You are on page 1of 18

Andargachew Tsege

otnoSedrspir96 tf0 c6t0Mc6t:l1mhh1ct1a37 a h98M672h8A3h3a3gi  · 
ወደ ወገኖቼ! ብዙዎቻችሁ ጽሁፍህ ባይረዝም ትሉኛላችሁ። እኔም ባይረዝም ፍላጎት አለኝ። ስንፍናዬ የሚመኘው ማሳጠሩን
እንጂ ማርዘሙን አይደለም። ግን የማነሳቸው ጉዳዮች ሰፋ ተደርገው መቅረብ ስላለባቸው ብቻ ነው ጽሁፌን የሚያረዝሙት።
በሃገሩ ጉዳይ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ የሚል የተማረ ሃይል፣፣ ሞልቶ ክተረፈው ጊዜው ጥቂት ደቂቃዎችን ሰውቶ
ጽሁፍ ማንበብ ሊከብደው አይገባም ባይ ነኝ። ሰፋ አድርገን ነገሮችን ማየት ካልቻልን እንዴት መግባባት በመረጃና በምክንያት
ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መወሰን እንችላለን። በዚህ መንፈስ ይህን ፌስ ቡክ በሁለት ክፍል እንድከፍል ያስገደደኝን ጽሁፍ
በትእግስት እንድታነቡ በትህትና እጋብዛችኋለሁ።
ቀን - የካቲት 2015
ክፍል 1
ወደ ሰላም ወይም ወደ ቀውስ፤ የትግራይ - ኢትዮጵያ ጉዳይ
ማሳሰቢያ፣ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የሚከተለው ምክንያት እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ማለቂያ
በሌለው ቀውስ እየታመሰች ነው። ከእነዚህ ቀውሶች መሃከል አንዱ በወያኔ የተቀሰቅሰው የሰሜን ጦርነት ነው። ይህ ጦርነት
ለጊዜው ቆሟል። ሆኖም ግን በደንብ በታሰበበትና በጥንቃቄ ሁኔታው ካልተያዘ ይህ ያልጠና ሰላም በቀላሉ መደፍረስ
የሚችል፣ እስካሁን ህዝብ ከቀመሰው መከራ በላይ የከፋ መከራ ሊያመጣበት እንደሚችል፣ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጠናው
የሚያናጋ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል በጊዜ ለማመላከት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጽሁፉ እንደሚያመላክተው በትግራይ
ውስጥ ድምጻችን እየተሰማ አይደልም የሚሉ ለሰላም የቆሙ አካላት ድምጽ ባስችኳይ እንዲሰማ የማድረግ ግፊት በመፈጠሩ
ነው። አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሉም ወይ? አዎ አሉ። ሞልተው ተርፈዋል። አቅሜ በፈቀደ መጠን ወደ እነሱ
እመለሳለሁ።
1) እንደ መነሻ!
ትንሽ እውቀት፣ ትንሽ ተመክሮ ያለው ራሱን የፖለቲካ ሰው አድርጎ የሚቆጥር ዜጋ፣ በዘርና በሃገር ጥላቻ፣ በነዋይ ፍቅር፣ በግል
ስምና ዝና ስካር፣ በስነልቦና ቀውስ፣ በስልጣን ሱስ፣ በፍራቻ ቆፈን፣ ስንፍና በወለደው ግድየለሽነት እና በሌሎችም የማሰላሰል
እና የመተንተን አቅምን በሚገሉ እንከኖች እስካልተሰለበ ድረስ የአንድን ሃገር እውነታ በፍጹም ነጻነትና ገለልተኛነት ለማጤን
የወደፊቱንም ለመተንበይ የሚቸገር አይሆንም።
እንደ አጋጣሚ ሆኖ በተከታታይ ስልጣን ከያዙት የቅርብ ጊዜ ሁለት መንግስታት፣ የወያኔ እና የብልጽግና መንግስታት ወይም
የመንግስት አመራሮች ጋር በነበረኝ ግንኙነት ሊመጡ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ችግሮችና የሃገሪቱ ፖለቲካ ወዴት ሊያመራ
እንደሚችል የሚመስለኝን ከመጠቆም ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም። በዚህ ጽሁፍ የቀረቡ መረጃዎችና እይታዎች በስልጣን ላይ
ላለው መንግስት እንግዳ ይሆናሉ የሚል እምነት የለኝም። አቅሜ፣ ልምዴ እውቀቴ በፈቀደ መጠን ያለምንም ይሉኝታ፣
ግብዝነትና አድርባይነት በድፍረት ሃሳቤን በቃል፣ በጽሁፍ አቅርቤያለሁ። ህዝብ በአደባባይ ከሚያውቀው ይበልጥ በግል
የሰጠኋቸው አስተያየቶች ይበዛሉ።
በተለይ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ፣ ከወያኔ ሰዎች ጋር በተለይ ትግራይን በተመለከተ ያደረግኋቸው ክርክሮች “ከፓፓሱ በላይ
ቄሱ እስኪሉኝ ድረስ” ከየትኛውም የኢትዮጵያ አርሶ አደር ይበልጥ ለማውቀው የትግራይ አርሶ አደር ወገንተኛነቴን
አሳይቻለሁ።
የወያኔ መሪዎች የትግራይ ህዝብ ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል የከፈለውን ከፍተኛ መስዋእትነት ለግል ስልጣናቸውና
ጥቅማቸው እንዴት እየመነዘሩ እያባከኑት እንደሆነ፣ እንዴት የእነሱ መጨረሻ የማያማር እንደሚሆን፣ የትግራይም ህዝብ
የእነሱ እብሪት ብልግና እና ዘረፋ የመጨረሻው እዳ ከፋይ እንደሚሆን ያለማታከት አስጠንቅቄያለሁ። አክረው ሲገፉት
የነበረው የዘር ፖለቲካ ህዝብን ለመከፋፈል ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ካልሆነ በስተቀር “በቁጥሩ አነስተኛ ለሆነው፣
በመላው ሃገሪቱ ተበትኖ ለሚኖረውና ለሚሰራው በኢትዮጵያዊነቱ ቀናኢ ለነበረው የትግራይ ህዝብ አይጠቅመውም” በማለት
ተሟግቻለሁ። የቋንቋን እና የባህልን እኩልነት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን በዘር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችና
ክልሎች ሳያስፈልጉ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑን፤ የዘር ፖለቲካው ሁሉንም ዘሮች እርስ በርሳቸው እንዲባሉ አድርጎ
ሃገር አውድሞ እንደሚጠቃለል ለማሳየት ሞክሪያለሁ። የቪዲዮ የድምጽና የሰነድ መረጃዎቹ በወያኔና በወቅቱ ኢህዴን ተብሎ
በሚጠራው በኋላ ብአዴን በተባለው ድርጅቶችና በየሚድያ ተቋማቱ እጅ እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ። ይህን ያደረግሁት ወያኔ
እየወደቀ ባላበት የመጨረሻው ሰአት ላይ አይደለም። ወያኔ ስልጣን ከያዘ ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ጀመሮ ነበር። ከወያኔና
ከተላላኪዎቻቸው የኢህዴንና የኦህዴድ ሰዎች ጋር ያደረግሁት ጭቅጭቅ ከአንድ አመት በላይ ቀጥሎ በመጨረሻም ከወያኔ/
ኢህአዴግ ጋር ለመለያየትና በ 1985 አ.ም ለሁለተኛ ዙር የስደት ህይወት መጀመር ምክንያት ሆኖኛል።
ዛሬ በህይወት ያሉ ከወያኔዎቹ ወገን፣ እነተወልደ ወልደማሪያም፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ከብአዴኖቹ እነበረከት ሰምኦን፣
እነተፈራ ዋልዋ፣ እነአዲሱ ለገሰና ታምራት ላይኜ፣ በምን ጉዳይ ምን እንደተነጋገርን ያውቁታል። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
በተለይ ተወልደ የኢህአዴግ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የወያኔ የፖሊት ቢሮ አባል በመሆኑና
በወቅቱ የድርጅት ጉድይ ትልቅ ተጽእኖ በሃገሪቱ ላይ የሚያደርግ ስለነበር፣ እኔም የዛ ኮሚቴ አባል በመሆን ካየኋቸው ችግሮች
በመነሳት የዛሬ ሰላሳ አመት፣ በ 1984 አ.ም፣ ቀኑን እና ሰአቱን ባልረሳሁት አንድ ማክሰኞ እለት ከጠዋቱ 4.30 ላይ፣ ቢሮው
ቀጠሮ በመያዝ የኢህዴን እና የኦህዴድ ድርጅቶች ደካማ መሆን ወያኔን ራሱን ለከፍተኛ አደጋ የሚዳርገው መሆኑን በማንሳት
ሰፊ ውይይት አድርጌያለሁ። የክርከሬ ጭብጥ “የእነዚህ ድርጅቶች ደካማነት በጊዜያዊንት ለእናንተ የሚያመች ሊሆን
ይችላል። ሆኖም ግን ስታጠፉ ማረም አለመቻላቸው፣ ድርጅታችሁ በስህተት ላይ ስህተት እየሰራ ገደል እንዲገባ ያደርጋል”
የሚል ነበር። የተወልደ መልስ “ድርጅቶች በሰው ሃይል ደካማ እንደሆኑ እናውቃለን፤ ግን ነጻ ድርጅቶች ስለሆኑ ብቃት
ያላቸውን ሰዎች ወደ ድርጅታቸው እንዲያመጡ ህወሃት ማዘዝ አንችልም” የሚል ነበር። በወቅቱ ይህ መልስ እንደማያሳምነኝ
ነግሬው ተለያይተናል።
ከወያኔዎች ጋር ወልቃይትና ራያንም በተመለከተ ብዙ ተባብለናል። በተለይ ገብሩ አስራት በ 1995 አ.ም እንግሊዝ ሃገር
በመጣበት ወቅት ወልቃይትና ራያን በተመለከተ ያደረግነውን ውይይት ይረሳዋል ብዬ አላስብም። የወልቃይትና የራያ ጉዳይ
ከፍተኛ ደም አፋሳሽ እልቂት እንደሚያስከትል፣ በመጨረሻም ወያኔዎች ተሸናፊ እንደሚሆኑ ነበር ለማስረዳት የሞከርኩት።
ያ ወቅት ገብሩና ጥቂት ጓደኞቹ በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ ከህወሃት አመራርነት የተባረሩበት ነበር። እቤቴ እራት ጋብዠው
በጫወታችን መሃከል ለገብሩ አንድ ጥያቄ አነሳሁለት።
“ያን ሁሉ ዘመን በረሃ ለበረሃ ተንከራታችሁ ይሄው አሁን መለስ ከድርጅቱ አባረራቸሁ ድካማችሁ መና ቀረ። ምን
አተረፋችሁ?” አልኩት።
ለዚህ አባባሌ ገብሩ እንዲህ ብሎ መለሰለኝ። “መና አልቀረንም አንቀጽ 39 ን በህገ መንግስቱ እንዲካተት አድርገናል።”
ይህ መልሱ በጣም ስላስገረመኝ። በተናገረው ላይ ሌላ ጥያቄ ጠየቅሁት። “ለመሆኑ ትግራይ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39
አማካይነት የመገንጠል መብት ብታገኝ የትኛውን ድንበር ይዛ ነው ነጻ ሃገር የምትሆነው?” በማለት፤
ገብሩም መለሰ፣ “የድንበር ጉዳይ ችግር አይደለም። ትግራይ በህገ መንግስቱ የጸደቀ ድንበር አላት” አለኝ
እኔም “ይህ ህገ መንግስታዊ የምትለው ድንበር በጉልበት ከወሎና ከጎንደር የጠቀለላችሁትን ወልቃይትና እና ራያን የሚያካትት
ከሆነ ችግር ይፈጠራል” አልኩት።
“ምን ችግር” አለኝ።
ለማስረዳትም እንዲህ አልኩት፣
“በአንድ ሃገር ውስጥ የአስተዳደር ወሰን አድርጎ ክልል መመስረትና የአንድ ነጻ ሃገር ድንበር መመስረት ሁለቱ ይለያያሉ።
ትግራይ ኢትዮጵያ አካል ስለሆነች የወልቃይትና የራያ ነገር እስከ አሁን የሚገባውን ትኩረት አላገኘ ይሆናል። ግን ወልቃይትን
እና ራያን የነጻ ትግራይ ሪፓብሊክ አካል አድርጌ ድንበር አሰምራለሁ ብለህ ስትነሳ ችግር ይፈጠራል” አልኩት።
ምን ችግር ? አለኝ በድጋሚ
“ጦርነት” አልኩት
የበለጠ ለማስረዳትም የኤትራን ጉዳይ አነሳሁ። “ኤርትራ ቅኝ ገዥዎች ያሰመሩት ግልጽ የሆነ ድንበር ኖሯት በባድመ ሰበብ
የደረሰውን እልቂትና ውድመት አስበው። እንዲህ አይነት ግልጽ የሆነ ነባር ድንበር የሌላቸውን ትናንትና ወያኔ ክልሎች አድርጎ
የፈጠራቸውን አካላት አስተዳደራዊ ወሰኖች ወደ ቋሚና ነጻ ድንበርነት እቀይራለሁ ብለህ ስተነሳ፣ አጎራባችህ ያለውና ከዛም
ውጭ ያለው ህዝብ ዝም ብሎ የሚያይህ ይመስልሃል? ሁሉም ለእያንዳንዷ ሳንቲሜትር መሬት መዋጋቱ አይቀርም። ይህ
ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ራሱን ነጻ ሃገር አደርጋለሁ ብሎ ለሚያስብ የትኛውም ትልቅ ሆነ ትንሽ ክልል የሚሰራ ነው። ኢትዮጵያ
እንደ ሃገር ከቅኝ ገዥዎችና ከሌሎች ወረራዎች ራሷን ተከላክላ የተረፈችውና የቆየቸውም ከሁሉም አካባቢ ዜጎቿ በሁሉም
የሃገሪቱ ምድር ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነው። እንደ ብሄር ወይም ህዝብ ብቻውን ራሱን ከውጭ
ወራሪዎች ተከላክሎ ያተረፈ ህዝብና ግዛት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት የትም ቦታ ሰርቼ መኖር እችላለሁ
በሚል እምነት የህዝቡን ቁጥር በማይመጥን መሬት ላይ የተቀመጠው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ አጎራባች የሆነውን ሰፊ መሬት
የኔ ነው ብሎ ለሚነሳ ተገንጣይ በህገ መንግስቱ መሰረት ያሻህን አድርግ ብሎ የሚተወው ይመስልሃል። ትግራይም
የሚገጥማት ችግር ይህ ነው” አልኩት።
ዝምታ ሰፈነ
ቀጥዬም ወያኔዎች በጦርነት እንዴት ራሳቸውን እንደሚያዩ ስለማውቅ፣
“ግጭት የሚነሳ ከሆነ የምትዋጉት በሁሉም መንገድ የውጊያ ታሪክ አቅምና ስነልቦና ካለው የአማራ ህዝብ ጋር ነው።”
አልኩት።
የራት ግብዣው በዚህ ቆምጣጣ ውይይት ተዘግቶ ገብሩን ወደሚሄድበት ሸኘሁት።
በግንቦት 7 ንቅናቄ የጸሃፊነት ሃላፊነቴ “የወያኔ ቅጣ ያጣ እብሪትና ዘረፋ ሌላው ህዝብ የትግራይን ህዝብ በበጎ
እንዳይመለከተው ማድረጉ አይቀርም” የሚል ስጋት ስለነበረኝ፣ በግሌ የትግራይ ህዝብና የትግራይ ገዥ ጉጅሌ የሚል ስያሜ
