You are on page 1of 6

የዳን

የዳንኤል ዕይዎታች
www.danielkibret.com

ቻይንዬ
ሴትዮዋ ልጃቸው ከቻይና ትወልዳለች አሉ፡፡ አንድ ወር እንደሞላት ልጂቱ ትሞትና ልቅሶ ይጠራሉ፡፡
ታድያ እያለቀሱ ወደ ድንኳኑ ሲገቡ ምን አሉ መሰላችሁ «እኔ ድሮም ጠርጥሬ ነበር፣ ጠርጥሬ ነበር፤
የቻይና ነገር ይኼው ነው አይበረክትም» አሉ ይባላል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሚዲያ ስማቸው ከሚነሣ ሀገሮች እና ሕዝቦች መካከል የቻይናን እና የቻይኖችን
ያህል ቦታ ያለው የለም፡፡

በመንገድ ሥራ፣ በግድብ፣ በማዕድን ማውጣት፣ በቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ በሸቀጣ ሸቀጥ፣ በፖለቲካ፣ ባህል
ሁለ ነገራችን ቻይና ቻይና ይላል፡፡ የኢትዮጰያ ቴሌቭዥን እንኳን በቀን ውስጥ ቢያንስ አንድ የቻይና ዜና
ሳያሳየን አይውልም፡፡ ጠላ ቤት፣ ጠጅ ቤት፣ ሥጋ ቤት፣ ጉልት ገበያ፣ መርካቶ፣ አትክልት ተራ፣ አጠና
ተራ፣ በግ ተራ፣ ካዛንቺስ፣ ቺቺንያ ዘወር ዘወር ብትሉ ከአሥሩ ሰው አንድ ሦስቱ ቻይና ሆኖ
ታገኙታላችሁ፡፡

እንዲያውም ከመብዛታቸው የተነሣ እንደ አንድ ብሔረሰብ ተቆጥረን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወንበር
ይሰጠን ብለዋል እየተባለ ይቀለድም ነበር፡፡

በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ ዑቃቤ እየሆኑ በየዘመናቱ የሚመጡ ሕዝቦች አሉ፡፡ ከግራኝ አሕመድ ጦርነት
በኋላ ፖርቱጋሎች መጥተው ነበር፡፡ በሀገሪቱ በነበሩ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ብጥብጦች ውስጥ
እጃቸውን ነክረው፣ በሌላም በኩል ቤተ ክርስቲያን እና ድልድይ ሠርተው ሄደዋል፡፡ በእነርሱ ዘመን
የተሠሩ ድልድዮች ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ተሻግረው ዛሬም ለታሪክ ተቀምጠዋል፡፡

ከፖርቱጋሎች ጋር ተዋልደው የቀሩ አያሌ ኢትዮጵያውያንም አሉ፡፡ በምዕራቡ የጎንደር ክፍል ራሳቸውን
የፖርቹጋል ዝርያ አድርገው የሚቆጥሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡

በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መጀመርያ ላይ ኢትዮጰያ ፈረንሳይ ፈረንሳይ ትሸት ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ
አሜሪካኖች የሀገሪቱ ውቃቤዎች ሆኑ፡፡ አሥመራ ላይ ቃኘው ጣቢያን ተክለው ፖለቲካውንም
ወታደራዊው ተቋሙንም የበላይ ጠባቂነት ተሾሙበት፡፡

የ1966 አብዮት ደግሞ ኩባ እና ራሽያ የሚባሉ የበላይ ጠባቂዎችን ይዞ መጣ፡፡ ኩባዎች ኢትዮጵያን
ተምነሸነሹባት፤ ኢትዮጵያውያንም ኩባ ሄደው ኖሩ፤ ተማሩ፡፡ እነ ፊደል ካስትሮን የአያቶቻችን ያህል

dkibret@gmail.com
-1-
የዳን
የዳንኤል ዕይዎታች
www.danielkibret.com
አወቅናቸው፡፡ የአራት ሰዓታት ንግግራቸውንም የቅዳሴ ያህል ቆመን አዳመጠን፡፡ ኩባ ከቆዳ ስፋቷ በላይ
በኛ ልብ ውስጥ ቦታ አገኘች፡፡

