You are on page 1of 3

በርባን

ታዋቂ ነኝ ፤ ሀገሬ ፣ ሰፈሬ፣ መንደሬ ከህፃን እስከ ሽማግሌ ጠንቅቆ ያውቀኛል፡፡ እንደው መልካም ነገር
ስላበረከትኩላቸው አልያም ፀባየ ሸጋ ሆኜ እንዳይመስላችሁ ፤ ድብን ያልኩ ወንበዴ በመሆኔ እንጂ፡፡ ሰዎች “ክፉ ነው”
ይበሉኝ አንጂ ለኔ የህይወት ትርጉሙ ይኸው ነው፡፡ ሰዎችን ማሸበር ደስታ ይሰጠኛል፡፡ እገድላለሁ፤ ካልሰማችሁኝ አዎ
እ….ገ…..ድ……ላ…..ለ…ሁ፡፡ ምነው ደነገጣችሁሳ፤ አሁን መግደል ብርቅ ሆኖ ነው፡፡ ብርቅ የሚሆነው እኮ ለናንተ ነው፡፡
ለኔማ ጨዋታ ነው፡ ብቻ ግን ምን ልበላችሁ “ነፍስ ማጥፋት ውስጤ ነው”፡፡ ድንገት ግን የማታውቁኝ ካላችሁ “በርባን”
እባላለሁ፡፡ አዎ ልክ ናችሁ ሰዎች ስለ እኔ ሲያወሩ የሰማችሁት በርባን፡፡ ቤተሰቦቼ ምን አስበው እንደሆነ ባላውቅም ስሜ
ሲተገጎም “የአባት ልጅ” ነው አሉ፡፡ ኤጭ… እኔን ብሎ የአባት ልጅ፡፡ “ስምን መልአክ ያወጣዋል” አሉ ፤ለኔ ግን የወደቁት
መላእክት ናቸው ያወጡት መሰለኝ፡፡ እንደውም ሰሞኑን መቀመጫው ላይ ከወጋሁት በኋላ ወዳጄ የሆነ አንድ ሰው
ሲያጫውተኝ ምን አለኝ መሰላችሁ፤ “እዛ እታች ሰፈር ህፃናትን ማስፈራሪያ ሆነሀል” አለኝ፤ “እንዴት?” አልኩት፤ “እናቶች
ልጆቻቸው እቃ እንዳይነኩ ሲፈልጉ “ትነካውና ዋ፤ የምጠራልህ በርባንን ነዋ” ሲሏቸው እንዴት እንደሚርበተበቱ
አጠይቀኝ” ብሎኝ እርፍ፡፡ “በቃ የልጆች ማስፈራሪያ ድረስ ከደረስኩማ መጨረሻዬ ቀርቧል ማለት ነው” ብዬ በልቤ
አሰብኩ፡፡

የፈራሁትም አልቀረ በቅርቡ ከተማ ውስጥ ሁከት በሉት ዓመፅ ሳነሳሳ እንዲሁም በነፍስ መግደል ወንጀል ተይዤ
ታስሬያለሁ፡፡ የእልልታ ድምፅ ሰማሁ ልበል? ለነገሩ እልል ብትሉ አልፈርድባችሁም፡፡ ለናንተ የእረፍት ዜና ነዋ፡፡ እልል
ማለታችሁ ካልቀረ ፤ ሌላ ለኔ መርዶ ለናንተ ግን የደስታ ዜና ልንገራችሁ፤ የታሰርኩበት ወንጀል የሚያሰቅል ነው አሉ፡፡
እናም በምንም አይነት ሁኔታ ይለቀቃል ብላችሁ አትስጉ፡፡ ሮማውያን እንደሆነ እኔ በሰራሁት አይነት ወንጀል
አይደራደሩም፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ተሰቅዬ ልሞትላችሁ ነው፡፡ አሁንም እልል አላችሁ፤ እንደው ባልታሰር ኖሮ ምላሳችሁን
ነበር የምቆርጠው፡፡ እና ያኔ ስሞት ኢየሩሳሌም በደስታ የምትሰክር ይመስለኛል፡፡ በሰው መሞት መደሰት ተገቢ
ባይሆንም፤ በኔ መሞት ግን ብትደሰቱም አልቀየማችሁም፡፡ እንግዲህ መልካም ደስታ ብያለሁ ፤ ከእኔ ከሟች፡፡

