You are on page 1of 8

ጠብቄሽ ነበረ

የማታምረው ቤቴ ቢያምርባት ብዬ

ሞገስ እንዲሆናት ፎቶሽን ሰቅዬ

ጠብቄሽ ነበረ

ከስስ ፍራሼ ላይ ቆንጆ ጥልፍ አንጥፌ

በትራሴ መሀል ዋጋው ረከስ ያል ሽቶ አርከፍክፌ

ጠብቄሽ ነበረ

የሚገርምሽ ውዴ

እኔ እራሴን ሳውቀው አልሽቀረቀርም

መዋብን አስቤ ጨርቄን አልቀይርም

መምጫሽ ግን ሲቃረብ

እራሱን ይጥላል እንዳትይኝ ብዬ ቅድሚያ ለኔ ሆነ ያቅሜን እቁብ ጥዬ

የሚማርክሽን ባላውቅም ገምቼ ስትመጭ ምለብሰው ሳልባጆች ሸምቼ

ጠብቄሽ ነበረ

ከእናቴ ጉያ እቅፍ እራሴን ፈልቅቄ

ከፍቅር አይኖቿ ከስስቷ እርቄ

ጠብቄሽ ነበረ

ለምን ይመስልሻል

ከእናት ጉያ በልጦ ያስጨከበኝ ነገር


ምን ሊሆን ይችላል ከድምጽሽ በስተቀር

እንዲ ነው አለሜ

ከሩቅ ፍቅርሽ በቀር የሚንከባከበኝ ከቶ አልሻም ብዬ

አካልሽን ነስቶኝ ካጠላው መንፈስሽ ነብሴን አስተንብዬ

ጠብቄሽ ነበረ

አንችው በሰራሽው ኑር ባልሽኝ አለም ስር ላንችው ተገልዬ

ጠብቄሽ ነበረ

ስለ ማንነትሽ አሷ ማለት ማለት

በግጥም በድርሰት በቃላት ሰንሰለት

ደረቴ ላይ ወድቀሽ ስትመጭ የማነበው

ወይ የቀረሽ እንደው በእንባዬ የማጥበው

በሌሊት ትጋቴ በሀሳብ ምጥ ጭንቀት ፋታ በማይሰጠው የፊደላት እውቀት

በብዕር ወልጄሽ በሌጣ ወረቀት

ጠብቄሽ ነበረ

ስሚኝ ናፍቆቴ ሆይ

እኔ ማለት እኮ

መድረሻውን እንደማያውቅ የሰማይ ጉም

ሩጥ ለምትል ህይወት የማዘግም

ከተፈጥሮ ተካስሼ በሆነ እውነት የምረታ

ዛሬ ይሄን አልፌ ነገን ታዛቢ ነኝ በትናንት ትዝታ


በህይወት ትዝብት ውስጥ ብዙ ስሜት አለ

የዬራሱን አለም ፈጥሮ የተከለለ

ኮልኩሎ እስከሚያስቅ እስከማይሽር ቁስል እራሱን ያመገለ

በህይወት ትዝብት ውስጥ ብዙ ስሜት አለ

ሌላው ቢቀር ፍቅሬ

ናፍቃኝ ለማላያት የማለዳ ጀምበር የሌሊቱ መንጋት ለእኔ ሀዘን ነበር

ለእኔ ፀሐይ መውጣት

ሰክና ያደርች ምድር እፎይታ በመንሳት ይመስለኝ ነበረ በደግ የተኛውን ለክፋት ማስነሳት

ደግሞ አለች

አመሻሽ ላይ ትኩላ የምትወጣ

ስሜት የማትሰጠኝ የፀሐይ ባላንጣ

እንደ ንጋት ሁሉ የሰማዩ መጥቆር የጨረቃ መውጣት ደስ አይለኝም ነበር

መምጫሽ ግን ሲቃረብ

መምጫሽ ግን ሲቃረብ

መካሪ ፍቅርሽን ሽማግልና ልኬ

ግልፍተኝነቴን በጸጸት ማርኬ

ከማለዳ ጀንበር ከምሽት ጨረቃ ፀቤን አስታርቄ

ሰማይ ጠቁሮ ሲመሽ በምስጋና ብዛት ደግሞ ንጋትን ሳይ በፈገግታ ሙላት

ተፈጥሮን አፍቅሬ በማድነቅ ሰክሬ

ጠብቄሽ ነበረ
እውነት እልሻለው

የመምጫሽ ቀን ሲደርስ ሳቅ የጠማት ነብሴን ሀሴት ላይ አንሳፍፌ

የታሰረ እውነቴን ትዝብቴን ገፍፌ

