You are on page 1of 36

የምናብ መንገድ

ቤተልሄም ተፈራ

2016 EC
የምናብ መንገድ

የሚጮህ ዝምታ ...........................................................................1

የዝምታ ውበት…. .....................................................................3

እገስፅሃለው ..................................................................................4

ያልፋል እንደተራ? ....................................................................5

አደራዎቼ .....................................................................................6

ብርታትም ድካምም ነው ልበል? ................................................7

ልክ ግን ምንድን ነው....................................................................9

ስህተት ወይ ትክክል.... .......................................................... 10

ወዴት እንሰደድ ......................................................................... 11

አንዲት ሀገር አለን…. ............................................................ 12

እልፍ በእንቅልፍ ....................................................................... 14

የማይነጋ ለሊት...................................................................... 15

እ ኔ ነኝ.................................................................................... 16

ስህተት እና ፍፁምነት ............................................................ 17

ዝምታን ተጠማው ..................................................................... 18

ከአንደበት የወጣ ቃል ............................................................. 19

ሀሳብ ነኝ .................................................................................. 20

መርጦ ማሰብ ........................................................................ 21

ሰውነት ..................................................................................... 23

በደም ተገዝተሀል ................................................................... 24

በእጆችህ ሸፍነች ........................................................................ 26


ሀይላችን ነህ .......................................................................... 27

የፍቅር መልክ ........................................................................... 28

ፍቅር ምን ይመስላል? ............................................................... 29

ሰላም ሲበልጥ ........................................................................... 30

ፍርሀተ ፍቅር ........................................................................... 31

ፍርሀት አርግዞ ፍርሀት የወለደው ፍቅር ................................. 32


መታሰቢያነቱን ፡- በቅን ልቦና ህይወትን ለመረዳት ለሚቃትቱ
የሰው ልጆች ሁሉ ይሁንልኝ፡፡
ቃላት ሳትናገር አፍህን ለጉመህ
ዝም ጸጥ እንደ ሬሳ ደርቀህ
ትንፋሽ ሳታወጣ ስጋህን አፍነህ
ቦታ ሳይገድብህ ጊዜን አሸንፈህ
ዝንታለም ሚሰማ ዜማ ትቀኛለህ
ምድርን የሚያርስ እቅድ ትነድፋለህ
እግርህ ሳይራመድ ኮቴህ ሳይሰማ
ምሽቱ ሳይነጋ እንዳለ ጨለማ
መነጠቅ መራቅን ነፍስ ስትጠማ
ትርጉሙ ሲጠፋ የሰፍሩ አላማ
እልም ትላለህ ካረጀው ከተማ
ስጋህን ልታድን ነፍስህም ታክማ
እንዲህ በዝምት እንዲህ በፀጥታ
ከሚታየው አለም ርቀህ ላንድ አፍታ
መንፈስህ ታድሶ ህይወትህ አብርታ
ምልስ ትላለ በፍሰሃ በደስታ
የደከመች ስጋም አዲስ ተስፋ አግኝታ
እንጭጯ ነፍስህም አብባ ጎምርታ
እስቲ ለአንድ አፍታ ...

ዝም ፀጥ ረጭ ወደ ውስጥ መኮብለል
ራስን ማበርታት ራስን ማባለል
ከልብ መመካከር ደግሞም ማሰላሰል
ከመንፍስ ትባብሮ ነፍስን ማደላደል

1
የውጪውን ሙግት ባልብት ሲትውት
የህይውትን ጥሪ ያኔ ነው ሚሰሙት
ከራስ ጋር ሲስማሙ የእወነት ይጀገናል
ይቻላል ይቻላል መልሳችን ይሆናል

2
የዝምታ ውበት….

ቃል ውስን ነው ቃል አቅሙ ትንሽ ነው ቃል የመንፈስን ከፍታ


እና ዝቅታ ቁልጭ አድርጎ ሊያሳይ አይችልም፡፡ ቃል ልብን
የሚርደውን ስጋት እምነት የሚሸረሽረውን ጭንቀት መግለፅ
ይከብደዋል፡፡ ቃል ፍፁም የሆነን ሀሴት ስጋን ያደከመን ሀዘን
አይናገርም፡፡

ቃል ህይወት እስከ መስጠት ድረስ ዋጋ የሚያስከፍለውን ፍቀር


ነፍስን እስከመንጠቅ ድረስ የሚያስጨንቀውን ጥላቻ እንዴት
አድርጎ ይገልጣል? ቃል እጅግ የገዘፈ ፍራቻን ከልክ ያለፈ
ድፍረትን ለመተንፈስ ሀይል ያንሰዋል፡፡

በዝምታ ጥበብ ግን ህይወት ትገለጣለች፡፡ ዝምታ የነፍስን እውነት


ለአለም ያሰተጋባል፡፡ መንፈስ ከመንፈስ ጋር እጅግ የረቀቀ
እውቀትን አይ ያላየውን ይነጋገራል ይወያያል ይግባባል፡፡
ብዝምታ ከሞት የጨከነ ጥላቻ ህይወትን የሚስጥ ፍቅር
ይገልጣል፡፡

ዝምታ እውቀት ነው ውብት ነው ሀይል ነው ብልሀት ነው፡፡


ከተፈጥሮ ጋር የምንግባባበት ብቸኛው ቋንቋችን ነው፡፡ ዝምታ
ተፈጥሮን የምንሰማበት መንገዳችን ነው

አንድ አለም አንድነት ለአንደ አላማ በአንድነት በፍቅር በሰላም


በመተባበር መትመም፡፡

3
ራሴን ይበላኛል ግን እኔ አላከውም

ሀይል ተጠቅሜ አላሸንፈውም

ከህሊናዬ ቤት ከአእምሮዬ ጓዳ

ሀሳብ ሲመላለስ ማይቆጠር እዳ

ዝም ጭጭ ብዬ ብርሀን ናፍቃለው

የጭንቀቱ ዥረት እንደሚያልፍ አውቃለው

ጊዜ ፍጠን ብረር አምልጠኝ አልያዝህ

ብቆዝም ብባዝን ላንተም ምን ሊበጅህ

እኔም በምኞቴ በተስፋ ሰክሬ

ዛሬን ልሰወራት ነገን ብቻ አፍቅሬ

ቀናቶች ይለፉ ወራትም ይንጎዱ

የሰመመን ህይወት ሩቅ ነው መንገዱ

ብቻ ዝም ጭጭ አላይም አልሰማ

በጨለማ ልክነፍ ብርሀንን ስጠማ

4
ያልፋል እንደተራ?