የሰጠሁትን የጥቂቶች ስብስብ ያላቸውን ልዩነት በየመድረኩ ለማሰረዳት ሞክሪያለሁ። በተለይ ከወያኔ ጋር ትስስር
ያልነበራቸው የትግራይ ምሁራን የወያኔን የግፍና የዘረፋ ስርአት በመቃወም ከፊተኛው እረድፍ ላይ ለምን መገኘት
እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ማብራሪያ በመስጠት ጥሪ አቅርቤያለሁ። “ህዝብ ሁሉም ትግሬዎች ወያኔዎች አይደሉም” የሚል
ጠንካራ አቋም እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው “እናንተ የትግራይ ልጆች ወያኔን በመቃወም ትግሉን ስትመሩት ብቻ ነው።
እኔ የትግራይ ሰው ያልሆንኩት ከምናገረው እናንተ ብትናገሩት የበለጠ ተደማጭነት ታገኛላችሁ” ብያለሁ። በጣት የሚቆጠሩ
ትግራዋይ ይህን ያደረጉ ቢኖሩም የእነዚህ ጥቂቶች ተሳትፎ ብቻውን እየገጠመን ከነበረው ፈተና ጋር ሲነጻጸር እርባና
አልነበረውም።
በኢትዮጵያ ወያኔን ከስልጣን ያስወገደው ለውጥ ከመጣና እኔም ከእስር ከተፈታሁ በኋላም ከተለያዩ የሚድያ ተቋማት ጋር
ባደረግኋቸው ቃለ መጠይቆች ህዝብ በወያኔ መሪዎችና በትግራይ ህዝብ መሃከል ያለውን ልዩነት እንዲያውቅ ስራዬ ብዬ
ስለትግራይ ህዝብ የማውቀውን የህዝቡን ስብእና እና ደግነት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገነዘብ ለማድረግ የቻልኩትን ጥረት
አድርጌያለሁ። ለብቻዬ ከሰው ሁሉ ተገልዬ በታሰርኩበት ቦታ ጠባቂዎቼ ተመርጠው ሁሉም የትግራይ ተወላጆች የነበሩ
ቢሆኑም ከነሱ መሃከል ከፍተኛ ስብእና የነበራቸው፣ ወያኔ ከሰጣቸው መመሪያ ወጭ ወጥተው ደግነትና ርህራሄ ያሳዩኝን
እንደ ለተማርያም ያሉትን ሰዎች በአደባባይ ህዝብ እንዲያውቃቸው ያደረግሁት “የዘር መጥፎ የለውም የግለሰብ እንጂ” የሚል
መልእክት ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስተላለፍ በመፈለጌ ነበር።
በአንድ ቃለ መጠይቅ በኢትዮጵያ ደም መፋሰስን፣ የበቀል አዙሪትን ለማስቆም፣ ጌታቸው አሰፋን ጋር ተቃቅፌ ሰላም
ለመባባል እንደማይቸግረኝ የተናገርኩት ጌታቸው በወያኔ ዘመን ለተፈጸሙ አሰቃቂ የስብአዊ መብት ጥሰቶች ዋናው ተጠያቂ
እንደሆነ አጥቼው አልነበረም። ሌሎችም የወያኔ አመራሮች ከኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ የዘረፉት አስደንጋጭ መጠን ያለው ሃብት
ለሚሊዮን ህፃናት በአጭር መቀጨት፣ በመቶ ሽዎች ለሚቆጠሩ እናቶች በወሊድ እንክብካቤ እጥረት መሞት፣ በሚሊዮን
ለሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ አጥነትና ተስፋ መቁረጥ፣ በሃገር ውስጥ በዜጎች መሃል እንደሰደድ እሳት ለተስፋፋው ሌብነትን ነወር
አድርጎ የማያይ ባህል ተጠያቂ እንደሆኑ ጠፍቶኝ አይደለም። በሃገሪቱ ሰላም ከወረደ መጪው ዘመን ብሩህ ይሆናል ከሚል
ተስፋ ብቻ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝም የወያኔዎች አስተሳሰብና አካሄድ በደንብ ስለሚገባኝ በወቅቱ መጥቶ የነበረውን ለውጥ ሁሉንም ህዝብ
በእኩልነት በሚታደግበት መንገድ መስመር ለማስያዝ፣ በተለይ ወያኔዎች ለውጡን በስጋት እንዳያዩትና ወደሌላ አላስፈላጊ
መንገድ እንዳይጓዙ ለጻድቃን (ጄ/ል) ሆነ ለአበበ ተክላይሃማኖት ግንቦት 7 ንቅናቄ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ነበር
በአካል ተገናኝተን እንምከር የሚል ጥያቄ እራሴ ስልካቸውን አፈላልጌ የደወልኩላቸው። የስልክ ጥሪዬን በጨዋነት
ቢመልሱልኝም ከዛ በኋላ ለመገናኘት ያደረግሁት ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል።
በማአከላዊ መንግስትና በወያኔ መሃከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ፣ ቱባ የወያኔ መሪዎችና ሌሎችም የወያኔ ሁነኛ ሰዎች ትግራይ
ላይ ሲሰባሰቡ ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ወያኔዎችን በደንብ ለሚያውቃቸው ለኔ አይነቱ ሰው ከባድ አልነበረም።
ቀደም ብሎ በትግሉ ወቅትና በኋላም ከወያኔዎች ጋር በሰራሁባቸው የተወሰኑ ወራቶች የተረዳሁት፣ ወያኔዎች በተከታታይ
የገጠሟቸውን ባላንጣዎች በውጊያ ስላሸነፉ “ከኛ በላይ ጀግና ተዋጊ፣ የሚሊተሪ ሳይንስና ስትራተጂ አዋቂ የለም” የሚል
ሰለራሳቸው እጅግ የተጋነነ ግምት እንዳለቸው አውቅ ነበር። ከዛም አልፎ ወታደራዊ ድሎቻቸው የመጡት በበሳልና ሳይናሳዊ
በሆነ የፖለቲካ አመራር ነው ብለው ከልባቸው ያምኑ ነበር።
ከወያኔ ጋር በሰራሁበት አጭር ጊዜ ወስጥ በተደጋጋሚ በሚደረጉ ግምገማዎች፣ “አሸናፊነትና ተሸናፊነትን የሚወስኑ በርካታ
ጉዳዮች ስለሆኑ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ብቃታችሁን ከሚገባው በላይ አጋናችሁ አትዩ። ከደርግ ጋር በተደረገው ትግል የሻብያ
እርዳታ፣ ከደርግ ጋር ሆድና ጀርባ
የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ደርግ ራሱን ሶሺያሊስት ነኝ በማለቱ እንዲፈርስ የሚፈልጉ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የአረብና
የጎረቤት አገራት ድጋፍ ለድላችሁ የነበራቸውን ሚና አትርሱ። ከዛም በተጨማሪ በአንድ ወቅት የሰራ ወታደራዊና ፖለቲካዊ
ስትራተጂ በሌላ ወቅት ላይሰራ ይችላል። እንዲያውም ስልጣን ከያዛችሁ በኋላ በሀገር ውስጥና በድርጅታችሁ ውስጥ
የሚታየው ቀውስ ጨብጠናዋል የምትሉት ሳይንሳዊ የፖለቲካ አመራር እንደምትሉት ያልተጨበጠ መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ
ልተፈትሹት ይገባል” በሚል ተሟግቻቸዋለሁ። በአንድ ግምገማ ላይ ይህን አባባሌን ከምር እንመልከተው የሚሉ ደጋፊዎችም
አግኝቼ ነበር። ጌዜው ሁሉም በድል አድራጊነት የስከረበት ወቅት ስለነበር የትም ሳይደርስ ቀርቷል።
ባለፉት ሁለት ንኡስ ምእራፎች ከጠቀስኳቸው ምክንያቶች በመነሳት ነበር የወያኔዎች ሰዎች አዲስ አበባን እየተው መቀሌ ላይ
መሰባሰባቸው ያሳሰበኝ። በተለይ ስዩም መስፍን እና ስዬ አብረሃን የመሳሰሉ ጉምቱ የወያኔ መሪዎች ከመቀሌው ድምጸ ወያኔ
የትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች የሰጧቸው አስተያየቶች የወያኔ ሰዎች አሁንም ከድሮ የአዋቂነትና
የጀግንነት የበላይነት ቅዥታቸው እንዳልተላቀቁ በሚያሳዩ ቃላቶች የተሞሉ መሆናቸውና በትግራይ የጦርነት ድግስ እየተደገሰ
መሆኑን ግልጽ ያደረጉ ነበሩ። እነዚህ ቃለ ምልልሶች ጦርነት ቢከፍቱ የውጭ መንግስታት የሚያግዟቸው እንደሆነ ቃል
የተገባላቸው እንደሆነ የሚያሳዩ አነጋገሮች ነበሩባቸው። “ጦርነት ከተነሳ ቀጠናዊና አለምአቀፋዊ ሃይሎች የሚሳተፉበት
ይሆናል የሚለው” የስዬ እና የስዩም አባባል ከጎናቸው ከሚቆሙ የውጭ ሃይሎች ጋር ስምምነት መድረሳቸውን ያሳይ ነበር።
በዚህ ላይ የወታደራዊ ሰልፉ፣ የትጥቅ ማስጣቱ (ኤግዚብሽኑ)፣ የፉከራውና የቀረርቶው ጉዳይ ሲታከልበት ሁኔታው ወደ
ጦርነት እንደሚያመራ ገሃድ ሆኖ ነበር።
በዚህም ወቅትም ቢሆን፣ ስዬ አብረሃ ከ 28 አመት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ
የተጠቀመባቸውን ቃላቶች ሳይቀይር “ጦርነት መስራት እንችልበታለን፣ ክፍለጦር አፍርሰን ክፍለጦር መገንባት ሜካናይዝድ
አፍርሰን ሜካናይዝድ መገንባት እናውቅበታለን።” የሚል በእብሪት የተሞላ ንግግር በትግራይ ቴሌቪዥን ሲናገር በሰማሁብት
ጊዜ ዝም ብዬ አላለፍኩም። የስዬና የጓደኞቹ የዛን ወቅት አነጋገርና አስተሳሰብ፣ የተቀየረውን የአለም፣ የቀጠናውን፣ የሃገርና
የትግራይም ሁኔታ በደንብ ያላገናዘበ፣ የትግራይን ህዝብ ለከፋ ችግር ሊዳርግ የሚችል መሆኑን የሚገልጽ መልእክት
እንዲደራሳቸው በአደባባይ የስዬን ስምና ንግግሩን ጠቅሼ መልእክቴን አስተላፌያለሁ። “ተው ይህ የጦርነት መንገድ
አያዋጣም” ብያለሁ።
ወያኔዎች ለራሳቸው በሰጡት የተጋነነ የአይበገሬነትና የአዋቂነት ቅዥትና በውጭ ደጋፊዎቻቸው ቃል በተገባላቸው ድጋፍ
ታውረው ወያኔዎች ጦርነት ከፈቱ። ለትግራይ ህዝብ ይህን ጦርነት ለምን እንደከፈቱ “የሰጡት ማብራሪያ የትግራይን ህዝብ
ከጥፋት ለማዳን” የሚል ማጭበርበሪያ ብቻ ነው። በተሳሳተ የራስ ጥንካሬና የሌላው ደካማነት ትንተና እና በአሜሪካ
የዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ባሉ ከረጅም ዘመን ጀመረው በገንዘብ በገዟቸው ባልስልጣናት ሸሪኮቻቸው አበረታችነትና
የአሜሪካ ጥቅም ለማስከበር የተከፈተ ጦርነት እንደሆነ ለትግራይ ህዝብ አልነገሩትም። የወያኔ መሪዎች አብይን ከአራት ኪሎ
ቤተመንግስት በቀላሉ አሽቀንጥረው ከጃቸው ያመለጠውን ስልጣን በዚህ ስልጣን አማካይነት የተቀዳጁትን የመዝረፍ መብት
መልሶ መያዝ ይቻላል በሚል የጀብደኝነት ስሌት የተጀመረ ጦርነት እንደሆነ ለትግራይ ህዝብ የነገረው የለም። ስልጣን ተይዞ
ምን ሲሰራበት እንደነበር የሚያውቀው የትግራይ ህዝብ ይህን ሃቅ አውቆ ቢሆን ኖሮ ለሶስተኛ ዙር ልጆቹን የመስዋትነት ጭዳ
በማድረግ የወያኔ መሪዎችን ህልውና እና የኢትዮጵያን ጠላቶች ጥቅም ለማስከበር ሆ ብሎ አይነሳም ነበር። የትግራይ ህዝብ
እንደርሱ በድህነት ተቆራምደው በሚኖሩ ደሃ የአማራ እና የአፋር ወንድሞቹንና እህቶቹ ላይ በአረመኔያዊ ጭካኔ አይዘምትም
ነበር።
አሁንም በዚህ ሰአት ይህ የወያኔዎች የጦርነት አጀማመር ትርክት ከአንድ ጉዳይ በስተቀር ብዙም የተቀየረ ነገር የለውም።
በአደባባይ ጦርነቱን በመብረቃዊ ጥቃት ጀመርነው ብለው እንዳልተናገሩ፣ ዛሬ ወያኔዎች ጀማሪዎቹ እነሱ እንዳልሆኑ
አድርገው እያቀረቡት ነው። “የትግራይን ህዝብ ከጥፋት ለማዳን” የሚለው የሃሰት ትርክት ግን ዛሬም በወያኔ አባላት መሃከል
ብቻ ሳይሆን በመላው ትግራይ እንደታመነ እንዲቀጥል አድርገዋል። ይህን ትርክት ለማስቀጠል እንዲቻል ወያኔዎች ከጦርነቱ
በፊት ለአለም አቀፍ ማህበረሰቡ የዲፕሎማሲ ስራቸው ግብአት እንዲሆን የተዘጋጁበትን የጄኖሳይድ ትርክትና ሰበብ
በማጠናከር፣ የጄኖሳይድ ኮሚሽን አቋቁመው በትግራይ ውስጥ ብቸኛው ስራ የሚሰራ፣ በቂ በጀት የተመደበለት የመንግስት
ተቋም አድርገው ገንብተውታል።
ኮሚሽኑ ወያኔዎች ከመደቡለት በጀት በተጨማሪ፣ አለም አቀፍ የትግራይ ምሁራን ድርጅት በሚያሰባስበው ገንዘብና ራሱ
የኢትዮጵያ መንግስት በሚያቀረበው ገንዘብና እርዳታ ተደግፎ የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግስት በአለም ፊት የሚያሳጣ፣
ምእራባውያኑ መውሰድ ለሚፈልጉት ጸረ ኢትዮጵያና ኤርትራ እርምጃ ሽፋን የሚሆን በሚገባ የታቀደና የተደራጀ፣ ወደፊት
ወያኔ ለሚያደርገው የዲፕሎማሲ ዘመቻ የሚያገለግል የተቀነባበረ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ በየቤቱ ሰራተኞቹን እየላከ ለጄኖሳይድ ክስና ለካሳ ማሰባሰቢያ የሚሆን መረጃ እየሰብሰብኩ ነው በማለት የትግራይ
ህዝብ ጄኖሳይድ ሊፈጸምብኝ ተሞክሮ ነበር በሚል እምነት ውስጥ እንዲኖር እያደረገው ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን “አሁንም
የትግራይን ህዝብ ከወያኔ ውጭ ከጄኖሳይድ የሚያተርፈው የለም የሚል” ሰበካውን ቀጥሎበታል። አሁንም የወያኔ መሪዎች
የሰላም ስምምነቱ በጦርነት አስገድደው ያገኙት ድል አድርገው ለትግራይ ህዝብ እያቀረቡለት ነው። ህዝቡ “የዚህ ድል ባለቤት
ወያኔ ስለሆነ፤ ከህልውና ጥፋት የታደገህ ወያኔ ስለሆነ፤ እጣህን ከወያኔ ጋር አቆራኝተህ መቀጠል አለብህ” እየተባለ ነው።
ወያኔዎች ያሻቸውን ቢሉ ይህ አላስፈላጊ የነበረ ጦርነት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱን የደሃ ልጆች ህይወት ቀጥፎ የዚችን
ደሃ ሃገር ሃብትና ጥሪት አራቁቶ በነሱ ወታደራዊ ሽንፈት ለጊዜው ቆሟል። ከጦርነት ጋር በተያያዘ የሆነው ሁሉ ጸሃይ የሞቀው
ጉዳይ ስለሆነ ብዙ ማተት አያስፈልግም። ከዚህ በላይ ያቀረብኩት መንደርደሪያ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣውን ዘመን በጥንቃቄ