በፈገግታ ፀዳል ጥቁር ማቄን ጥዬ

የዘመናት ኩርፊያ ሀዘኔን ገድዬ

ጠብቄሽ ነበረ

የትዝታን ዓለም ትናንትን እረስቼ

የነገዬን ተስፋ በጉጉት ሞልቼ

በሳቄ ጥላ ውስጥ እያሽኮረመመኝ

ፍቅርሽ ብርቱ እመሜን በቃል እያከመኝ

ጠብቄሽ ነበረ

ፍጹም በተረታ ለማግኘት ብልሀት

ነግሶ በማይረብሽ ደስ በሚል ፍርሃት

ሽው እንደሚል ንፋስ ድንገት እየወጋኝ

ቃልሽ ለመታመን ከቶ ሳያሰጋኝ

ጠብቄሽ ነበረ

ጠርጥር የሚለኝን ከንቱ ሀሳቤን ንቄ

የህልሜን ጓደኛ ምናቤን ጨፍልቄ

እውነቴን እኮ ነው

ገና ሳላገኝሽ አጥቼሽ ስሰበር ስሎ ልሚያሳየኝ


ለዚህ ከንቱ ምናብ ከመጨፍለቅ በቀር ምን መንገድ ይኖራል እረፍት የሚሰጠኝ

ምንም

ምንም የኔ ናፍቆት

እና ደጋግሜ ጠርጥር የሚለኝን ከንቱ ሀሳቤን ንቄ

የልቤን ደግ ወዳጅ ምናቤን ጨፍልቄ

ጠብቄሽ ነበረ

በመምጫሽ ቀን ብስራት

መልክ ያጣች ህይወቴን እንደ አዲስ ልፈጥራት

ምስጊን ጠባብ ቤቴ ጥበቷን አስፍታ

በማታውቀው ድባብ በጉጉት ተቃይታ

ትጠብቅሽ ነበር ብርሃኗን ለብሳ በፎቶሽ ፈገግታ

ከጎደላት ይልቅ ባላት ተመክታ

እና ናፍቆቴ ወይ

በዚህ ሁሉ ስሜት ጠብቄሽ ነበረ

ጠብቄሽ ጠብቄሽ ጠብቄሽ ነበረ

በመጠበቄ ውስጥ በርግጥ አልቀረሽም

ግን ከእኔ ሀሳብ ጋር አብረሽ አልመጣሽም

እንጅማ አልቀረሽም

በቃልሽ መሰረት በነገርሽኝ እለት ከቶ ሳይረፍድብሽ ሳትዘገይ ደርሰሻል

በኔ መጠበቅ ግን መምጣትሽ ሲሰላ ብትመጭም ቀርተሻል


በመምጣትሽ ውስጥ ግን መቅረትሽን ክንብንብ እውነት ስውር ቅኔሽን

ፈትቼ አልወቅስሽም

አንችማ ናፍቆቴ

በመጠበቄ ውስጥ ጭራሽ አልቀረሽም

ግን ከሀሳቤ ጋር አብረሽ አልመጣሽም

ከመጠበቅ ተስፋዬ ላይ የካብኩት ብዙ ጉጉት

ባንቀላፋች ባንድ ጀንበር ፈርሶ አየውት

እስኪ ንገሪኝ

ጉጉት ምኟት እንደቀላል ባንዲት ጀንበር ለካ ይጣላል

አለት እውነት እጅ ይሰጣል ባንዲት ጀንበር ለካ ይቀልጣል

በይ ንገሪኝ እስኪ

ለካ ተስፋ ተስፋ ይቆርጣል ባንዲት ጀንበር ምርኩዝ ያጣል

አንዲት ጀንበር አንዲት ጀንበር

ይችን አንዲት ጀንበር

ከልብሽ ላይ የጸነሻት ከመምጣትሽ ቀድመሽ ነበር

ጠብቄሽ ነበረ

በርግጥ አልቀረሽም ግን ከእውነቴ ጋር አብረሽ አልመጣሽም

ጠብቄሽ ነበረ

በቁሜ አሽኮርሙሞኝ ባንቀላፋኝ ዘመን

አንችን በመሰለ አስመሳይ ሰመመን


ጠብቄሽ ነበረ

በእርግጥ አልቀረሽም ደግሞም አልመጣሽም

በእርግጥ አልቀረሽም ደግሞም አልመጣሽም

..

..

ሁሌም ደስታሽን እና ስኪትሽን የሚመኝልሽ

አንችን ሲጠብቅ ሊሞት የተረፈው

ባንችው የተናቀው

You might also like