You are on page 1of 5

ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ (የበጋው መብረቅ)

ትውልድ እና የልጅነት የሕይዎት ዘመን


የጃገማ አባት ኬሎ ገሮ (አባ ጃገማ)፤ የሜጫ ኦሮሞ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ኬሎ ማለት “የመስቀል አበባ” ማለት ነው፡፡ ጃገማ
የአባታቸው የኬሎ ገሮ የፈረሳቸው ስም ነው፡፡ የጃገማ እናታቸው ወይዘሮ ደላንዱ ይባላሉ፡፡ ደላንዱ በኦሮምኛ ቋንቋ “ቄጠማ” ማለት
ነው፡፡ ወይዘሮ ደላንዱ ውብ የሆኑ ቆንጆ፤ የባላባትና የጀግና ዘር ሲሆኑ የአምቦ አካባቢ ሴት ናቸው፡፡ የመስቀል አበባው ኬሎ ገሮ እና
ቄጠማዋ ደላንዱ ተገናኝተው ትዳር መሠረቱ፡፡ ኬሎ ገሮ በአካባቢው ብዙ ሐብት ያላቸው የታወቁና የተከበሩ ሰው ነበሩ፡፡ የኬሎ ገሮ፤
ባለቤታቸው የሚወልዱት ልጅ ወንድ ከሆነ የፈረሴን ስም አሰጠዋለሁ ብለው ስለነበረ አባታቸው በተናገሩት ቀን የተወለደው ወንድ
ልጅ ጃገማ ተባለ፡፡ ጃገማ በኦሮምኛ ቋንቋ “ትልቅ ዛፍ” ማለት ነው፡፡ ጃገማ ኬሎ በቀድሞው አጠራር በጅባትና ሜጫ አውራጃ፣
በደንዲ ወረዳ ዮብዶ በተባለ ስፍራ ጥር 21 ቀን 1913 ዓ.ም. ማክሰኞ ማታ ተወለዱ፡፡ የጃገማ አባት ኬሎ ገሮ ልጃቸውን በ 70 ዓመት
የአዛውንት እድሜያቸው ወንድ ልጅ በማግኘታቸው ከልክ ያለፈ ደስታ ተሰማቸው፡፡
በአካባቢው ተከስቶ በነበረ በሽታ ምክንያት፤ ጃገማ በተወለደ በአንደ አመቱ እናቱ በመሞታቸው በአክስቱና በሞግዚት እንዲያድግ አባቱ
ወሰኑ ። አክስቱም ጃገማን ከወንድሙ ጋር ፀበል አስጠምቀው እና ቄስ ቀጥረው ዳዊት እንዲማር አድርገዋል። የጃገማ አባት ልጃቸው 10
ዓመት እንደሞላው በ 1923 ዓ.ም. አረፉ፡፡ የጃገማ አክስት ጃገማን ዘመናዊ ትምህርት እንዲማር በማለት በቀድሞው ተፈሪ መኮንን
ትምህርት ቤት አስገብታው ለ 3 ወራት ተምሯል፡፡ በኋላም ወደ ትውልድ ሥፍራው ተመልሶ በወጣትነቱ፤ ፈረስ ግልቢያ፣ ጦር
ውርወራ፣ ጋሻ ማንገብ፤ ምክቶሽ እና ውሀ ዋና ተማረ፡፡ ወጣቱ ጃገማ መራብና መጠማትን ሳይቀር ተለማመደ፡፡ አልፎ ተርፎ ዝሆንና
ጎሽ አድኖ ለመግደል ወደ ጌድዮ ሄዶ ተይዞ ተመልሷል፡፡

የአርበኝነት ጅማሮ
ፋሺስት ኢጣሊያ በ 1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ጃገማ ገና በ 15 ዓመቱ አርበኛ ሆኖ የፋሺስትን ጦር ለመፋለም ወሰነ። የአጎቱ ልጅ
ከሆነው ከአሰፋ አባ ዶዮ ጋር ወደ ጫካ ገቡ። እህቱና ወንድሞቹም ተከተሉት። ገበሬዎች፣ ወታደሮች እና ሾፌሮች ሳይቀሩ ከጃገማ ጋር
የተቀላቀሉት ቁጥራቸው 30 የሚደርሱ አርበኞች ጠላትን ለመውጋት ጫካ ገቡ። በአባቱ የተመረጠው፣ ግርማ ሞገስና የማስተዋል
ችሎታ የታደለውን ወጣት ጃገማን፤ እድሜያቸው ከእርሱ በእጥፍ የሚልቁት አርበኞች ተሰባበስበው ገና በለጋነቱ መሪያቸው አድርገው
መረጡት፡፡ የጃጋማ አባት ኬሎ ገሮ በአካባቢው ዘንድ ይወደዱና ይከበሩ ስለነበር የአካባቢው ሕዝብ በታዳጊው ጃገማ የሚመሩትን
አርበኞች በልዩ ልዩ መንገዶች ያግዛቸው ነበር። በፋሺስት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር የጠላትን ጦር መፈተን ጀመሩ። የጃገማ
