You are on page 1of 27

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

በሰ/ት/ቤ/ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን

ለቅድመ ግቢ ጉባኤ አገልግሎት


የተዘጋጀ ስርዓተ ትምህርት

ሃይማኖትና መንፈሳዊ ሰው

ኅዳር 2011
0
1. መግቢያ.................................................................................................................................................. 2

2. የትምህርቱ ዝርዝር ዓላማ፡................................................................................................................... 3

3. ሰውና የሰውነት ክብር ........................................................................................................................... 3

4. ሃይማኖት ምንድን ነው ...................................................................................................................... 4

4.1. ሃይማኖት መሠረት ነው፡-.......................................................................................................... 10

4.2. ሃይማኖት ከዕውቀት በላይ ነው፡- ...............................................................................................11

4.3. ሃይማኖት ተስፋ የምናደርገውን የሚያስረግጥ ነው፡- ................................................................11

5. እምነት ለምን አስፈለገ?......................................................................................................................12

5.1. ሰው ተፈጥሮውን ምንንቱን አቅሙን የሚያውቅበት የሚረዳበት ነው...................................... 12

6. መንፈሳዊነት ለምን? ...........................................................................................................................14

6.1. የሃይማኖት ሰው መገለጫዎች ....................................................................................................... 15

7. የክርስትና ሃይማኖት ምንነትና መገለጫዎቹ.....................................................................................16

8. የክርስቲያናዊ ስብእና መገለጫዎች..................................................................................................... 21

ዋቢ መጽሐፍት........................................................................................................................................... 26

1
1. መግቢያ

ሃይማኖት ለሰው ልጆች ብቻ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕሪው


ረቂቅ፤ አኗኗሩ ምጡቅ ስለሆነ የሰውም ሆነ የመላእክት አእምሮ ተመራምሮ ሊደርስበትና
ባሕሪው ይህ ነው፤ አኗኗሩ እንዲህ ነው፤ ወይም ይህን ይመስላል ሊሉት የማይቻል ነው፡፡
እርሱ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ዘለዓለማዊና ምሉዕ ሲሆን ፍጥራት በሙሉ ደግሞ በጊዜና
በቦታ የተወሰኑ ስለሆኑ ውስኑ የማይወሰነውን ሊያውቀውና በምርምር ሊደርስበት አይችልም፡፡

ሆኖም ግን ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ባሕርይና አኗር በራሱ ብቻ የሚታወቅ ረቂቅ አምላክ
ቢሆንም እኛ ፈጽሞ የማናውቀውና ስለ እርሱ ምንም ፍንጭ የሌለን ሆነን እንድንቀር
አልወሰነም፡፡ ከቸርነቱ የተነሳ ዓቅማችን ሊረዳው በሚችለው መጠን ማንነቱን፣ ህላዌውን፣
ባሕሪውን፣ መግቦቱን፣ ፈታሒነቱን፣ ፈቃዱን……… እናውቅ ዘንድ በተለያየ መንገድ
ገልጦልናል፡፡ ሃይማኖት የሚባለውም ይህ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ እናውቀው ዘንድ ስለ
ራሱ የገለጠው መገለጥ ነው፡፡ ስለሆነም ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ያሳየበት መንገድ
የሰው ልጅ ሊቀበለው በሚችለው መጠን ስለ ራሱ ማንነት ለእኛ የገለጠው እውነታ ነው፡፡

ስለሆነም ትውልዱ ሰው ከፍጥረቱ ጀምሮ እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳን እጆቹ አክብሮ


ያበጃጀው በኋላም ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚጠብቀው አውቆ በውስን አእምሮው
የማይመረመረውን አኗኗሩን የሚረዳበትን ሃይማኖትን (ስለ ራሱ የገለጠውን መገለጥ)
በመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው በገለጡልን መጠን በመማር
ሃይማኖቱንና የተፈጠረበትን አላማ እንዲረዳ እንደ እንስሳት ህይወት ሞቶ በስብሶ የሚቀር
ህይወት ያለው ሳይሆን ዘለአለማዊ ህይወት እንዳለው አውቆና ተረድቶ መንፈሳዊ ህይወቱን
እንዲያሳድግ ሰላሣ ስልሣ መቶ ያመረ ፍሬ በማፍራት ለሌሎች ተርፎ መስሪያ ቤቱ በሆነችው
ጊዜያዊ መቆያው የስራ ሰዓት በሆነው ጊዜው ተጠቅሞ የዘላለም መኖሪያውና ማረፊያው ወደ
ሆነው ቤቱ ለዘላለማዊ እረፍት ለመጓዝ የተዘጋጀ እንዲሆን ለማስቻል ይህ ትምህርት
ተዘጋጅቷል፡፡

2
2. የትምህርቱ ዝርዝር ዓላማ፡

 ሰው ከፍጥረቱ ጀምሮ ያለውን ክብር ማስገንዘብ


 ሰው የተፈጠረበትን ዓላማ ይገልጻሉ
 የሃይማኖትን ምንነት ያብራራሉ
 መንፈሳዊ የመሆንን አስፈላጊነት ይተነትናሉ
 የክርስትና ሃይማኖት መገለጫዎችን ይዘረዝራሉ
 የክርስቲያናዊ ሰብአና መገጫዎችን ያብራራሉ፡፡

3. ሰውና የሰውነት ክብር

ሰው ማለት ከመፈጠሩ በፊት ሁሉ ነገር የተዘጋጀለት የንጉሥ ልጅ ነው፡፡ በፍጥረት ተፈፃሚና


በፍጥረት ላይ የተሾመ ታላቅ የእግዚአብሔር የመንግስቱ ወራሽ ፍጡር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ
እግዚአብሔር ከእሑድ እስከ ዓርብ በኀልዮ፣ በነቢብ እና በገቢር ከፈጠራቸው 22 ፍጥረታት
አልቆ ሦስቱንም አጣምሮ አንድ ጊዜ የፈጠረው ታላቅ ፍጥረት ነው ፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር
ሰውን ልፍጠር ብሎ በሕሊናው አሰበ፣ "እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ
ምሳሌያችን እንፍጠር…" ዘፍ 1÷26-27 ብሎ በአንደበቱ ተናገረ በእጁ ደግሞ ከአክብሮተ አዳም
ጭቃ ይዞ ታየ፡፡ "አሁን ግን አቤቱ አንተ አባታችን ነህ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፤
እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን፡፡ " ኢሳ 64÷8 እንዳለ እግዚአብሔር አፈሩን አንስቶ ጭቃውን
አቡክቶ እንስሳዊና መልአካዊ ባሕርይን አዋሕዶ የፈጠረው ትልቅ የእግዚአብሔር ፍጥረት ነው፡

የሰው ክብር የሚጀምረው ገና ከፍጥረቱ ነው፡፡ ከላይ እንዳየነው ሌሎችን ፍጥረታት በኀልዮና
በነቢብ ሲፈጥር ሰውን ግን ገቢርንም ጨምሮ አምሳሉ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ሰው ማንን
ይመስላል ቢሉ ምላሹ እግዚአብሔርን ይሆናል፡፡ መላእክትን ጨምሮ ሌሎች ፍጥረታት በሙሉ
እግዚአብሔርን አይመስሉም እግዚአብሔርን የሚመስል ሰው ብቻ ነው ይህ ትልቁ ክብሩ ነው፡፡

ሁለተኛው የሰው ክብር ሕይወቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማብራራት በሥነ ፍጥረት ሦስት
ሕይወቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የእንስሳት ሕይወት ሲሆን ሲፈጠሩ ይሰጣቸዋል ሲሞቱ ደግሞ
ሕይወታቸው እንደተወሰደ ይቀራል፡፡ የእንስሳት ሕይወት ሲፈጠሩ ይሰጣል በሞት ደግሞ
ይወሰዳል፡፡ ሕይወታቸው ሲወለዱ ይጀምራል ሲሞቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሁለተኛው የመላእክት

3
ሕይወት ነው በተፈጥሮ ይሰጣቸዋል እንደ ተሰጣቸው ይቀራል ምክንያቱም አይሞቱም ሕያዋን
ናቸውና የመላእክት ሕይወት ሲፈጠሩ ይጀምርና እስከ ዘላለም ይቀጥላል፡፡ የሰው ሕይወት ግን
ከሁለቱ ሕይወቶች ተለይቶ እንደ እንስሳትም እንደ መላእክትም መኖር ተሰጥቶታል፡፡ የሰው
ሕይወት ሲወለድ ይሰጠዋል ሲሞት ይወሰዳል፡፡ እንደገና ደግሞ መልሶ በትንሣኤ ያገኘዋል፡፡
እንደ እንስሳት ሲወለድ ይሰጠዋል በሞት ይወሰድበታል እንደ መላእክት ደግሞ እንደገና
በትንሣኤ ሙታን ሲነሳ ይሰጠዋል እንደተሰጠው ይቀራል፡፡ እንደ እንስሳት ጥቂት ጊዜ መኖር
ይችላል እንደ መላእክትም ዘላለም መኖር ይችላል፡፡ ሰው እንደ እንስሳ አጭር ሕይወት ከልደት
እስከ ሞት ይኖረዋል፡፡ እንደ መላእክት ደግሞ በትንሣኤ ዘጉባኤ ጀምሮ ለዘለዘለም ይኖራል፡፡

የሰው ልጅ ምንም እንኳ ክብሩ እንዲህ ታላቅ ቢሆንም ከውድቀት በፊት የዋህና ገራገር
ኃጢአት የሚባለውን ነገር ጨርሶ አያውቀውም ነበር፡፡ አባታችን አዳምና እታችን ሔዋን
ከውድቀት በፊት ሁለቱም እርቃናቸውን ሆነው ሲተያዩ አይተፋፈሩም ነበር፡፡ ዘፍ 2÷25 በዚህ
ጊዜ ክፉውንና ደጉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ስላልበሉ ክፉ ነገር አያውቁም ነበር፡፡ እባቢቱ ጥርጣሬ
የማታውቀውን እናታችን ሔዋንን በመዋሸት ያታለለቻት እርሷ ስለ ውሸት ስለ ማታለል ስለ
ጥርጣሬ የምታውቀው ነገር ስላልነበራት ነው፡፡ አዳምና ሔዋን ከውድቀት በፊት የኖሩት
የቅድስና ህይወት የተዋበ ነበረ እንደ መላእክት ምስጋና ምግባቸው ነበረ ድካም ጉስቁልና
መውጣት መውረድ ማጣት ማግኘት ማርጀት መድከም የሌለበት የደስታ ህይወት የነበራቸው፡፡
ነገር ግን ከውድቀት ኃጢአት በኋላ ፀጋቸውን፤ ቅድስናቸውንና መለኮታዊ ገጽታቸውን
አጥተዋል ተጎሳቁለዋል በመጨረሻም ሰውን ከፈጠረበት ጥበቡ ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል
የተባለለትን ታላቅ ድኅነት የተደረገው ለዚሁ የሰው ልጅ ነውና ከዚህ የሚበልጥ ምን ክብር
አለ እንላለን፡፡

