You are on page 1of 11

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ትምሕርተ ሃይማኖት
ክፍል አንድ
1. ሃይማኖት፣ እምነትና መታመን
1.1 ሃይማኖት
ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው መግለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ባሕርዩ ረቂቅ አኗኗሩ ምጡቅ ስለ ሆነ የሰውም ሆነ የመላእክት አእምሮ ተመራምሮ
ሊደርስበትና ባሕርዩ እንዲህ ያለ ነው፣ አኗኗሩ ይህ ነው ወይም ይህን ይመስላል ሊለው የማይችል ነው፡፡ እርሱ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ዘለዓለማዊና ምሉዕ ሲሆን
ፍጥረት በሙሉ ደግሞ በጊዜና በቦታ የተወሰነ ስለ ሆነ ውስኑ የማይወሰነውን ሊያውቀውና በምርምር ሊደርስበት አይችልም፡፡

ሆኖም ግን ምንም እንኳ እግዚአብሔር ባሕርዩና አኗኗሩ በራሱ ብቻ የሚታወቅ ረቂቅ አምላክ ቢሆንም እኛ ፈጽሞ የማናውቀውና ስለ እርሱ ምንም ፍንጭ የሌለን
ሆነን እንድንቀር አልተወንም፡፡ ከቸርነቱ የተነሣ ዓቅማችን ሊረዳው በሚችለው መጠን ማንነቱን፣ ህላዌውን፣ ባሕርዩን፣ መግቦቱን፣ ፈታሒነቱን፣ ፈቃዱን፣ … እናውቅ
ዘንድ በተለያየ መንገድ ገልጦልናል፡፡ ሃይማኖት የሚባለው ይህ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ እናውቀው ዘንድ ስለ ራሱ የገለጠው መገለጥ ነው፡፡ ስለሆነም ሃይማኖት
እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ያሳየበት መንገድ፣ የሰው ልጅ ሊቀበለው በሚችለው መጠን ስለ ራሱ ማንነት ለእኛ የገለጠው እውነታ ነው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ
“የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” እንዳለ፡፡ ዮሐ.
16፡12-13

እግዚአብሔር አንድ ስለ ሆነ፣ ባሕርዩም የማይለወጥ ስለ ሆነ፣ ሃይማኖት (ይህ አምላክ ስለ ራሱ የገለጠው መግለጥ) አንድና የማይለዋወጥ ነው፡፡ ስለዚህም ሊኖር
የሚችለው እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሃይማኖቶች አሉ ማለት ግን፣ ወይ እግዚአብሔር በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነገር ይናገራል ማለትን፣ አለዚያም
ደግሞ ባሕርዩ ይለዋወጣል ማለትን ያስከትላል፤ ሆኖም እነዚህ አስተሳሰቦች ለእግዚአብሔር ሊነገሩ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጸያፎች ናቸው፤ እርሱ በተለያየ ጊዜ
እርስ በእርሱ የሚቃረን የተለያየ ነገር አይናርምና፣ ባሕርዩም አይለዋወጥምና፡፡ መለወጥ የፍጡር ባሕርይ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ መለወጥ የለም፡፡ ስለዚህ
ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ኤፌ. 4፡5 እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ
“. . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” በማለት ሃይማኖት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር
ለቅዱሳን የተሰጠ መሆኑን በአጽንዖት ገልጿል፡፡ይሁዳ 3

እንዲሁም ለሃይማኖት መታዘዝና መጠበቅ ይገባል፡፡ “የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ
ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም” በማለት ሃይማኖቱን ሳይክድ በመጠበቁ አመስግኖታል፡፡ ራእ. 2፡13
ቅዱስ ጳውሎስም “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫዬን ጨርሼያለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ” በማለት፤ እንደዚሁም “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ
ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፣ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ” በማለት ሃይማኖትን መጠበቅ እንደሚገባ በጽኑ አሳስቧል፡፡ 2 ጢሞ. 4፡7 ዕብ. 4፡
14
1.2 እምነት

እምነት እግዚአብሔር የገለጠውን እውነት (ሃይማኖት) አዎ፣ እውነት ነው፣ ትክክል ነው ብሎ “አሜን” ብሎ መቀበል ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚገልጠው እውነት
(ሃይማኖት) በሰው መቀበል ወይም አለመቀበል ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ምን ጊዜም እውነት ነውና፡፡ “ባናምነው እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ
አይችልምና” እንዳለ፡፡ 1 ጢሞ. 2፡13 እንዲሁም “የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?” እንደ ተባለ፡፡ ሮሜ 3፡3

ነገር ግን ይህን እግዚአብሔር ስለ ባሕርዩ፣ ስለ መግቦቱ በአጠቃላይ እኛ ልናውቀው የምንችለውን ያህል በአባታዊ ቸርነቱ የገለጠውን እውነት (ሃይማኖት) እውነት
ነው ብለን ስንቀበለው እምነት ይሆናል፡፡ ይህ ማመንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሚያስገኝ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር
ከአብርሃም ዘር በመወለድ በዕፅ የተረገመውን ዓለሙን (የሰውን ልጅ በሙሉ) በዕፀ መስቀል ላይ በመሰቀል ይባርከው ዘንድ ፈቃዱ ነበር፡፡ ይኸ የማይለወጥና
የማይናወጽ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን እውነት ለአብርሃም ሲገልጥለት፣ በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ልጅ እንደሚወልድና በእርሱ ዘርም አሕዛብ
ሁሉእንደሚባረኩ ሲነግረው ‘ሸምግያለሁ፣ ይህ እንዴት ይሆናል?’ ብሎ ሳይጠራጠር ስላመነ “አብርሃም አመነ፣ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ተባለ፡፡ ዘፍ.
15፡3-6

እንዲሁም ይኽ እግዚአብሔር እርሱ ባወቀ በመለኮታዊ ምክሩ የወሰነው፣ አስቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን ገና ከገነት ሲወጡ የሰጣቸው ተስፋ፣ ኋላም ለአብርሃም የነገረው
ተስፋ ዘመኑ ደርሶ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲደርስ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ተልኮ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ከእርሷ ሰው ሆኖ
በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወለድ ነገራት፡፡ ይኽ ማንም ሰው ሊለውጠው ወይም ሊያስተባብለው ወይም ሊያሻሽለው የማይችለው የእግዚአብሔር አምላካዊ
ውሳኔ (ቁርጥ ሃሳብ) (ነገረ ሃይማኖት) ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይኽን ነገር ስትሰማ ነገሩ ከዚያ በፊት ያልተደረገ፣ ከዚያም በኋላ የማይሆን ስለ ሆነ ግራ ቢገባት “እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ
ኢየአምር ብእሴ - ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” ብላ ጠየቀች፡፡ መልአኩም ሊያስረዳት ሞከረ፡፡ ነገር ግን ማስረዳቱ ብዙም የማያስኬድ ስለ ሆነበት
“እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር - ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና” ብሎ ዘጋ፡፡ እመቤታችንም ነገሩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነማ “ይኩነኒ
በከመ ትቤለኒ - አንተ እንዳልከው ይሁንልኝ፣ ይደረግልኝ” ብላ የእግዚአብሔር ቁርጥ ሃሳብና ፈቃድ እንደ ተነገራት በእርሷ እንዲፈጸም ይሁንልኝ ብላ በፍጹም
እምነት ተቀበለች፡፡ ይህ በእምነት “ይኩነኒ” ብላ መቀበሏም እግዚአብሔር ቃል በማኅፀኗ በተዋሕዶ እንዲፀነሥ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሔዋን እግዚአብሔርን አለማመን
ከእግዚአብሔር መለየትንና ሞትን እንዳመጣብን የእመቤታችን ማመን ደግሞ እግዚአብሔር ባሕርያችንን ባሕርዩ አድርጎ ከእኛ ጋር እንዲሆን እና ሞትን
የሚያስወግደው የሕይወት በር እንዲከፈትልን መነሻ ምክንያት ሆነን፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ለጌታችን መንገድ ጠራጊ ይሆን ዘንድ መንፈቀ ዓመት ተቀድሞ የሚወለደው የመጥምቁ ዮሐንስን የመወለድ ነገር በተመለከተ መልአኩ ገብርዔል ካህን
ለነበረው ለዘካርያስ “ዘካርያስ ሆይ፣ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፣ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ …” ሲለው
በእምነት አልተቀበለም፡፡ ሉቃ. 1፡13-17 ይልቁንም መልአኩን መልሶ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፣ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” አለው፡፡ 1፡
18 በእምነት ከመቀበል ይልቅ ማረጋገጫ ምልክት ጠየቀ፡፡ በዚሀም ምክንያት ተግሣፅ ደረሰበት፡፡ እምነት እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ፣ የገለጠውን እውነት እንደ
ዘካርያስ ሳጠራጠሩና ምልክት ሳይሹ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአግባቡ ተረድቶ አሜን፣ ልክ ነው፣ ለይኩን ለይኩን ብሎ መቀበል ነው፡፡

በጸሎትና ነገረ ሃይማኖትን በሚናገሩ አንቀጾች መሀልም ሆነ መጨረሻ ላይ “አሜን” የሚለው ቃል የጸሎትና የእምነት መግለጫ ማሳረጊያ ሆኖ የሚነገረው ለዚህ
ነው፡፡ ጸሎት ሲሆን ‘የተጸለየው ጸሎት ይሁንልን ይደረግልን’ ለማለት፣ የተነገረው ወይም የተነበበው ነገረ ሃይማኖት ሲሆን ደግሞ ‘አዎ፣ እኔም ይህንኑ አምናለሁ፣
የማምነው ይኸው ነው’ ለማለት ነው፡፡ ለምሳሌም ቅዱስ ጳውሎስ “ከእነርሱም (ከእስራኤላውያን) ክርስቶስ በሥጋ መጣ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም
የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን” ይላል፡፡ ሮሜ 9፡5 አሜን ማለቱ ከዚያ በፊት የተናገረውን - ‘ክርስቶስ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው’ - የሚለውን
አዎን፣ እውነት ነው፣ የእኔም እምነት ይኸው ነው እንደ ማለት ነው፡፡

