You are on page 1of 6

❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤

❤ ሰኔ ፲፪ (12) ቀን።

❤ እንኳን ለተባረከና ለተመሰገነ በሰማያት ያለ ምሥጢርን ለአየ፤ ዐሥር አስደናቂ ቤተ መቅደስን ከዐለት ላይ ላነፀ፤ ክብሩ
ልክ እንደ ሐዋርያት ለሆነ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለካህኑ ለቅዱስ ላሊበላ ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን።

+++

❤ ጻድቁ ካህኑ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ፦ ቅዱስ ላሊበላ ከአባቱ ከዐፄ ዛን ስዩም ከእናቱ ከልዕልት ኪሪዮርና በ 1101 ዓ.ም
ታኅሣሥ 29 ቀን በቤተ መንግሥ ተወለደ። ዐፄ ዛን ስዩም ከመንገሡ በፊት የዋግ ሹም ሆኖ ሲያስተዳድር ዑጽፍት ወርቅ
የምትባል ሴት አግብቶ ንጉሥ ቅዱስ ገብረ ማርያምና ዮዲት የምትባል ልጅ (ርብቃም) የሚሉ አሉ ከወለደች በኋላ
ዑጽፍተ ወርቅ ሞተች። ከዚህ በኋላ የክፍለ አገር ገዥ ከሆነው ረዳኢ ከተባለው የተወለደችውን ኪሪዮርናን አግብቶ
ቅዱስ ላሊበላን ወለደው። ቅድስት ኪሪዮርና ማለት ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው።

❤ ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ ጊዜ ነጫጭ ንቦች ሰፍረውበት እንደማር ሲልሱት እናቱ ስታይ በመደንገጥ "ላል ይበላል"
በማለት ተናገረች። ይህም በአገውኛ ቋንቋ ልጄን ንብ በላው ማለት ነው። በዚህ መሰረቴ ላልይበላል ተብሎ እየተጠራ
ሲኖር ከጊዜ ብዛት ላሊበላ ተብሏል። በነገራችን ላይ የተሳሳተ ትርጉም የያዙ አላዋቂዎች ላሊበላ ማለት ለማኝ እንደሆነ
አድርገው በአንዳንድ አካባቢዎች ይናገራሉ። ላሊበላ ማለት ግን ጣፋጭ የንስሃ ጋሻ የጽድቅ አባት ማለት ነው እንጂ ለማኝ
ለፍላፊ ማለት አይደለም።

❤ ከዚህም በኋላ እናትና አባቱ ልጃቸው ወደፊት ንጉሥ ሆኖ ብዙ ሰራዊት የሚከተለው ትልቅ ሰውና መንፈሰ
እግዚአብሔር ያደረበት መሆኑን በንቦች መክበብ በመረዳታቸው በ 40 ቀኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሰራዊትና ካህናት
ታጅበው በእልልታና በደስታ ዐፄ ካሌብ በአሰሩዋት ማይ ማርያም በተባለችው ቤተ ክርስቲያን የክርስትናውን ሥነ-
ሥርዓት አስፈጽመዋል። የክርስትና ስሙም ገብረ መስቀል ተብሏል። ቅዱስ ላሊበላ በቤተ መንግሥት ውስጥ ለነገሥታት
ልጆች እንደሚሰጥ እንክብካቤና ሥነ-ሥርዓት በጥበብና በሞገስ አደገ። ዕድሜውም ለትምህትተ ሲደርስ መምህር
ተቀጥሮለት ከፊደል እስከ ዳዊት የሚሰጠውን ትምህርት ያለማዳገም ከፈጣሪ በተሰጠው ፀጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ
ተማረ።

