You are on page 1of 5

=>+"+ እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት "ቅዱስ አባ በአሚን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ቅዱስ አባ በአሚን "*+

=>የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም:: ይልቁኑ:-

¤እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው::

¤እንደ ብዕር አጥንታቸው::

¤እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ:: ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው::

+ስለዚህም "ተጋዳዮች : የሚያበሩ ኮከቦች : የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለዋል:: እነሱ እየቀለጡ አብርተዋልና::

+ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ 150 እስከ
312 ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው::

+በተለይ ግን ከ 270 ዎቹ እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና የክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል:: የሰማዕታት
ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል: የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም:: (ማቴ. 10:16, ማር. 13:9, ሉቃ. 12:4, ዮሐ. 16:1,
ሮሜ. 8:35, ራዕይ. 2:9)

+የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::

=>ከዓበይት ሰማዕታትም አንዱ ቅዱስ በአሚን ነው:: በቤተ ክርስቲያን "ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ሰይፍ)" የሚባሉ ቅዱሳን አሉ:: ሰማዕት
ዘእንበለ ደም ማለት "እንደ ሰማዕታት መከራውን ሁሉ ተቀብለው ሳይሰየፉ (ሳይገደሉ) የመከራውን ዘመን ያለፉ" ናቸው::

+ለምሳሌ ከሠለስቱ ምዕት (ከ 318 ቱ ሊቃውንት) አብዛኞቹ እንደዚህ ባለ ሕይወት ያለፉ ናቸው:: ቅዱስ በአሚንም እንዲሁ ዓይነት ዜና
ሕይወት ያለው አባት ነው::

¤ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱስ በአሚን ተወልዶ ያደገው በደቡብ ግብጽ በ 3 ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ቅዱሱ ከልጅነቱ ክርስትናን የተማረ ነበርና ሰው ሁሉ
የሚወደው ታማኝ ሰው ሆነ:: ምንም ሀብታም ሰው ባይሆንም ተቀጥሮ ሠርቶ በሚያገኛት ገቢው መልካምን ይሠራ ነበር::
+በዘመኑም ከቅንነቱ የተነሳ "መታመንስ እንደ በአሚን" ይባል ነበር:: ቅንነቱን የወደዱ ሁሉ ይሹት ነበር:: በከተማው ውስጥ እጅግ ብዙ
ሀብት የነበራቸው ባል እና ሚስትም ወደ ቤታቸው ወስደው መጋቢ (ተቆጣጣሪ) አደረጉት::

+ጠባዩን ከተረዱ በኋላ ግን ሙሉ ሀብት ንብረታቸውን በእጁ አስረክበውት ያስተዳድርላቸው ነበር:: ሲወጡና ሲገቡም እያዩት ደስ
ይሰኙበት ነበር:: እርሱ ግን ልቡ በክርስቶስ ፍቅር የተመሰጠ ነበርና ለዚህ ዓለም ጉዋዝ ትኩረትን አይሰጥም ነበር:: ይጾም ይጸልይ ነበር
እንጂ::

+አንድ ቀን ግን የቤቱ ባለቤቶች (ባልና ሚስት) ሲመጡ ቤታቸው እንደሚገባ ተደራጅቶ: ቁልፉ ተቀምጦ አገኙት:: ወዳጃቸው በአሚን
ግን የለም:: ደንግጠው ቢያፈላልጉት ሊያገኙት አልቻሉም:: በመጨረሻ ግን መንኖ ገዳም መግባቱን ሰምተው ፈጽመው አዘኑ::

+ከእርሱ መለየትን አይፈልጉም ነበርና:: አልቅሰው ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ሲሉ ሚስት "አይሆንም! ሄደን እናምጣው" ስላለች ወደ
መነነበት ገዳም ሄደው: እያለቀሱ ይመለስላቸው ዘንድ ለመኑት::

+እርሱ ግን "ለሰማያዊ ሠርግ ታጭቻለሁና ከእንግዲህ የክርስቶስ ነኝ" አላቸው:: እንዳልተሳካላቸው ሲያውቁ ፈጽመው እያዘኑ ወደ
ቤታቸው ተመለሱ:: ቅዱስ በአሚን ግን ገዳማዊ ሕይወትን በተጋድሎ ጀመረ::

+ይጾማል: ይጸልያል: ይሰግዳል: ይታዘዛል:: በዚህ መንገድ ሥርዓተ ገዳምን በበረሃ ሆኖ ሲፈጽም በዓለም እነ ዲዮቅልጢያኖስ
ክርስቲያኖችን ይገድሉ ነበር:: ዜና ሰማዕታትም ቀስ እያለ ቅዱሱ ወዳለበት ገዳም ደረሰ::

+ነገሩን ሲሰማ ደስ አለው:: እርሱ ስለ ክርስቶስ ሲሉ ደምን ማፍሰስና መከራን መቀበል ከሁሉም ነገር የተሻለ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና::
ቀጥሎም ወደ ከተማ ሄዶ ደሙን ለማፍሰስ በቁርጥ ወስኖ ዘለቀ::

+በዚያም የንጉሥ ወታደሮች አግኝተውት ለጣዖት ይሰዋ ዘንድ ታዘዘ:: ቅዱስ በአሚን ግን "መስዋዕት የሚገባው ለጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ: ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ነው:: ለፍጡር አልሰዋም" ሲል መለሰላቸው:: በዚህም ምክንያት ወታደሮች
እየተፈራረቁ ደበደቡት::