1.3 መታመን

መታመን ሲባል እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋና የተናገረው ቃል ለእኔም ይሆንልኛል፣ ይደረግልኛል፣ እርሱ ያድነኛል ይመግበኛል … ብሎ ሙሉ ተስፋንና ተአምኖን
በእርሱ ላይ ማድረግ ነው፡፡ ቃሉ ከእምነት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ቢሆንም በተለይ ግን በራሳችን ላይ የሚደርሱ ነገሮችን ለመቀበልና ለማሸነፍ በእግዚአብሔር
ረዳትነትና አዳኝነት ላይ ያለንን የእምነት መጠን የሚገልጽ ነው፡፡ ለምሳሌም ሠለስቱ ደቂቅ በፊታቸው አስፈሪ የሆነ እሳት እየተንቀለቀለ እያዩ “የምናመልከው
አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፣ ከእጅህም ያድነናል፣ ንጉሥ ሆይ፣ እርሱ ባያድነን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል
እንዳንሰግድለት እወቅ” ብለው ወደ እሳቱ እስከ መግባት ደርሰው በእርሱ ታምነዋል፡፡ ዳን. 3፡16-18

“ባያድነን እንኳ” ማለታቸው አዳኝነቱን ወይም የሚያድን መሆኑን የመጠራጠር ሳይሆን አንደኛ የእግዚአብሔር ፈቃድ እነርሱ በሰማዕትነት ሞተው እንዲያከብሩት
ይሁን ወይም ሌላ ስላላወቁ፣ ሁለተኛ ደግሞ በኃጢአታቸው ምክንያት ሳያድናቸው ቢቀር ያላዳናቸው እርሱ ማዳን ስለማይችል ሳይሆን በእነርሱ ለማዳኑ የበቁ አለ
መሆን ምክንያት ስለሚሆን ነው፡፡ ሆኖም አረማዊው ንጉሥ ናቡከደነፆር ይህን ሁሉ ቢነግሩት ስለማይገባው “ባያድነን እንኳ” የሚል ጨመሩለት፤ ከእሳቱ ባያድናቸው
አምላካቸውን እግዚአብሔርን ማዳን የማይችል አድርጎ እንዳይረዳ ለጥንቃቄ የተናገሩት ነገር ነው፡፡ ስለዚህ መታመን ሁለንተናችንን በእግዚአብሔር አዳኝነትና
አባትነት ጥላ ሥር ማሳረፍ ነው፡፡

1.4 የሃይማኖት መገለጫዎች / ሃይማኖት እንዴት ተገኘ?

“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡” ይሁዳ 3

ሃይማኖት፡-

1) የተሰጠ፣ የተቀበልነው ነው፡፡

እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ፣ እኛ ደግሞ ተቀበልን፡፡ የእኛ ድርሻ መቀበል ነው፡፡ የሰው ልጅ ሃይማኖትን ይቀበላል እንጂ ሃይማኖትን ሊሠራ ወይም ሊያሻሽል
አይችልም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፣ እነርሱም ተቀበሉት፡፡” በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ ዮሐ. 17፡8

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ያመነውንና የያዘውን ሃይማኖት ከጌታ የተቀበለው መሆኑንና፣ ያን የተቀበለውንም በወንጌል ትምህርት እንዳወረሳቸው ለቆሮንቶስ
ክርስቲያኖች ሲያሳስባቸው እንዲህ በማለት ገልጾላቸዋል፡- “ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን፣ ደግሞም የተቀበላችሁትን፣ በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን፣
በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ … እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ፡፡” 1 ቆሮ. 15፡1-3 እንዲሁም ስለ ምሥጢረ
ቁርባን ባስተማረበት አንቀጽ ላይ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ደግሞ ከጌታ ተቀብያለሁና…” ብሏል፡፡ 1 ቆሮ. 11፡23

ወልድ ዋሕድ መድኃኒታችንም “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?” ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፡- “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣
ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ፣ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም
መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም
ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፣ የገሃነም ደጆች አይችሏትም፡፡” ማቴ. 16፡
13-18

በሥጋና ደም አስተሳሰብ (በሰው ምርምርና ሐተታ) ሰዎች ስለ ጌታችን ሊሉት የሚችሉት ያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች እንዳሉት ‘መጥምቁ ዮሐንስ፣ ወይም ኤልያስ ወይም
ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ከማለት ያለፈ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሆኖ እያዩት አምላክነቱን መረዳት በሥጋና በደም አስተሳሰብ ሊደረስበት
የሚችል ምሥጢር አይደለምና፡፡ ጴጥሮስ ግን የወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱ አብ የገለጠለትን ነገር - የኢየሱስ ክርስቶስን የአብ የባሕርይ ልጅነት -
ስለ ተናገረ ጌታችን አመሰገነው፤ “ስምዖን ሆይ፣ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ” አለው፡፡

መቼም ቢሆን በሃይማኖት እግዚአብሔር የገለጠውን ትተን በራሳችን አስተሳሰብና በሚመስለን መንገድ እንሂድ ካልን ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ልንደርስ አንችልም፡
፡ በሐዋርያት ዘመን ከነበሩት ዓይነት ሰዎች የተሻለ ነገር ልንል አንችልም፡፡ ከዚያ ለመውጣትና ጴጥሮስ የመሰከረውን ለመያዝ ከሥጋና ከደም አስተሳሰብ መለየት
የግድ ይላል፡፡ ጌታችን “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡” ያለው ለዚህ ነው፤ ስሙንም፣ ማንነቱንም ሊገባን በሚችለው መጠን የገለጠልን ራሱ ነው
እንጂ ሃይማኖት የሰው ልጅ በምርምር የደረሰበት ግኝት አይደለም፡፡ ዮሐ. 17፡6

ድጓ "ሃይማኖት እንተ እም ኀበ አብ ተፈጥረት፣ ኀበ ወልድ ታበጽሕ፣ኀበ መንፈስ ቅዱስ ትትፌጸም፡፡ይህ ማለት ሃይማኖት አብን ወላዲ /አባት/ ወልድን
ተወላዲ/ልጅ/ መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ በማለት ትጀመራለች፤ ትፈጸማለች፡፡ አብን ወላዲ አስራጺ ሳይሉ ወልድን ተወላዲ መንፈስ ቅዱስን ሰራጺ ማለት
አይቻልም፡፡ አብን በልብነት መቀበል ወልድን በቃልነት መንፈስ ቅዱስን በሕይዋትነት /በእስትንፋስነት/ አምኖ መቀበል ነውና እንተ እምኀበ አብ
ተፈጥረት አለ ሊቁ ተገኘች ማለቱ ሃይማኖት የተገኘችው ከእግዚአብሔር ነውና፣ ሃይማኖት ከአብ ተፈጠረች፤ወደ ወልድ ታደርሳለች፤ በመንፈስ ቅዱስም
ትፈጸማለች፡፡"የሚል ቃል እናገኛለን ፡፡ስለዚህ ሃይማኖት የሰው ልጆች ከዕውቀት ማነስ ከፍርሀትና ከድንጋጤ ያመጡት አይደለም፡፡

ድጓ በከመ ይቤ እግዚእነ በወንጌል ኵሉ ዘየዐቅብ ቃልየ ይመስል ብእሴ ጠቢበ ዘሐነጸ ቤቶ ዲበ ኰኵሕ ነፍኁ ነፋሳት፣ ዘንሙ ዝናማት ፣ ወውኅዙ
አፍላጋት ፣ ወገፍዕዎ ለውእቱ ቤት ፣ ወኢወድቀ ፣ እስመ ዲበ ኰኵሕ ተሣረረ፡፡ = ጌታችን በወንጌል እንዳለው ቃሌን የሚጠብቅ ሁሉ ቤቱን በዐለት
ላይ የሠራ ጥበበኛ ሰውን ይመስላል፤ ነፋሳት ነፈሱ፣ ዝናምም ዘነመ ፣ ወንዞችም ፈሰሱ ፣ ይህን ቤት ገፉት፤ አልወደቀም፡፡ በዐለት ላይ ተሠርቷልና”
ይላል።
ለምን ዝም ብለን በእምነት እንቀበላለን ቢሉ? እግዚአብሔር ባሕርዩ ረቂቅ፣ አኗኗሩ ምጡቅ ስለ ሆነ የሰውም ሆነ የመላእክት አእምሮ ተመራምሮ ሊደርስበትና ባሕርዩ
እንዲህ ያለ ነው፣ አኗኗሩ ይህ ነው ወይም ይህን ይመስላል ሊለው የማይችል ነው፡፡ እርሱ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ዘለዓለማዊና ምሉዕ ሲሆን ፍጥረት በሙሉ ደግሞ
በጊዜና በቦታ የተወሰነ ስለ ሆነ ውስኑ የማይወሰነውን ሊያውቀውና በምርምር ሊደርስበት አይችልም፡፡
አንዳንድ ሊቃውንት እግዚአብሔርን እንደ ሒሳብ እንደ ፊዚክስ ወይም እንደ አንድ የሳይንስ ዘርፍ ለመመርመር ይሞክሩና ሳይደርሱበት ሲቀሩ እግዚአብሔር የለም
ወደሚል ድምዳሜ ይደርሳሉ። ይህ ግን ስህተት ነው። ለእነዚህ ሰወች እንዲህ እንላቸዋለን፦ በምርምር ያልተደረሰበት ነገር ሁሉ የለም ማለት ነውን? አይደለም!
አለመታየት፣ አለመደመጥ፣ አለመዳሰስ የአንድን አካል አለመኖር እንደማያረጋግጥ ሁሉ በምርምር አለመድረስም እንዲሁ ለነገሩ አለመኖር ማረጋገጫ ሆኖ ሊቀርብ
አይችልም። ባለፉት ዘመናት የነበሩ ተመራማሪወች ያልደረሱባቸው በዘመናችን በሳይንሳዊ ምርምር የተረጋገጡ እውነታወች በዚያ ዘመን እውነት አልነበሩም ማለት
ነውን? አይደለም! ባለፈው ዘመን የነበሩ ተመራማሪወች በነበራቸው የዕውቀት ውስንነት የተነሣ አሁን በሳይንስ የተረጋገጡ እውነታወችን ሳይደርሱባቸው ቀሩ እንጂ።
ተመራምሮ አለማግኘት የተመራማሪውን የዕውቀት ውስንነት እንጂ የሚመረመረውን አካል አለመኖር እንደማያረጋግጥ አስተዋላችሁን? ይህስ ከሆነ ያልደረሱበትን
ነገር የለም ብሎ መፈረጅ “ሁሉን ዐውቀዋለሁ፣ ያልደረስኩበት ነገር የለም” ከሚል ትዕቢት የመነጨ የድንቁርና አስተሳሰብ እንደሆነ ነው የምንረዳው።
እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ካላቸው ሰወች የሚስተዋለው ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ፈጣሪን እንደ አንድ ተራ ነገር በሳይንሳዊ ምርምር ሊደርሱበት ማሰባቸው ነው። እነዚህ
ሰወች በራሳቸው ሰውነት ውስጥ ስለሚከናወኑ ሥርዓቶች በትክክልና በርግጠኝነት መናገር አይችሉም። ስለእንቅልፍ፣ ስለሞት፣ ስለሀሳብ ምንነት . . . ብንጠይቃችው
ከመላምት በቀር እርግጠኛ ሆነው መናገር አይችሉም። ስለራሳቸው በትክክል የማያውቁ ሰወች እነሱን ስለፈጠረ አካል እንዴት ነው እርግጠኛ ሆነው ሊናገሩ
የሚችሉት? ራስን በምርምር በምልዓት ማወቅ ካልተቻለ ፈጣሪን ለማወቅ ስለመመራመር እንዴት ማሰብ ይቻላል?

2) ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ ነው - ለቅዱሳን

“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት … ” ይሁዳ 3

ምግብናው እንደየ ዘመኑ ይለያያል፣ ይዘቱ ግን ያው አንድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕፃን ልጅ በሕፃንነቱ ወተትና ፍትፍት፣ ሲያድግ ደግሞ ጠንከር ያለ ምግብ ይሰጠዋል፣
የሰውነት ባሕርዩ ግን ያው አንድ ነው፣ አይለዋወጥም፡፡ ሃይማኖትም በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪት፣ በዘመነ ወንጌል የምግብናው ሁኔታ እንደየ ዘመኑ የሰዎች የመረዳት
ዓቅምና ሁኔታ ቢለያይም ይዘቱ (ጭብጡ) ግን ያው አንድ ነው፡፡ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን
ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ያለው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕብ. 1፡1-2 የቅዱሳን መላእክት፣ የአበው
ቀደምት የእነ አዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ዳዊት፣ የነቢያት፣ ኋላም የሐዋርያትና የሰማዕታት፣ የጻድቃንና የሊቃውንት ሃይማኖት አንድ ነው፡፡

ስለዚህ ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ፣ ያውም ፈጽሞ (ያለ መቀናነስና ያለ ቀረኝ) ስለ ሆነ ተሐድሶ ወይም ለውጥ አያስፈልገውም ማለት ነው፡፡ ሃይማኖትን
ይቀበሉታል፣ ይጠብቁታል፣ ያወርሱታል እንጂ ላድሰው፣ ላሻሽለው አይባልም፤ እንዲያ ከሆነ መጀመሪያ የተሰጠው ሃይማኖት ሕፀፅ ነበረበት፣ ወይም ምሉዕ
አልነበረም ያሰኛል፡፡ እግዚአብሔር የሰጣት፣ አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት ግን ፍጽምትና አንድ ጊዜ የተሰጠች ናት፡፡ ብልየት
እርጅና የለባትም፣ ተሐድሶ ወይም ማደስ የሚለው ቃል ብላሽና ለሃይማኖት ሊነገር የማይችል ጸያፍ ነው፡፡

3) ሃይማኖት ተጋድሎ ያስፈልገዋል

በሃይማኖት ተጋድሎ የሚያስፈልገው በተሰጠን ሃይማኖት ለመጠቀም እና ለመጠበቅ ነው፡፡ ጌታችን “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡ የአንተ ነበሩ፣
ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል፡፡” ያለው ቃሉን መቀበል ብቻ ሳይሆን መጠበቅም እንደሚገባ ሲነግረን ነው፡፡ ዮሐ. 17፡6 የተሰጠንን አጽንቶ ለመያዝና
የሕይወትን አክሊል ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ መጋደልና ታማኝነትን በተግባር ማስመስከር የግድ ይላል፤ “ኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት
- እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” ተብሏልና፡፡ ራእ. 2፡10

እንዲሁም በሃይማኖት ለመጠቀምም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁ በማመን ብቻ መጠቀም አይቻልም፤ ባመኑት ለመጠቀም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ
እስራኤላውያን በደብረ ሲና ከራሱ ከእግዚአብሔር፣ ኋላም ከሙሴ በተደጋጋሚ የእግዚአብሔርን ቃል በጆሯቸው ቢሰሙም በሰሙት ለማመንና ባመኑትም ለመጠቀም
ጥረት ስላላደረጉና ስላልተጋደሉ እንዳልተጠቀሙ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡- “የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም፡፡” ዕብ. 4፡2
ስለዚህ፡-
ሃይማኖትን
 ይቀበሉታል፣
 ይጠቀሙበታል
 ይጠብቁታል
 ያወርሱታል
እንጂ ማደስ፣ ማሻሻል በሃይማኖት የለም፡፡

2. ነገረ ሃይማኖትን የማጥናት ጥቅም


ሃይማኖት፡- ጥበብ ናትና ወደ ብቃት ታደርሳለች። /ምሳ. ፱፥፩-፯፣ ማቴ. ፳፪፥፩-፲፪፣ ፪ኛ ጢሞ. ፫፥፲፬-፲፯/ ድጓም እንዲህ ይላል ጥበብ ሐፀነተከ
ከመ ጥበ ልቡና ረሰየተከ መካና አእምሮ ታጌብረከ ለምህሮ ወንጌለ መለኮት ሰበከ ስምዐ ጽድቅ ኮንከ - ጥበብ እንደ ጡት አሳደገችህ፣ ልቡና
ቦታዋ አደረገችህ አእምሮም ለማስተማር ታበቃሀለች፣ ስለዚህ የመለኮት ወንጌልን ሰበክህ፣ የጽድቅም ምስክር ሆንህ» በማለት ያመሰጥራል።
እምነት
 ተስፋ ለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ ነው፡፡ /ዕብ. ፲፩፥፩/

 ኃይልና ሥልጣን ትሰጣለች። /ማር. ፲፮፥፲፮-፲፱ ፣ ማቴ. ፲፥፰/

የሐዋርያት ድጓ "አብሖሙ ይኪዱ ዲበ ኲሉ ኀይለ ጸላኢ፤ ወይቤሎሙ ወሀብኩክሙ ሥልጣነ፤ ዱያነ ፈውሱ፤ ዐቢይ ኀይል ወተአምር ይትገበር
በእደዊሆሙ ለሐዋርያት… ይቤሎሙ ኢየሱስ ለአርደኢሁ አጋንንተ አውጽኡ፤ እለ ለምጽ አንጽሑ፤ ጸጋ ነሢአክሙ በጸጋ ሀቡ - በእባቡ፣
በጊንጡ /በጠላት ኀይል ሁሉ/ ላይ ይረግጡ ዘንድ ድውያንን ትፈውሱ ዘንድ ሥልጣን ሰጠኋችሁ አላቸው ታላቅ ተአምር ታላቅ ኀይል በሐዋርያት
እጅ ይደረጋል… ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው አጋንንትን አውጡ ፣ ድውያንን ፈውሱ ፣ ለምጻሙን አንጹ ፣ ያለዋጋ የተቀበላችሁትን
ያለዋጋ ስጡ”የሚል ማብራሪያ ይሰጠናል፡፡
 ሰው ከኃጢአት ከሰይጣን ግዞት ነጻ የሚሆንበት ነው፡፡ ሮሜ. ፮÷፳፪፣፩ኛጴጥ. ፭÷፰፣፩ኛዮሐ. ፬÷፩-፮፣ያዕ. ፬÷፯

 በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣ ቅጣት ይሰውራል። /ዘፍ. ፮፣ዘፍ. ፱፣ዕብ. ፲፩÷፯/

 የጽድቅና የበረከት መገኛ ነው። /ዘፍ. ፲፪÷፩-፰፣ዕብ. ፲፩÷፰/

 ለሰማዕትነት ያበቃል፡፡ዳን.፮፣ዕብ. ፲፩÷፴፪-፵፣የሐዋ. ፮÷፰-፲፭፣፯÷፩-፷፣ማቴ. ፲÷፳፰፣ሉቃ. ፲፪÷፬-፭ .ዳን.፫÷፲፭

ድጓ ዘሠለስቱ ደቂቅ፡- “ይቤሎሙ ንጉሥ እምከመ ሰማዕክሙ ቃለ ቀርን ወዕንዚራ ስግዱ ለምስል ዘወርቅ ዘገበርኩ፡፡= ንጉሡም እንዲህ
አላቸው፡፡ የመለከቱንና የእንቢልታውን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ለሠራሁት ምስል ወድቃችሁ ብትሰግዱ መልካም ነው፡፡”አላቸው።
ድጓ ዘሠለስቱ ደቂቅ “ከመ ታእምር ንጉሥ አምላከከሂ ኢናመልክ አምላከነሂ ናመልክ ለምስል ዘወርቅ ዘገበርከ ኢንሰግድ ለከ፡፡= ንጉሥ ሆይ
ታውቅ ዘንድ እንወዳለን ፤አምላክህንም አናመልክም፤ አምላካችንን እናመልካለን እንጂ፤ ላቆምከው ለወርቅ ምስል አንሰግድም አሉ፡፡”
 ድንቅ ተአምራትን ማድረግ ያስችላል። /ዮሐ. ፲፬÷፲፪/ ለሚያምን ሁሉ ይቻላልና/ ማር. ፱÷፳፫/ በእርሱ በማመናቸው ሙት ያስነሡ፣
በጥላቸው ፣በልብሳቸው ሳይቀር ድውይ ይፈውሱ በርካታ ገቢረ ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡/ የሐዋ.፫÷፩-፲፣፱÷ ፴፪፣፲፮÷፲፮-፲፰፣
የሐ.፭÷፲፪፣፭÷፲፭ ፣፲፱÷፲፩
የሃይማኖት አስፈላጊነትም ጠቅለል ባለ መልኩ፡-