ኢትዮጵያ የሶቪየት አንዷ ክፍለ ሀገር እስክትመስል ድረስ የሶቭየቶች መንፈስ ወረረን፡፡ በወታደር ቤት
የነበሩት ቁምጣዎችም ብሬዥኔቭ ተባሉ፡፡ ሥነ ጽሑፋችንም ከግእዝ ወጥቶ ወደ ራሽያ አቀና፡፡ እንደ ሰው
በምድር እንደ ዓሳ በባሕር፣ የምንጮች መፍለቂያ ተራሮች ናቸው፤ ልጅነት፣ የሚባሉ መጻሕፍትን ኩራዝ
አከፋፈለን፡፡ እነ ማክሲም ጎርኪይን ከነሐዲስ ዓለማየሁ በላይ አደነቅናቸው፡፡ እነ ቀስተ ደመና
መጽሔቶችን አነበብን፡፡ የሞስኮ ራዲዮም አዳመጥን፡፡ ሌኒን የሚባል ሰው በአካል ባናገኘውም በመንፈስ
ከኛ ጋር ለአሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡

ያም ደግሞ አለፈና የቻይና ዘመን መጣ፡፡

ነገሩ ቻይኖች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡ እኛም ስንጓዝ እነርሱም ሲመጡ
መክረማችንን የሚያስረዱ ድርሳናት አሉ፡፡ ፒንግ የተባለው የቻይና ንጉሥ ነግሦ በነበረ ጊዜ (ከ1 እስከ 6
ዓም) አውራሪሶች በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኝ «አግአዚ» ከሚባል ሀገር ይገቡ እንደነበር የሚገልጡ
የቻይና መዛግብት አሉ፡፡ ይህ አግአዚ የተባለው ሀገርም ኢትዮጵያ ሳትሆን እንደማትቀር ይታመናል፡፡

በታግ ሥርወ መንግሥት ጊዜ (618 - 907 ዓም) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ግንኙነት ነበራት፡፡
በዚያም ባሮችን፣ ዝሆኖችን፣ አውራሪሶችን፣ የከበሩ ድንጋዮችን እና ሌሎችንም ታስገባ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ
ውስጥ በአርኬዎሎጂ የተገኙ የቻይና ሳንቲሞች የዚህ የንግድ ግንኙነት ውጤቶች መሆናቸው ይታመናል፡፡

በዘመናዊው ታሪካችንም በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ውስጥ ኢጣልያን ኢትዮጵያን መውረሯን ከተቃወሙት አምስት
ሀገሮች አንዷ ቻይና ነበረች፡፡ ሁለቱ ሀገሮች የመጀመርያውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እኤአ
በዲሴምበር 1 ቀን 1970 ዓም ነበር፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለች ቻይና እዚህ ደርሳለች፡፡

ኢትዮጵያውያን ቻይናን የሚያውቋት በብዙ ጠባይዋ ነው፡፡ አብዛኞቹ የመርካቶ ሰዎች የቻይኖች ደንበኞች
ናቸው፡፡ ሁለመናችን ከቻይና ሆኗል የሚመጣው፡፡ እንዲያውም ባለፈው ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ሥዕሎችም
ቻይና ተመርተው እንደሚገቡ ሰምቻለሁ፡፡ ነገ ንዋያተ ቅድሳትም ከቻይና ማስመጣታችን የማይቀር ነው
ማለት ነው፡፡

የቻይና ዕቃዎች ርካሾች ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ ለገሐር ላይ አንድ የቻይና ሙሉ ልብስ በአሥራ አምስት
ብር ሲሸጥ አይቻለሁ፡፡ እውነት ስላልመሰለኝ ጠጋ ብዬ አየሁት ልብስ ነው፡፡ ታድያ አንዱ ተረበኛ

dkibret@gmail.com
-2-
የዳን
የዳንኤል ዕይዎታች
www.danielkibret.com
«ለመሆኑ ይታጠባል?» ብሎ ጠየቀ፡፡ ሻጩ ምን እንዳለው ታውቃላችሁ «በአሥራ አምስት ብር
የሚታጠብ ሱፍ ያምርሃል? ባክህ ዩዝ ኤንድ ስሮው ነው»፡፡