አርበኞች ፋሺስቶች ጥይት የሚጭኑባቸውን እንስሳትን በጥይት በመምታት እና ፋሺስቶችና ባንዳዎች ሲሸሹ ደግሞ መሳሪያና ጥይት
እየሰበሰቡ ማከማቸት ቀጠሉ፡፡ ጣሊያኖችም ጃገማንና ተከታዮቹን ለመደምሰስ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። የጃገማ ተከታዮች
ቁጥራቸው ጨመረ። ፋሺስቶች ተጨማሪ ምሽጎችን ለመገንባት ቢያስቡም ቀድመው በገነቧቸው ምሽጎች ውስጥም እንደልባቸው
መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀሩ። የ 18 ዓመት ወጣት በሆነው በጃገማ ኬሎ የሚመሩት አርበኞቹ በሚያዝያ ወር 1931 ዓ.ም. ሐሮታና ጀልዱ
የነበረውን የጠላት ጦር ግንኙነት ለመበጣጠስ የወሰዷቸው እርምጃዎች አዲስ አበባ ድረስ ተሰሙ፡፡ አግብታ ወለጋ ጠቅላይ ግዛት
ትኖር የነበረችውም እህቱ ሌንሴ፤ የወንድሟን መሸፈት ስትሰማ ባሏን ፈታ ወንድሟን ለማገዝ ጫካ ገባች፡፡ ይህም ለወንድሟ ጥንካሬን
ፈጠረለት፡፡ ብዙ የነፃነት ተዋጊዎችም እነጃገማ ያሉበት ድረስ ሄደው ተቀላቀሉ፡፡ በጃገማ አባት ያልበላ፣ ያልጠጣ፣ ከብት ያልተቀበለ
ስለሌለ፤ የአባቱ ውለታ ያለበት የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ለወጣቱ አርበኛ ለጃገማ ደጋፊው ሆነ፡፡ ዶሮና እንቁላል ለጣሊያን ወታደሮች
እየሸጡ በሚያገኙት ገንዘብ ከባንዳዎች ጥይት ገዝተው ለአርበኞች ያቀብላሉ፡፡ ጠላትን እየሰለሉ መረጃ ለአርበኞች ያቀብላሉ፡፡የነጃገማ
አርበኞች የደፈጣ ውጊያ ስልትን በመጠቀማቸው የጠላት ጦር ጥይት እንዲያባክን በማድረግ፣ የአካባቢው ሰው ከፋሺስት ወታደሮችና
ከባንዳዎች ላይ ጥይት እንዲገዛ በማስተባበር የመሳሪያ ክምችታቸውን እያጠናከሩ ሄዱ፡፡ በጥቅምት ወር 1933 ዓ.ም. የ 20 ዓመት
ወጣቱን የጃገማን ጦር ለማጥቃት ወደ ሰንጎታ ተራራ የሄደው 350 የፋሺስት ጦር ጃገማ በሚመራቸው በ 17 አርበኞች ተሸነፈ። በዚህ
ውጊያ የጃገማ አርበኞች ብዙ የጠላት ወታደሮችን ገደሉ፤ ባንዳዎች የዘረፉትን ንብረት አስመለሱ። የጠላት ወታደሮችንና ብዙ መሳሪያም
ማረኩ። የጃገማ ጀግንነትም እየገዘፈ ሄደ ። የአካባቢው ሕዝብም የጃገማን ጀግንነት ከቅድመ አያቱ ጀግንነት ጋር እያነፃፀረ በማውራቱ
በጠላት ጦር ካምፕ ውስጥ ፍርሃት ይበልጥ ነገሠ። በኋላም ወደ ወሊሶ ሄዶ በአካባቢው ከፋሺስት ጦር ጋር ሲዋጉ ወደነበሩት ወደእነ
ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋር ሄዶ ተቀላቀለ። የፋሺስት ጦር በአርበኛው በደጃዝማች ገረሱ ላይ ውጊያ ከፍቶ በነበረበት ወቅት
ጃገማም በዚሁ ውጊያ ላይ ተሳታፊ ስለነበረ የማታ ማታ ድሉ የአርበኞቹ ሆነ። በዘህም በተገኘው ድል ምክንያት ደጃዝማች ገረሱ፤
“አንተን የመሰለ ጀግና የወለደች እናት ትባረክ።” በማለት ጃገማን አመሰግነውታል። ጃገማ በአንድ ውጊያ ላይ የማረከውን የኢጣሊያ
ወታደር እንደማይገደል ከነገረው በኋላ ስለአርበኞቹ ኃያልነት፤ ስለፋሺስቶች ፈሪነትና አረመኔነት አስረድቶት፤ “...ከምርኮኝነት ነፃ
