You are on page 1of 6

ጋሽ ማሞን ሳውቃቸው

ከአበራ ሣህሌ

እንደመግቢያ

ማሞ ውድነህ በሞት የተለዩን የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ነው። ታዲያ ይህ ፅሑፍ አሁን
ሲቀርብ “ምነው ከረፈደ?” የሚል ጥያቄ ያስከትል ይሆናል። በርግጥ ፅሑፉ ወረቀት ላይ
ከሰፈረ ቆይቷል። ለሁለት ሳምንታዊ ጋዜጦችም ልኬው ነበር። አንዱ እገኝበታለሁ ያለው
አድራሻ ልክ ባለመሆኑ መልዕክቱ ለላኪው ተመልሷል። ሌላኛው ደግሞ አላወጣውም።
በጋዜጦቹ ማሳበቤ እንዳለ ሆኖ ስንፍናም ድርሻ ነበረው። ይሁንና አሁንም ቢሆን ፅሑፉ
ስለአንድ ትልቅ የሃያኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊ የብዕር ሰው ግንዛቤ ያስጨብጣል
በሚል እምነት ለተለያዩ ድረ ገፆች ልኬዋለሁ።

እነሆ ታሪክ

በልጅነቴ ጊዜያት ከእኛ ጋር ትኖር የነበረችው ከገጠር የመጣች ዘመዳችን በድብቅ ከአንድ
መጽሐፍ ላይ ገፆችን እየገነጠለች ለእሳት ማቀጣጠያነት ታውላቸው ነበር። መፅሐፉ
በየጊዜው እየተገነጣጠለ ገፆቹ ሳስተው ሽፋኑ ብቻ ቀርቷል። ይህንን ነገር አባቴ ቢያውቅ
ቤቱ በአንድ እግሩ እንደሚቆም ግልጽ ነው። በእስራኤሎች ተዓምረኛነት የሚያምነውና
ከአይሁዶች ጋር የተያያዘ ርዕስ ጉዳዬ የሚለው አቶ ሣህሌ ያንን ሥራ እንደጸሎት
መጽሐፍቱ ነበር የሚያየው። ያንብበው አያንብበው በእርግጠኛነት መናገር አልችልም።

ልጅት ትገነጣጥለው የነበረው መጽሐፍ “የስድስቱ ቀን ጦርነት” ይባላል። ተርጓሚው -


ማሞ ውድነህ።

ሰባት አመት ያህል በፈጣኑ ወደፊት እናጠንጠጥን።

የተለያዩ መፃሕፍትን ከመርካቶ እየገዛን እናዞራለን። ከአማርኛ መፃህፍት የጀርባ ሽፋን


ጫፍ ላይ ያሉትን ዋጋዎች ፍቀን የራሳችንን ተመን እናወጣለን።በዚህ ሁኔታ ዋጋ
ከምንተምንላቸው ውስጥ በቅርብ የተለዩን የሰማንያ አንድ አመቱ አንጋፋ የብዕር ሰው
የአእምሮ ውጤቶች አሉ። በወቅቱ አዳዲስ የወጡ የማሞ ውድነህን የትርጉም ሥራዎች
የምንገዛው ከመጽሐፍ ተራ ሳይሆን የሀገር ባህል ልብሶች ከሚሸጡበት መርካቶ አዳራሽ

1
ከሚገኘው አበጀ የመጻሕፍት አከፋፋይ መደብር ነበር። ያ አከፋፋይ መፃሕፍቶቹን
ያሳትም ወይ ከሳቸው ጋር ውል ይግባ የሚያሳስበኝ ጉዳይ አልነበረም።