ከርዝመቱ የተነሳ ከጭንቀቴ የተነሳ ሰአት የቆመ ጨልሞ የቀረ


የመሰለች ለሊት ሲነጋ አይቻለው፡፡ ለዛም እኔ በህይወት ያለው
ለራሴ ምስክር ነኝ፡፡ ዛሬ በደስታ ብሰክር ዛሬ በስጋት ብወጠር ዛሬ
በህመም ብታሰር ዛሬ ሁሉ ቢሳካ ቢደምቅ አውቃልው እኔ ከዛ
በላይ ነኝ ከምችለው ከሆንኩት በላይ ነኝ፡፡

ያልፋል እንደተራ? ብዬ ራሴን ጠይቃልው አይመስልም ግን


ያልፋል ይሄዳል ይተናል በዚህ ውስጥ ግን እኔ ከትናንት
እጎመራለው አብባለው አምራለው አሸንፋለው ወደ ፍፁምነት
በጥቂት በጥቂቱ እጠጋለው፡፡ የህይወት ውበቷ እንዲሁ እየፈተነች
እያስተማረች እኛን ወደ ተሻለ ማንነት እየመራች ማለፉዋ ነው
ስጋችን ስታልፍ መንፈሳችን መልካም ስራች ትውልደ
የሚማርበት አሻራ ነው፡፡ ስራችን መንፈሳችን መልካምነታችን ስጋ
ቀይሮ አድጎ በዚሁ አለም ይኖራል፡፡ አላቂው ደካማው ስጋ ብቻ
አፈር ሆኖ ይቀራል መልካም ማንነትህ ሀሳብህ በዚች አለም
ደጋግሞ ይመላለሳል፡፡

አዎ እርግጠኛ ነኝ አስጨናቂ ጊዜ ሁሉ ያልፋል እንደተራ ደስታም


ያልፋል ግን በዛ ውስጥ ማንነታችን ይሰራል ይጠነክራ ያበራል
ያብባል፡፡

5
እኔን ደካማዋን በብዙ ብታምነኝ

የልጆቼ እናት እንድሆን መረጥከኝ

ባደራ ሰጠኸኝ እንዳሳድጋቸው

ከዚች አለም ጋራ ላስተዋውቃቸው

እጅግ ወደድኳቸው ከራሴ አብልጬ

ሰውም ላደርጋቸው ታምኜ ቆርጬ

እንዲህም ሆነና

ሰው ነኝና

አይኔን ባይናቸው አይቼ መርምሬ

የስጋን ድካሙን ፈተናን ቆጥሬ

ልቤ ራደብኝ አቅምም አነሰኝ

ከፊትህ መጣሁኝ እንድትደግፈኝ

በእያንዳንዷ ቅፅበት አንተን ፈልጋለው

ተገኝ በቤታችን ያኔ በረታለው

ጎብኘን ሁል ጊዜ በየእለት እለቱ

ጎብኘን በየሰከንደ እንድንሆን ብርቱ

ከእስትንፋስ ቀርበህ ከነፍሳችን ዘልቀህ

ጠብቀን ፈጣሪ በእጆችህ አቅፈህ

6
ብርታትም ድካምም ነው ልበል?

የአደራ ድንቅ ልዩ ስጦታዎቼ ውድ ልጆቼ ተስፋ በሚያስቆርጥ


ነገር ላይ ሁሉ እንደዳልቆርጥ ብርታቶቼ የትእግስቴ ምንጭ
የህይወቴ ትርጉም ናቸው፡፡ በረዥሙ መንገድ መልካምን እየናፈኩ
የምጓዘው ከፊቴ ሁል ጊዜ የሚታዩኝ እነሱ ስለሆኑ ነው፡፡ እንደ
አይን ብሌኔ ብቻ አይደለም ከህይወቴ አብልጬ እሳሳላቸዋለው
ህይወቴ ትርጉም ያገኘው መኖርን የወደድኩት እነሱን ካገኘውበት
እለት ጀምሮ ነው፡፡

አለምን ያስተዋልኳት በተስፋ ጠዋት ማታ የምሮጠው በእነሱ ነው


ቤቴ ሙሉ የሆነው መኖሬ ትርጉም ያገኘው በእነሱ ነው፡፡ልጆቼ
ውበቶቼ ያማርኩት ህይወት የጣፈጠችን እናንተ ስላላችውኝ ነው
እልና እልና እልና…. ገና ብዙ ይቀረኛል እናንተን እያየሁ በብዙ
ህይወትን ናፍቃለው እጓጓለው እኖራለው እመኛለው ሁሉን
አገኛለው፡፡

ራሴን ወደኋላ አይና ትክክለኛ ድክመቶቼ እነሱው ናቸው ብዬ


ደመድማለው፡፡ አልችልም ለእነሱ ስል ብቻ እሸነፋለው እነሱን
አፍቅሬ እሸነፋለው፡፡ እነሱን ከተቀበልኩባት አለት ጀምሮ ስስት
የሚሉት በሽታ ይዞኛል፡፡ እያየዋቸው እሳሳለው፡፡ ሰላም
ጤናቸውን ደስታ ስኬታቸውን አብዝቼ እመኛለው፡፡ የተመኘውት
አይበቃኝም ደግሜ ደጋግሜ እመኛለው እያየዋችው እየዳሰስኩ
እየነካዋቸው እሳሳለው፡፡