ለሰው ሁለንተና ሕይወት ሃይማኖት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚያስችለው
ሃይማኖት ነው፡፡ ሃይማኖት የሌለው ሰው ከሕይወት የተለየ ምውት ነው፡፡ በሃይማት የጸጋ ልጅነትን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን፣ርስቱን
መውረስን ወዘተ ያስገኛል። በዚህ ዓለም ሕይወትም መረጋጋትን፣ ተስፋን፣ ሰላምን፣ አርቆ ማሰብን፣ከሱስ መጠበቅን፣ በረከት ረድኤትን ያስገኛል።
ለሀገርም በማኅበረ ሰብእ ውስጥ መተማመንን፣ በሥራ ትጋትን፣ ፍትሕ አክባሪነትን ወዘተ ያበረክታል።
3. የነገረ ሃይማኖት ምንጮች /መሠረተ ሃይማኖት/
1. ዶክትሪን (ዶግማ)

ዶግማ ቃሉ የጽርዕ ሲሆን መሠረታዊ የሃይማኖት አስተምህሮ ማለት ነው፡፡ ይህም መሠረታዊ የሆነው እግዚአብሔር የገለጠው እውነት ሲሆን
አስቀድሞ በሕግና በነቢያት ያናገረው፣ ኋላም እርሱ ራሱ ሰው ሆኖ ያስተማረውና ቅዱሳን ሐዋርያት የጻፉልንና ያስተማሩነረ እውነት ነው፡፡
ለምሳሌም ዶክትሪን (ዶግማ) ከሚባሉት መካከል፡- ምስጢረ ሥላሴ፣ ምስጢረ ሥጋዌ፣ ምስጢረ ጥምቀት፣ ምስጢረ ቁርባን፣ ምስጢረ ትንሣኤ
ሙታን፣ የእመቤታችን ወለዲተ አምላክነትና የቅዱሳን አማላጅነት ወዘተ ናቸው፡፡
2. ቀኖና
ቀኖና ቃሉ የጽርዕ ሲሆን ትርጉሙም ሕግ፣ሥርዓት፣ደንብ፣ፍርድ፣ቅጣት፣መጠን፣ልክና መለኪያ መለት ነው፡፡
የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ምንጮች
1.መጽሐፍ ቅዱስ - መጽሐፍ ቅዱስ የቀኖናተ ቤተ ክርስቲያን ዋና መሠረት ነው፣ በውስጡም ብዙ ቀኖናት አሉ፡፡ ለምሳሌ ስለ ጾም፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ
ምጽዋት፣ (ማቴ. 6፡ 1-18) ስለ ምሥጢረ ቁርባን አፈጻጸም (1 ቆሮ. 11፡16-34)፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች አለባበስና ጸጉር አቆራረጥ ( 1 ቆሮ. 11፡1-
15) ወዘተ
2. የሐዋርያት ሲኖዶስ፡- ቀኖናተ ሐዋርያት እየተባሉ የሚጠሩ ሁለት መጻሕፍት አሉ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-
 ሲኖዶስና
 ዲዲስቅልያ ናቸው፡፡
3.ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት
 ጉባኤ ኒቂያ
 ጉባኤ ቁስጥንጥንያ
 ጉባኤ ኤፌሶን ናቸው
የቀኖና ጠቀሜታ
 መናፍቃንና ኑፋቄ ይለይበታል
 የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መልክ እንዲኖረው ያደርጋል
 የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ይጠብቃል፣ በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ የሆነ አገልግሎትና ሥርዐት እንዲኖር ያግዛል ዮሐ 15፡1-29
 በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ካልሆነው መለያ፣መለኪያ በመሆን ያገለግላል
ቀኖናትን ማን ይወስናል?
አንድ ሰው በዘፈቀደ ተነሥቶ ቀኖናትን መወሰን ወይም ማሻሻል አይችልም፡፡ ቀኖና በባሕርይው ሊሻሻል፣ ሊለወጥ የሚችል ነገር ነው፡፡ ይሁን
አንጂ መወሰኑም ሆነ ማሻሻሉ የሚፈጸመው በሐዋርያት እግር በተተኩ በጳጳሳት ጉባኤ (በቅዱስ ሲኖዶስ) ነው፡፡ ይህንንም ስንናገር ከእግዚአብሔር
የተቀበልነውን ነው እንጂ በልብ ወለድ አይደለም፡፡ ሥርዐትን የሠራ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሥርዐትን አስተማሪ ራሱ ፈጣሪያችን ነው፡፡መዝ.
፩፻፲፰÷፳፬፣፸፩
3.ትውፊት
ትውፊት አወፈየ ሰጠ ከሚለው የግእዝ ቃል ወጣ ሲሆን ትርጉሙም፡- ቅብብል፣ ርክክብ ማለት ነው፡፡
ትውፊትና ቤተ ክርስቲያን
ቤተ ክርስቲያናችን በክርስቲያናዊ ትውፊት ታላቅ ቦታ ትሰጣለች፡፡ ጥንታዊት በመሆንዋ ከቀደምት አበው የወረሰችው አያሌ ነገር አሏት፤ እነርሱም ሁለት
ዓይነት ናቸው፡፡
1. ቁሳውያን፡- መጻሕፍት ፣ ንዋየ ቅድሳት ፣ አብያተ ክርስቲያናት ፣ ገዳማትና አድባራት ወዘተ የዚህ ክፍል ናቸው፡፡
2. ቃላውያንና ራእያውያን፡- ትውልዱ ከአባቶቹ በመስማት ፣ በማየት ለኑሮው የሚጠቀምባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ባሕሉ ንግግሩ እና
ሥርዐቱ ከአባቶቹ አይቶና እየሰማ የሚቀበላቸው ናቸው፡፡

ትውፊትና ቅዱሳት መጻሕፍት


የቤ/ክ አስተምህሮ ከሁለት ምንጮች የተገኙ ናቸው፡- ቅዱሳት መጻሕፍት እና ቅዱስ ትውፊት (Sacred Tradition) ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት
የተገኙበት ዐውድ እንዲሁም የሚተረጎሙበትና የምንረዳበት ዐውድና መሠረት ቅዱስ ትውፊት ነው፡፡ ትውፊት ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የሚጋጭ
የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ደም ከደም ጋር እንደማይጋጨው ሁሉ እነርሱም አይጋጩም፡፡ ምክንያቱም ትውፊት መጽሐፍ ቅዱስን ያገኘንበት
መንገድ ነው፡፡ አበው መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ነው ብለው ባያስረክቡን ኑሮ ከየት ይመጣ ነበር? ይህ ትውልድ በምን ያውቀው ነበር? ለማግኝት የቻልነው
አበው ስላቆዩልን ቤተ ክርስቲያንም ስላረጋገጠችልን አይደለምን? ትውፊት የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዳይፋለስ ይጠብቃል፡፡ አበው መጻሕፍትን
ሲያስረክቡን የደራሲውን ገድል፣ የተጻፈበትን ባህል፣ የመጽሐፍቱን ትርጓሜ ከምንጩ የቀዱትን ጭምር ነው፡፡ ይህም ማንም በየትም ዘመን ተነሥቶ
የራሱን ሃሣብና ፍልስፍና በመጨመር የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል እንዳያጣምም አድርጐታል፡፡ በትውፊት የመጡልን ብዙ ትምህርቶች አሉ፤ ሆኖም
የትውፊት መመዘኛውና መለኪያው በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው ትምህርት ነው፤ “ኢትጻኡ እም ቃለ መጻሕፍት - ከተጻፈው አትለፉ” ተብሏልና፡፡ 1 ቆሮ.
4፡6

4. ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ማወቅ እንችላለን?

እግዚአብሔር የማይመረመር ረቂቅ በዚህ ጊዜ ተገኘ የማይሉት ቀዳማዊ በዚህ ጊዜ ያልፋል የማይሉት ደኃራዊ ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ
የፈጠረ ዳግመኛም ዓለምን ከመኖር ወደ አለመኖር አሳልፎ የሚኖር ኃያል ፈጥሮ የሚገዛ ጌታ ነው፡፡
 “በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር
ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም፡፡” 1 ቆሮ. 2፡11-12
 “ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፣ ከወልድም በቀር፣ ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፡፡” ማቴ. 11፡27
 “በፈጣሪና በፍጡር መካከል መጨረሻ የሌለው ሸለቆ (ጥልቀት) አለ፡፡” ቅ. ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
 “በፈጣሪና በፍጡር መካከል ማንም ሊያልፈው የማይችለው ክፍተት አለ፡፡” ቅ. ኤፍሬም ሶርያዊ
ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፡- “ቀዳማዊ ውእቱ ዘኢይብልዎ እማእዜ ወማእከላዊ ውእቱ ዘኢይብልዎ እስከ ይእዜ ወደኃራዊ ውእቱ ዘኢይብልዎ እስከ ዝየ= ከመቸ
ወዲህ የማይሉት ቀዳማዊ እስከ ዛሬ የማይሉት ማእከላዊ እስከዚህ የማይሉት ደኃራዊ ነው፡፡”
ቅዳሴ ጎርጎርዮስ፡- “አልቦ ጥንት ለህላዌሁ ወአልቦ ማኅለቅት ለክዋኔሁ - ለአኗኗሩ ጥንት የለውም ለአኳኋኑም ፍጻሜ የለውም፡፡”
ሰውን ጻድቅ ቢሉት ሐሰት ሀብታም ቢሉት ድህነት ኃያል ቢሉት ድካም ይስማማዋል። እሱ ግን ሐሰት የሌለበት ጻድቅ ድህነት የሌለበት ባለጸጋ
ድካም የሌለበት ኃያል ነው፡፡ መዝ ፯÷፲፩
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ ጥልቅ ነገረ መለኮታዊ ትምህርቶችን ባስተማረባቸው በአምስቱ ተከታታይ ትምህርቶቹ (Theological Orations) ላይ ስለዚህ ጉዳይ
እንዲህ ይላል፡-