+ደሙንም አፈሰሱት:: ምንም እንዳልተለወጠ ሲያውቁ ወደ እስር ቤት ጨመሩት:: ከዚያም በቀን በቀን እያወጡ ይደበድቡት: በእሳት
ያቃጥሉት: በተለያዩ ማሰቃያዎች በመከራ ያውሉት ነበር:: እርሱ ግን ክርስቶስን ከመቀደስ በቀር አንዳች አይመልስላቸውም ነበር::

+በብዙ አሰቃይተው እንቢ ቢላቸው ወስደው በጨለማ ቤት ዘጉበት:: በዚያም ጥለውት ዓመታት አለፉ:: ሁሉንም በጊዜው የሚሠራ ጌታ
ግን እነዚያን የመከራ ዘመናት አሳልፎ ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስን አጠፋቸው::
+በፈንታቸውም መፍቀሬ ክርስቶሳውያን ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን አነገሠ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጹ:: ስለ ክርስቶስ የታሠሩ ሁሉ ነጻ
ወጡ:: በዚህ ጊዜ ምዕመናን መጥተው ቅዱስ በአሚንን ከወደቀበት አነሱት::

+በወቅቱም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ "አጽመ ሰማዕታትን ሰብስቡ: በመከራው አልፈው በእድሜ ካሉትም መካከል መምጣት
የሚችሉትን አምጡልኝ" ብሏልና ቅዱስ በአሚንን የመሰሉ 72 ክቡራን ተገኙ:: ከእነርሱም መካከል ታላቁ አባ ኖብና አባ ዘካርያስ
ይገኙበታል::

+እነዚህ አበው ቅዱሱን ንጉሥ ባርከውት ሲመለሱ ቅዱስ በአሚን ወደ እስሙናይን ተጉዞ በበዓቱ ተቀመጠ:: በዚያም ደቀ መዛሙርት
በዝተውለት እንደ ገና ገዳማዊ ሕይወቱን ቀጠለ:: በዚያም ሳለ ብዙ ተአምራትን ሠራ::

+ድውያንን ፈወሰ:: መናፍቃንንም በጸሎቱ ከአካባቢው አራቀ:: አንድ ቀንም የሮም ንጉሠ ነገሥት ሚስት ወደ እርሱ ዘንድ መምጣቷን
ሰማ:: ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ገብተው "አባ! ንግሥቲቱ ትፈልግሃለች" አሉት::

+እርሱ ግን "እኔ ከምድራዊ ንግሥት ዘንድ ምን አለኝ! አልወጣም" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱ ግን መልሰው "አባ! እዘንላት: በመከራ
ውስጥ ናት"ሲሉት "እሺ" ብሎ ወጣ::

+ንግሥቲቱ ምንም ብዙ ሠራዊት ብታስከትል አንጀቷ ታጥፎ ተጐንብሳ ነበር የምትሔደው:: እርሱም በጀሮዋ ጠጋ ብሎ የሕመሟን
ምሥጢር ሲነግራት ተገርማ እግሩ ሥር ወድቃ ተማጸነችው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+ከ 15 ዓመታት በፊት አንድ የተባረከ ዲያቆን በቤተ መንግሥቷ አካባቢ ይኖር ነበር:: እርሱም (ዮሐንስ ይባላል) የዮሐንስን ራዕይ ቁሞ
ዘወትር ያነብላታል:: በዚህ የቀኑ የንጉሡ ባለሟሎች በሀሰት "ሚስትህን ዲያቆኑ እያማገጠ ነው" ሲሉ ለንጉሡ ነገሩት::

+ንጉሡም ነገሩ እውነት ስለ መሰለው ወታደሮቹን ዮሐንስን ከነ ሕይወቱ ባሕር እንዲያሰጥሙት አዘዘ:: ይህንን የሰማችው ንግሥት
ለቀናት ስታለቅስ አንጀቷ በመቃጠሉ ታመመች:: እየቆየም ሆዷ ታጠፈ:: ለ 15 ዓመትም የሚያድናት አጥታ ተንከራተተች::

+በኋላ ግን ሰዎች ስለ ቅዱስ በአሚን ቅድስና ሲናገሩ ሰምታ መጣች:: ለዛ ነው ቅዱስ በአሚን ምሥጢሯን ሹክ ያላት:: ቀጥሎም 2 በጐ
ነገርን ፈጸመላት:: መጀመሪያ ጸሎት አድርጐ ሆዷን ቢዳስሳት በቅጽበት ድና ቀና አለች::

+2 ኛው ግን "ያ የምትወጂው የተባረከ ዲያቆን ዮሐንስ አልሞተም:: መላእክት ከባሕር አውጥተው እገሌ በሚባል ደሴት አኑረውታል"
አላት:: እርሷም ተመልሳ በደስታ ለባሏ ነገረችው::

+ንጉሡም ተጸጽቶ ዮሐንስን ካለበት አስመጣው:: አበውም የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት አድርገውት ብዙ መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ቅዱስ በአሚን
ግን በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በዝማሬ ተቀብሯል::
=>አምላከ ቅዱስ በአሚን በጸሎቱ ይማረን:: ከትእግስቱ ይክፈለን:: ከበረከቱም ያሳትፈን::

=>ታኅሣሥ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ቅዱስ አባ በአሚን (ጻድቅና ሰማዕት)

2.ቅድስት አርምያ

3.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱሳን 318 ቱ ሊቃውንት

2.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)

3.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ

4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን

5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ

6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

=>+"+ አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ::
ልጆች ሆይ! አብን አውቃቾኋልና እጽፍላችኋለሁ:: አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ:: ጐበዞች ሆይ!
ብርቱ ስለ ሆናችሁ: የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር: ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ:: +"+ (1 ዮሐ. 2:13)

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት
ውኩፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ
መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ
ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

(ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ
አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች
መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ዳምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ
እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

(ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ እንዳዘጋጀው)

You might also like