❤ በዚህም ላይ እንዳለ የበለጠ ፈጣሪውን ማገልገል በመፈለጉና በመምረጡ ቤተ መንግሥቱን ትቶ ትምህርቱን ለማሻሻል
ወደ ምድረ ጎጃም ሄዶ አሉ ከተባሉ መምህራን በተለይም መምህር ኬፋ ከተባሉ ምሁር አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን
ትምህርት ተምሮ ወደ ደብረ ሮሃ ተመልሶ ሥርዓተ መንግሥትን ወንድሙ ቅዱስ ገብረ ማርያም እያስተማረው ሳለ
ለምቀኝነት የሚያርፈው ሰይጣን በንጉሥ ባለሟሎች(አማካሪዎች) ላይ አድሮ የሁለቱን ፍቅር በጠሰው። ሰዎቹ ወደ
ንጉሥ ቀርበው "ንጉሥ ሆይ ሺህ ዓመት ንገሥ እነሆ ላሊበላ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን በማግኘቱ አስተባብሮ
ንጉሥነትዎን መንግሥቱ ሊቀማዎት ነውና እወቁበት" በማለት ነገሩት። ንጉሡም በነገሩ እጅግ ተቆጥቶ ወደ ማረፊያ
ቤቱ ገብቶ እንጀራ አልበላም ውሃም አልጠጣም ብሎም እንደ ንጉሥ ዓክአብ ተጨንቆ ተጠቦ ሳለ እህቱ "ንጉሥ ሆይ ልብህ
አይዘን አትጨነቅ ነገሩን ለእኔ ተወው" ብላ አረጋጋችው። ላሊበላ ግን ይህን ሁሉ ነገር አላወቀም ነበርና በንጹህ ልቦናው
በቤተ መንግሥቱ እንደ ተቀመጠ ከዕለታት አንድ ቀን ኮሶ ታይቶት መድኃኒት እንድታጠጣው ቂመኛ እህቱን ጠየቃት
እሷም የምታጠምድበትንና የምትገድልበትን ስታስብና ስትፈልግ ስለ ነበር ይህን አጋጣሚ በማግኘቷ ሀሳቡን ደስታ
ተቀብለችውና ኮሶውን አዘጋጅታ መርዝ ቀላቅላ አቀረበችለት። ከእርሱ ጋራ የሚኖር የማለየው አንድ ዲያቆን ነበር።
በባህሉም መሠረት ዲያቆኑ ቀምሶ ስለሚሰጥ ያንን ሲቀምሰው አስታወኮት ሞተ። የዲያቆኑንም ትውኪያ አንድ ውሻ
በመላሱ ሞተ። ከዚህም በኋላ ላሊበላ መንፈሱ ታወከ። ከባድ ሀዘንም አደረበት። "እናንተ ንጹሐን ለእኔ በታዘዘው
መቅሰፍት በመሞታችሁ እኔም የእናንተን መንገድ እከተላለሁ እንጂ ወደ ኋላችሁ ቀርቼ ነፍስ ገዳይ አልሆንም" አለና
በውስጡ ፍቃደ እግዚአብሔር ስላለበት ፈጣሪ ሚስጥር ሊገልጽለት በመፍቀዱ በጽዋው የተረፈውን መርዝ አንስቶ
ጠጣው። እርሱም ወዲያው ተዘረረና ወደቀ። በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት መጥተው ነፍሱን ወደ ፈጣሪ ወስዷት።
ሥጋው ግን ሙቀት ስላልተለየው ሰዎች ለመቅበር ቢሞክሩ እንደእሳት እየፈጃቸው ሦስት መዓልትና ሌሊት በሚደንቅ
ሁኔታ ተቀመጠ።

❤ ቅዱሳን መላእክት ሰባቱን ሰማያት አንድ በአንድ እያሳዩ ወደ ፈጣሪ ነፍሱን ከአቀረቧት በኋላ እግዚአብሔር አምላክ
"ወዳጄ ላሊበላ ሆይ የጠራሁህ እኔ ነኝ በማለት ወሰን የሌለውን ፍቅሩን ከገለጸለት በኋላ ሀይሉንና ጥበቡን በእርሱ ላይ
አሳድሮ "ከከርሰ ምድር አብያተ ክርስቲያናትን እንደሚያንጽና በኢትዮጵያ አገር ላይ አርባ ዓመት እንደሚነግሥ ሕዝበ
እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን በመመልከት ድኅነትን፣ በረከትን፣ ፀጋን፣ እንደሚያገኙ በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝቦች
ኢየሩሳሌምን ለማየትና ለመሳለም ሲሔዱ የሚደርስባቸው መከራና ሞት ደማቸው ከፊቴ በመጮሁ በእርሱ ሥራ
ኢየሩሳሌምን እንደሚያንፅና ለምን እንደሚሰራ ጥቅሙን በመግለጽ ይሰራ ዘንድ መመሪያ ሰጠው። ቅዱስ ላሊበላ ግን
ይህን ማድረግ እንማይቻለው ቢገልጽም አምላክ ከእርሱ ጋራ እንደሚሆን ብቻ "ስሙ በአንተ ይሁን እኔ ነኝ የምሰራው"
በማለት ገለጸለት። ከላይ እንደተገለጸው በድኑ መንፈስ ቅዱስ ሳይለየው እንደ እሳት ሰዎችን እየፈጃቸው ተጨንቀው
ተጠበው በሁኔታው በመገረም ለሦስት ቀንና ሌሊት እንዳሉ በሦስተኛው ቀን ነፍሱ ከሥጋው ተዋሕዶ ተነሳ።