እንድንመለከት የእይታ ማእቀፍ ለመስጠት ብቻ ነው። የወያኔ መሪዎችን እና ከእነዚህ መሪዎች ጋር የተጣበቀውን የትግራይ
ልሂቅ የአእምሮ ውቅር በሚገባ ማወቅ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እውነተኛ ሰላም ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትግራይን ህዝብ
ጨመሮ ከዛም አልፎ ለቀጠናው እንዲያመጣ ከተፈለገ በስርአት መሰራት ያለባቸውን ነገሮች ለመዘርዘር ያግዛል በሚል እምነት
ነው።
ከዚህ ቀጥሎ አሁናዊ የትግራይ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? ይህ ሁኔታ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ላይ ምን
ተጽእኖ ያሳድራል፣ የሰላም ስምምነቱ አንኳር በሆኑት የስምምነት ነጥቦች ዙሪያ በምን ደረጃ ይገኛል? እውነተኛ ሰላም
በትግራይ ሆነ በተቀረው ኢትዮጵያ ለማስፈን ምን መደረግ ይኖርበታል? የሚሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት መንግስት ሆነ
የፖለቲካ ድርጅቶች ጉዳዩ በዋንኛነት ለሚመለከተው ህዝብ መስጠት የሚገባቸውን ነገር ግን እያደረጉት ያልሆነው ምልከታ
ለማቅረብ እሞክራለሁ።
2) የወቅቱ የትግራይ የፖለቲካ ሁኔታ ከሰላም ስምምነቱ ጋር በተያያዘ፤
በትግራይ ውስጥ የሰላም ስምምነቱ ከመፈረሙ ከወራት በፊት ወያኔ የጀመረው ጦርነት በትግራይ ህዝብ ላይ ያሳደረውን
እልቂትና ጥፋት የሚቃወሙ የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች በከተማው ጎዳናዎችና በየቤተክርስቲያኑ ይበተኑ ነበር። (የሰንድ
ማስረጃዎች አሉ) ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በጥቂት ሰዎች የሚደረግ ቢሆንም በራሱ በወያኔ ውስጥ ያሉ ጦርነቱ እንዲቆም
በሚፈልጉ የአመራር አካላት ጭምር የሚደገፍ ነበር።
ይህ እንቅስቃሴ ያሳሰባቸው የወያኔ አመራሮች “ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት አላቸው፣ የወያኔ መሪዎችን ለመግደል
አሲረዋል፤ እንዲሁም መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አስበዋል ” በሚል በወዲ ሃጎስ የምትመራዋን በመቀሌ ዙሪያ ለጥበቃ
የተመደበች ወደ አምስት መቶ የሰራዊት ብዛት የነበራትን አሉላ የተባለች ብርጌድ ላይ እርምጃ ወስደዋል። ወዲ ሃጎስ ለእስር
ተዳረገ። በመፈንቅለ መንግስት ክስ ተከሶ ዛሬም እስር ቤት ነው ። የሰራዊቱ አባላት ትጥቅ አውርደው መቀሌ ቢዝነስ ኮሌጅ
ውስጥ በተሃድሶ ስም በጥበቃ ላይ ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን እንዴት አታውቅም በሚል የመቀሌው የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር
ተስፋዬ ከስራው ተነስቶ ለቁም እስር ተዳርጎ ነበር። ኮሚሽነር ኪሮስ የተባለው የጸጥታ ሃላፊም ተመሳሳይ እጣ ገጥሞት ነበር።
የመቀሌው ከንቲባ ዶ/ር ገብረመድህን ከሃላፊነቱ በማንሳት ለእስር ተዳርጓል። በወያኔ ውስጥ ጦርነቱን የሚቃወሙ የአመራር
አካላት ቁጥራቸው እየተበራከተ በማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ አቅም እየፈጠሩ በመሄድ ላይ ነበሩ።
በዚህ ወቅት በጦር ሜዳ በኩል የሎጂስቲክ ችግር እያደገ፣ በሰራዊቱ ውስጥ የመንደርተኛነት ክፍፍል እየሰፋ፣ ወያኔ በገፍ
በቅርቡ ያሰባሰባቸው ወጣቶችና ከእስር ፈትቶ ወታደር ያደረጋቸው ወንጀለኞችና የድርጅቱ የቆዩ አባላቶች ተጣጥመው
መስራት እየተሳናቸው በሰራዊቱ ውስጥ ለጋራ አላማ መሰለፍ አዳጋች የሆነበት ሁኔታ በስፋት መስተዋል ጀመሮ ነበር። በርካታ
የሰራዊት አባላት ሰራዊቱን እየከዱ ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። እነዚህን ተመላሾች ስራዬ ብሎ
እያሳደደ የሚለቅም በኮማንድ ፖስት በኩል ሰፊ የተደራጀ ስራም ተጀምሮ ነበር። የሰራዊቱ መሪዎች የሙስና ድርጊት
እየባሰበት፣ ሙስናው የሰራዊቱን ቀለብ ከመሸጥ አንስቶ እንዲሁም አብዛኞቹ ወታደራዊ መኮንኖች (እንደወዲ እምበይትይ
የመሳሰሉ ጀነራሎች) ወደ ትግራይ የሚያስገቡ ኬላዎች እየዘጉ ከአፋር ፌዴራል ሃይሎች ጋር በመመሳጠር ከፍተኛ በሆነ
የጨው ንግድ በመስማራታቸው በሰራዊቱ ውስጥ ትልቅ መከፋፈል ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከአማራና ከአፋር ክልል የተዘረፈውን
ሃብት የግል እስከማድረግ ድረስ የሚያካትት ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ራሱ ወያኔ፣ ኮነኔል ጉና (ገብሩ) የአዋሽ አርባ አዲስ
ራእይ ማሰልጠኛ ሰራ አስኪያጅና በነበረው በሌሎችም ወታደራዊ አመራሮች ላይ የእስራት እርምጃ እስከመውሰድ ደርሶ
ነበር።
በራሱ በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ትግራይ ለገባችበት አሰቃቂ ሁኔታ ተጠያቂዎች መሆን የሚገባቸውን ሰዎች ለይተው
ሊጠየቁ ይገባል የሚል ድምጻቸውን ማሰማት የጀመሩ አባላት ብቅ ያሉበት ሁኔታ ተፈጠሮ ነበር። ወያኔ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ
ጠጋግኖ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ለማለት ነበር የሶስተኛ ዙር የወረራ ጥቃቱን በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ የከፈተው።
የሶስተኛው ዙር ወረራ አላማ ቀደም ብሎ እንደታሰበው አዲስ አበባ ለመግባትና የመንግስት ስልጣን ለመቆጣጠር ሳይሆን
ከወያኔ መሪዎች አቅምና ቁጥጥር ውጭ እየወጣ የነበረን መጨረሻው የማያምረውን የወያኔን የውስጥ ድርጅታዊ እና
የትግራይን ፈተናዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደራደር ለመፍታት የሚያስችል የተወሰነ የመደራደሪያ አቅም ለመፍጠር
የተደረገ ነበር። የትግራይ ህዝብና ወጣት የወያኔ አመራሮች ለጦርነቱና ለእልቂቱ የወያኔን ነባር መሪዎች ተጠያቂ
እንዳያደርጋቸው ከመስጋት የተደረገ የማደናገሪያ ወረራ ነበር። ወረራው ወያኔዎች እንዳሰቡት ሳይሆን የኢትዮጵያ ጦር ሰፊ
የትግራይን ክልል ተቆጣጥሮ ጭራሽኑ ትግራይ ወስጥ ገበቶ መቀሌን በቅርብ ርቀት የሚያይበት ሁኔታ ተከሰተ።
ይህ ወታደራዊ ሽንፈት በአንድ በኩል ወያኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲቀበል ያደረገው ቢሆንም
ከዚሁ ያልተናነሰ ጫና ያሳደረው በራሱ በወያኔ ውስጥ የተነሳው ነባር መሪዎቹን ሊበላ ወደሚችልበት ደረጃ እያደገ በመሄድ
ላይ የነበረው የውስጥ ትግል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
ወያኔዎች ከአሜሪካን መንግስት ባላስልጣናት ጋር በቅርበት እየተመካከሩ የሚሰሩ በመሆናቸው ወታደራዊ ሁኔታውን
የተረዳው የአሜሪካ መንግስት የወያኔ መሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመደራደር ራሳቸውን
ከጥፋት እንዲያድኑ ተጸእኖ ሳያደርግባቸው እንዳልቀረ መገመት ከባድ አይሆንም። የአሜሪካ ተጽእኖ በወያኔ ላይ ብቻ ሳይሆን
በኢትዮጵያ መንግስትም ላይ የተደረገ ለመሆኑ ፕሬዚደንት ኢሳያስ በጥር 2015 በሰጠው ቃለ ምልልስ ጥቆማ ሰጥቶናል።
በሌላ መንገድም ይህ ተጽእኖ ቀላል እንዳልነበር መረዳት ተችሏል። ይህም ሃቅ እንዳለ ሆኖ የወያኔ የውስጥ ሽኩቻን
ያሳደረውን ከፍተኛ ተጽእኖ አሳንሰን ማየት አይገባንም።
የውስጥ ሽኩቻው ከሰላም ስምምነቱ በፊት በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ በነባር አመራሮችና በወጣት አመራሮች መሃከል
ይካሄድ ነበር። ሽኩቻው ወጣቶች በጎደሉ የስራ አስፈጻሚ አባላት ምትክ አዳዲስ አባላት እንሙላ ሲሉ፣ ነባሮቹ ወቅቱ አዲስ
አባላት ለመሙላት አይፈቅድልንም የሚል ነበር። ወጣቶቹ አዲሶቹ አባላት ከወጣት መሪዎቹ ጎን ይቆማሉ ብለው ስለሚያስቡ
ሃሳቡን ሲገፉ ነበር። ነባሮች ይህን ስላወቁ ሃሳቡን ሲቃወሙ ነበር። ሌላው የሽኩቻ ነጥብ በስልጣን የሚታየው ያልተቀየረው
የአሻአ (የአክሱም ሽሬ እና አድዋ) ሰዎች በፖለቲካውም፣ በአስተዳደርም በወታደራዊ መስኮች የነበራቸው የበላይነት አሁንም
በከፋ መልኩ እየቀጠለ ከመሆኑ ጋር ተያያዞ የሚነሳ ነበር። በተደጋጋሚ በማእከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ይህ ጉዳይ እየተነሳ
ያወዛግብ እንደነበር ይታወቃል። ማወዛገቡ ብቻ ሳይሆን ሰዎች የመጡበትን አውራጃ እየጠቀሱ በታማኝነት በከሃዲነት
የመፈረጅ ንትርክ ጭምር የተለመደ ሆኖ ነበር።
ከሰላም ስምምነቱ በፊት በነበሩ ጥቂት ወራት በአጠቃላይ በወያኔ አመራር ካምፕ ውስጥ የነበረው ክፍፍል ለተፈጸመው ሁሉ
በተጠያቂነት እንያዛለን የሚሉ ጥቂት አመራሮችና ሊጠየቁ ይገባል በሚሉ በርካታ አባላት መካከል እያደገ የመጣ ክፍፍል
ነበር። እጣቸውን ከተጠያቂነት ጋር የሚያስተሳስሩ መሪዎች ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ራሳቸውን ለማዳን ሴራ በመሽረብ፣
እቅድ በማውጣት ነበር።
በዛን ወቅት የማእከላዊ ኮሚቴው ለሁለት እንደተከፈለ ሁሉ የሰራ አስፈጻሚውም ለሁለት
ተከፈሎ ነበር። ጌታቸው ረዳ እና ደብረጽዮን በአንድ ወገን፣ ጌታቸው አሰፋና ፈትለወርቅ አለም ገብረዋህድ በሌላው ጎራ
ቆመው ነበር። የጌታቸው ረዳ ነገር መቼም አስገራሚ ነው መባሉ አይቀርም። በዚህ የውስጥ ሽኩቻ በትግራይ ውስጥ ከሚገኙ
ከ 35 ቱ (ከ 37 ቱ ሁለቱ ውጭ ሃገር ናቸው) የወያኔ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መሃል በየቀኑ አቋማቸው የሚለዋውጡ አስራ
አራት አባላት ያሉት ሲሆን የተቀሩት በሁለት ጎራ ተከፍለው የእነዚህ የ 14 ኮሚቴ አባላት ድጋፍ በማሰባሰብ
የሚተናነቁባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ነበሩ።
የውስጥ ሽኩቻው የደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ የሚያሳየው ሃቅ በጥር 2015 ውስጥ ተከስተ። የወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ እና
ከእያንዳንዱ አርሚ ሶሶት ሶሶት ሰው የተወከለበት በደጀን የርእሰ መስተዳደሩ ቢሮ፣ ከጥር 7 እስከ ጥር 10 በተደረገው ስብሰባ
ኮሚቴው በወሰነው ውሳኔ መሰረት ደብረጽዮን ገብረሚካኢኤል፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አለም
ገብረዋህድና ጌታቸው ረዳ፣ ሁሉም የህወሃት የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ አባላት፣ በትግራይ ለሆነው ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው
በሚል ከስልጣናቸው ታግደው እንዲቆዩ እስከመወሰን እና ይህ ውሳኔ በምክር ቤት እንዲጸድቅ ጥያቄ እሰከማቅረብ ደርሶ
ነበር።
የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የጥቂት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የአቋም መገለባበጥ ከሚታይበት ሁኔታ በስተቀር በወያኔ
ውስጥ በትግራይ ለውጥ እንዲመጣ በሚፈልጉ እና በማይፈልጉ፣ የሰላም ስምምነቱን በሚደግፉና በሚቃወሙ ሁለት ዋና
ቡድኖች የማእከላዊ ኮሚቴው እንደተሰነጠቀ ነው።
አንዱ ቡድን የሞንጀሪኖ ቡድን በመባል የሚታወቀው ሲሆን የውናትና የባይቶና (በስም የተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸው ነገር
ሁኔታዎች ሲከፉ ከዚህ ቡድን ጋር የሚለጠፉ እንደሆነ ይታወቃል) ድጋፍ ሲኖረው፣ ከወታደራዊ ተቋሙም ጋር ከተወሰኑ
አካላት ጋር ቁርኝት ያለው ቡድን ነው። የዚህ ቡድን አባላት ጌታቸው አሰፋ ራሷ ሞንጀሪኖ (ፈትለ ወርቅ ገ/እግዚአብሄር
