You are on page 1of 3

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መስከረም 02 ቀን የሚነበብ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤል ድርሳን ይህ ነው፡፡ ልመናውና በረከቱ ከኛ
ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

እግዚአብሔር ያለእኔ ሌላ አምላክ አታምልኩ አለ፡፡

ዳግመኛም እንዲህ ብሏል፤ በእኔ ትእዛዝ ሰማይና ምድር ጸንተዋል፡፡ ፍጥረትም ሁሉ በእጄ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከእኔ በቀር
ተራራውን፣ ኮረብታውን፤ እንጨቱን፣ ደንጊያውን፣ ባሕሩን፣ ወንዙን ብታመልኩ ሊያድኗችሁ አይችሉም፡፡ አያዩም፤
አይሰሙም፤ አያድኑምና፡፡ በቁጣዬ ብይዛችሁ ከእጄ መውጫ ማምለጫ የላችሁም፡፡ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ
ባለጸጋ ንጉሥ እንደ ነበር አልሰማችሁምን? የሚያመልካቸው ጣዖቶቹም- “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ የምትሞትበት ቀን ደረሰ፡፡
ሠራተኞች ጠርተህ ሣጥን ይሥሩልህ፤ በውስጡ ትሰወር ዘንድ፡፡” አሉት፡፡ ያን ጊዜ ሣጥን ይሰሩለት ዘንድ ሰራተኞች ጠራ፡፡
ንጉሥ ነውና በዚያች ቀን መልአከ ሞቱ እንዳያገኘው በውስጡ ተሰውሮ ከባሕር ገባ፡፡ የሞት መልእክተኛ መጥቶ ፈለገው፡፡
አላገኘውም፡፡ ባጣውም ጊዜ እኔ አላገኘሁትም ብሎ ወደ እግዚአብሔር ተመለሰ፡፡ እግዚአብሔርም ባሕርን በቁጣዬ
እንዳልገርፍሽ ይሄን ባለጸጋ አውጪው አላት፡፡ ያንጊዜም ከውስጧ ወደ ዳር አወጣችሁ፡፡ እንደ ደንጊያም ወደዳር
ወረወረችው፡፡ መልአከ ሞት መጥቶ መውጫ ወደ ሌላት የሚነድ እሳት ወዳለባት መከራ ወሰደው፡፡ እናንተም እንደዚሁ
ሌሎች አማልክትን ብታመልኩ፣ ተድላ ደስታችሁ ይጠፋል፡፡ ስጋችሁም በእውነት እንደ ሰም ይቀልጣል፡፡ እግዚአብሔር
እጅግ ከሁሉ በላይ የሚያስፈራ ገናና ነውና፡፡ ከፊት እስከ ኋላ አኗኗሩን ባሕርይውን መርምሮ የሚያውቅ የለምና፡፡

በሆዷ የተሸከመችው ማርያምም- “አየሁት፤ ልረዳው አልቻልኩም፡፡” አለች፡፡

በደመና ምሰሶ ያየው ሙሴም- “አየሁት ልረዳው አልቻልኩም፡፡” አለ፡፡

በውሀ ያጠመቀው ዮሐንስም- “አየሁት ልረዳው አልቻልኩም፡፡” አለ፡፡

ኢሳይያስም- “እኔ የእሳት የሆነ ዙፋኑን አየሁ፤ አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡” አለ፡፡