4. ሃይማኖት ምንድን ነው


ሃይማኖት የቃሉን ፍቺ ስንመለከት አምነ አመነ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን
ትርጓሜውም ማመን፣ መታመን ማለት ነው፡፡ ሃይማኖት እራሱን ለፍጥረቱ በገለጠ
በእግዚአብሔር ተስፋ ለምናደርገው ማናቸውንም ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር ሁሉ
የሚያስረዳና የሚያስገነዝብ እውነታ ነው፡፡ ይኸውም ከሁሉ በፊት የነበረ ሁሉን አሳልፎ
የሚኖር ፍጠረትን ሁሉ የፈጠረ ማንኛውም ነገር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ለእርሱ ግን

4
አስገኝ አሳላፊ የሌለበት በአድነት በሦስትነት ያለ ሁሉን ቻይ የማይለወጥ አምላክ መኖሩን
ማመን ነው፡፡ (ሃይማኖተ አበው መቅደም)

ሃይማኖት የተገኘውና የተመሠረተው ፈጣሪ ዓለማት እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በመገለጡ


የተነሣና ከእግዚአብሔር ሕግና ፈቃድ ወጥቶ በበደሉ የተፈረደበትን ሰውን ለማዳንና ለሰው
ቀጣይ ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመስጠት በተለየ አካሉ በከዊነ ቃል ባሕርይ በተዋህዶ ሰው
የሆነውን የአካላዊ ቃል የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት ለመረዳት፡፡ በአጠቃላይ
ሁለቱን የእምነት ክፍሎች ማለትም ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌን ለመረዳት
ይጠቅማል፡፡

ሃይማኖት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ራሱን የገለጠበት አስተርእዮ(ክሥተት) እንጂ አንዳንድ


ፈላስፋ ነን ባዮች እንደሚሉት የሰው ልጆች ከእውቀት ማነስ ከፍርሃትና ከድንጋጤ ያመጡት
አይደለም፡፡/ይሁዳ 1፥3/ በዚህም የሃይማኖት ምንጩና ባለቤቱ እራሱ እግዚአብሔር መሆኑን
መገንዘብ ይገባናል፡፡

ሃይማኖትሰ ጥይቅት ይእቲ ለዘይሴፈዋ ዕብ 11፥1 ሃይማኖት ተስፋ ለምናደርገው ለአሁንና


ቀጣይ የሰው ልጆች ሕይወት የሚያስረግጥ የማናየውን ነገር እንድናይ የሚያደርግና የሚያስረዳ
ነው ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረ ያለ ሃይማኖት እግዚአብሔርን ማወቅና ማምለክ ለሕጉና
ለትእዛዙም መገዛት አይቻልም፡፡

ማመን ማለት በዋናነት እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን በፈቃዱ ያደረገውን ነገር ሁሉ ማመን
መቀበል እና በአጠቃላይ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት እንዲሁም በሥጋዌው የገለጸውን
የእውነት ትምህርት (ሃይማኖት) ሳይቆነጻጽሉና ሳያጎድሉ በምልአት መቀበል ነው ይኸውም
እግዚአብሔር ወደ ሰው ያደረገው የማዳን ጉዞ (ፍኖተ እግዚአብሔር) ሃይማኖት ይባላል፡፡ዘፍ.3፥
1

ሃይማኖት ማመን መታመን አመኔታ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ቅድመ ዓለም ከሁሉ በፊት የነበረ
ፍጥረታትን የፈጠረ ማዕከላዊ ዓለም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ ድህረ ዓለም ዓለምን ዓሳልፎ
የሚኖር ለእርሱ ግን አስገኝ አሳላፊ የሌለው በአንድነት በሦስትነት ያለ ሁሉን ቻይ አምላክ
እንዳለ ማመን ማለት ነው፡፡

5
ማመን ስንል እግዚአብሔር አንድ መሆኑን፣ በአንድነቱ ውስጥ ልዩና የማይመረመር ሦስትነት
ያለው መሆኑን ከሦስቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም
ሰው መሆኑን ሥግው ቃል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመወለድ
ጀምሮ ለሰው ሲል ያደረውን፤ መጠመቁን፤ ዞሮ ማስተማሩንና መከራ መቀበሉን በመጨረሻም
በራሱ ፈቃድ ለእኛ ሲል መሞቱን፣ መቀበሩንና በሦስተኛው ቀን መነሣቱን እና በአርባኛው ቀን
ወደ ቀደመ ክብሩ ማረጉን….. ሁሉ ማመን ለመዳን አስፈላጊነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ቃልና ትእዛዝ ማመንን ያዳነን አምላክ ማን
መሆኑን እርሱ ራሱ አምላካችን በገለጠልን መጠን ማወቅና ማመን ለመዳን ወሳኝ መሆኑን
ጌታችን በትምህርቱ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ ለአብነት ያህል ብንመለከት ከሳምራዊቷ ጋር
ሲነጋገር እርሷ “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ
በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ” ባለችው ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አላት….“እናንተስ
ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን፡፡ ነገር ግን
በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም ሆኗል፤
አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም
በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል፡፡”ዮሐ 4፥20-24 እዚህ ላይ ጌታችን
የምናመልከውንና የምንሰግድለትን እንድናውቅና እውቀታችንም በኑፋቄና በስህተት በተበከለ
ትምህርት መሠረት ሳይሆን በእውነተኛ ትምህርት የተመሠረተ እምነት ሊሆን እንደሚገባ
አስተማረን፡፡ አስተምህሮው የተሳሳተ እምነት አምልኮው ትክክል ሊሆን አይችልምና፡፡
የምንሰግድለት አምላክ ሰዎች በኑፋቄ ትምህርታቸው በምናባቸው የሣሉትና በሃሳባቸው
የፈጠሩት ሳይሆን እኛ በሚገባ መንገድ ራሱን ለእኛ የገለጠውና እንድናውቀው ያደረገን
እውነተኛው አምላክ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ እንደ ሳምራውያን “እናንተ ለማታውቁት
ትሰግዳላችሁ” የሚል ወቀሳ ያስከትልብናል፡፡ ስለዚህ ነው ጌታችን “እውነተኛ አምላክ ብቻ
የሆንህ አንተን የላከውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት”
በማለት እውነተኛ አምላክ የሆነውን እርሱን ማወቅ የዘለዓለም ሕይወት መሠረት መሆኑን
የተናገረው፡፡ ዮሐ 17፥3 ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም “ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት
እንዲጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ” በማለት ለመጽሐፍ ቅዱሳዊና
ሐዋርያዊ ትምህርት ታላቅና ከባድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስተምሮናል፡፡ 2ጴጥ 1፥19

6
ሐዋርያዊት የሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጌታችንና ከሐዋርያት
የተቀበለችውንና የምታምነውን ሁሉ በፍጹም ልብ ማመን ያስፈልጋል እግዚአብሔር እኛን
ለማዳን ያደረገውን ልዩ ቸርነት እናምነው ዘንድ የገለጠውን እውነት የማያምን ሰው ሊድን
አይችልም፡፡

ማመን መቀበል እንጂ ማወቅ ብቻ አይደለም፡፡ ማመን ማወቅ ብቻማ ቢሆን ኑሮ አጋንንት
ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን ያውቃሉና በጸደቁ ነበር፡፡ (ማር1፥24 ፣
ማቴ 8፥29፣ ሉቃ 4፥34) ክርስቶስን ማመን ትእዛዙን ተቀብሎ እርሱን ተከትሎ መሄድ ነው፡፡
ስለሆነም ሃይማኖትና ምግባር ሰው የሚቆምባቸው ሁለት እግሮች ናቸው፡፡ ይህኛው ቀኝ ያኛው
ግራ ነውም አይባባሉም፡፡ ባንድ እግር አይኬድም አይቆምምና እኩል መታየት አለባቸው፡፡

በአጠቃላይ የክርስትና ሃይማኖት፦እግዚአብሔር ወልድ ሁለት ልደት እንዳሉት ማመን ነው፡፡

1/ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከባህሪይ አባቱ ከአብ መወለዱ /መዝ.109፥3/


2/ ድህረ ዓለም ያለ አባት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ
ነፍስ ነስቶ በተዋህዶ መወለዱን ማመን /ማቴ.1፥25ሉቃ.1፥26/

ሃይማኖት ለትሑታን ዕውቀትን ስለምትገልጥ'ከእውቀት ባላይ ስለሆነች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ


ተብላ ትጠራለች /ምሳ.9፥1-7'ማቴ.22፥1-12'2ኛ ጢሞ.3፥14-17/፡፡ ይህም ጥበብ በዓይን
የማይታይ በእጅ የማይዳሰስ በጆሮ ብቻ ሰምቶ ይህ ሊደረግ እንደምን ይቻላል ማለት ትቶ
በእግዚአብሔር ዘንድ ኹሉ ይቻላል ብሎ በሕሊና የሚታመን ረቂቅ ምሥጢር መሆኑን
መረዳት የሚያስችል ነው፡፡ ይህንንም የምንረዳበት ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣
ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን፣ የተባሉ አምስት አዕማድ
አሉት፡፡

ሃይማኖት የድኅነት መሠረት ነው፡፡ ቤት ያለ መሠረት ሊቆም እንደማይችልና በአየር ላይ ሕንፃ


መገንባት እንደማይቻል ሁሉ የዘላለማዊ ድኅነት መሠረትም ሃይማኖት ነው፡፡

ሃይማኖት ከራሱ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ወይም የተገለጠ ነው፡፡ የሃይማኖት ምንጩ ሰማያዊ
አባት እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት በተመለከተ ደቀ
መዝሙሩ ስምዖን ጴጥሮስ የሚኖረው እውቀት በዘመኑ ከነበሩ ሌሎች ሰዎች የተለየና የተሻለ

7
ሊሆን አይችልም ነበር፡፡ ማቴ 16፥15-17 ነገር ግን ከሥጋና ደም (ከዚህ ዓለም ሥጋዊ
ምርምርና ፍለጋ) ውጭ የሆነው እግዚአብሔር እውነቱን ገለጠላቸው እንጂ፡፡ ለዚህ ነው
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስጠነቅቅ “እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ
እንዳይሆን ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለፅ ነበር እንጂ በሚያባብል በጥበብ ቃል
አልነበረም” በማለት የተናገረው፡፡ 1ቆሮ 2፥4-5

እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ፤ እኛ ደግሞ ተቀበልን፡፡ የሰው ልጅ ሃይማኖትን ይቀበላል እንጂ


ሃይማኖትን ሊሠራ ወይም ሊያሻሽል አይችልም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
“የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነሱም ተቀበሉት” በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ ዮሐ 17፥8
እንዲሁም “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ስሙንም
ምንነቱንም ሊገባን በሚችል መጠን የገለጠልን ራሱ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሃይማኖት የሰው
ልጅ በምርምር የደረሰበት ግኝት አይደለም፡፡ ዮሐ 17፥6 ሃይማኖት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር
የተሰጠ ነው፡፡ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት” እንደ ተባለ ሃይማኖት
ከእግዚአብሔር የተቀበልነው እንደ መሆኑ መጠን የሰዎች ድርሻ አምኖ መቀበልና በዚያ
መጠቀም የዘለዓለም ሕይወት መውረስ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት በዚህ አዓለም ያለ ማንም
ግለሰብም ሆነ አካል እግዚአብሔር በሰጠው እውነት(ሃይማኖት) ላይ የመጨመርም ሆነ
የመቀነስ ሥልጣን የለውም ማለት ነው፡፡

መዳን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ(ጸጋ) ነው፡፡ የእኛ ድርሻ ደግሞ በመጀመሪያ ያን


የእግዚአብሔር ስጦታ እሺ ብሎ መቀበልና ለእግዚአብሔር የማዳን ጥሪ በጎ ምላሽ መስጠት
ነው፡፡ በዚህ ላይ ይህ እሺ ማለታችንና መዳንን መሻታችን በተግባር የሚገለጽባቸው እና
ለሁሉም የሰው ልጅ በአዋጅ የተሰጠውን የመዳን ጸጋ ለእያንዳንዳችን ገንዘብ
የምናደርግባቸውንና እራሱ ያዳነን እግዚአብሔር አድርጉ ያለንን ነገሮች መፈጸም ይኖርብናል፡፡
መዳን እንዲሁ “አምኛለሁ“ በማለት ብቻ የሚፈጸም አይደለም፤ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሰው
በመሆን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ከመፀነስ ጀምሮ ከኃጢአት በስተቀር
በእኛ ላይ የሚደርሰውን ነገር ሁሉ እንደ ተቀበለና ብዙ ሂደቶችን እንዳለፈ ሁሉ የእኛ መዳንም
የሚፈጸመው አዳኛችን የሆነው እርሱ በተግባር ሠርቶ ባሳየንና በተጓዘበት መንገድ ስንጓዝ ነው፡

8
ሃይማኖት ከምግባር ጋር የተባበረ መሆን አለበት፡፡ ከተግባረ ሥጋ ከተግባረ ነፍስ አስቀድሞ
የቀናት ሃይማኖት ይማሩት ዘንድ ይገባል ሃይማኖት መሠረት ምግባረ ህንጻነውና 1ኛ ቆሮ.3፥
10 “ሃይማኖት መሠረት ናት የቀሩት ግድግዳና ጣሪያ ናቸው” እንዳለ ዩሐንስ አፈወርቅ ቅጽረ
መሠረቱ ያልጸና ቤት ከቀን ወራሪ ከሌሊት ሰባሪ አያድንም፡፡ ይህ ማለት ጥርጥርን ትቶ
ሃይማኖቱ ከጸና ምግባሩ ከቀና መምህር ተምሮ መጻህፍትን ተመልከቶ ሳይጠራጠሩ
በአንደበትም በልብም አሰተባብሮ አስተካክሎ ማመን ይገባል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “አመኑህ ስለዚህ
ተናገርሁ” እንዳለ መዝ 115፥1 ቅዱስ ጳውሎስም “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም
መስክሮ ይድናልና፡፡” እንዳለ /ሮሜ.10፥9፤ ዘዳግ. 30፥14 ለሰው ይምሰል በአፍ አምኖ በልብ
ቢክዱ እንደ ዩሁዳ እነደ አርዮስ መሆነ ነው፡፡ መከራ መቀበልን ፈርቶ በልብ አምኖ በአፍ
ቢክዱ ከንሰሐ በፊት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ የልብ እመነት ብቻ አያድንም
የአፍ እምነት ብቻም አይጠቅምም ቅዱስ ጴጥሮስ በልቡ አምኖ ሳለ አይሁድን ከመፍራት
የተነሳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “አላውቀውም” ብሎ በካደ ጊዜ የልቡ እምነት ብቻውን
አልጠቀመውም፡፡ በአፍ በመካዱ መጸጸቱ እንባው ንስሐው ጠቀመው እንጂ፡፡ ማቴ. 26፥69-75፡፡
ይሁዳም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ መምህር ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስን በመሳም አሳልፎ በሰጠ ጊዜ የአንደበቱ እምነት አልጠቀመውም ከጥፋቱም ተምሮ
ንስሐ ለመግባት አልታደለም፡፡ማቴ.26፥14-16-49 ፤27፥3-5፡፡ ሃማኖት የነገር መለኮትን
ትምህርት የአምልኮትን ሥረአት ከእምነት የተነሳ የሚከናወንን ተጋድሎ ያጠቃልላል
2ኛጢሞ.4፥7'ይሁዳ.3፥20/፡፡ “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል በአፉም መስክሮ ይድናል”/ሮሜ.10፥
8-10'ማቴ.10፥32-33'ሉቃ.9'26/ የዘላለምሕይወትም ይኖረዋል፡፡/ዮሐ3፥16-18-36'5፥24'6፥40-
47'8፥51'11፥25-26/፡፡ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ይቀበላሉ፡፡/የሐዋ2፥38'ኤፌ1፥13-13-14/፡፡
ሃይማኖት /እምነት/ኖሮት ምግባር ባይሠራ ሃይማኖቱን የካደ ትምህርቱን ያሰደበ ነውና፡፡

በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በወንጌል የተነገረውን ከመቀበል ወይም


እውነት ነው ብሎ ከመስማማት ያለፈ ነገር ነው፡፡ ማመን መሠረት እንጂ መደምደሚያ
መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም ይህንን ለመገንዘብ የሚረዱና ትርጉሙን የሚያብራሩ
ነጥቦችን ብንመለከት፡-

9
4.1. ሃይማኖት መሠረት ነው፡-
እምነት በአንድ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያሉ የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ለዚህ
ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "አሚንሰ መሠረት ይእቲ ወካልአኒሃ ሕንጻ ውንድቅ እሙንቱ"
ሃይማኖት መሠረት ናት ሌሎች ግን ሕንፃና ግንብ ጣራ ግድግዳ ናቸው ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ በ9ኛው ድርሳኑ በሕንፃና በግንብ መስሎ የተናገራቸውና ሌሎች ብሎ የጠቀሳቸው
ምግባርና ትሩፋት ናቸው፡፡ እምነት/ሃይማኖት/ ግን የእነዚህ መሠረት ናት፡፡ የአንድ ሕንፃ
ጥንካሬና ብቃት የሚታወቀው በመሠረቱ እንደሆነ ሁሉ የሰው ማንነቱ እና ሥነ-ምግባራዊ
ሕይወቱ ጠንካራ መሆኑ የሚታወቀው በእምነቱ ነው፡፡ እንደዚሁም የፈጣሪን መኖር ማመን
በሚሰሩት ምግባርና ትሩፋት የሚያምኑት ፈጣሪ የማያልፍ የማይጠፋ ዋጋን እንደሚሰጥ
ማመንና መቀበል ይቀድማል፡፡ 318ቱ ሊቃውንትም "ከሁሉ አስቀድሞ ሃይማኖት መማር
ይገባል” እንዳሉ፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ "ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ
እግዚአብሔር እንዳለ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ በእምነት መቀበል ይቀድማል፡፡" ዕብ 11፥6 ፤
1ኛ ቆሮ 3፥ 11-15 "መሠረቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ መሠረት" እዚህ ላይ ቅዱስ
ጳውሎስ አለት በተባለው በቅዱስ ጴጥሮስ እምነትና ምሥክርነት ማመን ማቲ 16፥16 ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ መሆኑን ማመን የሁሉ መሠረት መሆኑንና ከዚህ በኋላ
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን በፈተና ጸንቶ ለዋጋ የሚያበቃ ሥራን መሥራት እንደሚገባ
ሲያብራራ ነው፡፡ የቀና ሃይማኖት የሌለው ምግባር ከጸብአ አጋንንት ከሥጋዊ ጠላት ከገሃነመ
እሳት አያድንም ፍጹም ኢአማኒ መሆን ነው፡፡ማር.16፥16 ህንጻው ጣራው ያልጸና ቤት
ከሌሊት ቁር ከመዓልት ሐሩር አያድንም በጎ ምግባር የሌለው ሃይማኖት ከጸብዐ አጋንንት
ከሥጋዊ ጠላት ከገሃነም እሳት አያድንም፡፡ ከዚህም ሌላ ነፍስ የተለየው በድን ማለት ነው፡፡ነፍስ
የተለየው ሥጋ ልንቀሳቀስ ልነሳ ልቀመጥ ልረፍ ሲል እደማይቻለው ሁሉ በጎ ምግባርም
የሌለው ሃይማኖት ድውይ ልፈውስ ሙት ላንሳ ታምራት ልሥራ ቢል አይቻለውም፡፡ ነፍስ
እደተለየው ሥጋ የሞተ ነው፡፡/ያዕ.2፥22/ ቅጽሩ መሰረቱ ህንጻው ጠፈሩ የጸና ቤት ከሌሊት
ሰባሪ ከቀን ወራሪ ከሌሊት ቁር ከመዓልት ሐሩር ያድናል፡፡ የቀና ሃይማኖት ከበጎ ምግባር በጎ
ምግባርም ከቀና ሃይማኖት አንድ ሆኖ የጸና እንደሆነ ከጽብአ አጋንንት ከሥጋዊ ጠላት
ከገሃነመ እሳት ይድናል እናም ፍጹም መንግስተ ሰማያት ይገባል፡፡ /ዮሐ.15፥5'ዕንባ.2፥
4'ት.ኢዩኤል 3፥5' ዕባ.11፥6/

