You are on page 1of 4

የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

welkait.com/

Freedom

ANDM CC office

ከብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማእከላዊ ኮሚቴ ነሃሴ 17 እና 18 ቀን 2010


ዓ.ም ለሁለት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በብአዴን 12ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ረቂቅ
ሪፖርትና ለጉበዔው በሚቀርቡ ሌሎች ወቅታዊና መደበኛ ጉዳዮች ላይ ተወያቶ የተለያዩ
ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ባለቤትነት በሀገር ደረጃና ብአዴን
በሚመራው የአማራ ክልል የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝና ታሪካዊ
ጊዜ ላይ የሚካሄድ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ድርጅቱ የመሪነት ሚናውን ከምንጊዜውም በላይ
አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ለጉባኤው እንዲቀርቡ ጥልቀት
ያለው ውይይት ካካሄደ በኋላ በጉበዔ አጀንዳወችና በሌሎች ጉዳዮች ስምምነት ላይ በመድረስ
የሚከተሉትን ውሳኔወች አስተላልፋል፡፡

1) በመቀጣጠል ላይ ያለውን ክልላዊና ሃገራዊ ለውጥ ለመጠበቅ፣ መሰረቱን ለማስፋትና


ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንዲቻል ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ
የለውጥ እርምጃዎች በተከታታይ ይወሰዳሉ፡፡ በዚህ ሂደት ብአዴን የደረስንበት መድረክ
የሚጠይቀውን ደረጃ ያሟላ ተመራጭ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ በመገኘት የክልሉን፤ ብሎም
የሃገራችንን ህዝብ የዲሞክራሲና የልማት ጥያቄወች ከፍ ባለ ደረጃና በዘላቂነት እየመለሰ
ግንባር ቀደም አታጋይ ድርጅት ለመሆን ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ለመላው የአማራ ህዝብ፣
ለድርጅቱ አባላትና አመራሩ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ያበስራል፡፡

2) የአማራን ህዝብ ታሪክ፣ ትግል፣ ባህል እና ስነ ልቦና በአግባቡ የተገነዘበና የተረዳ፣ እንዲሁም
አሁን ከተፈጠረው አዳጊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚራመድ የፖለቲካ ፕሮግራምና
መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ድርጅቱ ቀደም ሲል ሲመራበት
የነበረው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ የህዝቡንና የአባላቱን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ግለጽ
በሆነ ተሳትፎ እነዲሻሻል ይደረጋል፡፡ በዚህ ረገድ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የድርጅታችን አባላት
ጥያቄ እስከሆነ ድረስ የድርጅቱን ስያሜ ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በአግባቡ
እየተፈተሹ ሥርዐቱን በጠበቀ መንገድ ማሻሻያ ሊደረግባቸው እነደሚችል መዕ/ኮሚቴው
ያምናል፡፡

1/4
3) የአማራ ብሄርተኝነት በህብረ-ብሄራዊነትና በዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ አንድነት መርህ ለይ
ተመስርቶ እንዲገነባ ብአዴን በጽናት ይታገላል፡፡ በፌደራል ሥረዐቱ ውስጥ የህዝቦች እራስን
በራስ የማስተዳደር፣ የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነጻነት
የመስራትና የመኖር መብቶች ሁሉ በትክክለኛው ገጽታና በተሟላ መንገድ እንዲከበሩና
ኢትዮጵያ ለሁላችንም የተመቸች ሃገር እንድትሆን ብአዴን ከሌሎች እህት ድርጅቶችና
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ይሰራል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ
ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግስት አባላት የሆኑ ክልሎች አከላለል በህዝቦች እውነተኛ
ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ፣ ብዝሃነትንና ሃገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ መንግስቱን
መሰረት አድርጎ እንዲከለል እንታገላለን፡፡ ባለፉት የትግል ዓመታት ክልላችንን ጨምሮ በመላ
ኢትዮጵያ ለህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋትና ንበረት መውደም ምክንያት
የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄወች ትኩረት ተሰጥቷቸው በህዝብ ነጻ ተሳትፎ እንዲፈቱ
ብአዴን በምክነያት ለይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ትግል ያካሂዳል፡፡

4) የሃገሪቱም ሆነ የክልሉ ሕግጋተ መንግሥታት ዘመናዊ፣ ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት


ድንጋጌወችንና መሰረታዊ የዲሞክራሲ መብቶችን አሟልተው የያዙ፣ የዜጎች የቃል ኪዳን ሰነድ
እንደመሆናቸው መጠን ለህገ መንግሰታዊ መብቶች መከበር ብአዴን በጽናት ይታገላል፡፡ ከሩብ
ምዕተ ዓመት በላይ ማሻሻያ ሳይደረግበቸው የዘለቁት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌወቻችን ውስጥ
አንዳንዶቹ አገራችን ዛሬ ከደረሰችበት የዲሞክራሲ እድገት ደረጃ ጋር ተጣጥመው መሄድ
አለባቸው የሚለውን የህዝብ አስተያየትና ጥያቄ ብአዴን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል፡፡ ስለሆነም
እንዲህ አይነት ጥያቄወች ሕገ መንግስቱ ራሱ ያስቀመጠውን ሥርዐት ጠብቀው እስከቀረቡ
ድረስ የሚነቀፉበት ምክንያት የለምና ሕጋዊና ትክክለኛ ምላሽ አግኝተው በሃገራችን
የተጀመረው የዲሞክራሲ ስረዓት ግንባታ የበለጠ እንዲጠናከር ብአዴን በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡

5) የህግ የበላይነት መከበር ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ብአዴን በጽናት
ያምናል፡፡ እስካሁን በተካሄደው ትግል በዜጎች ለይ የተፈጸመን ማንኛውንም ሓላፊነት የጎደለው
ኢ-ሕገ መንግስታዊ ተግባር እያወገዝን በእንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ ገብቶ የተገኘ
ማንኛውም ቡድን፣ የመንግስት ባለስልጣንና ግለሰብ የሃገሪቱ ህግ በሚፈቅደው አኳኋን ለህግ
ቀርቦ ተጠያቂ እንዲሆን በጽናት እንታገላለን፡፡ ከዚህም በኋላ በሃገራችን ሰብአዊና
ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ እንዲከበሩ፣ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው ተዋርደው ሊኖሩ
እነደማይገባ፣ በዚህ ረገድ የሚፈጸምን ማነኛውንም ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊትም ውጉዝ
እንደሆነ ብአዴን አጥብቆ ያምናል፡፡ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ፈር ለማሳት የሚፈጸም
ማንኛውንም ሕገ ወጥ ተግባር በመታገል በሃገራችንና በክልላችን ዋስትና ያለው ዲሞክረሲ
እንዲገነባ ይደረጋል፡፡

6) የግለሰብና የቡድን መብቶች ተጣጥመው መከበር እንዳለበቸው እናምናለን፡፡ የግለሰብ መብት


ባልተከበረበት የቡድን መብት ቦታ እንደማይኖረው፣ የቡድን መብት ባልተከበረበትም የተሟላ
ዲሞክራሲ እነደማይኖር የታወቀ ነው፡፡ ሁለቱን መብቶች አጣጥሞ በመሄድ ረገድ ሕገ
መንግስታችን ብዙ እርቀት ተጉዟል፡፡ በመሆኑም በሃገራችን ትክከለኛ ዲሞክራሲ እንዲገነባ
ትልቅ መሰረት ተጥሏል፡፡ ይሁን እንጅ ባለፉት ዓመታት በሁሉም መስክ በቂ ሥራ
2/4
ካለመሠራቱም በላይ በተለይ ደግሞ ለቡድን መብት መከበር የተሰጠውን ትኩረት ያክል
ለግለሰብ መብትም ስላልተሰጠ የተጀመረው የቡድን መብት የማስከበር ሥራ ወደፊት
ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የግለሰብ መብት
በሚዛናዊነት የሚከበርበት ሥረዐት እውን እንዲሆን ይደረጋል፡፡

7) ብአዴን በውስጡ ጤናማ የሆነ የአመራር ቅብብሎሽ ሥርዐት ይኖር ዘንድ ለአመራር ግንባታ
ሥራ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ በተለይም አሁን እየታየ ያለውን ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃትና
ምርጥ ህዝባዊ መዕበል በእድልነት በመጠቀም በድርጅቱ ውስጥ በብቃት የተገነባ ብልህ፣ አርቆ
አሳቢና አስተዋይ ተኪ አመራር እንዲኖር የተማረውን ወጣት መዕከል ያደረገ የአመራር
ምልመላና ግንባታ ስራ ያካሂዳል፡፡ በአነጻሩም አሁን ከተደረሰበት የትግል መድረክና ከለውጡ
እንቅስቃሴ ጋር አብረው መጓዝ በተሳናቸውና ህዝባዊ ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት
ባልቻሉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ድርጅቱ ራሱን የማጥራት
እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የብአዴን 12ኛ ድረጅታዊ ጉበኤም ይህንኑ ግምት ውስጥ
ያስገባ ውሳኔ የሚተላለፍበት እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ለመላ አባላችንና አመራራችን ጥሪ
እናቀርባለን፡፡

8) ሁለተኛው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ በብቃት እንዲመራና በቀሪ ጊዚያት በሚሰራ