ይህን ስሰማ አንድ የድሮ ቀልድ ትዝ አለኝ በድሮ ዘመን መንግሥት የመምህራን እጥረት ስለነበረበት
አሥራ ሁለተኛ ክፍል ያጠናቀቁትን መጠነኛ ሥልጠና ሰጥቶ ያሠማራ ነበር አሉ፡፡ እነዚህም «የድጎማ
መምህራን» ይባሉ ነበር፡፡ ደሞዛቸውም መቶ ሰማንያ አምስት ብር ነበር ይባላል፡፡ ታድያ አንዱ የድጎማ
መምህር የእንግሊዝኛ ክፍል ውስጥ ገብቶ ክኖው፣ ክናይፍ፣ ክኖውሌጅ፣ እያለ ያስተምራል፡፡ እንዳጋጣሚ
በዚያ ጊዜ ተቆጣጣሪ ይገባና የሚያስተምረውን ይሰማዋል፡፡ በኋላ ታድያ ቢሮው ጠርቶ «እንዴት
ክናይፍ፣ ክኖው፣ ክኖውሌጅ እያልክ ታስተምራለህ?» ይለዋል፡፡ ያ የድጎማ መምህርም «ታድያ በ185
ብር ደሞዝ ናይፍ፣ ኖው፣ ኖውሌጅ እያልኩ እንዳስተምርልህ ትፈልጋለህ?» አለው አሉ፡፡ በአሥራ
አምስት ብር የሚታጠብ ሱፍ ትፈልጋለህ» ያለውን እንዳትረሱ፡፡

ሌላኛው ቀበል አድርጎ «በተለይ ዝናብ ከመጣ ከቤትህ መውጣት የለብህም፡፡ ውጭ ከሆንክም ሮጠህ
አንድ ቤት መግባት አለብህ፡፡ ያለበለዚያ ዝናቡ ልበሱን አጥቦ ይወስደውና ራቁትህን ትቀራለህ» አለና
ሁኔታውን አሟሟቀው፡፡ «ኖ ኖ ኖ እንደርሱ አይ ደለም» አለ ደግሞ ሌላው፡፡ «ዝናብ ከመታህማ
ራስህን ታጣዋለህ፤ ምክንያቱም የልብሱ ቀለም ይቀየርና ሌላ ልብስ ነው የሚሆነው፡፡»

ቻይና ለአፍሪካ እና ለአሜሪካ ገበያ የምትሠራው ይለያያል፡፡ አሜሪካኖችም ቢሆኑ በቻይና ምርቶች ላይ
የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ እዚያ ግን ደረጃቸውን እና ጥራታቸውን የጠበቁ የቻይና ምርቶችን ነው የምታ
ገኙት፡፡ አንድ ቻይና የሚገኝ ወዳጄ እንዳለው ቻይና አንድን ምርት በምን ያህል ጥራት ልስራልህ? ብሎ
አይጠይቅም፡፡ በምን ያህል ወጭ ልሥራልህ? እንጂ፡፡ አንድን የጫማ ዓይነት መልኩ እና ቅርጹ
ተመሳሳይ ሆኖ የመቶም የአንድም ብር አድርጎ ማምረት ይቻላል፡፡ በቻይና፡፡

ቻይኖች መንገድ ሲሠሩ አንድ መንደር ይደርሳሉ፡፡ የመንደሩ ሰዎች ይጠመቁበት የነበረው ጠበል
በመንገዱ ሥራ ምክንያት ይቋረጥባቸዋል፡፡ ታድያ መንደርተኞቹ አንድ ሆነው ቻይኖቹ ጋ ይሄዳሉ፡፡
«ጠበላችን እንዲቋረጥ አድርጋችሁታል» ይሏቸዋል ቻይኖቹን፡፡ «ችግር የለም» አሉ ቻይኖቹ፡፡ «ሳምፕሉን
ስጡን እና አምርተን እናመጣላችኋለን»

dkibret@gmail.com
-3-
የዳን
የዳንኤል ዕይዎታች
www.danielkibret.com
አንዳንድ ነጋዴዎች የአሜሪካን ወይንም የአውሮፓን ሞዴል ይገዙና ወደ ቻይና ይሮጣሉ፡፡ እዚያም
በአነስተኛ ዋጋ እና በመናኛ ጥራት ያስመርቱታል፡፡ ከዚያም ለእነርሱ በመቶ ፐርሰንት ትርፍ፣ ለእኛ ደግሞ
በርካሽ ይሸጡልናል፡፡