መንገዳችውን ሁሉ ለመጥረግ እመኛለው ንፁህ ሰላም በሆነው


ጎዳና እንድትነጉዱ እመኛለው፡፡ በቀናው ባማረው በለሰለሰው

7
ብርሃን በተሞላው መንገድ እንደ አደይ አበባ ፍክት ብለው
እንዲሮጡ እመኛለው፡፡

ጌታ ሆይ መንገዳቸውን ሁሉ አንተ ጥረግ ውብ የቀና


አድርገላቸው፡፡ህይወትን እስከመስጠት ያፈቀርከን ጌታ ዘመናችንን
መባረክ ሰላም ማድረግ ላንተ እንደምን ቀላል ነው፡፡

ልጆቼ ብርታትም ድክመቶቼም ስል ሊያስግርም ይችላል፡፡


በእርግጥ እንዴት ሊያስብል ይችላል ግን ድካሜም ብርታቴም
እነሱው ናቸው፡፡፡ እምነቴ ተስፋዬም ናቸው ህይወትን ዳግም
መኖር የጀመርኩት ልጅነቴን ሰውነቴን እናትነቴን እናቴን
ያወኩባቸው የዝች አለም ብርቅዬ ስጦታዎቼ በደስታ የመኖር
ሚስጥሬ ናቸው፡፡ ህይወት ውበቷ ድግግሞሽ መሆኗ ነው፡፡ በልጅ
ውስጥ ልጅነት ዳግም ይኖራል፡፡

ወላጅነት ግን ብርታትም ድካምም ነው እምነትም ስጋትም ስስትም


ልግስናም የሚታይበት ጣፋጭ የዚች አለም ድንቅ ስጦታ ነው
እንበል?

8
የሰውነት ሚዛን የሰውነት ልኩ
የሰውነት ስሪት የሰውነት መልኩ
ከመንፈስ ከስጋ ፍፁም አንድ የሆነ
የሁለቱ ውህድ የተመጣጠነ
ስህተት እርማት የየቀን ህይወቱ
ዘላለማዊ ነው ደግሞ ሀላፊ ከንቱ
ስጋው ሲጎትተው መንፈስ ሲመልሰው
ገላውን ሲያስደስት ነፍስያው ሲወቅሰው
እንዲሁ ማህል ቤት ልቡ እንደባዘነ
ለምድርም ለሰማይ ፀንቶ አልታመነ
አለምን ሲመስል ነፍሱ ስትከፋ
አካሉ ሲበድል ደስታ ሳቁ ጠፋ
የሰውነት ጥጉ ልኩ ግን መንድነው?
የስጋን ሲያደርሱ ነፍስን ማሳዘን ነው?
ያዳም ዘር ተልኮ የአለም ህይወቱ
ብፁዕ እንዲሆን አካሉን መጉዳቱ
የቱ ያስብለው ብርቱ ጉዞውም አሳካ?
የምድር ቆይታው በፍሬ ሲለካ

9
ስህተት ወይ ትክክል....

የሰው ልጅ መምረጥ መቻሉ ከእንስሳ ቢለየውም አልፎ አልፎ ግን


እንስሳዊ ማንነቱ ገኖ አሸንፎ ይወጣል፡፡ ደግሞም ይገዳደረዋል
ስህተት ነው ብሎ ህግ አውጥቶ ተጠይፎ ከሸሸው ቦታ ተገኝቶ
ለማመን የሚከብድ ክፋትን ይፈፅማል በስጋው ክንውን እና ደስታ
ውስጥ ግን ነፍሱ ትታመማለች በፀፀት ተሞልቶ ይመለሳል
በይቅርታ ይረሳል ምኞት ገደብ የለውምና ትናንት ከጠላው
ከሸሸው መንደር ዳግም ይገኛል፡፡

ሕይወት ድግግሞሸ ቅብብሎሽ ነው ስጋ በቃኝ እስኪል ከኖሩበት


መንደር ደጋግሞ መኖር፡፡ ይህ ነው እውነታው ይህ ነው ህይወት
ይህ ነው፡፡

ህይወት ራሱ በስህተት እና ፍፁምነት መሀከል ሲዋትቱ ሲቃትቱ


የመኖር ጥበብ ነው፡፡ ሰው ፍፁም አይደለም መሀል ላይ ያለ
ፍጥረት ነው በጥበብ እየላቀ በመጣ ቁጥር ፍፁምነትን የሚታከክ
ስጋው ባየለበት ጊዜም ከሰውነት ክብሩ በብዙ ዝቅ የሚል ፍጥረት
በቃህ እስኪባል የማይበቃው ሁል ጊዜ በጉዞ ላይ ያለ ፍጥረት
ምን አልባት ጉዞው ወደፊት ወይም ወደ ኋላ ሊሆን ይችላል፡፡

ስህተት ከሆነ ስህተቱ ራሱ ሰውነት ነው፡፡ ሁለቱ ጫፎች


መመላለሱ ግን የሰውነት ተፈጥሮው ነው፡፡ ከተፈጥሮ መቃረን
ደግሞ አይቻልም፡፡

10
አባቴ አያቴ ከተወለዱበት መንደር ግዛታቸው
ካደጉበት ሀገር ከሜዳው ቦርቀው ከወንዙ ተራጭተው
ሰፈሩን ቆርቁረው ካቀኑት ሀገር
እንግዳ ቢያደርጉን መጤ ባይተዋር
ሹሙም ዝም ካለ ቤታችን ሲደፈር
ወዴት እንሰደድ ከየትስ እንደር
ግፍ እንዲህ ሲዛመት ሁሉን ሲያዳርስ
በልጆች ደም እንባ መሬቷ ሲርስ
መሰደጃ ጠፍቶን ክፉን ምናልፍበት
ቀንን ስንጠብቅ በተስፋ እና እምነት
ሊነጋ ሲል ይመሽ እያልን እያልን
ስንት ምሽት አለፍን እኛም እያለፍን
ግፉን እንገፋ ተስፋችን አያልቅም
ደጃፍ እንቆማለን የትም አንሄድም
በፈረሰው ምትክ ቤትም እንሰራለን
ካልሆነም ካልሆነም ከመሬቷ ገብተን ሰላም እናርፋለን

11
አንዲት ሀገር አለን….