ዮሐንስም- “ሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ሳያቋርጡ ዙፋኑን ያጥናሉ፤ በእውነት ልረዳው አልቻልኩም፡፡” አለ፡፡ እኚህም
አለቆች የአብን ትእዛዝ የሚቀበሉ የሚፈጽሙ ባለሟሎች ናቸው፡፡ ከሙሽራው ዙፋን ፊትም ለዘለዓለሙ ዘወትር
አይለዩም፡፡ ከሱ ጋርም ደስ እያላቸው ይኖራሉ፡፡ ዘወትር ከእጃቸው ማዕጠንት ከአንደበታቸውም ምስጋና ጸሎት
አይለይም፡፡ ይኸውም የቅዱሳን ጸሎት ነው፡፡ በየሰዓቱ እጣኑን ያሳርጉለታል፡፡ ከንፈራቸው የተንቀሳቀሰበትን ዋጋቸውን
ክብራቸውን ይሰጣቸዋል፡፡ እናንተም መታሰቢያቸውን ብታደርጉ፣ በማዕጠንታቸው ጊዜ ያስቧችኋል፡፡ አንድ አምላክ
ከሚሆን ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ በቀር ደስ ብሎት ደስ የሚያሰኝ ማነው? በየዕለቱ ዋጋን ሹመትን ክብርን
ጌትነትን ዘወትር የሚሰጥ ማነው? አያሳፍራቸውም፡፡ የነገሩትን ፈጥኖ ይሰማቸዋል፡፡ የለመኑትንም ሁልጊዜ
ይሰጣቸዋል፡፡ በቃልኪዳናቸው ያመናችሁ እናንት ሕዝበ ክርስትያን ስለናንተ በሚማልዱበት ጊዜ ቸል አይላቸውም፡፡
እናንተም በሚቻላችሁ መታሰቢያቸውን ማድረግን አትርሱ፡፡ ለቅዱሳን ርስት ሆና ወደተሰጠችው ወደ እግዚአብሔር
መንግስት ትገባላችሁ፡፡ ሚካኤልና ገብርኤል፣ አርባዕቱ እንስሳ እና ሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በሰማይ ወደለመኑላችሁ
ማደሪያ፡፡