ደግሞ ሳልነግራችሁ ፤ ሰሞኑን የፋሲካ በዓልም አይደል፤ ጲላጦስ እንደልማዱ አንድ እስረኛ ይፈታም የለ፤ እዚህ እስር
ቤት ቀውጢ ሆኗል፡፡ ማን ይሆን የሚፈታው እያለ ሁሉም ይጨነቃል፡፡ ታዲያ እንደኔ ያሉት የመፈታት ተስፋ የሌላቸው
እስረኞች የሚተኙት የሰላም እንቅልፍ አቤ….ት ሲያስቀና ፤ አንዳንዶቹ እንደውም እንደዚህ “ማን ይፈታ ይሆን?” ከሚል
ጭንቀት እንድንገላገል ምናለ እንደ እናንተ ከባድ ወንጀል በሰራን እያሉ ይፀፀታሉ፡፡ ታዲያ እኔ ልጃቹ አላኮራኋችሁም፡፡
እናማ ባለመፈታቴ እየተፅናናሁ ፤ እናንተም ከኔ መፈታት ስጋት እያረፋችሁ በደስታ ኑሩ፡፡ ምናልባት ይፈታ ይሆናል
ብላችሁ አንዳንዶቻችሁ ከሰጋችሁ እነ ማቴዎስን ፣ ሉቃስን፣ ማርቆስን እና ዩሃንስን ጠይቋቸው፡፡ “ዐመዕ ሲያነሳሳ ነው”
የታሰረው ይሏችኋል፡፡ ደግሞ ዐመፅ የማነሳሳው በማን ላይ ቢሆን ጥሩ ነው፤ በሮማ ኢምፓየር (መንግስት) ላይ፤ ደፋር
ነሽ ኦኮ “በርቢ” ትሉ ይሆናል፤ እኔ ግን እንደ እናንተ ፈሪ አይደለሁም፡፡ ……….. እናላችሁማ በሮማ መንግስት ላይ ዐመፅ
የሚያነሳሳ ሰው መጨረሻው የመስቀል ሞት እንደሆነ አትጠራጠሩ፡፡ ስለዚህ የምትሰጉ ሰዎች አንኳን ካላችሁ ስጋት
አይግባችሁ አልፈታም፡፡ ለነገሩ ከእናንተ ጋር ምን አጨቃጨቀኝ ዛሬ አይደል ቀኑ ፤ እናንተው እራሱ በአይናችሁ
ታዩታላችሁ፡፡

ከናንተ ጋር ስዳረቅ ሰዓቱ ሮጧል ለካ፤ ረፋድ ሆኗል፤ የሆነ ግርግር ከውጪ ይሰማኛል፡፡ በበዓሉ ምክንያት ወዲያ ወዲህ
የሚሉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አስቤ ነበር ነገር ግን አንዱን የእስር ቤቱ ወሬ አመላላሽ ጠጋ ብዬ ስጠይቀው አንድ
የሆነ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚባል ሰውዬ ሊያስሩት ይዘውት እየመጡ ነው አለኝ፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ ግርግር ለአንድ ሰውዬ

1
ነው? “አቦ ምን ያህል ሰው ቢገድል ይሆን እንደዚህ አጅበው የሚሸኙት” አልኩ፡፡ ወሬ አመላላሹም ቀበል አድርጎ “ኧረ
ንፁህ ሰው ነው፤ ካህናት ስለቀኑበት ነው ሊያስገድሉት የሚፈልጉት” አለኝ፡፡ ገረመኝ፤ ለካ ሰው በወንጀል ብቻ አይደለም
በቅናትም ይገደላል፡፡ እናማ ይህን ትዕይንትማ መከታተል እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡

የመስኮት ቀዳዳ ፈልጌም ቢሆን መከታተል ጀምሬያለው፤ በአካባቢው ብዙ ሰው ተሰብስቧል፤ ሁሉም ያጉረመርማል፡፡
ከርቀት ሆኜ እንደታዘብኩት ከኢየሩሳሌም ሰዎች ብዙዎቹ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚባለውን ሰውዬ አይወዱትም፡፡ ምን
አድረጓቸው ነው ግን ብዬ እብሰለሰል እንደጀመርኩ ፤ ድንገት ውስጤ ያለ አንድ መልአክ ተገርሞ “እንዴ… በርባን
ያልፈጠረብህን ለሰው ልታዝን፤ እንደፈለጉ ቢያደርጉትስ ምን አገባህ” ይለኛል፡፡ደግሞ አንተ ውስጥ መልአክ አለ እንዴ
ብላችሁ እንዳትገረሙ፤ እኔ እሱ ውስጥ አልያም እሱ እኔ ውስጥ መሆኑ ግራ ቢገባኝም የክፉው ነው፤ ሉሲፈርስ ቢሆን
መልዓክ አልነበር፡፡ ታዲያ የኢየሩሳሌም ሰዎች በዛ ንፁህ ሰው ማጉረመረማቸውን ቀጥለዋል፤ አገረ ገዢው ጲላጦስ ግን
ሊፈታው ፈልጓል መሰለኝ ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ የሚከራከር ይመስላል፤ ካህናቱ እና ህዝቡ ግን በዋዛ የሚረቱ አይነት
አይደሉም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ትዕይንቱን መከታተል እያስጠላኝ ስለመጣ ለምን ትንሽ አረፍ አልልም ብዬ መሬት
ላይ ቁጢጥ አልኩ፡፡ ኡፍፍፍ… የመሬቱ ቅዝቃዜ አንጀት ያርሳል፡፡

ሰመመን ውስጥ ሆኜ የባጥ የቆጡን ማሰላሰል ከጀመርኩ ጥቂት ደቂቃዎች ተቆጥረዋል፡፡ ድንገት ሳላስበው ግን ከሰመመኔ
የሚያነቃ ድምፅ ሰማሁ፤ “በርባን በርባን ትፈለጋለህ” ፤ የእስር ቤቱ ጠባቂ ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ተጠርቼ አላውቅም ነበር፡
፡ ውስጤን የሆነ የፍርሃት ወሽመጥ ቆርጦት ሲያልፍ ተሰማኝ፤ የመሞቻ ቀኔ ደርሶ ቢሆን እንጂ በዚህ ሰዓት ለምንም
ሊጠሩኝ አይችሉም፡፡ ፈራሁ፤ መሞትን ፈራሁ፤ ለስንቱ ስሸልመው የነበረ ሞት ለካ እንደዚህ ያስፈራል፡፡ እየተርበተበትኩ
“አ……..አቤት” ብዬ ተነስቼ ወደ ጠራኝ የእስር ቤቱ ጠባቂ ዘንድ ሄድኩ፡፡ እጄን እና እግሬን በሰንሰለት አስረው ቅድም
በርቀት ስከታተል ወደ ነበረበት ቦታ ወሰዱኝ፡፡ በቦታው ስደርስ የናዝሬቱ የሚሉትን ሰው ወታደሮች ከበውት ቆመዋል፤
“በቃ ከዚህ ሰው ጋር አብረው ሊሰቅሉኝ ነው” ብዬ አሰብኩ፡፡

አገረ ገዢው ጲላጦስም ንግግር ጀመረ፤ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ኢየሱስ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?”
አለ፡፡ ኧረ… ሙድ መያ….ዝ፤ “እነዚህ ሰዎች ፊት ለፊታቸው አቁመው ሊሳለቁብኝ ነው” እንዴ አልኩ በልቤ፡፡ እስቲ ቆይ
አስቡት እንደ እኔ ያለ ወንበዴና ነፍሰ ገዳይ እና ምንም ካልሰራ ንፁህ ሰው ጋር ሲያወዳድሩኝ፡፡ ጲላጦስም ቢሆን እኮ
የናዝሬቱን ኢየሱስን ለመፍታት ስለፈለገ ከእስር ቤቱ ካሉት ወንጀለኞች መካከል እኔን ባስ ያልኩትን ጠራ እንጂ ፤ ሌላ
ሰው ለመፍታት አስቦ ቢሆን ኖሮ ሌሎች መፈታት የሚችሉ ብዙም ወንጀል ያልሰሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ በዚህ መሀል ግን ጆሮ
ማልፋት ስለሆነ ህዝቡ ምን እንደሚል ለመስማት አልፈለኩም ነበር፤ ምክንያቱም መልሱ ግልፅ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን የኔ
ስም ይሰማኝ ጀምሯል ”በርባንን ፍታልን” ”በርባንን ፍታልን” የሚሉ ድምፆች መበራከት ጀምረዋል፡፡ “ኦ … ይሄ የናዝሬቱ
ኢየሱስ የሚሉት ሰው ቅፅል ስሙ በርባን ይሆን?” እያልኩ ግራ እየተጋባው ነው፡፡ “በርባንን ፍታልን” “በርባንን ፍታልን”፤
ስንት ዘመን ስጠራበት የነበረ ስም ዛሬ የኔ እንዳልሆነ ክጃለሁ፡፡ ታዲያ የኢየሩሳሌም ሰዎች ክርስቶስን ጠልተው “በርባንን
ፍታልን” ብለው የሚጮሁት ለኔ እንደሆነ ያወኩት አገረ ገዢው ጲላጦስ ንግግሩን ቀጥሎ “ታዲያ ክርስቶስ የሚባለውን
ኢየሱስ ምን ላድርገው?” ብሎ ህዝቡን ሲጠይቅ ነው፡፡ ህዝቡ በአንድ ድምፅ “ይሰቀል” ”ይሰቀል” እያለ ይጮሃል፤ እኔ
ማመን አልቻልኩም፤ “የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ እኔ እኮ በርባን ነኝ”፤ “ነፍሰ ገዳዩ በርባን” ፤ “ወንበዴው በርባን”፤ ”ይሰቀል”
“ይሰቀል”፤ ለካ ሚስጥሩ የኢየሩሳሌም ሰዎች እኔን ወደውኝ አይደለም፤ እሱ ለኔ ሲል ለመሞት በመፍቀዱ እንጂ፡፡ ኧረ
የናዝሬቱ ኢየሱስ የሆነ ነገር በል፤ ተከራከር እንጂ፤ “መሞት የሚገባው በርባን ነው” በል፤ “እኔ ንፁህ ሰው ነኝ ፤እንዴት
እኔን አስራችሁ ይህን ወንበዴ፣ ነፍሰ ገዳይ ትፈቱታላችሁ?”በል፤ ኧረ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተናገር፤ ዝም አትበል፡፡ እሱ ግን
አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።

