You are on page 1of 7

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

ዕንባዬ

ጥቂት ቢበራ ጥቁረቴ

አደብ ቢገዛ ስሜቴ

ቢፋቅ ቢታጠብ በደሌ

የብረት በሩን ገርስሰህ

ሃያሉን ግብድ ደርምሰህ

የዓይኔን ሽፋሽፍት ገላልጠህ

ፍሰስ ዕንባዬ በፊቴ ላይ

ደጉን ከክፉ ለይቼ እንዳይ፡፡

ሽልማት

ከአለም ትብታብ አምልጦ እስከ መልስቀል ለሮጠ

የኃጢአት ዝናብ ላልመታው ከውሽንፍሩ ላመለጠ

የኋላውን ወዲያ ጥሎ ወደፊት ለተራመደ

መሰናክሉን ለማለፍ ለበረታ ለለመደ

ከአምላኩ በረከት ሲሳተፍ የአምላኩን ትንሣኤ ሲያይ

እሱ አለው ትልቅ ሽልማት ከቀራንዮ ጫፉ ላይ

እንደ ዮሐንስ ቢፈጥን እንደ ጴጥሮስ ቢያዘግም

ጎለጎታ ይድረስ እንጂ ባዶውን አይመለስም፡፡

በደሙ አተመኝ

ለሌባ ዋስ የለው ለቀማኛ ዘመድ

ከጓደኛዬ ጋር ተቀብለን የሞት ፍርድ

ተገልፆ ሲታየኝ በደሉና ፅድቁ

የፀፀትን ዕንባ አይኖቼ አፈለቁ

ለካስ ከሞት ሃገር ሕይወትም ይገኛል

የዕደሜ ልክ ኃጢአት ንስሐ ያጠራል

ዕንባዬን አብሶ የተስፋ ቃል ሰጠኝ

ዳግም እንዳልጠፋ በደሙ አተመኝ


ቁልፉን ተረክቤ ከሕይወት ባለቤት

አዳምን ቀድሜ ገባው ወደ ገነት፡፡

ለራሴ ተረፍኩኝ

ልጄ በበሽታ በአጋንት ተለክፋ

የሚያድናት ሃኪም መድኃኒት ቢጠፋ

ጌታዬን አሰብኩት በአለቀ ሰዓት

የዳዊት ልጅ ማረኝ ስል ተማፀንኩት›

ዝምታው ቢበዛ የአምላክ ትዕግስቱ

‹‹አሰናብታት›› አሉት ደቀ-መዛሙርቱ

ጥፋቴን ነገረኝ ልጁም እንዳልሆንኩ

ኃጢአቴን አምኜ ፍርፋሪ ለመንኩ

በጣም የታመምኩት ለካ እኔ ነበርኩኝ

ልጄን ላድን ብዬ ለራሴ ተረፍኩኝ፡፡

ለእኔ ነው የሚያሻው

የቀናው ጉዞዬ ፍኖቴ ሲጣመም

በልጅነት ገዳም በእርጅና ወደ አለም

ለእኔ እንጂ እዬዬ ማቅ ለብሶ መባጀት

ወይኔ ብሎ መዝራት ዕንባን እንደ ጅረት

የላመ የጣመ ብልጭልጩ ማርኮኝ

ክብሬን ለገፋው በአቴን ለጣልኩኝ

ቀሚሴን አርዝሜ ቆቤን አንጋድጄ

ሳይወድቅ አይቀር ሆኜ እኔው ተንጋድጄ

ወበ ከንቱ ለሆንኩ

በደም የፀናውን ሕግ ለተላለፍኩ

ለዕኔ ነው የሚሻው ማረኝ ብሎ መውደቅ

ቸርነቱን አምኖ በዕንባ ለመታረቅ

ከቀለጠው መንደር ከተማ ለገደምኩ


ወርቄን ጠጠር ብዬ መክሊቴን ለቀበርኩ

ለእኔ እንጂ እዩዬ ልብን የሚያዋዛ

ከበዓት የሚያኖር አደብ የሚያስገዛ፡፡

እስጢፋኖስ

የሐዲስ ኪዳን ሠማዕት

የወንጌል ቃል መሠረት

ይሕን አለም ንቆ ትቶ

ለሃይማኖቱ ተሰውቶ

ውሃ ጥሙ ሳይበግረው

ጉስቁልናው ሳይታክተው

ባደባባይ ለወገሩት

ላሰቃዩት ለጎተቱት

ባለማወቅ ላስጨነቁት

ለጠላቶቹ ይቅርታን የጠየቀ

የአምላኩን ቃል የታጠቀ

የክርስትያን ድል አርበኛ

የፍቅር የሠላም መገኛ

የአምላኩን ቃል የፈፀመ

የጌታን ቃል የደገመ

እስጢፋኖስ ተወገረ

ተዋሕዶን ለተተኪው አስረከበ፡፡

ይችን ዓመት ተወኝ

ከአመት እስከ አመት ፍሬን ሳላፈራ ደረቅ እንደሆንኩኝ

በራድ ወይም ትኩስ ሁለቱንም ሳልሆን እንደው ለብ እንዳልኩኝ

አለሁኝ በቤትህ ለሙን ሕያው መሬት እያጎሳቆልኩኝ

አውቃለው አምላኬ ፍሬዬን ለመልቀም እንዳመላለስኩህ

ዛሬም ሳላፈራ እሾህን አብቅዬ ደርቄ ጠበኩህ


ያልተደረገብኝ ያላፈሰስክብኝ ያልሰጠኸኝ የለም

ነገር ግን ይህ ሁሉ አላርምህ አለኝ አለየኝም ከአለም

የማትሰለቸኝ ሆይ ተነስቼ እስክቆም እባክህ ታገሰኝ

የእኔን ክፋት ተወው መልዐክህን ሰምተህ ይችን አመት ተወኝ፡፡

ስንት አለ እንደኔ

ጎጂ ጠቃሚውን ማወቅ የተሳነው