)አለም ገብረዋህድ፣ አልማዝ ገ/ጻድቅ የክልሉ የትራንስፖርት ሃላፊ፣ ገነት አረፈ የማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ፣ ሃጎስ ጎድፋይ ጤና
ቢሮ ሃላፊ ( አሁን የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት ሃላፊ)፣ ፍስሃ ሃፍተፅዮን ፣ ሃዱሽ ዘነብ ፣ አማኑኤል አሰፋ ፣ ይትባረክ አምሃ
የመቀሌው አዲሱ ከንቲባ፣ አርአያ ግርማይ፣ ዶ/ር አማኑኤል ሃይሌ፣ ሊያ ካሳ የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ፣ እነዚህ የሰላም
ስምምነቱ በመቃወም በጋራ የቆሙ ሲሆን፤ በሌላ ወገን ከጌታቸው ረዳና ሌሎች ሰላሙን የሚደግፉ አባላት፣ ብርሃነ
ገብረየሱስን፣ የአሁኑ የምእራብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ነጋ አሰፋ፣ የህብረት ስራ ማህበር የክልሉ ሃላፊ፣ ሰብለ ካህሳይ
የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊ፣ በየነ ሙክሩ የፋይናንስ ሃላፊ፣ ሃብቱ ኪሮስ ቆይቶ የተቀላቀለ የደቡብ ዞን አስተዳዳሪ፣ ዶ/ር
አትንኩት መዝገበ፣ ረዳኢ ሃለፎም የትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ለምለም ሃድጉ ባህልና ቱሪዝም ሃላፊ
የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ በወያኔ ማእከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ተከራክረው ያሸነፉ ናቸው። አንዲሁም ከተለያዩ አርሚዎች
የተወከሉ የጦር መሪዎች አብዛኞቹ የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ ከእነዚህ የለውጥ ሃይሎች ጋር በመሆን የቆሙ ነበሩ፡፡ በዚህ
ስብሰባ ጌታቸው አስፋ አሞኛል በሚል ሰበብ ስብሰባውን አቋርጦ አስከመሄድ ደርሷል። በተጨማሪም ጄነራል ወዲ
እምበይተይ በስብሰባው ሊገኝ አልቻለም ፡፡
ይህም ሆኖ የሰላም ስምምነቱን ያልተቀበለው ቡድን በጁ ባለው የገንዘብና አሰተዳደራዊ አቅም እና በሰራዊቱ አመራር ውስጥ
ባለው ድጋፍ የተለያዩ እንቃስቃሴዎችን ማድረጉን አላቆመም። ይህን አቅም በመጠቀም ጥር 24 እና 25 /2015 ከመላው
ትግራይ የቡድኑ ደጋፊዎች ናቸው የሚላቸውን እስከ 600 የሚደርሱ ወጣት ካድሬዎች መቀሌ በሃውልት ሰማእትታ አዳራሽ
በማሰባሰብ፣ “ህወሃት ታሪካዊ ድርጅት ነው መፍረስ የለበትም፣ ይህን ታሪካዊ ድርጅት ለማፍረስ ከሚሰሩ ተንበርካኪዎች ጋር
መታገል አለብን” የሚል አጀንዳ መወያያ እንዲሆን አድርጓል። (በዚሁ አጋጣሚ ተንበርካኪዎች በሚባሉ ግለሰቦች ላይ ግድያ፣
የግድያ ሙከራ መፈጸም መጀመሩን፣ ወደፊት ይህ የወንጀል ድርጊት እየጨመረ እንደሚመጣ መታወቅ አለበት።) በዚህ
ስብሰባ ላይ ሁሉም የማእከላዊ ክሚቴ አባላት ተገኝተው ነበር። አላማው ለውጥ ፈላጊ አመራሮችን ለማሸማቀቅ ከተቻለም
ከዚህ በፊት በ 1993 መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቹን በካድሬዎች አማካይነት አዋክቦ ከድርጅቱ እንዲባረሩ ያደረገውን አሰራር
ለመድገም ነበር። እንዲህም ሆኖ ስብሰባው ለወጥ በሚፈልገው ወገን አሸናፊነት ተጠናቋል።
ይህ መንገድ አላዋጣ ያለው ጸረ ሰላም ቡድን ከለውጡ በኋላም ስምምነቱን የማጨናገፍ በኢትዮጵያ ደረጃም ሃገር የማናጋት
እቅዱን በስራ ለመተርጎም የራሱን እንቅስቃሴዎች ማድረጉን ቀጥሏል። ለስራ ገንዘብ ያስፈልገናል በሚል 350 ሚሊዮን ብር
ለማሰባሰብ አቅድ አውጥቶ ይህን ገንዝብ የመቀሌን ከተማ መሬት በመቸብቸብ ገንዘቡን ማሰባሰብ ችሏል። የመቀሌን መሬት
የገዙት ግለሰቦች ከአማራና ከአፋር ክልል እንዲሁም ከራሱ ከትግራይ ህዝብ ገንዘብና ንብረት የዘረፉ የሰራዊቱ መሪዎችና
ቤተሰቦቻቸው ናቸው።
ይህን ገንዘብ በመጠቀም ለውጥ የማይፈልገው ቡድን ሰራዊቱ ውስጥ ካሉት አጋሮቹ ጋር በመሆን በልዩ ሁኔታ ለተመለመሉና
ለሚያስለጥናቸው እስከ 7000 የሚደርሱ የሽብር ስራ በመላው ኢትዮጵያ ለማካሄድ ለሚሰለጥኑ ሴትና ወንድ አሸባሪዎች
ማሰልጠኛ በተግባር ላይ እያዋለው ነው(የመሰልጠኛ ቦታው ይታወቃል)። የአሰልጣኝነት ሚና የወሰዱት ግለሰቦች የልዩ
ኮማንዶ አሰልጣኞች ብቻ ሳይሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ የቀድሞ የኢትዮጵያ የደህንነት አባላት ጭምር ናቸው። እነዚህ
ወጣቶችን እስራኤል ጠላቶቿን በተለያዩ ሃገሮች ውስጥ ለማጥፋት እንደምታሰማራቸው የጥቃት ቡድኖች እንጠቀምባቸዋለን
በሚል ሂሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የተለያዩ የሽብር ስራዎችን የሚያከናውኑ ተደርገው እየተቀረጹ
ነው።
ከዚህ ውጭም ወያኔዎች በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖር ለመጠቀሚያነት ሲያዘጋጇቸው የነበሩ በተለይ አዲስ አበባ ገብተን
ስልጣን እንይዛለን ባሉበት ወቅት እንደ መናጆ ሊገለገሉባቸው አሰባስበዋቸው የነበሩ የተለያዩ ነጻ አውጭ ድርጅቶች ሰራዊቶች
ስልጠና እንዲቀጥል ተደርጓል። በመቀሌ አካባቢ ብቻ እስከ 8000 ቁጥር ያለው የኦነግ ሰራዊት አሁንም ያለ ሲሆን፣ በሮማይ
ኪሮስ የሚመራ የአገው ነጻ አውጭ ታጣቂዎችን ሳምረ በሚባል ቦታ ማሰልጠኑን አሁንም አላቆመም። የአፋርና የሌሎችም ነጻ
አውጭዎች ነን የሚሉ ድርጅቶች አሁንም ሰላም ከማይፈገው ቡድን ጋር ተቀራርበው እየሰሩ ነው።
የእነ ጌታቸው አሰፋና የነሞንጀሪኖ ቡድን፣ በአስተዳደርና በወታደሩ ውስጥ ካለው ጉልበቱ በላይ፣ በጁ የገባው ሃብት የሰላም
ስምምነቱን የራሱን ቡድን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት እየተጠቀመበት ይገኛል። መንግስት ከጦርነቱ በፊት ወደ ትግራይ ልኮት
የነበረው ገንዘብና የወያኔ የዶላር ክምችት አሁንም ያለው በዚህ ቡድን እጅ ነው። የተወሰነ ዶላርና ብር በተቀበረበት ብል
በልቶት ቢገኝም፣ አሁንም ከፍተኛ ክምችት ያለው ገንዘብ በእዚህ ቡድን እጅ በተለያዩ ግለሰቦች ቤት በአደራ ተቀምጧል።
ከኤፈርት ካምፓኒዎች አንዱ የሆነው በኢዛና የማእድን ኩባንያ ቀድሞ ሲወጣ የነበረና በጦርነቱም ወቅት እየወጣ የነበረው
ወደ አምስት ኩንታል የሚሆን ወርቅ በተመሳሳይ መንገድ የሰላም ስምምነቱን በማይደገፍው ቡድና ቁጥጥር ስር ሆኖ
በግለሰቦች እጅ ተቀምጧል።
በጦርነት ወቅት ይደረግ እንደነበረው ዛሬም ወርቅና ሳፋየር በእርድታ ማስተባበሪያ መኪናዎች፣ በተለይ በአፋር፣ በአፍዴራና
ሶርዶ ኬላዎች በአባዲ አፍሮ መኪናዎች ከትግራይ እየወጣ ኢትዮጵያ ውስጥና ጅቡቲ እየተሸጠ ነው። በጦርነቱ ወቅት ሲሸጥ
የነበረው ወርቅና ሳፋየር ብቻ ሳይሆን፣ ለትግራይ ህዝብ በእርዳታ የገባ መድሃኒት ወደ አፋርና አማራ ክልል እየወጣ ይሸጥ
እንደነበር የራሱ የወያኔ የግምገማ ሰነድ አመላክቷል። ይህ የእርዳታ መድሃኒት ዛሬም በዘመድ በተሳሰሩ የትግራይ መድሃኒት
ቤቶች ውስጥ መሸጡን እንደቀጠለ ነው ። ለምሳሌ መድሃኒቱ ሲሸጥባቸው ከነበሩ ቦታዎች መካከል ፋሚሊ ፋርማሲ ፣ ሂወት
ፋርማሲ ሲሆኑ እነዚህ መድሃኒትቶችም ከ EPSA ፣ ከዓይደር ሆስፒታል እና ከመቀሌ ሆስፒታል በአቶ አለማየሁ የ EPSA
ስራ አስኪያጅ፣ ዶ/ር ሃጎስ ጎዲፋይ፣ ዶ/ር ፊሊሞን የመቀሌ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አማካኝነት እየወጡ ይሰራጩ እንደነበረ
በሚስጥር የተያዘው፣ ጉጅለ ሰለስተ በተባለው / የወያኔ ኢንተለጀንሲ ሰርቪስ በ 3/12/2014 ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበ ሪፖርት
ያመለክታል ፡፡
በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ዳያስፖራዎች ለቤተሰቦቻቸው ይልኩት የነበረው ዶላር ጅቡቲ ውስጥ የወያኔ ተባባሪዎች በከፈቱት
አካዎንት እየገባ ብሩ ትግራይ ውስጥ እየተከፈለ ነበር። በዚህ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች የትግራይ ዳያስፖራ ለቤተሰቦቹ
ከሚልከው ገንዘብ እስከ 50 ከመቶ የሚደርስ ኮሚሽን ያስከፍሉ እንደነበር ይታወቃል። 30 በመቶ ኮሚሽን የተከፈለባቸው
የሰነድ መረጃዎች በእጃችን አሉ። ይህን ስራ ትግራይ ውስጥ የሚቆጣጠረው ሰላም የማይፈልገው ቡድን ሲሆን፣ ከትግራይ
ውጭ ደግሞ ስራ የሚያስተባብሩ ከወያኔ ጋር የሚሰሩ በስም የምናውቃቸው ትግራዋይ ያልሆኑ የኢትዮጵያ ባለሃብቶች
ጭምር አሉ። ሌሎችንም ከወያኔ ጋር የተያያዘ ከፍተኛ ሃብት የነበራቸውን ግለሰቦችን ሃብት የሚያንቀሳቅሱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ
ንብረት እየሸጡ ገንዘቡን በዶላር የሚያስተላልፉ፣ ዛሬ የወጭ ምንዛሪ ዶላር ከመቶ ብር በላይ በጥቁር ገበያ እንዲዘረዘር ያደረጉ
ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔዎች ተክተው እየተንቀሳቅሱ ነበር፤ አሁንም አልቆመም። በትግራይ የባንኮች መከፈት በጅቡቲ
ወስጥ ከፍተኛ ኮሚሽን በመውሰድ ይደረግ የነበረውን የዶላር ምንዛሪ ያስቀረው ቢሆንም በሌላ በኩል ከየትኛዎቹም ክልሎች
ይበልጥ ከባንክ ውጭ ትግራይ ውስጥ በጸረ ሰላም ሃይሉና በግለሰቦች እጅ የሚገኘውን ጥሬ ገንዘብ በትግራይና በሌላውም
የኢትዮጵያ ግዛት የዶላር ምንዛሬውን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ዘርዛሪዎቹ ከሞንጆሪኖ ቡድን ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ ግለሰቦች
ሆነዋል። ህገወጡን ምንዛሬ እስከ 120 ብር አድረሰውታል።
በትግራይ ውስጥ ያለውን በለውጥ ፈላጊና ለውጥ በማይፈልጉ ሃይሎች መሃከል ያለውን ሽኩቻ ከዚህ በላይ የተቀመጠውን
ሃተታ ከጀርባ በማድረግ ስንቃኘው ነው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ፖለቲካው የሚሄድበትን መንገድ መረዳት የምንችለው።
የሰላም ስምምነቱ በፖለቲካ መስኩ ያስቀመጠው መፍትሄ በትግራይ የሽግግር መንግስት እንዲሚቋቋም፣ ይህን የማቋቋም
ሃላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚወስድ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በስምምነቱ መሰረት የተሰጠውን ስልጣን ምን
እያደረገበት እንደሆነ ባናውቅም ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ቡድኖችና በሶስተኛ ደረጃ የተጨመረ የነጻድቃን ቡድን ታክሎበት
የሽግግሩን ሂደት በበላይነት ለመቆጣጠር እየተራኮቱ ያሉበት ሁኔታ ይታያል።
የተጠያቂነት ፍራቻ ያለበት የሞንጀሪኖ ቡድን የመጀመሪያውን እርምጃ በመውሰድ የካቲት 3 /2015 ሶስት ከወያኔ ማእከላዊ
ኮሚቴ፣ ሶስት ከወታደሩ ክንፍ፣ ሶስት ከምሁራን የተወጣጣ የጊዜያዊ መንግስት መስራች ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር። በዚህ ኮሚቴ
ውስጥ ፈትለወርቅና ራሱ ጌታቸው አሰፋ ራሳቸውን ማስገባት ያልፈለጉት በህዝብ ተቀባይነት ስለሌለን ከጀርባ ሆነን በራሳችን
ሰዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴውን እንመራለን በሚል ስሌት ነው። የዚህ ኮሚቴ አባላት ከህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ኢሳያስ
ታደሰ፣ አማኑኤል አሰፋ፣ ዶ/ር ሃጎስ ጎድፋይ በሞንጀሪኖ ቡድን የተመረጡ ሲሆኑ፣ ከሰራዊቱ ታደሰ ወረደ (ጀ/ል) ተክላይ
አሸብር (ጀ/ል)፣ ጉእሽ ገብረ (ጀ/ል) በተመሳሳይ ያለ ሰራዊቱ እውቅና እንዲካተቱ የተደረጉ፣ እንዲሁም ከምሁራን፣ ሙሉ
ኪዳነ ማሪያም፣ መረሳ ጸሃዬ፣ ሃንሳ ረዳ በቡድኑ በተመሳሳይ መንገድ የተመረጡ ናቸው። ከምሁራኑ፣ የተመረጡት ሙሉ ኪዳነ
ማሪያም፣ መረሳ ጸሃዬ፣ ሁለቱ የፌደራል መንግስቱ ያልተቀበለው በትግራይ የተደረገው ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚሽን
ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመነበር ሆነው በወያኔ ተሹመው የነበሩ ናቸው። ይህ ኮሚቴ በፍጥነትና በዚህ መልኩ የተዋቀረበት