ሰውነቱ በግፍ የረከሰ መንፈሱ በጥፋት የቆሸሸ ያደፈ ነብሰ በላ


በከበረበት ምድር አብረን እየዋልን አብረን እናድራልን፡፡ የሰው
የህይወት ትርጉም የአለም የምድር ቆይታ ትርጉም ግራ
እስኪሆንብን ድረስ የተፈጥሮ የሰው ሰራሽ ችግር እያመሰን
ይኸው እንኖራለን፡፡ ከማመስገን ግን አንቦዝንም የመጣውን
ከመቀበል ወዴትም አንሸሽም እምነታችንን አንተውም ከጥበቃም
አንቦዝንም፡፡

አይን ከማየት አይሞላምና ማየት በራሱ ልብን የሚሰብረውን


ሳንመርጥ እናያለን፡፡ ፈጣሪ መቻልን ሰቶናል ለዚህም
እናመሰግናለን፡፡ በእርግጥ ሁሉም ያልፋል የማያልፍ ምንም
የለም ጊዜውም ይሄዳል ደግሞ በሌላ ይተካል፡፡ ትናንት
ያንገዳገደንን አሸንፈን ቆመናል ነገም እንችላለን እንላለን፡፡ በብዙ
የረዳን አምላክ የታመነ ነውና፡፡

አንዲት ሀገር አለችን አንዲት ብቻ፡፡ ሌላ አማራጭ ብሎ ነገር


የለም መርጠን ሳይሆን ተመርጠናል በእሷ አንድንኖር ለእሷ
ተመርጠናል፡፡ በከፋ በመረረ ጊዜ የምንሸሽበት ሀገር የለንም
መሸሸጊያ ማረፊያችን እሱዋው ነች፡፡ ስንገፋ ጥለን የምንሄድበት
አማራጭ የለንም በቃ የለንም፡፡

ለመምረጥ ሚመረጥ አማራጭ ያስፈልጋል እኛ ግን አንድ ነው


ያለን፡፡ እየታመምን እየወደቅን እየፈራን እየሰጋን ሁል ጊዜ
ሀገራችን ብለን እንጠራታለን ብእሷ አናፍርም ተገፋን ብለን
አንሸሽም፡፡ በጨለመው ቀን ውስጥም አሻግረን እሷ ላይ ቆመን
ብርሀን እናያለን፡፡

12
የመረጥሽን ስለፈለግንሽ ብቻ ሳይሆን ስለምናስፈልግሽም ጭምር
ነው፡፡ ያለ ምክንያት የሚሆን ምንም ነገር የለም ሁሉ የሚሆነ
አንድና ትልቁን አላማ ለማሳካት ብቻ፡፡

ተወልደን በርቀን ያደግንብሽ ምድር፡፡ ካፈርሽ የበቀለውን በልተን


ያደግንብሽ ሀገራችን፡፡ ውሀሽን ጠጥተን አየርሽን ተንፍሰን ሰው
የሆንብሽ ሀገራቸን፡፡ በዛሬ ላይ ተስፍችንን መንምኖ ነገን
እንናፍቅብሻለን፡፡

13
የማይነጋ ለሊት የማይመሽ ቀን የለም
ያለ የሚረሳባት ቅዠት ናት ይቺ አለም
እልፍ ሂድት ጥፍት መሰወር መረሳት
ከከንቱ ድካሟ ለዘላለም መጥፉት
ግራ ግብት ሲል ሁሉ ትርጉም ሲያጣ
እርፍ በእንቅልፍ ፀሀይ እስክትወጣ
በሰው ቅዠት አለም ግብቶ ከመገኘት
በሞት ታናሽ ወንድ በእንቅልፍ መረታት
እስቲ ሁሉን ልርሳ ልተወው ልሽሸው
የዛለ መንፈሴን በእንቅልፍ ላድሰውው

14
የማይነጋ ለሊት

የአንዳንድ እለት ርዝመቱ አንደ አመት ይመስላል የማያልቅ


ይመስላል፡፡ ግን ሀቁ ይሄውን ነው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ
ያልነጋ ለሌት ያለመሸ ቀን የለም፡፡ ዘመን እንዲሁ ይነጉዳል ልጅ
እንደ ወራጅ ውሃ ያለፈው እየተረሳ ተተኪው ቦታውን ይይዘል
አንድም ቀን ወንዙ ደርቆ ውሃው ከመውረድ ታክቶ አያውቅ
ሁሌም ያነው የሚሆነው፡፡

አካልንም መንፈስንም እንድናድስ እንቅልፍን የሰጠን ጌታ ድንቅ


መልካም አምላክ ነው፡፡ እንቅልፍ በየቀኑ ያድሰናል ያፈረታናል
ለአዲስ እለት ለመልካም አላማ ያዘጋጀናል፡፡ እንቅልፍ ትናንትን
ረስተን ዛሬን እንድንኖር ሀይል ይሰጠናል፡፡ አላልፍ ያለንን ሁሉ
ያስረሳናል፡፡

ሞትም እንዲሁ ደከመውን ስጋ አስወግዶ በአዲስ አካል ጥበብን


የቀሰመን ነፍስ ሊሸከም የሚችል ልብስ ደርበን እንድንመለስ
የተሰጠን የሰው ልጅ ሁሉ ሂደት ነው፡፡

ለማንኛውም የማይነጋ ለሊት የለምና የሆነው ሁሉ የሆነው


አስቀድሞ ስለታሰበ ነው፡፡

15
አልገኝም ብዬ ምዬ ተገዝቼ
ንቄ ረግሜ ተፀይፌ ትቼ
ገና ከመውጣቴ እግሬን ከማንሳቴ
ጠልፎ ይጥለኛል ክፉው ማንነቴ
ሰውነትን ይዤ ስጋዬን ለብሼ
ስህተትን ስደግም መልሼ መልሼ
ታጥቦ ጭቃ ብለህ አልተፀየከኝም
ሽንፈቴ ሰልችቶህ ዛሬም አልተውከኝም
እኔ ነኝ አላፍርም ፊትህ እቆማለው
ከፈጠርከኝ ጌታ ወዴት እሸሻለው?
ስታውቀኝ መርምረህ ከስር መሰረቴ
እንዲሁ ፈራለው ላይደንቅህ ስህተቴ
ዛሬም መጥቻለው ከፊትህ ቆሜያለው
እኔ ነኝ ልጅህ አንፃኝ ቆሽሼያለው