10
4.2. ሃይማኖት ከዕውቀት በላይ ነው፡-
ሰው በስሜት ሕዋሳቱ መርምሮ ያውቃል፡፡ ጨለማውን ከብርሃን በዓይኑ አይቶ ጣፋጩን
ከመራራው በምላሱ ቀምሶ…ወዘተ በስሜት ህዋሳቱ ሲያውቅ ከዚህ ውጭ በርህቀት/ከእሱ
የራቀውን/ እና በርቀት/የረቀቀውን/ ያሉትን በስሜት ሕዋሳቱ መርምሮ በእውቀት ሊደርስባቸው
አይችልም፡፡ ይህም የሰው ልጅ ለእውቀቱ ድንበር ለአእምሮው ወሰን እንዳለበት ያሳያል፡፡ ነገር
ግን ወሰን ያለው ሰው ወሰን የሌለውን እግዚአብሔርን የሚያውቅበትና ከእግዚአብሔር ጋር
የሚገኛንበት እምነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ስለዚህ በዚህ እምነት/ሃይማኖት/ ከእውቀት በላይ
መሆኑን እንገነዘባለን ማለት ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ ማመን ከማወቅ በፊት እንደሆነ
መስክሯል፡፡ "እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንደሆንህ አምነናል፤
አውቀናል" በማለትዮሐ 6፥69

4.3. ሃይማኖት ተስፋ የምናደርገውን የሚያስረግጥ ነው፡-


"እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት፡፡" ዕብ
11፥1 ሰው በረቂቅነቱ ምክንያት በዓይነ ሥጋ የማያየውን የእግዚአብሔርን ህልውና የሚረዳው
በእምነት ነው፡፡ እምነት የማናየውን የምታስረዳ ተስፋ የምናደርገውን የሚያስረግጥ ነው፡፡

ሃይማኖትሰ ጥይቅት ይእቲ ለዘይሴፈዋ ዕብ 11፥1 ሃይማኖት/እምነት/ ተስፋ ለምናደርገው


ለአሁንና ቀጣይ የሰው ልጆች ሕይወት የሚያረጋግጥ የማናየውን ነገር እንድናይ የሚያደርግና
የሚያስረዳ ነው ብሎ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች እንደመሰከረላቸው ያለ
ሃይማኖት እግዚአብሔርን ማወቅና ማምለክ ለሕጉና ለትእዛዙም መገዛት ስለማይቻል ይህን
እንድንረዳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሃይማኖት አስፈላጊነት ሲናገር
እውነተኛ አምላክ የሆንህ አንተን ብቻ የላከውን ልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች
ናት የዘላለም ሕይወት በማለት ስለ ሃይማኖት በገለፀው መሠረት፡-ለመዳን ከማመን ቀጥሎ
ለድኅነት መሸኝና አስፈላጊ የሆኑ ምሥጢራትን መፈጸም ይገባል፡፡ እነዚህም በመጀመሪያ
ጥምቀት፤ ቀጥሎ ሜሮን እና ከዚያ ቅዱስ ቁርባን ሲሆኑ ከዚያ በኋላ በሕይወት ሂደት
ለሚገጥሙ ነገሮች ደግሞ ንስሐ ናቸው፡፡ እነዚህ ምሥጢራት የሚፈጸሙትም በቅድስት ቤተ
ክርስቲያን አማካይነት ነው፡፡ ለድኅነት መሠረታዊ የሆኑት ምሥጢራት ከቤተክርስቲያን ውጭ
አይፈጸሙም፡፡

11
ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር ሃይማኖት ብዙ ዓይነት አገላለጽና አፈጻጸም ይኖረዋል፡፡ ሲጠቃለል
ሃይማኖት የሚለው ቃል ለዓለም ፈጣሪ አለው እርሱም ሰማይና ምድርን ፈጥሬአለሁ ብሎ
የተናገረ እግዚአብሔር ነው ብሎ በፍፁም ልብ ማመን ነው፡፡ ስለሆነም ዓለም ፈጣሪ፣ ሠራዒና
መጋቢ፣ መነሻና መድረሻ የተጀመረበትና የሚፈጸምበት አለው ብሎ ማመን ዳግመኛም
ለሚሠሩት ሥራ ሁሉ ዋጋ ከፋይ መኖሩን አውቆና አምኖ መሥራት በሁሉም ሰው ዘንድ
ታምኖ ሊኖር የሚገባው ነው፡፡ ይህም “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ
እግዚአብሔር ነው፡፡” ዘዳ 6፥4 የሚለውን በማስታወስ ይህን አንድ አምላክ የማወቅ ግዴታ ነው፡
፡ ይህን አንድ አምላክ እንደሚገባ ማወቅና ማመን አንድ ነው ኤፌ 4፥4 እምነት የሚገለጽበት
ሥራ የመታመኛ መንገዱ ግን ብዙ ነው፡፡

5. እምነት ለምን አስፈለገ?


እምነት ለሰው ሕይወት መሠረት ነው ያለ እምነት መኖር የተፈጠሩበትን ዓላማ አለማወቅ
ነው፡፡ እምነት ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት፡-

5.1. ሰው ተፈጥሮውን ምንንቱን አቅሙን የሚያውቅበት የሚረዳበት ነው


ይህም ደካማነቱን ረዳት አጋዥ ጠባቂ የሚሰፈልገው መሆኑንና ያለ እግዚአብሔር
ፍቃድና ጥበቃ ምንም ምን ማድረግ እንዳይቻል የሚያውቀው የሚያስተውለው
በሃይመኖት ነው፡፡ ዮሐ.15፥5 2ኛቆሮ.3፥5 "እግዚአብሔር እሱ አምላካችን እንደሆነ
እወቁ እርሱ እንደፈጠረን እኛ ግን አይደለንም መዝ 99 ፥ 3" ሰው ማን እንደፈጠረው
ለምን እንደተፈጠረ አርያ ፈጣሪ'አምሳለ ፈጣሪ የሆነው ሰው ፈጣሪውን እግዚአብሔርን
የሚያውቅበት መንገድ ነው፡፡ “ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል የተዘጋጁ ስለዚህም
የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” እንዲል፡፡ ዕብ.11፥3
የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በምን ይመስለዋልና አርዓያ ፈጣሪ አምሳለ ፈጣሪ ተባለ ቢሉ
፡-
ሀ. በንጽሐ ጠባይ፣ በዕውቀት፡- እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በዕውቀትአክብሮ በቅድስና
ቀድሶ በንጽሐ ጠባይዕ ራሱን አስመስሎ በሥጋም በነፍስም ነፃነት ሰጥቶ ነውና፡፡
ለ. በአገዛዝ፡- እግዚአብሔር በባህይ፣ በነፍስ፣ በፍቃድ የሚገዛውን የሰው ልጅ በጸጋ፣
በሥጋ በግድ ይገዛዋልና፡፡ ይህም እግዚአብሔር ሰውን የፍጥረታት ሁሉ አክሊል አድርጎ
ሰለፈጠረው ነው፡፡
12
ሐ. በመልክ፡- እኛ የሰው ልጆች ዓይን'ጆሮ'እጅ'እግር'......... እንዳለን ሁሉ
እግዚአብሔርም ዓይን 'ጆሮ'እጅ' እግር'.....አለውና፡፡ “የእግዚአብሔር አይኖች ወደ
ፃድቃኖቹ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው”እንዲል መዝ.33፥15-16፤ መዝ.26፥8-9'32 ፥
18'118፥73'131፥7'ኢሳ 66፥1፡፡
መ. በነፍስ፡- እኛ የሰው ልጆች ልብ፣ ቃል፣ እስትፋንስ እንዳለን ሁሉ ሥላሴም
ለባውያን'ነባብያን ሕያዋን ናቸው፡፡
1. ሰው ዘለዓለማዊነቱን የሚያውቅበት ነው፡- 1ተሰ 4፥ 17 ሰው የተፈጠረው
ለዘለዓለማዊ ሕይወት ነው ከሞት በኋላ ሕይወት በትንሣኤ እንዳለው የሚያውቀው
በእምነት ነው፡፡
2. ሰው ከኃጢአት ቁራኝነት የሚላቀቅበት፡- ማቴ 8 ፥ 5 ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ
የሚሆንበት መንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያጋጥሙትን የሰይጣን ፈተናዎች ድል የሚነሳበት
ነው፡፡
3. ሰው ለእግዚአብሔር የሚታዘዘውን የጽድቅ ተግባራት ለመፈጸም ሐይልና ብርታት
የሚሆነው እምነት ነው ይኸውም የእምነት ሰዎች የእሳትን ኃይል ሲያጠፉ የአንበሶችን
አፍ ሲዘጉ ባህር ሲከፍሉ ፀሐይ ሲያቆሙ ሰማይን ሲለጉሙ ያየነው በእምነት ነው፡፡
በመሆኑም ሰው እግዚአብሔርን በእርሱ ላይ ያለው ዓላማ በትክክል ግቡን ይመታ ዘንድ
እምነት ያስፈልገዋል፡፡
4. ሰው የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆነው በእምነት ነው፡- የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ትልቅ
ስልጣን' ትልቅ ሥጦታ' ተልቅ ጸጋ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ
የሚሆንበት ትልቁ ምክንያት የመንግስቱ'የርስቱ ወራሽ መሆን ነውና ለዚህ ደግሞ
እምነት ያስፈልጋል፡፡ ዮሐ 3፥16፣ ዮሐ.1፥12፣ ሮሜ.8፥12-17፣ ገላ. 4፥1-7፣ ኤፌ.1፥5-
14 2ኛ ጢሞ.2፥11
5. ከሞተ ሥጋ፣ ከሞተ ነፍስ የሚድንበት ኃይል ስለሆነ ሰው በልቡ አምኖ በአፉ መስክሮ
ይጸድቃልና ሮሜ 10፥8 ስለዚህ እምነት ለሰው ሕይወት አስፈላጊ ነው፡፡ ሃይማኖት ሰው
ከሞተ ነፍስ ከደዌ ሥጋ የሚድንበት ድኅነተ ሥጋ ድኅነት ነፍስ ዘላለማዊ ሕይወት
የሚያገኝበት ነው፡፡"ያመነ የተጠመቀ ይድናል'ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል”
እዲል፡፡ማር.16፥16'የሐዋ. 2፥38'ያዕ. 5፥14-16'ሮሜ. 6፥22-23'መዝ. 144፥18-19”

