You are on page 1of 5

ትንሳኤ ከበደ

የፎክሎራዊ ሀሳቦች ኪነ ጥበባዊ አበርክቶ በተመረጡ የኢትዮጲያ ትውፊታዊ ቴአትሮች ውስጥ


በተለያየ ዘመን የአለምን የየቴአትር ጥበብ ታሪክ ያጠኑ ጸሀፍት ባቀረቧቸው የምርምር ስራዎች
ውስጥ እንደተዘገበው የቴአትር ጥበብን ጅማሮ ወይም መነሻ አስመልክቶ የጠራ ወይም ወጥ የሆነ
ሁሉንም የሚያስማማ አንድ ድምዳሜ እስካሁን የለም፡፡

ነገር ግን ጥበቡ ዘመነኛ ቅርጹን የያዘው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ 2500 ዓ/ዓ በፊት መጀመሪያ
በግብጽ የአባይዶስ (Abydos ) ሀይማኖታዊ ክብረ በአል ላይ ከሚቀርቡ የመስዋእት ዝማሬዎች
ሲሆን ቀጥሎም በዋናነት የድራማ ቅርጽ የያዘው ደግሞ በግሪክ አቴንስ ይከወን በነበረው የዳይኖሲያ
አመታዊ የመስዋእት ክብረ በአል ላይ ይከወኑ ከነበሩ ድራማ መሰል መዝሙር አቀፍ ሁነቶች መሆኑን
ማወቅ ይቻላል፡፡ ከዚህ ሀሳብ በመነሳት ፎክሎር የዘመናዊ ድራማ ቀደምት አባት ወይም መነሻ ምንጭ
ነው ለማለት እንችላለን፡፡

ፎክሎራዊ ጉዳዮች ከዚህ ቀጥሎ በነበሩት ወርቃማ የግሪክ ድራማ ዘመናትም ቢሆን የታሪክ ፣ የገጻ
ባህሪ ፣ የመቼት እነዲሁም የሀሳብ ምንጭ ወይም መነሻ በመሆን አገልግለዋል፡፡
በሀገራችንም ከመጀመሪያው ዘመናዊ ቴአትር ጽሁፍ ጀምሮ ፎክሎራዊ ሀሳቦች በተለያየ መልክ ኪነ ጥበባዊ ፋይዳቸውን
ገልጠው ተመልክተናል፡፡ በዚህም ግዜ የተውኔት አንድ ዘውግ በሆነው ትውፊታዊ ቴአትር ውስጥም ልዩ ልዩ የሆኑ
ፎክሎራዊ ጉዳዮች ኪናዊ ለዛን ተላብሰው ይቀርባሉ፡፡

ከዚህም በመነሳት እነዚህ ፊክሎራዊ ጉዳዮች በኢትዮጲያ ትውፊታዊ ቴአትር ውስጥ ያላቸው ጥቅል
ኪነ ጥበባዊ ፋይዳ በምን መልክ እንደሚገለጥ በሳይናሳዊ መንገድ ለመተንተን ይህን ርእሰ ጉዳይ
መርጫለው፡፡

ጊቻምዌ የሰባት ቤት ጉራጌ የሴቶች ቀን ከበራ ፋይዳ ትንተና


እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ባለ እረጅም ዘመን ታሪክ እና ጥንታዊ ትውፊት ባለቤት በሆኑ ሀገራት
እንደሚስተዋለው ስርአተ ጾትን መሰረት ያደረጉ ሚናዊ ክፍፍሎች አሁንም ቢሆን የማህበራዊ ስሪት
እና ማህበራዊነት አብይ መሰረቶች ናቸው፡፡ ይህን መሰሉ ማህበራዊ ስሪትም ሴቶችን ከአብዛኛው
ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚአዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲሁም ተጠቃሚነት ያገለለ ሆኖ ቆይቶአል፡፡
በተለያዩ መዛግብት ሰፍሮ እንደሚገኘውም በተለይም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ይህን መገለል
ለመታገል እና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተፈጠሩ
ቢሆንም እነዚህ እንቅስቃሴዎች ግን ውጤት ማፍራት የጀመሩት ከ 19 ኛው ክፍለ ዘመን
የእንስታዊነት እንቅስቃሴ መጀመር በኃላ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን፡፡
ይህ የእንስታዊነት እንቅስቃሴ በዚህ ደረጃ ተስፋፍቶ በአለም ዙሪያ ከመተዋወቁ በፊት ግን በተለያዩ
ማህበረሰቦች ውስጥም ሴቶች ይህን መሰሉን ኢ-ፍትሀዊ ማህበራዊ ስሪት ለመታገል ወይም
ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልቶችን ነድፈው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ማወቅ
ይቻላል፡፡ ጊቻምዌም ከእነዚህ እንደ አንዱ ሊቆጠር የሚችል ስርአተ ከበራ ሲሆን የሰባት ቤት ጉራጌ
ሴቶች በመረጧቸው ቀናት በአደባባይ በመሰብሰብ እርስ በእርስ በመመካከር፣ በመረዳዳት እና
በመማማር የራሳቸውንም ሆነ ከማህበራዊ ስሪቱ የሚከሰትባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ
የሚጠቀሙበት ማህበራዊ ተቋም ነው፡፡

