You are on page 1of 2

ለቤተ መጻሕፍትዎ

የኢትዮጵያ ታሪክ
(፲ ፭፭፭፻፺፯–
፭፭፭፻፺፯–፲ ፮፻፳፭)
የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል
ትርጉም፡- በዓለሙ ኃይሌ (2005ዓም)
ዋጋ፡- 45 ብር

ይህ የዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል ለብዙ ዘመናት በግእዝ ተጽፎ የኖረ ነው፡፡ በርግጥ የውጭ ሰዎች በተለይም
አውሮፓውያን በየቋንቋቸው ሲተረጉሙት ኖረዋል፡፡ ‹በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት› ሆነና አማርኛ አንባቢዎች
ግን አሁን ማግኘታቸው ነው፡፡ በዚህም አቶ ዓለሙ ኃይሌ ይመሰገናሉ፡፡ ከዚህ በፊት ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ
ባለሥልጣን ተርጉመዋቸው በመሥሪያ ቤቱ በኩል የታተሙላቸው ሁለት ዜና መዋዕሎች አሏቸው፡፡ የዐፄ ሠርጸ
ድንግል እና የዐፄ ገላውዴዎስ ዜና መዋዕሎች፡፡ በእነዚህ ቀደምት ሁለት መጽሐፎቻቸውም ሆኑ በሚገኙባቸው
መድረኮች ሁሉ ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍና ስለ ጥንታውያን ዕውቀቶች በተቆርቋሪነት መንፈስ ሲገልጡ
ታገኟቸዋላችሁ፡፡ ይህ ቁጭታቸውም ሳይሆን አይቀርም ይህንን የሱስንዮስን ዜና መዋዕል ያስገኘው፡፡

የሱስንዮስ ዜና መዋዕል በዋናነት አራት ነገሮችን የያዘ ነው፡፡

የመጀመርያው የመንግሥቱ መቀመጫ በግራኝ አሕመድ ወረራና በመካከለኛው ዘመን መጨረሻ በተከሰተው
የኦሮሞ ሕዝብ ፍልሰት ምክንያት ወደ ጎንደር ካመራ በኋላ የነበረውን የሥልጣን ትግል ያሳየናል፡፡ የጎንደር ሥርወ
መንግሥት መሥራች በሆነው በሠርጸ ድንግል ልጆችና ወራሾች መካከል ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣
ሃይማኖታዊና ወታደራዊ ትግግሎች ነበሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሱስንዮስ የ‹አማራ› እና የ‹ኦሮሞ›ን ጦር አስተባብሮ
የጎንደርን መንበር ሊቆናጠጥ የበቃው፡፡

በሁለተኛነት የምናየው የኢትዮጵያውያንን የውሕደትና የቅልቅል ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ጎኑ ከኦሮሞ የሚወለደው
ሱስንዮስ ያደገውና በሕይወት የተረፈው በኦሮሞዎች ተማርኮ በኦሮሞ ባህል መሠረት ነው፡፡ በኋላም ጎንደር ድረስ
ዘምቶ መንበር ለመያዝ የበቃው ኦሮሞንና አማራን አስተባብሮ አሰልፎ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ዋናው ነገር ፖለቲካዊና
ሃይማኖታዊ ነገር ስለሆነ አማራና ኦሮሞ አንድ ሆኖ ጎንደርን ሲወጋ፣ እንደገና አማራና ኦሮሞ አንድ ሆኖ ኦሮሞን
ሲወጋ እናየዋለን፡፡ ጦርነቱ የፖለቲካና የጥቅም እንጂ የዘር አልነበረም፡፡

በደቡቡ ክፍል ከዳሞት እስከ ግንደ በረት የነበሩት አማሮች ኦሮሞ ሆነው እንደቀሩት ሁሉ ሱስንዮስን ተከትለውም
ሆነ በወረራ አሸንፈው ጎጃም፣ ጎንደር፣ ትግራይና ኤርትራ የገቡት ኦሮሞዎችም አማሮችና ትግሮች ሆነው
ቀርተዋል፡፡ እንዲያውም ሱስንዮስ ከተወቀሰበት ምክንያቶች አንዱ ከሸዋ የተከተሉትን ኦሮሞዎች የቤተ ክርስቲያንን
ሰፊ መሬት ሳይቀር እየወሰደ በጎጃምና በጎንደር ስላሠፈራቸው ነበር፡፡
በጎንደርና በላስታ የነበሩት አማሮች በመንግሥቱ ላይ ሲሸፍቱ ጎንደር ሸፈተ፣ ላስታ ሸፈተ እያለ ኦሮሞና አማራ
አንድ ሆኖ እንደሚወጋቸው ሁሉ፣ በደቡብ የነበሩት ኦሮሞዎች ሲገፉበትና ሲሸፍቱትም ኦሮሞ ሸፈተ እያለ ኦሮሞና
አማራ አንድ ሆኖ ነበር የሚዋጋው፡፡