እግዚአብሔርም “ሚካኤልና ገብርኤልን፣ አርባዕቱ እንስሳ እና ሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይን ፈጽማችሁ አክብሯው፡፡”
ብሏል፡፡ “በእኔ ዘንድ ከነሱ የሚከብር የለምና በንጹሕ ልቦና በዓላቸውንና መታሰቢያቸውን አድርጉ፡፡ በመከራችሁ ቀን
ፈጥነው ይረዷችሁ፣ ያድኗችሁ ዘንድ በመታሰቢያቸው ቀን ስማቸውንና የፈጣሪያቸውን ስም ጠርታችሁ
ዕጣኑን፣መስዋዕቱን አቅርቡ፡፡ የሚካኤልን፣ የገብርኤልን፣ የአርባዕቱ እንስሳንና የሐያ አራቱን ካህናተ ሰማይ ስም ብትጠሩ
በእኔ ዘንድ ዋጋችሁ አይጠፋም፡፡ ተስፋችሁ አይበላሽም፡፡ በሰማይ የሕይወት እንጀራን ትመገቡ ዘንድ ከእንጀራችሁ
ለነዳያን አብሉ፡፡ በሰማይ የሕይወት መጠጥ ትጠጡ ዘንድ ከምትጠጡት ለተጠሙት አጠጡ፡፡ በሰማይ የማያረጅ
የማይለወጥ የክብር ልብስ ትለብሱ ዘንድ ከምትለብሱት ለታረዘ አልብሱ፡፡ በሰማይ የሕይወት ምግብን ትጠግቡ ዘንድ
ለተራቡት አጥግቡ፡፡ ቢኖርህ ስጥ፤ ባይኖርህ አስብላቸው፤ ጸልይላቸው፡፡ ይኸውም ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርልሃል፡፡ በሚካኤልና
በገብርኤል፣ በሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይና በአርባዕቱ እንስሳ ስም እስከ ግማሽ እንጀራ የሰጠ ዋጋውን አያጣም፡፡
እንግዶችን በቤቱ የተቀበለ፣ ቁራሽ እንጀራ የሰጣቸው፣ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ያጠጣቸው ቢኖር ቅዱሳን መላእክት ዘወትር
ስለእርሱ ከመጸለይ አያርፉም፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን በሰማያት በሕይወት መጽሐፍ ይጽፈዋል፡፡ ለሚወዱት
ያዘጋጀውን ርስትም ያወርሰዋል፡፡ በወንጌል “ስጡ ይሰጣችኋል” ያለውን አልሰማችሁምን? መጽሐፍ እንዲህ
አላላችሁምን? በምድር ምሕረት ያላደረገ ሰው በሰማይ ምሕረት የሚያደርግለት የለም፡፡ በምድር ያልመጸወተ ሰው
በሰማይ የሚመጸውተው የለም፡፡ በምድር ማደርያ ያልሰጠ በቁርጥ ፍርድ ቀን በሰማይ ማደርያ የሚሰጠው የለም፡፡
በምድር ንስሐ ያልገባ በሰማይ ንስሐ የለውም፡፡ በስንፍናው ነፍሱን የሚያጠፋ ሰው ወዮለት፡፡ በሕይወቱ ሳለ በዚህ ዓለም
በጎ ካላደረገ በዚህ ዓለም ያልሰጠው ገንዘብ ምን ይጠቅመዋል? የሚሞትበትን ቀን አያውቅምና፡፡ ገንዘቡንም ከርሱ ጋር
አይወስድምና ነፍሱም የነበራትን አጥታ ራቁቷን መላእክት በሚነድ እሳት እየገረፏት እየፈራች እየተንቀጠቀጠች ወደ
ምድርና ወደ ሰማይ ንጉሥ ወደ እግዚአብሔር ፊት ትደርሳለችና፡፡ ሳታስረጀን ይህችን ምድር እኛ እናስረጃት፡፡ ከሷ
ወጥተናል፤ ወደሷም እንመለሳለን፡፡ ሁላችንም ወደርሷ እሄዳለንና፡፡ ይህች የተናቀች ዓለም አላፊ ጠፊ ናትና፣ እንደ
ተውሶ ልብስም ናትና ምድራዊ ንብረትም እንደ ጥላ ታልፋለች፡፡ በምድር የተፈጸመ ደስታ ሁሉ ብላሽ ነው፡፡ ለዘለዓለሙ
ማደርያችን፣ መኖርያችን ፣ መመለሻችን ከዚያ ነውና፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ ፍዳ የምትቀበሉበት ቀን ሳትደርስባችሁ
ስለራሳችሁ እዘኑ፤ አልቅሱ፡፡ ወዳጆቼ ወንድሞቼ እስቲ እናንተ አስቡት፤ አስተውሉት፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን፣ የከበሩት
ታላላቆች ነገሥታት መኳንንት፣ ሕጻናቱና ሽማግሌዎቹ በወርቅ በብር ዋጋው ብዙ በሆነ በከበረ ልብስ ሲያጌጡ የነበሩ
ሴቶች ወዴት አሉ? እናንተም እንደነርሱ ትሞታላችሁ፡፡ የዚህን ዓለም ኑሮም ትተዋላችሁ፡፡ ኃላፊውን የዚህን ዓለም ኑሮ