በገበያ ዘንድ ተወዳጅነት ከነበራቸው መካከል “የካይሮው ጆሮ ጠቢ” ፣ “ጊለን የክፍለ ዘመኑ
ሰላይ” ፣ እንዲሁም “የበረሃው ተኩላ” ዋነኞቹ ናቸው። የነዚህ መፃሕፍት የሽፋን ስዕልና
ወረቀት፣ መጠናቸው እንዲሁም ገፆቻቸው ተመሳሳይ ነበር። ከነዛ ቀደም ብለው የወጡት
“ዘጠና ደቂቃ በኢንቴቤ” እና “የኦዴሳ ማህደር”ም እንደዛው። “ኦዴሳ”- ያኔ ባጭሩ
እንደምንጠራው - ፈላጊው ብዙ ነበር። በቀላሉም የሚገኝ አልነበረም። ሽፋኑ ላይ የግብጹ
ናስር፣ የዩኤሱ ኬኔዲ፣ የእስራኤሉ ዴቪድ ቤንጎሪዮን፣ እንዲሁም አንድ እስካሁን
የማላውቀው ሰው አንገቶች ነበሩ።

አከፋፋዩ ዘንድ ከሚገኙት ሶስት መጻሕፍት በተጨማሪ “ከዳተኞች”ም አለ። ስለመፅሀፉ


ይዘት ዛሬም ድረስ የማውቀው ነገር የለም። የሚገርመኝ ግን የከዳተኞች ሽፋን ፣ ዲዛይንና
ወረቀቱ ከላይ ከጠቀስኳቸው ከአምስቱም ይለይ ነበር። የላይኞቹ የሽፋን ወረቀት
አብለጭላጭ (Glossy) ሲሆን ከዳተኞች ግን ወፈር ያለ ሽሮ ገጽ የምንለው አይነት ነበር።
ማናችንም ሽፋኑ ስለማይመቸን ብቻ አንይዘውም። “መጽሐፍን በሽፋኑ አትመዝነው”
የሚለው ለእኛ አይሰራም ነበር። (በቅርቡ ባነበብኩት “Steve Jobs” በተሰኘ መጽሀፍ
የተነሳ ይህች እምነታችን ልክ ነበረች እንዴ ብዬ ሳልጠይቅ አልቀረሁም። የማክ
ኮምፒውተሮች አምራች ኩባንያ አፕል ኢንክ መስራች ስቲቭ ጆብስ በሞት ከተለየ ከቀናት
በኋላ በወጣው የህይወት ታሪኩ ላይ እንደተጠቀሰው ለምርቶቹ አስተሻሸግና አቀራረብ
የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ነው። ይህም “ሰዎች መጽሐፍን በሽፋኑ ይመዝኑታል”
ከሚል ጥልቅ እምነቱ የመነጨ እንደሆነ በቃል ተጠቅሷል። “People do judge a book
by its cover.”

ታድያ መፃሕፍቱ በእጃችን በነበሩበት ወቅት የተወሰኑ ሥራዎቻቸውን አንብቤአለሁ ።


መጀመሪያ ያነበብኩት ምጽአተ እስራኤልን ነው። “ምጽአት” በ1965 ዓ.ም.(ሁሉም ዘመን
አቆጣጠር በሃበሻ ነው) የታተመ ሲሆን በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም (እርግጥ ከብዙ
ዓመታት በኋላ በድጋሚ ታትሟል። ግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ 500 ቅጂ በ8 ብር ሂሳብ
መግዛታቸውን እዚህ ጋ ብንጠቅስ ለታሪክ ባለውለታ እንሆናለን::) ይሁንና ከአማርኛው
ይልቅ በሊዮን ዩሪስ የተጻፈው እንግሊዝኛው ኤክሶደስን (Exodus) ማግኘት ይቀል ነበር።
ዩሪስ ከነሮበርት ሉድለም፣ ሲድኔ ሼልደን፣ ፍሬድሪክ ፎርሳይዝ ፣ ሀሮልድ ሮቢንስና

