱ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን
መንግሥት እንዲከተል እንዲሁ በትኩረት የምንታገል ሲሆን፣ በንግድ ሰንሰለቱ ውስጥ ያለው
ከሞራልም ከሕግም ውጭ የሆኑ አሰራሮች ላይ መፍትሄ እንዲመጣ የሚያደርግ ፖለቲካዊ
ተጽዕኖን መፍጠር።

19
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተከተለው መንገድ
የተከበረ (noble) ሊባል የሚችል መንገድ ነበር። ነገር ግን በተጨባጭ ለማሳካት ከሚያስባቸው
ዋነኛ ዓላማዎች እና ዓላማውን ለማሳካት ከተቀመጡ ግቦች አንፃር መንገዱን ከመዘነው፣
በአሳዛኝ ሁኔታ መውደቁ ግልጽ ነው። በመሆኑም ፓርቲው ቆሜለታለሁ የሚለው ዜግነትን
መሠረት ያደረገ ፖለቲካን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የሚገባውን ቦታ እንዲይዝ
እና ፓርቲውም ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል እንዲሆን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባሮች መተግበር
ብቻ በቂ አይሆንም። እስካሁን የተከተልነው መንገድ የኢዜማ ቅቡልነት ላይ ከፈጠረው ኪሳራ
እንዲያንሰራራ በሚያስችል መልኩ አዲስ አመራር ይዞ መምጣት ይገባዋል።
• በቀጣዩ 3 ዓመታት ኢዜማ እስካሁን ከመጣበት መንገድ የተለየ መንገድ መውሰድ
እንደሚገባው ከልብ የሚያምን መሪ ያስፈልገናል!
• በቀጣዩ 3 ዓመታት ኢዜማ ሁሉን አውቃለሁ የማይል፣ ለአባላት ድምጽ
ጆሮ የሚሰጥ እና በአባላት መካከል ልዩነትን የሚያሰፋ ሳይሆን አሰባሳቢ
ስብዕና ያለው መሪ ያስፈልገናል!
• በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ኢዜማን መምራት የሙሉ ጊዜ ሥራው የሆነ
መሪ ያስፈልገናል!
• በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ከገዢው ፓርቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር
ተቀራርቦ ለመነጋገር የሚፈልግ እና በሌሎች ፓርቲ መሪዎች ሊታመን የሚችል እና
በተለያዩ ኃይሎች መካከል መቀራረብ መፍጠር የሚችል መሪያ ያስፈልገናል!

በመሆኑም የኢዜማ 1ኛ መደበኛ ጉባዔ የኢዜማን ዓላማ በኢዜማ ቀለም ማሳካት የሚችሉ እና
የሚፈልጉ መሪ/መሪዎች እንዲመርጥ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!

አንዱዓለም አራጌ
ሐብታሙ ኪታባ

20
21
Email: andualem4leader@gmail.com

You might also like