You are on page 1of 2

“የማህበራዊ አደንቋሪዎች” የጭቃ ጅራፍ…!

ከሁለት ቀን በፊት ያሰራጨሁትን መጣጥፍ በተመለከተ በተለምዶ “ማህበራዊ አንቂዎች” ተብለው


የሚጠሩ፣ እኔ ግን “ማህበራዊ አደንቋሪዎች” ብዬ የምጠራቸው የብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎች
የፈጠራ አሉባልታ ዘመቻ ከፍተውብኛል፡፡ እነዚህን ሆን-ብለው የሚያጠፉ ማህበራዊ አደንቋሪዎች
ምንም ዓይነት መልስም ሆነ ማስተባበያ በመስጠት ማስረዳትም ሆነ ማሳመን እንደማይቻል
ባውቅም እነርሱን በማድመጥ አንዳንድ የዋህ ዜጎች ሊወናበዱ ይችላሉ ብዬ በመገመት ይህንን
አጭር ማስተባበያ ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡

በመጣጥፌ ላይ ያስተላለፍኳቸው መልዕክቶች በዋናነት ሶስት ናቸው፡፡

እነርሱም -

1. “ችግራችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንጂ በጦርነት ሊፈታ ስለማይችል በአስር ሺህዎች


የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ህይወት እያሳጣን ያለው የወቅቱ አውዳሚ ጦርነት ተገዳድለን
ከማለቃችን በፊት በአስቸኳይ መቆም አለበት፤

2. “በጦርነቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላትና የውጪ ኃይል የሆነው የሻዕቢያ ሰራዊት
ቀጥተኛ ጣልቃ-ገብነትና ወረራ በአስቸኳይ መቆም አለበት፤

3. “በጉርብትና፣ በባህል፣ በታሪክና በማንነት ተጋምዶ የኖረው የአማራና የትግራይ ሕዝብ


ግንኙነት ከጦርነትና ከፍጥጫ ወጥቶ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት መሸጋገር አለበት” የሚሉ
ናቸው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ካድሬዎች የሆኑ የማህበራዊ አደንቋሪዎች ለእነዚህ የእኔ ግልፅ አመለካከቶችና
አቋሞች ምክንያታዊ የሆነ ትችት የማቅረብ አቅም ስላላገኙ ያልተባለን ጉዳይ እንደተባለ አድርገው
በማቅረብ በእኔ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድን መርጠዋል፡፡ ብዙውን እንቶ-ፈንቶ ወደጎን
ትቼ ዋና መልዕክታቸውን ለመረዳት እንደሞከርኩት ማህበራዊ አድንቋሪዎቹ በጥቅሉ
ሊያሰራጩት የፈለጉት አሉባልታ “ልደቱ ሕወሓትን እንደግፍ አለ” የሚል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ሆኖም በሰሞኑ ፅሁፌም ሆነ በማንኛውም ሌላ ጊዜ “ሕወሓትን እንደግፍ” የሚል ሃሳብ በእኔ


በኩል ቀርቦ አያውቅም፡፡ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የማልደግፍ እስከሆነ ድረስም በዚህ ጦርነት
ሕወሓትንም ሆነ ብልጽግና ፓርቲን ለይቼ ልደግፍ እንደማልችል ግልፅ ነው፡፡ ስለሆነም
የአሉባልታ ዘመቻ ከማካሄድ ይልቅ ከእኔ አቋም በተጻራሪ “የወቅቱ አውዳሚ ጦርነት መቀጠል
አለበት”፣ “የሻዕቢያ ሰራዊት ቀጥተኛ ድጋፍና ጣልቃ-ገብነትም ሕጋዊና ጠቃሚ ነው”፣ “የአማራና
የትግራይ ሕዝብም ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር አያስፈልጋቸውም” ብሎ በድፍረት ለመከራከር
የሚፈልግ የመንግሥት ወይም የፓርቲ አመራር ካለ በእኔ በኩል በግልፅ መድረክ ተገኝቼ

