You are on page 1of 2

ከ41 ዓመታት በኋላ ካራማራን ስናስታውስ፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2011 ዓ.ም(አብመድ) ወቅቱ ከሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት
ወር 1970 ዓ.ም ነው፡፡ ቦታው ደግሞ ምሥራቃዊው የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን፡፡ ቦታው
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሶማሌ ላንድን የሚያዋስን ከመሆኑም በላይ ግመል፣ በግና ፍየል
በማርባት ላይ ኖሯቸው የተመሠረተ አርብቶ አደሮች የሚኖሩባት ሞቃታማ የኢትዮጵያ
ምድር ነው ኦጋዴን፡፡
ሶማሊያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በርዕሰ ብሔርነት የመሩት ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ
የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሰው ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሌ ላንድ
የመመሥረት የቆየ ራዕይ ነበራቸው፡፡ ዕቅዳቸውን ዳር ለማድረስ ያልደገፉት የኢትዮጵያ
መንግሥት ጠላት ያልተጠቀሙበት መንገድ ሁሉ አልነበረም፡፡ የፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ
መንግሥት ይፋዊ ድጋፍ ከሚያደርግላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀናቃኞች አንዱ
የምዕራባዊ ሶማሌ የነፃነት ግንባር አንዱ ነበር፡፡ የዚህ ድርጅት ዋና ተልዕኮ ደግሞ ሶማሌ
በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ከመፈፀሟ በፊት በህቡዕ ተደጋጋሚ ጥቃት
በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም ነበር፡፡
ጦርነቱ በግልፅ በታወጀበት 1969 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት
የሶማሌ ጦር የበላይነቱን ወስዶ ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬድዋ ድረስ ዘልቆ ገባ፡፡ በምዕራባዊ
የሶማሌ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ሲዳከም የነበረው የኢትዮጵያ የመከላከያ
ኃይልና ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዘርበት የነበረው የኦጋዴን አካባቢ ነዋሪ በቀላሉ ጥቃት
እንዲደርስበት አደረጉት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመጀመሪያ በሶብየት ኅብረት እና
በመቀጠልም በአሜሪካ ድጋፍ የነበረው የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ፡፡
ሶማሌ ግልፅ ጦርነት ካወጀችበት ጊዜ ጀምሮ ለምዕራባዊ የሶማሌ ነፃነት ግንባር
የምታደርገውን ድጋፍ አቋረጠች፡፡ ነፃ አውጭ ግንባሩም የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ የታላቋን
ሶማሌ ላንድ የመመሥረት ዓላማ ድጋፍ በማቆም ነፃ ምዕራባዊ ሶማሌን ለመመሥረት ትግል
ጀመረ፡፡ የሁለቱም ትግል ግን ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ግዛት ማውጣት ነበር፡፡
ምንም እንኳን ቀስ በቀስ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት ቢመጣም የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ጦር
የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን
ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር፡፡
በመጨረሻም የፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ወደ ፍፁማዊ ማጥቃት እና እልህ
አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ እርምጃዎች መታየት ጀመሩ፡፡ ከኦጋዴን
ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ ‹‹ካራማራ›› ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የጦር አረሮች
ምድሪቱን ዘነቡባት፡፡ ገብሩ ታሪክ (2000) በካራማራ ጦርነት ላይ ባደረጉት ጥናት ከሁለቱም
ወገን ከ6 ሺህ 100 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ፤ ከ12 ሺህ 900 በላይ ደግሞ ለአካል ጉዳት
ተዳረጉ፡፡
ታላቋን ሶማሌ ላንድ የመመሥረት ራዕዩ ጫፍ የደረሰ የሚመስለው ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ
በመጨረሻም ‹‹በዚች ዓለም ላይ ምንም ቋሚ የሆነ ነገር የለም›› ለማለት ተገደደ፤ የዚያድ
ባሬ ጦር ድል ሆነ፡፡ በዚያውም ታላቅ ለመሆን የታቀደላት ሶማሊያ ከሁለት አስርት ዓመታት
በላይ በማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብታ ፈራረሰች፡፡
የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት ሀገር ወዶ ዘማቾች እና 16 ሺህ የሚደርሱ
የፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮዋ ኩባ አጋር ወታደሮች ይህን ታሪካዊ ጦር ተቀላቅለው የዚያድ
ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት አወጁ፡፡
ልክ ከ41 ዓመታት በኋላ በዚህ ታሪካዊ ቀን ዛሬ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም የሶማሌ
ፕሬዚዳንት ሙሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የምጣኔ ሀብት፣ ሰላምና
ደኅንነት ትስስር እንዲሁም ለሁለትዮሽ ስምምነቶች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የማያልፍ የለም፤ ጠብም ፍቅርም ያልፋል፡፡ ለሚያልፍ ስልጣንና ሐሳብ የሰው ሕይወት
ማስከፈል ግን ተገቢ አልነበረም፤ ዚያድ ባሬ ከ41 ዓመታት በፊት ሺዎች እንዲቀጠፉ ምክንያት
ነበሩ፡፡ ድርጊታቸው ግን እርሳቸውን ጨምሮ ማንንም አልጠቀመም፡፡
ምንጭ፡- አፍሪካ ፎከስ እና የገብሩ ታሪክ ጥናት
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

You might also like