የምትወጣው ለጥይት መግዣ የሚሆነኝን 10 ሺህ ሊሬ ከከፈላችሁኝ ብቻ ነው።” አለው። ጃገማም በአንድ ኢጣሊያዊ መልዕክተኛ
አማካኝነት 10 ሺህ ሊሬ ተቀብሎ ምርኮኛውን ፈቶታል፡፡ ምርኮኛውም ወደጦር ሰፈሩ ሄዶ ስለጃገማ ጀግንነት ለአለቆቹ ሲነግራቸው
በንግግሩ ደስ ባለመሰኘታቸው ምርኮኛውን ወደ ሌላ ስፍራ አዛውረውታል በአንድ ወቅት ጃገማ ከጭልሞ ወደ አሬራ ሲሄድ ጊንጪ
ገበያ ውለው ወደ ጭልሞ ሲሄዱ የነበሩ ገበሬዎች በሽፍቶች ሲዘረፉ ተመለከተ፡፡ ጃገማ ተወርውሮ ሄዶ ዘራፊዎቹን በማባረር
የገበሬዎቹን ንብረት አስመለሰ፡፡ በዚህን ወቅት ጃገማን ያዩት ፋሺስቶችና ባንዳዎችም በጃገማ ላይ አደጋ ለመጣል ሞክረው በጃገማ
አስደናቂ የአፀፋ ውጊያ ለቁስለኛነትና ለሽሽት ዳረጋቸው፡፡ በአካባቢው የነበረው የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ስለሁኔታው ሰምቶ ለጃገማ
ደብዳቤ ፃፈለት፡፡ የደብዳቤው ይዘትም ጃገማ የገበሬዎቹን ንብረት ማስመለሱ መልካም እንደሆነ፣ ራሱን ለመከላከል በወሰደው እርምጃ
የኢጣሊያ መንግሥት እንደማይጠይቀውና ምኅረት ስለተደረገለት በአካባቢው ለሚገኘው የኢጣሊያ ጦር እጁን እንዲሰጥ የሚገልፅ
ነበር፡፡ ጃገማም ደብዳቤውን ተመልክቶ፤ “…ከሰው አገር ላይ መጥቶ፤የሰው መሬት ወስዶ ...‹ሙሉ ምኅረት ተደርጎልሃልና ግባ› አለኝ፡፡
አነዚህ ደፋሮችና ግፈኞች አገሬን ለቀው እስካልሄዱ ድረስ አይማረኝ ብምራቸው፡፡” በማለት ለጓደኞቹ ተናግሯል፡፡ እኔ የማውቀው አለ
ጃገማ፤ “እኔ የማውቀው፤ ምኅረት ሰጪ አንድ ፈጣሪን ነው፡፡ ሰው ምኅረት የሚሰጥ ከሆነ ግን ምኅረት ሰጪው አገር የወረረ ሳይሆን
አገሩ የተወረረበት እኔ ነኝ፡፡” በማለት የመልስ ደብዳቤ ለፋሽስቶች ልኮላቸዋል፡፡
ከምሽግ ሰበራ ታሪካቸው በጥቂቱ
የአዲስ ዓለም የፋሽስት ምሽግ ሰበራ
ጃገማ በአርበኝነት ዘመኑ ከፈጸማቸው አኩሪ ገድሎች መካከል የፋሺስት ጦር ይመካበት የነበረው የአዲስ ዓለም ምሽግ ሰበራ ፈፅሞ
የሚዘነጋ አይደለም። ጃገማ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪን ለመርዳት ወደ ወሊሶ ሄዶ በነበረበት ወቅት፤ “...ጃገማ፤ ያን የተመካከርንበትን ጉዳይ
ጨርሻለሁና ዛሬ ነገ ሳትል ሰራዊትህን ይዘህ ቶሎ ና።...” የሚል መልዕክት ከስመ ጥሩዋ የውስጥ አርበኛ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ
ደረሰው። ጃገማም ከአዲስ አበባ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዲስ ዓለም በፍጥነት አቅንቶ የምሽግ ሰበራው የጦር
አዝማች ሆነ። ጥቃቱ እንዴት እንደሚፈፀም የሚያሳይ መመሪያ ለባልደረቦቹ አስረድቶ የሥምሪት ትዕዛዞችን ሰጠ። ራሱ ምሽጉ ውስጥ
ገብቶ ቦምብና ሌሎች መሳሪያዎችን ይዘው የነበሩ የፋሺስት ጦር ባለስልጣናትን ገድሎ 3 ሺህ ጠመንጃዎችንም ማርኮና ዘርፎ
እስረኞችንም አስፈትቷል። በዘመቻው ላይ ከአርበኞቹ ወገን የሞተው አንድ ሲሆን ቁስለኛ አንድ ብቻ ነው፡፡ ከጠላት ወገን ግን 73
የኢጣሊያ የምሽጉ ጠባቂዎች ተገድለዋል፡፡
የጭልሞ የፋሽስት ምሽግ ሰበራ