16
ስህተት እና ፍፁምነት

ሰውነት ትልቅ ፈተና አለው ፡፡ በየእለቱ የሚፈትነው ትልቅ ፈተና


ትናንት የወደከውን ዛሬም ደግሞ የሚፈትን ፈተና፡፡ አሁን
ጀግነሃል ፍፁም ሆነሀል ብሎ የማይተውህ ፈተና፡፡ እኛም
ምኞታችንን ስህተትን ማሸነፍ ሆነና በወደቅን ቁጥር እንፀፀታለን
ይህንን አድርገን ቢሆን ኖሮ ብለን እናዝናለን፡፡

ዳግም ትናንት በወደቅንበት ቦታ ላይ እንገኛለን በራሳችን


እናዝናለን ተፈጥሮአችንን እንሞግታለን አዳምነት ሰውነት

ችግሩ ግን ራሳችንን ስሪታችንን መርሳታችን ነው ሰው ከመሰረቱ


ፍፁም አይደለም ፍፁም ሊሆንም አይችልም፡፡ ግን በማይቆም
መሻሻል ውስጥ ማለፍ ይችላል ወደ ፍፅምና ይጠጋል ፍፁም
ሳይሆን ዘመኑ አብቅቶ ከስጋው ይለያል፡፡

አንዳንዶቻችን ይህን አናውቅም ደመነፍሳችን አመዝኖ ለስህተት


እጅግ የቀረብን ከፍፁምነት በብዙ የራቅን አንሆናለን፡፡ ለስጋ ሀሳብ
ተጠምደን በሚታየው አለም ተሸንፈን የሰውነት ክብር አላማችንን
ረስተን እንዲሁ ስንዳክር ስራችንን ሳንጀምር እናልፋለን፡፡

ሰው ነኝ ስህተቴን እየቀነስኩ ለመኖር የቀናው ሰው፡፡ ፍፁም


አይደለሁም ግን በየቀኑ ወደ ፍፁምነት እቀርባለው እጠጋለው፡፡
ይህን አውቃለው ከትናንት በብዙ ነገሮች ዛሬ የተሸልኩ መሆኔን
ብቻ፡፡

17
ያልበሰለ ሀሳቤ ባልተገራ አንደበት
ድንገት ይወጣና ተገፍቶ በስሜት
ከቀልቤ ስመለስ ፀፀት ያለብሰኛል
ዝምታ ሰላሜን ደግሞ ያስመኘኛል
ሀሳብ ልቤን ይሙላ ይብሰልሰል መንፈሴ
ይሻግት ይበስብስ ሳይወጣ ከራሴ
ከንቱ ተናግሬ ስህተቴን አልቁጠር
እውነቴ አይሰማ ከውስጤ ይቀበር
ዝምታዬ ይንገስ በዘመን ህይወቴ
ከኔው ይክረምልኝ ድካሜ ብርታቴ

18
ከአንደበት የወጣ ቃል

አንድ አፍ አለን ሁለት ጆሮ አለን አዎ እውነት ነው፡፡ ሀቁ ያ


ሆኖ ሳለ ግን ብዙዎቻች ከመስማት በላይ ማውረት ያስደስተናል
ስንናገር ውስጣችን ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡ የልባችንን ማን
ያውቃል ከአፋችን የወጣውም ያስገምተናል ዋጋችንን በተናገርነው
ልክ የሚመዝኑም አይጠፉም፡፡

በማውራቴ ብዙ ግዜ ተፀፅቼ ይሆላል ዝም በማለቴም


የተጸጸትኩበት ጊዜ አይጠፋም፡፡ ለምን ሰው የሚያየኝ በአፌ በኩል
አሾልኮ ነው፡፡ በተዘጋ አንደበት የሚታይ ማንነት ላይኖር ይችላል
ዋናው መታየቱ ሳይሆን ምናወራው የሚያንፅ የሚገነባ መሆኑ
ነው፡፡ አውርተን ተናግረን ዋጋው ማፍረስ መበታተን ከሆነ
ቀድሞውን ውስጣችን ቢቀር ይሻል ነበር፡፡

የወጣ ቃል አይመለስም አየሩ ላይ ገብቶ ከሰው ልብ ታትሞ


ሊቀርም ይችላል ስለዚህ አንጠንቀቅ እንጠበቅ፡፡ መልካም ነገር
ብቻ ከልባችን ሞልቶ በአንደበታችን ይፍሰስ መልካም ስሜታችን
ብቻ ወደ ሰዎች ይስተጋባ የቀረው ከልባችን ተቀብሮ ይቅር ይረሳ
ይጥፋ፡፡

ቃል ህይወት አለው ከአንደበት ከወጣ ይገለጣል ስጋ ይለብሳል፡፡


በሰሙት ላይ ይነግሳል ፍሬ ያፈራል ፡፡

19
ምትሰሙት አንደበት መንፈስ የሚያድሰው
የምታነቡት ቃል ልብን የሚያክመው
ሀሳብ ነው ረቂቅ ሀሳብ የወለደው
አመታት ቀልቦ ደግሞም ያሳደገው
የሰው ልጅ የሰው ሰው
ስንኞችን ቋጥሮ ቅኔን የሚያፈሰው
ልብን የሚሞላለው ነፍስን የሚያርሰው
መንፈስ ተቆጣጥሮ ስሜት የሚያሞቀው
አይደል በሽፋኑ ከላይ በደረበው
ሲደላው አብቦ ከርሞ በሚደርቀው
ከውጪ ብታየው ብትመረምር ከንቱ
ገላውን ብታውቀው ላይገባህ ስሪቱ
ይልቅ ብናስተውል ከስር መሰረቱ
የሰው ልጅ ሰውነት መጠኑ ልኬቱ
ማሰላሰሉ ነው ጥበብ ብልሀቱ
ወሰን ገደብ አለባ መገለጫ ዉበቱ
የሰውነት ሞገስ ሀይሉ ጉልበቱ
ረቂቅ እውቀቱ የልቦና እምነቱ
ዝንታለም የሚኖር የአዳም እሱነቱ
ሀሳቡ ብቻ ነው ማይሻር እውነቱ