 “እግዚአብሔር በባሕርዩ ማን እንደ ሆነ እስካሁን ማንም ሰው አላየውም አላወቀውም፣ ወደፊትም ሊያውቀው አይችልም፡፡ በእምነቱ የጸደቀውና እንግዳ
መሥዋዕት ያቀረበው ታላቁ አባት አብርሃም እንኳ እንደ ሰው ሆኖ ለተገለጠለት ለእርሱ የሚበላ አቀረበለት እንጂ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ
አላየውም፡፡ የተመሰገነው የእግዚአብሔርን ባሕርይ ስለ መረመረ ሳይሆን እግዚአብሔርን በእምነት ስላመለከ ነው፡፡ ያዕቆብም መላእክት የሚወጡበትና
የሚወርዱበት ታላቅ መሰላል አየ፣ በመሥጢራዊ ሁኔታም ድንጋይን በዘይት ቀባ (ይህም ስለ እኛ በተዋሕዶ የሚከብረውን ዓለት - ክርስቶስን የሚያመለክት
ነበር)፣ ቦታውንም ቤቴል - የእግዚአብሔር ቤት - ብሎ ሰየመው፤ እንደ ሰው ሆኖ ከተገለጠለት አምላክ ጋርም ታገለ፣ በሰውነቱም የመታገሉን አሻራ
(ምልክት) ተሸከመ፣ በዚህም ስሙ ከያዕቆብነት ታላቅና ገናና ወደ ሆነው ስም - ወደ እስራኤልነት - ተለወጠ፡፡ ሆኖም እርሱም ሆነ ከዘሩ ማንም
እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ ፊት ለፊት አላዩትም፡፡ ታላቅነቱ ይታወቅና ይለጥ ዘንድ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማያት የተወሰደው ኤልያስም በብርቱው
ነፋስም ሆነ በምድር መናወጡ፣ እንዲሁም በእሳቱ ውስጥ እግዚአብሔር አልነበረም፡፡ ከዚያ ተከትሎ በሆነው በትንሽ የዝምታ ድምፅ ውስጥ
የእግዚአብሔርን መገለጥ አመለከተው፣ ‘ኤልያስ ሆይ፣ በዚህ ምን ታደርጋለህ?’ የሚል ድምፅም ወደ እርሱ መጣ፤ ባሕርዩን [ያመለከተው] ግን አልነበረም፡
፡ 1 ነገ. 19፡11-13 የሶምሶን አባት ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልእክተኛ (መልአክ) በማየቱ ብቻ እንኳ እግዚአብሔርን ማየት ይቅርና መልእክተኛውን
ማየት እንኳ በሰዎች ዘንድ የሚቻል አይደለም ብሎ በማሰብ ‘እግዚአብሔርን አይተናልና ሞትን እንሞታለን’ እስከ ማለት ደረሰ፡፡ መሣ. 13፡22”

(ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ አምስቱ ተከታታይ ነገረ መለኮታዊ ትምህርቶች)

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ደግሞ እንዲህ ይላል፡-


 “መለኰታዊና ቅዱስ የሆነው ሕይወት [እግዚአብሔር] መለኪያና ስፍር የሌለው የመሆኑ ነገር ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እርሱ በጊዜ
ውስጥ የሚኖር አይደለምና፣ ጊዜ ራሱ የተገኘው ከእርሱ ነው እንጂ፡፡ ፍጥረቱ ሁሉ ግን ከታወቀ መጀመሪያው ወደ ታወቀ ፍጻሜው ይሄዳል፣ በመካከልም
በጊዜ በሚለኩ ሂደቶች ውስጥ ያልፋል፤ ስለዚህም ሰሎሞን እንዳለ (ጥበብ 7፡18) ለፍጥረታት መጀመሪያውን፣ መካከለኛውንና መጨረሻውን መለየት
ይቻላል፡፡ ሩቅና ምጡቅ፣ ዘለዓለማዊና ቅዱስ፣ ሕያወ ባሕርይ ለሆነው ለእርሱ ግን ስፍርም ሆነ ቦታ የለውም፡፡ የተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ምንም እንኳ የሰው
አእምሮ ውስንነት ሊደርስባቸው ላይችል ቢችልም እንኳ በፈጠራቸው በእርሱ ዘንድ የታወቁና የተሰፈሩ፣ በሥነ ፍጥረት ሀልወት ክበብ ውስጥ የታጠሩ
ናቸው፡፡ ለተፈጠሩት ነገሮች ሁለ ዳርቻቸውንና ወሰናቸውን ያስቀመጠላቸው ፈጣሪ እርሱ ግን ገደብና ወሰን የለበትም፣ ወሰን ወደ ሌለው ወደ እርሱ አኗኗር
የሚደረጉ ፍለጋዎችንና የመለኰታዊ ባሕርይን ጥንት ምንነትና የትመጣነት ለመመርመር ከፍ ከፍ ብለው ሊወጡ የሚሞክሩትን አስተሳሰቦች ሁሉ እጅግ
ይረቅባቸዋል፣ ባለመደረስ ውስጥም ይዘጋቸዋል፡፡ የጊዜን ድንበር በመሻገር በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ካለው ባሕርያዊ ክፍተት (diastēma) አልፎ
ለመሄድ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ሁሉ ያ ክፍተት ሊታለፍ የማይቻል መሆኑን ከሚያይበት ደረጃ ላይ ብቻ ይደርሳል፤ የሰው አእምሮና ሃሳብ
መለኪያውና ወሰኑ ጊዜ (ho aiōn) እና በእርሱ ውስጥ ያለው ሌላው ነገር ሁሉ ነው፡፡ እነዚህን የሚያልፍ (ከእነዚህ ውጭ) የሆነ ነገር ሁሉ ለሰው አእምሮ
ከዓቅሙ በላይና ሊደረስበት የማይችል ይሆንበታል፡፡

 “የተፈጠረ ነገር ሁሉ አኗኗሩ (ህልውናው) በጊዜ እና በቦታ የተወሰነ ነውና፡፡ ዘለዓለማዊ በሆነው ህልውና ዘንድ ግን ጊዜም ሆነ ቦታ የለም፣ ራሱ ከራሱ
ነው፣ ከእነዚህ በፊትና ውጭ ነው፣ በጊዜ የማይለካ ነው፣ ያለፈ እና የወደፊት በሚባሉ የጊዜ ጽንሰ ሃሳቦች የማይከፈል ነው፣ በእምነት ብቻ ልንረዳው
የምንችለው ነው፡፡ ጊዜ ነክ የሆኑ ልምዶች በፍጥረት ውስጥ ላሉ ነገሮች ብቻ የሚሠሩና የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሁሉ ነገር ዛሬ ለሆነለት ለዚያ ቅዱስና ገናና
ህልውና ግን ያለፈውና የወደፊቱ በአንድ አምላካዊ የእውቀት ቅጽበት ጥላ ሥር ናቸው፡፡ . . . ከመጀመሪያ ሁሉ በላይ፣ ከጊዜ ውጭ የሆነው ህልውና እርሱ
ለባሕርዩ ፍለጋ የለውም፣ የሚታወቀው ባሕርዩ ሊታወቅ የማይችል በመሆኑ ብቻ ነው፡፡”

(ቅዱስ ጎርርዮስ ዘኑሲስ፣ በእንተ ዩኖሚየስ፣ መጽሐፍ 1፣ ገጽ 36-37)

የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማወቅን በተመለከተ ስለ መላእክት ሲናገርም እንዲህ ብሏል፡-

 “የመላእክት ኃይል ከእኛ ጋር ሲነጻጸር በማንኛውም መንገድ የበለጠ ሆኖ ይታያል፡፡ ሆኖም ሕያወ ባሕርይ ከሆነው ከእርሱ ገናናነት ጋር ሲነጻጸር ግን
የእነርሱ ታላቅነት እንኳ ከእኛ የእውቀትና የመረዳት ታናሽነት (ደካማነት) ያንም ያህል የበለጠ አይደለም የሚል ቢኖር ከእውነት የራቀ ነው ሊባል አይቻልም፡
፡ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ካለው ባሕርያዊ ርቀት (diastēma) ለእኛም ሆነ ለመላእክት የእግዚአብሔርን ባሕርይ በቀጥታ ለማወቅ የማይቻል
ያደርግብናል፡፡ ቀንን ከኋላውና ከፊቱ እንደሚወስኑት ሁለት ሌሊቶች ፍጡራንን ከፊታቸውና ከኋላቸው ይወስናቸዋል፡፡ ጊዜና ቦታ ፍጡራንን ሊያልፉት
በማይችሉት ወሰን ይከብባቸዋል፡፡ የሥነ ፍጥረትን መሪነት ልንከተል የምንችለው እስከዚያ ድንበር (መዳረሻ) ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ላይ ግን የሰው
አእምሮ ያቆማል፡፡ የፈጣሪ ባሕርይ ከፍጥረቱ ሁሉ ሕሊና በላይ ነውና፣ መጀመሪያና መጨረሻም የለውምና፣ ከፍጥረት ውስጥ ተነሥቶ በሚደረግ ፍለጋና
ጉዞም ሊደረስበት አይችልምና፡፡”
(ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ለዩኖሚየስ ሁለተኛ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ)
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም እንዲህ ይላል፡-

 “ብዙ የማውቃቸው ነገሮች አሉ፣ ሆኖም እንዴት ላብራራቸው (ልገልጻቸው) እንደምችል ግን አላውቅም፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ እንዳለ (ምሉእ
በኩለሄ እንደሆነ) አውቃለሁ፡፡ ሆኖም እንዴት ብሎ በሁሉም ቦታ እንደሚኖር ግን አላውቅም፡፡ ዘለዓለማዊ እንደ ሆነና መጀመሪያ እንደ ሌለው አውቃለሁ፤
እንዴት እንዲህ እንደ ሆነ ግን አላውቅም፡፡ አንድ በራሱ ህልው የሆነ ሕያው ህልውናውን ከሌላም ሆነ ከራሱ ሳይቀበል እንዴት ሊኖር እንደሚችል አእምሮዬ
ለመረዳት አይቻለውም፡፡ እርሱ የባሕርይ ልጅ እንዳለው አውቃለሁ፣ እንዴት እንደ ሆነ ግን አላውቅም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ እንደ ሠረጸ አውቃለሁ፣
መንፈስ ቅዱስ እንዴት ብሎ ከእርሱ እንደ ሆነ ግን አላውቅም፡፡