በመጋቢት ወር 1933 ዓ.ም ጃገማ የጭልሞን ምሽግ ከቦ በፋሺስት ጦር ላይ ተኩስ ከፈተ። “…እጃችሁን ካልሰጣችሁ አንላቀቅም!” የሚል
መልዕክትም አስተላለፈ። የፋሽስት ጦር እንደራደርና እጅ እንሰጣለን ካሉ በኋላ አዘናግተው ሊያመልጡ ሲሉ ከአርበኞቹ ተኩስ
ተከፈተባቸውና 13 የኢጣሊያ ወታደሮችና 1 ሺህ 500 ባንዳዎች ተማረኩ። ጊንጪም በጃገማ አርበኞች ቁጥጥር ስር ዋለች።
የሐሮታ የፋሽስት ምሽግ ሰበራ
ጃገማ ወዲያውኑ የኢጣሊያ ጦር የሚተማመንበት የሐሮታ ምሽግ ላይ ጥቃት እንዲከፈት አዘዘ። የጠላት ጦር አንድ ጊዜ እየሸሸ፤ ሌላ
ጊዜ እያጠቃ መፋለሙን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ ጃገማ ብቻውን ሆኖ ቦታ እየቀያየረ መድፍ ሲተኩስ የፋሺስት ጦር ተስፋ ቆርጦ ለመጨረሻ
ጊዜ ሸሸ፤ ከሞት የተረፈውም ተማረከ። የጃገማ ጦርም ድል አድርጎ አዲስ ዓለም ገባ። ሆለታንም በቁጥጥሩ ስር አደረገ፡፡ ጃገማ ኬሎ
ይመራቸው የነበሩት የአርበኞች ብዛት 3 ሺህ 500 ይደርስ እንደነበረ ተገምቷል፡፡
ጃገማ ኬሎ ከድል በኋላ
በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት፤ የፋሽስት ወራሪ ጦር በጅማ ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ይኖር ስለነበር ንጉሠ ነገሥቱ ከስደት እንደተመለሱ
የጠላትን ምሽግ ሰብረው ጣሊያንን ከቦታው እንዲያባርሩ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ከንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ተሰቷቸው ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ፤
አስፈላጊው አጋዥ ጦርም ከተዋቂ አርበኛ ጋር እንደሚላክላቸው ተነገራቸው፡፡ ደጃዝማች ገረሱም፤ የጅማው ምሽግ እንዲሰበር የሚሹ
ከሆነ ሌላ ሳይሆን ጃገማን ይዘዙልኝ በማለት ለንጉሠ ነገሥቱ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ ንጉሠ ነገሥቱም ሌሎች በርካታ እውቅ አርበኞች እያሉ
በደጃዝማቹ ጥያቄ ግራ ተጋቡ፡፡ የሆኖ ሆኖ የጠላት ምሽግ በአስቸኳይ እንዲሰበር ንጉሠ ነገሥቱ ስለፈለጉ ወደ ጅማ ከደጃዝማቹ ጋር
እንዲዘምቱ የትእዛዝ ደብዳቤ ለጃገማ ኬሎ ላኩ፡፡ ጃገማ ኬሎም ደብዳቤው ሲደርሳቸው፤ “…ወይድ ወደዛ! ጣለው ወረቀቱን! የት
ያውቁኝና ነው የሚያዙኝ! እኔ ወታደር አይደለሁ፡፡ ቢፈልጉ መሣሪያቸውን ይውሰዱ እንጅ አልሄድም፡፡” በማለት መልስ ሰጡ፡፡ በኋላም
ተዋቂዋ የውስጥ አርበኛዋ ሸዋአረገድ ገድሌ፤ ጃገማ፤ መልከ መልካምና ጀግና ሰው መሆኑን፣ ንጉሠ ነገሥቱን ባለማየት እንጅ እምቢተኛ
ሰው አለመሆኑን፤ እርሳቸው በአካል ጃገማ ኬሎ ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደው እንዲያይዋቸው በማስረዳት ለንጉሠ ነገሥቱ ሀሳባ አቀረቡ፡፡
በዚህም መሰረት ንጉሠ ነገሥቱም ሀሳቡን ተቀብለው፤ “…ለልጅ ጃገማ ኬሎ፤ ጦርህን መጥተን እናያለንና ጠብቀን፡፡” የሚል መልእክት
የያዘ ደብዳቤ ለጃገማ ኪሎ ተላከላቸው፡፡ ጃገማም ጊንጭ ላይ 3 ሺህ 500 ባለጎፈሬ፤ ባለሹሩባና ባለጋሜ አርበኛ ወታደሮቻቸውን