አምናችሁ ተደላድላችሁ ትቀመጣላችሁ እንጂ እስከዛሬ የሚጠቅማችሁን አላወቃችሁም፡፡ ወንድሞቼ እናንተ ግን
ምድራዊ ሞትን አትፍሩ፡፡ ለዘለዓለም ፍጻሜ የሌላት የሚነድ እሳት መከራ ያለባትን የሰማይ ቅጣትን ፍሩ እንጂ፡፡ አሁንም
በሚካኤልና በገብርኤል ስም ምጽዋትን ስጡ፡፡ ቢኖራችሁ ብዙ፣ ባይኖራችሁ ግን ጥቂት፡፡ በምትሞቱበት ቀን
በእግዚአብሔር ፊት መዳኛ ይሆኗችኋልና፡፡ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ፋሲለደስን እንደረዳውና እንደጠበቀው በብርሃናዊ ክንፉም ተሸክሞ ወደ ሰማይ እንዳወጣውና ገነትን እንዳሳየው
የሚናገር የቅዱስ ሚካኤል ተአምር ይህ ነው፡፡ በረከቱ ከኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ፋሲለደስም በልቡና ጭንቀት፣ በጽኑ ሐዘን፣ በብዙ ልቅሶ በሌሊት ተግቶ ሲጸልይ ያድር ነበር፡፡ሰማዕት ሊሆንም ይሻ ነበር፡፡
እነሆ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተኝቶ ሳለ ደስታን በተመላ መልክ ታየው (ተነጋገረው)፡፡ እንዲህም አለው፤
“የክርስቶስ ጭፍራ ፋሲለደስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ ደስ ይበልህ፡፡ ስምህ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በሕይወት መጽሐፍ
ተጽፏልና፡፡ ፋሲለደስ ሆይ ምጽዋትህ ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ፊት ደርሷልና ደስ ይበልህ፡፡ ፋሲለደስ ሆይ ደስ ይበልህ፡፡
ዛሬ በዚህ ዓለም ታላቅ እንደሆንክ በሰማያትም አንተ ታላቅ ትሆናለህና፡፡ ፋሲለደስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፡፡ ስምህና
የዘመዶችህ ስም ከክርስቶስ ወገኖች ጋር በመንግስተ ሰማያት ተጽፏልና ፋሲለደስ ሆይ ደስ ይበልህ፡፡ እግዚአብሔር
በሰማያት ቤትን ሰርቶልሃልና፡፡ ፋሲለደስ ሆይ ሰላምታ ላንተ ይገባሃል፡፡ ማደርያህን የዮስጦስንም ማደርያ ከልጆችህም
የእያንዳንዱን ቤት እንደንጉሥ ዳዊት ቤት በሰማይ ከፍ ከፍ አድርጎላቸዋልና፡፡ ፋሲለደስ ሆይ ደስ ይበልህ፡፡ በእግዚአብሔር
በበጉ ሀገር ውስጥ ከከበሩ ደንጊያዎችና ከእንቊ ላንተ አክሊልን አዘጋጅተውልሃልና፡፡ ፋሲለደስ ሆይ መከራን ታገስ፡፡
ከልጅነትህ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ካንተ ጋር ያለኹ፣ ከመከራ ሁሉ ያዳንሁህ እኔ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነኝ፡፡
ዳግመኛም የእኅትህን ልጅ ዮስጦስን ያዳንኹት ከፋርስ ሰዎችም እጅ ያወጣኹት እኔ ነኝ፡፡ ጠላቶቹን እስካጠፋቸው ድረስ
ልጅህ አውሳቤዎስን ያበረታሁት እኔ ነኝ፡፡ ዛሬም እኔ በክንፌ ተሸክሜ ወደ ሰማይ ላወጣህ መጣሁ፡፡ ወደጌታዬ ወደኢየሱስ
ክርስቶስም ላቀርብህ የሚደርስብህን የምትሰራውንም ሁሉ እንዲያሳይህና እንዲያስረዳህ፡፡ ያንጊዜ ፍራቱን ከሱ
አራቀለት፡፡ በብርሃን ክንፉ ተሸክሞ ወደሰማይ አወጣው፡፡ የእግዚአብሔር መልእክተኛ የመላእክት አለቃ ቅዱስ
ሚካኤልም የከበረ ፋሲለደስን በክርስቶስ ፊት አቆመው፡፡ ዳግመኛም በብርሃን ክንፉ ተሸክሞ ወደ ሕይወት ወንዝ
ወሰደው፡፡ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” እያለ ሦስት ጊዜ አጠመቀው፡፡ ደጋጎቹ ጻድቃን ሁሉ ወዳሉበት
አገባው፡፡ ከዚያ በደረሰ ጊዜ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በእንቊና በመረግድ በያክንት የተሰራ ታላቅ አዳራሽ አየ፡፡