2
ኧርቪንግ ዋለስ ጋር በእንግሊዝኛ መፃሕፍት አንባቢያን ዘንድ ተፈላጊነት ከነበራቸው
ደራሲያን አንዱ ነበር (በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ አብዛኞቹ በእነ ኤፍሬም እንዳለ ፣
ፋንታሁን ዮሴፍ ፣ አውግቸው ተረፈ ፣ ታደሰ መለሰና በሌሎችም በአማርኛ
ተተርጉመዋል።) ቀጥሎ የሳበኝ “የእኛ ሰው በደማስቆ” ሲሆን ትንሽ መጽሐፍ ከመሆኑ
በተጨማሪ “የዘመኑ ምርጫ”ም ነበር። መጽሐፉን ማግኘት አይደለም ለአንባቢ ለእኛም
አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሳለሁ። ለእኔ ሶስተኛ መጽሐፍ “አሉላ አባ ነጋ” ነበር። ጥቅጥቅ
ብለው የተጻፉ መፃሕፍትን ለማንበብ ካለኝ ስልቹነት አንፃር ያንን አንብቤ መጨረሴ
ይገርመኛል። ስለጽሁፉ ጥቅጥቅነት ከወሬ ባላለፈ እንደሰማሁት የገፆቹን ብዛት በዛውም
የሕትመት ወጪውን ለመቀነስ ታስቦ በዛ መልኩ እንደወጣ ነው። በንጉሱ ዘመን አሉላ አባ
ነጋ በቴአትር ተሰርቶ ቀርቧል።

በኋላ በእንግሊዝኛ የተጻፉ ልብወለዶችን ለማንበብ ድፍረት ሳገኝ በአንድ ወቅት


ካነበብኳቸው ሁለት መጽሐፍት አንዱ Battle Cry ነበር። መጽሐፉን የመረጥኩበት
ምክንያት በማሞ ትርጉም አማካኝነት ደራሲውን ሊዮን ዩሪስን በማወቄ ብቻ ነው።

ማሞ ባስተዋወቁን ጉዳዮች ላይ አንድ ነገር ላክል። በ1968 ዓ.ም. ከእስራኤል ተነስቶ


ወደፈረንሳይ ያቀና የነበረው የኤር ፍራንስ አውሮፕላን በግሪክ የአየር ክልል ሳለ
በፍልስጥኤም ነፃ አውጭ ድርጅት አንጃ ተጠልፎ የዩጋንዳ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው
ኢንቴቤ አውሮፕላን ጣቢያ እንዲያርፍ ይገደዳል። ጠላፊዎቹ አብዛኛዎቹን መንገደኞች
ለቅቀው ወደ መቶ የሚጠጉትን አይሁዳዊያንን ለይተው ያግታሉ። የእስራኤል ልዩ
ሀይሎች እጅግ በሚያስደንቅ ጀግንነት 90 ደቂቃ ብቻ በፈጀ ግዳጅ ጠላፊዎቹንና ወደ
ሃምሳ የሚጠጉ የዩጋንዳ ወታደሮችን ገድለው ዜጎቻቸውን ነጻ ያወጡበት ታሪክ “ዘጠና
ደቂቃ በኢንቴቤ” በሚል ተተርጉሟል። እስከማስታውሰው ድረስ ስለዩጋንዳና በወቅቱ
ስለነበረው መሪ ኢዲ አሚን ዳዳ የሰማሁት በዚህ ትርጉም አማካይነት ይመስለኛል።
ፎሬስት ዊታከር ኢዲ አሚንን ሆኖ በሚጫወትበት በ1998 ዓ.ም. በወጣው Last King of
Scotland ላይ የጠለፋው ሁኔታ በመጠኑ ተዳስሷል።

አሁንም እንደቅድሙ አስር ዓመት ያህል ወደፊት እናጠነጥናለን።

ይኸኔ ደግሞ ሚናዬ ተቀይሯል። ዜና ለቀማ በየቦታው በምሰማራበት ጊዜ በተደጋጋሚ


ማሞን ለማግኘት ችያለሁ። በ1994 ዓ.ም. ገደማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አውደሰብ የተሰኘ

3
ፕሮግራም በተጀመረበት ወቅት ከአዘጋጆች አንዱ ነበርኩ። እያንዳንዳችን የቡድኑ አባላት
በዝግጅቱ ለመስራት የምናስባቸውን ሰዎች ከአሳማኝ ምክንያት ጋር በጽሑፍ ማቅረብ
ነበረብን። እኔ ማሞ ውድነህን ለመስራት ያቀረብኩት ዕቅድ ተቀባይነት በማግኘቱ
እሳቸውን በቅርበት ለማወቅ መንገድ ከፍቶልኛል።