አሰልፈው ንጉሠ ነገሥቱን ጠበቋቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እንደደረሱ በልማዱ መሠረት ጃገማ እንዲፎክሩ በታዘዙት መሠረት፤

““……ጃጌ ጃገማቸው፣ ”እንደገጠመ የሚፈጃቸው፤

፤ ገዳይ በልጅነቱ፣፣ ዶቃው ሳይወጣ ካንገቱ፤፤””

በማለት መጠነኛ ፉከራ ካሰሙ በኋላ፤ “…ጃንሆይ! እኔ ሥራ እንጅ ፉከራ አላውቅም፡፡” ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ ሲመልሱላቸው፤ ንጉሠ
ነገሥቱም፤ ““ምን ቀረህና!” ” ብለው መልስ ሰተዋቸዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የልጅ ጃገማ ኬሎን ጦር ከአልጋ ወራሽ አስፋወሰን ጋር
መጥተው ከጎበኙ በኋላ፤ የአልጋ ወራሹ መኪና ከሾፌሩ ጋር ተዘጋጅቶላቸው ወደ አዲስ አበባ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተጓዙ፡፡ አዲስ አበባ
እንደደረሱም ልጅ ጃገማ ኬሎ ፎቶ እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ፤ 15 ሺህ ብር፤ የወርቅ ሰዓትና የገበርዲን ኮትና ሱሪ ለልጅ
ጃገማ ኬሎ በሽልማት ሰተዋቸዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ከስደት እንደተመለሱ ፋሽስት ኢጣሊያ ሙሉ በሙሉ ከአገሪቱ ለቆ ስላልወጣ
በተለይ በጅማ ጠንካራ ምሽግ አደራጅቶ ይኖር ነበር፡፡ በመሆኑም በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ አዛዥነት በጅማ የመሸገውን የጠላት ጦር
እንዲደመስሱ በታዘዙት መሠረት፤ ደጃዝማች ገረሱ እዚያው ጊቤ እንዳሉ ልጅ ጃገማ ኬሎ በጅባትና ሜጫ በኩል አድርገው የጠላትን
ምሽግ በሽዎች በሚቆጠሩት ወታደሮቻቸው ከበው ፋታ የማይሰጥ ውጊያ በጠላት ላይ ከፍተው ምሽጉን ሰብረው አኩሪ ድል
ተጎናጽፈዋል፡፡ ልጅ ጃገማ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ፤ የጅማን የጠላት ምሽግ በሰበሩበት ወቅት 500 የሚያህሉ የኢጣሊያ ወታደሮችን
ማርከው ለእንግሊዝ ወታደሮች ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡ ድሉን ከተቀዳጁም በኋላ ሁለት የፋሽስት ጀነራሎችን በሚያሰገርም የውጊያ
ስልት ማርከው ጅማን መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ከዚህ በኋላም አርበኞች የያዛችሁትን አገር እያስተዳደራችሁ ቆዩ ተብሎ ከንጉሠ ነገሥቱ
በተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ጃገማ ኬሎም፤ አጋሮን፣ ጌራንና በደሌን እንዲያሰተዳድሩ ሹመት ተሰጣቸው፡፡

ጃጋማ በግርማዊነታቸው ትእዛዝ በሱም ፍላጎት 1933 አመተ ምህረት በሻለቃ ማእረግ በሆለታ ገነት ጦር ትምሕርት ቤት ገብቶ
የአዛዥንት ኮርስ በመውሰድ የምድር ጦር ስራዊትን በማቆቆምና በሃላፊነት በተለያይ እግረኛ ብርጌድ ውሰጥ ከሰሩ በኃላ በውጭ ሃገር
የከፍተኛ አዛዥነት ኮርስ ከወሰዱና የስራ ልምድ ካካበቱ በሆላ፤በብርጋዴር ጀነራል ማእረግ የብሔራዊ ጦር አዛዥ፤ቀጠሎም በሜጀር