አዚም የወደቀበት እጅግ ብዙ ሰው ነው

እንዲሁ የሚጓዝ ሳያስብ ለነፍሱ

ኃጢአት የሆነበት የጌት ካባ ልብሱ

ሳያጣ መካሪ ለነብሱ አስተማሪ

ጆሮዳብ ብሎ በቀጠሮ አዳሪ

በጠዋት የመሸበት ንስሐ ሳይገባ

ፅድቅ እሩቅ ሆናበት በኃጢአት እየባባ

ስንት ይሆን እንደኔ ትዕዛዝ የሚያዛባ

ከጭንቀት እንድድን ዘላቂ ሕይወቱ

ለሥጋወ ወደሙ የሚቀርብ በወቅቱ

ከጸሎት የማይለይ ዘውትር አንደበቱ

ቢቆጠር ስንት ይሆን ቢታወቅ አኀዙ

ቂም አዝሎ የሚዞር አለምን አላሚ

ስንት አለ እንደኔ ለንስሐ አቅማሚ

ዛሬ ነገ እያለ በኃጢአት ደካሚ

ምን ያሕል ይሆናል ቢታይ ከየቤቱ

እንደኔ የሆነ ምክንያተ ብዙ፡፡

ወዴት ጣልሽው

የሥጋ ክምር ቋጠሮሽን

የአፍላነት ስጦታሽን

የአመታት ሸክምሽን
የት አረግሽው ጉብጠትሽን

ወዴት ጣልሽው መለያሽን

ከየት ተሰጠ ማንባቱ

እኔ ኃጥዕ ነኝ ማለቱ

ከወዴት መጣ ብልሃትሽ

ማረኝ ፋሸኝ ማለትሽ

አንቺ የ 18 ዓመት ድውይ የኢያሪኮ ህመምተኛ

ዕጣሽ ዝምታ የሆነብሽ ዘመድ አልባ ገለልተኛ

ወዴት ሔዶ ከየት ገባ የቋጥኝ ክምር ሸክምሽ

እንደ ሻማ ነው የቀለጠው ወይስ እንደ ቅርፊት ነው የተጣለልሽ

ንገሪኝ እባክሽ ልረዳው

ጨቅላ አዕምሮዬ አይጭነቀው

እየተነነ እንደ ትነት በሠማይ ነው የተረጨ

ወይስ በደም ስርችሽ እየገባ በሰውነትሽ ተሰራጨ

ወዴት ገብቶ ነው የተቃናሽ

ያ ጉብጠትሽ የጠፋልሽ

ከረገጥሻት መሬት ውጪ ሰማይን ለማየት የታደልሽ

እጁ ሲያርፍብሽ ምን ተሰማሽ

ቀና ስትይ ከጉብጠትሽ

አልገረመሽም ድንቅ ስራው

ክምሩን ሲበትነው ድካምሽን ሲፈታው

ንገሪኝ እባክሽ ልረዳው ጨቅላ አዕምሮዬ አይጭነቀው፡፡

እናንተን ልከተል

አልትብላ ያለውን በልቶ እንደ ዋዛ

አዳም ወልደ አዳም ሆነ ቀበዝባዛ

ጽድቃችን በሙሉ ቢሆን የመርገም ጨርቅ

እስራኤል በሙሉ በሲዖል ሲማቅቅ

ደረሰ ክርስቶስ የአለሙ ቤዛ

ፍጥረቱን ሊታደግ በደሙ ሊገዛ

የአዳም የዳዊት የዕንባችሁ ዜና

የአባቶች ተማፅኖ የሐዋርያት ምልጃ


ጾም ጸሎታቸው ድህነትን ማወጃ

ከረበከታቸው እኔም እንድካፈል

ምልጃ ጸሎታቸው እንዲሆነኝ አክሊል

ጾማችሁን ጸሜ እናንተን ልከተል፡፡

ተዋሕዶ

ቅዱሱ ከአለም ተሰዶ

እምነትን ከተግባር አዋሕዶ

ባንቺ የዳነው አንቺን ወዶ

አይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

የሐዋርያት የጸሎት ቤታቸው

የቅዱሳን ክብር መጠጊያቸው

አረ አንቺ ነሽ ፅዮን ቤታቸው

ዛሬ በአለም ፍቅር የታጠሩ

በዲያቢሎስ መንፈስ የታወሩ

አንቺን ለማጥፋት የሚጥሩ

አረ ብዙ ናቸው ቢቆጠሩ

ታዲያ ወገኖች ምን ይሻላል

በአጥፊው መንፈስ ተከበናል

ለዚህ መጸለይ ይገባናል

ከአምላክ የፅድቅ አክሊል የታደሉ

በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ያሉ

ስለኛ ድህነት ይማልዳሉ

እንግዲህ በተዋሕዶ ያመናችሁ

አሉ መላዕክት ጠባቂያችሁ

ድንግል ማርያም ናት መከታችሁ

ፈጣሪ አለ አምላካችሁ

ምንም የለ የሚያስፈራችሁ
በተዋሕዶ ይፅና እምነታችሁ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ከመለከት እና ከሐመር መፅሔት ላይ የተወሰዱ ግጥሞች

አዘጋጅ፡- ፋሲል ኪዳኔ

የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ እና ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ኆኅተ ጥበብ ሰ/ት/ቤት

You might also like