2
በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ
ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ
ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ
አዘነበለ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። መሞት የሚገባው በህይወት ኖሮ፤ በህይወት ሊኖር
የተገባው ሞተ፡፡

አሁንማ ነፃ ሰው ነኝ፤ በእስር ቤት ስላሳየሁት መልካም ምግባር አይደለም፤ ሞቴን የሚሞትልኝ ተገኝቶ እንጂ፡፡ እኔን
“የአባት ልጅ” አሉ፤ እውነተኛው “የአብ ልጅ” ሞቶ፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ እኛስ ቢሆን ከወንበዴው በርባን በምን እንለያለን፤ እንደው አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ “ሀጢያትን
ይቅር የመባል ስሜቱ ይገባችኋል? ግን” ፤ አንዳንዴ እንደዚህ አስባለው፤ ከክርስትያን ቤተሰቦች ስለተወለድን አልያም
ጌታን ስንቀበል ብዙም የባህሪ ችግር ስላልነበረብን የሀይማኖት ተቋም ለውጥ እንዳደረግን እንጂ ክርስቶስ ኢየሱስ ምን
ያህል ዋጋ እንደከፈለልን እና የቱን ያህል ሀጢያት ይቅር እንደተባልን የምንረዳ አይመስለኝም፡፡ ለኛ የሚገርም
አዳዳን(መዳን) ብለን የምናስበው ከትልቅ ሱስ ነፃ የወጣ አልያም እንደ በርባን ያሉ ሰዎች ጌታን ሲያገኙ ነው፤ በእርግጥ
ሰው ከተለያየ ቀንበር ነፃ ሲሆን እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ቢሆንም፤ ቅዱስ ቃሉ እኮ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም
የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል” ይላል፡፡ እስኪ ንገሩኝ በአንድ ጥይት ከሞተ ሰው እና በአስር
ጥይት ከሞተ ሰው የቱ ይሻላል፡፡ መቼስ ሬሳ የማወዳደር አባዜ ውስጥ እንደማትገቡ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ታዲያ እኛ ሁላችን
የምንቅም የማንቅም፤ የምናጨስ የማናጨስ ፤ የምናመነዝር የማናመነዝር፤ የተመታንበት የጥይቱ ብዛት ይለያይ እንጂ
ሟቾች አይደለን፡፡ “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ” አይልስ ቃሉ፤ እንደው ከብዙዎችችን ላይ ጮሆ
አልወጣም እንጂ “በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ
ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸውስ” አይልም፡፡ እናማ ቁም ነገሩ “እጅግ
ወዳለችና ብዙው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ በትንሹ የተሰረይለት ግን የሚወደው በትንሹ ነው” አንዲል ኢየሱስ ብዙ
እንደተማርን(ምህረት እንደተደረገልን) አውቀን ለክርስቶስ ብዙ እናድርግ።

You might also like