13
6. ዘለዓለማዊ ደስታንና ክብርን የሚያስገኝ ነው "እርሱ ሳታዩት ትወዱታላችሁ አሁንም
ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ የእምነታችሁን ፈፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን
እየተቀበላችሁ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሴት ደስ ይላችኋል" 1ጴጥ 1፥8 የዚህ
አለም ደስታ አጭርና ጊዜያዊ ነው ጊዜያዊ ደስታ ደግሞ ከሃይማኖት ውጭ የሆኑ
ሰዎች የሚፈልጉትና የሚጠብቁት ነው፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ሰው ግን ተስፋ
የሚያደርገው ጊዜያዊ ደስታን ሳይሆን ዘለዓለማዊ ደስታን ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው
በእምነት ነው፡፡ "ሃይማኖት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር
የሚያስረዳ ነው፡፡"/ዕብ.11፥1 1ጴ. 1፥8-9
7. ሃይማኖት የሰው ልጅ በኑሮው በሕይወቱ ሁሉ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን ደስ
የሚያሰኝበት በዚህም እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ከገቡ መውጣት ካገኙ ማጣት
የሌለበትን ሰማያዊት መንግሥት ዘለዓለማዊት ርስት የሚወርስበት ነው፡፡

6. መንፈሳዊነት ለምን?
በሰው ሕይወት እንስሳዊ እና መላእካዊ ሁለት ተቃራኒ ባሕርያት አሉ በእንስሳዊ ባሕሪው
ይርበዋል ይበላል፤ ይጠማዋል ይጠጣል፤ ይታመማል፣ ይሞታል፣ ይፈርሳል ይበሰብሳል፡፡
በመላእካዊ ባሕሪው ደግሞ ምግበ ነፍስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ይመገባል፣ ይዘምራል፣
ይቀድሳል እግዚአብሔርን ያመሰግናል መላእክት ሕያዋን ናቸው ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ነገር
ግን እንዚህ ሁለቱ በጣም ተቃራኒ ናቸው ሥጋ(እንስሳዊ ባሕርይው) ልብላ ስትል
ነፍስ(መላእካዊ ባሕሪው) የዘላለም ሕይወትን እያሰበች ልፁም ትላለች ስለዚህ እነዚህ ሁለት
ተቃራኒ የሆኑ የሰውልጅ ባሕሪያትን አጣጥሙ ለመኖር መንፈሳዊ/ክርስቲያን/ መሆን
ያስፈልጋል፡፡

መንፈሳዊ ሰው እንደ እንስሳ ሥጋዊ ስሜቱ የሚለውን ብቻ አይፈጽምም፤ እንደ መላእክትም


ፍፁም መሆን አይችልም ነገር ግን ሁለቱን አጣጥሞ የመኖር ግዴት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ
ከጌታችን መድኃኒታችን ጀምሮ ብዙ ቅዱሳን ዋኖች አሉንና ከሕይወታቸው ፍሬ እየተማርን
መልካሙን ገድል እየተጋደልን ሩጫችንን በመልካም እንድንጨርስ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ መንፈሳዊነት ማለት ሥጋንና ነፍስን አስማምቶ ሁለቱን ለፈጠራቸው ለእግዚአብሔር


በማስገዛት ሕግጋቱን ጠብቆ ለዘለዓለማዊው መንግስት የሚያበቃ ሥራን ለመስራት መትጋት

14
መጋደል ነው፡፡ የሰው ልጅ ፍጡርነቱንና ዘላለማዊነቱን ካሰበ ሁል ጊዜ በትህትና ይህንን ዓለም
ለማሸነፍ የሚተጋበትን ጥበብ ይፈልጋል ይህ ጥበብ ደግሞ መንፈሳዊነት ነው፡፡

በአጠቃላይ መንፈሳዊነት ሰው ዘለዓለማዊነቱን ተረድቶ ይህንን ዓለም፣ ሥጋንና ባላጋራችን


ዲያቢሎስን በጥበብ መንፈሳዊ አሸንፎ ዘላለማዊት ርስቱን ለመውረስ የሚያበቃን ተጋድሎ
የምንጀምርበትን ብርታት መያዝ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰው የተፈጠረበት አላማ ማለት
ነውና ሁላችንም ልንኖርበት የሚገባ ሕይወት ነው፡፡

6.1. የሃይማኖት ሰው መገለጫዎች


ከጌታና ከሐዋርያት በተማርነው መሠረት እምነት አለን የምንል ክርሲቲያኖች እምነታችን
በሚከተሉት ተግባሮች ሊገለጥ ይገባዋል እነሱም፡-

1. ዘወትር በመጸለይ፡- የእምነት ሰው ሃይማኖቱ ኃይል እንዳለው ሥራ መሥራት


እምደሚችል ከፈተና ማውጣት እንደሚችል ማመንና መጸለይ ይጠበቅበታል፡፡ ማር.16፥
16
2. መልካም ተግባራትን ማከናወን፡- ሰው እምነቱን መግለጽና እውነቱን ማረጋጋጥ
የሚችለው በበጎ ሥነ-ምግባር ነው “የሰው ልብ መንገዱን ያዘጋጃል እግዚአብሔር ግን
አካሄዱን ያቀናታል” ምሳ. 16፥9
3. ከክፉ ተግባራት መራቅ፡- ሰው በእምነት ሲኖር ማንነቱ የሚያረጋግጠው እና
የእግዚአብሔር መሆኑ የሚታወቀው መልካም የሆኑ ተግባራትን በማከናወኑ ብቻ
ሳይሆን ከክፉ ተግባራት በመራቁም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በጣም
ክፉና መጥፎ ናቸው ያልናቸው ሰዎች አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት በአጋጣሚ መልካም
ተግባራትን ሲያከናውኑ ይታያሉ ስለዚህ እነዚህን የሃይማኖት ሰዎች ናቸው ማለት
አይቻልም፡፡ ነገር ግን ከክፉ በመሸሽ መልካም ተግባራትን መሥራት ሲችሉ
የሃይማኖት ሰዎች መሆናቸው በዚህ ይታወቃል፡፡ “አንደበትህን ከክፉ ከልክል
ከንፈሮችህንም ሽንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ” መዝ 33፥14 ማቴ
5፥16
4. በእግዚአብሔር ቃል ይመራል፡- ምንም እንኳን ቢሆን ሳይጠራጠር ለእግዚአብሔር ክብር
እየሰጠ በተስፋ ይኖራል፡፡ ሮሜ. 4፥16 ዕብ. 11

15
የእምነት ሰው የሚመላለስባቸው መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖት ሰው እንዴት
መመላለስ እንዳለበት በምልአትና በስፋ ይገለጻል ይኸውም ሰው በእምነት ሲኖር ሊጓዝባቸው
የሚገቡ መንገዶችን ማወቅና መፈፀም እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡

እነዚህም፡-

1. በብርህን መመላለስና የጨለማ ክፉ ተግባራት ማራቅ ብርሃን ሲባል መልካም ስራ


ማለት ነው በብርሃን መመላለስ ማለትም በእግዚአብሔር ፍጹም ማመን ማለት ነው
በአንጻሩ ከጨለማ መራቅ ሲባል ከክፉ ተግባራት መራቅ፤ ዲያቢሎስን መቃወም
ማለት ነው፡፡ 1ዮሐ. 1፥7
2. በፍቅር መመላለስ ፍቅር በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉት የሃይማኖት ሰው የሚያምነው
እግዚአብሔርን ነው እግዚአብሔር ደግሞ ፍቅር ነው ኤፌ.5፥2 1 ዮሐ. 4፥1
3. በጥበብ መመላላስ እንደ እባብ ልባሞች እንደ እርግብ የዋሆች ሁኑ ብሎ
እዳስተማረን በሃይማት የሚኖር ሰው ማስተዋልን ብልህነትን ገንዘብ ማድረግ አለበት
አርቆ የሚያይና በጥበብ ኅጢአትን ከጽድቅ የሚለይ በማስታዋል የሚራመድ ነው፡፡
ቆላ.4፥5
4. በመንፈስ ቅዱስ መመላለስ መንፈሳዊ ተግባራትን ማከናወን ከሥጋ ፈቃድ በመራቅ
የሥጋ ክፉ ተግባራት በማራቅና በመናቅ መኖር ገላ.5፥5
5. በመልካም ስራ መመላለስ በመንፈሳዊ ሕይወት ተግባራት አሉ እነሱም ጾም
ምጽዋት ናቸው፡፡
6. በእምነት መመላለስ ሀሰትን መናቅና ከሐሰት መራቅ
7. በጥንቃቄ መመላለስ፡-ምክንያቱም በሰው ጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ የሚመጡ
ጉድለቶች በጣም ከባድናቸው ስለዚህ የእምነት ሰው በጥንቃቄ መመላላስ
ይጠበቅበታል፡፡ይህም ማለት ክፉ ከማድረግ ከማየት ከመስማት ማለት ነው፡፡

7. የክርስትና ሃይማኖት ምንነትና መገለጫዎቹ


የክርስትና ሃይማኖት ከቀደሙት አበው እምነት ይለያል፡፡ አበው አንድ እግዚአብሔር ብለው
የሚያምኑ ቢሆኑም በገጽም አንድ ይሉ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ግን “…..ስታጠምቋቸውም በአብ
በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በሉ” ማቴ. 28፥18 ከሚለው የጌታችን ትእዛዝ

16
እንደምንመለከተው አንድ እግዚአብሔር በስም በአካላት በግብር ሦስት የሚሉ ስለሆነ
ከቀደሙት ይለያሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የሚለይ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የእነርሱ አማላክ ሊባል
የማያፍርባቸው ወዳጆቹ ብዙ ናቸው፡፡ ይሁን አንጂ በሰዎች ውስጥ ያለው መታመን
ስለሚለያይ ሰው የሚያፈራው የሃይማኖት ፍሬም ይለያያል፡፡ ጌታችን በወንጌል “እንዲህ ያለ
ታላቅ እምነት በእስራኤል ስንኳን አላገኘሁም” ማቴ.8፥10 ሲል ማመስገኑ በመታመናችን መጠን
እምነታችን እንደሚወሰን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ የክርስቲያኖች እምነት፡-

1. በሥራ የሚገለጥ ነው፡- ማመናቸውን በመታመን ይገልጹታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ


ከተሰበከና በልቦናው እውን ሆኗል ተደርጓል ብሎ ካመነ በኋላ “እንዳልጠመቅ
የሚከለክለኝ ምንድነው ማለቱ አምኖ አለመቅረቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ ወዲያውኑ ታምኖ
ተጠምቋልና፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ አምነው የሚቀሩ አይደሉም ታምነው በሥራ
ይፈጽሙታል እንጂ፡፡ በጥንት ተፈጥሮም ሆነ በኋላ በሐዲስ ተፈጥሮ የተፈጠርነው
በሃይማኖት መልካም ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ እየሱስ ተፈጠርን፡፡” /ኤፌ.2፥10/
እምነትም ከሥራ ከተለየ የሞት ነው ያፅ.2፥20እንዲል ፡፡
2. ተስፋ ያለው ነው፡- ያለ ተስፋ መኖርም አይቻልም፤ ማመንም አይቻልም፡፡ይሁን እነጂ
ተስፋ ማለት እርግጠኛ የሚሆን ነገር ግን ጊዜው ያልደረሰለትና የሚጠበቅ ማለት እንጂ
ላይሆን የሚችል በጥርጣሬ (Probability) ያለ ማለት አይደለም፡፡ በተስፋ
እግዚአብሔርን አምነው ደስ ያሠኙትን እግዚአብሔር አይረሳቸውም፡፡ ለዚህም ነው
ቅዱስ ጰውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ላይ የዘረዘረው፡፡ “ ሃይማኖት ተስፋ
ለሚያደርጋት ሰው ዋጋ በመስጠት የተረዳች ናት ቀድሞም የማይታየውን የማያልፈ
መንግሥተ ሰማያት ገንዘብ በማድረግ ጸንተው የሚኖሩ ነበሩ፡፡” /ዕብ.11፥1/ በማለት
ቀድመው አምነው በተስፋ የጸኑትንና ስለ መንግሥት ሰማያትም መከራ የተቀበሉትን
ቅዱሳን ይዘረዝራል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያክል ብንመለከት፡-
 የአቤል እምነት፡- የእግዚአብሔርን ንጽሐ ጠባይዕ በፍጹም በማመን የነበረና
የሚሰጠውን መልስ ገለጠ እግዚአብሔርን መሥዋቱን በመቀበል መሰከረለት፡፡
”ሞቶም ሳለ እስካሁን በመሥዋዕቱ ይናገራል፡፡” ያለለት ለዚህ ነው፡፡
 ሄኖክ፡- የደጉን የአቤልን መሞት አይቶ “ደግ መሆን ይገድላል” ቢል የሞኝ ብሂል
ሳይደናገርና ሞት በአቤል ብቻ በታወቀበት ተስፋውን ሰንቆ በሕግ በአምልኮት
እግዚአብሔር በመጽናቱ አምላኩም ወደ ብሔረ ሕያዋን በመውሰድ እምነቱን
17
መሰከረለት፡፡እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው ግን ወደ ብሔረ ሕያዋን ሳይወሰድ መሆኑ
ሊስተዋል ይገባል፡፡
 አብራሃም፡- ሊቀበለው ያለውን ሥፍራ ከነዓንን አያውቀውም ግን አልተጠራጠረም፤
አምኖና ተስፋ አድርጎ ሄደ፡፡ ሁለተኛም እርሱ ዘር ካቋረጠ ሚስቱም ደሟ ከደረቀ
ቡኋላ ወንድ ልጅ ትወልዳላችሁ ሲለው እግዚአብሔርን ያለ ማመንታት ተቀበለ፡
ተስፋ አድርጎም በእምነት የሣራን ማህጸን የራሡንም ሥጋ ተመለከተ፡፡ ሮሜ.4፥17-
22 ሦስተኛውም ተስፋ የተነገረለትን ልጁን ይስሐቅን መስዋዕት አድርገህ አቅርብ
ሲባል አብርሃም “ከሞት እንኳን ሊያስነሣው ይቻለዋል” ብሎ ተስፋ ሳፈጸም
እንደማይቀር አመነ ተስፋም አደረገ፡፡
 ሣራም፡- ደሜ ደርቋል፣ ልምላሜዬ ጠፍቷል ሳትል በእምነት ዘርን ለመጸነስ
ኃይልን አገኘች፡፡ ቁ.11-12፡፡
 የሙሴም፡- ከእርሱም በኋላ ያሉት አበው እምነት የጠነከረው በተስፋ ሩቅን
በመመልከት ነው፡፡ “ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ
የሚበልጥ ባለጠግነት መሆኑን አስቧልና…ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና፡፡
ቁ.23-22 እንዲ ፡፡ ይህን ተስፋቸውን ነበር ቅዱስ ጳውሎስ ከ ቁ.13-16 የገለጸው፡፡
“እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ የተሰጣቸውን ተስፋ ቃል አላገኙምና ዳሩ ግን ከሩቅ
ሆነው ተሳለሙት በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ፡፡ ያን
የወጡበትን አገር አስበው ቢሆን ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፡አሁን ግን
ሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ ነገር ያናፍቃሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው
ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና” በማለት
ገልጠውታል፡፡

አበውን ያስደነቀው ጌታ ገና በሥጋ ሳይገለጥ ነፍሳትም ወደ ገነት ሳይመለሱ በተስፋ


አምነው ሥራ መሥራታቸው ነው፡፡ ታድያ ገና በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት ተስፋቸው
የላቀ ሆኖ በእምነት ሥራ መሥራት ከቻሉ እኛ ክርስቲያኖች ራሱ በአካል አስተምሮ
የተስፋውንም “ሥፍራ አዘጋጀላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና….እኔ ባለሁበት እናንተ ደሞ
እድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ፡፡” .ዮሐ.14፥1-4 በማለት
ነግሮን ሳለ ተስፋውን ተቀብለን የማናምን ከሆንን ምን ብልጫ አለን፡፡ “የእግዚአብሔር
ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁ የተስፋ ቃል እድታገኙ መጽናት ይገባችኋል፡፡” ዕብ.
18
10፥36 በማት ጽፎልናልና፡፡ ስለዚህ የክርስቲያኖች እምነት ተስፋ ያለው እንደሚሆን
እርግጠኖች በመሆንና ጊዜን በመጠበቅ የሚኖሩት ተስፋ ህይወት ነው፡፡

3. የፍቅር ህይወት ነው፡- የክርስቲያኖች እምነት ወንጌልን መቀበል ነው፡፡ ወንጌል


ደግሞ ከኦሪት ትበልጣለች፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ በሁለት ምሳሌ አቅርቦታል፡፡

1ኛ. በይስሐቀ በረከት፡- “ይስሐቅ ሊመጣ ስላለው ነገር ያፅቆብና ዔሳውን በእምነት
ባረካቸው፡፡” ዕብ. 11፥20 ይላል፡፡ ፤ በሮሜ.9፥10-3 ላይም “…ይህ ብቻ አይደለም፤ ነገር
ግን ርብቃ ደግሞ ከአንዱ ከአባታችን ከይስሐቅ በጸነሰች ጊዜ ፥ ልጆች ገና ሳይወለዱ ፤
በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ፤ከጠሪው እንጂ ከስራ ሳይሆኑ በምርጫ የሚሆን
የእግዚአብሔር ሀሳብ ይጸና ዘንድ፤ ለእርሷ ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት፡፡ ያዕቆብን
ወደድሁ ዔሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ “ስለ አንድ መብል በኩርንቱን
መነጠቁ፡፡” በማለት ገልጦታል፡፡ እነዚህን ታሪኮች በዘፍ 25፥21-34 እና በዘፍ 27፥27-
29 እናገኛችዋለን ይሁን እንጂ ታሪኩን ባጭሩ አሥቀምጠን ወደ ምሥጢሩ እንሄዳን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ገና ሳይወለዱ እግዚአብሔር ያቆብን መርጧል፡፡ ይህም


አድሎዎ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የነገረን ፍጻሜውን ከመጀመሩ በፊት የሚያውቀው
በመሆኑ፡ ከመወለዳቸው በፊት ያዕቆብ ምን አይነት ሰው እንደ ሆነ ዔሳውም ምን
እንደሚሆን ያውቅ ነበር፡፡ “ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ካወቀ” 1 ኛጴጥ 1፥21 እንዲል
ርብቃ ግን ጽንሱ በማህጸኗ ይነዋወጥባት ስለነበር በጊዜው “መካነ ዕራይ” ወደሚባለው
ስትሂድ ቦታው መልከ ጼዲቅ የሚኖርበት ስለነበር እግዚአብሔር በአፈ መልከ ጼዲቅ
ታላቅ ለታናሹ እንደሚገዛ ነግሯት ነበር፡፡

እግዚአብሔር “ያዕቆብን ወደድሁ” ማለቱም ሕገ ነፍስን /ብኩርና ምሳሌዋ ነበረችና/ ስለ


መምረጡ “ዔሳውን ጠላሁ” ማለቱም የዔሳውን ለሕገ ሥጋ ማድላቱን ማወቁን
ለመናገር ነው፡፡ ዔሳው ከአደገ በኋላ ዔሳው ለቤተሰቦቹ የማይታዘዝ ያዕቆብ ግን
የሚታዘዝ ፈቃዳቸውንም የሚፈጽን ነበር፡፡ አባታቸው አርጅቶ እመረቃለው ባለ ጊዜም
ርብቃ ለያቆብ ምክር መምከሯ ታዛዥ በመሆኑና እግዚአብሔርም የመረጠው እንደ ሆነ
ስለምታውቅ ነው፡፡ ያዕቆብም በእናቱ ምክር መሰረት በመጠቀሙ ሥራው ሠመረለት
አባቱም ፍጹም በረከትን ሰጠው፡፡

