You are on page 1of 8

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን

📖📖መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ላንብብ📖📖

ክፍል ፩(1)

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ለሚያመልኩ በእውነተኛው የእምነት ሕይወት መመራት ለሚፈልጉ


ሁሉ የእምነትን በጎ ሥራ ማጣፈጫ የውስጥን ማንነት መለወጫ የውጪን ገጽታ በስነ-ምግባር
መገንቢያ መሣሪያ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ እውነተኛ ይዘቱ አኳያ ሊነበብ ይገባል! የማንበቡን
ጥቅም 2 ጢሞ 3፡17፤ ት.ሕዝ 3፡1፤መዝ 118፡103 "የሰው ልጅ ሆይ አፍህ ይብላ በምሰጥህም በዚህ
መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ።እኔም በላሁት በአፌ ውስጥ እንደማር ጣፈጠ"

የእግዚአብሔር ቃል አንደበትን የሚያጣፍጥ ህሊናን በበጎ ነገር የሚማርክ ውስጥን እየወቀሰ የሚያርም
ነው! ስለዚ ዘውትር ልንበላውና በአፋችን ሊጣፍጥ ይገባል።መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማንበብ
እንዳለብን ወደሚጠቁመን መሠረታዊ ነጥብ ስናልፍ፦ሁለት መሠረታዊ ነገሮች መረዳት አለብን።

1. አፍአዊ(ውጫዊ) ዝግጅት

2. ውስጣዊ(የውስጥ) ዝግጅት

ሁለቱንም በቅደም ተከተል ስንመለከት

1. አፍአዊ ዝግጅት

አፍአዊ ዝግጅት የሚባለው መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነበው አካል ለማንበብ ከመቅረቡ በፊት ከልቦናውና
ከአይምሮው ውጪ ሊያዘጋጀውና ለያመቻቸው የሚገባን የሚያጠቃልል ነው።አፍአዊ ዝግጅትን የግል
ዝግጅትና የማህበር ዝግጅት በማለት በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።

1.1 የግል ዝግጅት(የግል ንባብ)

የግል ዝግጅት (የግል ንባብ) አንባቢው በግሉ ሊያረግ የሚገባውን ሁሉ የሚመለከት ነው።ማለትም

👉የራስ(የግል) መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት

መጽሐፍ ቅዱስ ዕለት በዕለት የኑሯችን የመንፈስ ምግብ በመሆኑ ሊለየን አይገባም።በሕይወታችን ዋጋ
ከፍለን መግዛትም ሆነ ማንበብ ካለብን መጽሐፍ ቅዱስ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለን እራሳችንን
የምንተረጉምበትን ማብራሪያ አልያዝንም ማለት ነው።ለሰዎች የሕይወታቸው የመጀመሪያው ሀብት
መጽሐፍ ቅዱስ ነው።መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት መሆን ግድ ነው።

ኦ.ዘዳ 6፡6-9 "ይህን ቃል በልብህ ያዝ ለልጅህም አስተምረው በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድህም


ስትሄድ ስትተኛም ስትነሳም ተጫወተው በእጅህ ምልክት አርገህ እሰረው በአይኖችህም መካከል እንደ
ክታብ ይሁንልህ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።" የመጽሐፍ ቅዱስና የሰው ትስስር
ይህን ያህል ሊሆን ይገባል።

👉የሚያነቡበትን ቦታና ጊዜ መምረጥ

መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የሚገኘው የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ስናነበው ከእግዚአብሔር ጋር


እየተነጋገርን መሆኑን መዘንጋት የለብንም።ስለዚህ ንግግራችን የተዋከበ ያልተሰበሰበ ሕሊና
የሚታወክበት እንዳይሆን የሚደረገውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንባብ ጫጫታ፣ወሬ፣ግርግር፣ በዓይን እየታዩ
ሊረብሹ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ ይገባል።ይህንን ለማድረግ የምንመርጠው ቦታና ጊዜ ወሳኝ ነው።