❤ ቅዱስ ላሊበላም ከሰው ተለይቶ ከዘመድ ርቆ የሰው ድምጽ ከማይደርስበት ቦታ ሄዶ ሌት ከቀን በመጸለይ በጾምና
በጸሎት ተወስኖ ከአምላኩ ጋር በበለጠ ግንኙነቱን እያጠናከረ እንዳለ አንድ ቀን ፈጣሪ ቅዱስ ገብርኤልን ላከውና መልአኩ
ቅዱስ ገብርኤልም ላሊበላን "የእግዚአብሔር አገልጋይ ላሊበላ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን እንሆ እግዚአብሔር አምላክ
በኢትዮጵያ ላይ ካህንና ንጉሥ ሆነህ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃ ነህና በህገ አብርሃም ትወሰን ዘንድ ወዳንተ
መጣሁ ስለሆነም ነገ በአሁኑ ሰዓት የምትመጣ በድንቅ ሥራዋ አምላክን ያስደሰተች አንዳንተ የተመለጠች ቅድስት ሴት
ትመጣለችና እርሷን አግብተህ ልጅ ትወልዳለህና በሚያስደስት ቃል ተቀበላት" አለው። ቅዱስ ላሊበላ ግን ፍቃዱ
እንዳልሆነ ቢገልጽም የእግዚአብሔር ትዕዛዝ እንደሆነ በድጋሚ ሲነግረው ቃሉን ተቀበለው።

❤ እንደተባለውም በማግስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ እንደ ብርቱካን፣ መዝ፣ የመሳሰሉትን ፍራፍሬዎች ይዛ ወደ ቅዱስ
ላሊበላ ሄደች እርሱም በደስታ ተቀበላት። ከዚያም ነገረ እግዚአብሔርን ተነጋግረው ወደ ቤተሰቦቿ ወሰደችው።
ለቤተሰቦቿ መልአኩ በህልም ነግሯቸው ስለነበር በደስታ ተቀበሉት። በዚያም በፈቃደ እግዚአብሔር በሥርዓተ ቤተ
ክርስቲያን ጋብቻቸውን ፈጽመው በጾምና በጸሎት ተወስነው በመኖር ላይ ሳሉ ለምቀኝነት የማያርፈው ሰይጣን አሁንም
ፈተናውን አዘጋጅቶ ሶስናን በሐሰት ዝሙትን ፈጽማለች ብለው እንደወነጀሏት ሁሉ ቅዱስ ላሊበላንም "ከቤተ
መንግሥት ጠግቦ ወጥቶ የሰው እጮኛ ያባልጋል" በማለት ለንጉሡ ሹክተኞች ነገሩት። ንጉሡም ወታደሮችን ልኮ
አስመጣውና ቀኑም ዐርብ ቀን በመሆኑ እንዲገረፍ አዝዞ ወደ ቅዳሴ ሄደ። ዘጠኝ ሰዓት ላይ ወደ ቤቱ ሲሄድ የጅራፍ ጽምጽ
በመስማቱ "ምንድነው? የሚሰማው" ብሎ ባለሟሎቹን ሲጠይቃቸው "ቅዱስ ላሊበላ እየተገረፈ ነው" አሉት ንጉሡም
ወዲያውኑ እንዲያመጡለት አዘዘ። ሲመለከተውም በሰውነቱ ላይ ምንም የግርፈት ምልክት አላየበትም ንጉሡም ጻጽቅና
እውነተኛ መሆኑን ፈጣሪም ከግርፋትና ከጥፍት ከልሎታልና "እንኳንስ ሊሞት ግርፋቱ አልተሰማውም" በማለት እጅግ
አደነቀ። ከባድ ሀዘንም ተሰማው። "አምላኬን በድያለሁ የማይገባ ሥራ ሰርቻለሁ" ብሎ ቅዱስ ላሊበላ በሕዝቡ መካከል
"ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት ለአንተ ይገባል በግፍ አስገርፌሀለሁ በድዬሀለሁም ይቅር በለኝ" በማለት ከጫማው ወድቆ
ይቅርታ ከጠየቀው በኋላ መንግሥቱን አስረክቦ መንኖ ለመሔድ ወሰነ።