ዋናው ምክንያት የሽግግር ሂደቱን ነባሮቹና በተጠያቂነት እንያዛለን ብለው የሰጉት የህወሃት አመራሮች ለመቆጣጠር አስበው
ነበር።
ይህን በነጌታቸው አሰፋ ውሳኔ ወደ ሽግግር መንግስት አሸጋጋሪ በሚል ስም የተቋቋመ ኮሚቴ ከህበረተሰቡ ቅቡልነት
ለማግኘት ብዙ ጥረት አድርጓል። የተሳካለት ሊሆን አልቻለም። የካቲት 9 2015 ከሶስት በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ
ፓርቲዎች ጋር በዘማሪያስ ሆቴል ለአሸጋጋሪ ኮሚቴው ድጋፍ ለማሰባሰብ የተጠራው ስብሰባ አብረው ፎቶ ከመነሳት የዘለለ
ሌላ ምንም ውጤት ሳያመጣ በተቃውሞ ተበትኗል። በተከታታይ ቀናትም በፕላኔት ሆቴል ከሙያ ማህበራት፣ ከጋዜጠኞች
ማህበር፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከነጋዴዎች ማህበር፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ማህበራት ጋር የተደረገው ስብሰባ ሃያ ደቂቃ
ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በተቃውሞ ተበትኗል። ከዚህ በኋላም ከመላው ትግራይ ከእያንዳንዱ ወረደ 3 ተወካዮች በመጥራት
በደጀን የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት የተደረገው ስብሰባ የኮሚቴውን አባላት ማን መረጣችሁ በሚል ጥያቄ በማፋጠጥ ተበትኗል።
ከዚህ በተጨማሪ ከሰራዊቱ ተወክለዋል የተባሉትን ግለሰቦች ሰራዊቱ ያልመረጣቸው፣ እነ ጻድቃን እንኳን የማያውቋቸው
በመሆናቸው ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ከዚህ ውዝግብ በኋላ ነው ጻድቃን የኮሚቴው አመሰራረት ትክክል እንዳልነበር እና
ሁሉንም አካታች ሊሆን ይገባዋል የሚል ረጅም ሰነድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “አዘጋጅቶ” ለአለም ያሰራጨው። በእንግሊዝኛ
ቋንቋ የተጻፈበት ምክንያት ሪፖርቱ ለአሜሪካ መንግስት እንዲቀርብ ታስቦ የተደረገ እንጂ የመጀመሪያው አድማጭ የትግራይ
ህዝብ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።
ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ ቅቡልነት ያጣው ኮሚቴ የካቲት 13 2015 ስራውን በተመለከተ ሪፖርት ለማቅረብና ግምገማ
ለማድረግ በሚሉ አጀንዳዎች ሰበብ የህዋሃት ስራ አስፈጻሚና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ እንዲቀመጡ አደረገ። ይህን
ስብሰባ ከጀርባ ሆኖ የሚመራው ያው ሰላሙን ተቃውሞ የቆመው ቡድን ነው። ይህ ስብሰባ የትም መድረስ ባለመቻሉ የካቲት
15 2015 የሴንትራል ኮማንድና ወታደራዊ ኮማንድ እንዲካተቱበት ተደርጎ ስብሰባው ቀጠለ።
በእዚህ እለት በተደረገው ስብሰባ ደብረጽዮን ከስልጣን እንዲወርድ ተጠይቆ ከስልጣን ከሚወርድ ሞቱን እንደሚመርጥ በፊት
ለፊት በስብሰባው ላይ በመናገሩና ደብረጽዮን ከሞንጆሪኖ ቡድን ሰዎች በላይ በህዝብ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የሞንጆሪኖ
ቡድን ሴረኞች አካሄድ ችግር ገጠመው። በዚህ ስብሰባ ላይ ደብረጽዮን አፉን ሞልቶ “ዶ/ር አብይ ከፈለግህ በፕሬዚደንትነት
መቀጠል ትችላለህ” ብሎኛል በማለት ተናግሯል።
አሁንም ከገባበት ችግር ለመውጣት የሞንጆሪኖ ቡድን አስቀድሞ የተዘጋጀበትን የተሳታፊውን ቁጥር ያበዛ በተከታታይ
የተደረገ ስብሰባ ላይ ተቀመጠ። ስብሰባው ጉባኤ የሚል ስም የተሰጠውና በህዝብ ተወክለናል የሚሉ ነባር አመራሮች፣
የህወሃት የስራ አስፈጻሚና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የሰራዊቱ ኮማንድ እና የሴንትራል ኮማንድ አባላት የተሳተፉበት ነበር።
የጉባኤተኞች ብዛት በጥቅሉ 401 ሲሆን 351 ድምጽ በመስጠት የሚሳተፉ፣ 50 ድምጽ መስጠት የማይችሉ ታዛቢዎች ነበሩ።
በዚህ ስብሰባ ላይ ጻድቃን አልተሳተፉም ነበር ። ሆኖም ግን በምግበይና ወዲ አሸብር አሸማጋይነት ከሰአት በኋላ ተሳትፏል ።
በጉባኤው ላይ ፣ ሰራዊቱ የመረጣቸው ተወካዮች፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከሲቪክ ማህበራት ቢሳተፉም የተወከሉበት መንገድ
ትክክል ባለመሆኑና ህወሃት የመረጣቻው በመሆናቸው በህዝቡ እና እንወክለዋለን በሚሉት አደረጃጀት ተቀባይነት ኣላገኙም
። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ሙሉ በሙሉ አልተሳተፉም።
ይቀጥላል
ህዳር 2011
በሃገራችን ህልውና እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ያንዣበቡ አደጋዎች እና የመውጫ መንገዶች
ካለፈው የቀጠለ
3. የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተገኘ ጠባብ እድል የውርጃ አደጋ
በጣም የሚገርመውና የሚያሳሰበው ሌላ ጉዳይ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች የዴሞክራሲ ስርአት ምስረታ
ህልማችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የከፋ አደጋ ውስጥ መውደቁን ለማየት ፈቃደኞች አለመሆናችን ነው። ይህን
አደጋ እንዳናይ የሚያድርጉ ነገሮች ብዙ ናቸው። “ከሞላ ጎደል የፖለቲካ እስረኛ የሚባል ነገር አለመኖሩ፣
ሚድያዎች በነጻነት የሚዘግቡ መምሰላቸው፣ የታገዱ የፖለቲካ ድርጅቶችና ድረ-ገጾች አለመኖራቸው፣
በፌደራል መንግስቱ በኩል እውነተኛ ዴሞክራሲ በሃገር ላይ እንዲኖር አስፈላጊ ናቸው የተባሉት ተቋማት ነጻና
ገለልተኛ ሆነው እንዲቁቋሙ ባለስልጣናቱ ደፋ ቀና ማለታቸው፣ በመንግስትና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መሃል
ቅርበት ያለው፣ ግልጽነት የተሞላበት ግንኙነት መኖሩና ወዘተ፣ ለተሳሳተ የሁኔታዎች እውነተኛ ግንዝቤ
እንዳይኖረን እያደረጉ ነው።
ሆኖም ግን ሁኔታዎችን በጥሞና ለተመለከተ የዴሞክራሲ ምህዳሩ አደገኛ በሆነ መንገድ እየጠበበ መሆኑን
ማየት ይችላል። የፖለቲካው ምህዳሩን በማጥበብ ላይ ያለው መሰረታዊ ምክንያት አሁንም የዘር ፖለቲካ
ነው። የፌደራል መንግስቱ የፈለገውን ያህል ቅን ቢሆን ዋነኛ የፖለቲካው ትግል በሚደረግበት ቦታ ላይ
የሚገኙት የመንግስት አካላት ተመሳሳይ ቅንነት ማሳየት ካልቻሉ የፌደራል መንግስቱ ጥረት ከንቱ ሆኖ የሚቀር
ነው።
ችግሩን ባጭሩ ለመግለጽ ልሞክር። ተጨባጭ የሆነው የሃገሪቱ የፖለቲካ አውደማ የሚገኘው በፌደራሉ እጅ
ሳይሆን በክልሎች እጅ ነው። ፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ የሆነው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት
ያለው በፌደራል ደረጃ ሳይሆን በክልሎች እጅ ነው። ፌደራል መንግስቱ ዜጎችን የሚያኖርበት የራሱ ነጻ ክልል
ወይም ወረዳ የለውም። ኢትዮጵያ የፌደራሉ መንግስት ጉዳይ ትሁን እጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንተናዊ
ህይወት በክክሎችና በስራቸው ባሉ ዞኖች ወረዳዎችና ቀበሌዎች እጅ ነው። መሰረታዊ የሆነው የዜጎች
ህይወት ተጀምሮ የሚያልቀው በክልሉ መንግስታት ስልጣን ስር በሚገኙ ግዛቶች ውሰጥ ነው። በፖለቲካው ላይ
ብቻ ስናተኩር፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ስልጣንን በወረዳ ይሁን ወይም በክልል ወይም በሃገር አቀፍ ደረጃ
መያዝ የሚችለው የምርጫ ወረዳዎች ላይ በሚያደርገው ወሳኝ እንቅስቃሴና ፉክክር ነው። እነዚህ የምርጫ
ወረዳዎች በክልል መንግስታት እጅ እንጂ በፌደራል መንግስቱ እጅ አይደሉም። የምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ
ስርአት፣ የመከለካያ፣ የደህንነት የፖሊስና የሚድያ አካላት በፌደራል መንግስቱ ጥረት ምንም ያህል ነጻና
ገለልተኛ ሆነው ቢደራጁ በወረዳ ደረጃ የሚፈይዱት ነገር አይኖርም። ወረዳዎች የሚገኙት ዘርን መነሻ አድርጎ
በተዋቀረ የክልል አስተዳደርና ዘርን መሰረት አድርገው በተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች እጅ ነው።
እነዚህ ክልሎች የራሳቸው በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሚሊሻ አባላት፣ በሽዎች የሚቆጠሩ የልዩ ሃይል አባላት፣
የፖሊስ አባላትና የደህንነት አባላት አሏቸው። በዚህ ላይ በነዚህ በዘር በተደራጁ ፓርቲዎችና በስራቸው ባለ
የክልል መንግስት ሙሉ ቁጥጥር ስር ያለ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች አሏቸው። እነዚህ ክልሎች በዘር
ላይ የተመሰረተ ፓርቲ የሚያንቀሳቅሰው የሲቪል ሰርቪስና ይህ ፓርቲ የሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ በጀት
አላቸው። ከፍተኛ የመሬትና የቤት ሃብት አላቸው። ይህንን ሁሉ ጉልበት እንዳሻቸው መጠቀም የሚያሰችል
የፌደራል መንግስቱ ገድብ ሊያበጅበት የማይችል ነጻነት አላቸው። ይህን ሃብትና ጉልበት ተጠቅመው ዜጎችን
በፈለጉት መንገድ ለነሱ አጎብድደው እንዲኖሩ የሚያስደርግ የበላይነት አጎናጽፏቸዋል። አንድ ዜጋ ቤት
ቢሰጠው በነሱ በጎ ፈቃድ እንጂ ቤት በዜግነቱ ማግኘት የሚገባው መብት እንዳልሆነ አድርጎ እንዲያይ
አድርገውታል። እነሱን ሲያስቀይም ቤቱን እንደሚያጣ ያውቀዋል። በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች
የሚያገኙት ብድር፣ ብድር የሰጣቸውን የክልል መንግስትና ፓርቲ እስከደገፉና እስከሚደግፉ ብቻ እንደሆነ
ያውቁታል። ብድሩ ቢስማማቸው ነገር ግን ብደር የሰጣቸው የመንግስት አካልና የፓርቲው ፖሊሲዎች
ባይጥማቸው የፖለቲካ ነጻነታቸውን ተግባራዊ ማድረግ አይችሉም። ቤት፣ ብድር፣ መሬት ከፓርቲ ጋር
በሚደረግ ቁርኝት በሚሰጥበት፣ ግለሰቦች ምንም አይነት የኢኮኖሚ ነጻነት ሊኖራቸው በማይችል ኢትዮጵያን
በመሰለ ደሃ ሃገር ውስጥ የመንግስት ስልጣን የሚይዙ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዴት ሁሉንም ህዝብ ያለፍላጎቱ
የፖለቲካ ድርጅታቸው ቁራኛ ወይም ምርኮኛ ማድረግ እንድሚችሉ ግልጽ ነው። ሃብታሙ ሁሉ ለኢህአዴግ
በሚሊዮኖች ሲያዋጣ የኖረው ያለማዋጣትን መዘዝ በሚገባ ስለሚያወቀው እንጂ ኢህአዴግን ወዶ እንዳልሆነ
የታወቀ ነው። ከባለስልጣናቱ ጋር በሽርክና ከሚዘረፈው ሃብታም ውጭ ስላለው ሃብታም ነው የማወራው።
የደሃው እጣ ደግሞ ከሃብታሙም የባሰ ነው። በክልሎች ውስጥ የንብረት፣ የሃብት፣ የቅጥር፣ የሰራ ዋስትና
ሌሎችንም ለማንኛውም ዜጋ በዜግነቱ ማግኘት የሚገባውን ግልጋሎቶች ፈልጎ ከክልል መንግስታት ገዥ
ፓርቲዎች የተለየ የፖለቲካ ልዩነት ይዞ መገኘት የማይታሰብ ነው። በሆዱ ወይም መኝታ ቤቱን ዘግቶ፣
ሚስቱንና ሰራተኛው እንዳይሰሙት ተጠንቅቆ፣ የሚያምንበትን የፖለቲካ እመነት ይጮህ ካልሆነ በስተቀር
በአደባባይ ሰለክልል ባላስልጣናት ያለውን በጎ ያልሆነ አመለካክት ደፍሮ የሚናገር ያበደ ብቻ ነው ።
እነዚህ ከላይ የጠቀኳቸው በክልሎች እጅ ያሉ ወታደራዊና ሲቪል ተቋማት በፌደራል እጅ እንዳሉት ተቋማት
ነጻና ገለልተኛ ማድረግ አይቻልም። ከፍጥረታቸው አንድን ዘር ለይተው እንዲያገለግሉ የተደራጁ ናቸው።
የፍጥረታቸው ድርና ማግ ገለልተኛነት ሳይሆን ውግንና ነው። ዋናው የፖለቲካ አውደማ ላይ በዚህ ደረጃ
ፈጽሞ የገለልተኛነት እሳቤ ሊዘራባቸው የማይችሉ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ በምን አይነት ሳይንስና ቀመር ነው
በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሆነ ዴሞክራሲያ ሽግግር ማድረግ የሚቻለው? ዴሞክራሲው
ቀርቶብን እንዲህ አይነቶቹ የፈረጠመ ጡንቻ ያላቸው የፌደራል መንግስቱን በጉልበት መገዳደር የሚችሉ
ክልሎች በተመሰረቱበት ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነው የሃገርን ህልውና ማስከበር የሚቻለው?