 “ዳዊት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማወቅን በተመለከተ ባሰበ ጊዜ ማለት የቻለው ‘እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች በረታች፣ ወደ እርሷም ለመድረስ
አልችልም’ ነው፡፡ መዝ. 138፡6 ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ልደት መናገር የሚችል አለመኖሩን በማድነቅ ‘ወመኑ ይነግር ልደቶ - ልደቱን ማን ሊናገር
ይችላል?’ በማለት በአግራሞት ይጠይቃል፡፡ ኢሳ. 53፡8 ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔር ፍርዱ የማይመረመር፣ ለመንገዱም ፍለጋ የሌለው መሆኑን
በማድነቅ ይናገራል፡፡ ሮሜ 11፡33 እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጀው ሽልማት የማይመረመር ነው (ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው፣ በሰውም ልብ
ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ 1 ቆሮ. 2፡9)፤ የእግዚአብሔር ሰላም አእምሮን ሁሉ ያልፋል (ፊል. 2፡9)፤
ስጦታውም ሊነገር አይችልም (2 ቆሮ፣ 9፡15)፡፡

 ታዲያ የእግዚአብሔር ፍርዱ የማይመረመር፣ መንገዱ ፍለጋ የሌለው፣ ሰላሙ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ፣ ስጦታው ሊነገር (ሊገለጽ) የማይችል፣ ለሚወዱት
ያዘጋጀው ነገር በሰዎች ልቡና ያልታሰበ ከሆነ እነዚህ ከእርሱ የሚገኙት ነገሮች የማይመረመሩና የማይደረስባቸው ከሆኑ እነዚህን ያዘጋጀው ራሱ
እግዚአብሔርማ ምን ያህል የማይመረመር ነው ይሆን! መናፍቃን ሆይ፣ የተፈጠሩት የማይታወቁ፣ የማይለጹና የማይመረመሩ ሲሆኑ እነዚህን የፈጠራቸው
እርሱ ግን ይታወቃል፣ ይመረመራል ከማለት በላይ ምን እብደት አለ?
 “መላእክት በእግዚአብሔር መገለጥ ፊት ሲቆሙ ፊቱን እንኳ ማየት የማይችሉ ከሆነ ‘እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ላውቀው እችላለሁ’ ይል ዘንድ ሰው
ማን ነው? . . . ወገኖቼ ሆይ፣ አርዮሳውያንን (አኖሚያኖችን) አእምሯቸው የታመመና የማሰብ ዓቅማቸውን በሕመም ያጡ ሰዎችን እንደምታዩ አድርጋችሁ
ልትመለከቷቸውና ልታዝኑላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን በባሕርዩ ላውቀው እችላለሁ ማለት ከአእምሮ መታወክ እንጂ ከጤና የሚመጣ አይደለምና፡፡

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም፣ ስለ መለኮታዊ ባሕርይ አይመረመሬነት)

አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም እንዲህ ይላል፡-


 “. . . ወኢርቱዕ እንከ ናስተማስሎ በእሳት ምድራዊ እሳትሰ ቦቱ መጠን ወቦቱ አካል ወመለኰትሰ ኢይትከሃል ይትበሃል ዘንተ የአክል ወዘንተ ይመስል -
በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም፣ ለእሳትስ መጠን አለው፣ ልክም አለው፡፡ መለኰት ግን ይህን ያህላል፣ ይህንም ይመስላል ሊባል አይቻልም፡
፡” ቁ. 47
 “አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ክበብ ከመ ፀሐይ ወወርኅ ወዐቅም ከመ ሰብእ አላ መንክር ውእቱ ወንቡር ዲበ አርያሙ ኀበ ኢይበጽሖ ሕሊና ሰብእ ወኢዘመላእክት
አእምሮ - ለመለኮት እንደ ፀሐይና እንደ ጨረቃ ክበብ፣ እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም፣ ድንቅ ነው እንጂ፤ የሰው ሕሊና የመላእክትም አእምሮ
በማይደርስበት በአርያሙ የሚኖር ነው እንጂ፡፡” ቁ. 48
 “ወሶበ እኄሊ ዘንተ ይፈቅድ ሕሊናየ ይጽብት ዕመቀ አብሕርቲሁ ለወልድኪ ወያመዐብሎ መዋግደ ምሥዋራቲሁ ለፍቁርኪ ወሶበ እሔሊ ዘንተ ካዕበ
ይፈቅድ ሕሊናየ ይዕርግ ላዕለ ወይጻእ በሥውር ወይቅላዕ መንጦላዕተ ምሥዋራቲሁ ለሕያው ወይፈርህ እምነደ እሳት ወኢይበጽሕ እስከ መጠነ መንፈቆሙ
ለዐየራት - ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ሕሊናየ የልጅሽን የባሕሩን ጥልቅነት ሊዋኝ ይወዳል፣ የወዳጅሽ የመሠወሪያው ማዕበልም ያማታዋል፡፡ ዳግመኛም ባሰብሁ
ጊዜ ሕሊናየ ተሰውሮ ወደ ላይ ወጥቶ የሕያው መሠወሪያ የሆነውን ሊገልጥ ይወዳል፣ ከነደ እሳትነቱ የተነሣ ይፈራል፣ ከዐየራት ከእርቧቸው እርቦ
አይደርስም፡፡
 “ወሶበ እሔሊ ዘንተ ይፈቅድ ሕሊናየ ይጸዐን መትከፈ ነፋሳት ወይስርር ምሥራቀ ወምዕራበ ሰሜነ ወደቡበ ወውስተ ኩሉ አጽናፍ ይርአይ ህላዌሆሙ
ለፍጡራን ወይመጥን ዕመቃቲሆሙ ለአብህርት ያእምር ሉዐሌሁ ለሰማይ ወየአይይ እንተ በኩለሄ ወበኩሉ ይስእን ወይገብእ ኀበ ዘትካት ሉዐሌሁ - ይህንም
ባሰብሁ ጊዜ ሕሊናየ በነፋስ ትካሻ ተጭኖ በምሥራቅና በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ በዳርቻውም ሁሉ ሊበር ይወዳል፡፡ የፍጡራንን አኗኗር ያይ ዘንድ፣
የአብሕርትንም ጥልቀታቸውን ይለካ ዘንድ የሰማይ ርዝመቱን ያውቅ ዘንድ በሁሉ ዘንድ በሁሉም ይዞራል፣ አቅቶት ወደ ቀደመ አኗኗሩ ይመለሳል፡፡
 “ወይእዜኒ ኢንኅሥሥ ዕበያቲሁ ወኢንጠናቀቅ ማዕምቅቲሁ ዘኢይክል ልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት ለወድሶተ መጠነ ዕበዩ - አሁንም ገናንነቱን አንመርምር፣
ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ፣ የገናንነቱን መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው፡፡”

(ቅዳሴ ማርያም፣ ቁ. 44-87)


ይህ አይመረመሬነቱና አይደረሴነቱ ግን የባሕርዩን አለመታወቅ በተመለከተ እንጂ እግዚአብሔር ከማኛውም ነገር በላይ ለፍጥረቱ ቅርብና የፍቅር አምላክ ነው፡፡
እግዚአብሔር በባሕርዩ ሩቅና ምጡቅ፣ ማንም ፍጡር መርምሮ ሊደርስበት መቸም መች የማይቻለው (Transcendent) ሲሆን በፍቅሩ ደግሞ የቅርብ አምላክ
(Immanent) ነው፡፡ ሰው ሆኖ በእኛ ባሕርይ የተገለጠ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር እስከ ማጠብ፣ በመስቀል መራራ ሞትን ስለ እኛ እስከ መሞት ደርሶ ፍቅሩን የገለጠ
ትሑት የፍቅር አባት ነው፡፡

“ሙሴም እግዚአብሔርን እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለው፡፡ … እግዚአብሔርም፡- ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ፡፡ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ
አለ፣ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፣ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፣ ጀርባዬንም
ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም፡፡” ዘጸ. 33፡17-23
ይህን ታላቁ ሊቅ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ እንዲህ ተርጉሞታል፡-
o ፊት - የተባለ ባሕርዩ ነው፡፡ “ፊቴ አይታይም” ማለቱ ሰው የእግዚአብሔርን ባሕርይ ሊደርስበት የማይችል መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡

o ጀርባ - የተባለው ምንም እንኳ አንድን ነገር በትክክል ለማወቅ የሚያስችለው ፊቱን ማየት ቢሆንም፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ጀርባውን ማየት ከምንም የሚሻል
መጠነኛ ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ስለዚህ ፊት የተባለ ባሕርዩን ማወቅ ባንችልም ጀርባ የተባለ ስለ እርሱ ለማወቅ የሚረዱ ነገሮችን ሰጥቶናል ማለት
ነው፤ “ጀርባዬን ታያለህ” ማለት ይህ ነው፡፡
ስለዚህ የምናውቀው ባሕርዩን ሳይሆን ኃይሉንና ሥራውን ነው ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር የተገለጠባቸው (እርሱን የምናውቅባቸው) መንገዶች፡-

1) ሥነ ፍጥረት
2) አምላካዊ መግቦት
3) መጽሐፍ ቅዱስ
4) ኢየሱስ ክርስቶስ
1) ሥነ ፍጥረት

ከምንም ነገር በፊት እግዚአብሔር ራሱን የገለጠው በሥነ ፍጥረት አማካኝነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን በነቢዩ በዳዊት ሲናገር እንዲህ ብሏል፡-

“ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር


ወግብረ እደዊሁ ያየድዓ ሰማያት
አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዓ ቃሎሙ
ውስተ ኩሉ ምድር ወጽአ ነቢቦሙ” መዝ. 18፡1-2

ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና፡፡ የማይታየው ባሕርይ እርሱም
የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታዉቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን
ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፡፡” ሮሜ 1፡ 19-21 ስለዚህ ሰው ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለውን ያህል ለማወቅ ከሥነ ፍጥረት መምህርነት
ሊያውቅና ሊማር ይችላል፣ እግዚአብሔርን ላለማወቅና እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ተገቢውን ክብር ላለማክበርና ላለማመስገን መምህር ስላላገኘሁ ነው ብሎ
ማመካኘት አይችልም ማለት ነው፡፡