ይኸውም በልዩልዩ ጌጥ የተሸለመ ነው፡፡ እነዚህንም ያማሩ የተጌጡ አዳራሾች ሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ይዞሯቸዋል፤ ግን
በውስጣቸው ሰው የለም፡፡በመካከላቸው ያለው አዳራሽም ከሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ማንም ክብሩን ሊናገር አይችልም፡፡ ክቡር
ፋሲለደስም ይህን ባየ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እንዲህ አለው፤ “በእንደዚህ ያለ ሥራ የተሸለሙ፤ ይህ
ፍጹም ክብር ያላቸው እነዚህ አዳራሾች ለእነማን ናቸው? ከቤቶቹ ሁሉ የሚበልጠው በመካከላቸው ያለው በእንደዚህ
ያለ አይነት የተሸለመው ይህ አዳራሽስ ለማን ነው? ይህ ክብር እነዚህም ቤቶች በሰማያት ካሉት ሁሉ የበለጠ ጸጋና ክብር
ለተሰጣቸው መሆን ይገባቸዋል፡፡ ይልቁንም ይህ በመካከላቸው ያለው ክብሩ የበዛው ቤት፡፡” የመላእክት አለቃ ቅዱስ
ሚካኤልም መልሶ እንዲህ አለው፡፡ የክርስቶስ ወዳጄ ፋሲለደስ ሆይ ከታላላቆቹ አዳራሾች ሁሉ የሚበልጠው ይህ አዳራሽ
ላንተ ነው፤ የቀሩት ግን ለወገኖችህና ለንጉሡ ልጅ ለዮስጦስ ነው፡፡ ዳግመኛም “ና ከዚያ የሚኖሩትን የቅዱሳን
የደስታቸውን ገነት የዕረፍት ቦታቸውን ላሳይህ፡፡” አለው፡፡ አብርሃምን፣ ይስሐቅን ያዕቆብንም አሳየው፡፡ አይተው ሰላምታ
ሰጡት፡፡ “ወንድማችን ሆይ ደኅና መጣህ፡፡ በርታ አትፍራ፡፡ በሥራህ ሁሉ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሁን፡፡” አሉት፡፡ ያንጊዜ
መድኀኒታችን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን በብርሃን ክንፎቹ ክቡር ፋሲለደስን ተሸክሞ ወደቤቱ ይመልሰው ዘንድ
አዘዘው፡፡ ያንጊዜ ተሸክሞ ወደ ቤቱ መለሰው፡፡ ሰውነቱ ብሩህ፣ መዓዛውም ከሽቱ ይልቅ እጅግ የተወደደ ሆነ፡፡ የመላእክት
አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ክቡር ፋሲለደስን ራሱን ሳመው፤ ኃይልንና ደስታንም መላው፤ ሰላምታም ሰጥቶት ወደ ሰማይ
ዐረገ፡፡

የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል ልመናውና ምልጃው ከኛ ጋር ይኑር፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም፡፡

መስከረም አሥራ ሁለት ቀን በዚህች ዕለት የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል ነው፡፡

ክብር ይግባውና እግዚአብሔር በዚህች ቀን ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነብዩ ኢሳይያስ ልኮታልና፡፡ ከተቆጣው በኋላ አዘነለት፤
ይቅርም አለው፡፡ ከማረውም በኋላ ሐያ ስምንት ዓመት ተቀመጠ፡፡ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስም ይሄድ ዘንድ አዘዘው፡፡
እግዚአብሔር ከደዌው እንዳዳነው ሚስት አግብቶ ምናሴን እስኪወልድ ድረስም በዕድሜው ላይ አሥራ አምስት ዓመት
እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ፡፡

ስለዚህ አባቶቻችን የቤተክርስትያን መምህራን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ በአሥራ
ሁለት ቀን እንድናደርግ አዘውናል፡፡ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል ልመናውና በረከቱ፣ ፍጹም ምልጃው ከኛ ጋር
ይኑር፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

You might also like