ቻይኖች ጠንካራ ሠራተኞች መሆናቸውን አበሻ በሙሉ መስክሮላቸዋል፡፡ ሥራ አይንቁም፣ በሥራም


አያለግሙም፡፡ እንዲያውም «በሥራ መለገምን ኢትዮጵያ መጥተን ነው የተማርነው» ይላሉ አሉ፡፡ እነርሱ
የሠሩትን የመንገድ ዳር ብረት አበሻ ነቅሎ ሲወስድባቸው «እነዚህ ሰዎች ሌላ ሀገር አላቸው ወይ?»
ብለው የጠየቁትም ወደው አይደለም፡፡

የቻይኖች የሀገር ፍቅር በመፈክር እና ባንዴራ በመልበስ ብቻ የሚገለጥ አይደለም፡፡ ለሀገራቸው


የማይሆኑላት ነገር የለም፡፡ አሜሪካ ያሉ ቻይኖች አንድ የሚጠረጠሩበት ነገር ማንኛውንም ለሀገራቸው
የሚጠቅም ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ወደ ቻይና በማሸጋገራቸው ነው፡፡ ለቻይኖች ቻይናም ተወለዱ
አሜሪካ ሀገራቸው ቻይና ናት፡፡ እንኳን በቀላሉ የሚገኘውን ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ቀርቶ በድብቅ እና
በስለላ የሚገኘውን ወታደራዊ ምሥጢር እንኳን እየፈለፈሉ ወደ ሀገራቸው ይልካሉ ተብለው ይታማሉ፡፡
ይህንን ያህል የሀገራቸው ፍቅር ዘልቆ የገባቸው ቻይኖች እኛን «ሌላ ሀገር አላቸው ወይ?» ብለው
ቢጠይቁ አይፈረድባቸውም፡፡

ቻይኖች ያኙትን ሁሉ የሚበሉ ናቸው እየተባለ ተመርጦ በሚበላበት በሐበሻ ምድር ይታማሉ፡፡ ታድያ
1.5 ቢሊዮን ሕዝብ ያገኘውን ካልበላ እንዴት ሆኖ ሊኖር ኖሯል? ገበሬው ቻይኖች መንገድ
ከሚሠሩበት ቦታ አጠገብ ነበር አሉ ቤቱ፡፡ ለመኪኖቻቸው እና ለራሳቸው የሚሆን ውኃ የሚያመላል
ስላቸው አህያ ይፈልጉና ቻይኖቹ ያነጋግሩታል፡፡ ሰውዬውም በዋጋ ይስማማል፡፡ «ነገር በአህያዬ ፋንታ
እኔ ነኝ ውኃውን የማመላልሰው» ብሎ ታድያ በየቀኑ ውኃ የሚያመላልሰው ራሱ ነበረ፡፡ ቻይኖቹ
ገረማቸውና ጠየቁት፡፡ «አንተ ከምታመላልስ ለምን አህያህን አታከራየንም?» ሰውዬውም መለሰ «አህያዬ
እንደወጣች ባትመለስስ?» ቻይና ያገኘውን ነው የሚበላው ሲባል ሰምቶ ነዋ፡፡

ቻይኖችን እንደ ሌሎች የውጭ ዜጎች በውድ እና በተለዩ የሥራ ቦታዎች ላይ አታዩዋቸውም፡፡ ከትናንሽ
እስከ ግዙፍ ሥራዎች ላይ ተሠማርተዋል፡፡ ከከተማ እስከ ገጠር ገብተዋል፡፡ እንዲያውም አንድ ቦታ
የሰማሁት ቀልድ አለ፡፡ አንድ የገጠር መንገድ ቻይኖች ያሸንፉና ሠርተው ያስረክባሉ፡፡ እነርሱ ፕሮጀክቱን
በጨረሱ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በመንደሩ የሚወለዱት ሁሉ ዓይናቸው ሞጭሟጮች ቁመታቸው
አጫጭሮች ሆኑ አሉ፡፡ ደግሞ የሚገርመው የአብዛኞቹ ልጆች ስሞች «ቻይና» ነው የሚባለው፡፡

dkibret@gmail.com
-4-
የዳን
የዳንኤል ዕይዎታች
www.danielkibret.com
እና በዚህ የተነሣ ቻይኖች ኮንትራት በወሰዱባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ዳር እና ዳር ያሉ መንደሮች
ወንዶቹ እርሻ እና ከብት ጥበቃ መሄድ እያቆሙ ነው ይባላል፡፡ አንድ አባ ወራ ሲወጣ አንድ ቻይና
እየገባ ተቸግረው ነው አሉ፡፡