ጠርጠሉስ የተባለው ሊቅም እንዲህ ብሏል፡- “እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ በኋላ ዘመን በመጽሐፍ የሚያስጽፈውን አስቀድሞ በሥነ ፍጥረት መጽሐፍነት አስጽፎታል፡
፡” አንድ ፈለስፋም ቅዱስ እንጦንዮስን፡- “በዚህ በረሃ ስትኖር ምን ታነባለህ? ከምንስ ትማራለህ?” ብሎ ጠየቀው፤ ቅ. እንጦንስም ሲመልስ፡- “ፈላስፋ ሆይ፣ የእኔ
መጻሕፍት ሥነ ፍጥረት ናቸው” አለው፡፡ የሥነ ፍጥረት የዓይነቱ ብዛት፣ ውበቱ፣ ስምምነቱ፣ ሥነ ሥርዓቱ፣ የረቂቃኑ ርቀትና የግዙፋኑ ግዝፈት፣ … ስለ አስገኚያቸው
መኖርና ከሃሊነት ሳያቋርጡ የሚናገሩ መምህራን፣ ሳይታጠፉ ሁል ጊዜ ተዘርግተው የሚነበቡ መጻሕፍት ናቸው፡፡

2) አምላካዊ መግቦት
ከሥነ ፍጥረት በተጨማሪ ሌላው ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔር የሚያስተምረው አምላካዊ መግቦት ነው፡፡ ለሥነ ፍጥረት በሕይወት መኖር መፈጠራቸው ብቻ
አይበቃም፡፡ አንድ ሕፃን በየጊዜው የእናቱን ጡትና ተገቢውን እንክብካቤ ካላገኘ በስተቀር መወለዱ ብቻ በሕይወት እንዲኖርና እንዲያድግ አያስችለውም፤ እንዲሁም
ፍጥረታትም እንደየ ተፈጥሯቸው የሚያስፈልጋቸውን ምግብና በየጊዜው ካላገኙ በስተቀር መፈጠራቸው ብቻውን ለመኖር አያበቃቸውም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ
ፍጥረት፣ ረቂቃኑም ሆኑ ታላላቆቹ፣ ግኡዛኑም ሆኑ ባለ አእምሮዎቹ እያንዳንዷን የመጨረሻ ትንሽ የምትባለውን የጊዜ ቅጽበት እንኳ የሚኖሩት በእግዚአብሔር
መለኮታዊ መግቦት ነው፡፡

ፍጥረትን መፍጠር በመጀመሪያዎቹ ስድስት ቀናት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህን የተፈጠረውን ፍጥረት የመመገቡና የመንከባከቡ አምላካዊ መግቦት ግን በሰባተኛውም ቀን
ያልተቋረጠ ሥራ ነው፡፡ መግቦቱ ከተቋረጠ ፍጥረት ሁሉ ህልውናው ያከትማልና፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን “አቡየሂ እስከ ይእዜ ይገብር ወአነሂ እገብር - አባቴ እስከ ዛሬ
ይሠራል፣ እኔም እሠራለሁ” ያለው፡፡ ዮሐ. 5፡17 ዛሬም ድረስ ያልተቋረጠውና ወደፊትም የሚቀጥለው ሥራ ይህ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መግቦት ነው፡፡

ሐዋርያውም “እስመ ኩሉ እምኔሁ ወኩሉ በእንቲአሁ ወኩሉ ቦቱ ወሎቱ ስብሐት ለዓለመ ዓለም አሜን - ሁሉ ከእርሱ፣ ሁሉ በእርሱ እና ሁሉም ለእርሱ ነውና
ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ያለው ይህንኑ ጥልቅ ምሥጢር በጥልቀት በመረዳቱ ነገሩ እጅግ ድንቅና ከሐተታ በላይ ስለ ሆነበት ነው በአድናቆትና በምስጋና
የዘጋው፡፡ “ሁሉ ከእርሱ ነው” ማለት ማንኛውም ፍጥረት ሁሉ የተገኘው ከእርሱና ከእርሱ ብቻ መሆኑን መናገሩ ነው፤ “ወኩሉ በእንቲአሁ - ሁሉ በእርሱ ነው”
ማለት ደግሞ ፍጥረት ሁሉ የሚኖረው በእርሱ መጋቢነትና ጠባቂነት መሆኑን ሲሆን “ወኩሉ ቦቱ - ሁሉ ለእርሱ ነውና” ማለቱ የፍጥረት መጨረሻና መዳረሻ እርሱ
መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሮሜ 11፡36፡፡ ነቢዩ ዳዊትም በመዝ. 103 ላይ የእግዚአብሔርን መግቦት ያደንቃል፡፡

3) መጽሐፍ ቅዱስ
እግዚአብሔር ቅዱስ ቃሉን በመጽሐፍ ቅዱስ በነቢያትና በሐዋርያት አማካኝነት አስጽፎ የሰጠን ቅዱስ የሆነውን ፈቃዱንና ወደ እርሱ የሚመራውንና የሚያደርሰውን
የሕይወትን መንገድ በግልጽ እናወቅ ዘንድ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ይነግሮሙ ለሕዝቡ በመጽሐፍ - እግዚአብሔር ሕዝቡን በመጽሐፍ ይነግራቸዋል” እንዳለ፡፡ መዝ.
86፡6 ወልድ ዋሕድ መድኃኒታችንም “መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፡፡” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ. 5፡39 ሰው ሲፈጠር በሕሊናው አምላካዊ ሕግ የተጻፈበት
ቢሆንም በኃጢአት ብዛትና በግዴለሽነት ምክንያት ያ የአእምሮው ሕግ እየደበዘዘ ስለ ሄደ የጽሑፍ ሕግ መስጠቱ ያን ለመርዳት ነው፤ ነቢዩ “ወወሀበ ሕገ ለረድኤት
- ሕግን ለእርዳታ ሰጠ” ያለው ይህን ሲመሰክር ነው፡፡ ኢሳ. 8፡20

4) ኢየሱስ ክርስቶስ

የመገለጥ የመጨረሻው ደረጃ ራሱ አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ የተገለጠው መገለጥ ነው፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ ሲል እንደ ገለጸው፡- “ለእግዚአብሔርሰ አልቦ ዘርእዮ ግሙራ
አላ ወልድ ዋሕድ ዘሀሎ ውስተ ሕፅነ አቡሁ ውእቱ ነገረነ” ዮሐ. 1፡18 ጌታችንም፡- “ከእንግዲህ ባሮች አልላችሁም፣ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤
ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄያችኋለሁና፡፡” ዮሐ. 15፡15 ስለሆነም በምሥጢረ ሥጋዌ የተፈጸመው መገለጥ የመገለጥ ሁሉ
ርእስ (አክሊል) ነው፡፡ ምክንያቱም ራሱ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆኖ “እኔን ያ አብን አየ” በማለት ራሱን ገልጦልናል፣ ፈቃዱን አሳውቆናልና ከእንግዲህ ወዲህ ይህ
ቀረን የምንለው ነገር የለምና ነው፡፡
5. በነገረ ሃይማኖት ላይ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች
ሃይማኖት ከእግዚአብሔር የተሰጠና የተቀበልነው እንደ መሆኑ፣ እንዲሁም በአንድ በኩል ሰጭው እግዚአብሔር ባሕርዩ የማይደረስበት ረቂቅና ምጡቅ በመሆኑ፣
በሌላ በኩል ደግሞ ተቀባዮቹ እኛ ሰዎች ዓቅማችን ውስን ስለ ሆነ፣ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ በነገረ ሃይማኖት ከሚያስፈልጉት ጥንቃቄዎች ዋና ዋናዎቹ
የሚከተሉት ናቸው፡፡

1) ከተጻፈው አለማለፍ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ኢትጻኡ እምቃለ መጻሕፍት - ከተጻፈው አትለፍ” በማለት ጠንካራ መንፈሳዊ መመሪያ ሰጥቶናል፡፡ 1 ቆሮ. 4፡6 ስለዚህ ያልተጻፈ
መመርመር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያልተጻፈን ወይም ያልተነገረን ነገረ ሃይማኖት እመረምራለሁ ማለት ታላቅ ስህተት ነው፤ ከዚያም በላይ እግዚአብሔርን መዳፈር
ነው፡፡

ከተጻፈውም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሁሉንም ነገር አውቃለሁ ወይም ማወቅና መመርመር አለብኝ የሚል መንፈስ ሊኖር አይገባም፡፡ ሊቀ ነቢያት
ሙሴ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ሕግ ለሕዝቡ በድጋሜ ከነገረ በኋላ ወደ መጨረሻው ላይ ሲያጠቃልል“ምሥጢሩ ግን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው” በማለት
ነበር የደመደመው፡፡ ዘዳ. 29፡29

ሐዋርያው ስለዚህ ሲያስጠነቅቅ ለቲቶ በላከለት መልእክቱ እንዲህ ብሏል፡-

“እግዚአብሔርን የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፣ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ፡፡ ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤ ነገር ግን
ሞኝነት ካለው ምርመራና ከትውልዶች ታሪክ ከክርክርም፣ ስለ ሕግም ከሚሆን ጠብ ራቅ፤ የማይጠቅሙና ከንቱዎች ናቸውና፤ መለያየትን የሚያነሣ ሰው ጠማማ እንዲሆን
በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ አንድ ጊዜ ሁለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ፡፡” ቲቶ 3፡8-11

ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱም “አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ” ይላል፡፡ 2 ጢሞ. 4፡4 እንዲሁም ይህን በአጽንዖት ሲያሳስብ “ይህን አሳስባቸው፣ በቃልም
እንዳይጣሉ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፣ ይህ ምንም የማይረባ፣ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና፡፡” ብሏል፡፡ 2 ጢሞ. 2፡14

2) ዓቅማችንን ማወቅ

ሃይማኖት ነገረ እግዚአብሔርን የተመለከተ እንደ መሆኑ የእግዚአብሔርን ባሕርይና አሠራሩን እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ እኛ ዓቅማችን ይፈቅዳል ወይ? የሚለውን
ነገር ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ነቢዩ ስለ ወልድ ልደት ሲናገር ከሕሊናው በላይ ቢሆንበትና ቢረቅበት ዓቅሙን በማወቅ “ወመኑ ይነግር ልደቶ - ልደቱን ማን ይናገራል?
(ማን ይናገር ዘንድ ይችላል?)” አለ፡፡ ኢሳ. 53፡8፤ የሐዋ. 8፡33