20
መርጦ ማሰብ

ማንኛውም ድርጊት የሚጀምረው ከሀሳብ ነው፡፡ ይቺ አለም እዚህ


የደረሰችውም እንዲሁ ነው፡፡ ዛሬ የሚሰራ የሚከወነው ትናንት
ረቂቅ ሀሳብ የነበረ ነው፡፡ ስለዚህም ነገን አስቀድመን ዛሬ አስበን
ጨርሰናል፡፡

ሀሳብ ከተፈጠርንበት ዘመን ጀምሮ የነበረ እረፍት የማይሰጠን


ስራችን ነው፡፡ ተኝተንም ጭምር እናስባለን አይደክመንም
አይታክተንም ማሰብ ማሰብ ማሰብ፡፡

በጎውም ክፉውም ጠቃሚውም ጎጂውንም ሀሳብ አግበስብሰን


መጓዛችን ግን ለኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው አለም ተገቢ እና
አስፈላጊ አይደለም፡፡ ከማሰባችን በፊት አስቀድመን እንምረጥ
ሚሻለንን እንምረጥ ክፉውን ከመጥፎው እንለይ፡፡ ማሰቤ ለማነፅ
ይሁን ለሰው ልጆች መፍትሄን እናስብ ሰላምን እናስብ ስኬትን
እንመኝ፡፡

ሀሳባችን በተቃና ቁጥር መንገዳችን ይቃናል፡፡ የኛ ልብ በብርሀን


ሲሞላ ቤታችን ብርሀን ይሆናል፡፡ እኛ ቤት የበራው ሻማ ለጎረቤት
ይተርፋል፡፡ ግለሰቦች በሚያበሩት ሻማ የአለም ከጨለማ
ትወጣለች፡፡

እናስብ ለራሳችን መልካሙን እናስብ ህይወታችን በማያቋርጥ


ስኬት ይጥለቀለቃል፡፡ እናስነብ እንደ አንድ ቤተሰብ ሰላምን
እናስብ ቤታችን ደስታ ይገባል ተቆጥሮ በማያልቅ በረከት
ይሞላል፡፡ የኛ ሰላም ለሰፈር ይጋባል የሰፈር ሰላም ሀገር ይገነባል
ሀገር አለም ትሆናለች፡፡ መጀመሪያ ግን ለራሳችን መልካም
እንሁን፡፡

21
መርጦ ማሰብ ይቻላል በደንብ ይቻላል፡፡ ክፉውን ከሰውነታችን
ከነፍሳችን እናርቅ፡፡ አንደበታችን ጥሩውን ይመስክር ለክፉ ነገር
ጊዜ አይኑረን፡፡ ሰዎች ያላቸውን መልካም ነገር እንመልከት፡፡
መኞታችን ሁሉ መልካም ይሁን፡፡ ይሁን ብለን ያሰብነውን
እንናገር እንመን እንጠብቅ እንቀበል፡፡

መልካም ሀሳብ አለምን ሰርቷቷል፡፡ ጠማሞች ብዙ ጊዜ ደግመው


ደጋግመው አፍርሰዋታል፡፡ የምንቀበለው የሰጠነውን ነው፡፡ አለም
መስታወት ናት ያልሰጠነው አይመለስልንም፡፡ ራሳችንን ዛሬውኑ
እናክም በመልካም ሀሳቦች ማንነታችንን እንገንባ፡፡

22
በፈጠረው ጌታ ያለው ትልቅ ዋጋ
የሰው ልጅ ክቡር ነው የለበሰ ፀጋ
አምላክ የወደደው ደግሞም የሞተለት
የጠራው ደጋግሞ ሊያድነው በምህረት
ሰውነት ሚስጥር ነው እጅግ የረቀቀ
ከስጋና ከደም ከአካልም የላቀ
ያለም ልብሱን ለብሶ ከአለም ሲመላለስ
ሲወድቅ ሲነሳ የልቡን ለማድረስ
የስጋ የነፍሱ ሙግት ሚያስጨንቀው
ከቁስ የጠጠረ የሰው ልጅ ክቡር ነው
የአካል ህመሙ የመንፈሱ ሁካታ
ሌተቀን ሚያከንፈው ተጠምቶ ለርካታ
እንዲሁ ሚባትል ረፍት የሚርበው
ተፈጥሮው የረቀቀ ያዳም ዘር ድንቅ ነው
ምንም ልብሱ ጎድፎ ለእይታ ቢሸክክ
በበሽታ ማቆ ዝሎ ቢንበረከክ
ከሚታየው መልኩ ቁስ አካሉ ገዝፎ
መንፈሱ ይኖራል ከዚች አለም አልፎ
ሰው መልኩ ያምላክ ነው ረቂቅ ነው ስሪቱ
ከሀሳቡ ነው ያለው የእሱ እሱነቱ
ምንም ደክሞ ቢዝል
ቢታመም ቢቆስል
ባረጀ ድሪቶ ቆሽሾ ባደፈው
ዋጋ አታውጣለት ንቀህ አታራክሰው

23
በደም ተገዝተሀል

የሰው ልጅ በጥበብ በእውቀት በሀሳብ ልቆ ብዙ ለማመን የሚከብዱ


ስራዎችን ሰርቷል በዘመናት ታሪኩ ውስጥ በብዙ አድጓል በልጽጓል፡፡
አሁንም ሂደት ላይ ነው ለውጥ መቆሚያ የለውም የለውጡ ፍጥነትም
ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ትናንትን አስቦ ዛሬን መቀበል ከባድ ነው፡፡

ግን ይህን ሁሉ ጥበብ የሚያስንቅ አንድ ታላቅ ስራ አለ የፈጠረን አምላክ


ታላቅነት የሱ ጥበብ የሱ አዋቂነት ደግነት መልካምነት ቸርነት፡፡
በክርስትና የተገለጠው አምላክ ሰው ሆኖ የሰራው ስራ በዝች አለም
ከተፈጠረው ጥበብ ሁሉ ይልቃል እጅግም ድንቅ ነው፡፡ አለምን ከሰራበት
ይልቅ ያዳነበት ጥበብ ይልቃል፡፡