❤ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ቅዱስ ላሊበላም "ለይቅርታው ይቅር ብብያሁ ነገር ግነ መንግሥት የእግዚአብሔር
ገንዘብ ናትና መንግሥትህን የምቀበለው ከእግዚአብሔር እንጂ ከአንተ አይደለም አንተም በዙፋንህ መቆየት አለብህ እኔ
ግን መልካም ፈቃድ ከአምላኬ እስካገኝ ድረስ እጠይቃለሁ" ብሎ የዐፄ ገብረ ማርያም ጫማ ስሞ በፍቅር ተሰናብቶ ወጣ።
በዚህ ጊዜ ሕዝቡና "መንግሥትን ያህል ነገር እንደ ቀላል ነገር ቆጥሮ አልነግሥም ብሎ በመሄዱ እንዴት የእግዚአብሔር
መንፈስ ቢያድርበት ነው?" በማለት በችሎት ተቀምጦ ሁኔታውን በግብር ሲከታተል የነበረው ሁሉ እያለቀሱ ቅዱስ
ላሊበላን ተከትሎ ወጣ። ቅዱስ ላሊበላ ግን በአላማው ፀንቶ በሰዎቹ ፍቅር ሳይታለል እግዚአብሔር የሰጠውን ረዳቱን
ቅድስት መስቀል ክብራን ይዞ ወደ አክሱም ሄደ።

❤ በአክሱም አካባቢ በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም በጾምና በጸሎት ተወስነው ፈጣሪያቸውን እየተማፀኑ ሳለ ከእግዚአብሔር
የታዘዘ መልአክ መጥቶ "ሰማያዊ ኢየሩሳሌምን እንዳየህ ምድራዊት ኢየሩሳሌምንም አይቶ ህንፃ ቤተ መቅደሱን
በሰማያዊትና በምድራዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ያንፅ ዘንድ ኢየሩሳሌም ሔዶ የተወለደበት ቤተልሔም፣ የተጠመቀበትን
ዮርዳኖስ፣ የተሰቀለበትን ቀራንዮ፣ የተቀበረበትን ጎልጎታን፣ ደብረ ታቦርን ምስጢረ መለኮቱን የገለጸበትን አጠቃላይ ብዙ
ተአምራት ያደረገበትን ሁሉ እንዲያይና እንዲሳለም መልአኩም እንደሚመራው መስቀል ክብራ ግን በዚሁ ከደናግሎች
ጋር እንደምትቀመጥና ቅዱስ ሚካኤል እንደሚያጽናናት እንደሚጠብቃት መታዘዙን ነገረው።

❤ በዚህም መሠረት ቅዱስ ላሊበላ ወደ ኢየሩሳሌም በፈቃደ አምላክ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ጠባቂነት በሱዳንና
በግብጽ አድርጎ ኢየሩሳሌም ገባ። በዚያም ከላይ የተጠቀሱትን ቅዱሳን መካናትንና ሌሎችንም ቅዱሳት ስፍራዎች
ለዐሥራ ሦስት ዓመታት በመዘዋወር ተመለከተ። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ የጉብኝቱንና የተፈቀደለትን ጊዜ ሲፈጸም
አሁንም መልአኩ ተገልጾ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሄደ መንግሥትን ከዐፄ ገብረ ማርያም ተረክቦ የታዘዘውን እንዲሰራና
በመንገድ በግብጽ ምድር የተበተኑትን ወገኖችን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ እንዲሄድ የታዘዘ መሆኑን ገለጸለት። ቅዱስ ላሊበላም
በፈቃደ አምላክ በግብጽ ያሉትን ክርስቲያኖች ሰብስቦ በጊዜው የነበረው የግብጽ መንግሥት የእስላም ሃይማኖት ተከታይ
በመሆኑ እንዴት አድርጎ እንደሚያስተዳድራቸው ጠየቃቸው። ክርስቲያኖቹም እግዚአብሔርን ማምለክ እንደተከለከሉና
በሀዘን በሰቀቀን የሚኖሩ መሆናቸውን ገለጹለት። በዚህ ዘመንም በመካከለኛው ምሥራቅ 3 ኛው የመስቀል ጦርነት
በመኖኑ ግብጻውያን ፊታቸውን ወደዚያ አዙረው ስለነበር ቅዱስ ላሊበላ በፈቃደ አምላክ በርካታ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ
ኢትዮጵያ መጣ።