👉ማስታወሻ መያዝ

አበው በብሂላቸው "በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል" እንዲሉ በቃል ብቻ ማንበብ ለጊዜው
በአንባቢው ህሊና ውስጥ ከሚፈጥረው ስሜት በስተቀር ሊረሳ ይችላል።እንዲህ አይነቱን ችግር
ለመፍታት ማስታወሻ መያዝ ጥቅሙ የላቀ ነው።መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ማስታወሻ የሚይዝ አንባቢ
ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ
የሕይወታችንን ታላቁን ጥያቄ የምንመልስበት በመሆኑ ተገቢ ነው።

1 ጴጥ 3፡15 "በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር


የተዘጋጃችሁ ሁኑ"

👉የማህበር ዝግጅት

ይህ ዝግጅት መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ቦታና ጊዜ በጋራ የሚያነቡ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባቸውን
ዝግጅት ያጠቃልላል።

2. ውስጣዊ ዝግጅት

ውስጣዊ ዝግጅት የሚባለው አንድ ሰው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብ ከመቀመጡ በፊት በልቦናው
ሊያደርገው የሚገባውን ዝግጅት ነው ሚያመለክተው
ጠቅለል ባለ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ፦

1. የመጽሐፍ ቅዱስን አከፋፈልና ቁጥሮች ማወቅ

2. በፈሪሀ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን በመፍራት) መኖር

3. የምናነበው እንዲገባን መጸለይ

4. ያልገባንን ንባብ የምንጠይቃቸውን መምህራን አጋር ማረግ እጅግ ወሳኝ ነው።

በቀጣይ

📖የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም

📖የመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤ

📖የመጽሐፍ ቅዱስ አከፋፈል

📖የመጽሐፍ ቅዱስ ህዳግ አወጣጥ

📖የግዕዝ ቁጥር

📖መጽሐፍ ቅዱስን በጊዜና በሰአት ከፋፍሎ የማንበብን ስልት ይዤ እቀርባለሁ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን

📖📖መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ላንብብ📖📖

ክፍል ፪(2)

#የመጽሐፍ #ቅዱስ #አከፋፈል

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ለሚሻ ሰው አከፋፈሉን ማወቅ ግድ ይለዋል የመጽሐፍ ቅዱስ አከፋፈል
ሳይታወቅ የሚደረግ የንባብ ሂደት ወደማያውቁት ሀገር ገብቶ እንደ መቸገር ይቆጠራል።የንባብን አካሄድ
ለማወቅ የመጀመሪያው በር የመጽሐፍ ቅዱስን አከፋፈል ማወቅ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ይከፈላል

1. ብሉይ ኪዳን(የቆየ ስምምነት)

2. ሐዲስ ኪዳን(አዲስ ስምምነት)ይባላሉ

እነዚህ በሁለት ተከፍለው የምናያቸው ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን የሰው ልጅ የሕይወቱ ምስጢር
መገኛ ናቸው።ብሉይ ኪዳንን ለብቻው ከፍለን ስናይ፦
ብሉይ ኪዳን በአራት ይከፈላል

1. የሕግ ክፍል

2. የታሪክ ክፍል

3. የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት

4. የትንቢት መጻሕፍት

ብሉይ ኪዳንን ስናነብ እነዚህን አራት ዓይነት በብሉይ ኪዳን የሚገኝ የመንፈስ ምግቦችን ለይቶ
ማስተዋል ያስፈልጋል።በትክክለኛ አከፋፈላቸው ሲነበቡ አይደባለቁም ግብና አቅጣጫ ያለው ንባብ
እናነባለን።በአራት የከፋፈልናቸውን የብሉይ ኪዳን አከፋፈል እንመልከት!

