You are on page 1of 2

ተነሺ!

...ታደለ ሲሳይ...
============
ላያምርብሽ ማንቀላፋት ላይስማማሽ የዕረፍት ዓለም
ላያሰክንሽ የስካር ጠጅ ላያጠፋሽ የጠላት ደም
አትተኝ ነቃ በይ አትድከሚ እናታለም።
የምዕራቡ የጎን ሕመም የምሥራቁ የዐይን ብሌን
የአፍሪካ ኩራት ካባ የአረቡ የፍርሐት ቀን፤
አንቺን አይቶ ጠላት ላያርፍ ብትተኝም ለማይተኛ
ተነሽና ሆነሽ ታይው የሕይወቱ ቂም መጋኛ።
ያንቺን መዳን ስንናፍቅ ስናማትር ትንሣኤሽን
እንዳትነሽ ቢመኙልሽ ቢጠብቁም መቃብርሽን
ድንጋዩን ፈነቃቅለሽ አሣያቸው መነሣትሽን።
እኛ እንደው ተስፋ አንቆርጥም
እስካልጠፋን ከዚህ ዓለም።
እምነት ተስፋ ያውም ፍቅር
እንዲኖሩ በትብብር
አስተምረሽ አኑረሽን ከቶ ለምን ተስፋ እንቁረጥ
ሐውልተ ፄው እስከምንሆን እንዳየናት ብእሲተ ሎጥ።
ለተስፋችን ስንቅ ሆነሽ ለፍቅራችን ታላቅ ማማ
ለእምነታችን ጉልህ ሚዛን ለጠላትም የእሾኽ ሳማ
ሆነሽ አየን ስታኖሪን በእውነት ዓለም በከተማ።
እናማ እናታለም
አትድከሚ ለዚህ ዓለም።
ጠንከር ብለሽ እንዳባትሽ ዘራፍ ብለሽ እንደ ልጅሽ
አዚም ካባሽን አውልቀሽ ወኔ ሱሪሽን ታጥቀሽ
አኑሪን በጀግንነት ድኩም ጉልበት አይጣልብሽ።
አስተምሪን በፅናትሽ አስተሣሥሪን በወንጌሉ
አጀግኒን በማተብሽ እምነት ስጭን በመስቀሉ
እንዳንደክም ጉልበት ሁኚኝ እንዲያድርብን ኃያል ኃይሉ
የፍቅር ጧፍ እንዳይጠፋ አብርቶታል ሕያው ቃሉ።
ፅዮንን አቅፎ ይዞ የግሸኑን ቃል ተሳልሞ
የላሊበላን በረከት በሕያው ግንባር አትሞ፤
የጣና ቂርቆስ ጠበሉን በንጋት ኮከብ ተረጭቶ
የጣናን የጥበብ ውሃ በግዮን ማንኪያ ጠጥቶ፤
የቤተልሔምን ድጓ የዙራምባውን አዚሞ
የጎንጂን ቅኔ ጠጥቶ የጎጃም አዝመራን ለቅሞ
አሸተን ማርያምን አይቶ ያውም ቁልቢን ተሳልሞ፤
መተኛት የግፍ ፅዋ እንጂ ድካም አይሆንም ከቶ
ተነሥተሽ ሙታንን አንሺ ቅደጅ የሐዘን ቡትቶ።
ኮቸሮ ዓለም ቆርጥመሽ ላይሞላ የፍቅር ከርሥሽ
በሶ ሕይወትን በጥብጠሽ ላይቀና የፍቅር ቀንሽ
አንገት በመድፋት አባዜ እንዳይመሽ የንጋት ጊዜሽ።
ተነሽ እንዳባቶችሽ
ዘምሪ እንደልጆሽ
አብሪ እንደ ከዋክብት
ዘምሪ እንደ ካህናት።
ዘራፍ ተብሎ እንጂ በወኔ የሚገኝ የአንድነት መና
በፍርሐት ጉልበት ከራደ አይገልጥም ስቃይ ደመና።
=============
የቴሌግራሜ ቤተሰብ ይሁኑ!

You might also like