❤ ዐፄ ገብረ ማርያም ወንድሙ ቅዱስ ላሊበላ ሕዝበ ክርስቲያንን ይዞ የኢትዮጵያ ምድር እንደረገጠ በሰማ ጊዜ በክብር
የሚቀበሉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰራዊት አሰልፎ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣ ላከበት። ቅዱስ ላሊበላም ከባለቤቱ
ጋር እና ከሕዝቡ ጋር በአክሱም ስለነበር የእግዚአብሔር ፍቃድ እንደሆነና ጊዜም እንደደረሰ በማወቁ ልዋል ልደር ሳይል
ወደ ቤተ መንግሥቱ መጥተ ከዐፄ ገበረ ማርያም ጋር ተገናኘ። ንጉሡ ዐፄ ገብረ ማርያም ቅዱስ ላሊበላ ወደ እርሱ
መምጣቱን በሰማ ጊዜ በፍቅር እንባ ተቀበለውና ሕዝቡን ሰብስቦ አዋጅ ነግሮ "እንሆ የአምላክ ፈቃድ ደርሷል መንግሥት
ለዚህ ቅዱስ ሰው ይገባል ብሎ ዙፋኑን ለቅዱስ ላሊበላ አስረክቦ ተሰናብቶ ዛሬ ቅዱስ ሐርቤ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳም
ዘግቶ በጾም፣ በጸሎት፣ በቀኖናና በንስሐ ሰውነቱን ለፈጣሪው አስገዝቶ በክብር የካቲት 16 ቀን ዐርፎአል።

❤ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ ንጉሥ ነኝ ብሎ ሳመካ ስልጣኑን ለሕዝቡ በመስጠት ሕዝቡን ይመራ ነበር። ሕዝቡም
የቅዱስ ላሊበላን የሃይማኖት ጽናትና ደግነት እያየ "ይህን ጻድቅ ንጉሥ ዕድሜውን አርዝምልን" እያሉ ይጸልዩለት ነበር።
የቅዱስ ላሊበላን ደግነት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ በውጭም ያሉ ነገሥታትና ሕዝብ ጭምር ያውቁ
ነበር በዚህም መሰረት እስላሙም ክርስቲያኑም ቅዱስ ላሊበላን አንስተው አይጠግቡም ነበር። በቅዱስ ላሊበላም ዘመነ
መንግሥት ጊዜ ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ያላት ግንኙነት የሰላም፣ የፍቅር፣ የክብርና የደስታ ግንኙነት ነበራት ለዚህም
ነበር 1189 ዓ.ም አካባቢ ሳላህ አዲን የተባለው የእስላም ንጉሥ በሦስተኛው የመስቀል ጦርነት ኢየሩሳሌምን በያዘ ጊዜ
ከክርስቲያን ቅርሶች ዋና ዋናዎቹን በጎልጎታ በሚገኘው በጌታችን መቃብር አጠገብ ያለውን ዕሌኒ ንግሥት ቅዱስ
መስቀሉን ያስወጣችበት ዋሻና በቤተልሔም ጌታ የተወለደበትን ጎል (በረት) ለቅዱስ ላሊበላ በስጦታ ያበረከተው።