የእሳቸውን ታሪክ ለመስራት ከካሜራ ፊትና ኋላ ብዙ አውርተናል። ቤታቸውን


አስጎብኝተውኛል። ከቤተሰቦቻቸውም ጋር ለመተዋወቅ ዕድል ገጥሞኛል። የካ ክፍለ ከተማ
ቤልጂየም ኤምባሲ አካባቢ ያለው ግቢያቸው አረንጓዴነቱ ከሁሉም ቀድሞ ይታወሰኛል።
ቤታቸው ውስጥ ያለው የመጽሐፍ ብዛት ማለቂያ የለውም ። የጽሕፈት ጠረጴዛቸው፣
የመብራቱ አቀማመጥ ፣ እንዲሁም ፀጥታው ይገርመኛል።

በዚህ ሁሉ መካከል ግን ከማሞ ውድነህና ቤተሰቦቻቸው እስካሁን የማልረሳው እንግዳ


ተቀባይነታቸው ነው። የባለቤታቸው የወ/ሮ አልማዝ ገብሩ ሳቅ ከልብ ነው። ከት ብለው
ይስቃሉ። ሳቅ ደግሞ ይጋባል። ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ያልተዘመረላቸው ጀግኖች
ናቸው። ወ/ሮ አልማዝ አቶ ማሞ ሳይረበሹ የሚሰሩበትን ሁኔታ አመቻችተዋል።ልጆቻቸው
በትየባና በእርማት (ያውም ኮምፒውተር ባልነበረበት ጊዜ) ይህ ነው የማይባል ውለታ
አበርክተዋል። አንዳንዶቹ ከአባታቸው ስራ ጋር የተዋወቁት በዚሁ ሂደት ነው። ነገር ግን
ስላበረከቱት ድርሻ ካልተጎተጎቱ በስተቀር ከማናቸውም የሚሰማ ነገር የለም። በሰፊው
ሲታይ አባታቸውን ሳይሆን መላውን ህብረተሰብ ነው ያገለገሉት።

ማሞና ባለቤታቸው በትዳር ህይወት የቆዩት ከአንድ ኢትዮጵያዊ አማካይ የሕይወት ዘመን
አይተናነስም። ለአምሳ ሁለት ዓመት አብረው በመኖራቸው በርካታ የልጅ ልጆችን
ለማየት ታድለዋል። ባለትዳሮቹ ግን ከባልና ሚስትነት ይልቅ ጓደኝነት አልፎ አልፎም
የወንድምና እህት ፉክክር ይታይባቸዋል። በወቅቱ ያደረግነው ቃለ ምልልስ ሕልፈታቸውን
አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሳምንታት በፊት ባስተላለፈው ዝግጅት ላይ
በቅንጭብ ቀርቧል።

አንጋፋው የብዕር ሰው ከ60 በላይ መጻሕፍትን ጽፈዋል። አሁን ባለው መረጃ መሰረት 54
መጻሕፍትን አ-ሳ-ት-መ-ዋ-ል። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ክብረወሰን ነው። ሁለተኛ የሚወጣ
ካለ የዚህን ግማሽ ማሳተሙን እጠራጠራለሁ። ማሳተም ቀላል ቋንቋ ነው። ነገር ግን

4
መጽሐፍ ቀርቶ መጽሔት እና ጋዜጣ ለማሳተም ያለው ውጣ ውረድ ስስ ቆዳ ላላቸው
የሚታዘዝ አይደለም።

ማሞ እንደሌላው ታዋቂ ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ሁሉ በመደበኛ ትምህርት እጅግም