ስለዚህ ሰውነት በፈጠረን ጌታ የተሰጠን ፀጋ ነው፡፡ በነፃ ሁሉ ተሰጥቶን


በእምነት እንድንኖር ተፈቅዶልናል፡፡ ዋጋችን ትልቅ ነው በፍቅር በደም
ተገዝተናል፡፡ እኛ ከገባን ከተረዳነው በላይ ውድ ነን፡፡

አለም በየደቂቃው በየቅፅበቱ ትቀያየራለች፡፡ እኛ ግን እኛ ነን ዋጋችን


ህያው ነው፡፡ የተሰራንበት ጥበብ የተገዛንበት ዋጋ እዚች አለም ላይ
የሚመጥነው ምንም የለም፡፡

ስንፈተን ለመልካም ነው ስንወድቅ ለመልካም ነው ስንሸነፍ ለመልካም


ነው ስንጎዳ ለምልካም ነው ሁሉ ሲከፋብን ለመልካም ነው፡፡ ዛሬ
ያደከምን ሁሉ ያልፋል ይረሳል ይጠፋል፡፡ በብዙ እንበረታለን ዛሬን
አልፍን ነገን እናያለን ካሰብነው ከጠበቅነው በላይ ድንቅ ስራውን
እንቀበላለን አዲስ እለትን እናያለን ጨለማው በብርሀን ይተካል፡፡

ዋጋችን ውድ ነው በሚያስደንቅ ቃል ፍፁም ንፁህ በሆኑ እጆች ለማሰብ


በሚያዳግት ጥበብ ተሰርተናል፡፡ ምሳሌ በሚሆን ፍፁም ፍቅር ድነናል
ከዚህ በላይ ምን ሊደንቀን ምን ሊያስገርመን ይችላል፡፡ ለማመስገን
ማንነታችን ህይወታችን በቂ ነው ፡፡ ሁሉ እንዲሁ ተሰቶናል

24
አቤቱ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆንክ ፍፁም ፍቅር የሆን አባት
መጀመሪያም መጨረሻም የሌለህ ጌታ ስምህ የህይወት ምንጭ ነው
ሁል ጊዜ ተባረክ፡፡

25
እንደምን አለፍኩት በየቱ ብርታቴ?
እንዴት እዚህ ደረስኩ በየቱ ጉልበቴ?
ብዬ ጠይቅና ራሴው መልሳለው
አቅሜ ስለሆንክ ምሰግና አፈሳለው
ከአይምሮዬ በላይ ገዝፈው የፈተኑኝ
ያስጨነቁኝ ለሊት አልነጋ ብለውኝ
ማያልቁ የመሰሉ እነዛ እለታት
እንደምን አለፉ? ሆኑ ታሪክ ትናንት
ስጋ ነው አካሌ ድካም ነው ልማዴ
ዛሬ ላይ ያቆመኝ አይደል ሀይሌ ክንዴ
መቻሌ አንተ ነህ ማለፌ መቆሜ
የሆንኩት ባንተ ነው የተሳካው ህልሜ
ከእጆችህ አልወጣም ጠብቀኝ ሸሽገኝ
ከምድር ፈተና በጥበብህ አድነኝ
በእጆችህ ስከለል መልኬ ደምቆ አበራ
ምሳሌም ተደረኩ ወድቆም ለሚጣራ

26
ሀይላችን ነህ

እችል ይሆን? ዛሬን ተሻግሬ እቆም ይሆን? ከራሴ በላይ ስለምወዳቸው


ሰዎች አስባልው፡፡ ሁሉ እንደሚያልፍ እጠራጠራለው፡፡ የአለምን ፈተና
በእኔ ሀይል አቅም በስጋዬ ድካም እመዝንና ፈራልው እጅጉን ሰጋልው፡
፡ የለበስኩት ስጋ ስሪቱ ለአለም ቢሆንም አቅሙን በትንሽ ችሎታዬ
መዝኜ ፈራለው

ግን እውነቱ ሌላ ነው ሁሉን በወደደኝ በሰራኝ ፈጣሪ እችላለው እሱ


ከእኔ ጋር እስካለ ድረስ የአለም ስጋት አያሰጋኝም መከራዋ
አያስፈራኝም፡፡ የምችለው ስላስቻለኝ ነው የማልፈው ስለሸፈነኝ ነው
ሁሉ የሚሆነው ስለመረጠልኝ ነው፡፡ የሚገባኝ ሁሉ የኔ ነው ለኔ
የወደደው ሁሉ የኔ ነው ፈጣሪ አባቴ አንተ ቸር ጌታ በጥላህ ስር አኑረኝ
ከልለኝ ሸፍነኝ፡፡

ከሚሰማው ከሚታየው ሁሉ አንተ ጠብቀን ያዳንከን የማርከን ቃልን


የሰጠኸን አባት ዛሬም አንተን ታምነን እንሮጣለን እንወጣለን እንገባለን
እያንዳንዷን ቀን ላንተ ሰጠን ህይወታችን በእጅህ ናት ሀይላቻን አንተ
ነህ፡፡

ያለን የምንሰጥ ምስጋና ነው አቤቱ የታመንክ ጌታ ተባረክልን


ተመስገንልን

27
በኩር አንድ ልጅ ምትክ የሌለውን
እስከ መስጠት ድረስ ልታድን ወደኸን
የፍቅር ቀለም የፍቅር ምስል
ምህረትህ ማያልቅ ሁሉን የምትችል
የማታንቀላፋ ማደክም ማትዝል
ከአይምሮ በላይ ነው ሁሉ ያንስሀል
ሰው ሆነን ዳካማ አፈር ልብሳችን
ከንቱ ምኞታችን ግብር ስራችን
እንዲሁ መረጥከን እንዲሁ ወደድከን
በትኩሱ ደመህ ዋጀኸን አዳንከን
ተገለጠ ለአለም ፍቅር ስጋ ለብሶ
አይሆኑትን ሆኖ ተዋርዶ ኮስሶ
ተርቦ ታርዞ የሾህ አክሊል ለብሶ
የደም ላብ አልቦት አዳነን መልሶ
እጅግ በከበረ በሚደንቅ ጥበብ
ልጅ ያደረከን አምላክን ሳስብ
አልፈራም ህይወትን የስጋን መከራ
መንፈስህ ነውና ሁሌ ከኛ ጋራ