በእነዚህ በዘር በተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎች የሚዘወሩ መሳሪያ የታጠቁና ያልታጠቁ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ
እንኳን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የምርጫ ውጤትን መቁጠርና የምርጫ ወጤትን
በጸጋ መቀበል ቀርቶ ምርጫ የሚባል ነገር ገና ስሙ ባልተጠራበት ወቅት እንኳን በእነዚህ ክልሎች ነጻ ሰላማዊና
ህጋዊ የፖለቲካ እንቅስቅሴ ማድረግ ወደማይቻልበት ሁኔታ ሃገራችን ገብታለች። በዚህ ረገድ የሚታየው ችግር
የለውጥ ሃይሎቹ ከመምጣታቸው በፊት ከነበረውም የከፋ ሆኗል።
ቀደም ባሉት አመታት ምርጫውን በጉልበት ወይም በሌብነት አሸንፈዋለሁ የሚል መተማመን የነበረው
ኢህአዴግ በሃገር ወስጥ ለነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች በየትኛውም ቦታ ዞረው ማደራጀትና መቀስቀስ ይፈቅድ
ነበር። በወቅቱ ግን የፌደራል መንግስቱ ስለዴሞክራሲ የሚያስተላልፈው መልእክት የምር መሆኑን ክልሎች
ተረድተውታል። በዚህ የተነሳ “ዴሞክራሲ ያለ ለማስመሰል ለተቃዋሚዎች ነጻነት እንስጣቸውና በክልላቸን
ይንቀሳቀሱ” የሚለውን ጨዋታ አቁመዋል። “ወደ ቀያችን ትደርስና ውርድ ከራስህ” የሚል ማስፈራሪያ
ከየክለሉ መድረስ የሚጀመረው ተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ክልሉ መንቀሳቀስ ከማሰባቸው በፊት ሆኗል።
የክልሎች ዴሞክራሲያዊ ጭምብል ወልቆ አይን ያወጡ አፋኝ አሰተዳደሮች ሆነዋል።
ዛሬ ባለንበት ወቅት ከአዲስ አበባ ውጭ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበበት
ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። አዲስ አበባ ውስጥም የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ በዘር በተደራጁ
የፖለቲካ ቡድኖች ተጽእኖ የተነሳ ነጻና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚስተጓጎልበት ሁኔታ ይታያል። ከአዲስ
አበባ ውጭ ይህ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ምን እንደሚመስል እንመልከት፤
3.1. በየክልሎች ስልጣን ላይ ያሉ በዘር የተደራጁ ሃይሎች የፖለቲካ ምህዳር የማጥበብ ሚና
በስልጣን ላይ ያሉ ክልሎችን እየተቆጣጠሩ ያሉ ሃይሎች ከማንም በላይ የፌደራል መንግስቱ በአንጻራዊነት
ያሰፋውን የፖለቲካ ምህዳር የማጥበብ ጉልበቱ አላቸው። የማጥበቡ ስራ በዋንኛነት የሚሰራው በፌደራል
ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ በመገናኘት የተለያዩ ክልሎች በመወከል በሚሰሩ ከፍተኛ የክልል ባለስልጣናት
አይመስልም። እነዚህ ባለስልጣናት፣ ሁሉም ባይሆኑ፣ ሃገርና ህዝብ የገባበትን አደገኛ አጣብቂኝ በመረዳት
በግላቸው ስልጣንና ጥቅም፣ በራሳቸው ድርጅት ኪሳራ ጭምር ሃገርና ህዝብን ለማዳን ቆርጠው
ለመነሳታቸው ጥርጥር የለኝም። ችግሩ የሚጀምረው ከነዚህ ባለስልጣናት ቀጥሎ በሚመጣው የስልጣን
እርከን ላይ በተቀመጡት የየክልሉና የየዞኑ ሃላፊዎች መውረድ ስንጀምር ነው።
የለውጥ ሃይሉ በፌደራል ደረጃ መፈጸም ከሚችለው ጉዳዮች ውጭ የለውጥ ህልሙን በክልሎች ማስፈጸሚያ
መሳሪያ የለውም ወደሚል መደምደሚያ ያደረሰኝ ይህ ትዝብት ነው። በፌደራል ደረጃም ቢሆን የለውጥ ሃይሉ
የሚፈልገውን ማስፈጸም የሚያስችል በቂ በተለያዩ ሙያዎችና ክህሎቶች የሰለጠነ የሰው ሃይል አቅም ያለው
ለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። አቅም የጉልበት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የለውጥ መሪዎቹን ሰፊና
ጥልቅ ራእይ መገንዝብና በተግባር ለመተረጎም የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎት፣ ስብእና እና የሞራል ልቀት
ያለው የሰው ሃይል መኖሩን ነው የምጠራጥረው። ሃገሪቱ ባለፉት 40 አመታት በተለይ ደግሞ ባለፉት 27
አመታት ማህበራዊ ምሁራዊና ሞራላዊ ካፒታሏ ክፉኛ ሲደቅ የነበረባቸው ዘመናት እንደነበሩ ልብ ይሏል። ይህ
የስብአዊ ካፒታል ወፍጮ ፍጥነቱን ጨምሯል እንጂ አልቀነሰም።
ከላይ ስለፌደራል መንግስቱ ያልኩት እንዳለ ሆኖ ትልቁ የለውጡ እንቅፋት ያለው በወሳኙ የፖለቲካ ስራ
መስሪያ መድረክ በሆነው በክልል ውስጥ ነው። ክልሎች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ የሚገለገሉበት ከፍተኛ
ትጥቅ፣ የመንግስት ሃብት፣ የአስተዳደር ስልጣን በጃቸው እንዳለ በተደጋጋሚ ገልጫለሁ። የየክልሉ የስልጣን
ባለቤቶች፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲዎች በመሆናቸው የክልሉን ሙሉ አቅም ፓርቲያቸውን ከማናቸውም ተቀናቃኝ
ሃይሎች ለመከላከል ይጠቀሙበታል።
እነዚህ የክልል ባለስልጣናትና የክልል ገዥ ፓርቲዎች በፖለቲካው መስኩ ሁለት ተቀናቃኞች ይታዩዋቸዋል።
አንዱ ተቀናቃኝ “የዘር ፖለቲካ ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከስደት፣ ከመፈናቀል፣ ከመዘረፍ፣ ከመብት መገፈፍ፣
አላዳነህም ወደፊትም ለከፋ መከራ ይዳርግሃል ከመከራህ መውጫው ብቸኛው አማራጭ ከዘር ነጻ የሆነ
የዜግነት ፖለቲካ ነው። በዜግነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ብቻ ነው።” የሚል አቋም ያለው ማንኛውም
የፖለቲካ አካል ነው። ሌላው ተቀናቃኛቸው እነዚህን የስልጣን ባለቤቶችና የገዥውን ፓርቲ መሪዎች
“የዘራቸውን ህዝብ ያጠቁና ያስጠቁ፣ የዘረፉና ያዘረፉ ለዘራቸው ህዝብ ምንም አይነት ተቆርቋሪነት የሌላቸው
ከሃዲዎች” አድርጎ በመሳል ከህዝብ ነጥሎ በእነሱ እግር መተካት የሚፈለገው ሌላው በዘር የተደራጀ የፖለቲካ
አካል ነው።
ባለንበት ወቅት በስልጣን ላይ ያሉ የየክልሉ አካላት እነዚህን ሁለት ሃይሎች ይፈራሉ። በአካባቢያቸው እነዚህን
ሁለት ሃይሎች በነጻ እንዲንቀሳቀሱ እንዲያደራጁ የፖለቲካ ስራ እንዲሰሩ ቢፈቅዱ የፖለቲካ ሽንፈት
ይከተለናል የሚል ስጋት አለባቸው። የፖለቲካ ሽንፈት ደግሞ መዘዙ ብዙ ነው። ያለችሎታቸው ስልጣን
አግኝተው ይኖሩ የነበሩና በዘረፋ ያከበቱት ሃብት የሌላቸው ሌላ ስራ ማግኘት ስለማይችሉ ጦማቸውን ወደ
ማደሩ ሊሄዱ ይችላሉ። የረሃብ ስጋት የሌለባቸው ደግሞ በዘረፉት የህዝብ ሃብትና በስልጣን ዘመናቸው
በተሰራ ወንጀል የምንጠየቅበት ዘመን ሊመጣ ይችላል ብለው ሊሰጉ ይችላሉ።
በዚህ የተነሳ እነዚህ የክልል ሃይሎች ሁለቱም ተቀናቃኞቻቸውን በክልላቸው ውስጥ በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ
የተለያዩ እንቅፋቶች ይፈጥራሉ። በሁሉም ክልሎች ይነስ ይብዛም ይህ እየተፈጸመ ነው። መንግስታዊ
ተቋማትን ገንዘብና ንብረትን በሙሉ፣ እንዲሁም በክልሉ ያሉ ሚድያ ተቋማትን በቅጥረኞች
የሚዘውሯቸውን ማሀበራዊ ሚድያዎችን ጭምር በመጠቀም ተቀናቃኝ የሚሏቸውን ድርጅቶች እንቅስቃሴ
ለማደናቀፍ ሲጥሩ እያየን ነው።
3.2. ክልላዊ የዘር የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ረገድ ያላቸው ሚና።
በሁሉም ክልሎች በስልጣን ላይ ያለውን በዘር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎችን የሚገዳደሩ በዘር ላይ የተመሰረቱ
ተቀናቃኝ ድርጅቶች ተፈጥረዋል። ይህ ሂደት ከለውጡ በኋላ ተጠናክሮ ቀጥሏል። እነዚህ ተቀናቃኝ ድርጅቶች
ባላንጣ አድርገው የሚያዩት በፌደራል ደረጃ ስልጣን ላይ ያለውን የለውጥ ሃይል፣ በየክልሉ ያለውን የክልል
መንግስት ገዥ ፓርቲና የዜግነት ፖለቲካ የተሻለው አማራጭ ነው የሚለውን የተፎካካሪ የፖለቲካ ሃይል ነው።
በፌደራል ደረጃ ስልጣን ላይ ያለው የለውጥ ሃይል በባላንጣነት የተፈረጀበት ምክንያት ስለሃገራዊነት፣
ስለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት፣ ስለአንድነት፣ መቻቻል፣ አብሮነት በተደጋጋሚ የሚያስተላላፋቸው መልእክቶች
በዘር ላይ ለተመሰረቱ ድርጅቶች እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል በመረዳት ነው።
በመላው ሃገሪቱ የሚገኙ በዘር ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ተቃዋሚ ይሁኑ የገዥው ፓርቲ አካል
ድርጅቶች፣ በለውጥ ሃይሉ ላይ የመረረ አመለካከት አላቸው። ቢቻላቸው ይህን ሃይል ገና ከጅምሩ ለመቅጨት
ከፕሮፓጋንዳ አንስተው እሰከ አመጽ ለመጠቀም ወደኋላ የማይሉ መሆናቸውን አስመስክረዋል። የምሬታቸው
መነሻ የለውጥ ሃይሉ የዘር ፖለቲካን የማምከን እድሉ ትልቅ ነው ከሚል ስጋት ጋር የተሳሰረ ነው። የለውጥ
ሃይሉ የሚያቀነቅናቸው አመለካከቶች በዜግነት ላይ ፖለቲካችን ይመስረት ከሚሉ ተፎካካሪ ሃይሎች ጋር
ተቀራራቢነት ስላለው ይህን ሃይል የዜግነት ፖለቲካ ከሚያራምዱ ተፎካካሪ ሃይሎች ጋር አዳብሎ ማየት
በአንድነት እንዲጠፋ መመኘት፣ በሁለቱ አካላት በጋራ የሚሸረብ ሴራ እንዳለ በማስመሰል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ
ማሰራጨት በዘር የተደራጁ ተቀናቃኝ ድርጅቶች የሙሉ ጊዜ ስራ ከሆነ ሰንበት ብሏል።
እነዚህን በዘር ላይ የተደራጁ ተቀናቃኝ ቡድኖች በዘር የተደራጀውን ገዥ ፓርቲ ለማዳከም ከክልል ክልል
የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች በገዥው ፓርቲ ስር ያሉ አሰተዳደሮችን አፍርሶ
በራስ እስከ መቆጣጣርና ጠመንጃ ጭምር ያካተተ እርምጃ የወሰዱ ተቀናቃኝ ድርጅቶች እያየን ነው።
ጠመንጃ የሌላቸው በተራ ጉልበትና ማስፈራራት የመንጋ ተቃውሞ በማነሳሳትና በመቀስቀስ አሳፋሪ የሆነ
የሃሰት ፕሮፖጋናዳ በማካሄድ በክልሉ ገዥ ፓርቲ ላይ የበላይነት ለማግኘት ጥረቶች ሲያደርጉ ይታያሉ።
በአንዳንድ ተቃዋሚዎቹ ለዘብተኛና ስልጡን በሁኑባቸው ቦታዎች ገዥዎች መብታቸውን እንዲያከብሩ
ከመጣር ያለፈ ነገር የማይሰሩ እንዳሉ ሳልጠቅስ አላልፍም። እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው።
ከነዚህ ከመጨረሻዎች አይነቶች ለዘብተኛ በዘር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች በስተቀር በዘር ለተደራጁ
የተቀናቃኝ ድርጅቶች ሌላው ጠላት ተደርጎ እየተወሰደ ያለው በዜግነት ፖለቲካ የሚያምነው የፖለቲካ ሃይል
ነው። ይህ የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ የያዙ ድርጅቶችና ግለሰስቦች እምነታቸውን ለህዝብ
እንዳይገልጹ በማድረጉ ስራ ላይ እነዚህ በዘር የተደራጁ ድርጅቶች በየክልሉ በስልጣን ላይ ካለው ገዥ ፓርቲ
ያልተናነሰ ችግር ፈጣሪዎች ሆነዋል።። የዜግነት ፖለቲካ አመለካከት የያዙ ድርጅቶች የመንቀሳቀስ እድል ካገኙ
በቀላሉ ባብዛኛው የዘር ፖለቲካው አሳርና መከራ ውስጥ በጨመረው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛሉ የሚል
ስጋት ወስጥ በመግባታቸው፣ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ተራ ወንጀል
እስከ መፈጸም የማይመለሱ መሆናቸው እየታየ ነው።
በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ማስፈራራት መደብደብ፣ የንግድ ስራዎቻቸውን
ማስተጓጎል፣ ቢሮዎችን መስበር፣ ስበሰባዎችን በተደራጀ መንገድ ማወክ የመሳሰሉ ድርጊቶች በመፈጸም
የፌደራል መንግስቱ በአንድ በኩል ለማስፋት እየጣረ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ከመቼውም በከፋና ይፋዊና
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እያጠበቡት ይገኛሉ። ሁሉም በዘር ላይ የተደራጁ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች
በየክልሉ በተመሳሳይ በተደራጁ ገዥ ፓርቲና አስተዳደሮች ውስጥ ደጋፊ ተባባሪና አባል ስላላቸው በዜግነት
ፖለቲካ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሃይሎችን ለማጥቃት መንግስታዊ አቅም ሲጠቀሙ ይታያል።
3.3. የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ስራ የተጠመዱ ሃይሎች አደገኛ ቅንጅት
በክልሎች ወስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ስራ ላይ የተጠመዱ፣ በመሃከላቸው መሰረታዊ ቅራኔዎች
ያሏቸው፣ ነገር ግን እንደ አስፈላጊነቱ የሚስማሙ ሶስት ሃይሎችን እናገኛለን። የመጀመሪያው ሃይል፣
የተጀመረው የለወጥ እንቀስቃሴ የዲሞክራሲ በሩን እስከ ክልል ድረስ ከከፈተው ከያዝኩት ስልጣንና ከዚህ
ስልጣን ጋር ያገኘሁትን ተጠቃሚነት በተቀናቃኞቼ ተሸንፌ አጣለሁ የሚል ስጋት ውስጥ የገባው ከላይ
በኢህአዴግ ወስጥ ለተጀመረው የለወጥ እንቅስቃሴ ቀና አመለካክት የሌለው የየክልሉን የኢህአዴግን
የድርጅትና የክልሉን አሰተዳደራዊ መዋቅር በአብዛኛው የተቆጣጠረው ሃይል ነው። ሌላው ይህን ሃይል አባሮ
በቦታው እተካለሁ ብሎ ቀንና ለሊት የሚያልመው በዘር የተደራጀ ሃይል ነው። ሶስተኛው የፖለቲካ ሳይሆን
የኢኮኖሚ ጉልበት ያለው ቡድን ነው። ከነባሩ ስርአት ጋር በተለያዩ መንገዶች ተሳስሮ እንደ ወያኔ ባለስልጣናት
እንኳን ባይሆንም እንደ አቅሙ ከፍተኛ ሃብት ያፈራና ነባሩ ስርዓት እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ሃይል
ነው።
አንደኛውና ሶስተኛው የቆየ ወዳጅነት ያላቸው በመሆኑ ለጋራ ጥቅም መቆማቸው የሚጠብቅ ነው። ይሁንና