ብሉይ ኪዳን

1. የሕግ መጻሕፍት፦

=>ኦሪት ዘፍጥረት

=>ኦሪት ዘጸዓት

=>ኦሪት ዘሌዋውያን

=>ኦሪት ዘኁልቅ

=>ኦሪት ዘዳግም

2. የታሪክ መጻሕፍት

=>መጽሐፈ ኢያሱ

=>መጽሐፈ መሳፍንት

=>መጽሐፈ ሩት

=>1 ኛ ሳሙኤል

=>2 ኛ ሳሙኤል

=>1 ኛ ነገስት

=>2 ኛ ነገስት
=>1 ኛ ዜና መዋዕል

=>2 ኛ ዜና መዋዕል

=>መጽሐፈ ዕዝራ

=>መጽሐፈ ነህምያ

=>መጽሐፈ አስቴር

3. የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት

=>መጽሐፈ ኢዮብ

=>መዝሙረ ዳዊት

=>መጽሐፈ ምሳሌ

=>መጽሐፈ መክብብ

=>መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን

4. የትንቢት መጻሕፍት

=>ትንቢተ ኢሳይያስ

=>ትንቢተ ኤርምያስ

=>ትንቢተ ሕዝቄል

=>ትንቢተ ዳንኤል

=>ትንቢተ ሆሴዕ

=>ትንቢተ አሞፅ

=>ትንቢተ ሚክያስ

=>ትንቢተ ኢዩኤል

=>ትንቢተ አብድዩ

=>ትንቢተ ዮናስ
=>ትንቢተ ናሆም

=>ትንቢተ ዕንባቆም

=>ትንቢተ ሐጌ

=>ትንቢተ ዘካርያስ

=>ትንቢተ ሚልክያስ

ናቸው!ይሄ የብሉይ ኪዳን አከፋፈል በ 66 ቱ መጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ነው።

ሐዲስ ኪዳንም እንደ ብሉይ ኪዳን በአራት ይከፈላል።

1. የወንጌል ክፍል

2. የታሪክ ክፍል

3. የመልዕክት ክፍል

4. የትንቢት ክፍል ናቸው

እነዚህንም እንደብሉይ ኪዳን በዝርዝር ስናይ

ሐዲስ ኪዳን

1. የወንጌል ክፍል

=>የማትዮስ ወንጌል

=>የማርቆስ ወንጌል

=>የሉቃስ ወንጌል

=>የዮሐንስ ወንጌል

2. የታሪክ ክፍል
=>የሐዋርያት ሥራ

3. የመልዕክት ክፍል

=>ከሮሜ መልዕክት እስከ ዕብራውያን ያሉት 14 መጻሕፍት

=>1 ኛ እና 2 ኛ ጴጥሮስ

=>1 ኛ, 2 ኛ እና 3 ኛ ዮሐንስ

=>የያዕቆብ መልዕክት

=>የይሁዳ መልዕክት

በአጠቃላይ ቁጥራቸው 21 ነው።

4. የትንቢት ክፍል

=>የዮሐንስ ራዕይ

ከላይ እንደተገለጸው ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን እንዴት እንደሚከፈል ግንዛቤ በሚሰጥ መልኩ
አይተናል።መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ በመጀመሪያ ሊረዳ የሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ በሥርአቱና
በየክፍሉ የተቀመጠ መሆኑን ነው።በመቀጠል የሚያነበው ክፍል ምን እንደሆነ ከአከፋፈሉ በስፋት
መረዳት መቻል ነው።የሐዲስ ኪዳንና የብሉይ ኪዳንን አከፋፈል አጠቃለን ስንደምራቸው 8 ናቸው።

ሁለቱንም በተነጻጻሪነት ስንመለከት

ብሉይ ኪዳን ሐዲስ ኪዳን

1. የህግ ክፍል 1. የወንጌል ክፍል

2. የታሪክ ክፍል 2. የታሪክ ክፍል

3. የመዝ. የጥበብ 3. የመልዕክት ክፍል

4. የትምቢት ክፍል 4. የትንቢት ክፍል

የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት አከፋፈል ለይቶ የሚያውቅ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ
የሚሄድበትን አቅጣጫ የሚያውቅ ሰው ይመስላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ከላይ ከተገለጸው
አከፋፈል ተረድቶ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወደ ብዙ እውቀትና ጥበብ ያሻግራል።
በቀጣይ

📖የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም

📖የመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤ

📖የመጽሐፍ ቅዱስ ህዳግ አወጣጥ

📖የግዕዝ ቁጥር

📖መጽሐፍ ቅዱስን በጊዜና በሰዓት ከፋፍሎ የማንበብን ስልት እናያለን

አቡ ናክ(ወንዴ)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

You might also like