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ለእመቤታችን ስለ ነገረ ፅንሠቱ ሲናገር “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል” አለ እንጂ እንዴት
እንደሚፀነሥ ሐተታና ማብራሪያ አልሰጠም፤ ይኸ ምሥጢር ከራሱ ከመልአኩም ዓቅም በላይ ነውና፡፡ መልአኩ የተላከበትን ተናገረ እንጂ ከዚያ አልፎ ከዓቅሙ በላይ
የረቀቀ ስለ ሆነው የፅንሠቱ ምሥጢር ወደ ማብራራት አልሄደም፡፡ እንዲሁም መልአኩ ለአረጋዊ ዮሴፍ ሲነግረው “እሰመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ
- ከእርሷ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነውና” በማለት ነው የዘጋው፡፡ ማቴ. 1፡20

ወንጌላውያኑም የጻፉት ይኸንኑ የመላእክትን ቃል እንዳለ ነው፣ በዚያ ላይ ሐተታ አልሰጡም፡፡ ስለዚህ መልአኩም ሆኑ ወንጌላውያኑ ዓቅማቸውን አውቀው “የመንፈስ
ቅዱስ ምሥጢር ነው” ያሉትን አልፈን እናትታለን፣ እንመረምራለን ብለን እንዳፈር ዘንድ እኛ ማን ነን? ስለዚህ ነገረ ፅንሠቱን፣ ነገረ ልደቱን፣ ነገረ ትንሣኤውን፣
ምሥጢራቱን … በታላቅ አክብሮት ማሰብና ለመተንተን ከመዳፈር ይልቅ በአንክሮና በተደሞ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነት በማድነቅና በማመስገን
ብንቀበላቸው፣ የቀረውንም በምንችለው መጠን እንዲገልጥልን በጸሎት ብንጠይቀው በእጅጉ መልካም ይሆንልናል፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞንም “እግዚአብሔር በሰማይ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፣ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፤ ስለዚህም ቃልህ
ጥቂት ትሁን፡፡” ያለው ለዚህ ነው፡፡ መክ. 5፡2-3 እንዲሁም “ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ” ይላል፡፡ መክ. 5፡6

3) እግዚአብሔር እናውቀው ዘንድ ግልጽ ያላደረጋቸውን ነገሮች አለመዳፈር

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመዳን አስፈላጊና ወሳኝ የሆኑት ነገሮች በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ተገልጸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈውም ማወቅ የሚገባንን መሠረታዊ
ነገር አውቀንና አምነን ሕይወትን ለማግኘት እንድንችል ወደ ድኅነት ለመምራት ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ጽፎ ወደ መጨረሻው ገደማ ሲደርስ
እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡- “ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርሰቶስ የእግዚአብሔር ልጅ
እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፏል፡፡” ዮሐ. 20፡30-31፡፡ ስለዚህ አምነን ሕይወትን እናገኝ ዘንድ የሚያስፈልገን
በቅዱሳት መጻሕፍት በበቂ ሁኔታ ተጽፎልናል ማለት ነው፡፡

ሆኖም ግን አምነን ሕይወትን ለማግኘት የግድ አስፈላጊ ያልሆኑና በመጽሐፍ ቅዱስ ረቀቅና ሰወር ባለ ሁኔታ የተገለጹ ነገሮችን ከመጠን አልፎ አለመዳፈር ተገቢ ነው፡
፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ ወተት ለሚጋቱ ለሕፃናተ አእምሮ እና ጠንከር ያለ ነገር መመገብ ለሚችሉም ለሁሉም የሚሆን አለው፡፡ ገና ሕፃናት የሆንነው ለበሰሉት
የሚሆነውን ካልበላሁ ሞቼ እገኛለሁ ብንል ትርፉ ጥርስ መሰበር ጤና መቃወስ ነው የሚሆነው፡፡ ዕብ. 5፡12-14፤ 1 ቆሮ. 3፡2 ከዚያም ባለፈ እርሱ ባወቀ ሰወር ባለ
ሁኔታ የተነገሩና የተጻፉ ነገሮችን ግድ ካልመረመርሁ ማለት ጭቅጭቅና ንትርክን ብሎም መለያየትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
4) አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ አለመንጠልጠል

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ ብቻ አይደለም፤ ጥቂት ጥቅሶች ብቻም አይደለም፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ጥቅሶችንና ሃሳቦችን የያዘ ታላቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ሆኖም
ሁሉም ጥቅሶችና መጻሕፍት የያዙት ሃሳብ እርስ በእርሱ የሚስማማና ወጥ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት መጻሕፍት ከ1,500 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ
ገደማ አንሥቶ እስከ 1ኛው መቶ ዓመት ድኅረ ልደተ ክርስቶስ የተጻፉ ናቸው፤ ይህም ማለት በጥቅሉ 1,600 ዓመታት ዘመንን የያዘ ማለት ነው፡፡ ከዚሁም ጋር
በተለያዩ ዘመናት በነበሩና የተለያየ የትምህርት ደረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ፣ … በነበራቸው ሰዎች የተጻፈ ቢሆንም የሃሳቡ ባለቤት እግዚአብሔር ስለ ሆነ ሁሉም የጻፉትና
የተናገሩት እርስ በእርሱ የሚመጋገብና አንዱ ሌላውን የሚያብራራ እንጂ የሚቃረን ነገር የለውም፡፡

ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ስንረዳ ከዚህ መንፈስ አንጻር ሊሆን ይገባል፡፡ ይህን ከዚህ በታች በሚታየው ሥዕል (ፒራሚድ) መስሎ ማየት ይቻላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ
ተደጋግመው በአጽንዖት የተገለጡትና ለመዳን አስፈላጊ የሆኑት መሠረታውያን እውነታዎች እንደ ፒራሚዱ መሠረት ናቸው፡፡ የክርስትና ትምህርት መሠረት እነዚያ
ናቸው፡፡ ከዚህ በስተቀር ምናልባት ለመረዳት አስቸጋሪ የሚመስል ወይም ገጸ ምንባቡ ሲታይ ከሌሎቹ ወጣ ያለ ሃሳብ የያዘ የሚመስል አንድ ጥቅስ ወይም ኃይለ ቃል
ወይም ጥቂት ጥቅሶች ቢገጥሙን ከታች ካለው ከመሠረቱ ጋር ተስማሚ በሆነ መልኩ መረዳትና መተርጎም ይገባል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውጭ አንድ ጥቅስ ብቻ
አንጠልጥሎ “እንዲህ ይላል” እያሉ መሮጥ ሌላውን ሁሉ ጥቅስና ሃሳብ የሌለ አስመስሎ መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ጥቅስ ብቻ ማስመሰል ነው፡፡ ከታች እንደሚታየው
የተገለበጠ ፒራሚድ ይሆናል፣ ይህ የተገለበጠ ፒራሚድ ሊቆም እንደማይችል ሁሉ የክርስትና አስተምህሮ መሠረታዊው እውነታም በአንድ ጥቅስ ተገልብጦ ሊቆም
አይችልም፡፡

ትክክለኛ የፒራሚድ አቋቋም የተገለበጠ ፒራሚድ

የመናፍቃን አንዱ መገለጫቸውና መነሻቸው አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ መመሥረትና ሌላውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ሁሉ የሌለ እስኪመስል ድረስ ያንን ጥቅስ ብቻ
ከመጠን በላይ በመለጠጥና ለራሳቸው እንዲመች አድርገው በመተርጎም ስተው ማሳት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም የሚከተሉትን መናፍቃን ማየት እንችላለን፡-
 ክርስቶስ በዚህ ዓለም እንደ ገና ተገልጦ ሺህ ዓመት ይነግሣል፣ ያን ጊዜም ምርጦቹን ከእርሱ ጋር ይሾማቸዋል እያሉ ቤተ ክርስቲያንን ሲያዉኩ የነበሩት ሺህ ዘመነኞች
(Millenarianists) ተብለው ይጠሩ የነበሩት መናፍቃን ብቸኛ መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው በራእየ ዮሐንስ በምዕራፍ 20 ከቁጥር 4-5 የተገለጸው ብቻ ነበር፡፡

 አርዮስና ተከታዮቹ አርዮሳውያን የሚያቀነቅኑት ዋና ጥቅሳቸው ምሳ. 8፡22 ላይ የተጻፈው ነበር፡፡ ይኸን ከሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ ነጥለውና ገንጥለው በመሮጥ
እንደ እብድ ውሻ ያገኙትን ሁሉ እየለከፉ አስጸያፊ የሆነ ደዌአቸውን እንደ ወረርሽኝ ያስተላልፉ ነበር፡፡

 ፕሮቴስታንቶች ደግሞ በሌላ ቦታ የተነገሩትንና አጠቃላይ የክርስትናን አስተምህሮ ሁሉ ወደ ኋላ ጥለው በቅል ውስጥ እንዳለ አንድ ወይም ጥቂት የባቄላ ፍሬ እያንኳኩ
የሚረብሹት ሮሜ 8፡34 ን በመጥቀስ ነው፡፡ እንዲሁም ስለ መዳን የሚያንኳኳቸው አንድ ሁለት ጥቅሶችን ነው፡፡ ሌሎች መናፍቃንም ጠባያቸውና አካሄዳቸው ተመሳሳይ
ነው፡፡

በአጠቃላይ እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን ያህል እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነ መጽሐፍ ይቅርና ማንኛውንም መልእክት እንኳ በትክክል ለመረዳት ሙሉ ይዘቱን በጥሞና መረዳት የግድ
ይላል፡፡ “አንብባ ለመልእክት እምጥንታ እስከ ተፍጻሜታ” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ጥርስ እንኳ የሚያምረውና አገልግሎቱን በጤናማ ሁኔታ የሚሰጠው ሁሉም በየቦታው በአንድ
ላይ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፤ አንድ ጥርስ ብቻውን ለምንም አይሆንም፡፡ ከቤት ክዳን መካከል የተመዘዘ አንድ ሣር ወይም አንድ ቆርቆሮም ብቻውን ጣራ ወይም ክዳን አይሆንም፡፡
ስለዚህ ነገረ ሃይማኖት ማስተዋልና ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

You might also like