አሁን እየታዬ ያለውና እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ እነዚህ ሶስት ሃይሎች በጋራና በቅንጅት የሚሰሩበት ሁኔታ
መከሰቱ ነው። በዘረፋ የከበሩ ባለሃብቶች ከሁለቱም በዘር ከተደራጁ ሃይሎች ጋር በቅርብ በመስራት
ገንዘባቸውን ሁለቱም ሃይሎች የፖለቲካውን ምህዳር ለማጥበብ እንዲጠቀሙበት እያደረጉ ነው። እነዚህ
ባለሃብቶች በዘረፋ ባከማቹት ሃብት ላይ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች ባለመኖራቸው ይህን ከፍተኛ
ነዋይ ምንጩ መታወቅ እንዳይችል በሚያደርግ የሽያጫና የስም መዛወር ሂደት እንዲያልፍ እያደረጉት ነው።
በግለሰቦች እጅ በዘረፋ የተከማቸ ለከት የሌለው ብር የውጭ ምንዛሪውን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ
ደረጃ ከኦፊሲያሊያዊ ምንዛሪው በላይ እንዲመነዘር እያደረገው ነው። ቋሚ ንብረቶች እየተሸጡ ወደ
ተነቀሳቃሽ ንብረትነት፣ ወደ ዶላርና መኪናነት እየተቀይሩ ነው። እነዚህ ንብረቶች በማእከላዊ መንግስት
አይደረስበትም ተብለው መተማመኛ ወደ ሚገኝባቸው ክልሎችና የውጭ ሃገራት በየፈርጃቸው እየተከማቹ
ነው።
ይህ መጠነ ሰፊ ህገ ወጥና ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሃብት፣ እነዚህን ባለሃብቶች ሃገር አቀፍ የሆነ መረብ
ዘርግተው በተለያዩ ክልሎች የሚታዩትን የመንጋ እንቅስቅሴዎችና ግጭቶች ፋይናንስ አድራጊዎች
አድርጓቸዋል። እነዚህ ባለሃብቶች በየክልሉ አስተዳደር ወስጥና በዘር በተደራጁ ተቀናቃኝ ድርጅቶቹ ውስጥ
ያሏቸውን ቅጥረኞች በመጠቀም በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን አባላትና ደጋፊዎችን
በየክልሉ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በማድረግና የፌደራል መንግስቱ ያነፈሰው የለወጥ አየር በክልሎች
እንዳይነፍስ ወሳኙን ሚና ተጫዋቾች ሆነዋል። እነዚህ ባለሃብቶች እነዛን በዘር ተደራጀተው ‘እኔ ካንተ
በላይ ለዘሬ እቆረቆራለሁ” በሚል ግጭት ወስጥ የሚገኙትን ሁለት ሃይሎች በማስተባበር በኢህአዴግ ወስጥ
የተንሳውን የለወጥ ሃይልና የዜግነት ፖለቲካ በሚያራምዱ ሃይሎች ላይ የሚሰነዘሩትን ማናቸውንም ጥቃት
በገንዘባቸው አሳላጮች ሆነዋል። ግር የሚለው ነገር ይህን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ተዘርፎ በየሌባው ቤት መጋዘን
ተሰርቶለት የተከመረን ህገ ወጥ ገንዘብ ትርጉም አልባ የሚያደርግ እርምጃ ለምን በመንግስት እንደማይወሰድ
ብቻ ነው።
ሶስቱ ሃይሎች በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ክፉኛ ከመፍራታቸው የተነሳ የዜግነት ፖለቲካ
አራማጆችን በማጥቃቱ ስራ በግንባር እየተንቀሳቅሱ ነው። በተለያዩ ቦታዎች የክልሉ ባለሃብቶች ፋይናንስ
የሚያደጓቸው የመንጋ ፈጥኖ ደራሾች የሌሎችን ድርጅቶችን የፖለቲካ ስብሰባዎች ሲረብሹ፣ ተሰብሳቢዎቹን
ሲደበድቡ ንብረታቸውን ሲዘርፉ የክልል አስተዳዳሪዎችና ፖሊሶች ቆመው የሚያዩበትን ሁኔታዎች
ታዝበናል። ባሁኑ ሰአት የክልል ባለስልጣናትና በየክልሉ የተሰባሰቡ በዘር ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች የመንደር
ጉልበተኞች በተናጠልና በጋር በሚወስዷቸው እርምጃዎች በተለይ በዘር ፖለቲካ የማያምኑ የህብረተሰብ
ክፍሎች ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በመጀመሪያ የለውጡ ወራቶች ግራ ተጋብተውና ተደናግጠው በየአካባቢያቸው የዜጎችን ነጻነት መገደብ
የተሳናቸው የየክልሉ ባልስልጣናት ውሎ ባደረ ቁጥር ቀልብ እየገዙ፣ ከመደናገጥ እየወጡ ሲመጡ
በየአካባቢያቸው በግርግር ተፈጥሮ የነበረውን የነጻነት ምህዳር ለመዝጋት ጊዜ አልፈጀባቸውም። የዛሬ 6 ወር
በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፎካካሪ ድርጅቶች ህዝብን ለመድረስ የሚጠሯቸውን ስብሰባዎች መከልከልና
ማወክ የማይደፍሩት የየክልሉ ባላስልጣናት ዛሬ ማንንም ሳይፈሩ “በአካባቢያችን ብትደርሱ ወየውላቸሁ”
የሚል ማስፈራሪያ እስከማስተላለፍ ደርሰዋል።
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይህን ማስጠንቀቂያ ተፈጻሚ ለማድረግ ከሚቀናቀኗቸው ሌሎች የዘር ድርጅቶች
ጋር ሳይቀር ለዚህ እኩይ አላማ በጋራ እሰከማሴር ሲሄዱ እየታየ ነው። የተለያዩ ሰበብ አሰባቦች በማቅረብ
በየትኛውም ክልል በተለይ በዜግነት ፖለቲካ ዙሪያ የተደራጁ ሃይሎች መንቀሳቀስ የማይቻሉበት ሁኔታ
ፈጥረዋል። ማስፈራራት፣ ዱላ፣ ዘረፋ፣ እስራት መንግስታዊ የደህንነት ጥበቃና ማናቸውንም መንግስታዊ
አገልግሎት መከልከል በተግባር የዋሉ አንገት ማስደፊያ እርምጃዎች ናቸው። ለህክምና የሄዱ ዜጎችን “የኛን
ዘር ፖለቲካ አራማጅ ብትሆን ኖሮ እናክምህ ነበር” በማለት በሽተኛን የህክምና አገልግሎት እስከ መከልከል
የደረሰ የሰብአዊ መብት ገፈፋ በሃገራችን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ለመሆኑ በደሉ የደረስባቸውን ግለሰቦች
በማስረጃነት ማቅረብ ይችላል።
የለውጡ እንቅስቃሴ እውን ነው ብለው በማሰብ ቀደም ባሉት የለውጡ ወራት እውነተኛ የፖለቲካ
እምነታቸውን በአደባባይ የገለጹ ዜጎች ልክ ከምርጫ 97 ማግስት እንደሆነው ሁሉ በየክልሉ ተለይተው ጥቃት
እየደረስባቸው እንደሆነ ይታወቃል። ሰልፍ ወጥታችኋል፤ ቲ-ሸርት ለብሳችኋል፤ ህዝብ ቀስቅሳችኋል፤
በተደራጀ መንገድ ተንቀሳቅሳችኋል፣ ገንዝብ አዋጥታችኋል በሚሉ ውንጀላዎች ዜጎች ብዙ መከራ እየተቀበሉ
ነው። በነዚህ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት የተመለከቱ ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የክልሎች
ኗሪዎች ተመልሰው “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ነው” የአፈና ዘመን እሳቤ እየተመሩ የዜግነት መብታቸውን
በጉልበተኞች አስገፍፈው በውርደት መኖሩን ተያይዘውታል።
በማስፈራሪያ ምክንያት ተወልደው ካደጉበት መንደራቸው የተፈናቀሉ፣ ንብረታቸውን የተቀሙ ለሌሎች
መቀጣጫ እንዲሆኑ የታሰሩ፣ የተደበደቡ ዜጎችን እያየን ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ፣ በተለይ በበርካታ
የኦሮሚያና የደቡብ ከተሞችና ገጠሮች ፍራቻ ነግሷል። ለውጡ በፈጠረው እፎይታ ወደ ሃገራቸው የተመለሱ
በርካታ የዳያስፖራ አባላት በአንዳንድ የሃገሪቱ ገጠሮች የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ሄደው እንዳይጠይቁ
“አትምጡ” የሚለው ምክር የሚመጣው ከቤተሶቻቸው ሆኗል። “እዚህ ያለው ሁኔታ ስለማያስተማምን
ከአዲስ አበባ አትንቀሳቀሱ እኛ እንመጣለን” እየተባሉ ነው። በፖለቲካ አመለካክታቸው በዳያስፖራ የሚታወቁ
ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው የዚህ ስጋት ሰለባ ሆነዋል።
በየጊዜው ከፌደራል መንግስቱና በየክልሉ በሚገኙ ጥቂት አርቆ አሳቢ የክልል ባለስልጣናት በኩል የሚደረጉ
ጫናዎች ባይኖሩ በሁሉም ክልሎች ከአዲስ አበባ በስተቀር የመንግስትን ጥሪ አክብረው ወደ ሰላማዊና ህጋዊ
ትግል የተመለሱ ድርጅቶች በየትኛውም ክልል አንድ ጋት መራመድ የሚችሉበት ሁኔታ እንደማይኖር ግልጽ
ሆኗል። ይህ የማእከላዊ መንግስት ጫና በየትኛዎቹ ክልሎች በምን ያህል ደረጃ ተፈጻሚ ይሆናል፣ ምንስ ያህል
አስተማማኝና ቀጣይነት አለው ለሚለው ጥያቄ በድፍረት መልስ መስጠት የሚችል አካል ያለ አይመስልም።
4. ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች የተሸከመች ሃገር ናት። ከዘመን ዘመን ችግርቿ እየበረቱና እየተወሳሰቡ የሚሄዱ
ሆነዋል። በየዘመኑ ህዝብ ከዚህ የከፋ ዘመን ሊገጥመው አይችልም እየተባለ እዚህ ደርሰናል። ያሁኑንም ዘመን
በዚሁ ቋንቋ መግለጽ ጀምረናል። ይህ አገላለጽ የተለመደ በመሆኑ ይህ ዘመን ካለፉት ዘመናት ልዩነት የሌለውና
እንዲያው ዝም ብለን ችግሮችን የምናጋንን ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በበኩሌ ግን “የዚህን ዘመን ችግሮች
እንደ ሌሎች ዘመን ችግሮች እንደዋዛ ማለፍ ግዙፍ ታሪካዊ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከዛም አልፎ ታሪካዊ ወንጀል
ከመፈጸም የሚለይ አይሆንም” ባይ ነኝ። የለውጥ ሃይሎች የምንላቸው ቡድኖች ወደ መድረክ ብቅ
ከማለታቸው በፊት ሃገሪቱ እየተጓዘች የነበረችበትን የገሃነም መንገድ መለስ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል።
ያንን የገሃነም መንገድ እንድትጀምረው ያደረጓት መሰረታዊ ችግሮች፣ ከፖለቲካ ከኢኮኖሚ ከማህበራዊ
ጉዳዮች ጋር የተሳሰሩ መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች ስር ሰደውና ተወሳስበው የቀጠሉበት ሁኔታ እንጂ
የተቀነሱበት ሁኔታ የለም። የገሃነሙን መንገድ ለጊዜው የዘጋው ለውጡ በብዙሃኑ ውስጥ በተለይ ወጣቱን
ጨምሮ የጫረው ተስፋ ብቻ ነው። ይህ ተስፋ ግን በጊዜ ተጨባጭ ችግሮች በመፍታት ካልተደገፈ ለነፋስ
እንደተጋለጠ ዱቄት ብን ማለቱ የማይቀር ነው። ሃገራችናን ህዝቧን ከመቀመቅ አፋፍ የመለሰውን ተስፋ
ለማስቀጠል ግን እንዲሁ በዋዛ ፈዛዝ የሚቻል አይደለም።
5. ካለንበት ቅርቃር እንዴት እንወጣለን?
• ያለንበት ሁኔታ እጅግ ልዩና አሳሳቢ መሆኑ መገንዝብ የመጀምሪያው የመፍትሄ እርምጃ ነው
(extraordinary-challenges)
• ከዚህ ልዩና አሳሳቢ ሁኔታ ለመውጣት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ልዩና በሚገባ የታሰበባቸውና አፋጣኝ
ሊሆኑ እንደሚገባ መገንዘብ ሁለተኛ የመፍትሄ እርምጃ ነው። (solving these extraordinary challenges
demands taking extraordinary measures)
• ሃገሪቱ የገጠማትን ችግሮች ለመፍታት ከቆየው የአመለካክት የአደረጃጀት እስር ቤት መውጣትና አስፈላጊ
ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ስር ነቀል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት ይገባል።
• በመግቢያው ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሃገሪቱ ህዝቦች ችግሮች በተለያዩ ዘርፎች የሚታዩ ቢሆኑም
በቅድሚያ በዋንኛንት በፖለቲካ ዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ሳይፈቱ ሌሎችን ችግሮች መፍታት እንደማይቻል
መገንዝብ ከሃገራችን የፖለቲካ እውነቶች ሁሉ ቁንጮው እውነት መሆኑን መረዳት፣ ሶስተኛውና ወሳኙ
እርምጃ ነው።
• የፖለቲካ ችግሮች ከምንላቸው መሃል ደግሞ ዋነኛው ችግር ከዘር ፖለቲካ ጋር ተሳሰሮ በሃገር የተረጋጋ
ህልውና ዙሪያ ያሰፈሰፈው ችግር መሆኑን መቀበል ሌላው የእውነቶች ሁሉ እውነት ነው።
• ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ካልሆነ በስተቀር በሌላ መልኩ ተገነጣጥልው በብዙ አዳዲስ
ሃገራት ኗሪዎች ሁነው፣ በሰላም የሚኖሩባቸው ግዛቶች ሊኖሯቸው ከቶውኑ የማይችል መሆኑ መረዳት ሌላው
ወሳኝ ነጥብ ነው።
• ኢትዮጵያን እንደሃገር ማስቀጠል የወያኔ ህገ-መንግስት ሊነግረን እንደሚሞክረው የተለያዩ ብሄረሰቦቿ
መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን፣ አንድነት ምርጫ የሌለው የህልውናቸን መሰረት
መሆኑን መረዳት ሌላው ትልቅ ጉዳይ ነው።
• ኢትዮጵያ በምንላት ሃገር ወስጥ መከበር የማይችሉ የማህበረሰብ መብቶች ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር
በሌለችበት ሊከበሩ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይችሉ፣ የመብት ዋስትና ሳይሆን ውሎ የማደር፣ ስጋ ከነፍስ አጣብቆ
የመኖር ዋስትና የሚጠፋበት ምድራዊ ሲኦል ውስጥ ሁላችንም እንደምንወረወር መረዳት ብልህነት ነው።
• በሃገር አንድነትና በሃገር ህልውና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ድህነትን በማስወገድ ሰብአዊ መብት
በማስከበር ሙስናን በማጥፋት ህልማቸን ላይ ትልቅ አደጋ እንዲያንዣብብ ከአደረጉት ምክንያቶች ሁሉ
ትልቁና ዋንኛው የዘር የፖለቲካ አደረጃጃት ወይም የዘር የክልል አደረጃጃት ሳይሆን (ይህ ለጊዜው በሁለተኛ
ደረጃ ሊታይ የሚገባውና ዋንኛው ችግር ከተፈታ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ሊነካካ የሚችል ነው) የማእከላዊ
መንግስትን ስልጣንና ሃላፊነት መጋፋት የሚያስችል ለአያንዳንዱ በዘር ለተደራጀ ክልል የራሱ አመጽ
መፈጸሚያ የታጠቀ ሃይል እንዲኖረው ወያኔ የወሰነው ውሳኔ ነው። ይህንንም ውሳኔ ወያኔ ሲወስን ቅድሚያ
የሰጠው በሃገርና በህዝብ ላይ መሪዎቹ ለሚፈጽሙት ወንጀል ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማምለጫ
በመሳሪያነት ሊገለገሉበት ስላሰቡ እንጂ የብሄረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ ወይም ለሃገር ይበጃል በማለት
እንዳልሆነ ባለንበት ወቅት እየፈጸሙት ባለው ድርጊታቸው መረዳት እንችላለን። በየትኛውም በአለማችን
ውስጥ በተዘረጉ የፌደራል ስርአቶች፣ የፌደራል መንግስቱን ስልጣን ሊጋፋ የሚችል የክልል ታጣቂ ሃይል
እንዲደራጅ ተፈቅዶ አያውቅም። የፌደራሊዝም አንዱ የአስተዳደራዊ ስርአቱ መገለጫ በአመጽ መሳሪያ
ባለቤትነትና ተጠቃሚነት እንዲሁም በውጭ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ የስልጣን ሞኖፖል ፍጽም መሆኑ