1
ለማስረዳትም ሆነ ለመረዳት ወይም ለማሳመንም ሆነ ለማመን ፍላጎት ያለኝ መሆኑን እየገለፅኩ
በዚህ አጋጣሚም ግብዣዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሊሰራጭ የተሞከረው አሉባልታ “ልደቱ ይህንን ሃሳብ ያቀረበው ሕወሓት
ሊሸነፍ ስለሆነ ነው” የሚል ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ትችት በእኔ ላይ እያቀረቡ
ከሚገኙት የብልጽግና ካድሬዎች በላይ ለ28 ዓመታት ሕወሓትን በምክንያትና በሰላማዊ መንገድ
ስታገል የኖርኩ ሰው በመሆኔ ማንም እኔን በሕወሓት ወዳጅነት የመክሰስ የሞራል ብቃት
የለውም፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የሕወሓት ወዳጅ ብቻ ሳይሆን አሽከርና ተላላኪ ሆነው የኖሩት
የወቅቱ የብልጽግና ፓርቲ መሪዎች ናቸው፡፡ ዛሬም የሻዕቢያ አሽከር ለመሆን የበቁት በዚያው
ልማዳቸው ነው፡፡

ሲቀጥልም እኔ ስለሰላም ያለኝ ሃሳብ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡
የወቅቱ ጦርነት ከተጀመረ በኋላም “ጦርነት መቆም አለበት” የሚለውን አቋሜን ሕወሓት
ተንቤንም፣ መቀሌም፣ ጣርማ-በርም በነበረበት ወቅት ሳራምደው የነበረ ነው፡፡ እንዲያውም የእኔን
አቋም በአግባቡ የሚከታተል ሰው ሊረዳው እንደሚችለው ከዓመት በፊት ያልተናገርኩትና በአሁኑ
ፅሁፌ ላይ የተገለፀ ምንም ዓይነት አዲስ ሃሳብ የለም፡፡ የወቅቱን ጦርነትም የትኛውም አካል
በዘላቂነት ሊያሸንፍ ይችላል የሚል እምነት ስለሌለኝ “ጦርነት ይቁም” የሚል አቋም የማራምደው
የወታደራዊ የኃይል ሚዛን አይቼ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የእኔ ወገንተኝነትም ለጦረኛ
ፓርቲዎች ሳይሆን በጦርነቱ ምክንያት ያለ-አበሳው እያለቀ ላለው ወጣት ትውልድ፣ እየተፈናቀለና
በየዕለቱ በድህነት አረንቋ ውስጥ እየተዘፈቀ ላለው ሕዝብ እና በግልብ ፖለቲከኞች የአመራር
ድክመት ህልውናዋን እያጣች ላለቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ነው፡፡ ችግሩ የብልጽግና ካድሬዎች
በጥላቻና በመርህ መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ስለማይረዱት ምክንያታዊ ፖለቲካ ምን
ማለት እንደሆነ እንዲረዱት መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡

በአጠቃላይ - ‘ለትግራይ ሕዝብ’ የተቆረቆረ ሁሉ ‘ሕወሓት’ በሚመስላቸው ዘረኛ የብልጽግና


ፓርቲ ካድሬዎች እየተሰራጨ ያለው አሉባልታ እንደተለመደው ከእውነት የራቀ የስም ማጥፋት
ዘመቻ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በሀገራችን የጥላቻ ፖለቲካ እንዲነግሥና ወደዚህ
ዓይነቱ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ እንድንገባ ካደረጉን ምክንያቶች ውስጥም እነዚህ ማህበራዊ
አደንቋሪዎች አንዳንድ ጊዜ እየፈጠሩ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እያጋነኑ ወይም እያዛቡ የሚያሰራጩት
ሀሰተኛ መረጃ እና አሉባልታ ስለሆነ ህብረተሰቡ የዚህ እኩይ ተግባር ሰለባ ከመሆን እንዲቆጠብ፣
ኃላፊነት የሚሰማችሁ መገናኛ ብዙኀንም የጥላቻና የሀሰት መረጃ ለሕዝብ የሚያሰራጩ አካላትን
በማጋለጥ ሞያዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ልደቱ አያሌው

መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም

You might also like