19
ይህቺ ቀን በዘመነ አበው ትውፊት አባት ከመሞቱ በፊት ልጆቹን የሚባርክበት
የተለየች እለት ናት፡፡ ከዚህ በኋላ ያዕቆብን ዔሳው እንዳይገድለው ጠፋ ከብዙ ዘመንም
በኋላ በእናት እና አባታቸው ምክር መሠረት ዔሳው ያዕቆብን በአንድ ቀን ተዘርተን
“በአንድ ቀን የታጨድን ነን፡፡” ከታረቀ በኋላ ግን ልጆቹ ቀድሞ አላግባብ ጨጥክ አሁን
ደሞ የማይሆን ዕርቅ ታርቀህ ብለው በመቆጣት ሰይፍ አንሥተው አባታቸውን መንገድ
መሪ አድርገው ያዕቆብን ለመዋጋት ሄዱ፡፡ የአከባቢው ሰዎችም ያዕቆብን ይወዱ ነበርና
ወንድሙ ጦር አሳልፎ መምጣቱን በነገሩት ጊዜ ሁለት መቶ ቤተሰቦች ይዘው አራት
በር ባላት ቤት ሃምሳ ሃምሳውን በእያንዳንዱ ገጽ አሠልፎ ጠበቀው፡፡ ይሁዳ ባለበት
በር በኩል ዔሳው ልቡ ለቀስት ተመጭቶ ታየው፡፡ በማለት አነጣጥሮ ለአባቱ ሰጠው፡፡
ያዕቆብም ዔሳውን ገደለ ጦሩም ተበተነ፡፡ ከዚህ በኋላ የዔሳውን ዘሮች ሲያገብሯው
ኑረዋል፡፡ ታሪካቸውም እንዲህ ይደመደማል፡፡ ኩፋ.26፥47-48፡፡ አስቀድሞ
የተመለከተው ታዲያ ምንድን ነው ከታሪኩስ ያለው ምሥጥር በመጀመሪያ ያዕቆብ
የዔሳውን ብኩርና መግባቱ በእስራዔል አሕዛብ የመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ዔሳው
የእስራኤል የዕቆብም የህዝብ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በኋላም ያዕቆብ ፍጹሙን በረከት
ከአባቱ መቀበል ለሕገ ነፍስ የሚያደላ በመሆኑ ወልደ እግዚአብሔር ከእርሱ ልጆች
ሰው ይሆን ዘንድ አስቀድሞ እግዚአብሔር ግብሩን አውቆ የመረጠው ስለሆነ ነው፡፡
ሁለተኛው ደሞ ያዕቆብ የጌታ ከያዕቆብ ጋር ያሉት የምእመናን ዔሳው የዲያቢሎስ
ከዔሳው ጋር ያሉ የአጋንንት የመስቀል ቀስት የሥልጣነ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው፡፡
በድጋሚ ያዕቆብ የታላቁ ሊቅ የቄርሎስ ከእርሱ ጋር ያሉ ሁለት መቶ ሰዎች የሁለት
መቶው ኤጲስ ቆጶሳት'ዔሳው የንስጥሮስ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ዳግመኛም ታላቁ ለታናሹ ይገዛል የሚለው ከያዕቆብ ቤት ከይሁዱ ወገን የሚወለደው


ጌታ ንጉሠ ሰማያት ወምድር ስለሆነ ሁሉንም የሚገዛ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ
ጳውሎስ ይህን ታሪክ በሚስጥር ያመጣው የወንጌል በረከት የተቀበለው ያዕቆብ ከዔሳው
የበለጠው በተቀበለው በረከተ ወንጌል ነው፡፡ ይህም የወንጌልን ታላቅነት አስቀድሞ
ይስሐቅ አውቆታል ለማለት አምጥቶታል፡፡

2ኛ ያዕቆብ በረከት፡- “ያዕቆብ ሲሞት በእምነት የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን


ባረካቸው” ዕብ 11፥21 ታሪኩ ዘፍ.48÷15 ላይ ተገልጿል፡፡ ያዕቆብ እጆቹን አመሳቅሎ

20
የባረካቸው ወንጌል ተገልጦለት አስቀድሞ አይቶ በሚበልጠው የመስቀል በረከት
ሲባርካቸው ነው፡፡

እነዚህን ሁለት ማስረጃዎች አስርጅ አድርገን የጠቀስነው ኦሪት ከመመስረቷ በፊት በተስፋ
የጸኑትንና ስለ መንግሥት ሰማያትም መከራ የተቀበሉ ቅዱሳን እንደነበሩ ለማሳየት ያክል ነው፡

8. የክርስቲያናዊ ስብእና መገለጫዎች


ክርስቲያናዊ ስብእናን ውጫዊና ውስጣዊ ብለን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

1. ውስጣዊ ስብእና/ተግባር/

ውስጣዊ ተግባር ማለት በሥጋና በመንፈስ መካከል ከውስጥ የመነጨ መልካምም ይሁን
መጥፎ ስሜት ያስገኘው ሀሳብ ማለት ነው ይህ ሀሳብ ቁርጥ ሀልዮና ነቅዓ ሀልዮ በመባል
በሊቃውንቱ ዘንድ ይታወቃል፡፡ ይህ ሐሳብ እንደ ይዘቱ መጥፎ ከሆነ ያስቀጣል፤ መልካም
ከሆነም ያሸልማል፡፡ ይህን ውስጣዊ ስሜትን ምክንያት በማድረግ በሥጋዊና መንፈሳዊ ሐሳብ
መካከል ጣልቃ እየገቡ ዓላማን ለማስቀየር የሚጥሩ ኃይሎች ብዙዎች ናቸው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ "እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ
እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ፡፡ በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፡፡ ነገር
ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ ኃጢአት የሚማርከኝን ሌላ
ሕግ አያለሁ፡፡" ሮሜ 7÷21 በማለት በስብዕና ውስጥ ታላቅ ውጊያ መኖሩን ከራሱ ተሞክሮ
በመነሳት ሰዎች ያውቁት ዘንድ ለሮሜ ሰዎች አስገንዝቦአል፡፡

ስለዚህ የመልካም ሥራ ዋጋ የሚገኘው በዓለምና በመሰሎቿ የሚመጣውን ልዩ ልዩ ፈተናና


መከራ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው በትዕግሥትና በፍቅር በመጽናት ነውና ማቴ 24÷13 ይህን
መጥፎ ስሜት አስወግዶ በመንፈሳዊ ስሜት መቀየርና ሥጋዊ ወይም ጊዜያዊ እንዲሁም
ሰይጣናዊ የሆነውን ሁሉ ዘለቄታ ባለው ሐሳብ ቀይሮ በመልካም መኖር ከአንድ ክርስቲያን
ይጠበቃል፡፡ ከቅዱሳት መጽሐፍት ይዘት በመነሳት ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በድጓ ዘአስተምሕሮ
"ተዐገሡ ወአፅንኡ ልበክሙ" "በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ በርቱ ልባችሁም ይጥና"
መዝ 30÷24 "ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፡፡" ኤፌ 4÷26 "አትታበዩ በኩራትም አትናገሩ
እግዚአብሔር አዋቂ ነውና እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና ከአፋችሁ የኩራት ነገር

21
አይውጣ" 1ኛሳሙ2÷ 3 እየጠቀሰ ቻሉ ልባችሁንም አጽኑ ክፉ ንግግር ከአንደበታችሁ
አይውጣ፡፡ ፀሐይ ሳይወጣም ቁጣችሁን አብርዱ የምትሠሩትን ሁሉ የይቅርታ አምላክ
በሚመሰገንበት መልኩ አድርጉ ብሏል፡፡

ሥራ ሁሉ መጥፎ ስሜትን በዝምታ ገትቶ ቁጣን አብርዶ አንደበትን አለዝቦ ለሰው ሳይሆን
እግዚአብሔርን ደስ ያስኛል ተብሎ ከተሠራ እንደ አቤል መሥዋዕት ዋጋን ያሰጣልና በቀልን
በመተው ሊሠሩት ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያን ከአረማውያን የሚለዩበትም ለዘላለም ይኖሩ ዘንድ
በቀልና ፍርድን ለእርሱ ትተው ለክፉዎቹ ሁሉ መልካም በማድረጋቸው ነው፡፡

2. ውጫዊ ስብእና/ተግባር/

ውጫዊ ተግባር የሚባለው ዓይን የሚያያቸው፤ ጆሮ የሚሰማቸው፤ ቀልብ የሚገዙ ስሜቶች


ስሕበት ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ድርጊት የባሕርይ ገንዘብ ያልሆኑና ከሥጋ ፍላጎት
ያልተገኙ የድርጊት ሰንሰለቶች ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን እኚህ ነገሮች ሥጋዊ ስሜትን መሠረት
እያደረጉ የሚሠሩና እየቆዩም በልቡና ውስጥ ማረፊያ ከተሰጣቸው ስሜትን እየተቆጣጠሩ
አእምሮን ወደ ተግባር የመመለስ ዓቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ሰው ምድራዊ ፍጡር ከመሆኑ
አንፃር ከሌላም ሆነ ከራስ ሊቀበለውና ላይቀበለው የሚገባው ሐሳብና ምክር ይመጣበታልና
በዚህ ጊዜያዊ ነጸብራቅ ሳይሳብ፤ ሳይታለልና ሳይደለል መልካም የሆነውን መሥራት ለማንም
ግድ ነው፡፡ ሰውም ከእንስሳት የሚለየው በእየጊዜው እንደየሁኔታው የሚከሠተውን መጥፎ
ሐሳብ ከመልካሙ ለይቶ በማወቅ ረገድ ባለው ግንዛቤው ነው፡፡ "ልጄ ሆይ ኃጢአተኞች
ቢያባብሉህ እሺ አትበል" ምሳ 1÷10 ልጄ ሆይ የሃይማኖትን ሥራ የምታሥረሳ ክፉ ምክር
አትሰልጥንብህ፤ ልጄ ሆይ የወጣትነትን ሥራ ናቃትና የጽድቅን ሥራ ተከተላት፤
በእግዚአብሔር ፊት ክፋትን አታድርግ፤ መልካምን አስብ፤ የልብህን ምኞት ይሰጥሃልና በእርሱ
ታመን፤ እርሱም ይፈጽምልሃል፤ ይሞላልሃል እንዳለ ሊቁ ያሬድ /ድጓ ዘአስተምሕሮ/ መጥፎ
መካሪ ካለ መልካም ሥራ መሥራት በሠሩት ሥራ የህሊና እርካታ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ
ነውና ሊቁ ያሬድ ከዳዊት ቃል በመነሳት፡- "ከክፉ ሽሽ መልካምን አድርግ፤ ለዘለአለምም
ትኖራለህ፤ መልካም እናገኝ ዘንድ ክፉ አናድርግ የሚሉ አሉና በጎስቋሎች ምክር አትሂድ፤
ሰላምንም ፈልጋት፤ ልጄ ሆይ ተው ልብህን መልስ፤" ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ኑሮ
ሁሉ የከንቱ ከንቱ ነው ያለውን የመክብብ ቃል ሰምተህ ጠብቅ ይላል፡፡ ለራሳቸው ጥበበኞች
እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች ምክር ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ከዓለም ከንቱነት የከፋ
22
ነው፡፡ በጥንት ዘመን "ኑ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ" መዝ 37÷8 ተብሎ
እንደተፃፈ ሁሉ በአሁኑ ዘመንም ቢሆን ክፉ መሥራት ዘመናዊነትና ምርታማነት መልካም
እየሰሩ እግዚአብሔርን ማገልገል ኋላ ቀርነት እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አሉና
እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳኑ ላይ ባሳደረው መንፈሱ ለዚህ ዓለም ጥበበኞች ሞኝነት
የመሰላቸውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በጠቢቡ ሰሎሞን አንደበት "ልጄ ሆይ የአባትህንተግሳጽ
አታቃልል እግዚአብሔርም የወደደውን ይገስፃልና" ምሳ 3 ÷ 11 በማለት ከገንዘብ ይልቅ
እውነትን የመረጠ በሰማይ አዳራሽ የተመረጠ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡ ከነዚህ ዓይነት ሰዎች
መራቅ እንዳለብን ጌታም በወንጌል "አባታችሁ አንዱ እርሱ የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም
አባት ብላችሁ አትጥሩ" ማቴ 23÷9 ብሏል፡፡