ነው።
በመሆኑም ይህን አመጽ የመፈጸም ማናቸውንም ሃይል ሙሉ በሙሉ ከክልሎች እጅ አውጥቶ በፌደራል
መንግስቱ እጅና እጅ ብቻ ማድረግ የወቅቱ ብቸኛና ትልቅ ሃገራዊና ህዝባዊ ጉዳይ ነው። ይህን ማድረግ
ከተቻለ፣ በፌደራል መንግስቱ ስር በሚዋቀሩ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት አማካይነት በመላው ሃገሪቱ ሰላምና
መረጋጋት ማስፈን፣ የህግ የበላይነትን፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች ማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ፣
ሙስናን መግታት፣ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች እርስበርሱ የተቆላላፈና የተመጣጠነ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት
ማስመዝገብ፣ ከውጭ ጠላቶች ጣልቃ ገብነት ራስን በቀላሉ መከላከልና ሌሎችንም የለውጥ ሃይሉንና
የህዝቡን ቀና ህልሞች ማሳካት ይቻላል።
• አሁን እየታየ እንዳለው በፌደራል መንግስቱ የለውጥ አካላት ዘንድ እየታሰበ ያለውን ሃገር የማዳን፤
ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባትና በፍጥነትም ሌላውን ቀውስ ፈጣሪ ድህነትን ለመወጋት እንዳንችል
እያደረገን ያለው ችግር የፌደራል መንግስቱ አቅመ ደካማነት መሆኑን መካድ አንችልም። ከተናጠል ክልሎች
ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ክልሎች ይበልጥ የሁሉንም ዜጎች መብቶችና ጥቅሞች በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች
ያለምንም ተገዳዳሪ በእኩልነት ማስጠበቅና ማስከበር የሚችልበት አቅም ሊኖረው የሚገባው ማእከላዊ
መንግስት ህገ መንግስታዊ ስልጣኑን በአንዳንድ ክልሎች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅም የሌለው ሆኖ
መገኘቱ ነው ዋናው የሃገራችን የጊዜው የፖለቲካ በሽታ ።
• በሃገራችን ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ዜጎች በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል መብታቸው ተከብሮ፣ በማናቸውም
የዜጎች እንቅስቃሴ ባለሙሉ የመብቶች ባለቤቶች ሆነው እንዲንቀሳቅሱ የሚያደርግ፣ ሁሉም ዜጎች ፍትህን
ዴሞክራሲን ነጻነትን በእኩልነት እንዲቋደሱ ማድረግ የሚቻለው፣ ማህበረሰቦች ከወል ተፈጥሯዊ
መብቶችቻቸው (ይህ መብት እርስ በርስ መባላትን የሚጨምር መሆኑ መታወቅ አለበት) ቀንሰው እነዚህ
መብቶች መከበር የሚችሉበትን ብቸኛው የፌደራላዊ መንግስት ስልጣን ከራሳቸው ስልጣን በላይ ሊሆን
እንደሚገባው እንዲረዱ ማድረግ ሲቻል ነው። በየቦታው በወል መብት ስም ለመደፍጠጥ ሲሞከር የኖረው
የዜጎች መብት የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ሁሉ መሰረት መሆኑን ይህንን መብት ደግሞ ማስከበር የሚችለው
የሁሉም ዜጎች ስልጣን መገለጫ የሆነው ፌደራላዊው ማእከላዊ መንግስት መሆኑን መቀበል ይጠይቃል።
• ይህን ያልተረዳ ካለ እንዲረዳ ማድረግ ይገባል። ከዛም ተሻግሮ በኢትዮጵያ ምድር ማናቸውንም ሰብዓዊ
ስልጡን ማህበራዊ ክንዋኔዎችን ለማከናወን፣ የሃገር ህልውና በቅድሚያ ቀጥሎም የዴሞክራሲያዊ ስርአት
ግንባታ መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንና ይህ መፈጸም የሚቻለው በየትኛውም የሃገሪቱ ክልል አመጽ የመፈጸሚያ
አቅም በማእከላዊ መንግስትና በማእከላዊ መንግስት እጅ ብቻ መሆን እንዳለበት ዜጎች እንዲቀበሉት ማድረግ
ይገባል።
• የኢትዮጵያ ህዝብ በሃገሩ ላይ ያሰፈሰፈውን የመበታተን አደጋ መግታትና ከጥቂት ወራት በፊት የፈነጠቀው
የዲሞክራሲ ጮራ እንዳይጨልም ማድረግ የሚቻለው በቅድሚያ ሁሉም ክልሎች በዘር ያደራጁትን ሚሊሺያ፣
ልዩ ሃይል ፤ ደህንነትና ሚድያ በክልሉ በዘር ተደራጅተው ከሚያዙት ሃይሎች እጅ አውጥቶ በሃገሪቱ
ማናቸውንም የአመጽ እርምጃ የመውሰድ አቅምና መብትና እንዲሁም የመንግስት የሚድያ ተቋማት የማዘዝ
ስልጣን በሙሉ የፌደራል መንግስቱ ብቻ እንዲሆን ሲደረግ መሆኑን ማወቅ ይገባል። እንዴት እነዚህን ተቋማት
ባሉበት የባለቤትነት ሁኔታ ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው።
አይቻልም።
• ይህ ወሳኝ እርምጃ በቅድሚያ ሳይወሰድ፣ ወገንተኛ የሆኑ ታጣቂዎችና የሚድያ አውታሮች በክልል
መንግስቶችና በክልል ፓርቲዎች እጅ እንዳሉ በሃገራችን ስለምርጫ፣ ስለዴሞክራሲ ግንባታ፣ በፌደራል
መንግስቱ ስለሚቁቋሙ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት ማውራት ለህጻናት ተረት ከመተረት የተለየ ትርጉም
ሊሰጠው አይገባም።
• እንዲህ አይነቱ አይን ያወጣ በሃገር አንድነትና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ዙሪያ ያሰፈሰፈ መአት ባለበት
ሁኔታ ምርጫው የተያዘለትን የቀን ቀጠሮ ጠብቆ ይደረግ የሚሉ አካላት ይህን አጀንዳ ለምን እንደሚገፉት
መረዳት የሚቸግር አይሆንም። መሰረታዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ለመኖር ወሳኝ የሆኑት
ሁኔታዎች ፈጽመው በሌሉበት ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ ይደረግ የሚሉት አካላት
የዴሞክራሲ ምህዳሩን በመሳሪያ፣ በጉልበት፣ በዘረፋ፣ በህዝብ ውስጥ ፍርሃት በማንገስ፣ ብጥብጥ በመፍጠር፣
የማእከላዊ መንግስትን ስልጣን በመጋፋት የታወቁ ሃይሎች መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በታፈነ
ሁኔታ ምርጫ ቢካሄድ ሃገር በማፍረሱም ይሁን በጉልበት ለሚገኝ የምርጫ ድል ባለቤቶች እንደሚሆኑ
የተማመኑ ሃይሎች ብቻ ናቸው በህገ መንግስት ስም ምርጫ ይከበር እያሉ የሚጮሁት።
• ከዚህ በላይ የተቀመጠውን ቁልፍ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት በብዙ ነገሮች ዙሪያ በርጋታ በብልሃት ማሰብን
በድፍረትና በቆራጥነት መወሰን ይጠይቃል። ቁልፉ ጥያቄ ችግሩ እውነተኛ ችግር መሆኑን አለመገንዘብ ላይ
አይሆንም። ችግሩ ትልቅ ውስብስብና አስቸጋሪ፣ የለውጥ መሪው አካል አቅም ደግሞ ደካማ መሆኑ ላይ ነው።
ይህን ችግር ለማቃለል በፖለቲካው፣ በህዝብ ግንኙነት፣ በወታደራዊ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሰው ሃይልና በሌሎችም
ዘርፎች ምን ማድርግ እንደሚቻል ማሰብ ይጠይቃል። በፌደራል መንግስቱ ወስጥ ሆነው ለውጥ ለማምጣት
እየደከሙ ያሉት ሃይሎች፤ ለውጡን ለመጻረር ከሚፍጨረጭሩ ማናቸውም ሃይሎች የላቀ እምቅ አቅም
አላቸው። እያደር እየቀነሰ ቢሆንም አሁንም ሰፊ የህዝብ ድጋፍ አላቸው። በሚገባ ከታሰበበት ይህን እምቅ
አቅም ወደ እውን አቅም ቀይሮ ወደ መፍትሄ ሰጭነት ለመሸጋገር ከባድ አይደለም።
• የተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎች የመሰረት ድንጋዮች የሚከተሉት ናቸው፤
o የኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር ይሁን በዚህ ድርጅት አባላት የተያዙት መንግስታዊ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና
አባላት ራሳቸው የችግሩ አካል እንጂ የመፍትሄው አካል እንደማይሆኑ መረዳት፣
o የለውጥ ሃይሉ፣ ሰላምና የተረጋጋ ህይወት መኖር በሚፈልገው ህይወቱ እንዲሻሻል በሚሻው፣ እጅግ ከፍተኛ
ቁጥር ባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል።
o የለውጥ ሃይሉና ለውጡን የሚደግፈው ህዝብ በቀጥታ የሚገናኙበት መዋቅራዊ ሰንሰለት በፍጥነት መፍጠር
ለውጡን ከአደጋ መጠበቂያ ብቸኛ መሳሪያ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ህዝቡ እንጂ የኢህአዴግ የድርጅት
መዋቅር የለውጥ አስፈጻሚው ዋንኛ ኤጀንት አለመሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። ህዝቡ የለውጡ ኤጀንት
መሆን የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ እንደሆነ ለውጡ መቀጠል፣ የለውጥ ሃይሎቹም ከአደጋ መትረፍ
የሚችሉት መሆኑን ማመን ይጠያቃል፣
o ወቅቱ ሃገርን ማዳን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባበት፣ ሰላምና መረጋጋት ከሁሉም ነገር ሊቀድም የሚገባው
የሆነበት፣ የሌሎች ነገሮች ህልማችን በሙሉ ይህ ሁኔታ ሳይረጋገጥ ከንቱ ድካም መሆኑን የተቀበሉ ሃይሎች
ሁሉንም ልዩነቶች ወደጎን አሰቀምጠው በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲተባበሩ የማድረግ ስራ መስራት የለውጥ ሃይሉ
ሌላው ተግባር ነው። የለውጥ ሃይሉ ከማያቁት መልአክ የሚያቁት ሰይጣን ይሻላል በሚል አደገኛ ብሂል
የሚመራ ይመስላል። ይህን የለውጥ ሃይል አምነው ወደ ሰላማዊ ፖለቲካ የተመለሱትን ሃይሎች ከማመን
የቆየውን በብዙ ነገሮች የተበከለ ድርጅታዊና አስተዳደራዊ መዋቅር ማመን የቀለለው፤ ወይንም ችግር
እንዳለው ቢያውቅም እንኳን ከዚያ ውጭ ሌላ መንገድ የለም ብሎ ያመነ ይመስላል። ሰይጣን ሁል ጊዜም
ሰይጣን ነው። የለውጥ ሃይሉን አምነው ከገቡት መሃል የለውጥ ሃይሉ ጥረቶች እንዲሳኩ ከልባቸው የሚፈለጉ
በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዳሉ በማመን፣ ሁሌም ጥቁር በግ እንደሚኖር ሳንዘነጋ፣ የነዚህን
ድርጅቶች በጎ ፍላጎትና አቅም አሟጦ ለመጠቀም መዘጋጀት ያስፈልጋል። ሃገር ለማዳን የለውጥ ሃይሉ
ህዝቡና ለውጡን የሚድግፉ ሃይሎች በጋራ መስራት ከልባቸው ወደ ሰላም፤ የህግ የበላይነት፣ የመአከላዊ
መንግስት ተደማጭነት እስክንሻገር በጋራ ተባብረውና ተመካክረው የማይሰሩበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።
o ሃገሪቱ ያለችበትን ፈታኝ ሁኔታ ለህዝብ ያለምንም መሸፋፈን፣ ሁሉም ዜጋ እንዲያውቀው፣ ዜጎች
መንግስት ችግሬን ይፈታልኛል ከሚል ጠባቂነት ወጥተው መንግስት በሚያመቻችላቸው ሁኔታ
የአካባቢያቸውን ሰላምና መረጋጋት፣ የመንግስት አገልግሎቶችና የልማት እንቅስቃሴዎች የሚቆጣጠሩና
የሚያስፈጽሙ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል።
o ህዝብን ከታች የጉልበት መሰረት በማድረግ የፌደራል መንግስቱ በእጁ የሚገኘውንና የሚያዘውን የፌደራል
መንግስት የጦር፣ የፖሊስ፣ የደህንነት ሃይልና የሲቪል ተቋማት ሁለንተናዊ ብቃት በፍጥነት ማሳደግ
የሚያስችል ፈጣንና ቀልጣፋ እርምጃዎች አስቀድሞ መውሰድ ይገባል።
o በተለያዩ የሙያ መስኮች በሃገሪቱ ያለውን ምሁራዊና ሙያዊ አቅም ድክመት ማከም የሚችል ከኢህአዴግ
ሳጥን ውጭ ተወጥቶ ምሁራዊና ፕሮፌሽናል አቅም ያለውን ሃገር ወዳድ የሰው ሃይል የማሰባስብ ስራ
በተቀላጠፈ መንገድ እንዲሰራ ማስቻል፤ የለውጥ ሃይሉን ያለምንም ወጪና ራስ መቆጠብ ሊያገለግሉ
የሚችሉ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በከፍተኛ ደረጃ በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ዜጎችን ማግኘት
የሚያስቸግረው አይሆንም።
o የለውጥ ሃይሉ በወሰዳቸው በርካታ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ውሳኔዎች የተነሳ ከአለም አቀፍ ማህበርሰቡ
ያገኘውን ተቀባይነትና አድናቆት በመጠቀም ራሱ የአለም አቀፍ ማህበረስቡ የሃገሪቱ ችግሮች ናቸው ብሎ
ለሚያምናቸው ከላይ የዘረዘርኳቸው ችግሮች እንዲፈቱ የራሱ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በቀላሉ ማድረግ
ይችላል።
o እግረ መንገዱን ሃገራቸን በዲፕሎማሲ መድረኩ ሊኖራት የሚገባው ተጸእኖ አድራጊነት ከሚያዳክሙ
ነጥቦች ዋንኛው፣ እንዲሁም ለሃገራችን ብሄራዊ ደህንነትና ጥቅም ትልቁ አደጋ በዘር የተሰነጣጠቀ አገር
ባለቤቶች መሆናችንን መረዳትና፣ ይህ ችግር ለሃገሪቱ ጠላቶችም ትልቁ የትሮይ ፈረስ እንደሆነ በመረዳት
ይህን መሰረታዊ ችግር ማቃለል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ በዚህ ችግር መፈታት ዙሪያ የጎረቤት
ሃገራት ትብብራቸውን እንዲለግሱ ማድረግ በተለይ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለየ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉትን
ሃገራት ለይቶ የተለየ ትብብር መጠየቅ ይቻላል። ባሁኑ ጊዜ ከጎረቤቶቻቸን መሃል ለትብብር ጥያቄያችን
አሉታዊ መልስ ሊመልሱ የሚችሉ አለመኖራቸው የለውጥ ሃይሉን ድካም የሚቀንሰው ይሆናል።
o ማእከላዊ መንግስት ስልጣኑን በሃገር ደረጃ በማያወላዳ መንገድ ለማረጋገጥ የሚወስዳቸው እርምጃዎች
በሁሉም ግንባር ከሁሉም ጋር በአንድ ጊዜ መፋጠጥን ያስወገደ፣ ቁልፍና ወሳኝ በሆኑት አካላት ላይ ያተኮረ
ወሳኝ የመፍትሄ ርምጃ በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታት መከፈል ያለበትን የመስዋእትነት ዋጋ የሚያስቀንስ
ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል።
ከዚህ በላይ የቀረቡት ምክረ ሃሳቦች ጥቅል ናቸው። በመሰረታዊ ጉዳይ ላይ ስምምነት ካለ ማለትም
የሁኔታዎች አሳሳቢነትና አሳሳቢነቱን በፈጠሩት ቁልፍ ችግሮች ዙሪያ መግባባት ካለ በሁሉም መስኮች እንዴት
ከምክረ ሃሳብ ወደ ድርጊት እንሸጋግራለን የሚሉትን ጥያቄዎች በዝርዝር ማቅረብ በጣም ቀላል ነው።

You might also like