ይህ ከሠርጸ ድንግል ዘመን የቀጠለው የመስተጋበር ሂደት ነው የዛሬዋን ኢትዮጵያ የፈጠራት፡፡ ለዚህም ነው
ታዋቂው ሰሎሞን ዴሬሳ ስለ ማንነቱ ሲጠየቅ ‹በቅድመ አያቴ ደጅ ማን እንደሄደ አላውቅም› የሚለው፡፡ የዐፄ
ሠርጸ ድንግልን ዜና መዋዕል ስናነበው ኦሮሞዎች እስከ ኤርትራ ከሠርጸ ድንግል ጋር ዘምተው ቱርክን ከኤርትራ
ለማባረር መሥዋዕትነት ሲከፍሉና ከፊሎቹም እዚያው ኤርትራና ትግራይ ተሸመውና ተሠርተው ሲቀሩ እናያለን፡፡

እነዚህን ዜና መዋዕሎች የሚያነብ ሰው ዛሬ የምንወዛገብባቸው ማንነቶች ራሳችን ለፖለቲካ እንዲያመቹን


የፈጠርናቸው እንጂ የተሠራንባቸው አለመሆናቸውን ያያል፡፡ የሱስንዮስን ዜና መዋዕል ከምዕራፍ 23 እስከ 100
ያለውን የጻፉት አዛዥ ተክለ ሥላሴ (አዛዥ ጢኖ የተባሉት የኦሮሞ ተወላጅ) ታሪኩን ሲጽፉ ኢትዮጵያዊነት እንጂ
የዘር ስሜት አይታይባቸውም፡፡

ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያን ከግራኝ ወረራ በኋላ ሲያምሳት የነበረው የፖርቹጋል ካቶሊኮች ጉዳይ
አጀማመሩንና አጨራረሱን በመጽሐፉ የምናገኝ መሆናችን ነው፡፡ በርግጥ ጸሐፊዎቹ የንጉሡ ዜና መዋዕል
ጸሐፊዎች በመሆናቸው ለዚህ ጉዳይ እምብዛም ትኩረት አልሰጡትም፡፡ ልክ በዐምደ ጽዮን ዜና መዋዕል ላይ
ከአበው ጋር የነበረውን ግጭት እንደማናየው ሁሉ፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ለነገሮች ዝርዝር መረጃ ይሰጡናል፡፡

በሱስንዮስ ዜና መዋዕል ላይ በኢትዮጵያ ጥናት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችም አሉ፡፡ በአኩስም ያከበሩትና በውጭ
ሰዎች ሳይቀር እጅግ የተደነቀው ሥርዓተ ንግሣቸው፡፡ አንዳንድ ማኅበረሰቦች ከሕዝቡ የተለየ ምግብ መብላታቸው
ወደ ክርስትና እንዳይመጡ እንደማይከለክላቸው ማወጃቸው፤ እንደገና ራእየ ዮሐንስን ከላቲን ወደ ግእዝ
ማስተርጎማቸው፤ የባርያ ንግድን ለማስቆም ያደረጉት ትግል፤ ሀገሪቱን ለማዘመን ያደረጉት ጥረት፤ በዚሁ ዜና
መዋዕል ውስጥ ይታያል፡፡

መጽሐፉን የሚያነብ ሰው የዚያን ዘመን ባሕልና ቦታ ዛሬ ባለው ሁኔታ እንዲረዳው ለማድረግ ተርጓሚው በግርጌ
ማስተዋሻ ማብራርያ በመስጠት ያግዙናል፡፡ በመግቢያ ጽሑፋቸውም አጠቃላዩን ሁኔታ ከሀገሪቱ ታሪክ አንጻር
እንድንገነዘበው ሰፊ ሐተታ ያቀርቡልናል፡፡

አቶ ዓለሙ ኃይሌ ለሰጡን ስጦታ እግዜር ይስጥልን እያልን፤ ዕድሜ ሰጥቶዎት ሌሎችንም ለመተርጎም እንዲችሉ
እንጸልያለን፡፡

መልካም ንባብ፡፡

You might also like