ገፍተው አልሄዱም። ያንን ለማካካስ ብዙ አንብበዋል። የንባባቸው አድማስ በስራዎቻቸው
ፈርጀብዙነት በግልፅ የሚታይ ነው። ከጦርነት ታሪኮች ብንጀምር በ1954 ዓ.ም. የወጣው
“ሁለተኛው የዓለም ጦርነት” የበኩር ስራቸው ነው። ጦርነቱ በአብዛኛው አውሮፓ ውስጥ
ይካሄድ እንጂ ከ1928ቱ የጣሊያኖች ወረራ ጋር ውጊያው የተሟሸው በኢትዮጵያ ነው።
ማሞ የተወለዱባት በአማራው ክልል ዋግ ኸምራ ዞን የምትገኘው ደሀና ወረዳ በቦምብ
ተደብድባለች። ወላጆቻቸውንም በዚህ ሁኔታ አጥተዋል። ስለዚህ ለጦርነቱ ብዙም ሩቅ
አልነበሩም። ሌሎች በዚህ ዘርፍ ከሚካተቱ ሥራዎቻቸው መካከል - የ17ቱ ቀን ጦርነት ፣
የደቡብ ሱዳን ብጥብጥ፣ የበረሃው ማዕበል ይገኙባቸዋል። የሰዎች ታሪክ (Biography) –
ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ፊልድ ማርሻል ሞንትጎመሪ፣ ሮሜል የበረሃው ተኩላ፣ ዮሃንስ። ሳይንሳዊ
ክስተቶች - ዩፎስ በራሪ ዲስኮች፣ የዘመኑ ትንቢታዊ ድምጽ፣ መጪው ጊዜ እና ሌሎች
ዓለማት። ልብ ወለድ - ዲግሪ ያሳበደውና ካርቱም ሄዶ ቀረ፣ ብዕር እንደዋዛ፣ ዕቁብተኞቹ፣
ዕድርተኞቹ። ምናልባትም ስማቸው ከስለላ ታሪኮች ጋር ተዛማጅነት እስኪኖረው ድረስ
በርካታ ስራዎችን ያበረከቱት በስለላው ዘርፍ ነው። የሁለት ዓለም ሰላይ፣ ሰላዩ ሬሳ፣
አደገኛው ሰላይ፣ ስለላና ሰላዮች፣ ኬጂቢ ውስብስቡ የስለላ መዋቅር እና የመሳሰሉት
ጥቂቶቹ ናቸው።

ማሞ ይህን ያህል መፃህፍት ከማበርከታቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን


ለ12 ዓመታት በሊቀመንበርነት አገልግለዋል። ያም ሆኖ ግን ከደራሲነት ይልቅ ራሳቸውን
የሚቆጥሩት እንደጋዜጠኛ ነበር።በአዲስ ዘመንና በሰንደቅ ዓላማችን ከመስራታቸው በላይ
ፖሊስና ርምጃው የተባለው የፖሊስ ሰራዊት ጋዜጣ በ1952 ዓ.ም. ሲቋቋም የመጀመሪያው
አዘጋጅ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል። ከሙያው ጋር ያላቸው ቁርኝት የተጀመረው
ጋዜጦች በአህያ ተጭነው ይከፋፈሉ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ እንደነበር በኩራት
ይናገራሉ።

ግን ማሞ የብዕርና ወረቀት ሰው ብቻ አልነበሩም። ተናጋሪም(Public Speaker) ናቸው::


በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ እውቀት አላቸው:: ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀሳባቸውን
ለማካፈል ሁሌም ዝግጁ ናቸው። ብዙ ጊዜ ከአንድ የስልክ ጥሪ በላይ አይፈጁም።

5
ከማሞ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው በጀርመን ኤምባሲ በተደረገ የምሳ ግብዣ ላይ
ነው። ወ/ሮ አልማዝ የሃገር ልብሳቸውንና ሳቃቸውን ይዘው መጥተዋል። ጋሽ ማሞም
ከእንግዶች ጋር መጫወታቸውን ይዘዋል። ለእኔም የአቅሜን ያህል የአየር ሰዓት
አልነፈጉኝም። በማሞ ውድነህ ስራዎች ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት የመመረቂያ
ሥራ(thesis) የሰሩ እንዳሉ አውቃለሁ። ለሙያዊ ትንታኔ እነሱን ደጅ መጥናት
ያስፈልጋል። እኔ ግን ይህን ያህል አውቃቸዋለው።

ሀዘኑ እጅግ መራር ለሚሆንባቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ ገብሩ እንዲሁም በሃገር
ውስጥና በውጭ ሃገር ለሚኖሩ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ።
እግዜር ይስጥልኝ ጋሽ ማሞ!

 ፅሑፉን ታይፕ ያደረገልኝን ወዳጄ ሀብታሙ ሙላቱን አመሰግናለሁ።

You might also like