ቻይኖች ማኅበራውያን ናቸው፡፡ ለጠጥ ያለ ሆቴል፣ ቀብረር ያለ ቡና ቤት አታገኟቸውም፡፡ ጠጅ ቤት፣


አረቂ ቤት፣ ሥጋ ቤት፣ ሽሮ ቤት፣ እማማ ቤት፣ ብትገቡ ቢያንስ አንድ ቻይና አታጡም፡፡ እያቃጠ
ላቸውም ሆነ እያንገበገባቸው ከቃርያ እና ሚጥሚጣ ጋር ሲታገሉ ታገኟቸዋላችሁ፡፡ ድሬዳዋ በሄድኩ ጊዜ
ቻይኖች መንገድ ዳር አንጥፈው ጫት ሲቅሙ አይቼ ገርሞኝ ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን ሌሎችን ማስመጥ የምንችል ሕዝቦች መሆችንን ያየሁት በቻይኖች ነው፡፡ ቻይና አሜሪካ
መጥቶ ራሱንም ባሕሉንም ጠብቆ ይኖራል፡፡ አንድ ቻይና ዛሬ ከታየ ከዓመት በኋላ «ቻይና ታውን»
ይመሠረታል ተብሎ የሚነገርላቸው ቻይኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰምጠው ቀርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘፈንለት፣ የሚለፈፍለት እና ቅኔ የሚወርድለት ዓባይ ካይሮ ላይ ስታዩት


ያናድዳችኋል፡፡ ማንም እንደ ፈለገ በየመንደሩ ሲጎትተው ታያላችሁ፡፡ አንዱ ከብት ያጠጣበታል፤ አንዱ
ይዋኝበታል፣ አንዱ ልብስ ያጥበበታል፣ አንዱ ቆሻሻ ይደፋበታል፣ አንዱ መንገድ ያጥብበታል፣ አንዱ ጀልባ
ይቀዝፍበታል፡፡ ጎጥ ለጎጥ፣ መንደር ለመንደር፣ ቱቦ ለቱቦ፣ ስርቻ ለስርቻ ያንከራትቱታል፡፡

ቻይናም ኢትዮጵያ እንዲሁ ነው የሆነው፡፡ አረቂ ጠጭ፣ ጫት ቃሚ፣ ጥሬ ሥጋ ቆራጭ ሆኖ ቀርቷል


ቻይና፡፡ ካዛንቺስ እና ቺቺንያ ያመሻል ቻይና፡፡ «ከተቀላቀልክ ማን ይለይሃል» አለ የወሎ ገበሬ
እውነቱንኮ ነው፡፡ መንገድ የሚሠራ ቻይና አህያውን ይገጭበታል፡፡ ገበሬው ዘራፍ ብሎ አንገቱን
ይጨመድዳል፡፡ «ክፈል» ይላል ገበሬው፡፡ ቻይና ሆዬ «ገንዘብ አልያዝኩም ካምፕ እንሂድና ልስጥህ»
ይላል፡፡ «አይሆንም» አለ ገበሬ፡፡ «እዚያ ከዘመዶችህ ጋር ከተቀላቀልክ ማን ይለይሃል? ሁልህም
ተመሳሳይ ነህ» አለ አሉ፡፡ ቻይና ተቀላቅሏል፡፡

የዓለምን ኢኮኖሚ እያስጠነገሩ፣ ለአሜሪካ እያበደሩ፣ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው በሚለው
የዲፕሎማሲ መርሐቸው እየተመሩ ቻይኖች አዲሶቹ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ ቢያንስ ሌላ የሚተካቸው
እስኪመጣ ድረስ፡፡ ይቺን ፎርጅድ ምርታቸውን ቢተውን ግን እንዴት በወደድናቸው ነበር፡፡

አሌክሳንድርያ፣ ቨርጂንያ

© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው ““አዲስ


አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ
በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም
አይገባም።።

dkibret@gmail.com
-5-
የዳን
የዳንኤል ዕይዎታች
www.danielkibret.com

dkibret@gmail.com
-6-

You might also like