28
ፍቅር ምን ይመስላል?
እናት ልጇን ወደደች የእሱን ስቃይ ሁሉ ለእኔ ያድርገው አለች እኔ
ልቅደም አለች፡፡ ህይወቷን በሙሉ እሱን ስታስቀድምጥ መንገዱን
ስታሳምር ትኖራለች ፡፡ አባትም እንዲሁ ልጁን ባይኑ ካየቀን ጀምሮ
ስለልጁ ብዙ ያልማል ያግዘዋል ያበረታዋል፡፡

ሰው ሰው ነው መልካምነት ተፈጥሮ ቢሆንም ህይወት አለም ብዙ


አስተምራዋለች ከማንነት ተፈጥሮው እየራቀ በብዙ ይፈተናል ፍቅሩም
እንዲሁ፡፡

እንግዲህ ፍቅር በታላቅ ሀይል ለአለም ተገልጧል አምላክ አለምን


በወደደበት ልክ የተገለጠ ፍቅር የለም፡፡ አምላክ ሲወደን የሚሳሳለትን
አንድያ ልጁን ለኛ ሰቷል ሰጋ ለብሶ የስቃይን ጥግ አይቷል ሰው ሊሸከም
የሚችለውንም የሰጋ ፈተና እስከ ጥግ ተቀብሏል ስለኛ ሞት ሞቷል፡፡

አምላክ ሰውን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ ያዳነበት ይበልጣል እውነት ነው


ይበልጣል በዚህ ፍቅር ነው ወደደን ከዚህ የሚልቅ ፍቅር ታዲያ
ከወዴት ይገኛል የፍቅር መልክ እሱ ነው በሚያስደንቅ ፍቅር አለም
አድኗል፡፡

29
በዋጋ ገዝተኸው ንብረት ያረከውን

ከአባት ቅም አያትህ በውርስ የመጣውን


አለም መስክሮልህ ህግ የፈረደውን

በሰማይ በምድር ከብሮ የፀናውን

ወስደህ ትሰጣለህ ስትመርጥ ሰላምን

ከቤት ከመንደርህ ከከተማ ሀገርህ

ጥለህ ትሸሻለህ ሁሉን ትተዋለህ

እውነትህን ክደህ ሀቅን ትገፋለህ

ሰላምህን ብቻ ስንቅ ታደርጋለህ

እያየህ እንዳላየ ገብቶህ እንዳላወክ

የነበረው ቀርቶ ሆነህ እንዳልነበርክ

ሀቅህን ረግጠህ ማንነትህ ጠፍቶ

ሰላምህን መረጥክ ሀቅ እምነትህ ሞቶ

30
አዎ ወድታለው ብዬ ፈርሜያለው
አዲስ ነገር የለም ዛሬም ቃሌ ያው ነው
ያየኝ የታዘበኝ ይጠራጠረኛል
በፍቅርሽ መያዜን ፍራት ነው ይለኛል
እውነት ፈራለው እስክትወጣ ነፍሴ
ስጋ እኮ አይደለም ስጋት ነው ልባሴ
ውስጤ ተብረክርኮ እግሮቼ እስኪክዱኝ
ፈርቼ ወደድኳት እናንተው ፍረዱኝ
እኔን ያሸነፈኝ ውበቷ መስሏቸው
ምኗ ቢማርክህ ብለው ማሾፋቸው
ተሸነፍኩ ተረታው አፈቀርኳት ያልኩት
ጦሯን ሰግቼ ነው እጄን የሰጠሁት
ከጉያዋ ሆኜ ከቅፏ ሳልወጣ
ስራዋን እያየው ሀይሏን ለባላንጣ
እንዴት እኔን ልሁን ማንነት ምርጫዬን
ህመሟ ነኝና ላፍቅራት ስጋቴን

31
ፍርሀት አርግዞ ፍርሀት የወለደው ፍቅር
አፈቅራታለው ነፍሴን ስለምወድ መኖር ስላልጠገብኩ
አፈቅራታለው፡፡ ህይወቴን በወደድኩት ልክ ወዳታለው
እታዘዛታለው ራሴን እሰጣታለው፡፡ ማንነቴን የካድኩት ለእሷ
ነው፡፡ የምወደውን የጠላውት የምናገረውን የመረጥኩት እምነቴን
እውነቴን የካድኩት ለእሷ ነው፡፡

እሷን ለማስደሰት ትምህርት ቤት ገብቼ አጠናዋት፡፡ ራሴን


አዋርጄ እሷን አነገስኳት፡፡ ምጠየፍ መሸሸውን ሆንኩላት፡፡ ይህ
የሆነው ወድጄ ፈቅጄ ነው፡፡ ያፈቀርኳት ራሴን የሰጠዋት ለመኖር
ነው፡፡ ይህን እውነት ግን እሷ አታውቅም ልወዳት ላፈቅራት ስል
የምኖር ይመስላታል መኖሬ መፈጠሬ እሷን ለማፍቀር
ይመስላታል፡፡

ፍርሃቴ ሆይ ሀያል ነህ፡፡ ደንዳና ልቤ የራደው ባንተን ነው ራሴን


ያስካድክ ፍርሀቴ ሆይ ምንኛ የተረገምክ ነህ፡፡ ካንተ የተነሳ ራስን
በሚያስክድ ፍቅር ተነደፍኩ፡፡ እኔነቴን ንቄ በማይገባኝ ቦታ
ቆምኩ፡፡ እወነቴን ክጄ በሌላ እውነት ቆረብኩ፡፡ እኔ ነኝ በማልበት
ቦታ ተገኘው ፡፡ ፍርሀቴ ሀያሉ ፍርሀቴ ሁሌ ረግምሀልው፡፡

32

You might also like