❤ የቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶች አሰራርና ፍጻሜ፦ ቅዱስ ላሊበላ በዘመኑ ይህን ድንቅ ሥራ የሰራው ጮማ በመቆራረጥ
ጠጅ በማማረጥ ልብስ መንግሥትን ለብሶ በመሽሞንሞን አልነበረም። ለአንዲት ደቂቃ መንፈስ እግዚአብሔር
ያልተለየው ቅዱስ አባት ነበር። ፈጣሪው የሚመሰገንበትን የእርሱም ስም ለዘላለም የሚጠራበትን ቤተ መቅደስ
ለማነፅም ሱባኤ ገብቶ ቦታው የት እንደሆነ ተረዳ። ነገር ግን የተገለጸለት ቦታ ቀይት የምትባል ባላባት ትኖርበት ነበር።
ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሌላ ቦታ ሰጥቶ መጠቀም ይችል ነበር። ግን የትሕትና አባት ነውና መብቷን ሳይነካ እራሱን ዝቅ
አድርጐ "ቦታውን ለሥራ ፈልጌዋለሁና በገንዘብ ሽጭልኝ" አላት። እርሷም እጅግ ከፍ ያለ ገንዘብ ጠየቀችው። ይኸውም
አርባ ጊደር ላም መግዛት የሚችል ገንዘብ ነበር የጠየቀችው እርሱም ምንም ምን ሳይል ወርቁን ከፈላት። ቀይትም
ገንዘቧን ተቀብላ ሔደችና እንደገና ተመልሳ "የምኖርበት ቦታ ስጠኝ" አለችው። እርሱም "ወደፊት ሌላ ቦታ እስክሰጥሽ
በዚህ ቆይ" ብሎ ዛሬ ቆይታ የምትባለውን ቦታ ሰጣት ከዚህም የተነሳ ከግዜ ብዛት የቦታው መጠራያ ስም ቆይታ ተባለች።
ይህች ቦታ የምትገኘው ከላሊበላ ከተማ በስተ ምሥራቅ በግምት ሁለት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው። ለዚህ ነበር አባቶቻችን
ንጉሥ ላሊበላ በአንጡራ ገንዘቡ የገዛውን ቦታ ስለሆነ በቦታው የሃይማኖት ሸቃጮች የሃይማኖት ሸቀጥ አያካሂዱበትም
በማለት ለመስዋዕትነት የተዘጋጁት አሁንም ቢሆን ወደፊትም በዚህ ዙሪያ ላይ መናፍቅ ቦታ እንደሌለው ሊያውቅ
ይገባል።

❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ላሊበላ የህንፃ ሥራውን ለመጀመር ቦታው ጫካ ስለነበር በሰፊው የማጽዳት ዘመቻ ካካሄደ በኋላ
የት ቦታ መጀመር እንዳለበትና የማንን ቤተ መቅደስ መጀመሪያ እንደሚሰራ እንደገና በሱባኤ ለፈጣሪው ጥያቄ አቀረበ።
በጥያቄው መሠረትም ቅዱስ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ እንዳየው የወርቅ መሰላል ከሰማይ እሰከ ምድር የብርሃን አምድ
ተተክሎ ዛሬ ቤተ ማርያም ካለችበት ቦታ አርፎ መላእክት ሲወጡበት ሲወርዱበት ቅዱስ ላሊበላ አየ።

❤ ቅዱስ ላሊበላ ሥራውን ከዚህች ቦታ እንደሚጀምርና መጀመርያ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን እንደሚሰራ አወቀ
በዚህም መሰረት በመጀመርያ ደረጃ ቤተ ማርያም ሠራ። ከዚያም ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ መስቀልን፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ
ጊዮርጊስ፣ቤተ ገብርኤል ወቤተ ሚካኤል፣ ቤተ መርቆሬዎስ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ አባ ሊባኖስ። እነዚህን ቤተ መቅደሶች
መንፈስ ቅዱስ ጥበብን ገልፆታልና ግድግዳውን፣ ጣራውን፣ በሩንና መስኮቱን፣ አእማዱን ቅኔ ማህሌቱን ልዩ ልዩ ቅርፅ
እያመጣ እያስጌጠና እያሳመረ ከመላዕክት ጋር እመቤታችን እየተራዳችው በ 23 ዓመት በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ እነዚህን
አስደናቂ ቤተ መቅደሶች ሰርቶ አጠናቀቀ።

❤ ቅዱስ ላሊበላ የአነፃቸው አብያተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በውጭም አገር ብዙ እንደሆኑ ታሪኩ ይገልጻል። ከብዙዎቹ
ጥቂቶቹን እንደ ምሳሌ ብንመለከታቸው፦ አዲዲ ማርያም፣ አሸተ ማርያም ጀምሮ ነበር፣ ሶማልያ መቅደስ ማርያምን
(መቃዲሾ ውስጥ) ብዙ የተጀመሩና ተሰብስበው አገልግሎት የሚሰጡ በኢትዮጵያ ብቻ 23 እንደሚደርሱ ታሪክ ያወሳል።