ጀነራል ማእረግ በአዲሰ የተቆቆመውን 4 ኛ ክፍለ ጦርን በአዛዥነት መርተዋል።በምድር ጦር ሰራዊት ውስጥ ባገልገሉባቸው የጦር
ክፍሎች በአመራራቸውና በአስተዳደራቸው በሰራዊቱ በጣም የተከበሩና የተወደዱ በስፓርት ወዳድነታቸውም ብዙ ግዜ የጦር ሐይሎችን
ስፓርት በሃላፊነት የመሩ ጀነራል መኮንን ነበሩ። ጀነራል ጃጋማ በ 1959 አመተ ምሕረት በባሌ በነዋቆ ጉቱ መሪነት የተቀሰቀሰውን
የገበሬዎች አመጽ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ግዜ የባሌ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪና የጦሩ የበላይ በመሆን ዘመቻውን በመምራት
ዋቆ ጉቱ ከነተከታዮቹ እጁን እንዲሰጥ በማድረግና ለግርማዊነታቸውም በሞትና በእስራት መቅጣት ለችግሩ መፍትሄ እንደማይሆን
በማስረዳት እንዲያውም በተወለደበትና በሸፈተበት ደሎ መና አውራጃ አስተዳዳሪ እንዲሆን በማማከር የባሌ ክፍለ ሐገር ሙሉ ለሙሉ
ሰላማዊ እንድሆን ከማድረጋቸው በላይ በገናሌ ወንዝ ላይ ያሰሩት ድልድይ፤የዲንሾ ፓርክን በማጠርና በመከለል የመሰረቱ የሐገር
ባለውለታ መኮንን ናቸው።
ሌፍተናት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ከአብዮት በኃላ በጡረታ ተገልለው ከሠራዊቱ ቢሰናበቱም፤ መንግስት እስካፈረሰውና እስከ ሸጠው
ድረስ ከደሞዛቸው 2 % እየተቀነሰ ካቋቋሙት መኮንኖች ክበብ አንድም ቀን ሳይለዩ በሚወዳቸውና በሚያከብሮቸው መኮንኖች (ጃክ)
እንድተባሉ በፍቅርና በመወደድ የተከበሩና የታፈሩ፤ታላቅ የሰራዊቱ ድንቅና ብርቅ መመኪያ ጀነራል መኮንን ነበሩ!!!
ሌፍትናንት ጀነራል ጃገማ ኬሎ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆችን፣ 5 የልጅ ልጆችን እና 4 የልጅ ልጅ፤ ልጆችን
አፍርተዋል።የልጆቻቸውም ስም በእድሜ ቅደም ተከተል፤

1. ሰለሞን ጃገማ
2. ፀዳሉ ጃገማ
3. የትምወርቅ ጃገማ
4. ሸዋዬ ጃገማ
5. ብሩክታይት ጃገማ
6. ምህረት ጃገማ
እውቁና ጀግናው አርበኛ ሌፍትናንት ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የቀብር ሥነ
ሥርዓታቸው ሲከናወን ሲረዱ ቆይተው ዐርብ ዕለት መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በተወለዱ በ 96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት
ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው እሑድ፣ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ
ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ለጀነራል ጃገማ ኬሎ መታሰቢያ የሚሆን በአዲስ አበባ ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አንድ የሕዝብ ጤና ጣቢያ
በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡

You might also like