በዚህ ርእሰ ጉዳይ ይህን ጽሁፍ ለማቅረብ ያሰብኩትም ይህንን እንደ የቃቄ ወርደወት መሰል ጀግና
ከዘመናቸው የቀደሙ ተራማጅ ሴቶችን የፈጠረውን ማህበራዊ ተቋም ለማስተዋወቅ እንዲሁም
ምናልባትም በሌሎች አካባቢዎች ባልተለመደ ሁኔታ በጉራጌ ማህበረሰብ ውስጥ ለሴቶች የሚሰጥን
ከፍተኛ አዎንታዊ ግምት እና ሴቶቹም በማህበራዊ መዋቅሩ ውስጥ ያላቸውን የላቀ ሚና ለማሳየት
በማሰብ ነው፡፡

ኬርታ የጉራጌ ማህበረሰብ የእርቅ እና የመለማመኛ ስርአት


አለም አሁን ከደረሰበት ውስብስብ የአነዋወር ጠባይ አንጻር መደበኛው የፍትህ ስርአትም በየወቅቱ እንዲሁ
እየዘመነ እና እየተወሳሰበ መቷል፡፡
ምንም እንኳን ይህ መደበኛ የፍትህ ስርአት በየግዜው እየተሻሻለ እና እየዘመነ የመጣ ቢሆንም ለሁሉም
ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅም ያለው እንዳልሆ ግን መናገር ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት
በተለያየ አጋጣሚ የሚከሰቱ የፍትህ መጓደል ወሬዎችን መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡

ከዚህ መደበኛ የፍትህ ስርአት መዘርጋት እቀድሞ በሀገራችን በሚገኙ ሁሉም ማህበረሰቦች የአካባቢውን ሰላም
ለማስጠበቅ፣ ፍትህን ለማስፈን፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚአዊ መስተጋብሩን በአግባቡ ለማስቀጠል፣ በህዝቦች
መካከል መተማመንን ለመፍጠር እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ባህላዊ የፍትህ ተቋማት ወይም
ስርአቶች ይገኛሉ፡፡

የጉራጌ ክፍለ ህዝብም ለዘመናት ሰላሙንና ውስጣዊ አንድነቱን ጠብቆ በዙሪያው ካሉ ሌሎች ማህበረሰቦችም
ጋር ተከባብሮ እና ተግባብቶ እንዲኖር፣ ጠንካራ የስራ ባህሉን ይበልጥ እንዲያዳብር እንዲሁም በተለያየ
ምክንያት የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጣሪን የሚለማመንበት እርቅ የሚወርድበት
ስርአቱ ነው ኬርታ፡፡

ይህ የኬርታ ስርአት የጉራጌ ክፍለ ህዝብ ለዘመናት ሲጠቀምበት የኖረ ሲሆን አሁንም ድረስ በሰባቱ የጉራጌ
ማህበረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ውስጣዊ ግጭቶችን እንዲሁም ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ሊኖሩ የሚችሉ
ግጭቶችን በማክሰም የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የበደሉ የሚክሱበት፣ ተራርቀው የሚኖሩ የሚገናኙበት፣ በቀደ
ዘመን የተሰራ ግፍ ጡር የሚወጣበት የማህበረሰቡ በጎ እሴቶች የሚበረታቱበት እና በውስጡ በርካታ ባህላዊ
ስርአቶች የሚከወኑበት የሰላም መድረክ ነው፡፡

እኔም በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ይህን ጽሁፍ ለማቅረብ የተነሳሁት የባህላዊ ስርአቱን የተለየ አከዋወን ለማሳየት፣
ስርአቱ ለማህበሩ የሚሰጠውን አዎንታዊ ግልጋሎት በግልጥ ለማሳየት እንዲሁም በአሁኑ ግዜ ማህበረሰቡ
በተለያዩ አካላት እየደረሰበት ያለውን ውስጣዊ የመከፋፈል አደጋ ይህን ማህበራዊ ተቋም ተጠቅሞ እንዴት
እንደተቋቋመው ለማሳየት በማሰብ ነው፡፡

You might also like