❤ ቅዱስ ላሊበላ መዋዕለ ዘመኑን በሰላም፣ በፅኑ፣ በእምነት፣ በፍቅርና በአንድነት ከአሳለፈ በኋላ ንግስናውን ለወንድሙ
ልጅ እንዲሁም ለአሳደገውና በረከቱን ለሰጠው ለቅዱስ ነአኵቶ ለአብ አስረክቦ በጾም በፀሎት ተወስኖ ኖረ። ከዚህም
በኋላ የሚያርፍበት ጊዜ ሲደርስ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብርሃን ሠረገላ ተቀምጦ የሚአስፈራ
መብረቅን ተጐናጸፎ አእላፋት ሠራዊቶቹ ዙሪያውን ሁነው ወደርሱ መጥቶ እንዲህ አለው "ወዳጄ ላሊበላ ሆይ ሰላም
ይሁንልህ እኔ በማይታበል ቃሌ እነግርሃለሁ ማደሪያህ ክብርር ሁሉ ከከበሩ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያቶቼ ጋራ ይሁን።
በጸሎትህና በቃልኪዳንህ ለሚታመን እምነቱ እንደ ቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ደም መፍሰስ ይሆንለታል።

❤ ወደ ቤተ መቅደስህም የሔደ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደሴ እንደ ሔደ ይሆንለታል መቃብርህንም የተሳለመ


የሥጋዬን መቃብር እንደ ተሳለመ ይሆንለታል በዓመታቱ ወሮች ሁሉ የተራቡትን እያጠገበ፣ የተጠሙትንም እያጠጣ
መታሰቢያህን የሚያደርግ እኔ የተሠወረ መና እመግበዋለሁ የሕይወት ጽዋንም አጠጣዋለሁ። በመታሰቢያህ ቀንም ዕጣን
ወይም ስንዴ የሚያገባውን እኔ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በውስጠኛው መጋረጃ አስቀምጬ ከተቆረሰው ሥጋዬ
አቆርበዋለሁ፤ በአማላጅነትህም እየታመነ የገድልህንና የቃል ኪዳንህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ያንተ ስም በተጻፈበት ቦታ
እኔ ስሙን እጽፋለሁ፣ በፍጹም ልቡ ለሚያምን ይሁን የማይታበይ ቃል የተናገርኩ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እኔ ኢየሱስ
ክርስቶስ ነኝ" አለው።

❤ ቅዱስ ላሊበላም ይህን ቃል ኪዳን ስለ አጸናለት ክብር ይግባውና ጌታችንን እያመሰገነ በምድር ላይ ወድቆ ሰገደ።
ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቶት በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ። ከዚህም በኋላ ጥቂት ሕማም ታሞ ሰኔ 12 ቀን በ 1197
ዓ.ም በ 96 ዓመቱ በሰላም ዐረፈ። ሲያርፍም ደገኛው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር ነገራተ እግዚአብሔርን
እየተነጋገሩ እንዳለ ድንገት እንደ እንቅልፍ ሸለብ አድርጎት እንደሆነ ታሪኩ ይገልፃል። ነፍሱንም የብርሃን መላእክት
ተቀብለው የዘላለም ሕይወት ማደሪያ ወደሆነ ማረፊያው አስገቡት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ
ላሊበላ በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ የሰኔ 12 ስንክሳርና ቅዱሳንና ድንቅ ሥራቸው የአራቱ ቅዱሳን ነገሥታት ታሪክ
ከሚለው መጽሐፍ።

+++
❤ "ሰላም ለላሊበላ ሐናፄ መቅደስ በጥበብ። በዕብን ይቡስ መሬት ርጡብ። ነሢኦ መባሕተ እምእግዚአብሔር አብ።
በዘይትአመር ሎቱ ምስፍና ወምግብ። ወዝንቱ መዐር ተድላ ነገሥት ወሕዝብ። በዕለተ ተወልደ ተዐግተ በንህብ"። ሊቁ
አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 12።

@sigewe

You might also like