ስለዚህ የአንድ ክርስቲያን ውስጣዊ እና ውጫዊ ስብእናዎቹ የሥነ ምግባር መርሆች በሆኑት
ፍቅር፤ ሰላምና ትህትና የተዋቡ ሊሆን ይገባዋል፡፡

1. ፍቅር

"ፍቅር የሕግ ሁሉ ፍፃሜ ነው፡፡" ሮሜ 13÷10 ፍቅር በባልንጀራ ላይ ክፉ አያደርግም፤ ፍቅር


እግዚአብሔር በሰው ልቦና የሳለውና የቀረጸው ፀጋ ነው፡፡ ፍቅር እራሱ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ተፋቀሩ ብሎ ያዘዘም እራሱ ነው፡፡ እርሱ እንዳዘዘን እንፋቀር ጽድቅን
የሠራ ሁሉ ጻድቅ ነውና ፈጽሞ ሲወደን ጌታ፤ ሎሌ፤ ሴት፤ ወንድ፤ አይሁዳዊ፤ አረማዊ
አላለም ዝማሬ ገጽ 77 ስለዚህ ጥቅምን መሠረት ሳያደርግ ባልንጀራውን የሚወድ ምስጉን
ነው እንዲህ አይነት ፍቅር ከእግዚአብሔር የታዘዘ ነውና፡፡

ፍቅር ኃጢአትን ይሸፍናል፤ በሰውና በሰው መካከል ያሉ ክፉ ሥራዎች ሁሉ ተሸፍነው


የሚኖሩት በፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር የአለምህ ኃጢአት የሚታገሥ ፍቅር ነው፡፡
የፍቅር ማሳያዎች እግዚአብሔርና እናት ብቻ ናቸው፡፡ በክርስቲያናዊ የሕይወት መንገድ ላይ
ቆሞ ከእግዚአብሔር ፍቅር በመውጣት አልጫውን ዓለም በመምሰል ወደ ኋላ መመለስ
ከጣፈጠው ጨውነት ወጥቶ ወደ ውጭ ተጥሎ ለመረገጥ ወደሚበቃ ድንጋይነት የመቀየር
ያህል ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የሰዎችን ኃጢአት እስከመታገስ የደረሰ ፍቅር ሊኖረው
ይገባል፡፡ በአገልግሎታችን ፍቅር ሊኖረን ይገባል የቱንም ያህል ብንደክም የሕግ ሁሉ ፍፃሜ
የሆነው ፍቅር ከሌለን ከንቱ ነው፡፡ 1ቆሮ 13÷1-3

23
2. ሰላም

ሰላም በሰዎች ልቦና ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ህብረትና እስከ ፍፃሜ ድረስ ያለውን
ግንኙነት በዚህ የተነሳ የሚገኘውን መረጋጋት ያመለክታል፡፡ ሰላም የማንኛውም መልካም ነገር
መግቢያ በር ነው፡፡ ስለዚህ ሰላም ከሌለ በመልካም ፈንታ ክፉ መልስ እየጸና ይሄዳል እንጂ
መልካም ሥራ ሊኖር አይችልም፡፡ ማንኛውም ሰው ያለ ሰላም የጠየቀውን ማግኘት መውያየት
ወዘተ አይችልም፡፡

ሰላም የሕይወት ዋልታና ዋስትና በመሆኑ ሰው ከመሰሉ ጋር ይቅርና ሰውንና እንስሳን


ያስማማል፡፡ "ስለዚህ ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ፡፡ ትቀድሱ ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ
ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና" በማለት ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡ ዕብ 12÷1 ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲሁ የማንኛውም ሥራ መጀመሪያ ሰላም በመሆኑ
ለደቀመዛሙርቱ "በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ ወደ ሳምራዊያን ሀገርም አትግቡ ወደ ቤት ቤትም
ገብታችሁ መጀመሪያ ሰላም ለዚህ ቤት በሉ፤ በዚያ ሰላማዊ ው ቢኖር ሰላማችሁ
ይድረሰው"ማቴ 10÷5 በማለት የሰላምን ጥቅም አስረድቶናል፡፡ እንዲሁም ሰላም ለእናንተ
ይሁን ብሎ እውነተኛ ሰላም ለደቀመዛሙርቱ በማደሉ የእርሱ የሆኑት ሁሉ ሰላምን ለማደል
የተጉ ሆነዋልና ስለዚህ ሰላም፡- በሰላም ባለቤት በኩል ለቅዱሳን በቅዱሳን በኩል ለፈላጊዎቿ
ትሰጣለች፡፡ ከእግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ያሉ ክፉ አድራጊዎች ግን ፈጥነው እስካልተመለሱ
ድረስ ውስጣዊ ሰላም የላቸውምና በአፋቸው ቢናገሯት በልባቸው ቢመኗትም እርሷን ማግኘትና
መንፈሳቸውን ማደስ አይችሉም፡፡ ኢሳ 57÷21

ጥልንና የመለያየትን ግድግዳ በመስቀሉ አፍርሶ የራቁትን የሚያቀርብ የቀረቡትን በቅርበት


የሚያጸና ሰላም እርሱ ብቻ ነውና ከእውነተኛው ሰላም ከእርሱ በመራቅ ፍላጎትን ሟሟላት
በተለያየ መንገድ የደፈረሰውን የሰላም ወንዝ ማጥራት አይቻልም ለዚህም ኢሳ 48÷
17"የብዙዎች ነፍስ ታዳጊ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላልና እኔ የምነግርህን ነገር
የማስተምርህ በምትሄድበት መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ ትዛዜን ብትሰማ
ኖሮ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባህር ሞገድ በሆነ ነበር ዘርህም እንደ አሸዋ
የሆድህም ትውልድ እንደ ትቢያ በሆነ ነበር"

24
ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የሰው ሕይወት መሰረት የሆነውን ሰላም መጠበቅ፤ ለሰዎች ማሰብ
ከሰውምይሁን ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ተግሳጽና ቅጣት ለመቀበል ከልቡና ገርነት
በመነጨ ፍላጎት መዘጋጀት፤ በሰዎቸች አነሳሽነት የሚመጣውን የመጥፎ ሐሳብ ምክር
መቋቋም፤ ከሁሉም በፊት ረስንሰላም አድርጎ ሰዎች ሁሉ ሰላማውያን እንዲሆኑ መጸለይ
ይኖርበታል፡፡ ማቴ 5÷45

3. ትሕትና

ትህትና በትዕቢት ያለ ልቡና ከትዕቢቱ የአንገት ማጎንበስ የሚያሳይበት ትርኢት የሚያሳይበት


ሳይሆን ከትዕቢትና ከትዕቢተኞች የሚለይ የልቡና መሰበሪያ ኃይል ነው በተጨማሪም ትህትና
በሰው አማካኝነት ለአምላክ በመገዛት ለመንግሥተ ሰማያት ያለንን ፍላጎት ማመንጫ ነው፡፡
በአጠቃላይ ትሕትና የአምላክን ልቡና የምንገዛበት ልዩ ገንዘብ ነው፡፡ ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ
"አሕዛብ አለቆቻቸው እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ ለእናንተ ግን እንደነርሱ አይደለም የሰው
ልጅ ሊያገለግል እንጂ ሊያገለግሉት አልመጣምና ማንም ከእናንተ የበላይ ሊሆን የሚወድ
የእናንተ አገልጋይ ይሁን፡፡" ማቴ 20÷25 "እኔ ጌታችሁ ሳለሁ አርአያዬን እሰጣችሁ ዘንድ
እግራችሁን አጠብኩ፤ እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ፡፡ እኔ ካደረግኩት የበለጠ
የበለጠ እናንተ ባደረጋችሁት እደሰታለሁ፤ ሰላሜንም እተውላችኋለሁ፡፡" ድጓ ዘትንሣኤ/ ዮሐ
13 ÷ 13 ሲያውቁ መተው የዋህነትን የተላበሰ ጠቢብነት ነውና ማንም ሰው በዚህ ዓለም ላይ
ሲኖር እንደ እባብ ጠቢብና እን ርግብ የዋህ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ዝቅተኛ ከሆኑት ፍጥረታት
ወፍን አለመርሳቱን ማውሳቱ እግዚአብሔር አምላክ የትሑታን አለኝታ በመሆኑ ዝቅተኞችን
የማይረሳ መሆኑን ለማስታወስ ነውና ሰው ራሱን ዝቅተኛ አድርጎ በመቁጠር ራሱን ሊንቅ
ይገባል፡፡ ሁሉን መታገሥ ሃይማኖትን ትጠብቃለች ምግባርም መንግሥተ ሰማያት
ታደርሳለች፤ ሥነ ምግባር የክርስቲያን ስብዕና መርከብ ነው ሰው ሥነ ምግባር ካለው
ፈጣሪውን በማሰብ ብዙውን ነገር ይታገሣል፡፡ በመታገሡም ሃይማኖቱን ያጸናል ሁሉን
መታገሥ ሃይማኖትን ትጠብቃለች ምግባርም መንግሥተ ሰማያት ታደርሳለች ሥነ ምግባር
ማለት በአጭሩ እርቅ ፈላጊነት፤ በጎ አድራጊነት፤ ከክፋት መራቅ፤ ያና ልቡናን ማዘውተር፤
እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት ብሎ መናገር እብደ ኢዮብ " ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን
እንደተቀበልን ከፉ ነገርንስ አንቀበልምን" ኢዮ 1÷10 በማለት የእግዚአብሔርን ተግሳፅ በበጎ

25
መቀበል የጊዜውን መከራ በሚመጣው ደስታ መርሳት ራስን በትህትና ዝቅ ማድረግ እና
የመሳሰሉት ከክርስቲያናዊ ስብእና መገለጫዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ዋቢ መጽሐፍት
 ርጢን ከመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ
 አንድ እረኛ አንድ ምንጋ ከቀሲስ አለማየሁ ሞገስ ደረሰ
 ኮክሐ ሃይማኖት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ
 ዶግማ ትምህርተ ሃይማኖት ከቀሲስ ታደሰ አይፎክቁ
 ሁለቱ ኪዳናት ከመርጌታ ኃየሎም
 ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር በሊቀ ጉባኤ አባ ገ/መስቀል
 መድሎተ ጽድቅ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ
 መንፈሳዊ ሰው አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎመው
 ማህቶተ ዘመን በመምህር በሙሉ አስፋው

26

You might also like