ስራ ያለፈውንም ማካካስ በሚችልበት ደረጃ ለይ እንዲደርስ ህዝቡን፣ ወጣቶችን፣ ባለሃብቱንና
ምሁራንን በማረባረብ ክልላዊና ሃገራዊ እድገት እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡

9) የመንግስት የልማት ድርጅቶች የክልሉ ህዝብ ያሉበትን ተጨባጭ የልማት ችግሮች እየፈቱና
ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው ስረዓት መመራት እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ በመሆኑም የጥረት
ኮርፖሬት እና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) የተባሉት የልማት ድርጅቶች የክልሉ
ህዝብ ሃብት እነደመሆናቸው መጠን የላቀ ልማት ማረጋገጥ በሚችሉበት አኳኋን መመራት
ስላለባቸው ተጠሪነታቸውም ለክልሉ መንግስት እንዲሆን የፖለቲካ ውሳኔ ተወስኗል፡፡
አፈጻጸሙም ሕጉን ተከትሎ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

10) በአሁኑ ሰአት የተፈጠረውን ምቹ ሃገራዊና ክልላዊ ሁኔታ በመጠቀምና የዲሞክራሲ


ምህዳሩን መስፋት እድል በማድረግ ሃገር ውሰጥ ከሚንቀሳቀሱም ሆነ ውጭ ሃገር በስደት
ቆይተው ከተመለሱ ተፎካካሪ ፓረቲወች ጋር በሚያለያዩን ጉዳዮች ተከባብረን አንድ
በሚያደርጉን ጉዳዮች አብረን ለመስራትና ዲሞክራሲን ለማስፋት ጽኑ ፍላጎት እንዳለንና በዚሁ
መሰረት ለመራመድ ወስነናል፡፡

11) በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድነበር ማካለል ጉዳይ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ
የሁለቱም ወገን አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻና የደን መሬት እንደያዙ እየተጠቀሙ እንዲቆዩ
በሁለቱ ሃገራት መንግስታት መካከል ስምምነት ተፈርሞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ
በተለይ በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ
መብታችንን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት
ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አውቀናል፡፡ ይህ ውሳኔ ብአዴንና አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ በህዝብ ዘንድ
ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው በፌደራል
3/4
መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት እንጠይቃለን፡፡ ለጋራ የጸጥታ ማሰከበር
ስራ ይጠቅማል የሚለውን ስምምነት ምክንያት በማድረግ በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ነፍስ ገበያ
በተባለው አካባቢ ለጊዜው ሰፍሮ የነበረው የሱዳን ወታደርም ይዞታ እያሰፋፋና ቋሚ ካምፕ
እየገነባ ከያዘው ጊዚያዊ ይዞታ ሳይለቅ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ መዕከላዊ ኮሚቴው
ገምግሟል፡፡ የካመፑም መኖር የድንበሩን ጉዳይ የበለጠ እያወሳሰበውና የክልሉ አርሶ አደሮችም
የእርሻ ስራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የሱዳን ወታደር
እስካሁን ድረስ ከያዘው ይዞታ ለቆ አለመውጣቱ ተገቢ ባለመሆኑ በፍጥነት ከይዞታችን ለቆ
እንዲወጣና የፌደራል መንግሥትም ይህንኑ እንዲያሰፈጽምልን እንጠይቃለን፡፡ ብአዴን
በክልላችን የሚገኘው ይህ የኢትዮ ሱዳን የድነበር ጥያቄ የነዋሪወችንና የአርሶ አደሮቻችንን
ይዞታ መሰረት አድርጎ፣ ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅና የሃገርን ሉዓላዊ ጥቅም ባስከበረ መንገድ
የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድበት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

12) ምሁራን የአማራ ክልልን የልማትና የመልካም አስተዳር ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው
ርብርብ የድርሻቸውን ለመወጣት እያሳዩ ያሉትን የጋለ ተሳትፎና ጥቁር መጋረጃውን የቀደደ
ሞያዊ ግዴታን የመወጣት ታሪካዊ ዘመቻ ከልብ እናደንቃለን፡፡ በዚህም አጋጣሚ የአማራ ህዝብ
በመላ፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የድርጅታችን አባላት ከብአዴን ጎን ቆማችሁ
ክልላችንና ሀገራችንን የመገንባት ጉዞ እንድትደግፉ ጥሪ እናቀርብላችኋለን፡፡

ለውጡን በመጠበቅ፣ በማጥለቅና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅዱን


እናሳካለን!!

የብአዴን መዕከላዊ ኮሚቴ፡፡

ነሃሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም


ባ/ዳር

4/4

You might also like